Back to Front Page

ብርሃነ ንርአ፤ መነጋገር መልካም ነው

ብርሃነ ንርአ፤ መነጋገር መልካም ነው

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 03-21-20

ብርሃነ ንርአ የተባሉ ፀሃፊ በዓይጋ ፎረም ላይ በ11/07/2012 ላይ ባወጡት ፅሁፍ የትግራይ ህዝብ በመስመርና በህወሓት እንጂ በመሪዎች ላይ ተማምኖ እንደማይኖር አስምረውበታል፡፡ ክርክር እናድርግበት የሚለው ግብዣቸውም ተመችቶኛል፡፡ የራሱን አመለካከት የሚገልፅ ፀሃፊ አመለካከቱ የመንግስት አዋጅ አድረጎ አለማየቱ ትልቅነት ነው፡፡ እንደ ባህል ሆኖ የተለመደው ነገር የራስን ብቻ መወርወርና ምንም አይነት አስተያየት ያለመጠበቅ ነው፡፡ ብርሃነ በከፈቱት የክርክር በር ሰተት ብየ ለመግባት የተበረታታሁትም ለዚህ ነው፡፡ በፅሁፈዎ ላይ የምስማማባቸውም፤ የማርማቸውም፤ አጥብቄ የምቃወማቸውም ጉዳዮች አሉ፡፡ በምስማማባቸው ሃሳቦች ልጀምርና ማንም ህዝብ ለሰላሙና ለእድገቱ የሚበጀው ቀና መንገድ ለይቶ እሱን መከተል እንጂ ልምራህ ያለውን ሁሉ ተከትሎ መሄድ አዋጪ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ሊሆን ይችላል፡፡ መሪዎች በቀደዱላቸው ቦይ የፈሰሱት ሁቱዎች አንድ ሚልዮን ወገናቸውን አርደዋል፡፡ መሪውን የተከተለ የጀርመን ህዝብ ለጀርመን ውድመትና ለ50 ሚሊዮን የአለም ህዝብ ሞት ምክንያት ሆኗል፡፡ መሪውን የተከተለ የፒፕልስ ቴምፕል አማኝ ደቡብ አሜሪካ ደን ውስጥ በእምነትና በየዋህነት በመርዝ አልቋል፡፡ ሌላም ብዙ ተመሳሳይ ክስተቶች መጨመር ይቻላል፡፡

Videos From Around The World

ብርሃነ እንደገለፁትም ኢትዮጵያን ከውጭ ወራሪ ማደን የሚል መርህ ሳይሆን ጌታችን አፄ ዮሃንስ ወደመሩን ውጊያ እንሄዳለን በሚለው መንፈስ ስለሄደ ሰራዊቱ መተማ ላይ ያሸነፈው ጦርነት ወደ ሽንፈት ተቀየረ፡፡ አፄ ዮሃንስ በግልፅ የሚታወቅና የተዘጋጀ አልጋ ወራሽ እንዳልነበራቸው ግልፅ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የተዳራጀ የሚኒሊክ ሃይል ባይኖር ኖሮ የአውሮፓውያን ሃይሎች መጫወቻ ትሆን እንደነበር የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ዳግማዊ ሚኒሊክም የሚተካቸው ጠንካራ መሪ ባለማዘጋጀታቸው ከህልፈታቸው በኋላ የተፈጠረው የቤተመስግስት ሽኩቻና ጦርነት ለሃገሪቱ ጎጂ ሆኖ አልፏል፡፡ አፄ ሃይለስላሴም ቢሆኑ በሰማኒያ ሁለት አመት እድሜ ዙፋናቸውን የሚወርስ ጠንካራ ሰው ባላዘጋጁበት ከሳቸው በኋላ አገሪቱ ምን ልትሆን ነው ብለው ሲያስቡ እንደነበር ማወቅ አልተቻለም፡፡ የተሰማው አንድ ወሬ ግን እጅግ የሚዘገንን ነበር፡፡ ነጉሱ ከኔ በኋላ አስከ ሰኮና ድረስ የሚያጠልቅ ደም ይፈሳል ብለው ትንቢት ተናግረዋል ተብሎ ያኔ ከዙፋን የወረዱ ሰሞን ሲወራ ነበር፡፡ እውነትም እሰከ ሰኮና ሳይሆን እስከ ጉልበት የሚያጠልቅ ደም ፈሰሰ፡፡ ከራሳቸው የማይወርድ ክፉ ትንቢት ከመናገር ያ እንዳይመጣ አቅሙ እያለ ጥረት ማድረግ ይመረጥ ነበር፡፡ መንግስቱ ሃይለማሪም ከሱ በስተቀር ኢትዮጵያ ሌላ መሪ ሊኖራት እንደማይገባ ገና ከማለዳው ነበር የወሰነው፡፡ አንዲት ኢትዮጵያ አንድ መሪ፤ ያ መሪ መንግሰቱ ብሎ የሱ ቢጤ የነበረው ካውንዳ በ1979 የመንግስቱን ፐሬዚደንትነት ለማብሰር ተሰብሳቢውን ሲያስጨበጭብ ያለኔ ሌላ አታምልኩ ያለው አምላክ ነበር ወይስ መንግስቱ ብለን እንድንጠራጠር አድርጎናል፡፡ ኢትዮጵያን እወዳለሁ ሲል የነበረው መንግስቱ ገና ከጅምሩ ዘመናዊ አስተዳደር ያስተዋወቁትን ሚኒስትሮች፤ አገሪቱን ከወራሪ ሲጠብቁ የነበሩት የጦር አዛዦች በአንድ ሌሊት ፈጀ፡፡ ከዛ ቀጥሎም አብረውት የጀመሩ ግን ለኢትዮጵያ ከሱ የተሻለ ህልም የነበራቸውን መኮንንች አንድ በአንድ ለቀማቸው፡፡ ደርግ ከመንግስቱ በፊት ጀመረ እንጂ ከመንግስቱ በላይ ሆኖ አልዘለቀም፡፡

ህወሓትም ብርሃነ እንደሉት ከመለስ ዜናዊ አመራር በፊት ብትመሰረትምና መለስን ብታፈራም መለስ ባይኖር ከትግራይ ውጪ ያጋጠማትን ፈተና ልትወጣ አትችልም ነበር፡፡ የጋራ አመራር ነበረን የሚለው ተረት ነበር፡፡ የመለስ ህልፈት የህወሓት የቁልቁለት መንግድን እንዳስጀመረ ለምን በቅንነነት አይታመንም፡፡ እንደሌሎቹ የኢትዮጵያ መሪዎች መለስም የሚተካውና ከሱ የሚበልጥ መሪን አላዘጋጀም ነበር፡፡ አንድ አስተማሪችን በአንድ ወቅት ሲናገሩ የምናስመርቃቸው ከኛ ካልበለጡ፤ እነሱም ከነሱ የሚበልጡትን ካላስመረቁ አገር ወደ ኋላ እንጂ ወደፊት ልትሄድ አትችልም ብለዋል፡፡ ስልጣን ላይ የወጡ መሪዎች የነሱ የስልጠን ዘመን ብቻ ወርቃማ ዘመን ተብሎ እንዲጠራ ይሻሉ፡፡ ሙጋቤ የዚምባብዌን ህዝብ ከኢያን ስሚዝ ነፃ አውጥተው የራሳቸው ባሪያ አደረጉት፤ በቁማቸው የሙት መንፈስ እስኪሆኑ ድረስም እኔ ካልገዛሁ ብለው አገሪቱን ምስቅልቅል ውስጥ አስገቧት፡፡ ህወሓትም እንደ ሙጋቤ ከደርግ ነፃ አውጥታ የትግራይን ህዝብ የራሷ ባሪያ አደረገችው፤ ሌላ እንደይደርስበትም አጠረችው፡፡

ስለ ሌላው አገር ባላውቅም የኢትዮጵያ መሪዎች አንዳቸውም ሳይቀሩ የሚተካቸውን ከነሱ ያነሰ ሳይሆን ከነሱ የበለጠ ሰው አዘጋጅተው ከህዝብ ጋር ሲያስተዋውቁ አይቆዩም፡፡ ይልቁንም የሚወዳደራቸው የሚመስላቸው ሰው ራሱን ብቅ ባደረገ ቁጥር ያላደረገውን አደረገ በማለት ስሙን ከማስጥፋት አልፈው ለእስርና ለሞትም ሊዳርጉት ይችላሉ፡፡ ይህን የሚያደርጉ መሪዎች እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንደምትለው እንስሳ የህዝብን የወደፊት እጣ በማስተካከል ላይ ጊዜያቸውን አይባክኑም፡፡ ለዚህ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተንገራገጨ ሽግግር ኖሮ የማያውቀው፡፡ ለዚህ ነው አገሪቱ ሁል ጊዜ ወደኋላ እየተመለሰች ከዜሮ የምትጅመረው፡፡ ይህ ማለት ግን መልካም መንገድ የሚያሳዩ፤ የነሱ አመራር ባይኖር አገር መስመር ስታ ልትሄድ የምትችልበት አጋጣሚዎች አልፈዋል፡፡ ያለ ቴዎድሮስ፤ ያለዮሃንስና ያለሚኒሊክ አመራር ኢትዮጵያ የቅኝ ዢዎች ሲሳይ ልትሆን ትችል እንደነበር ማንም አይስተውም፡፡ እነማንዴላ፤ እነጁልየስ ኔሬሬ፤ እነኑክሩማ፤ እነጋንዲ፤ እነ ዋሺንግተን፤ እነሩዝቬልትና እነ ቸርችል ህዘባቸውን ከድል ወደ ድል ያሸጋገሩ መሪዎች ናቸው፤ ፓርቲዎች ነበሯቸው የነሱ ሰበእና ግን ከፓርቲዎቼ በላይ ነበር፡፡፡፡

ወደ ህወሓት መሪዎች ጉዳይ ስንመጣ መሪዎቹን ከህወሓት ለይቶ ማየት የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ በህወሃት ውስጥ የውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ ባህል ባለመኖሩ አመራሩ ስልጣኑን ከስር ጀምሮ እንደ ርስተጉልት ቆጥሮ የኖረ ነው፡፡ ብታጠፋ የማትቀጣበት ብትዘርፍም ከሃላፊነት የማትነሳበት አሰራር ለብዙ አመታት ሰፍኖ ቆይቷል፡፡ ህወሓትና አመራሩ ተለይተው ሊታዩ የሚችሉት በመቶሺዎች የሚቆጠሩት የድርጅቱ አባላት አመራሩን የመቆጣጠርና ሲያጠፋ እርምጃ የመውሰድ አቅምና ፍላጎትም ሲኖራቸው ነው፡፡ አባላቱ አመራሩ ለላቀ ህዝባዊ አላማ እንዲተጋና በወጣት ሃይል እንዲተካ በአመራሩ ላይ የበላይነት ይዞ ውሳኔ ሰጪ ከመሆን ይልቅ አሁን በሰሩት ሳይሆን የትግል ሜዳ ጀብዳቸው እያዳነቀ አማልክት እንደሆኑ ያህል ሲያመልካቸው ይኖራል (ይህንን ሃቅ በርሃነ ከኔ በበለጠ አገላለፅ አስቀምጠውታል)፡፡ ይህ የሚያመለክተው የህወሓት አመራርና ህወሓት በቲዎሪ እንጂ በተግባር የተለያዩ እንዳልሆኑ ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ እስካሁን ድረስ የተማረውና አይምሮው ውስጥ ገብቶ የሚነዳው ነገር ቢኖር ህወሓት ሳትሆን አመራሮቹ ናቸው፤ አመራሮቹ ደግሞ ህወሓት ናቸው፡፡ ደብረዮን እንዲህ አለ፤ ጌታቸው ረዳ ልክልካቸው ነገራቸው፤ አቦይ ስብሃት ነገሩን አፈረጡት እያለ ስለመሪዎቹ በከፍተኛ አድናቆት መናገር እንጂ ጌታቸው ሲናገር ህወሓት እንዲህ አለች የሚል የለም፡፡ ለዚህም ነው የትግራይ ህዝብ የኑሮ ተስፋው መሪዎቹ በተናገሩ ቁጥር የሚለመልመው ወይንም የሚረግፈው፡፡ ለዚህም ነው በነባር መሪዎች የስልጣን ቀናኢነት የተነሳ ጠንካራ ወጣት ተተኪ አመራሮች አለመምፍለቃቸውን እያየ ህዘቡ በመሪዎቹ እድሜ መግፋት ጭንቀት ውስጥ የሚገባው፡፡ ለዚህም ነው አመራሩ ከፌደራል መንግስት ስልጣን ሲወገድ የህወሓት ፍፃሜ የሆነ ያህል እየታሰበ ያለው፡፡ የህወሓት ህልውናና ጥንካሬ የሚለካው መሪዎቿ በፌደራል መንግስት ስልጣን መያዝ አለመያዝ የሆነ ይመስላል፡፡ ህወሓት እንደ ድርጅት ከአመራሩ የላቀ አቅም ቢኖራት ከፌደራል መንግስት ስልጣን መወገድ ፀጉሯን ሊነካት አይገባም ነበር፡፡ ህወሓት እኮ ተፈጥራ ያደገችው ለትግራይ ህዝብ ነበር፡፡ ህወሓት እንደ አመራር ሳይሆን እንደ ድርጅት የበላይነት ቢኖራት ኖሮ የአመራሩ ከአዲስ አበባ ወደ ትግራይ መመለስ መሰረታዊ አላማዋን የበለጠ የሚያሳካ አድርጋ እንደ ምርቃት ትቆጥረው ነበር፡፡ ሃቁ ይህ አይደለም፡፡ ህወሓት ማለት የአመራሮቹ ስሜት ናት፡፡ አመራሮቹ ከፌደራል መንግስት ስልጣን በመነሳታቸው ድርጅቷ ከመሰረቷ ተናወጠች፡፡

ብርሃነ በመሪዎች ሳይሆን በመስመር መመራት ስላሉት ጉዳይ ብዙ የሚያነጋገር ነገር አለው፡፡ ህዝቡ ራሱ እንደ ህዝብ ነድፎ ያፀደቀውው መስመር አለው ነው የሚሉኝ ወይስ ህወሓት እንደማንኛውም ፓርቲ በርእዮተ አለሟ ላይ የተመሰረተውን መስመር ማለቶ ይሆን፡፡ የአንድ ህዝብ ዘላቂ መስመር ራሱን የቻለና ጊዜ የማይሽረው ነው፡፡ የዩኤስ አሜሪካ ህዝብ የራሱ የሆነ ቋሚ ቪዥን አለው፤ ዴሞክራት ቢመጣ ሪፓብሊካን ቢመጣ እንዲቀይረው የማይፈቀድለት፡፡ የትግራይ ህዝብም ከህወሓትና ከሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች በላይ የሆነ፤ ፓርቲዎቹ ምንም የርእዮተ አለም ልዩነት ቢኖራቸውም ህዝባዊ ህልሙን የማስፈፀም ግዴታ አለባቸው፡፡ ፓርቲዎች ስልጣን ላይ ሲወጡ ሊለያዩ የሚችሉት ያንን ህዘባዊ ህልም እውን ለማድረግ በሚጠቀሙበት ስትራተጂ ተግባራዊነት ብቻ ነው፡፡ ፓርቲ እኩል ይሆናል የህዝብ ሚሽን የሚባል የሂሳብ ስሌት የለም፡፡ ብርሃነ ህዘባዊ መስመር ያሉት አሁን ቀደም ብየ የጠቀስኩት ከሆነ መልካም ነው፤ግን ጥያቄው እንዲህ አይነት የህዝብ መስመር እውን አለ ወይ ነው፡፡ በቅርቡ በአይጋ ፎረም ላይ ባወጣሁት ፅሁፍ አቶ ሰብሓት ነጋ የትግራይ ህዝብ እጣ ፈንታውን ራሱ ይወስናል ባሉት ላይ ትችት ቢጤ ፅፌ ነበር፡፡ የትችቴ አንኳር ህወሓት የትግራይ ህዝብ እጣ ፈንታውን ራሱ እንዲወስን የሚያስችለው አቅም አልገነባችለትም የሚል ነው፡፡ ከፓርቲ ፖለቲካ በላይ የሆነ የህዝቡ ህልም የተዘጋጀ አለ ብየ አላምንም፡፡ የህወሓት ህልም የህዝቡ ህልም እንዲሆን ተደርጓል፤ ይህ ደግሞ አደገኛ ነው፡፡

የብርሃነ ፅሁፍ መነሻ 50 ከመቶ የህወሓት አመራሮች ወደ ብልፅግና ፓርቲ ገቡ የሚለው ሪፖርት ነው፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ ጉልህ የሆነው ስሜታቸው የተገለፀው ወደ ብልፅግና ገቡ የተባሉት አመራሮቹ መራራ ወይኖች ናቸው በሚል ነው፡፡ የብርሃነ ፅሁፍ ወደ ብልፅግና ፓርቲ የገቡ የህወሓት አመራሮችን እንድ ሳር ቢመዘዝ ናቸው ብሎ የሚያቃልላቸው ይመስላል፡፡ እኔ በብልፅግና ፓርቲ አመሰራረት ላይ በጣም የከረሩ ትችቶች ስፅፍ ቆይቻለሁ፤ ይህ ብልፅግና ፓርቲን በመጥላት አይደለም፡፡ ማንም ሰው ሆነ ቡድን ፓርቲ የመመስረት መብቱ የተከበረ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ የኔ ትችት አካሄዱ ህግን የተላለፈ ነው በሚል አመለካከት ላይ የተመሰረተ ነበር፡፡ ከህወሓት ጋር አብረው በሙስና የተጨማለቁና የአስተዳደር በደል የፈፀሙ ሌሎች የኢህአዴግ አባል ፓርቲዎች ሁሉም ነገር ህወሓት ላይ ከምረው እንደ ፒላጦስ እጃቸውን ታጥበው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ገብተው ተሰውሩ የሚል ጭንቀትም ስለነበረብኝ ነው፤ አገሪቱን ከራሱ ከተኩላው ይልቅ የበግ ለምድ የለበሰ ተኩላ አዘናግቶ ሊያጠፋት ስለሚችል፡፡ ነገሩን በፅሞና ሳስበው በኢሰፓ ያላየሁት፤ በኢህአዴግ ያላየሁት የፖሊቲካ ብፁእነት ከብልፅግና ፓርቲ መጠበቄ ነበር ችግሩ፡፡ የፖለቲካ ጨዋታ ህጉ በየትኛውም ቦታና ጊዜ አንድ አይነት ነው፤ ሳይቀድሙህ መቅደም! በዶር. አቢይ አህመድ የሚመራው የፖለቲካ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያ መንግስት ስልጣን የጨበጠና ጦር ሃይሉንና ፋይናንሱን የሚያዝ ነው፡፡ ዶር. አቢይን ማየት የነበረብኝ እንደ ማንኛውም መደበኛ ማኪያቬሊያዊ ፖለቲከኛ እንጂ እንደ ክርሰቶስ አልነበረም፡፡ የብልፅግና ፓርቲ በህወሓት ላይ እየተጠቀመ ያለው የማዳከም ዘዴ ህወሓት ራሷ ስትጠቀምበት በነበረውና ለሌሎችም ባስተማረችው ዘዴ ነው፡፡ ከህወሓት በኩል የሚጠበቀው አንዴ የፖለቲካ ጨዋታውን የበላይነት ካጣች በኋላ (ያጣችውም በራሷ ማናለብኝነት ነበር) ከመራራ እውነታ ጋር በመስማማት አካሄድን የማስተካካል ብስልነት ነው፡፡ በተቃራኒው ግን ህወሓት ህጋዊ ይሁን ህጋዊ ያልሆነ መንገድ ተጠቅመው ሊያጠፏት ከቆረጡት ሃይሎች ጋር የያዘችው ግብግብ መደበኛ የሆነው የፖለቲካ ስልት የጎደለው ነው፡፡ በረቀቀ የፖለቲካ ስልት እየመጣባት ያለውን ሃይል ወታደራዊ አቅም በማሳየት ልትገድበው ትሞክራለች፡፡ በዙሪያዋ ቀለበታቸውን እያጠበቡ በሄዱ ቁጥር ህወሓት የምትደጋግመው ነገር ቢኖር ህግ ይከበር ነው፡፡ ህግና ፖለቲካ በየትኛው አለም ተገደው እንጂ ወደው ተስማምተው አያውቁም፡፡ ጄኔራሎቹ ይህ የፖለቲካ ምስቅልቅል በትግራይ ህዝብ ላይ የሚያስከትለው ጦስ ምን እንደሆነ ሳያስቡ ትግራይ ላይ ጦርነት ቢጀመር ቀላል ጦርነት አይሆንም የሚሉት በህዝብ ጥፋት የግል ዝና ግንባታ ታክሎበት የትግራይ ህዝብ በጦርነት ስጋት ተወጥሮ ይገኛል፡፡

የጀግንነት ዋናው መመዘኛ በግትርነት ቆሞ ማለቅ ሳይሆን ጊዜና ሁኔታን እያገናዘቡ አካሄድን ማስተካከል ነው፡፡ ዓረናና ሌሎች ተቃዋሚዎች በምርጫ እንዳያሸንፏት ስትታገል ዶር. አቢይ ትግራይ ውስጥ እጃቸውን አስገብተው ለፓርቲያቸው አባላት ሊመለምሉ ይችላሉ ብላ ለማሰብ እድል ሳትሰጥ የቆየችው ህወሓት የትግራይ ፖለቲካ ጨርሶ ልትቆጣጠረው ወዳልቻለችው አቅጣጫ መጓዝ ጀመሯል፡፡ መገንጠልን እንደማስፈራሪያ መጠቀምም ሌላው የባሰ ጥፋት ሆኗል፡፡ ህወሓት ለህልውናዋ ስትሰጋ ትግራይን በታጋችነት የምትይዝበት ምክንያት የለም፡፡ አቶ ጌታቸው ስለመገንጠል አማራጭነት ሲናገሩ የትግራይ ህዝብ ስለጉዳዩ ምን እንደሚያስብ በትክክል ስለማወቃቸው አርግጠኛ አልነበሩም፡፡ ህወሓት ሁሉም ነገር መኸተ በማለቷና ክልሉ በጦርነት ስሜት ተወጥሮ ሌላ ስራ በአግባቡ መስራት ሲያቅት የህወሓት አባል ይሁን አይሁን ከዚህ አጣብቂኝ መውጫ ቀዳዳ የሚፈልግ ብዙ እንደሚሆን እሙን ነው፡፡ የግንጠላ ቅስቀሳም ሲጧጧፍ መሃል አገር ኑሮ የገነባው የትግራይ ተወላጅና ከሱ ጋር የተጣመረ ኑሮ ያለው ትግራይ ውስጥ የሚኖር ህዝብ፤ ደሞዝተኛውም ጭምር፤ አቅጣጫው በጠፋው የትግራይ ፖሊቲካ ሲሸበር ከዚህ ወጥቶ በግሉ ይሻለኛል ወዳለው የፖለቲካ ፓርቲ መግባቱ ሊገርም አይገባም፡፡ በጭንቅ ጊዜ ማንም የሰው ፍጡር የሚወስደው የደመነፍስ እርምጃ አለ፤ አሱም ከፊቱ ያገኘውን አማራጭ ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ ለትግራይ ህዝብ እድገት እሰራለሁ እስካለ ድረስ እንደ ጠላት የሚታይበት ምክንያት የለም፡፡ ቀደም ብየ እንደገለፅኩት የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው ነው፡፡ የትግራይ ህዝብ የልማት ህልሙን ከማሳካት እንጂ ከህወሓት አምልኮ የሚጠቀመው ነገር የለም፡፡ የህወሓት አመራሮች ወደ ብልፅግና ገብተው ከሆነ የግል ውሳኔቸው ቢከበር መልካም ይመስለኛል፡፡ የትግራይን ህዝብ በሚገባ ለማገልገል ያስችለናል ብለው የመረጡት መስመር ያ ሆኖ ካገኙት እነሱን ጭቃ መቀባቱ የሚጨምረው እሴት የለም፡፡ የትግራይ ህዝብ በግዳጅ ሳይሆን በነፃ ምርጫ ብልፅግናን ከመረጠ የህዝቡን ውሳኔ በአክብሮት መቀበል ግዴታ ነው፤ ህዝብ ማለት ጡጦ የሚጠባ ህፃን ማለት ስላልሆነ፡፡ አምነትና አምልኮ ለፈጣሪ እንጂ ለፓርቲ የተመደበ አይደለም፡፡

አዚህ ላይ የአራዳ ቋንቋ ለመጠቀም ያህል ትንሽ የሚደብር ነገር አለ፡፡ በህወሓት ላይ ተቀውሞ የሚያነሱ ሰዎች በግልሰብነታቸው ደረጃ እንደማየት ወደ ተወሰነ አካባቢ ህዝብ የማስጠጋት አደገኛ አዝማሚያ እየታየ ነው፡፡ ይህ ትግራይን የሚጎዳ አዝማሚያ በግዴለሽነትና በማናለብኝነት በከፍተኛ የህወሓት መሪዎች ሳይቀር በአደባባይ ሲንፀባረቅ ቆይቷል፡፡ የትም አይደርሱም የሚል የህወሓት የተለመደ ትእቢት ህወሓትን ከመሰረቷ ሊንዳት ይችላል፡፡ አብርሃ ግለሰብ ነው፤ ነብዩም ቢሆን እንደዚሁ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች የሚይዙት የፖለቲካ አቋም የግላቸው ስሜት እንጂ የእንደርታ ህዝብን ሸንጎ ጠርተው ድምፅ በማሰጠት አይደለም፡፡ በህወሓት አመራር አንድን ህዝብ በዘፈቀደ እንደጠላት በመፈረጅ እንደልብ መናገር የሚቻል ከሆነ ያ የሚነካው ህዝብ መቀየሙና ማፈንገጡ አይቀሬ ነው፡፡ ጠላት ሁን እያሉ በመወትወት ህዝብን ጠላት እንዲሆን ማድረግ ማንን እንደሚጠቅም ግልፅ አይደለም፡፡ የተገፋ ህዝብም ከጥቃት ሞት ይሻላል ብሎ የቀረበለትን ሌላ አማራጭ ቢውስድ ተጠያቂው ማን ሊሆን ነው፡፡ ብርሃነ አለሰገባው አንስተው የከተቱት የ1969 ሕንፍሽፍሽ ጉዳይ አንስተው ብዙ ፅፈዋል፡፡ ይህ ጉዳይ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ምንም የሚያገናኘው ነገር ባይኖርም ያነሱበት አላማ ግን ከምን ጋር አስታከው እንደሆነ መገመት አያስቸግርም፡፡ ትንተናው የብልፅግና-እንደርታ-ሕንፍሽፍሽ ሶስትዮሽ ለማሳየት የታለመ እንደሆነ ምንም የሚያምታታ ነገር የለውም፡፡ የብርሃነ ፅሁፍ እንደርታ በሕንፍሽፍሽ ከደርግ ጋር ሆኖ ህወሓትን ሊያጠፋ ሞከረ፤ አሁን ደግሞ ከብልፅግና ጋር ሆኖ የጀመረውን ሊጨርስ ነው የሚል የፈጠራ አስተሳሰብ ትግራይ ህዝብ አይምሮ ውስጥ ለመክተት ያለመ ይመስላል፡፡ እንደ እንግሊዝ ህወሓትም ህዝብን ለያይቶ አርስበርሱ እንዲጠራጠርና እንዲፈራረጅ በመድረግ ከሆነ ህልውናዋን የምታረጋግጠው ቆም ብላ ብታስብ ይሻላል፡፡

ፍርጥርጥ አድርጎ መነጋገር ራሱ ፈውስ ነው፡፡ ያበጠ ነገር ፈርጦ ካልታከመ ካንሰር ይሆናል፡፡በእንደርታና በአድዋ መካከል ያለው ችግር አንድ የአፄ ዮሃንስ ቤተሰቦች ከሆኑት በደጃዝማች ገብረስላሴና በራስ ስዩም መካከል የነበረ የዘመድ ጥል የተነሳ ነው፡፡እነሱ ተጣልጠው ላይቆራረጡ ህዝቡ ውስጥ የጥላቻ መርዝ ትተው አልፈዋል፡፡ ከእንደርታ በተነሳው የመጀመሪያው ወያኔ መክሸፍ የጎላ አስተዋፅኦ ያደረው በደጃች ገብረሂወት የሚመራ የአድዋ ጦር ነበር፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ብዙም አይነሳም፤ በእንደርታ ህዝብ ዘንድ ግን የሻከረ ሆድ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ከሰላሳ አመት በኋላ ህወሓት የአድዋ ሰዎች በርከት ባሉበት አመራር ስትመሰረት የእንደርታ ወጣት የወላጆቹን ቅያሜ ሳይቆጥር ወደ ትግል ሜዳ ጎረፈ፡፡ በ1969 ሕንፍሽፍሽ ጉዳይ ላይ በቅርቡ የፃፍኩት ፅሁፍ እንዲሁ በሰሚ ነጋሪ የቅብብሎሽ ወሬ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በአይኔ በብረቱ እያየሁና በጀሮየ እየሰማሁ የተገነዘብኩት ሃቅ ነበር፡፡ ከዚህ ፅሁፌ በኋላ የጠበቅሁት እኔ እንዳደረግሁት አይነት በመረጃ የተደገፈ ግብረ መልስ ሳይሆን ፅሁፉ ከፋፋይ ነው፤ አሁን መነሳት አልነበረበትም የሚሉ በብእር ስም የተፃፉ የኢሜል ተግሳፆችና ትችቶች ነበሩ፡፡ ሰዎች በአደባባይ የወጣውን ነገር ባደባባይ እንደመጋፈጥ ውስጥ ለውስጥ መሄድን ለምን እንደሚመርጡ በትክክል ባይገባኝም ሃቁን ደብቆ ለማስቀረት ካላቸው ጉጉት የተነሳ ይመስለኛል፡፡ የሕንፍሽፍሹን ፅሁፍ ካወጣሁ ከበርካታ ሳምንታት በኋላ በቀጥታ ለኔ ፅሁፍ በወቅቱ መልስ መስጠት የነበረባቸው ብርሃነ የሚመቻቸውን ጊዜ ጠብቀው የተለመደውና 40 አመት ሙሉ የተደጋገገመውን የህወሓት የሕንፍሽፍሽ 69 ትርክት አዲስ ነገር ይመስል ሰፋ ያለ ቦታ ሰጡት፡፡ ብርሃነ ማለት የፈለጉት ቀደም ብየ እንደጠቀስኩት ሕንፍሽፍሹን ከአሁኑ የብልፅግና ጉዳይ ጋር ማያያዝ ነው፡፡

በ1968 ወደ ህወሓት የጎረፉት የእንደርታ ወጣቶች ከደርግ ጋር ተመሳጥረው ህወሓትን ለማጥፋት ነበር የሚባለው ያልተጨበጠ ወሬ ነው፡፡ በዛ ጊዜ ደርግ ራሱ ምን ያህል ከህወሓት የበለጠ የፖለቲካ አቅም ኖሮት ነው ህወሓትን ለማጥፋት ይህን ያህል የረቀቀ ዘዴ የሚጠቀመው፡፡ እውነቱን ለመነጋገር በዛን ጊዜ ደርግ ትኩረቱ በህወሓት ላይ ሳይሆን በኤሪትሪያ ላይ ስለነበር በህወሓት ላይ ጠበቅ ያለ ዘመቻ የጀመረበት ሁኔታም አልነበረም፡፡ ህወሓት አድጋ ለደርግ የጎላ ፈተና ትሆናለች የሚል እምነትም አልነበረውም፡፡ በሕንፍሽፍሹ ህወሓትን ለቀን መቐለ ከተማ ስንገባ ህብረተሰቡ የተናገረንን አልረሳውም፤ ለካ የመጣነው ከህወሓት ወደ ህወሓት ነበር፡፡ በ1969 የከተማ የህወሓት መዋቅር ከደርግ ፖለቲካ የበለጠ አቅም ነበረው፡፡ ብርሃነ ከሁለቱ አንዱን እንደ ሕንፍሽፍሽ መነሻ ቢመርጡ ይሻላቸዋል፡፡ ሕንፍሽፍሹ ስልጣን እኩል አካፍሉን ነበር ወይስ ከደርግ ጋር ተመሳጥሮ ህወሓትን ማፍረስ፡፡ አፍና ሚድያ የጨበጠ ጎልቶ ስለሚሰማ ካልሆነ በስተቀር እኔ በተጨባጭ የማውቀው በእንደርታ ታጋዮች በኩል ህወሓትን የሚጎዳ ነገር እንደልተሰራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ስልጣን እኩል እንጋራ ማለትስ ወንጀል ነወይ፡፡ ዲሞክራሲን ለማስፈን በርሃ የወጣ ድርጅት ከራሱ ላይ ዴሞክራሲን ካልተገበረ ምን እርባና ይኖረዋል፡፡ በርግጥ በርሃ ላይ ስልጣን መጠየቅ ለመስዋእትነት ነው፡፡ በጨዓ መስከበት ውጊያ የሃይል አስራ አንድ አንዱ ጋንታ መሪ በመሰዋቱ ወዲያው ያሬድ የሚባል ንቁ ልጅ በጋንታ መሪነት ተመደበና በማግስቱ በተከዜ በርሃ ውጊያ ላይ ተሰዋ፡፡ ይህን አይነት ስልጣን ነው የእንደርታ ታጋዮች ድርጅቷን አስኪጎዳ ድረስ የደረሰ ጥያቄ ያቀረቡት፡፡ ጠይቀውም ከሆነ የሚያገኙትን ጥቅም አስልተው ሳይሆን (ምንም ጥቅም አልነበረም፤ አብሮ ቂጣ መብላት ነበር) ለድርጅቷ የሚከፍሉት መስዋእትነት ከፍ ለማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ ገና ለገና ድል ተገኝቶ ሚኒስትር እሆናለሁ ብሎ የሚያስብ ከነበረ አሰገራሚ ምኞት ነው፡፡ ከህወሓት ሲወጡ ምርጥ ምርጥ መሳሪያ ወስደው ለደርግ አስረክበዋል የሚል የፈጠራ ወሬ እየነዙ ጥላቻን ለማቀጣጠል መሞከርስ ምን የሚሉት ፖለቲካ ነው፡፡ ሲጀመር በ1969 ህወሓት ምን አይነት ምርጥ መሳሪያ ነበራትና ነው፡፡ ያላት ምርጥ መሳሪያም ሲሰጥ የነበረው ለጋንታ መሪዎች ነው፡፡ የእንደርታ ታጋዮች አመራር ላይ ካልነበሩ ምርጥ ምርጡን ጠመንጃ ከየት አገኙት፡፡ ከህወሃት መሳሪያ ይዞ መጥፋት ወንጅል መሆኑ የማያውቅ የእንደርታ ታጋይ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም መሳሪያው የተገኘው ራሱም መስዋእት በሆነበት ውጊያ መሆኑን ስለሚያውቅ ነው፡፡ ህወሓት በበላይነት ስሜት የሕንፍሽፍሽ ትርክቷን በየአጋጣሚው የምትደጋግመው ከሆነ ለህዘቦች አንድነት የሚጠቅም ነገር የለውም፡ የሚጎዳ እንጂ፡፡ የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ አጉል ንቀትና ጥላቻ ባደረበት የአድዋን ህዝብ በማይወክል ስብስብ የተፈበረከ መሆኑን ተማምነን ከፊታችን ያለው ጊዜ ይረዝማል በሚል ስሜት በይቅርታና በመግባበት ማለፍ እንጂ እውነትነት የሌለው ታሪክ ለሌላ የፖለቲካ ጠቀሜታ ማዋል የጋራ ጉዳትን ያስከትላል፡፡ አገሩ ሰላም ይሁን፡ አሜን!

Back to Front Page