Back to Front Page

ከአንድ ሰው ሥልጣን ይልቅ ህዝብ ይቅደም!!

 

ከአንድ ሰው ሥልጣን ይልቅ ህዝብ ይቅደም!!

ከአብሳር፤07/07/2020

ሰሞኑ አሳዛኝ ቢሆንም የድርጊት ሰሞን ሆኗል። በአርቲስት ሃጫሉ ግድያ የመስከረምን ጎርፍ የመቀነስ ሴራ በአብይ ቡድን ተጀምሯል። የአርቲስት ሃጫሉን ደም በሰኔ ወር ለአዲስ አበባው ቆሪጥ ግብር ተከፍሏል። እነሱ የሰኔ ወር አዙሪት ቢሉትም የዘመኑ የፖለቲካ ሴራ ሆኖ መመዝገቡ አልቀረም ። ሴራው የተፈጸመው መስከረም ወር ከሚያጋጥመው የፖለቲካ አጣብቂኝ ለማምለጥ አስቦ እንደሆነም የሚገመት ነው። በአገራችን ለገጠመው ህገ መንግስታዊ ቀውስ የፖለቲካ መፍትሄ ከመሻት ይልቅ የተመረጠው መንገድ የመላላጥ ፖለቲካ መሆን አልነበረበትም ። አገራችን በታሪኳ መሰል ሁኔታዎችን ማለፍ እና መሻገር አቅቷት ዘለግ ላለ ግዜ ቀውስ ውስጥ የገባችበት ጊዜ ጥቂት አልነበረም። የችግሩ ምንጭ ደግሞ በአጋጣሚ የፖለቲካ ሥልጣን የያዙ ግለሰቦች አምባገነን መሆናቸው ነው። የአሁኑ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ የፖለቲካ ወንጀል በማብዛት የሚፈታ አይሆንም። የመስከረም የፖለቲካ እሳት የሚፈታው ከህዝባዊ ሀይሎች ጋር በመደራደር አዲስ የሽግግር መንግስት በማቋቋም ይሆናል። ይህም በህገ መንግስቱ መሰረት ሥልጣኑን ለብሄራዊ ሀይሎች ማስረከብ ከቻለ ብቻ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሥልጣኑን በማጭበርበር የማራዘም ሴራው ከቀጠለ ግን ወደ ባሰበት የእርስ በርስ ጦርነት መግባታችን አይቀሬ ይሆናል። አሁንም አገሪቱ ጦርነት ውስጥ መሆንዋ የሚታወቅ ነው። ሁላችንንም የሚያድነን ህገ መንግስት እና ህገ መንግስት ብቻ ነው። ሰሞኑን የኦሮሞ ማህበረሰብ የፖለቲካ መሪዎች ታስረዋል። ደም ማፍሰስ፤ ማሰር ህዝባዊ ትግልን ያጋግለው እንደሆነ እንጂ ሊያቆመው አይችልም። የገዢው ቡድን ተንኮልና ትንኮሳ ተከትሎ በገጠመው ህዝባዊ ተቃውሞ የብዙ ሰው ህይወት ተቀጥፏል። በማከታተልም ነጻ ሚድያዎች መታገዳቸውን ሰምተናል። አገር ወዳድነት የሚለካው ለህዝብ ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት እንጂ የፖለቲካ አየሩን የሚረብሽ ጠበኛ እርምጃ በመውሰድና በማፈን እንዳልሆነ ሊታመንበት ይገባል ።

የሰሞኑ የፖለቲካ ድርጊቶች በራሳቸው ትላልቅ ጉዳዮች ቢሆኑም ትርጉሙ የተሟላ የሚሆነው ከዋናው የትግል አውድ ከህገ መንግስታዊ ስርአቱ ጋር አስተሳስረን ከተመለከትነው ብቻ ነው። በአሁኑ የትግል መድረክ ሁለት ተቃራኒ ሀይሎች ለመሸናነፍ እየተቧቀሱ ይገኛሉ ። በአብይ የሚመራው ቡድን ህገ መንግስቱን በመቅደድ አሃዳዊ መንግስት ወይም ስርአት ለመመስረት ጥድፊያ ላይ ይገኛል። በሌላ በኩል ደግሞ ፌዴራሊስት ሀይሎች ህገ መንግስታዊ ሥርአቱን ለማዳን ያላሰለሰ ትግል በማካሄድ ላይ ይገኛሉ። የመስቀል አደባባይ ፍንዳታ፤ የስመኘው ፤ የሰአረ እና የአማራ ክልል መሪዎች ግድያዎች የትግሉ መገለጫዎች ናቸው። ወንጀሎቹ የተፈጸሙት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሰፍኗል በተባለበት ወቅት መሆኑ ሲታሰብ የፖለቲካ ሴራ ቀመር መጀመሩን ያረጋግጣል ። የተጠቀሱት ወንጀሎችና ሌሎችም ተድበሰብሰው ሲቀሩ የተመለከተ ሰው በመንግስት ላይ ጥርጣሬው ቢጎላ የሚገርም አይሆንም። በፖለቲካ ቀመሩ በአሸናፊነት ለመወጣት ታስቦበት የተፈጸመ ለመሆኑ አስረጂዎች ናቸው።

Videos From Around The World

ገዢ ቡድኑ በተቀየረ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ላይ መገኘታችንን ሊገነዘብ ባለመቻሉ እና ያለው የአቅም ውስንነት ተደምሮ የሴራ ፖለቲካ መርጧል። የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮምያ የተፈጠረውን ሁኔታ ስንመለከት የኦሮሞ ህዝብ የፖለቲካ ሃይል መሆኑን አስመስክሯል። ወጣቱ ትውልድ የኦሮምያ ይሁን ሌላው ኢትዮጵያዊ የትላንት እረኛ አይደለም። የተማረ እና መረጃ የሚያጣጥም ምክንያታዊ ትውልድ ተፈጥሯል ። የሚታለል ትውልድም አይደለም። እንደውም በቴክኖሎጂ የታገዘ ነው።

የኦሮሞ ህዝብ ትግል በአገራችን ትልቅ ንቅናቄ ፈጥሯል። የአረብ አብዮት(Arab spring) በአገራችን ቀስቅሷል። ትግሉ በኦሮሞ ህዝብ ብቻ ሳይታጠር የመላው ህዝቦች ትግልም ሆኗል። ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች የትግል አጋርነታቸውን አሳይተዋል። ትግሉ በአገር ደረጃ እንዲቀጣጠል ድርሻቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። ትግሉ መስመር ይዟል። ትግሉ ፍትህ ፍለጋ እንጂ ማንንም ብሄር የማግለል አላማ የለውም። ሲዳማ ወላይታ ከምባታ ወዘተ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛሉ። ዛሬ ዋናው የትግል ቋጠሮ ህገ መንግስቱን ከጨፍላቂው የአብይ ቡድን መታደግ ነው። ህገ መንግስቱ የሁላችንም የአበበ ፤ የገመቹ ፣ የሃጎስ እና የመሀመድ የጋራ ማሰባሰቢያ እና ጥሪት ነው። የአብይ ቡድን በኦሮሞ መሪዎች ላይ የወሰደው የፈሪ እርምጃ አዲስ እስትንፋስ አይፈጥርለትም። የበከተ ፖለቲካ እንደገና ሊያንሰራራ የሚችልበት ዕድል ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም።

የቀበሮ ባህታዊያን አብይ እና ግብረ አበሮቹ ፍላጎት ሁላችንም በየጓዳችን ተለያይተን ሃይላችንን በታትኖ እርስ በርስ እንድንተራመስ ነው ። የድሮ ዘመን ገዢዎች ከመጋረጃ በስተጀርባ ከፋፍለህ ግዛ ዘይቤ ሲጠቀሙ የቆዩ ሲሆን የዛሬ ገዢዎቹ ግን ፊት ለፊት በቴሌቭዥን በአደባባይ ሲፈጽሙት ይታያል። አማራና ትግራይ ጀርባ ለጀርባ ተሰጣጥተው እንዲሰነብቱ ሴራ ተሰርቶባቸዋል። በአብይ ዘመን ሁለቱም ህዝቦች እንዲነጋገሩ የሚፈቀድላቸው አይመስለኝም ። በተመሳሳይ ሁኔታ በኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ትብብር እንዳይኖር አበክሮ ሲሰራበት ቆይቷል ። ፌደራል ሃይሎች እንዳይተባበሩ በገንዘብ ይገዛል ያስኮበልላል።

ህገ መንግስታዊ ስርአትን ለማዳን በመካሄድ ላይ ባለው ትግል ሁሉም ወገን እንዲሳተፍበት ይጠበቃል ። የአማራ ህዝቦችም ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ትግላቸውን እንዲያስተሳስሩ ይጠበቃል። እንኳንና ዛሬ በጨለማው ዘመን ሳይቀር ዋለልኝን የመሰለ ፋና ወጊ መስዋዕት የከፈለበትን ፈለግ መከተል ያስፈልጋል። ነፍጠኝነት የቀድሞ ገዢዎች እንጂ የአማራን ህዝብ አመለካከት አይወክልም። የአገራችንን ተስፋ ያጨለመው የአብይ ቡድን የሁሉም ህዝብ ጠላት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። በዚህ ትግል የአማራ ህዝብ ከሌሎች ህዝቦች ጋራ ትግሉን ማስተባበር አለበት። የአማራ ህዝብ ከገዥዎች ጋር የሚያስተሳስረው የለም። የአሁኑ ተስፈኞችም ከህዝቦች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የላቸውም። ትግላችን ከገዢዎች ብቻ ነው ።አብይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያንን ተስፋ የዘጋ ነው።ሌሎች ታጋዮችም ይህን ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ኢትዮጵያ ከኦሮሞ ብሄረተኝነት ጋር ታርቃ መኖር ትችላለች። ኢትዮጵያዊነት የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ድምር እንጂ በምትሃት የተገኘ አይደለም። ኦሮሞነትን ማቀንቀን የሚበረታታ እንጂ ስጋት የሚሆንበት ምክንያት የለም፡፡

ህገመንግስታዊ ስርአት የፖለቲካ መረጋጋት መሰረት መሆኑ የሚታመንበት ቢሆንም የህገ መንግስት ጥሰት የአፍሪካ ዕዳ ከሆነ ሰነባብቷል ። አንዳንድ የአፍሪካ መሪዎች የአገሪቱ ህልውና ከነሱ በሥልጣን መሰንበት ጋር ያቆራኙታል። ይህን ሲፈጽሙ ደግሞ አጎብዳጆች ተአምራታዊ ሃይሉን እንዲመሰክሩለት በማስገደድም ጭምር ነው ።አንተ ከሌለህ አገሪትዋ ትጠፋለች ተብሎ ንግርት ይነገርለታል። በልጅነቴ ንጉሱ በወረዱ ሳምንት በአካባቢያችን ንፋስ በዝቶ የንጉሱ ቁጣ ነው ሲባል እንደነበር አስታውሳለሁ። ነብሰ ገዳዪ መንግስቱም ቢሆን መሃንዲስ፣ ሃኪም፣ ወታደር፣ ወዘተ መስሎ በመቅረቡ ለአገራችን የተላከ ምትክ የለሽ ብቸኛ ሰው መሆኑን የሚያሳይ ትርክት እየተሰራለት ነበር፡፡ ጠ/ሚሩ በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ አዳኝ ነው ተብሎ እንዲታመንለት በርትቶ ሲታትር ይታያል። ይህን ለማሳመንም በሰው ፊት አንገቱን ደፍቶ የማስመሰል ጸሎት ሲያደርግም ይታያል።

አብይ እስካሁን በአገራችን ለተፈጸሙት ወንጀሎች ገና ደማቸው ሳይደርቅ ባለቤት ሲያፈላልግ ይስተዋላል ።በአገራችን ይህን የሚገልጽ አነጋገር የሰረቀ ሌባ ሌባ ሌባ እያለ ይሮጣል የሚለው ነው።ገራሚው ነገር ቡድኑ ከተፈጸሙት ወንጀሎች ለማትረፍ ሲታትር መታየቱ ነው። በመጀመርያ ራሱን ከወንጀሉ ነጻ ያደርጋል። ቀጥሎም ሌሎች አካላትን በመወንጀል ዘመቻ ያካሂዳል ። ግድያዎቹ ትላልቅ የፖለቲካ ግድያ መሆናቸው ሲታይ ደግሞ መንግስት ቀጣይ ወንጀል ከመፈጸም እንደማይመለስ መገመት ይቻላል። ሃጫሉ ከተገደለ በኋላ አብይ ተቃዋሚዎቹን ለመጥረግ የተጠቀመበት ቢሆንም ትርፉ ዘላቂ አልሆነም። በተቃራኒው ድርጊቱ ያስከተለው ኪሳራ ከባድ ነው ። አርቲስቱ ግዙፍ ስብዕና ያለው ለብሄር ብሄረሰቦች እኩልነት የታገለ የዘመናችን ብርቅ አርቲስት በመሆኑ ግድያው ተዳፍኖ የነበረውን ቁጣ አቀጣጥሎታል፡፡

በአሁኑ ሰአት ብዛት ያላቸው የፖለቲካ ሰዎች ዘብጥያ ተወርውረዋል ። ብዙዎቹ በለውጡ እምነት አሳድረው ከውጭ የመጡ ናቸው። ባንድ አገር ደግም የፖለቲካን እምነት ከመብላት የባሰ ወንጀል የለም። ከእንግዲህ ያበደ ካልሆነ በስተቀር አብይን የሚያምን አይኖርም። አሁን በቤተመንግስት የተኮለኮሉትም ቢሆኑ አገልግሎታቸው እስኪሟጠጥ እንጂ እንደ ሎሚ ተመጠው መጣላቸው አይቀርም ።

ሌላው ትኩረት ትግራይ ነው። የሚኒሊክ ቤተመንግስት ከተጀመረ ግዜ ጀምሮ በትግራይ ላይ ተኝቶ አያውቅም። ቤተ መንግስቱ ሁሌም ቢሆን በትግራይና በኦሮሞ ጉዳይ ሁሌም ተንኮል እንደጎነጎነ ነው። የአዲስ አበባ እስር ቤቶች በትግራይና በኦሮሞ ልጆች የተሞሉትም ያለምክንያት አይደለም። የነበረ ነው። ትግሉም ይህን ለመቀየር ነው። የአዲስ አበባን ፖለቲካ ለማስተካከል የተደረገው ጥረት ችግር ገጥሞታል። የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶች እሴት ነፍጠኝነት በመታገል ህብረ ብሄራዊ እኩልነትን መሰረት ያደረገ ስርአት መገንባት ነው። ህወሃት የፈጸማቸው ስህተቶች መሰረታዊ ማንነቱን የሚንዱ ነበሩ ማለት አይቻልም። ትግራይን አልወድሽምም አልፈታሽምም እያሉ መቀጠል አይቻልም። the game is over በተቃራኒው እንደሚሰራ መገመት ይበጃል።

ሌላው አስተውሎ የሚፈልግ ጉዳይ አሁን እየተፈጠረ ያለው የሀይል አሰላለፍ ነው። ባሁኑ ወቅት ቤተመንግስትን የተቆጣጠረው አሃዳዊ ሃይል ብጤዎቹን እያሰባሰበ ይገኛል። በዙሪያው ነፍጠኛ ሚዲያዎች አሰልፏል። የቀድሞ የደርግ አባላት የቡድኑ አባላት ሆነዋል። የትላንት የቅንጅት ቀኝ አክራሪዎች ወይዘሪት ብርቱካንንም ጨምሮ ሁሉንም አይነት ድጋፍ በማድረግ ላይ ናቸው። ብሄር ብሄረሰብ ጠል ቡድኖች ከጎኑ ተሰልፈዋል። አምባገነኑ ኢሳያስ እና የጸጥታ ሃይሉ ከቡድኑ ጎን ቆመዋል። በተቃራኒው ግንባር የፌዴራል ዲሞክራሲ ሃይሎች ናቸው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ድጋፍ አላቸው። ግንባሩ ማዶ ለማዶ ሆኖ የአቋም አንድነት ያለው መሆኑ ቢታወቅም ሰፋ ያለ ግንባር መፍጠር ሲችል በተበታተነ ሁኔታ ትግሉን እየመራ ይገኛል። አሜሪካ የሚገኙት ታጋዮች የተሻለ መቀራረብ ያላቸው ቢሆኑም በተመሳሳይ ሁኔታ በአገር ደረጃ መፈጠር ነበረበት። በመቀሌ ተፈጠረ የተባለው የፌዴራሊስት ቡድኖች ጥምረት የሚደገፍ ቢሆንም የተቀላቀሉት ቡድኖች ማህበራዊ ተቀባይነታቸው በአግባቡ ሊጤን ይገባዋል። አሁን የpolitical opportunism ማብቃት አለበት። የአቋም ወቅት ነው።

 

በመጨረሻም አገራችንን ከዲሞክራሲ ውጭ ለማስተዳደር መሞከር አይቻልም። ዲሞክራሲ ሁሌም በለውጥ ሃዲድ እንድትጓዝ ይረዳል። በአገራችን የፖለቲካ ስልጣን የብሄር ብሄረሰቦች እንጂ የግለሰቦች አይደለም። የፖለቲካ ስልጣን በጓደኝነት ተጠራርተህ የምትከፋፈለው ቅርጫ አይደለም። ይህም ቢሆን በየወቅቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች እየታደሰ የሚሄድ መሆን አለበት ። የኢትዮጵያ ትልቅነት የሚገኘው ከህብረ ብሄራዊ ዲሞክራሲያዊነት ብቻ ነው። አገራችን በአፍሪካ ያላት ተቀባይነት እየተረጋገጠ እንዲሄድ ስራው ከቤት መጀመር አለበት። አንድ ቀንም ቢሆን ባልተመረጠ መንግስት ስር ማደር የለብንም። አገራችንን ከቀውስ ለማውጣት ያለው ብቸኛ መንገድ ምርጫ ማካሄድ ብቻ ነው ።

 

 


Back to Front Page