Back to Front Page

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀይ መስመር

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀይ መስመር

 

ከጡረተኛው ሻምበል አታክልቲ ገብረፃዲቅ

መቐለ

ጥቅምት 2013 ዓ/ም

 

መግብያ

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አፈጣጠር ልዩ የሚያደርገው ከህዝቦች አብራክ የወጣ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የጭቆና ቀንበር ለመስበር ከህዝብ ጎን በመቆምና በመታገል የህዝብ ትግል ግንባር ቀደም ተዋናይ ከሆነው ትውልድ ጭምር የተፈጠረ መሆኑ ነው። ይህ ተፈጥሮው በአገሩ ብቻ ሳይሆን እስካሁን ድረስ በዓለም አቀፍ የሰላም ማስከበር ግዳጅ ላይ በተሰማራባቸው አገሮችም የተረጋገጠ ነው። ህዝባዊነቱ ከሌሎች አገሮች ሰራዊቶች በመሰረቱ የተለየ ሆኖ እንዲታይና የህዝብ ፍቅርና አለኝታነትን እንዲጎናፀፍ አስችሎታል። የሰራዊታችን መሰረታዊ እሴት በጠንካራ ዲሲፒሊን ከራስ በላይ የአገርና የህዝብ ጥቅም ማስከበር ላይ የተመሰረተና የህገመንግስቱ የመጨረሻ ምሽግ እንዲሆን ተደርጎ የተገነባ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዋና ጠላት የሆነውን ድህነት ለማጥፋት አገራችን በምታደርገው ትግልም ሰራዊታችን ለዕድገትና ለዲሞክራሲ ግንባታ መሰረት የሆነውን ሰላምና መረጋጋትን በማረጋገጥ ወደር የማይገኝበት ሚና ሲጫወት ቆይቷል። አገራችን በልማትና በዲሞክራሲ ስታስመዘግባቸው የቆየቻቸው ዕድገቶችና ለውጦችም ላይ የራሱን ደማቅ አሸራ ሲያስቀምጥ ቆይቷል።

 

ነገር ግን በአሁን ወቅት አገራችን ጀምራው የነበረችው ፈጣን የልማትና የዕድገት ለውጥ በተለያዩ የአመራር ችግሮችና እጥረት ተደናቅፎ ቀውስ ውስጥ ገብታ ለመውጣት እየዳከረች የምትገኝበት ወቅት እንገኛለን። በአመራር ውድቀት ምክንያት የፖለቲካ፣ የዴሞክራሲ፣ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ቀውስ ውስጥ ስለገባን የአገራችን ህዝቦች በሰላም እጦት ታምሰዋል፣ መረጋጋት ተስኗቸዋል፣ ሞት፣ መፈናቀልና የንብረት መውደም ዕለታዊ ክስተት ሆኖው ይገኛሉ። በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ ሆነና አገራችን በአየር መዛባት ምክንያት በድርቅ፣ በጎርፍ አደጋ እና በአንበጣ መንጋ ጥቃት ከአስራ ሁለት ሚልዮን ህዝብ በላይ የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሆናል። በተጨማሪም የውጭ ሀይሎች በሰበብ አስባቡ ሉዓላዊነታችንና ነፃነታችንን ደፍረውት ይገኛሉ። የፖሊሲ ነፃነታችን ተቀምተናል። ስለ ቀጣይ ጉዛችን ትዕዛዝ የሚሰጡን ሐያላን የውጭ ሀይሎች ናቸው። ከኛ አገር የማይሻሉ አገሮችም ጌቶቻችን አየሆኑ መጥተዋል።

 

በአጠቃላይ በለፉት ሁለት ዓመታት የአገራችን ሁኔታ ከመሻሻል ይልቅ በሁሉም ሁኔታ በእጅጉ እየከፋ ነው። አገሪቱ ወደ መፍረስ እና ህዝቦችዋም የመበታተን አደጋ አፋፍ ላይ እየደረሱ ነው። በዓለማችን እንደታየው ትናንት አንቱ ይባሉ የነበሩ አገሮች በትንሽ ምክንያት የተጀመረው ችግር በእንጭጩ ባለመፈታታቸው እያደገ መጥቶ ፈራርሰው ህዝባቸው ለእልቂትና ለስደት ተዳርገው እያየን ነው። በተጨባጭ ሶርያ፣ ሊብያና የመን እንደ አገር ፈራርሰው እያየን ነው። ህዝባቸው ተፈናቅሎ በየአህጉሩና በየአገሩ ተሰዷል። በአገራችን በሚገኙ ዋና ዋና ከተማዎች ጭምር መንገድ ዳር ህፃናት ልጆቻውን ታቅፈው ሲለምኑ እያየን ነው። ትናንት በአገራቸው የራሳቸው ቤት የነበራቸውና ልጆቻቸውን ትምህርትቤት ልከው የሚያስተምሩ ዜጎች እንደነበሩ ማስታወስ ተገቢ ነው። የገጠማቸው ነገር በዳተኝነታቸው ምክንያት የአገራቸው ሁኔታ ከመቅፅበት ተቀያይሮ በህይወታቸው ገጥሟቸው ብቻ ሳይሆን ገምተውት የማያቁቱን የአገራቸው የመፍረስ ክስተት ስለአጋጠማቸው ነው። ነግበኔ ነው! አገራችን ኢትዮጵያም ወደ እንደዚህ አገራት ሁኔታ በፍጥነት እየነጎደች ትገኛለች። በፍጥነት መፍትሔ ካላበጀን አደጋው መከሰቱ አይቀሬ ነው።

 

በአጭሩ የአገራችን ዋና ዋና መገለጫዎችና የመከላከያ ሰራዊታችን ሁኔታና ቁመና በማየትና በመተንተን የመከላከያ ሰራዊታችን አገራችን ኢትዮጵያ ከመፍረስ ለመታደግ መቼ ጣልቃ ገብቶ የማዳን ግዴታው ይወጣል? ቀይ መስመሩ ምን ሊሆን ይገባዋል? ቀይ መስመሩ ሲታለፍ ምን ማድረግ ይኖርበታል? በሚሉት ነጥቦች ላይ እንደሚከተለው እዳስሳሎህ።

 

የአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ

Videos From Around The World

በአገራችን በአሁኑ ወቅት ሰላም የለም። ሞትና ግድያ ከተራው ህዝብ አልፎ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው ባለስልጣናት ጭምር አዳርሷል። የአገሪቱ ቁልፍ አመራሮች በጠራራ ፀሐይ የሚገደሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ገዳዩችም የራሱ የፀጥታ አካላት መሆናቸው ችግሩ ምንኛ ስር የሰደደና ውስብስብ መሆኑ መገመት አይከብድም።ሠራዊቱም የአመራራችን ግድያ በተመለከተ ማብራርያ ይሰጠን ጥያቄ ጠብቁ በማለት እንዲረሳ እና ምርመራው ሲያልቅ ከህዝቡ ጋር አብሮ ሲገለፅ ትሰሙታላቹህ በሚል የረባ መልስ ሳያገኝ ቀረ።

 

በአገራቸን ልማት አጀንዳ መሆኑ ከቀረ ቆይቷል። የአገራችን ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘና አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው። ሰው በሰላም ወጥቶ በሰላም መመለስ እርግጠኛ ባልሆነበትና በየትኛው የአገሪቱ ክፍሎች መዘዋወር በማይችልበት ሁኔታ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ልማት ይኖራል ብሎ መገመት ያዳግታል። ሙስና ከነበረው በላይ በእጅጉ በመስፋፋቱ በንፅህና የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች በልማት ዙርያ ለመሳተፍ የሚያሳዩት ፍላጎትና የሚያደርጉት እንቅስቃሴ እየሞተ ይገኛል። በአጠቃላይ የኢኮኖሚው አሰራር ከአገር ውስጥ ባለሃብቶች ይልቅ ቅድሚያ ለውጭ ሰዎችና ካምፓኒዎች ዕድል እየተሰጠ ነው። የአገር ባለሀብቶችን እያንቆሸሹ ለውጭ ካምፓኒዎችና በተስፋ ኢንቬስት እናደርጋለን ለሚሉ የስራ ዕድል እየተሰጠ ነው። በሰላሙና በልማቱ ጊዜ ሀብት ያፈሩ ባለሀብቶች ለብልፅግና ስብከት በግዴታ የገንዘብ ድጋፍ አድርጉ ተብለው ከእስርና ከግድያ ለማምለጥ የቀራቸውን ገንዘብ አራቁተው በማዋጣት ህይወታቸውን አትርፈዋል። በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ባለሀብቶችና ኢንቨስተሮች ሰላም በአገሪቱ ሁሉም አከባቢዎች ባለመኖሩ ኢንቨስትመንታቸውን እያቃረጡ ባሉበት ወቅት አዳዲሶች ኢንቨስትመንቶች ይጀምራሉ ማለት ዘበት ነው።

 

በተመሳሳይ ሁኔታም የለውጥ ሀይል ነኝ የሚለው ቡዱን አትራፊና ያገር ኩራት የነበሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድና ቴሌኮሚኒከሽን በከፊል ለመሸጥ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል። ከጎረቤት አገር ኬንያም ለመማር አልፈለገም። ኬንያዊያን አየር መንገዳቸውን በከፊል ሽጠውት የነበረ ቢሆንም ለብዙ ሚልዮን ዶላር ኪሳራ ስለዳረጋቸው ከኢትዮጵያ ተምረው አየር መንገዳቸውን ተመልሰው ሙሉ በሙሉ የመንግስት ለማድረግ በአሁኑ ወቅት እየተሯራጡ ይገኛል። በተቀራኒ ደግሞ የኛው መንግስት ተብይ ምንም ችግር የሌላባቸውን የአገሪቱ የኢኮኖሚ አውታር የሆኑ ካምፓኒዎች ለመሸጥ መሯራጡን ተያይዞታል። ይህም ከልማታዊ መንግስት መንገድ በመውጣት በኒዮ ሌበራሎች ተፅእኖ ስር መውደቁና የነሱ መሳርያ እየሆነ መምጣቱ ማሳያ ነው።

 

የሉዓላዊነት ዋና መገለጫው የፖሊሲ ነፃነት መኖርና የውጭ ንግድን ተፅእኖ መቀነስና መቋቋም መቻል ማለት ነው። እንደ አገር ቀደም ብለን የተበደርነውን አለምአቀፍ ብድር በየአመቱ ትንሽ በትንሽ መክፈል በመቻላችን በአበዳሪዎቻችን እምነት አሳድረን መልካም ገፅታም ፈጥረን ነበር። አሁን ግን ታጥቦ ጭቃ ሁነን የተበደርነው ብድር መክፈል ተቸግረን ተጨማሪ ብድር የሚሰጠን የታጣበትና በፈጣኑ የኢኮኖሚ እድገት ያስፋፋናቸውና ያፈራናቸውን ሀብቶች ለመሸጥ የተገደድንበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ ጀምሮ የነበረው ድህነት ተመልሶ ጥርሶቹን አሽሎ እየመጣ ነው። ለነገሩ ያሉን አንጡራ ሀብቶቻችን ሽጠን ሽጠን የሚሸጥ ስናጣ ምን እንደሚከተል ከአሁኑ መገመት አያስቸግርም። ለውጭ ሀይሎች ተጋላጭነታችን ጨምሮ አገሪቱ ህልውናዋ አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ጥርጥር የለውም።

 

የኢትዮጵያ ህዝቦች የትናንትናው ጥያቄዎቻቸው መልካም አስተዳደር እንዲሰፍንላቸው፣ ስራ አጥነት እንዲቀረፈላቸውና ፍትሕ እንዲነግስላቸው ነበር። ጥያቄዎቻቸው ከተመዘገበው ልማት የተሻለና ፍጥነቱ የጨመረ ብልፅግና እንዲመጣና እንዲስፋፋ እንጂ ተስፋ ሰጪ የነበረው ዕድገት ጠፍቶ ድሮ ወደ ነበርንበት እንድንመለስ አልነበረም። እንደ ድሮ በድህነት አረንቋ መኖር በአሁን ግዜ አይቻልም። የህዝብ ብዛት በተለይም የወጣት ቁጥር መጨመር፣ የኑሮ ውድነት መናር፣ የቴክኖሎጂ ፈጣን ዕድገትና የኢንፎርመሽን ስርጭት ቀላል መሆንኑና (በእያንዳንዱ ሞባይል በያዘ ሰው ቁጥጥር ስር መውደቅ) ያስከተለው የአስተሳሰብ ለውጥና ተጨባጭ ሁኔታ በድህነት ለመኖር ከባድና ውስብስብ አድርጎቷል። አማራጩ በህልውና ለመኖር ፈጣን ዕድገት ብቻ ነው። ከዛ ውጭ ጥፋትና የአገራችን ኢትዮጵያ ህልውና አደጋ ላይ መውደቅ ነው።

 

ለአለፉት 30 ወራት ለውጥ/ሪፎርም በሚባል ውሉ ባልታወቀ አባዜ ስንዳክር ወደ ወደፊት ሳይሆን በፖለቲካውም፣ በኢኮኖሚውም፣ በዲፕሎማሲው እና በጭራሽ በሰላምም ወደ ኃሊት በመጋዝ ላይ እንገኛለን። አገራችን የሚመራት እንደሌለ ሁሉ አገርችን ስትፈርስም የሚታደጋት እንደሌለ ታይቷል። ገዳይና ተገዳይ እኩል ጀግኖች ነበሩ የሚል አመራርና ድርጅት በውል አለ ማለት ያስቸግራል። አመራሩና የሾማቸው የመከላከያ ኤታማዦር ተገድሎበት ምርመራ አድርጎና በየጊዜው የምርመራ ውጤቱን የማይገልፅና ተጠያቂ የማይዝ አመራር በጤና አለ ማለት አይቻልም።

 

ባለፉት ዓመታት የተመዘገበው ፈጣን የኢኮኖሚ ለውጥ በብቃት የመራው ኢህአዴግ በስልጣን ጥመኞችና ሴረኞች አቅሙ ሽባ እንዲሆን በመደረጉ፣ ያጋጠመውም ቀውስ ለመፍታት ሳይችል በመቅረቱ እና ውስጡ በልዩነት በመወጠሩ ምክንያት ውስጡ የተቦረቦረ ድርጅት ሆኖ እንደነበር ይታወቃል። በአሻጥር በኢህአዴግ ውስጥ ህጋዊ በሚመስል ሴራ ከፓርቲው ህገ ደንብ ውጭ በድብቅ ምስጥራዊ ቡዱን በመፍጠር ፓርቲ ውስጥ ሌላ ፓርቲ ማደራጀት ተቻለ። በዚህም ኢህአዴግ በአንድነትና ወጥ የሆነ አመራር መስጠት እንዳይችል በስመ ለውጥ በምርጫ ያገኘውን ኮንትራት ሳይፈፅም ሆነ ተብሎ በቅድምያ እንዲፈርስ ተደረገ። ኢህአዴግ ካልፈረሰ ስልጣኑን ለማደላደልና ማራዘም እንደማይችል አውቆ ኢህአዴግን በማፍረስ ሌላ ባዕድ ፓርቲ ፈጠረ። በአንድ ሰው የሚዘወር ህገወጥ አዲስ ፓርቲ ራሱን ብልፅግና ብሎ ከፓርቲ አዋጅ ህግ ወጭ ተመሰረተ። ጉባኤ አድርጎ አመራሩን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ምርጫ ሳያደርግ በቡዱን ራሱን መሪ አድርጎ ሾመ። ህገመንግስቱ ስልጣን የሚገኘው በምርጫ ብቻ ነው የሚለውን ህገ መንግስታዊ ድንጋጌ በመጣስና በህዝብ ባልተመረጠበት ፕሮራም በኃይል ስልጣን ተቆጣጠረ። የህዝብ ውክልና የሌለውና ያልተመረጠ መንግስት ሆኖ ቀጠለ። በጉልበት! ከዚህ በፊት ፈጣን ዕድገት እንዲመጣ ያስቻለውን የሰላም፣ የልማትና የዲሞክራሲ መስመርና ፖሊሲ ጥሎ አቅጠጫው ወዴት አንደሆነ በማይታወቅ መንገድ አገሪትዋንና ህዝቦችዋን ይዞ ነጎደ።

 

 

ይህ ቡዱን የህዝብ ጥያቄዎች በዴሞክራሲያዊ መንገድ፣ በውይይትና በህግና በህግ ብቻ መፍታት እየተገባው አንድም ጥያቄ መፍታት አልቻለም። እንዳውም ሁኔታዎች በማባባስና በማጓተት ህዝብ በብስጭት ወደ አልተፈለገ የሀይል እርምጃ እንዲገባ በማድረግ ከፖሊስ በተጨማሪ የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንዲበታተኑ አደረገ። በህዝብ የሚከበረውና የሚወደደው የመከላከያ ሀይላችን ከህዝብ ጋር ፊት ለፊት እያጋጨ የነበረውን የህዝብ ተቀባይነትና አለነት እንዲሸረሸር አድርጎቷል። አመራሩ ራሱ መጋፈጥ ሲገባው በአመራር ውድቀቱ ምክንያት የተፈጠሩ ችግሮች ወደ ህዝቡ በማላከክ በህዝባዊነቱ የሚታወቀው የሰራዊታችን ሀይል ተጠቅሞ ከህዝቡ እንዲላተም እያስገደደው ነው። ኮ/ል አብይ በአገሪቱ ውስጥ ከአፋርና ከትግራይ ክልሎች በስተቀር ህገመንግስታዊ ያልሆነ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ ባልተመረጠና ሲቪል ባልሆነ ሀይል እያስተዳደረው ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።

 

በአሁኑ ወቅት መከላከያ ሰራዊታችን የራሱ የሆነ የስጋት ትንታኔ አስቀምጦ በሱ የተመሰረተ የወደፊት ራዕይና ተልእኮ ይዞ እየተዘጋጀ አይደለም። የይሆናል ጦርነት በየት አቅጣጫ ይመጣል ብሎ በየትኛው ዶክትሪን እንደሚዘጋጅና እንደሚዋጋ አያቅም። እንደ ሚሊሻና ፖሊስ በመላው አገሪቱ ተበትኖ ይገኛል። ሆን ተብሎ ፀረ ህዝብ እርምጃ እንዲወስድ በማድረግ የመከላከያችን ባህርይ ህዝባዊነትና ህገ መንግስታዊነት እንዲሸረሸር እያደረገው ነው። መከላከያም የሰዎች ስብስብ ስለሆነ በዚህ ግልፅ ባልሆነ ራዕይና ተልእኮ ሆኖ በህገ ወጥ መንግስታዊ ስልጣን በያዘው ብልፅግና ውስጥ ያሉ ኃላ ቀር አስተሳሰቦች ተፅእኖ ውስጥ እየወደቀ መሆኑ እየታየ ነው። ትላንት ከልብ ሲቀራረቡ የነበሩ ወታደሮችና መኮነኖች ዛሬ የብሄር ጎራ ፈጥረው አይቀራረቡም። ቢቀራረቡም ልብ ለልብ አይሰጣጡም። ይህ አሁን በስልጣን ያለው ቡዱን ለስልጣን መወጣጫ ብሎ የፈጠረው ብሄርን ማዕከል ያደረገ ቅዱስ ያልሆነ ቡድነኝነትና በሌሎች የጥላቻ ስራ መስራቱ የፈጠረው ተፅእኖ መከላከያችንም ውስጥ ገብቶ አንድነቱን እንዲሸረሸር አድርግታል።

 

ኮ/ል አብይ አገር መምራት ይቅርና ብርጌድና ክ/ጦር መምራት እንደማይችል እያወቀና እየታወቀ በስንት እጥፍ የሚበልጡትን ጀነራል መኮንኖች ሰብስቦ ከዛም ከዛም የለቃቀመው፣ ያልተሟላና ያልበሰለ፣ በጥልቀት የማያቀውን ግን የሚያቀው የሚመስለውን ዕውቀት ለማስተማር በተደጋጋሚ ሞክሯል። አሁን አሁን ደግሞ የተመረጡ የበላይ መኮነኖችን ለይቶ በመጥራት ከፋፋይ የሆነ ስበካ እያደረገ መከላከያ ሰራዊቱ የእናት ልጅና የእንጀራ ልጅ እያወጣለት ነው። ከስጋት ለመዳንም በሹመትና በገንዘብ እየደለለ ለመያዝ እየመኮረ ነው። በስብእናቸው የማይደለሉትን ደግሞ አንተ የለማ መገርሳ፣ የጁሓር፣ የኦነግ፣ የህወሓት እና ወዘተ ነህ በሚል ያለወንጀላቸው እየወነጀለ ማሸማቀቁን ተያይዞታል። ለሌሎቹ ደግሞ በግል ጠርቶ ልመናም ማስፈራርያም አስምቷል፣ በምደባ ስም ምንም ስራ ወደ ማይሰሩበት ቦታና ከአገር ውጭ አርቆ መድባቸዋል፣ የጠቀመቻው አስመስሎ ደግሞ በተለየዩ ሁኔታዎች አግልላቸዋል፣ በጡረታም ቀድሞ ሸኘታቸዋል፣ ያለ ስራ ደሞዝ እየተከፈለው የሚንሳፈፍም ደግሞ አለ። ይህ ዘዴ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ በጣም የሚወደው አሰራር ነው። ዘዴው ማደስከል ወይም ማበስበስ ይባላል። ለዓመታት ደሞዝና መኪና ተመድቦልህ ያለ ስራ ቁጭ ብለህ እያብሰለሰልክ እንድትኖርና በዚያውም እንድትበሰብስ ይደረጋል ማለት ነው። አሁን ይህ ከላይ ያየነው ሁኔታ የሰራዊታችን የእርስ በርስ መተማመንና የሞያው ፍቅር በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው ይገኛል። በቅርቡ ደግሞ ወጥተው የነበሩት የመካላከያ ሽማሙንትና አባላት ወደ መከለከያ እንዲቀላቀሉ እያደረገ ነው። ያሉቱን ያላቸው አቅም በቅጡ ሳይጠቀም፣ ሳይመራ፣ ሳያምን በተለያየ ሁኔታ የተወገዱትንና ጥሮታ የወጡትን ተሞልሶ ማስገባት ተጨማሪ ክፍተት ይፈጥር እንደሆነ እንጂ ለመከለከያ ሰራዊቱ ለውጥ አይኖርም።

 

በየትም አገር የአገር ሉዓላውነት የመጨረሻ ምሽግ መከላከያ ነው። በግብፅ፣ በቱርክ እና በቅርቡ ዶግሞ በሱዳን የታየው ይህ ነው። አገር እንደ አገር እንዳይበታተኑ የመከላከያ ሰራዊታቸው የሰጠው ምላሽ ማየት ይቻላል። አገር በማንኛውም ምክንያት ከፈረሰ ፈርሷል። ከፈረሰ በኃላ ሉዓላዊነት የሚባል ነገር የለም። ሰራዊትም አብሮ ይፈርሳል። ለፈረሰ አገር ስራዊት አያስፈልገውም። ሊኖረውም አይችልም። ቢኖረውም በቡዱን በቡዱን ተቦድኖ እርስበራሱ እየተጨራረሰ እልቂቱን የሚያፋፍም ነው የሚሆነው። በሶማሊ፣ በሊብያና በመን እይታየ እንዳለው የየአካባቢ የጦርነት ጌቶች /war lords/ ዓይነት በመፍጠር በየቀኑ እርስ በራሱ በሞት የሚቆላ ነው የሚሆነው። ይህ ሳይሆን የመከላከያ ሰራዊታችን አገር ከእልቂት፣ ከብተና እና ከመፍረስ እንዴት ለመታደግ ይችላል? ቀይ መስመሩ ምን ሊሆን ይችላል ብለን ማየቱ ተገቢ ነው።

 

 

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቀይ መስመር

የአገር ህልውና ከሁሉም ስጋቶች በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው የደህንነት ጉዳይ ነው። ሌሎች ከባድ የአገር አጀንዳዎች የሚባሉት ሁሉም ከአገር ህልውና አንፃር ሲታዩ አንገብጋቢ አይደሉም። በማንኛውም መንገድ የአገር ህልውናን መጠበቅ ከሁሉም ጉዳይ በላይ የሚታይ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የህልውና ጉዳይ ማለት መሰረታዊ የብሄራዊ ጥቅም የሚጎዳና አገር እንደ አገር ህዝብ እንደ ህዝብ የማቀይጥልበት ሁኔታ መፈጠርን ይመለከታል። ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው። ይዋል ይደር መባል የማይገባው ብቻ ሳይሆን የማይቻል ጉዳይ ነው። ሰለዚህ የህልውና አደጋ ቀይ መስመር ላይ ደርሰናል የምንለውና መከላከያ ሰራዊታችን አገርና ህዝብን ማዳን አለበት የምንለው ምን ሲሆን ነው ብሎን ለይተን ማወቁ ከአደጋው ለመውጣትና ለመዳን ቁልፍ ጉዳይ ነው።

 

ቀይ መስመር አንድ፡-

ህገ መንግስቱና ፌደራላዊ ስርዓቱ እየተጣሰ ነው። የህዝቡ የበላይነትና ሉዓላዊነት መጣስ ቀይ መስመር ነው። ህዝቦች ወደ ፈለጉበት መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሮ ቆይቷል። ህዝቦች በማንኛውም የኢትዮጵያ ግዛት ክልል የመዘዋወርና የመኖር ህገ መንግስታዊ መብት ተጥሷል። መንግስትም ይህን ችግር መፍታት አልቻለም ሳይሆን በተዘዋዋሪ እያበረታታና እያባባሰ ነው። የፌደራል መንግስትም የክልል መንግስታትም እርምጃ ካለመውሰድ ጀምሮ በስተጀርባ እየገፋፉ በአደባባይ የጥላቻ ንግግር በማድረግ እያባባሱ መሆናቸው ይታወቃል። ተጠያቂ ባለመኖሩ በበርካታ ክልሎች ብሄር ተኮር ጥቃት ተስፋፍቷል። በዚህም የተገደሉ፣ የቆሰሉ፣ የተፈናቀሉ፣ ንብረታቸው የተዘረፉና የተቃጠለባቸው በሚልዮኖች እንደሚቆጠሩ የዓለም መገናኛ ቡዙን እየገለፁት ነው። ይህ ከአሁን በኃላ ከቀጠለ አገሪቱን ወደ ማፈራረስ የሚመራና ህገመንግስታዊና ፌደራላዊ ስርዓቱን የሚያናጋና ምሰሶ የሌለው አገር ፈጥሮ አገራችን የሶርያ፣ የሊብያና የመን ዕጣ እንዲደርሳት የሚያደርጋት ስለሆነ የህልውና ስጋት አድርገን መቁጠር ይገባናል። ቀይ መስመር ስንል ይህ አደጋ ማለታችን ነው።

 

የራስ ዕድል በራስ የመወሰን መብት ተጠቅሞ በነፃ ፍላጎት በህግ የበላይነት እና በራስ ፈቃድ የተመሰረተ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመገንባት ዓላማ ያለው ህገመንግስት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ በከፍተኛ ደረጃ ተጥሷል። በቅርቡ ደግሞ በስልጣን ያለው መንግስት ስልጠኑን ለማስረዘም ከህገ መንግስት ውጭ በመወሰን ህገ መንግስት ተጥሶ ምርጫ ከአምስት ዓመት በላይ ለማራዘም በህገወጥ መንገድ ተወስኗል። የስልጣን ምንጭ የሆነውን ብቸኛ መንገድ የሚጥስ ውሳኔ ወስኗል። ከህግ በላይ ሆኗል። ፀረ ህገ መንግስትና ፀረ ዲሞክራሲ መሆኑን አስመስክሯል። በኢትዮጵያ ህዝቦች ትግልና መስዋእትነት የተገኘው ዲሞክራሲ ዘላቂነቱ አደጋ ላይ ወድቋል። የህዝብ ጥያቄ በፖለቲካ መፍታት ቀርቶ በሀህሀይል፣ በመከፋፈል፣ በመደለልና በማስፈራራት ማዳፈን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ባህሪ መገለጫ ሆኗል። ምርጫ መካሄድ አለበት የሚሉ ሀይሎችና ከገዥው ፓርቲ በተለየ ሽግግር መንግስት ይመስረት የሚሉት ሀይሎች ላይም የጅምላ እስር እርምጃ ወስዳል። ምርጫ ባካሄደው ክልልም ጦርነት አውጆ ውግያ ጀምሯል።

 

ህገ መንግስት ማንም ይጣሰው ማንም ቅቡልነት የለውም። በስልጣን ያለውም የሌለውም ሁሉም ዜጋ ህገመንግስትን መጠበቅና ተገዥ መሆን አለበት። ህገመንግስት የሁለም ህጎች የበላይ ነው። ከህግ በላይ ደግሞ ማንም የለም። ስለዚህ ህገ መንግስትና ፌደራሊዝም ስርዓት ማፍረስ የህልውና ጉዳይ ስለሆነ ቀይ መስመር ነው።

 

ቀይ መስመር ሁለት፡-

ሰላም መኖር ለሀገር ህልውና ቁልፍ ጉዳይ ነው። ሰላም የሚረጋገጠው ደግሞ በወሳኝ መልኩ በህዝቡ ነው። የፀጥታ አካላት ድርሻ ብቻውን ወሳኝ አይደለም። ሰላም በመቻቻል፣ በመደማመጥ፣ በመከባበር፣ የህግ የበላይነት በመረጋገጥ፣ በመልካም አስተዳደር መርሆዎች መረጋገጥና በህዝቦች ዲሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ መብቶች መረጋገጥ ነው እውን የሚሆነው። የመንግስት የፀጥታና የህግ አስከባሪዎች የተረጋገጠው ሰለም የሚደፈርሱ ጥቂቶች ሲኖሩ ከህዝቡ ድጋፍ እየተደረገላቸው ሰላም ለማስከበር እጅ እና ጓንት ሆኖው ሲስሩ የአገሪቱ ሰላም የበለጠ አስተማማኝ ይሆናል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ግን መንግስት ይህንን መሰረታዊ ነገር ማሟላት አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን ሰላም እንዲኖር የሚያደርጉትን ጉዳዮች ብስመ ለውጥ ባለመፈፀሙና ባለማክበሩ ሰፊው ህዝቡ ሰላምና መረጋጋት ተስኖቷል። የዚህ የሰላም እጦትና የህውከት ምንጩ ደግሞ በስልጣን ማማ ላይ የተቀመጠውና ራሱን ብልፅግና ፓርቲ ነኝ የሚለውና የኮ/ል አብይ አመራር ውድቀት ነው። ይህ ቡድን የስልጣን ወንበሩን ዕድሜ ለማስረዘም ሁሉንም ነገር ለማድረግ የሚፈልግ ነገር ግን ሰላም ማረጋገጥ የማይችል፣ የመምራት ብቃት የሌለው፣ ያልተረጋጋ፣ የሚነካውና የሚይዘውን የማያቅ በመሆኑ ነው።

 

በመላው አገሪቱ በምዕራብ፣ በምስራቅ፣ በደቡብና በስሜን ተቃውሞ እየገጠመውና ተስፋ እየቆረጠ ሁሉን ነገር በሀይል፣ በአምባገነንነትና በግብታዊነት ለመፍታት ሲሞክር ሌላ ውስብስብ ነገር እየተፈጠረ ከባሰ ችግር ወደ ባሰ አዘቅት እየገባ የአገሪትዋ ህልውና ወደ ገደል አፋፍ እየከተተው ነው። በዚህ ምክንያት በአሁን ወቅት አገራችን በብዙ አከባቢዎችዋ በጎበዝ አለቃ የምትተዳደር አገር ሁናለች። ስርዓት አልበኝነት ነግሷል። ሰው ወደ ፈለገበት ቦታ እምነት ኖሮት መንቀሳቀስ የማይችልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ፌደራል መንግስት ይህን የፖለቲካ ችግር የፖለቲካ መፍትሔ እንደ መፈለግ በተደጋጋሚ በፌደራል ፖሊስና በመከላከያ ሰራዊት ጉልበት ለመፍታት እየሞከረ ነው የሚገኘው። የመከላከያ ወታደሮች ግጭት በተነሳባቸው ሁሉም ቦታዎች ወደ ፖሊስና ወደ ሚልሻ ዓይነት ስምሪት ተሰማርቶ ተበትኗል። ይህ የግዳጅ ስምሪት ሰራዊቱ ከተልእኮው ውጭ ማሰማራቱ ብቻ ሳይሆን ከህዝብ እንዲነጠልና መልካም ስሙና ገፅታው እንዲሸረሸር እያደረገው ነው።

 

ሰላም ማረጋገጥ የሚቻለው የህዝቡን ጥያቄ በፍጥነትና በህገ መንግስቱ መሰረት ሲፈተና የጥላቻ ንግግሮች የሚያደርጉና ይህን የሚያስተጋቡ ባለስልጣኖችና ሚድያዎች መጠየቅ ሲጀምሩ ብቻ ነው። የህገመንግስቱ መከበር ነው የሰላም ምንጭ። ህገመንግስታዊነት መጥፋቱ ነው ቀውስ ውስጥ ገብተን መውጫና መግብያው የጠፋት አገር የሆነው። የሰላም እጦትና አለመረጋጋት አገራችን ወደ ውድቀት አፋፍ ላይ እንድትደርስ እያደረጋት ነው። በሁሉም የአገራችን አካባቢዎች የማያባራ ጦርነት አለ። የጅምላ ጭፍጨፋ ተስፋፍቷል። ብሄር ተኮር ጥቃት ተበራክቷል። እስከ አለፈው ሳምንት ብቸኛ ሰላም ሰፈኖበት የነበረው የትግራይ ክልል ህዝብና በህጋዊ ምርጫ የተመሰረተ መንግስት ላይም ኮኔሬሉ ጦርነት በማዋጅ መጠነ ሰፊ ውግያ እያካሄደ ነው። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የሰላም አጀንዳ የሁሉም ህዝቦች ቅድሚያ የሚሰጠው አጀንዳ ሆኗል። ይህ የሀገር ህልውና ጉዳይ ስለሆነ ሌላው ቀይ መስመር ነው።

 

ቀይ መስመር ሦስት፣

ሉዓላዊነታችን አደጋ ላይ ወድቋል። የውጭ ሀይሎች የሚፈነጭባትና የፈለጉትን የሚያደርጉባት አገር ሁኗለች። አክራሪ ኒዮ ሌበራሎች የፖሊሲ ነፃነታችንን ለመንጠቅ በኢህአዴግ ውስጥ ሰዎች መልምለውና የቀለም አብዮት አካሂደው ኢህአዴግን አፈራርሰው እንዳሻቸው በአገራችን ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የሚገቡበትን ሁኔታ አመቻችተዋል። የአረብ አገሮችን በተላላኪነት በመጠቀም ከልማታዊ መንግስትነትና ከአርበኛ መንግስትነት ወደ ጥገኛ፣ አገር የሚሸጥና ተፈትኖ ያለፈ ፖሊሲ ሳያቅማማ አገር በቀል በሚል በስም አሽመንምኖ ህዝብን የሚጎዳ ፖሊሲ ከአይ.ኤም.ኤፍ. /IMF/ ፕሮራምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ቀድቶ የሚቀይር ዓለማ ቢስ ቡዱን ተፈጥራል። ይህ ጥገኛ ቡድን ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአሜሪካ አደራዳሪነት ለግብፅ በሚመች ስምምነት ለመፈራረም ትንሽ ሲቀረው የህዝብና የፖለቲከኞች ተቃውሞና ጫጫታ አስደንግጦትና የስልጣን ዕድሜየን ያሳጥራል በሚል ለጊዜው ድርድሩ አቋርጦታል። መዘዙ ግን ያው ሁሉም ዓለም የሚያውቀው የአሜሪካ ዛቻ ሰለባ መሆን ነው።

 

ሌላው ከኤርትራ የተቃጣብን ወረራ በህዝባችንና በመከላከያ ሰራዊታችን ጀግንነትና ከፍተኛ መስዋእትነት በብቃት መክተን የሰላም ጥሪ ብናደርግም የኤርትራ መንግስት መሪዎች አሻፈረኝ በማለታቸው ሰላም የሌለው ቀጠና ሆኖ ለረጅም ዓመታት ቆይቷል። ከብዙ ጥረት በኃላ በሁለቱም ህዝቦች ግፊትና ፍላጎት ከሁለት ዓመት በፊት በሁለቱም መንግስታት የሰላም ስምምነት ተደርሷል። ስምምነቱ በሁለቱም ህዝቦች ደስታ ፍጥሮ የነበረ ነው። ነገር ግን ስምምነቱ በሁለቱም መሪዎች በሚስጥር በመካሄዱ ዝርዝሩ አይታወቅም። በህዝብ ቢጠየቁም ሁለቱ መሪዎች ዝርዝሩን ለመግለፅ ፍቃደኞች አልሆኑም። ይህም በመሆኑ በድንበር ላይ ተጀምረው የነበሩ የሁለቱም ህዝቦች እንቅስቃሴ ያለምንም ምክንያት ግልፅ ባልሆነ አግባብ ድንበሩ በኤርትራ መንግስት በኩል ሲዘጋና ሲከፈት ቆይቷል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የኤርትራ መንግስት ሰራዊቱን በሰው ሀይል ለማጠናከር አስገዳጅ ምልመላውን (ግፋ) አጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። እግረኛ ክፍለ ጦሮቹ፣ ልዩ ሀይሎቹ፣ ኮማንዶ ክፍለጦሮቹንና ሜካናዝድ ክፍለጦሮቹን በተከታታይ እያሰለጠነ ነው። በየደረጃው ያለ አመራሩና ከቀላል የቡዱን መሳርያ እስከ ከባድ መሳርያ ቶካሽ የሰው ሀይሉን እያሰለጠነ በግልፅ የሚታይ የጦርነት ዝግጅት እያደረገ ይገኛል። በድንበር አካባቢም የሰራዊቱ እንቅስቃሴ በደንብ እየታየ ነው። በሌላ በኩል የኤርትራ ሰራዊት የሰላም ስምምነት ከተደረገ በኃላ ለምን የጦርነት ዝግጅት እናደርጋለን ብሎ በጥብቅ ቢጠይቅም የኤርትራ መንግስት ምላሽ መሬታችን አሁንም በኢትዮጵያ ቁጥጥር ነው። እናንተ ወታደሮች ናችሁ ዝግጅት ማድረግ ብቻ ነው ግዴታቹየሚል መልስ እንደተሰጣቸው ይታወቃል።

 

ኢሳያስ ኢትዮጵያ በውስጥ ችግር ውስጥ እንዳለችና እንደተዳከመች እነሱ ግን ጠንካራ እንደሆኑ አድርጎ ሰራዊቱን እየቀሰቀሰ ይገኛል። እብሪተኛውና ወራሪው የኤርትራ መንግሰት ላካሄደው ወረራ የኢትዮጵያ ሰራዊት ወረራውን ከመቀልበስና ሉዓላዊነቱ ከማስከበር በዘለለ በኤርትራ ሰራዊት ያደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት በሰራዊቱ የተሸናፊነትና ዝቅተኝነት ስነ ልቦና ተፈጠሮ እንደነበር ይታወቃል። ኢሳያስ አፈወርቂ ተጠያቂ የነበረ ቢሆንም ራሱ ያበላሸውን ስነልቦና በዚህ አጋጣሚ የሰራዊቱ ስነልቦና ለማከም ጥረት ለማድረግ በሁሉም ዙርያ እያዘጋጃቸው ቆይታል። ኢሳያስ በግልፅ በአገራችን የውስጥ ጉዳይ ገብቶ በመፈትፈት ምርጫ መደረግ የለበትም እያለም ነበር። በሚመራው አገር ምርጫ አድርጎ የማያውቀው፣ ህገ መንግስት የሌላት አገር የሚመራና በግዝያዊ መንግስትነት ለ29 ዓመታት ራሱን ፕሬዚደንት ከደረገ አምባገነን ምክር የሚቀበል የኢትዮጵያ መንግስት ካለን ሉዓላዊነታችን ምኑ ላይ ነው? በቅርቡ ደግሞ በመንግስት ሚድያ ሳይቀር የትግራይ መንግስትና ህዝብን ከኤርትራ መንግስትም ተባብሮ በጦርነት መውጋት መደምሰስ እንዳለበት ያለህፍረት ሲነገር እየሰማን ነው። ጭራሽ የራስን አገር ክልል ከሌላ ከውጭ መንግስት በመሻረክ ለመምታት ዝግጅቱ አልቆ ሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በቅርቡ ደግሞ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆናቸው እያየን ነው። ኢሳያስም የብሄራዊ ደህንነት ተቋሞቻችን ከመቆጣጠር አልፎ በግልፅ የኢትዮጵያ የመከላከያ ስትራተጂካዊ ዓቅሞች የሚገኙበት ደረጃ እንዲጎበኝ ተደርጋል። በኢሳያስ መንግስት ይህ ሁሉ ተንኮል ሲሸረብ በኢትዮጵያ አገራችን በኩል ደግሞ ምንም ዝግጅት የለም ሳይሆን ሰራዊታችን በፖሊስና በሚሊሻ ስራ ተጠምዶ የተበታተነበት ሁኔታ ላይ ይገኛል። የሌሎች የውጭ ሀይሎች ሀያልም ይሁኑ ሀብት ያላቸው የአረብ አገሮች በግልፅ የአገራችን ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ናቸው። ታድያ ሉዓላዊ አገር ነን ነፃ አገር ነን ማለት እንችላለን? የሉዓላዊነታችን መደፈር ሌላው የህልውና አደጋ ላይ መሆናችን መገለጫ ነው። ይህም ቀይ መስመር ነው።

 

ቀይ መስመር አራት፣

አገራችን በሚመራውና በለውጡ ምክንያት ከውጭ የገቡ ሀይሎች ውስጥ ያለው የፖለቲካ በሽታ ወደ ህዝቡ እንደተስፋፋው ወደ ሰራዊቱም በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ ነው። የግንቦት ሰባት ሚድያ በሆነው ኢሳት ቲቪና በብሄራዊ ሚዲያዎቻችን ጭምር ሰራዊታችን ለማፍረስ የደርግ ጀነራሎች በቴሌቭዥን በማቅረብ ውትድርና እና የውትድር ፕሮፎሽን ድሮ ቀረ በሚል የአሁኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ብቃት ለማሳነስ ከመሞኮር አልፎው መፍረስ አለበት ብለው በግልፅ የሚናገሩበትና ተው የሚል በጠፋበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ገዥው ፓርቲ ውስጥ ያለ ዘረኛ አስተሳሰብም ወደ መከላከያ ሰራዊት የተዛመተበት ሁኔታ ተፈጥሮ የሰራዊታችን የቆየው አንድነትና መተሳሰብ የተሸረሸረ ነው።

 

በተጨማሪም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ቀስ በቀስ የህገመንግስታዊ ሰራዊትነቱ ባህሪ እየደበዘዘ እንዲጠፋ በሀሳብም በተግባርም እየተሰራ ነው።ከፓርቲ እንጂ ከፖለቲካ መገለል የሌለበትን የፖለቲካ መሳርያ የሆነ መከላከያ ፍፁም ገለልተኛ ነው በማለት የሱ ስልጣን ማራዘሚያ የሚያደርግ ዶክትሪን ቀየሰ። ይህም በግልፅና በተደጋጋሚ የታየ ነው። ኮ/ል አብይ ዘወትር የሚያሰበው እውነታ ህገመንግስት መጠበቅ የናንተ ስራ አይደልም ብሎ በከፍተኘ መኮነኖች ፊት መናገሩና አመራሩ ደግሞ ተቃውሞ ማሰማቱ ይታወቃል። የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳም በሌላ ስብሰባ የሰራዊቱን ከፍተኛ መኮነኖች ሰብስቦ ሰራዊቱ የህገመንግስቱ የመጨረሻ ምሽግ ነው በማለት አስጨብጭበዋል። ኮ/ል አብይም ይህንን የለማ መገርሳ ንግግርና የሰራዊቱ ግበረመልስ በመስማቱ እንደለመደው ባክሃንድ ሰርቶ ሌላ መድረክ አዘጋጅቶ በተሳሳሳተ መንገድ ገባቹሁ እንጂ እኔ ሰራዊቱ የመጨረሻ ምሽግ አይደለም ማለቴ አልነበረም በማለት ቢያድበስብስም በተግባር ግን ሰራዊቱ የመጨረሻ ምሽግነቱ ሚና እንዳይጫወት ብዙ ሴራ እየፈፀመበት ነው። ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ለጎን ህገ መንግስታዊ ያልሆነ ሪፓፕሊካን የሚባል ሌላ ሰራዊት አደራጅቶና በኦሮሚያም ግዙፍ ሰራዊት በማሰልጠን (እስከ 50 ሺ ይደርሳል የተባለና ዘመናዊ ትጥቅ የታጠቀ ምንጩ በማይታወቅ የፋይናንስ ወጪ የሚደረግለትና ደሞዙና የተመቻቸ ህይወት ያለው) እየገነባ ነው። ሪፓፕሊካን ሰራዊቱ በድንገተኝነት ግዙፍ ሀይል በማድረግ ግንቦት ሰባት/አዜማ/ኢሣት የመከሩትን የመከላከያ ሰራዊት ቀስ በቀስ የማፈራረስ ስራ በመስራት ሰራዊታችን ላይ ያለው ጥልቅ የሆነ ጥላቻውን ፊት ለፊት ሳይሆን እየሳቀና ሰራዊቱን የሚያታልሉ የደሞዝና የኑሮ ማሻሻያ እርምጃ በመውሰድ ደሮን ሲያታሉላት የሚለውን ስትራተጂ ተከትሎ ህገ መንግስቱ ያለጠባቂ ለማስቀረት ስራዬ ብሎ እየተጣደፈ ነው። የህዝብ ሉዓላውነትና የአገር ሉዓላውነት መጠበቅ ትቶ የፌደራልና የክልሎች ባለስልጣኖች እድሜ ለማራዘም ዓላማ ያለው ስምሪት ለመስራት ተበትኖ አቅሙ በከፍተኛ ደረጃ እንዲዳከም እየተደረገ ነው። ከተልእከው ውጭ በመሰማራት አገራችን ያለ አስተማማኝ ዳር ደንበር ጠባቂና የህገ መንግስት ዘበኛ የሌላት እንድትሆን ተዳርጋለች። መከላከያ ሰራዊታችን ህዝባዊ ባህሪውን ሆን ተብሎ መቀየርና በጥበብ ሰራዊቱን ማፍረስ ደግሞ የህልውና አደጋ ነው። አገር ያለጠባቂ መተው ነው። አንድነቱንም የመሽርሻር ሁኔታ በፍጥነት ካልተገታ በተቃሙ በራሱ የመፍረስ አደጋ አለው። ይህ አደገኛ ሁኔታ የአገር ህልውና ጉዳይ ነው። ቀይ መስመር ነው።

ሰለዚህ ቀይ መስመር ሲታለፍ ዝምታን አንመርጥም! በማለት ከጀግናውና ከሁሉም በላይ ህዝቤ ከሚለው መከላከያችን ይጠበቃል። መፍትሔውም፣

 

       ሀገር የሚያድኑ ሀይሎች ጎን መሰለፍ። አገር ከመፍረሱ በፊት ህገ መንግስቱን በማዳን አገር ለማዳን የሚደረግ ሰላማዊ እንቅስቃሴ መደገፍ ተገቢ ነው።

 

       የህዝብ ጥያቄዎችን ለማፈን የሚደረግ እንቅስቃሴ በተለያዩ ጥበብ ማስቀረት። እስካሁን በኦሮሚያ፣ በሶማሊ፣ በደቡብ፣ በአማራ ክልል የተደረጉት ጥፋት መሆኑን ተቀብለን ማረም ተገቢ ነው። የራስን ህዝብ እንደ ደርግ በጦር ሄሊኮፕተሮች መጨፍጨፍ የባህሪ መዛነፍ መጀመሩን ያሳያል። የህዝብ ጥያቄዎች ለማፈን የሚደረግ እንቅስቃሴ ከአሁን በኃላ መቆም አለበት። ይህ የአፋና መሳርያ ሆኖ ማገልገል በተዘዋዋሪ አገር ለማፍረስ ህገ መንግስት ለመናድ ለሚደረገው እንቅስቃሴ መሳርያ ሆኖ ማገልገልና ማቀላጠፍ ነው። ስለሆነም መሳርያ አንሆንም በማለት ከህዝብ ጎን መሰለፍ መፍትሔ ነው።

       ሀገር አንዴ ከተበተነ መመለስ ስለማይቻል አገርም ሀገመንግስታዊ ስርዓቱን ለማዳን እስከ ፀረ ህገ መንግስት የሆነውን መንግስት ማውረድና ለህገ መንግስታዊ ምርጫ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር ተገቢ ነው። ለአገርም ሰራዊትም እርስ በርስ ለእልቂት እንዳይደርስ የሚያደርግ ትክክለኛ ህጋዊ መፍትሔ ነው። ህገ መንግስት ለማዳንና ተመልሶ ነብስ እንዲዘራ ለማድረግ የተወሰደ እርምጃ እስከሆነ ድረስ ህዝባዊም ለሀገር አንድነት የተወሰደ እርምጃ ነው። የሰራዊታችን ለህገ መንግስቱ የመጨረሻ ምሽግ መሆኑ የሚያረጋግጥ እርምጃ ነው። ስልጣን ከህዝቦች ድምፅ ውጭ ለመቀማት እስካልሆነ ድረስ ሰራዊቱ አገር እየፈረሰች ዝም ብሎ ማየቱ ብቻ ነው ስህተት የሚሆነው።

 

መልእክት፣

ቀይ መስመሩ ከተላለፈ ቆይቷል።

       ኢትዮጵያችን ከመፈራረስና ከእልቂት ለማዳን በሁሉም የጦር ክፍሎች ያሉ ሐቀኛ የኢትዮጵያ ልጆች ይህን ከላይ የተዘረዘሩትን የህልውና ጉዳዮች መሰረት በማድረግ ሲያስቡ እንደቆዩ አያጠራጥርም። የዚህ አካል የሆነው የሰሜን ዕዝ በቅርብ ባደረጉት አስቸካይና ምስጥራዊ ስብሰባም የዚህ ጭንቀታቸው ማሳያ ነው። የአብይ መንግስት ምንም ጥፋት በሌለው በኢትዮጵያዊነቱ በተግባር ያስመሰከረ ሁሌም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ የሆነውን ባንዲራችንን እያውለበለበ በሳለፍነው ሁለት ዓመታት በደል እየተፈፀመበትም (በለውጥ መሪ ነኝ በሚል መንግስት በአደባባይ በማንነቱ እየተሰደበም እየተገለለም ቢሆን ሳይበገር) ከጎናችን የቆመውን ህዝብ ከእብሪተኛው የኢሳያስ መንግስት ጎን በመሰለፍ ለማጥቃት ተባባሪዎች መሆን አንፈቅድም በማለት ከትግራይ ህዝብና ከትግራይ ክልላዊ መንግስት ጎን በመሰለፍ አገራችን ከእልቂት ከመፈራረስ ለማዳን ቆርጠን ተነስተናል በማለት የአብይ አህመድ ጦርነት ሊያስከትለው የነበረውን ጥፋት ታድጎታል። ይህ የሚያኮራ ታሪክ በደማቅ ቀለም ተፅፎ ይኖራል። የኢሳያስ ሴራም በማክሸፍ የሰሜኑ የአገራችን ዳር ደንበር ለማስከበርም አሁንም ዝግጁነቱን አሳይቷል። ኮ/ል አብይ ቀይ መስመሩ በመተላለፉ የሰሜን ዕዝ ይህን እርምጃ ለመውሰድ ተገዷል።

 

       ሌሎች አካባቢ የምትገኙ የጦር ክፍሎችም ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ከመላው የአገራችን ህዝቦች ጎን በመቆም ህገ ወጡ መንግስት ከስልጣኑ እስኪወርድ ድርስ አብረውት እንዲታገሉ የሰሜን ዕዝ ጥሪ አድርጎ በምሳሌነት የበኩሉን ድርሻም ተወጥቷል። የህገ መንግስቱ ምሽግ መሆናችን በተግባር የምናረጋግጥበት ጊዜው አሁን ነው በማለት ጥሪውን አሰምቷል። ኢትዮጵያችን እየፈረሰች ማየት የለብንም እንታደጋት ብሏል። የመከላከያ አባላት ሁናቹሁ ይህን መልዕክት መቀበል የማትፈልጉ መብታችሁ ነው ማደናቀፍ ወይም ለጥቅም ተገዝታቹሁ በተፃራሪው መቆም ግን የሚያስጠይቃቹሁም ነው ብሏል። በፍቃዳቹሁ ሙያችሁን መልቀቅ ጥሩ አማራጭ እንደሆነም መክራል። አሁንም ለጀግኖቹ የሰሜን ዕዝ ታላቅ ክብር ይገባቸዋል። ታላቅ ምስጋናም እንቸራቸው።

 

       የሰሜን ዕዝ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሆይ በስልጣን ላይ ያለው ምላሱ ብቻ ያልተቆረጠው ውሸታም ፀረ ህዝብ መንግስት አንታዘዝም ብለን ካንተ ጎን ለመሰለፍ ቆርጠን ተነስተናል ብሏል። በደማቹሁ የተገኘውን ህገ መንግስት ለማዳን ተቃውመን የናንተን ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ወስነናል በማለት መልእክትም አስተላልፏል። በህገ መንግስቱ መሰረት የመጨረሻው ዳኛ እናንተ ስለሆናቹሁ በምርጫሁ ያሻቹሁን በድምፃቹሁ የራሳቹሁን መንግስት እስክታቆሙ ድረስ አገር እንዳይፈርስ ሚናችን እንድንወጣ ከጎናችን እንድትሆኑ በትህትና እንጠይቃለንም ብሏል። ድጋፋችሁም አይለየን በማለት ጠይቓል። ይህ ከአንድ ህዝባዊ ተቋም የሚጠበቅ በመሆኑም በጣም ያኮራል። አገራችን ከመፈራራረስ አደጋ ለመታደግ እየተደረጉ ከሚገኙ ስራዎች ፋና ወጊ ሁኖ በአገራችን ታሪክ ተመዝግባል።

 

 

የሰሜን ዕዝ ሁሉም የአገራችን ህዝቦች እያደረጋቹሁት ባለው ትግል እኛም ከጎናቹሁ እንቆማለን በማለቱ የሚያኮራ ነው። መከለከያ ሰራዊታችን እስካሁን በህገ ወጡ መንግስት ታዘን በሁሉም የኢትዮጵያ አከባባቢዎች ላደረስነው ጥፋትም ይቅርታ እንጠይቃለን የሚል መልዕክትም አለው። ደግ ብሏል እላለሁኝ።

 

እኔም በዚህ ፅሑፌ እንደ የድሮ መከላከያ አባልነቴ በብርቱ ማሳሰብ የምወደው በዚህ ውስብስብ ሁኔታ ብሄር በመለየት በየአካባቢው የሚኖሩ የሌሎች ብሄር ህዝቦች ላይ በስሜት ተነሳስተን ጥቃት ማድረስ በስልጣን ያለውን ህገ ወጡ መንግስትን የሚጠቅም እንጂ ለህዝቦች የሚጠቅም አንዳች ነገር የለውም እላለሁ። ጠላታችንና ወዳጃችን ለይተን እንደኛ የሚበደሉትን ወገኖቻችንን የሌላ ብሄር በመሆናቸው ብቻ ማግለል ማጥቃት በፍፁም ልንሞክረውና ልናስበውም አይገባንም እላለሁ። ጠላታችን ህገወጡ የባለፀጎቹ ፓርቲ አባላት ናቸው። እነዚህንም በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲቀርቡ ማድረግ አለብን። ምንም ጥፋት የሌላቸውን ቤተሰቦቻቸውንም ማጥቃትም መንካትም አይገባንም። ስርዓት የሌለውን አካል የምንታገለው በስርዓት ነው።

 

ኢትዮጵያችን አትፈርስም! ብለን እምቢ የምንልበት ጊዜ አሁን ነው።

 

ድል ለኢትዮጵያ ህዝቦች!

ህገ መንግስታችን በመጠበቅ አገራችን ኢትዮጵያ ከመበታተን እናድናታለን!

Back to Front Page