Back to Front Page

የምናላቸው ስማቸው ዓይነት ዘረኞች ከዚህ በላይ ማሰብ አይችሉም ወይም ማሰብ አይፈልጉም

የምናላቸው ስማቸው ዓይነት ዘረኞች ከዚህ በላይ ማሰብ አይችሉም ወይም ማሰብ አይፈልጉም

ክፍላይ ገብረሂወት (kflay77@gmail.com, @kfloma)

06-08-20

 

ሚድያ ለአንድ አገር እድገት የበኩሉ ሚና እንደሚጫወት የማይካድ እዉነት ነው። በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ታማኝ እና በመረጃ የተደገፈ ነገር ለህዝብ የማቅረብ ማህበራዊ ሃላፊነት እና ሞያዊ ግዴታ ኣለባቸው። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲሰሩ ብቻ ነው ሃላፊነታቸው ተወጡ ማለት የሚቻለው።

ከዚህ አንጻር ስናየው ብዙዎቹ የኢትዮጵያ ሚድያዎች ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ ምንም ዓይነት ጥናት ሳያከናዉኑ የጠረጠሩትን ጉዳይ እዉነት እንደሆነ አድርገው ለህዝብ የሚያጋሩ፣ ህዝብ ከህዝብ በፖለቲካ ሰበብ እንዲጠፋፋ እሳት የሚያቀጣጥሉ ናቸው። ይህንን የመሳሰሉ ጉዳዮች ከሚነዙት ሚድያዎች አንዱ ኢትዮ 360 የሚባል በyoutube እና በመረጃ ቲቪ የሚሰራ አንዱ ነው። ይህ ጣብያ በርካታ ጥሩ ነገሮችን የሚያቀርበው ያህል መረጃ ኣልባ ውይይቶችን በማድረግ የከረፋ ጥላቻ ሲነዛ ይውላል። ዛሬ እንድጽፍ ያስገደደኝ ስለ ጣና ዝም አንልም ጣናን በሚመለከት ባደረጉት ውይይት እና የቀድሞ የኢሬቴ ባልደረባ የነበረ አቶ ምናላቸው ስማቸው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊን እና ባልደረቦቻቸው ተጠያቂ ያደረገበት ጉዳይ ነው።

ብዝሃ-ህይወት የሁሉም ነው። ጣናም ባህር ዳር ሰለተገኘ ብቻ የባህር ዳር ነው ማለት አይደለም፣ የኢትዮጵያ አለፍ ሲልም የዓለም መሆኑን መታወቅ አለበት። በዚህም ምክንያት ነው በUNESCO Man and Biosphere (MAB) reserve እንዲመዘገብ የተደረገው። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ስነ-ምህዳር በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ጣና ሲጎዳ እንደሚጎዳ ምንም ጥርጥር የለዉም። የብዙ ኢትዮጵያውያን ማህበራዊ እንዲሁም ኢኮኖምያዊ እምርታም ጉዳቱ ቀላል አይደለም። በመሆኑም ተጠያቂ ፍለጋ ከመዋተት ይልቅ ጣና ሳያመልጠን የምናድንበት መንገድ መፈለግ ብልህነት ነው። ይህ ደግሞ ሁላችንንም ይመለከተናል።

በተጨማሪም ስለ እምቦጭ አረም (Eichornia crassipes) አጠቃላይ ባህሪ ለምሳሌ መቼ ገባ፣ እንዴት ይራባል፣ ዘሩ እንዴት ይበተናል እንዲሁም ተያያዥ ጉዳዮችን ማወቅ ለመቆጣጠር ጉልህ ድርሻ አለው። ሌሎች ጉዳዮችን ትቼ እምቦጭ አረም (Eichornia crassipes) ኢትዮጵያ ዉስጥ መቼ ገባ የሚለዉን ትንሽ ላስረዳ (መነሻዬ Prosopis juliflora (የወያነ ዛፍ) እና Eichornia crassipes (እምቦጭ አረም) በጠ/ሚ መለስ ዜናዊን እና ባልደረቦቻቸው ነው የገቡት የሚል የአቶ ምናላቸው ስማቸው ውንጀላ ነው)። ትንሽ ኣለፍ ሲልም ጣና ትግራይ ላይ ቢሆን እያሉ ይመኙ ስለነበር ነው በቅናት ያንን ያደረጉት ሲል ምንም ሳያመነታ (ለነገሩ ዘረኛ ማመንታት የት ያውቃል እና) ኣፉን ሞልቶ ደረቱን ነፍቶ ሲናገር ነበር። ሀብታሙ ኣያሌውም ምናላቸው እዳለው በተጨማሪ .. በማለት የሐሳቡን ትክክለኛነት አረጋግጧል። በጣም ያሳፍራል። በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ይህንን የሚጋሩ ቀላል የማይባሉ ቁጥር ያላቸው የምሁር መሃይሞች መኖራቸው ነው።

ማወቅ ያለብን ነገር ግን ሁለቱም እጸዋቶች ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ከ50 ዓመት በላይ የሆናቸው መሆናቸው እና ከተተቀሱት ሰዎች ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌላቸው ነው። እምቦጭ ለመጀመርያ ጊዜ የታየው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1965 በቆቃ እና አዋሽ ወንዞች ነው። ከዛ በኋላ ግን በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ወንዞች ላይ ተሰራጭቷል፣ ጣናን ጨምሮ ማለት ነው። ይህንን ለማረጋገጥ በእጸዋቱ ዙርያ የተጠኑት ጥናቶቹን 20 ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ማግኘት ይቻላል። Prosopis juliflora በረሃነትን ለመቋቋም በሚል በ1960 መጨረሻዎቹ ዓመታት እንደገባ ነው ጥናቶች የሚያመለክቱት። በዚህም የተነሳ Prosopis juliflora ዓፋር ውስጥ ሁለት ስም ነው ያለው፣ የመጀመርያ ስሙ ደርጊ ሃራ ሲሆን በሂደት የተሰጠው ደግሞ ወያኔ ሃራ የሚሉ ናቸው። ነዋሪዎቹ ለምን በሂደት ስሙን ቀየሩት ሌላ ጥናት የሚፈልግ ቢሆንም እጸዋቱ የገባው ግን አቶ ምናላቸው ስማቸው እንዳለው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እና ጓዶቻቸው ያስገቡት ሳይሆን ገና ህወሓት የትጥቅ ትግል ሳይጀምር ደርግ ኢትዮጵያ ይመራበት በነበረ ጊዜ ነው። የእምቦጭ ኣረም ማ ጭራሽ በሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነው ለመጀመርያ ጊዜ ኢትዮጵያ ዉስጥ የተመዘገበው። ታድያ እውነታው ይህ ሁኖ እያለ የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እና ጓዶቻቸውን ስም ማጉደፍ ለምን ኣስፈለገ? መልሱ

የዋህ እንሁን ካልን በመረጃ ያልተደገፈ እና ከእዉነት የራቀ ኣቀራረብ ስንለው፣ እውነታው ግን የከረፋ ዘረኝነትና የሆነን ኣካል በተለይ ደግሞ ተጋሩን የማጥቃት ከትውልድ ሲሸጋገር የመጣ በሽታ ነው።

በመሆኑም አቶ ምናላቸው ስማቸው እና ኢትዮ 360 ይህ እውነት የሌለው ማንንም የማይጠቅም ውንጀላቸው ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝበው እርምት እንድያደርጉ እና መላው ኢትዮጵያውያን የበኩላችን አስተዋጸኦ በማድረግ ጣናን እንዲሁም እንደ አኽሱም ሓወልት ያሉ ሌሎች ቅርሶቻችን እንታደግ እላለሁ።

Back to Front Page