Back to Front Page

እውን ትግራይ "አንድ ሳር ቢመዘዝ..." ናትን?

እውን ትግራይ "አንድ ሳር ቢመዘዝ..." ናትን?

ዮሃንስ አበራ (ዶር)

10-02-20

በአሁኑ ጊዜ ብዛት ባላቸው ግን ከአንድ ስቴንስል የተራባ የሚመስል ፅሁፍ የሚያነቡ የሚመስሉት ሚድያዎችና የድረ ገፅ ፎረሞች 'ኢትዮጵያ ሲቀነስ ትግራይ' (Eth -Tig= United Eth) በሚል የሞኝ ፎርሙላ ላይ የተመሰረተ ትንተና ማቅረብ ከጀመሩ ብዙ ጊዜ ሆናቸው። ይህ አስተሳሰብ ከጥላቻ የተነሳ ብቻ ሳይሆን ለተለማማጅም፣ ለሰነፍም፣ በማያውቀው ጉዳይ በስሜት ለገባውም፣ ከፍርሃት የተነሳ አድፍጦ የቆየና አሁን መስዋእትነት የሌለው ቀላልና ትርፍ የሚገኝበት የፓለቲካ ሜዳ ያገኘ የመሰለው ፓለቲከኛ ነኝ ባይ ሁሉ እንደመዋኛ ገንዳ በደስታ እየዘለለ የገባበት ነው። እንደዚህ አይነት ሰዎችና ሚድያዎች በእጃቸው ይዘው የሚዝናኑበት አስተሳሰብ አሻንጉሊት ሳይሆን የእውነት አገር የሚያጠፋ ፈንጂ መሆኑን ለመገንዘብ የሚያበቃቸው የአእምሮ ብስለት ያላቸው አይመስልም።

Videos From Around The World

አፄ ዮሃንስ ግብፅን ሁለት ጊዜ አሸንፈው የመለሱበት ድርጊት ከኢትዮጵያ ታሪክ በላጲስ ለማጥፋት የሚታገሉ የታሪክ ምሁራንና ፓለቲከኞች ሊረዱ ያልፈለጉት ዋናው ቁምነገር ግብፅ ሁለት ጊዜ ሰራዊት አሰልፋ የመጣችው መቀሌን ለመያዝ ሳይሆን ከትግራይ 700 ኪሎሜትር በላይ የሚርቀውን አባይን ለመቆጣጠር ነበር። ራስ አሉላ የኢጣሊያን ጦር ወሬ ነጋሪ ያሳጡበት  አስታዋሽ ያጣው የዶጎሊ ድልም መቀሌን ሳይሆን የያኔዋን አዲስ አበባን ለመቆጣጠር ዋና አላማ በነበረው ሃይል ላይ የተገኘ ነበር። አፄ ዮሃንስ ከማህዲስቶች ጋር ሲዋጉ ህይወታቸውን ያጡት ከመቀሌው ቤተ መንግስታቸው ጥግ የነበሩት አብያተ ክርስትያናት ስለተቃጠሉና ቀሳውስቱ ስለታረዱ ሳይሆን በወቅቱ ከመቀሌ ለይተው ባላይዋት ጎንደር ከተማ ውስጥ ግፍ በመፈፀሙ ተበሳጭተው ስለነበር ነው። የአሁኑ ትውልድ ስህተት ስህተቷን ሲለቅም ስማቸውን እንኳን በበጎ ማንሳት ይቀፈዋል። በውቅቱ የጎንደር ህዝብ "የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ፣ አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሃንስ" ብሎ አልቅሶላቸዋል። እንደሌሎቹ ጎንደር ራሱን ያውጣ ብለው ችላ ቢሉ ኖሮ ጣልያን የባህሩን ዳርቻ አይቆጣጠርም ነበር። ተጠቃሚዎቹ በውለታቢስነት  መስዋእትነታቸውን ዋጋ ለማሳጣት "የተሰዉት ለሃይማኖታቸው ብለው ነው" እያሉ የአሁኑንና ቀጣዩን ትውልድ መስመር ያስታሉ። መሰረተ ቢስ ጥላቻቸውን ትክክል ለማስመሰል አለም ያወቀውን ታሪክ ሲደፍቁ ይታያሉ።

ማንም የትግራይ ተወላጅ ምንም ቢወዳቸው አፄ ዮሃንስ በክህደት ተበሳጭተውም ቢሆን በጎጃም ላይ የፈፀሙትን ስህተት "እሰይ እንኳን አደረጉት!" የሚል የለም። አፄው ራሳቸው የተቆጩበት ድርጊት እንደነበር ይነገራል። የትኛው ሌላ ንጉስ ነው በህዝብ ላይ በፈፀመው የተቆጨ? ነገስታትን የማሞገስ ፍላጎት ኖሮኝ አይደለም ይህን የምለው። ንግስና አድሃሪና ጨቋኝ ስለሆነ ነው 1966 ህዝባዊ አብዮት የተገረሰሰው። ይህን የሚያናግረኝ የነገስታት መልካምነትና ጀግንነት መመዘኛ የሆነው ለሃገራቸውና ለህዝባቸው የዋሉት ውለታ ሳይሆን አፈኛ ልሂቅ ከበዛበት ብሄር መወለዳቸውና አለመወለዳቸው ነው። ጎጃም ውስጥ የበደል ነገር ከተነሳና ሚዛኑ አንድ ቢሆን ኖሮ አፈወርቅ ገብረየሱስ የአካባቢው ጀግና አፄ ዮሃንስ ግን ጠላት ሆነው መታየት አልነበረባቸውም። በአገሬ  የማልደራደር ጀግና ነኝ እያለ እድሜ ልክ በላይ ዘለቀን በሚያወድስበት ልሳኑና ብእሩ የበላይ ደመኛ የነበረውንና አገሩን ለፋሺሽት አሳልፎ የሰጠው ባንዳ አፈወርቅ ገብረየሱስን የሚያሞግስበትና አፄ ዮሃንስን ከነዘር ማንዘራቸው የሚያወግዝበት እንቆቅልሽ ፍቺው "አገር ስጠኝ" የማይባልበት ግልፅ ነው። የአፄው ወንጀል የሰሜን መሆናቸው ብቻ እንጂ ግፍ ያልሰራ ንጉስ እስቲ በመብራት ይፈለግ! መለስ ዜናዊ ግድብ በቆራጥነት ቢያስጀምር እውቅና ላለመስጠት "ቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ አስበውት ነበር እኮ" ይባላል። ሊዋጋ ያሰበ ተዋግቶ ካሸነፈው በልጦ የሚነሳ ከሆነ እንድንሞገስና ስማችን ለታሪክ እንዲበቃ አሜሪካን ተዋግተን ለማሸነፍ ብናስብ ይሻለናል።

ሁሉ እውቅና መንፈግ፣ እንደ ወንጀለኛና እንደ ባዳ ማየት ከሰሜን የመጣ ሁሉ ሌላ ሰርቶት የማያውቅና እድሉን ቢያገኝም የማይሰራው መጥፎ ድርጊት ስለፈፀመ አይደለም። የሰሜን ህዝብ በኢትዮጵያ ላይ ከሰራቸው መጥፎ ድርጊቶች ይልቅ መልካም ድርጊቶቹ መቶ እጥፍ ይበልጣሉ። በእጅ የተጋረደ አይን ከፊቱ የተደቀነውን ሃቅ ማየትና ማስተዋል አይችልም። የጋረደው እጅም መነሻውና መድረሻው የማይታወቅ ጥላቻ ነው። እኔ ይህን የምፅፈው በእድሜየ በደረሱብኝ አስከፊ በዘር ጥላቻ ላይ የተመሰረቱ ቁጥራቸው የበዛ ተከታታይ በደሎች ላይ ተመስርቼና ይህም ስላነቃኝ ባደረግሁት በቂ የሆነ ሚዛናዊ ክትትል ነው። አንድ የደረስኩበት ድምዳሜ አለ። የሰሜን ህዝብ እንዲህ "ካካ የነካ እንጨት" የተደረገው አገራዊ ስልጣን እንዳይዝ ወይንም እንዳይጋራ ነው። ለዚህ የማሳነሻ መመዘኛዎች ተቀምጠዋል። 1/ቁጥሩ አናሳ መሆኑ; 2/ ለአገራዊ ፋይናንስ ፈሰስ የሚያደርገው አነስተኛ መሆኑ ግን የሚሰጠው በጀት ብዙ በመሆኑ እንደ አክሳሪ ስለሚቆጠር; 3/ የተፈጥሮ ሃብቱ ውስን መሆኑና የረባ አገራዊ ፋይዳ የለውም በሚል; 4/ ህወሓት የፈፀመቻቸው ስህተቶች ብቻዋን እንደሰራቻቸው አድርጎ ከልክ በላይ አግንኖ በማሳየት ከትግራይ የመጣ አስተዳደር ሁሉ አገር አጥፊ ስለሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ ለወደፊቱ ከዛ ለመጣ አመራር ምንም እድል እንዳይሰጥ በከባድና የማያቋርጥ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የህዝቡን አመለካከት እስከ ወድያኛው ማበላሸት፣ 5/ ከትግራይ ህዝብ ይልቅ የኤሪትርያ ህዝብ ለኢትዮጵያ ጥሩ እንደሆነ ተደርጎ ስውር በሆነ ስልት የሚካሄደው ሞራል የሚነካ ጨዋታ የትግራይ ተወላጆችን ከኤሪትርያ አሳንሶ እንዲያይ እያደረገው መሆኑ የሚያሳዝን ነው። እንድገባ በማይፈቀድልኝ ጉዳይ መግባት ብችል የሚታየኝ ነገር ቢኖር ኤሪትርያውያን ኢትዮጵያን ከተጋሩ የበለጠ ይወዷታል ብየ ማሰብ አልችልም፣ ምን መልሶ የሚያስወድድ ነገር ስትሰራላቸው ኖረችና? አይናቸው በትክክል የሚያይ ቢሆን እነሱን ለመገንጠል የገፋፋቸው ጥላቻና በደል በትግራይ ላይ እየተደገመ በመሆኑ ይህን ከታሪክ የማይማርና ጥፋቶቹን እንደ በጎ ምግባር የሚደጋግመው የኢትዮጵያ ፓለቲካን ከማበረታታትና ከማገዝ ይልቅ "አደብ ግዛ; አገሪቱን የሚያጠፋ ተግባር አትፈፅም" ብለው ይመክሩ ነበር።

የቁጥር ወይንም የፐርሰንት ጉዳይ ሲነሳ ቁጥር በየትኛውም አውድ ላይ ብቸኛ ወሳኝነት እንደሌለው ሁሉም በሆዱ ይዞ ግን አውጥቶ ለመናገር ጣረሞትና ጥቃት ይሆንበታል። ስለዚህም 70 ከመቶ የሆነው አማራና ኦሮሞ አንድ ከሆነ ትግሬው ዝሆን ጀርባ ላይ እንደተቀመጠች ገለባ ሆኖ ይታሰባል። ይቺ ገለባ ተሸራታ መሬት ብትወድቅ እንኳ ዝሆኑ ምንም የሚታወቀው ነገር የለም ነው ምስጢሩ። ትግራይ ብትገነጠል የሚመጣ ችግር ቢኖር ወደብ ማጣት ሳይሆን፣ የእርሻ ውጤት እጥረት መፈጠር ሳይሆን መቶ አስር ሚልዮን ስድስት ሚልዮን ሲቀነስ: መቶ አራት ሚልዮን መቅረት ብቻ ነው" ትግራይን እንደቁጥር ብቻ ማየቱ የሚያስከትለው አስተሳሰብ ይህን ይመስላል። በመቶ አስር ሚልዮን ሳሮች የተከደነ ትልቅ ጎጆ ቤት ስድስት ሚልዮኑ ሳር ቢመዘዝ ቤቱ አይፈርስም ማለት ለሚቀላቸው አዎ ቀላል ነው። ስድስት ሚልዮን ሳር ሲመዘዝ ወዲያው ቤት ባያፈርስም በሚፈጠረው ክፍተት የሚገባው ዝናብ ቤቱን ከጥቅም ውጭ እንደሚያደርገው ግን ለማሰብ አቅም የሚያንሳቸው ጥቂት አይደሉም። ትግራይ ባለው ከፍተኛ "አንፈልጋችሁም" አይነት ግፊት ከተገነጠለች ትግራይ ላይ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም፣ የበደል አምላክ ይታደጋታል ብየ ግን አምናለሁ። በኢትዮጵያ ላይ ስለሚፈጠረው ነገር ግን ያኔውኑ ካላዩት ማንም በትክክል መተንበይ አይችልም፣ አይናቸው ከሸፈኑ ተስፈኞች ወይንም ህልመኞች በስተቀር ከዛ በኋላ ኢትዮጵያ ሰላማዊና ታላቅ አገር ሆና ትኖራለች የሚል እምነት ያለው ሰው አለ ብየ አልገምትም። ካለም ጤነኛ ሰው አይመስለኝም። ስለዚህ መፍትሄው ሁሉም እንዳመጣለት አይናገር። ስለ ፓርቲ እያስመሰሉ ህዝብን ማዋረድ፣ መወንጀል ይቁም። ትግራይን እንደ አንድ ሳር መቁጠር  አንድ ሊባል ይገባል። በኢትዮጵያ ውስጥ ስምምነት (consensus) ፈጣሪ ብቸኛ ነገር ህወሓትን፣ በዛው አሾልኮ የትግራይ ህዝብን፣ የኢትዮጵያ አንደኛ ጠላት ማድረግ ነው። ይህ ደካማ በሆነ ክር የታሰረው ጥምረት ክሩ ሲበጠስ (ትግራይ ተገፍትራ ራሷን ከቻለችና ከኢትዮጵያ ፓለቲካ ከወጣች) ምን እንደሚፈጠር እኔ ብነግራችሁ ይሻላል ወይስ ራሳችሁ በነፃ አእምሮ ብታንሰላስሉት? በቀላሉ
ሊፈታ የሚችል ችግርን በግዴለሽነትና በማልናለብኝነት ሲወሰብ ይታያል። ብዙዎቹ የሚመጣው ችግር ህወሓትን ብቻ ነጥሎ እንደሚጎዳና ሌላው ምንም እንደማይሆን አድርገው ማሰብን መርጠዋል። ህወሓት እንዴት በዝግታ እየሞተች እንደሆነ ትንፋሽ እስኪያጥራቸው ድረስ በፌዝ ይናገራሉ። ህወሓት በጥፋትዋ መጠን ተገቢ ህጋዊ ቅጣትዋን ማግኘቷን የሚቃወም ሰው ሊኖር አይችልም፣ የምትቀጣው የትግራይ ስለሆነች ከሆነ ግን የሚቀበለው ሰው የለም። አሁን ግልፅ ነው። ጥያቄው በሚገባ ተመልሷል። የትግራይ ህዝብ ህወሓትን መርጧል? መልሱ አዎ ነው። አሁን ስለህወሓት የምናወራው ወሬ ህዝብ ስለመረጣት ድርጅት እንጂ ስለሽብርተኛ፣ ስለ ሌባ፣ ሰለ ወንበዴ ድርጅት አይደለም። ህዝብ እንደህዝብ መከበር አለበት። ህወሓትን የመረጠው 2.7 ሚልዮን ህዝብ ሮቦት ሳይሆን ህዝብ ነው። ህዝቡ በፍላጎቱ መምረጡን አለመቀበል ይቻላል፣ አልመረጥክምና እንደገና ምረጥ ማለት ግን ምን የሚሉት የፓለቲካ ፈሊጥ ነው? እንደገና ምረጥ ከተባለስ መጥቶ ለመምረጥ የሚሰለፈው ማነው? ትግራይ ለሌላ ምርጫ ያስቀመጠችው ተጠባባቂ የሆነ ሌላ 2.7 ሚልዮን ህዝብ የላትም። በእልክና አጉል ፉክክር የሚከተለው ጦስ ሁሉም የሚሞቀው ሳይሆን ሁሉንም የሚያቃጥል እሳት ያመጣል።

Back to Front Page