Back to Front Page

የዋሁ ህዝባችን ኣሁን ተፈታ፤ ሃገሬም በመበታተን ቋፍ ላይ ነች

የዋሁ ህዝባችን ኣሁን ተፈታ፤ ሃገሬም በመበታተን ቋፍ ላይ ነች

ርእሶም ኣባኩኖም ኣባበልጉ

09-20-20

ኢትዮጵያ ሃገራቸን በመጠራ ታስቦ በይሓ ተፀንሶ በኣክሱም ተወልዶ፣ ኣድጎ በጎለመሰው ኣስገራሚ ስልጣኔዋ ዓለምን ብዙ ነገሮች ኣስተምራለች። ኣክሱምን እንደኔ ሄዳችሁ ጎብኟት፤ ኣስተሳሰባችሁን የሚቀይር የተግባር ትምህርት ኣብርሆት ታገኛላችሁ። የኣክሱም ትምህርት/ጥበብ በክልሰ-ሃሳብ ሳይሆን በሞዴልና በሰርቶ ማሳያዎች የተደገፈ ተግባራዊ የእውቀት ሽግግር ይፈፀም እንደነበር የኣክሱም ሙዚየም ለጎበኘ ሰው ግልፅ ነው። ለምሳሌ ከ2800ዓ/ዓለም በፊት የተሰራው እርፍ፣ድግር፣ወገል፣ ማርሻ፣ሞፈር ፣ቀንብር የኣንድ ጥማድ የእርሻ መሳሪያ ሞዴል፤ የኣሁኑ የቆርቆሮ የቤት ክዳን (ጣራ) የሚመስል ሞዴል እንዲሁም በ5ኛው ክ/ዘመን ኣክሱምን የጎበኘው የግሪክ ንጉስ የፃፈው የኣክሱምን ታሪክና የወሰደው የገናናው ንጉስ ተክኣማርያም ቤተመንግስት ፕላን መጥቀስ ይቻላል።  ይህን ሁሉ ለማድረግ ኣክሱም ህግና ስርዓት የሚከተሉ ጠንቃቃ መሪዎች ስለነበሩዋት ነው። መሪዎቿ በስርዓትና ስልጣኔ በልጠው ኣብዛኛው ኣፍሪካንና እስከ ኣሁኗ ሳውዲ ኣረብያ ድረስ ሰፊ ግዛት በህግና በስርዓት ያስተዳድሩ ነበር።

ህግና ስርዓት የሌለው ሃገር፤ ሃገር ኣይደለም። ህግና ስርዓት የተጓደለ ዕለት ህዝቦች ህግና ስርዓት ፍለጋ ይዋትታሉ፣ ይባዝናሉ። ይህም የህዝቦች ኣምራችነት ይቀንሳል፤ ረሃብና ቸነፈር፤ ስደትና መከራ ይበዛል። ችግሩን የሚቋቋምበት የትዕግስት እንጥፍጣፊ ኣልቆ ህዝብ ይፈታል። በመጨረሻ የተፈታ ህዝብ ኣንዱ ባንዱ ላይ ይነሳል፤ ወንድም በወንድም ሚስትም በባልዋ ላይ ተነሳስቶ በግላጭ ነውሮች ይፈፅማል። ለምሳሌ የሌላን ሰው ሚስትና ንብረት ያለሃፍረት ይዘርፋል፣ ይደፍራል፣ይሸጣልም፤ ህዝብ እንደ ህዝብ፣ ሃገርም እንደ ሃገር ይዋረዳል፤ ሃገርም ይፈርሳል። እንደዚህ ዓይነት የማህበረሰብ የመፈታትና የውርደት ክስተቶች  በዓለማችን ተከስተዋል፤ ለምሳሌ በኣውሮፓ በተለይ በእንግሊዝ እንዲሁም በእስራኤል ሰው የተበላበት ሴቶች ልጆቻቸውን እስከመብላት የደረሱበት ግዜ እንደነበር ታሪክ ያስተምረናል።

Videos From Around The World

ኣብዛኛዎቹ  የማህበረሰብ ዝቅጠቶች የሚከሰቱት ክፉ መሪዎቻቸው በሚያደረሱባቸው የስርዓት ዝንፈት ነው። ስለዚህ ሃገር የምትቆመው በህግና ስርዓት ብቻ ስትመራና ይህ ህግ በተግባር የሚመራ መንግስት ሲኖራት ብቻ ነው። ኣሁን የሃገራችን ህዝቦች ላለፉት ኣራት ዓመታት ያለምንም እረፍት በኑሮ ውድነትና ሰላም ማጣት ኣበሳው እያየ ነው። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ህዝባችን ኣዕምሮው ከሚቀበለው በላይ የተጠላለፉ (complex) ዘርፈ ብዙ ችግሮች ኣእምሮው ተጨንቆ እንዳይፈቱት የሃገራችን የህክምና፣ የስነኣኣእምሮና የስነህዝብ ሙሁራንና ባለሙያዎች ፖለቲከኞቻችን ማማከርና የስልጣን ሽኩቻቸውን እንዲያለዝቡ ለነገ የማይባል ኣስቸኳይ የሃገር ጥሪ መሆኑ መገንዘብ ይገባል። በተጨባጭ ኣሁን የህዝቡን ስርዓትና ወግ ሊፈቱ  የሚችሉ ኣደገኛ ኣዝማሚያዎች እየታዩ ነው።

የማያባራ የሴራ ፖለቲካ እሽክርክሪት ውስጥ የሚያኖር የስልጣን ጥመኛ ቡዱንና መዘዙ?

ባለፉት ኣራት ዓመታት ሃገራችን ከውስጥና ከውጭ የተሸረበባትን ሴራ መሪዎቻችን ማየትና ማሰብ ኣቅቷቸው፤ ገሚሱ ከጥንተ ጠላቶቿ ኣብሮ፤ ዋናው የሃገር ጠላት ትተው እርስ በእርስ ለስልጣን ተቧድነው፤ እኛ የዋሆቹ ኣበሳችን ሲያሳዩን ቆይተዋል። ወጣቶች በወጡበት ቀርተዋል፤ ሴቶች ክብራቸው ተደፍረዋል፤ ህፃናትና ኣዛውንቶች ያለጧሪና ቀባሪ ቀርቷል። የሃገሪቱ ኣንጡራ ሃብቶች ተዘርፈዋል፤ ተቃጥሎ ኣመድ ሆነዋል። ኣለፍ ሲልም ክቡር የሰው ልጅ በኣደባባይ በድንጋይ እንደ እባብ ተወግሮ ተገድለዋል፤ ተሰቅለዋልም። ይህ ሁሉ ለስልጣን ሲባል በስልጣን ጥማት በነደዱ ዕብዶቸ ተሸርቦ የዋሁ ለፍቶ ኣዳሪና ሚስኪኑ ህዝብ ሲያባሉት ቆይቷል።

ኣሁን ደግሞ ወገን በወገኑ ላይ እንዲነሳ መራሄ መንግስት የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስተር ኣብይ፤ በወገኖቹ ላይ መጨከን ኣቅቶት በኑሮ ውድነትና ሰላም ማጣት የሚሰቃየው የፀጥታ ሃይላችን ህዝቡን ዝረፍ ብሎ ማዘዝ የሴራዎች ሁሉ ጫፍ ነው። እንዴት ህዝቡንና ሃገሩን በክብር ለመጠበቅ ልዩ ወታደራዊ ስልጠና ወስዶ ጦር መሳሪያ የታጠቀ  ሃይል ስቪል ህዝቡን መሳሪያ ተጠቅሞ እንዲዘርፍ ይታዘዛል? ወገን በወገኑ እንዲነሳ የህዝብ መሪ እንዴት ጥሪ ያደርጋል? ይህ ብልፅግና የተባለው ቡዱን በምን ፎርሙላ ወይም ማነው የሰባብሰባቸው? ኣንዱ ሲሳሳት ሌላው ኣያርምም ወይ?  ሁሉም ደንቆሮዎችና ግብፅ የቀጠረቻቸው ከሃዲ ባንዳዎች ናቸው ወይ? እንዴት ኣንድ ባለስልጣን ኣባቱን፣ ኣጎቱ፣ እህቱና ወንድሙ ኣደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ተባባሪ ይሆናል? 

ይህ ደርግ/ኢሰፓ ካደረገውና ሃገራችንን ቁልቁል ከደፏት  ኣደጋዎች የባሰ ኣደጋ ነው። ደርግ በህዝብ ጉልበትና ሃብት ተጠቅመው ለምሳሌ ገበሬውን ጭሰኛ ኣድርገው ሃብት ኣካብተዋል ብሎ የሃፀይ ሃ/ስላሌ መሳፍንትና ጥረው ግረው የከበሩ ነጋዴዎች ንብረትና ሃብት እንዲወረስ ኣድርገዋል። መጀመሪያ በደርግ ኣዋጅ ብዙ መሳፍንት በህዝብ ላብ ይሁን በላባቸው ያፈሩት ሃብት መሳፍንት በመሆናቸው ብቻ ተዘርፈዋል፤ ቀጥሎ ደግሞ ነጋዴዎች ከ500ሺ ብር በላይ ያላቸው እንዲወረስ ተደርገዋል። በዚህ ሂደት ደርግ ጦር ሰራዊቱን ያዘዘው ወርሶ  ወደ መንግስት እንዲያስገባ እንጂ “የዘረፍከው ለራስህ” ኣላለም። ከተዘረፈው ለመስረቅ የሞኮሩትና የተነቃባቸው በኣደባባይ የሞት ፍርድ ተፈፅሞባቸዋል። ደርግ ቆየት ብሎ “ሁሉም ሰው ኣንድ ኣንድ ቤት ብቻ እንዲኖረው፤ ሁለት ቤት ያለው ኣንዱ ለቀበሌ ያስረክብ፤ ቀበሌም ቤት ለሌላቸው ድሆች በርካሽ ኪራይ ያድል” ብሎ ኣወጀና በላባቸውና በእውቀታቸው ሁሉም ችግሮች ኣልፈው ጥረው ግረው ያፈሩትን ሃብት በጠራራ ፀሃይ ተቀምተዋል። እስከ ኣሁን ድረስ ከትግራይ በስተቀር በሁሉም የኢትዮጵያ ከተሞች የቀበሌ ቤት ተብለው የሚከራዩት ቤቶች፤ ኣብዛኛዎቹ በደርግ የተወረሱት የነጋዴዎች ንብረት ሲሆኑ ብዙዎቹ የተወረሱ ነጋዴዎች የኣእምሮ በሽተኞችና እብድ ሆነው በየሜዳው ለማኝና ተባራሪ ሆነዋል፤ የተወሰኑት ደግሞ ተረሽነዋል። ያ ኣዋጅ በኢትዮጵያ ላብንና እውቀትን ተጠቅሞ ሃብት ማፍራት ወንጀል በማድረጉ ደርግ ከወደቀ በኃላም ልበሙሉ ነጋዴ ለመፍጠር ኣዳጋች ኣድርጎት ነበር። ይህ ኣሁን የሚታየው ሚሊየነርና ቢልየነር ሁሉ በኢህኣዴግ/ ህወሓት መንግስት የነፃ ገበያ ስርዓት የፈጠረው ነው። ኣሁን ግን ወዮላችሁ ባለ ሃብቶች፤ ሃብት ማፍራት ሃጥያት የሚሆንበት ዋዜማ ላይ ነን።

ደርግና ብልፅግና ልዩነት ኣላቸው ወይ?

ኣንድነትም ልዩነትም ኣላቸው። ደርግ ንብረት ሲወረስ በኣዋጅ ኢንጂ በመንግስቱ ሃ/ማርያም ቀጥታ ትእዛዝ ኣልነበረም። ደርግ የሃገሪቱ ህዝብ በከፍትኛ ደረጃ የድህነት ማቅ ውስጥ በነበረበት ጊዜና መንግስትም በቂ ሃብት ባልያዘበት ወቅት በስርዓት የታወጀ ኣፍራሽ ኣዋጅ ነበር የተጠቀመው። ደርግ የሃገሪቱ ሃብት ከብዙ ባለሃብቶች ወደ ኣንድ ቋት ሰብስቦ የህዝብን ጥያቄ ለመመልስ ሙከራ ኣድርገዋል። ብልፅግና ግን በዶ/ር ኣብይ “ ንጉስ” ቀጥታ ትእዛዝ ሃገር ሃብትዋ እንዲዘረፍ ጥሪ ተደርገዋል። ኣንዴ ሲናገሩ 99 ጊዜ የሚያስተጋባ ፓርላማና የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲሁም ሳይጠሩት ኣቤት ሳይልኩት ወዴት የሚል ካቢኔ እያላቸው፤ በግላቸው ኣምባገነናዊ ትእዛዝ ሃብት ከተሰበሰበበት የባለ ሃብት እጅ ወደ ሚሊዮን ቀማኛ ቦዜኔዎች እጅ የመበተን ስራ ነው እየሰሩ ያሉት። ይህ ብር ለሌላ ወንጀል ሃገርና ወገን ለማወክ ብቻ ነው የሚውለው። በህገወጥ መንገድ የተገኘ ሃብት በመብልና መጠጥ ያልቃል እንጂ ኢንቨስትመንት ሆኖ ለዘራፊው እሴት ኣይጨምርም።

ሁለትም የሚወረሰው ሃብት ደርግ የወል ሃብት ሲያደርግ ብልፅግና ለወራሹ የፀጥታ ሃይል የራስህ ኣድርግ ተብለዋል። በደርግ ጊዜ ጥቂት ሰዎች ሲጎዱ ብዙ ድሆቸ የቤት ባለቤት ስላደረገ የድሃው ህ/ሰብ ችግር በጊዜያዊነት ፈተዋል። የተሰበሰበው ሃብትም መንግስት ለተለያዩ ወጪዎች መሸፈኛና የስራ ዕድልም ፈጥሮበት ነበር። ለምሳኤ የእድገት በህብረትና ማሃይምነት ላማጥፋት ብዙ ተኣምራዊ ውጤቶች ኣስመዝግበዋል። የዶ/ር ኣብይ “ትእዛዝ” ግን 100% ሁሉም ሰው የሚያዝንበት ነው፤ ሃፀይ ካሌብ እንዳሉት “የዘገነም ኣዘነ ያልዘገነም ኣዘነ” ይሆናል። የተዘረፈም፣ ኣንድም፣ መቶም፣ ሺም፣ ሚሊዮንም የዘረፈ እኩል ያዝናሉ፤ በፍፃሜው ደስተኛ ኣይኖርም። ሁለቱም መሪዎች ባለሃብቶችን ሲያዘርፉ ለብዙሓኑ ኣሳማኝ የሚመስሉ ምክንያቶች ነበሯቸው፤ የሃገር ሃብት በጥቂቶች ተዘርፈዋል የሚል ነበር፤ ነገር ግን ባለማውቅ ደርግ ሃገር ያወደመበት ኣሁን እየተደገመ ነው።

ብልፅግና የዘመነ ሳይሆን ኃላቀር ደርግ ነው!!! ኣሁን የብዙ ተከታታይ ጥፋቶች መጀመሪያ ከ1.5ሚሊዮን በላይ ዝረፉ ኣለ፤ በዘራፊውና ተዘራፊው መሃል ህግ ማን ያስከብር? ኣሁን እየተሰማ እንዳለው ጥሬዎቹ ኣህመድ ሽዴና ይናገር ደሴ በተለቪዥን ቀርበው “ነዳጅ ማደያዎች እና የመሳሰሉ ተቋማት ሽያጫቸው ከኣንድ ሚሊዮን በላይ ቢሆንም ኣትንኩ፤ ሽፌሮችም እስከ 30ሺ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ኣትዝረፉ” ብሏል። ታድያ ህግ ኣስከባሪው ዘርፈህ ለራስህ ከተባለ ይህ ማን ህግ ያስከብር? ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ብቻ እየዘረፈ ከሆነ፤ ለምን ሽፌሮች እስከ 30ሺ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ኣትዝረፉ ተባለ? በጠቅላዩ ትእዛዝ ሃብታምን ብቻ ሳይሆን ድሃንም ጥሪቱን እየተዘረፈ መሆኑ ምስክር ነው። ሌላው ነገር ዝርፊያው ነገ ወደ ቤትና ድርጅት ይገባል፤ “ከኣንድ ህንፃ በላይ ያለው ውረስ ይባልና” ሁለት የመኝታ ክፍል ያለው የኮንዶሚኒየም ቤትም ዘራፊዎች በደባልነት ይገባሉ ማለት ነው። የታዘዘው ትእዛዝ ቆሞ ማስፈፀም የነበረበት ዘርፈህ ለራስህ ስለተባለ ህግ ኣስከባሪ የለም። ኣቤት የሚባልበትና ዳኝነት የሚገኝበት ስርዓት ጠፍቷል። ከዚያ በኃላ የውጭ ሰዎች ይቅርና የሃገሬው ሰው እንኳ ነግዶ መክበር ህልም ይሆንበታል።

ከሁሉም በላይ ግን የሃገራችን መልካም ገፅታ ለረዥም ጊዜ ያጠፋል፤ የተወሰኑ የውጭ ባለሃብቶች ኣሁን እየተዘረፉ ነው፤ ነገ ሁሉም ኣይቀርላቸውም። ታዲያ የውጭ ኢንቨስትመንትና ምንዛሪ ከየት ይገኛል? የሰራ ዕድልስ እንዴት ይፈጠራል? ሃገርስ እንዴት ታድጋለች? የትኛው እብድ  ባለሃብት ነው የፀጥታ ሃይልዋ ባለሃብቶችን የሚዘርፍ ባላት ሃገር ኢንቨስት የሚያደርገው?።

የብልፅግናው ንጉስ ሰይጣናዊ ኣዋጅ እስካወጁበት መስከረም 07/2013ዓ/ም ድረስ የፀጥታ ኃይሎች (ፖሊስና ሚሊሻ) ባሉበት ኣካባቢ መንቀሳቀስ ደህንነት ይሰማን ነበር፤ ኣሁን ግን እንደነግጣለን። የፀጥታ ኣባላት በስጋትና በጥርጣሬ ያያቸዋል። እነሱ ባሉበት ኣካባቢ መንቀሳቀስ (ከትግራይ ውጭ) ኣደገኛ ሆኗል፤ መዘረፍን ያስከትላል። ኣሁን ህዝቡ ተሸብረዋል እምነቱ ጠበንጃውና ቤተሰቡ ላይ እንጂ ህግ ላይ ኣይደለም። ታዲያ ከሳምንታት በኃላ ምን ዓይነት ሃገር ነው የሚኖረን? 

ኣሁን ብልህ ነጋዴ፣ ሙሁርና ባለሙያ መሆን ሳይሆን የታጠቀ የፀጥታ ሃይል መሆን ይሻላል፤ በኣዲሱ ትእዛዝ ሳትሰራ ሚሊየነር መሆን ይቻላልና። ይህ ሁኔታ ሁሉም ዜጋ ሆ ብሎ ካላስቆመው ብዙ ነገሮች ከቁጥጥር ውጭ ይሆናሉ።

1.      ህዝቡ የመንግስት መኖር ፋይዳ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። መንግስት የሚያስፈልገው መጀመሪያ ህግና ስርዓት እንዲያስከብር፤ ህዝቡ ከሌባና ቀማኛ እንዲጠብቀውና ፍትሕ እንዲያሰፍን፤ የልማት ጥያቄዎች እንዲመለስ ነው። ይህ ባልሆነበት ሰዓት ዓመፅና የመገንጠል ጥያቄ በትጥቅ ትግል ታግዞ ህዝቦች ሌላ የሰላም ኣማራጭ ፍለጋ ይባዝናሉ። ሃገር ይፈታል ማለት ነው። 

2.      ህዝቡ የፀጥታ ሃይሉን እንደጠላት ያየውና የፀጥታ ስራ መስራት ኣዳጋች ያደርገዋል።

3.      ሙስናና ብልሹ ኣሰራር ያስፋፋል። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ ህዝቡ በየኣካባቢው የሚገኙት የጎበዝ ኣለቆች ከፀጥታ ሃይሎች ዝርፊያ ይከላከልልኛል ብሎ መንከባከብና ለእነሱ ግብር መክፈል ይጀምራል። መንግስት በኣግባቡ የሚቆጣጠራቸው ኣከባቢዎችና ልማት ለማምጣት ግብር መሰብሰብ ያቅተዋል።

4.      የፀጥታ ሃይሉ ልክ ሌሎች የኣፍሪካ ሃገራት እንደምንሰማው ግለኛና ሃገሩን ለገንዘብ የሚሸጥ ያደርጋል። ይህ የሆነ ዕለት ኣሽባሪዎች እንዳሻቸው ጦር መሳሪያ በግላጭ ማዘዋወር ይችላሉ። በኣንዱ የጎረቤት ሃገር ኣልሻባብ ጥቃት ለማድረስ የፀጥታ ሃይልዋ እንደሚተባበር ይወራል፤ ኣልሸባብም የፈለገውን ሰው እስከ የሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ቤተሰብ ለማገት በገንዘብ ይደራደራል፤ ሽብር ይፈፅማል። የፋይናንስ ተቋማት የሚጠብቁት በዱላ እንጂ መሳሪያ ኣይሰጣቸውም፤ ዘበኛው መሳሪያ ከያዘ ተቋሙ ቀድሞ የሚዘርፈው ራሱ ይሆናል ይባላል። ይህ ሁኔታ በኣሁኑ ኣካሄድ እኛ ሃገር ላለመከሰቱ ምንም ዋስትና የለንም።

የባለጠጎች ሃብት መዝረፍ ደርግ ሲውል ሲያድር ተቀባይነቱ መሬት ያዘና ህዝቡ የያኔው ኣማፅያን (ህወሓትና ምርኮኞቹ) በመደገፍ ዕድሜው ኣሳጥሮታል። ኣሁንስ ብልፅግና በራሱ ኣዋጅ ራሱን ሊያጠፋው ይችላል ወይ? ኣብረን እናየዋለን።  

ኢትዮጵያ ሃገሬ ናት የሚል ዜጋ ሁሉ ማድረግ ያለበት ምንድነው?

1.     የፖለቲከኞች

በኣሁኑ ሰዓት በብልፅግናና ተቃዋሚ ጎራ ያላችሁ ፖለቲከኞች ኣሁን እየሄድንበት ያለነው መንገድ ኢትዮጵያ ሃገራችን ወደ 2014 ዓ/ም እንደ ሃገር መሻገር ኣያስችላትም። ስለዚህ ብሩ ይቀየር ግን ለፀጥታ ሃይሉ የተሰጠው ትእዛዝ በተሎ መቆም ኣለበት። ካልቆመ ግን ሃገራችን መበታተንዋ ግድ ይሆናል ማለት ነው። ይህ በታኝ ኣዋጅ ኣንዲቆም በኣንድነት ታገሉ፤ በማወቅም ባለማወቅም ትእዛዙ ያስተላለፉት ጠቅላዩ ከተግባራቸው እንዲታቀቡ ግድ ማለት ኣለባችሁ። “ጥፋት ከሚሰሩ ወንጀለኞች ይልቅ ወንጀል እየተሰራ ዝም ብልው የሚያዩ የባሱ ወንጀለኞች ናቸው” የሚባለው ነገር ኣስታውሱ። ሃገር ወደኣዘቅት እየገባች እያያችሁ ለጊዜያዊ ጥቅም ዝም የምትሉ ከሆነ ከታሪክ ተጠያቂነት ኣታመልጡም።

2.     በዩኒቨርሲቲና በሌሎች ተቋማት የምትገኙ ሙሁራንና ተማሪዎች

ሃገራችን በኣሁኑ መንገድዋ ብዙ እንደማትሄድ ለእናንት መካሪ ኣያስፈልጋችሁም፤ ምርምርም ኣያስፈልገውም። ታዲያ ለምን ዝም ትላላችሁ? ዕውቀታችሁን ተጠቅማችሁ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የዘርፈህ ብላ ኣዋጅ ውጤቱ ሃገርንና ህዝብን የሚፈታ ስርዓትን የሚያደፈርስ ብቻ ሳይሆን የሃገራችን የምንኮራባቸው ወርቅየ ወግ፣ ባህሎቻችንና ስርዓታችን የሚንድ መሆኑ  በጥናት መንግስትን ሞጉቱ።

ስርቆት ተፀይፎ የወርቅ ሱቅ በር ላይ ተቀምጦ የሚለምን ዜጋ ያላት ሃገር ኣሁን የፀጥታ ሃይልዋ ኣንዲዘርፍ ታዞ እሴቶቻችን እየተናዱ እያያችሁ ዝም ማለት ኣለባቸሁ ወይ?። ኣለበለዚያ ግን ሁሉም ነገር እያየነው ይጠፋል፤ ሃገር ኣይኖረንም። የምንዝናናበት ይቅርና ውለን የምናድርበት ሃገር ኣይኖረንም? ሌላኛዋ ሶማሊያ እየተፈጠረች ዝም ባላችሁ ኣትዩ? ሶማሊያውያን ሃገኣቸው ስትፈርስ ምን እንደደረሳቸው በዓይናችን ኣይተናል፤ የነሱ እጣ-ፈንታ በራችን እያንኳኳ ነው። ታዲያ ዝም ማለት ኣለብን ወይ? የሃፀይ ሃይለስላሴ፣ ደርግና ኢህኣዴግ ስርዓቶች ስህተት እያየናቸው በትጋት ሳንታገላቸው ቀርተን ዓይናችን እያየ ተንኮታኩተው ሲወድቁ ኣይተናል። ሃገራችን ሁሌ በባለ ጊዜ ሞገደኛ ፖለቲከኞች እየታመሰች የኣያቶቻችን፣ የኣባቶቻችን፣ የእኛና የልጆቻችን ህይወት ሲበላሽ ኣየን፤ ኣሁንስ ዝም ብለን የልጅ ልጆቻችን ዕድል ይበላሽ ወይ? እኛስ እርጅናችን በሰላም ሃገር መሆን የለበትም ወይ? በስተመጨረሻችን ጉልበታችን ባዛለ ጊዜ ወዴት ኣንሰደዳለን? ስደትም እኮ መልካም ስም ይዞ ነው የሚያምረው። ስለዚህ ክፉውን ነገር ስር ሳይሰድ ታገሉት።  ሃገራችንና ህዝብዋ እግዚያብሄር ይታደግ!!!

Back to Front Page