Back to Front Page

ለፓለቲካ ስልጣኗ አለንልህ ያሉት በአንበጣው ወረራ ድምፃቸው ጠፋ!ለፓለቲካ ስልጣኗ አለንልህ ያሉት በአንበጣው ወረራ ድምፃቸው ጠፋ!

ለፓለቲካ ስልጣኗ አለንልህ ያሉት በአንበጣው ወረራ ድምፃቸው ጠፋ!

ዮሃንስ አበራ (ዶር)

10-16-20

 

ፈረንጆች እንዲህ አይነት ነገር ሲገጥማቸው የሚተርቱት እንዲህ በማለት ነው:- "የጭንቅ ቀን ጓደኛ እውነተኛ ጓደኛ"። ከቦምብና ጥይት በላይ የትግራይን ህዝብ የሚጎዳው ድርቅና አንበጣ ነው። ጦርነት ላይ ሰው ይሞታል ቤት ይቃጠላል ይፈርሳል፣ ይህ ሲያበቃ በነበረው ወይንም በሌላ መልኩ ኑሮ ይቀጥላል። በሚከፈለው መስዋእትነት ከጦርነት በፊት ከነበረው ህይወት የተሻለ ሆኖ ሊገኝም ይችላል። የትግራይ ህዝብ የ17 አመት ትግል ያስመሰከረውም ይህንኑን ሃቅ ነው። እንደ ድርቅና የአንበጣ ወረራ ያሉት የተፈጥሮ አደጋዎች ግን በግብርና ላይ የተመሰረተ ኑሮ ያለውን ህዝብ ከስሩ ነቅለው እንደሚያጠፉት የታወቀ ነገር ነው። የ1977 ድርቅ የህወሓትን ህዝባዊነት ያረጋገጠና ከትግሉና መስዋእትነቱ በላይ ህዝቡንና ድርጅቱን ያጣመረ ነበረ፣ እርዳታ ለፓርቲ ምስረታ ዋለ የሚለውን አጉል ክርክር ወደጎን ጥለን። ለትግራይ ህዝብ ልጆችና ወዳጆች ሁለተኛው ታላቅ ፈተና የአሁኑ የአንበጣ ወረራ ነው። እናቶቻችን አፈር ለብሰው፣ አፈር እያፈሱ አምላክን ሲማፀኑ የሚያሳይ የሚዘገንን ትእይንት እየታየ የህዝብ ጠላትም ቢሆን ቀን ፓለቲካን ሲያማስል ውሎ ማታ ተኝቶ ሊያድር አይችልም።

Videos From Around The World

የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም ህዝብ የተሻለ አማራጭ አመራር እንደሚፈልግ የታወቀ ነው። ከህወሓት የተሻለ ካለ ምንም እንኳን ህዝቡ ከህወሓት ጋር ከሚያራርቀው የሚያቀራርበው ነገር የላቀ ቢሆንም የተሻለ ካገኘ እድሉን ለመጠቀም አይኑን አያሽም፣ የኢኮኖሚ እንጂ የአእምሮ ድህነት የለበትምና። እዚህ ላይ መጠየቅ ያለበት ጥያቄ የትግራይ ህዝብ የተሻለ አመራር የሚለው ምን የሚያደርገውን ነው? የሚል ነው። የትግራይ ህዝብ እንደማንኛውም የአለም ህዝብ: ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር የሚያጎናፅፈውን፣ ከጥቃት የሚከላከልለትን፣ በመከራውና በጭንቀቱ ጊዜ ከጎኑ የማይለየውን፣ ከድህነት አላቆ የኑሮ እድገት የሚያቀዳጀውን ነው። ይህን ሁሉ ማከናወን የሚከብድ ሲሆን ጨርሶ በሰበብ የማይዘለል ነገር ግን አለ፣ ይህም የህዝቡ ህልውና ነው። ማንም ለትግራይ ህዝብ ቆሚያለሁ የሚል ግለሰብ ሆነ ቡድን ሊዘለው ከቶ የማይቻለው ቀይ መስመር ይህ ነው። ለዲሞክራሲ፣ ለመልካም አስተዳደር፣ ለኢኮኖሚ እድገት መጀመሪያ በህይወት ሆኖ መተንፈስ መቻል ያስፈልጋል።

በ1977 ድርቅ ጊዜ መለስ ዜናዊ እንደሌሎች "የነፃነት ትግል መሪዎች" ለንደን ሆቴል አዳራሽ ውስጥ ክራባት ለብሶ አይደለም ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጠው። መናኛ ፋቲክ ለብሶ፣ አለት ስር ተወሽቆ፣ ፀጉሩ ተንጨፍርሮ እንባ እየተናነቀው ነበር "ህዝቤ እያለቀ ለማን ነው የምዋጋው?"ብሎ ጋዜጠኛውን የጠየቀው። እኩል ከትግራይ ህዝብ የተወለዱት ግን "የእርዳታውን ብር መሳሪያ ገዛበት" እያሉ ሲያወግዙት ነበር። ይህ ህዝብን በረሃብ የመጨረስ ግፍ ሊወገድ የሚችለው በትግል ብቻ ነበረና ለህዝብ እህል መስፈርና ለትግል መሳሪያ መግዛት የአንድ ሳንቲ ሁለት ገፅታዎች ነበሩ።  የትግራይ ተወላጆች ሆነው፣ ከህወሓት ይልቅ ለትግራይ ህዝብ የቆምነው እኛ ነን እያሉ በውስጥም በውጪም ሆነው ሲለፍፉ የነበሩት ህዝብን በማዳን ስራ ላይ ከነበረችው ህወሓት እንከን በመፈለግ ላይ ተጠምደው ነበር። "በሌላው አይን ውስጥ ያለችውን ቅንጣት ከማጋነን መጀመሪያ በራስህ አይን ውስጥ ያለውን ምሶሶ ቆርጠህ አውጣ" እንደተባለው ቅዱስ ቃል ህወሓት አይን ውስጥ ጉድፍ መኖሩ እንኳንና የውጭ ተመልካች ህወሓትም ራሷ አምና የተቀበለችው ድክመት ነው።

መደጋገሙ ፋይዳ የለውም እንጂ ህወሓት እኮ የትግራይን ህዝብ ክፉኛ በድላዋለች። ህዝቡ እኮ "በገዛ ዳቦየ ልብ ልቡን አጣሁት ሆኖበት እኮ ነው ለሶስት አስርት አመታት የታገለለትን ዲሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ልማት ርቦት ጠምቶት ያሳለፈው። መርተው ያታገሉትና የህይወትና የአካል ዋጋ ያስከፈሉት ልጆቹማ ሸገር ላይ ማክሮ ኢኮኖሚው ተመችቷቸው ወደ ሰሜን አቅጣጫ ድንጋይ ወርውረው ፊታቸውን አዙረው ተኙ። የአቢይ አላርም ጊዜውን ጠብቆ በድንጋጤ ባይቀሰቅሳቸው ወደ ዋናው መደበኛ ስራቸው አይሰማሩም ነበር። የትግራይ ህዝብ ይቅር ብሎ የተቀበላቸውም ሁለተኛ  ምርጥ ምርጡን ወደ ትግራይ እንጂ ወደ አራት ኪሎ እንደማይልኩ በመተማመን ነው። ህዝቡኮ አራት ኪሎ ተቀምጦ ላስተዳድርህ የሚባል ቋንቋ መሮት ነው 17 አመት የፈጋው! የአሁኖቹ "አማራጭ" ፓርቲዎችም የሚመኙት በስልክና በኢንተርኔት በሪሞት ማስተዳደር ነው። ራስ ስዩም መንገሻ ትግራይን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ፈረንሳይ ለጋሲዮን ኬላ ላይ ከሚገኘው ቋሚ መኖሪያ ቪላቸው ሆነው ነበር፣ ጉዞው በእግርና በበቅሎ፣ ስልኩ በሌለበት ዘመን ነበር ይህ ሲሆን የነበረው። ደጃት ገብረስላሴም አድዋን ለወፍ ሰጥተው ሽገር ተቀምጠው ኖሩ። አስተዳዳሪ ከጎኑ ያልነበረው የትግራይ ህዝብ ሲቸገር የሚያስታውሰው የለም፣ መሮት ሲያምፅ ግን በፍጥነት ጦር ይላክበት ነበር።

እኔ ህወሓትን፣ ትዴፓን፣ ዓረናን፣ ባይቶናን፣ ሳልሳይን አበላልጬ ማየት እንደሌለብኝ አውቃለሁ። ሚዛን ላይ ማስቀመጥ ግን የግድ ይላል። ሚዛኑ የኔ የግል ፍቅር ወይንም ጥላቻ ሳይሆን የትግራይ ህዝብ መሰረታዊ ጥቅም ነው። እዚህ ላይ "መወለድ ቋንቋ" መሆኑ ግልፅ መሆን አለበት። የትግራይ ህዝብ ለመሰረታዊ ጥቅሙ ያልቆመ ወይንም ይህን መሰረታዊ ጥቅም ተፃሮ የተነሳውን ተወላጅ አቅፎ ጡት ወይንም ጡጦ የማጥባት ግዴታ የለበትም። ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ወዳጅነት የለም የሚባለውን እዚህ ላይ "ቋሚ የህዝብ ጥቅም እንጂ ቋሚ ተወላጅነት የለም" በሚል መተካት ያስፈልጋል። "ህወሓትና ህዝብ አንድ አይደሉም፣ ህወሓት የትግራይን ህዝብ በድላለችና መወገድ አለባት፣ ወዘተ" የሚለው መስመር የለቀቀ አነጋገር የሚናገሩት ለትግራይ ህዝብ ቅንጣት ታክል ቁምነገር ሰርተው ያላሳዩት ናቸው። ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ስራ ለመስራት የግድ መቀሌ ላይ ስልጣን መያዝ አያስፈልግም። መቀሌ ሳይሆን የትግራይ "ዋና ከተማቸው" ከሆነችው አዲስ አበባ ውስጥ የተቀመጡት ተቃዋሚ ድርጅቶችና ግለሰቦች "ህወሓትን መሳደብ ብቻውን ትግራይን እያሳድግም፣ የልማትና ዴሞክራሲ ግባችሁን ግልፅ አድርጉ" ሲባሉ እንደ ቅድመሁኔታ የሚያቀርቡት የህወሓትን ከስልጣን መውረድ ሳይሆን ጨርሶ መጥፋትን ነው። አመራሮቹ አዲስ አበባ ተቀምጠው "አለንልህ፣ ከህወሓት እኛ እንሻልሃለን፣ ህወሓትን ብቻ ገርስስልን" ይሉታል። "ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት" ነውና ህዝቡ ከፋችም በጀችም ከጎኑ የቆመችውን ህወሓትን ማንም እንዲነካበት አይፈልግም። የትግራይን ህዝብ የማያውቀው ሌላው ህዝብ ቢናገር አይገርምም፣ "ህወሓት የትግራይን ህዝብ በግዴታ አፍና ነው የያዠችው፣ በየቤቱ ሰላይ አለ፣ ህወሓትን ለማጥፋት ህዝቡ ድጋፍ ይፈልጋል፣ ወዘተ" እያሉ የሚወተውቱት ከትግራይ ህዝብ አብራክ የተፈጠሩና የህዝቡን እምቢ ባይነት አሳምረው የሚያውቁት ናቸው። የትግራይ ህዝብ ለዘመናት የትኩረት ማእከል የሆነው ጭቆናን አሜን ብሎ የማይቀበል ህዝብ መሆኑ ስለሚታወቅ ነው። የጂኦፓለቲክስ አባት የሆነው ሰር ሃሊፎርድ ማኪንደር "መካከለኛውን እስያ የተቆጣጠረ፣አለምን ተቆጣጠረ" የሚል ቲዮሪ ነበረው። ይህን ተከትሎ ነበር ሂትለር ወደ ሶቭየት ህብረት የዘመተው። ይህን ያከሸፈው ብዙም ተወዳጅ ያልነበረው ጆሴፍ ስታሊን ነበር። የሶቭየት ህዝብ ስታሊንን ተክትሎ ነፃነቱን አስከበረ እንጂ "ስታሊን አይበጅህም፣ ጨካኝ ነው፣ አስወግደው" የሚለውን የምእራቡ ጩኸት አላዳመጠም። ይህን እያሉ ሲወተውቱ የነበሩት የውጭ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ በስደት በምእራቡ አለም ሲኖሩ የነበሩት የሶቭየት ተውላጆች ናቸው። ያልገባቸው ነገር በቀውጢው የህልውና አደጋ ጊዜ ከህዝቡ ጎን የነበረው ግን እነሱ ሳይሆኑ ስታሊን ነበር። አስከፊ ችግሮች ነበሩበት፣ ለሶቭየት ህዝብ በቅርብ የደረሰለት ግን እሱ ነበር። ፍፁም የሆነው አምላክ ብቻ ነው። አልፎ አልፎ የጠቆረውን ሙዝ መጣል ሳይሆን ነጭ ነጩን እየመረጡ መብላት ነው የሚመከረው።

የአለም ጦርነት ግዙፍ ነው የትግራይ የእንበጣ ወረራ በተነፃፃሪ ኢሚንት ነው፣ በመርህ ደረጃ ግን እኩል ናቸው። አምበጣ የትግራይን ህዝብ ህልውና በሚፈታተን ደረጃ በመከሰቱ ህዝቡ ተደናግጦ ትርምስምሱ ሲወጣ ሚድያው የኢትዮጵያዊነት ስሜት በሌለው ከፍተኛ ጭካኔ የሚያወራውና የሚከራከረው ህወሓትን እንዴት አዳክሞ ማንበርከክ እንደሚቻል ነው። የትግራይ ተውላጅ የሆኑ ተቃዋሚዎችን ባካተተ ሁኔታ እንደርታና ራያ ላይ በየማሳው በጃኬትና በፌሽካ ከአንበጣ ጋር የምትሯሯጠውን ህወሓትን የትግራይ ህዝብ ጠላት ናት የሚባልበት ምስጢረ ፓለቲካ ምንድነው? ህወሓትን ሲኮንኑ፣ ለትግራይ ህዝብ አለኝታ እንደሆኑ በየሚድያው ሲሰብኩና ሱያሰብኩ ከነበሩት የሚጠበቅ ትልቅ ነገር ነበረ። ዝምታ ሳይሆን! በሚያስገርምና በሚያሳዝን  ሁኔታ አብዛኛዎቹ ከህወሓት እኛ እንበልጣለን የሚሉት ተቃዋሚዎች አሁን አንበጣ ከወረረው አካባቢ የተወለዱ ናቸው። የሚራበው የነሱ ዘመድ አዝማድም ጭምር ነው። አንበጣን ከእንደርታና ከራያ ለማባረር ያላቸውን ነገር ይዘው የመጡት ከሁመራና ከኤሪትርያ ሳይቀር ነው። ከነሱ ይጠበቅ የነበረው በህወሓት ላይ ያነሱትን የፓለቲካ ብትራቸውን ቁጭ አድርገው እዛ ሄደው አንበጣ ማባረር እንኳ የማይቻላቸው ቢሆን እርዳታ ማስተባበር፣ በሚድያ ያለውን ውዥምብር ማጥራት፣ አንበጣንና ፓለቲካን የሚቀላቅሉትን ማረምና አስተሳሰባቸውን ለመቀየር መሞክር ነው። የክልሉ ፕሬዚደንት ከገበሬው መሃል ተገኝተው ሲያበረታቱ፣ የመቀሌ የኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፈትየን አባይ እንደእብድ ከአምበጣ ጋር ስትሯሯጥ፣ የትግራይ ምሁራን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ፣ ነፍስ አድን መዋጮው ሲጎርፍ፣ ይህ ሁሉ ማለፉ አይቀርምና የትግራይን ህዝብ ምረጠን ብላችሁ ትጠይቁት ይሆን? ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት ቃለመጠይቅ ላይ የተናገረው ነገር ሆድ የሚያስብስ ነው። እንዲህ አለ:- "አውሮፕላኑ ቆቦ ላይ ከረጨ በኋላ ኩታ ገጠም ወደሆነው ትግራይ ራያ ሳይዘልቅ ተመልሶ ሄደ፣ በህይወቴ እንዲህ ያለ የሚያሳዝን ነገር አጋጥሞኝ አያውቅም"። ጋዜጠኛው ለቃለ መጠይቅ ስለጠራው እንጂ አንበጣ ለማባረር ወደ ገጠር እንደሚሄድ ሲናገር አንድ ላይ ፈገግታም ሃዘንም መጣብኝ። ኢትዮጵያ የምታክል አገር እያለች የአንዱ ክልል ህዝቧን የወረረ አንበጣ በፕሮፌሰር ጃኬት መባረር ነበረበት? አንድ የክልሉ ባለስልጣን በቴሌቪዥን ቀርበው በተናገሩት ልደምድም። ጋዜጠኛው ባለስልጣኑን "ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል የአንበጣውን አደጋ ለመከላከል ትብብር መነፈጉ አያናድደዎትም?" ሲለው ባለስልጣኑ እንዲህ አለ- "እኔ አልናደድም፣ ምክንያቱም ሰው የሚናደደው ተስፋ በሚያደርግነት ነገር ነው፣ ተስፋ የቆረጥክበት ነገር አያናድድም!"። ይህ መፃህፍት የሚወጡት አባባል ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ መጠንቀቅ ያለበት የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያ ተስፋ እንዳይቆርጥ ነው።


Back to Front Page