Back to Front Page

ፕሮግራም አልባ የሕዝብ አደራ ተሸካሚዎች

ፕሮግራም አልባ የሕዝብ አደራ ተሸካሚዎች

 

ባይሳ ዋቅ-ወያ

01-25-20

 

ባላፈው ሳምንት ከዘቀጥንበት ወጥተን እንዴት ወደ ፊት እንራመድ? በሚል ርዕስ ያቀረብኩት ጽሁፍ በተለያዩ የሚዲያ ገጾች ላይ ከታተመ በኋላ፣ በቅርጽ የተለያዩ በይዘት ግን የሚመሳሰሉ ብዙ አስተያየቶች ከተለያዩ አቅጣጫዎች ደርሰውኝ ይዘታቸውን ከገመገምኩ በኋላ ያነሳሁት ጉዳይ ተጨማሪ ትኩረት የሚያስፈልገው መስሎ ስለታየኝ ይህንን ተከታይ ጽሁፍ ለማሳተም ወሰንኩ። በዚህ ጽሁፌ ሁለት ቁም ነገሮችን ማለትም ሕዝባዊ አደራና የፖሊቲካ ድርጅቶች ፕሮግራም ግልጽ አለመሆንን በተመለከተ አንዳንድ አስተያየት ሰጥቼ ሌሎችም የየበኩላቸውን አንዲያዋጡ ለመጋበዝ እሻለሁ። የኔ ሃሳብ ብቻ ትክክል ነው ከሚለው ፊውዳላዊና ኋላ ቀር አስተሳሰብ ተላቅቀን በየበኩላችን የሚሠማንን ወደ ውይይት መድረኩ ካመጣን አንድ ታላቅ ታሪካዊ እርምጃ የወሰድን መሆኑን አውቀን ሁላችንም እንድንካፈልበት ከወዲሁ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ሕዝባዊ አደራ

ያገራችን የፖሊቲካ ድርጅቶች የተቋቋሙት በማህበረሰቡ ውስጥ የተሻለ ንቃት ባላቸው ጥቂት ግለሰቦች ስብስብ መሆኑ እሙን ነው። በመላው ዓለም ያለው ልምድም ከዚህ የተለየ ስላልሆነ ድርጊቱ ብዙም አያሳስብም። ሕዝቡ መድረክ ወይም አቅም ከማጣት የተነሳ ለየብቻው ሆኖ በየቤቱ የሚያጉረመረምበትን ጉዳይ በአደባባይ ይዞ ለመቅረብ የነቁ የማሕበረሰቡ አካላት ተሰባስበው ድርጅት ማቋቋም ለሕዝብ ከመቆርቆር የመነጨ የዜግነት ግዴታ ነውና። የኛን የፖሊቲካ ድርጅቶች ልዩ የሚያደርጋቸው ግን በጓደኝነት ተሰባስበው ድርጅቱን ከመፍጠርና በጣም መሠረታዊ የሆነ የመህ መግለጫ ፕሮግራም ገና ከመጀመርያው ለሕዝብ በአደባባይ ከማሰማታቸው ባሻገር ያገሪቷን ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ችግር ሥልጣን ላይ ካለውና ከሚቃወሙት መንግሥት በተሻለ መንገድ እንዴት አድርገው እንደሚቀርፉት የሚይሳይ አንዳችም ፍኖተ ካርታ ለሕዝብ አለማቅረባቸው ነው። አንድ ሁላቸውም በድፍረት የሚናገሩት፣ ግን ደግሞ አሳሳች የሆነው፣ ይህ ህዝባችን አደራ ሰጥቶናል ሕዝባችንን እንወክላለን የሚሉት ፖሊቲካዊ ቅጥፈት ነው።

Videos From Around The World

አዎ! ድርጅቶች የአንድን ማህበረሰብ ኤኮኖሚያዊና ማህበረሰባዊ ችግር፣ ሕዝቡ በተለያየ መንገድ ከሚያንጸባርቃቸው ድርጊቶቹ ተነስቶ በመገምገም የዚህን ሕዝብ ችግር በዚህ ዘዴ እንቀርፋለን ብሎ እቅድ ማውጣት ይቻል ይሆናል። ነገር ግን ስለፈጠሩት ድርጅት ምንነትና የማሕበረስቡን ችግር እንዴት እንደሚቀርፉ ለራሱ ለሕዝብ አቅርበው ሳያወያዩና ሕዝቡ አመኔታ ሳይሰጣቸው በአቋራጭ የሕዝቡን ፍላጎት በትክክል የተረዳሁትና መፍትሄ ላገኝ የምችለው እኔ ብቻ መሆኔን አውቀው ሥልጣን ይዤ ችግራቸውን እንድቀርፍላቸው አደራ ሠጥተውኛል ማለት ደግሞ አንድም ሕዝብን መናቅ አለያም የፖሊቲካን ሀሁ አለማወቅ ነው። አንዳንድ የድርጅት መሪዎች አባላትና ደጋፊዎች በዚህ አባባሌ ላይስማሙ ይችላሉ። ምክንያቱም ዋናው የችግሮች መቅረፍያ ኃይል የሚመነጨው የሥልጣን ወንበር ላይ ከተቀመጡ በኋላ ስለሆነ፣ ገና ሥልጣን ሳይያዝ ምኑ ተይዞ ነው ለሕዝብ ቃል የሚገባው ከሚሉ ብዙ ጓደኞቼ ጋር ብዙ ቦታ ላይ ክርክር ገጥሜያለሁ። ሁሌም የምከራከርባቸው ግልጽ አቋሜ፣ አንድ የፖሊቲካ ድርጅት የማህበረሰቡን ችግር እንዴት፣ መቼ እና በምን ዓይነት ዘዴ እንደሚቀርፍ ዛሬ ከምርጫው በፊት በግልጽ ሳያስቀምጥ እኔን ብትመርጡኝ ፓርላማ ገብቼ ለችግራችሁ መፍትሄ እፈልጋለሁ ለሚል ድርጅት እንዴት ድምጻችንን አንስጥ የሚል ነው። አለበለዚያ ግን ዝም ብሎ፣ የአዲስ አበባን ሕዝብ ጥቅም አስከብራለሁ የአማራን ሕዝብ ታሪክ አድሳለሁ የኦሮሞን ሕዝብ ማንነት አስከብራለሁ እና ለዚህ ደግሞ አደራ ተሰጥቶኛል ብለው የማይዳሰሱና የማይጨበጡ ግን ደግሞ ስሜት ቀሳቃሽ የሆኑ መፈክሮችን ብቻ እየመገቡን የኦሮሞ ወይም የአማራ ሕዝብ አሥር የተለያየ ችግር ያለው ይመስል አሥር የተለያዩ ድርጅቶች ፈጥረው መንቀሳቀሳቸው ከልብ ለሕዝባችን ችግር መፍትሄ ለማግኘት ሳይሆን፣ የነዚህ የተለያዩ ድርጅቶች ባለሥልጣናትን ፓርላማ ለማስገባት ብቻ ይመስለኛል።

የድርጅቶች ፕሮግራም ግልጽ አለመሆን

አንድ ትልቁ ያገራችን ችግር፣ የፖሊቲካ ድርጅቶች የተፈጠሩ ዕለት ከነደፏቸው ድፍንፍን ያለ መሠረታዊ አጄንዳ ውጭ የሕዝቡን ማሕበረሰባዊ፣ ኤኮኖሚያዊና ፖሊቲካዊ ጥያቄ እንዴት አድርገው እንደሚፈቱ ፕሮግራማቸውን በዝርዝር ለሕዝብ አቅርበው አለማወያየታቸው ነው። ፖሊቲከኞቻችን ሕዝብን የሚቀሰቅሱት ከቃላት ጨዋታ ያለፈ ብዙም ድካም የማይጠይቀውን የፖሊቲካ ጥያቄ አቅርበው እንጂ መሠረታዊውንና ለመቅረፍ እጅግ በጣም ከባድ የሆነውን ማሕበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ችግርን አይደለም። እንደው በደፈውና ለኦሮሞ ወይም ለአማራ ሕዝብ ማንነት የአዲስ አበባን ሕዝብ መብት ለማስጠበቅ የኦሮሚያን ልዩ ጥቅም ማስቀረት ወይም ማስጠበቅ ላባንዲራችን ለማንነታችን ለሶስት ሺህ ዓመት ታሪካችን ወዘተ ከማለት ባሻገር፣ ተመርጠው ፓርላማ ሲገቡ ለአዲስ አበባ፣ ለአማራ ለኦሮሞና በአጠቃላይም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ያላቸውን ፕሮግራም አይነገሩንም። የአዲስ አበባ ሕዝብ ዋናው ችግር በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተተው አንቀጽ 49 ወይም የታከለ ኡማ ማንነት ሳይሆን ለዘመናት የተጣበቀበት የቤት እጥረት፣ የሥራ ማጣት፣ የትራንስፖርት ችግር፣ የሓኪም ቤቶች እጥረት፣ የትምሕርት ጥራት መጓደል፣ የበሽታ መስፋፋት፣ የወንጀል መበራከት፣ በየቦታው የተኮለኮሉ የአደንዛዥ ዕጾች ሰለባ የሆኑትን ወጣቶች በየመንገዱ እያየ ለመርዳት አለመቻል፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስኳርና የዘይት እጥረት፣ ሙሰኝነት ወዘተ የመሳሰሉ ናቸው። እነዚህ እጥረቶች ደግሞ ከአንቀጽ 49 ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ስለሌላቸው፣ አዲስ አበቤ ያልሆነው ታከለ ኡማም በአዲስ አበቤው ቢልልኝ አዳነ ወይም ኤርሳሞ ቲራሞ ቢተካና ይህ ለሰላሳ ዓመት የአዲስ አበባን ሕዝብ ኑሮ ያመሰቃቀለውን አንቀጽ ከሕገ መንግሥቱ ቢፋቅም እንኳ ከላይ የዘረዘርኳቸውን የአዲስ አበቤውን መሠረታዊ ችግር ለመፍታት ቅንታት ታህል አስተዋጽዖ አይኖረውም።

አዎ! ችግሮቻችን የመብዛታቸውን ያህል ለመቅረፍም ረጅም ጊዜና ቁርጠኝነትን የሚጠይቁ ናቸው። ከአምስት ሚሊዮን በላይ ተምሮ ሥራ ያጣና ተስፋ ቆርጦ የተቀመጠ፣ ግን ደግሞ አያድርስ እንጂ ጊዜውን ጠብቆ ከፈነዳ የአገሪቷን ብቻ ሳይሆን የቀጠናውን ሰላምና ጸጥታ ለማደፍረስ ሙሉ ጉልበት ያለው ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ ቦምብ ትክ ትክ እያለ ነው። እነዚህን ቦምቦች ሳይፈነዱ ማክሸፍ ደግሞ ልዩ የፖሊቲካ ጥበብን ይጠይቃል። ለነዚህ ወጣቶች ሥራ ማጣት ምክንያት ከሆኑት አንዱ ለምሳሌ የሕዝባችን ቁጥር እጅግ በጣም በፈጥነ ሂደት መጨመሩ ነው። ችግሩ ማሕበረሰባዊ ከመሆኑም በላይ የተለያየ እምነት የሚያስተናግዱ ተቋማት ችግሩን በተለያየ መነጽር ስለሚያዩት ደፍሮ ይህንን ብሔራዊ አደጋ ለውይይት የሚያቀርብ የፖሊቲካ ድርጅት ያስፈልገናል። በአጠቃላይ ሲታይ፣ ዛሬ ባገራችን ሰፍኖ ያለው ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ለዘመናት የተከማቸ በመሆኑ፣ የሚቀጥለውን ምርጫ የሚያሸንፈው ድርጅት ወይም የድርጅቶች ጥምረት ማንም ይሁን ማን፣ የሕዝባችንን ዘላለማዊ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ቀርፎ ሰላምና ዕድገትን ያመጣል የሚል አንዳችም ተስፋ የለኝም። ግን ደግሞ ካሁኑ ችግሩን ለመቅረፍ ያለበትን ፈተና በውል የተረዳና እነዚህንም ችግሮች በግልጽ ለሕዝብ አቅርቦ ያወያየ የፖሊቲካ ድርጅት ወደ ብሩህ ነገ ለሚደረገው ረጅም ጉዞ ጥሩ ስንቅ ይዟል ብዬ አምናለሁ። የነዚህን ችግሮች ይዘትና ጥልቀት በውል ያልተረዳ የፖሊቲካ ድርጅት ግን የአመራር አባላቱ ፓርላማ ገብተው የተከበሩ የሚለውን ቅጽል ከስማቸው በፊት ከማስቀደም ባሻገር ለችግሮቻችን አንዳችም ዓይነት መፍትሔ እንደማያቀርብ እሙን ነው። ችግሩን ለመቅረፍ እንደማይችሉ እያወቁ ወይም የሚቀረፍበትን ዘዴ ለሕዝብ ሳያሳውቁ ደግሞ ምረጡኝ ብሎ በአደባባይ ወጥቶ ቅስቀሳ ማካሄድ ግን በድርጅቶቹ ላይ ምንም ዓይነት እምነት እንዳይኖረን ያደርገናል።

ሕዝቡ እኮ ዛሬውኑ ዳቦ ማግኘት ይፈልጋል። የኑሮ ውድነት ጣራ ስለነካ አብዛኛው ሕዝባችን ሠርቶ በሚያገኘው ደሞዝ ቤተሰቡን መቀለብ አልቻለም። መንገድ ላይ የተኮለኮለው ወደ ስምንት ሚሊዮን የሚጠጋ ሥራ አጥ ወጣት ዛሬውኑ ዳቦ፣ ሥራና መጠለያ ይፈልጋል። ምንም የተስፋ ጭላንጭል አልታይህ ያለው ብዙው ሥራ አጥ ወጣት ደግሞ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ድንበር አቋርጦ በመኮብለል ራሱን ለብዙ አደጋ እያጋለጠ ነው። ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ የተፈናቀሉት ወገኖቻችን በቀድሞ ቄያቸው ሰላም ሰፍኖ በክብር ለመመለስ ይፈልጋሉ። ይህ ደግሞ ሰላምና መረጋጋትን ማስፈን ብቻ ሳይሆን፣ ሰዎቹ ከተፈናቀሉ በኋላ ሃብት፣ ንብረታቸውና ቤታቸው ስለወደመባቸው ከተመለሱ በኋላ ዘርፈ ብዙ የሆነ የመንግሥት ድጋፍ ይሻሉ። 85% የሚሆነው አርሶ አደሩ ሕዝባችን ለአንድ ምዕተ ዓመት ያህል ተከታታይ መንግሥታት በዘረጉት ትክክል ያልሆነ የግብርና ፖሊሲ ምክንያት መሬታቸው ጠፍ ሆኖ፣ የዘሩትን ያህል እንኳ መልሰው ለማጨድ ባለመቻላቸው ከዓመት ዓመት ለረሃብ ተዳርገው፣ የተሻለ ኑሮ ለመምራት ዛሬውኑ ቁርጠኛ ውሳኔ ከመንግሥት ይጠብቃሉ። ባገሪቷ ያለው የጤና ጥበቃ ሽፋን ከሚጠበቀው በታች እጅግ የዘቀጠ በመሆኑ ዛሬ ያለው የጤና ፖሊሲ አብዛኛውን ሕዝባችንን እየጠቀመ አይደለም። በወሊድ ላይ የሚሞቱ እህቶቻችን፣ ለሳንባ ነቀርሳ፣ ለወባ እና ለመሳሰሉ አደገኛ በሽታዎች የተዳረጉ ዜጎቻችን ያገሪቷ ኤኮኖሚ የተሻለ ቢሆን ኖሮ ሊቀረፉ የሚችሉ ክስተቶች መሆናቸውን አውቆ ሕዝቡ በተቻለው መጠን የመንግሥት ያለህ እያለ ጩኸቱን እያሰማ ነው። የሚቃጠሉት መስጊዶችና የተዋህዶ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው። የእውቀት ምንጭ በመሆናቸው ለዘመናት ይከበሩ የነበሩ የዩኒቬርሲቲ ቅጥር ግቢዎች ዛሬ የተማሪዎች መገደያና ማሰቃያ ቦታ ሆኗል። ትላልቅ ከተሞቻችን የአደገኛ ዕጽ ሱስ በሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ተወርሯል። እነዚህን ልጆች ከጎዳና አንስቶ ወደ ትምሕርት ቤት ተመልሰው ከወላጆቻቸው ጋር በመሆን ጤናማ ኑሮ የሚያኖራቸው መንግሥት ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ፣ የችግሮቻችን ማሰሮ ካቀፋቸው ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ የማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ ዝርዝር ውስጥ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው።

እስከዛሬ እየተካሄደ ያለው የፖሊቲካ ድርጅቶቻችንም ሆነ የአክቲቪስቶቻችን እንቅስቃሴ ግን ያተኮረው በነዚህ አንገብጋቢ የሕዝብ ጥያቄዎች ላይ ሳይሆን ምናልባት ላንዳንዶቻችን የኅሊና ዕረፍት ይሠጠን እንደሁ እንጂ በገበታው ላይ ቁራሽ እንጀራ እንኳ ጣል በማያደርግ የፖሊቲካ ጥያቄዎች ላይ ነው። ዛሬ የተራበውን ሕዝባችንን እንዴት እናብላው ብሎ ከመወያየት ይልቅ ለዛሬው ችግራችን ተጨማሪ ችግር እንጂ አንዳችም መፍትሄ ሊሠጠን የማይችለውን የሶስት ሺህ ዘመን ታሪክና የባንዲራችን ቀለም አንስተው ያከራክሩናል። ከመቶ ዓመት በፊት የተደረገውን ግጭት ዛሬም እንደ ልዩነቶቻችን መገለጫ ወስደን ሕዝባችንን ስናጋጭበት፣ ከመቶ ዓመት በኋላ ደግሞ መጪው ትውልድ ዛሬ በኛ ስህተት ምክንያት እየተፈጸመ ያለውን የርስ በርስ ግጭቶች ሰለባ የሆኑትን ወገኖች ጉዳይ አንስተው ከመቶ ዓመት በፊት ቄሮና ፋኖ የተባሉ ጽንፈኛ የወጣት ስብስቦች፣ ወይም አብንና ኦነግ የተባሉ የፖሊቲካ ድርጅቶች ያራምዱት በነበረው የተሳሳተ ፖሊቲካ ምክንያት፣ ከኔ ወገን ይህን ያህል ሕዝብ በግፍ ተገደሎብኛልና ለነሱ መታሰቢያ ሓውልት እናቋቋም አናቋቁም በሚለው አርዕስት ላይ አለመግባባት ጠፍቶ እርስ በርስ

እንዲገዳደሉ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀንላቸው መሆኑን በውል የተረዳን አይመስለኝም።

ማሕበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮቻችን ከመቅጽበት የሚቀረፉ ባይሆንም ሕዝቡ ግን ዛሬውኑ መፍትሔ ይሻል። ስለዚህ ከፖሊቲካ ድርጅቶቻችን የምንጠብቀው ይህንን የሕዝቡን አንገብጋቢ ጥያቄ ከዕውኔታው ጋር አገናዝቦ፣ ችግሩን እንዴት መቼና በምን ዘዴ ለመቅረፍ ያዘጋጁትን እቅዳቸውን ለኛ ለመራጩ ሕዝብ የማቅረብ ግዴታ እንዳለባቸው እንዲያውቁ ነው። እኛ መራጮች እኮ ድምጽ ስንሰጥ ከተመራጮች ጋር ውል እንደመፈራረም ነው። ውል ደግሞ ከተፈረመ ተፈጻሚ መሆን አለበት። ውድ ዋጋ የሚያወጣውን ድምጻችንን ሰጥተን ውሉን ከመፈራረማችን በፊት ግን የኮንትራቱ ይዘት ግልጽ እንዲሆንልን እንፈልጋለን። ሁሉ ነገር በግልጽ ተቀምጦልን በፈቃዳችን ድምጻችንን ከሠጠን በኋላ ድርጅቶቹም አፋቸውን ሞልተው ከሕዝብ አደራ ተቀብለናል ብለው መናገር ይችላሉ። ታዲያ ውሉን ለመፈራረም የሚረዳንን ድርድር መጀመር ያለብን ዛሬ ነው! በዚህ ድርድር ውስጥ የመንግሥትና የግል የሚዲያ ተቋማት ደግሞ መጫወት ያለባቸው አንድ ትልቅ ሚና አለ። ይኸውም፣ የተለያየ ቡድንን እንወክላለን የሚሉትን የፖሊቲካ ድርጅቶችን ወደ መድረካቸው ጠርተው ፕሮግራማቸውን ለሕዝብ አቅርበው እንዲወያዩ ተከታታይ ፕሮግራሞችን ማዘጋጀት እጅግ በጣም ጠቃሚ ይመስለኛል።

የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን ሆይ! መቼም የምትወዳደሩት ሥልጣን ያለውን መንግሥት አውርዳችሁ ራሳችሁ ሥልጣን ለመያዝ ስለሆነ እስቲ እንደው በለስ ቀንቷችሁ ፓርላማ ብትገቡ ወይም መንግሥት ብትመሠርቱ ከላይ የዘረዘርኳቸውን እና ከዚህ ቀጥሎ ያስቀመጥኳቸውን ወቅታዊ የሆኑ የሕዝባችንን ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮች እንዴት ለመቅረፍ እንዳቀዳችሁ የመንግሥትና የግል ሚዲያ ተቋማት በሚያዘጋጁላችሁ ወይም ደግሞ ራሳችሁ በምታዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ ያላችሁን ፕሮግራም አቅርቡና በግልጽ ስትወያዩበት እንስማችሁ።

ሀ) ቁጥሩ በትክክል ባይታወቅም ዛሬ ባገራችን ከአምስት እስከ ስምንት ሚሊዮን የሚደርስ ተምሮ ሥራ ያጣ ወጣት ትውልድ አለ። ዛሬ ብትመረጡና ፓርላማ ብትገቡ፣ የነዚህን ወጣቶች የአጭር ጊዜና (ምግብና መጠለያ) የረጅም ጊዜ ፍላጎት (ሥራ መያዝ፣ ወላጅን መርዳት፣ ትዳር መመሥረት) ለመቅረፍ ምን ዓይነት ፕሮግራም ይዛችኋል?

ለ) ከሌሎች አገራት ሁሉ በፈጠነ መንገድ በፍጥነት እየጨመረ ያለውን የሕዝባችንን ቁጥር እኛን ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ እያወያየ ነው። ይህ ማሕበራዊ ችግራችን በአስቸኳይ ዕልባት ካላገኘ ደግሞ ከላይ በ ሀ የጠቀስኩት ችግር እጥፍ ይሆንና ማህበራዊ ቀውሱን ማባባሱ ዕሙን ነው። በዚህ ችግር ዙርያ የተለያዩ አክራሪ እምነት ተከታዮችና ባሕል አክባሪዎች አስተሳሰብ ከዘመናዊው የቤተሰብ ምጣኔ ጋር ስለማይጣጣም የፖሊቲካ ድርጅቶች ከሚያጋጥማቸው ፈተና አንዱ ነው ይባላል። ስለዚህ እንናተ ይህን ወሳኝና ዛሬውኑ ሁሉ አቀፍ ፕሮግራም ወጥቶለት በተግባር መተርጎም ካልተጀመረ እጅግ በጣም የከፋ ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊና ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችለውን ጉዳይ ለመቅረፍ ምን ዕቅድ አላችሁ?

ሐ) ብዙ ሚሊዮን ወጣቶቻችንን ለሥራ አጥነት ከዳረጉት የኤኮኖሚና የፖሊቲካ አመራር ጉድለት በተጨማሪ ያገራችን የትምሕርት ፖሊሲ የተዛባ እንደሆነ ምሁራን ይናገራሉ። የወደፊቱን ትውልድ በትክክል ቀርጾና ሞርዶ ለማዘጋጀት ደግሞ ካገሪቷ የኤኮኖሚ ዕድገትና የማምረት ዘዴ ጋር የተጣጣመ የትምሕርት ፖሊሲ መቀየስ ወሳኝ ነው። ታዲያ እናንት ይህንን አገራዊ ችግር ለመፍታት ምን ምን ዘዴ ቀይሳችኋል?

መ) ዛሬም የኢኮኖሚ ዋልታችን የሆነው 85% ሕዛባችን አርሶ/አርብቶ አደር ነው። ይህ ሕዝባችን፣ ከመቶ ዓመት በፊት ይጠቀምበት የነበረው ማረሻና ሞፈር ዛሬም አንዳችም መሻሻል ሳይደረግበት እያረሰበት ስለሆነ፣ ሌላው ሁሉ ይቅርና በቀን አንድ ጊዜ እንኳ ጠግቦ ሊበላ አልቻለም። እስቲ ድርጅቶቻችሁ ይህንን የኤኮኖሚ ዋልታችንን ተሸክሞ ዘላለሙን በችግር አለንጋ ለሚገረፈው አርሶ/አርብቶ አደር ሕዝባችን ያላችሁንና በፕሮግራማቸሁ ውስጥ ያካተታችሁትን ፍቱን መድኃኒት በአደባባይ ንገሩን።

ሠ) አገራችን ዛሬ ወደ ሶስት ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች አሏት። እነዚህ የርስ በርስ ግጭት ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችን ከቄያቸው ተፈናቀለው በጎረቤት ክልሎች ተጠልለው በተረጂነት እየኖሩ ነው። ያስጠለሏቸውም ጎረቤቶቻቸው የእንግድነት ጊዜው በመራዘሙ ምክንያት ሊሸኟቸው ይፈልጋሉ። ተፈናቃዮቹ ግን በቀድሞ ቄያቸው አካባቢ ያለው የጸጥታ ሁኔታ አስጊ በመሆኑ የመመለስ ፍላጎት የላቸውም። ዛሬ በተጠለሉበት አካባቢ ያለው የትምህርትና የጤና ተቋማት እንዲሁም ሠርቶ የመኖር ዕድላቸው በጣም ጠባብ ከመሆኑ የተነሳ ያስጠጓቸውን ሕዝቦች የተመናመነ የገቢ ምንጭና አገልግሎት እየተሻሙ ስለሆነ በመካከላቸው ራሱን የቻለ ግጭት መፈጠሩ አይቀሬ ነው። እስቲ ለነዚህ ወገኖቻችንን ያላችሁን ዘላቂ መፍትሔ ንገሩን።

ረ) ያገራችን የኤኮኖሚ ችግር ለዘመናት የተከማቸ መሁኑን እና በዛሬው ሁኔታ ማንም ውድድሩን አሸንፎ አራት ኪሎ ቢገባም በአጭር ጊዜ ሊያቃልለው የማይችለው ጉዳይ መሆኑን ጠንቅቃችሁ ታውቃላችሁ። ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ከፊተኞቹ የወረሰውን ችግር አገሪቷ በምታመርተው የእርሻም ሆነ የማምረቻ ዕቃ ለመቅረፍ ባለመቻሉ በዓለም አቀፍ የብድር ተቋማትና ከተለያዩ መንግሥታት በሚያገኘው ድጎማ ትንሽ እያንቀሳቀሰን ነው። እስቲ እናንተ አራት ኪሎ ስትገቡ እንዴት አድርጋችሁ ከዚህ ዘላለማዊ ዕዳ እንደምትገላግሉን አሳውቁን።

ሰ) በብሔሮች መካከል ግጭቶች በየቦታው እየተከሰቱ ነው። አንዳንዶቻችሁ የግጭቶቹን መንስዔ ኢትዮጵያ ከምትከተለው የፌዴራሊዝም አስተዳደራዊ ሥርዓት ጋር ስታያይዙ፣ ሌሎቻችሁ ደግሞ በፌዴራሊዝም ጥያቄ ላይ አንዳችም ድርድር አይኖርም ትላላችሁ። የግጭቶቹ ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ ግጭቶቹ ያላንዳች መዘግየት ዛሬውኑ መቆም አለባቸው። እስቲ እንዴት አድርጋችሁ ይህንን እጅግ ወደ ከፋ የርስ በርስ ጦርነት ሊወስድ የሚችለውን ግጭት ለማስቆም ያላችሁን ፕሮግራም አካፍሉንና ድጋፋችንን እንስጣችሁ።

ሸ) ሙስናና ብልሹ አስተዳደር፣ በአገልግሎት ሰጪ የመንግሥት መሥርያ ቤት ሠራተኞች ዘንድ የወንጀል ድርጊት መሆኑ ቀርቶ መደበኛ አሠራር ከሆነ ሰንብቷል። ይህን የሚያክል መንግሥታዊ ተቋም ደግሞ ለውጦ ሕዝባዊ ለማድረግ አነሰ ቢባል የአንድን ትውልድ ዕድሜ ይጠይቃል። ዛሬ ያለው ይህ ብልሹ ቢሮክራሲ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ በመሆኑ የዶ/ር ዓቢይም መንግሥት መጠነኛ ለውጥ እንኳ ለማድረግ እንደተሳነው ይስተዋላል። ታዲያ እናንተ ምርጫውን አሸንፋችሁ አራት ኪሎ ብትገቡ ይህንን ከስድስት ሚሊዮን በላይ ሠራተኛ ያቀፈውን ቢሮክራሲ ብልሹ አስተዳደር ለመቀየር ያላችሁ ፍኖተ ካርታ ምን ይመስላል?

ቀ) ዛሬ ኢትዮጵያ የምታራምደውን የውጭ ጉዳይ ፖሊቲካ ዜጎች በተለያየ መንገድ ይተረጉሙታል። አንዳንዶች ኢትዮጵያ በአሜሪካን መንግሥት ፍጹም ተጽዕኖ ሥር ናት ሲሉ ሌሎች ደግሞ የጎረቤት ዓረብ አገሮች ኢትዮጵያን እየተቆጣጠሩ ነው ይላሉ። የግብጽ አካሄድም ወደ ከፋ ጦርነት ሊያስኬድ ይችላል የሚሉም አሉ። እስቲ እናንተ አራት ኪሎ ስትገቡ እነዚህን የተወሳሰቡ የአገራችንን የውጭ ጉዳይ ፖሊቲካ እንዴት ለማራመድ ታስባላችሁ?

በነዚህ ጥያቄዎች ላይ በአደባባይ ስተወያዩ በጥሞና ከሰማናችሁና የያንዳንዳችሁን የፕሮግራም ሸቀጥ ይዘትና ጥራት ካመዛዘንን በኋላ ተሽሎ ላገኘነው ድምጻችንን በመስጠት ኮንትራት እንፈራረማለን። ያኔ እናንተም በሙሉ ልብ የሕዝብ አደራ አለብን ማለት ትችላላችሁ። ከዚያ በኋላ ከአራት ኪሎ ወንበራችሁ የተከበሩ ተብላችሁ ማይክሮፎኑን ይዛችሁ ከሌሎች እንደዚሁ የሕዝብ አደራ ተሸካሚ ከሆኑ ወዳጆቻችሁ ጋር ችግሮቻንን ለውይይት አቅርባችሁ ስታወያዩባቸው በቴሌቪዥን መስኮታችን እያየናችሁ፣ አይዟችሁ በርቱልን፣ የሠጠናችሁን አደራ ከግብ አድርሱ እያልን እናጨበጭብላችኋለን።

ለማጠቃለል ያህል፣

ውድ የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን ሆይ፣ የፖሊቲካ ሥልጣን አንድን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የምንጠቀምበት መሣርያ (tool) እንጂ በራሱ ግብ ወይም ዓላማ (objective) አይደለም። ስለዚህ አራት ኪሎ ብቻ አድርሱን እንጂ ለችግራችሁ የሚሆን መፍትሔ ከዚያ በኋላ እንፈልግለታለን ብላችሁ የኛን ድምጽ ለማግኘት አትጣሩ። መናጆ ሆነን ለዘመናት በኛ ስም ተመርጠው ኋላ ግን ራሳቸው ተመልሰው የችግሮቻችን አካል የሆኑብን ብዙ ወኪሎቻችንን አይተናል። ነገሩ እባብ ያየ በልጥ በረየ ከሆኖብን ሰንብቷል። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እስከ ዛሬ አንዳችሁንም በፈቃዳችን አልወከልናችሁም፣ አደራም አልሠጠናችሁም። አዎ! ማሕበራዊና ኤኮኖሚያዊ ችግሮቻንን ቀድማችሁ ተረድታችሁ ለችግራችን መፍትሔ ለመፈልግ መደራጀታችሁ እሰዬው ነው። ሆኖም ግን የኛን ችግር በትክክል ለመረዳታችሁ ማስተማመኛ ይሆነን ዘንድ በአደባባይ ቀርባችሁ ከሌሎች የፖሊቲካ ድርጅቶች ጋር ስትወያዩ፣ እግረ መንገዳችሁንም የኛን ችግር ለመፍታት የቀየሳችሁት የአጭርም ሆነ የረጅም ጊዜ ፕሮግራማችሁ ተመሳሳይ ወይም ተቀራራቢ ከሆነ ለምን አንድ ላይ ሆናችሁ በተባበረ ክንድ ይህን ለዘመናት የተጣበቀብንን ችግር ከሥሩ የማትነቅሉበትን ምክንያት ብትነግሩን ደስታችን ወሰን አይኖረውም። ማወቅ ያለባችሁ ግን ምርጫው ሊካሄድ ጥቂት ወራት ብቻ ነውና የቀረው እባካችሁ ተጣደፉና የምርጫ ሸቀጦቻችሁን አቅርቡልን። እኛም እኮ ወደ ምርጫ ገበያ ሄደን የሚስማማንን ሸቀጥ ለመግዛት ጊዜ ያስፈልገናል።

ውድ አንባቢዎች! በበኩሌ ይህንን ለውይይት መነሻ ይሆን ዘንድ አቅርቤአለሁ። ሁለት ነገሮችን ግን አንስቼ ጽሁፌን መጨረስ እፈልጋለሁ። በተለምዶ ዝም ብለን የፖሊቲካ ድርጅቶቹ የሚያቀርቡልንን ስሜታዊና ባዶ የሆነ፣ መሠረታዊ ችግሮቻንን ሊቀርፍ በማይችል የምርጫ ቅስቀሳ ብቻ መመራቱን እናቁም። በማንኛው ዘዴ ብናሰላው መሠረታዊ ችግራችን ደግሞ ድህነታችን ብቻ መሆኑን ጠንቀቀን ስለምናውቅ እንወክልሃለን ከሚሉን የፖሊቲካ ድርጅቶ መስማት የምንፈልገው ይህንን መሠረታዊ ችግራችንን እንዴት እንደሚፈቱልን ብቻ መሆን አለበት። ስለሆነም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየተጠቀምን ይህንን መሠረታዊ ጥያቄ ለድርጅቶቹ ማቅረብ አለብን። ድርጅቶቹ ለነዚህ ጥያቄዎቻችን መልስ ከሌላቸው ወይም ለመመለስ ካልፈለጉ ደግሞ፣ የፓርላማ በርን ለመክፈትም ሆነ ለመዝጋት ቁልፉ የኛ ድምጽ ስለሆነ፣ ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ፣ አለበለዚያ ድንጋይ ተብለህ ትጣላለህ ብለናቸው ሌላ የተሻለ ዘዴ እንፈልጋለን። በቸር ይግጠመን፣

*******

አዲስ አበባ፣ ጥር 23 ቀን 2020 ዓ/ም wakwoya2016@gmail.com

Back to Front Page