|
የሰኔ 16ቱ ፍንዳታና የዐቢይ አህመድ ቆሻሻ ፖለቲካ
ሙሉጌታ ወልደገብርኤል (ስትራቴጂስት) 09-29-20
የምንኖርባት ዓለም የሰው ልጅ (በተለይ እንደ እኛ ዓይነቱ የኃይማኖት ሰዎች ኢትዮጵያውያን) ሊያስበውና ሊደርሰው ከሚችለው በላይ እጅግ በተወሳሰበና ጥልቅ በሆነ አረመኔያዊና የጨለማ ስራ የተሞላች ዓለም ናት። ሰዎች (አገራትና መንግሥታት) የሚፈልጉት ለማግኘትና የማይፈልጉትን ለማስወገድ፤ የሚመቻቸው ለመሾምና የዓይኑ ቅንድብ ያላማራቸው ደግሞ ለመሻር፤ በአጠቃላይ፥ ጥቅማቸው ጠብቀው ለማስጠበቅ፥ የማይፈጥሩት፣ የማይሰሩት፣ የማያደርጉት፣ የማያከናውኑትና የማይፈጽሙት ተንኮል፣ ሴራና ደባ የለም። በዚች ምድር ላይ ያልተነገረ እንጅ ያልተፈጸመ የሰይጣን ሃሳብ የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። መንግሥታት የራሳቸው ጥቅም ጠብቀው ለማስጠበቅ፥ ክፍዎችና አረመኔዎች መስለው በመገልጥ ሳይሆን በዲሞክራሲ፣ በነጻነት፣ በፍትህና በእኩልነት ስም፥ ረዳት፣ ታዳጊ፣ መልካም አሳቢዎችና አድራጊዎች ብሎም የብርሃን መልዓክ መስለው መታየት የተለመደ ነው። የሰላም ሓዋርያትና መልዕክተኞች መስለው በመግባት አገራት ሲያፈራርሱ፣ ሲያተረማምሱና ሲያወድሙ፤ ህዝብ በህዝብ ላይ በማስነሳትና በመቀስቀስ ህዝቦች ደም ሲያቃቡ በዘመናችን አይተናል። ተቋዋሚዎች የሚመኙትን ስልጣን ለማግኘት፣ ገዢዎች በአንድም በሌላም የተቆናጠጡት ሥልጣን ላለመልቀቅ በዜጎቻቸው ህይወት ላይ መቆመርና ቁማር መጫወት፣ ዜጎቻቸው ሰውተው መክበርና መንገስ፣ በንጹሐን ዜጎች የህይወት መስዋዕትነት ሀብትና ንብረት ማፍራትና ማካበት ለዓለማችን እንግዳ ነገር አይደለም። በጥንት ዘመን፥ በከተማዋ ውበት ብዙም ደስተኛ ያልነበረ የሮም ዝነኛው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ፥ እ.አ.አ በ64 ዓ/ም የከተማዋን ውበት ለማደስ፣ አብዛኞቹ ለመለወጥና አዲስ ቤተ መንግሥት ጨምሮ ሌሎች በርካታ አዳዲስ ግንባታዎች የመገንባት ፍላጎት እንዳደረበት ታሪክ ይመሰክርልናል። ይህን ለማድረግ ደግሞ የከተማዋ አንድ ሦስተኛ ይዞታ ማፍረስ እንደሚጠበቅበት ይረዳል። በሴኔቱ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ኔሮ ግን እጅና እግሩ አጣጥፎ አልተቀመጠም። ህልሙን እውን ለማድረግ ሁለት ሚሊዮን ነዋሪዎች የሰፈሩባት ከተማ በእሳት እንዳወደማት፤ ከዚህ የተነሳም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ህይወት መጥፋቱንና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩም ቤት አልባ እንደሆኑ የታሪክ ሊቃውንት ያትታሉ። የኔሮ ሴራ ግን ከተማዋን በማቃጠል ብቻ የሚያበቃ አልነበረም። በዘመኑ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋና ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣው የክርስትና እምነት አስተምህሮ ለንግሥናው እንደ ስጋት (threat) ስለተመለከተው እንቅስቃሴው ለመግተት የእሳት ቃጠሎው ክስተት በመጠቀም ለክስተቱ የክርስትና እምነት ተከታዮች ተጠያቂዎች በማድረግ በእምነቱ ተከታዮች ላይ ከፍተኛ ስደትና መከራ ከማስነሳቱ በተጨማሪ በመቶዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖችን በቁጥጥር ስር አውሏል፣ አሠቃይቷል፣ አስገድሏልም። እ.አ.አ የካቲት 1933 ዓ/ም በተመሳሳይ ናዚዎች ሪችስታግ ተብሎ የሚታወቀው የራሳቸው የምክር ቤት አባላት ህንጻ በእሳት ማቃጠላቸውንና ክስተቱም ተከትሎ የፓርቲው መሪ አዶልፍ ሂትለርና የፓርቲው የፕሮፓጋንዳ ባለ ሥልጣን ጆሴፍ ጎብል የናዚ ፓርቲ ብቸኛ የበላይነት ለማስጠበቅ የዶች ኮሚኒስቶችን ተጠያቂዎች በማድረግ በጀርመን የኮሚኒስት ፓርቲ አባላት በነበሩ ዜጎች ላይ መግደልን ጨምሮ ከፍተኛ የማጽዳት ስራ እንደሰሩና የፖለቲካ ተቀናቃኞች ለማስወገድ እንደተጠቀሙበት ይታወቃል።
ቀዳማዊ ኢህአዴግ ሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ ቦታዎች ሲፈልግ ድልዲ ስር፣ ሲያምረው ታክሲ ውስጥ የሚፈነዳ ቦንብ እየቀበረና እያፈነዳ፤ አንዳንድ ጊዜያትም ለማስፈራርያ ሳይፈነዳ ሊያፈነዳ ሲል ያዝነው! ደረስንበት! እያሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን እንዴት ሲያሸብሩ እንደነበር እናውቃለን። ከዚህ የተነሳም እነሱ የፈጠሯቸው የውሸት የፖለቲካ ፓርቲዎች ካልሆኑ በስተቀር ሌሎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ አንገታቸውን እንዲደፉና ህልውናቸውም እንዲመናመን አድርጓል። ዜጎቹን እንደ ጥጃና እንደ ጥቦት ደም እያፈሰሰና መስዋዕት እያደረገ የፖለቲካ ተቃሚዎቹን ድባቅ ሲመታ፤ የዜጎች በነጻ ሃሳብን የመግለጽ፣ በነጻ የመንቀሳቀስና የመሰባሰብ ህገ መንግስታዊ መብቶቹን ንዶና ገፎ ስልጣኑን ሲያደላልድ የነበረው የኢህአዴግ ቡድን በዚህ የሽብር ድርጊት የተካኑ ነበሩ። የማያልፍ ነገር የለምና በተራቸው አለፉ ኢትዮጵያ አዲስ አመራር ለማስተናገድ በቃች። ፖለቲከኞችና የሀገር መሪዎች ሰፊው ህዝብ ከጎናቸው ለማሰለፍ፣ ደጋፊና ወዳጅ ለማፍራት፤ የፖለቲካ ተቃዋሚዎቻቸውን ለማጽዳት፣ ህዝባዊ ቁጣ ለመቅስቀስ፤ ዒላማ የተደረገ አካል በጠላትነት ለመፈረጅና ለማሳጣት፣ ለማስመታትና ለማስጠቆር፣ ጥግ ለማስያዝና ለማሸማቀቅ፣ ከጨዋታ ውጭ ለማድረግና ለመበቀል፣ ለመምታትና ለመደምሰስ ታስቦው የተዘጋጁና የተካሄዱ ቆጥረን የማንዘልቃቸው በንጹሐን ዜጎች ደምና አጥንት ላይ የተሰሩ እጅግ የሚሰቀጥጡ ኦፕሬሽኖች በዓለማችን ላይ ተከናውነዋል። በመቀጠል፥ በሰፊው የምንዳስሰው የሀገር መሪዎች፥ ስልጣናቸውን ለማደላደልና ጠላቴ ነው በሚሉት አካል ላይ ህዝባዊ ቁጣ ለመቅስቀስ ብሎም ጠላቶቻቸውን ለመበቀል በገዛ ዜጎቻቸው ላይ የሚሰሩትና የሚፈጽሙት አስነዋሪና አሰቃቂ ጥቃቶች ጥቂቶች አንስተን እንመታለን አያይዘንም በአገራችን በኢትዮጵያ በአዲሱ አመራር በዐቢይ ዘመነ መንግሥት ከተፈጸሙና ካስተናገድናቸው ብዥታ ያጠላባቸው በራሱ በአዲሱ አመራር ቀጥተኛ እጅና ትዕዛዝ የተፈጸሙ በርካታ ሴራዎች መካከል በዋናነት በሰኔ 16, 2010 ዓ/ም ላይ በመስቀል አደባባይ የተፈጸመው የቦንብ ጥቃት ጀርባ ያለው የዐቢይ መንግስትና ሴራ እናመሳጥረዋለን። ኦፖሬሽን ሂምለር ኦፖሬሽን ሂምለር ሁለተኛ የዓለም ጦርነት በይፋ ከመቀስቀሱ በፊት ለጦርነቱ መንስኤ የሆነው የናዚ አባትና መሪ አዶልፍ ሂትለር ፖላንድን ለመውረር የፈበረከውና የሰራው የሐሰት ድራማና ውንጀላ (false flag) ነበር። ሂትለር ፖላንድን ለመውረር ሲያስብ ብድግ ብሎ የሰው አገር ለመውረር አልተነሳም። ፖላንድ የመውረር አጀንዳ ስላለኝ ለጦርነት ተነስ! በማለትም የጀርመንን ህዝብ ለዘመቻ አላነሳሳም፤ ጦርነትም አልቀሰቀሰምም። ይልቁንም፥ ሂትለር ፖላንድን ለመውረር ስያስብና ለሚወስደው ወታደራዊ እርምጃም ፍትሐዊ መሆኑን ለማሳየት የጀርመንና የዓለም ህዝብ ማሳመን ይጠበቅበታልና ይህን ለማድረግ አንድ ምክር መከረ። ይህ ጥብቅና ምስጢራዊ ምክር (ኦፕሬሽን) በናዚ ልዩ ኃይል (SS) እና የናዚ የደህንነት ክፍል (SD) የተውጣጣ ግብረ ኃይል አማካኝነት ለማከናወን አሴረ። ይህ በአልፍረድ ኗጆክስ (Alfred Naujocks) የሚመራው ግብረ ኃይል ከስር የጀርመን ከላይ ደግሞ የፖላንድ ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሰው በአከባቢው የውሸት ተኩስ በመክፈትና እግረ መንገዳቸውም መጠነኛ የውንብድና ስራ በመስራት በጀርመንና በፖላንድ ድንበር አቅራቢያ የሚገኘውን የጋሊዊትዝ የሬድዮ ጣቢያ ስርጭት (Gleiwitz station and broadcast) በመቆጣጠርም በፖሊሽ ቋንቋ የብሮድካስት ጣቢያው በፖላንድ እጅ ወድቋል! ሲሉ ያውጃሉ። ልብ ይበሉ፥ የፖላንድ ወታደራዊ ዩኒፎርም ለብሰው በገዛ ከተማቸውና የሬድዮ ጣቢያቸው ይህን ሁሉ ግርግርና ውንብድና እየፈጸሙ ያሉ በእውነት የፖላንድ ወታደሮች ሳይሆኑ ሂትለር የፖላንድ መንግስት ለመወንጀል የፖላንድ ወታደራዊ ዩኒፎርም አስለብሶ ያሰማራቸው የራሱ ወታደሮች ናቸው። ጭጉራፍ እራስዋ ገርፋ እራስዋ ትጮኻለች! በሰዓታት ውስጥ የጀርመን የሬዲዮ ጣቢያዎች በጋሊዊትዝ ላይ ስለተፈጠረው ነገር ሰበር ዜና! ሲሉ እየተቀባበሉ ይዘግቡታል። ቢቢሲም (BBC) ከምሽቱ 8 ሰዓት አካባቢ የፖላንድ ታጣቂ ኃይሎች በጋሊዊትዝ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውንና የሬድዮ ጣቢያው በመቆጣጠርም በፖላንድ ቋንቋ መግለጫ ማሰራጨት በጀመሩበት በአስራ አምስት ደቂቃ ውስጥ ከጀርመን ታጣቂ ኃይሎች የተኩስ ልውውጥ መክፈታቸውን፤ በርካታ የፖላንድ ወታደሮች መገደላቸውን፤ የሞቱት ቁጥር ግን እስከ አሁን አይታወቅም! ሲል ዜናውን ለመላ ዓለም ያሰራጨዋል። በነገታው ጥዋት ደግሞ ሂትለር ጀርመን በፖላንድ መወረርዋንና የጀርመን ህዝብና መንግሥትም ሉዓላዊነቱን ጠብቆ ለማስጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ለመውሰድ እንደሚገደድ በማወጅ አስቀድሞ ያቀደውን ፖላንድን የመውረር ህልሙ እውን ለማድረግ ሠራዊቱን አንቀሳቀሰ። ይህ ኦፖሬሽን ከመከናወኑ በፊት ግን የጀርመን መገናኛ ብዙሐን፣ ሂትለርን ጨምሮ ከፍተኛ የናዚ ባለሥልጣናት የፖላንድ መንግስት በፖላንድ ውስጥ የሚኖሩት ጀርመናውያን ላይ ያነጣጠረ የብሔር ማጽዳት ጥቃት ለማካሄድ አመጽ እየቀሰቀሱ ነው! ሲሉ የፖላንድ መንግሥትና ባለሥልጣናት በመወንጀል ከፍተኛ የሆነ ፕሮፓጋንዳ ከፍተው እንደነበር ይታወሳል። በነገራችን ላይ፥ በሬድዮ ጣቢያው ደጃፍ ላይ የፖላንድ ወታደራዊ ዩኒፎርም አስለብሰው የገደልዋቸው ሰዎች በናዚ እስር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ እስረኞች ናቸው።
የኩርቻክ ጥቃት
እ.አ.አ በ2008 ዓ/ም በጆርጅያ የደረሰው የኩርቻክ ጥቃት ተብሎ የሚታወቀው ይህ ጥቃት መንግሥታት በሰፊው ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘትና ጠላቶቻቸውን ለማስጠቆር ብሎም ለማስመታት አስበው በንጹሐን ዜጎች ላይ በዓላማ ከተፈጸሙ ጥቃቶች መካከል አንዱ ነው። ይህ ጥቃት በጆርጅያና በአብከዢያ ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው በኩርቻክ መንደር የፓርላማ አባላትና የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ በተዘጋጁ የጆርጅያ ዜጎች የጫኑ አውቶቡሶች ላይ የተሰነዘረው የመሣሪያና የቦንብ ጥቃት ነበር። በተሰነዘረው ጥቃት የሞተ ባይኖርም ጥቃቱ ሦስት የጆርጅያ ዜጎች አቁስሏል። የጆርጅያ መንግሥት ጥቃቱ አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የአብከዢያ አደጋጣዮች/ሰርጎገቦች ተጠያቂ ቢያደርግም የኖርዌይ ሄልሲንኪ ኮሚቴና የጆርጂያ የሰብአዊ መብቶች ቢሮ ጨምሮ በተለያዩ አጥኚዎችና ገለልተኛ መሪማሪዎች ለማረጋገጥ የተቻለው ግን ጥቃቱ የተፈጸመው ለፖለቲካ ትርፍ ሲባል በራሱ የጆርጂያ የደህንነት ቢሮ አገልግሎት የቀናጀ መሆኑን ነበር የተረጋገጠው። እንደ መርማሪዎቹ የመጨረሻ የምርመራ ውጤት መሰረት ድራማውን በግልጽ ያጋለጡ ክስተቶች ከብዙ በጥቂቱ የተመለከትን እንደሆነ፥ ሰበር ዜና ሲል ጥቃቱን የዘገበው የጆርጅያ መንግስታዊ ሚድያ ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊቱ ጥቃቱ በተፈጸመበት ቦታ ላይ አስቀድመው በስፍራው መገኘታቸው፤ ምንም እንኳ ጥቃቱ የተፈጸመበት ቦታ ማለትም የኩርቻክ መንደር ከወታደራዊ ካምፕ የአስራ አምስት ደቂቃ ርቀት ላይ የሚገኝና በተጨማሪም የኩርቻክ መንደር ከማናቸውም ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ነጻ የሆነ አከባቢ ቢሆንም (ሆኖ ሳለ) ጥቃቱ በተፈጸመበት ቅጽበት የጆርጅያ ታጣቂ ኃይሎች በስፍራው መታየታቸውና መገኘታቸው፤ በተደረገው ምርመራና የዐይን እማኞችም እንዳረጋገጡት ጥቃቱ በአንድ መቶ ሜትር ርቀት ውስጥ መሆኑና የተሰነዘረውም በጆርጅያ ግዛት ክልል ውስጥ መሆኑ፤ ስለ ምርጫ ምንም ሳይነገር የአከባቢው ነዋሪዎች በኳስ ሜዳው በመግኘት የቪድዮ ቀረጻ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ጥሪ መደረጉ ይገኙበታል። በተጨማሪም፥ የተባበሩ መንግስታት የምርመራ ውጤት መሰረትም ጥቃቱ የተፈጸመው ከጆርጅያ ግዛት በኩል መሆኑን በማረጋገጥ እ.አ.አ በ2013 ዓ/ም በሁለት የጆርጂያ የደህንነት ቢሮ ከፍተኛ ሸማሙንት ላይ ስልጣናቸውን በመጠቀም የሽብር ድርጊት ፈጽሟል ሲል ክስ መስርቶባቸዋል።
ኦፕሬሽን ኖርዝውድስ
ኦፕሬሽን ኖርዝውድስ፥ እ.አ.አ በ1962 ዓ/ም አሜሪካ በኩባ ላይ ያፋዊ ጦርነት ለማወጅና የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ ለመግደል ያስችላት ዘንድ በመከላከያ ሚንስትር፣ በአገሪቱ የደህንነት ቢሮና ጆይንት ቺፍ ኦፍ ስታፍ በጋራ አዘጋጅነት የተነደፈ ኦፔረሽን ነበር። የዚህ ኦፔረሽን ዋና ዓላማ ፊደል ካስትሮን ማስወገድ/መግደል ሲሆን፤ ይህን ለማድረግ እንደ ምክንያት፥ አንድ፥ ኩባውያን ስደተኞች ይዛ ከኩባ ወደ አሜሪካ የምትቀስፈውን ጀልባ ባህር ላይ ማስመጥ፣ ጓንታናሞ በሚገኘውን የአሜሪካ የባህር ኃይል ጦር ላይ ጥቃት መፈጸም፤ በፔንታጎን የሚመራ ግብረ ኃይል በአሜሪካ ግዛት ውስጥ በተለይ በዋሽንግተን በፍሎሪዳ ሌሎች ከተሞች ላይ ህዝባዊ አገልግሎት በሚሰጡ በተመረጡ ስፍራዎች ላይ የቦንብና መሰል ጥቃቶች በመፈጸም ንጹሐን አሜሪካውያን መግደልና ደም ማፍሰስ፤ ንብረትነቱ የአሜሪካ የሆነው የህዝብ ማመላለሻ አውሮፕላን ማጋየትና ለዚህ ሁሉ እልቂትና ቀውስም የኩባ ፕሬዝዳንት ፊደል ካስትሮ ቀዳሚና ቀጥተኛ ተጠያቂ በማድረግ የአሜሪካና መላ የዓለም ህዝብ በአሜሪካውያን ንጹሐን ዜጎች ላይ የተፈጸመው ዘግናኝና አሰቃቂ ግፍ የተነሣ ቁጣውን እንዲነድ በማድረግ ኩባን መውረር ክስትሮን መግደል! ያለመ በአሜሪካ ከፍተኛ የፖለቲካ ባለ ሥልጣናት የተሰነደ ኦፕሬሽን ነበር። በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በነበሩ ጆን ኦፍ ኬኔዲ ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ኦፕሬሽኑ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቷል። ከዚህም የተነሳ በፕሬዝዳንቱና በአሜሪካ የደህንነት ቢሮ ባለ ሥልጣናት መካከል መራራቅና አለመቀባበል ተፈጥሮ እንደነበር ይነገራል።
የሙክደን ክስተት
የሙክደን ክስተት፥ የሙክደን ክስተት፥ እአአ 1931 ዓ/ም የቻይና ከተማ ማክደን ከተማ አቅራቢያ የሚገኘውን ንብረትነቱ የራሳቸው የጃፓናውያን የባቡር ሃዲድ በቦንብ በማጋየት ለክስተቱም የቻይና ተወላጆች ተጠያቂ በማድረግ በሁለቱም አገራት መካከል የቀሰቅሱት ጦርነት ነበር። የጃፓን ሠራዊት በባቡሩ ሃዲድ አቅራቢያ ላይ ያጠመዱት ፍንዳ ደካማና የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባያስገኝላቸውም ፍንድታዳው በጃፓን ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ነው! ሲሉ ጃፓናውያን በሰሜናዊ ምስራቅ ቻይና የምትገኘውን ማንቹሪያ ለመውረር ግን አስችሏቸዋል። የሙክደን ክስተት፥ እ.አ.አ 1932 ዓ/ም በለይቶን ሪፖርት የተጋለጠ ሴራ ሲሆን የጃፓን መንግሥት ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎ አልፏል። የሴራው በገሃድ መውጣት ተከትሎ ጃፓን ከዲፕሎማሲው ዓለምና የዓለም መንግሥታት ማኅበር/ሸንጎ (ሊግ ኦፍ ኔሽን) እንድትገለል ያደረገም ነበር።
የሰኔ 16ቱ የቦንብ ፍንዳታ
በቢዝነስ ዓለም ሆነ በግጭት አፈታት ቋንቋ Scarcity models ተብሎ ይታወቃል። ይህ የእሴት ፕሮፖዛል፣ ስትራቴጂና የንግድ ሥራ ሞዴል ሁለት ዓይነት መልክ ያለው ሲሆን እውነተኛ እና አርቴፍሻል ተብሎም ይታወቃል። የዚህ ሞዴል ዋና ዓላማ ምርቱን ከማስተዋወቅ ያለፈ ምርቱ በሸማቾች ዘንድ ተፈላጊነቱና አስፈላጊነቱ እንዲጨምር በማድረግ ሸማቹ፥ በጉጉትና በናፍቆት፣ በወረፋ፣ አምራቹ ድርጅት በቂዬ ነው ብሎ በተመነው ዋጋ ብቻም ሳይሆን ከአከፋይ አከፋፋይ እየተቀባበለ ከትክክለኛ ዋጋው መቶ ፕርሰንትም ቢጨምር ሸማች ኪሱ ላይ ያለው ሁሉ አራግፎም ሆነ ተበድሮ በደስታ የሚገዘው በውድ ዋጋ የሚሸጥ ዓይነት ዕቃ ማድረግ ነው። ይህ ስልት አርቴፊሻል በሆነ መንገድ ተግባራዊ የሚሆነው ለምሳሌ፥ ፋብሪካው በቀን አንድ መቶ የማምረት አቅም እያለው ሃምሳ የሚሆነው ብቻ በማምረትና ለገበያ በማቅረብ የገበያ እጥረት እንዳለ በማስመል የሚደረግ የማደናገሪያ ብልሃት ነው። ይህ ስልት ቀደም ሲል እንደተገለጸው የዕቃው ተፈላጊነት የሚጨምር ብቻ ሳይሆን ሸማቹ ዕቃው አቅራቢው ድርጅት በሚለው ዋጋ ሁሉ ሳያቅማማ እንዲገዛም ያስገድደዋል። ይህ ዓይነት የቢዝነስ ሞዴል በፖለቲከኞች ዘንድም በተመሳሳይ መልኩ አገልግሎት ላይ የሚውል ከሰፊው ህዝብ ዘንድ የተሰወረ ስልት ነው። መሪዎች ስማቸው ለመገንባት፣ ሥልጣናቸው ለማረጋገጥ፣ ከህዝቡ ያገኙትን ይሁንታ፣ ድጋፍና ተቀባይነት በ12 ቁጥር ሚስማር በሰፊው ህዝብ ላይ በሚገባ ለማጣበቅና ጠላቶቻቸው ለመወንጀል የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይቆፍሩት ጉድጓድ የለም። የፖለቲካ መሪዎች፥ በራሳቸውና በደጋፊዎቻቸው ላይ ያነጣጠረ ከጠላት የተቃጣ ጥቃት የሚመስል ዳሩ ግን በሚገባ የተቀናጀ የውሸት ኦፐሬሽን በማቀነባበር ስብእናቸው መገንባት በዓለማችን የፖለቲካ መድረክ የተለመደ ተግባር ነው። እርግጥ፥ እውነት ሲባል ከልበ ወለድ ይልቅ እንግዳ ነገር ነው። በመሆኑም፥ አንዳንድ ጊዜ የምንሰውማው ነገር ለማመን ስለሚያቅተን እውነት እየተነገረንም (ብዙዉን ጊዜ ከቅንነት የተነሳ) እውነቱን ለማመንና ለመቀበል ስንቸገር እንስተዋላለን። ኢየሱስ ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፥ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም (የዮሐንስ ወንጌል 3፥ 12) ያለበት ምክንያትም ተመሳሳይ ችግር ስለገጠመው ነበር። ጠ/ር ዐቢይ አህመድና ሌሎች በርካታ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለጠ/ር ዐቢይ አህመድ ያላቸው ድጋፍ ለመግለጽ በመስቀል አደባባይ በተገኘው ህዝብ ላይ የተወረወረው ቦንብ ሁላችን የምናስታውሰው አሳዛኝ ክስተት ነው። የድርጊቱ ፈጻሚ በተመለከተ፤ ጠ/ር ዐቢይ አህመድ ደቂቃዎች ሳያባክኑ ያለ አንዳች ተጨባጭ መረጃና ምርመራ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በገደምዳሜ ቋንቋ የተቆሙን ሲሆን፤ የቀድሞ ህወሐት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት የደህንነት የብሔራዊና መረጃ ደህንነት ሹም ጌታቸው አሰፋ አቀነባባሪነት፣ አመራርና የፋይናንስ ድጋፍ ሰጪነት የተፈጸመ ወንጀል መሆኑን ደግሞ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በምርመራ እንደደረሰበት አክለው አስረግጠው ገልጸውልን ነበር። የሚደንቀው፥ እንደ ዓቃቤ ህጉ አባባል ተጠርጣሪው ግለሰብ፤ (ሌላ የፎረንዚክ ምርመራ ውስጥ መግባት ሳይስፈልግ)፥ 1. በእርግጠኝነት ለመናገር ባይቻልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግዛቴ ሥር ነው ብለው በሚያምኑበት በትግራይ ክልል ግዛት ውስጥ ተዘሎ በሰላም መኖር መቻሉ፤ 2. ተጠርጣሪው ግለሰብ በህወሐት ማዕከላይ ኮሚቴ ስራ አስፈጻሚ አባል ሆኖ መመረጡ፤ 3. ተጠርጣሪው ግለሰብ ፓስፖርት ተቀይሮለት ለህክምና በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ባሰኘው ሰዓት ወጥቶ መግባትና መመላለስ መቻሉ፤ 4. የብዙዎች ንጹሐን ኢትዮጵያውያን ዜጎች አካል ያጎደለና ነፍስ የቀጠፈ የወንጀል ድርጊት ጨርሶ እንዳልተፈጸመ እስኪመስል ዘንድ ጉዳዩ በጠቅላይ ሚንስትሩ ዘንድ ክፉኛ መረሳቱ፤
5. ጉዳዩ፥ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጭንቅ ጥብብ ሲለው የኢትዮጵያ ህዝብ ለመዘናጋት አልፎ አልፎ የሚመዘው ጆከር ከመሆን ያለፈ መንግስት ፍንዳታው በተመለከተ በትክክል ወንጀል ተፈጽሟል! ብሎ የሚያምን ከሆነ ወንጀለኛ በፈጸመው ወንጀል በህግ ፊት ቀርቦ ተጠያቂ እንዲሆን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ከተራ ፉከራ ያለፈ ያሳየው ቁርጠኝነት ባለመኖሩ የንጹሐን ኢትዮጵያውያን ዜጎች ነፍስ የቀጠፈና አካል ያጎደለ የሰኔ 16ቱ ፍንዳታ አዲሱ አመራር እንጀራውን ለመጋገር፣ ለማብሰልና ከነተረቱም የወደቀ ዛፍ ምሳር ይበዛበታል እንደሚባለው የህወሐት መሪዎች ባልዋሉበት ነጥሎ ለማስመታት ታስቦ የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት በንጹሐን ወንድም እህቶቻችን ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ የተጫወተው ቁማርና የፈጸመው ወንጀል ነው! የሚለውን የብዙሐኑ ጥርጣሬ እውነት ሊሆን ነው ማለት ነው። ጎበዝ፥ የዐቢይ መንግሥት እንደማንኛውም ዓለማዊ መንግሥት ስልጣኑን ለማደላደል፣ ህዝባዊ ድጋፍና ተቀባይነቱን ለማጠናከር፣ ከመንበረ ሥልጣናቸው የተገፈተሩት በህወሐት መሪዎች ላይ ህዝባዊ ቁጣ ለመቀስቀስና የህወሐት መሪዎች ባልፈጸሙት ወንጀል ብላክ ሜይልና ተጠያቂዎች ለማድረግ በንጹሐን ኢትዮጵያውያን ደምና አጥንት የተሰራ ድራማ ላለመሆኑ ምንም ማስረጃ የለንም። ምናልባትም ከዚህ የተቀናጀ ሴራ ጀርባ ያሉ ባለሥልጣናት አልተሳካላቸውም እንጅ የህወሐት መሪዎች የድርጊቱ ተጠያቂዎች ከማድረግ ያለፈ የዳሚኖ ጌም ጨዋታ ለመጫወት አስበው የሰሩት ስራም ሊሆን ይችላል። በወቅቱ በዙሪያቸው የነበሩ ባለ ሥልጣናት ጠቅላይ አቃቤ ህጉ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ ጨምሮ የአዲሱ አመራር እጅ ያለበትና የተገኘውን ድጋፍ ለማጥበቅ ታስቦ በመንግሥት የተፈጸመ ወንጀል ለመሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም። ይህ ባይሆን ኖሮ መንግሥት ሆነ የሚመለከተው አካል ክስተቱን በተመለከተ የተሟላ መረጃ ለመስጠት ባልተልፈሰፈሰ ነበር።
ጽሑፉ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ ከሚል መጽሐፍ የተገኘ ነው። E-mail: mahbereseytan@gmail.com |