Back to Front Page

የሃገር መከላከያ ሰራዊት ቃል-ኪዳን እና የህገመንግስት አጣብቂኝ

የሃገር መከላከያ ሰራዊት ቃል-ኪዳን እና የህገመንግስት አጣብቂኝ (Constitutional Deadlock):

 

Esayas Hailemariam May 7, 2020

 

(ሀ) ትእዛዝ ማክበር ወይስ ለቃለ-መሃላ መገዛት? Following Order or Upholding Oath?


፩) ቃለ-መሀላ/Oath:


በመከላከያ ሰራዊት አዋጅ 1100/2019፣ ክፍል 2 አንቀፅ 8 መሰረት፣ "ማንኛውም ምልምል ወታደር መሰረታዊ የዉትድርና ስልጠናውን እንዳጠናቀቀ [...ህዳግ/omitted...] ወታደራዊ ቃለ-መሐላ ይፈፅማል" ይልና፣ አንቀፅ 9 (2) ደግሞ "ማንኛውም የሰራዊት አባል፣ ሕገ-መንግስቱን እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን የማክበርና ማስከበር ግዴታ" እንዳለበት፣ የቃለ-መሃላው ዋና አላማም ሕገ-መንግስቱንና የህገመንግስታዊ ስርዓቱን ማስከበር መሆኑን ይጠቁማል።military-and-constitution.jpg

፪) ትዕዛዝ/Order:


በተጨማሪ፣ በአዋጁ ክፍል 2፣ አንቀፅ 9፣ ንዑስ አንቀፅ (3) መሰረት፣ "የሰራዊቱ አባል፣ ሌሎች የሃገሪቱን ህጎች፣ ወታደራዊ ህጎች፣ መመሪያዎችና ቛሚ ትእዛዞችን የማክበር ግዴታ[ም]" እንዳለበት ያስረዳል።


(ለ) የህጎች ተዋረድ /Hierarchy of Laws:


፩) ሕገ-መንግስት /Constitution:
በኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 9 (1): "ሕገ-መንግሥቱ የሀገሪቱ የበላይ ሕግ ነው፡፡ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር፣ እንዲሁም የመንግሥት አካል ወይም ባለሥልጣን ውሳኔ ከዚህ ሕገ መንግሥት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም" በማለት ሕገ-መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግ (supreme law) ብቻ ሳይሆን ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ትእዛዝ፣ ውሳኔ፣ ደንብ፣ አዋጅ ወዘተ…ከሕገ-መንግስቱ ከተቃረነ ተፈፃሚነት እደሌለው ያስረዳል።


በሆኑም፣ አንድ የሰራዊት አባል ቃል ከገባለት የህገመንግስት ድንጋጌ የማይቃረኑ ውሳኔዎችን፣ ትእዛዞችን፣ መመሪያወችን ብቻ ያከብራል ማለት ነው። በ ሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9 (1) በግልፅ እንደሰፈረው፣ የማናቸውም የመንግስት ባለስልጣን፣ የአስፈፃሚ አካል እና ሃላፊ ትእዛዝ ወይም መመሪያ የሕገመንግስቱን መሰረታዊ መርሆዎች ከጣሰ ተፈፃሚ እንደማይሆን ያመላክታል።


፪) የበታች ህጎች/ Subordinate Legislations:


ሕገ-መንግስቱን ለመሙላት የሚወጡት የበታች ህጎች፣ ለምሳሌ፥ የፓርላማ አዋጆች፣ የሚኒስትሮች ምክር-ቤት ደንቦች፣ የመከላከያ ሚኒስቴር መመሪያዎች፣ የበላይ መኮነን ትእዛዞች ከሕገመንግስቱ ተቃርኖ ካላቸው ቅድሚያ ሊሰጠዉ የሚገባው ሕገ-መንግስቱ ይሆናል ማለት ነው።


(ሐ) ትዕዛዝ ወይስ ቃለ-መሀላ/Order vs. Oath?


ሕገ-መንግስት የህጎች የበላይ ስለሆነና የሰራዊት አባላት በቀዳሚነት ቃለ-መሃላ የሚገቡት ህገመንግስቱን ለመጠበቅ በመሆኑ፤ በሌላ መልኩ፣ አዋጆች፣ ደንቦች፣ መመሪያዎች እና ትእዛዞች ተፈፃሚነታቸዉ ከሕገ-መንግስቱ በታች ስለሆነ፣ የህግ ተቃርኖ ሲከሰት፣ ከመመሪያ፣ ደንብ ወይም ሌላ ህግ ይልቅ ልእልና ላለው ሕገ-መንግስት እና ለህሊናችው ታማኝ ይሆናሉ ማለት ነው።


(መ) አለማቀፍ ልምዶች/International Norms:


አለመረጋጋትና ብጥብጥ በሰፈነባቸው ሃገራት የመከላከያ ሰራዊት ጣልቃ እንዲገባ በሚታዘዝበት ወቅት ሰራዊቱ ሶስት መሠረታዊ የህሊና ግጭቶችን ያስተናግዳል:


● እንዲከላከልና እንዲጠብቅ ቃል የገባለት ሲቪል ዜጋ ላይ ጉዳት ማድረስ የሚፈጥረው የስነልቦና ተፅእኖ (insoluble moral dilemma)፣


●ጉዳት ካደረሰ ሊከተል የሚችለውን በ አለም አቀፍ የጦር ወንጀለኛ ፍርድ ቤት (international military tribunal) ተጠያቂነት ስጋት፤


● በሌላ መልኩ፣ የበላይ አለቃን ትእዛዝ (superior order) ባለማክበር የማእረግ መነጠቅ (reduction in rank)፣ ያለ ክብር መሰናበትና (dishonorable discharge) ብሎም በወታደር ፍርድ ቤት (martial court) መጠየቅን እስከ መፍራት ይደርሳል::፩ኛ) ምሽግ መቀመጥ፣ አለመሳተፍ/Quartering:


በመንግስትና ዜጎች መካከል ፍጥጫ፣ የርስበርስ ግጭት፣ ህዝባዊ አመፆች ሲቀሰቀሱ፣ ያንዳንድ ሃገራት ልምድ እንደሚያሳየው፣ የሰራዊት አባላት ምሽግ ውስጥ ወይም የተለየ ቦታ በመቀመጥ፣ በገለልተኝነት የየትኛውንም ጎራ ባለመደገፍ (neutral/passive)፣ ሊከሰት ይችል የነበረን አላስፈላጊ ደም መፋሰስ በማስቀረት፣ ሰላማዊ፣ ህጋዊና ሁሉን ያሳተፈ ዘላቂ መግባባት እንዲፈጠር የሚያደርጉበት ስልት አንድ ቦታ በመቀመጥ አለመሳተፍ /quartering/ ነው።


"The dominant strategy for militaries during moments of crisis is quartering—remaining confined to the barracks—and refusing to take sides. This finding is confirmed by... miIlitary actions during three constitutional crises in Latin America—Argentina in 2001, Venezuela in 2002, and Bolivia in 2003." David Pion-Berlin and Harold Trinkunas-Comparative Politics
Vol. 42, No. 4 (July 2010), pp. 395-411, New York University.


ከላይ የተጠቀሰው ጥናት እንደሚያሳየው፥ በላቲን አሜሪካ:- (፩) አርጀንቲና በ 2001(፪) ቬኔዙዌላ በ 2002 እና (፫) ቦሊቪያ በ 2003 [እ.ኤ.አ]፣ ሀገራዊ አለመረጋጋት በተከሰተ ወቅት የመከላከያ ሰራዊት ገለልተኛ ያለመሆን ሊያመጣ የሚችለውን ህዝባዊ ቀውስ እና የህገመንግስት ኪሳራን ያመላክታል። በአፍሪካም፣ በቡርኪናፋሶ [እ.ኤ.አ 2014]፣ከ ፕሬዝደንት ኮምፓሬ (Compaoré) ስልጣን መልቀቅ ጋ በተያያዘ በተፈጠረ አለመረጋጋት ሰራዊቱ ጣልቃ በመግባቱ፣ ስልጣን በወታደር እጅ ገብቶ የህገመንግስት ኪሳራ ተከስቷል።


Videos From Around The World

በሌላ መልኩ፣ የመከላከያ አባላት ገለልተኝነት (impartiality) ተቋማዊ ነፃነት (institutional independence) ከሚለካባቸው መስፈርቶች አንዱ የአባላቱና አመራሩ ከፖሊቲካ ፓርቲ እና ወገንተኝነት ነፃ መሆን ነው። የመከላከያ አባላት የሚያገለግሉት ሃገርንና ህዝብን፣ የሚጠብቁት ደግሞ ሕገመንግስት እስከሆነ ድረስ፣ የፖሊቲካ ፓርቲ ተፅዕኖን የሚቋቋም፣ ለህሊናዉና ህግ ታዛዥ የሆነ ሰራዊት የሞራል ልዕልና ይኖረዋል።


(ሠ) የኢትዮጵያ ተሞክሮ /the Ethiopian Case:


“ምርጫ ለማድረግ በሚነሳ ላይ እርምጃ እንወስዳለን”- ጠቅላይ ሚኒስቴር አብይ አህመድ


ሕዝብ ተገዶ በምርጫ ሂደት እንደማይሳተፍ ሁሉ፣ ተገዶ እንዳይሳተፍ ማድረግም አይቻልም፤ ምክኒያቱም፣ ምርጫ በህዝብ ፍላጎትና ፍቃድ የሚከወን ሂደት በመሆኑ። ምርጫ ለማድረግ መጣር ትርጉም ላለው ዴሞክራሲ (functioning democracy) መሰረት ሲሆን፣ ምርጫ እንዳይደረግ መጣር ደግሞ በተቃራኒው።


በህግና ስርዐት፣ ከስሜት ይልቅ በእውቀት የሚመራ ሀገር ለ አላስፈላጊ ኪሳራ፣ ደም መፋሰስና የምጣኔ ሃብት ውድቀት አይዳረግም። ህግ ማክበርና በህግ መመራት ስንል፣ በመጀመሪያ ሀገሪቱ የምትተዳደርበትን ህገመንግስት፣ ከዚያም በየደረጃው ያሉ ህጎችንና ደንቦችን ማክበር ሲሆን፣ ሀገሪቱ ካለችበት የህገመንግስት አጣብቂኝ፣ የፖሊቲካ አለመረጋጋት፣ የዴሞክራሲ ባህል አለማበብ፣ እንዲሁም የዳበረ ነፃ የፍርድ ተቋም (independent judiciary) ያለመኖር፣ በቀጣይ እጣ ፈንታው ያልታወቀ የምርጫ ሂደት ሲጨመር፣ ሊፈጠር የሚችልውን አደጋ በሰከነ፣ ከፖለቲካ ወገንተኝነት በፀዳ፣ ህገመንግስትና ህሊናን ያማከለ መንገድ መከተል አላስፈላጊ ዋጋ ከመክፈል ያድናል።


ወታደራዊ መመሪያዎች፣ ትእዛዞችን፣ ደንቦችን በሚመለከት የመከላከያ ሰራዊት አዋጅ 1100/2019፣ ስለ መሰናበት- ክፍል 3፣ አንቀፅ 21 (2)፤ ስለ የወታደር ፍርድ ቤት ስልጣን- ክፍል 5፣ አንቀፅ 37-39፤ በወታደር ፍርድ ቤት ስለሚወሰን የሞት ቅጣት-ክፍል 5፣ አንቀፅ 42 ድንጋጌዎች ተቀምጠዋል።


ልማዳዊ የአለማቀፍ ህግ (customary international law)፣ የኢትዮጵያ ሕገመንግስት፣ በታጠቁ ሰዎች የሚደረግ ግጭትን በሚቆጣጠር ሕግ (law of armed conflict)፣ እንዲሁም የሃገራት ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ህዝብ ምርጫ ለማድረግ በማሰቡ ጦርነት የሚታወጅበት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት እንደሌለ ሁሉ፣ ሕገ-መንግስቱን ተከትሎ "በንፁሃን ዜጎች ላይ ጉዳት አላደርስም" ያለ የሰራዊት አባልም በወታደራዊም ይሁን መደበኛ ፍርድ ቤት በህግ የሚጠየቅበት አገባብ የለም።


በመሆኑም፣ ለህግና ሞራል ተገዥ የሆነ ሰራዊት ሊከሰት የሚችልን አላስፈላጊ ጉዳት በማስቀረት ሃገርን ከህገመንግስት ኪሳራ 'ና ፍጂት ይታደጋል።


 


Disclaimer:
ችግርን ነቅሶ ማውጣት የመፍትሄው ግማሽ መንገድ ነው። ችግር ከመከሰቱ በፊት ውይይት ማድረግ ደግሞ የሰለጠነ አካሄድ ነው። የዚህ ፅሁፍ አላማ፣ ችግሮችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የመፍታን ጥቅም ከማሳየት ውጭ ሌላ አላማ የለውም። የተሻለ ሃሳብ ያለው/ላት፣ በሃሳቤ የማይስማማ ወይም ጥያቄ ያለው አካል በኢሜይሌ: esayas.law@berkeley.edu ሊያገኘኝ ይችላል።


 

 

Top of Form

Bottom of Form

 

Back to Front Page