Back to Front Page

የኢህአዴግ ጥልቅ ተሀድሶ ከህዝብ ሉአላዊነት አንፃር

 በሚካኤል ምናሴ michillili@gmail.com 

04-16-20

 

 ባለፈው ሳምንት "ኢህአዴግን የገደለው የቡሪዳን አህያ ምንታዌ'" በሚል ርእስ፣ ለኢህአዴግ ሞት ዋናው     ምክንያት ያልኩትን፣ በጨረፍታ ለማሳየት ሞክሬ ነበር(1) ። የአስከሬን ምርመራው እንቀጥልበት። ኢህአዴግን ለህልፈተ ህይወት የዳረገው ሌላው ምክንያት፣ ለህዝብ በገባው ቃልና በሰጠው ምላሽ  መካከል የተፈጠረው የሚያዛጋ ክፍተት ነው። በገባው ቃል የተፈጠረው ተስፋ በለጋስነት እየመዠረጠ፣ ግዜን መግዛት ሲጀምር ነው፣ የመጨረሻው መጀመርያ መታየት የጀመረው። ተስፋ ደግሞ አላቂ "ሸቀጥ" ነው። በተለይ፣ ለህዝብ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ ሰጪ አለመሆኑና፣ ተጠያቂነትን አለማስፈኑ፣የዚህ የተስፋ ችርቸራ ነፀብራቆች ነበሩ።ይህኛው አባዜ ደግሞ፣ኢህአዴግ በህዝብ ሉአላዊነት ላይ የነበረው ፅኑ እምነት እየተሸረሸረ የመሄዱ ውጤት ነበር።የዓላማው ማጠንጠኛና የሚሞትለት የነበረው         ይህ መርሆ፣ የሚፈራውና የሚከላከለው ወደ መሆን እንዴት እንደወረደ ለመረዳት፣ የሚከተለውን  የዒራቃውያንጥንታዊተረት(2)  በተምሳሌትነትእናያለን። ኢህአዴግ በደንብ አርጎ ከቸበቸባቸውና ህዝቡ እምነቱን ከጣለባቸው ተስፋዎች አንዱ፣ እንደ አካል የመታደሱና ኋላም በጥልቀት የመታደሱ ቃልኪዳን አንዱ ነበር።

Videos From Around The World

ተረቱ፣ ይህ የኢህአዴግና የህዝቡ ቃልኪዳን እንዴት ላይመለስ እንደተበጠሰ፣ ኮለል አድርጎ ያሳየናል፡፡ እነሆ፦

አንድ ተኩላ በዕድሜ እያረጀ ሲመጣ፣እንደወትሮው አድኖ መብላት ስላልቻለ፣ከመታዉ የረሀብ ጠኔ እንዴት መላቀቅ እንደሚችል ማሰላሰል ያዘ፡፡ምንም ቢያስብ መፍትሄዉ ስላልተከሰተለት፣ የጥሞና ግዜ እንደሚያስፈልገዉ ተረዳ፡፡ በመሆኑም፣ አንድ ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ፣ በጥልቀት ለማሰብ ወሰነ፡፡በየጫካውና በየበረሀዉ ሲኳትን የነበረ አንድ አንበሳ፣ ተኩላዉ ከነበረበት አከባቢ ደርሶ ወደ ጉድጓዱ “ ቁልቁል ሲመለከት፣ ተኩላዉን ለብቻዉ ቁጭ ብሎ ያየዋል፡፡ የጫካው ንጉስም፣ እዛ ጥልቅ ጉድጓድ  ውስጥ ምን ትሰራለህ?” ሲል ተኩላዉን ጠየቀዉ፡፡ ተኩላዉም፣ ፀጉራም ኮት እየሰራ መሆኑን ይነግረዋል፡፡ አያ አንበሳም፣ “እንግዲህ እንደምታየዉ ወቅቱ ብርዳማ ስለሆነ፣ ለኔም ፀጉራም ኮት ስራልኝ አለዉ”፡፡ ተኩላውም፣ “ጌታዬ ምን ገዶኝ፣ እሰራለሁ እንጂ፣ ግን የበግ ቆዳዎች ያስፈልጉኛል” ይለዋል፡፡ አንበሳዉ  በዚህ ተስማምቶ፣ ለአደን ተሰማራ፡፡ ሁለት የደለቡ ግልገል በጎች አምጥቶም፣ ወደ ጉድጓዱ ወረወረለት፡፡ተኩላው ተቀብሎ ሲያበቃ፣ “እነዚህ ብቻ በቂ ስላልሆኑ፣ ስራው እስኪያልቅ በየቀኑ እየመጣህ አንድ ሁለት በጎች ጣል አድርግልኝ” ይለዋል፡፡ አንበሳውም በየቀኑ አንድ ወይም ሁለት በጎች እየወረወረለት መሄድ ጀመረ፡፡ በመጣ ቁጥር “እህሳ፣ ኮቱን ሰርተህ ጨረስክ?”   ሲለው፣ ተኩላው “ጌቶች፣ የጫካው ንጉስ ኮት መስራት መች እንዲህ በቀላሉ ይሆናል?  ገና በርካታ የበግ ቆዳዎች ያስፈልጉኛል” ይላል፡፡

በኋላ ግን፣ አንበሳዉ በስንት መከራ ያደናቸውን በጎች ይዞ ሲመጣ፣ ተኩላው አንዴ፣ “ከሰሞኑ ጤና አይሰማኝም” ፣ በሌላ ግዜም፣ በዓል ስለነበር አልሰራሁም ፣ የሚሉና ሌሎች ምክንያቶች እየደረደረ  ስላስቸገረዉ፣ በጣም እየተናደደ መጣ፡፡ አንድ ቀን፣ አያ አንበሳ፣ “ስማ ከዚህ በላይ አልታገስህም፣ ከሁለት ቀን በኋላ እመጣለሁ፣ኮቱን ጨርሰህ አዘጋጅተህ ጠብቀኝ” በማለት ተኩላውን አስጠንቅቆት ይሄዳል፡፡

 

በቀጠሮው ቀን አንበሳው ሲመጣ ተኩላው፣ “በቃ አሁን ኮቱ እንዳለቀ ቁጠረው፣ ትንሽ ማበጃጀት ብቻ ነው  የቀረዉ፡፡ ነገ ጧት ገመድ ይዘህ ናና በዛዉ አቀብልሀለሁ” አለዉ፡፡ አንበሳው በማግስቱ መጣና፣እንደተባለዉ ገመዱን ወደ ጉድጓዱ ወረወረለት፡፡ጥቂት ቆይቶም ገመዱን መጎተት ጀመረ፡፡ በገመዱ ጫፍ የታሰረዉ ነገር ከባድ ስለነበረ፣ አንበሳዉ ፈርጣማ ክንዱን ተጠቅሞ ሲጎትተው፣ አዲስ ፀጉራም ኮቱን  የማየት ጉጉት ከፊቱ ይነበብ ነበር፡፡ የክብደቱ ምክንያት ግን ራሱ ተኩላዉ ነበር፡፡ አንበሳዉ ሲያቀርብለት የከረመዉ የበጎች ስጋ እየበላ እጅግ የደለበዉ አያ ተኩላ ከተወሰኑ የበግ ቆዳዎች ጋር ነበር በገመዱ ጫፍ  ታስሮ ወደ ላይ የወጣው፡፡ ያየውን ማመን አቅቶት አፉን ከፍቶ ሲያይ የነበረው አያ አንበሳ፣ ገና ወደ ቀልቡ  ሳይመለስ፣ተኩላው ቆዳዎቹን ፊቱ ላይ ጥሎለት ተፈተለከ፡፡

ራሱን በማዳንና አገሪቱን በማዳን ምንታዌ ተወጥሮ የነበረው ኢህአዴግ እንደ ተኩላው ነበር ያደረገዉ፡፡የወራት ሱባኤ የገባውም ምርጫውን ሳይወስን ነበር። እንደ ተኩላው አንድ ግዜ “እየታደስኩኝ ነዉ” ፣ ሌላ ግዜ ደግሞ “በጥልቅ እየታደስኩኝ ነዉ” እያለ የማያልቅ የመሰለውን ተስፋ ለህዝቡ እየቸረቸረ ግዜ ነበር ሲገዛ የነበረዉ፡፡ በመጨረሻም ህዝቡ የቸረዉን የተስፋ ፍሬ ጨርሶ፣ ቅራፊውን ፊቱ ላይ ወርውሮ ሄደ፡፡ ኢህአዴግ አሁን የለም፣ ህዝቡ ግን አለ፣ ይኖራልም። መመለስ ያለበት ጥያቄ ህዝቡ ከዚህ ምን ተምሯል  የሚልነው።

 

  *** (1)http://m.aigaforum.com/?url=http%3A%2F%2Faigaforum.com %2F&utm_referrer=#3157 (2)E.S. Stevens, Ed. “It Is Not The Lion’s Fur Coat!”, Folktales of Iraq. New York: Dover Publications, Inc. 2006: pp. 83-84.

Back to Front Page