Back to Front Page

መከላከያ ሰራዊታችን ምን ይመስላል?

መከላከያ ሰራዊታችን ምን ይመስላል?

 

ዑሱማን ሙሉዓለም

ከሐራ-ገበያ

ጉንቦት 15፣ 2012ዓ.ም.

 

የማንኛውም አገር ሰራዊት ጥንካሬ የሚመዘነው በመዋጋት ሐይሉ ብቃት ነው። ይህም ወታደራዊ መሳርያ በማንኛውም ወቅት ዝግጁ ሆኖ ከውጭ ወረራና ጥቃት አገርን ሕዝብ ለመከላከል የሚችል ሆኖ መገንባት ይኖርበታል። የመዋጋት ሐይል ሲባል ሦስት ግን ተነጣጥለው መታየት የሌለባቸው ነገሮችን (components) አዋህዶ ያቀፈ አቅም ሲኖረው ነው። እነዚህም ፅንሰ ሀሳብ፣ ተጨባጭ አቅም፣ እና ሞራል ናቸው።

 

አንደኛው ፅንሰ ሀሳባዊ ነገር በምናይበት ወቅት የሰራዊቱ አስተሳሰብን የሚፈትሽና ሙሁራዊ አቅሙንም የሚመዝን ነው። ይህም ሰራዊቱ በጦርነት መርሆው ምን አስተሳሰብ እንዳለው እና ፍልስፍናው ይዳስሳል። ወታደራዊ ዶክትሪኑ /መስመር/ መኖርና በሰራዊቱ ምን ያህል ገዢ አስተሳሰብ እንደሆነ ይፈትሻል። ሰራዊቱ ስለ ቀጣይ ጦርነት ያለው አስተሳሰብና ከለውጦች ጋርና ለሚያጋጥሙ ችግሮች ቀድሞ ፈጠራዊ ችሎታ ማዳበሩንና በቀጣይነትም ራሱን ለማሻሻል ያለው ዝግጁነት ይመዝናል።

 

Videos From Around The World

ሁለተኛው የውጊያ መሳርያ ተጨባጭ አቅም ነው። በዚህ የሰው ሐይል ብዛትንም ጥራትንም ይዳስሳል። የጦር መሳርያና ሌሎች ወታደራዊ ቁሳቁሶችን አቅም ይመዝናል። የሰው ሐይልና የጦር መሳርያ ተቀናጅቶ በጋራ ግዳጅን የመፈፀም አቅም ምን አንደሆነ ይፈትሻል። በመጨረሻም ይህ አቅም በቀጣይነት ዝግጁ መሆኑና ዘላቂነቱን ይመረምራል።

 

ሶስተኛው ከላይ የተዘረዘሩትን ሁለት ነገሮች ትርጉም እንዲኖራቸው የሚያደርገው በኔ አመለካከት ወሳኙ የሆነው ነገር ሞራል የሚለው ንጥረ ነገር (ባእታ) ነው። ጦርነት የሰው ልጅ እንቅስቃሴ ነው። የሰዎች ሞራል በጦርነት ስነልቦና በግልም በጋራም ተፅእኖው ወሳኝ ነው። ሞራል ስንል ትክክል እና ስህተት ነው ብለን እንድናስብ የሚያደርገን መርሆ (principles of right and wrong) ነው። ይህ ደግሞ በራስ የመተማመንና ጤነኛ ስብእና በመፍጠር ተነሳሽነትና ቆራጥነትና ዝጉጁነት ይፈጥራል። ይህ የመዋጋት መሳርያ ሞራል ንጥረነገር ሰዎች በጦርነት እንዲዋጉ የማድረግ አቅም ይፈጥራል። ሦስት ነገሮችንም ያጠቃልላል። ለውጊያ ዝግጁ እንዲሆኑ የመነሳሳት፤ ጉጉት (motivation) እና ብቁ አመራር በመፍጠር ተፅእኖ መፍጠር የሚችል አቅም ናቸው። ይህ ሦስተኛው ነገር በሰራዊቱ በመፈተሽ የሰራዊቱን ማንነት ማወቅ ይቻላል።

 

የአንድ አገር ሰራዊት ብቃት መመዘን ከሌሎች አምሳያ አገራት   ሰራዊቶች ያለው ልዩነት ለማወቅ ይረዳል። አንደ የአገሩ ኢኮኖሚ፣ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዕድገት መለያየታቸውን ሳንረሳ እነዚህ ሦስት ነገሮች እንደመገምገሚያ ልንጠቀምባቸው እንችላለን።

 

በነዚህ መመዝኛዎች ሰራዊታችን በምናይበት ወቅት በጃንሆይ ጊዜና በደርግ ጊዜ የነበሩ ፅንሰ ሀሳቦች ብሎ በመከፈል በአጭሩ ማየት ይቻላል፡፡ በጃንሆይ ግዜ ሰራዊታችን የነበረው ፅንሰ ሀሳብ በቀጥታ ከአሜሪካ የተቀዳና የራሳችን የጦርነት ፍልስፍና እና ዶክትሪን ያልነበረበት ነው፡፡ ሰራዊቱ በዋናነት የዘውዳዊ አገዛዙ በተለይም የአፄ ኃይለስላሴ የስልጣን ዕድሜ በመጠበቅ ላይ ያተኮረ ነበር። ይህም ሆኖ በውስጡ በወቅቱ አገሪቱ በነበራት አቅም በአገር ቤትም በውጭም ወታደራዊ ትምህርት የወሰዱ ሰዎች የነበሩበት ሰራዊት ነበር። በአጠቃላይ ሲታይ ወቅቱን የሚመጥኑ ወታደራዊ ሙሁሮች ነበሩን ሊባል ይችላል። ይህን አቅም ሁሉም እንደሚያውቀው ወታደራዊው ደርግ በከፍተኛ ሁኔታ አዳከመው። ሶሻሊስት ሁኛለሁ በሚልም በለብለብ ስኮላርሽፕ በሶቭየትና በሌሎች የሶሻሊስት አገሮች ነን በሚሉ ቢያስተምርም በቁጥርም በጥራትም ብቁ የነበሩ አይደሉም፡፡ አገሪትዋ ያለምንም የራስዋ ወታደራዊ ፍልስፍና እና ዶክትሪን /መስመር/ በሶቭየት ህብረት ፍልስፍናና መስመር የሚመራ ሰራዊት በመገንባት ከጥራት ይልቅ በመጠን ላይ አትኩሮ ግዙፍ ሰራዊት ግን የሚመራበት የራሱ የሆነ አገራዊ ፅንሰሀሳብ የሌለው በቆራጡ መንግስቱ አመራር ወደፊት እያለ አገር ከውጭ ወረራ መከላከል ሳይሆን የፋሽስታዊ ደርግ ዕድሜ ለማስረዘም በእርስ በርስ ጦርነት ተጠምዶ በህዝቦች ትግል የተገረሰሰ ነው።

 

የጃንሆይም የደርግም ሰራዊቶች ተጨባጭ አቅማቸው ብቃት የነበረው ቢሆንም በሌሎች ምክንያቶች ዝግጁነታቸውና ዘላቂነታቸው አስተማማኝ አልነበረም።

 

በሦስተኛው መመዘኛ ሞራል ጉዳይ ሲታይ በጃንሆይ ሰራዊት በሶማሊያ ወረራና በውጭ በተባበሩት መንግስታት ግዳጅ ተሰጥቶት ከፍተኛ ጀብድ በማሳየቱ ትልቅ ታሪክ የሰራ ቢሆንም በአገሪቱ በነበረው አስተዳደር የተከፋና ሞራሉ በከፍተኛ ደረጃ እየተጎዳ የመጣ ነበር። የደርግም ሰራዊት ከዝያድባሬ ጦር ወረራ ለመከላከል በነበረው ፍልሚያ በከፍተኛ ወኔ የተዋጋ ቢሆንም የሶቭየት አዛዦችና አማካሪዎች የኩባ ሰራዊት በማሳተፉ በኢትዮጵያውያን ወታደሮች ሞራል ላይ ጠባሳ ጥሏል። ደርግ በአገር ውስጥ ይከተል በነበረው ፖለቲካ በሁሉም የአገሪቱ ህዝቦች ተቃውሞ ሲገጥመው መደበኛ ሰራዊቱን በማሰለፍ በታንክና በአውሮፕላን በመደብደብ ከፍተኛ ቅራኔ በህዝቡና በሰራዊቱ በመፍጠሩና ሰራዊትም የሚመለመለው ብሄራዊ ውትድርና በሚል ሰበብ በግዴታ ስለነበረ ሞራሉ በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ ያለ ነበር። ወታደራዊ አመራሩም በደርግ ፖለቲካዊ አመራር ደስተኛ ያልነበረና ሞራሉ በከፍተኛ ደረጃ የወረደና በየአካባቢው ሲማረክ የነበረ ነው።

 

በክፍል ሁለት በኢህአዴግ ዘመን የነበረው የሰራዊት ግንባታና የሰራዊት ብቃት እናያለን።

 

ቸር ሰንብቱ።

ግንቦት 20 በኢትዮጵያ ህዝቦች ልብ ለዘላለም ይኖራል!         

 

 

Back to Front Page