Back to Front Page

መከላከያ ሰራዊታችን ምን ይመስላል?ክፍል አራትና የመጨረሻ

መከላከያ ሰራዊታችን ምን ይመስላል?

ክፍል አራትና የመጨረሻ

 

ዑሱማን ሙሉዓለም

ከሐራ-ገበያ

ግንቦት 25፣ 2012ዓ.ም.

 

ውድ አንባቢዎች በክፍል ሦስቱ ፅሑፌ አሁን ያለው የመከላከያ ሰራዊታችን የፅንስ ሐሳባዊና ተጨባጭ አቅም ለማሳየት ተሞክሯል። በዚህ የመጨረሻ ክፍል ደግሞ የሞራል አቅሙ/moral component/ ምን ላይ እንደሚገኝ እናያለን።

 

አውደ ጦርነት ያለ የሰዎች እንቅስቃሴ ሊኖር አይችልም። ሰዎች ከሌሎች መሰል ሰዎች በውትድርና ብልጫ የሚኖራቸው ደግሞ በሞራል ብቃታቸው ነው። ይህ የማይታበል ሐቅ ነው፡፡ ሳይንስ ነው፡፡ የሰራዊት የሞራል ብቃት ስንል የሚከተሉትን ያጠቃልላል።

 

በመጀመርያ ደረጃ ጦርነት ለውጊያ የተዘጋጀ ሞራላዊ ልበሙሉነት ያለው ሐይል ይጠይቃል። ይህ ማለት አካላዊ ብቃት፣ ቁርጠኝነት፣ ታማኝነት፣ ችግር የመssም ብቃት፣ በራስ በመተማመን ሁኔታዎችን መሞከር፣ ፈጥኖ ነገሮችን ማገንዘብና መንቀሳቀስ፣ ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር ራስን ማስተካከል እና ከሌሎች አብሮ የመስራት ፍላጎትና ችሎታ ያለው የሰው ሐይል ማዘጋጀት ነው። አደጋ ለመጋፈጥ የተዘጋጀ በስሜት፣ በቁርጠኝነትና በፍላጎት ህይወቱን ለመሰዋት የሚያስችል የአገር እና የህዝብ ፍቅር አላማ ማንገብንም ይጠይቃል። የእምቢ! አልገዛም! ባይነት ስሜትና ታሪክ ያለው ትውልድና ይህ ልምድና ታሪክ በትክክለኛ መንገድና ሙያዊ በሆነ መንገድ ለሰራዊቱ ግንባታ ሲውል ነው። በዚህ ግንባታ ሞራላዊ ስብእና ያለው ሰው ማዘጋጀትና መፍጠር ሲቻል ነው።

Videos From Around The World

 

በአሁኑ ግዜ አብዛኛው የመከላከያ ሰራዊታችን ጦርነት የሚፈልገው ሞራላዊ ልበሙሉነትና ዝግጁነቱን መጠበቅ የማይችልበት ሁኔታ/ደረጃ ላይ ይገኛል። ከኢትዮ-ኤርትራ ግንባር ከተሰለፈው የመከላከያ ሰራዊት ውጭ ያለው ሰራዊት እንደ ሚሊሻ ተበጣጥሶ ተልእኮው ባልሆነ ስምሪት ላይ እየተሳተፈ ይገኛል። የሚሰጠው ግዳጅም የሚሊሻ ወይም የፖሊስ ነው፡፡ ለዚህ የስምሪት ግዳጅ ምንም ስልጠና አልተሰጠውም፡፡ በህግም ሐላፊነት አልተሰጠውም፡፡ ወደ ግዳጅ እየተሰማራ ያለው በአብይ አገዛዝ በደል ተፈፅሞብናል ብለው ጥያቄ በሚያቀርቡ ህዝቦች፣ ሐይሎችና ቡዱኖች ላይ ነው በራሱ በአብይ መንግስት እርምጃ ውሰድ እየተባለ ያለው። በዚህም የተነሱት ዓመፆች ለመቆጣጠር በሚያካሂደው ግዳጅ የሚሞትና የሚቆስል ወታደር ቀላል የሚባል አይደለም። ከተበታተነው የመከላከያ ሐይል አንድም ሁለትም ሲሞትና ሲቆስል እየታያ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለጦርነት ያውም የአገር ዳርድንበርና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ የተዘጋጀው የመከላከያ ሐይል በተበጣጠሱና ውጤት በማይታይባቸውና የማይመለከቱት ግዳጆች ብዙ ወራት ተበታትኖ በመቆየቱ የመደበኛ ሰራዊትነት ስሜቱ ጠፍቶታል፡፡ ሞራላዊ ልበሙሉነቱም እንዲሁ ተሸርሽሯል።

ህገመንግስታዊ ባልሆነና በይፋ ባልታወጀ የአስቸካይ ጊዜያዊ አዋጅና በኮማንድ ፖስት ስም በተደጋጋሚ ስምሪት እየተሰጠው ነው፡፡ የመካላለያ ሰራዊቱም የማያምንበትና በየሄደበትም ውጤት የማያገኝ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የነበረው ቁርጠኝነትነ እና በራስ መተማመን ተዳክሞ ሞራላዊ ስብእናው ተነክቷል። በኢትዮ-ኤርትራ ድንብር ያለው ሰራዊትም ከኤርትራ ጋር የተደረገው የሰላም ስምምነት ደስ አሰኝቶት የነበረ ቢሆንም አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግልፅ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ግራ እየተጋባ ነው። የራሱ መንግስት በድብቅ ከኢሳያስ ጋር የሚያሴረው ምን እንደሆነ ባለማወቁም በራሱ መንግስት ላይ ጥርጣሬ አድሮበታል። ግራ መጋባቱና ጥርጣሬው ከግዜ ወደ ግዜ እየጨመረ ነው፡፡

 

ሰራዊታችን ዳርድንበሩ በመጠበቅ ላይ ሞራሉና ልበሙሉነቱ እንደተጠበቀ ነው፡፡ ነግር ግን በተለይ ከቅርብ ግዚያት ወዲህ ከፊት ለፊቱ ያለው የጠላት ሰራዊት በተኩስ የተደገፈ ልምምድ ሲያደርግ፣ የቅኝት ስራ ሲሰራ፣ የወገንን ምሽግና አሰላለፍ ዝርዝር ሁኔታ ሲያጠና፣ ተዳጋጋሚ ስብሰባዎች በብዛት ከአስመራ እስከ ግንባርና ከክፍለጦሮች እስከ ጋንታዎች ሲያካሂድ ይታያል፡፡ በኛ መንግስት ደግሞ የኢሳያስ መንግስት ምንም ትንኮሳ ወይም ወረራ አይፈፅምብንም እየተባለ ስለሚሰበክ የሚያየውና የሚነገረውን እየተለያየበት ግራ ተጋብቷል። ይህ ግልፅ ያልሆነ ግን በጣም የሚያጠራጥር ሁኔታ በሰራዊቱ ሞራላዊ ስብእና

የሚያጎድለው ነገር ይኖራል። በተጨማሪም በኢትዮ-ኤርትራ ድንብር ያለው ሰራዊት በደጀን ያለው አካሉ የሆነው የመከላከያ ሰራዊት መበታተንም ያሳስበዋል፡፡ ኢህገመንስታዊ በሆነ ግዳጅ በሚፈፅማቸ ተግባራትም ሞራሉን የሚነኩ ናቸው።

 

ሁለተኛው ለውጊያ የተነሳሳ ሐይል መኖር ነው። ተነሳሽነት ለውጊያ በቁ ምክንያት ይጠይቃል። ተነሳሽነት የብቁ ስልጠና፣ በታጠቀው መሳርያና በመሪዎቹና በአስተዳደሩ መተማመን፣ በጥሩ ስራውና በውጤቱ ልክ የሚያገኘው እውቅናና ሽልማት እና በሚያገኘው ክብር የሚገኝ ድምር ውጤት ነው። የተነሳሽነት ሁኔታ ለማወቅ አሁን ያለው የተነሳሽነት ስሜት ምን ላይ ነው ያለው እናምንስ ይጠበቃል የሚሉትን ሁለቱም መገንዘብን ይጠይቃል። ተነሳሽነት በውጭ የህዝብና በሌሎች ተፅእኖ ስር ነው። የመዋጋት ፍላጎት በዋናነት የሚጠናከረውና ዘላቂነት የሚኖረው ሰራዊቱ የአገሩ ህዝብ ይደግፈኛል ደጀኔ ነው ብሎ እምነት ሲያሳድር ነው። በእያንዳንዱ የሚሰራውና እርምጃው ውጤት ሲያገኝ ነው። ውጤቱም በሰራዊቱ ገፅታ አውንታዊ ነገር በህብረተሰቡ የሚፈጥር ሲሆንና ለቀጣይ ስራውና ግዳጅ መነሳሳት ሲፈጥር ነው፡፡

 

የመከላከያ ሰራዊታችን ተነሳሽነት በአሁኑ ግዜ ሲታይ ከማንኘውም ጊዜ በላይ ተጎድቷል። የሚወደው፣ የሚያከብረውና የሚተማመንበት መሪው ጀነራል ሰዓረ መኮነን መገደሉ እንዳይበቃ አሟሟቱ ሳይጣራ እስካሁን መቆየቱ በሰራዊቱ ከፍተኛ ሀዘንና የተደበቀ ቁጣ ፈጥሯል። በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ሁለተኛ እንዳትጠይቁ! ይህ የመንግስት ጉዳይ ነው መንግስት ራሱ ያጣራዋል ተብለው እንዳይጠይቁ በመታፈናቸውም ቅሬታ አሳድራል። የሰራዊቱ ሪፎርም ነገር ወሬ ሆኖ መቅረቱ ከፍተኛ ተስፋ መቁረጥ አስከትሏል። ሰራዊቱ ለትልቅ ጦርነት ስልጠና ማድረግ የሚችልበት ጊዜና ሁኔታ የለውም። የሰራዊቱ ሞራል በብር ለመግዛት ያሰበው የአብይ መንግስት ሊሳካለት አልቻለም። ኑሮ በከፍተኛ ደረጃ ውድ በሆነበት ወቅት የ50% ዶሞዝ ጭማሪ አድርጎ የሰራዊቱ ሞራል ለማሻሻል ቢሞክርም በኑሮ ሁኔታው ምንም ለውጥ ባለማምጣቱ በሰራዊቱ ሞራል ያመጣው ፋይዳ የለም። እዚህ በአደባባይ መግለፅ በማልፈልገው በብዙ መንገድ ሰራዊቱ ቅሬታውን እያንፀባረቀ ነው። ተነሳሽነት የህዝቡ ተፅእኖም በአዎንታዊም በአሉታዊም ይነካዋል። በሰራዊቱ ያሉ ኦሮሞዎች በኦሮሞ ህዝብ እየደረሰ ያለው ግፍና መከራ ይሰማቸዋል። በተሳሳተ አተያይ የኛ መንግስት ብለው ለአብይ ድጋፍ የነበራቸውም አሁን ያ ድጋፍቸው የለም። የደቡብ ክልል ተወላጅ የሆኑትም የተለያዩ የህዝቡ ጥያቄዎች ማለትም የሲዳማ፣ የከምባታ እና የወላይታ ህዝቦች ጥያቄዎች በሐይል፣ በአፈና፣ በግድያ፣ በማሰር፣ በገንዘብ በመደለልና በሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች በመታፈኑ ደስተኞች አይደሉም። የአማራ ተወላጆችም በተሳሳተ የፖለቲካ አተያይ በመጀመርያ የነበረው የድጋፍ መነሳሳት የሚመስል ስሜት አሁን በቦታው የለም። በቅማንት ላይ የሚደረገው ጭፍጨፋ፣ ያለው ጎንደሬ፣ ጎጃሜ፣ ወሎየ የሚል መከፋፋል እና በሌሎች ጉዳዮች ምክንያት ትላንት ጠንካራ የነበረ ክልል ወደኃሊት መጓዙና መገዳደል መብዛቱ የአማራ ክልል ሰላም የሌለው በመሆኑ በጣም ተከፍተዋል። የትግራይ ተወላጆችም በትግራይ ህዝብ ያነጣጠረ የጥላቻ ፖለቲካና ጥቃት፣ እስር እና መገለል በከፍተኛ ደረጃ ቅሬታ እንዲሰማቸው ሁነዋል። ከሌሎች ክልሎች የመጡ የሰራዊቱ አባላትም በየክልላቸውና በአጠቃላይ በአገሪቱ ባለው ሁኔታ ደስተኞች አይደሉም፡፡ ይህ እያለ የመከላከያ ሰራዊታችን ሞራልና ተነሳሽነት አለ ለማለት ያስቸግራል። ከሁሉም በላይ ደግሞ መንግስት ይህን ሰራዊት ወደ ጎን አስቀምጦ የራሱ አምሳያ የሆነ ቅልብ የሚመስል ሰራዊት ሪፐፕሊካን ጋርድ በሚል በአስር ሺዎች እያደራጀ መሆኑም የሰራዊቱ ተነሳሽነት የሚገድል ተግባር የፈፀመ ነው።

 

ሦስተኛው የሞራል ብቃት ምንጭ መሪነት /leadership/ ነው። ወታደራዊ መሪዎች የሰው ልጅ ተፈጥራዊ ባህሪ ተገንዝበው የነዚህ የሚመሯቸውን ሰዎች ጭንቅላት በብቁ ሀሳብ መማረክና ያዘዙትን የሚፈፅም ሐይል መፍጠር የሚችሉ ማለታችን ነው። መሪነት በሰራዊትና በወታደራዊ ዓለም አረአያነት፣ ራስ መተማመን መፍጠር እና ግዳጅ እንዲፈፀም ማስቻልን ያጠቃልላል። ብቁ መሪዎች የሚባሉት ጠንካራና ማመዛዘን የሚችሉ ሙያዊ ብቃት የተጎናፀፉና ችግርን ለመፍታት ወደኃላ የማይሉና መልካም አጋጣሚዎችን መጠቀም የሚችሉ ናቸው። በሚመሩት ሰራዊት ተቀባይነትና ክብር የሚኖራቸው ብቁ መሪዎች መሆናቸው በተግባር ሲያሳዩና ዲሲፒሊን ያላቸውና በጀግንነታቸው በተግባር የታወቁና ሁሉ የሚመሰክርላቸው ሲሆኑ ነው። ሰራዊቱን ሁሌ ማዘጋጀት የመሪዎች ቁልፍ ስራ ነው። ጦርነትን በሰላም ጊዜ ሰርተው መገኘት ይጠይቃል። ሞራል ያለው ሰራዊት በሰላም ጊዜም በጦርነት ጊዜም መስራት የመሪዎች ስራ ነው። መሪዎች ብቃት ያለው የመሪነት ሚና የሚጫወቱት ጥሩ አስተዳዳሪዎች በመሆን የተነሳሳ እና በራሱ የሚተማመን ሐይል መፍጠር ሲችሉ ነው።

 

የመከላከያ ሰራዊታችን መሪዎችን ስንመለከት አንድ ወጥ የሆነ አመራር በሌለበት የመሪነት ብቃታቸውን መገምገም ፋይዳ የለውም። መከላከያ ሚኒስትሩ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተኮራረፉ ወራቶች አስቆጥሯል። ሰራዊቱ ይህን በሚገባ ያውቃል። ከክፍለጦር አዛዥች በላይ በተሰበሰቡበት ስብሰባ አቶ ለማ መገርሳ የህገመንግስቱ የመጨረሻ ምሽግ ናቹሁ! ሲል ተሰብሳቢዎች ጭብጨባቸውን ያቀለጡት ቀደም ብሎ በነበረውና አብይ አህመድ በሰበሰበው ስብሰባ ህገመንግስት መጠበቅ የናንተ ስራ አይደለም የመንግስት ነው በማለቱ ተከፍተው ቆይተው ስለነበር ነው። ልዩነቱን ራሳቸው ያዩትና አገር ሁሉ የሚያቀው ነው። ጀነራል ሰዓረ በግፍ ከተገደለ በኃላ የተሾመው ጀነራል አደም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ በሰራዊቱ ማንም የተቀበለው የለም። ምንም ብቃት የሌለው ሰው ነው ተብሎ በሁሉም የሚመዘን ነው። ይህ ያራሱም የሰራዊቱም ሞራል ይነካል። ነክቷልም። ብቃት ያላቸው እያሉ ለምን እሱ ተመረጠ? የሁሉም የሰራዊት አባላት ጥያቄ ነው። መላሽ የለም እንጂ! ጀነራል ብርሃኑ ጁላን ጨምሮ የጀነራል አደም ሹመት ማንም አልተቀበለውም አይቀበለውም። በዚህ የተነሳም በሁለቱም መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ አይደለም። እንደ ለማና አብይ ባይኮራረፉም ደካማ ግንኙነታቸው ሰራዊቱን ለመምራት ዕንቅፋት ነው። በአሁን ሰዓት ጀነራል ብርሃኑ ጁላ ይፋዊ ያልተሾመ ኤታማዦር ሹም ነው። ጀነራል አደምም እጅ ሰጥቶ ስልጣኑና ሐላፊነቱ ካስረከበ ቆይቷል። ጄነራል ብርሃኑ የተሻለ ብቃት አለው። በሰራዊቱም ዘንድ ተቀባይነት አለው። በጀነራል ሰዓረ የቀብር ስነስርዓት የተናገረው ንግግር በሰራዊቱ ብቻ ሳይሆን በመላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ተስፋ ያሳደረ ነበር። ሆኖም ግን በኃላ የኦሮሞ ህዝብ በሰራዊቱ ሲጨፈጨፍ፣ የሲዳማ ህዝብ በሰራዊቱ ሲጨፈጨፍ እና ህገመንግስቱ በኮ/ል አብይ በጠራራ ፀሐይ ሲጣስ የመከላከያ ሰራዊት የመጨረሻው ምሽግነቱ መቼ እንደሆነ ሰራዊቱ ግራ ገብቶታል። በተጨማሪም ብዙ ጀነራሎች ከስራ ውጭ ሁነው ደሞዝ የሚወስዱ መኖራቸው ሞራልን የሚገድል እንጂ የሚፈጥር አይደለም። የሚመለከታቸው አመራር አንድነት ባጡበትና ህገመንግስት እየፈረሰ ባለበት ሁኔታ የሰራዊት የሞራልና ልበሙሉነትና ስብእና ይኖራል ማለቱ ያስቸግራል። በዚህ ዓይነት ሁኔታም የሰራዊቱ ሞራል መፍጠርና መጠበቅ አይቻልም፡፡

 

በማጠቃለል ሲታይ የመከላከያ ሰራዊታችን ሁኔታ እንደ አገራችን ሁኔታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል። ከአሁን በኃላ አገርንም ለማዳን መጀመርያ መከለከያ ሰራዊታችን ራሱን ማዳን ሲችል ነው። ትልቅ ስም በጥሩ ተግባር ፈጥሮ የበረው ሰራዊታችን ፅንሰሐሳባዊ አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክሞና የነበረው ሞራላዊ ብቃት ተሸርሽሮ ተጨባጭ አቅሙ የተበተነና ያልተዳረጀ ሆኖ ይገኛል። ኮ/ል አብይ ይህን የኢትዮጵያ አጋር ሰራዊት ሊያፈርስ ቆርጦ መነሳቱ የተነሱት ነጥቦችና ሂደቱን በማየት መገንዘብ ይቻላል እላለሁ። ሰራዊታችን ነቃ በል! ለማለትም እወዳለሁ።

 

መልእክት ለሰራዊታችንና ለአመራሩ፡-

 

በአሁኑ ወቅት በስልጣን ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠውና ለለውጥ ተዘጋጅቶ የነበረውን ኢህዴግን ከውጭ ሐይሎችና ከፀረ ህዝቦች ጋር በመሆን አፍርሶ ባልተመረጠና ህዝቡ በማያቀው ፕሮግራም የተመሰረተ እና ራሱን ብልፅግና ብሎ በሰየመ ሐይል ህገመንግስታዊ ባልሆነ መንገድ ስልጣን ተቆጣጥሯል። የክልሎች ህገመንግስታዊ ስልጣን ጥሶ በክልሎች ውስጣዊ ጉዳይ መፈትፈት የጀመረው ገና ከጥዋቱ ነበር። ከዛም ብዙ የህገመንግስታችን ድንጋጌዎች ሲጥስና ሲያፈርስም ቆይቷል። ኮ/ል አብይ ሰራዊቱ የህገ መንግስት የመጨረሻ ምሽግ አይደለም ያለበት ምክንያትም አሁን ግልፅ ሆኗል። ህገ መንግስት በጠራራ ፀሐይ እየጣሰ ስልጣኑን የሚቃወሙና ጥያቄ የሚጠይቁ ህዝቦች፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና ሂስ የሚያቀርቡ ጋዜጠኞች የሚታሰሩበትና የሚገደሉበት አሁን ደግሞ በኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ ጦርነት የሚታውጅበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ሰራዊቱ ለዚህ ፀረ ህገመንግስት እርምጃ ተባባሪ መሆን አይጠበቅበትም። አይገባምም፡፡ በአገራችን ያለው ቀውስ የማይፈታ ከሆነም አገር እየፈረሰች ዝም ብሎ ማየት አይጠበቅበትም። ከህገመንግስት ጎን ከቆሙ ህዝቦች መቆም ይጠበቅበታል።

 

የውጭ ሐይሎች በአገራችን የውስጥ ጉዳይ እንዳሻቸው እንዲፈተፍቱ በሚፈቅድው የኮ/ል አብይ መንግስት ፖለቲካ አያገባኝም ማለት የህገመንግስት የመጨረሻ ምሽግነቱ የሰጠውን የኢትዮጵያ ህዝቦች አደራ መብላት ነው። የአሜሪካ መንግስት የግብፅ መንግስትን ደግፎ በህዝቦች ላብ የተገነባውን ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ በታቀደለት ጊዜና አቅም እንዳይፈፀም የራሳችን መንግስት ፈቅዶ እጃቸውን እንዲያስገቡ ዕድል አንዴ ስለሰጣቸው ሲፈተፍቱ ህዝቡ በተለይም አገር ወዳድ ሙሁራን ከጫፍ ጫፍ ጉዳዩን በመቃወም በመጮሃቸው የአብይ መንግስት ደንገጥ ብሎ ቢያዘገየውም ሙሉ በሙሉ ነገሩን ወደ እጁ መልሶ ባለማስገባቱ ፕሮጀክቱ አደጋ ላይ ወድቃል።

 

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ አብይ አሕመድ በእብሪተኛነት አገራችን ወሮ ለጦርነት ዳርጎን ከነበረው ቀንደኛ ጠላታችን የሆነው የኤርትራው ፕሬዝደንት ብቻ ጋር የሰላም ስምምነት አድርጎ የህዝቦች እንቅስቃሴ ገድባል፡፡ ኢሳያስ አሁንም ሰራዊቱ በተጠንቀቅ አሰልፎና ሰፊ የስለላ ስራ በመስራት አገራችንን ለመውረር ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በተጨማሪም የኤርትራ ሰላዮች በኢትዮጵያ እንዳሻቸው የሚንቀሳቀሱበትና የኢትዮጵያ ሉአላዊት አካል በሆነችውን የትግራይ ክልል ላይ ደባ እንዲፈጥር ተፈቅዶላቸው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ። በኢትዮጵያ የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ካምፖች እንዲፈርሱ በኢሳያስ ቀጥተኛ ትዕዛዝ ተወስኗል። ሰራዊታችን ይህን ቀጥተኛ የሆነ በአገራችን የውስጥ ጉዳይና ብሄራዊ ጥቅማችን የሚፃረር ጣልቃ ገብነት በችላ ማየት አይገባውም።

 

ከሱዳን የነበረን መልካም ግንኙነት በኮ/ል አብይ የዲፕሎማሲ ውድቀት ተበላሽቷል። ለግብፆችና ለኤርትራው አምባገነን ኢሳያስ ይህ ከሱዳን ጋር የነበረው ግንኙነት መበላሸት ትልቅ ድልና ዕድል ነው። የአጭር ጊዜ ብቻ የሚያዩ አንዳንድ ወገኖችም ከሱዳን የነበረን ግንኙነት የሚያበላሽ ሁኔታ እየፈጠሩ ነገሩን እያባባሱት ናቸው። በሱዳን በኩልም ከኢትዮጵያ የሚኖራቸውን ስትራተጂካዊ ጥቅም ትተው በትናንሽ ጥቅማጥቅም ነገሩን ማጋጋል የሚፈልጉ አሉ። ሱዳን ከግብፅም ከኤርትራም የበለጠ ብሄራዊ ጥቅሟን ማስጠበቅ የምትችለው ከኢትዮጵያ ጋር ነው። ኢትዮጵያም እንዲሁ። ስለዚህ ይህን ሁኔታ በጥበብ መፍታት እየተቻለ ለውጭ ሐይሎች በሚጠቅም መንገድ እየተባባሰ ነው። በቅርቡ ተወረናል የሚባለው ከሱዳን ከሆነ በምንም ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት የለብንም። በውይይትና በድርድር ብቻ ሊፈታ ይገባል። ለኤርትራው ኢሳያስና ግብፆች የተመቸ ሁኔታ ማመቻቸት የለብንም።

 

በመጨረሻ ግን ከሁሉም በላይ አገራችን እንድትፍረስ አንፍረድባት። አገር ከፈረሰ ሰራዊትም መፍረሱ የግድ ነው። የሰራዊታችን ገፅታ እንዲበላሽ ሆነ ብሎ እየሰራ ያለው ቅጥረኛው ኮ/ል አብይን ፖለቲካዊ ችግርህን ትፈታ እንደሆነ ፍታ ሰራዊቱ ህገመንግስታዊ ያልሆነ መንግስት ትዕዛዝ አይፈፅምም ብለን እምቢ እንበለው! ስልክህ ጮኸ ተብሎ ሰው አይገደልም እንበለው!።

 

ቸር ሰንብቱ!

 

ግንቦት 20 በኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ ለዘላለም ይኖራል!         

ኢትዮጵያችን ለመፍርስ አልተፈረደባትም!

ሰራዊታችን የህገመንግስቱ የመጨረሻ ምሽግነቱ አሁን ያረጋግጥልን!

Back to Front Page