Back to Front Page

የምርጫው ጊዜ መራዘም በሕግ መነጽር ሲታይ

የምርጫው ጊዜ መራዘም በሕግ መነጽር ሲታይ

ባይሳ ዋቅ-ወያ1 *****

5-14-20

የምርጫ ቦርድ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዘንድሮውን ምርጫ በተያዘለት ቀጠሮ ቀን ለማካሄድ እንደማይቻለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቁን ተከትሎ አንዳንድ የፖሊቲካ ድርጅቶች በቂ ውይይት ሳይደረግበት የተላለፈ ውሳኔ ነበር ብለው ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ነበር። እንደ ማንኛውም ሌሎች እስካሁን ሲካሄዱ እንደነበሩ የፖሊቲካ ውይይቶች አሁንም የምርጫ ቦርድ ከፖሊቲካ ድርጅቶች ጋር ስላካሄደው ውይይት በቂ መረጃ ባይኖረንም አሁን ባገራችን ላይ እያንዣበበ ያለውን የቫይረሱን አደጋ አስመልክተን ብዙዎቻችን የምርጫው ጊዜ መራዘሙ ትክክል ነው ብለን ተቀብለናል። ዛሬ የኮሮና ቫይረሱ ወረርሽኝ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገራት ቀርቶ ባደጉ አገራትም ማሰብ ከሚቻለው በላይ ማህበረሰባዊና ኤኮኖሚያዊ ቀውስ እያመጣ ባለበት ሁኔታ፣ ያገራችን መንግሥት ተረጋግቶ ምርጫን ማካሄድ ይችላል ብሎ መጠበቅ የሚቻል አይመስለኝም።

አሁን ሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥታችን በጣም ብዙ ክፍተቶችን ያዘለ ነው። ወጣም ወረደ ግን ሕገ መንግሥቱ እስከነጉድለቱ ብቸኛና የሕጎቻችን ሁሉ መሠረት ስለሆነ ይህንን የምርጫን ጊዜ ማስተላለፍን ማየት ያለብን በሕገ መንግሥቱ መነጽር ብቻ መሆን አለበት ። ሕገ መንግሥታዊ ችግሩን መፍታት የሚቻለው በሕገ መንግሥቱ ቃልና መንፈስ እንጂ በፖሊቲካ ድርድር ስላይደለ፣ አሁን ካጋጠመን ቀውስ ለመገላገል መፍትሔው ሕገ መንግሥታችንን መሠረት አድርገን እና የሕገ መንግሥቱን ቃላትና መንፈስ (letters and spirit) ተከትለን በምናደርገው ሙያዊ ሃሳቦችን ስንለዋወጥ ብቻ ነው። የዚህ ጽሁፌ ዋና ዓላማ፣ የመስኩ ባለሙያዎች የድኅረ መስከረም የኢትዮጵያ ሁኔታ በሕግ መነጽር ሲታይ መሆን አለበት ብለው የሚያስቡትን መፍትሄ እንዲያቀርቡና እንዲያስተምሩ ለመጋበዝ ነው።

Videos From Around The World

ለትንተናዬና ለደረስኩበትም ድምዳሜ መሠረት እንዲሆነኝ አስቀድሞ ያገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ በአጭር ማስቀመጡ አግባብ ያለው ይመስለኛል፣

ሀ) ሕገ መንግሥታችን ሲደነገግ ዲሞክራሲያዊ የሆነ የሕዝብ ተሳትፎን ያካተተ አልነበረም። ሆኖም ግን፣ ሕዝባችንም ሆነ የፖሊቲካ ድርጅቶች ሕገ መንግሥታችን ነው ብለው ተቀብለውታል። በመሆኑም፣ የፖሊቲካ ድርጅቶቹ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት የተቋቋመው የምርጫ ቦርድ ባወጣው መስፈርት የሚፈለግባቸውን አሟልተው ተመዝግበው ሴርቲፊኬት ወስደዋል። ስለዚህ በሕገ መንግሥቱ የበላይነትና ባቀፋቸው አንቀጾች ይዘትም ሆነ በአጠቃላይ በያዘው የሕግ መንፈስ ቅሬታ ያለው የፖሊቲካ ድርጅት ያለ አይመስለኝም።

ለ) ሕገ መንግሥቱ ብዙ ክፍተቶች አሉበት። በምዕራፍ ሶስት ሥር የተካተቱት የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ዝርዝር በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስመስግነውን ያህል፣ በተቀረው ክፍል ግን የተለያዩ ክፍተቶችን በማቀፉ ይኸው ለዛሬው ችግራችን ዳርጎናል። በመሠረቱ ሕገ መንግሥታዊ ክፍተቶች ያልተለመዱ አይደሉም። ዋናው ነገር ክፍተቶችን ለመሙላት ሕገ መንግሥቱ ዕድል ይሠጣል ወይ የሚለው ነው። ሕገ መንግሥታችንም በአንቀጽ 104 እና 105 ሥር የሕግ ክፍተቶችን ለመሙላት ሲባል ሕገ መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ቅድመ ሁኔታዎች ግልጽ በሆነ ቋንቋ አስቀምጧል።

ሐ) በኢትዮጵያ ውስጥ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(3) ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን የመንግሥት ሥልጣን መያዝ አይቻልም። በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጠው አንቀጽ 50(3) ደግሞ ብቸኛ የሥልጣን መያዣ መንገድ ሕዝባዊ ምርጫ ብቻ መሆኑን ሲያስረዳ የፌዴራል መንግሥቱ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ይልና በአንቀጽ 54(1) ሥር ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሁሉ አቀፍ፣ ነጻ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምጽ በምሥጢር በሚሠጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ ይላል።

መ) በሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 58(3) ሥር በግልጽ እንደተቀመጠው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ስለሆነ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የመንግሥትና የፓርላማው የሥራ ዕድሜ የሚያበቃው መስከረም ላይ ነው። ይህም ማለት ያሁኖቹ የሕዝብ ተወካዮች ሕገ መንግሥቱ በደነገገው መሠረት የአምስት ዓመት አገልግሎታቸውን ሲጨርሱ፣ ወይ እንደገና ለመመረጥ ወደየአካባቢያቸው ተመልሰው መወዳደር፣ አለያም ደግሞ ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲመርጣቸው ለሌሎች ግለሰቦች ቦታውን መልቀቅ አለባቸው። ከቁጥጥር ውጪ የሆነ አገራዊ አደጋ ቢከሰትና ምርጫን በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ ካልተቻለ መወሰድ ስላለበት አማራጭ ግን ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ነገር የለም። ይህ አንዱ የሕገ መንግሥቱ ትልቅ ክፍተት ነው።

 

ሠ) ያሁኑ ፓርላማና መንግሥት የሥራ ዘመን ለማክተም ጥቂት ወራት ሲቀሩት የኮሮና ወረርሽኝ አስጊ ሆኖ በመታየቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 95(1)(ሀ) መሠረት .. የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት የፌዴራሉ መንግሥቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው በተባለው መሠረት የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት አዋጁን ዓውጆ ፓርላማውን አስጸድቆ ተግባር ላይ አውሎታል። የኮሮና ቫይረስ ወረሽኝን አስመልክቶ መንግሥት የወሰደው የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ሕጋዊ መሆኑን ተቃዋሚ ድርጅቶችም ተቀብለውታል። የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ደግሞ ከወትሮው የተለየ ተፈጥሮያዊ ወይም ሰው ሰራሽ የሆነና በተለመደው አሠራር የማይገታ አደጋ ሲከሰት፣ ያገሪቷን ኅሊውናና የሕዝቦችን ሰላም ወይም ጤንነት ለመጠበቅ ሲባል ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚወሰድ ከባድ ውሳኔ ነው። አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅን ከባድና የዕድሜ ገደቡም አጭር እንዲሆን አስፈላጊ ከሚያደርጉት የመጀመርያው፣ ዓዋጁ በመሠረቱ አንዳንድ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ስለሚገድብ ነው። ረ) በሕገ መንግሥታችን በአጠቃላይና በምዕራፍ 3 ሥር ከተካተቱት ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ውስጥ አንቀጽ 1፣ 18፣ 25 እና 38 ብቻ አይነኬ ተብለው ተደነገጉ እንጂ የተቀሩት በሙሉ በአስቸኳይ ዓዋጁ ጊዜ ሊገደቡ የሚችሉ ናቸው። ከነዚህ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ መሠረት መንግሥት ሊገድባቸው ከሚችላቸው ሰብዓዊ መብቶች ለምሳሌ አንዱ አንቀጽ 38 ሥር የተካተተው የዜጎች የመምረጥ መብት ነው። እንግዲህ መሰብሰብና ማሰባሰብ ካልተፈቀደ እንዲሁም የመመረጥ መብት ከተገደበና መንግሥትም ሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከዜጎች ጋር ተሰብስበው ለመወያየትና የምርጫ ቅስቀሳ የማያደርጉና ዜጎችም ሰላምና መረጋጋት ባለበት ሁኔታ ነጻና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ የማይችሉ ከሆነ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ በሥራ ላይ እስካለ ድረስ የሚቀጥለው ምርጫ ሊደረግ አይቻልም ማለት ነው። ይህን እንግዲህ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚ ድርጅቶችም በውል መረዳት ያለባቸው ጉዳይ ነው።

ሰ) አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ የሕገ መንግሥቱን የፓርላማ የሥራ ዕድሜ በአምስት ዓመት የመገደቡንና ብሎም ምርጫው በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ በአምስት ዓመት ለማካሄድ የማያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁና ሕገ መንግሥቱ ደግሞ ያሰቀመጠው መፍትሄ ስለሌለ ሕጋዊውን መንገድ ትተን ፖሊቲካዊ መፍትሄ መፈለጉ ይበጃል እያሉ ነው።

የሕገ መንግሥቱን ይዘት ከላይ ካስቀመጥኳቸው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር አመላክቼ ለመዳሰስ ልሞክርና፣

ሕገ መንግሥታችን የሕጎቻችን ሁሉ የበላይ መሆኑን የተቀበልነውን ያሕል ብዙ ክፍተቶችንም ማቀፉን ሁላችንም የምንስማማበት ጉዳይ ነው። ከነዚህ ክፍተቶች አንዱ እና አሁን አላስፈላጊ የሆነ ጭቅጭቅ እየፈጠረ ያለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን ሲያበቃና ብሔራዊ ምርጫን ደግሞ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ምክንያት በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ ባይቻል አማራጩ ምንድነው የሚለውን በግልጽ አለማስቀመጡ ነው። በሕጎች ሰነድ ውስጥ የክፍተት መኖር እንግዳ ነገር አይደለም። ሕጎች የሚደነገጉት በጊዜው ባገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታ ከግምት በማስገባት ነው። ጊዜያት ሲያልፉ ያኔ ውቅታዊ የነበረው ጉዳይ አላስፈላጊ ይሆንና ወይም ያኔ ሕጉ ሲደነገግ ከግምት ያልገባ ነገር ዛሬ ለማሕበረሰቡ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የጎደለውን ለመሙላት ወይም አላስፈላጊ የሆነን ለማስወገድ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ግድ ይላል። ይህ በየትም አገር በተግባር የምናየው ነው። በመላው ዓለም በጥንታዊነቱ እንደ ተምሳሊት የሚቀርበው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በሁለት መቶ ሰላሳ ዓመት ዕድሜው ወደ አሥራ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሃሳቦች ቀርበው፣ ኸያ ሰባት መሻሻሎች (amendments) ተደርጎበታል። ስለዚህ ያገራችን ሕገ መንግሥት ክፍተቶችን ብቻ ሳይሆን ከፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉንን ሕጋዊ መንገዶችን ማቀፉ በማንኛውም አገር ከሚደረገው የሕገ መንግሥት ማሻሻል ልምድ የተለየ አለመሆኑን ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ነው ብሎ በአንቀጽ 58(3) አስቀምጦ፣ በሆነ አደጋ ምክንያት በአምስት ዓመቱ ውስጥ ደግሞ ምርጫውን ለማካሄድ ካልተቻለ መወሰድ ስላለበት እርምጃ በቀጥታ ከዚሁ አንቀጽ ጋር አያይዞ ሌላ ዓረፍተ ነገር አለመጨመሩ ግር ያሰኛል። ይህንን ክፍተት ግን ለመሙላት የሚያስችል ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ብሎ በአንቀጽ 104 እና 105 ማስቀመጡ ትክክለኛ አካሄድ ነው። በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ምክንያት መደበኛው ምርጫ እንደማይደረግ ከታወቀ ዘንዳ፣ ከመስከረም በኋላ አገሪቷን ሊያስተዳድር የሚችል መንግሥት ለማቋቋም መፍትሔው ያለው በነዚህ ሁለት የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ውስጥ ብቻ ነው። ይህ አጋጣሚ እያለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምን በሕግ ትርጓሜው ላይ አተኩሩ ብዬ ደጋግሜ ራሴን ብጠይቅ ያገኘሁት መልስ፣ ምናልባት ዛሬ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ አሳብቦ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም ሲባል ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል መጠየቅ፣ ለወደፊት እንደ ልምድ (precedent) ይወሰድና አምባገነኖች አላስፈላጊ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጆችን እያወጁና ያላግባብ ተጠቅመውበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን ሊያደፈርሱ ይችላሉ ከሚል ግምት ተነስቶ መሰለኝ። አለበለዚያ ይህ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሞከር ወጪው ብዙ ነው፣ ጊዜውም አጭር ነው የሚለው ምክንያት እምብዛም አልተዋጠልኝም።

 

እንግዲህ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት እንዲታወጅ የተስማሙበት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በሥራ ላይ እስካለ ድረስ ምርጫን ማካሄድ የማይቻል ከሆነና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ደግሞ ያሁኑ ፓርላማ የአራት ኪሎ ዕድሜ መስከረም ላይ ሲያከትም አገሪቷን በሕግ ሊመራ የሚችል አካል ማን ይሁን የሚለው ጉዳይ አነጋጋሪ መሆኑ አግባብ ያለው ነው። በሕግ መነጽር ከታየ መልሱ መገኘት ያለበት በሕገ መንግስቱ ቃላትና መንፈስ ውስጥ ብቻ ነው። ችግሩ ያለው እና ከላይም አንዳልኩት ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ካላስቀመጣቸው ጉዳዮች አንዱ አሁን አገራችንን የገጠማት መላውን ሕዝብ ሊያጠቃ የሚችል ወረርሽኝ ዓይነት ሲያጋጥም እና መደበኛውን ምርጫ ማካሄድ በማይቻልበት ሁኔታ ከመስከረም በኋላ አገሪቷን ማን ይምራት ለሚለው ግልጽ አንቀጽ አላካተተም። አንድ በግልጽ በአንቀጽ 9(3) ላይ የተቀመጠው እና የማያሻማው ጉዳይ ቢኖር በዚህ ሕገ መንግሥት ከተደነገገው ውጪ በማናቸውም አኳኋን ሥልጣን መያዝ የተከለከለ ነው የሚለው ነው። በሕገ መንግሥቱ የተካተተው የአራት ኪሎ መዳረሻ ባቡሩ ደግሞ አንቀጽ 58(3) ላይ በግልጽ የተቀመጠው በየአምስት ዓመቱ በሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ ውጤት በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖሊቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች የፌዴራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል ይመራል የሚለው ነው። ሕገ መንግሥቱ ከዚህ ውጪ ወደ አራት ኪሎ ሊያደርስ የሚያስችል ሌላ ምንም አማራጭ አላስቀመጠም። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ የሕጎቻችን ሁሉ የበላይ ነው ብለን እስከ ተቀበልን ድረስ ዛሬም ሆነ ከመስከረም በኋላ የአገሪቷን የሥልጣን አስፈጻሚ አካል (መንግሥት) ለመመስረት የሚቻለው በምርጫ ሂደት በተገኘው አሸናፊነት ብቻ ነው። ከዚያ ውጭ ያለው ሂደት ሁሉ ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ነው ማለት ነው።

ታዲያ ባንድ በኩል በአስቸኳይ ዓዋጁ ምክንያት በታቀደለት ጊዜ ብሔራዊ ምርጫ ማካሄድ የማይቻል ከሆነ፣ የሕገ መንግሥቱን ቃልና መንፈስ ሳንጥስ እንዴት አድርገን ከመስከረም በኋላ አገሪቷን ሊመራ የሚችለውን መንግሥት እንመሠርታለን የሚለውን ዓቢይ ጉዳይ መዳሰሱ ግድ ይላል። ጉዳዩን የሕግ ጨዋታ ምን ያደርጋል፣ በፖሊቲካ ጨዋታ እንፍታው የሚሉ አማተሮች በየሚዲያው እየቀረቡ ሕዝቡ ግራ ለማጋባት ሞከሩ እንጂ ባለ ሙያዎቹማ ሕገ መንግሥታችንን ተጠቅመን መፍትሔ ማግኘት እንደሚቻል ጠንቅቀው ያውቁታል። በሕግ መነጽር ሲታይ ብቸኛው መፍትሔ፣ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያላስቀመጠውን ወይም ክፍተቱን ሕገ መንግሥቱ ራሱ ባስቀመጠው መሠረት ማሻሻያ አድርጎ የጎደለውን መሙላት ብቻ ነው። በቀላል አነጋገር፣ የሕገ መንግሥትን ጉድለት በሕግ እንጂ በፖሊቲካ ጨዋታ አይፈታም ማለት ነው።

ከላይ እንዳልኩት፣ ዶ/ር ዓቢይ በአንቀጽ 62 መሠረት የሕገ መንግሥቱን ትርጓሜ ከመጠየቅ ይልቅ አንቀጽ 104 እና 105ን ተጠቅሞ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ሃሳብ ቢያቀርብ የተሻለ ይሆን ነበር የሚል ግምት አለኝ። ሁለቱ አንቀጾች (104 እና 105) የሕገ መንግሥቱን የማሻሻል ሂደት በጊዜ ያልገደቡ በመሆናቸው መንግሥት እንደ አስፈላጊነቱ ተጠቅሞባቸው በጥቂት ወራት ውስጥ፣ ማለትም ከመስከረም ወር በፊት ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ይችላል የሚል ግምት አለኝ። አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የሕግ ትርጓሜ የሚጠየቀው አሻሚ የሆነና በቀጥታ ሲተረጎም የተለያዩ መልሶችን ሊሰጥ የሚችል አንቀጽ ሲኖር ብቻ ነው ይላሉ። ይህ አባባል ግማሽ እውነትነት አለው። የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁንና በዓዋጁ ምክንያት ሊገደቡ የሚችሉትን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ስናመላክት ምናልባትም የሕግ ትርጓሜ እንደሚያስፈልግ ጥርጥር የለውም። ምክንያቱም ዓዋጁና ምርጫው በቀጥታ የማይገናኙ ቢመስልም በዓዋጁ ምክንያት የተገደቡ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ምርጫው እንዳይካሄድ ሊያደርጉ ስለሚችሉ በተዘዋዋሪ ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጓል። ዓዋጁ ራሱም ሆነ በዓዋጁም ምክንያት የመሰብሰብ፣ የመመረጥና የመምረጥ መብቶችን የመሳሰሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች መገደባቸውም ሕጋዊ ቢሆንም፣ በዚህ ሁሉ ሕጋዊነት ውስጥ ከመስከረም በኋላ አገሪቷን ሊመራ የሚችል መንግሥት ማን እንደሚሆን በአንቀጽ 58(3) እና አንቀጽ 93(4)(ለ) መካከል ስላለው ቀጥተኛ ግንኙነት ሕገ መንግሥታዊ ትርጓሜን መጠየቅም ከሕግ ሂደት አንጻር ሲታይ ትክክለኛ አካሄድ ነው።

በኔ ግምት የሕግ ትርጓሜ መጠየቅም ሆነ በቀጥታ አንቀጽ 104 እን 105ን ተጠቅሞ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ዞሮ ዞሮ ሊያመጡ የሚችሉት መፍትሔ አንድ ዓይነት ይመስለኛል። የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት፣ በአንቀጽ 58(3) እና አንቀጽ 93(4)(ለ) መካከል ስለሚኖረው ግንኙነት ከሕግ ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የተላለፈለትን የውሳኔ ሃሳብ መሠረት አድርጎ አስፈላጊውን ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል። የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ ሊሆን የሚችለው፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በመገደቡ ምክንያት ዜጎች በመደበኛው ምርጫ መሳተፍ ስለማይችሉና አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መደበኛ የሥራ ዘመን ደግሞ መስከረም ላይ ስለሚያበቃ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁን ለማወጅ ምክንያት የሆነው ጉዳይ እስኪወገድ ድረስ አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ከመደበኛ የሥራ ዘመኑ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በመደበኛው ሥራው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ይቀጥል ዘንድ፣ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 104 እና 105 ተጠቅሞ አንቀጽ 58(3) ላይ አንድ አንድ ንዑስ አንቀጽ በመጨመር ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ነው ብሎ የሚወስን ይመስለኛል። ( በነገራችን ላይ፣ አንቀጽ 58(3) ላይ ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ውሳኔ ከተሠጠበት፣ የማሻሻያ ሃሳቦ ቹ በግድ የዚህን መንግሥት የሥራ ዕድሜ ማራዘም ብቻ ሳይሆን፣ የሽግግር መንግሥትን፣ ባለ አደራ መንግሥትን ወዘ ተ የመሳሰሉትን እንደ አማራጭ አቅርቦ ሕዝቡ ተወያይቶ በት እንዲወስን ማድረ ግ ም ይችላ ል ። ዋናው ነገር ሕዝቡ ይሻለኛል ብሎ መረጠውን ሃሳ ብ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አስፍሮ ሕገ መንግሥታዊ ማድረግ ብቻ ነው። )

የፖሊቲካ ድርጅቶች የሚያቀርቧቸው መፍትሄዎች፣

የፖሊቲካ ድርጅቶቻችን በሙሉ በአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ ላይ ቅሬታ አላሳዩም። ዓዋጁም ከመታወጁ በፊት ጠ/ሚኒስትሩ ሰብስቦ እንዳነጋገራቸውና ሁላቸውም የዓዋጁን ሕጋዊነትና ወቅታዊነት አምነውበት መቀበላቸውን በተለያዩ የመንግሥትና የግል ሚዲያ ተቋማት በኩል ገልጸውልናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከተቃዋሚዎች ጎራ፣ ሕገ መንግሥቱ የፓርላማውን የሥራ ዕድሜ በአምስት ዓመት ስለ ገደበ ከመስከረም ሰላሳ በኋላ የዶ/ር ዓቢይ መንግሥት አገሪቷን መምራት ስለማይችልና ብሎም የአስተዳደር ክፍተት እንዳይፈጠር ከማሰብ የተለያዩ መፍሔዎችን እያቀረቡ ነው። ከነዚህም መካከል ጎልተው የቀረቡት ሁለት መፍትሔዎች ሀ) ያሁኑን መንግሥት ጨምሮ ሁሉም ተቃዋሚ ኃይሎች በእኩልነት ሥልጣን የሚጋሩበት የሽግግር መንግሥት እንዲፈጠር፣ ወይም፣ ለ) ከዚህ በፊት የፖሊቲካ ተሳትፎ ያልነበራቸውና ወገናዊነት በማያጠቃቸው ምሁራን የሚመራ የቴክኖክራቶች ባለ አደራ መንግሥት ማቋቋም ነው የሚሉ ይገኙበታል።

በመሠረቱ የሽግግር መንግሥትን ማቋቋም ያልተለመደ አሠራር አይደለም። የቀደመውን ሥርዓት በሙሉ ገርስሶ፣ ሕገ መንግሥቱን ሽሮ፣ ፓርላማውን አፍርሶ አዲስ መንግሥትን በአዲስ ሥርዓት ለማዋቀር ሲባል አብዛኛውን ጊዜ የሽግግር መንግሥት ፍቱን ሆኖ ይቀርባል። የሽግግር መንግሥቱ አስፈላጊነት አዲሱ ሥርዓት የሚመራበትን ፖሊሲ በተግባር ለመተርጎም የሚረዳ አዲስ ሕገ መንግሥት ለማውጣትና አዲስ ቢሮክራሲ ለመፍጠር ነው። ዛሬ ባገራችን ያለው ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው። አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት አንዳንድ ለውጦችን አመጣ እንጂ ያው ላለፉት 29 ዓመታት አገሪቷን ሲመራ የቆየው የኢሕአዴግ መንግሥት ወራሽ ነው። በሥራ ላይ ያለው ሕገ መንግሥትም ሆነ በዚሁ ሕገ መንግሥትም መሠረት ሥልጣን የጨበጠው የሕአዴግ (ብልጽግና) ፓርቲ/መንግሥት ሕጋዊ መሆናቸውን ሁላችንም በመሠረቱ ተቀብለነዋል። ስለዚህ ሕገ መንግሥቱ መሻሻል ተደርጎበት እና በሕገ መንግሥቱ ውስጥ እስካልተካተተ ድረስ ተቃዋሚ ኃይሎቹ የሚያቀርቡት የሽግግር ወይም የባለ አደራ መንግሥት መፍትሔ በአንቀጽ 9(3) እና አንቀጽ 58(3) መሠረት ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንደሆነ ይቀራል። በኔ ግምት የሽግግር መንግሥት ሃሳብ አመንጪዎቹን ሊያዋጣቸው የሚችለው፣ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም ብሎ ከመሞገት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 58(3) ላይ መሻሻል ተደርጎበት የሽግግር መንግሥት እንደ አንድ አማራጭ መፍትሔ ተደርጎ እንዲካተት መቀስቀስ ነበር።

ለማጠቃለል ያህል፣

አገራችን ያለችበት ሁኔታ በዕውነትም አሳሳቢ ነው። በአንዳንድ አካባቢዎች ወደ እርስ በርስ ጦርነት ደረጃ ከፍ ባይሉም አነሰተኛ ግጭቶች በተለያዩ ማሕበረሰባት መካከል እየታዩ ነው። በነዚህም ግጭቶች ምክንያት ሰላምና መረጋጋት እየጠፋ ነው። የኤኮኖሚያችንም ሁኔታ የሚያዝናና አይደለም። ተምረው ሥራ ያጡ ወጣቶቻችን ቁጥር ወደ አሥር ሚሊዮን እንደሚጠጋ መረጃዎች ይጠቁማሉ። የሚወነጀሉበት ጉዳይ ወይም የታሠሩት ሰዎች ቁጥር እንደዚሁም በየእሥር ቤቱ መሠቃየቱ ይቀንስ እንደው እንጂ ዛሬም ዜጎች እየታሰሩ ነው። አሁንም ሥልጣንን መከታ አድርገው ተቃዋሚ ብለው የሚያስቧቸውን ዜጎች የሚያስሩ ግለሰቦች በብዛት እንዳሉ ታስረው የተፈቱ ሰዎች ከሚናገሩት መደምደም ይቻላል። በሚቀጥለው ሕዝባዊ ምርጫ ለመጀመርያ ጊዜ ፍጹም ዲምክራሲያዊ በሆነ መንገድ ተወካዮቻችንን መርጠን ወደ አራት ኪሎ ለመላክ የነበረን ተስፋ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መነመነብን። ቀኑ አይታወቅም እንጂ፣ ወረርሽኙን በሰው ሰራሽ ሕጎችና ምናልባትም በክትባት እርዳታ እንወጣዋለን የሚለውን ተስፋ ግን ሁላችንም ሰንቀናል። ያ እንግዲህ ከቁጥጥራችን ውጭ ነው። በቁጥጥራችን ሥራ እያለ በትክክል ልንጠቀምበት እያቃተን ያለው ጉዳይ ግን ሕገ መንግሥታችንን አሁን ለተደቀነብን የፖሊቲካ ቀውስ ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ ለመቀበል አለመቻል ነው።

ሕገ መንግሥታዊ ቀውስን በፖሊቲካ ጨዋታ ለመፍታት መሞከር ዘላቂነት የለውም። ጊዜያዊ ነው። ዛሬ አንድ ከሌሎቹ የበለጠ ጥንካሬ ያለው ድርጅት ጊዜያዊ ጥንካሬውን ተማምኖ በሌሎቹ ላይ በሚያደርገው ጫና ምክንያት ለርሱ ብቻ የሚመቸውን ፖሊቲካዊ መፍትሔ አቅርቦ ውጥረቱን ያረገበ ቢመስለውም፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ ባላተራው ጠንካራ ድርጅት ብቅ ብሎ የራሱን ፖሊቲካዊ መፍትሔ አቅርቦ በተግባር ይተርጎምልኝ ይልና አዙሪቱ ይቀጥላል። በሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ መፍትሔ ግን ሕጋዊ ስለሆነ ሕጉ ከሚፈቅደው ውጪ ማንም ባለጡንቻ መጥቶ እንደ ፈለገው ሊጠቀምበት አይችልም። ፖሊቲካዊ ቀውስ በሕገ መንግሥት ይፈታል እንጂ የሕገ መንግሥት ክፍተት በፖሊቲካ ጨዋታ አይሞላም። ስለዚህ የችግራችን መፍትሔው የሚገኘው እዚያው ሕገ መንግሥታችን ውስጥ መሆኑን ተገንዝበን በሕጋዊ መንገድ ብቻ ችግራችንን ለመፍታት የሕገ መንግሥቱን ጉድለቶች ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለመሙላት ቀና ውይይት እናድርግ። ፈጣሪ አስተውሎትን ያብዛልን።

**** 1 ጸሃፊው ቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባለሥልጣን የነበሩ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያ ናቸው።

 

ጄኔቫ፣ wakwoya2016@gmail.com

Back to Front Page