Back to Front Page

ዳሰሳ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብዙሪያ

ዳሰሳ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ

በይዲድያ ብፁእ 02-28-20

ዉሃ ሕይወት ነው። ለሰው ልጅ አስፈላጊ ከሆኑት በግንባር ቀደምትነት የሚሰለፈውውሃ ነው።የውሃ አጠቃቀምበአግባቡ ካልተያዘ ጎሮቤት ከጎሮቤት፤ መንደር ከመንደር፤ ወረዳ ከወረዳ፤ ክልል ከክልል ጋር ሊያጋጭና ሊያጣላ የሚችል ነው። ከዚህ በተጓዳኝ ድንበር ዘለል ወንዞች በሃገሮች መካከል ጥልና ከዚያም አልፎ ጦርነት ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። በዚህ አጭርና አጠቃላይ ዳሰሳ ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ወቅታዊ ዝርዝር ሁኔታና ስለ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞቻችንበአጠቃላይም ስለ ውሃ ፀጋችን ለማየት እንሞክራለን።

ጥቁር አባይ ክኢትዮጵያ ደጋማዎቹ ስፍራዎች የሚመንጭ ሲሆን፤ ከነጭ አባይ ጋር ተቀላቅለው ወደ ግብፅ የሚፈስሱት የሱዳን ርእስ ከተማ በሆነችው ካርቱም ላይ ነው። አባይ ወይም ናይል በዓለም ረዥሙ ወንዝ ነው። ናይል አሥራ አንድ አገሮችን አቆራርጦ የሚያልፍ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ነው።

ወደ ታህታይ ተፋሰስ ሃገሮች ማለትም ወደ ሱዳንና ወደ ግብፅ  85% ውሃ የሚፈስሰው ከጥቁር አባይ (ክኢትዮጵያ) ሲሆን፤ ቀሪው 15% ነጭ አባይ ተብሎ የሚጠራው ወንዝ የሚያልፍባቸውየላእላይ ተፋሰስ ሃገሮች፤የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ፤ ኬንያ፤ሩዋንዳ ታንዛኒያ፤ደቡብ ሱዳንና ዩጋንዳ ናቸው። ጥቁር አባይና ነጭ አባይ ካርቱም ላይ ከተገናኙ በኋላ ወደ ግብፅ በመፍሰስ ወደ ሜድትሪያንን ባህር ይቀላቀላሉ።

የውሃው አጠቃቀም ታሪክ ሲታይና ሲወሣ በ1929 እና 1959 የላይኞቹ ተፋሰስ አገሮች ሳይጨምር፤ የታችኞቹ ተፋሰስ ሃገሮች ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የሚያደርግ ውል ተደርጓል። በ 1929 የተደረገው ውል የአንግሎ-ኤጅብሺያን (Anglo Egyption Treaty) ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፤ በታላቋ ብሪታንያየተፈረመ ውል ነው። በዚህ ወቅት ታላቋ ብሪታንያ ከኢትዮጵያ ውጭ አብዛኛዎቹ የምስራቅ አፍሪካ አገሮች ቅኝ ገዥ ሃገር ነበረች።  በዚያ ወቅት ግብፅ በመሳፍንት የምትገዛ አገር የነበርች ሲሆን፤ በታላቋ ብሪታንያ ቅኝ ግዛት ሥር የነበረች ሃገርናት። እንግሊዝ ግብፅን አበክራ የፈለገችው በዋናነት በዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ወሳኝ የሆነውን የሰዊዝ ካናልን ለመቆጣጠር ነበር። አሜሪካም ግብጽን አሁንከምትደግፍበት አንዱ ምክንያት ይኼው ሲሆን፤ እስራኤል ከፊልስጤሞች ያላት ፍጥጫና ረመጥ ለማብረድ ግብፅን እንደ ማራገቢያ ወይም ማቀዝቀዣ ስለምትጠቀምባት ነው።

የ1929ውል ታላቋ ብሪታንያ በገዛ ፈቃዷ የናይል ውሃ ሙሉ በሙሉ ግብጽና ሱዳን እንዲጠቀሙበት የሚፈቅድ ሲሆን፤  በዓመት ግብፅ 48 ቢልዮንና ሱዳን ዳግሞ 4 ቢልዮን ኩቢክ ሜትር ውሃ እንዲጠቀሙ የሚፈቅድ ውል ነበር። ይህም በዓመት በድምር 84 ብልየን ኩቢክ ሜትር ተብሎ ይገመት የነበረ የናይል ውሃ መጠን ነው።

በ1959 ሌላ አዲስ ውል በእንግሊዝና በነፃይቱ ግብጽ የተፈረመ ሲሆን፤ ውሉ የግብፅን የውሃ ድርሻ ወደ 55.5 ብልየን ኩቢክ ሜትር ከፍ ያደረገና፤ የሱዳንም ወደ 18.5 ብልየን ኩብክ ሜትር ያሳደገ ነበር። ቀሪው አንስተኛ የውሃ ድርሻ ደግሞ ለላእላይ ተፋሰስ ሃገሮች የሚፈቅድ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም አዲሱ ውል የ 1929 ውል የሚያጸና ከመሆኑ ባሻገር፤ በናይል ወንዝ ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት (Veto Power) ለግብፅ የሚያቀዳጅ ነበር። ይህ ስልጣን የናይል አጠቃቀም፤ ግንባታና ቁጥጥር የሚያካተት ነው።

ግብፅና ሱዳን ለበርካታ ዓመታት ያለ ተቀናቃኝ በእነዚህ ሁለት የቅኝ ግዛት ውሎች መሰረት የናይል ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ከማድርጉ ባሻገር፤እነዚህ ውሎች እስከ አሁን ድረስ መከበርና መፈጸም እንዳለባቸው በየመድረኩ አሁንም ማንሳታቸው አላቋረጡም። እነዚህ ውሎች ግን በዚህ ወቅት ያለውን ነበራዊ ሁኔታ በትክክል የማያንጸባርቁና ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። የላዕላይ ተፋሰስ ሃገሮች የህዝብ ቁጥር፤ ከግብፅና ከሱዳን ህዝብ እንደሚልቅ የሚታወቅ ሲሆን፤ በገዛ ምድራቸው ፈልቆ የሚፈሰስውን ውሃ፤ ለመጠጥና ለመጸዳጃ፤ለመስኖና ለሃይል ልማት፤ ለአሣና ለደን ልማት መጠቀም አትችሉም ብሎ መከራከር አግባብነትና ተቀባይነት የሌለው ነው።

ለህዝባቸው ህልውናና እድገት በገዛ ምድራቸው ፈልቆ በምድራቸው የሚፈስሰውን ውሃ መጠቀም ሁለተኛ የሌለው ቀዳሚ ምርጫ ነው። የታችኛው ተፋሰስ ሃገሮች ህዝባቸው በጠኔ፤ በሃይል እጦትና በመሰረተ ልማት እየተቸገሩ በሚገኙባቸው የውሃው አመንጭ ሃገሮች ላይ፤ እነርሱን ባልጨመረና ባላካተተ የቅኝ ግዛት ውሎች ‘አንዲት ጭልፋ ውሃ ካለኛ ፈቃድና እውቅና ንክች አታደርግዋትም’  ማለት ፍርደ- ገምድልነት ነው።

የህዝባቸው ቁጥር በአስደንጋጭ ሁኔታ እየጨመረ የመጣባቸው የላእላይ ተፈሰስ ሃገሮች፤ ውሃ ለተለያዩ የቀን ተቀን ግልጋሎትና ለታናናሽ፤ መካከለኛና ታላላቅ መሰረተ ልማት መጠቀም ግድ ብሎአቸዋል። ከእነዚህ ግንባር ቀደም የችግሩ ሰለባ የናይል ውሃ 85% የምታበረክተውና በዚህ ወቅት ወደ 110 ሚልየን ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ናት።

ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከመሆኗ በተጨማሪ ህዝቦችዋ በተደጋጋሚ አሰቃቂ ድርቅ የሚሰቃዩባትና የእህል እጥረት የሚገጥማት አገር ናት። ድርቁ በተፈጥሮ ይሁን በሰው ሰራሽ መንገድ በተወሰኑ ዓመታት በተከታታይ የሚከሰት ከመሆኑ ባሻገር፤ በሌላም ጊዜ ህዝቦችዋን ሊመግብና ሊቀልብ የሚችል በቂ የእህል ሰብልማምረት የማትችል አገር ናት። ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት በአብዛኛው በክረምት በጥቂት ውስን ቀናት የሚጥለው የትሮፒካል ብርቱ አጣዳፊ ዝናብ (Run Off Water)፤ ተዳፋቱ በበዛበት ደጋማ ምድር ወደ ከርሷ ምድሯ በሚገባ ሳይሰርጽና ለመስኖና ለሃይል፤ ለአሣና ለደን ልማት ገድባ ሳትጠቀምበት፤ ለግብፅና ለሱዳን ሲሳይ ይሆን ዘንድ እያንዳንዱ ገባር ወንዝ ተሰባስቦና ተጠራቅሞ ጥቁር አባይን ፈጥሮ ያለ ቅሪት ስለሚነጉድ ነው።

ተወደደም ተጠላ የኢትዮጵያ ህልውና፤የልማቷና የእድገቷ አምድና መሰረቱ ውሃዋ ነው። ውሃ ለሁሉም ሰዎችና አገሮች ወሳኝ መሆኑ ባያጠያይቅም ምጥኔ ሃብቷ በዋናነት ግብርና ላይ መሰረት ባደረገች አገር የውሃ አስፈላጊነት የላቀ ነው። ኢትዮጵያ ለወደፊቱ ከግብርናእንዱሰቱሪ መርወደ ሆነ ልማት በምታደርገው ሽግግርም ውሆችዋን ገድባ ለመስኖና ለሃይል፤ እንዲሁም በራሷ የምርት ውጤቶቿን ዋጋ ጨምራ ለገዛ ህዝቧ በኢንዱስቱሩ ያለፉ ምርቶች (Industrail Processed Products) ለማቅረብና የውጭ ምንዛሪ ለማሰገኘት ወደ ውጭው ዓለም የእንዱስቱሪ ምርቶች መላክ ይኖርበታል። ለእነዚህና ተመሳሳይና ተጓዳኝ ለሆኑት ልማቶችና ግልጋሎቶች ውሃ ግንባር ቀደም ተዋናይ ነው። ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ ከግብፅ ለሚነሳ ተግዳሮት ዋና ተፋላሚ ሆና መታየቷ የሚያስገርም አይደለም።

Videos From Around The World

ምንም እንኳን ሌሎቹ የላእላይ ተፋሰስ ሃገሮች ተደምረው የኢትዮጵያ ያክል የውሃ መጠን ወደ ታችኞቹ ሃገራት ባያበረክቱና የህዝባቸው ቁጥር ከኢትዮጵያ ህዝብ ባይተካከልም፤ ውሆቻቸው ለተለያዩ መርሃ ግብሮች የመጠቀም መብታቸው ግን የተጠበቀ ነው። በመሆኑም በስምንቱ የላእላይ ተፋሰስ ሃገሮች መካከል የናይል ተፋሰስተነሳሽነት (The Nile Basin Initiative) በሚል ርእስ  በ1999 የጋራ ምክክር ተጀመሯል። ከበርካታ ተከታታይ ውይይት በኋላ ኢትዮጵያን ጨምሮ ፤ አራት ሃገሮች ናይልን ለማልማት ተስማምተው በፊርማቸው ያጸደቁት ሲሆን፤ ሁለቱ ለጊዜው ይፈርማሉ ተብለው እየተጠበቁ ነው። በዚህ ውይይት የታህታይ የተፋሰስ ሃገሮች ማለትም ግብፅና ሱዳን ተሳታፊ ሆነው ቢቀርቡም፤ ስምምነቱ እንዳይጸድቅ ልዩ ልዩ እንቅፋቶችን መደቀናቸው አልቀረም። ይሁንና “የብቻየና ለብቻየ”በማለት ስትንጠራራ የነበረችው ግብፅ ወደዚህ ጉባኤ ሳትወድ በግድ ተገፍታ መግባቷ አንድ ትልቅ ድልና እመርታ ነው። ግብጽ የሙጥኝ ብላ ተንጠላጥላበት የነበረው የቅኝ ገዠዎች ውል አከርካሪው ተመቶባት ወደዚህ ወደማትፈልገው ጉባኤ እንደ እባብ እየተሳበች ብትገባም፤ አሁንም የቕኝ ግዛቱ አባዜዋ ሙሉ በሙሉ እርግፍ አድርጋ እንዳልተወች በሚድረጉት ስብሰባዎችና ድርድሮች በግልጽ የሚስተዋል ነው።

በተፋሰሱ ሃገራት በታዛቢነት ያለችው ኤርትራን ሳይጨምር በቁጥር አሥር ሲሆኑ ግብጽና ሱዳን ተቃውሟል። ከላይኛው ተፋሰስአራት አገሮች ምንም እንኳ በውሉቢስማሙበትምበፍርማቸው ስላላጸደቁት፤ አራት ለስድስት በሆነ ውጤት ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ህጋዊና ተግባራዊ ሊሆን አልቻለም። በዚህ ቡድን የሚሳተፉ አገሮች ቡሪንዲ፤ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፤ ኢትዮጵያ፤ ኬንያ ርዋንዳ ዳቡብ ሱዳን ታንዛንያ ዩጋንዳናየታችኛ ተፋሰስ ሃገሮቹ ግብጽና ሱዳን ናቸው። በዚህ ቡድን ኤርትራ እንደ ታዛቢ ሆና ቀርባለች። ይህ የናይል ተፋሰስ ቡድን የተቋቋመው በ 22 Feb 1999 በዩጋንዳ ርእስ ከተማ በካምፓላ ነበር።

ከተፋሰሱ ሃገራት ካልፈረሙት አራት አገሮች ሦስቱ ውሉን ቢፈርሙበት 7 ለ 3 በሆነ ድምጽ ስለሚያሸንፉ ወሉ ዓለም አቀፋዊ እውቅና ተችሮት ህጋዊ ሰውነት ያገኝና ግብፆች ዝም ሊያሰኝ የሚያስችል ነው። በዚህ ዘርፍ ኢትዮጵያ ሦስቱን ወይም አራቱን አገሮች አሳምና ለማስፈረም ያላሰለሰ ዴፕሎማስዊ ጥረት ማካሄድ ይኖርበታል።ይህ በእንዲህ እያለ የኢትዮጵያውጠቅላይ ሚንስቴር አቶ መለስ ዜናዊ በ2011 ኢትዮጵያ በራሷ ወጪና በህዝቧ ትብብር ታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደምትሰራ የሚያሰችለውን የመሠረት ድንጋይ ለሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትር በሚርቅ በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ጥሏል። ይህ ድርጊት የኢትዮጵያዊያን ወኔ ከጫፍ እስከ ጫፍ የቀሰቀሰና አንድነቱን የገለጸበት ነበር። ህዝቡም በታላቅ ተነሳሽነት ቦንድ እየገዛና ልዩ ልዩ መዋጮችን በማድረግ በከፍተኛ ጉጉትና ስሜት ይሳተፍ ነበር።

በዚህ ወቅት ግብጽ በከፍተኛ ነውጥ የነበረች ስትሆንበእስላም ወንድማማች ህብረት በወቅቱ የግብጽ መራሄ መንግስት በነበሩት ሙሐመድ ሙርሲ ካብኔ ኢትዮጵያ ላይ ማድረግ የሚኖርባቸውን ክፉ ሁሉ የተመካከሩበት ቪድዮ ታይቷል። ጀነራል አልሲሲበምርጫ ሳይሆን በጉልበት በስልጣን ኮሬቻ ከተፈናጠጡ በኋላ፤ ዋና ትኩረታቸው በአባይ ላይ አደረጉ። ግብፆች ኢትዮጵያን ጦርነት አውጀው ፊት ለፊት ባይዋጉም ሃገሪቱ እንድትፈራርስና እንድትዳከም ያልፈነቀሉት ድንጋይ ከቶ አልነበረም። በዚህ ሥራ ግብጽ ትጠቀምባቸው ከነበሩት አንዷና ዋናዋ ኤርትራ ስትሆን፤ በወቅቱ ኢህአዴግን ተቃዉመው ይፋለሙ የነበሩና በአሥመራ ይንቀሳቀሱ የነበሩ ኢትዮጵያዊያን ፓርቲዎች በግብፅ ድጋፍ ይደረግላቸው እንደ ነበር ይነገራል። የሚገርመው በሰላ ብርአቸው ከሚታወቁት ትውልደ ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊያን ከሆኑት ምሁራን ሽንጣቸውን ታጥቀው በገሃድ የህዳሴው ግድብ መገንባት ይቃወሙ ከነበሩት አሁንግድቡ አካባቢ ከወቅቱ የሃገሪቱ መሪ ሲጎበኙ ማየት ነው። ከዚህ በተቃራኒ በዓለም አቀፉ መድረክ ሁሉንም ልቀውና በልጠው አሳማኝ ምልከታ ያቀርቡ የነበሩት መለስ ዜናዊ፤ የመሰረቱን ድንጋይ ደፍረውከጣሉ በኋላ በዲፕሎማሲው ድል ይነሱ ስለ ነበሩ፤ ግብፆችበሬዲዮአክቲቭጨረርበስብሰባ ላይ በነበሩበት ወቀት እንደበከልዋቸው ይታማል።

ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ የጠቅላይ ሚንስተርነቱን ቦታ የተኩት አቶ ሃይለ-ማርያም ደሳለኝ ሲሆኑ፤ የግብጾች የአባይ ትኩሳት ወይም ግለት በርትቶባቸውና ጠንክሮባቸው ነበር። ግብፅ ዋና ስልት አድርጋ የያዘችው የህዳሴው ግድብ እንዲጓተትና፤ ለዚህም በተራዘመ አሰልቺ ስብሰባ ማንቀርፈፍና ከተቻለም በሃገሪቱ ህዝብ ከህዝብ ጋር ተለያይቶ እንዲጋጭና እንዲቆራቆስ በማድረግ አገሪቱን መበታተንና መበጠበጥ ነበር። ግብፆች እነዚህን ሁለት ስልቶች ጎን ለጎን በማስኬድና በርካታ ምውአለ ንዋይ ለተቃዋሚ ድርጅቶችና ታዋቂ ፖለቲከኞች በመስጠትና በማፍሰስ ብዙ ስረታበታለች፤ እየሰራችበትም ነው። የሚያረካ ውጤትም እይታበታለች።

ይህ በእንዲህ እያለ፤ በ 2015በግብፅበኢትዮጵያና በሱዳን መካከል በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ “የመርህ መግለጫ” (Princeples Of Declaration) ውል ተካሄደዋል። የመርህ መግለጫው በኢትዮጵያ፤ በግብጽና በሱደን መካከል በ 23 ማርች 2015 በካርቱም የተካሄደ ሲሆን ለአራት አመታት በሃገራቱ መካከል ስፍኖ የነበረው ውጥረት ጋብ እንዲልያደረገና ያስተነፈሰ ነበር። የመርህ መግለጫው ከአሥሩ የተፋሰሱ ሃገራት ቡድን ፈንጠር ብሎ በሦስቱ አገሮችመካከል የተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያና የግብጽ ፍጥጫ ለጊዜውም ቢሆን ረገብ እንዲል አድርጓል። መርሁ፤ አሥር አንቀጾችን ያቀፈ ሲሆን፤ በሃገራቱ የቴክኒክ ቡድኖች ውይይትና ድርድር እልባት እንዲያገኝና፤ ከዚህ አልፎ ስምምነት ላይ ካልተደረሰበመጨረሻው አንቀጽ ማለትም አንቀጽ አሥር በመራሄ መንግስታቱ የፓለቲካ ውሳኔና በሌሎች አደራዳሪነት መፍትሄ ለማግኘት የወጣ ነው።

ግብፅን “የብቻየና ለብቻየ” ከምትለው ጽኑ ምሽጓ አውጥቶ፤ ከኢትዮጵያ ጋር ለመደራደር ዝቅ ማለቷ አንድ እመርታ ቢሆንም፤ ውሉ በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለው አሉታዊ ተጽእኖ እንዳለ፤ አሁን ጉልህ ሆኖ እየታየ መጥቷል። ግብጾች አቋማቸውን በየስብሰባው በመቀያየር የውሃው ሙሌት እንዲጓተትና፤ በተሰጣቸው ጊዜ ኢትዮጵያን ለማመስና ለመበታተን የተጠቀሙበት ስልት ሲሆን፤ በተፈጠረው የፖለቲካ ስልጣንና የመንግሥት ለውጥ ሳቢያ ኳስዋን በኢትዮጵያ ሜዳ ላይ እያንከባለሉ ለመጫወት አስችሎአቸዋል። ኢትዮጵያ ዘጠኙ የላእላይ ተፋሰስ ሃገሮች ያቀፈው የናይል ተፋሰስ ኢኒሼቲቭ (Nile Basin Initiative) ፈንጠር ብላ ከግብፅና ከሱዳን  ጋር  በፕሪንስፕልስ ኦፍ ዲከላሬሽን ( Principles Of  Declaration) መጠመዷ ትክክለኛ አልነበረም።

የግድቡ ዋና መሐንዲስ የኢንጅነር ስመኘው በቀለ መገደል ለኢትዮጵያ ህዝብ እንቆቅልሽ ሲሆን፤ በህዝቡ ላይ መደናገጥንና መደናገርን ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም የጠ/ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ “ግድቡ ከአሥር ዓመት በኋላ እንኳን አያልቅም” የሚል ዜና ህዝቡን ግራ ያጋባ ከመሆኑ ባሻገር፤ በግድቡ ዙሪያ የተሰሩት ዶክሜንቴሪዎችና መግለጫዎች፤ ግብፆችን እፎይ ያሰኘና የኢትዮጵያህዝብአንገቱ እንዲደፋያደረገ ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካይሮ ሄደው በነበሩበት ጊዜ የግብጽ መራሄ መንግሥት አባይን አስመልክቶ “እንዳትጎዱን ማልልኝ” ብልው አጥብቀው የጠየቅዋቸው ጊዜ “ወላሂ አንጎዳችሁም” ብለው በበአድ ሃገር ቋንቋ መማላቸው ከዴፐሎማሲ አንጻርተገቢ ካለመሆኑ ባሻገር፤ ብዙ ኢትዮጵያዊያንእንዲጠራጠርዋቸውና አሜኔታ እንዳይጥሉባቸው አድርጓል። ኢትዮጵያ የውሃ ፀጋዎችዋና ሃብቷ የምትጠቀመው ግብፅን ለመጉዳት ሆነ ብላ አስባበት ሳይሆን፤ ለህልዋናና ለእድገቷ ውሃዎችዋን ለልዩ ልዩ ልማቶች መጠቀም ተከታይ የሌለው የመጀመሪያ ምርጫ ስለሆነባት ነው።

የህዳሴው ግድብ 6 ሺህ ሜጋ-ዋት ሃይል ከማመንጨት አቅም በ1300ሜጋ-ዋት ቁልቁል ተንከባሎ መውረዱ የሚያጠያይቅ አድርጎታል። መንግሥት ይህ ያክል የሃይል መጠን ያለ በቂ ምክንያተ እንዲቀንስ ምን እንዳስገደደው ለህዝቡ በመገናኛ ብዙሃኑ ያልገለጸ ከመሆኑ በተጨማሪ፤ በድርድሩ የሚደረጉ ውይይቶችና ውጤታቸው በወቅቱ ለህዘቡ ይፋ ያለመድረጉምግራ አጋቢ ትእይንት ነው።

ለመሆኑ በሦሰቱም መንግስታት ጠ/ሚነስቴሮች መሪነት በ2015 የተካሄደው ‘Principle of Declaration’ የተባለው ሰነድ ለኢትዮጵያ ፋይዳ ነበረው ወይ? ለጊዜው ከነበረው ፍጥጫ እፎይታ የሰጠ ቢሆንም፤ ግብፆች ጊዜ ለመሸመትና ኢትዮጵያን ለማዘናጋት አስበውና አሰላስለው ያደርጉት ስልት ነው የሚል እይታ ብዝዎች ይጋሩታል። የግብጽ የቴክኒክ ቡዱን ከአቻው የኢትዮጵያው የቴክኒክ ቡድን ሃሳቡን እየቃያየረ ለበርካታ ስብስባዎች የተቀመጠ ሲሆን፤ ይህ የግድቡ ሥራ በፍጥነት እንዳይሠራ ሆን ተብሎ ይደረግ የነበረ የብልጣ ብልጦች ደባ ነው። ግብፆች ጉዳዩ ከረዥም ጊዜ በፊትበቴክንክ ቡድኖቹ መካከል በሚደረግ አሰልቺና አታካች ውይይትና ድርድር እንደማያልቅና የመጨረሻ እልባት የሚገኘው በመራሄ መንግሥታቱ የፖለቲካ ውሳኔ እንደ ሆነ በመገንዘብና በማስላት፤ የኢትዮጵያ የውስጥ የፖለቲካ ነውጥና ሁከት በመንተራስ መሪዎቹን በዚህም በዚያም አዋክበውና ደልለው የሚፈልጉት ነገር እንደሚያገኙ ዲክላሬሽኑ ከመውጣቱ ቀድመው በማሰብ (by design) ያወጡት ነው። አሁን ያለንበት ደረጃሁሉም ርቀቶች ተጉዘን ጉዳዩ በመጨረሻውና ውሳኙ አንቀጽ 10 አፋፍ ላይ ነን። ይህም በኢትዮጵያው የወቅቱ ጠ/ሚንስቴር እጅ ላይ ያለ  አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ጠ/ሚንስትሩ ካላቸው የፖለቲካና የኤኮኖሚ ጫናና አጣብቅኝ፤ በተጨማሪ ካየነው የአመራር፤ የአቋምና የባህሪ መዋዠቅ ተነስቶ የሃገሪቱ ልዓላዊነትና ጥቅም አሳልፈው ይስጣሉ የሚል ግምት በብዙዎች ዘንድ የሚገመት ሲሆን፤ ጊዜ እውነቱን ቁልጭ አድርጎ ከማሳየቱ በፊት ከባድ ማሰጠንቀቅያ አዘል ምክር አሁን ፀሐይቱ ከመጥለቅዋ በፊት ሊሰነዘርባቸው ይገባል። ክቡር ጠ/ሚነስቴር ታሪክ በዚህ ቀጭንና ፈታኝ ወቅት እርስዎን ባላደራ አድርጋ  ሾሟለችና፤ እናት ሃገራችንንና ምስኪን ህዝቧን በጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅምና ፋይዳ ተገፋፍተው ጎጂ ውሳኔ እንዳያሳልፉና እንዳይፈርሙ በአጽንኦት እንማጠንዎታለን!!

ከዚህ አንጻር ሲታይየዲክላራስዮን መርሁ ጣጣና መዘዝ አመጣብን እንጂ ምንም የፈየደው ነገር የለም።  ኢትዮጵያ የዓለም ባንክና የአሜሪካ መንግስት ግምጃ ቤት እንዲሁም ሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አይስፈልጉኝም ብላ የግድቡን ሥራ ማቀላጣፍ ይዛ እንደ ነበረችው ብትገፋበትና ከግብጽና ከሱዳን በ2015 የተዋዋለችው ሰንድ ቢቀር ይሻላት ነበር። ግብፅን ለአያሌ ዓመታት በቅኝ ገዠዎች በወጣ ውል ተነፈላስሳ ከነበረችበት አውድማ እወጥቶ ለድርድር ማቅረብ ትልቅ እመርታ ቢሆንም፤ አሁንም የኢትዮጵያን ጥቅም፤ ሉዓላዊነትዋን፤አንድነትዋን፤መረጋጋትዋንናሠላምዋን ለማወክና ለማናወጥ ባንድም በሌላ መንገድም ደፋ ቀና ከማለት አልቦዘነችም።

የሦስቱ ሃገሮች የቴክኒክ ቡድኖች ባደረግዋቸው ተካከታታይ በርካታ ስብሰባዎች አዳዲስ ሃሳቦች በመፈብረክና ስምምነት ተደርሶባቸው የነበሩትን በመቀልበስና በመለወጥ የግብፅ ቡድን ስምምነት ላይ እንዳይደረስ አድርጓል። ይህም ሆን ተብሎ በግብጽ መንግሥት የተጠነጠነ ማሰነካያ እንጂ ባጋጣሚ እንዲሁ የሆነ አይደለም። ግብፆቹ በውይይቱ መካከል የቅኝ ገዥዎቹን ያለፉት ውሎች እያነሱ ቡራ ከረዩ ማለታቸው እንደገፉበትተሰምቷል። ኢትዮጵያ በፕሪንስፕልስ ኦፍ ዲክላሬሽን ውሉ አጥብቃ ማንሳትና አበክራ ከዚህ ውል በኋላ ግብፅና ሱዳን የቅኝ ግዛቱ ውል ባዶና የማይሠራ (Void & Ineffective) መሆኑ አስረግጣ ማሰሰብና ማሰፈረምነበረባት። ይህ ስላልተደረገና በውሉ ሌሎች ቡድኖች ታዛቢ፤ አደራዳሪ፤ የስምምነት ሃሳብ አቅራቢና አፍላቂ ሆነው እንዲሳተፉአድርጎ ለማቅረብ መስማማት ኢትዮጵያን የሚጠቅም ከቶ አልነበረም። በርካታ ስመ-ጥር የውሃና የኤነርጂ ምሁራንና ባለሞያተኞች በ 2015  ኢትዮጵያ ከግብፅና ከሱዳን ያደረገችው ባለ አሥር አንቀፅ ውል ጉዳት እንዳለው ቢያሳስቡም በፖለቲከኞቹ ጀሮ ተሰሚነት አላገኘም ነበር።

ከዚህ በተጓዳኝ ሦስቱም የተፈሰሱ ሃገራት ስለ ሥራው አጠቃላይ ሂደትና የግንባታው ጥራትና አሰተማማኝነት እንዲያጠኑ የታወቁ ሁሉት ዓለም አቀፍ ኤክስፐርት ተቋሞች ቀጥረው እንዲሠሩ ተስማምተው፤ ግብፅየኤክስፐርት ተቋሞቹ በተጠበቀወ ፍጥነት እየሠሩ አይደለም በማለት ኮንናለች። ግብፅ ስሞታወን ለማቅረብ የፈለገችው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በፍጥነት ተካሄዶ ካለቀ ችግር ይፈጥርብኛል ብላ በማሰብ ነበር።

 

የኢትዮጵያ የውሃ ሃብት መጠንናወሰን ተሻጋሪ ወንዞቿ

ኢትዮጵያ በውሃ ጸጋዋ በጣም የታደለችና፤ መጠነ ሰፊ ውሃ የሚፈስባት በውሃ ሃብት የተመነሸነሽች ሃገር ናት። የሃገሪቱ የምድር ገጽ የውሃ መጠን ማራኪ ቢሆንም ጥቅም ላይ ግን አልዋለም። ሃገሪቱ 12 አበይት ወንዞች ያሏት ስትሆን፤ በአራት የተለያዩ እቅጣጫዎች ድንበር ዘልለው የሚፈሱ ናቸው። አጠቃላይ የገፀ- ምድር የውሃ መጠን 120 ብልየን ከይብ ሜትር በዓመት ሲሆን፤ የከርሰ ምድር የውሃ መጠን 20 ብልየን ኩይብ ሜትር ይሆናል ተብሎ ይታሰባል።

ጥቁር ናይል ተብሎ የሚጠራው አባይ፤ ባሮ-አኮቦ፤ ሰቲት-ተከዘ/አትባራ እና መረብ የሚያካትት ሲሆን የሃገሪቱ 33% የቆዻ ስፋት የሚሸፍን ነው። የአባይ ተፋሰስ ከሃገሪቱሰሜንና ምእራብእንዲሁምመካከለኛ ስፍራዎች በመነሣት ወደ ምዕራብ እቅጣጫ በመፈሰስ ወደ ደቡብ ሱዳንና ወደ ሱዳን አቅንቶ ወደ ግብፅ የሚፈስስ ነው። ባሮ-አከቦ ወደ ደቡብ ሱዳን በመፈሰስ ከነጭ አባይ ጋር የሚቀላቀል ሲሆን፤ የሃገሩ ልጅ ከሆነው ከናይል 85% ድረሻ ካለው ከጥቁር አባይ የሚቀላቀለው ካርቱም ላይ ከነጭ አባይ ጋር ደቡበ ሱዳን  ላይ በመቀላቀል ነው። ሰቲት-ተከዘ/አትባራ ጥቁርና ነጭ አባይ ካርቱም ላይ ከተገናኙ በኋላ ወደ ሰሜን አቅንተው ወደ ግብፅ ከመግባታቸው በፊት አትባራ በተባለች ከተማ ይቀላቀላሉ።

ወደ ሱዳን የሚፈሰው የውሃ መጠንበዓመት 64.6ብልዮን ሜትር ኩይብ ሲሆን፤ ከጥቁር አባይና ከገባሮቹ 52.6ብልየን ሜትር ኩይብ፤ ከአትባራ 4.37 ብልየን ሜትር ኩይብ በዓመት፤ ከሰቲትና ተከዘ 7.63ብልየን ሜትር ኩይብ በዓመት ናቸው። 13 ብልየንሜትር ኩይብ ውሃ በዓመትከባሮና አኮቦ ማለትም ሶባትከምዕራብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ ሱዳን በመፍሰስ ወደ ነጭ አባይ ይቀላቀላል።

 

የስምጥ ሸሎቆው ተፋሰስ አዋሽ፤ ደናክል፤ ኦሞ-ግቤና የማህል ሃይቆች የሚያጠቃልል ሲሆን የሃገሪቱ 28% የቆዳ ስፋት የሚሸፍን ነው። ተፋሰሱበዓመት 8.2 ብልየን ሜትር ኩይብ ወደ ሶማልያ የሚፈስስ ሲሆንበጋራ ጁባ ተብለው ከሚጠሩት ከገናሌናከዳዋ ወንዞች 5.9ብልየን ሜትር ኩይብ፤ ከዋቢ-ሸበሌ ወንዝ በዓመት 2. 3ብልየን ሜትር ኩይብ ውሃ ወደ ሶማልያ ይፈስሳል። ኦሞ ወንዝም በዓመት 10 ብልየን ኩብ ሜትር ውሃ ይዞቱረካና ወደተባለ በኬንያ ወደሚገኝ ሃይቅ ይቀላቀላል። ከዚህ በተጨማሪም በዓመት 0.7ብልየን ኩብ ሜትርውሃ ወደ ኤርትራ ይፈስሳል::

ካለአባይ ተፋሰስ ወንዞች ሁሉም ወንዞች በበጋ የውሃ እጥረት የሚያጋጥማቸው ናቸው (EU, 2011)። በኢትዮጵያ የሚገኙ ወንዞች አብዛኛዎቹ ወቅታዊ ሲሆኑ ከ1500 ሜትር ከፍታ በታች የሚፈስሱት በክረምት ብቻ ናቸው፡፡ ከወንዞቹ 70% ጎርፍ አዘል (Runoff) ሲሆኑ፤ ከሰኔ እስከ መሰከረም በሚጥለው ዝናብ ምክንያት የሚፈስሱ ናቸው። በደረቅ ወራት የሚፈሱስት ወንዞችና ጅረቶች ከምንጮች የሚፈልቁ ሲሆኑ ለዝቅተኛ የመስኖ ልማት ለመዋል አመቺ ናቸው።

ከፍተኛ የትነትነት ብክነት(Loss to evaporation) ስለሚያጋጥማቸው አንዳንዶቹ ወንዞች ድንባር ሳይሻገሩ የሚደርቁ ናቸው። ለምሣሌ በስምጥ ሸለቆ የሚያልፈው ኦሞ- ግቤ  በዓመት ከሚፈሰው 17.9ብልየን ኩዩብ ሜትር ኬንያ ድንበር ላይ የሚደርሰው 10 ብልየን ሜትር ኩይብ ብቻ ነው። የአባይ ተፋሰስ ከሆነው በዓመት 23. 6  ሚልዮን ሜትር ኩይብ ከሚፈሰበት ከባሮ- አኮቦ ደቡብ ሱዳን ድንበር የሚደረሰው 13 ብልየን ሜ/ኩዩብ ነው።አንዳንዴ የሚጥለው ከባድ ዝናብ በተለይም በአዋሽ ወንዝናበዝቅተኛው ባሮ- አከቦ የበቀሉ እህሎችና መሰረተ- ልማቶች አደጋ የሚያስከትል ነው።

ኢትዮጵያ 11 ንፁሕ ሃይቆች፤ 9 ጨዋማ ሃይቆችና 4 በእሳተ- ጎሞራ የተፈጠሩ(Crater) ሃይቆች አሏት። ከዚህ በተጨማሪም በምድሯ12 ዋና ዋና እርጥብ አዘል ከባቢዎች (Wetland regions) አሉ። የአባይ ምንጭ ከሆነው ከጣና ሃይቅ ውጭ ሁሉም ሃይቆች የሚገኙት በስምጥ ሸለቆ ነው። አብዛኞቹ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆች መውጫ የሌላቸው የተዘጉ ሃይቆች ናቸው። ስለሆነም ብዙዎቹ በጣም ጨዋማ (Saline) ናቸው። ላንጋኖ፤ አባያና ጫሞ ንጹሕ ቢሆኑም፤ ወደ ውጭ ስለማይፈስሱና ስለማይተነፍሱጨዋማነታቸው እለት እለት በመጨመር ላይ ነው። አብዛኛዎቹ ሃይቆች አሣ የሚኖርባቸው ናቸው። የሻላና አብያታ ሃይቆች የታጨቀ የከሚካል ክምችት በተፈጥሮ የታደሉ ከመሆናቸው በተጨማሪ ሶዲየም ካርቦኔት (Sodium Carbonate) አላቸው (IWMI, 2007)።

አጠቃላይ የኢትዮጵያ እርጥብ መሬት ስፋት ከ 1.4 እስከ 1.8 ሚልየን ሄክታር ይሆናል ተብሎ ይገመታል፤ ቀሪው ደረቅ ቆላማ ስፍራ ነው (EPA, 2003; IUCN, 20100):: የኢትዮጵያ የከርስ-ምድር የውሃ እቁር መጠን በውል ባይታወቅም መጠነ-ሰፊጸጋ እንዳለ ይታመናል። ከዚህ ውስጥ በልማት ላይ የዋለው እጅግ አንስተኛ ነው። የጉድጓድ ውሃ በባህላዊ መንገድ በአንዳንድ ጣቢያዎች የሚለማ ሲሆን፤ በአርብቶ አደሮቹ ዘንድ ጠቀሜታው ጎላ ብሎ የሚታይ ነው። የምድር-ገጽ የውሃ መጠንበዓመት 120 ብልየን ሜ/ኩይብ  ሲሆን፤ በክርሰ-ምድርና በገፀ-ምድር የሚኖረው የውሃ መጠን በ20 ብልየን ኩ/ሜትር የሚፈራረቅ ነው። ከሃገሪቱ ለቆ የሚወጣው ጠቅላላ የውሃ  መጠን 96. 5ብልየን ኩብክ ሜትር በዓመት ነው።

ኢትዮጵያለኤሌክትሪክ፤ለመስኖና ለመጠጥ አገልግሎት የሚውሉ በርካታ ዝቅተኛ፤ መካከለኛና ከፍተኛ ግድቦች አሏት። በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ 12 የውሃ የሃይል ማመንጫ ጣብያዎች ያሏት ሲሆን፤ ከእነዚህም በድምር 1945 ሜጋ-ዋት ሃይል ይመነጫል (ODI, 2015)። ዝቅተኛ ግድብ ተብሎየሚመደበው ከ 0.15 ሚልየን ኩ/ሜትር በታች የሚይዝ  ሲሆን፤ ለመስኖ ልማት በ1999 እና 2000 በትግራይናበአማራ ክልሎች በርካታ አንስተኛ ግድቦች ተገንብቷል።በ 2008  አጠቃላይ የሃገሪቱ ግድብ መጠን 6.5ብልዮን ኩ/ሜትር ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፤ በቅርብ ጊዜ ግን ወደ 31. 5ብልየን ሜትር ኩይብ ከፍ እንዳለ ይታመናል። አዲሱ የተከዘ ግድብ በ2009 የተገነባ ሲሆን ፤ ውሃ የመቋጠር አቅሙ 9ብልየን ኩ/ ሜትር ሲሆን በጣልያን ከተሰራው ከቆቃ ግድብ በእጅጉ የሚበልጥ ነው፤ የቆቃ ግድብ ውሃ የመያዝ አቅሙ 1. 9ብልየንኩ/ ሜትር ነው። አዲሱ ሦስተኛው የግልገል ጊቤ ግድብ 14 ብልየን ኩ/ ሜትር መያዝ የሚችል ሲሆን፤ በ 2015 ግንባታው ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

አወዛጋቢው ታላቁ የህዳሴ ግድብ (GERD) ግንባታው በ2011 የተጀመረ ሲሆን በሱዳን ድንበር አካባቢ በዋናነት ለሃይል ማመንጫነት የሚውል ነው። ይዘቱ 74ብልየን ኩ/ ሜትር ሲሆን ሥራው 70% ተጠናቋል። ግድቡ ከተጠናቀቀ ከ6000 ሜጋ ዋት ሃይል በላይ ያመነጫል ተብሎ ቢጠበቅም መንግስት በ1300 ሜጋ ዋት ዝቅ እንደሚል ይፏ አድርጓል። ውሃን ከጨው የመለያ አሰራር (Desalination) ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ሃገር ስለሆነች ሊተገበር የሚቻል አይደለም። የባከነ ውሃ መልሶ አጥሮቶ የመጠቀም ሥራ (Wastwater Treatment)  በሃገሪቱ በስፋት የተለመደ ባይሆንም፤ በአዲስ አባባና ባንዳንዶቹ ትልላቅ ከተሞች እየተካሄደ ነው። በርእስ ከተማዋ በአዲስ አበባ ሁለት የውሃ አሸንዳ (Sewarage) ያሉ ሲሆን እነዚህም በቃሊቲና በኮቶቤ የሚገኙ የባከነ ውሃ ማጣሪያዎች ብቻ ናቸው።

 የኤነርጂ መጠንና አጠቃቀም በኢትዮጵያ

ለአንድ ሃገር ህልውናና ብልፅግና ኤነርጂ የጀርባ አጥንት ነው። ከ 85% በላይ የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርና የሚተዳደር ስለሆነ፤ ለነዳጅ የሚጠቀመው ሃይል እንጨት ወይም ከሰል ነው። ኩበትም በአብዘኛው የገጠር ህዝብ ለሃይል ፍላጎት የሚውል ነው። እንጨትና ከሰል የደንና የእጽዋት ተዋጽኦ ስለሆኑ፤ በደኑና በእጽዋት ጥገኞች ናቸው። በኢትዮጵያ ከደን ሃፍቷ ከ90% በላይ የሚዉለው ለማገዶ ነው። ከዚህ ለሃገሪቱ ደን መመናመን ዋና ምክንያት ማገዶ እንደ ሆነ ለመረዳት አዳጋች አይደለም። በመሆኑም ኢትዮጵያ በባዮ-ማስ አጠቃቀም ዙሩያ ብዙ መስራት ይጠበቅባታል።

የኢትዮጵያ ሃይል አቅርቦት በባዮ-ማስ ላይ በአመዛኙ ጥገኛ ነው። የባዮማስ ምድጃ ብቃት (Efficiency) ድሮ 8% ብቻ ነበር። ይኽ ከ100 የአህያ ጭነት 92 ጭነት ያለጥቅም ባክኖ 8 ጭነት ብቻ ጥቅም ይውላል ማለት ነው። ይኽ እንዴት ዓይነት ኪሳራና ጉዳት እንደሚያደርስ ሊሰመርበት ይገባል። የድሮው የማዕድንና ኤነርጂ ሚ/ር መስሪያ ቤት በምድጃዎችና በምጣድ ዙሩያ 24% ኤነርጂ መቆጠብ የሚችሉ ምርጥ የተባለ የምጣድ ምድጃና፤ ላቀች የሚባል የከሰል ምድጃ ማቅረቡ ትልቅ እመርታ አሳይቷል። ምድጃዎቹ በሥራ በመዋላቸው ሳቢያ በርካታ ደን ከብርሰት/ከመጥፋት ታድጓል። አሁንም የኤነርጂ ብቃቱ ከፍ ለማድረግ ስፊ እድል ስላለ የሚመለከታቸው ባለሞያተኞች  ብቃቱን በሳይንሳዊ መንገድ  ከፍ ለማድረግና ለማሻሻልመጣር ይኖርባቸዋል።

ምጣድና ምድጃዎቹ በአብዛኛውቹ የሃገሪቱ ክፍሎች በሦሰት ጉልቻ ወይም በድንጋይ ክፍት በሆነ መልኩ የተሰሩ ስለ ሆኑ ብክነቱ ከፍተኛ ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ዝግ ምጣድና ምድጃ በደረቅ ጭቃ ስለሚሰራ የተሻለ ብቃት አለው። ይሁንና የምጣዱ ውፍረት፤ የምጣዱ ምድጃ ከፍታና ምን ያክል ነዳጅ በምን ያክል ኦክስጂን በሚል በሣይንሳዊ መንገድ ስለማይሰራ በክነቱ የጎላ ነው። ምርጥና ላቀች ይህን በቁጥር በማስገባት በሳይንሳዊ መንገድ የተፈበረኩ ስለሆኑ ብቃታቸው ላቅ ያለ ከመሆኑ በሻገር ደን ከመናመን የሚታደጉ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ነዳጁና ኦከስጅኑ በንንጽር (Fuel to Oxygen ratio) ከባህላዊው ምድጃና ምጣድ የበለጠ የተመጣጠነ ስለ ሆነ የሚያሰከትለው ጢስ ዝቅ ያለ ነው። የማብሰልና የመጋገር ሥራ በሴቶች ጫንቃ ላይ የተጣለ በመሆኑ በጢሱ ጠንቅ የበርካታ እናቶችና እህቶች ዓይን ጤናማ አይደለም። ከጤንነት አኳያም የተሻሻሉ የማገዶ ምድጆች የሚታይ ጥቅም አሳይቷል።

85% የኢትዮጵያ ህዝብ በግብርና የሚታደደር ከሆነ፤ አሁን የኢትዮጵያ አጠቃላይ የህዝብ ቁጥር 110 ሚለየን ነው ብለን ከወሰድን ጠቅላለ የማገዶ እንጨት፤ ከሰልና ኩበት ተጠቃሚ ቁጥር ወደ 90 ሚልየን የሚጠጋ ነው። አንድ ቤተሰብ አምስት ሰዎች ያቅፋል ብለን ብንወሰድ ጠቅላላ የባህላዊ ማገዶ ተጠቃሚ ቤተሰብ ቁጥር18 ሚልየን ይሆናል። በባህላዊ ምድጆችበዓመት 90 ሚለዮን ኪሎ ግራም እንጨት እንጠቀም ብለን ብናስብና በባህላዊ ምትክ ቆጣቢ ምድጃ ቢለወጥ፤ ለነዳጅ የሚወጣው ማገዶ በሦስት እጥፍ ይቀንስናወደ 30 ሚልዮን ኪሎ ግራም ማገዶ ዝቅ ይላል። በዓመት ደኑን ይበዘብዝና ያመነምን ከነበረው መጠን በ60 ሚልዮን ኪሎ-ግራም ይቀነሳል ማለት ነው።በ5 ዓመት ችግኝ ተክሎ ደኑን ከማዳን የበለጠ ቆጣቢ ምድጆች በማምረትና በማከፋፈል በአንድ ዓመት ሊገኝ የሚችል ስልት ነው።መንግሥት በደን ልማትና በአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ፖሊሲው የቆጣቢ የባዮ-ማስ ምድጆችና ምጣዶች ድረሻና ጥቅም ተገንዝቦ  ለማምረትና ለማሰራጨት ትኩረት ሊሰጠው የተገባ ነው።

አንድ ወቅትየትግራይ የደን የድርጊት ፕሮግራም (TFAP) ተብሎ በተሰየመ ጥናት ላይ ኤነርጂን በተመለከተ ከሌሎች 8 ዘርፎች (በብዛት የግብርና) እንዳጠና እድሉ አግኝቼ ነበር። ጥናቱ ከአላማጣ እስከ ቃፍታ ሁመራ የተወሰኑ ወረዳዎች የሚሸፍን ነበር። ከወረዳዎቹም ሁሉት ወይም ሦሰት ጣቢያዎች መርጦ በመውሰድ በየፊናችን አሰሳና አጠቃቀምንያየንና የዳሰስን ሲሆን፤ በመጨረሻ ከጣቢያው ከታወቁ እንስትና ተባእት ነዋሪዎች ጋር ስለ እያንዳንዱ ዘርፍ ያሉበት ሁኔታ፤ የሚከሰት ችግርና መፍትሄው ውይይት ይካሄድ ነበር። ገበሬዎቹ ስለ ደን፤ ስለ እንስሳትና ስለ እርሻ ስለ አዝርእትና ስለ ውሃና አፈር ጥበቃ ጥሩ እውቀት የነበራቸውና ያላቸው ሲሆኑ፤ ኤነርጂን በተመለከተ ሲጠየቁ ግን ለመመለስ የሚቸገሩና መፍትሄው ምንድ ነው ተብለው ሲጠየቁ “ኤሌክትሪክ አሰገቡልን” የሚል ግልጽና አጭር መልስ ያቀርቡ ነበር።ከውሃና ጤና ቀጥሎ ችግራቸው የማገዶ እንጨት እንደ ሆነ አምርረው ይናገሩና መፍትሄው ጋር ደርሶ ሊኖር የሚችል የሃይል አቅርቦት አማራጭ ለመጠቀም የሚያስችል እውቀት የላቸውም። እናቶችና እህቶች ዛሬ ዛሬ ለማገዶ የሚሆን እንጨትና ኩበት ለማግኘት ሲሄዱና ሲመጡ ከ8 ሰዓት በላይ እንደሚፈጅባቸው ይታወቃል። ባንዳንድ እንጨት በሚያጥርባቸው የትግራይ ከተሞች እንጨት እንደ እህል በሚዛን ሲሸጥም አይተናል። የእንጨት ዋጋ በኪሎ ግራም ካንድንድ የጥራ-ጥሬ እህል ዋጋ እንደሚበልጥም በጥናቱ ተስተውሏል።

የኤኔርጂ ጥቅምና የእጥረቱ ችግር አፈታት አረዳድ ችግር በገበሬዎቹ ብቻ የሚታይ ሳይሆን፤ ከጣብያ ጀምሮ እስከ ክልልና በፖሊሲ አውጭዎችና በህዝብ ምክር ቤትም ጭምር የማይታወቅ ውስጥን አድቅቆ የሚገድል ደዌ ነው። አንድ ወቅት በክልል የነበርን ባለሞያዎች ፕሮጀክት ቀርፀን በአንዱ ዞባ ፕሮፖዛል እንድናቀርብ በተጋበዝነው መሰረት፤ የቆጣቢ ምድጃ ጥቅምና ስርጭት በሚል አቅርቤ፤ የዞባው የወቅቱ አስተዳዳሪ “ይሄማየማድ ቤት ተራ ፕሮጀክት ነው” ብለው አጣጥለውታል። ይህ ከግንዛቤ ማነስና ነገሩን ከሳይንስ አንጻር የሚኖረው ፋይዳካለማወቅ የሚነሣ ነው። ስለዚህ መንግስት ለኤኔርጂ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ካልተንቀሳቀሰ አደጋው እየከፋ እንደሚሄድ ማወቅ ያስፈልጋል።

ለመሆኑ ተበታትኖ በግብርና ሙያ ለሚኖረው ህዝብ በኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ማድረግይቻል ይሆን ወይ? በድፍኑ አዋጭ እንዳልሆነ ጠቀስ አድርጌ በማለፍ፤ ሌሎች አማራጭ ሃይሎች መጠቀም ግድ የሚል ነው። በዋናነትም የገጠሩ ነዋሪ ለተወሰኑ አሰርት ዓመታት የባዮ-ማስ ተጠቃሚ ከመሆኑ አይወጣም። ታድያ መንግስትና ገብረ-ሰናይ ድርጅቶች (NGO) ቆጣቢ ምድጆችና የነዳጅ መጠቀሚያ እቃዎችን ብቃት ለማሻሻል የሚያደርጉት ጥረት መቀጠል ይኖርበታል።

የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ የሆነው የከተማው ህዝብ ከአጠቃላዩ ህዝብ በቁጥር ዝቅተኛ ሲሆን፤ ለቤት አገልግሎትና ለእንዱስቱሩ በቂ ሃይል አይቀርብለትም። ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ታሪፍ ከዓለም ዝቅተኛ ነው። ህዝቡ ዋጋውን የመክፍል አቅም ስለሌለው ሁል-ጊዜ በመንግሥት ድጎማ የሚንቀሳቀስ ነው። ይህም የመንግስት ምጣኔ ሃብታዊ አቅም እንዳይጠነክርየሚያደርግና መንግስት ለሌሎች አንገብጋቢ መሰረተ ልማቶች የሚሆን የፋይናንስ አቅም እንዳይኖረው የሚያደርግ ነው። ካለው የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ክፊያ አንጻር የመንግሥት አቅም እንዲጎለበትና ዜጋም በድጎማ ለጊዜው እየኖረ፤ ኢትዮጵያ የኤኮኖሚ አቅሟ እስኪፈረጥም ድረስ በውጭ ምንዛሪ በውድ ዋጋ ለጎሮቤቶችዋና አልፎም ለአውሮፓ ብትሸጥ በጎ ነው። ሁኔታዎች ባለመገናዘብ ዜጎችኤለክትሪክ ሳይቀርብልን፤ ይኸውና መንግሥት ለውጭ እየቸበቸው ነው ሊል ይችላል። መንግስት ግን በሚመለከታቸውተቋማት ለምን ለውጭ አቅርቦት እንደሚውል በግልፅ ለህዝቡ ማሰረዳትና መግለጽ ይገባዋል።

በዚህ ላይ የኤለክትሪክ ሃይል፤ ከዋናው ቋት (Grid) ጠልፎ ራቅ ላሉ ጥቂት የገጠር ቤተሶበች አገልግሎት ለመስጠት አዋጭ አይደለም። ሃገሪቱ ቀስ በቀስ ከግብርና ወደ ኢንዱስቱሪ መር ኤኮኖሚ ስትሸጋገር ራሱ በራሱ ያለ ጫና ከገጠርነት ወደ ከተማነት እየተለወጠ ሲመጣ ሊቀረፍ የሚችል ችግር ነው። በዚህ ወቅት የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትም እየሰፋ ይሄዳል። ገበሬው የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንዲሆን ታቅዶከቀየው አፈናቅሎና ያለፍላጎቱ ከሌሎች ጋር ጨምሮ ከተማ መስርት መባል ከቶ የለበትም። ገጠር እንዲከትም መንግሥት በፖሊሲው ስፍራ ሊሰጠው የሚገባ ከመሆኑ ባሻገር፤ ለዚህ ግብአት የሚውሉ መሰረተ ልማቶችም ማሳለጥ ይገባዋል። ይህ እስኪሆን ድረስ ግን ገጠሩ በአመዛኙ የባዮ-ማስ ተጠቃሚ መሆኑ የማይቀር ነው። በመሆኑም ለቆጣቢ ምድጆችና ምጣዶች ልዩ ስፍራ መስጠት ተገቢ መሆኑ ተሰምሮቦት በገጠር ለማቀዝቀዣ በተለይም ለክሊኒኮች መድሃኒት መያዣ ፍሪጆች፤በቅርብ ርቀት ከጉድጓድ ውሃ ለማውጣት ሶላረ ፓነል (Solar Panal) መጠቀም ያሻል። ነፋስ ባላቸው የገጠር አካባቢዎችም በመንግስት እገዛ የነፋስ ውሃ ማውጫና (Wind pump) ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የነፋስ ተርባይን (Wind Turbine) እንዲጠቀሙማድረግ አስፈላጊ ነው። ከእበት ባዮ ጋዝ መጠቀም አንዱ አማራጭ ሲሆን በአጠቃላይ የተቀናጀ የኤነርጂ  አጠቃቀም እንዲኖር ያስፈልጋል። እንግዲህ ኢትዮጵያ ዜጎችዋ ካሉበት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ሊወጡ የሚችሉት በዚህ መልኩ ሲሆን፤ ውሆቿ ለኤሌክትሪክ አገልግሎት ማዋል ግን ለምርጫ የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ከታዳሽ የሃይል ምንጮች አስተማማኙ ሃይድሮ ፓወር ሲሆን፤ መጠነ ሰፊ ሃይል ማመንጨት የሚችል ነው። በርቀት ተበታትነው ለመኖሩ የገጠር ጣቢያዎች፤ አሁን የፀሐይና የነፋስ ማመንጫ ሃይል (Solar Panals) ዋጋ በመቀነስ ላይ ስላለ መጠቀም ያስፈልጋል። ውሃ ለኤነርጂ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ልማቶች እንደሚውል ሁሉ፤ ኤኔርጅም ከውሃ ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የሃይል ምንጮች ስለሚገኝ ሁሉን አቀናጅቶ በአግባቡ እንዲሰሩ ማድረግ መንግሥት ይጠበ      

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጥቅምና የተጋረጠበት እንቅፋት

ታላቁ የህዳሴ ግድብ በቤንሻንጉልና ጉምዝ ክልል ወደ ሱድን ድንበር በ 20ኪ/ሜትር ርቀት በመገንባት ያለ ሲሆን፤ የመሰረት ድንጋዮ በጠ/ሚነሰተር መለስ ዜናዊ በ2011 ተጥሎና ተመርቆ የተከፈተ ነው። ግድቡ ያላንዳች የውጭ እርዳታና ብድር ኢትዮጵያዊያን በራሳቸው ገንዘብ የሚገነቡት ነው። የታላቁ ግድብ መጀመር ኢትዮጵያዊያን ዘንድ ልዮ ስሜት የፈጠረ ሲሆን፤ የመጭው የሃገሪቱ ተስፋ የተጣለበት ነበር። ግድቡ 155 ሜትር ከፍታ፤ 1.78 ኪ/ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ 74 ብልየን ከቢክ ሜትር ዉሃ የማቀብ አቅም ይኖሯል። ይህ ግድብ ከ 6 ሺህ ሜጋ-ዋት በላይ ሃይል የሚያመነጭ ሲሆን፤ በአፍሪካ ቀዳሚና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰባተኛ ነው። የግድቡ  ስፋት በንጽጽር ሦሦት የጣና ሃይቅ የሚያክል ሲሆን፤ ፈረንጆቹ ደግሞ Greater London ያክላል ይላሉ።

ግድቡ ሲጠናቀቅ በሃገሪቱ ያላው የሃይል እጥረት የሚቀርፍ ከመሆኑ ባሻገር፤ ለጎረቤት ሃገሮች ለገበያ በማቅረብ ዳጎስ ያለ የውጭ ምንዛሪ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በሦስቱም የተፋሰስ ሃገሮች የሚኖረው ዝምድናና መቀራረብም ያጠነክረዋል ተብሎ ይታሰባል። ከዚህ በተጨማሪ የህዳሴው ግድብ ለዘጎች ብዙ የሥራ እድል የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር፤ የአሣ ሃብት ልማትም ሊካሄድበት የሚችል ነው። ግድቡ ለሃይል ማመንጫ እንጂ ለመስኖና ለደን ልማት ስላይደለ በግብፅና በሱዳን ላይ የሚያሳድረው ስጋት ሊኖር አይችልም። የውሃ የሃይል ማመንጫ (Hydro Power) ተርባይኖችን አሽከርክሮ ሃይል እንዲፈጠር ካደረገ በኋላ የሚፈሰስ እንጂ  አግቶ የሚያሰቀረው ወሃ የለም።

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ከግብጹ የአስዋን ግድብ በትነትነት ከሚባክነው ውሃ በእጅጉ የተሻለ ነው። የአስዋን ግድብ ከሚይዘው የውሃ መጠን አንድ አምሥተኛው በትነትነት የሚባክን ሲሆን፤ የ55 ብልዮን ኩብክ ሜትር አንድ አምሰተኛ 11 ብልዮን ኩቢክ ሜትር መሆኑ ነው። ሌላውበክረምት ወራት ከኢትዮጵያ ደጋማና ተራራማ ምድር ደፍርሶ የሚጎርፈው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ተጣርቶ ስለሚፈስስ፤ የግብፅና የሱዳን ግድቦች ከደለል ሙሌት (Siltation) ይታደጋቸዋል። ሱዳኖች ብርቱ ጎርፍ በሚፈስበት ጊዜ በርካታ በጥቁር አባይ አጠገብ የሚኖሩ ጣብያዎች፤ ከተሞች፤ የመስኖ ልማቶቻቸው ይጥለቀለቁባቸው እንደ ነበሩና፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ መገንባት ሳቢያ በየዓመቱ ጉዳት የማያደርስ ተመጣጣኝ ውሃ እንዲኖራቸው በማድረግ ጣቃሚ ሚና ይጫወታል።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ አሁን ባለበት ስፍራ እንዲገደብ የተመረጠበት ምክንያት ባላውቅም፤ እንደ ስልት ኢትዮጵያ ሌላ አማራጭና ለሃይል ማመንጨ አመቺ ስፍራ ቢኖራት፤ ግድቡ ተርባይኖቹን አዙሮ ወደ ጎሮቤት ሃገር ከሚፈሰስ፤ ከሃይል አቅርቦቱ በብዙ እጥፍ በመስኖ ልማት መርሃ ግብር የእህል ምርት የሚገኝበትና በአካባቢውየኢንዱሰቱሩ ግብአት ማሳለጫ ማእከላት (Indstrail Products Processing Centers) ቢተከሉ ለህዝቡና ለሃገሪቱ ሊጠቅም ይችላል። የሆነ ሆኖ የህዳሴው ግድብ መገንባት ግብፆች ሆኑ ሱዳኖችበእጅጉ የሚጠቅማቸው እንጂ የሚጎዳቸው ከቶ አይደሉም።

በህዳሴው ግድብ ግንባታ የግብፅ ስጋት ማግኘት የሚገባኝና የሚያስፍልገኝ ውሃ አጣለሁ የሚል ነው። በእርግጥ ግብፅ ካሁን በፊት ያለ ማንም ተጫራችና ተካፋይ በቸሩ የ 1959 ውል ታገኘውና ትንበሸበሸው የነበረው 55 ብልየን ኩቢክ ሜትር አጣለሁ ብላ መንፈራገጧ ተፈጥሯዊ ነው። ዳሩ ግን በተለይም ኢትዮጵያ ከጓዳዋና ከምድሯ የሚፈስሰውን ውሃ ህዝቧ በራብ፤ በጥም፤ በድህነት አረንቋ ውስጥ ገብቶ የበይ ተመልካች ሆኖይኑር ብሎ መወሰን ፍረደ- ገምድልነት ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ ሲራብ፤ በጠኔ ሲመታና በኋላ ቀርነት አዙሩት ሲዋትት ግብፅ ምድር ላይ ፀሐይ ደምቃና ሙቃ፤እርሻ አፍርቶና አምርቶ አውድማም በርክቶ ነበር። ስንራብ ስንጠማናበድህነት አርጩሜ ስንገረፍ አይዞአችሁ ሊሉንሲገባ፤ በተቃራኒው አስዮው ይሉን ነበር። በኤኮኖሚ ጡንቻዋ የፈረጠመች እናት ኢትዮጵያን ይቅርና በጋህድ በህልማቸውም ዝርና ውልብ እንድትላቸው አይሹም።”የአህያ ሞት ለጅብ ሠርጉ ነው” እንዲሉ፤ የበለፀገች፤ ሠላምዋና አንድነቷ ተጠብቆ የጠነከረች ኢትዮጵያ ማየት ሳይሆን የደከመችና የሞተች ኢትዮጵያን ማየት ነው።

የኢትዮጵያ ማንሰራራትና ህዳሴ ጆሮአቸው ጭው የሚያደርግ፤የሚያሰደንግጣቸውና የሚያስደነብራቸው ቃጭል ነው። ታድያ በኢትዮጵያ አድማስ ከጫፍ እስከ ጫፍ ያስተገባ ድምጽ በጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ታወጀ፤ ግብጾች ዘንድም ዝምታና ጭርታ ሰፈነ። የማስፈራሪያና ማስጠንቀቂያ መልእክቶች ከግብፆች እንደ ናዳ ቢወርድም፤ ኢትዮጵያዊው የራብና የጤናረዥም ስቃይ የበዛበት አሟሟት ከምሞት፤ ለህዝቤ ጥቅምና ለሃገሬ ልዓላዊነት ግንባሬን ለአረር ሰጥቼ ባልፍ በአያሌው የበለጠ ነው ብሎ ጸንቶ ቆመ። ግብፆች ራሳቸውን በማረጋጋትና ትንፋሻቸውን ዋጥ በማድረግ ስልታቸውን በመቀየር በድርድር ጠሬጳዛ ዙሪያ ለመቀመጥ ፈቀዱ።

ግብፅ ስጋትዋን ሁሉ ጊዜ የምትገልፀው ከዚህ በፊት በነፍ ብቻዋን ያለ ተቀናቃኝ ታገኘው ከነበረው አንጻር ነው። ይህ የውሃ መጠን ግብፆች ምንጊዜም ከምናባቸው የሚጠፋ አይመስልም። ዳሩ ግን በምድር ላይ ያለው የናይል ተፋሰስ ሃገራት ሁኔታ ከግብፆች ህልም ጋር የሚጣጣም አይደለም። ውሃ ሁለ-ገብና ለሕይወት እጅግ ወሳኝ የሆነ የእግዚአብሔርስጦታ ነው። ለመጠጥ፤ ለመፀዳጃ፤ ለመስኖና ለሰብል ምርት፤ ለሃይል አቅርቦት፤ ለደን ልማት፤ ለአሣ ልማት፤ ለኢንዱሰቱሪ ማምረቻ እቃዎች ተፈላጊ ነው። ታድያ በተፈጥሮ ያገኙትን የውሃ ባለጠግነት ለእነዚህ ትግባሮች ማዋል አትችሉም ማለት እንዴት ይቻላል?ዓለም ለአያሌ ዓመታት ለሃይል የምትጠቀምበት የነዳጅ ድፍድፍ (Crud Oil) ጥንፍፍ ብሎ ሊያልቅ ከሠላሳ ዓመት በላይ እድሜ እንደማይኖረው አውቃ ፊቷን ወደ ሌሎች አማራጭ የሃይል ምንጮች እያዞረች ያለችበት ጊዜ ነው። ከእነዚህም አሰተማማኙ ከውሃ የሚፈልቀው ኤሌክትሪክ ነው። እናማ ውሃችን አትጠቀሙ እንዴት እንባላለን?

ግብጽ የአስዋን ግድቤ በ2% ከቀነሰ በግድቡ ተሰማረተው ካሉት ከ 1 ሚልዮን ሠራተኞች በላይ ሥራ ይፈታሉ ትላለች። የ55 ብልዮን ኩዩብ ሜትር ውሃ 2% 1. 1 ቢልየን ኩብክ ሜትር ነው። ኢትዮጵያ 1.1 ብልዮን ኩብ/ሜትር ለመሰኖና ለሃይል ብትጠቀም ከ 10 እስከ 20 ሚልየን ለሚደርሱ ዜጎቿ የምግብ አቅርቦት ሽፍና ለበርካታዎቹም የሥራ እድል ሊፈጥረላቸው ይችላል ። ግብፅ በታላቁ የህዳሴ ግድብ አመካኝታ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያንየውሃ ፀጋ ለመቆጣጠር የሚከጅላት ሲሆን፤ ይህ ተወደደም የማይነካና የማይደፈርየኢትዮጵያ ጥቅመና ልዓላዊነት የሚገዳደር ነው። በመሆኑም የቴክኒክ ቡድኑ ይሁኑ የፖለቲካው ባለስልጣኖች ይህን ጉዳይ በምንም ትአምር ለድርድር ሊያቀርቡት አይገባቸውም። በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልተኝትና ንዝህላልነትምንም ስፍራ የላቸውም። የመጭው ኢትዮጵያዊ እድል የሚያመክንና የሚያጨናጋፍ እርምጃ እንዳይወሰድ የሚመለከታቸው ክፍሎች ያለመታከት ሳያሰለሱ መትጋት ይጠበቅባቸዋል።

ደቡብ አፍረካ ለመጠጥና ለልዩ ልዮ የቀን ተቀን  የውሃ ፍላጎቷ ውሃን የምታገኘው ከእርሷ ከፍ ብላ ከምትገኘው ከጎሮቤቷ ከቦትሰዋና ነው። ደቡብ አፍሪካ ለዚህ ታላቅ ውለታዋ በየዓመቱ የጥሩ ውለታ ገፀ- በረከት (Loyality payment) ለቦትስዋና መንግሥት ትከፍላለች። ግብፅእንዲህ ዓይነቱ ሰናይ ምግባር እጅግ ከፍተኛ ውለታ ለምታበረከትላት ለኢትዮጵያ አድርጋ አታውቅም፤ ለወደፊቱም ታደርገው ይሆናል ተብላ አትታማም። ይልቅ የኢትዮጵያ ውሎታ የሚከፈለው ጀርባ ጀርባዋን በጅራፍ መግረፍ፤ማስፈራራትና አልፎም እንድትፈረካከስናእንድትበታተን የረቀቁ ደባዎችና ሴራዎች መጎንጎንና መፈጸም ነው። የኢኮኖሚ እቅም ያለመፈርጠም ጉዳይሆኖ ድህነትም ጉልበት አልባ አደረገን እንጂ፤ ወደ ላኦስ፤ ቬትናም፤ ካምቦዲያና ሌሎች ታህታይ ተፈሰስ አገሮች የሚፈሰሱት የቻይና ወንዞች ላይ፤ ቻይና ከሃያ በላይ ከፍተኛ ግድቦች ለሃይል፤ ለመስኖና ለአሣ ልማት ግንብታ ስትገነባ ማንም አልደነፈባትም፤ አሁንም አዳዲስ ግድቦችን እየገነባች ባለችበት ውቀት ምን እየሠራሽ ነው ብሎ ያስጠነቀቃት የለም። ታድያ ጉልበታምና የፈረጠመ የኤኮኖሚ ጡንቻ ያለመኖርም ልዓላዊነትህንለድርድር አልፎ የሚሰጥ ሁኔታ ነው። ለዚህ መፍትሄው ደግሞ አንድያውን ዓይንን ጨፍኖና ጥርስን ነክሶ የኤኮኖሚ ጡንቻ እንዲፈረጥም ማድረግ ነው። ሌላ አማራጭ ከቶ የለም። ይህም በባለ ብዙ ዘርፍ የውሃ ልማት እቅድ እግዜር የሰጠንን ፀጋ ያለፍርሃትና ያለ ሰቀቀን ሌት ተቀን ደፋ ቀና ብለን መስራት ነው።

ከዚህ ቀጥሎ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ከግብጽ አኳያ በምን መልኩ ለሚፈልጉት ግብ መንደርደሪያ አድርገው ሊጠቀሙበት እንዳሳቡና፤ ኢትዮጵያም ያንን የሩቅ ራእያቸው ነቅታበት ውሉ በግድቡ አጠቃቀምና ቁጥጥር ብቻ እንጂ፤ ኢትዮጵያ በሚፈስሱ ወንዞች የሚኖር የውሃ ድርሻና ክፍፍል አይደለም የሚለው ነው። ግብፆች የታላቁ የህዳሴ ግድብ እንደ ጭንብልና ማመኻኛ ይጠቀሙበታል እንጂ ያነጣጠሩት ኢትዮጵያ ውሃዋ ለልዩ ልዩ ልማቶች በተለይም ለመስኖ ልማት መጠቀም እንዳትችል ነው።

በእሥራ ዘጠኝ መቶ ዘጠናዎቹ መጨረሻ ግድም ገና የህዳሴው ግድብ ከመጣሉ በፊት ከግብጽና ከሌሎች አገሮች በውሃና በሃይል እውቅና ያላቸው ባለሞያተኞች በአዲስ አበባ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር። የግብፁ የውሃ ባለሞያ ባደረጉት ንግግር “ኢትዮጵያ ከዝናብና ከከርሰ ምድሯ የምታገኘው ውሃ በቂዋ ነው” ብለዋል። በወቅቱ ከባለቤቷ ኢትዮጵያ በላይ ግብጽ ስለ ኢትዮጵያ ዝናብና የውሃ መጠን የበለጠ የብሔራዊ ሜትሮሎጂ መረጃ ነበራትና ባለሞያው ንግግራቸውን ያቀረቡት ይህን መረጃ ተደግፋው ነበር።

ከአሜሪካ ተጋብዘው የመጡ አንዱ የውሃ ጠበብት ግብፆቹን “አሁን ኢትዮጵያ አቅም ኖሯት ለተለያዩ ልማቶች ትልቅ ግድብ በትሰራ እናንተ ምን ታደርጋላችሁ?” በማለት ሲጠይቅዋቸው፤ የግብፁ ባለሞያ ፊታቸውን ክርችም አድርገውና ፈርጠም ብለው “ይኼማ የሚታሰብ አይደለም፤ ፈፅሞ አይሞከርም እንጂ!” በማለት አሰጠንቅቀው ነበር። ለጠቅ አድርገው አሜሪካዊው ባለሞያ “እሺ ኢትዮጵያ ትልቅ ግድብ ትሰራ ብለን በንወስድ እናንተ በቦምብና በሚሳኤል ለማፈረስ ይመቻችሁ ይሆናል፤ ዳሩ ግን ኢትዮጵያ በዝቅተኛ በመካከለኛ ደረጃ በቤተሰብና በጣቢያ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት ለማሳለጥ በየቀየው አንስተኛ ግድብ በትገነባና  ቤተሶቦችም በየጓሮቻቸው የውሃ ማጠራቀሚያ ጉዱጓድ ቆፍረው በክረምት ሞልተው በበጋ ቢጠቀሙበትና አሁን ተጅምሮ እንዳለው በያካባቢው የውሃና አፈር እቀባና የደን ልማት ቢያሳልጡ የቱን ከይቱ ለይታችህ ለትደበድቡትና ሊታፈርሱት ትችላላችህ?” ብለው ሲጠይቅዋቸው ምንም መልስ ለመስጠት አልቻሉም ነበር።

የወቅቱ የግብፅ መራሄ-መንግሥት አል-ሲሲ በፈረንጆች 5/10/19  በቲዊተር ገጻቸው ‘የናይል ወንዝ አላህ ለግብጽ ህዝብ የቸረውስጦታ ነው’ በማለት ዘግቧል። ፕሬዝዳንቱ  ለዓለም አቀፉ ማህበረ- ሰብ ለማሰተላለፍ የፈለጉት መልእክት ናይል በማንኛውም መለኪያ የግብፅና የግብፅ የሚል አንደምታ ያለው ነው። በናይል ውሃ ባለቤትነት ለሚነሣባት ግብፅ አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ሁሉ የምትወስድ መሆንዋን መስረገጣቸው ነው። ይህ ገላጻ ኢትዮጵያ ከገዛ ምድሯ ፈልቆ ከ800 ኪ/ሜትር በላይ በሚፈሰሰው ወንዟ ላይ መጠቀም የማትችል መሆኗ የሚያስጠነቅቅ። አል-ሲሲ ይህንን የገለጹት የሦስቱም ሃገሮች የቴክንክ ቡድኖች በውይይት ተጠምደው በነበሩበት ከ2015 በኋላ መሆኑ የሚገርም ነው። ገለፃው የፕሪንስፕል ኦፍ ድክላራሽን (Principles of Declaration) ውል የሚያጣጥል ነው። ከዚያም አልፎ በቅርብ ጊዜ ግብፅ ለህልውናዋና ለህዝቧ ስትል ጦርነት ልትከፍት እንደምትችል ዝተው ነበር። አጸፋውን የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ በፓርላማ ተናግረው ፍጥጫው በርትቶ ነበር።

የሁለቱም አገሮች መሪዎች በራሻያ ከፕሬዝደንት ፑቲን ጋር መክረው የቴክንክ ቡድኖቹ ውይይት እንዲቀጥሉ ተስማምቷል። በዚህ መካከል ግን አልሲሲ በዓለም መንግሥታቱ ስብሰባ ላይ ለኛ ታደላለች ብለው የሚያስብዋት የዓለም ኃያሏ አገር አሜሪካ ጉዳዩ ጋር በታዛቢነት እንድትገባ ጠየቁ። አሜሪካም ዓይኗን ሳታሽ ጥሪውን ተቀብላ ሹር ጉድ ማለት ያዘች፤ የዓለም ባንክና የአሜሪካው መንግስት ግምጃ ቤት በታዛቢነት እንዲቀመጡ ተደረገ። ሚስኪኗ እናት ሃገር ወደ ግብዣው፤ የራሷ ጉዳይ እንዳይደለ ተጋበዘች። ምንም ሳታቅማም ግብዣውን ተቀበለች። የሦስቱ ሃገራት የቴክኒክ ቡድኖችና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮቻቸው ዋሽንግተን ላይ መጀመሪያ ላይ ተገናኙ። በሁለት ወራት አራት ስብሰባዎች እንዲያደርጉና ለችግሩ በመወያየት እልባት ላይ እንዲደርሱ ተጠበቀ። እንደተጠበቀው ስምምነት ላይ ሊደረስ አልተቻለም። በረዠሙ የሦስቱ ሃገራት የቴክኒክ ቡድኖች ስብሰባ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ትወግን የነበረቸው ሱዳን፤ ድንገት ፊቷን አዙራ ግብፅን መደገፍ ጀመረች። የግፍ ግፍ በእንጥል ላይ ጀሮ ደግፍ እንዲሉ፤ ታዛቢ ሆነው የቀረቡት ድርጅቶች በኢትዮጵያው ቡድን ላይ ጫና ማድረጉን ያዙ። የ BBC AMHARIC NEWS በወቅቱ  “ኢትዮጵያ 4 ለ 1 እየተመራች ናት” በማለት ዘግቧል። በፌብ 12ና 13 2020 ሦስቱም ሃገሮች በስምምነት መድረስ ይኖርባቸዋል በተባለው ቀጠሮ፤ ኢትዮጵያ ባለመቀበሏ በእንጥልጥል ቀረ። የቴክኒክና የህግ ቡድኖቻችን እንዲያ ማድረጋቸው የአገሪቱ ልዓላዊነትነትና የራሷ ፀጋ የመጠቀም መብቷ እንዳይደፈር ድንቅ ሥራ ሰርቷልና ሊመሰገኑ ይገባቸዋል።

የኢትዮጵያው ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት፤ ለመንግስት ቀሬቤታ ያላቸው ሙሁራንና ዜጎች እንዲሁም የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ስለ ህዳሴው ግድብ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በኢትዮጵያው ቡዱን ላይ ጫና ይደረገበት እንደነበረ አስነብቧል። ከዚህ በኋላ የነበረው ትእይንት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ማለታቸው ነው። ማይክል ፐንፕዮ፤ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዋናው ጉዳይ ባዶ እጃቸው ሳይሆን፤ ሃገራቱን ሊያስማማ የሚችል አዲስ የእርቅ ሰነድ ይዘው ነው። ጫና የሌለውና አድላዊ ያልሆነ አስታራቂ ሃሰብ ይዞ ሸምጋይ ሆኖ መቅረብ እስዮው የሚያሰኝ እንጂ በራሱ ክፉ ከቶ አይደለም። ዳሩ ግን ፓንፒዮ ይዘውት የመጡት አስታራቂ ሃሳብ ከምር ወደ ግብፅ አድልቶ ኢትዮጵያን የሚጎዳ አይደለምን? በአሜሪካ የቀረብ የማስማሚያ ሰንድ ሳያዩ እንዲህና እንዲያ ብሎ መናገር ባይቻልም፤ ካለፉት ሂዶቶች ብርሃን ሊፈነጥቁ የሚችሉ ሃቆች ያለ ሰቀቀን ማንሣት ግን የሚቻል ነው።

በህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ዙሪያ በድርቅና በተደጋጋሚ ድርቅ ተብሎ የቀረበው ሃሳብ በግብፅ የቀረበ ሲሆን፤ ምን ያክል ዝቅተኛ የውሃ መጠን በወቅቱ ኢትዮጵያ መልቀቅ እንዳለባት የሚያስገድድ ነው። ግብፆቹ ቢያንስ 40 ብልየን ኩ/ ሜ ያሉ ሲሆን ኢትዮጵያ 31 ብልየን ኩይ/ሜትር የሚል የመደራደሪያ መጠን አቅርባለች። ታዛቢ ሆነው በመጀመሪያ የቀረቡት ቡድኖች የማስታረቅያ ሃሳብ ነው ብለው ግብጽ ትንሽ ዝቅ እንድትል ኢትዮጵያ ግን አሳምራ እንድትለገስና ፊርማው እንዲፈረም ግፊት እያደረጉ እንደ ነበር ተስምቷል። በድርቅና በተከታታይ ድርቅ ኢትዮጵያ ይቅርና 40 ብልየን ኩ/ ሜትር ውሃ በዓመት፤ 31 ሚልየን ኩይ/ ሜትርም ማቅረብ የለባትም ብየ አምናለሁ። ድርቁ በተፈጥሮ የሚመጣብን አበሣ ነው፤ ወደድነው የሚሆንና ከኛ ውጭ የሚሆን ክስተት ነው። የዝናብ እጥረቱ ህዝቡንና እንስሳቱን በረሃብና በጥም የሚገድልና የሚፈጅ ነው። እንዲህ ባላ ፈታኝ ወቅት ሰማይ ምድርን አላርስ ብሎ ሲያምፅ፤ ህዝብና እንስሳት ሲያልቁ፤ በጎ ላደረገ ህዝብ እናግዝህ እንርዳህ ይባላል እንጂ፤ አንተ ስትራብና ስትሞት ከግድብህ ውሃ ይኼን ያክል ካላቀረብክ ብሎ ድርድር መያዝ ከቶ የተገባ ነውን? “ወርቅ ላበደረ አፈር ይመለስለታል” እንዲሉ እየሆነ ያለው ይኼው መሆኑ ልብን የሚነካ ነው።

አባይ እስካሁን ድረስ በተራሮች፤ ቁልቁለቶች፤ አባጣ ጎርባጣና ሸለቆ እየነጎደ ስለሚጎርፍ እስካሁን ድረስ በሚፈስበት 800 ኪ/ ሜትር ርቀት ከምንጩ  አጠገብ ከምትገኝ የባህር ዳር ከተማ ሌላ ከጠና ሃይቅ ውጭ የተቆረቆረ ከተማ ይቅርና በአካባቢው የሚጠቀምበት ገጠርና እንስሳ የለም። ይኽ የአቅም ማነስ ጉዳይ ሆኖ እንጂ እንዲህ አይቀጥልም። ለመስኖ ልማት፤ ለሃይል ግልጋሎት፤ ለአሣ ማፍሪያና ለደንና ላፈር ለምነት፤ በመንግስት እርዳታና በህዝብ ተሳትፎና ትጋት በርካታ ግድቦች መሰራታቸው የማይቀር ነው።  ስለዚህ ለወደፊቱ ለተለያዩ መስተጋብሮች ኢትዮጵያ ብዙ ብልዮን ኩዩ/ ሜትር ውሃ በየዓመቱ ስለምትጠቀም ወደ ታችኞቹ ሃገሮች የሚፈስሰው የውሃ መጠን ከ31 ብልየን ኩዩ/ ሜትር በታች መሆኑ አይቀርም። በመሆኑም ግብፆች በዚህ ውል አመኻኝተው ውሆቻችን ለእነዚህ ተግባራት እንዳንጠቀምባቸው እያስገዱንና እየከለከሉን እንዳለ መረዳት ያስፈልጋል። አሁን እንኳን ባናደርገውም ለሚቀጥለው ትውልድ ማሰብም ግዴታችን ነውና መጨውን አሻግረን ማየት ግድ ይለናል። በመጨረሻ በዋሽንግተን በቴክኒክና በህግ ቡድኖቹ መካከል በተደረገው ድርድር፤ ድርድሩ  ከታላቁ የህዳሴ ግድብ አጠቃቀምና ቁጥጥር ወጥቶና አፈትልኮ ወደለየለት የውሃ ድርሻና ክፍፍል ድርድር ቀርቦ እንደ ነበር ተሰምቷል። ይኽ በኢትዮጵያ ጥቅምና ልዓላዊነት ላይ የተቃጣ ደባ ነው።

ግብፅና የውሃ ፀጋዋ

ለዘመናት ተመችቷት ለጥ ብላ መተኛቱ ስለማራት እንጂ ግብጽ የውሃ እጥረት ያላት አገር ከቶ አይደለችም። ግብጽ እንደ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ውደብ አልባና በውሃ ያልተከበበች ሃገር አይደለችም። ታላቆቹ የሜድትሬንያን ባሕርና ቀይ ባህር ከበበዋት እነሆን ብይን ጠጭን የሚልዋት ሃገር ናት። ሳዊዲ አረቢያ ከ70% በላይ ውሃን የምታገኘው ዲሳሊነሽን (Desalination) በተባለ ጨውን ከውሃ ነጥሎ በማውጣት የሚጠጣና ለመስኖ ብቁ በሚያደርግ ሳይንሳዊ ስልት ነው። ሊብያም አባይደርሶ ስለሚያረሰርሰትና ስለሚያጠጣት ሳይሆን የሚያስፈልጋትን ውሃ የምታገኘው ከሜድትረኒያንን ባህር ጨውን በሳይንሳዊ መንገድ በማጥራት ነው። ኢትዮጵያ ግብጽን ይህ አማራጭ እንዳላት ልትሞግታት ይገባል። አዎ! አባይ ከባህር ከሚገኘው ውሃ የተሻለና ወጪ የማያስወጣ ሊሆን ይችላል፤ ዳሩ ግን አማራጮች እያሉህ ለኔ ብቻ ይመቸኝ ስለ ሌላው ምን ገዶኝ በማለት ሌላው ህዝብ በገዛ ሃብቱ እንዳይጠቀም በአንድም በሌላም መንገድ መከልከል ግን አግባብነት የሌለው ነው።

ግብጽ ዝናብ ሳይኖራት በሚፈስሰው ናይል አመካይነት በሚፈጠረው እርጥበትና በማርከፍከፍም ለአንድ መቶ ዓመት የሚበቃ የከርሰ ምድር የውሃ ክምችት እንዳላት ጥናቶች ያሳያሉ። የግብፅ የከርሰ ምድሩ የውሃ መጠን ከኢትዮጵያው የከረሰ-ምድር የውሃ መጠን የበለጠ ነው። ከዚህ በተጨማሪም ግብፅ የናይልን ውሃበሲና በረሃ አሻግራ ለሌሎች ሃገሮች በተለይም ለስዑድ አረብ ለማቅረብ እያቀደች እንዳለች ታውቋል። ይኽ በዓለም አቀፍ ህግ የተከለከለ ነው። ሌላው ግብፅ ያለ ጥቅም የሚፈሰውን የኮንጎ ወንዝ 800 ኪ/ሜትር ካናል ሰርታ ለመጠቀም እቅድ እንዳላት እየተሰማ ነው። ይኽ በጎ ሃሳብና የናይልንጫና ረገብ ሊያደርግ የሚችል እርምጃ ነው። በመሆኑም ግብፅ ናይል ላይ ብቻ የሙጡኝ ከማለት ሌሎች የውሃ ፀጎቿ ልትቃኝና ልትፈትሽ ይገባታል። በዚህ ዙሩያ ኢትዮጵያ ለዓለም ማህበረ-ሰብ ማሳወቅና መስረዳት ይኖርበታል። ግብፅ መጉደል የለበትም በምትለው የአስዋን ግድብ ለይ ተገቢ ያልሆነ የውሃ አጠቃቀምና መባከን እንዳለ ይሰማል፤ በግድቧላይ ኢትዮጵያን ቁጥጥር እናደርግብሻለን ብላ ግብፅ እንደምትደራደር፤ ኢትዮጵያምበግብፅ የውሃ ፀጋ አጠቃቀም አማራጮችና በተለይም በአስዋን ግድብ አጠቃቀምና አያያዝ  መደራደር አለባት።

በቅርብ ጊዜ በዋሽንግተን በተካሄደው የሦስቱን ሃገሮች የቴክኒክ ቡድኖች ስብሰባ ከግብፁ ቡደን እኩል የውሃ ከፍታ እንዲኖራቸው የህዳሴ ግዱቡና የአስዋን ግድብ ማያያዝ የሚል ተቀባይነት የሌለው ሃሳብ ይዘው ቀርቧል። ከዚህ ዘለውም በሦስቱም ሃገሮች የሚኖረው የውሃ ድርሻና ክፍፍል እንዲደረግ አንስቷል። ይህ የኢትዮጵያነ ጥቅምና ልዓላዊነት የሚጋፍ ስለሆነ ህዝብና መንግስት በፅናት ተግተው ሊቃወሙት የተገባ ነው።

 

ምክረ-ሳቦች (Recommendations)

1.   ከታላቁ ግድብ ሙሌታና አጠቃቀም ጀርባ ግብፅ የምታደርገው ደባና ሴራ በሚገባ አውቆ መንግስት ለጊዜያዊ የራሱ ጥቅም እንዳያውልና ትውልድን እንዳይጎዳ ቆፍጠን ብሎ መቆም አለበት።

2.   የዓለም ባንክና የአሜሪካው ግንጃ ቤት መጀመሪያም አደራደሪ ሆነው ሲቀርቡ ኢትዮጵያ መቀበል አልነበረባትም፤አሁንም መቀጠል የለባትም።

3.   የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ህዝቡ በአገሪቱ ጥቅምና ልዓላዊነት የጠነከረ አቋም ሊኖረው ይገባል።

4.   የኢትዮጵያ መንግስት የበለጠ ግኑኝነት ማድረግ የሚኖርበት ከአረብ ሃገራትና ከኤርትራ መንግስት ሳይሆን ከአፍረካ ህብረት ነው።

5.   በኢትዮጵያ መንግስት የሚተዳደሩት የመገናኛ ብዙሃን ስለ ህዳሴው ግድብ ያላው ሁኔታ ሳይደብቁና ሳይሸሽጉ ለህዝቡ ማቅረብ አለባቸው።

6.   መንግስት ህዝቡ ሳይወያየበትና በተለይም በሙያው እውቀት ያላቸው በውጭም በውስጥም የሚኖሩ ምሁራን ሳይነጋገሩበት አደጋ ሊጢል የሚቸል ውሳኔ እንዳይወስንና ተጣድፎ እንዳይፈርም፤ፓርላማው ጉዳዩን ተከራክሮበትና ባለሞያዎች ጋብዞ ተገቢ ማብራራያ  እንዲያገኝ ማድረግና ያለ ፓርላማው እውቅና ፍርሚያ እንዳይደረግ።

7.   መንግስት ህዝቡ በሃይል አቅርቦት ልማት ብቻ ላይ ሳይሆን፤ በመለሰተኛ በመካከለኛና በከፍተኛ የመስኖ ልማት እንዲሳተፍ ህዝቡን መደገፍና ማበረታት፤ የአሣ ሃብት ልማት እንዲስፋፋ ማድረግ፤ በትግራይ ክልል አመርቂ ውጤት ማሳያቱ እንደተመሰከረለት የውሃና የአፈር ጥበቃ በሌሎች ክልልችም እንደተገበር ማድረግና ማገዝ፤ የባዮ-ማስ ሃይል ቆጣቢ ምድጆችና ምጣዶች ተመርተውለገጠሩ ማህበረ-ሰብ እንዲሰራጩ ማድረግና አሁን ካለው ብቃታቸው ከፍ እንዲል መጣር፤ መበጀትና ማበረታት አለበት።

8.   ገጠር ወደ ከተማ የመለወጡ ሂደት በተገቢ ጥናትና እቅድ ማካሄድና ኢንዲሰቱሪ የመሪነቱን ስፍራ እንዲጨብጥ ማድረግ፤ ይህም የተቀነባባረ የውሃና የኤነርጂ አጠቃቀም የሚጠይቅ ነው።

9.   በኤነርጂ ዘርፍ የተሰማሩት የመንግስት መዋቅሮች ለምሳሌ ውሃና ኤነርጂ ሚ/ር፤ የግብርናው የገጠርና ቴክኖሎጂና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚ/ር እንዲሁም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በቅንጅት በውሃው ልማትና በኤነርጂ ብቃት ማሻሻል ላይ እንደሰሩ ማድረግ። በተለይ እንደ ምርጥና ላቀች የመሳሰሉ የኤነርጂ መጠቀሚያ ቁሳቁስ ብብዙ መሪዎች ዘንድ ትንሽ ተደርገው ስለሚወሰዱ የጎላ ጥቅማቸው ታውቆ መንግስት ለማምረትና ለማከፋፈል እንዲረዳና እንዲያስተባበር። በመኪና የነዳጅ አጠቃቀም ዙሪያም ብዙ ቁጥጥር ያስፈልጋል። ምክንያቱም ብቃታቸው በጣም ዝቅተኛ የሆኑት ተሽከርካሪዎች በብዙ ትግል በውጭ ሚንዛሪ የሚገዛውን ነዳጅ ስለሚያባክኑ ነው።

10. ከዚህ በተጓዳኝ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች  ስለ አገራቸው የውሃ ፀጋ እንዲያውቁ፤ በግብፅ የተጋረጠባት እንቅፋት አንስተው እንዲነጋገሩበት፤ ኤነርጅንና የአጠቃቀም ብቃትን (Efficiency) በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተግባር በስራው ከተሰማሩ ተቋሞች ጋር በመገናኘት ተግባራዊ እውቀት እንዲለማመዱ ማድረግና የተሻሻሉ የኤኔርጂ መጠቀሚያ ቁሳቁስ እንዲያመርቱ መደገፍና ማበረታት።

11. ኢትዮጵያ በድርቅ ሆነ በተከታታይ ድርቅ ከግድቧ የተወሰነ ውሃ መልቀቅ የግብጽ የማከማቻ ጋን ወይም ቋት ማድርግ መሆኑ ታውቆ ጉዳዩ ተከልሶ እንዲታይ ማድረግ። ይህ ውሃችን  ከግድቡ በላይ ባሉት ስፍራዎች ለሌሎች ልማቶች በየዓመቱ እንዳንጠቀምበት የሚሸብብ ስለ ሆነ፤ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው።

12. ኢትዮጵያ አሜሪካ በዓለም ባንክና በገንዘብ ግምጇ ቤቷ “ታዛቢነት” በሚል ስም ከገቡበት ድርድር መውጣት ይኖርባታል። ጉዳዩ ገፍቶ ከመጣ እንኳ ታዛቢ ሆነው መቅረብ ያለባቸው የአፍረካ ህብረት አገሮች ናቸው።

13. በ1999 በተደረገው የናይል ተፋሰስ ሃገሮች ውይይት ሃሳቡ ተቀብለው ነገር ግን ያልፈረሙ አራት አገሮች በዲፕሎማሲ አሳምኖ እንዲፈርሙ ጥረቱ መቀጠል።

14. ህዝቡመለያየትን ገትቶ ለጥቅሙና ለልዓላዊነቱ አንድ ሆኖ መነሣትና፤ ከህዝባቸው በላይ ለውጭ ሃገር መንግስታት ለሚንበረከኩ መሪዎች መቃወም ይኖርበታል።

15. ወቅቱ የኢትዮጵያ ምርጫ የተቃረበበት በመሆኑ የአሁኑ መንግሥት በህዘብ ለሚመረጠው መንግሥት እንዲወሰን እንዲተውለትና አሁን በጥፍድያ እንዳያደርገው ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ህዝቡ በተለያዩ መድረኮች ማሳሰብና ማስጠንቀቅ።

16. ምንምእንኳ በተቋዋሚ ፓርቲዎች መካከል ልዩነት ቢኖርም በህዳሴ ግዱቡና በውሃ አጠቃቀም መብታችን አንድ ሆነው እንዲነሱና በምርጫ ውድድሩ ጊዜ በሚያገኙት እድል አቋማቸውን አጠንክረው ለገዥው ፓርቲ፤ ለውጭ ተደራደራዎችና ታዛቢ ነን ብለው ጫና በሚፈጥሩ ሃይላት ሳያሰለሱ መግለጽ።

17. መንግስትጥቅማችን፤ ልዓላዊነታችንና ሰላማችንና እንድናጣ የምታደርገን ግብፅ የመጠቀሚያ የጦር እቃ አድርጋ ከሚትጠቀምባት ከኤርትራ መንግስት መወዳጀትና በሽሽግ መመካከር ትቶ፤ ከገዛ ህዝቡና ከተቋዋሚ ፓርቲዎቹ ጋር መምከርና መመጎት ይኖርበታል። ትክክለኛና ግልጽ በሆነ መንገድ የኤርትራ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም ከትግራይ ህዝብ ጋር ጤናማ ትስስርና ግኑኝነት መፍጠር የተገባ ቢሆንም፤ አንዱ ሃገር በሌላው ሃገር ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም። የወቅቱ ገዢ ፓርቲም የፈለገው ነገር ይፈጠር ራሱ ከሚያስተዳድረው ህዝብ በላይ በውጭ ላይ የሚታመንና የሚደገፍ መሆን የለበትም።

18. መንግሰት መጪውን ትውልድ መዘንጋት የለበትም። ከሰላሣ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ 200 ሚልየን ይደረሳል ተብሎ ይገመታል። አንድ እንግሊዛዊ በቀን 160 ሊትር እንደሚጠቀም ጥናቶች የሚጦቁሙ ሲሆን፤ የአንድ ግብጻዊ የቀን የውሃ ፍጆታ 200 ሊትር ነው። አንድ ኢትዮጵያው በቀን በአማካይ የሚጠቀመው ውሃ ከ5- 6 ሊትር ነው። የውሃ ፍጆታችን በጣም ዝቅተኛ መሆኑ የድህነታችን ደረጃ የሚገልፅ ነው። ይሁንና ከሳላሳ ዓመት በኋላ ይኖራል ተብሎ የሚታሰበው 200ሚልየን ህዝብ አንድ ሰው አሁን ግብጽ የምታገኘው ግማሽ ማለትም 100 ሊትር በቀን ከተጠቀመ፤ በቀን ሃገሪቱ የምትጠቀመው ውሃ በድምር 200 ብልየን ሊትረ ይሆናል። በዓመት ህዝቡ በቤት ለመጠጥና ለመጸዳዳት የሚጠቀመው ውሃ መጠን 7 300 000 000 000 ሊተር ነው። አንድ ኩብ ሜትር 1000 ሊትር ስለ ሆነ፤ በጠቅላላ ሃገሪቱ ለቤት ግልጋሎት በዓመት የምትጠቀማው ውሃ 73 ብልየን ሜትር ኩብ መሆኑ ነው። ይህን ሳናስብ አሁን ተቻኩለንና በሁኔታዎች ተገፋፍተን ለግብጽ ብንፈርምላት የሚመጣው ትውልድ ለጉሮሮው ማራሻ የሚሆን ዋሃ እንኳን እንደምናሳጣው መገንዘብ ይኖርብናል።

 

                    እግዚአብሔር እናት ኢትዮጵያን ይጋርዳት፤ ይጠብቃትም

                                            አሜንና አሜን

 

Back to Front Page