Back to Front Page

የዘመናችን አድዋ ዘመቻ ክፍል ሁለት

            

                  የዘመናችን አድዋ ዘመቻ  ክፍል ሁለት

መጋቢት 13 ቀን 2012(22-03-2020)

የመጀመሪያው ያድዋ ዘመቻችን የተካሄደውና በድል አድራጊነት ያገራችንን ነጻነትና ልዑላዊነት ያስከበርነው ከዛሬ መቶ ሃያ አራት ዓመት በፊት ነበር።በዚያን ጊዜ ድንበር ሰብሮ ለመውረር ከውጭ የመጣውን ጠላት እንደ አንድ ሰው መክረን እንደ ንብ ተሰልፈን ካለበት መሬት ድረስ በመሄድ ድባቅ መትተን በመመለሳችን እኛ ብቻ ሳንሆን ሌላው ነጻነቱን ወዳድ ሕዝብ በኩራትና በአድናቆት የሚመለከተውና እንደምሳሌም የሚወስደው ታሪካችን ነው።ያ ያያቶቻችን ገድል አሁን ላለው ትውልድ በነጻነት የመኖር መብቱን አረጋግጦለታል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአድዋ ወዲህ በየጊዜው የሚመጡበትን  የወረራና የትንኮሳ ሙከራዎች ከአባቶቹ በወረሰው ጀግንነት ተባብሮ በመመከት ያገሩን ህልውናና የመኖር መብቱን ሲያረጋግጥ ቆይቱዋል።አሁንም ሆነ ወደፊት ክብርና መብቱን አሳልፎ የሚሰጥ ኢትዮጵያዊ ትውልድ አይኖርም።ይህንን የኢትዮጵያውያኑን ተፈጥሮዋዊ ወኔና አገር ወዳድነት ያላወቁ ጠላቶች ሁኔታ ተጠቅመው ፍላጎታቸውን ለማሙዋላት ያልሞከሩበት ወቅት የለም።አሁንም በመሞከር ላይ ናቸው።

Videos From Around The World

የዘመናችን አድዋ ዘመቻ ጥሪ እንድናስተላልፍ ያስገደደን  በአባይ ወንዝና በሚገነባው የህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተነሳው ያልተገራ የግብጾች የይገባኛል ጥያቄ አገርሽቶበት የኢትዮጵያን ህልውና ከመፈታተን ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው። የአሁኑን ጊዜ ልዩ የሚያደርገው በግብጽ ጀርባ ጥቅማቸውን ለማስከበር ኢትዮጵያን መስዋእት ለማድረግ የተሰለፉ መንግሥታት መኖራቸው ነው።ወዳጅና አሳቢ መስለው ጉዳዩ የሚመለከታቸው አገሮች ማለትም  ኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብጽ እንዲደራደሩና እነሱም በታዛቢነት ለመሳተፍ ፈቃደኞች ሆነው የቀረቡት የአሜሪካ መንግሥትና የዓለም ባንክ ድርድሩ ከመጀመሩ በፊት ይኖረናል ያሉትን  የታዛቢነት ቦታቸውን በአደራዳሪና በዳኛነት ለውጠው የድርድሩ ውጤት ወደ አንድ ሚዛን ማለትም ወደ ግብጾች እንዲያደላ በኢትዮጵያ ተወካይ ተደራዳሪዎች ላይ ጫና በማስቀመጥ ውሉን እንዲቀበሉና እንዲፈርሙ በማስገደድ ላይ መሳተፋቸው የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ስሜትና ቁጣ ቀስቅሱዋል።

በቅርቡም የአረብ አገሮች ህብረት ተመሳሳይ ጫና በኢትዮጵያ ላይ ማስቀመጡ ተስተውሉዋል።በአውሮፓ አገሮችም በኩል በጀርመን መንግሥት ፊት አውራሪነት የአባይ የባለቤትነት መብትና የህዳሴ ግድብ ግንባታ ሥራ መጠኑ ተቀንሶ  በገንዘብ ካሳ እንዲቀዬርና የግብጽ የይገባኛል ጥያቄ ፍትሃዊ እንዲሆን፣የማድረጉ ሙከራ  ይፋ ወጥቱዋል።

ይህ ኢፍትሃዊና የማንአህሎኝነት ምግባር ከወረራ የተለዬ ተደርጎ አይታይም።ኢትዮጵያ ለሌሎች አገሮች ጥቅም መስዋዕት የምትሆን ጠቦት አይደለችም።የመቶ ሚሊዮን ጀግናና ለጥቃት የማይመች ሕዝብ አገር ነች።ኢትዮጵያውያን በሆነባልሆነው ብንጨቃጨቅም ብሔራዊ መብታችንን አሳልፈን እንደማንሰጥ ካለፈው ታሪካችን ሊማሩ ይገባ ነበር።ጠላቶቻችን ስህተት ውስጥ እንዲገቡ ያደረጋቸው አሁን የገጠመንን የፖለቲካ ቀውስ ተገን በማድረግና አገሩን የሚወጋ ፣የሚክድ የውስጥ ጠላት አለ ብለው በማመናቸው ነው።ይህ ግን  ዱሮም አልሆነም አሁንም እንደማይሆን ሊያውቁት ይገባል።አባይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ንብረትና ኩራት ነው።ለጊዜያዊ ጥቅም ብሎ አገሩን የሚከዳ አይኖርም።የከዱ በታሪክና በትውልድ የሚኖራቸውን ቦታ ጠንቅቀው ያውቃሉ።

 የግብጽ አባይን የመቆጣጠር ሙከራ ከአስር ዓመት ወዲህ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተከሰተ ሳይሆን ዘመናት ያስቆጠረ ነው፤በጦር ሃይልም ያደረጉት ሙከራ ሳይሳካላቸው ቀርቱዋል።ጠንካራ የኢትዮጵያ መሪዎች በነበሩበት ዘመን ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላትን ባለቤትነት በማወቅ ለምታገኘው የውሃ ተፋሰስ ግብጽ ኪራይ ትከፍል እንደነበረ ታሪክ ይመሰክራል። አሁን ለአገሩ አንድነትና ክብር ደንታ የሌለው የጎሰኞች ስብስብ ስልጣን ላይ ተቀምጦ ሕዝቡን በጎሳና በቋንቋ እየከፋፈለ ባለበት ሁኔታ የግብጾችም ሆነ የሌሎች ድፍረት የሚያስገርም አይሆንም።ግን ይሞክራሉ እንጂ አይሳካላቸውም።

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ(International Ethiopians Solidarity Forum) በአባይ ጥያቄ ላይ ያለው አቋም የሚከተለው ነው

1 የአባይ ወንዝ ማንም የውጭ ሃይል የይገባኛል ጥያቄ የማያቀርብበት የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሃብት ነው።

2 አትዮጵያ በግዛቱዋ ውስጥ በሚፈስ ወንዝና ጅረት የመጠቀም መብቱዋን ማንም ሊከለክልና ጣልቃ ሊገባበት  አይችልም።

3 ኢትዮጵያ ወንዞችዋን በአግባቡ ተጠቅማ ከድንበሩዋ አልፎ በሚሄደው የውሃ ተፋሰስ ላይ አገሮች ለሚያደርጉት አጠቃቀም ጣልቃ አትገባም።ሱዳኖችም ሆኑ ግብጾች  በመሬታቸው ላይ የሚፈሰውን ውሃ የመጠቀም መብታቸውን ታውቃለች።በአስዋን ግድብና ተመሳሳይ ዕቅዶች ላይ ጥያቄ   እንዳላነሳችና  ችግር እንደማትፈጥር ሁሉ በእሱዋም የህዳሴ ግድብም ሆነ በተመሳሳይ ተግባር ላይ ችግር እንዳይፈጠርባት ትሻለች።ይህ መብቱዋ እንዲከበርላት ድምጻችንን እናሰማለን፤የሚያስፈልገውን ሁሉ ለማበርከት ዝግጁ ነን።

4  ምንም እንኳን በሕዝብ ባይመረጥም፣አጋጣሚውን ተጠቅሞ ሥልጣኑን የጨበጠው ቡድን በሌላው ዙሪያ እንደታዬው የአገሩን ጥቅም በመደራደር አሳልፎ እንዳይሰጥ፣ከተጀመረውም ድርድር ውስጥ እንዲወጣ እንጠይቃለን። በሆነ ባልሆነው ሰበብ መልሶ እንዳይገባም እናሳስባለን። የአገራችንን ህልውና የማስከበር እንጂ ተደራድሮ አሳልፎ የመስጠት ሥልጣን የለውም።ጉዳዩ ምንም እንኳን ያፍሪካ ጉዳይ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ፣ከሱዳንና ከግብጽ ሌላ  ከተጽእኖ ነጻ ያልሆኑ ወይም ሊሆኑ የማይችሉ ያፍሪካ አገሮች  እንዲገቡበት ማድረጉ መፍትሔ አይሆንም።

5 የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን የባዕዳን ሴራ እንደ ጥንት አያት ቅድመ-አያቶቹ በአንድነት ተሰልፎ እንዲቋቋመው ጥሪ እናደርጋለን።ይህ የፖለቲካ ጥያቄ ብቻ  ሳይሆን የህልውናም ጥያቄ ነውና  ለህልውናችን መከበር ስንል ለዚህ ዳግማዊ አድዋ ዘመቻ በህብረት እንቁም እንላለን።ለአገራዊ አንድነት፣ለመብታችንና ለህልውናችን መከበር አብረው የማይሰለፉትን ብሎም ከጠላቶቻችን ጋር የሚሰለፉትን ቡድኖች ለይቶ ማወቅና በአገር ክህደት ተገቢ እርምጃ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ልናወቅ ይገባል።ጊዜው ወዳጅና ጠላትን የምንለይበት ወቅት ነው። 

6 በሥልጣን ላይ ያለው አካል በአባይ ግንባታ ዙሪያ የተፈጸሙ ወንጀሎችን፣ዘረፋዎችን፣ግድያዎችን (የኢንጅነር ስመኘው በቀለን አሙዋሙዋት ጭምር )መሸፋፈኑን ትቶ ለህዝቡ በማያሻማ መልኩ ማቅረብ ይጠበቅበታል።ከግብጽና ግብረአበሮችዋ ሴራ የራቀ አለመሆኑ ሁኔታው ያመላክታል።

7 ሥልጣኑን የያዘው ቡድን ለብድርና ለፖለቲካ ድጋፍ ሲል ከሌሎች አገሮችና የገንዘብ ተቋማት ጋር ከሚያደርገው ውልና ስምምነት እንዲታቀብ እንጠይቃለን።የሚደረጉ ውሎችና ስምምነቶች ሕዝብ የሚያውቃቸውና ሕዝብ በመረጠው  ምክር ቤት  ፈቃድና ውሳኔ እንጂ አንድ መሪ ወይም አንድ ነጠላ የመንግሥት አካል ለዛውም ያልተመረጠ ቡድን  የሚወስነው መሆን የለበትም እንላለን።

በዚህ አጋጣሚ ወደተዘነጋው የሕዝብ ጥያቄ ስንመለስ፣-

8 መንግሥት የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታ አለበት።አሁን በኢትዮጵያ ያለው መንግሥት ነኝ ባይ ቡድን ግን ይህንን በተግባር ሲገልጸው አይታይም።ኢትዮጵያ ሽፍታና አሸባሪ እንደልቡ የሚፈነጭባት አገር ሆናለች።ከዚያም አልፎ ተርፎ ንጹሃን ተማሪዎች ታግተው ያሉበት ሳይታወቅ ውራቶች አልፈዋል። ወላጆች በሃዘን ሰቀቀን እዬተገረፉ ለጥያቄያቸው መልስ ለማግኘት ቀርቶ መጠዬቃቸው እንደ ወንጀል ተቆጥሮ የሚቀጡበት ሁኔታ ሰፍኑዋል።ባለሥልጣናቱ መሸፋፈናቸውን ትተው የታገቱት ወጣቶች (ተማሪዎች)ሁኔታ ትኩረት እንዲሰጠውና መፍትሔ እንዲያገኝ እንጠይቃለን። ሕዝቡም በተለይም የፖለቲካ ፓርቲ ነን ባዮች ቸልታውን ትተው ከሚሰቃዩት ተማሪዎችና ቤተሰቦች ጎን እንዲቆሙና የታገቱት እንዲለቀቁና አጋቾቹም ለፍርድ እንዲቀርቡ፣የሚመለከተውን ክፍል እንዲጠይቁ ጥሪ እናደርጋለን።ለሕዝብ ብሶት ደንታ የሌለው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ ድርጅት እንኳንስ ሥልጣን ላይ ለመቀመጥ ቀርቶ  ምረጡኝ ለማለት የሞራል ብቃት አይኖረውም።በውጭና  በአገር ውስጥ ያሉ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ተቋማት፣የማህበራዊ ስብስቦች፣ምሁራንና የሕግ ባለሙያዎች ተባብረው ይህንን የተዘነጋ ዶሴ አንስተው ለዓለም ማህበረሰብና ለዓለም አቀፍ የሕግ መድረኮች ለማሳወቅ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪ እናደርጋለን።

በዬጊዜው በሚወረወሩ አጀንዳዎች እዬተጠመዱ ፣አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ ከመራኮት፣ከውሃ ቅዳ ከውሃ መልስ ጉዞ  ይልቅ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በአግባቡ የተደቀኑ ችግሮችን እየቀረፉና እያቃለሉ መሄድ ተገቢ ነው።ጠላቶቻችን የሚፈልጉትም ውል ያለው ሥራ ሳንሰራ መባከናችንን ነው።ስህተታችንን ልናርመው ይገባል።   

የታገቱት ይለቀቁ፤አጋቾች ለፍርድ ይቅረቡ!

አንድነታችን ሃይላችን ነው! የባዕዳንን ሴራ ተባብረን እናክሽፍ!!

ኢትዮጵያ ለዘላለም በነጻነት ትኑር!!!

ዓለም አቀፍ የኢትዮጵያውያን የትብብር መድረክ (International Ethiopian Solidarity Forum)

Email    inter.ethiopiansolidarityforum1@gmail.com

  

 

Back to Front Page