Back to Front Page

የምርጫውን ቀን መራዘምና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ጥሪ

የምርጫውን ቀን መራዘምና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው ጥሪ

ባይሳ ዋቅ-ወያ 05-22-20

****

ቀደም ሲል የሕገ መንግሥቱ አጣሪ ጉባዔ ባስተላለፈው ጥሪ መሠረት ሙያዊ አስተዋጽዖአቸውን ለማበርከት በኢትዮጵያና በመላው ዓለም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሕግ ባለሙያዎች ሜይ 16 እና 18 በሸራቶን ሆቴል በመገኘት ሰፋ ያለና በቀጥታ ለሕዝብ የተላለፈ ምናልባትም በታሪካችን የመጀመርያው የሆነውን ውይይት አካሄደዋል። በሆነ የግል ምክንያት የሚፈለግብኝን ለማበርከት ባልችልም አሁን አጋጣሚ ሳገኝ የሂደቱ ተካፋይ መሆኔ ይታወቅልኝ ዘንድ ይህንን አጭር ጽሁፍ ላካፍላችሁ ወሰንኩ። በአጣሪ ጉባዔው ፕሬዚዴንት ሊቀመንበርነት የተመራው ውይይት ብቸኛ ትኩረቱ ቀደም ሲል በሚዲያ ተቋማት በኩል ባቀረባቸው ሁለት ዓቢይ ጉዳዮች ላይ ነበር ። እነሱም፣

ሀ) የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል?

ለ) የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ ምርጫው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል? የሚሉ ነበሩ።

ለጥያቄዎቹ መልስ ከመመለስ በፊት ግን ከጥያቄው ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን ነባራዊ ሁኔታዎች (እውኔታዎች) ባጭሩ ማጤን ዝቅ ብዬ ለምሰነዝረው ሃሳብ ጥሩ ድጎማ ይሆነኛል ብዬ እገምትታለሁ።

ሀ) መላውን ዓለም በድንገት የወረረው የኮሮና ቫይረስ ባገራችንም በመከሰቱ፣ ወረርሽኙን ለመግታት ሲባል መንግሥት ለአምስት ወር የሚቆይ አስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ አውጇል። ተቃዋሚ ፓርቲዎችም መታዋጁን አልተቃወሙም።

ለ) በአስቸኳይ ዓዋጁና ዓዋጁም ባቀፋቸው የመብቶች መገደብ ምክንያት፣ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ማካሄድ እንደማይቻል የምርጫ ቦርድ ለፓርላማው ባቀረበው ማሳሰቢያ መሠረት በነሓሴ ወር ሊካሄድ ታስቦ የነበረው ስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ላልተወሰነ ጊዜ ተላልፏል።

ሐ) አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እና ምክር ቤቶቹ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54(1) መሠረት ስልጣን ላይ ሊቆዩ የሚችሉት እስከ መስከረም ወር ብቻ ነው። ከዚያ በኋላ አገሪቷን ማን ሊመራ እንደሚችል ሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተካተተ ነገር የለም። ሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 9(3) ሥር በግልጽ ያስቀመጠውና በምንም መልኩ አማራጭ የማይኖረው ግን የመንግሥት ሥልጣን የሚጨበጠው በሕዝባዊ ምርጫ ብቻ መሆኑን ነው።

Videos From Around The World

መ) አስፈጻሚው አካልም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይህንን ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት በራሳቸው መሙላት ስለማይቻላቸው፣ ከመስከረም ወር በኋላ አገሪቷን ማን ሊመራት እንደሚችል ውሳኔ እንዲሰጥበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለውሳኔ ተጠየቀ። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔን ሃሳብ ጠየቀ። አጣሪ ጉባዔውም ጉዳዩ በታሪካችን የመጀመርያው በመሆኑና ችግሩን በቀላሉ መቅረፍ ከባድ ሆኖ ስላገኘው፣ ከላይ ያስቀመጥኳቸውን ሁለት ጥያቄዎች ሙያዊ ምክር እንዲለግሱት በሙያው የተካኑትን ምሁራን አሰባስቦ አወያየ።

ሠ) ወረርሽኙ በመላው ዓለም ያሰፈነው ሥጋትና እያደረሰ ያለው ተጨባጭ አደጋ ሳይንቲስቶችንም ግራ እያጋባ ስለሆነ፣ መቼ በቁጥጥር ሥር እንደሚውል አይታወቅም። ወረርሽኙ እንኳን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ደሃ አገሮች ይቅርና እጅግ በጣም ባደጉ አገሮችም ባጭር ጊዜ ውስጥ እንደማይቆም ስለተረጋገጠ ብሔራዊ ምርጫችንን በቅርብ ጊዜ ልናካሄድ አንችልም።

ረ) የሕገ መንግሥት አጣሪው ጉባዔው በአንቀጽ 84(1) በተቀመጠው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራትና በሚያደርገው ማጣራት መሠረት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ማቅረብ ይችላል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ላቀረባቸው ሁለት ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ለመስጠት እነዚህን ነባራዊ ሁኔታዎች ከግምት ማስገባት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው። በሸራተን ሆቴል በተካሄደው ስብሰባ በአካልና በቴክኖሎጂ ድጋፍም የተካፈሉት የመስኩ ባለሙያዎችም በግልም ሆነ በቡድን የደረሱበትን ግምገማ በየተራ ባቀረቡት ሃሳብ በሙሉ ባልስማማም፣ ባቀረቡት ሙግት ኮርቼባቸዋለሁ። አገራችን እነዚህን ሁሉ ብርቅዬ የሕግ ባለሙያዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እያሏት በምድሪቷ

የሕግ የበላይነት ሊሰፍን አለመቻሉ ግን አስገርሞኛል። ይህ ደግሞ ሌላ ታሪክ ስለሆነ እናቆየው።

የጉዳዩ ይዘት፣

ከወዲሁ ውይይቱን ለማካሄድ እንዲረዳን ሁላችንም የምንስማማባቸው ሕጋዊና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች መታወቅ አለባቸው። አሁን በተግባር ላይ ያለው ሕገ መንግሥትና በሕገ መንግሥቱ መሠረት ተመርጫለሁ ብሎ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትን በተመለከተ ስምምነት መኖር አለበት። የምንስማማው ሕገ መንግሥቱ ሕዝባዊ ተሳትፎ ስለነበረው የሕዝብ ነው ወይም አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ዲሞክራቲክ በሆነ መንገድ የተመረጠ ነው ለማለት ሳይሆን፣ ሳንወድ በግድ እንድንቀበለው ያደረገን ነባራዊ ሁኔታ ስለነበር አሁን ሕጋዊነታቸውን ጥያቄ ውስጥ መክተት የለብንም። ሕገ መንግሥቱ ገዢያችን መሆኑን ሁላችንም አምነን ተቀብለናል። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይህንን ተቀብለው ሕጉ በሚያዘው መሠረት በምርጫ ቦርድ ተመዝግበው ሕጋዊ ስለሆኑ የሚያከራክረን አይመስለኝም። ወደ አጣሪ ጉባዔው ሁለት ጥያቄዎች እንመለስና፣

1) የቅድመ ምርጫ ዝግጅቶች እና ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ ለማወጅ የሚያስገድድ ሁኔታ ቢከሰት፣ በዚህም የተነሳ ምርጫ ማድረግ የማይቻል ቢሆን የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል?

የምርጫ ዘመናቸው ያበቃ የምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመን ምን ይሆናል ለሚለው ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ መልስ ስለሌለ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተውን የፌዴሬሽን ምክር ቤትን መጠየቁና የፌዴሬሽን ምክር ቤቱም የሕግ አጣሪ ጉባዔን ሙያዊ ሃሳብ መጠየቁ ሕጋዊ አሠራር ነው። የሕገ መንግሥቱ አጣሪ ጉባዔም ሕገ መንግሥቱ ባጎናጸፈው ሁለት ሥልጣኖች ማለትም፣ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን የማጣራትና በሚያደርገው ማጣራት መሠረት ሕገ መንግሥቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ለፌዴሬሽኑ ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ ለማቅረብ ይረዳው ዘንድ ባለሙያዎችን ማወያየቱ ትክክል ነው። በኔ ግምት ከውይይቱ በኋላ የአጣሪ ጉባዔው ሊወስድ የሚችለው እርምጃ፣

ሀ) የቀረበለትን ጥይቄ አጣርቶ፣ የምርጫ ዘመናቸው ያበቃው የሁለቱ ምክር ቤቶችና የአስፈጻሚው አካል የሥራ ዘመንን በተመለከተ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ራሱ አንቀጽ 104 እና 105 ተጠቅሞ ሕገ መንግሥቱን አሻሽሎ ለችግሩ መፍትሔ ሊያገኝ ስለሚችል የሕገ መንግሥት ትርጓሜ አስፈላጊ አይደለም፣ ወይም፣

ለ) ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ለወደፊቱ አላስፈላጊ የሆነ ልምድ ሊያስከትልና ሥልጣንን ተጠቅሞ የሥራ ዕድሜን ለማራዘም ከማለት የአስፈጻሚ አካላት ሊባልጉበት ስለሚችሉ ያንን ለማስወገድ ሲባል ያሁኑን ችግር ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ ለአንድ ጊዜ ብቻ የሚሆን እና ተፈጻሚነት ያለው ውሳኔ መስጠት ይመስለኛል።

ለሁለቱም ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት በመጀመርያ ደርጃ መመርመር ያለብን ሕገ መንግሥቱን ነው። ሕገ መንግሥቱ ቀጥተኛ መልስ ሊሰጥ የማይችል ከሆነ የሕገ መንግሥቱን መንፈስ መርምረን መልስ ለማግኘት መሞከር አለብን። አሁን በተግባር ላይ ያለው ሕገ መንግሥታችን ከመስከረም ሰላሳ በኋላ ሊኖረን ስለሚችለው መንግሥት በቀጥታ መልስ ሊሰጠን አልቻለም። የስው ልጆች ማህበረሰብ ከተፈጥሮ ጋር ያለው ግንኙነት አንድ ወጥ ያልሆነና በየጊዜው ሊለዋወጥ የሚችል ስለሆነ፣ ያኔ ሕገ መንግሥቱን ያረቀቁ ባለሙያዎች ከግምት ያልከተቱት ነገር ዛሬ ላይ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ሊያስገርመን አይገባም። ስለሆነም፣ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ክፍተት መፈጠሩ እንግዳ ነገር መሆን የለበትም። አስገራሚ ሊሆን የሚችለው፣ ሕገ መንግሥቱ በውስጡ ሊያቅፍ የሚችለውን ክፍተት አስቀድሞ ግምት ውስጥ በመክተት ክፍተቱ የሚሞላበትን ሁኔታ አለማመቻቸት ነው። በኔ ግምት፣ የሕገ መንግሥቱ አርቃቂዎች ይህንን በትክክል አስቀድመው ገምተውት ኖሮ ክፍተቱን ለመሙላት አንቀጽ 104 እና 105ን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ስላካተቱ ሕገ መንግሥቱን በማሻሻል ለተነሳው ጥያቄ መልስ ማግኘት ይቻላል ባይ ነኝ።

እነዚህ ሁለት አንቀጾች በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የታየውን ጉድለት ለመሙላት ወይም አሻሚ የሆነን ጉዳይ ለማጣራት የሚያስችል ፍቱን መሳርያ ሠጥተውናል። መሳሪያዎቹም የሕዝብ ድምጽ ነው። በአንቀጽ 8(1) ሥር በተደነገገው መሠረት ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሠጡ የሚችሉት የሉዓላዊው ሥልጣን ባለቤት የሆኑት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝቦችም ሉዓላዊነት ደግሞ የሚገለጸው በአንቀጽ 54(1) መሠረት በሚመርጧቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ተሳትፎ አማካይነት ነው። ስለዚህ አሁን ያጋጠመንን የሕገ መንግሥት ክፍተት ለመሙላት የሚቻለው አንቀጽ 104 እና 105ን ተጠቅሞ በቀጥታ ከክልል ምክር ቤቶች፣ ከሕዝብ ተወካዮችና ከፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ጋር ተወያይቶ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ሂደት በቀረበው ሃሳብ ላይ በሚካሄደው ውይይት የማሻሻሉ ሃሳብ አብላጫ ድምጽ ካገኘ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፊትም ሊገጥመን ለሚችል ተመሳሳይ ጥያቄ መፍትሔ እንዲሆን ያንን በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ማካተትና ማጽደቅ ብቻ ነው።

አዎ! ሕገ መንግሥቱን ዝም ብሎ የመበወዝ (የማሻሻል) ባሕል ካዳበርን ራሱን የቻለ አደጋና የማንወጣው ቀውስ ውስጥ ሊከተን ይችላል የሚል ፍርሃት አለ። አሁን ያጋጠመንን የሕግ ክፍተት በሕገ መንግሥቱ መሠረት የምንሞላው ግን ዛሬ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት ዕድሜ ለማራዘም ሳይሆን፣ ከላይ እንዳልኩት ተፈጥሮ በራሱ ፕሮግራም መሠረት አንድ ቀን የሆነ ማህበረሰባዊ ችግር ቢያመጣብን የሚያስከትለውን ሕገ መንግሥታዊ ውዝግብ በቀላሉ ልንወጣው እንድንችል ይረዳናል ብዬ ስለማምን ነው። ሌሎችም አገራት ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ሁኔታ ሲከሰት ምርጫና የምክር ቤቶችን የሥራ ዕድሜ ለማራዘም ተመሳሳይ አንቀጾች በየሕገ መንግሥታቸው ውስጥ ማካተታቸው አንድ አሳማኝ ድርጊት ነው። ስለዚህ አንድ ራሱን የቻለ ለወደፊት ተመሳሳይ ችግር ሲያጋጥመን ልንጠቀምበት የሚያስችለንን አንቀጽ 54 ሥር አንድ ንዑስ አንቀጽ በመጨመር ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ፍቱን ነው ባይ ነኝ።

በፌዴሬሽኑ የአንድ ጊዜ ውሳኔ (one-time-use) ዛሬ ላጋጠመን ችግር ብቻ የሚሆን መፍትሔ ለመስጠት ከመሞከር፣ አንቀጽ 104 እና 105ን ተጠቅሞ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ዘላቂ መፍትሄ ይሆናል የምልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ፣ የምንተዳደረው በተጻፈ (coded) ሕግጋት ስለሆነና፣ በጊዜያዊ የፖሊቲካ ቀውስ ምክንያት ወቅታዊውን ችግር ብቻ ለመቅረፍ ተብሎ የሚወሰድን እርምጃ ሌላ ጊዜ ደግመን እንደ ሕጋዊ ውሳኔ ልንጠቅምበት ስለማንችልና (precedent)፣ ተመሳሳይ ችግሮች ለወደፊት ባጋጠሙን ቁጥር ተመሳሳይ ውሳኔን ከፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ከመጠበቅ፣ የተሻሻለው ሃሳብ አንዴ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከተካተተ ለወደፊት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚፈጥረው ችግር እምብዛም ነው ከማለት ነው።

በርግጥ የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻል ከመወሰን ይልቅ፣ አንድ ያሁኑን ችግር ብቻ ሊቀርፍ የሚችልና ተፈጻሚነት ያለው ውሳኔ የማስተላለፍ ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው። ይህ አያከራከርም። መወሰንና ተዓማኒነትን ማግኘት ደግሞ ተያያዥ ቢሆኑም ያንኑ ያህል ግን የተለያዩ ግንዛቤ ያላቸው ነገሮች ናቸው። የምክር ቤቱን አፈጣጠር ታሪክ፣ ከኢሕአዴግ መንግሥት ተፈጥሮ ጋር ስናያይዘው እምብዛም የሕዝብ ዓመኔታና ቅቡልነት ስለሌለው፣ የሚያሳልፈውም ውሳኔ በተለይ አሁን ባገሪቷ ሰፍኖ ባለው የፖሊቲካ ውጥረት ዓይን ሲታይ የሕዝባችንን የፍትሕ ጥም ሊያረካ የሚችል አይመስለኝም። የብዙዎቻችን ችግርና ሥጋት በደንብ ይገባኛል። እባብ ያየ በልጥ በረየ ሆኖብን ነው። ላለፉት ሰላሳ ዓመታት መንግሥትና ፓርቲን መለየት አስቸግሮን እና ፓርላማው መቶ በመቶ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ሆኖ ስናይ፣ ጉዳዩ በፌዴሬሽን ምክር ቤትም ተወሰነ በአንቀጽ 104 እና 105 መሠረት ወደ ክልል ደረጃ ወረደ፣ ዞሮ ዞሮ ውሳኔ ሰጪዎቹ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ያው የሕአዴግ (ብልጽግና) አባላት ስለሆኑ ለውጥ የለውም የሚል ጨለመተኝነትን ተላብሰናል። አይፈረድብንም። ግን ደግሞ የምንታገለውና የምንመኘው ፓርላማው የምርጫ ቦርዱን መስፈርት ባሟሉ ብዙ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሞላና ለወደፊት ተመሳሳይ ፖሊቲካዊ ቀውስ ሲያጋጥመን በፓርላማው ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ውይይት ተደርጎ ሕገ መንግሥታዊ በሆነ መንገድ ቀውሱን ለማርገብ ስለሆነ፣ የዛሬውን ባለ አንድ ቀለም የኢሕአዴግን ፓርላማ ሳይሆን ከሚቀጥለው ምርጫ በኋላ ሊኖረን ስለሚችለው ቡራቡሬ ፓርላማ መሆን አለበት ባይ ነኝ።

2) የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ ምርጫው በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ሊከናወን ይገባል?

የምርጫ ቦርድ ወረርሽኙን ምክንያት በማድረግ ባስቀመጥኩት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሄድ አልችልም ብሎ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውሳኔ ማቅረቡ አግባብ ያለው ሕጋዊ አካሄድ ነው። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም በምርጫ ቦርዱ ማሳሰቢያ መሠረት ምርጫውን ለማራዘም የወሰደው ውሳኔ በመላው ዓለም ከአምሳ የሚበልጡ አገራት በወረርሽኙ ምክንያት ብሔራዊና ክልላዊ ምርጫዎችን ለማዘግየት ከወሰዱት እርምጃ ጋር ተመሳሳይ ስለነበር የኢትዮጵያም መንግሥትም በዚያው ምክንያት ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማካሄድ እንደማይቻል ማስታወቁ አግባብ ያለው ነው።

የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት መታወጁ ትክክል መሆኑን ሁሉም ተቀብሎታል። በማሕበረሰቡ ውስጥ መግባባት ያልተደረሰብት ጉዳይ ቢኖር፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ እስከ መቼ ይቀጥላል የሚለው ነው። በሌላ አነጋገር፣ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ አብቅቶ ወደ ምርጫ የምንገባው መቼ ነው የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው። ከሕግ አንጻር ካየነው መልሱ ቀላል ነው። አንድ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ በሥራ ላይ የሚቆየው ዓዋጁ የታወጀበት ምክንያት መኖር እስኪያበቃ ድረስ ነው። የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ የታወጀው በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ስለሆነ፣ የሚያበቃውም የኮሮና ወረርሽኝ ቁጥጥር ሥር ሲውል ብቻ ነው። ይህን ደግሞ መወሰን የሚችሉት ፖሊቲከኞች ሳይሆኑ የጤና ዘርፍ ባለሙያዎች ብቻ ናቸው። በዚህ ላይ ሂሳባዊ ፎርሙላ ማቅረብ የሚቻል ባይሆንም በመስኩ ልምድ ያላቸው ሳይንቲስቶች እንደሚሉት ከሆነ ለጊዜው ሕዝቡን በማራራቅና በወሸባ በማስቀመጥ የቫይረሱን ሥርጭት የገታን ቢመስለንም፣ አሁን የታጎረው ሕዝብ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ሲመለስ ቫይረሱ እንደገና የጥቃት ዘመቻውን ሊጀምር ይችላል የሚል ግምት አላቸው።

ያም ሆነ ይህ፣ ቫይረሱ የሕዝባችንን የኑሮ ዘዴና ማህበረሰባዊ ግንኙነት እሴቶቻችንን መለወጡ አይቀሬ ነው። አገራችን በኢንዱስትሪ ያደገች ባለመሆኗ በወሸባው ምክንያት ሥራ ያቆመ ፋብሪካ ስለሌለ ለሥራ አጥነት የተጋለጡ ኢትዮጵውያን ቁጥር ያን ያሕል ባይሆንም፣ የንግድ እንቅስቃሴ በመቀነሱ ምክንያት የአገሪቷ ኤኮኖሚ የባሰውኑ ሊደቅቅ እንደሚችል የመስኩ ባለሙያዎች ይተነብያሉ። ስለዚህ የቫይረሱ ሥርጭት እንኳ ተገትቶ ሰላም ቢሰፍንም፣ ምርጫ ቦርድ እንደገና ኃይሉን አሰባስቦ ለምርጫ ዝግጅት እስኪያደርግ እና ለምርጫው የቀን ሰሌዳ አዘጋጅቶ የምርጫ ታዛቢዎችን ለማሠልጠን የሚያስፈልገውን በጀት ይደጉሙ የነበሩ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እርዳታ ሰጪ አካላት ወደ ኢትዮጵያ እስኪመለሱ ድረስ ጊዜ መፍጀቱ የታመነ ነው። እንደው በሆነ ተዓምር ወረርሽኙ እንኳ በቅርብ ጊዜ ቢገታ፣ የምርጫ ቅድመ ዝግጅት ተደርጎ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ፕሮግራማቸውን ለመራጮች ለማስተዋወቅ ቅስቀሳ እስኪያካሄዱ ድረስ ወራት ይፈጃል። በአጠቃላይ፣ ወረርሽኙ ከተገታ በኋላ እንኳ ያገሪቷን ኤኮኖሚ፣ ማህበረሰቡን እንደገና መልሶ ሰላም ማስፈንና የተበጣጠሰውን የማህበረሰብ ድርና ማግ መልሶ ለመስፋት የተወሰነ ጊዜ ያስፈልጋል።

ስለዚህም የቫይረሱ ሥርጭት ከተገታ በኋላ በዚህን ያሕል ጊዜ ውስጥ ምርጫ ይደረጋል ብሎ ካሁን ከመተንበይ፣ የምርጫ ቦርድ በወቅቱ ሁኔታውን ከጤና ባለሙያዎች ጋር ተወያይቶና የራሱን የማዘጋጀት አቅም መርምሮ የምርጫውን የቀን ሰሌዳ እንዲያዘጋጅ መወሰኑ ትክክለኛ አካሄድ ይመስለኛል። ስለዚህ ተሻሽሎ በሚቀርበው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 54 ሥር ለምሳሌ የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጅ እንዲታወጅ ምክንያት የሆነው ክስተት ከተወገደ በኋላ ምርጫው የሚካሄድበትን ቀን ምርጫ ቦርዱ ከሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት ጋር በመመካከር ሊወስን ይችላል የሚል ተጨማሪ ንዑስ አንቀጽ ቢካተት አግባብ ያለው ይመስለኛል። በሌላ አነጋገር ወረርሽኙ እንኳ ሲያበቃ ወዲያውኑ ምርጫ ማካሄድ ስለማይቻል ዛሬ ላይ ሆነን ስለሚቀጥለው የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ማውራት አንችልም። የአስቸኳይ ጊዜ ዓዋጁ መቼ እንደሚነሳ በትክክል መገመት ባይቻልም፣ ከባለሙያዎች ግምገማ ተነስቼ አንድ በቁርጠኝነት ለማለት የምችለው ግን አሁን የተያዘለት የአምስት ወር ዕድሜ አጭር ነው የሚለው ነው።

ለመደምደም ያህል፣ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔው አንዳች የውሳኔ ሃሳብ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከማቅረቡ በፊት ከመስኩ ባለሙያዎች ጋር በአደባባይ መወያየቱ በፖሊቲካችን ውስጥ ያልተለመደ ቢሆንም እጅግ በጣም መደገፍ ያለበት አካሄድ ነው። ጥቂት ግለሰቦች በሕዝብ ስም ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው በሚወስኑል(ብ)ን ውሳኔዎች ለዘመናት ሳንወድ በግድ ተገዝተን እንኖር ስለነበር እንደዚህ በአደባባይ ወጥቶ በቀጥታ ስለሚመለከተን ጉዳይ ባለሙያዎቹ ሲወያዩ ማየቱ አንድ እርምጃ ወደ ፊት መሄዳችንን ይጠቁማል። ሁለት ተያያዥ ጉዳይ ቢኖር፣ አንደኛ፣ በባለሙያዎቹ ሃሳብ ሙሉ በሙሉ መስማማት የለብንም። በነሱ መካከልም ስምምነት የለም። አለመኖሩም ሊያስገርመን አይገባም። ይካሄድ የነበረው ውይይት እንጂ ውሳኔ ስላልሆነ፣ አጣሪ ጉባዔው በውይይቱ ጭብጥ ላይ ተመርኩዞ ወገናዊ ያልሆነ የውሳኔ ሃሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀርባል የሚል ግምት አለኝ። ሁለተኛው ደግሞ፣ የሕግና ሕገ መንግሥትን ጉዳይ ከተራ ፖሊቲካ ጋር አያይዞ ሓኪሙና መሃንዲሱ፣ ነጋዴና የታሪክ ባለሙያውም ሳይቀር በየሚዲያው እየቀረቡ ለሕጋዊ ችግር ፖሊቲካዊ መፍትሔ ለመስጠት ደፋ ቀና ማለታቸው ሕዝባችን ትክክለኛውንና ሕጋዊውን አካሄድ እንዳያውቅ ሊያደርግ ስለሚችል፣ የሕግና ሕገ መንግሥትን ጉዳይ ለባለሙያዎቹ ብንተው ለአገርም ለወገንም ይጠቅማል የሚል ግምት አለኝ።

******

ጄኔቫ፣ ሜይ 22 ቀን 2020 ዓ/ም

wakwoya2016@gmail.com0

Back to Front Page