Back to Front Page

መከላከያ ሰራዊታችን ምን ይመስላል? ክፍል ሁለት

መከላከያ ሰራዊታችን ምን ይመስላል?

 

ክፍል ሁለት

 

ዑሱማን ሙሉዓለም

ከሐራ-ገበያ

ግንቦት 18፣ 2012ዓ.ም.

 

 

ውድ አንባቢዎች በመጀመርያው ክፍል በአፄ ኃይለስላሴና በደርግ ዘመን የኢትዮጵያ ሰራዊት (ሰራዊታችን) ምን ይመስል እንደ ነበር በአጭሩ አቅርቤ ነበር። በዘመነ ኢህአዴግ የነበረው ሰራዊት ለማየት የኢህኤዴግ ሰራዊት ፀረ-ደርግ ባደረገው ጦርነት በአጭሩ ምን ይመስል ነበር? ከዛም የአገር መከላከያ ሰራዊት ለመመስረት የተደረገው እንቅስቃሴና ውጤቱ ምን እንደሚመስል በአጭሩ እናያለን።

 

በዋነኛነት የህወሓት ስራዊት በኃላ ደግሞ የኢህዴን ሰራዊት አንድ ላይ ተደራጅተው የኢህአዴግን ሰራዊት ፈጥረው ነበር። ሁለቱም የግንባር አባላት የየድርጅቶቻቸው ሰራዊትና ግዳጆች የሚፈፅሙ ቢሆንም አብዛኛው ጊዜ በጋራ ተቀናጅተው ውጊያዎች ያደርጉ ነበር። ይህም ሆኖ ግዙፍ ሰራዊት የነበረው የህወሓት ሰራዊት ነበር። ህወሓት ትጥቅ ትግል ከጀመረበት ከ1967ዓ/ም ጀምሮ የሰራዊት ሐይል እያደራጀ ነበር፡፡ ወደ ደርግ መደምሰሻው ወቅት ብዙ ክፍለጦሮች ብቻ ሳይሆን ብዙ ግምባሮች ላይ በአንድ ጊዜ ኦፕረሽን ማድረግ የሚችል በዕዝ የተደራጀ ሐይል ነበረው። ሜካናይዝድ ብርጌዶችም አደራጅቶ ይዋጋ ነበር። የኢህዴን ጦርም በክፍለ ጦሮች የተደራጀበት ሁኔታ ነበር። ሶስተኛው የግንባሩ አባል የነበረው ኦህዴድም መጨረሻ አካባቢ ሲደራጅ በሻለቃዎች የተደራጁ ተዋጊ ሰራዊት ነበረው። ይህ ሰራዊት በሦስቱ የመዋጋት አቅም ሲመዘን እንዴት ነበር ብሎ ማየቱ ጠቃሚ ነው። የውጊያ/ጦርነት ፅንሰሐሳቡ፣ ተጨባጭ አቅሙና ሞራላዊ አቅሙ እንዴት ስለነበረ ነው እስከ አፍንጫው የታጠቀውና ወደ ሚሊዮን የሚጠጋ የሰው ሐይል የነበረውን የደርግ ሰራዊት በአውደ ውግያ ለማሸነፍ የቻለው የሚለውን ለማየት ይረዳልና።

Videos From Around The World

 

ህወሓት እስከ 1976ዓ/ም አጠቃላይ ጦርነቱን የሚመራበት አቅጣዎች የነበሩት ቢሆንም የጠራ ወታደራዊ መስመር /ዶክትሪን/ አልነበረውም፡፡  በአጠቃላይ ጦርነቱንና እያንዳንዱ ውጊያዎችንም የሚያካሂድበት መመርያና መርሆ መንደፍ እንዳለበት የአስር ዓመቱ የትግል ጉዞውን ሲገመግም አመነ፡፡  ህዝባዊ ጦርነቱንና ውጊያዎችን እንዴት ይመራና ይፈፅም እንደ ነበረ መሰረታዊ ግምገማም አደረገ፡፡  መሰረታዊ ለውጥ ለማድረግም ወሰነ። ጦርነቱ ለማሸነፍ የሚያስችል ወታደራዊ መስመር እና ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ለመታጠቅ ብዙ ጥልቅ ጥናት በማካሄድ  ለመጀመርያ ጊዜ ወታደራዊ መስመር  /ዶክትሪን/  መቅረፅ ቻለ። በመሆኑም በብዙ የአፍሪካ አገራት በመንግስት ደረጃም ይሁን በነፃ አውጪ ይሁን አርነታዊ ሰራዊቶች የሌለ ባለዶክትሪን ሰራዊት መፍጠር ቻለ። በዚህም ግልፅ ወታደራዊ ስትራተጂያዊ ፕላን በማዘጋጀት እንዴትና መቼ የደርግን ሰራዊት የመዋጋት ብቃት በማምከን የፋሽስት ደርግ ስርዓት ማንኮታኮት እንደሚቻል ዝግጅቱን እና እንቅስቃሴውን በመጀመር ውጤታማ ስራ መስራት ቻለ። የኢህአዴግ ሰራዊት በተጨባጭ አቅሙ በምንም መመዘኛ ለምሳሌ በሰው ሐይል፣  በመሳርያ እና በስንቅና ሎጂስቲክ አቅሙ ከደርግ አቅም ሲነፃፀር በጣም አነስተኛ ነበር። የነበረው አቅም በቁጠባ አሟጦ የመጠቀም ችሎታ ግን ነበረው። ሞራል፣ ተነሳሽነት፣ የዓላማ ፅናት፣ ህዝባዊነት፣ ቁርጠኛ አመራር እና የአስተሳሰብ ልዕልና እና ብቃት ነበረው። የግንቦት 20 ድል የዚህ ፅንሰ ሐሳባዊ አቅምና የሞራል የበላይነት ውጤት ነው።

 

ከ ግንቦት 20 ድል በኃላ ይህንን ሐይል እንደ እርሾ በመጠቀምና ከደርግ ሰራዊትም ወጣቶች፣ ዕውቀትና ችሎታ የነበራቸውን በመጠቀም በህገመንግስቱ መሰረት ከማንኛውም ፓርቲ እና ከማንም ፖለቲካ መሪ አሽከርነት ወይም ስልጣን የማራዘም ግዳጅ ነፃ የሆነ ለህገመንግስት ተገዥና የህገመንግስቱ የመጨረሻ ምሽግ እንዲሆን ተደርጎ በህገመንግስቱም በአዋጅም በመመርያም ተደንግጎ የኢትዮጵያ ሰራዊት በአዲስ መልክ የተደራጀው። የግንባታው ማእከልም ህገመንግስታዊና የህዝቦች ሉዓላዊነት የሚያከብርና የሚያስከብር ፕሮፈሽናል ሰራዊት ለመገንባት የሚያስችል ስልጠና በሰፊው ተሰጠው። ዋናው የአገራችን ህዝቦች ጠላት ድህነት እንደሆነና ድህነትን ለማጥፋት በሚደረገው ርብርብ የአገር ዳር ደንበር እንዲጠብቅ በሚል ለልማትና ለፈጣን ዕድገት የተመቻቸ ሰላም ማረጋገጥ የሚያስችል ሆኖ ስምሪቱ ታቀደ። በአካዳሚም በወታደራዊ ዕውቀትና ችሎታ ብቃት እንዲኖረው ብዙ ማሰልጠኛ ተማትና እስከ ዩኒቨርስቲ የሚደርስ ት/ቤቶች በማደራጀት የወታደራዊ ባለሙያዎችና ልሒቅ ተማራማሪዎች እንዲኖሩት ሰለተደረገ ውጤታማ ሁኗል።  ለዚህ ከፍ ያለ ግንባታ ዝግጅትና አንዳንድ የግንባታ ጅማሮ ስራ እየተሰራ እያለ በዚህ መሐል ኢሳያስ አፈወርቅ በእብሪት ተወጥሮ በወረራ የኢትዮጵያ ዳር ድንበር ጥሶ ሰራዊቱ እንዲገባ ሲያደርግ የኢትዮጵያ ሰራዊት በአጭር ጊዜና ዝግጅት ወረራውን ለመቀልበስ ችሏል። ጦርነቱ ሲጀመር ሁለቱ ሰራዊቶች /የኤርትራናየኢትዮጵያ/ በተመሳሳይ ሐይል በተመሳሳይ መሳርያና በተመሳሳይ የጦርነት ልምድ ነበሩ። የኢትዮጵያ ሰራዊት ወረራውን መቀልበስና አከርካሪውን መስበር የቻለበት ምክንያት የፅንሰሐሳብ ብልጫ በከፍተኛ ደረጃ በመጎናፀፉና ተወረርኩኝ ተደፈርኩኝ ብሎ የተቆጣ ህዝብና ሰራዊት የሞራል ልዕልናም ስለነበረው ነው። የኢህአዴግ ሰራዊትም ሆነ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ሰራዊት በውዴታ በፍቃዱ የተመለመለ ወታደር ነበር። ይህ ደግሞ ትልቁ የሞራል ምንጭ ነው። እንደ ደርግ በብሄራዊ ውትድርና አገልግሎት እየታፈሰና እየተገደደ የሚስለፍ አልነበረም። የኢትዮጵያ ሰራዊት ወይም እንደ ኢሳያስ አፈወርቂ ሰራዊት በሳዋ ሀገራዊ አገልግሎት በሚል በአስገዳጅ ግፋ የተሰለፈ ሰራዊት ዓይነት አይደለም። በተጨባጭ አቅም በወታደራዊ ልምዱም ከኢሳያስ ሰራዊት ተመሳሳይነት ቢኖረውም በውዴታ የተሰለፈ በመሆኑ የሞራል የበላይነት እንዲጎናፀፍ አድርጎታል።

 

የኢትዮጵያ ሰራዊት ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በኃላም ላይ በተገለፀው መሰረት በከፍተኛ ደረጃ ራሱን የሚገነባበት ስራ ላይ ተጠምዶ ነበር። በተባበሩት መንግስታት ተልእኮ በመሳተፍ ባለው ህዝባዊነትና ዲሲፒሊን የአገሩን ገፅታና ክብር ከፍ እንዲል አድርጓል። በጣም አነስተኛ በጀትና ደሞዝ ኖሮትም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሲያድግ የህዝቡ ድህነት ሲቀረፍ የኔም ችግር ይቀረፋል በሚል ንቃተህሊና እና ስነልቦና ይዞ ከሱ የሚፈለገውን ሁሉ መስዋዕትነት ከፍሏል።

 

ይህ ሰራዊት በአገራችን ቀደም ብለው ከነበሩት ሰራዊቶች ይሁን በክፍለ አህጉራችን ካሉ ሲነፃፀር ከአብዛኞቹ በላይ በፅንሰሀሳብና በሞራል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። የራሱ የሆነ ወታደራዊ ዶክትሪን የታጠቀና በወታደራዊ ሳይንስ የዳበረ ዕውቀትና ችሎታ የያዘ ነበር። ከፍተኛ ወታደራዊ ሙሁራን ማፍራት ችሏል። ነገር ግን በተወሰኑ አመራሮቹ የሙስና እና የእርስ በርስ ፉክክር የሚመሰሉ ዝንባሌዎች መታየት ጀምረው እንደ ነበር ይታወቃል። ይህን ሁኔታ ለማረም በወቅቱ የነበረው ጠቅላይ ሚኒስተር ሀይለማርያም ደሳለኝ ሳይችል ቀረ። ይህ ደግሞ በአብዛኛው የሰራዊቱ አመራር ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ በመገንዘብ ለመንግስት በተለያየ መንገድ ቢገልፁም ሰሚ በመታጠቱ በሰራዊቱ የሞራል አቅም ላይ ያስከተለው ጠባሳ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በአገራችን የቀለም አብዮተኞችንም ይህንን ችግር ብዙ ልብወለድ ትንታኔዎች  በመጨመርና የአንድ ብሔር ብቻና ሌባ እንደነበረ አድርገው ለመከፋፈል ተጠቀሙበት። አገር በቀለም አብዮት ስትናጥ በመሰረቱ ጤነኛ የነበረው ሰራዊት አንድነቱን ጠብቆ የውስጥ ችግር በይደር አድርጎ አገራችን እንዳትበታተን ህዝባችን በነውጡ እንዳይጎዳ መስዋዕትነት ከፍሎ መጠበቅ ችሏል። ፖለቲኮኞች በለውጥ ስም ስልጣን ላይ ሲመጡም ጣልቃ ሳይገባ በህገመንግስቱ ራሳቸው ፖለቲከኝቹ ይፍቱት በማለት በተልእኮው ላይ ብቻ አትኩሮት በመስጠት ዲሲፒሊንነቱን አሳይቷል። ያ በመለስ የተገነባው ሰራዊት ይህ ዓይነት ጥንካሬና የመዋጋት ብቃት እና ጦርነትን ማስቀረት የሚችል ልዩ ወታደራዊ ጥበብናብቃት ነበረው። አሁንስ? ከቀለም አብዮቱ ለውጥ በኃላስ? በሚቀጥለው ክፍል ሶስት በዝርዝር እናየዋለን።

 

ቸር እንሰንብት።

ግንቦት 20 በኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ ለዘላለም ይኖራል!

 

 

 

Back to Front Page