Back to Front Page

ክስ ተነሳላቸው?

ክስ ተነሳላቸው?

 

ከኡስማን ሙሉዓለም

የካቲት 03-03 2020

ከ ሃራ ገበያ

 

በህገወጥ መንገድ ስልጣን የያዘው የአብይ የባለፀጎች ፓርቲ አስተዳደር በያዘነው ሳምንት ታስረው የነበሩ የፖለቲካ እስረኞችን ክሳቸው እንዲቃረጥና ከእስር እንዲፈቱ አደረኩኝ ብሎ በገዛቸው ሚድያዎች የፕሮፖጋንዳ ዜና ሲነዛ ሰንብቷል። ዋናው ጉዳይ ግን ለምን ታሰሩ? ለምን ክሳቸው ተነሳ? ምን ጥቅም ለማግኘትና ቀጣይ ምን ታሳቢ ተደርጎ ነው ክሱ የተቃረጠው? የሚሉ ጥያቄዎች ማየቱ ለትግላችን ፍንጭ ይሰጣል።

 

በመጀመርያ ደረጃ ያለምንም ጥፋት በእስር ሲሰቃዩ ለቆዩትና ከእስር የተለቀቁት ስልሳ ሶስቱ ዜጎች እንኳን ደስ አላቹሁ። እንኳን ከምትወዱዋቸው ቤተሰቦቻችሁና ወዳጆቻችሁ በሰላም ተገናኛቹሁ ለማለት እወዳለሁ። ለደረሰባቹሁ ጥቃት በፅናት መክታቹሁ መቆየታቹሁ ፍትሕ አጥተው አሁንም በአፋኙ መንግስት እስር ቤቶች በግል ቂምና በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት ታስረው እየተሰቃዩ ላሉትና በትግል ለሚገኙት ለመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ብርታት ነውና ሳላደንቃችሁ ማለፍ ተገቢ አይሆንም።

 

ለምን የፖለቲካ እስረኞች ማሰር ከመጀመርያው ተፈለገ?

በኔ ዕይታ የአብይ መንግስት ምንም የለውጥ ራዕይና አጀንዳ ሳይኖረው የስልጣን እርካብና መንበር ላይ ለመውጣት የህዝቡን የለውጥ ፍላጎት ጠልፎ ራሱን የለውጥ ሃዋርያ ሰይሞ በባዶ የቀለም አብዮት የሚያምሩና የሚስቡ ቃላቶች ማንነቱን ሸፍኖ በሴራ፣ በህገወጥና በውጭ አገር ሃይሎች ድጋፍ ስልጣን ተቆጣጠረ። ሁሉንም የህዝብ የለውጥ አጀንዳ አቀዋለሁኝ፣ ለውጥ አመጣለሁ፣ ህዝቡ ዝም ይበል እኔ ራሴ ወደ ዲሞክራሲ አሸጋግራቹሃለሁኝ ብሎ ባዶ ተስፋ በመስጠት ከጫፍ እሰከ ጫፍ ጊዚያዊ ተቀባይነትና ታዋቂነት አገኘ። ምንም ራእይና ብቃት ሳይኖረው ስልጣን የወጣው የስልጣን ጥመኞች ቡድን መሪ አብይ አህመድ ስልጣን ተቆጣጥሮ ከያዘ በኃላ ስልጣን ከሩቅ ሲያዩት ያምር ሲይዙት ግን ያደናብር ሆኖበት የትኛውን ችግር ፈቶ የትኛውን በሂደት እንደሚፈታው ችሎታም፣ ብቃትም፣ ፍላጎትም የሌለው ጨቅላ ተደነባባረ፡፡ ማጠፍያው ሲጠፋው ሰበብ መፈለግ ውስጥ ለመግባት ጊዜ አልፈጀበትም። አጭር የጫጉላ ሽርሽር ጊዜውን ጨርሰ፡፡ በአሸዋ ላይ መሰረት አድርጎ የነበረው ጊዚያዊ ድጋፍ እንደ ጉም መብነን ጀመረ። ይህን ክስተት የራሱ ችግር አድርጎ መቀበል ሲገባው ችግሩ ወደ ፀረ-ለውጡ ናቸው ብሎ የሰየማቸው ህወሓትና በኃላ ደግሞ ኦነግን ቆየት ብሎም አብንን ላይ መቀሰር ተያያዘው።

Videos From Around The World

 

ከመጀመርያው ጀምሮ በጥልቀት የታደሰውና ኢህአዴግ በገመገመውና መፍትሄ ብሎ ባስቀመጠው መንገድ መሰረት ህገ መንግስቱን እና ፌደራል ስርዓቱን በማጠናከርና የህዝቦች ጥያቄ በቅድመ ተከተል እንፍታና የህዝበኝነት (populist) መንገድ ጊዚያዊ ሞቅታ ካልሆነ መሰረታዊ ለውጥ አያመጣም ያለውን ህወሓትን ያለፉት ሁሉም ችግሮች ብቸኛ ተጠያቂ በማድረግ አባላቱንና አመራሩን ብቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብንም ዒላማ አድርጎ መስደብ፣ ማጥቆር፣ ማሳደድ፣ ማሰርና መግደል ተያያዘው። ኮሽ ባለ ቁጥር ወያኔን መክሰስ አፍ መፍቻው እስኪመስል ድረስ ደጋገመው። ማሰርም ጀመረ። ከድህንነት መስርያቤት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከማረምያቤት እና ከሜቴክ ትግርኛ ተናጋሪዎችንና የትግራይ ተላላኪ ናቹሁ ብሎ አገራቸውን በቅንልቦና ያገለገሉ የሌሎች ብሄር ተወላጆችን ጨምሮ ዘረኛ በሆነ አግባብ ማሰር ጀመረ።

ለምን ዓላማ?

1ኛ) ህወሓትና የትግራይን ህዝብ መድፈር ሌሎችን በቀላሉ ለመድፈር እችል ይሆናል ብሎ በጨቅላ አንጎሉ በማሰቡ ነው።ይህን በተደጋጋሚ ከአደረጋቸው ንግግሮች ማረጋገጥ ይቻላል።የሲዳማ ህዝብን ጥያቄ ለማዳፈን ፓርላማ ፊት ቀርቦ በጨቅላ ድፍረቱ እንደ ሶማሊ ክልል ህገመንግስት ሳይበግረንና ጨፍልቀን እንዳደረግነው እናድርጋቹኃለን ብሎ መናገሩ በቂ ማሳያ ነው።

 

2ኛ) የህዝብን ጥያቄ መመለስ ሲያቅተው የራሱን ችግር ለመሸፋፈን ህግ ማስከበር እጀምራለሁ የሚያደናቅፉኝ መጀመርያ ላስወግድ ብሎ ያለ አበሳቸው ወነጀለ፡፡ አሰረም።

 

3ኛ) የውጭና የውስጥ ሽብርተኞች፣ ፀረ-ሰላም የሆኑትንና የህዝብ ጠላቶችን ለማስደሰት፡፡ ህዝባዊ መሰረት ስሌለው የነዚህን ወንጀለኞች ድጋፍና ትብብር ለመግዛት በተለይም ከግንቦት ሰባትና ከኤርትራው ኢሳያስ የተሰጠውን ስም ዝርዝር ይዞ ማሰር ጀመረ።

4ኛ) ይህ ስልጣንና ስልጣን ብቻ! ብሎ ቆርጦ የተነሳው ቡዱን ጥገኛ በሆነ መንገድ ራሱን ወደ ገዥ መደብ ለመቀየርና በሌብነት መንገድ ለመበልፀግ የሚያደርገው ጉዞ ያደናቅፉኛል ብሎ የለያቸውን የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በፍርሓትና በቂም በቀል ማሰሩ በሱ ቦታ ሁነህ ሲታይ ትክክል ነው።

 

ታድያ አሁን ምን ተገኝቶ ነው የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት የጀመረው?

 

1ኛ) የፍርድ ቤት ሂደቱን እንደተከታተልነው እስረኞች ምንም ዓይነት ክስ ለመመስርት የሚስችል እንከን እንደሌላቸው ታይቷል። ብዙዎቹ ምስክሮች የተባሉትም ተጨባጭ ነገር ሊያቀርቡ አልቻሉም።ብዙዎች ምስክሮችም የተባሉም ዐቃቤ ህግ ተብየው ሊያቀርብ ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱክሱ ሰርዞታል። የትኛውም ዓይነት የተከሰሱበት ክስ እስር ቤት የሚያቆይ ምክንያት የለውም በማለት ፍ/ቤት በዋስ ይፈቱ ብሎ አዛል፡፡ ይሁንእንጂ የኮኔሬል አብይ መንግስት አዲስ ክስ መስርቶ መረጃና ማስረጃ አለኝ ብሎ በግላጭ ከፍ/ቤቱ በላይ ሆኖ ግግም ብሎ አልፈታም እንዳለ በተደጋጋሚ ያየነው ነው።አሁን ደግሞ ቀድመን ክስ አነሳን ብለን በማንኛውም ጊዜ መልሰን ብናስራቸው ይመረጣል ብሎ መፍታቱን ወስኗል።

 

2ኛ)በማሰር፣ በማሳደድና በመግደል የህዝቡን ትግል ማስቆም እችላሎህ፣ ማንበርከክ ይቻላል ቢልም አልቻለም።ሊቀረቅረው ያሰበውን ህዝብ ሊቀረቀርልት ሳይችል ቀርቶ በህዝቦች ትግል ራሱ ተቀረቀረ።ይህም በመሆኑ ክስ አነሳሁኝ እኛ የሰለም የእርቅ ሃይሎች ነን ብሎ አዲስ የገፅታ ግንባታ ለማካሄድ ነው።

 

3ኛ) በተለይም የትግራይ ተወላጆችን አስሮ መደራደርያ ለማድረግ የነበረው የአብይ መንግስት ፍላጎት ውጤት አልባ በመሆኑ ስልት መቀየሩ የግድ ስላለ ክስ ለማንሳት ተገዷል።ኢህአዴግ በነበረበት ወቅት አብይ የህወሓትን አመራር እስረኞቹን እፈታቸዋለሁ እናንተም ለምን ፈታ አታደርጉም ትግላቹሁንና የሚድያ ስራቹሁን? ዐቃቤህግ ነው ያሰራቸውና ለማስፈታት እስቲ እንነጋገርበታለን ሲል ነበር።ህወሓት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማሳደዱና ማሰሩ ይቁም፣ የታሰሩትም ካለ ቅድመ ሁኔታ ይፈቱ፣ የተገደሉትም በገለልተኛ ይጣራና ይመርመር! ነበር አቋሙ። አብይ ይህ የድርድር አጀንዳ ሊሆን አይችልም ብሎ ፅኑ አቃም ያዘ።በዚህ ምክንያት የድርድር ዕድሉ ዝግ ነበር፡፡ አሳሪው ራሱ! አሁን ይፈቱ ባዩም ራሱ! ክስ አነሳሁኝ ባዩም ራሱ! ፈቺውም ራሱ ሆነ።

 

4ኛ) ወሳኙ ምክንያት! የህዝቦች ትግል እያየለ መምጣቱና የአብይ መንግስት ቀን ተቀን በህዝብ ክፉኛ እየተጠላ በመምጣቱ ነው።ፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው የህዝብ ትግል ውጤት ማምጣት መጀመሩ ዋነኛው ምክንያት ነው።የባለጠጎች ፓርቲ የህዝቡን ልብ ሊያለሰልስ ይችል እንደሆነ ብሎ ነው የፖለቲካ እስረኞችን የፈታቸው።

 

ክስ በማንሳት ምን ትርፍ ለማግኘት?

1ኛ) እያየለ የመጣውን የህዝቦች ትግል ለማለሳለስ ይቻል እንደሆነ ሙከራ ማድረግ ነው። በፀረ ትግራዋይነታቸው በግላጭ የታወቁት ኮነሬሉ ፓርቲያቸው ፒፒ የማለሳለስ ስራ ለመስራት አስቦ ነው። ለሽማግሌዎቹ ፍታ አላቹሁኝ ፈታሁኝ! በኔ በኩል ለሰላም ለዕርቅ ብዬ ፈትቻቸዋለሁኝ።እኔ ፀረ ትግራዋይ አይደለሁም ለማለት ነው።በህወሓት በኩልም ቢሆን ምሳጋና ቢቸሩኝ ባይሆንም በኔና በፓርትዬ ላይ የሚያደርጉት ዘመቻ ቢቀንሱ አገር መረጋጋት ላይ ቢተባበሩኝ ብሎ ሽማግሌዎችን ሰብኮ ለመላክ ነው። እንደኔ ግን ኮነሬሉ እውነተኛ ከሆኑ ለምን የትግራይን ህዝብ ለምን ይቅርታ አይጠይቁም?ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች ለምን አይፈቱም?የነሰዓረ ገዳዮችን ለምን አይነግሩንም?

 

2ኛ) ከህወሓት ጋር እርቅ ጀምረናል ብሎ የህብረፌደራላዊ ሐይልን ለመበተንና ሞራል ለመስበር ነው። ነገርግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ህወሓት ለብቻው የሚደራደርበት ምክንያት የለውም።የአብይ መንግስት ከትግራይ ህዝብና ከድርጅቱ ህወሓት የተጣላው በአላማ ልዩነትና ህገመንግስቱንና የፌደራል ስርዓቱን በጠራራ ፀሓይ በማፍረሱ ነው፡፡ የትግራይ ተወላጆች በመሆናቸው ትግርኛ ተናጋሪ በመሆናቸው የሚገደሉበትና የሚፈናቀሉበት ምክንያት በመቃወማቸው ነው።ሌሎች ህዝቦችም ተመሳሳይ ምክንያት ይዘው ከአብይ መንግስት ተጣልተው የትግል ትብብር ፈጥረው የሚታገሉበት ድርጅትና መድረክ ፈጥረው ማኒፌስቷቸውን ቀርፀዋል።ሌሎችም በደቡብ የሚገኙ ፌደራላዊ ሐይሎች የትብብር ድርጅት ፈጥረው እየታገሉ ነው።ድርድር ከሆነ የሚፈለገው የአብይ መንግስት በህገወጥነት ከያዘው ስልጣን ወርዶ እሱና የግሉ ፓርቲ የሆነው ፒፒ በአንድ በኩል ሌሎች ደግሞ ህገመንግስቱና ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማዳን ብሎም አገራችን ከመበታተን ለማዳን የቆሙ ሐይሎች በሌላ በኩል ሆነው ነው መካሄድ ያለበት።ለየብቻ በተናጠል የሚባል ነገር አይኖርም። የአብይ ዓላማ ግን ክስ አቋርጫለሁኝና እርቅ ይፈፀም ይላሉ፡፡ ከዛ ደግም በትግራይ ህዝብና በፌደራል መንግስት መካከል የነበረው አለመግባባት ተፈታ ይባላል። ለጥቆም በትግራይና በአማራ ክልል መንግስታት የነበረው አለመግባባት ተፈታ ተብሎ ይሰበካል።የፒፒ ሊቀመንበሩ ተሳስቼ ነው የፒፒ ፕሬዝደንት አብይ አህመድ እነዚህን እግሮች ፈቱት ተብሎ ተቀባይነታቸው ከፍ ለማድረግ ነው።በምርጫ የማሸነፍ ዕድላቸው ከፍ ብሎ ነበር ተብሎ አጭብረብረው ለመመረጥ በጌቶቻቸው የውጭ መንግስታት ለሚደረገው የምርጫ ማጭበርበር ሴራ ዝግጅትና ትርፍ ለማግኘት የተደረገ የእስረኞች መፍታት ሙከራ ነው።ከኤርትራም ጋር ዕርቅ ሽምግልና ከህወሓት ጋር ይደረግ ተብሎ የወደቀ ገፅታቸውን ምንም እሴት ያልፈጠረው የኖቤል ሽልማት መመለስና የስልጣን ዕድሜ መጨመርም ያለመ ነው።

 

3ኛ) ዋነኛው ትርፍ በነሱ አተያይ (በአብይ ቡዱንና በውጭ አገር ደጋፊዎቹ) አብይን በስልጣን ላይ ለማቆየት ነው፡፡ ምርጫ አጭበርብሮ ቀጣይ አምስት ዓመት ስልጣን ይዞ ለመቀጠል ቀንደኛ ጠላትና አደናቃፊ የሆነው ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አሁን አንበርክኮ ማሽነፍ፡፡ ካልተቻለ ግንተፅእኖውን ከትግራይ ውጭ እንዲቀንስና እንዲያቆም ማድረግና በትግራይ አጀንዳ ብቻ ታጥሮ እንዲቆይ ማድረግ፡፡ ይህንን ለማድረግ ጊዜ ገዝተው ውስጥ ውስጥ ህውሓትና የትግራይ ህዝብን አንድነት ለመሸራረፍና የሁሌም ምኞታቸውን ስልጣናቸው ማሳካትና በረዥም ጊዜም ህወሓትን ማጥፋትና የትግራይን ህዝብ ማንበርከክ።ስለዚህ የአጭር ጊዜ ስልታቸው የህብረ ፌደራሊስት ሐይሎችን ከህወሓት ጋር የምታደርጉት የትግል ህብረት አቁሙ።መቐለ አትመላለሱብሎ ማስፈራራት።በሚድያም ለሃያ ሰባት ዓመት ሲያስራቹሁ ሲገድላቹሁ ከነበረ ህወሓት ወያኔ እንዴት ግምባር ተፈጥራላቹሁ? ህወሓት በስልጣን እያለ ፌደራል ስርዓት አልነበረም፡፡ የኦሮሞ ክልላዊ መንግስት የአማራ ክልላዊ መንግስት የሚባል አልነበረም።ተላላኪዎች ብቻ ነበሩእያሉ ይሰብካሉ።ሌላው በአጭር ጊዜ ከትግራይ አሁን ለጊዜው ሰላም ማውረድ ብለው ስትራተጂና ታክቲክ ቀይሰው እየተሯሯጡ ነው።

 

በመጨረሻም ይህንን ለመስረገጥ አንድ መረጃ ላካፍላቹሁ። እስከምን ድረስ የውጭ ሐይሎች በአገራችን የውስጥ ጉዳይ በሩ ተበርግዶ እንደተከፈተላቸው የሚሳይ ነው። ምን አለ የሀገሬ ሰው? አገሬን ለወራሪ አሳልፌ አልሰጥም አለ! እያልን ገዥዎቻችን ግን እየሸጡን ነው። ፈጥነን ግብረምላሽ ካልሰጠን መመለስ የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንወድቃለን። አንድ የአሜሪካ የሪፓፕሊካን መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት በኢትዮጵያ የአብይ አህመድ ተቀባይነት ጥናት አካሂጄ አገኘሁት ያለውን ውጤት አሁን ውስጥ ለውስጥ ሌላ ጊዜ ደግሞ በአደባባይ ዘርግፎ አብይን ለማስመረጥ እያደረገ ያለውን ጥረት ለማየት ያስችላል። በኦሮሚያ ህዝብ ላይ ጦርነት ከፍቶ በአውሮፕላን ሳይቀር ጭፍጨፋ እየፈፀመ ያለው አብይ 90% ተቀባይነት እንዳለው አጠናሁ እያለ ነው። በአማራ ክልል ሰላም አንድነት እንዳይኖር አድርጎ መንግስት አልባ ባደረገው ክልልም 65% ተቀባይነት አለው ብለው አስቀምጠዋል። ህገመንግስትን ጥሶ የናይሮቢ መንግስት የሚባለውን የሞስጠፌን መንግስት ባቃቃመበት ሶማሊ ክልልም አብይ 95% ከፍተኛውን ተቀባይነት ሰጥተውት አረፉት። ሌላው የሚያስቀውም መዋሸት ካልቀረ ብለው በትግራይ ክልልም 29% ተቀባይነት አለው እያሉ ነው። ወዘተ። ትንሽ ቆይተውም እስረኞች ከተፈቱ በኃላ ሽምግልና ተደርጎ ዕርቅ ከተደረገ በኃላ ተቀባይነታቸው መጨመሩ በጥናት አረጋገጥን ይሉናል። ይህ ቀልድ አይደለም! እውን ለማድረግ እየታገሉን ነው። በታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሻቸውን እየፈተፈቱ ነው። በመንግስት ልማት ድርጅቶች ሽያጭ የደላላነት ስራ እየሰሩ ነው። ሆኖም ግን በዚህ ጫወታ የሚገባ የውጭ ካምፓኒ/ኢንቨስተር ማንም እንደማይቀበለው አውቆ ቀልጦ እንዳይቀር ቢጠነቀቅ ቀድመን እንመክራለን። በኢትዮጵያ ህዝቦች ደም የለሙ ልማቶች በህገወጥ ተላላኪ መንግስት ተዋውሎ ገዥቻለሁ ማለት አይችልም። በአድዋ ድላችን የምንኮራ ህዝቦች በስልጣን ጥመኞች አመካኝነት በኤሌትሮኒክስና በፌክ ኒውስ ለዛውም በጥልቅ ውሸት በዙር እጅ ቅኝ ሊገዙትን ቆርጠው ተነስተዋልና ወጊድ እንበላቸው።

 

እኛ ምን እንበላቸው?

ከሁሉም በፊት

         አብይ ከስልጣን ይውረድ።

         ሁሉም የፖለቲካ እስረኛች ይፈታ።

         በህገ መንግስቱ መሰረት አብይ ከስልጣን ወርዶ ፓርላማው ፈርሶ ፕሬዝደንቱ የሚመሩት የባላደራ መንግስት ይቋቋም። የዚህ ባላደራ መንግስት ተግባር ባለው ህገመንግስት መሰረት የምርጫ ዝግጅት አድርጎ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ እንዲደረግ ማድረግ ብቻ ነው።

ለዚህም በአብይ አስተዳደር የተሾሙ ገለልተኛ ያልሆኑ የምርጫ ቦርድና የፍ/ቤት ሹመኞች በገለልተኛ እንዲተኩ ማድረግ ይገባል። በዚህ ሂደት የማንኛውም የውጭ የምዕራብም የምስራቅም የአረብም ጣልቃ ገብነት አንሻም። እርዳታ ከፈለግንም እኛው ራሳችን የምንመርጣቸውና በውስጥ ጉዳያችን የማይወስኑ ጥሪ ማድረግ እንችላለን!

 

ቸር እንሰንብት።

የኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ያሸንፋል!

የአድዋ ውግያ ድል የህዝቦች የተባበረ ትግል ውጤት መሆኑን አንረሳም!

 

Back to Front Page