Back to Front Page

ውሸት መርሖ ያደረጉት ኮ/ል አብይ

 

ውሸት መርሖ ያደረጉት ኮ/ል አብይ

 

ታዘብ ከዓዲአውዓላ

ጥቅምት 12፣ 2013ዓ/ም

 

የኮ/ል አብይ ነገር እንዲህ ነው። አንዴ ከነካኩት አይቀር ጭምልቅልቅ እስኪሉ መነከር የሚሉት ዓይነት ነው። በኢትዮጵያ ምድር ውሸታምና እና እያደረ የሚለው የአበው ቢሂል ረስተውት ነው ወይስ ውሸት ተደጋግሞ ሲነገር እውነት የሚሆን መስሏቸው ይሆን ኮ/ል አብይ ደጋግመው ነጋጠባ የሚዋሹት? የድሮ ገዥዎቻችን አፄ ኃይለስላሴ ይሁኑ ኮ/ል መንግስቱ እውነታውን አሳስተው በራሳቸው የገዥዎች መነፅር እያዩ ሲተነትኑ እንጂ ነጭ ውሸት ሲዋሹ አልሰማንም። ያኔ ኢህአዴግ እንኳን ሊዋሽ አገሪትዋን በልማት ለውጥ እያነጎዳት በታሪክዋ ያልነበረ ዴሞክራታይዘሽን ጀምሮ እያለ እኔ በምፈልገው ደረጃ ውጤት አልመጣም። ይቅርታ! በስብሰናል! የመንግስት ሌቦች ህዝቡን በደሉት! እያለ ራሱን ክፉኛ ይወቅስ ነበር። ታድያ ጥልቀት ተሃድሶ እያለ ማጭበርበር ከጀመረውና ከእውነት ከተጣላው ኢህአዴግ በፊት የነበረው ኢህአዴግ ማለቴ መሆኑ ይታወቅልኝ።

 

የኮ/ል አብይ ኢህአዴግማ (ፒፒ ሳይሆን) እንደ ድሮው ኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ብድብብቆሽ ሳይሆን በላይቭ/በቀጠተኛ የሚድያ ስርጭት ትመለከታላቹሁ፣ ትስማላችሁ ሲለን ቆይቶ የለመድነውና የተለመደውም መግለጫም ሳይሰጥ እንቁልልጭ አለን። ይባስ ብሎ የውሸት ቋቱ ይዞ ከተፍ አለ። ጠቅላዩ ዋሹ ብለን እንዳንገመግማቸው ግራ ተጋባን። ምላሳቸው አዳልጣቸው ይሆናል እንጂ የአገሪቱ መሪ እንዲህ ያል ንግግር አያደርጉም እንዲያውም ጆሯችንን መጠራጠር ይሻላል የሚለውን መርጠን ጭጭ አልን። እስቲ ይታረሙ ይሆን ብለን በትግዕስት እንጠብቅ ብንል እሳቸው ግን በሳባቸው። ይዋሻሉ። ቀዳዳ ሆኑ።ኢህዴግን አፍርሰው ወንጌላዊው ብልጥግና ከመሰረቱ በኃላ ግን ውሸት መርሖቸው ሆኖ አገኘነው።

 

 

Videos From Around The World

የህወሓቱ ጌታቸው ረዳ ሁሉንም የአብይ እንቅስቃሴ ድራማ ነው እያሉ ሲናገሩ ስሰማ ድራማ እወዳላሁና እስቲ ድራማውን ልከታተል ብዬ ስራዬ ብየ ድራማቸው ስመለከት እውነትም የተዋጣለት ተውኔት መሆኑ እኔም ደረስኩበት። ለምስክርነት ደግሞ በቅርቡ ለሲዙኑ በለቀቁዋቸው አንድንድ ተውኔታቸው ልግባ።

 

ከዛ በፊት ግን አንድ መሰረታዊ ነገር ላስታውሳችሁ።። መስከረም 25፣ 2013ዓ/ም በህገመንግስቱ መሰረት በሚከተሉት አንቀፆችና ቁጥሮች ስልጣናቸው ህጋዊነት ያጡት ኮ/ል አብይና የግላቸው የሆኑት ሁለቱም ምክር ቤቶች ስድስተኛ ዓመት በሚል ስብሰባቸውን በውሸት አደራሽና በውሸት አጀንዳ እየቀጠሉ መሆኑን እናስታውስ። ነገር ግን አንቀፅ 54 ቁጥር 1 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፣ ሁሉ አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛ፣ ትክክለኛ በሆነና ድምፅ በሚስጥር በሚሰጥበት ሥርዓት በየአምስት ዓመቱ በሕዝብ ይመረጣሉ። ይላል አንቀፅ 58 ቁጥር 2 ደግሞ የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ነው። በመካከሉም ምክርቤቱ በሚወስነው ጊዜ የአንድ ወር ዕረፍት ይኖረዋል። ይለናል በተመሳሳይ ደግሞ አንቀፅ 67 ቁጥር 1 የፌደረሽኑ ምክር ቤት የሥራ ዘመን አምስት ዓመት ይሆናል ብሎ ያስረግጥልናል።

ታድያ በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ህገ መንግስት ይህ ከላይ የሰፈረው ህገመንግስታዊ ድንጋጌ ይተርጎምልን ብለው አምስት ዓመት የሚለውን ቁጥር በመደመር ሂሳብ ደምረው የስልጣን ዕድሜያቸውን በማስረዘም ግግም ብለውና የሙጥኝ ብለው ስልጣናቸውን በማስቀጠል እስካሁን ሁለት የምክር ቤት ስብሰባዎች በህገወጥ መንገድ አካሂደዋል። በህገመንግስቱ መሰረት የፌደራል አስተዳደሩ ውስጥ ብቸኛ ህጋዊ እውቅና ያላቸው ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ቢሆኑም በህገወጡ ስብሰባ ተገኝተው የህገወጡ አስተዳደር ሪፖርት በማቅረባቸው ህገ መንግስቱን በመተላለፍ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። የተሰጣቸው የውሸት ሪፖርትም እንዳለ በማቅረባቸው በተባባሪነትም በህሊናም በህግም የሚያስጠይቃቸው ነገር ነው።

 

በነገራችን ላይ ኮ/ል አብይ በውሸት ሪፖርቱ ላይና ከህገወጥ ምክርቤቶቹ ለቀረበለት የውሸት ጥያቄዎች የውሸት መልሶች ለመስጠት የተሰየመው በኢሠፓ አደራሽ ነበር። በኢሠፓ አደራሽ መሰየሙ ብቻውን ፓርላማው አደራሽም ለህገ መንግስቱ ወግኖ ለውሸት ምክር ቤትና ለህገወጥ ምክር ቤት አባላት አልተባበርም ብሎ እምቢ ያላቸው ይመስላል። መስከረም 2 ስልጣኑን በሃይል ከተቆጣጠረው ወታደራዊ ደርግ አትለዩም እና እዛው ኢሠፓ አደራሽ ተሰብሰቡ እንጂ እዚህ የተከበሩት የህዝብ እንደራሴዎች መሰብሰብያ አደራሽ ለመሰብሰብ ህግ አይፈቅድላቹሁም። እናንተ ባታደርጉትም እኔ ጉዑዙ አደራሽ ግን በጭራሽ አልተባበርም ያላቸው ይመስላል። የኮ/ል አብይ የውሸት መልስ ለመስማት የም/ቤቱ ህገወጥ አባላት አደራሹ ለመግባት የነበረው ፍተሻም ለጉድ ነው። ሪፓፕሊክን ጋርዱ ገና በተሞክሮ ያልዳበረ በመሆኑ ወንዶቹንም ሴቶቹንም ሲፈትሽ የሚቀረው ነገር የለም። በሸካራ እጃቸው የሁሉም ታሳታፊዎች መላ ኣካላት መዳበስ ሳይሆን መጎነታተላቸው ያልተጠበቀ ነበር። ግራ የገባቸውም አባላት አጋጥመዋል። አንድንዶቹ ኣባላት ማሽኑን የማያምኑት ከሆነ ለምን አስቀመጡት? ብለው ሲንሾካሸኩ ነበር። ኮ/ል አብይም ይህ ሁሉ ፍተሻ ተደርጎም ጥላቸውንም ስለማያምኑ ግንባራቸውን የማይከላከለው የለበሱት መከላከያ እንደባለፉት ግዝያት ደረታቸው ላይ ተወጣጥሮ እንዳያስታውቅባቸው ደማቅ ሕብረ ቀለም ያለውን የክልል ጥያቄ መልስ ያልተሰጠውን የደቡብ ህዝቦች አንዱ ብሄር ባህላዊ ልብስ ለመልበስ ተገደዱ። ለሌላም ምክንያት ተጠቅመውበታል። በኃላ እመለስበታለሁ። ነገር ግን ምን አስጨነቃቸው? እንደ ደርጉ ባለስልጣን የጎንደሩ ነብሰ በላ መላኩ ተፈራ ጥይት የማያስመታ የክታብ ማተብ በግራ እጃቸው ቢያስሩኮ ባልተቸገሩ ነበር። የአማራ ብልፅግና ይህን ችግር አይቶ ለምን እስካሁን መላ እንዳልፈለገላቸው ለትዝብት ይዳርገዋል።

 

ወደ ኮኔሬሉ ውሸት ስመለስ የዋሹትን እዚህ አንስቼ መደርደሩ በናንተን ግዜ፣ ጉልበትና ገንዘብ መቀለድ አልፍልግም። ነገር ግን ያስገረሙኝ፣ ያሳቁኝ እና የኮ/ሉ ጨቅላነት ያሳዩኝ አምስት ጉዳዮች ላይ አጠር አድርጌ ላቅርብ። የትኛው ውሸት ነው ትልቁ ውሸት የሚለው ለማወዳደር ብፈልግም ስለከበደኝ ፍርዱን ለአንባቢዎች ትቸዋለሁኝ።

 

ውሸት አንድ፡ በየትኛውም ክልል የውስጥ ጉዳይ ላይ አንድም ቦታ ላይ ጣልቃ አልገባንም።

 

ይህ መልሳቸው እውነት ሊሆን የሚችለው በአንድ ምክንያት ብቻ ነው። ክልል የሚለው አሁን ባለችው ኢትዮጵያ ትግራይ ብቻ ናት በሚል ከተተረጎመ ብቻ ነው። ጣልቃ ለመግባት ብዙ ሙከራ አድርገው አዎ ያልተሳካላቸው ትግራይ ክልል ብቻ ነው። በተጨማሪም ለአብይ ለሁሉም ኤርትራዊያን ኢትዮጵያ ሲመጡ የተፈቀደው የመቐለ ጎደናዎች መጎብኘት ነፃነት ለወዳጃቸው ለኢሳያስ (ኢሱ) መከልከሉ ሁሌም የሚያበሳጫቸው ነው። የትግራይ ክልል መንግስትን አስገድደው ኢሳያስ አፈወርቂ እንዲጎበኝ ባለማስደረጋቸው እውነትም ጣልቃ አልገቡም ያስብል ይሆናል። ሌላው ግን አብዲ ኤሌን ፈንግለው ሞስጠፌን፣ አምባቸውን አስገድለው ተመስገንን፣ ሚልዮን አባርረው እንዲሁም የደቡቡንና የአፋሩን አረ የስንቱ ልቁጠር እየተኩ መሾማቸው ጣልቃ መግባት ሳይሆን ንጉስ ነገስት የሚያደርገው ሹመት ነው ለማለት ፈልገው እንደሆነ መቼ አጣነው።

 

ውሸት ሁለት፡ ፓርላማ ያልሰጠኝን በጀት እንዴት በእንጦጦ ላይ መዝናኛ ትሰራለህ ብሎ ሊጠይቀኝ ይችላል?

ይህ በጣም ጥሩ ድራማ ነው። ህገወጥ መሪና ህገወጥ ምክር ቤት ሲሸዋወዱ የሚተውኑበት መድረክ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ህጋዊና ትክክለኛ ምክር ቤት ቢሆን ንሮ ብያንስ ሶስት ጉዳዮች መጠየቅ ይችል ነበር። ይችል ነበር ነው ያልኩት። አንደኛ የገንዘቡ ምንጭ የመጠየቅ ስልጣን ስላለው ይጠይቅ ነበር።ቢልዮኖች ወጪ በማድረግ አልጠየቅም ማለት ውሸትም ፌዝም ነው። ሁለተኛ የእንጠጦ መሬት የኮ/ል አብይ እናት ርስት ወይም ይዞታ ስላልሆነና መሬት የመንግስት ስለሆነ መሬት ደግሞ የሃብት ምንጭ ስለሆነ በምን አሰራር ነው ለጥገኛቹ ባለፀጎች የሸነሸኑት? በሱ ፋንታስ እርስዎ ምን ተጠቀሙ? ብሎ የሚጠይቅ አባል እንካን ይጥፋ። በቀላሉኮ ያኔ ይይዛቸው ይችል ነበር። ነበር ሲያስጠላ። የደቡብ ኮርያ ምክርቤት ወይም ዐቃቤ ህግ ዓይነት ቢኖረን ኖሮ መሪያቸውን ያደረጉትን ዓይነት እርምጃ ማድረግ ነበረ በማለት በቁጭት የምገልፀው ጉዳይ ነው። ሦስተኛው የሚያስጠይቃቸው የነበረው የአንድ መሪ ጊዜ አጠቃቀምም ምክር ቤቱ ያገባዋል። አንድ ሚኒስተር መስርያ ቤት ታች የሚገኝ ክፍል ሃላፊ የሚሰራው ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስተር ነኝ የሚል ጊዜውን በከንቱ ሲያጠፋ ለምን አይጠይቅም። የህፃናትና ታዳጊ ልጆች ጭዋታ መጫወት የሚያምረው መሪ አባቱ ወይም እናቱ ትጠይቀው ብሎ ምክር ቤቱ ማለፍ በተገባ ነበር? JEEP ሲነዳ ሲጫወት ይውልና የቻይናው መሪ ያደረጉልን ድጋፍ ብሎ አለሁ ብሎ ይናገራል።

 

ውሸት ሶስት፡ ከትግራይ ያለውን ልዩነት ምክርቤቱና ፌዴረሽኑ በወሰኑት መሰረት በህግ መሰረት የምንሄድበት ይሆናል

በጣም ያሳቀኝ ውሸት ይሄኛው ነው። ህገወጥ ሁኖ ስለ ህግ የሚያወራ ጉድ። ያልተመረጠ መንግስት የተመረጠን መንግስት በህግ የምንሄድበት ነው ሲል አያስቅም? እንዴት? በምን መንገድ ጥቃት ልፈፅምባቸው እችላለሁ ብሎ ሲይስብ እና አንዱን መርጦ እሱን ደግሞ ጥሎ ሌላ አማራጭ ሲያማትር የሚውል መንግስት ተብዬ በህግ እናስኬደዋለን ሲል አያስቅም? ጨቅልዬ ሞክራት! ጨ ነው ያልኩት ጠ እንዳይመስለው ደግሞ። እሱ ቀጥርም፣ ፍደልም፣ ሀሳብም ይደፋራልም ይምታታዋልምና።

ውሸት አራት፡ ፍርድ ቤት የወሰነውን ያለማመንታት መተግበር አለብን።

በኔ ግምት ትልቁ ውሸት ይህ ይመስለኛል። ኢሳያስ ዳኛው (የጀነራል ክንፈ ዳኛው ወንድም) ለረዥም ጊዜ ታስሮ ከቆየውና እስከ ቅርብ ጊዜ የታሰረው ልደቱ አያሌው ፍርድ ቤቱቹ በነፃ ይፈቱ፣ በዋስ ይፈቱ፣ ሲሉ የለገጣፎው የህዝብ ስቃይ አራት ኪሎ ሆኖ እንዳተልሰማው ሁሉ አልሰማሁኝም ማለቱ ይሆን። ልደቱ አያሌውን በኦሮሚያ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ዳኞቹ እንደ ፒፒ ዘረኛ መስሏቸው ነፍጠኛ አገኘን ብለው እንዲያሹት ነበር። ነገሩ ግን የተማረ ይግደለኝ ሆነና የኦሮሚያ ዳኞች ምንም የሚያስጠይቅ ነገር የለውም ብለው ብይን ቢሰጡም ፒፒዎች በሰባው ጆሯቸው መስማትና ማዳመጥ አልቻሉም። የኢሠፓ አዳራሽ ቀርበው ኮ/ል አብይ ይህ እየተደረገ ከሆነ የምናካሂደውን የዴሞክራታይዘሽን ሂደቱን የሚፃረር ነው በማለት ዋሹ። ነገሩ እንደዚህ ነው። በቅርቡ የአውሮፓ ሕብረት ተወካዮች አዲስ አበባ መጥተው በኢትዮጵያ እየተፈፀመ ያለው ጆኖሳይድና በግፍ ማሰር በመኮነን እንዲቆም አስጠነቅቀዋል። ሙፍርያት ዘላ ሚድያ ወጥታ መስከን አለብን ብላ አዲስ የሯሳ ሃሳብ አስመስላ የተናገረችውም የነዚሁ አውሮፓ ሕብረት እርቀ ሰላም ታወርዱ አውርዱ አለበዝያ ግን ዋ! የሚል ማስጠንቀቅያ ስለሰጡ ነው። ይህ ነገር ከተሰጠ በኃላ ፒፒዎች ሽንት በሽንት ሁነውና ሁሉም ነገር ረጥቦ የመጣ ለውጥ ነበር። ጨቅላው ሽንቱን ጠራርጎ የራሱን ሐሳብ አስመስሎ ተናገረ። እንደ የደርጉ ሙርከኛ ካሣ ጨመዳ ከምክርቤቱ ስብሰባ በኃላ ኮ/ል አብይም እንዴት አያቹሁት? እንዳላቹሁኝ ተናገርኩ አይደል? ብሎ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደሮችን ጠይቆ ይሆናል።

 

ውሸት አምስት፡ ፌደራሊዝም እንቀበላለን። እኛ ብልፅግና ትክክለኛ ፌዴራሊዝም ይሁን ነው የምንለው

 

ከዋሹ አይቀር በደንብ አርጎ መዋሸት ነው። አብይ ልብሱ ከሁሉም አደራሹ ውስጥ ከተሰበሰቡት ተሳታፊዎች ተለይቶ ብቻውን የደቡብ ህዝቦችን የሚወክል ባህላዊ ልብስ መልበሱ ለትወናው ያለው ፍቅር እያየለ መምጣቱንና የወከለው ገፀ ባህርይ ለመምስል ምንኛ ጥረት እንደሚይደርግ የሚያሳይ ነው። አቃቂረኛው የአይዶል ሸው ዳኛ ሳይመን yes! ታለንቱ አለህ ባይለውም የአገራችን የአይዶል ሸው ዳኞች ግን የሆዳቸውን በሆዳቸው አኑረው no ሳይሉ ተመችቶኛል ለሚቀጥለው ዙር አልፈዋል የሚያስኝ ትወና አቅርባል። ለመረጃ ያህል በለበሰው ልብስ ውስጥ ያለውን ክራባት ግን የብልፅግና ምልክት አድርገን ብናየውና ፀጉር መስንጠቁ ቢቀርብን እላለሁ።

 

ለማጠቃለል ግድያ፣ አምበጣ፣ ጎርፍ፣ ድርቅ፣ መፈናቀል፣ የሰላም እጦት፣ የኢኮኖሚ ቀውስና አገር መፍረስ እና ግድያና እስራት በኢትዮጵያ የአሁኑ ተጨባጭ ሁኔታዎችና እውነታዎች መሆናቸው ሁሉም ይስማማል። ነገር ግን በራሱ ውሸት ጆሮው የደነቆረው ኮ/ል አብይና መስማት የማይፈልገው ወንጌላዊው ብልጥግና በውሸት ግልኮስ ዕድሜውን ለማስረዘም እየሞከረ ነው። መቆየት ግን አይችልም። ዋና ችግሩ የውሸት መርከቡ ብልጥግና ብቻውን ብቻ ሳይሆን አገሪትዋን እና ህዝቧን ወደ መቀመቅ እየከተታቸው መሆኑ ነው። በዚህ ማለቅያ በሌለው የውሸት አራሙቻ አገራችን ኢትዮጵያ እየፈረስች ነው።

 

በውሸት መርሖ የሚድን አገር የለም። ቱልቱላውን በቃ የምንልበት የመጨረሻ ሰዓት እየደረሰ መሆኑን ሁላችንም አውቀን የኢትዮጵያ ህዝቦች እርምጃ የምንወስድበት ወሳኝ ጊዜ ደርሰናል። ሓሳዊ ተውኔት እያይንና ቀዳዳውን እይሰማን መሳቅ ባልከፋ ነበር ነገር ግን ጊዜ የለንም። መነሳት አለብን። አገራችን ኢትዮጵያ ከሶማልያ፣ ከየመንና ከሶርያ እጣ ለማዳን የተሻለ የመማር ዕድል አግኝተን እያለን በአጭሩ ካላሳካነው የነዚህ አገራት ስሕተት ከደገምን እደጋግመዋላሁ አገራችን ትፈርስላች፡፡ አገራችን ከፈራረሰችና ከተበታተነች በሃላ የዘለዓለም ፀፀቱን አንችለውም። አገራችንን የማዳን ዕድል እያለን ካልተጠቀምንበት የኃላ የኃላ ምንም ዓይነት ምክንያት ማቅረብ የማንችልበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ሰለዚህ ይበቃል! አሁንኑ በአንድ ላይ ተነስተን ብልጥግናን እንፈንግለው! አገራችንም ከመፍረስ አደጋ እናድን!

 

ቸር ይግጠመን።

 

 

Back to Front Page