Back to Front Page

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሥራ ላይ መዋል በዓይኔና በሕይወት ዘመኔ ማየት እጅግ እጓጓለሁ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ ሥራ ላይ መዋል በዓይኔና በሕይወት ዘመኔ ማየት እጅግ እጓጓለሁ።

Y Bitsue 08-02-20

የመርሆዎቹ መግለጫ (Declaration of Principles) በ2015 ከወጣበት ማግስት ጀምሮ አቅሜና እውቀቴ በፈቀደልኝ መጠን ለበርካታ ዓመታት ጎጂ ነገር በእንት አገራችን ላይ በችኮላና በራስ ጥቅም እንዳይፈጸም አጥብቄ እወተውት እንደ ነበርኩ ይታወቃል።

ዛሬ የህዳሴ ግድቡ በተያዘለት ዕቅድ 4. 9 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ መሞላቱ ስሰማ እንደ ዜጋ ደስ ብሰኝም፤ ከደስታየ ስጋቴ እንደሚያይል ግን ሳልገልጽ ለማለፍ ህሊናየ አይፈቅድልኝም። የምን ስጋት ነው? ተብየ ምናልባት ልጠየቅ እችላለሁ። ስጋቴ አንድ ሳይሆን በዛና ጠጠር ያሉ በርካቶች ናቸው። ቀጥሎ እነዚህ ስጋቶቼ በዝርዝር ለማቅረብ እሞክራለሁ።

መለስተኛ ስጋቶቼ

Videos From Around The World

1)   አጠቃላይ የሙሌቱ ዓመታት ከ 4 አስከ 7 ዓመት ድንገት ወደ 9 አስከ 12 ከፍ ማለት፦

 

2)   የተርባይኖቹ ቁጥር ከ 16 ወደ 13 መቀነስ፤ ይህ የሚመነጨው ኃይል ከ 6450 ወደ 3500 ሜጋ ዋትስ ዝቅ የሚያደረገው ከመሆኑ ባሻገር አራት የተከዘ የኃይል ማመንጫ እንዲታጣ የሚያደርግ ነው። ተርባይኖቹ በመቀነሳቸው ሳቢያ የሚቀንሰው የኃይል መጠን 2 ሺህ ሜጋ ዋትስ የሚጠጋ መሆኑ ልብ ይሏል።

 

3)   አሃዱ ተብለው የሚሞከሩት ሁለት ተርባይኖች የመመኮሪያ ጊዜአቸው ድንገት ባልታወቀ ምክንያት ከሚቀጥለው ሕዳር ወር ወደ መጪው ሰኔ መስፈንጠሩና እንዲዘገይ መደረጉ፦

 

እነዚህ ከላይ በቁጥር ያቀርክዋቸው ስጋቶች መለስተኞ ስጋቶች ናቸው። ዳሩ ግን ቁልፍና ቀዳሚ ስጋቶቼ እነዚህ አይደሉም። ይልቅስ ተደራዳሪዎቻችን ከድርድሩ 90% እንደተጠናቀቀና፤ ይሁንና ቀሪው 10% ካለቀወ 90% በጣም አወዛጋቢነ አዳጋች እንደ ሆነ ገልጸውልን እንደ ነበር ይታወሳል።

ለመሆኑ በአሜሪካ አደራዳሪነትና ከዚያ በፊት በሦስቱ ሃገራት መካከል እልባት ካላገኙት በመቶኛ በጣም ትንሽ፤ ነገር ግን አዳጋች 10% የድርድር ነጥቦች ይዘታቸው ምን ይመስል ይሆን? በመርሆቹ መግለጫ (DoP) ሰነድ ኢትዮጵያ ለታህታይ ተፋሰስ ሃገራት ማለትም ለግብጽና ለሱዳን significantly harmful ያልሆነ ወይም የማይጎዳ ውሃ መጠን በግርድፉ ወይም በጥቅሉ ለመስጠት እንደተስማማች ይታወቃል። ችግሩ የጀመረው ከዚህ ስምምነት በኋላ ነው የሚል እምነት አለኝ። ስምምነቱ በ2015 ሲፈረምም ደስተኛ አልነበርኩም። በዚህ ወቅት በመሪነት የነበሩት አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ቴድሮስ አድሓኖም ደግ መሠረት አልጣሉም ብየ ልወቅሳቸው በቂ ምክንያት አለኝ።

ዒላማቻውንና የመጨረሻ ግባቸው አርቀው በማየት ያነጣጠሩት ግብፆች በቴክኒክ ቡዱኖች መካከል በሚደረገው ድርድር የማይጎዳው ወይም significant harm የማያደርሰው የውሃ መጠን በአሃዝ ምን ያክል እንደ ሆነ መታወቅ አለበት ብለው ወጥረው የያዙት ገና ከጥዋቱ ነበር። እንዲያ መጠየቃቸው ባህሪያዊና የተገባ ነው፤ ዳሩ ግን ወደ ግብቸው ሊያደርሳቸው የሚችል መረማመጃ ቀዳሚ ውጤታማ እርምጃ ነበርና።

በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዲሉ፤ ጠ/ሚ አብይ አሕመድ ካይሮ ሄደው በአልሲሲ በማያዉቁትና በማይረዱት ቋንቋ ወላሂ አንጎዳችሁም! ብለው መማላቸው በዲክላረስዮን ኦቭ ፕርንሲፕሊስ ወይም የመርሆቹ መግለጫ ላይ የማይጎዳ የውሃ መጠን እንሰጣለን ለሚለው ተጨማሪ የማቀጣጠያ ነዳጅ ጨምረውበታል።

ግብፆች አጥብቀው የሚያነስዋቸውና፤ አሁንም መልኩን በማቀያየር የሚያቀርብዋቸው ማነቆ ሆነው አላላውስ ያሉትና ከ 10% በታች ሆነው እልባት ያላገኙት ምጉቶች የሚከተሉት ሦስት ሲሆኑ ዋናዎቹ ወይም ቁልፍ ስጋቶች የሚቀሰቅሱ ናቸው።

 

1)   በድርቅ፤ በተከታታይ ድርቅና በደረቅ ዓመት ግድቡ በምን መልኩና እንዴት መሞላት እንዳለበት፦

 

2)   ከድርቅ፤ ከተከታታይና ከደረቅ ዓመት በኋላ ግድቡ እንዴት መሞላት እንዳለበት (Re-filling of the dam)

 

3)   ኢትዮጵያ ከግድቡ በላይ በአባይ ተፋሰስ ላይ የልማት ፕሮዤ ማካሄድ ለባትም የሚል ሲሆን፤ ይህ የኢትዮጵያን ልዓላዊነቷን የሚጋፋና ጸጋዋ ለመጠቀም እንዳትችል የሚከለክል ነው።

 

ሁሉም መንገዶች ወደ ሮማ ያደርሳሉ እንዲሉ፤ ግብፆች ሄደው ሄዴውና ወድቀውና ተላልጠው ማግኘት የሚሹት ግዱን ምክንያትና ተገን አድርገው፤ ኢትዮጵያ ከኃይል ማመንጫው ውጭ ገባር ወንዞችዋ ለልዩ ልዮ ልማቶች እንዳትጠቀም ማድረግ ነው።

ኢትዮጵያዊያን የቴክኒክና የሕግ ባለሞያ ቡዱኖች በአሜሪካ አደራዳሪነት እንዳይፈርሙ ያደረግዋቸው አብይትና አስቸጋሪዎቹ ከ10% የማይበልጡት የድርድር ነጥቦች ከሞላ ጎደል እኚሁ ናቸው። እንዲህ በማድረጋቸው ሁለቱም የቡድኑ አባለት የዜግነት ሃላፊነታቸውና ሞያዊ ግዴታቸው በታማኝነትና በቅንነት ፈጽመዋልና ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።

ከዚህ ቀጥሎ ግን ኳሷ ከእነርሱ ወጥታ በመርሆች መግለጫዎቹ (DoP) አንቀጽ 10 መሠርት ወደ መራሄ መንግሥታቱ እጅ ስለምትገባ የኛው መራሄ መንግሥት ምን እንደሚወስኑና እንደሚፈርሙ ስላማይታወቅ ስጋቴ ግብዴ ነው።

ግብጾች ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ልማት እንዳታካሂድ እየተጠቀሙበት ያለ አዲስ የረቀቀ ስልት ማወቅ ያስፈልጋል። በድርቅ፤ በተከታታይ ድርቅና በደረቅ ዓመት ኢትዮጵያ ከግድብዋ መልቀቅ የሚገባት ድረድር በማመክነይና፤ ኢትዮጵያ ከግድቡ በላይ ለልማት በየ ዓመቱ ከተጠቀመች ግድቡ ላይ የሚደርሰው ውሃ significantly መቀነሱ የማይቀር ነው።

ግብፆች ድርቅ፤ ተከታታይ ድርቅና ደረቅ ዓመት የሚሉት ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሰማይ ተዘግቶባትና ዝናብ ነስቶታ የሚጠፋውና የሚቀንሰው ውሃ ብቻ ሳይሆን፤ በልማት ይሁን በፈለገው ጠንቅ ወደ መከረኛው ግድብ የሚገባው ውሃ ከቀነሰ፤ ኢትዮጵያ ቀድሞ ካጠራቀመችው ጋንዋ ቀንሳ እነርሱ ይህ ያክል ውሃ በዓመት መልቀቅ አለብሽ ብለው ሊያስፈርምዋት ነው።

ኢትዮጵያ በዚህ ውል ከተስማማችና ከተፈራረመች ከፊት ለፊትዋ ከሚቀርቡላት ሁለት የጎመዘዙና የመረሩ ፅዋዎች አንዱ መጎንጨት ግድ ሊላት ነው። አንድም በአባይ ገባር ወንዞችዋ ላይ ምንም ልማት ሳታካሂድ እጆችዋን አጣምራና እግሮችዋን አመሰቃቅላ የሚፈሰውን አባይ እያየች ቁጭ ማለት፤ ያለበለዚያም ልማቱ እያካሄደች፤ በልማቱ ሰንክ ወደ ግድቡ ይገባ የነበረው የሚቀንሰውን ውሃ አምስት ወይም ስድስት ወይም ጌታ አይበለውና ከዚያም በላይ ተርባይኖችን አቁሞ ውሃው ከግድቡ መልቀቅ ነው።

እነዚህ በእውን ስጋቶች ካልሆኑ ስጋት ከቶ ምን ሊሆን ነው? እነዚህ ስጋቶች በጫንቃ ላይ ተሸክሞስ ስለ መጭው ያለ መጨነቅ እንዴት ይቻላል?

ከእኔ በላይ የቴክኒክና የሕግ ቡድኖቻችን ፍሬ ጉዳዩን በዝርዝር በልተውና ተንትነው ስለሚያውቁት ጉዳዩ እንቅልፍ እንደሚነሣቸውና እንደሚያሣስባቸው አያጠያይቅም። ይሁንና ይህ ሁሉ አሳሳቢና አነጋጋሪ ጉዳይ በእናት አገር በቅርበት ተደቅኖባት ባለበት ወቅት ሁሉም እንዳለቀ አድርጎ በመቁጠር ጮቤ መርገጥና ከበሮ መደለቅ የተገባ አይመስለኝም።

ሲጠቃለል በዘንድሮው የግድቡ የውሃ ሙሌት ደስተኛ አይደለሁም ማለቴ ያይደለ፤ የኢዩቤልዩ የፌሽታ የመለከት ድምጽ ተነፍቶልን በሆታና በዕልልታ እንኳን ደስ አለህ/አለሽ/አላችሁ/አለን የምንባባልበት ጊዜና ሁኔታ ላይ አይደለንም። አሁን ብዙ ስጋትና ውጥረት የነገሰበት እንጂ እርግጠኝነትና ዋስትና አለ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገር የሚቻልበትና በደስታ አደባባይ ወይም ሻምፓኝ በምንራጭበት ፖዲየም ላይ እንዳይደለን መግለጽ ያስፈልጋል።

ውጤቱ በጎ ይሁን ክፉ መሆኑ የሚታወቅበት ጊዜ ቅርብ እንደ ሆነ የወቅቱ አደራዳሪ የአፍረካ ሕብረት ለተደራዳሪዎቹ ሃገራት ይፋ እንዳደረጉና በዚህ ድርድር መስማማት ወይም እልባት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል፤ የተባባሩት የዓለም መንግሥታትም ጉዳዩን በጽሞናና በአጽንኦት እየታከታተለው እንዳለ አስታውቆዋል።

በዚህ ድርድር በአሜሪካ እንደ ተደረገው ድርድር አልስማማም ወይም አልፈርምም ብሎ የሚወጠባት ዕድል ያለ አይመስለኝም። ምንም እንኳን ይሄ ድርድር እንጂ የፍርድ ቤት ክርክር ባይሆንም፤ እንደ የአልጀርሱ የፍርድ ውሳኔ ሳይስማሙና ሳይፈራረሙ መውጣት የሚቻል አይደለም። ውጤቱ ለመስማት የቀሩን ቀናት ጥቂት ናቸው፤ ጊዜ ምን እንደሚያመጣልን ወይም እንደሚያመጣብን ስለማናውቅ የሚሆነውን ለመስማት በምጥ ላይ ነን። ዘንቢል የተላያዩ ቁሳቁሶች ጠቅልሎ እንደሚይዝ፤ ምጥም ህመምን (pain)፤ ስጋትንና ደስታን አፈራርቆ እንደሚይዝ ዘንቢል ነው።

ጆሮ በመስማት አይሞላም፤ ዓይንም በማየት አይጠግብም። አዎ የዚህ በጉጉት ልንሰማው የምንፈልገው ዜና ለመስማት የጆሮአችን ቀዳዳ ከዚህ በፊት በሰማው አልሞላምና ውጤቱ ምን ይሁን ምን፤ አሰይ ልንል ወይም ዎዮ ጆሮአችን በቂ ከበቂም በላይ ያልተሞላ ቅዳዳ አለው። ብቻ ጌታ የነጌ ሰው ይበለን።

ሰላም ለኢትዮጵያና ለመላ ሕዝቦችዋ እንዲሁም ለእያንዳንዱ ዜጋ!!!

 

Back to Front Page