Back to Front Page

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ድል ያደረጉበት ግንቦት 20

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ድል ያደረጉበት ግንቦት 20

አበበ ተ/ኃይማኖት (ሜጄር ጄኔራል)

05-27-20

ግንቦት 20 ከምን ገላገለን? በደርግ ጊዜ ላልነበራችሁ ወጣቶች ለማሳወቅ እና ሆን ብላችሁ ለማዘናጋት ለምትፈልጉ አዳዲስ ደርጎች ለማስታወስ፤ክቡር ጠ/ሚኒስቴር ዶክትር ዓብይ አህመድ ሰተቴ ብለው በብዕር ስማቸው በፃፉት መፅሃፍ፤ ቅድመ ግንቦት ሃያ የነበረችዉን ኢትዮጵያ እንደሚከተለዉ አስፍረው ነበር፡፡

ደርግ ስላቅ አድምቆ የሚረሽን፣ የሚገድል፣ የሚወርስ፣ የሚቀማ መንግስት እንደነበር በግልፅ ይታወቃል። አባት፣ እናት፣ ልጅ፣ አዛዉንት ወጣቱን ሁሉ ረሽኖ ቤተሰብን የጥይት ወጪ የሚያስከፍል፤ ክቡሩን የሰው ልጅ ገድሎ ሬሳዉን ጎዳና ላይ የሚጥል፤ ወላጅን አስክሬን መከልከሉ ሳይበቃው አታልቅስ ብሎ የሚያግድ፤ በጅምላ መቃብር ጎድጏድ ዉስጥ ሬሳ ወርዉሮ በግሬደር አፈር የሚመልስ፣ ጨካኝ ስርዓት የነበረ መሆኑ የሚልየኖች የቅርብ ግዜ ትዉስታ ነው። አያሌ ንፁሃን ዜጎች፣ የእምነት አባቶች የደርጉ የግፍ በትር ሰለባ ለመሆን በቅቷል። (ሰተቴ ገፅ: 67)

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የግንቦት 20 ድል እያከበሩ የተጫነባቸውን ሁለቱ መንታ ጦርነቶች በሰለማዊ መንገድ ለማሻነፍ በመዘጋጀት ላይ ይገኛሉ፡፡ ኮቪድ 19 ያመጣውና መብታቸውን ለመደፍጠጥ ከሚታገሉት የ 21 ክፍለ ዘመን ደርጎች ጋር የሚደረግ ፍልሚያ፡፡

የፀረ - ዲሞክራቲክ ዘበኛ የሆነው ደርግ በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግል ከዛሬ 29 ዓመት በፊት 20/1983 ዓ.ም ተሸነፈ፡፡ ከዚህ በኃላ ነበር አዲስ ምዕራፍ በሀገሪቱ የተከፈተውና ዲሞክራቲክ ቻርተር እንደዚሁም ሕገ-መንግስት ፀድቆ ህዝቦች በታገሉለት የራስ በራስ የማስተዳደር መብቶቻቸውን ማጣጣም የጀመሩት፡፡

ደርግነት ማለት በኢትዮጵያ አንድነት ስም የህዝቦች መብት በሁሉም መንገድ በተለይ በኃይል መደፍጠጥ መግደል፣ ማቃጠል በማሰር፣ በማግለል.ወ.ዘ.ተ ፖሊቲካዊ ጉዳያችን መፍታት ነው፡፡ ውይይት፣ መግባባት፣ መደራደር፣ የሚባል የለም፡፡ ፡፡ ደርግነት ማለት በብዙ መቶ ሺዎች ሰዎች አልቀውም ቢሆን አንድ ትውልድ ጠፍቶም ቢሆን የኢትዮጵያ አንድነት የሚል ጥንቆላ አይሉት መሃላ ያለው በኃይልና በጉልበት የሚያምን አስተሳሰብ ያለው ነው፡፡ ይህ አስተሳሰብ የህዝቦች አንድነት ሳይሆን የመሬት አንድነት ላይ የተቸከለ ነው፡፡ ለህዝቦች የመብት ጥያቄ መልሱ ጥይት ማጉረስ ነው፡፡ የማትረባ ፍየል ዘጠኝ ትወልዳለች ልጆችዋም ያልቃሉ እስዋም ትሞታለች ነው ዘፈኑ:: ደርጎች ነባር ይሁን አዲሱ የኢትዮጵያዊነት ምስክር ወረቀት መስጠት የሚችሉት እነሱ ብቻ እንደሆኑ በትዕቢት ይፎግራሉ፡፡ አንደንዱ እማ ኢትዮጵያዊነት ተጠይፈው የውጭ አገር ፓስፖርት ይዘው ነው በውሸት ለኢትዮጵያ አንድነት ቆሞናል ብለው አካኪ ዘራፍ የሚሉት፡፡

Videos From Around The World

ለኔ የኢትጵያዊነት መንፈስ ክብሬ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ኩራቴ ነው፡፡ በልጅኔቴ በሁልም ቦታ በቤተክርስቲያንም ጭምር የሚያቃጭል ነበር፡፡ ከተንቤን አውራጃ በየጊዜው የሚመጡት የአባቴ ዘመዶች የአፄ ዮሐንስ እና ራስ አሉላ ጀግንነት ሲያወሩ ከኢትዮጵያ ጋር አስተሳስረው ሲነግሩኝ ልዩ ስሜት ይፈጥርልኝ ነበር፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ እንድታድግ እንድትለመለም እፈልጋሎህ፡፡ ስሜትና ፍቅር ብቻ ሳይሆን በዋናነት ዴሞክራቲክ አንድነት ለሁሉም ህዝቦች እጅጉን ይጠቅማል የሚል ፅኑ እምነትም ስላለኝ ነው፡፡

ሁሉም እንደኔ ነው ለማለት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ስም ብዙ ግፍ የተፈፀመባቸው አገሬን እንዲጠሉ የተደረጉ ህዝቦች እንዳሉም እገነዘባለሁ፡፡ ስሜታቸውም እጋራለሁ፡፡ በአገር ግንባታ ወቀት በየትኛወም ዓለም እጅግ ዘግናኝ ግፎች ተፈፅሟል ያለፈው ይቅር ብለን አንድነት የሚፈጥረው ዓቅም ፈጥረን ወደፊት መጓዝ ነው ለሁላችን የመጠቅመን፡፡

አዲስቷ ኢትዮጵያ የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች እና የትስስራቸው አገር ናት፡፡ ከዛ አትበልጥም ከዛም አታንስም፡፡ ትልቅነቷ በፈቃዳቸው የሚገነባ በነበራቸው ጠንካራ ትስስር የሚመሰረት ግን የተፈፀው ግፍ እንዳይደገም በምናደርገው ትግል ነው፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት በብሔር ብሔርሰቦች ፍቃድ ብቻ የሚመሰረት ነው፡፡ከዛ ውጭ ላሳር ነው፡፡ በኃይል አንድነት ለማረጋገጥ የሚደረግ ሙከራ ይከሽፋል አልያም ፈለግነው አልፈለግነው መበታተን ሊያስከትል ይችላል፡፡

በመሆኑም ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ደርግነት ተሸናፊነት የሚሆነው አመክንዮ በኃይል የህዝቦችን መብቶች ለመደፍጠጥ የሚደረግ ሙከራ በመሆኑ ነው፡፡ ታሪክ እንደማይቻል አሳይቶናል፡፡ ደርግነት በየግዜው ሽፋኑ እየቀያየሩ ጎልቶ የሚመጣ ሲሆን በህዝቦች ትግል ሲሸነፍ መልኩን እየቀያየረ የሚከሰት ኃላቀር ፀረ ህዝብ አስተሳሰብ ነው፡፡

ደርግን ለማስወገድ ሲታገል የነበረውን ኢህአዴግ በትግሉ ወቅት ከፍተኛ ተቀባይነት በማግኘት አልኝታነቱ አስመስክረዋል፡፡ የሽግግር ቻርተሩ በማቀነባበርና ሕገ መንግስቱን በሁሉም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ተሳትፎ እንዲሰራ በማድግረግና ፣ በማፅደቅና በተግባር መሬት ላይ ወርዶ ለውጥ በማምጣት የሚደነቅ ስራ ሰርቷል፡፡ ለ25 ዓመታት ያክል ከዚያ በፊት በኢትዮጵያ ያልታያ ተነፃፃሪ ሰለም አስገኝቶ ነበር፡፡ እጅግ አመርቂ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም አስመዝግቦ ነበር፡፡ ነገር ግን በሂደት በሕገ መንግስቱ ስም እየማለና እየተገዘተ የብሔር ብሔረሰቦች መብት መደፍጠጥ በመጀመሩ በሂደት የጀመረውን መንገድ ስቶ በደርግነት አስተሳሰብ ተጠልፎ በህዝቦች አመፅ ተገዝግዞና ተገርስሶ ሞቶ ተቀበረ፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ የደርግነት ባህሪ ተሸናፊነት ተረጋገጠ፡፡ ሦስተኛወ ሽንፈት መቼ ይሆን? የዴሞክራስያዊ ግንባታ ሁሉም ዓይነት ደርግነት በማሸነፍ የሚረጋገጥ ነውና፡፡

አሁን ደግሞ አዳዲስ ደርግነት አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ካለፉት ስህተቶች የማይማሩ ብቅ እያሉ ነው፡፡ የግለሰብ መብት እንጂ የብሔር ብሔረሰቦች መብት አንቀበልም እያሉ ናቸው ኣዳዲሶቹ ደርጎች፡፡ ግለሰቦች ተሳስበው በፓርቲ እንደራጅ ሲሉ የለም የጎሳ ፖለቲካ ኃላቀር ነው እኛ ብለናል ብለው በህግ ይታገድ ይላሉ፡፡ ለራሳቸው ጥቅም ካልሆነ የግለሰብ መብትን አያከብሩም፡፡ ግለሰቦች ተሰባስበው እንደራጅ ሲሉ አይፈቀድላችሁም የሚሉ የዘመኑ ደርጎች፣ የብሔር መብት የግለሰብ መብት ከፍተኛ መግለጫ መሆኑን ለመቀበል የማይችሉ እንከፎች ናቸው፡፡ ደርግነት በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ሊህቃን ያለና የሚኖር ኃላቀር አስተሳሰብ ነው፡፡ ከብሔሩ ውስጥና ከብሔሩ ውጭ ብዙሐነትን የማይቀበል አስተሳሰብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች አሁንም በሁሉም መልኩ ለመብታቸው መከበር እየታገሉ ነው፡፡ ነገር ግን ለህዝቦች ቆሞናል በሚሉ ሊሂቃን ድክመት አዳዲስ ዓይነት ደርግነት ጡንቻቻቸውን እያፍታቱና እያሳበጡ ይገኛሉ፡፡

ከምስራቁ የሀገራችን ክፍል ብንጀምር በሙስጠፊ የሚመራው የይስሙላ (የዕቃ ዕቃ) ፓርቲ የሶማሊያ ብሔር ታግሎ ከነሁሉ ችግሩ ያረጋገጠውን መብት በሚፃረር መልኩ የአብዲ ዔሌን መንግስት ድክመት በመጠቀምና ጥፋቱን በማጉላት የሶማሌ ብሔርን አንድነት በመሸርሸር ላይ ይገኛል፡፡ ወደ ደቡብ ጎራ ስንል ደግሞ ትንቅንቁ በዘመናዊ ደርጎችና በህዝቦች መካከል ከፍተኛ ደረጃ ደርሷል፡፡ ተፈጥሮአዊ ግን ደግሞ ህገ መንግስታችን እውቅና የሰጠውን በክልል የመደራጀት መብት እንዲከበርላቸው ህዝቦች በነቂስ ወጥተው ያረጋገጡትንና ከፍተኛ መስዋእትነትን የከፈሉበትን መብት እስካሁን አልተከበረላቸውም፡፡ የደቡብ ክልል መንግስት ከኢሰፓ መንግስት በምን ይለያል? የሲዳማ ክልል አልተመሰረተም ህዝቦችም ለመብታቸው እንዳይታገሉ ታፍነው ይገኛሉ፡፡ ሌሎችም እንዳይፈናፈኑ ጥያቄያችሁ በጥናት ላይ ነው በሚል ትንፍሽ እንዳይሉ ተደርጓል፡፡ የኢትዮጵያ ጌጥና ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉት ህዝቦች በኮማንድ ፖስቱም እየማቀቁ ነው፡፡

ወደ መኃል ወደ ኦሮሚያ ፊታችን ስናዞር ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ አሁንም ለብሔራዊ መብቱ በከፍተኛ ደረጃ እየታገለ ነው፡፡ ኦሮሞነት ለኢትዮጵያ ክብር ነው፡፡ በዚህ ምክንያትም ሌሎቻችን ኢትዮጵያውያን ጥያቄውን እንደግፈዋለን፡፡ በኦሮሞ ስም ስልጣን ይዘው በኦሮሞዎች ግፍና በደል እየተፈፀመ እንዳለ የኦሮሞ ፓርቲዎች በግልፅ እየተናገሩ ነው፡፡ በደርጋዊና ህገ-ወጥ ኮመንድ ፖስት የሚተደደሩ ዞኖች መኖራቸው የሚታወቅ ነው፡፡

የህዝቡን የመቻቻል ባህል የሚፃረሩ ደርጎችም አሉ፤እነዚህ ኃይሎች ከመንግስትም ከመንግስት ውጪም ያሉ ሆነው ፡፡ መጤ የሚሏቸውን በተለይ አማራውንና የደቡብ ተወለጆችን እንደጠላት በመቁጠር ውጣልን እያሉ ግፍ ይፈፅማሉ፡፡ በኦሮሞው ላይ ግፍ ለመፈፀምና ለዝርፊያ እንዲመቻቸው ሁሉም ችግሮች መጤ በሚልዋቸው ህዝቦች ያሳብባሉ፡፡

ወደ ሰሜን ስናቀና ደግሞ የአማራ ህዝብ እያደረገ ያለው ትግል እየተጋጋለ በመሄድ ላይ ነው፡፡ ልክ ደርግን ለመደምሰስ በተደረገው ትግል እንደነበረው ተሳትፎ አሁንም የአማራ ብሔርተኛነትን ከዴሞክራሲ እና ልማት አስተሳስሮ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጎለብት እየታገለ ነው፡፡ ነገር ግን በአማራ ክልል ይሁን ውጭ ያሉ ዘመናዊ የደርግ አሰተሳሰብ የተጠናወታቸው አንድ ጊዜ አማራ የሚባል ብሔር የለም፤ሌላ ጊዜ በብሔረ መደራጀት የለበትም ሲሉ አማራነት እንደሚያሳፍር ሁሉ በአማራነት አትጥሩን በሚል በኃላ ቀር አስተሳሰብ የተበከለውን የኢትዮጵያዊነት ካባ በመደረብ ለመስበክ ሲጥሩ ይታያሉ፡፡ እነዚህ ደርጎች በአማራ ውስጥ ያሉትን የሰላም፤ልማት፤ዴሞክረሲ ችግሮች ከመፍታት ይልቅ ውጫዊ የሆኑ ውስብስብ ችግሮችን በማራገብ አማራውን ከሌሎች ክልሎች ህዝቦች ጋር ለማጋጨት ከትግራይ ከኦሮሞ ከቤንሻንጉል በመሬት ወይም በግዛት አንድነት ስም መሬትህ ወረሩህ በሚል ለጦርነት እንዲዘጋጅ ይቀሰቅሱታል፡፡ ሰላም ወዳዱና ታጋሹ የአማራ ህዝብ በትግል እየከሸፈ ይገኛል፡፡ የበለጠ ትግል ቢያስፈልገውም፡፡

በሌላ በኩል የትግራይ ህዝብ በከፍተኛ መስዋእትነት የገነባው ሕገ መንግስታዊ ስርዓት እንዲለመለምና እንዲጎለብት እየታገለ ይገኛል፡፡ ምርጫ ሉዓላዊ መብት ነው በማለት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡በውስጡና በራሱ ለውጥ ለማምጣት እየታገለ ሲሆን በትግሉም የተሸለ ሰላም በማረጋገጥ ለሌችም አብነት ሆነዋል፡፡ ነገር ግን ትግራይ ውስጥም ዘመናዊ ደርጎች አሉ፡፡ ብዙሐነት የማይቀበሉ፤ለለውጥ የሚደረግ ትግል የሚያደናቅፉ ትግራዎት የጠራና ልዩ ደም አለን በማለት የሚፎክሩ አሉ፡፡ እንዚህ ዘመናዊ ደርጎች በትግራይና በአማራ ህዝቦች ያለውን በዘመናት የተገነባውን ሁሉም ዓይነት ማለት ታሪካዊ፤ሃይማኖታዊ፤ማሕበራዊና ግንኙነት ክደው አማራ ታሪክ እንደሌለው የሚሰብኩ የትግራይን ህዝብ ከአማራ ወንድሙ እየጣሉ እነሱ በተንደላቀቀ ንሮ ለመኖር የሚንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ በህዝቡ ሰለም ወዳድነት እና አስተዋይነት እየከሸፈ ነው እንጂ፡፡እንደዚሁም በአፋር ቤንሻንጉል በጋምቤላ ብሔር ያለው ሁኔታም በተመሳሳይ ዘመናዊ ደርጎች ብቅ እያሉ ናቸው፡፡ በመሆኑም ህዝቦች ለመብታቸው እየታገሉ ሲሆን ደርጎች ደግሞ ለስልጣናቸው ሲሉ የህዝቦች መብትን እያፈኑ ይገኛሉ፡፡

በፌደራል ደረጃም ቢሆን እንደደርግ ዘመን መንግስት ስለኢትጵያ አንድነት ይሰብካል፣ ይዘምራል ዲስኩር ይደሰኩራል፡፡ አንዳንድ ጊዜማ በስመ አንድነት እየተሰበከ ማለቃቀስም ተያይዘውታል፡፡ ለዚህም አለፍ ብለዉም ስብከታቸውን በማጠናከር ብሔር ብሔረሰቦች በራሳቸው አደረጃጀት መደራጀቱ ስለማይጠቅማችሁ በፌደራል ደረጃ በሚቋቋም ፓርቲ የሚሰጣችሁን ቅርንጫፍ ነው ልትበለፅጉ የምትችሉት በማለት ብሔር ብሔረሰቦችን ለማታለል ይሞክራሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ዘመናዊ ደርጎች የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ምርጫ ከተካሄደ ማንን እንደሚመርጡ ስለሚያውቁ የምርጫው ጊዜ ሰሌዳ በማራዘም ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለሆነም በ2012 ዓ.ም በተለመደው በግንቦት ወር ሊካሄድ የነበረውን ምርጫ አንዴ የቦርድ ሊቀመንበር ለመምረጥ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ የቦርድ አባላት ለመሰየም እንዲሁም የምርጫ ሕግ ለማወጣት በሚሉ አጓጉል ምክንያቶች በመደርደር ወራቶች በወራቶች እየተደራረቡ ጊዜ ባክኖ ወደ አጣብቂኝ አስገብተዉት ይገኛሉ፡፡

በተጨማሪ በኮቪድ -19 ወርረርሽኝ ውስጥ ሆነን ምርጫ ማካሄድ ይቻላል ወይስ አይቻልም በሚል ሰፊ ሳይንሳዊ ጥናት ሳይደረግ ምርጫውን ማካሄድ አይቻልም በማለት ወደ ሌላ አጣብቂኝ ገብተናል፡፡እዚህ ላይ ወደድንም ጠላንም ምርጫ የህዝቦች የሉዓላዊነት መገለጫ መሆኑን እየታወቀ አስቀድሞ መዘጋጀት ከዚህ ሁሉ አጣብቂኝ መውጣት ይቻል ነበር፡፡ አልተፈለገም፡፡ አጣቢቂኝ ከተገባም መንገዱ ተስቷል፡፡ሕገ መንግስታችን በባህሪው የመግባባት (consensus) ዲሞክራሲ መስረት ያደረገ በመሆኑ በዛ መንፈስ ሰፊ ተሰሚነት እና ተቀባይነት ካለቸው ህጋዊ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት ተወያይቶና ተቻችሎ መፍትሔ መምጣት እየተቻለ ስልጣን ለማራዘም ተብሎ ወደ ውስብስብ ችግር እየገባን ነው፡፡ በአጠቃላይ አሁንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መብታቸውን ለማረጋገጥ በከፍተኛ ደረጃ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት በየእውነት ፌደራሊስቶች ድክመት ኢትዮጵያ አሁንም በመስቀለኛ ጎዳና ትገኛለች፡፡ በዙ ችግሮች ላይና ታች ሊኖር ቢችልም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ማሻነፋቸው እና የኢፌዴሪ ሕገ-መንግስት ማበቡ ግን አይቅርም፡፡

ጀንዳ ለማስለወጥ ወይስ ለማሰቀየስ ወይስ ራስን ለመጥፋት?

የግንቦት 20 መልእክት ፅፌ እንደ ጨረስኩ አንድ ክስተት፣ አንድ ድራማ፣ አንድ ሕገ-ወጥ ዘመቻ በትግራይ ላይ ያነጣጠረ ተከፈተ፡፡ የኤርትራው ደርግ ቴልቪዥን ስለ ባድመ ጦርነት ያጓራል፡፡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ ፋናና ዋልታ የአንድ ፓርቲ ፍፁም ቱልቱላዎች መሆናቸው ሳያንሳቸው አሁንም በአንድ ዓይነት ጡሩንባ ትግራይ ላይ ብጥብጥ ለመፍጠር የሀሰት መረጃ አቀነባብረው የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ አሉ፡፡

እንዴት የመንግስትና የገዢው ፓርቲ ሚዲዎች የሐሰት ዘገባ ይዘው በተነፃፃሪ የተሸለ ሰላም ያለውን ትግራይ ለማፍረስ እንቅስቃሴ ይደረጋሉ፡፡ ገዢው ፓርቲ አጣብቂኝ በገባበት ስልጣኑን ለማራዘም የጀመረው ድራማ ተቀባይነት አለመገኘቱን እየተረዳ ሲሄድ አጀንዳ ለመለወጥ ወይም ሌላ የአስቸኳይ አዋጅ ለማስቀየስ ነው እንዴ?

የኮረና አደጋ ስላለ ብሎ ከአራት ሰው በላይ መሰብሰብን ክልክል ነው ያለ መንግስት ትግራይ ላይ ደርሶ ህዝባዊ ዓመፅና ሺዎች የሚሳተፉበት ሰልፍ እንዲደረግ ይቀሰቅሳል። ምርጫን በኮረና ሰበብ አስባብ ይራዘም ዘንድ ሌት ተቀን የሚሰራ ትግራይ ላይ ደርሶ ህዝቡ እንዲሰበሰብና አይበለው እንጂ ለኮረና ተጋላጭ እንዲሆን እየሰራ ነው። ምን ይሉታል?

የትግራይ ህዝብ በህወሓት የሚመራው መንግሰት የተለያየ ቅሬታዎች አሉት፡፡ መብቶቹ የበለጠ እንዲረጋገጥለት እየታገለ እንደለ እሙን ነው፡፡ በኔ ግምት አብዛኘው የትግራይ ህዝብ በ ጠ/ሚ ዶክትር ዓቢይ አህመድ የሚመራው የፌዴራል መንግስት ለትግራይ አየስብም ብቻ ሳይሆን ከሻዕቢያ ጋር በመመሳጠር ትግራይን ለማደከም ሽጣራ እየፈፀመ ነው ያለው የሚል አመለካት ሠፊ ነው ፡፡ አዲስ አበባ ያሉት ቅልቦች ካልሆኑ ሁሉም ሊባል በሚችል ትግራይ ያሉ ተፎከካሪ ፓርቲዎች የፌደራል መንግስት ያለአግባብ ጣልቃ ለመግባት ከከጀለ ህወሓት ከሚመራው ጎን ተሰልፈው እንደሚከላከሉም ይገልፃሉ፡፡

የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስቴር አቶ ስየ አብርሃ በቅርቡ ያደረጉት ቃለመጠይቅ ጥልቀት ያለው ነው፡፡ በተለይ የኃይል መንገድ በኢትዮጵያ አንዱ ሊጀምረው ይችላል፤ማብቂያው ግን አይታወቀም ያሉት ልዪ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ ጦርነትን ከሚያወቁ ጦርነቱን ከሚፈሩ የተሰጠ ነውና፡፡ አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት ከሁለት ዓመት በፊት የተሰፋ ብርሃን ማየት ቢጀምርም አሟልቶ ሳያይ በጨለመበት ሁኔታ እና በተከፋበትና ክህደት ተፈፅሞብኛል ባለበት ሁኔታ ሁሉም ነገር ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ማለት ራስን ማጥፋት አይሆንም? የተከፉት ብሔር ብሔረሰቦች ከኋላ ሌሎች ጦር ግንባርች ከፍተው አይዋጋም?፡፡ በተለይ የዓመፁ መእከል የነበረው ኦሮሚያ እንኳንስ ዘንቦበሽ ድሮውም ጤዛ ነሽ ጦርነት ተጨምሮበት አሁን ያለው ሁኔታ አስጊ ነው ፡፡ በርካታ ዞኖች በኮማንድ ፖሰት ስር መሆናቸውን ይታወቃል፡፡ በእሰት ጎመራ የተቀመጠ አገር የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ የሚለው የ ቅንጦት አዋጅ ያዋጣልን?

እንደ ተቋም መከላከያም በዚ ሕገ-ወጥ ተግባር መሳተፍ የለበትም፡፡ ከመከላከያ ጥቂት ጀብደኞች እና ተኩስ ገና ከርቁ ሲሰሙ የሚሸሹ ካድሬዎች ይዞ ጦርነትን ማሸነፍ ይችላል? ተሸናፊው የታወቀ ነው፡፡ ምክንያቱም የትግራይ ህዝብ የሚያደርገው የመከላከል ፍትሓዊ ጦርነት ነው፡፡ በአንድነት ስለቆመም ጭምር ነው፡፡ ይህ ጥቃት በነሱ ላይ እንደተቃጣ የሚገነዘቡት መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች ስለሚደግፉትና ከጎኑም ስለሚሰለፉ ነው፡፡ ደርግም በዚህ መንገድ ነው የተሸነፈው፡፡

ክብር ጠ/ሚ ዶክትር ዓቢይ የሚያደርጉትና የሚናገረት ስከታታል ይገረመኛል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ለማመን በሚያስችግርና ታይቶ በማይታቅ ሁኔታ በሁሉም አቅጣጫ የነበራቸው ተቀባይነት በአጭር ጊዜ ሲሟሸሽ ይረዱታል?፡፡ ነፃና ፈትሓዊ ምርጫ ቢካሄድ እሳቸውና ፓርቲቸው በአንድ ክልል ቢሆን ማሸነፍ እችላለሁ ይላሉ? በሁሉም ያለ ቢሆንም በተለይ በትግራይ ህዝብ ያላቸው ግንዘቤ ሳይ በእውነት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ያሉት? ያሰኛል፡፡

በዙርያቸው ያሉ ግልገል ደርጎችና ከድርጅት ግርድና ለግለስብ ህልምና ፖለቲካዊ ፍላጎት በአሽከርነት የተሰለፉ የህግ ባለሞያዎች፤አርቲሰቶች ሚድያዎችና ጋዘጠኞችም እየፈጠሩት ስእል ይሆን እንዴ? ከረዳ ምናልበትም for the benefit of doubt ከማህበራዊ ሚድያ ያገኝሁተን (H.C.Andersen) እንዲነበብ አቀርባለሁ፡፡

ንጉሱ ልብስ ሰፊያቸውን ጠርተው እስኪ ለየት ያለ ልብስ ስፋልኝ ይሉታል። ልብስ ሰፊውም የመኳንንቱና የልሂቃኑን ኣድርባይነት ጠንቅቆ ይረዳ ነበረ። ወደንጉሱ ሄዶም ንጉስ ሆይ የሰፋሁልዎ ለእርስዎ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ብቻ የሚያዩት ሌሎች ታማኝና ብቁ ያልሆኑ ባለሟልና ዜጎችዎ ግን ሊያዩት የማይችሉ የማይታይ ባለማእረግ ልብስ ነው ይላቸዋል፡፡ ንጉሱም ይሄማ ማለፊያ ነው ይሉትና ልብስ ሰፊው ምንም ሳያለብሳቸው ነገር ግን በኣገሩ ሁሉ ለንጉሱ ታማኝና ለያዙት ቦታ ብቃት ያላቸው ባለሟሎችና ዜጎች ብቻ ሊያዩት የሚችሉ፣ ነገር ግን ለንጉሱ የማይታመኑና ለያዙት ስልጣን የማይመጥኑ ሰዎች ሊያዩት የማይችሉ ረቂቅ ልብስ እንዳዘጋጀ አስነገረ፡፡

በሚቀጥለው ቀን ንጉሱን ምንም ሳያለብስ ወደኣደባባይ እንዲወጡ ኣደረገ። ንጉሱም ያገኙትን መሳፍንትና መኳንንተ ኣዲሱ ልብሴ እንዴት ነው እያሉ ይጠይቁ ነበር። ሁሉም በከፍተኛ ኣድናቆት እንዲህም ያለ ረቂቅ ልብስ ኣላየንም በጣም ኣምሮብዎታል እያሉ ራቁቱን የሚሄደውን ንጉስ ኣሞካሹት። ልሂቃኑም ስለልብሱ ረቂቅነት ብዙ ደጋግመው ኣወሩ። ኣንድም ሰው ንጉስ ሆይ ምንም ልብስ ኣይታየኝም ያለ አልነበረም፡፡ በዚህ መሃል ኣንድ ህፃን ልጅ በስመኣብ ንጉሳችን ራቁታቸውን ወጡ ብሎ ጮኸ። የተቀረውም ህዝብ እንዴ ንጉስ ምን ነካቸው እያለ ግማሹ በሹፈት ግማሹ በእፍረት ሲያየው ንጉሱ ራቁቱን መሆኑን ኣወቀ።

መልካም በዓል

Back to Front Page