Back to Front Page

በህገመንግስታችን የስልጣን ማሳጠሪያ አንቀፅ፣ ለስልጣን ማራዘምያ መጠቀም ተገቢነት የለውም

በህገመንግስታችን የስልጣን ማሳጠሪያ አንቀፅ፣ ለስልጣን ማራዘምያ መጠቀም ተገቢነት የለውም

 

ህዳሴ ኢትዮጵያ

ሚያዝያ 22፣ 2012 ዓ.ም.

 

 

ግልፅ ደብዳቤ

         ለጠ/ሚ ፅ/ቤት

         ለሁሉም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች

         ለምርጫ ቦርድ

         ለመከላከያ ሰራዊታችን

         ለሁሉም ነፃ ሚድያዎች

 

መንግስት በኮቪዲ-19 ምክንያት የ2012 ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ ችግሩን ህገመንግስታዊ ስርኣቱን በማያፋልስ መልኩ ለመፍታት የሚያስችል ያላቸውን 4 አማራጮችን አቅርቧል፡፡ እነዚ ኣማራጭ ሃሳቦች የሚከተሉትን ናቸው፡፡

1.   የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መበተን

2.   አስቾኳይ አዋጅ ማወጅ

3.   ህገመንግስቱ ማሻሻል

4.   የህገመንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ናቸው

በነዚህ አማራጮች ያላቸውን ህገመንግስታዊ እንድምታዎች ምንድን ነው?

ወደዚህ ሁኔታ ለመግባት የተገደድነው ዋናው ምክንያት የመንግስት ችግር ነው፡፡ ምክንያቱ መንግስት ገና ወደ ስልጣን እንደ መጣ ሁሉም እንቅስቃሴው ምርጫ በማራዘም የስልጣን ጊዜው ለማቆየት በማሰብ የሚደረጉ ስለነበር፡፡

አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በትክክል እውነተኛ ለአገር እና ለህዝብ አሳቢ መንግስት ቢሆን ኑሮ ኢህአዴግ አብቅቶለታል በተባለበት ወቅት ነበር ፓርላማው በመበተን በ6 ወራት ውስጥ ወደ ምርጫ መግባት የነበረበት፡፡ ይሁንና ይህ ሀይልለስልጣን ካለው አተያይ የተነሳ፣ ለስልጣኑ ዋስትና በማጣቱ ምክንያት ህጋዊው ኢህአዴግ በማፍረስ አዲስ ብልፅግና ፓርቲ በማቋቋም የህጋዊው ኢህአዴግ ስልጣን ተቆጣጥሮ እስከ አሁን ድረስ ዘልቋል፡፡ የገዢውን ፓርቲ የኢህአዴግ ስልጣን ይዞ መቆየት ስለመረጠ ምርጫ ማካሄድ አልፈለገም፡፡ በዚህ ጉዳይ ጠ/ሚ በርካታ አከራካሪ መለስተኛ የሕግ ግድፈቶች ወይም ጥሰቶች እየፈፀሙ ያሉ ቢሆኑም፣ የኢህአዴግ ስልጣን የሚያበቃበት ጊዜ /ሰኔ 2012 በመሆኑ/ በመቃረቡ ለአገር አንድነት እንዲሁም ለሰላም እና መረጋጋት ሲባል ግድፈቶቹ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በቻይነት እና በትእግስት እየታለፈ ይገኛል፡፡

Videos From Around The World

እንደ አጋጣሚ ሆኖ ይህ የኮቪዲ-19 ወረርሽኝ በማጋጠሙ ምክንያት ምርጫውን ለማካሄድ እንደማይቻል መግባባት ላይ ሊደረስ የሚችል ሓቅ ነው፡፡ በእርግጥ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮቪዲ-19 ምክንያት የ2013 ዓ.ም ምርጫ የማራዘሙ ፍላጎት እንደሌለ በታቀደለት ጊዜ እንደሚካሄድ አሳውቋል፡፡ ስለዚ ኮቪዲ-19 ለአሜሪካ ምርጫን ለማራዘም ምክንያት ሊሆን አይችልም፡፡ ለምን ቢባል አሜሪካ ለበርካታ ዘመናት ምርጫ የማካሄድ ስርዓት ዘርግታ ከፍተኛ የብቃት ደረጃ የደረሰች በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ያደረገች በመሆኗ በኮቪዲ-19 ምንም እንቅፋት እንደማይደርሳት አስታውቃለች፡፡ ይሁንና ኮቪዲ-19 ለኢትዮጵያም እንደ አሜሪካ ምክንያት ኣይሆንም ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ ምርጫ ስርዓት ከዘረጋች ጥቂት አስርት ዓመታት ወይም 5 ዙር ብቻ ነው ያደረገችው፡፡ የተቋሙ ብቃት ገና በዝቅተኛ ደረጃ ያለ ነው፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ገና አልተጀመረም፣ የሰዉ የምርጫ አስተሳሰብ ገና አልተገነባም ስለዚህ ያለው አማራጭ በተለመደው የምርጫ ኣካሄድ መሄድ ነው፡፡ ይሁንና በአሁኑ ወቅት በተለመደው የምርጫ ኣካሄድ ለመሄድ መሞከር ማለት በኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ህዝብን መጨረስ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የኮቪዲ-19 ወረርሽኙ እስኪጠፋ ወይም የህዝብን ዕልቂት በማያስከትልበት ደረጃ እስኪ ደርስ ድረስ ምርጫው ማራዘሙ የግድ ይላል፡፡ በዚህ ሁሉም ዜጋ ሊስማማበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድሮው አንድነቱ አጠናክሮ በህገመንግስቱ መሰረት ለግንቦት 2012 ምርጫ ለማካሄድ አቅዶ ሙሉ ዝግጅቱን ቢጨርስ ኑሮም ቢሆን ይህ ምርጫ በኮቪዲ-19 ምክንያት ሊካሄድ አይችልም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚ ህገመንግስታዊ ስርዓቱ በማያፋልስ መልኩ ይህን ጉዳይ እንዴት እናድርገው የሚል ጉዳይ በማንሳት ለምክክር ፓርቲዎችን መጋበዝ በጣም ዘግይቶ የተደረገ ቢሆንም መልካም ነው ለማለት እወዳሎህ፡፡ ወደ ዋናው አጀንዳ ለመግባት በቀረቡ አማራጮች ላይ የህገመንግስት ጥሰቶች የሚታዩባቸው ነገሮች ስላሉ መስተካከል ኣለበት ከሚል መነሻ ይህ ፅሁፍ ሳዘጋጅ የዜግነት ግዴታዬ በመወጣት ስሜት ነው፡፡

1. የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት መበተን

የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የመበተን ጉዳይ እንደ አማራጭ ሊቀርብ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ ህገመንግስቱ እንደ ሚደነግገው አንድን ፓርላማ ሊበተን የሚችለው በሶስት ምክንያቶች ናቸው፡፡ ሁለቱ ምክንያቶች በልዩ ሁኔታ ሲሆኑ ሶስተኛው ምክንያት ግን የስራ ዘመኑ በማለቁ ምክንያት ነው፡፡ ሶስቱም ምክንያቶች ዘርዘር አድርገን እንያቸው፡-

ሀ/ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለመበተን አንደኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው

በህገመንግስቱ አንቀፅ 60 ንኡስ አንቀፅ 1 መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክርቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል ይላል፡፡ እዚህ ላይም በአተረጓጎም መዛነፍ ይታያሉ፡፡ እንዴት የሚል ጥያቄ ለመመለስ ይህ አንቀፅ የተቀመጠው የአንድን ምክርቤት የስራ ዘመን በማጠናቀቅ ላይ ላለ ፓርላማ ሳይሆን የስራ ዘመኑ ለማጠናቀቅ ረዘም ያለ ጊዜ ላለው ፓርላማ ነው፡፡ ምክንያቱ የስራ ዘመን በማጠናቀቅ ላይ ያለ ምክርቤት የግድ አዲስ ምርጫ በግንቦት ውስጥ ማድረግ ስላለበት፡፡ እዚህ ብልፅግና ፓርቲ እንደ አከራካሪ ሀሳብ የሚያስቀምጠው የስልጣን ዘመን ከማለቁ በፊት የሚለው ሀረግ በመውሰድ፤ ሲተረጉም እስከ መስከረም ወይም እስከ ጳጉሜን 5፣ 2012 ዓ.ም. ያለው ጊዜ ማለት ነው ብሎ ጳጉሜን 2012 ዓ.ም. ውስጥ ምክርቤቱ ለመበተን ሀሳብ እያቀረበ ይገኛል፡፡

የዚህ ትርጉም መሰረታዊ ችግር አንቀፁን በተሟላ ያለመውሰድ ነው፡፡ ትክክለኛ ትርጉሙ ይህ አንቀስ ያስፈለገበት ምክንያት ያለውን መንግስት አሳማኝ በሆነ ምክንያት የግድ መደበኛው የምርጫ ጊዜ (ማለትም በአሁኑ ጉዳይ ግንቦት 2012 ዓ.ም) ከመድረሱ በፊት መቀየር አለበት የሚል ግምገማ ከተደረሰ ቶሎ ወደ ምርጫ ተገብቶ ያለውን መንግስት ለመቀየር በማሰብ ነው፡፡

ታድያ ይህ አንቀፅ መቼ ነው መጠቀም ያለብን?

የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ይህ አንቀፅ መጠቀም ያለብን ከግንቦት ወር በፊት ምርጫ የምናካሂድበት ሁኔታ ካለ ብቻ ነው፡፡ ዓላማውም የስልጣን ጊዜ ከማለቁ በፊት ምርጫ ማካሄድ ካስፈለገ ብቻ ነው፡፡ አሁን በብልፅግና ፓርቲ እየቀረበ ያለው ሃሳብ ግን ለስልጣን ጊዜ ማሳጠርያ የተቀመጠ አንቀፅ ለስልጣን ጊዜ ማራዘምያ ለመጠቀም ነው፡፡ ብልፅግና ፓርቲ በትክክለኘኛ ግምገማ ኢህአዴግ በስብሷል መፍረስ ያለበት እና መተካት ያለበት ድርጅት ነው የሚል እምነት ቢኖሮው እና የአገራችን ህገመንግስት አስከብሮ መሄድ ከፈለከ ሕገመንግስቱ ትክክለኛ መፍትሄ አስቀምጦለት ነበር፣ ዓምና ካቻምና አዲስ ጠ/ሚ ሲመረጥ በቀጥታ ይህን አንቀፅ ተጠቅሞ ከ6 ወር ባልበለጠ አዲስ ምርጫ በማካሄድ ህዝብ የሚፈልገው መንግስት መመስረት ይቻል ነበር፡፡ ነገር ግን አሁን እየተደረገ ያለው እንዴት የስልጣን ጊዚያችን እናራዝም የሚል ሆነ፡፡ ስለዚህ ይህ አንቀፅ ፈፅሞ አማራጭ ሊሆን አይችልም ምክንያቱ በስራ ላይ ያለው ፓርላማ የስራ ዘመኑ የሚያበቃው ሰኔ 2012 ዓ.ም. በመሆኑ (ይህ እታች ተዘርዝረዋል)

ለ/ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለመበተን ሁለተኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው

በህገመንግስቱ አንቀፅ 60 ንኡስ አንቀፅ 2 መሰረት በጣምራ የመንግስት ስልጣን የያዙ የፖለቲካ ድርጅቶች ጣምራነታቸው ፈርሶ በምክርቤቱ የነበራቸውን አብላጫነት ያጡ እንደሆነ የሚኒስትሮች ምክርቤት ተበትኖ በህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ሌላ ጣምራ መንግስት በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ለመመስረት እንዲቻል ፕሬዚዳንቱ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይጋብዛል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹ አዲስ መንግስት ለመፍጠር ወይም የነበረውን ጣምራነት ለመቀጠል ካልቻሉ ምክር ቤቱ ተበትኖ አዲስ ምርጫ ይደረጋል፡፡ ይላል፡፡

ይህን አንቀፅ መተግበር ያለበት በምን አኳያ ነው?

የአሁኑ የአገራችን ሁኔታ ሲታይ ኢህአዴግ ራሱ በራሱ ህልውናውን አጥፍቷል፡፡ ኢህአዴግ የ4 ብሄራዊ ድርጅቶች ጥምር ግንባር ሲሆን ሶስቱ ድርጅቶች ራሳቸውን በማክሰማቸው ህወሓት ብቻ ነው ህጋዊ የፓርላማ አባል ያለው፡፡ እንደሚታወቀው በ2007 ዓ.ም. የተካሄደው በ5ኛው የህዝብ ምርጫ የኢህአዴግ ፕሮግራም ተቀባይነት አግኝቶ በተወዳደረባቸው ቦታዎች 100% በማሸነፍ መንግስት በመምራት ላይ ነበር፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የህዝብ ይሁንታ ያገኘውን የኢህአዴግ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂና ፖሊሲዎች ይዞ እንዲመራ ነው፡፡ ስለዚህ በህገመንግስቱ መሰረት ሶስቱ ድርጅቶች የኢህአዴግ ፕሮግራም፣ ስትራቴጂና ፖሊሲዎች ያረጀ ያፈጀ ነው በዛ አንጠቀምም በማለት ድርጅታቸው በማክሰም ሌላ አዲስ ድርጅት ማቋቋማቸውና የምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅና መስጠታቸው ይታወቃል፡፡

በዚህ ጊዜ ህገመንግስት አስከባሪ ሀይል ወይም ጠያቂ ካለ በቀጥታ ራሳቸውን ያከሰሙ ሶስቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ፓርላማው መልቀቅ ነበር የሚገባቸውም፣ የሚጠበቅባቸውም፡፡

ፓርላማው ከለቀቁ አገሪቷ ማን ያስተዳድራታል? የሚል ጥያቄ መቅረቡ አይቀርም፡፡

ፓርላማው ከለቀቁ ሶስቱ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ከ70% የማያንስ ወንበር ክፍት ይሆናል፡፡ የህወሓት ብቻ ወይም ከተቀሩ በጥምረትም ቢሆን መንግስት ለመመስረት አያስችልም፡፡ ስለዚህ በዚህ አንቀፅ መሰረት ፓርላማው ተበትኖ አዲስ ምርጫ መካሄድ ነበረበት፡፡ መቼ? የብልፅግና ፓርቲ ህጋዊ እውቅና ባገኘበት ዕለት ፓርላማው ተበተነ ማለት ነው፡፡ ህወሓት ይህን መጠየቅ ነበረበት ነገር ግን የተፈጠረው አለመረጋጋት ላለማጋጋል ብሎ ዝም ብሎ አለፈው፡፡ ለሰላም እና መረጋጋት ሲባል የከፈለው መስዋእትነት ነው ብዬ እወስደዋሎህ፡፡ ስለዚህ ይህን አንቀፅ መጠቀም የነበረበት ህወሓት እንጂ በስልጣን ላይ ያለው የብልፅግና ፓርቲ ኣይደለም፡፡ ስለዚ ይህ አማራጭ አሁን አይሰራም ምክንያቱ ግንቦት ደርሷል፡፡

ሐ/ የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ለመበተን ሶስተኛው ምክንያት ሊሆን የሚችለው

በህገመንግስቱ አንቀፅ 58 ንኡስ አንቀፅ 3 መሰረት የህዝብ ተወካዮች የሚመረጠው ለ5 ዓመት ሆኖ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቅ አለበት ይላል፡፡ ስለዚህ በዚህ ህገመንግስት መሰረት አሁን በስራ ላይ ያለው ተወካዮች ምክርቤት ሌላ አንቀፅ ሳያስፈልግ የስራ ዘመኑ በሚያልቅበት ቀን የግድ በራሱ ጊዜ መበተን አለበት፡፡ የስልጣን ዘመኑ ለማራዘም ቢፈለግም የህገመንግስት ድጋፍ የለውም፡፡ ስለዚ የግድ መበተን አለበት፡፡

እዚህ ሊነሳ የሚችል ጥያቄ ወይም አከራካሪ ነገር ቢኖር የስልጣን ዘመን የሚያልቅበት ቀን መቼ ነው የሚል ነው፡፡

የምክርቤቱ የስራ ዘመን የሚያበቃለት በግልፅ ስላልተቀመጠ በስልጣን ላይ ያለው አካል 5ኛ አመታችን ጳጉሜን 5፣ 2012 ዓ.ም. ነው የሚያልቀው በሚል እሳቤ ሲንቀሳቀስ ይታያል፡፡ ይህ አካሄድ አካራካሪ ቢሆንም ስህተቱ ያመዝናል፡፡ በትክክል ካየነው በህገመንግስቱ መሰረት አሁን በስራ ላይ ያለው ምክርቤት የስልጣን ዘመኑ ማብቃት ያለበት ሰኔ 30፣ 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ለዚህ ሁለት ምክንያቶች ማለትም ህገመንግስቱ ድንጋጌ እና በተግባር እየተተገበረ የነበረው መጥቀስ አስፈላጊ ነው፡-

ሀ/ በህገመንግስቱ አንቀፅ 58 ንኡስ አንቀፅ 2 መሰረት

የምክር ቤቱ የስራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ 30 ነው፡፡ ይላል፡፡ ታድያ ከሓምሌ 1 እስከ መስከረም የመጨረሻው ሳምንት እሁድ ያለው ጊዜ የዕረፍት ጊዜ ይሆን?ይህን ለመረዳት በሁለት ከፍለን እንየው፤ይህም የመጀመሪያ 4 ዓመታት እና የመጨረሻዋ 5ኛው ዓመት በሚል፡፡ በዚህ መሰረት የመጀመሪያው 4 አመታት ውስጥ ያሉት ከሓምሌ 1 እስከ መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት እሁድ ያለው ጊዜ እንደ እረፍት ሲወሰድ የ5ኛ ዓመት ከሓምሌ 1 እስከ መስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት እሁድ ያለው ጊዜ እንደ የምርጫ ሂደት ማጠናቀቂያ ሆኖ አዲሱ የተመረጠው ምክርቤት ሰኞ ስራውን ይቀጥላል፡፡ ስለዚህ ሰኔ 30፣ 2012 ዓ.ም. ነባሩ ፓርላማ ላይመለስ ይሰናበታል ማለት ነው፡፡

ለ/ ባለፉት 5 ተከታታይ ምርጫዎች በተግባር የታየው፡-

ባለፉት 5 ተከታታይ ምርጫዎች ህገመንግስቱ መሰረት በማድረግ የምክርቤቱ የስራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት የሚለውን ሲተረጎም አሮጌው ፓርላማ ሰኔ እንዲሰናበት በማሰብ 5ቱም ምርጫዎች በግንቦት ወር ነበር የተካሄዱት፡፡ ስለዚህ በድንጋጌው መሰረት ይሁን በተግባር እየተካሄደ የነበረው ሲታይ የምክርቤቱ የስራ ዘመን ማብቅያ የህገመንግስቱ ትርጓሜ ሰኔ 30፣ 2012 ነው፡፡ ስለዚህ ልዩ አንቀፅ ወይም ምክክር ሳያስፈልገው አሁን በስራ ላይ ያለው ፓርላማ፣ በህገመንግስቱ መሰረትከሁለት ወር ቦሀላ ሰኔ 30፣ 2012 ዓ.ም. የግድ መበተን ወይም መሰናበት አለበት፡፡

2 አስቾኳይ ጊዜ ማወጅ

አሁን የምንገኝበት ወቅት በኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በአስቾኳይ ጊዜ ውስጥ ነን ያለነው፡፡ ስለዚ ለምርጫ ወይም ለህገመንግስት ለማሻሻል ተብሎ ተጨማሪ አስቾኳይ አዋጅ አያስፈልግም፡፡ ይህ አዋጅ ሊያጥርም ሊረዝምም ይችላል፡፡ ወረርሽኙ ቶሎ ተቆጣጥረን አስቾኳይ አዋጁ ከተነሳ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡ በቀጥታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ምርጫ እንገባለን ምክንያቱ ከድንጋጌው ቦሃላ ያለን ጊዜ ዋነኛ ስራ የምርጫ ስራ እና የዕለት ተዕለት የመንግስት ስራ ስለሚሆን፡፡ ምናልባት ወረርሽኙ ከታወጀው የአስቾኳይ አዋጅ በላይ ከቀጠለ እንደ አገር የመቀጠል እንደ ህዝብ የመቀጠል ሁኔታ ከባድ ይሆናል፣ ለመተንበይም በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ምክንያቱ 5 ወር ሙሉ እንቅስቃሴ ተገድቦ፣ እንደገና ሌላ 5 ወይም 6 ወር እንቅስቃሴ በመግታት ለመቀጠል ያስቸግራል፤ ምናልባት ሌላ ሊበትነን ወይም ሊያውከን የሚችል ችግርም ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ መንግስት በአጭር ጊዜ ወረርሽውን ለመግታት ጠንክሮ መስራት አለበት፡፡ ከአቅም ውጭ ከሆነ ምን ይደረግ ከተባለ ግን የህገመንግስት ትርጓሜ ጥያቄ በመጠየቅ አስቾኳይ አዋጁ ለህዝብ ደህንነት፣ ለአገር አንድነት ሲባል በሚኒስትሮች ምክርቤት ወይም በክልሉ ካቢኔ እንዲያራዝም ትርጓሜ መስጠት ነው፡፡

3. የህገመንግስት ትርጓሜ መጠየቅ ናቸው

ህገመንግስታችን በጣም ዘመናዊና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንዳለብን በደንብ ይዞ የተደነገገ ነው፡፡ ይሁንና ያልታሰቡ ችግሮች ሲደራረቡ ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ሳይፋለስ ተደራራቢ ችግሮችን ለመፍታት የህገመንግስት ትርጓሜ እንደ አንድ አማራጭ መቅረቡ ትክክል ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አማራጭ ተቀባይነት ያለው ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ነገር ግን ትርጓሜ የሚጠየቅበት አንቀፅ ወይም ይዘት ምንድን ነው? የሚል ግን መመለስ አለበት፡፡ ትርጓሜ መጠየቅ አለበት የምለው ፡-

         በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በአስቾኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ባለንበት ወቅት፤ እንዲሁም የፓርላማ የስራ ዘመን በማለቁ ምክንያት ፓርላማው በተበተነበትጊዜ እያለን ወረርሽኙ ቁጥጥር ስር ከዋለ አዋጁ ተነስቶ በቀጥታ ወደ ምርጫ ስራ ገብተን በ6 ወር ምርጫ እናካሂዳለን ልዩ ትርጓሜ አያስፈልግም፡፡ ነገር ግን ወረርሽኙ በዚይ የአስቾኳይ ጊዜ አዋጅ ገደብ ውስጥ ካልተቆጣጠርነው እንዴት ይቀጥል? ኣዋጁ ማራዘም ቢያስፈልግ ፓርላማ ስለተበተነ ምን እናድርግ? የውጭ ወረራ ቢያጋጥም ምን እናድርግ? የሚሉ ጥያቄ የህገመንግስት ትርጓሜ እንዲሰጥ መጠየቅ፡፡ ይህም ከሰኔ 30፣ መድረሱ በፊት ምላሽ ማግኘት አለበት፡፡ ምክንያቱ ከሰኔ 30፣ ቦሀላ ሁሉም ምክርቤቶች ስለሚበተኑ፡፡

         አንድ ሰላም እና መረጋጋት ፈላጊ ዜጋ፣ አገር ከትርምስ እና ከመበታተን ለማዳን የሚፈልግ ዜጋ ትርጓሜው ቀላል ነው፣ የዚህ ወረርሽኝ ጉዳይ በጊዜ ገደቡ ካልተወገደ ኣጣሪው ኣካል በሚያቀርበው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ጠ/ሚ ኣዋጁ ማስቀጠል፤ የውጭ ወረራም ቢያጋጥም ጠ/ሚ ትእዛዝ በመስጠት መከላከል ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱ ፓርላማ ተበትነዋል ብሎ ኣዋጁ በማንሳት ህዝባችን ለወረርሽኙ ማጋለጥ ወይም ደግሞ የውጭ ወረራ አጋጥሞ የመከላከል ጦርነት የሚያውጅ ፓርላማ የለም ብሎ ወራሪውን ዝም ብሎ ማስገባት ተቀባይነት ስለሌለው፡፡ ፖለቲካዊ አስተያየት ሊሆን ይችላል ግን ደግሞ የፌደሬሽን ምክርቤት ከመበተኑ በፊት የዚህ ትርጓሜ በማስቀመጥ ከመበተኑ በፊት ሃላፊነቱ መወጣት አለበት፡፡

4. ህገመንግስቱ ማሻሻል

ህገመንግስቱ የማሻሻል አማራጭ አሁን ባለንበት ሁኔታ አይቻልም፣ እንደ አማራጭም መቅረብ ያለበት ጉዳይም አይደለም፡፡ ምክንያቱም አሁን በስራ ላይ ያለው የፌደራልም የክልልም ምክርቤት በቀጣይ ሰኔ 30፣ 2012 ዓ.ም. የስልጣን ዘመኑ ስለሚያበቃ፤ በህገመንግስታችን የምክርቤቶች የስልጣን ዘመን የማራዘም ዕድል ስለሌለ፣ ህገመንግስት ለማሻሻል በራሱ ጊዜ ስለሚወስድ፣ በአጭር ጊዜ ለመፈፀም ቢፈለግም የኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ዕድል ስለማይሰጠን፤ ይህ አማራጭ ህጋዊነት አይኖረውም ነባራዊው ሁኔታም ለዚህ አመቺ አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ አማራጭ ውድቅ ነው፡፡

ማጠቃለያ

ለማጠቃለል አሁን ላጋጠመን ችግር ህገመንግስታችን በቅንነት እና በህዝባዊነት መንፈስ ካየነው ህገመንግስቱ ማሻሻል ሳያስፈልግ መፍትሄው እዛው እናገኘዋለን፡፡ የሚያስፈልገው ሁሉም በአገራዊ መንፈስ በቀና መወያየት ብቻ ነው፡፡ ጠ/ሚ በጠሩት ስብሰባ የፓርቲዎች ሁኔታ ሲታይ በጣም በጣም አሳሳቢ ነበር፡፡ ከአንድ ለምርጫ የተዘጋጀ ፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቅ ግብኣት ተገኘ ማለት አይቻልም፡፡ ቢዘገይም አሁን በስልጣን ላይ ባለው ፓርቲ ተበልጠዋል፡፡ ስለዚህ ይህ የአገር ጉዳይ ነው፤ ይህ የሰላም እና የመረጋጋት ጉዳይ ነው፣ ይህ የአገር አንድነት የማስጠበቅ ጉዳይ ነው በማለት ሁሉም ፓርቲዎች እዚህ ላይ በንቃት መሳተፍ ይገባቸዋል፡፡

አማራጭ አንድ ፓርላማ መበተን የሚለው እንደ አማራጭ ሳይሆን በቃ በራሱ ጊዜ የተበተነ ፓርላማ ነው፡፡ ስለዚ በተበተነ ፓርላማ እንዴት አገር ይመራል የሚል ጥያቄ በማንሳት መልስ መስጠት ያስፈልጋል፡፡

ፓርላማው ተበተነ፤ አገር እንዴት ይመራ?

እላይ እንደተገለፀው ፓርላማ የሚበተንበት መንገዶች ሶስት ሆኖው አንደኛው መደበኛ የስራ ጊዜዉን ጨርሶ ሲበተን ሲሆን ሁለቱ ግን የስልጣን ጊዜ ሳያልቅ መበተን ነው፡፡ አሁን ያጋጠመን ግን ይህ ፓርላማ (የክልልም የፌደራልም) መደበኛው የስልጣን ዘመኑ በመጨረሱ ምክንያት መበተኑ የግድ በሆነበት ጊዜ ደርሰናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የስልጣን ዘመኑ ከማለቁ ከአንድ ወር በፊት ምርጫ ማካሄድ የግድ ነበር፤ ነገርግን የመንግስት እንዝህላልነት ወይም ምርጫ የማድረግ ፍላጎት አጠያያቂ ቢሆንም አጠያያቂ ያልሆነው የኮቪድ-19 ሁኔታ ግን ምርጫ ማካሄድ እንደማንችል ተረጋግጧል፡፡ በእርግጥ የመንግስትም የምርጫ ቦርድም ዝግጅት አጥጋቢ ነው ማለት አይቻልም፤ ነገር ግን አጥጋቢም ቢሆን ነባራዊ ሁኔታው ምርጫ ማካሄድ አይቻልም፤ ስለዚህ እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ፤ እንደ አንድ የአገሬ ሁኔታ በጣም ያሳስበኛል የሚል ዜጋ ይሆናል የምለውን ሃሳብ እንደሚከተለው ላቅርብ፡፡

መነሻዬ

ኢትዮጵያ አገራችን ባለፉት ሁለት አመታት በተለይ አዲሱ ጠ/ሚ ከተመረጡ ቦሃላ ሰላምዋ ተናግቶ ህዝቦችዋ በከፍተኛ እንግልት፣ መፈናቀል፣ ንብረት መውደም፣ የሰው ህይወት መቀጠፍ የመሳሰሉ ክስተቶች የዕለት ተእለት ክንዋኔዎች ሆኖውባታል፡፡ መንግስት ይህን ነገር ማቆም አልቻለም፡፡ የኮሮና ቫይረስ በአገራችን እስኪታይ ድረስ የነበረው ሁኔታ ይህ ነው፡፡ ይህን የሰላም እና የመረጋጋት ሁኔታ ኮሮና ቫይረስ ከመጣ ቦሀላ ጋብ ብለዋል፡፡ የትግራይ ክልል መንግስት እና የፌደራል መንግስት ህገመንግስታቸው በሚፈቅደው መሰረት በኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ሊከሰት ከሚችለው አስከፊ እልቂት ህዝባቸውን ለመታደግ አስቾኳይ አዋጅ በማወጅ አመርቂ የመከላከል እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡ ይህ እርምጃ በሁሉም በኩል ተጠናክሮ በማስቀጠል ወረርሽኙ በአጭር ጊዜ መቀጨት አለበት፡፡

አሁን በፌደራል የመንግስት ስልጣን ላይ ያለው ሀይል አዲስ ፓርቲ ከተመሰረተ ቦሀላ ህጋዊነቱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ የህጋዊነት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የመንግስት የመምራት ብቃትም፣ የህግ የበላይነት የማክበር እና የማስከበር አቅምም ቁርጠኝነትም ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም፤ ምርጫው ጥቂት ወራት ነው የቀሩት ከሚል አርቆ አስተዋይነት ወደ ብጥብጥ እና አመፅ ከመግባት ይልቅ በትእግስት ምርጫን መጠባበቅ ላይ ይገኛል፡፡

አሁን ካለን የዕድገት ደረጃ አንፃር ሲታይ በኮቪዲ-19 ወረርሽኝ ምክንያት በተለመደው አኳሀን ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል አብዛኛው ህዝብ የሚስማማበት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ዝርዝር የህገመንግስት ድንጋጌ ባይኖረውምከዚህ ወረርሽኝ ለመከላከል፣ ህጋዊ ምክርቤት ቢበተንም የአስቾኳይ ጊዜ አዋጅ በሚደነግገው መሰረት ተግባራዊ ማድረግ ይገባል፡፡ አሁን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የህጋዊነት ጥያቄ ቢኖሮውም በአገራችን የተደቀነው የመበታተን አደጋ ለመታደግ፣ የአገር መንግስትና ስርዓት ለማስቀጠል በሚል ምክንያት አሁን ያለው መንግስት ምርጫ የሚካሄድበት ሁኔታ የማመቻቸት ዕድል ሊሰጠው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እንዴት?

1.   አሁን በአስቾኳይ ጊዜ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ይህ አስቾኳይ ጊዜ የዜጎች እንቅስቃሴና መሰብሰብ የሚከለክል ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ከኮቪድ-19 ሊመጣ የሚችል አስከፊ እልቂት ለመከላከል ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ወረርሽኝ፤ ወረርሽኝነቱ እስካላበቃ ድረስ፣ የተወካዮች ምክርቤት ቢኖርም ባይኖርም አስቾኳይ አዋጁ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ይሁንና ይህ ወረርሽኝ በሚገባ ከተከላከልንና ከአገራችን መጥፋቱ ካረጋገጥን ግን አስቾኳይ አዋጁ ተነስቶ በቀጥታ ወደ ምርጫ የሚያስገባ ስራ በመሰራት ከተቻለ በአጭር ጊዜ ካልተቻለ ግን ከ6 ወርባልበለጠ ምርጫ ማካሄድ፡፡

2.   በዚህ ጊዜ የመንግስት ክፍተት እንዳይፈጠር መደረግ ያለበት አሁን በስልጣን ላይ ያለው አካል በህገመንግስቱ አንቀፅ 60 ንኡስ አንቀፅ 5 መሰረት ኣዳዲስ ኣዋጆች፣ ደንቦችንና ድንጋጌዎች ሳያወጣ ወይም ሳያሻሽል በነበረው ኣዋጆች፣ ደንቦች እና ድንጋጌዎች ብቻ መሰረት በማድረግ የዕለት ተዕለት የመንግስት ስራ ከማከናወን እና ምርጫ ከማካሄድ ይኖርበታል፡፡

3.   የክልሎችም በተመሳሳይ መልኩ በዚህ አንቀፅ 61 ንኡስ አንቀፅ 5 መሰረት ክልላቸውን መምራት እና ነፃ ምርጫ የሚካሄድበት ሁኔታ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል፡፡

4.   የመከላከያ ሰራዊት የተሰጠውን ህገመንግስት የማክበር እና የማስከበር ሀላፊነት ከማንም ጊዜ በላይ አሁን ጠንክሮ የሚሰራበት ጊዜ ነው፡፡ እስካሁን በእንዝላልነት፣ በሆደ ባሻነት ወይም በፖለቲካ ውግንና ወይም በተለያዩ ሌላ ምክንያቶች ህገመንግስቱ እየተጣሰ፣ አድልዎ እየተሰራ፣ ዜጎች በማንነታቸው እየታሰሩ፣ እተፈናቀሉ፣ እየሞቱ አስፈላጊውን የማስተካከያ እርምጃ አልወሰደም፡፡ የችግሩ አስከፊነትም የሰራዊቱ ኢታማጆር ሹም እስከ ማጣት ተደርሷል፡፡ ከአሁን በሀላ ህገመንግሱ እየተጣሰ ዝም ብሎ ማየት ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለዚህ የፌደራል መንግስት ከህገመንግስት ውጭ አንድም ስንዝር እንዳይሄድ በንቃት በመከታተል እና በመጠበቅ ታሪካዊ ሀላፊነቱ መወጣት አለበት፡፡

በመጨረኛ ግን የጠ/ሚ መግለጫ ተከታትየው ሁለት ትዝብት አለኝ

1.   አሁን ከውጭ ጠላቶች የሚተባበሩ ባንዳዎች እንዳሉ ሲናገሩ ትዝብት ላይ ነው የጣላቸው፡፡ በራሳቸው አንደበት ለኦነግ፣ ለአርበኞች ግንባር ለሻዕብያ ውስጥለውስጥ ሲሰሩ አልነበረም ወይ? በምን ሞራል ነው ባንዳ ብለው ለመናገር የደፈሩ?

2.   ትላንት ከማንኛውም ፓርቲ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል፤ ግን ደግሞ በባሌ ህወሓቶች ሰበርናቸው እንዳሰሩን አሰርናቸው፣ በኛ ፈቃድ ብቻ ነው መውጣት የሚችሉት፣ ከህወሓት ጋር ከመስራት ሞት ይሻላል ያሉት እንዴት ተረሳ?

በአጠቃላይ የጠ/ሚ ትልቁ ችግር አቋም የለሽ፣ መርህ የለሽ በጠቅላላ የተናገሩትን የሚረሱ በመሆናቸው እምነት ለመጣል በጣም ያስቸግራል፡፡

አስተያየት በሚከተለው የኢሜይል ኣድራሻ ማድረስ ይቻላል

hidaseethiopia@yahoo.com and/or hidaseethiopiaa@gmail.com

 

Back to Front Page