Back to Front Page

ጆሮ ያለው...

ጆሮ ያለው...

በሚካኤል ምናሴ 03-25-20

michillili@gmail.com

 

 

የአገሬ ሰው ብዙውን ግዜ ነገር የሚገባው በተረት፣ በምሳሌ ነው ከሚል ሂሳብ ይቺን የዒራቃውያን የቆየች ተረት መነሻ በማድረግ፣ አንድ ጉዳይ ላካፍላችሁ ወደድኩኝ። ከዓረብ ቋንቋ ወደ እንግሊዘኛ ተተረጉማ አግኝቻት፣ ወደ አማርኛ መለስኳት።

በድሮዋ የባግዳድ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ መንደር፣ አንዲት አረጋዊት ሴት በአንድ ደሳሳ ጎጆ ይኖሩ ነበር። ብቸኛ ጥሪታቸው የሆነች አንዲት ፍየል ነበረቻቸው። 

አንድ ቀን ታድያ፣ ሀይለኛ ዝናብ መዝነብ ጀመረ። የቤቱ የሳር ክዳንም ያፈስ ገባ። እኝህ ብልህ ሴት፣ ለክፉ ቀን መሸሸጊያ ጉድጓድ አዘጋጅተው ነበርና፣ የዝናቡ ወጀብ እስኪያልፍ፣ እዛ ውስጥ ተጠልለው እንዲቆዩ ፍየልዋን ጠየቅዋት። ፍየልዋ ግን፣ ጉድጓዱ ውስጥ አልገባም ብላ አሻፈረኝ አለች።

ፈርታ እሺ ብትል በማለት፣ ሴትዮዋ ፍየልዋን እንዲህ አሉዋት፦ "እማትታዘዢ ከሆነ፣ አራጁን እጠራውና አራርዶ ይበልትሻል" ይሏታል። አሁንም ፍየልዋ ማስፈራርያውን ከቁብ አልቆጠረችውም። 

Videos From Around The World

ሴትዮዋ ወደ አራጁ ሄዳ፣ የፍየልዋን ዳተኛነት በመንገር፣ ሂዶ እንዲያርዳት ይጠይቁታል። ከመቅፅበት ተፈላጊነት በማግኘቱ፣ ኩራት ቢጤ የተሳፈረችበት አራጅ "የራስሽ ጉዳይ" ብሎ ሲጀነንባቸው፣ ሴትዮዋም "በል ቆይ፤ ታያለህ፤ አንጥረኛው ጋ ሄጄ፣ ቢላዎችህ እንዲያዶለድማቸው እነግረዋለሁ።" አሉት። ጆሮ አልሰጣቸውም።

አንጥረኛውም ጋ ሄደው አልቀናቸውም። እሱንም፣ "እማትረዳኝ ከሆነ፣ ወደ ጅረቱ እሄድና እሳትህ ላይ ውሃ ቸልሶ እንዲያጠፋው አደርጋለሁ" ብለው ዛቱበትና ወደዚያው ሄዱ።

የራሱን ሙዚቃ እያዳመጠ፣ ተረጋግቶ ይፈስ የነበረው ጅረትም፣ መልሱ "ዞር በይልኝ፣ ዝም ብዬ ልፍሰስበት" ሆነ። የሱንም ትእቢት እንዴት እንደሚያስተነፍሱት ትንሽ አሰብ አረጉና፣ "የበረሀው መርከብ አለልኝ አደል - ባንዴ ፉት ብሎ ይጨርስህና ደርቀህ ትቀራለህ" ብለውት እየተጣደፉ ሄዱ።

በትላልቅ ቅልጥሞቹ በረሀውን በኩራት ሲያስስ የነበረው አያ ግመል፣ እንደ ዘበት ከሰማቸው በኋላ "ሴትዮ፣ ልኑርበት፣ ከፊቴ ጥፊ" ብሏቸው ጉዞውን ቀጠለ። ንቀት በተመላበት የግመሉ ንግግር የበገኑት አረጋዊት፣ ልኩን ማስገባት እንደማያቅታቸው በማወቅ፣ ግመሉን አንቆ እንዲገድልላቸው ገመድን እንደሚያሰማሩበት ፎክረው ተነሱ። 

ገመድ ሆዬ፣ አንድ ቦታ ተጎልቶ የለመዳትን ማጣጣም ላይ ነበርና፣ የሴትዮዋ ተማፅኖ ምንም አልመሰለውም። አይጥ ጋ ሄደው ገመዱን እንድትቀረጣጥፍላቸው እንደሚያዟት፣ በደም ፍላት ቢነግሩትም በጀ አላለም።

አይጥ ያግበሰበሰችውን ጥሬ እየቆረጠመች፣ በሙሉ ቀልብ ስታዳምጣቸው ብትቆይም፣ የሹፈት ሳቅ ስቃ "ስራሽ ያውጣሽ" አለቻቸው። 

"የድመትን ስም ከጠራሁ ቀልቧን እገፈዋለሁ" ብለው ያመኑት ሴትዮ፣ በውሮ እንደሚያሳድዷት ቢናገሩም፣ "ጌት ኤ ላይፍ" በማለት አሳሳቢውን አጋጣሚ፣ ጭራሽ የእንግሊዘኛ ችሎታዋን ለማሳየት ተጠቀመችበት። 

ሴትዮዋ፣ ድመትን አግኝታ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ያጋጠማትን እንግልትና የሁሉም እምቢተኝነት ሲነግሯት ውሮ ሳታቅማማ "አይጥ እኔን ነው የደፈረችው። ለመሆኑ አሁን የት ናት? ወደ'ሷ ከመሩኝ የማረገው እኔ ነኝ እማቀው" ብላ ለተግባር ተነሳች። 

ድመቲቷ በደረቷ እየተሳበች ስትመጣባት ከሩቅ የተመለከተች አይጥ፣ ዘላ ዱብ ሳትልባት በፊት፣ "አረ! ይህ ሁሉ አያስፈልግም ነበር'ኮ። ገመዱን ዛሬ ጧት በሞረድኳቸው ጥርሶቼ ዘነጣጥዬ ለመጣል እየሄድኩኝ ነው" አለች። 

ወሬው አስቀድሞ የደረሰው ገመድ "አረ፣ አሁንኑ ሄጄ ግመሉን ሲጥ አረገዋለሁ። ለማነቅ ደሞ፣ ከኛ ወዲያ ላሳር..." ምናምን ብሎ ተምዘገዘገ። 

ገመድ እንኳን ሊያጠናቅቀው ዝቶበት፣ በሱ እየተጎተተ፣ በመቶዎች ኪሎሜትሮች በረሀ ለበረሀ መኳተን ምን ማለት እንደሆነ የሚያቀው አያ ግመል፣ "የጅረቱን ነገር ለኔ ተውት፤ እንደውም ጠምቶኝ ነበር፤ ምጥጥ አርጌ አሰናብተዋለሁ" ብሎ ድሉን ቀድሞ ለማብሰር አናፋ።

ከዛማ፣ ዙሩ እየከረረ እንደሄደ፣ ለሁሉም ግልፅ ሆነ። "የታል አንጠረኛው? መከራውን አይቶ ያንቦገቦገውን እሳት ባንዴ እንዳልነበር አረገዋለሁ" የጅረቱ ፉከራ ሆነ። 

"ጥጋበኛው አራጅ ጋ ውሰዱኝ ቢላዎቹን እስከ ወድያኛው እንዳይሰሩ፣ መናኛ ክር እንኳን እንዳይቆርጡ አደርጋቸዋለሁ" ቡካት በቡካት የሆነው አንጠረኛ ማቅራራት ነበር።

"ጣጠኛዋ ፍየል ከወዴት አለች? በዚህ ብዙ የደም ጅረቶች በፈጠረው ስለታም ቢላ፣ ሸርከት ሳላረጋት ዛሬ እንቅልፍ ባይኔ ዝር እንዲል አልፈቅድም" የደነበረው አራጅ ወፍራም ድምፅ አስተጋባ።

በመጨረሻም፣ ፍየልዋ ቀድሞውንም ማለት የነበረባት ነገር ተነፈሰች፦ "አረ እኔ ምን ገዶኝ?" ብላ ወደ ጉድጓዱ ሰተት ብላ ገባች። 

መልእክቴ

"የኮሮና ስጋት እስከሚረግብ፣ ከየቤታችሁ አትውጡ፣ እጆቻችሁን ታጠቡ፣ ርቀታችሁን ጠብቁ"፣ ወዘተ እያሉ የጤና ባለሙያዎች፣ የአገር መሪዎች፣ የሀይማኖት አባቶች፣ የመገናኛ ብዙሀን ሲያስጠነቅቁን ያልሰማን፣ እንደ ፍየሊቱ ቅብጠት ያሳበደን፣ ግዚያዊ ገበያና ትርፍ አሳውሮን፣ በአራጁ ጥንውት የተያዝን፣ እንደ አንጠረኛው በዕለታዊ ነገር ተጠምደን መጪውን ማየት የተሳነን፣ ግዚያዊ ደስታን ብቻ ሽተን "ተዉን፣ እንንፈላሰስበት" እያልን እንደ ጅረቱ "ጆሮ ዳባ ልበስ" ያልን፣ ባለማመንና በትእቢት ተወጥረን እንደ ግመሉ የምንንገዋለል፣ እንደ ገመዱ ደንታ ቢስ ሆነን ባልሆነ ቦታ የተጠመድነው፣ እንደ አይጧ ያግበሰበስነውን ይዘን ስናተራምስ ራሳችንን እና ወገኖቻችንን አደጋ ውስጥ የምንዘፍቅ ሁላ፣ ከኋላ የሚያሯሩጠን ነገር እስክናይ ባንጠብቅ ይበጃል እላለሁ። 

ይልቁንም፣ ሁሉም ሰው እንደ ድመትዋ ቢሰማ፣ ሰምቶም በየተሰማራበት ተገቢውን ቢያደርግ ውጤታማ እንሆናለን።

 

 

Back to Front Page