Back to Front Page

የብሄር መብት የግለሰብ መብት ከፍተኛ መገለጫ መሆኑን መቀበል የማይችሉ እንከፎች

የብሄር መብት የግለሰብ መብት ከፍተኛ መገለጫ መሆኑን መቀበል የማይችሉ እንከፎች

ሜ.ጄ. አበበ ተክለሃይማኖት

 

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 05-31-20

ለሜጀር ጄኔራል አበበ ተክለሃይማኖት ሰላምታየን እያስቀደምኩ ባለፈው በአይጋ ፎረም ላይ ያወጡት ፅሁፍ ላይ የምጋራውን ትቼ በማላልጋራው ላይ አስተያየት ለመሰንዘር ነው፡፡ ከምጋራቸው ነገሮች አንዱና ዋነኛውን ግን ሳልጠቅስ ማለፍ የለብኝም፡፡ ከበርሃ በህይወት አዲስ አበባ ለደረሱትና በህይወት ለመድረሳቸውና ድል አድራጊ ሆነው ለመወደስ ያበቋቸው ሰማእታት አላማ ተዘንግቶ መስዋእትነቱ ለግል ምቾት ማደራጃ የመሆኑ ክህደትና ትራጀዲ ለስለስ አድርገው ያቀረቡትም ቢሆን እስማማለሁ፡፡ አርሶ ራስዎ በከፍተኛ ደረጃ የነበሩበት ይህ የግንቦት 20 ድል አላማውን ለምን እንደዛ እንዳከሸፋችሁት አብሮ በንስሃ መልክ ቢገለፅ መልካም ይሆን ነበር፡፡ ሰማእታቱ የተሰዉት ሰማይ ጠቀስ ሃውልት እንዲሰራላቸውና በአመት አንድ ጊዜ የህሊና ፀሎት እንዲደረግላቸው ፈልገው ሳይሆን በህይወት የደረሳችሁት አላማቸውን ተግባራዊ በማድረግ ከሞት የበለጠ መስዋእትነት በቁማችሁ ትከፍላላችሁ ብለው ያስቡ ስለነበር ነው፡፡ አለበለዚያማ ስለ ትግሉ እየተረከ ፎቅ ሰርቶ ዊስኪ የሚጠጣውን ሰው ህይወት ለማትረፍ ማን ዘንዶ አፍ ውስጥ በደስታ ይገባ ነበር? ሌላው እንዲከብር የሚሰዋው እኮ ቅጥረኛ ወታደር ብቻ ነው፡፡ እፅ አዘዋዋሪ ከበርቴዎችን ሚልዮነር ለማድረግ የሚያልቁት በሺዎች የሚቆጠሩ ቅጥረኞች ናቸው፡፡ የሞቱትም እንደተሰበረ ብርጭቆ ወዲያው ባዲስ ይተካሉ፡፡ የህወሓት አመራር ኑራችሁ ከድርጅቱ የለቀቃችሁት የትግሉ አላማ መስመር ስቷል ብላችሁ ሳይሆን ራሳችሁ ሉአላዊት አገር እንድትሆን በፈቀዳችሁላትና ባገዛችኋት ምናልባትም በማያገባችሁ በኤሪትርያ ጉዳይ ላይ ነበር፡፡

Videos From Around The World

የፖለቲካ ክርክር የራሱ የሆነ የስነ ምግባር ደንቦች አሉትና አዲሶቹ ደርጎች ባሏቸው ላይ የሰነዘሯቸው ቅፅሎች (ለምሳሌ በዚህ ፅሁፍ ርእስ ላይ እንደተመለከተው) ተገቢ ናቸው ብየ አላስብም፡፡ እኛ እኮ የጠላነው የፖለቲካ አመለካከት ልዩነትን አይደለም፡፡ እሱማ ትልቅ ሃብት ነው! እኛ የምንጠላው ከልዩነቱ መግለጫዎች ጋር አብረው የሚወርዱት ስድቦችን ነው፡፡ በነገራችን ላይ አያት ቅድመ አያቶቻችን እርስ በርስ የሚዋጉት በእስበርስ አክብሮት ታጅበው ነው፡፡ ልዩነት በጦር ይፈታ በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀናቃኞች ተራ ስድብ መሰዳደብ የለባቸውም፡፡ ህዝብ እኮ በንዴት ፀጉሩ የቆመው በጅምላ የቀን ጅብ፤ ፀጉረ ልውጥ በመባሉ እንጂ እንተ ውረድ እኛ እናስተዳደር ስለተባለ አይደለም፡፡ በዚህማ ለምን ህዝብ ይቆጣል? ነገሩ የፖሊቲካኞች የወር ተራ ጉዳይ ስለሆነ፡፡ ለህዝቡ ከሚቀርቡት ይልቅ እርስ በርሳቸው የበለጠ ይተዋወቁ ይቀራረቡ የለ፡፡ ህዝብ እኮ በፖሊቲከኞች እጅ ያለ የቼዝ ጠጠር ማለት ነው፡፡ የራሴ የሚባል ፖለቲካኛ የለም፤ የራሱን ጠጠር አስቀድሞ የሚያስበላው የራስ የተባለው ፖለቲከኛ ነው፡፡ አዲሶቹ ደርጎች ያሏቸው እነማን እንደሆኑ በዝርዝር ለአንባቢዎችዎ ግልፅ ማድረግ አለብዎት፡፡ አዲሶቹ ደርጎችና እንከፎች ያሏቸው አሃዳዊነትን የሚያራምዱትና የግለሰብ መብት ይቀድማል የሚሉትን ይመስላል፡፡ ባላለቀለት የክርክር አጀንዳ ላይ ፍረጃ መልካም አይደለም፡፡ የአሃዳዊነትና የፌደራላዊነትም ይሁን የግልሰብ መብት ወይንም የቡድን መብት ቀዳሚነት ክርክሮች እንኳንና በሰላማዊ የፖለቲካ ክርክር ገና ጨቅላ በሆነባት በኢትዮጵያ ቀርቶ በዚሁ ክርክር ጥርሱን በነቀለው የምዕራቡ አለም ውስጥ እንኳን የዚህ ጉዳይ ክርክር ገና እልባት አላገኘም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የግለሰብ መብት፤ የቡድን መብት፤ አሃዳዊነት፤ ፌደራላዊነት ተጠላልፈው ይገኛሉ፡፡ የግለሰብ መብት ያስቀደመ አሃዳዊ ነው፤ የቡድን መብት ያስቀደመ ፌደራላዊ ነው የሚል በፍጥነትና በቀላሉ የተሰሩ ጥንዶች ሆነዋል፡፡ ከዛ ቀጥሎ አሃዳዊ ጨፍላቂ ነው፤ ፌደራላዊ ዴሞክራቲክ ነው የሚል ድምዳሜ ይከተላል፡፡ ትንተናየን በግለሰብና በቡድን መብት ልጀምርና ወደ አሃዳዊነትና ፌደራላዊነት እቀጥላለሁ፡፡ እዚህ ላይ መግለፅ የምፈልገው የማንም የፖለቲካ ድርጅት አባልም ደጋፊም ስላልሆነኩ የምሰነዝራቸው አመለካከቶች የግሌ ብቻ ናቸው፡፡ መብት የሚባለው ከስር መሰረቱ በመርህ ደረጃ ሲታይ የግለሰብ መብትን የሚመለከት ነው፡፡ የሰው መብት የሚጀምረው በህይወት ለመኖር ካለው መብት ላይ ነው፡፡ ህይወቱን የማሳጣት መብት የሚኖረው ፈጣሪው ወይንም በነፃ ፍርድ ቤት ቀርቦ በሰራው የወንጀል ክብደት በአገሪቱ ህግ መሰረት ብቻ ነው፡፡ ይህ መብት የሚጀምረው በብዙዎች አመለካከት ነፍስ ከዘራ ሽል ጀምሮ ነው፡፡ ፅንስ ማስወረድ ሰው እንደመግደል ተደርጎ የሚቆጠረውም ለዛ ነው፡፡ ሰው ቡድን ሆኖ ስለማይፈጠር፤ ወደየትኛው ቡድን እንደሚፈጠርም መርጦ ስላልሆነ የሚፈጠረው ከተወለደበት ሌላ ቡድን ውስጥ እንደግለሰብ የመቀላቅል መብቱ የተከበረ ነው፡፡ ሰው የሚወለደው ለብቻው ነው የሚሞተውም ለብቻው ነው፤ በቡድን አይወለድም በቡድን አይሞትም፡፡ ይህ ነው የግለሰብ መብት ተፈጥሯዊ መነሻ፡፡ ለዚህም ነው ከክርስትያን ማህበረስብ የተወለደው ሙስሊም የመሆን መብት ያለውና የሚሆነው፡፡ ለዚህም ነው ከአንድ ጎሳ ወይንም ብሄረሰብ የተፈጠረ ከማህበረሰቡ ወጪ የሆነውን አግብቶ ልጆች ወልዶ የሚኖረው፡፡ የግለሰብ መብት ቀዳሚ በመሆኑ ነው ሰው ትውልድ አገሩን ትቶ የሌላ አገር ዜግነት የሚወስደው፡፡ የግለሰብ መብት ቀዳሚ በመሆኑ ነው ሰው ወደ ምርጫ ሳጥን ካርድ ይዞ ሲጠጋ ማንም ሌላ ሰው ካጠገቡ እንዳይቆም የሚደረገው፡፡ ምርጫ ነው የግለሰብ መብት ቀዳሚ መገለጫ፡፡ ቡድኖች የግለሰብን መብት የሚረግጡበት ዋናው መስክም ይኸው የምርጫ ሂደት ነው፡፡ ቡድኖች ያለ ተፅእኖ የሚሰጥ የግለስብ ምርጫ ካርድ ሳያገኙ በወረፋ ስልጣን ላይ ለመቆናጠጥ ይረባረባሉ፡፡ ይህንም የሚያደርጉት ቡድናቸው ስleጣን ሳያገኝ ተገልሎ መቆየቱን ምክንያት በማድረግ የቡድን መብት ስለሚጠይቁ ነው፡፡ በቡድኖቹ ውስጥ ያለው ግለሰብ ቡድኖቹ የሚሉትን ተቀብሎ የማራገብ ግዴታ ይጣልበታል፡፡ ባለፈው እንደጉድ ስንሰማ የከረምነው የአሮሞ ወንዶች ከኦሮሞ ሴቶች ውጪ ሌላ እንዳታገቡ አየተባለ የቡድን መብት ሲከበር የነበረው የወደደውን-ያፈቀረውን የማግባት የማይነካው የግለሰብ መብት የደፈጠጠውን አካሄድ ነበር፡፡ እንዲህ ሲሆን ነው የብሄር (የቡድን) መብት የግለሰብ መብት ከፍተኛው መግለጫ ነው የተባለው?

እርግጥ ነው የግለሰብ መብት ቀዳሚና ተፈጥሯዊ ቢሆንም ያለ ቡድን መብት የተሟላ አይሆንም፡፡ የቡድን መብት የግለሰብ መብት ወሳኝ ድጋፍ ሆኖ የሚቀርበው በግለሰብ መብት ብቻ የማይሸፈኑ ልዩ ባህርያት ያላቸው ግለሰቦች የተሰባሰቡበት የህብረተሰብ ክፍል ሲኖር ነው፡፡ ይህ የአካል ጉዳተኞች፡ ሴቶች፤ ህፃናት፤ አናሳ የሃይማኖትና የቋንቋ ማህበረሰቦችን ይመለከታል፡፡ የግለሰብ መብት ዘወትር ታሳቢ የሚያደርገው የተሟላ አካል ያለው፤ በፆታ ወንድ የሆነ፤ ለአካለ መጠን የደረሰ፤ ወዘተን ነው፡፡ ህንፃ ሲሰራ ለአካል ጉዳተኞች እንደሚያመች ሳይሆን የተሟላ አካል ላለው ሰው ታስቦ ነው፡፡ መስማት የተሳናቸው፤ በጋሪ ወንበር የሚሄዱ፤ ማየት የተሳናቸው ህንፃውን በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችላቸው የግንባታ ህግ ሊወጣላቸው የሚችለው እነሱን እንደማንኛውም ግለሰብ በማየት ሳይሆን ከሌላው ጋር ከሚጋሩት የግለሰብ መብት በተጨማሪ በተለየ መልክ እንደ ልዩ ባህርይ ቡድንነታቸው በየትኛውም ዘርፍ የግለሰብ መብታቸውን የሚተገብሩበት የቡድን መብት እውቅና ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሴቶችን በተመለከተ ያለውመ ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ በተለምዶ ቀጥሎም በህግ የግለስብ መብት ማእከል የሚያደርገው ወንድነትን ነው፡፡ ሴቶች ያለፍላጎት ሲገረዙ፤ ሲጠለፉ፤ ሲደፈሩ፤ ከቤት ድብደባ ሲደርስባቸው፤ ያነሰ ደሞዝ ሲከፈላቸው፤ ሹመት ሲነፈጋቸው ህብረተሰቡ ብዙም ትኩረት አይሰጠውም፤ ህግ እንደተጣሰም አይቆጠርም፡፡ ስለዚህ የግለሰብ መብት መኖር ብቻውን በቂ አይደለም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ሴቶችን እንደ ልዩ ባህርይ ቡድን በልዩ አይን አይቶ የሚያስተናግድ ተቋማዊ የመብት አሰጣጥ ስራ መሰራት አለበት፡፡ ህፃናትም 18 አመት ካልደረሱ የግለሰብ መብታቸው በአሳዳጊ እንጂ በህግ እጅ አይደለም፡፡ ስለዚህ ህፃናት ላይ የግለሰብ መብታቸው ሊከበር የሚችለው እንደ ህፃናት በልዩ ቡድንነት ሲታዩ ነው፡፡

ይህ የመብት ጉዳይ የተነሳው ቀደም ብየ በጠቀስኳቸው አካል ጉዳተኞች፡ ሴቶች፤ ህፃናት በሚመለከት ሳይሆን ሰፋ ባለው የማህበረሰብ ቡድንን በሚመለከት ነው፡፡ የአካል ጉዳተኞች፡ ሴቶች፤ ህፃናት ጉዳይ ላይ ያተኮርኩት ለመነሻ ያህል እንጂ የነሱ ጉዳይ የሚያከራክር ጉዳይ አይደለም፡፡ ባህርያቸው ለምደባ የሚመች ግልፅ የሆነ ድንበር አለው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የግለሰብና የቡድን መብት በሚመለከት የክርክር አጀንዳ የሆነው ብሄር ብሄረሰቦችን እንደ ቡድን የነዚህ አባለት የሆኑትን እንደ ግለሰብ በመቁጠር የየትኛቸው መብት ቀዳሚ ይሁን በሚል ነው፡፡ የግለሰብ መብቶች ከመብዛታቸው የተነሳ ተሰፍረው አይልቁም፡- በህይወት ከመኖር ጀምሮ፤ ጋብቻ፤ ቋንቋ፤ ፍትህ፤ ምግብ፤ ሃይማኖት፤ መኖሪያ ቦታ፤ ትምህርት፤ ጤና፤ ፖለቲካ አመለካከት፤ ወዘተ፡፡ የቡድን መብት ደግሞ አንድ ግልፅ መለያና እንድነት ያለው የህብረተሰብ ክፍል ከሌላው የሚለዩት ግልፅ የሆኑ ሃይማኖታዊና ባህላዊ ባህርያትን ያለ ጣልቃ ገብነት ለማራመድ የሚያስችሉት ከአባላቱ የግለሰብ መብት በተጨማሪ የቡድን ልዩ ባህርያቱን የሚጠብቅበት የተለየ ህግ ያስፈልገዋል፡፡ በአሜሪካ የግለስብ መብት ጥቁር አሜሪካውያንንም የሚመለከት ቢሆንም ለጥቁሮች እንደ አንድ ልዩ ባህርይ ያለው የህብረተሰብ ክፍል ታይቶ ተጨማሪ የቡድን መብቶችም መደንገግ አስፈላጊ ነበር፡፡ ማንም አሜሪካዊ የህዝብ ትራንስፖርት የመጠቀም መብት አለው እየተባለ ጥቁሩ ሲሳፈር በህግ አስከባሪ ሳይሆን በግልሰቦች ውረድ የሚባል ከሆነ ችግሩ ያለው ከግለሰብ መብት አሰጣጥ ሳይሆን ህብረተሰቡ በጥቁሮች ላይ ያለው አመለካከት ብልሹ ስለሆነ ነው፡፡ ለዚህ መፍትሄ የግልሰብ መብቱን ሽሮ የቡድን መብትን በማግነን ለጥቁሮች የራሳቸው ትራንስፖርት ማዘጋጀት በግልፅ የመንግስት ስርአት መውደቁን ያሳያል አንጂ ፍትሃዊነት አይደለም፡፡ ፍትሃዊ የሚሆነው የግለሰብ መብቱን ተፈፃሚነት ለማጠናከር ጥቁሮችን እንደ አንድ የተለየ የህብረተሰብ ክፍል (ቡድን) አይቶ ተጨማሪ ህጎችን ማውጣትና ተፈፃሚነታቸውን በጥብቅ መከታተል ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ109 ሚልዮን ግለሰቦች አሉ፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ሁሉም የየራሳቸው የሆነ ፍላጎት አላቸው፡፡ ህገወጡን ፍላጎት እንተወውና ህጋዊ የሆነ ፍላጎታቸውን በግለሰብ ደረጃ ማስተናገድ የመንግስት ግዴታ ነው፡፡ ስለዚህ መብቱ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ የግለሰብ መብት በጥብቅ እንደተጠበቀ ሆኖ በግልሰብ መብት የህግ ማእቀፍ ብቻ የማይሰተናገዱ የቡድን መብቶች አሉ፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት የግለሰብ መብት የሚሰጠው ሰው ሰው በመሆኑ ነው! ሰው ሰው የመሆኑ ነገር ደግሞ ከሁሉ የሚቀድም ነገር ነው፡፡ ሰው ራሱን የቻለ ቁመና እንዳለው ፍጡር ሳይሆን ሰውን እንደ የሆነ ማህበረሰብ ቡድን አባል ብቻ አድርጎ የሚያይ መንግስት ጫካውን እያየ ዛፎችን የማያስተውል ደን ጠባቂ አይነት ይሆናል፡፡ እያንዳንዱ ዛፍ ቅንቅን እየበላው ይሁን ምስጥ እየጨረሰው ይሁን ካላስተዋለ ከጊዜ በኋላ ደኑ ስለማይኖር የሚጠብቀው ደን አይኖረውም፡፡ ለሳንቲሟ ጥንቃቄ አድርግ፤ ዶላሮቹ ለራሳቸው ይጠነቀቃሉ የሚለው ከኢነግሊዝኛ የተረጎምኩት አባባል ዶላሮች የቆሙት በሳንቲሞች ላይ በመሆኑ ነው፡፡ መቶ ሳንቲሞች ከባከኑ ዶላሩ በህይወትሊኖር አይችልም፡፡ አንድ ሰርአት ከይዘቶቹ ድምር የላቀ ነው የሚለው ሌላው አባባል በተፈጥሮ ሳይንስ ትክክል ቢሆንም በማህበራዊ ሳይንስ ግን ደፍጣጭ አባባል ነው፡፡ የቡድን መብት በኢትዮጵያ የሚተረጎመው የብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ነው፡፡ ራስን በራስ የሚለው ቁልፍ አባባል ትርጉሙ ግልፅ መሆን አለበት፡፡ ሜ.ጄ. አበበ እንዳሉት ከሆነ የግልሰብ መብት የሚመነጨው ከዚህ ነውና የዚህ ትብትብ ቋጠሮ ውሉን መግኘት አለብን፡፡ ራስን በራስ ለሚለው ትርጉም ለማግኘት መጀመሪያ ራስ የሚለው ይተንተን፡፡ ራስ የተባለው ለኔ እንደገባኝ ግለሰቡ ሳይሆን ቡድኑለማለት ነው፡፡ ቀጥሎ የሚነሳው ጥያቄ ቡድኑ የምን (ምንን ያካተተ) ቡድን ነው? የሚል ነው፡፡ ቡድኑ የሃይማኖት ቡድን ነው? የባህል ቡድን ነው? አንድ የመግባቢያ ቋንቋ ያለው ስብስብ ነው? አንድ የተለየ ጂኦግራፊያዊ መኖሪያ (ተራራ ላይ፤ ደን ውስጥ፤ ባህር ዳርቻ፤ በርሃማ ስፍራ፤ ወዘተ) ያለው ነው? አንድ አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ ያለው ነው? እንድ ታሪክ የሚጋራ ነው? በቆዳ ቀለም የተለየ ነው? የተለየ ሙያ (አንጠረኛ፤ ሸክላ ሰሪ፤ ወዘተ) ያለው ነው? እነዚህ ጥያቄዎች ሳይመለሱ ሌላ ግን ወሳኝ ጥያቄ ማስከተል አስፈላጊ ነው፡፡ እነዚህ ቡድኖች ግልፅ የሆነ ድንበር አላቸው?!

ግለስብ ግልፅ የሆነ ማንነት አለው፡፡ ለዚህም ነው በጣምራ በቡድን ሳይሆን መታወቂያ ለያንዳንዱ ሰው ፎቶው ተለጥፎ መታወቂያ የሚሰጠው፡፡ በቀለና ገ/ህይወት ያላቸው የየራሳቸው እጆች እንጂ እጅ የሚጋሩበት አፈጣጣር የለም፡፡ ቡድኖች ግን ኣማዞን ጫካ ውስጥ ከሌላው አለም ተለይተው የሚኖሩት አናሳ ነገዶችች ካልሆኑ በስተቀር ከሌላ ቡድን ጋር የሚጋሩት ባህርይ የለም ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ በቋንቋ የመጠቀም መብት ለማስከበር የተፈጠረ ቡድን አባላት በተለያ የእምነት መብት የማስከበር ቡድኖች አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አማራ፤ ትግራይ፤ ኦሮሞ፤ ጉራጌ የቋንቋ መብቱን ለማስከበር የየራሱ ቡድን ቢፈጥርም የነዚህ ቡድን አባላት ደግሞ የሌሎች ቡድኖች አባላት ናቸው፡- ኦርቶዶክስ ክርስትና፤ እስልምና፤ ፕሮቴስታንት ወዘተ፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ብለን ካልዳበቅነው በስተቀር በቁንቋ መብት ማስበር የተደራጀው ቡድን ራሱ ወጥ አይደለም፡፡ በቡድን መብትነት የቋንቋ መብቱን ቢያስከብርም ከውስጡ የሌሎች የቡድን መብቶች የሚደፈጠጡበት ሁኔታ አለ፡፡ በቋንቋ ቡድን ማእቀፍ ውስጥ አንዱ የሃይማኖት የውስጥ ቡድን በሌላው የሃይማኖት የውስጥ ቡድን ላይ የመብት ረገጣ ሊፈፅም ይችላል፡፡ የሱማሊኛን ቋንቋ የመጠቀም መብት ለማስከበር የቆመ ቡድን ሱማሊኛ ተናጋሪ የሆኑ ክርስትያኖችን ደብር የሚያቃጥሉ ከሆነ እንኳንና የግለሰብ መብት መነሻ ሊሆኑ ቀርቶ የቡድን መብትም ለማስከበር አይበቁም፡፡ የግለሰብ መብት መነሻውና መግለጫው የቡድን መብት ቢሆን ኖሮ ለምን ይሆን የቡድን መብታችንን አስከብረናል የሚሉት ኦሮሞዎች ሆኑ ሌሎች የግለስብ መብት የሆነውን በኢትዮጵያ ውስጥ የትም አካባቢ የመኖር መብትን በመጣስ ግለሰቦችን ከኖሩበት ቤታቸው የሚያፈናቅሉትና የሚጎዱት? የቡድንን መብት ከግለሰብ መብት ማስበለጥ ማለት ማንም ግለሰብ በሌላው የብሄር ወይንም ብሄረሰብ ክልል ውስጥ አይኑር ከማለት የሚተናናነስ አይደለም፡፡

የብሄር ወይንም የብሄረሰብ ክልል የቡድንን የቋንቋ መብት ለማስከበር ለቡድን የተደራጀ የአስተዳደር ክፍለ ግዛት ነው፡፡ የበላይነት ያለው የቡድን መብት ከሆነ የግለሰብ መብት ሁለተኛ ደረጃ ነው ማለት ነው፤ የሚከበረውም ሲያመች ብቻ መሆኑ ነው፡፡ ገዢ በሆነው የቡድን መብትን በመጠቀም መሬቱ የኛ የቡድኑ ነው፤ ከተማው የኛ የቡድኑ ነው ከተባለና የቡድኑ አባላት ያልሆኑ ግለሰቦች ከክልሉ ከተባረሩ አሰራሩ የቡድን መብትን ያሰከበረ ትክክለኛ እርምጃ ተብሎ ሊደነቅ ይሆን? በአንድ በኩል ሜ.ጄ. አበበን ጨምሮ በርካታ የትግራይ ፖለቲከኞች የትግራይ ተወላጆች ከጎንደር (አማራ ክልል) ተባረሩ በማለት ያማርራሉ፡፡ በሌላ በኩል ለዚህ ድርጊት የህግ ከለላ የሚሰጠውን የቡድን መብት የበላይነት ያወድሳሉ፡፡ ምኑን እንጨብጠው? የትግራይ ተወላጆች ጎንደር (አማራ ክልል) ውስጥ በሰላም የመኖር መብታቸው የሚከበረው እኮ በግለሰብ መብትነት እንጂ በቡድን መብትነት አይደለም፡፡ የመብት ህጉ የሚለው እኮ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ (ግለሰብ ማለት ነው) በየትኛውም የኢትዮጵያ ክልል የመኖር መብት አለው ነው እንጂ ትግራዋይ የትም ክልል፤ አማራ የትም ክልል መኖር ይችላል እኮ አይደለም፡፡ እንደ ቡድን መብቱ የሚሆነው በክልሉ ውስጥ መኖር ብቻ ነው፡፡ ለግለሰብ መብት ቅድሚያ ከተሰጠ ይህ ህግ ተግባራዊ ይሆናል፤ የህግ አስገዳጅነትና ቅጣትም ይስከተላል፡፡ ህዝብ ከየክልሉ ሲባረር የነበረው የቡድን መብትን በማስቀደም በግለሰብ መብት ላይ የገዢነት ሚና እንዲኖረው የተደረገበት የኢህአዲግ ፖለቲካ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የብሄርና ብሄረሰብ የቡድን መብት በሃይማኖት ሳይሆን በቋንቋ መመዘኛ ብቻ የተደራጀ ነው፡፡ ይህ መመዘኛ ብዙ አደገኛ ክፍተቶች እንዳሉት እሙን ነው፡፡ ቡድን ማለት የውስጥ እንድነት ያለው ማለት ሲሆን እንደ ቡድን መብቱን የሚያስከብረው ከቡድኑ ውጪ ከሚመጣበት ጫና፤ ማግለልና መብት መንፈግ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ጫና፤ ማግለልና መብት መንፈግ የሚመጣው ከየት ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በሌላ ቡድን ከተዋቀረ ማእከላዊው መንግስት ነው? ሌላ የጎረቤት ወይንም ከሩቅ ያለ ቡድን ነው? ጫናው፤ ማግለሉና መብት መንፈጉስ እውነታነት ያለው ነው ወይስ የቡድኑን አባላት ወለም ዘለም እንዳይሉ በአንድነት ጠፍሮ ለመያዝ የታቀደ ዘዴ ነው? የቡድን አባላት ያስተሳሰራቸው መመዘኛ ቋንቋ ብቻ ከሆነ ከሌላ ቡድን ጋር በሌላ መመዘኛ የአንድ ቡድን አባላት የመሆን ስሜት ይኖራቸዋል፡፡ አማራ ክልልና ትግራይ ክልል ውስጥ ያሉ ሙስሊሞች በቋንቋ መመዘኛ ብቻ በተለያየ ቡድን ውስጥ መሆናቸው ብቻ የተለያየ ማንነት ያላቸው ሆነው ሊሰማቸው አይችልም፤ ሙስሊም በመሆናቸው በሃይማኖት መመዘኛ አንድ ቡድን ውስጥ ናቸውና፡፡ ቋንቋን መሰረት አድርጎ በሚነሳ የሁለት ቡድኖች ውዝግብ ቋንቋ ድንበር ዘለል የሆነው የሃይማኖት ቡድን አባላትን ጭንቀት ውስጥ እንደሚከታቸው ግልፅነው፡፡ ስለዚህ አንዱን የቡድን መብት (ቋንቋ)ን ለማስከበር ሌላውን የቡድን መብት (ሃይማኖት)ን መሻር ሊሆን ነው፡፡ ግጭት ቢፈጠር ሙስሊም ወንድሞቻቸውን ሊገድሉ ስለሚገደዱ!

ቋንቋን ለብቻው ብንወስደው ቋንቋ አንድ ወጥ የሆነ የውስጥ እንድነቱ የጠነከረ ቡድን የመፍጠር አቅም የለውም፡፡ አንድ ቋንቋ የተለያ ያነጋገር ዘየዎች አሉት፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ውስጥ የራያ፤ የእንደርታ፤ የአድዋ፤ የሽሬ፤ የአጋመ፤ የተምቤን የትግርኛ አነጋገር ዘየዎች በደምብ ይለያሉ፡፡ እዚህ ላይ ነው ችግሩ የሚከሰተው፡፡ እነዚህን ልዩነቶች እንደ ሃብት ከመቁጠር ይልቅ የዘየ ደረጃ በማውጣት የአንዱ መደበኛ (ንፁህ ትግርኛ) አድርጎ በመሰየም የሌላውን ዘየ የትግርኛ ቋንቋን እንደማበላሸት እየተቆጠረ ለለፌዝና ለቀልድ አገልግሎትይውላል፡፡ ይህ ሁኔታ በአማርኛም በኦሮሚኛም ውስጥ ያለ ችግር ነው፡፡ ወደ ቡድኑ ስንመለስ በቋንቋ የተሰራ ቡድን በዘየው ልዩነት የተነሳ ያለው ማፌዝና ማንቋሸሽ ሌላ የውስጥ የቡድን መብት ጥያቄ እያስነሳ ያለ ነው፡፡ ይህ የሆነው የአንዱ የቋንቋ ዘየ የበላይነት በመማሪያ መፃህፍት ዝግጅት፤ በሚድያውና በአስተዳደርና ፍትህ ስራ ላይ በሰፊው ሲንፀባረቅ ቅሬታ እየፈጠረ ስለሆነ ነው፡፡ በአደባባይ በግልፅ የማይታየው ይህ የቡድን ውስጥ ተፅእኖ በቡድን ውስጥ ሌላ የቡድን መብት ይጨፈለቃል፤ ደረጃቸው ያልጠበቁ የተባሉት የዘየዎች ተናጋሪ ግለሰቦችም ኋላ ቀር የሚል ተረብ ላለመስማት በማይመቻቸው የትግርኛ ዘየ ሲቸገሩ ይታያል፡፡ መብት ለማስከበር የተዋቀረው ቡድን ራሱ የአናሳ ቡድንም የግለሰብ መብትም ረጋጭ ይሆናል፡፡

የቡድን መብት የበላይነት የተወሳሰበ ገፅታ የሚኖረው መሬት የረገጠ እለት ነው፡፡ የቡድን መብት ጂኦግራፊያዊ መገለጫው ምንድነው? የሚል ነው ወሳኙ ጥያቄ፡፡ ቀደም ብሎ እንደተገለፀው የብሄር ብሄረሰብ ቡድን መገለጫው ክልል ነው፤ ወሰን ያለው ክልል፡፡ እዚህ ላይ ታሰቢ የሚሆነው አንድ በአንድ መመዘኛ ላይ ተመስርቶ የተዋቀረ ቡድን የራሱ ነው የተባለ ክፍለ ግዛት ይሰጠዋል ነው፡፡ ራሱ በራሱ እንዲያስተዳድርበት የተሰጠው ክፍለ ግዛት ውስጥ የሚኖረው ቡድን አንድ ንፁህ ቡድን እሱ ብቻ ከሆነ ሰላማዊና ፍትሃዊ ነው፡፡ ሌሎች የቋንቋና የሃይማኖት ቡድኖች ካሉ ግን የቡድን መብት ለራስ ይሆንና በሌላ ቡድን ላይ አምባገነንነት ይፈጠራል፡፡ ስለዚህ ማጆሪቲ ነኝ የሚለው ቡድን የራሱን የአንድ ብቻ መመዘኛ ቡድን መብት ሲያስከብር የሌሎች በሌላ መመዘኛ የተዋቀሩ ቡድኖችን መብት ይጨፈልቃል፡፡

በቡድን መብት ላይ የተመሰረተ የአስተዳደር ክልል አመራር የቡድኑም አመራር እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ መሪዎቹም ቀሳውስት ወይንም ፃድቃን ሳይሆኑ ፖለቲከኞች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ስለዚህ የቡድኑን መብት ተከልለው ለፖለቲካ አላማቸው ማስፈፀሚያ እንደሚያደርጉት በቲዮሪ ደረጃ ሳይሆን በተግባር የታየ ነው፡፡ በአማራ፤ በትግራይ፤ በኦሮሞ፤ በጋምቤላ፤ ወዘተ ህዝቦች የቡድን መብት ማስጠበቅ ስም ስንቶች ሃብት እንዳካበቱና ስልጣን ላይ ተቀምጣው እንደቀሩ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የቡድን መብት የበላይነት ለማስከበር ሲባል ከበርቴ የሆነውና በስልጣን የባለገው ፖለቲከኛው ብቻ አይደለም ከሃይማኖት መሪው እስከ የሱቅ ሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር ድረስ የደረሰ ነው፡፡ ለቡድን መብት ማስከበር የተመደቡት ወይንም ከማእከል ጋር በሚደረግ የፖለቲካ ድርድር ራሳቸውን በቋሚነት የመደቡት መሪዎች በስመ ራስ አስተዳደር ግለሰብ ገበሬዎችን ከመሬታቸው ያለ ተመጣጣኝ ካሳ እያፈናቀሉ ለልመና የሚዳረጉት ምን ያለው የቡድን መብት አከባበር ነው? የቡድን መብት ተብሎ የቡድን መብት ማስከበሪያ ስርአት ባይፈጠርስ ኖሮ እነዚህ መሬታቸውን የሚቀሙት ገበሬዎች ግፋ ቢል የሚገጥማቸው ያው መሬት መቀማት አልነበር!? የመናገር፤ የመፃፍ፤ የመቃወም፤ መብት የቡድኑን መብት አደጋ ላይ የሚጥልና የቡድኑን አንድነት አላልቶ ለጠላት የሚያጋልጥ ነው በሚል ፈሊጥ የግለሰብ መብት በግፍ የሚታገድግበትና የጠላት መሳሪያ የሚል ሰሌዳ የሚለጥፍበት የቡድን መብት ልእልና ምን የሚሉት ልእልና ነው? በቡድን መብት የበላይነት ቋንቋውን ለትምህርት፤ ለፍርድ ቤት፤ ለአስተዳደር መጠቀም ከቻለ በኋላ የኢኮኖሚ መሰረቱ የሆነው መሬቱን ቢቀማ ምን አይነት መብት ነው የተቀዳጀው? ፌዝ ነው! ቋንቋውን በመሬቱ ቢለውጥ አይሻለውም ትላላችሁ?

ሌላው የቡድን መብት የበላይነት ችግር በቡድኑ ውስጥ አስኳል ነን የሚል በዝምድና ወይንም በፖለቲካ አመለካከት ወይንም በሃይማኖት ወይንም በትውልድ መንደር የተሰባሰበ ጥቅመኛ የሆነ ንኡስ ቡድን መፈጠሩ ነው፡፡ ይህ ቡድን የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቅም ያለው ከመሆኑ የተነሳ ያለ ውጤታማ ተቀናቃኝ ለብቻው የሰፊው ቡድን አባላትን ሳይሆን የአስኳል ንኡስ ቡድኑን ዘላቂ ጥቅም ሲያስከብር ይኖራል፡፡ ቀሪ የቡድን አባላትም መብታችንን እናስከብራለን ብለው የገቡበት ቡድን የአስኳል ንኡስ ቡድኑ አገልጋዮችና አድናቂዎች፤ ለሱ ህልውና ሟቾች ሆነው ይቀራሉ፡፡ አዚህ ላይ ነው አሃዳዊነትና ፌደራላዊነት ከግለሰብና የቡድን መብት ጉዳይ ጋር አለ አግባብ ተተብትቦ የምናገኘው፡፡ የግለሰብ መብትን የሚያስቀድመው ጨቋኙና አማባገነኑ አሃዳዊነት፤ የቡድን መብትን የሚያስቀድመው ዲሞክራሲያዊ የራስ በራስ አስተዳደር ላይ የተመሰረተው ፌደራሊዝም! ቀደም ብሎ የራስ በራስ አስተዳደር ምን ማለት እንደሆነ አንስቼ ነበር፡፡ የራስ ማለት የቡድን ማለት መሆኑን አይተናል፤ ቡድን ደግሞ ምን አይነት ተፈጥሮ እንዳለው አስተውለናል፡፡ ቡድኑ (የራስ) በቡድኑ (በራስ) ማስተዳደር ማለት እንደሆነም ግልፅ ነው፡፡ ሆኖም ግን ከላይ እንደተነተንኩት የራስ በራስ አስተዳደር በመፅሃፍ ላይ እንጂ በተግባር ሲታይ ከአሃዳዊነት የበለጠ ህዝባዊ አስተዳደር ነው ብሎ ለመሟገት የሚያበቃ ግብአት አልተገኘም፡፡ ይህ የቡድን መብት አጠባበቅ ስልት የፌደራሊዝም ባህርይ ከሆነ የአሃዳዊነትና የፌደራሊዝም የአምባገነንነት ደረጃቸው በምን ሊለይ ነው፡፡ በዚህ አካሄድ ልዩነታቸው አምባገነንነት ከአንድ ዋና ከተማ ወደ አስር የክልል ከተማ መሰራጨቱ ብቻ ነው፡፡ በሌላ አገላለፅ ከማላውቀው የዋና ከተማ ጅብ የራሴ አገር (ክልል) ጅብ ይብላኝ የተባለ ይመስላል፡፡

ከዋናው ከተማ አገዛዝ የበለጠ መልካም አስተዳደር፤ ነፃ ምርጫ፤ ህዝቡን ያሳተፈ ልማት፤ ማህበራዊ ህይወቱን ያዳበረ ኢኮኖሚ፤ ሰላማዊና መግባባት የሰፈነበት ህብረተሰብ፤ ከሙስናና ከዝምድና የጥቅም መሳሳብ ነፃ የሆነ አስተዳደር የሚኖረው ከሆነ ለፌደራሊዝምና ለቡድን መብት እንደ ፃድቃን ታቦት ሊሰራለት ይገባል፡፡ ይህ እኮ በአምላክ ዘንድ የሚወደድ ታለቅ ፅድቅ ነው፡፡ ያኔ አሃዳዊነት እንደ ስይጣን በድነጋይ ይወገራል፡፡ ይህ ግን ህልም ነው፡፡ ከፌደራላዊነትና የቡድን መብት የበላይነት በቲዮሪ ሳይሆን በተጨባጭ ተግባር የሚገኘው የመልካም አስተዳደር እጦት፤ የዲሞክራሲ መዳፈን፤ የክልል አምባገነንነት፤ ድህነት፤ ስደት፤ የጥቂቶች መክበር፤ ከሁሉም በላይ የራስ ክልልን እንደ ርስተ ጉልት የዞ የሃገር እንድነትን ማናጋት ከሆነ አሃዳዊነት ገድሎ ይቅበረኝ፤ ቢያንስ ቢያንስ በሃገር አንድነት ላይ አይደራደርም፡፡ አገር ማለት ደግሞ ፌደራሊስቱም አሃዳዊውም በጋራ የሚኖሩባት ቤታቸው ናት፡፡ ሙግትና ክርከር የሚደረገው አገር ሲኖር ነው፡፡ ሜ.ጄ. አበበ ኢትዮጵያ መሬቷ አይደለችም የህዝቡ አንድነት ነው ያሉት ሁለቱም (ህዝብና መሬት) ናቸው ቢሉ የበለጠ ደስተኛ እሆን ነበር፡፡ የኢትዮጵያዊነት ስሜታቸው ጥልቅ እንደሆነ የገለፁበት አማርኛ ከአንድ ከፍተኛ የጦር መኮነን በመስማቴ የልብ ልብ ተሰምቶኝ ለዚች አገር ተስፋን ሰንቄያለሁ፤ የኢትዮጵያ ጠላቶችን ቅስም የሚሰብር አነጋገር ስለሆነ፡፡ በተግባር እንድናየውም ምኞቴ ነው፡፡ ህዝብ ትውልድ ነው፤ይኖራል ያልፋል፡፡ የማታልፈውና የመጣው ሁሉ ትውልድን የምታስተናግደው መሬቷ (ኢትዮጵያ) ናት፡፡ የማንኛውም ትውልድ ዋና አላማ መሆን ያለበት የሚቀጥለው ትውልድ የሚኖርባትን መሬት መጠበቅ ነው፡፡ አሁን የምንወልደውና የምናሳድገው ልጅና የልጅ ልጅ እኮ ነው የወደፊት ትውልድ ማለት! ያሁኑ ትውልድ ይቺ አገር እንዳለች ለልጆቹ ለማቆየት ራሱን መስዋእት ማድረጉ ያለ የኖረ ለወደፊቱም የሚደረግ ነው፡፡ አባቶቻችንና አያቶቻችን ወደ ጦር ግንባር እየፎከሩ ሲተሙ የነበሩት ዲሞክራሲ ባልነበረበት በፊዩዳል ስርአት ዘመን ነበር፡፡ ዴሞክራሲ ይከበር አየተባለ አገርን ለአደጋ የሚያጋልጥ ተግባር ላይ መሰማራት የኢትዮጵያ ባህል አይደለም፤ ውርሳችን አይደለም፡፡ ስለዚህ ወንድሜ ከፖለቲካ አገር ይቀድማል ልበልዎትና እንሰነባበት፡፡ ስላም ይሁኑ፤ አገራችንም ሰላም እንደትሆን ፀሎት እናድርስ፡፡

Back to Front Page