Back to Front Page

በፌደራላዊ ስርዐት ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ የማካሄድ ህጋዊ መሰረት፣ ባልተረጋጉ (fragile) እና የከሸፉ (failed) ሃገራት:

በፌደራላዊ ስርዐት ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ የማካሄድ  ህጋዊ መሰረት፣ ባልተረጋጉ (fragile) እና የከሸፉ (failed) ሃገራት:

 

Esayas Hailemariam (05-03-20)

 

ህገ-መንግስት የህግ እና የፖሊቲካ ሰነድ (legal and political document) በመሆኑና ፖሊቲካ ደግሞ አንፃራዊ (subjective) ስለሆነ፣ በርካታ አከራካሪ ጉዳዮችን ያቀፈ ነው። ሰዎች የተለያየ የፖለቲካ አስተሳሰብ ስለሚኖራቸው፣ በፖለቲካ ከመግባባት ይልቅ፣ የህግ ፅንሰ ሃሳቦችን የተመረኮዘ ምክንያታዊ ውይይት ለመግባባት ይቀላል የሚል እምነት አለኝ። 

 

መንደርደሪያ:

ዩናይትድ ስቴትስ፣ ከአለም ቀደምት እና እጅግ የዳበረ የፌደራላዊ ሥርዐተ-መንግስት አወቃቀርን ከሚከተሉ ሃገራት አንዷ በመሆኗ፣ ከአሜሪካ የህገ-መንግስት ሳይንስ (constitutional jurisprudence) አንፃር፣ የኢትዮጵያን ህገ-መንግስት ከምርጫ መብት አኳያ በመገምገም፣ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የተከሰተውን አከራካሪ የምርጫ ውዝግብ ለመመልከት እንሞክራለን። 

 

Videos From Around The World

 (ሀ) ፌደራሊዝምና የምርጫ ጉዳይ በአሜሪካ:

 

(፩) በ አሜሪካ የፌደራሊዝም ስርአት መስራቾች ሃሳብ:

(the Framers' Legislative Intent):

 

የአሜሪካ የፌደራሊዝም መስራች ተደርገው የሚወሰዱት የአሌክሳንደር ሃሚልተን፣ ጄምስ ማዲሰን እና ጆርጅ ዋሺንግተን ዋና አላማ፣ በአንድ ሃገር ውስጥ የህግና ስርኣት (law & order) መስፈን ከግለሰብ ነፃነት (individual liberty) መከበር ጋር ተጣጥሞ፣ ስልጣን በመአከላዊ መንግስት ብቻ ተከማችቶ አምባገነንነት (tyranny) እንዳይሰፍን በማሰብ ነበር።

 

በ በርካታ የፌደራል ስርአቶች (ጥምር/dual፣ ተባባሪ/cooperative፣ በጀት/fiscal፣ አዲስ/new ወዘተ ...ፌደራሊዝም)፣ የስልጣን ምንጭ ሕዝብ በመሆኑና ለህዝብ ቅርበት ያላቸው ደግሞ የአካባቢ መስተዳድሮች (local governments) ስለሆኑ፣ ከፌደራል መንግስት ይልቅ ክልሎች በይበልጥ የሉአላዊነት መገለጫ ናቸው። የክልሎች ስብስብ የፌደራል መንግስት ስለሚፈጥር፣ የፌደራል መንግስት የክልሎች ፖለቲካዊ ፍጥረት ነው  ማለት ይቻላል። 

 

ባጠቃላይ፣ የአሜሪካ ፌደራሊዝም፣ ክልሎች/ግዛቶች ሰፋ ያለ ስልጣን ለራሳችው በማስቀረት፣ ከመአከላዊ መንግስት ጋር ሚዛናዊ የስልጣን ክፍፍልና ጤናማ መስተጋብር እንዲፈጠር ታልሞ የተቀረፀ ስርኣት ነው። 

 

(፪) በአሜሪካ የፌደራል እና የግዛቶች የስልጣን ክፍፍል:

 

የፌደራል መንግስት ስልጣኖች (powers of the federal government): 

በክልሎች መካከል ንግድ (interstate commerce) እና ከውጭ ሃገራት ጋር የሚደረግ ንግድን (foreign trade) መቆጣጠር፤ ገንዘብ ማተም፤ የፖስታ ቤትን ማስተዳደር፤ ጦርነት ማወጅ፣ ጦር ማደራጀት፤ የውጭ ጉዳይ ማከናወን፣ የፌደራል ፍርድ ቤቶችን ማዋቀር እና የዜግነት ጉዳዮች ላይ መወሰን።

 

የግዛቶች ስልጣኖች /powers of states/:

ምርጫ ማካሄድ፤ የታችኛውን የመንግስት መዋቅር ማቋቋም (establishing local government)፤ የህዝብን ሰላም፣ ጤና እና ደህንነት ማስጠበቅ፤ ሚሊሻ ማደራጀት፤ የህገ-መንግስት ማሻሻያወችን ማፅደቅ (ratification) እና በክልሎች መካከል የሚደረግ ንግድን መቆጣጠር።

 

● የፌደራል እና ግዛቶች ጥምር ስልጣን /concurrent power/:

ግብር መሰብሰብ፤ ህግ ማውጣት እና ማስፈፀም፤ ለባንኮች እና ኮርፖሬሽኖች ፈቃድ መስጠት፤ መሬትን ለህዝብ ጥቅም መውረስ (imminent domain)፤ ፍርድ ቤቶችን ማቋቋም እና ገንዘብ መበደር።

 

(፫) የፌደራል መንግስት ከክልሎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት እና የስልጣን ገደብ መርሆ (principle) መነሻዎች ከዚህ የሚከተሉት ናቸው።

 

  * በግልፅ የተሰጠ ስልጣን /Enumerated Power/:

ከላይ እንደተጠቀሠዉ፣ በግልፅ ለፌደራል መንግስቱ ወይም ለክልሎች የተሰጡት ስልጣኖች በሙሉ የፌደራል መንግስቱ፣ ወይም ለክልሎች ብቻ መሆኑ ግልፅ ነው።   

 

በመሆኑም፣ ምርጫ የማካሄድ፣ ሂደቱንም መቆጣጠርና ማስፈፀም ለክልሎች/ግዛቶች በግልፅ የተሰጠ ስልጣን ሲሆን፣ የብሄራዊ ምርጫ ሂደትን በሚመለከት ኮንግረስ ባወጣው ህግ መሰረት ቀኑ እና አጠቃላይ ሂደቱ እንደሚወስን ያስረዳል። 

 

   ❌ በአሜሪካ ህገ-መንግስት ፕሬዝደንት ምርጫን የማራዘም እና የመቀየር ስልጣን የለውም:

በአሜሪካ ህገ-መንግስት ሃያኛ ማሽሻያ (Twentieth Amendment) መሰረት፣ ፕሬዝደንት ምርጫን የማራዘም፣ የመቀየር፣ ወይም ግዛቶች ምርጫን በተመለከተ ምን ማድረግ እንዳለባቸው የማዘዝ ስልጣን  እንደሌለው በግልፅ ያስረዳል። በ ማሽሻያው እንደተገለፀው፣ የፕሬዝደንቱ እና ምክትል ፕሬዝደንቱ አራት አመት የስራ ዘመን ጥቅምት ፩፩ ቀትር ላይ (January 20 noon) እንደሚያልቅ እና ከዚያ በፊት ድጋሜ ያልተመረጠ ፕሬዝደንት ስልጣን ማስረከብ እንዳለበት በግልፅ ተደንግጓል። 

 

🚨አሜሪካ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላይ ነች፤ ሰባ ሺ አካባቢ ዜጎች በኮሮናቫይረስ ሞተዋል፣ ከተሰረዘው የኢትዮጵያ ምርጫ  በሁለት ወር ልዩነት ውስጥ ግን ብሄራዊ ምርጫ ታካሂዳለች:: የዜጎች ጤናና ደህንነት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ጥርጥር የለውም፤  በሌላ መልኩ፣ ማንኛውም የመንግስት እርምጃ (ለዜጎች ጥቅምም ቢሆን)ህግን በሚጥስ መልኩ መተግበር የለበትም። 

 

የአሜሪካ ፕሬዝደንት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ (state of emergency) ሰበብ ምርጫን የማራዘም ስልጣን ይኖረዋል ወይ ለሚለው፣ በህገ-መንግስቱ ይሄን በሚመለከት ለፕሬዝደንቱ ስልጣን የሚሰጥ አንድም የህግ ድንጋጌ የለም።

 

ከጉዳዩ ጋር ተዛማች በሆነው የ" Youngstown Sheet & Tube Co. v. Sawyer [1952]" ዉሳኔ መሰረት:

 

በኮሪያ ጦርነት ጊዜ የአሜሪካ ዜጎች ስራ ካቆሙ ሊፈጠር የሚችለውን የብረጥ እጥረትን በመፍራት (ብረት ጦር መሳሪያ ለማምረት ይፈለግ ስለነበር) ፕሬዝደንት ሄሪ ትሩማን በአስቸኳይ ጊዜ እርምጃ ሰበብ የሃገሪቱን የብረት ማምረቻወች ለመውረስ ያወጣውን የፕሬዝደንቱን ትእዛዝ (executive order) ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሙሉ በሙሉ ውድቅ በማድረጉ፣ ፕሬዝደንት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጠቅሞ ምርጫ ማራዘም እንደማይችል ያ ዉሳኔ የህግ መሰረት (case precedent) ሊሆን ችሏል::

 

የዜጎች መሰረታዊ ዴሞክራሲያዊ መብት የሆነው የመምረጥና መመረጥ መብት ይቅርና፣ የምርት ተቋማትን በ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሰበብ ማገድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን የአሜሪካ ህግ እዚህ ላይ የማያወላዳ አቋም አለው።  

 

በመጥፎም ይሁን ጥሩ ጊዜ ህግ የማውጣት ስልጣን የኮንግረስ እንጂ የፕሬዝደንቱ እንዳልሆነና፣ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ተጠቅሞ ካላግባብ ስልጣንን መጠቀም ከሃገሪቱ መስራች አባቶች/እናቶች አላማ ጋር እንደሚጋጭ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንዲህ ብሎ ነበር የወሰነው:

 

 “The Founders of this Nation entrusted the lawmaking power to the Congress alone in both good and bad times. It would do no good to recall the historical events, the fears of power, and the hopes for freedom that lay behind their choice.”

 

 በተለይ፣ ዳኛ ሮበረት ጃክሰን (Justice Robert Jackson) እንዲህ ነበር ያሉት፥ "emergency powers would tend to kindle emergencies." 'አስቸኳይ ጊዜ ስልጣን/እርምጃዎች ሌላ አስቸኳይ ጊዜ ችግሮች ሊፈጥሩ ይችላሉ' በማለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚያመጣውን ጣጣ አስረድተዋል።

 

  * ያልተጠቀሱ/የተተው ስልጣኖች (Implied Powers):

 

በግልፅ ለፌደራል መንግስቱ ከተሰጡት ስልጥኖች ውጭ ያሉት ደግሞ ለክልል መንግስታት የተተው ስልጣኖች ናቸው ማለት ነው። ይህ የሚያሳየው፣ ክልሎች በግልፅ ከተሰጣችው ስልጣንና ሉኣላዊነት በተጨማሪ በፌደራሉ ህገ-መንግስት ያልተከለከሉ ጎዳዮች ላይ ጭምር ሰፊ ስልጣን እንዳላቸው ነው። የፌደራል  ስርዐቱ መስራቾች አላማም ለፌደራል መንግስት ውስን ስልጣን መስጠት ብቻ ሳይሆን፣ የስልጣን ምንጭ የሆኑት ክልሎች  ሰፋ ያለ ሉኣላዊነት እንዳላቸው ለማረጋገጥም ጭምር ነው። 

 

የፌደራል መንግስት አገር ማስተዳደር ካልቻለ፣ ክልሎች ከፌደራል መንግስቱ ጋር የገቡትን የማህበራዊ ውል (social contract) ከተጣሰ፣ መአከላዊው መንግስት የክልሎችን ጥቅም ማስከበር ካቃተው ወይም ካልፈለገ፣ ክልሎች የራሳቸውን ምርጫ ከማካሄድ ጀምሮ፣ ህጋዊና ፖሊቲካዊ አማራጮችን ከመጠቀም የሚያግዳቸው ምንም ምክንያት የለም።  

 

ከምርጫ በተጓዳኝ፣ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ክልሎች/ግዛቶች የሚበጃቸውን ውሳኔ የማሳለፍ መብታቸው ሰፋ ያለ እንደሆነ በርካታ የቅርብ ጊዜ አጋጣሚዎችን ማንሳት ይቻላል። 

 

  የካሊፎርኒያ ግዛት ኮሮናቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የፌደራል መንግስቱን ህግ አልተቃረነም:

በቅርብ ጊዜ አንዳንድ የዩናትድ ስቴትስ ግዛቶች የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከፌደራል መንግስቱ አፈንግጠው በራሳቸው የህግ መወሰኛ ምክርት ቤት (Legislative Assembly) አፅድቀው ያስፈፀሟቸው ህጎች ክልሎች የዜጎቻቸውን ጤንነትና ደህንነት የመጠበቅ አንዱ የሉአላዊነታቸው መገለጫ ነው። 

 

የካሊፎርኒያ ግዛት ህገ-መንግስትን በመጠቀም የካሊፎርኒያ ገዢ ጋቪን ኒውሰም፣ ፴፪ (32) ትእዛዞችን (orders) ያለ ፕሬዝደንት ትራምፕ (የፌደራል መንግስት) ይሁንታ፣ አፅድቆ እንዲፈፀሙ አድርጓል፤ የፌደራል መንግስትም የክልሎችን ስልጣን ወሰን ስለሚረዳ የፖሊካ ውዝግብ ውስጥ አልገቡም። 

 

በካሊፎርኒያ ህገ መንግስት የአደጋ አገልግሎቶች ድንጋጌ (Emergency Services Act) መሰረት፣ የነዋሪዎችን ሰላም፣ ጤና እና ደህንነት ለማሰጠበቅ ግዛቷ የራሷን ህግ በማፅደቅ የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የራሷን መንገድ ተከትላለች። 

 

የምእራብ ዩናይትድ ስቴትስ ህብረት (Western United States Pact) የፌደራል መንግስቱን አላስቆጣም፣ የፌደራል ህግም አልጣሰም፤ 

 

ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ፣ አምስት የምእራብ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች (ካሊፎርኒያ፣ ኔቫዳ፣ ኦሬገን ዋሽንግተን ስቴት እና ኮሎራዶ)፣ የፌደራል መንግስቱ የኮሮናቫይረስን ለመከላከል የሚያደርገው ጥረት ስላላረካቸው፣ የምእራብ ዩናይትድ ስቴትስ ግዛቶች ህብረትን  መስርተዋል። ይህ የሚያሳየን የክልል ግዛቶች የነዋሪዎቻቸው ህይወት አደጋ ላይ በወደቀ ጊዜ ያለ ፌደራል መንግስቱ ቡራኬ ይበጃል ያሉትን ህጋዊ መንገድ መከተል እንደሚችሉ እና ቀጥተኛ ተጠሪነታቸው ለግዛቱ ህዝብ መሆኑን ነው።

 

ከዚህ ጋ በተያያዘ፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን የህግ ባለሙያዎች እና የፖሊቲካ ምሁራን የትግራይ ክልል፣ የፌደራሉን መንግስት ይሁንታ ሳያገኝ በራሱ ተነሳሺነት የኮሮናቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ላይ ሰፊ ክርክር ሲያካሂዱ ታዝቤያለሁ። 

 

ክልሎች፣ የነዋሪዎቻቸውን ደህንነትና ጤና ለመጠበቅ፣  ህገ-መንግስታቸውን ተንተርሰው፣ የፌደራል መንግስቱ ይሁንታና ፈቃድ ሳያስፈልጋቸው፣ ክልሉን ብሎም ሃገሪቱን አደጋ ላይ ሊጥል በሚችል የጤና ቀውስ ሲፈጠር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የማወጅ ህጋዊ መብታቸው ብዙም እንደማያከራክር በርካታ ማስረጃወችን ማቅረብ ይቻላል።

 

 (ለ) ፌደራሊዝምና የምርጫ ጉዳይ በኢትዮጵያ:

የ ኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት ጉዳይ ሲነሳ፣ ሁለት መሰረታዊ የሃሳብ ልዩነት ያላቸው አካላት አሉ። የመጀመሪያዎቹ ህገ-መንግስቱን ከነ ችግሩ የሚቀበሉት  ሲሆኑ፣ ሌላው ክፍል ደግሞ ህገ-መንግስቱ ፈፅሞ አይወክለንም ብለው የሚያምኑት ናቸው ። የዚህ ፅሁፍ አላማ የትኛው ትክክል ነው የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ባለመሆኑ፣ በዚህ ሰአት ሃገሪቱ እየተዳደረችበት ያለውን ሕገ-መንግስት ታሳቢ በማድረግ ነው ሃሳቤን የምሰነዝረው። 

 

የህገ-መንግስቱ ቅቡልነት (legitimacy) ላይ ጥያቄ ያለው አካል ጥያቄው ተገቢ ሊሆን ቢችልም፣ በአንድ ጎን  ህገ-መንግስቱን ፈፅሞ ሳይቀበሉ  በሌላ ጎን ህገ-መንግስቱን ጠቅሶ ራሱን ህገ-መንግቱን ለማሻሻል የሚቻልበት የህግ አገባብ ይኖራል ብዬ አላምንም፤ ምክንያቱም፣ ህጋዊነቱን ካልተቀበልነውና ሕገ-ወጥ ከሆነ ነገር ተነስተን ህጋዊ ውጤት ያለው ነገር ማድረግ ስለማይቻል::

 

(፩) የስልጣን ምንጭ በኢትዮጵያ ህግ: 

 

● ፌደራል /federal/:

የ ኢትዮጵያ ህገ-መንግስት መግቢያ (Preamble)፤ "እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች፥ በሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም፣ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን…[ህዳግ/omitted]፣ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፣…[ህዳግ/omitted] በነፃ ፍላጎታችን በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማኀበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤... [ህዳግ/omitted]... እንዲወክሉን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት ...አጽድቀነዋል።" ይላል። 

 

ልክ እንደ አሜሪካና ሌሎች የፈደራል ስርአቶች ሁሉ፣  በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ስርአት መሰረታዊ ሰነድ (basic law) ተደርጎ በሚቆጠረው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ-መንግስትም የስልጣንና ሉላዊነት ምንጭ ህዝብ፣ ፌደሬሽኑም በኢትዮጵያውያን መፈቃቀድ የተመሰረተ ህብረት እንደመሆኑ መጠን የህገ-መንግስቱ ህልውና በኢትዮጵያውያን ይሁንታ  እንደሚወሰን ይጠቁማል። 

 

በኢፌዴሪ ህገ መንግስት አንቀፅ ፴፰ - ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሕዝብ አስተዳደር ጉዳይ የመሳተፍ፣ ዕድሜው ፲፰ ዓመት ሲሞላ የመምረጥ መብት እንዳለው፣ እንዲሁም በአንቀፅ ፴፱ መሰረት ማንኛውም የኢትዮጵያዊ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን መብቱ ተደንግጓል። 

 

● ክልሎች /states/:

 

 * በትግራይ ክልል ህገ- መንግስት አንቀፅ ፰ መሰረት፣ የክልሉ ህዝብ በክልሉ ጉዳይ ላይ የሉአላዊነት ባለቤት እንደሆነ በመግለፅ፣ በአንቀፅ ፰ ንኡስ አንቀፅ ፪ መሰረት ደግሞ ይህ ሉአላዊነት የሚገለፀው  የክልሉ ነዋሪዎች በቀጥተኛ ዴሞክራሲያዊ ሂደት በመረጧቸው ተወካዮቻቸው እንደሆነ በማስረዳት፣ አንቀፅ ፱ (፩) ደግሞ ይህ መብት በምንም መልኩ ሊገደብ እንደማይችል ያስረግጣል። 

 

* በተመሳሳይ፣ በአማራ ክልል ህገ-መንግስት ምእራፍ ሁለት፣ አንቀፅ ፰ ንኡስ አንቀፅ ፪ መሰረት፣ የክልሉ ህዝብ የሉአላዊ ስልጣን ባለቤት እንደሆነና፣ ይህ ሉአላዊነት የሚገለፀው ደግሞ፣ በሚመርጧቸው ተወካዮች እና ራሳቸው በቀጥታ በሚያደርጉት ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ እንደሆነ ይገልፃል። 

 

ባጭሩ፣ ምርጫ የማካሄድ መብትን በሚመለከት፣ የፌደራሉም ሆነ የክልል ህገ-መንግስቶች በግልፅ እንዳሰፈሩት፣ ክልሎች  በምርጫ ጉዳይ የራሳቸውን ጉዳይ የመወሰን ስልጣናቸው በምንም መልኩ ገደብ ሊጣልበት እንደማይችልና የፌደራል መንግስቱ አገር አቀፍ ምርጫን በሚመለከት የሚወስደው ማናቸውም እርምጃ የክልሎችን ጥቅምና ሉአላዊነት የሚፃረር ከሆነ ክልሎች ውድቅ የማድረግ ህጋዊ መሰረት እንዳላቸው ሊታወቅ ይገባል (የፌደራል ህገ መንግስቱ  የህዝቦችን ሉአላዊነት ለማስጠበቅ እንጂ ለማሳነስ ታስቦ የተረቀቀ ስላልሆነ)። 

 

ከዚህ በፊት ስለምርጫ መራዘምና የፓርላማው እጣፈንታ ላይ የፃፍኩትን በመዋስ፤ በሕገ- መንግስቱ አንቀፅ ፶፰ (፪) መሰረት፣ የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ሲጠናቀቅ ምክር  ቤቱ እንደሚበተን ይገልፃል። በመሆኑም፣ ከ ጥቅምት ፪ ሺ ፲፪ ጀምሮ ፓርላማው ህጋዊ የስራ ዘመኑ ስለሚያከትም ሌላ ምርጫ ተካሂዶ የሕዝብ ተወካዮች የሚተኩበት ጊዜ ቅርብ አይሆንም። ፓርላማ ከሌለ፣ የሃገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስቴር መሾም ሹመቱንም ማፅደቅ እንደማይቻል ግልፅ ነው (አንድም ፓርላማው ስለማይኖር በሌላ መልኩ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነዉ ግለሰብ የፓርላማ አባል መሆን ስላለበትና ምርጫ አካሂዶ የፓርማ አባላት በወቅቱ በመምረጥ ጠቅላይ ሚኒስቴር መምረጥ ስለማይቻል)። 

 

 (፪) የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ምርጫ ማድረግ ካልቻለ፣ ካልፈገ፣ ወይም ከህገ-መንግስቱ ድንጋዎች ዉጭ ስልጣን ካራዘመስ? 

 

የመምረጥና መመረጥ መብት ወሳኝ ዴሞክራሲያዊ መብት መሆኑ ግልፅ ነው።

በኢትዮጵያ ህገ መንግስት አንቀጽ ፴፰ (፩) መሰረት "ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በቀለም፣ በዘር፣ በብሔር፣ በብሔረሰብ፣ በጾታ፣በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ ወይም በሌላ አመለከካከት ወይም በሌላ አቋም ላይ የተመሰረተ ልዩነት ሳይደረግበት… በቀጥታ እና በነጻነት በመረጣቸው ተወካዮች አማካኝነት በሕዝብ ጉዳይ አስተዳደር የመሳተፍ" እንዳለው ይገልፃል። 

 

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ጨምሮ ማናቸውም የአስፈፃሚ አካሉ ፖሊቲካዊ እርምጃዎች  የመምረጥና መመረጥ መብትን ሊገድብ እንደማይገባ፣ የኢትዮጵያ ህገ- መንግስት ምንጭ በሗላም አካል በሆነው፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለማቀፍ  ሰብአብዊና ፖለቲካዊ መብቶች ቃልኪዳን (ICCPR) ላይ በግልፅ ተቀምጧል። 

 

"ICCPR  PART I, Article 1 (1). All peoples have the right of self-determination. By virtue of that right they freely determine their political status and freely pursue their economic, social and cultural development."  

 

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  ለዜጎች ደህንነትና ጤና ሲባል መፈፀሙ አስፈላጊነቱ ባያከራክርም፣ የህዝብ መሰረታዊ በራስ ጉዳይ የመወሰን መብትን አደጋ ላይ በሚጥል፣ ስልጣንን ካለ አገባብ ለመጠቀሚያነት፣ ህግን ለመጣስ ሰበብ መሆን ግን የለበትም። 

 

(፫) አማራጭ (Plan B):

 

የመምረጥና መመረጥ መብት አደጋ ላይ ሲወድቅ የክልሎች ራስን የማዳን ህገ-መንግስታዊ፣ ሞራላዊ እና ፖሊቲካዊ መብት: 

 

✅Stable, ⛔Fragile and ❌Failed States, and Electoral Democracy- የተረጋጉ፣ በመፍረስ ላይ ያሉና የከሸፉ ሃገራት፣ እና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ: 

 

ኢትዮጵያ እንደ ስዊድንና ፊንላንድ የተረጋጋች ሃገር ብትሆን ኖሮ፣ ምርጫና ህገ መንግስት የመወያያ አጀንዳ ባልሆኑ ነበር። ወደ ዝርዝር ጉዳዩ ከመግባታችን በፊት፣ አጣብቂኝ ውስጥ ያሉ ሃገራት የተጋረጠባቸው አደጋ በሚለካበት አለማቀፍ ቀመር (CAST Framework) የኢትዮጵያን ሁኔታ እንገምግም። 

 

Security Apparatus (የደህንነት መዋቅር);

Factionalized Elites (በአንጃ የተቧደኑ ልሂቃን);

Group Grievance (የቡድን ቅሬታ/አቤቱታ);

Economic Decline and Property (የምጣኔ ሃብት ዝቅጠት እና ድህነት);

Uneven Economic Development (ያልተመጣጠነ የምጣኔ ሃብት እድገት);

Human Flight and Brain Drain (የሰው ሃይል እና የምሁራን ፍልሰት);

State Legitimacy (የመንግስት ቅቡልነት);

Public Services (የህዝብ አገልግሎቶች);

Human Rights and Rule of Law (የሰብአዊ መብቶች እና የህግ የበላይነት);

Demographic Pressures (የህዝብ አሰፋፈር ጫናዎች);

Refugees and Internally Displaced Persons 

 (ስደተኞችና በሃገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች);

External Intervention (የውጭ ጣልቃ-ገብነት). 

 

ከላይ በተዘረዘሩት የአለማቀፍ  መስፈርቶች መሰረት ኢትዮጵያን ስንገመገም፣ ከጉዳዩ ውስብስብነትና የያንዳንዱ ግለሰብ የፖሊቲካ አመለካከት አኳያ፣ አንዳንዶቹ  ጉዳዮች አከራካሪ ሊሆኑ ቢችሉም፣ ተጨባጭ የሰብአብአዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች፣ የአይን እማኞች፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን አውታሮች ዘገባ እንደሚያሳየው:

 

የጋዜጠኞች ለብቀላ እስራት መዳረግ፤ 

 

ገለልተኛ ፍርድ ቤት (independent judiciary) ያለመኖር፣ 

 

ከፍተኛ የጦር መኮንኖች፣ የክልል ፕሬዝደንትና ታላቅ የልማት መርሃግብር ይመራ የነበረ እውቅ መሃንዲ ደመከልብ የሆኑበት ልል የደህነንት ተቋም (loose security apparatus)፤ 

 

በማህበራዊ ድረገፅ ከምክንያታዊ ውይይት ይልቅ በጎሳ፣ ነገድና ብሄር የተቧደኑ ልሂቃን መብዛት፤

 

ከጫፍ እስከ ጫፍ በዘርፈ ብዙ ጥያቄዎች የተወጠረ ነገር ግን ጥያቄዎቹ ያልተፈቱለት ህዝብ፣

 

የምጣኔ ሃብት ዝቅጠት ብቻ ሳይሆን የዋጋ ግሽበት (inflation) በታሪክ ሆኖ ወደማያውቀው ፳፪ (22%) ፐርሰንት መድረሥ፤ 

 

🚫በሌላ መልኩ የድህነት እየተባብሰ መምጣት፤

 

🚫በሃብታምና ድሃ መካከል ያለው ልዩነት መስፋት፤

 

🚫የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰት (brain drain)፤ 

 

🚫ከላይ በተጠቀሱት ፖሊቲካዊ ችግሮች ሳቢያ የመንግስት ቅቡልነት (legitimacy) መቀነስ፤

 

  የህዝብ አገልግሎቶች ተገቢ እና የተቀላጠፈ  አገልግሎት መስጠት ያለመቻል:- በተቃራኒ የሙስና ብልሹ አሠራር    መንሰራፋት፤

 

🚫ዜጎች በጠራራ ፀሃይ ፖሊስ ፊት መሰቀል (extra-judicial killing)፤

 

🚫የባንኮች መዘረፍ እና የዘራፊዎች በህግ አለመጠየቅ፤

 

🚫የህግ የበላይነት ያለመከበር፤

 

🚫በክልሎችና ፌደራል መንግስት መካከል ለሚነሱ የህዝብ አሰፋፈርና የመሬት ጥያቄዎችን ህጋዊ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ለፖለቲካ ፍጆታ መዋል፤

 

🚫ከሶሪያና ደቡብ ሱዳን በመቀጠል ከአለም በሃገር ውስጥ ተፈናቃይ (IDP) ቁጥር ከመጀመሪያዎቹ ተርታ መሰለፍ፤

 

🚫የሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በመካከለኛው ምስራቅ አረብ ሃገራት እና ጎረቤት ሃገራት መዘወር፤

 

ወሳኝ የልማት መርሃ ግብሮች (flagship development projects) ሆን ተብለው እንዲያዘግሙ እየተደረጉ ያለበትን ሁኔታ ስንታዘብ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሶሪያ የከሸፈች (failed state) ባትሆንም፣ በርግጥም የመፍረስ አደጋ ከሚያጋሰጋቸው ሃገራት (fragile states) ተርታ እየተሰለፈች እንደሆነ ግልፅ ነው። 

 

የህገ-መንግስት ኪሳራ (constitutional crisis) በተጋረጠበት፣ መረጋጋት ባልሰፈነበት እና ቅቡልነቱ (legitimacy) ጥያቄ ውስጥ የወደቀ ስርኣት የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት ለመገደብ የሚያስችል የህግም የሞራልም መሰረት የውለም።

 

የመምረጥና መመረጥ መብት የዴሞክራሲ መሰረት ነው። በመሆኑም፣ በበርካታ ሃገራት ህጎች የመምረጥና መመረጥ መብትን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመገደብ መሞከር በከባድ የአገር ክህደት ወንጀል (treason) እንደሚያስከስስ በመደንገግ ለጉዳዩ ክብደት ይሰጣሉ ። በሌላ መልኩ፣ የአንድ ሃገር ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ምርጫን ተጠቅሞ፣ በቀጣይ የሚያስተዳድሩንት ተወካዮች እንዳይመርጥ፣ የ አስተዳደር ስርዐት እንዲስተጓጎል የተለያዩ እንቅፋቶችን እና የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ አሻጥር (sabotage) መጠቀም ህገ-ወጥ ነው። 

 

በአሁኑ ሰአት ኢትዪጵያን የሚታስተዳድረው መንግስት፣ በቀጥታ በኢትዮጵያውያኖች ተመርጦ ሳይሆን፣ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተረፈውን የስልጣን ዘመን (leftover power) ለመጨረስ እንደ የአደራ መንግስት (caretaker government) የሚቆጠር አስተዳደር ነው። የአደራ መንግስት መሰረታዊ የህገ መንግስት ድንጋጌዎችን መጣስ ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ (directive) እንኳ የማውጣት ስልጣኑ እጅግ ውሱን ነው።

 

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ተቋማዊ ገለልተኛነት አከራካሪነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የስልጣን ዘመኑ ማለቅ ያሳሰበው አስተዳደር ያቀረበው የሞተን ጉዳይ ለማዳን የምርጫ ቦርድን እጅ ጠምዞ ያስወጣው "ህግ" የህግ መሰረት የሌለው ፖለቲካዊ ውሳኔ በቀጣይ በሃገሪቱ የሚደረጉ የምርጫ ሂደቶች ላይ አሉታዊ ጎን አለው። 

 

የፌደራል መንግስቱ በማናቸውም ምክንያት ብሄራዊ ምርጫ ማድረግ ካልቻለ፣ ካልፈለገ፣ የህግ ክፍተቶችን ተጠቅሞ ስልጣን ካራዘመ፣ ወይም "የህግ ክፍተት" በመፈለግ ለመሸፋፈን ወደሗላ ተመልሶ ሌላ ጠጋኝ ህግ (expost facto law) ስላወጣ፣ ክልሎች ህጋቸው በሚፈቅደው አገባብ የአካባቢ ምርጫ (local election) በማድረግ የመንግስት አስተዳደራቸውን የማስቀጠል ህጋዊ መብት ይኖራቸዋል።

 

 

 

Back to Front Page