Back to Front Page

ኢህአዴግን የገደለው "የቡሪዳን አህያ ምንታዌ"

ኢህአዴግን የገደለው የቡሪዳን አህያ ምንታዌ

 

በሚካኤል ምናሴ

michillili@gmail.com

ሚያዝያ 4 ቀን 2012 ዓ.ም.

 

ነፍስሄር ኢህአዴግ ከሁለትና ሶስት ዓመት በፊት የነበረበት ሁኔታ ስናየው የቡሪዳን አህያ አሟሟትን ያስታውሰናል። "ባንድ ግዜ በብርቱ ረሀብ የተጎዳ አህያ ከግራና ከቀኙ በአንድ ግዜ እስር ሳር/ጥቅል ቢቀርብለት፣ ወደሱ የቀረበውን እስር ይመርጣል። በህይወት እንዲቆይ የሚያደርገው ሳር በበግራውና በቀኙ በእኩል ርቀት እና መጠን ቢቀመጡለት ግን አህያው አንዱን images (6) (1).jpegመምረጥ ያቅተውና በረሀብ ይሞታል" ይላል የቡሪዳን አህያ ምንታዌ - Buridan's Ass Paradox/Dilemma(1)። 

 

በዚህ ፍልስፍናዊ ሀልዮት መሰረት፣ አህያው፣ የትኛው የበለጠ እንደሚጠቅመው የማመዛዘን ችግር ስላለበት፣ የመወሰን ምንታዌ ቀስፎ ይይዘውና አላላውስ ይለዋል።

 

ይሄ ምንታዌ (dilemma) ስያሜውን ያገኘው ጉዳዩን ካሰላሰለው ዣን ቡሪዳን ከተባለ ፈረንሳዊ ፈላስፋ ነው። ኢህአዴግ የዛኔ የገጠመውም ይህ አይነት ምንታዌ ነበር። የኢህአዴግ አመራር ራሱ ድርጅቱን ማዳንና ኢትዮጵያን ማዳን እኩል ሚዛን ላይ አስቀምጦ ነበር። ያን ለማድረግም በሁለት ግንባሮች እኩል ርቀት መጓዝ፣ እኩል ግዜውን እና ጉልበቱን ማፍሰስ እንዳለበት አምኖ ነበር።

 

Videos From Around The World

ኢህአዴግ እንዲያ ተሽመድምዶ አገሪቷ በአመፆች እየተናጠች በነበረበችት ወቅት አመራሩ እንደ የኮሮና ፅኑ ህመምተኛ ያልጋ ቁራኛ ሆኖም፣ እንደ እባብ አፈር ልሼ እነሳለሁ፣ እንደ ንስር በጥልቀት ታድሼ ኢህአዴግንም ኢትዮጵያንም አድናለሁ(2) ይበለን እንጂ ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አቅቶት ሲዋልል ነበር። ውጤቱም "ሁለት የወደደ ..." ሆነ።

 

የቡሪዳን አህያ ምንታዌ፣ አመክንዮን የሚጋፋ ሀልዮት እንደሆነ የሚቀርብበት ትችት፣ በተለይ ሀልዮቱ ከአህያ ውጪ ባሉት ሁኔታዎች ስናየው ትክክለኛ ትችት እንደሆነ ግልፅ ይሆንልናል። ለምን ቢባል፣ ለሁለቱም ኣማራጮች እኩል ክብደት የሚሰጥ ሰው፣ ስሌት ሳይሰራ፣ በዘፈቀደ አንዱን ቢያነሳ እንኳን፣ ተጠቃሚ ነው የሚሆነው። ኢህአዴግ በአንዱ እንኳን ቢረባረብ፣ እሱን ምናልባትም ሁለቱንም ያተርፍ ነበር። ኢህአዴግ ይህንን ባህሪያዊ አመክንዮ እንኳን መከተል ስላቃተው ሀልዮቱን በሞቱ አድኖታል። የርቀቱን ልኬት አሳስቶም ቢሆን አንዱን አቅርቦ እንዳያይ ደግሞ በመለኪያው ትክክለኛነት ላይ ከልክ በላይ እርግጠኛ ነበር። ኢህአዴግ ሲጀመር ኢትዮጵያን የማዳን መሳርያ እንደነበር ረስቶ ግብ መሆን ከሚገባቸው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ጋር እኩል ማስቀመጡ የብዙ ድክመቶቹ ምንጭ የሆነው "ድርጅታዊ ትምክህት" ነበር።

 

ስለሞተ፣ ስላበቃለት ነገር ማውራት ምን ይጠቅማል የሚል ካለ በህክምናው ዘርፍ የድህረ ሞት ምርመራ (autopsy) ጥቅም ያልተረዳ ነው። የዚህ ዓይነት ምርመራ ዓላማ ሞቱን ያስከተለው ምክንያት፣ የአሟሟቱ አኳኋን፣ ሰውየው ከመሞቱ በፊት የነበረበት የጤና ሁኔታና በህይወት እያለ ተገቢ ምርመራና ህክምና ማግኘት አለማግኘቱ ለማወቅ ነው። ሌሎች ሰዎች ከዚህ ትምህርት ወስደው ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከዛም አልፎ ለሞቱ ተጠያቂ ካለ በህግ እንዲጠየቅ ጭምርም ነው። እንዳውም አለ እያልነው ስለሞተው፣ ለሰራቸው መልካም ነገሮች አልቅሰን ሳንቀብረው እንደ ጉም ስለተነነው ኢህአዴግ፣ ብዙ ምርምርና ጥናት ቢካሄድ ከጥንካሬውም ከጉድለቱም የምንማርበት ብዙ ነገር ይኖረዋል። አሁን በምንገኝበት ድህረ ኢህአዴግም ሁኔታዎች በርካታ አማራጮችን በአገሪቱ ደቅነዋል። ሀላፊነት የሚሰማቸው ሃይሎች ለጋራ ወደፊታችን ሚዛን የሚደፋው አማራጭ በመምረጥ ሙሉ አቅማቸውን በዛ ላይ ማረባረብ ይጠበቅባቸዋል።

---------------------------------------

የመረጃ ምንጮች

(1) Lamport, Leslie. Buridan's Principle. Digital Equipment Corporation Systems Research Center, 2012.

(2) ከኢህአዴግ ስራ አስፈሚ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ፣ ታህሳስ 11 ቀን 2011 ዓ.ም.

 

Back to Front Page