Back to Front Page

የብሄር ፓለቲካ በኢትዮጵያ ማን ፈጠረው? በአዋጅ ማገድስ ይቻላል ወይ?

የብሄር ፓለቲካ በኢትዮጵያ ማን ፈጠረው? በአዋጅ ማገድስ ይቻላል ወይ?

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 10-08-20

በአሁኑ ጊዜ የኢትዮጵያ ችግር በሙሉ ምንጩ ህወሓት የፈጠረው የብሄር ፓለቲካ ነው፣ ብቸኛ መፍትሄው ደግሞ የብሄር ፓለቲካውን በአዋጅ ማገድ ነው የሚል በእርግጠኝነት የሚነገር ትርክት አለ። ይህ እውነት ከሆነ ምን ችግር አለ? የፈጠረውም ከስልጣን ተገልሏል፣ አዋጁንም በአንድ ማርሽ ወይንም በአንድ የዋሽንት ዜማ በመገናኛ ብዙሃን መልቀቅ ነው! በአንድ ሚድያ የሰማሁትም አዋጁ ከታወጀ አብን የመጀመሪያ ፈራሚ እሆናለሁ ብሎ ቃል እንደገባ ነው። እንደ ተኩስ-አቁም በፊርማ የፓርቲ ዋና አላማ ተብሎ የተያዘውም ሳይቀር እርግፍ አድርጎ ይተዋል ማለት ነው፣ እንደ እቃ እቃ ጨዋታ! በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር የተወሳሰበውን ነገር የላቫ ያህል አቅልሎ ማየትና መፍትሄውም እንደ ኬክ የለሰለስ አድርጎ መቁጠር ነው። ለዚህም ነው የፓለቲካ ተንታኝ መሆን በቀላሉ የሚገባበት ስራ ሆኖ የተገኘው። ጠላቶቼ ሁሉ አንገታቸው አንድ ቢሆንልኝ እሷን በአንድ ምት እቀነጥሳት ነበር ብሎ የመመኘት ያህል ነው። የኢትዮጵያ ችግር ሁሉ ምንጩ ህወሓት የፈጠረችው የብሄር ፓለቲካ ነው በሚል ችግሩ ሁሉ አንድ አንገት እንዲሆን በማድረግ  በአንድ የአዋጅ ሰይፍ ቀንጥሶ ለመገላገል  ማሰብ በሰልን ከሚሉ የፓለቲካ ተንታኞች የማይጠበቅ ቀናሽ (ሪዳክሽኒስት) አስተሳሰብ ነው።

Videos From Around The World

በቅድሚያ መተማመን የሚያስፈልገው  የብሄር ፓለቲካ ያስጀመረችው ህወሓት አይደለችም። ይህን የማድረግ አቅምም አልነበራትም፣ ሊኖራትም አይችልም። ይህ አባባል የኢትዮጵያ ህዝብና ፓለቲከኞች እንደ ህፃን ጭንቅላታቸው ነጭ ወረቀት ነበረና ህወሓት የፈለገችውን ነገር ሞነጫጨረችበት ብሎ ደፍሮ የመናገር ያህል ነው። ህፃን ባይኮንም ህወሓት ያለ ፍላጎት ህዝብን በሃይል አስገድዳ ህግ ደንግጋ የብሄር ፓለቲካ እንዲያራምድ አድርጋዋለች የሚለው ክርክር ሊቀርብ ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን በግዴታ የተፈፀመ ከሆነ ደግሞ አስገዳጁ (ህወሓት) ሲወገድ  የብሄር ፓለቲካ የሚያግድ አዋጅ ሳያስፈልገው የብሄር ፓለቲካ ለምን ብን ብሎ ከአገሪቱ እንዳልጠፋ እንቆቅልሽ ነው። ለምንስ አስገዳጅ ሁኔታ የፈጠረውወሓት ህገ መንግስት” ህዝብ አላስወገደውም? እየታየ ያለው ግን አስገራሚና አደናጋሪ ነው። አሁን ያለው የድህረ-ህወሓት ፓለቲካ የብሄር ፓለቲካ የሚያራምደውን ህገመንግስትን አጥብቆ ይዞ ነው የብሄር ፓለቲካን ለመጣል የሚታገለው። ወደራስ የዞረ አፈሙዝ ያለው ብረት ይዞ ከጠላት ጋር መግጠም ማለት ነው።

አዋጅ ማወጅ ማለት እኮ አስገዳጅ ህግ ማውጣት ማለት ነው። አስገዳጅነት አስፈላጊ የሚሆነው ሰው ማድረግ የፈለገው እንዳያደርግ የሚከለክልና ከተደረገም ለመቅጣት ነው። ለብሄር ፓለቲካ አዋጅ ማውጣት አስፈላጊ ሆኖ የሚገኘው አስገዳጅ ህግ ካልወጣ በስተቀር ሰው የብሄር ፓለቲካ ማራመዱን ማቆም አይፈልግም ማለት ነው። ህዝብ የሚጎዳው ነገር ቀድሞውኑም በውዴታ አይቀበልም፣ ለመተውም አዋጅ አያስፈልገውም። ለምሳሌ ሰው እርቃኑን አደባባይ የሚወጣው ልብስ መልበስ ስለደበረው ነው ወይንም በሃይል ተገዶ ነው። ልብስ መልበስ ስለደበረው ከሆነ በአዋጅ ቢከለከልም ማድረጉን አይተውም፣ ድርጊቱ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ስለሆነ። በግድ እርቃኑን አደባባይ እንዲወጣ ተደርጎ ከሆነም አስገዳጅነቱ ሲቀር ያለ አዋጅ በደስታ ልብሱን ለብሶ ይወጣል።

ኦነግ የኦሮሞን ህዝብ ወክያለሁ ብሎ የብሄር ፓለቲካ የጀመረው ህወሓት የብሄር ፓለቲካን ያማከለ የትጥቅ ትግል የጀመረችበት የጊዜ አቅራቢያ ነው። “ክፉምክር መምከርም ለመመካከር አጋጣሚው አልነበረም። ኦነግ የህዝቡን ሁኔታ ገምግሞ የብሄር ፓለቲካ ጀመረ እንጂ ከህወሓት ጋር የዋለ ጊደር ሆኖ አይደለም። የሲዳማ፣ የአፋር፣ የሶማሊ፣ ወዘተም እንዲሁ። በሌላቸው የብሄር ጥያቄ ባልተቸገሩበት የብሄር ጭቆና ህወሓት በነዚህ ቡድኖች ላይ የብሄር አጀንዳ ያለ ውዴታ አሸከመቻቸው ብሎ ማሰብ የነዚህ ህዝቦችንና የፓለቲካ ልሂቃንን የእውቀትና የብስለት ደረጃ ታች አውርዶ መጣል ነው። የኦሮሞ የብሄር ፓለቲካ ሜጫ ቱለማ የሚል ቅርፅ በመያዝ ቀደም ያለ እንቅስቃሴ እንደነበረ ይታወቃል። በባሌም ተመሳሳይ ህዝባዊ መሰረት ያላቸው እንቅስቃሴዎች እንደነበሩ ታሪክ መዝግቦታል። እንደ ሰጎን ከእውነታው ለማምለጥ ጭንቅላትን አሸዋ ውስጥ መቅበር አያስፈልግም። እውነታው ከአሸዋው በላይ ስላለ። የብሄር ፓለቲካ የሚከሰተው የአንድ ብሄር ህዝብ ባህልና ቋንቋየን በነፃነት መጠቀምና ማሳደግ አልቻልኩም፣ ራሴ በራሴም ማስተዳደር አልቻልኩም ብሎ ሲያስብ የሚፈልገውን ነፃነት ለማግኘት የሚጠቀምበት የፓለቲካ ስልት ነው። በርግጥ በስመ የብሄር መብት ጥያቄ አንዳንዶቹ የብሄር ልሂቃን ለራሳቸው የስልጣንና የኢኮኖሚ ጥቅም ሊያውሉት እንደሚፈልጉና በተግባርም እንደሚፈፅሙት ምንም የሚያጠራጥር አይደለም። ይህ ግን የአፈፃፀም ችግር እንጂ የመሰረታዊው ጥያቄ ጉድለት አይደለም። ሶሻሊዝምን የተገበሩ ፓለቲከኞች ከመሰረታዊ የሶሻሊዝም ህዝባዊነት አፈንግጠው ህዝቡን በመፍጀታቸውና በሙስናና ስልጣን መባለግ ላይ በመሰማራታቸው የካፒታሊዝም አስከፊ ገፅታ የወለደው ሶሻሊዝም የተሳሳተ ርእዮተ አለም እንዲሆን አያደርገውም። መታረም ወይንም መወገድ ያለበት ሶሻሊዝም ሳይሆን የተበላሸው አፈፃፀሙ ነው። የብሄር ጥያቄ የፈጠረው ራስን በራስ የማስተዳደር አስፈላጊነት ከሆነ ችግር አይደለም ፍትሃዊነት እንጂ። ችግር የሚሆነው በአፈፃፀም ላይ በብሄር መብት ማስከበር ስም የብሄር አምባገነን አስተዳደር የሚፈጥር ከሆነ፣ የህዝቡ ሳይሆን የተወሰነ ቡድን ወይንም ቡድኖች ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርግ ከሆነ፣ የሃገር አብሮነት አደጋ  ላይ የሚጥል ከሆነ መወገድ ያለበት ክቡር የሆነው የህዝብ ጥያቄ ሳይሆን በመብት ስም የተፈጠሩትና ባህርያዊ ያልሆኑት ጉድፎች ናቸው። ህፃን ልጅ ሲቆሽሽ ገንዳ ውስጥ ይታጠባል፣ ከዛም ህፃኑን ከገንዳው አውጥቶ ቆሻሻውን ዉሃ መድፋት እንጂ ህፃኑንና ቆሻሻውን ዉሃ አንድ ላይ ከገንዳው አውጥቶ መድፋት አላማ ቢስነት ነው። እኔ አውቅልሃለሁ፣ የኔን ባህልና ታሪክ የራስህ አድርገህ ተቀበል፣ ያለ ውዴታ አስተዳዳሪህ ከማእከል ይመደብልህ የሚሉት አስገዳጅ ሁኔታዎች እስካሉ ድረስ የብሄር ፓለቲካ እየተጠናከረ መሄዱ አይቀርም፣ ህወሓት ኖረች አልኖረች!

ስለዚህ መፍትሄው "ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ የቀየሰው ነው" እያሉ ራስን በማታለል ችግሩ ያለመፍትሄ እንዲወሳሰብ ከመፍቀድ ይልቅ ለጉዳዩ በሚመጥን ጥልቀት የጋራ መፍትሄ መፈለግ ነው። ሁሉም በብሄር ፓለቲካ ድንኳን በተጠለለበት ሁኔታ የብሄር ፓለቲካ የሚያግድ አዋጅ ይውጣ ብሎ ነገሮችን ማቅለል እጥፍ ድርብ ሆኖ የሚመጣ ችግርን መጋበዝ ነው። ደግሞም አስደማሚው ነገር ብሄርተኛውን ብሄርተኛ እያሉ ሲያወግዙ የሚሰሙት ባመዛኙ ራሳቸው ብሄርተኝነትን የሚያራምዱት ናቸው። አውጋዦቹ ራሳቸውን ለመከላከል በበጎ ጎኑ ብሄርተኝነትን የሚያራምዱት ሳይሆኑ ሌላውን አምበርክኮ ለመግዛት የሚያልመውን ብሄርተኝነት አጥብቀው የታጠቁት ናቸው። መጥፎው ብሄርተኝነት መልካሙን ብሄርተኝነት በአገር አፍራሽነት እየከሰሰ ነው፣ አመድ በዱቄት እየሳቀ ነው። ለዩጎዝላቪያ መፍረስ ተጠያቂ የክሮሽያ ወይንም የቦዝኒያ ተከላካይ ብሄርተኝነት ሳይሆን አጥቂና የማይደራደር፣ እኔ ብቻ ነኝ የሃገር አንድነት መከታ፣ ሌላው ሁሉ አፍራሽ ነው ሲል የነበረው የሰርቢያ ሄርተኝነት ነበር። ግትርነቱ ዩጎዝላቪያን ከመበታተን አላዳናትም፣። ታሪክን በሞኝነት አንድገም፣ ከመበታተን መወያየት እጅግ የቀለለ መሆኑ መናገር የማያስፈልገው ግልፅ የሆነ ሃቅ ነው። በአልበገር ባይነት መጥፋት ከፈለግን ግን ሜዳው ይኸው ፈረሱም ዝግጁ ነው።


Back to Front Page