Back to Front Page

“የሕገ መንግሥት ቀውስ፤ “የሥልጣን ጥመኞች” በምናባቸው የፈጠሩት ቀውስ”

“የሕገ መንግሥት ቀውስ፤ “የሥልጣን ጥመኞች”

 በምናባቸው የፈጠሩት ቀውስ”

 

በጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ፤ 05-07-20

 

ሰለሕገ መንግሥት ቀውስ ጥያቄ ሲነሳ፤ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ አይደለችም። የሕገ መንግሥት ቀውስ ጥያቄ የሚነሳው፤ አንድም በሃገር ጉዳይ እና በሕግ ጥሰት ከልብ በሚቆረቆሩ ሰዎቸ ሲሆን፤ ሌላ ደግሞ፤ በምርጫ ተወዳድረው፤ የሕዝብን አዎንታዊ ፈቃድ አግኝተው ሥልጣን ለማያዝ በማይችሉ የፖለቲካሃይሎች በአቋራጭ ሥልጣን ለማግኘት የሚያነሱት ጥያቄ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት ስለሕገ መንግስት ቀውስ መኖር የሚናገሩ ሰዎች፤ ከልብ ስለሕግ አስበው እና ለሃገር ተቆርቁረው ነው ለማለት ያስቸግራል። አንዳንዶቹ ሕግ ሲጥሱ፤ ሲያስጥሱ እና አሁንም ሕግ በመጣስ ላይ ያሉ መሆናቸው ነጋሪ አያሻውም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሕገ መንግስት ቀውስ ተፈጥሯል እያሉ የሚከራርከሩ ሰዎች ክርክራቸው ውኃ አይቋጥርም፡፡ በዚህ ፀሃፍ እምነት፤ ሕገ መንግስቱ ቀውስ ውስጥ አልገባም፤ አሁን አለ ለሚባለውም “የምርጫ ውዝግብ” መልሱ በሕገ መንግስቱ ውስጥ በግልጽ ተቀምጧል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጉዞ፤ ሕዝቡ የሥልጣኑ ባለቤት እንዲሆን አቅጣጫ በያዘበት በዚህ ወቅት፤ ምንም ዓይነት የሕዝብ አመኔታ የሌላቸው የፖለቲካ ሃይሎች፤ ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝ፤ “የሽግግር መንግስት” የሚለውን ቀረርቷቸውን በአደባባይ ተያይዘውታል። ስለሕገ መንግሥቱ ምንም ዓይነት ጭብጥ እና እውቀት የሌላቸው ድንክዬ የፖለቲካ ሃይሎች፤በየዜና አውታሩ ስለጮሁ ብቻ፤ ጩኸታቸውን እውነት አያደርገውም። “ሃገሪቱ የሕገ መንግሥት ቀውስ ውስጥ ገብታለች” ብለው የድንቁርና ፊሽካቸውን ሲነፉ ስንሰማ ደግሞ፤ ‘ድሮስ ከነሱ ምን ይጠበቃል’ ብቻ ብለን ልናልፈው አንችልም።

Videos From Around The World

       በመጀመርያ፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ቀውስ ውስጥ ነው ወይ ብሎ ከመመለስ በፊት፤ የሕገ መንግስት ቀውስ ምንድነው የሚለውን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል። ይህንን ጥያቄ ለመመለስ ጁልያ አዛሪ የተባሉ የማርኰት ዩኒቨርስቲ አሶስየት ፕሮፌሰር እና ሴት ማስኬት የተባሉት የዴንቨር ዩንቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰር ያስቀመጡትን መመዘኛ መመለከቱ ይበጃል። በነዚህ የፖለቲካ ሳይንስ ልሂቃን አመለካከት፤ የሕገ መንግስት ቀውስ ተፈጠረ የሚባለው አራት ነገሮች ሲከሰቱ ነው። እንዚሀም ፩. ሕገ መንግስቱ ስለተነሳው ጉዳይ ምንም ሳይል ሲቀር፤ (፪) የሕገ መንግስቱ ትርጓሜ አውዛጋቢ ሲሆን (፫) ሕገ መንግስቱ ምን መደረግ እንዳለበት ግልጽ ቢሆንም፤ ሕገ መንግስቱ ተግባራዊ እንዳይሆን ፖለቲካዊ ሁኔታው የማይቻል ሲያደርገው፤ (፬)ተቋማቱ በራሳቸውውድቅ ሲሆኑ ወይም ሲፈርሱ ነው።

       እነዚህን መመዘኛዎች ስንገመገም፤ የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት ቀውስ ላይ ነው ለማለት እጅግ ያስቸግራል። በአሁኑ ሰዓት ሕገ መንግሥቱ ቀውስ ውስጥ ገብቷል የሚሉን ሰዎች፤ ሕገ መንግሥቱን በቅጡ ያልተረዱ እና ያላነበቡ፤ወይም፤ እኩይ የፖለታካ ዓላማ አንግበው፤ ደጋፊዎቻቸውን በሃስት በማነሳሳት፤ ከሕገ መንግስታዊ አሰራር ውጭ፤ ያለሕዝብ ፍላጎት እና ፈቃድ፤ በራሳቸው አነሳሽነት በሚፈጠር ቀውስ እራሳቸውን ወደ ሥልጣን ማምጣት በሚፈልጉ ሃይሎች ሊሆን እንደሚችል አልጠራጠርም። የሕገ መንግስትቀውስ አለ ሲሉ የሚከራከሩብት ምንም ዓይነት ተጨባጭ መረጃ አያቀርቡም፤ አላቀረቡምም። ለሃሳባቸው መከራከርያ የሚያነሱት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ፤ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ሊካሄድ ስለማይችል፤ አሁን ያለው የመንግስት የሥልጣን የጊዜ ገደብ በመስከረም ያበቃል፤ ከዛ በኋላ ይህ መንግሥት እንደ መንግሥት ሊቀጥልበት የሚችል ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የለውም የሚል ነው። ይህ ክርከር፤ ትንሽም ቢሆን ሕገ መንግስቱን አተኩሮ ካየ ማንም ዜጋ የሚጠበቅ አይደለም። የእነዚህ ሰዎች ክርክርም፤ጭብጥ በመመርኮዝ የሚደረግ ክርክር ሳይሆን፤ የሰዎችን ስሜት በመኮርኮር ቀውስ ለመፍጠር እና በአቋራጭ ወደ ስልጣን ለመምጣት የሚደረግ “በአሸዋ ላይ የቆመ” ክርክር ነው።

       የመጀመሪያውን የመመዘኛ ጥያቄ ለመመለስ፤በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት፤ እንዲሁም አሁን ያለው የሕዝብ ተወካይች ምክር ቤት፤ ቢበተን፤ ሃገሪቱን ማን እንድሚመራ እና እንዴት መመራት እንዳለባት ሕገ መንግስቱ የሚሰጠው መልስ አለ ወይ ነው? ለዚህ ቀጥተኛ እና ትክክለኛ መልሱ አዎ የሚል ነው፡፡ የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 60 ቁጥር 2 ምክር ቤቱን የመበተን ሥልጣን የሚሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ ከተበተነ በኋላ ደግሞ ሥልጣን ተረክቦ “በጊዚያዊነት” የሚሰራው፤ በምክር ቤቱ አብላጫ ቁጥር ያለው የፖለቲካ ፓርቲ ወይም በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ መሆኑን በግልጽ ያስቀምጣል። ምክር ቤቱ ከተበተነም በኋላ፤ 6 ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ ሕገ መንግስቱ ይደነግጋል፡፡ አሁን ያለው መንግስት የሥልጣን ጊዜው ሲያበቃ መበተን አለበት እንኳን ብንል፤ ሕገ መንግስቱ ሃገሪቱን እንዲያስተዳደር ሥልጣን የሚሰጠው፤ ሥልጣን ላይ ላለው የፖለቲካ ድርጅት እንጂ፤ በየትኛወም አንቀጽ፤ ሕገ መንግሥቱ፤ የሽግግር መንግስት ይቋቋም አይልም።

       በተለይ አሁን ላለንበት ሁኔታ ግልጽ መልስ የሚሰጠን፤ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ነው። አንቀ93ን በቀናነት አንብቦ ለተረዳ፤ አሁን ላልንበት ወቅታዊ ሁኔታ፤ ይህ አንቀጽ የማያሻማ መልስ እንደሚሰጥ ለመገንዘብ፤ ማንም ሰው፤ የፖለቲካም ይሁን የሕግ ምሁር መሆን አይጠበቅበትም፤ የሚጠበቅበት፤ እራሱን ያስተማረ፤ ቀናኢ ዜጋ መሆን ብቻ ነው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ፤ ሃገሪቱ እንዴት እና በማን እንደምትተዳደር ግልጽ ሆኖ በሕገ መንግስቱ ተቀምጧል፡፡ይህን ለመረዳት የሚያስፈልገው ‘በቀናነት ልባችንን መክፈት ብቻ ነው’። ሆኖም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለዓመታት የታዘብነው አንዱ ነገር፤ በሥልጣን ጥም የውስጥ ደዌ ሕመም የተጠቁ ሰዎች፤ በሕዝብ አዎንታ ሥልጣን ለመያዝ ከመትጋት ይልቅ፤ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈጥሩት ውዝግብ እና አልፎም፤ የሚያስከትሉት የደም መፋሰስ ነው። እነዚህ የፖለቲካ ሃይሎች፤ዛሬ አለም ያለበትን ቀውስ ተጠቅመው፤ በሕዝብ አዎንታ ሳይሆን፤እራስቸው በምናባቸው ባለሙት የሕገ መንግስት ቀውስ፤ የስልጣን ባለቤት ለመሆን ቀና ደፋ ሲሉ ማየት፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጥርስ ለነቀልነው፤ ምንም አስደናቂ አይደለም። የሃገራችን ሕዝብ በነፃ እና ፍትሃዊ በሆነ ምርጫ ተወካዮቹን መርጦ፤ በራሱ ፍላጎት የሚተዳደርበት ሥልተ ስርዓት እውን እንዲሆን እና ጽንፈኛ ፖለቲካ ሃይሎች፤ የሕዝቡን ሥልጣን ዳግም እንዳይነጥቁ፤ሕገ መንግስቱ ቀውስ ውስጥ እንዳልገባ፤ ጭብጥ ላይ ተመርኩዘን የመግለጽ ሃላፊነት እና ግዴታ አለብን።

ወዳጄ ሙሉጌታ አረጋዊ ፎርቹን ጋዜጣ ላይ “The Constitution is not silent (ሕገ መንግሥቱ ይናገራል)” በሚል ርዕስ በሃገራችን የሕገ መንግስት ቀውስ እንደሌለ፤በእንግሊዘኛ ጽሁፉበሰፊው አትቶታል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት ሥልጣን የማን መሆን እንዳለብት፤ ሃገሪቱ እንዴት እንደምትተዳደር፤ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ አስቀምጦታል። የሕገ መንግስቱ አንቀጽ 93 ቁጥር 1ሀ እንዲህ ይላል፤“አንቀጽ 93 -ስለ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ(1ሀ) የውጭ ወረራ ሲያጋጥም ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲከሰትና በተለመደው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቋቋም የማይቻል ሲሆን፣ ማናቸውም የተፈጥሮ አደጋ ሲያጋጥም ወይም የሕዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ሲከሰት፣ የፌዴራል መንግሥት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመደንገግ ሥልጣን አለው::” ቁጥር 4ሀ ደግሞ እንዲህ ይላል “(4ሀ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚታወጅበት ጊዜ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣቸው ደንቦች መሠረት የሀገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብን ደህንነት፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥልጣን ይኖረዋል፡፡” ሕገ መንግስቱ በግልጽ እንድሚያስቀምጠው፤ በሕገ መንግስቱ ከተደነገጉት አንቀጽ 1፤ 18፤ 25፤ እና 39 በቀር፤ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ ማናቸውንም ሕገ መንግስታዊ መብቶች የመገደብ ሥልጣን አለው፤ ይህም የምርጫ ጊዜ የማራዝመን እና የሕዝብ ተወካዮችን የሥራ ጊዜ ማስቀጠልን ይጨምራል፡፡”

ከላይ እንደተጠቀሰው፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፤ አስቸጋሪ ሁኔታ በሃገሪቱ ሲከሰት፤ ሃግሪቱ እንዴት እና በማን እንደምትተዳደር በግል አስቀምጧል፤ ሌላው ቀርቶ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንኳን ቢበተን፤ ምርጫ ተካሄዶ ሕዝብ የመረጠው የፖለቲካ ሃይል ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ፤ሃገሪቱ እንዴት እና በማን እንደምትተዳደር በግልጽ አስቀምጦታል። ስለዚህ በሁለቱ የፖለቲካ ሳይንስ ምሑራን የቀረበውን የመጀመርያውን መመዘኛ ስንመለከት፤ አህን ላለንበት ሁኔታ ሕገ መንግስቱ ዝምታን አልመረጠም፡፡ ግልጽ የሆነ አቅጣጫ ሰጥቷል። አሁን ያለንበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ወቅት በመሆኑ፤ ይህ አዋጅ እስኪነሳ ድረስ፤ ሃገሪቱን የመምራት፤ የማስተዳደር፤ ሕግና ደንብ የማውጣት ሃላፊነት የተጣለበት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው። ታድያ በምን ሕግ ነው፤ የሽግግር መንግሥት ይቋቋም የሚለው አጀንዳ የሚራገበው? በሃገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ ሕዝብን የማስተዳደር ሥልጣን እንዲይዙ፤ ማንም አዎንታ አልሰጣቸውም፡፡ ሕዝቡን እንወክልሃለን አሉ እንጂ፤ ሕዝቡ ወክሉኝ አላላቸውም፡፡ ምርጫ እስኪደረግ ጠብቀው፤ የሕዝቡን ውሳኔ ለመጠበቅ እራሳቸውን መግራት ያቃታቸው የፖለቲካ ሃይሎችንስ፤ እንዴት ሕዝብን የመምራት እና ሃገር የማሰትዳደር ብቃት አላቸው ብለን ልንተማመንባቸው እንችላለን?

ቀጣዩ ነጥብ የሕገ መንግሥቱ ትርጓሜ አሻሚ ነው ወይ የሚል ነው፡፡ ለዚህ መልሱ አው እና አይደለም የሚል ነው፡፡ ይህ እንዳተርጓገም ይለያል፡፡ አንቀጽ 60ን ካየነው ትርጉሙ አሻሚ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳን አንቀጽ 60 የሚነግረን፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጊዜው ሳይደርስ ከተበተነ ስለሚኖር ሂደት ቢሆንም፤ ሕገ መንግስቱን አስፍተው ለሚተረጉሙ ሰዎች (broad interpretation of the constitution)፤ ይህን አንቀጽ፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተበተነ በማንኛውም ጊዜ ብለው ሊተረጉሙት ይችላሉ። ሆኖም ሕገ መንግስቱን አጥበበው ለሚተረጉሙ (narrow interpretation)ደግሞ፤ አንቀጽ 60 የሚለው፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጊዜ አገልግሎቱ ሳያበቃ ቢበተን ብቻ ነው ብለው ሊተረጉሙት ይችላሉ። አንቀጽ 60ን እንኳን አጥብበን ብንተረጉመው፤ የአንቀጽ 93ን ድንጋጌ አይቀይረውም፡፡ በዚህ ጸሃፍ እምነት፤ አሁን ላለንበት ወቅት፤ አንቀጽ 93፤ ለትርጉም የማያሻማ፤ ግልጽ መልስ አለው፡፡ ከዚህ መመዘኛም አንፃር፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕገ መንግሥት ቀውስ የለም። ሶስተኛው መመዘኛም ሆነ አራተኛው መመዘኛ ብዙ ትንታኔ አያስፈልገውም። በሃገራችን በአሁን ስዓት የሽግግር መንግስት ይቋቋም ብንል፤ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ምቹ የፖለቲካ ሁኔታ የለም። ከምንም በላይ ግን፤ ህዝብ የመረጠው የፖለቲካ ሃይል ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ አሁን ያለው መንግስት እንዳይቀጥል የሚያደርግ ምንም ዓይነት አስቸጋሪ የፖለቲካ ክስተት የለም። አራተኛው መመዘኛ የሚለው የመንግስት ተቋም በራሱ ከፈረሰ (ከወደቀ) የሕገ መንግሥት ቀውስ አለ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ ይህንን አያመለክትም። ስለዚህ በየትኛውም መመዘኛ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕገ መንግስት ቀውስ አለ ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ምንም ዓይነት መመዘኛ የለም። አለ ለምትሉ በጭብጥ ተከራከሩ፤ የምትጮኹት እናንተ ብቻ ስለሆናችሁ፤ ክርክራችሁን እውነት አያደርገውምም። ሁሉም እየሰራ ያለው አሁን ባለው ሕገ መንግስት በመሆኑ፤ሕጉን እናክብር፤ ሕገ መንግሥቱ ሲመች ተቀብለን የምንገዛበት ሳይመች አጣጥለን የማንግዛበት ሊሆን አይችልም፡፡ ፈረንጆቹ እንደሚሉት፤ “ በአንድ ጊዜ ኬክህን መብላትም፤ ሳትበላ ማስቀመጥም አትችልም”፡፡ 

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ የሕግ ትምህርቱን በከፊል በጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ፤በከፊል ደግሞ በዩኒቨርስቲ ኦፍ ካሊፎርኒያ የሕግ ፋክልቲ ተምሯል፤ ከዚህ በተጨማሪ፤ በሌሎች የትምህርት ዘርፎች የቅድመ ምረቃ እና የድኅረ ምረቃ ትምህርቶቹን አጠናቋል። ፀሃፊው ለመጣጥፎች፤ የትምህርት ደረጃ መግለጽ ተገቢ አይደለም ብሎ ቢያምንም፤ ለዚህ ውይይት ግን አስፈላጊ ነው ብሎ አምኖበታል።  

 

 

Back to Front Page