Back to Front Page

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ወርልድ ክላስ ማይንድ(አለም አቀፍ አይእምሮ)

ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ወርልድ ክላስ ማይንድ(አለም አቀፍ አይእምሮ)

 

ሙሉጌታ በሪሁን ከሃገረ ካናዳ 08-06-20

 

በዚህች አለም ውስጥ ፣ ስዎች ተወልደን ፣ አድገን ፣ አርጅተን ፣ የማይቀረውን የዚህች ምድር ስንብታችን የተፈጥሮ የስው ልጅ እጣ ፋንታ ነው ። ቁም ነገሩ ተወልደን መሞቱ ሳይሆን ፣ መወለዳችንና ፡ ተወልደን ማለፋችንን የሚያመላክት ማህበረሰባዊ አሻራ ትተን ስናልፍ ፣ የወጣንበት ማህበረሰብ ስማችንን ከመቃብራችን በላይ ለተተኪው ትውልድ ታሪክ ሆኖ ይኖራል።

 

ለምሳል ዊልያም ጀፈርሰን ፣ አብርሃም ሊንከን ፣ ቭላድሚር ኤሊች ሌኒን ፣ ቸርማን ማኦ ቱስቲንግ ፣ ማህተመ ጋንዲ ፣ ኔልሰን ማንዴላ ፣ሳሞራ ማሽል ፣ ማርቲን ሉተር ኪንግ ፣ ማዘር ተሪሳ  ፣ መለስ ዜናዊ ፤ የወጡበትን ማህበረሰብ ከማገልገል ባሻግር ፣ ለአለም ጥሩ ምሳሌና ለህብረተሰባቸው እድገት የቻሉትን ያህል አስተዋፅኦ በማድረጋቸው አለም አቀፍ እውቅናን ተጎናፅፈው አልፋል ።

 

Videos From Around The World

በተፃራሪው የነዚህን ግለሰቦች ማህበራዊ ለውጥ ኂደት የሚቃረን ተግባር በመፈፀም የመጡበትን ማህበረሰብና የአለምን ህዝብ ለሰቆቃና ለሃገራት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ውድቀት የዳረጉ መሪዎችም ይህች አለም አፍርታለች ።

 

ለምሳሌ አዶልፍ ሂትለር ፣ ቪኑቶ መሶለኒ ፣ ጆሴፍ ስታሊን ፣ ኢዲ አሚን ዳዳ ፣ መንግስቱ ሃይለማርያም ወ.ዘ.ተ መጥቀስ ይቻላል ። በዚህች አለም ሰዎች ለስልጣን ፣ ለገንዘብ ሲስገበገቡ ፣ ቀላሏን የሰው ልጅ ሂወት ውጥንቅጧንና ፍዳዋን ያሳይዋታል ።

 

እንደ ሰው ልጆች፣ እራቁታችን ተወልደን ፣ እራቁታችን እንደምንቀበር እንረሳለን ፤ በዚህች አለም ውስጥ ትተነው የምንሄድ እንጂ ፣ ይዘነው የምንሄድ ስልጣንም ሆነ ሃብት የለም ። የሂውት ጉዞ ይህችው ነች ፤የምጥቁ አእምሮ ባለቤት ክቡር ጠ/ሚ መለስ ዜናዊም ፣ ኢትዮዽያና ፡ የኢትዮዽያ ችግር ፣ ከዚህ በፊት ከነበሩት የኢትዮዽያ መሪዎች ፣ ለየት ባለመልኩ ፣ ጠለቅ ባለ ሁናቴ ፣ የሃገሪቱን ችግር ተረድቶ ለሃገሪቱ ይበጃል ያለውን ፖለቲካዊና ፣ ኢኮኖሚያዊ ንድፈ ሃሳብ ቀይሶ ፣ መሬት ላይ በሰራ እየተገበረ የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ ከማስመዝገቡም በላይ ፣ ሃሳቡን በምእራባውያን ተቀባይነት እያገኘ መሄዱን ፣ የአለም መሪዎች ኽእንደነ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ፣ አነ ጠ/ሚ ጎርደን ብራውን ፣ ቻንስለር አንጌላ ማርከል ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉትን መሪዎች የተሰልፈ ብቸኛው የአህጉሪቱ የአፍሪካ ወኪል ነው በመሆን ፣ የኢትዮዽያንና የአፍሪካን ኩራት በመሆን  በአለም መድረኮች ተንፈላሰዋል ።

በኔ የግል አመለካከት ፣ በኢትዮዽያና የኢትዮዽያን ህዝብ ፣ መለስን ያክል የሃገሪቱ ችግር የተረዳ ምሁርም ይሁን ማሃይም የለም ፣ ለወደፊትም አይኖርም፣መለስን ለመረዳት የመለስን ንጝሮች በትክክል ተረድቶ ከሃገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታዎች ፣ ከሃገሪቱ ታሪካዊ እውነታዎችና ፤ ከአለም ተጨባጭ እውነታዎች ጋር ማገናዘብ ያስፈልጋል ።

 

ታጋይ በረኸት ስሞኦን ስለመለስ የምስክርነት ቃሉ ሲሰጥ ፣ ገና ኢትዮዽያን እንደተቆጣጠሩ ሁሉም የትግል ጏዶቹ ከስራ ስአት በኃላ እየተሰባሰቡ ሲጫወቱና ሲዝናኑ መለስ ከቢሮው ሳይወጣ ተደፍቶ መፃህፍት እያገላበጠ ለረጅም ስዓት ሲያሳልፍ ፣ አቶ በረኸት ቢሮው ድረስ ገብቶ ከጏደኞቹ ጋር ለምን እንደማይዝናና ሲጠይቀው መለስ የመለሰለት መልስ ፣ በረኸትን ያስገረመ ነበር ። የሰጠው መልስ ኮት ፨ ፈራሁኝ ፨ ነበር ያለው ፣ ለምን ? ብሎ ሲጠይቀው የኢትዮዽያ ችግር እንደምንጠብቀው ሳይሆን ከምንጠብቀው እጅግ የባሰና የከፋ ነው አለው ። ቀጥሎም የሃገሪቱ ችግር በኔ ትከሻ ላይ ነው ፤ እኔም ሃገሬን መታደግ አለብኝ ፣ ለዚህ ነው ተደፍቼ የማነበው ነበር ያለው ።

 

መለስ ሂወቱ እንደ ሻማ እስኪቀልጥ ሰርቶም ለውጥ አሳይቷል ፤ ከሱ በኃላ የመጡና የሃገሪቱ ህዝቦች ፤ እቅዱና ራእዩን የማስቀጠልም ሆነ ያለማስቀጠል የነሱ ፋንታ ነው ። ጆርጅ ዋሽንግተን ፣ የአሜሪካ ህገ መንግስት አስረቅቆ ፣በማፅደቅ ፡ ከሁለት መቶ አመት  በላይ ፡ እየተሻሻለ ፣ የሚጨመረውን እየጨመሩ ፣ የሚስተካከለውን እያስተካከሉ ፣ እንሆ እስከ ዛሬዋ እለት ፣ የአሜሪካ የሕጎች የበላይ ሕገመንግስት ያስተዳድራቸዋል ። አሜሪካኖችም ዘፋውንዲንግ ፋዘር በማለት ጆርጅ ዋሽንግተንን ህያው ስሙን ያከብሩታል።

 

አሜሪካ በባርያ ንግድ ተዘፍቃ፣ የስሜኑና ፣የደቡቡ ግዛቶቿ ፣ አውዳሚ የእርስ በርስ ጦርነት ፣ አሳዛኝ የወንድማሞች ጦርነት ከተካሄደ በኃላ , በአብርሃም ሊንከን አሸናፊነት የባርያ ንግድ ስርአትን አስወግዶ ፣ ሰሜንና ደቡብን አዋህዶ ፣ የነበረውን የአሜሪካ ህገ መንግስት አሻሽሎ ፣እንሆ ከአንድ መቶ ሰባ ዓመት በላይ አሜሪካ እስከነ ልዩነታቸው አለምን እየመሩ ይገኛሉ ። እኛ ቱልቱላዎቹ ፣ የወሬ ቛቶች ፣የ(3000) የሶስት ሺ ዘመን ስልጣኔ ያለን ህዝቦች ፣ እያልን ባለን እንደመጨመር ፤ የተገነባውን እያፈረስን ፣ በአፈ ታሪክ የምንኖር ጉዶች ነን ።

 

መለስን ለመረዳት የመለስ ንግግሮችን ማድመጥ ብቻ በቂ ነው ። በአንድ ወቅት ካቢኔውን ሰብሰቦ ሰለ ሃገሪቱ የትራንስፎርሜሽን እቅድ ሲያስረዳ ። መጀመርያ የራሳችን ነባራዊ ሁኔታ መረዳት አለብን ፣ ቀንደኛው ጠላታችን ድህነት ነው ፣ ድህነትን ለመዋጋት ደግሞ ፣ድህነታችንን አምነን መቀበል አለብን። ካልሆነ የ፫ሺ (3000) ዘመን ታሪክ አለን ፣ የአክሱም ሃውልት ባለቤት ፣ ላሊበላ የገነባን ፣ ፋሲለደስ ያለን ፣ እያልን ድህነታችንን የምንሸፋፍን ከሆነ ሃቁን እየሸሸን ለውጥ ማምጣት አንችልም ነበር ያለው።

እንደ ሃገር መሪ ፣ ሃላፊነቱን በግልጽነትና ፣ በቅንነት ለካቢንዬውና ለህዝቡ በሚዲያም ጭምር ነበር በማስረዳት ወገንትኝነቱን ያሳየው ። ኢትዮዽያም ከተኛችበት ጥልቅ እንቅልፍ ባነነች ።

 

ትክክል ነበር ፣ ከዛ በኃላ ነበር የኢትዮዽያ ህዝብም መንቀሳቀሥ የጀመረው ። መለስ በርግጥ ድክመቶች አልነበሩትም ማለት ባልችልም ፣ የመለስን ሃሳቡ የተረዱት ሰዎች ግን በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ ብዬ አምናለሁኝ ። በተለይ ሌብነትና ፣ ሙስና መንግስት በያንዳንዱ ቤት ገብቶ መቆጣጠር አይችልም ።

ለምሳሌ በአንድ ወቅት ፖርላማ ቀርቦ ስለ ሙስና ተጠይቆ ሲመልስ ፣ እናውቃለን እስከ አንገታችን በሙስና እንደተጨማለቅን ፣ ግን ሁሉንም ደግሞ ማሰር አይቻልም ነበር ያለው ።መለስ እንዴት ለማኝ እንሆናለን የሚል የቁጭት መንፈስ በህዝቡ ሲያሳድር ፣ መሰንበት ደጉ ልመና እንደ ጀግንነት የሚሰብክልን መሪም ማየት ችለናል ። ይህ ምን ማለት ነው  ? ለሚገባው ህዝብ ሃገር በአንድ ስው ብቻ አይመራም ፣ ሁሉም የየራሱ ሃላፊነት ሲወጣ ሃገር ታድጋለች ። ለምሳሌ በኢትዮዽያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ የነፃነት ጮራ የፈነጠቀው በመለስ ጊዜ ነበር ፤ መለስ መላጣዬን እስካልነካቹህ የፈለጋችሁትን ፃፉ ፣ ነገር ግን ጥቁር ካልን ቀይ ብላቹህ ከፃፋቹህ እናግዳቹሃለን ነበር ያለው ።

ወፈፌዎቹ የኢትዮዽያ ሚዲያዎች ፣ወጥ መርገጥ ሲጀምሩ፣  ለሰሩት ቅጥፈት ሃላፊነት እንደመውሰድ ፣ መንግስትን መወንጀል ጀመሩ።  መለስም ይጠረቅማቸው ጀመር ፣ ይህ ነው ሃቁ ለምሳሌ የ፺፯ቱን (97)ምርጫ እንመልከት ፣ ቅንጅት ፳፫ቱን(23) የአዲስ አበባ ወንበር አሸነፈ ፣ መለስም በትክክል አሸንፋችሃል አዲስ አበባን ተረከቡ አለ፣ አልጠግብ ባይ ሲተፋ ያድራል ሆነና ፣ የለም ድፍን ኢትዮዽያን ነው ያሸነፍነው ፣ በማለት ብርሃኑ ነጋ ሙጥኝ አለ ፣ መለስም ያልተወዳደርከው እንዴት ማሸነፍ ትችላለህ ብሎ ቢጠይቀው መልስ አልነበረውም ፣ በዚህ የተነሳም ብርሃኑ ነጋ አዲስ አበባ ላይ ሁከት ፈጥሮ ስልጣን ሲቛምጥ ፣ መለስ ጋ ቀልድ የለም ተገቢውንና ተመጣጣኝ ብሎ ያመነበትን እርምጃ ወስዶ ቀላዋጩ ብርሃኑ ነጋም ዘብጥያ አወረደው ። ሃገርን ስትመራ ከውሸትና ከፍርሃት ነፃ መሆን አለብህ ። መለስ የሚታወቀውም በዚህ በሳል አመራሩና ለውሳኔው ባለው ቆራጥነት ነው ።

 

ከዚሁ ሳልወጣ መለስ ቅን አስተዋይ ርህሩህና ብልጥ ነው ። ጠቅለል ባለ አገላለፅ አራዳ ያራዳ ልጅ ነው ፣ በዚህ ላይ ለክፉዎች ለተንኮለኞች ከነሱ የባሰ ክፉና ተንኮለኛም ነው ፣ ለምሳሌ ወይዘሮ ብርቱካን ሚደቅሳ የአሁና የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ፣ከነብርሃኑ ነጋ ጋር ዘብጥያ ከወረዱ የቅንጅት አባላት መካከል ነበረች ፣ ታድያ በዘመድ አዝማድ ተለምኖላት አጥፍቻለሁኝ ይቅርታ ብላ ከወጣች በኃላ፣ አውሮፓ ሂዳ እኔ ይቅርታ አልጠየኩም ብላ መቦጥረቅ ፣መለስም የዋዛ አይደለም ፣ ከጉዞዋ አገር ሰላም ብላ ስትመለስ ወህኒ  ወረወራት ።

 

ታድያ መለስ ምክኒያታዊ ነው ወይስ አይደለም ብለን ለመመዘን ፣ ከመለስ ባሻገር የራሳችንን ድርጊትና ፍላጎትን መሰረት በማድረግ, መለስን መረዳት አንችልም ።አንድ እውነተኛ ታሪክ ላጫውታቹህና ማነው ? ማንን ያልተረዳው ? ለሚለው ጥያቄ ትክክለኛ መልስ ይሆናል ብዬ ያመንኩበትን ውሳኔ ፣ በምሳሌ ላስረዳ ።ይህ ታሪክ በአክሱም ከተማ የተከሰተ ክስተት ነው ። ምህረይ ወልደ ዮውሃንስ የሚባሉ አዋቂ የቤተክህነት ምሁር ነበሩ ። ነዋሪነታቹው በዛና ወረዳ ሲሆን በአንድ ወቅት ድርቅ ገብቶ ስደት ይሄዳሉ ፣ መንገድ ላይ ችግር ፣ ርሃብ ፣ መከራ ፣ ሚስታቸው ልጆቻቸው ሲነጥቃቸው ፣ ከ፫ ዓመት ስደት በኃላ ወደ መንደራቸው ይመለሳሉ ።

 

አስቡት እኝህ ሊቅ ፣ የኔ የሚሉትን ሁሉ ተፈጥሮ ነጥቛቸዋል ። ወደ ቄአቸው ሲመለሱ ያቺ ተስፋ

አድርገውባት የተመለሱትን ጎጆአቸው ፈራርሳ ፣ መሬታቸው ደግሞ ጎረቤታቸው ሲያርሰው ይደርሳሉ እሳቸውም ምነው ? ወንድሜ መሬቴን ተመኘህ የኔኮነው ፣ ሲሉት ሂድና ክሰሰኝ አላቸው ፣እሳቸውም ሌላ አማራጭ ስላልነበራቸው ይከሱታል ። ታድያ ከቀነ ቀጠረው በፊት ፣ የወረዳው ዳኛና ተከሳሹ አብረው ሲጠጡ ያገኟቸዋል ፣ ብልሁ ቄስም በቀጠሮአቸው ቀን የአስከሬን መጠቅለያ ሰሊን ይዘው ፍርድ ቤት ቀረቡ    ምነው ? ምህረይ ቢሏቸው ፣ ከእንግዲህ እኔ የመኖሬ ትርጉም ምኑ ላይ ነው ? ግነዙኝ ፣ ቅበሩኝ አሉዋቸው ። ዳኛውም ለተከሳሹ ፈረደለት ። ምህረይም ዛናን ትተው ወደ አክሱምና ሽሬ እየተመላለሱ ቀሪውን የሂወት ዘመናቸው ገፉ ። ህብረተሰቡ እብድ እያለ እውቀታቸው በውን ሳይረዳ ፣ እስከ ህልፈተ ሂወታቸው ኖሩ ። ያበደው ህብረተሰቡ እንጂ ምህረይ አልነበሩም። አንዳንድ ጊዜ ግለሰቦች ከህብረተሰቡ ላቅ ያለ አስተሳሰብ ያላቸው እንደሆነ ፣ እነሱን የመረዳት አቅም ስላሌለን ፣ የነሱን አሰተሳሰብ በማጥላላትና በማንቛሸሽ የምንረካ ጉዶች መሆናችንን ብናውቅ ሃገራችን የት በደረሰች ነበር ። መለስን ውሃ ቀጠነ ብለው የሚተቹት ግለሰቦች ፣ ሃሳብን በሃሳብ የማሸነፍ ብቃትም ፣ ችሎታም የላቸውም ። ለምሳሌ የመለስ ፖለቲካዊ እምነት ልማታዊ መንግስት ከተቃወሙት ከኢትዮዽያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተጣምሮ ኢትዮዽያን ሊቀይር የሚችል የፖለቲካ ፕሮግራም አቅርቦ ማሸነፍ ነው ። እነሱ ግን ከኢትዮዽያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይሄድ የምእራባውያን አይዲዮለጂን ሊያቀርቡ ይፈልጋሉ ።

 

እንደመጥፎ አጋጣሚ ሆኖ ክቡር ጠሚ መለስንም በክፍለ ዘመን አንዴ ብቅ ከሚሉ ውድ የኢትዮዽያ ፍሬዎች አንዱ ነበር ። የኢትዮዽያ ህዝብ ግን ከሚሰራለት ይልቅ የሚዋሽለት ዋሾ ቱሪናፋ ስለሚያምን የመለስን አስተሳሰብ ባይረዳው አይፈረድበትም ፣ ደግነቱ መለስ ሃሳቡን በፅሁፍ ለተተኪው ትውልድ ከትቦለት ስላለፈ ጎልጉሎ ተረድቶ ወደተግባር የመለወጥ ፋንታ የወጣቱ ትውልድ ነው የሚል እምነት አለኝ።

 

እኔ በግሌ አፍቃሬ መለስ ነኝ ፤ መለስ ለኔ ንድፈ ሃሳብ ነው ፣ፖለቲካዊ መስመር ነው ፣ መለስ የልማታዊ ዲሞክራሲ ቀያሽ ነው(የመለሲዝም )ፍልስፍና አባት ነው  ። የሶሻሊዝም ቀያሾች ማርክስና ኤንግልስ ሲሆኑ ፣ ለውጤታማነቱ በውን ተረድቶ ፼፱፻፲፯ቱ (1917)የራሻ አብዮት ሌኒን በብቃት መርቶ አሳክቶታል ። ይሁን እንጂ ትሮትስኪ ደግሞ የጎደለውን ሞልቶ ሊያስቀጥለው ቢሞክር ፣በስው ደም የሰከረው ጆሴፍ ስታሊን ፣ የራሻ የወዛደሮች አብዮትን ፣ ወደ ፋሽስታዊ አስከፊ ስርአት ቀየረው ። አሁን ኢትዮዽያ የገጠማት የፖለቲካ ችግርም ከዚህ የተለየ አይደለይም ። በአሁኑ ስዓት መለስን የሚተቹ ሰዎች የመለስን ያክል የፖለቲካ እውቀት የላቸውም ። የፖለቲካ እውቀት በንባብ የሚገኝ እውቀት አይደለም ፣ እወክለዋለሁኝ የምትለውን ህብረተሰብ መስለህ ኖረህ ፣ ችግሩን መከራውን ደስታውን ከሱ ጋር መሬት ላይ ወርደህ የምትረዳለት ሁነህ ስትገኝ ብቻ ነው። የዛን ማህበረሰብ ችግር የምትረዳው ፣በመኖር ከማንበብ በላይ ነው ። መለስ ስለገበሬው አውርቶ አይጠግብም ፣ ስለሴት እህቶቻችን አውርቶ አይጠግብም ፣ ስለወጣቱ ትውልድ አውርቶ አይጠግብም ፣መለስ ማውራት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ መንገዶች ተንትኖ የማስረዳት ብቃት አለው ።

 

ለዚህም ነው መለስን የሚቃውሙ ፣የሚተቹ ሰዎች ፣ የመለስን ስነ ሃሳብ ሳይሆን ፣የመለስን እርምጃና ፣ ድርጊት ብቻ የሚተቹት ። ለምሳሌ መለስ ልማትና ዲሞክራሲ በፍፁም የማይለያዩ ሂደቶች ናቸው ብሎ ያምናል ይከራከራል ። መለስን የሚቃወሙ ስዎች የሚመኙት የምእራባውያን ዲሞክራሲ ሲሆን ፣ እነሱ በውስጣቸውና በድርጅቶቻቸው የማያውቁትን ዲሞክራሲ ከመንግስት ይጠይቃሉ ። ሌላው ኢትዮዽያ ህዝብ እነሱ ለሚመኙት ዲሞክራሲ ፖለፒካዊ ግንዛቤው ብቁ ነው ወይ ? ይህንንም በቅጡ የሚረዱ አይደሉም ፣ የነሱ ፍላጎት አንድና አንድ ስልጣን ብቻ ነው ።

 

አንድ ምሳሌ ላስቀምጥ እዚህ በምኖርበት ሃገር ካናዳ ፣ኢፍ ዩ ዶንት ቮት, ዩ ዶንት ሰይ ፤ማለትም (ካልመረጥክ ፣ መናገር አትችልም )ማለት ነው። ይባላል መምረጥ መብቴ ነው የመረጥኩትን ሰው ወይም ፖርቲ የመጠየቅ መብት አለኝ ። የመረጥኩት ግለሰብና ፓርቲ በቀጠሮ ቀርቤ ቅሬታዬን የማሰማት መብት አለኝ ። የትኛው የኢትዮዽያ ፖለቲከኛ ነው ለህብረተሰቡ ቢሮው ክፍት የሆነው ?  ሌላው የሕብረተሰቡ የህግ ተገዥነትስ ምን ያህል ነው ? እዚህ አገር መንገድ ላይ ስትነዳ ፣ ፎር ወይ ስቶፕ ፨ ከ፬ቱ አቅጣጫ ፨ ትቆማለህ ፣ ያለምንም ትራፊክ እንደቅደም ተከተላችን እንሄዳለን ህግ ነው ፣ ህግ ከተጣስ   የጣሰው ተሽከርካሪ ታርጋውን ደውለህ ለፖሊስ መስጠት ነው ፣የማሕበረሰቡ የእኔነት መንፈስ ስርአትን የራሴ ነው ብለህ ማክበር ነው ፣የኛ ህዝብ ለህግ ተገዢ ነውን ? ዲሞክራሲ የሚስፋፋውኮ ስለተመኘነው ሳይሆን ከራሳችን ስንጀምረው ነው ። የፈለጋችሁትን ፃፉ መላጣዬን ግን መንካት አትችሉም። ጥቁር ካልኩኝ መለስ ጥቁር አለ ብላቹህ ፃፉ፣ ያላልኩትን ቀይ ብሏል ካላቹህ ግን እጠረቅሟቹሃለሁኝ ። ሕግ ማለት ላልገባው በሚገባው ቛንቛ ማስረዳት ማለት ነው ።

 

መለስም የተቻለውን ያህል ሞኩረዋል  ፣ ግን ችግሩ ያው ማህበራዊ ችግር ሆኖ ፣እሱም እንደግለስብ የማይረሳ አሻራ ትቶልን አልፏል ። ሂወቱ በዕፀደ ገነት ያኑርልን።

መለስ ኩሩ ኢትዮዽያዊ ፣ለሃገሩ ሽንጡን ገትሮ በአለም አደባባይ ተከራክሮ ያሸነፈ ፣ ብርቅዬ የኢትዮዽያ መሪ ነው ።

ለምሳሌ በአለም ፍርድ ቤት ላይ ጣልያንን ገትሮ ፨ ከሶ ፨ የአክሱምን ሃውልትን አስመልሷል ።ጣልያን የትራንስፖርትና ፡ የመገጣጠምያ ወጭዋን ችላ፣ የተሰረቀችው ሃወልታችን በቦታዋ ተተክላለች ።

የውጭ ዲፕሎማሲ ፣ ኢትዮዽያ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ አለማቀፋዊ ግኑኝነት ነበራት ፤መለስ ማንኛውም በጸረ ድህነት ትግላችን አንድ ተጨማሪ ጉልበት ድጋፍ የሚያደርግልን ወዳጃችን ፣ በድህነት ትግላችን ውስጥ አንዲት እርምጃ የሚያደናቅፈን ጠላታችን ነው ፣ በሚል ስትራተጂ ነበር ሃገሪቷን የሚመራት ፣ አመርቂ ውጤትም አግኝቶበታል። መለስ በአለም አስገራሚው የፖለቲካዊ ብቃቱ ማረጋገጫ ካስፈለገ የሁለቱ ሱዳኖችን እንመልከት ለዘመናት በጦርነት የተቧቀሱት ሱዳንና ፣ ደቡብ ሱዳን አስታራቂአችን ፣ኢትዮዽያ መሆን አለባት ብለው ፡ ሁለቱም ሃገራት በፍቅር የመረጧት ሃገር ፣ የመለስ የአመራር ብቃት ማረጋገጫ ነው ።

 

የማይንበረከክ ኢትዮዽያዊ መሪ መለስ ዜናዊ ፣አሜሪካ በሶማልያ ለነበራት ፀረ ሽብር ጦርነት ፡ አሜሪካኖች ግባ ሲሉት ፡ እምቢ የሃገሬ ጥቅም አያስከብርም ፡ ብሎ ሲዘጋቸው የኢትዮዽያን ጥቅም ይጠብቅልኛል ብሎ ያመነ ስአት አትግባ ሲሉት ፡ አልሸባብን ዘልቆ ገብቶ ደምስሶታል ። ዛሬ ጨለምተኞቹ የኢትዮዽያ መሪዎች አሰፍስፈው ለምዕራባውያን እንደገፀ በረከት ሊያቀርቡት በመንተፋተፍ ላይ ያለውን የኢትዮዽያ አየር መንገድ ፣ ቴሌኮም ፣ ባንኮች ፣ መብራህት ሃይልና ፣ ምድር ባቡር በመለስ ዜናዊ ልማታዊ ዲሞክራሲያዊ የፍልስፍና መርህ ፣ አቆጥቁጠው ፣ ዳብረው የሃገሪቱ ህዝብ ፍሬውን ፣ እንደመብላት ፡ በተንኮልና ሴራ ፡ ለምዕራባውያንና ፣ ለዓረቦች ሊሸጡ እየተዘጋጁ ነው ። የሚያሳፍረው ደግሞ የኢትዮዽያ ምሁራንና ፣ ፖለቲከኞች ፡ የፓርላማ አባላት ትንፍሽ አለማለታቸው ፣ ምን ያህ ሃገሪቱ የምሁሯን መካን ፣ የሆድ አደሮች ፣ ማፈርያ ፖለቲከኞች ፣ መፈልፈያ መሆኗን ነው ። ያልታደለች ሃገር ፣ ፨ እምዬ ኢትዮዽያ እምዬ አዶላየ ፨ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ ፨ አሉ ከዛም ባሻገር ያልታደለ ህዝብ መሆኑን ሳስብ አዘንኩኝ።

 

መለስ ብዙ የአለም መሪዎችና ፣ እውቅ ሙሁሯን የሚያደንቁት ብርቅዬ የኢትዮዽያ መሪ ከመሆኑ ባሻገር ። ኢትዮዽያን በቅንነት የሚወዱ ታዋቂ ሙሁራንም ያደንቁታል ፣ ያከብሩታል ፤ ከነዚህ ሙሁራን መካከል ደግሞ እንደነ ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴና ፣ ዶር ኢሌኒ ገብረመድህን የኢትዮዽያ ምርት ገበያ መስራች ይገኙበታል ። ዶር ኢሌኒ መጀመርያ ሃገሯን ለማገልገል ፕሮጀክቷን ይዛ እንደመጣች ለጠ/ምኒስትሩ ፕሮፖዛሏን እንደሰጠችው ለሚቀጥለው ቀን ነበር የቀጠራት ፣ በሚቀጥለው ቀነ ቀጠሯዋ ስትቀርብ ፣ ጠ/ምሩ ፕሮፖዛልዋ እንብቦት ፣ ተረድቶት ፣ መሆን አለበት ብሎ ያቀረበላትን ሃሳብ ፣ ስትሰማ ማመን አቃተኝ ነበር ያለችው ። ያም ብቻ ሳይሆን ወደ አሜሪካ ከሱ ጋር ይዟት በመሄድ እቅዷን መቶ በመቶ በመደገፍ እንሆ በአሁኑ ስአት ከኢትዮዽያ አልፎ አለም አቀፍ የምርት ማገበያያ ማእከል ሆኗል ።

 

መለስ ኢትዮዽያን የሚገልፅበት መንገድ ፣ ኢትዮዽያ እንደ አባይ ወንዝ ነች ይላታል ። ለዚህም ሲያስረዳ አባይ ፡ አባይ የሚለውን ስም ይዞ የኢትዮዽያ ድምበር ከመሻገሩ በፊት ፣ በጣም በርካታ ወንዞችና ፡ ጅረቶች ወደ ውስጡ ይቀላቀላሉ ። ድምበር ተሻግሮ ሲሄድ አባይ ወንዝ ይባላል።

ኢትዮዽያም ፣ ኢትዮዽያ የሚያስብላት ፡ የብዙ ብሄር ብሄረሰቦች የድምር ውጤት ስለሆነች ነው ይላል ። ለምሳሌ ትግሯዋዩ የሃረሬው ታሪክ ባህል የኔ ነው ካላለ ፣ አማራው የጋምቤላው ባህልና ታሪክ የኔ ነው ካላለ ፣ ኦሮሞው የሶማሌው ባህልና ታሪክ የኔ ነው ካላለ ፣ ወላይታው የቅማንቱ ባህል የኔነው ካላለ ጉራጌው የአገው ታሪክና ባህል የኔ ነው ካላለ ፣ እያንዳንዱ ብሄር ብሄረሰብ የየራሱ ተውፊት ይዞ በመቅረብ ውብ ኢትዮዽያን ይፈጥራል ። ከዚህ ውጭ አንዱ ብሄር ሌላውን ረግጦ ፣ ኢትዮዽያ ሃገሬ የሚባል ትርክት አይኖርም ።ያቺ ጨፍላቂዋ አሃዳዊት ኢትዮዽያ ላትመለስ ተቀብራለች ይል ነበር ። ይህ ደግሞ ፣ የኢትዮዽያ ነባሯዊ ሁኔታ መሰረት ያደረገ ፣ ተጨባጭ የሃገሪቱ ምንነትን ይገልፃል ። እኔም እንደ ግለሰብ የመለስን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ አምንበታለሁኝ ።

 

ለማንኛውም ሃሳቤን ከማጠቃለሌ በፊት መለስ ለኢትዮዽያ ህዝብ ትልቅ ባለውለታ ሰርቶ ያሳየ ጀግና መሪው እንደነበረ። የመሞቱ ዜና እንደተሰማም የኢትዮዽያ ህዝብ ሃዘኑን በአኹሪ ሁናቴ በክብርና በፍቅር ገልጿል ። የኢትዮዽያ ህዝቦች ብሄር ብሄረሰቦች ዛሬም ቢሆን ቃላችሁን ስጡ ቢባሉ ፸፭ (75)ፐርሰንቱ ድሃው ህዝብ መለስን የሚወድና የሚናፍቅ ህዝብ ነው ። ይህች በሚዲያ በሬ ወለደ የውሸት ኢትዮዽያ ሃገሬ ለ፮(6)ወር ሰርታለች ። ውሃና ውሸት እያደር ይጠራል አይደል ፣ አሁን እውነታውና ሃቁ ለይቷል ህዝቡም አፍቃሬ መለስ መሆኑ ለዓለም ህዝብ አሳይተዋል ። መለስ መሞቱ ከተሰማችበት ደቂቃ አንስቶ ፣ ኢትዮዽያዊ የሆነ ሁሉ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ፣ ከምሁር እስከ በረንዳ አዳሪ ፣ ከወጣት እስከ አዛውንት ፣ ከቶኒ ብሌር እስከ ሱዛን ራይስ ፣ ከታገል ሰይፉ እሰከ ንዋይ ደበበ ፣ ሲያለቅስለት የተገረሙት የትምክህተኞች ፣ የኢሳት ሚድያና የትምክህተኞቹ ዳያስፖራ ፣ ይህማ አይሆንም ፡ ህዝቡ ተከፍሎት ነው የወጣው ነበር ያሉት ። ለዚህም ነበር ታገል ሰይፉ ፣ የመልስ ምት በሚመስል በመረዋው ድምፁ ፣ አዎ ተከፍሎን ወጣን ፣ ተከፍሎን አለቀስን ፣ የሚለውን ግጥሙ የለቀቀው  ፣ አዎ በአባይ ክፍያ ፣ አዎ በልማት ክፍያ ፣ አዎ በመንገድ ክፍያ ፣ አዎን በሆስፒታሎች ክፍያ ፣ አዎን በባቡር ክፍያ ፣ አዎን በግቤ ፩ በጊቤ ፪ በጊቤ ፫ ክፍያ ፣ አዎን በእድገት ክፍያ ተከፍሎን አነባን ነበር ያለው ። መለስ ህያው ነው ።መለስ ቢለየንም የመለስ ቱርፋቶች ለዘልዓለም ይኖራሉ የህዳሴ ግድቡ ከስጦታዎች ሁሉ የከበረው የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ትልቁ ለኢትዮዽያ ህዝብ የተስጠ የታሪክ የአሻራ ስጦታ ነው ። የኢትዮዽያ የህዳሴ ግድብ በጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መሪነት ፣ በኢንጅነር ስመኘው በቀለ ማሃንዲስነት የተሰጠ የአሻራ ስጦታ ነው ።ህይወታቸውን በዐጸደ ገነት ያኑርልን አሜን።

 

ሃሳቤን ለማጠቃለል ፣ አገራችን ኢትዮዽያ አሁን የገባችበትን ውጥንቅጡ የወጣው ፣ የፖለቲካ ጉዞ ፣ አቧሯው መስከን ሲጀምር ፣ ወደ ጀመረችው የልማታዊው ዲሞክራሲ ርእዮተአለም ትመልሳለች የሚል ፅኑ እምነት አለኝ ። አብይ አህመድና የነፍጠኞች ሃይል ፣ ሚዲያ ላይ ከእምባከረዩ የዘለለ መሰረት የላቸውም ፣ እንደ እኔ እምነት ብሄር ብሄረሰቦች ፣ የህልውናቸው ዋስትና በሚወስኑት ውሳኔ እንጂ ፣ ከላይ ሌሎች በሚወስኑላቸው ውሳኔ ከቶውኑ ይተዳደራሉ ብዬ አላምንም ። ይህ ውጤት የሚገኘው ግን ሁሉም ብሄር ብሄረሰብ ለመብቱ ፀንቶ አስፈላጊውን የትግል መስዋእትነት በመክፈል ነው ። እንደ ከዚህ በፊቱ  ለብሄር ብሄረሰቦች ሲባል ፣ ያልተገባ መስዋእትነት ሌሎች ህዝቦች የሚከፍሉት መስዋእትነት አይኖርም ። ሁሉም እራሱን ነፃ ማውጣት አለበት ። ካለፈው ስህተት መማር የሰው ልጅ ተፈጥሮዋዊ  ፀጋ ነው በመጨረሻም ክቡር ጠ/ሚ መለስ ከተለየን ፰ኛው የሙት አመቱ እየተቃረበ ነው ።እርግጥ ነው መለስ በአካል ቢለየንም ፣ ትቶልን የሄደው ርእዮተ አለም(መለሲዝም) ፣ለኢትዮዽያ ፍቱን በተግባር የታየ የእድገታችን መስመር ነው ። ከኛ ባሻገርም ድፍን የአፍሪካ የእድገትና የለውጥ መስመር ስለሆነ ወጣቱ ትውልድ የሚጨመር እየጨመረ ፣ የሚታረም እያረመ ፣ እንደየ ወቅቱ ና እንደየ አሰፈላጊነቱ  እየተጠቀመ ሃገሪቷን ወደተሻለ እድገት ትደርሳለች የሚል እምነት አለኝ ። በዚህ አጋጣሚ ለክቡር ጠ/ሚ መለስ ቤተሰቦች ፍቅርን ፣ ሰላምንና ፣ ክብርንና ፣ ኩራትን እመኛለሁኝ።

 

አስተያየት ሃሳብ ካለ በደስታ እቀበላለሁኝ አመሰግናለሁኝ።

mba1277@gmail.com

 


Back to Front Page