Back to Front Page

ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም

ኢትዮጵያዊ ዜግነት እንጅ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም

 

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል (ስትራቴጂስት) 7-28-20

 

የጽሑፉ ዓላማ፥ ጽሑፉ በይዘቱ አብዛኞቻችን አፍ አውጥተን እንድንናገረው የማንፈልገውና የማንደፍረው ርዕሰ ጉዳይ የሚዳስስ ሲሆን ዓላማው፥

 1. የምድራችን መሰረታዊ ችግር መጠቆም፤
 1. ከነ ልዩነቶቻችን ሁሉን እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ አንድነት መፍጠር እንደሚቻል ለማበረታታት፤
 1. ኢሳትና የመሳሰሉ ጸረ ህዝብ ሚድያዎችና ድረ ገጾች ከምን ጊዜም በላይ አንድን ሕዝብ ላይ ያነጠጠረ የከፈቱት የጦርነትና የጥላቻ ዘመቻ አደብ ለማስያዝ ተጻፈ።

ማሳሰቢያ፥

 • ጽሑፉ በማንነት ዙሪያ የሚያጠነጥንና የሀገራችን የፖለቲካ ችግር የሚጠቁም እንጅ ብሔር ተኮር አጀንዳ የለውም። የጽሑፉ ዓላማ ከሚለው ሥር ግልጽ በሆነ ቋንቋ ከሰፈረው ውጭ ሌላ ምንም ዓይነት ዓላማ እንደሌለው በድጋሜ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ሐተታ፥

የኦሮምያ ክልል ተወላጆች አይደለም በማንነቱ ኦሮሞ ለሆነ ሰው ኦሮምኛ ቋንቋ የመናገር ችሎታ ላለው ሰው ያላቸው አቀባበል፣ እምነትና አስተሳሰብ ከሌላ ብሔር ለሆነ ወገን ማለትም ለአማራ፣ ለትግራይ፣ ለደቡብ ያላቸውን እይታ ሲነጻጸር ለማወዳደር በማይቻል ሁኔታ አድሎአዊነት እንደሚንጸባረቅበት በመዲናይቱ እየተፈጸመና እየሆነ ያለ ዓይን ያወጣ አስጸያፊ ድርጊት መመልከት በቂ ነው።

የአሁኑ አያድርገውና አማራ ዳውን! ነፍጠኛ ዳውን! እየተባለ ከፍተኛ የሆነ የልዩነትና የጸብ መፈክር ከመስተጋባቱ በፊት ዓመት ከመንፈቅ አካባቢ (በለውጡ ማግስት መሆኑ ነው) ኦሮማራ ተብሎ ብዙ የተዘፈነለትና የተጨፈረበት፤ ከተራ ዲስኩር አልፎ በመጻህፍትና ሰፊ ተደራሽነት ባላቸው በመንግስት መገናኛ ብዙሐን ሳይቀር ኦሮሞና አማራ ከአንድ አባት የተወለዱ፣ ከአንድ ምንጭ የተቀዱ አንድ ህዝቦች ናቸው እየተባለ ጸረ ኢትዮጵያዊነት የሆነ አግላይ መለከት ሲነፋና ነጋሪት ሲጎሰም በእነዚህ ክልሎችና አከባቢዎች ነዋሪዎች በነበሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጨምሮ በሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ላይ የደረሰ የንብረት መወደም፣ ግፍና በደል፣ ከዚህም አልፎ ሞትና መፈናቀል ሁላችን የምናስታውሰው የቅርብ ትዝታችን ነው።

እነዚህ ሰዎች በተለይ የትግራይ ክልል ተወላጆች እንደ ዕቃ እዚህም እዚያም ሲጣሉ፤ ሀብት ንብረታቸው በእሳት ሲወድም፣ ሲፈናቀሉና ህይወታቸውን ሲያጡ ኢትዮጵያውያን ተጎዱ! ብሎ ድምጹን ያሰማ ኢትዮጵያዊ የለም፤ አልነበረምም። ምን ነው? ቢሉ፥ ኢትዮጵያዊነት ኩራቴ! ኢትዮጵያዊነት ክብሬ! ወዘተ በማለት በሚታወቀው ማኅበረሰብ ዘንድ የትግራይ ክልል ተወላጆች ኢትዮጵያውያን አይደሉምና። አንድምታው፥ ተጋሩ ኢትዮጵያዊነትን አይመለከታቸውም ነው መልዕክቱ።

እርግጥ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው የኢትዮጵያ ችግር የህዝቡ በተፈጥሮ ልዩ ልዩ ከመሆን የሚያገናኘው (የሚመነጭ) አንዳች ነገር የለውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር የልሒቃኖቹ ችግር ነው። ሲስማሙ ይስማማል፤ እነዚህ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ጥቅም ሲያጣላቸው ደግሞ እነሱ በሚያነዱትና በሚያያዙት እሳት የሚለበለብና የሚባላ ህዝብ ነው።

የሚበቅለው የተዘራ ነው። አንድ የአማራ ክልል ተወላጅ ወገኔ የሚለው ከአማራ ነገድ የተገኘ እንደሆነ ነው። አንድ የአማራ ብሔር ተወላጅ አማራን በሚያይበት መነጽር የትግራይ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ ተወላጆችን እኩል አያይም። የሲዳማ ተወላጆችም እንዲሁ የራሴ የሚለውን የሲዳማ ሰው በሚያይበት መነጽር የወላይታ ወይም የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ እኩል አያይም ከዚህ ሁሉ የከፋ ነገር ደግሞ በተረኝነት መንፈስ ስልጣን የሚቆናጠጠው አካል በሚዘረጋው አድሎአዊ አሰራርና አግላይ መንግስታዊ መወቅር ህዝቦች ሁሉ በኢትዮጵያዊነታቸው በእኩል ዓይን የሚያይ አይደለም።

 • በግልጽም በስውርም እያፋጀን ያለው የማንነት (የብሔርተኝነት) የበላይነት ጥያቄ ነው (የብሔር ጥያቄ ማንሳት በራሱ ኃጢአት ነው እያልኩ አይደለም። ለጥያቄው የሚሰጠው መልስ ግን ይሄው ደም እያቃባን ነው ላይ ነው)
 • ኢትዮጵያውያን በእውነት አንድ ማንነት ያለን አንድ ህዝቦች ብንሆን ኖሮ አንዱ አንዱን ለመግደል ባላሴረና ባልተሳ ነበር። እየተጠላለፍን ያለነው ለልዩነቶቻችንን እውቅና በመስጠት ለመፍትሔው ከመትጋት ይቅል የውሸት መዝሙር እየዘመርን መፋጀት ስለመረጥን ነው።
 • ታሪካችን የመገዳደል ታሪክ ነው። ከዚህ ታሪክ ጀርባ ያለው ታሪክ ደግሞ የብሔር የበላይነትና የማንነት ጥያቄ ነው። አንዱ፥ ኢትዮጵያን የመግዛት መለኮታዊ ስልጣን የተሰጠኝ እኔ ነኝ! ይላል ሌላኛው ደግሞ ዘወር በል! ሲል ይታገላል። የአቅም ጉዳይ ሆኖባቸው ነው እንጅ ሌሎቹም ቢሆኑ ተኝተው አላደሩም።
 • ኢትዮጵያውያን የአንድ ማንነት ባለቤቶች ብንሆን ኖሮ እዚህ ሁሉ ችግር ውስጥ ባልገባን ነበር። በሌላ ስፍራ እንደተገለጸው፥ ጥያቄአችን በዲሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በሰብዓዊ መብት ወዘተ ሸፋፍነን አሰማመርነው እንጅ ጥያቄአችን የማንነት ጥያቄ፤ የበላይነት ጥያቄ ነው። ባይሆን ኖሮ ችግሮቻችን ለመፍታትና ለመደማመጥ ባልተሳነን ይህን ያህልም ባልተቸገርን ነበር። ማንም የበታች ሆኖ መኖር ስለማይፈልግ ግን ዘልአለም ጦርነት ውስጥ እንገኛለን።
 • የኢትዮጵያ ችግር የሚፈታ ፖለቲካዊም ሆነ ሌላ አማራጭ መንገድ ታጥቶ አይደለም። ታድያ ጥያቄው ማን ይሁን የበላይ? ነው። ጥቂቶቹ ወደ ልባቸው ካልተመለሱና ካልታረቁ የሚታረቅ ህዝብ፤ በሰላም የምትተኛ ኢትዮጵያ አትኖርም። መሬት ላይ ያለው ሐቅ ይህ ነው።

 

ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው?

የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ለዘመናት እያቧቀሰና እያባለ ያለ ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊነት ክብር! ኢትዮጵያዊነት ኩራት! ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው! ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት! ኢትዮጵያዊነት አትንኩኝ ባይነት ነው! ዘራፍ! ወዘተ አይደለም የእኔ ጥያቄ። በእርግጥ እነዚህ አባባሎችና መፈክሮች በሙሉ ከድስት በታች እንደሚቃጠል እሾህ ድምፅ የውሸት መፈክሮች ናቸው። አደንዛዥ ዕጽ የመውሰድ ያህልም በዜጎች አእምሮ ውስጥ አዚም የሚረጩ አፈዝ አደንግዞች ናቸው። ይህን ቋንቋ የሚያስተጋቡ ግለሰቦችም፥ ገሚሰቹ መልዕክቱ ሳይገባቸው ስለ ተባለ ብቻ የሚሉ ሲሆን ዋኖቹ ግን የሌላውን ወገን ሃሳብና እምነት የመስማት ምንም ዓይነት ፍላጎት የሌላቸው፣ ጨፍላቂና አምባገነናዊ ባህሪይ የነገሰባቸው የተምታታባቸው ህልመኞች (ባለ ራዕዮች ማለቴ አይደለም) ሰዎች ናቸው። እኔ የምለው፥ የቋንቋ ጨዋታ እየተጫወትን መሸናገሉን ትተን መፍትሔ ፍለጋ እውነት እውነቱ እንነጋገር ባይ ነኝ። ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው?

ኢትዮጵያዊነት፥ የአንድነትና የጀግንነት መገለጫ ነው?

ይህ አባባል በተደጋጋሚ ሲነገርና ሲስተጋባ ሳንሰማ አንቀርም። ለመሆኑ አንድነት ማለት ምንም ማለት ነው? ጀግንነትስ ምንድ ነው? ጀግናስ ማለት ነው? በውኑ ኢትዮጵያውያን አንድ ነን? የአንድነት መገለጫ ምንድ ነው? ለመሆኑ፥ ጀግና ነኝ! የማይል ህዝብና አገር አለ? አጉል ትህትና ካልሆነ በስተቀር ራሱን፥ እኔ ትል ነኝ፣ ሸክላ ነኝ፣ ጭልፋ ነኝ፣ ማንኪያ ነኝ የሚል ህዝብና አገር አለ ወይ? አሜሪካውያን ጀግኖች ነን ይላሉ፤ ራሽያውያን ጀግኖች ነን ይላሉ፤ ቻይናዊያን ጀግኖች ነን ይላሉ፤ ኮሪያውያን ጀግኖች ነን ይላሉ፤ ጎረቤት አገር ሶማልያና ኤርትራ ሳይቀሩ ጀግኖች ነን! ይላሉ። ጀግንነት ማለት፥ ድህነት፣ ጦርነት፣ ጸብ፣ ምቀኝነት፣ ኋላቀርነት፣ ዓለም ስትለወጥ በብዙ ነገር እንደ ኩሬ ውሃ ደርቀህ መቅረት ማለት ካልሆነ በስተቀር የቃሉ ትርጉም አሻሚ ነው።

አንባቢ ሆይ! ጀግንነት ሁሉንም የዓለም ህዝቦችና አገራት የሚያካትትና የሚመለከት ቋንቋ ወይም ቃል ከሆነ፤ ጀግንነት ከኢትዮጵያዊነት ጋር በተለየ መልኩ የሚያገናኘው ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ጀግንነት ምንድ ነው የሚያመላክተው? ከምን ጋር በተገናኘ ነው ኢትዮጵያዊነት ማለት ጀግንነት ነው! የምንለው? ከጦርነት በተገናኘ ከሆነ ሁሉም ህዝቦችና አገራት ያሸንፋሉ ይሸነፋሉ። ኤርትራን ለጣሊያን ማስረከብ ማሸነፍ ማለት ከሆነ ደግሞ ነገሩ ህሊና ላለው ሰው ችቸዋለሁ። ሥልሳና ሰባ ሺህ ኢትዮጵያዊያን ገብረን ስናበቃ ባድመን ማስረከብ ጀግንነትና አሸናፊነት ከሆነ በእውነቱ ነገር በአማርኛ ሳይሆን በጅብርሽ ነው እያወራሁ ያለት ማለት ነው። አንድም፥ ጀግንነት ሆነ አሸናፊነት የአማርኛ ተናጋሪ ሰው የማያውቀው ትርጉም አላቸው ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት ነው ስንል ጀግና ነኝ! የሚል የዓለም ዜጋ በሙሉ ኢትዮጵያዊ ነው! እያል እንዳሆንም እጠራጠራለሁ። በመሆኑም፥ ጀግና ማን ነው? ጀግንነትስ ምንድ ነው? ብሎ ራሱን የሚጠይቅ ሰው ብጹዕ ነው። የማንም ፕሮፓጋንዳ ሰለባ አይሆንምና።

Videos From Around The World

ኢትዮጵያዊነት፥ አትንኩኝ ባይነት ነው?

 

ለመሆኑ አትንኩኝ ባይነይ ምን ማለት ነው? ምዕራባውን (አውሮፓውያን) የአፍሪካ አገራት በሚቀራሙበት ዘመን ኢትዮጵያ ብቸኛ ነጻ አገር እንደ ነበረች ታሪክ ይመሰክራል። መልኩን ለውጦ ከመጣው 21 ክፍለ ዘመን የቀኝ አገዛት ወጥመድ ግን ኢትዮጵያ ነጻ አገር አይደለችም። ኢትዮጵያዊነት ማለት እያልን የምናሰማው መፈክር በሙሉ መሰረት የሌለው የባዶ ቃላት ስብስብ ነው። ቀለል ባለ አማርኛ፥ እየኖርን ያለነው በታሪክ ነው።

ኢትዮጵያ፥ ነጻነትን እያወሩ ነጸነትዋን አስደፍረው የባንክ ነጻነታቸውን ባወጁ ግሳንግስ ፖለቲከኞች የተከበበች አገር ናት። በመሰረቱ ነጻ ነኝ ለማለት የነጻነትን ትርጉም ማወቅን ይጠይቃል። ከባርነት ውጭ ሌላ ዓለም የማያውቅ፤ ነጻነት በሚመስል ባርነት ውስጥ ተወልዶ በባርነት ላደገ ትውልድ ባርነት የነጻነት እኩሌታ ትርጉም ነው ያለው። በመሆኑም፥ ባለፈው ታሪካች የራሳችን ያህል በመቁጠር ራሳችንን አናታልል። ታሪክ - ታሪክ ነው። ታሪካችን ማንም አይወስድብንም። ጥያቄው፥ ዛሬ የት ነው ያለኸው ነው? ድህነትና ጦርነት እያሳደደህ ታሪክ ተንተርሰህ የምትተኛው እስከ መቼ ነው?

አማራ እንደ ህዝብ አትንኩኝ ባይነት ነው፤ ትግራይ እንደ ህዝብ አትንኩኝ ባይነት ነው፤ ኦሮሞም ይሄው አትንኩኝ እያለ ያለ ይመስላል። አትንኩኝ የማይል ማኅበረሰብ፣ ህዝብና አገር ማን አለ? ኬንያዊነት አትንኩኝ ባይነት ለመሆኑ ለማወቅ የኬንያ ቦርደር መጣስ ብቻ ነው። ያን ጊዜ በአፍሪካ ምድር የሌለ ዘመናዊ የእንግሊዝ ጦር መሳሪያ ሲያዘንብብህ ታውቀዋለህ። ሱዳንም እንደዚሁ። ከሱዳኖች ጋር በነጋ በጠባ ቁጥር በቦርደር እየተሳሳብነው ያለነው እኛም እነሱም አትንኩን ባዮች ስለሆን ነው። አትንኩኝ ባይነት ኢትዮጵያዊነት ማለት ብቻ ቢሆን ኖሮ ሱዳን ያለ አንዳች ማቅማማት መሬትዋን አሳልፋ ትሰጠን ነበር። በነገራችን ላይ፥ አትንኩኝ ባይነት ጦርነትን ከማሽነፍና ከመሸነፍ አንዳች የሚያገናኝ ነገር የለውም። አትንኩኝ ባይነት የጥቃት ሰለባም ብትሆንም፤ እንደማታሸነፍም እያወቅክም ራስህን ለሞት አሳልፈህ መስጠት ነው። የሰው ባሪያ ከመሆን የትል ምግብ ለመሆን መምረጥ ነው።

ኤርትራዊነት አትንኩኝ ባይነት ባይሆን ኖሮ ወይም አትንኩኝ ባይነት ኢትዮጵያዊነት ማለት ብቻ ቢሆን ኖሮ ባድመ የፈሰሰውን ደም አይፈስም ነበር። የተፈረደልኝ መሬት ሳልወስድ የሚፈጠር ተዓምር የለም፤ አንገቴ ለሰይፍ! እያለች ያለችው ኤርትራ እንኳ በአቅሟ ኤርትራዊነት አትንኩኝ ባይነት ቢሆን አይደለምን? ኢትዮጵያዊነት አትንኩኝ ባይነት ነው! እያሉ ህዝብን እያተረማመሱ ያሉ ሰዎች እንደ እስስት መልካቸውን እየለዋወጡ የቋንቋ ጨዋታ ለመጫወት መምረጣቸውን የሚያሳይ እንጅ የኢትዮጵያ ችግር የመፍታት ፍላጎት እንደሌላቸው ግልጽ ነው።

አንድም፥ ኢትዮጵያዊነት አትንኩኝ ባይነት ነው የሚለው አባባል አንድምታው በህዝቦች እኩልነት የማያምን ፍርደ ገምደል አስተሳሰብ የተጸናወተው ህልመኞችን ይሆን እንዴ ስልም ራሴን እጠይቃለሁ። መልሼ ደግሞ አትንኩኝ! በማለት ህልማቸውን መና ያስቀረው ማን ቢሆን ደግሞ እላለሁኝ። ወጣም ወረደ፥ ጦርነት ለእነዚህ ሰዎች ቢዝነስ ነው። ሰላም ሲፈጠር በኪሳራ እንዳይመቱ ደግሞ እሳቱን ሳያቋርጥ እንዲነድ የሚያደርጉት እንዲህ ዓይነት መልካም የሚመስል ዳሩ ግን ማንንም የማይጠቅም ከፋፋይ የአመጽ ቋንቋ በማስተጋባት ነው።

 

 

ኢትዮጵያዊነት፥ ፍቅር ነው?

ጥያቄው፥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች በኢትዮጵያ ታሪክ መቼ ነው በሰላም ተኝተው ያደሩ ያደሩ? ልዩነት በየትም ዓለም ያለ ነገር ነው። በእኛ መካከል ያለ ልዩነት ግን ከልዩነትም ያለፈ በጦርነት ደም ስንፋሰስና ስንገዳደል ነው የሚታወቀው። የሚደንቀው፥ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው የሚለው ትርክት የሚያስተጋቡ ሰዎች ናቸው ሲያሻቸው ደግሞ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው! እያሉ የሚጽፉና የሚናገሩ። እውነት ነው፥ የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው። በዘመነ መሳፍንት ሆነ በአጼዎቹ፤ ኦሮሞን ያቀፈች ኢትዮጵያ ከተቆረቆረች በኋላም የኢትዮጵያ ታሪክ ፍለጠው ቁረጠው የበዛበት ታሪክ ነው።

የቅርቡ እንኳ ብናነሳ፥ የጃንሆይ መንግስት ከሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል (አገሪቱ ማለት ጸረ ኢትዮጵያዊነት ነው ሲባልም ሰምቻለሁ) የትግራይ ትግሪኚ ህዝብ ሰላም አልነበራቸውም። ደርግም በተመሳሳይ ለአስራ ሰባት ዓመታት በገዛበት ዘመን ኢትዮጵያ ሰላም አልነበራትም። አንጻራዊ ሰላም ነበረ ተብሎ በሚነገርለት የቀዳማዊ የኢህአዴግ ዘመንም ቢሆን መልኩን ነው የቀየረ እንጅ ኢትዮጵያ በከፋ የጦርነት ዓይነት (Hybrid warfare) ስትታመስ የኖረች አገር ናት። በዐቢይ አህመድ የሚመራ ዳግማዊ ኢህአዴግ ስመ ክርስትናው የብልጽግና መንግስትም እሄው ህዝቡ የለየለት ጦርነት ውስጥ ነው የሚገኘው። ፍቅርና መቃብር መለየት የሚያቅተው ሰው ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው ለማለት የሚደፍር ሰው እውነትም ከፍቅር ጋር የተጣላ ሰው መሆን አለበት።

ፍቅር ምንድ ነው? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ በትርጉም ደረጃ ይሄ ነው ለማለት ባይቻልም፤ የፍቅር ባህሪ ግን አንድ በአንድ መዘርዘርና ማስቀመጥ ይቻላል። ቅዱሳት መጻህፍት እንደሚያስተምሩትም፤ ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤ ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል እንዲል። እስቲ እዚህ ውስጥ ራሳችንን እንፈለግ፥ የሚባለው መፈክር እውነትነት አለው? ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን በዚህ ሚዛን ሲመዘን ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው! ስንል የምናስተጋባው ቋንቋ ተመዝኖ ሚዛን የሚደፋ፤ ተፈትኖ የሚያልፍ ነው ወይ? መሬት ላይ ያለ እኛነታችን በዚህ ሚዛን ሲለካ ዋጋ የሚያወጣ ነው ወይ? መጽሐፍ፥ በእርሱ ውስጥ ካለው ከሰው መንፈስ በቀር ለሰው ያለውን የሚያውቅ ሰው ማን ነው? እንዲል ፍርዱ ለእርስዎ ትቸዋለሁ።

ኢትዮጵያዊነት፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው?

እግዚአብሔርን የማይፈሩና ከእግዚአብሔር ጋር የተጣሉ ሰዎች፤ የእግዚአብሔር ስም ለፕሮፓጋንዳቸው መጣፈጫ ሲያደርጉት ከማየትና ከመስማት በላይ እግዚአብሔርን መሳደብ ሌላ ምንም ነገር የለም። ለመሆኑ እነዚህ ኢትዮጵያዊነት፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው እያሉ አፋቸውን የሚከፍቱ የሲዖል አጋፋሪዎች ስለየትኛው እግዚአብሔር ነው እየተናገሩ ያሉ? ተመልሰው እኔን ስንት እግዚአብሔር ነው እንዴ ያሉት? ማለታቸው አይቀርም። የእኔም ጥያቄ እሱ ነው። ለህልውናው እስከ ተብሎ የማይነገረው፤ ጥበቡንና ማስተዋሉን ከሰው አእምሮ በላይ የሆነው፤ የሰው እውቀትና ጥበብ የማይገልጸው፤ መንገዱ በምርምር የማይደረስበት፤ ሁሉንም አሳልፎ ስለሚኖር፤ ልብንና ኩላሊት የሚመረምር፤ የሰውን ሃሳብ ከሩቅ የሚያውቅ፤ ፍጥረታትን ከአለመኖር ወደ መኖር ያመጣ፤ ስህተት የማያውቀው፤ ኃጢአት ለባህሪው የማይስማማው፤ ጻድቅና እውነተኛ ፈራጅ ስለሆነው እግዚአብሔር ከሆነ እያወራነው ያለነው ኢትዮጵያውያን ይህን እግዚአብሔር የምንፈራ ዓይነት ዜጎች አይደለንም። ኢትዮጵያ እግዚአብሔር በደህና ጊዜ የሸጣት አገር ናት። ኢትዮጵያ የከሰረች አገር ናት (በመንፈሳዊ)

መጽሐፍ፥ አጋንንትም ያምናሉ ይንቀጠቀጡማል (ያዕ 29) እንዲል፤ የእኛ ፍርሃት፥ ክፋት፣ አመጸኝነት፣ ሌብነት፣ ሙሰኝነት፣ ምቀኝነት፣ አመንዝራነት፣ አዱላዊነት፣ ተንኮልና ሴረኝነት ተከትሎ የሚመጣውን ሽሽት (ዘፍ 38-10) እንጂ እግዚአብሔርን ከመውደድና እግዚአብሔራዊ የሆነ ህይወት ከመኖር የሚመነጭ ዓይነት የተቀደሰ ፍርሃት አይደለም። ቅድስት ድንግል ማሪያም፥ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ (ዮሐ 25) እንዳለችው እግዚአብሔር መፍራት እንደ እግዚአብሔር ቃል መኖር ነው። እንደ እግዚአብሔር ቃል ለመኖር ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ማንበብ፣ ማወቅ፣ ማጥናትና መማር ይጠይቃል። ዛሬ፥ ኢትዮጵያዊነት ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው እያሉን ያሉ ሰዎች፥ መጽሐፍ ቅዱስን ለቅዠት መከላከያ ተንተርሰው ከመተኛት ውጭ ከመጽሐፉ ቃል ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች ናቸው። እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው በለው እጨደው እያለ ዘራፍ አይልም። እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ከአመጽ ጋር ህብረት የለውም። በለው እጨደው አመጽ ነው። እንዲህ ያለ ሰው ደግሞ የእግዚአብሔር ስም አንስቶ የመናገር የሞራል ብቃት የለውም። ለነገሩ ሰይጣም ቢሆን ሲፈትን እያጣቀሰ ነው።

ጥጉ፥ በደመ ነፍስ እውቀት የሚኖር ወይም የሚመጣ እግዚአብሔርን የመፍራት ህይወት የለም። መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውቀት ላይ ያልተመሰረተ፤ ህይወት የሌለው ፍርሃት፤ እግዚአብሔር መፍራት አይደለም። ይህ ዓይነቱ ፍርሃት የድፍረት ኃጢአት ይባላል። ኢትዮጵያዊነት ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው የሚለው አባባልም ከዚህ የሙውታን መዝገብ ውስጥ የተገኘ አባባል እንጅ አንዳችም መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የለውም።

እግዚአብሔርን መፍራት በዕለት ዕለት ኑሮአችን የሚገለጽ ሰውና ሰይጣን የሚመሰክሩት የተገለጠ ህይወት እንጅ ቤተ ክርስትያን ቅጽር ግቢ ጫማህን አውልቀህ መሄድ ማለትም አይደለም። ሰው፥ እንደምን አደርክ? ሲልህ እግዚአብሔር ይመስገን ብለህ ስለመለስክ እግዚአብሔር ትፈራለህ ወይም ታመልካለህ ማለት አይደለም። እንደ ኤሊ ልጆች ለእግዚአብሔር ስለሚቀርበው መስዋዕት ዝርዝር የሚያውቅ አንድም ሰው ተፈልጎ አይገኝም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኤሊ ልጆች የሚለው ግን፥ በእግዚብሔር ፊት የተናቁ ምናንምቴዎች ነበሩ ሲል ነው የሚገልጻቸው። አሟሟታቸውም መልካም አልነበረውም።

እግዚአብሔርን መፍራት፥ ከአመጻ፣ የራስህ ያልሆነውን ከመመኘት፣ ከመውሰድ፣ ከመስረቅ፣ ከሌብነት ህይወት፣ ከሙስና መራቅ ነው። እግዚአብሔርን መፍራት፥ ቃል ኪዳንህን ደብቀህና አፍርሰህ ከመፈንጠዝና ከመማገጥ ነውር ከሞላበት ህይወት መራቅ ነው። እግዚአብሔር መፍራት፥ ከድሃ አፍ መመንተፍ ማለት ሳይሆን ያለህን ለሌለው ማካፈልና ለምስኪኖች ማዘን ነው። ማማለጃ (ጉቦ) እየተቀበለክ ፍትህን ማጣመም፣ ማጓደል፣ ድሃን መበደልና ማስለቀስ ማለት ሳይሆን እግዚአብሔር ያየኛል ማለትና ትክክለኛ የሆነ ነገር ማድረግ ነው። እግዚብሔር መፍራት፥ ከምንም በላይ ራስህን መግዛትና ጥጋብህን መቻል ነው። እግዚአብሔር መፍራት፥ ልክህን ማወቅ ነው። ዛሬ፥ ኢትዮጵያዊነት ፈሪሃ እግዚአብሔር ነው እያሉን ያሉ ሰዎች ግን በእጃቸው ደም ያላቸው ሰዎች ናቸው።

እግዚአብሔር መፍራት፥ ከውሸትና የማጋነን ህይወት መውጣትና መራቅ ነው። እግዚአብሔር መፍራት፥ እላፊ የሆነ ነገር አለማናገርና አንደበትህን መግራት መቻል ነው። እግዚብሔር መፍራት፥ ለስጋ ፍላጎት ተላልፈህ አለመሰጠት ነው። እግዚብሔር መፍራት፥ ሰውን በሰውነቱ መቀበል፣ ማክበርና መውደድ ነው። እግዚአብሔር መፍራት፥ በዘፈቀደ ከሚኖር ዓይነት ህይወት ውስጥ መውጣትና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ነገር እየመረመርክ የሚኖር ጥበብና ማስተዋል የተሞላበት ህይወት ነው።

በሌብነት በሙስና በዓመጽ ባገኘኸውና በሰበሰብከው ሀብት፥ ጸበል ጻዲቅ ቅመሱ እያልክ እልል ያለ ድግስ ደግሰህ ወዳጆችህ ጠርተህ ድሃ እንዳይገባ ደግሞ AK-47 መሳሪያ የታጠቀ ሚኒሻ በር ላይ አቁመህ ማብላትና ማጠጣት፣ ጥዋፍና ጃንጥላ ለቤተ ክርስትያን መስጠት ማለት አይደለም። እነዚህ በሙሉ በሙስናና በሌብነት የታወረው ልብህን ለማጽናናት፣ ራስህን ለማታላል፣ እግዚአብሔርንና የእግዚአብሔር መላክዕክት የወንጀልህ ተባባሪዎች ለማድረግ፣ በሙስና ለመጥለፍ፣ ለመደለልና አፍ ለማስዘጋት የሚደረጉ ድርጊቶችና ጥረቶች እንጅ እንዲህ ያለ ድርጊት እግዚአብሔር ከመፍራት የሚያገናኝ አንዳች ነገር የለውም። ለቤተ ክርስትያን የምትሰጠው ነገር ሁሉም አንተ ራስህ ነው ተመልሰህ የምትገለገልበት።

ታድያ፥ ሰማይ ዙፋኔ ነው፥ ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት፤ የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው? የማርፍበትስ ስፍራ ምንድር ነው? እነዚህን ሁሉ እጄ ሠርታለችና እነዚህ ሁሉ የእኔ ናቸው። የምድረ በዳ አራዊት ሁሉ በሺህ ተራራዎች ያሉ እንስሶችም የእኔ ናቸው! ለሚለው ለእግዚአብሔር ወርቅና ጨርቅ በመስጠት የምንገልጸው ፍቅር የለም። በነገራችን ላይ፥ እግዚአብሔርን መፍራት የፍቅር ህይወት መኖር ነው። በለው እጨደው! የሚለውን ስብከት እግዚአሔርን ከሚፈራ ሰው አንደበት አይወጣም።

የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች የኢትዮጵያ ህዝብ ድካም ጠንቅቀው ስለሚያውቁ የእግዚአብሔር ስም እያነሱ ሲመጻደቁበትም እግዚአብሔርን አይፈሩም። አፋቸው በከፈቱ ቁጥር ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው! ኢትዮጵያዊነት ጀግንነት ነው! ኢትዮጵያዊነት የሰላምና የአንድነት መገለጫ ነው! ኢትዮጵያዊነት ፈሪሐ እግዚአብሔር ነው! ወዘተ እያሉ ውሸታቸውን ደማችን ውስጥ ከተውብናል። ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያውያን ስለ ራሳችን የተጋነነ ምስል እንድንይዝና ችግሮቻችንን አጥርተን እንዳናይ፤ ከስህተታችን በመታረም ወደ ፊት እንዳንገሰግስ አድርጎናል።

ዘመናችን በሙሉ ፍቅር በማጣት ከተራ ጸብና ሁከት ያለፈ በጦርነት እየታመስንና እየተላለቅን ያለን ህዝቦች ሆነን ሳለን ኢትዮጵያዊነት ፍቅር ነው! ሲሉን እንዴት? ብለን እንዳንጠይቅ እንኳ አቅም አሳጥተውናል። እነዚህና ሌሎች የውሸት መፈክሮች እያስተጋቡ እኛ እሳት ውስጥ ይከታሉ እነሱ እሳት ይሞቃሉ። እኛ እንሞትላቸዋለን እነሱ በእኛ ሞት አለማቸውን ይቀጫሉ። ጥቂቶች ሆነው ሳሉ፥ ወደ ፈለጉት አቅጣጫ እንዲዘውሩንና እንዲያሽከረክሩን አቅም የሰጣቸው ሌላ ምንም ሳይሆን ከመጠየቅ ይልቅ ነው! ሲሉን ነው! እያልን ለመድገም በራሳችን ላይ ስለፈረድን ነው።

አንድ ነገር ልጨምርና ወደ ሌላ ርዕስ ልለፍ። ጠቢቡ፥ በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ አራተኛውንም ትሸከም ዘንድ አይቻላትም፤ ይልና እንዲህም ያመሳጥረዋል፥ ባሪያ በነገሠ ጊዜ፥ ሰነፍም እንጀራ በጠገበ ጊዜ፥ የተጠላች ሴት ባል ባገኘች ጊዜ፥ ሴት ባሪያም እመቤቷን በወረሰች ጊዜ፤ እንዲል፥ ኢትዮጵያውያን እህል ውሃ ተገኝቶ በልተን ያደርን ዕለት ከአንደበታችን የሚወጣ ቃል፣ ውሎአችንና ሥራችን ይመሰክርብናል።

ወርቅ ወርቅነቱ የሚፈተነው በእሳት እንደሆነ ሁሉ፥ ሰው የምግብ፣ ሀብትና ንብረት የማፍራት ዕድልና አጋጣሚ ሲያገኝ ትክክለኛ ማንነቱ ይመዘናል። ከዚህ ውጭ ያለ የድህነትና የስራ አጥነት ውጤቶች ናቸው። ከሌለህ እንደ እንቁራሪትዋ ትፈነዳለህ እንጅ በማንም ልታቅራራ አትችልም። ሰው በልቶ ሲያድር፣ ሀብትና ንብረት ሲያፈራ፣ በሌሎች ላይ የሚሰለጥንበት ስልጣን ላይ ሲወጣ፥ በነገር ሁሉ ራሱን የማይገዛ ከሆነ፣ ክፉ (የትዕቢትና የእብሪት) ቃል ከአንደበቱ የማይወጣ ከሆነ፤ ሌሎችን ዝቅ ብሎ የማያገለግልና የት ህትና ህይወት የማይኖር ከሆነ፥ እግዚአብሔር አውቃለሁ ቢል ራሱን ብቻ ነው የሚያታልለው።

ኢትዮጵያዊነት፥ የጋራ ታሪክ ነው?

በጸረ ኢትዮጵያውነት የሚያስፈርጅ ጥያቄ ቢሆንም፥ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ታሪክ ነው ሲባል የትኛው ታሪክ? ብሎ መጠየቅ ጥበብ ነው። መቼም ይህን ሁሉ የሚሉ ሰዎች እንደ ቅዳሴ እነሱ ያሉትን ተቀብለን አሜን ካላልንና ካልደገምነው በጸረ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት የሚያስፈርጅ ነው። ታሪክ የሌለው ህዝብም ሆነ አገር በዓለም የለም። በጊዜ ውስጥ የሚያልፍ ህልውና ያለው፤ እኔ ማለት የሚችል ስሜት ፈቃድና እውቀት ያለው ሁሉ የኖሮው ዘመን ያህል የግልም የጋራም ታሪክ አለው። ታሪክ የሌለው፤ ሊኖረውም የማይችል፥ ያልነበረና የሌለ ብቻ ነው። በህልውና ያለፈ ሁሉ ታሪክ አለው። በተጨማሪም፥ ታሪክ ማለት ያለፈውን መተረክ ማለት እንጅ ታሪክ ማለት የተለየ ምትሃት ወይም ተአምር ማለትም እንዳይደለ ልብ ማለቱ አስፈላጊ ነው።

ኢትዮጵያ እንደ አገር ታሪክ ያላት አገር ናት። የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችም የራሳቸው የሆነ ታሪክና ስልጣኔ ያላቸው ህዝቦች ናቸው። ኢትዮጵያዊነት የጋራ ታሪክ ነው? ሲባል ግን ግልጽነት የጎደለበትና የተዘበራረቀ መልዕክት ያዘለ አባባል ነው። የርቁን ትተን የቅርቡን ብናነሳ እንኳ፥ ከኢትዮጵያ ምስረታ ጋር በተያያዘ ስማቸውና ታሪካቸው ጎልቶ የሚታወቀው የአጼ ምንሊክ ታሪክ እንመልከት። እኔ በግሌ ያለኝ አመለካከት ለማካፈል ያህል፥ አጼ ምንሊክ መወደስም መነቀፍም ካለባቸው፥ እንደ አንድ የአገር መሪ በሰሯቸው በጎ ስራዎች መመስገን፤ በፈጸሟቸው ስህተቶችና ግፎች ደግሞ መነቀፍ ይገባቸው የሚል እምነት ነው ያለኝ። ምንም ይሁን ምን፥ አጼ ምንሊክን መውቀስ የፈጣሪ የዓይን ብሌን የመንካት ያህል አድርገው የሚያስቡና ሌላውን ! እያሉ ሲያስፈራሩና ሲራገሙ የሚውሉ ሰዎች በእኔ ዘንድ ቦታም የላቸውም። የኢትዮጵያ ታሪክ በተነሳ ቁጥር የአጼ ምንሊክ ታሪክና አስተዋጽዖ በውዝግብ የታጠረ፣ የተዘበራረቀና አሻሚ የሆነበት ዋና ምክንያትም ይህ ነው።

የአማራ ክልል ተወላጅ የጻፈው እንደሆነ ምንሊክ ከሰው የተወለዱ፣ እንደ ማንኛውም ሰው ግድፈትና ህጸጽ የሚያውቃቸው፣ በዘመናቸው ፍጻሜ ሞተው አፈር የለበሱ መሆናቸውን ይቀርና፥ ጭራሽ ሰውዬው የመላእክት ዘር እንዳላቸው፣ እንከን የሌላቸውና የማይገኝባቸው፣ ሲያንቡም በመብረቅ ያነቡ እንደነበር የሚተርክ ፍጹም ከምድራዊም ሆነ ከሰማያዊ እውነት የተፋታ ውሸትና የተጋነነ ታሪክ ነው የሚጽፈውና የሚናገረው። የሌላ ክልል ተወላጅ የጻፈው እንደሆነ ደግሞ በአንጻሩ ምንሊክ አገር በማቅናት ረገድ የነበራቸውን ሚና አንኳሶ ጭራሽ ሰውየው የሰፈር አውራ ዶሮ ዓይነት ወረበላና አደገኛ ቦዘኔ እንደ ነበሩ ነው የሚያስነብበን። ሁለቱም ትክክል አይደሉም። ክፉም ይሁን ደግ ታሪክ በታሪክነቱ ነው በጻፍና መነገር ያለበትና የነበረበት። ነገር ግን፥ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ሁሉ በረከትና ስጦታ አልታደልንም። እርግጥ፥ ኢትዮጵያዊነት የጋራ ታሪክ ነው ብለን ከማውራት የሚከለክለን ኃይል የለም።

አንድም፥ ሊበልዋት የፈለጉ አሞራን ጃግራ ይሏታል እንደሚባለው፤ ፍቅር፣ አንድነትና ጀግንነት፥ የማያባራ ሁከት፣ ጸብ፣ ጦርነትና መፋጀት ማለት ካልሆነ በስተቀር የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በሰላም ተኝተው ያደሩበት ዘመን እንደሌለ ለማንም ግልጽ ነው። እንግዲያውስ ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው?

ኢትዮጵያዊ ሲባል ጥሬ ቃሉ በተባበሩት መንግስታት ዘንድ እውቅና ያላት፤ በህግ ኢትዮጵያ ተብላ የምትጠራ ሉዓላዊት አገር ዜጎች የሆኑ ህዝቦች ለመጠሪያ የሚውልና የሚያገለግል የዜግነት መጠሪያ ቃል ነው። ነት የምትለዋን ግን ከዚህ ያለፈ ትርጉም ያላትና የማንነት አንድነትን የሚያመላክ ቃል ነው። በርግጥ ይህ እውነት ሲበራልን፥ በኢትዮጵያ ታሪክ የት ቦታ ነው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በኢትዮያዊነታቸው እኩል ተጠቃሚ የሆኑትና የነበሩ? ማለታችን የማይቀር ነው።

የአሁኒትዋ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል ስያሜ ከያዘች ጊዜ አንስቶ በየትኛው ዘመን ነው ብሔር ብሔረሶች እኩል መብትና ስልጣን ኑሮአቸው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተሳታፊዎች የነበሩ የአገሪቱ ሀብተ በረከት እኩል ተካፋዮች የሆኑ? ጥቅማ ጥቅሙ ቀርቶባቸው ህልውናቸውስ ቢሆን በውል ይታወቁ ነበር ወይ? ቢታወቁስ በክብር ነበር ስማቸው የሚነሳና የሚጠራ? ይህ ለእያንዳንዱ ህሊና ያለውና ለህሊናው የሚያድር አንባቢ የሚተው ጥያቄ ነው።

ነት የሚለው ተጨማሪ ቃል አደናጋሪ መደለያ ቋንቋ በቅንነትና በእውነት አለተመግበሩና ስራ ላይ አለመዋሉ፥ ኢትዮጵያ እንደ አገር ቁልቁል ከመድፋቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች በሰላም እንዳይኖሩ የሁከትና የመበጣበጥ መሳሪያ ሆኖ ዛሬ ላይ ደርሷል። አይደለም ሐረሬ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤንሻንጉል ጉምዝ ቀርቶ አርባ ሚልዮን ቁጥር አለኝ የሚለው የኦሮሞ ብሔር በኢትዮጵያ ታሪክ እኩል ተጠቃሚ አልነበርኩም፤ ተገፍቼ ነው የኖርኩት እያለ ነው። ሌሎቹ ለጊዜው አፍ ስላልከፈቱ የሚሰማቸውን ስሜት ለማወቅ ይከብዳል።

በእርግጥ፥ በቅርቡ አስራኛ ክልል የሆነው የሲዳማ ህዝብ እአአ 19 ጁላይ 2020 / ሪፖርተር የሲዳማ አዲሱ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሾሙት ከአቶ ደስታ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ፣ እንዲሁም የወደፊት የክልሉን ዕጣ ፈንታ በማስመልከት በነበረው ቆይታ፥ ከተቀሩት የደቡብ ሕዝቦች ዞኖች አንፃር ሲታይ ሲዳማ ያደገና በፖለቲካም ረገድ ተሰሚነቱ ከፍ ያለ ነው ይኼ ሆኖ ሳለ ሲዳማ ክልል ለመሆን የፈለገበት ምክንያት ምንድነው? ሲል ላነሳላቸው ቀዳሚ ጥያቄ የሰጡት ምላሽ የሚከተለው ነበር፥ ምክንያቶች ሥነ ልቦናዊም ናቸው። ኢኮኖሚያዊም ናቸው የሚሉ ፕሬዝዳንቱ አባባላቸው በዝርዝር ሲያስረዱ ደግሞ፥ ሥነ ልቦናዊ ናቸው ስንል ሲዳማ ኢትዮጵያ በማዕከላዊ መንግሥት ከመሰብሰቧ በፊት የራሱ አስተዳደር የነበረው ሕዝብና አካባቢ ነው። ኋላ ላይ የራሱ የነበረው አስተዳደር በማዕከላዊ መንግሥት ተፅዕኖ ሲፈርስበት፣ በቦታው የተተካው ሥርዓት የተመቸው አልነበረም። ከቀዬው ያፈናቀለው፣ መሬቱን የቀማውና በአስተዳደሩም ከራሱ አብራክ የወጡ ልጆች ሲያስተዳድሩት አልነበረም። ከሌላ አካባቢ የመጡና በዚህ አካባቢ ሲያስተዳድሩ ነበር የቆዩት። ስለዚህ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዕድሉን ጭምር የተነፈገ ነበር። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሲፈጸምበት የነበረው በደል ብሶትን የወለደ ነበር ለማለትም ይቻላል። መሬቱ ሲነጠቅ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱ አደጋ ላይ ወደቀ ማለት ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ ነፃ ሆኖ ጉልበቱን በማይጠቀምበት ሁኔታ ነበር የጭሰኛ ሥርዓት የነበረው። በሳምንት ስድስት ቀን ለሚያስተዳድረው ነው የሚያርሰው። ለራሱ የእረፍ ቀን ተብሎ የተሰጠው እሑድ ቀን ብቻ ነበር። ይበዘበዝ ነበር። በቋንቋውም መጠቀም አይችልም ነበር። በአንድ ወቅት እንዲያውም የነበረውን እምነት በአግባቡ መፈጸም እንዳይችል ተደርጎ ሌላ ሃይማኖት እንዲቀበል፣ አንድ ወጥ ሃይማኖት እንዲተገበር በፈቃድ ሳይሆን በኃይል የታወጀበት ሁኔታ ነው የነበረው። ስለዚህ በዕምነቱ የሚያከውናቸውንና ጥሩ ናቸው የሚላቸውን ተግባራት እንዳይተገብር ተገዶ ነበር። በባህሉም እንዲሸማቀቅ የተደረገበት ሁኔታ ነበር። እነዚህ ምክንያቶች ከዚያን ጊዜ ጀምረው ነፃ የመውጣት ስሜትን የወለዱ ናቸው። ስለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ ግጭቶች ነበሩ። ይኼ ሁኔታ ሄዶ ሄዶ የአፄዎቹን ሥርዓት በተደራጀም ባልተደራጀም መንገድ እየታገለ፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በተነሳበት ትግል ሥርዓቱ ሊወድቅ ችሏል። ከዚያ በኋላ የመጣው የደርግ ሥርዓት በራሱ መጀመርያ ላይ መሬት ላራሹ አውጆ ነበርና የሲዳማ ሕዝብ ተነጥቆ የነበረውን መሬት መለሰለት። በዚያም ምክንያት የደርግ ሥርዓትን ደገፈ። ይሁንና ቀደም ብሎ ያነሳኋቸው በቋንቋው እንደ ልቡ የመጠቀም፣ ባህሉን የመግለጽ፣ በማንነቱ የመኩራትና ራሱን በራሱ የማስተዳደር የመሳሰሉ ቀደም ብዬ ሥነ ልቦናዊ ያልኩት አስተሳሰብ አብሮ ይጓዛል። ሰውም በየጊዜው ጥያቄ ያነሳል። እነዚህን ጉዳዮች ሲመዝን አሁንም ያልተመቸው ሆነ ይላሉ። ከአጼዎቹ ጊዜ ጀመሮ ለመቶ ዓመታት የመብት ጥያቄ ማቅረቡን ያላቆመ የሲዳማ ህዝብ ይደርስበት የነበረው ግፍና በደል በአጭሩ ሲያስረዱም፥ በዚህም ምክንያት 100 ዓመታት በላይ በትግል ሕይወት ውስጥ ከባድ ዋጋዎችንም ከፍሏል። የምንሰማቸው ታሪኮች እንደሚሳዩት የሰው አንገት ተቆርጦ በገበያ ሥፍራ በእንጨት ተሰቅሎ ገበያተኛው እያየ እንዲፈራ፣ እንዲሸማቀቅና መሰል ትግሎችን እንዳያደርግ የሚያደርጉ ሁኔታዎች በርካታ ነበሩ ይላሉ። የሲዳማ ህዝብ ክልል የመሆን ጥያቄ ሆነ የፕሬዝዳንቱ መልዕክት ግልጽ ነው ብዬ አምናለሁኝ።

እንግዲያውስ፥ ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው? ዓላማውስ ምንድ ነው? ኢትዮጵያዊስ ማን ነው? አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ተብሎ ለመታወቅ ሆነ ለመጠራት ምንድን ማድረግ ይጠበቅበታል? መመዘኛ የለውም፥ አያስፈልገውምም! የሚባል ከሆነ ደግሞ በእውነቱ ነገር ሲጀመር ኢትዮጵያዊነት አየር ላይ የተንጠለጠለ መፈክር ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያዊነት እውነት ነው! ተብሎ የሚታመን ከሆነ ግን ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው? ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ከስድብና ከእርግማን ይልቅ አጥጋቢ ምላሽ መስጠት ይጠበቅብናል። አይመስሎትም?

ኢትዮጵያዊነት የሰላም አርማ ነው?

የሰላም አርማ? እኔ እስከማቀው ድረስ አርማ ማለት ምልክት ወይም አንድን ነገር የሚገልጽ ልዩ መታወቂያ ማለት ነው። ሌላ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ያለች እንደሆነች አላውቅም። በሰሜን ኤርትራ፣ በምስራቅ ጁቡቲና ሶማሊያ፣ በምዕራብ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን፣ በደቡብ ሀገረ ኬንያ የሚያውስንዋት አፍሪካዊትዋ ኢትዮጵያ የሆነች እንደሆነ ግን ከሰላም ጋር የምትተዋወቅ አገር አይደለችም። አጼዎቹን ስንረግም፣ ንጉሡን ስናማርርና ስናብጠለጥል፣ ደርግን አይቅናህ! የህወሓት መሪዎችን ይድፋቹ ስንል፣ አሁን ደግሞ / ዐቢይ አህመድን ዳውን ዳውን ዐቢይ! ስንል ሰላም የምናውቅ ሰላማውያን ዜጎች ብንሆን ነው? ባይሆን የጸናብን የማጉረምረም በሽታ የትውልድ ጉልበት የሚበላ እርግማን ተብሎ ቢታወቅና መድኃኒት ብናፈላልግለት ነው የሚሻለው።

እርግጥ ዳውን ዳውን ኢትዮጵያ! ለማለት በአደባባይ የወጡ ሰዎች ጤና ያላቸው ሰዎች ናቸው የሚል እምነት የለኝም። እነዚህ ግለሰቦች አብዛኞቹ መራራነት በልባቸው ውስጥ በቅሎ ያደገባቸውና አመጸኝነት የነገሰባቸው፤ የህይወት ትርጉምና ጣዕም የጠፋባቸው፤ የሚሰሩትና የሚያደርጉት የማያውቁ፤ መረጋጋት የተሳናቸው፤ ለእርግማን ተላልፈው የተሰጡ፤ ሁሉን ነገር የተምታታባቸው፤ ሰላማቸው ያጡና ሌላውን ማኅበረሰብ ለመበከልና ሰለባ ለማድረግ ታጥቀው የተነሱ፤ ዕረፍት ያጡ ተቅበዝባዦችና የጠፉ ግለሰቦች እንጅ የአገር ፍቅር ስለሚበላቸውና ግድ ስለሚላቸው ነው ብሎ ማመን ሲበዛ የዋህነት ነው። በዚህ አጋጣሚ ከእንደዚህ ዓይነት አጥፍቶ ጠፊዎች ራሳችንን እንድንጠብቅ እጠይቃለሁኝ።

እውነት ነው ለኢትዮጵያ ያልተከፈለ መስዋዕነት የለም። እኔ የማስታውሰው የባድመ ጦርነት የተከፈለ የህይወት መስዋዕትነትና የፈሰሰ ደም ቀላል አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ፥ ኢትዮጵያ ቆሎ ብትሆን ኖሮ የራሱን ኪስ ለማደለብ ያልላበበት ሀብትና ንብረት ለማግበስበስ ያልበላትና ያልሸጣት ባለሥልጣን የለም። በተበላችና በተሸጠች ቁጥር፤ ድሃ ፍትህ ባጣና በተበደለ ቁጥር፤ በተገፋና ባለቀሰ ቁጥር የምታንስ ብትሆን ኖሮ በዚህ በያዝነው 2012 / ኢትዮጵያ የምትባል የአንድ ቀበሌ የቆዳ ስፋት አይገኝባትም ነበር። ኢትዮጵያዊነት የሚገልጽ አርማ ካለ ይህ ነው አርማችን። ሙስና።

ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል የሰላም አርማ ነው ካልተባለ በቀር ሰላም አርማችን ሊሆን አይችልም። ሰላም ስላጣን አይደለም ወይ ስላምን ፍለጋ እየጮህን ያለነው? ሰላም ስላጣን አይደለም ወይ ጸጉረ ልውጥ ያያችሁ እየተባለ ያለው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ጸጉረ ልወጥ ህዝብ ማን ነው?

 

ኢትዮጵያዊነት አንድነት ከሆነ ኢትዮጵያ ውስጥ ጸጉረ ልውጥ ማን ነው? የሚለው ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው። በተለይ ህዝባዊ አመጹን ተከትሎ ስልጣን የተቆናጠጠ የዐቢይ አህመድ መንግስት ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ለሚፈጠረው ችግሮች በሙሉ ተጠያቂ የሚያደርገው መልምለውና ቆፍቁፎው ያሳደጉትን የህወሓት ሰዎቹን ነው። ችግር በተፈጠረ ቁጥር ምንም ዓይነት የፖሊስ ምርመራ ባልታከለበት ሁኔታ በደቂቃዎች ውስጥ በመንግስት ደረጃ ፈጣሪው ወያነ ነው እየተባለ ህዝቡ ጸጉረ ለወጥ ሰው እንዲከታተል በተደጋጋሚ ሲነገር ተስተውሏል። ይህን ዓይነቱ ጸረ ኢትዮጵያዊነት ፕሮፓጋንዳ አንድም ምንም ዓይነት ህጋዊ እርምጃ ላይወሰድ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከአማራ ክልል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት በይፋ ሲነገርና ሲስተጋባ መስማት የመተንፈስ ያህል የተለመደ ነው።

ጥያቄው፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ጸጉረ ልወጥ ህዝብ ማን ነው? እኔ እስከማቀው ድረስ የቃሉ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ጸጉረ ልወጥ ማለት ምጻተኛ ማለት ነው። ይህም ሆኖ፥ እግዚአብሔር ስለ መጻተኛ ህዝብ ግድ የሚለው አምላክ ነውና፥ መሴ እስራኤልን ምጻተኞችን እንዳትገፋና እንዳትበድል፣ በጽድቅ እንድትፈርድ፣ በእኩልነትና ፍትሐዊነት በሆነ ዓይንም እንድትመለከት፥ አስተምሯል፤ አዝዘዋል፤ አስጠንቅቀዋልም ከወንድሞችህ ወይም በምድርህ በአገርህ ደጅ ውስጥ ከሚቀመጡት መጻተኞች ቢሆን፥ አታስጨንቀው። ድሀ ነውና፥ ነፍሱም ጠንክራ ትፈልገዋለችና ወደ እግዚአብሔር እንዳይጮኽብህ ኃጢአትም እንዳይሆንብህ ደመወዙን ፀሐይ ሳይገባ በቀኑ ስጠው። የመጻተኛውንና የድሀ አደጉን ፍርድ አታጣምምባቸው (ዘዳ 2414) እንዲል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሌሎች የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ይህን ከፋፋይ ሰይጣናዊ መልዕከት ህዝቡ ውስጥ ሲያስተገቡ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ወይም ፈረጅ ማለታቸውን እንዳይደለ የታወቀ ነው። ታድያ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ጽጉረ ልውጥ ህዝብ ማን ነው? ትግራኛ ተጋሪው ማኅበረሰብ? ፊቱ የአስራ አንድ ቁጥር አንድም የመስቀል ምልክት ያለበት ሰው? መታወቂያው ገብረመዲሂን፣ ደብረጽዮን፣ ሐጎስ፣ ተኽለማሪያም፣ ተኽለ ወይኒ፣ ለተማርያም፣ ለተስለሰ ወዘተ የሚል የትግርኛ ተናጋሪ ማኅበረሰብ ስም ያለው ሰው?

ኢትዮጵያ ውስጥ ጸጉረ ልውጥ ማን ነው? ኢትዮጵያ ውስጥ ጸጉረ ልውጥ ህዝብ አለ! ተብሎ የሚታመን ከሆነ ኢትዮጵያዊነት አንድነት ነው! ኢትዮጵያዊነት እኩልነት ነው! ተብሎ የሚነፋው መለከት መሰረቱ ምንድ ነው? የኦሮሞ ተወላጅ ሆኖ ጽጉረ ልውጥ ህዝብ ተከታተሉ የሚል ከሆነ፥ ገመቹ፣ ቢፍቱ፣ ሀጫሉ፣ እያመላከተ እንዳይደለ ግልጽ ነው። የአማራ ክልል ባለ ስልጣናት ጽጉረ ልውጥ ሰው እያሉ መሸለልን ከተያያዙት፥ በላቸው፣ ቁሙላቸው፣ ደመላው፣ ደመቀ፣ አስናቀች፣ ስመኝ፣ ስንሻው ወዘተ ማለታቸው የታወቀ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኑ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣት ይህን ቃል በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ በሰሚ ጆሮ ቀድሞ የሚመጣ የትኛው ህዝብ ሊሆን እንደሚችል ፍርዱ ለእርስዎና ለእግዚአብሔር እተወዋለሁ። ለሰው መዋሸት ቢቻለንም ከህሊናው ሊያመልጥ የሚቻለው አንድም ሰው ግን አይኖርም። አንድም፥ በድን ካልሆነ በስተቀር።

ኢትዮጵያዊ ማን ነው?

የኢትዮጵያ ፓስፖርት ያለው ማንኛውም ሰው ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነው። አንድ ሰው ኢትዮጵያዊ ተብሎ በህግ ለመታወቅ፥ ከአማራ፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሞ ወይም ከደቡብ ወዘተ መወለድ አይጠበቅበትም። ኢትዮጵያዊ ተብሎ ለመታወቅ በህግ የተቀመጠውን የሚያሟላ ማንኛውም ሰው ኬንያዊም ሆነ ሱዳናዊ ኢትዮጵያዊ መሆን ይችላል። በህጉ መሰረት በተመሳሳይ ጊዜ ኬንያዊ ሆኖ ኢትዮጵያዊ፤ ሱዳናዊ ሆኖ ኢትዮጵያዊ መሆን ነው የማይችለው እንጅ ኬንያዊነቱንና ሱዳናዊነቱ ጥሎ ኢትዮጵያዊ ለመሆን የሚያበቃው መመዘኛ ካሟላ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ከመታወቅና ከመጠራት የሚያግደው ሆነ የሚከለክለው ነገር የለም።

ኢትዮጵያዊነት ከዜግነት ያለፈ ሌላ ተአምር የለውም። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያዊነትን በትክክል መተጎም እንጅ አንዳንዶች እንደሚያስቡትና እንደሚሉት ኢትዮጵያዊነት ማቃለል አይደለም። ኢትዮጵያዊነት ማቃለልና ማራከስ የሚሆነው ኢትዮጵያዊነት በአግባቡ አለመረዳት፤ አለመተርጎም፤ ያልሆነ ትርጉም መስጠት፤ ለህቡእ የፖለቲካ አጀንዳ እንደ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም፤ ለጸብና ለህውከት በሚጋብዝ መልኩ የተጣመመ ትርጉም መስጠትና ሸውራራ አመለካከት ማራመድ ነው። ጥሬ ቃሉን በተመለከተ ይህን ካልን ዘንዳ አንድምታው ደግሞ እንመልከት።

ኢትዮጵያዊነት ከዜግነት ያለፈ የማንነት ትርጉም ሊይዝ የሚችል እንደሆነ አይተናል። እንግዲህ፥ ትግራዋይ ትግራዋይነቱን፣ አማራ አማራነቱን፣ ኦሮሞ ኦሮሞነቱን ትቶ፣ ሀረሬ፣ አፋር፣ ደቡብ ሁሉም የራሱ ልዩ ማንነት (መታወቂያ) ትቶ በማንነቱ ኢትዮጵያዊ ተብሎ ይጠራና ይታወቅ ዘንድ የተፈለገበት ምክንያት ምንድ ነው? የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ኢትዮጵያዊ ተብለው መትወቅ አይችሉም አላልኩም። ታሪካቸውንና ባህላቸውን ጠብቀው እንዲኖር ቢፈቀድላቸው እኮ ኢትዮጵያዊነት ጦስ ባልሆነን ነበር ምስጢሩ ያለው ግን ወዲህ ነው።

የህወሓት መሪዎች ለለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመዝብሩና በዜጎች ላይ -ሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙ የትግራይ ህዝብ አማክረው፣ የትግራይ ህዝብ ይሁንታና ፈቃድ አግኘተው አልነበረም። የህወሓት አረመኔያዊ ባህሪይ ክቡር ከሆነው የትግራይ ህዝብ አንዳች የሚያገናኝ ነገር የለውም፤ የሌባና የወንጀለኛ ብሔር የለውም! በማለት ለትግራይ ህዝብ ትልቅ ክብር እንዳለው አውስቶ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የህወሓት መሪዎች በመቃወም ድምጹን ያሰማ አዴፓ በሰጠው መግለጫ የሰፈረ ቃል ነው።

በተመሳሳይ፥ ኢትዮጵያዊነት በማቀንቀናችን ነው ይህ ሁሉ ግፍና በደለ የደረሰብንና እየደረሰብን ያለ፤ በማለት የሚታወቁ እነዚህ የአማራ የፖለቲካ ልሒቃን የሚያራምዱት ፖለቲካ የአማራ ህዝብ ስለላካቸው፤ አንድም፥ የአማራ ህዝብ መላ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአማርኛ ካልተናገረ፤ የራሱን ጥሎ የአማራ ባህል ካልያዘ ሙቼ እገኛለሁ! በማለት አላካቸውም። ይህ ለሁሉም ግልጽ ሊሆንለት ይገባል። ኢትዮጵያዊነት በማቀንቀናችን ነው እንደ ጠላት የተቆጠርነው የሚሉ የአማራ የፖለቲካ ልሒቃን ከአማራ ህዝብ ጥያቄ አንዳች የሚያገናኝ ነገር የለውም። ንግዳቸው የሚያጧጥፉት ግን እንደ ማንኛውም ህዝብ የማንም መገፋትና መበደለ የማያስደስተው በአማራ ህዝብ ስም ነው። በጉያ ተወሽቀው ነው።

ለዘመናት እንቆቅልሽ የሆነብን፤ ጉልበታችንን የበላ የሴራ ፖለቲካ ይህ ነው። ኢትዮጵያዊነት ሲባል እንዲሁ ሳይሆን አንድ ባህል አንድ ቋንቋ አንድ ህዝብ የመፍጠር አባዜ ነው ውስጥ ለውስጥ እያባላንና እያጨራረሰን ያለው። በኢትዮጵያዊነታችን መግባባት ተስኖን በአንጻሩ ኢትዮጵያዊነት እርስበርስ የሚያጨራርሰን ከሆነ ኢትዮጵያዊ መባል የሚያስገኘው ልዩ ጥቅም ምንድ ነው? ቻይናዊ? ኢትዮጵያዊ ተብሎ ባለ መጠራቱ ምን ቀረበት? ሁከትና ጦርነት ካልሆነ በስተቀር ምንም አልቀረበትም።

አንዳንድ ቅንነት የሚጎድልባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ፥ አንድን ነገር ሲሰሙ ሆነ ሲያነቡ ለእነሱ በሚያመች መልኩ በመቃኘት ስለሚሰሙና ስለሚያነቡ ይህ አባባሌ ከጽሑፉ ዓላማ ውጭ በመተርጎም ለሌላ ዓላማ ማስፈጸሚያ ሊጠቀሙበት ይችላሉ። እኔ ደግሞ እንደዚህ ያለ አላስፈላጊ ብዥታና ውዥንብር እንዲፈጠር አልፈልግም፤ አልፈቅድምም። ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት እያልኩ አይደለም፤ አላልኩም። ስለ ኢትዮጵያ አሉታዊ አመለካከት እያንጸባረቅኩም አይደለም። የማጥራት ስራ መስራት ማለት መቃወም ማለት አይደለምና። በተረፈ፥ ኢትዮጵያ ለእኔም አገሬ ናት። ማንም ሰለወደደ ወይም ስለጠላ የሚሰጠኝና የሚነሳኝ አንዳች ነገር የለውም።

ከእኔ በላይ ላሳር የምል ዓይነት ሰው ባልሆንም፤ ከማንም ባልተናነሰ ግን አገሬን እወዳለሁ አገሬን አከበራለሁ። አመል ያለበትና በግብዝነት የተጠመቀ ካልሆነ በስተቀርም በአገር ጉዳይ ማንም በማንም ላይ የመመጻደቅ ማንኛውም ዓይነት መብት የለውም። በብርድ ልብስና በአንሶላ ፈንታ ባንዴራ ተጠቅልሎ የሚተኛ ሰውም ቢሆን ቁርጡን ሊያውቅ ይገባዋል። ጥያቄው፥

 • ኢትዮጵያውነት እኩልነት ካልሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት ፍትሐዊነት ካልሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት እያንዳንዱ ብሔር ብሔረሰብ ትልቁም ትንሹም የምድሪቱ በረከት እኩል ተካፋይ የማያደርግ ካልሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች የማንነት ጥያቄ የማይመልስ ከሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት የብሔር ብሔረሰቦች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ነጻነት ዋስትና የማይሰጥና የማያረጋግጥ ከሆነ፤
 • ኢትዮጵያዊነት አንዱ የበላይ አንዱ የበታች ማለት ከሆነ ኢትዮጵያ የምትባል አገር በመኖርዋ/በህልውናዋ ተጠቃሚ የሚሆነው ማን ነው? ኢትዮጵያዊነት በቀጥታም በተዘዋዋሪም አንድን ሕዝብ እየነጠልክ ማጥቃት ማለት ከሆነ ኢትዮጵያ! ኢትዮጵያ! ከሚለው ጩኸትና ሽለላ ጀርባ ያለው አንጀንዳ ማንንም እንደማይጠቅም ሊታወቅ ይገባል። ደግሞም ውጤቱ መሬት ላይ በተጨባጭ እያየነው ነው። ተከባብረንና ተጠባብቀን የምንኖርባት አገር መፍጠር ከተሳነን ኢትዮጵያ የምትባል አገር እንድትኖር የተፈለገበት/የሚፈለግበት ምክንያትም ቢሆን ግልጽ አይደልም። ጦርነት ናፋቂ ህዝቦች ካልሆን በስተቀር።

ይህ የምለው ከመሬት ተነስቼ አይደለም። ሳትወለድ የተጨናገፈች ሀገር መሪ የሆኑት የሲዖል ፈላስፋ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያን አስመልክተው የሰነዘሩት ቃል ማስታወስ አስፈላጊ ነው።

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ኢትዮጵያ የጠላቶቼ አገር ናት ብለው በሚያምኑበት ዘመን ኢትዮጵያን በማስመልከት የሰነዘሩት አስተያየት ኢትዮጵያ ከሁለተኛ የዓለም ጦርነት በኋላ በእደ ምዕራባውያን ተጠፍጥፋ የተሰራች አገር ናት ነበር ያሉት። ታድያ ፕሬዝዳንቱ አፋቸው ሞለተው ይህን ሲሉ፥ የተገፋሁት ኢትዮጵያዊነት በማቀንቀኔ ነው፣ ስምዋ ሲነሳ ሆዴ ይቆርጠኛል፣ የልብ ምቴ ይጨምራል፣ አያስችለኝም፣ ያንገበግበኛል፣ ወባ እንደያዘው ሰውም ያንቀጠቅጠኛል፤ ራሴን መቆጣጠር አልችልም ወዘተ የሚለው ምድረ አክቲቪስት ነኝ፣ አርቲስት ነኝ፣ ጋዜጠኛ ነኝ የሚለው በክስና በማጉረምረም የሚታወቁ ተራጋሚ ግለሰቦች አገሬ ተነካች ብለው ግን አንዳች ቃል አልተነፈሱም። በኢትዮጵያዊነቱ ለድርድር የማይቀርብ ሕዝብ ለመዝለፍና ለማዋረድ ግን ተኝተው አላደሩም። ያልደረስባቸው የትግራይ ተወላጅ ግለሰብ መንገድ ላይ ሲያዩ እንዳበደ ውሻ የማይሆኑትና የማይሉት ነገር የላቸውም። ምዕራባውያን፥ የዕብሪተኛ ሰው ችግር፣ አፉ ሁል ጊዜም ክፍት ነው እንደሚሉት ከእነዚህ ሰዎች አፍ የሚወጣ የስድብ መዓትና የውዝጅብኝ ቃል ላለመስማት እግዚአብሔር ራሱ ጆሮቹን እንደሚደፍን ነው የማምነው።

በነገራችን ላይ እነዚህ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች፣ ጋዜጠኛ፣ አክቲቪስት ወዘተ ተብለው የሚታወቁ ግለሰቦች ብዙሐኑ ለሞያው የሚመጥን ምንም ዓይነት ትምህርትም ሆነ እውቀት የሌላቸው የልምድ አዋላጆች ናቸው። አንዳንዶቹ የደርግ መንግስት የሰራዊት አባላትና የፕሮፓጋንዳ ሰራተኞች የነበሩ በጥላቻ የተበከሉና ህመሙ የጸናባቸው፤ በዚህ አዲስ ትውልድ መካከል መኖር የማይገባቸው የጸብና የአመጽ ሰዎች ናቸው። በመሆኑም፥ እነዚህ የአመጽ፣ የደምና የጦርነት አጋፋሪዎች ተደብቀን ሳይሆን ፊት ለፊት አብረን ልንታገላቸው ይገባል።

ይህ ጽሑፍ ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው ከሚል ተሻሽሎ ከወጣው አዲስ መጽሐፍ የተወሰደ ነው። መጽሐፉን ለመግኘት አማዞን የገበያ ድረ ገጽ በመግባት የመጽሐፉን ስም በመጻፍ (ኢትዮጵያዊነት ምንድ ነው?) ማግኘት ይቻላል።

E-mail: mahbereseytan@gmail.com

 


Back to Front Page