Back to Front Page

"እኛ የመጀመሪያዎቹ በታኞች ላለመሆን ነው እየጣርን ያለነው" አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው

"እኛ የመጀመሪያዎቹ በታኞች ላለመሆን ነው እየጣርን ያለነው" አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 08-27-20

አምባሳደር ወንድሙ የተጠቀመበት አገላለፅ ትግራይ ውስጥ ያለውን ስሜት በግልፅ የሚያንፀባርቅ ነው። ህወሓት ሙስናና የአስተዳደር በደል ፈፅማለች በሚል የሰራችውን ሰማንያ ከመቶ በጎ ተግባር ወደጎን በማሽቀንጠር ከያቅጣጫው የሚወረወርባት የነገር ዱላ አብሮ እየተመታ ያለው የትግራይ ህዝብ ነው። የህወሓትን አመራር ነጥሎ መምታት አይቻልም። ይህንን ሃቅ ወርዋሪዎቹ አሳምረው ያውቁታል። ይፋ የማይደረገው ውስጣዊ ኢላማቸው ህወሓትን የወለደውና ያቀፈው ህዝብ መሆኑ ለህዝቡ የተሰወረ አይደለም። ስድስት ፐርሰንት እየገዛን ነው ሲባል የኖረው ትግሬ ገዛን ለማለት እንጂ ህወሃት ገዛችን ለማለት አይደለም። ስድስት ፐርሰንት የህዝቡ የስነህዝብ ድርሻ እንጂ የህወሃት አይደለም። ህወሓት ስትታይ የኖረችው እንደ ህዝብ ተወካይ እንጂ እንደ ማንኛውም ፓርቲ አልነበረም። ከስልጣን ከተገለለች ወዲህ ግን ህወሓትና የትግራይ ህዝብ አንድ አይደሉም እየተባለ ነው። ህወሓትን ከስልጣን ለማግለል የስድስት ፐርሰንት ህዝብ ወኪል ናት ተባለ፣ ከተገለለች በኋላ ደግሞ ነጥሎ ለመምታትና የትግራይ ህዝብ በቂ መከታ የሌለው አድርጎ እንደድሮ በወኪል ለመግዛት ህወሓት የህዝቡ ተወካይ አይደለችም ተባለች። የኢትዮጵያ ፓለቲካ ራሱን የሚቃረን ሲሆንም "ልክ ነው" ይባላል። ከትግራይ ሲመጣ ልኩ ስህተት፣ ከመሃል ሲመጣ ስህተቱ ልክ ይሆናል። ሃቅ አንፃራዊ ቢሆንም በትግራይና በመሃል ባለው ግንኙነት ግን ቅጥ ያጣ ይመስላል።

Videos From Around The World

ከየትም አቅጣጫ የሚወረወሩት ቃላትና የሚፈፀሙት የህግ ከለላ ያላቸው የሚመስሉ ህገወጥ ድርጊቶች ትግራይ ላይ ሲዘንቡና የጊዜ ገደብ ሳይኖራቸው ሲቀጥሉ ለተቀባዩ ወገን ትልቅ ፈተና ነው። እየተፈፀመ ያለውን "ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው" የሚለው ተረት በትክክል ይገልፀዋል። በአንድ በኩል ትግራይ ከኢትዮጵያ ልትገነጠል ነው የሚል ወሬ ሲሰማ አንዱ "ዘራፍ: እስቲ ይሞከር!" ይላል፣ ሌላው ደግም "ትግራይ እኮ የኢትዮጵያ መነሻ ናት እንዴት ይሆናል?" ብሎ ይሟገታል። ይህ በካሮት ይሁን በዱላ ትግራይ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቆይ ፍላጎትና ቁርጠኝነት ያለ ያስመስለዋል። በተቃራኒው ደግሞ "ትሂድ፣ ግልግል ነው፣ ምን ይቀርብናል፣ የረባ አስተዋፅኦ ሳያደርጉ በጀታቸውን መሸፈን ነው የሚቀረልን፣ ኢትዮጵያ ሰላም ታገኛለች" የሚሉት ደግሞ ቁጥር ስፍር የላቸውም። አንዳዶቹማ "ትሂድ ግን ወልቃይትንና ራያን ይዛ ግን አትሄድም" የሚል የትግራይን ህዝብን ባእድ የሚያደርጉ ቃላት ይናገራሉ ይፅፋሉ። ኤሪትርያ ወደቦቿን ትታ የምትገነጠል ቢሆን ኖሮ በእልልታ ትሸኝ እንደነበር የሁሉም ሰው ሆድ ያውቃል። ወደቦቿ በማይፈለጉበት ዘመንማ ኢጣሊያ በነፃ ተረክባት የለ። ሰሜኑን በሚመለከት ታሪክ ራሱን እየደገመ ነው።

ትግራይ ምን እንደምትወስን ተጨንቃለች። ትግራይ በግዴለሽነት ወደ ግንጠላ እየተገፋች ነው። እንደ አንዲት የኢትዮጵያ አካል የሆነች ክልል ሆና መታየት ካቆመች በጣም ቆይታለች። የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓት ለኢትዮጵያ ደህንነት፣ ሰላም፣ እድገትና አለም አቀፍ ዝና ያበረከተቻቸው ታላላቅ ስትጦታዎች ከህዝብ አዕምሮ ጨርሰው እንዲጠፉና በመጥፎ ድርጊት ብቻ እንድትታወስ ከፍተኛ ዘመቻ እየተካሄደ ስኬት እያስመዘገበ ነው። የ27 አመት ጨለማ ተብሎ "ትልቅ ነበርን፣ ትልቅ እንሆናለን" እየተባለ ነው። ከህወሓት በፊት (በፊዩዳሊዝምና ወታደራዊ አምባ ገነንነት ዘመን) ትልቅ ነበርን በህወሓት ዘመን ትንሽ ሆንን፣ ህወሓት ከጠፋችና የትግራይ ህዝብ ከተዳከመ ወይንም ከተገነጠለ ግን እንደድሮው በድሮዎቹ እየተመራን ትልቅ እንሆናለን ነው ትርጉሙ። ከትግራይ ይልቅ ከሲዳማ አንድ አመት ቀደም ብላ የኢትዮጵያ ሰሜናዊ "ክልል" የሆነችው ኤሪትርያ ናት። በቲዮሪ ሳይሆን በተግባር ኤሪትርያና ትግራይ ቦታ ተቀያይረዋል። የማይመለስ በሚመስል ሁኔታ ትግራይ ከኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ስነ አዕምሮ እንድትሰረዝ ከፍተኛ የሆነ የባህል፣ የሚድያ፣ የፓለቲካ፣ የትምህርት ዘመቻ እየተካሄደ ነው። በርካታ ህዝብና የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑ ከያንያን የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ከትግራይ ይልቅ ወደ ኤሪትርያ እንዲያዘነብል ስልታዊ የሆነ ስራ እየሰሩ እንደሆነ ልብ ብሎ ለተከታተለው በጣም ገሃድ ነው። ህዝብ አንድ ሆኖ ተሳስሮ የሚኖረው በፓለቲካ ገመድ ሳይሆን በማህበራዊ ገመድ ነው። ይህን የኢትዮጵያን ህዝብ ከትግራይ ጋር የሚያስተሳስረው ማህበራዊው ገመድ በየመኖሪያ ሰፈሩ፣ በየስራ መስኩ፣ በየትምህርት ተቋሙ ውስጥ እንዲበጣጠስ በቡድን ይሁን በግለሰብ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት እንዳለ እሙን ነው። ምንም ፓለቲካ የማያውቁ ሴቶች ቡና እየጠጡ "ትግሬዎች ናቸው እኮ የሚበጠብጡን" እያሉ እየተቀባበሉ ሲያወሩ እንደመስማት የሚያስፈራ ነገር ምን አለ? ምግብ ቤትና መዝናኛ ቤት ውስጥ ስልክ ላይ ጠሪውን በትግርኛ የሚያናግር ሰው ከሌላ ፕላኔት የመጣ ባእድ ወይንም ቦምብ ኪሱ ውስጥ እንደያዘ ሽብርተኛ  የሰዎች አይን ሊበላው እስኪደርስ ድረስ የሚያፈጥበት ከሆነ እንዴት ነው ዜጋ ነኝ ብሎ በራስ መተማመን የሚኖረው? የትግራይ ተወላጅ ከትግራይ ክልል ውጪ ሲኖር ማንነቱን ደብቆ የሚኖር ከሆነና አንድ ቀን ሲታወቅ ሰው ሁሉ ቀበሮ የገባበት የበግ መንጋ አይነት ባህሪ የሚያሳይ ከሆነ የትግራይ ህዝብ እንደ ባእድ ብቻ ሳይሆን እንደ ጠላትም እየታየ ነው ማለት ነው። ብዙ የመሃል አገር ሰዎች ይህን ሲነግሯቸው ሽብር እንደምታወራ አድርገው  ነገሩን ማቃለል ይቀናቸዋል። ሚስማሩ የሚፈጥረው ህመም የሚያውቀው ጫማ ለባሹ ነው እንጂ ሚስማሩ ራሱ አይደለም።

ትግራይ እንድትገነጠል የሚገፋፉት ሁሉ ለመገንጥሏ ሃላፊነት መውሰድ አይፈልጉም። የኤሪትርያ መጨረሻ ላይ መገንጠል ሃላፊነት የሚወስደው ነገር ከተበላሸ በኋላ መልክ ለማስያዝና ህዝቡን ለመታደግ የመጣው ሻዕቢያ አይደለም። በጊዜ ሂደት ለኤሪትርያ ጨርሶ መገንጠል ቀዳሚ ምክንያት የሆነው የመሃል አገር ግፊት ነበር። ያመረረ ሲሄድ ግን በራሱ ፍላጎት ሄደ ይባላል አድላዊ በሆኑት የታሪክ መዛግብት። ሻዕቢያን የወለደው ማእከላዊ መንግስትና ተባባሪዎቹ ነበሩ። ሻዕቢያ ሆነ ጀብሃ የማእከላዊ መንግስት በኤሪትርያ ላይ የነበረው የተሳሳተ ፓሊሲ ውጤቶች ናቸው። ቢያንስ ሁለት ታላላቅ የፓሊሲ ጥፋቶች ታይተዋል። በትግራይም የትግራይ ነፃነት ፓርቲ የሁለት አመት የማእከላዊ መንግስትና የቀድሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ግዴለሽ ንግግሮችና ድርጊቶች የፈጠሩት የተስፋ መቁረጥ ውጤት ነው። የድመትን ባህሪይ አሳምረው የሚያውቁት አይጦች ናቸው "እኛም መክረናል ጉድጓድ ጭረናል" ያሉት። የሚፈልጓቸው ለፍቅር ሳይሆን ለጣፋጭ ምሳነት እንደሆነ ስለተገነዘቡ። እኔ በበኩሌ የትግራይ ነፃነት ፓርቲ መመስረትን አክርሬ ስቃወም ቆይቻለሁ። በመሃል አመራርና ደጋፊዎቹ የሚነገሩት ቃላትና የሚፈፀመው ድርጊት ግን እንዲህ አይነት ፓርቲ መመስረቱን ለመቃወም የሚያበቃ የሞራል ልእልናን ይነፍገኛል።

አምባሳደር ወንድሙ በጥሩ ቃላት የገለፀው ጉዳይ ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው። የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች ውስጣቸው ትግራይ እንድትገነጠል ይፈልጋሉ፣ ለዚህም የሚገፋፉ አቀጣጣይ ቃላት ይናገራሉ ግብረመልስ የሚጋብዙ ድርጊቶች ይፈፅማሉ። ለትግራይ መገንጠል ግን ሃላፊነት መውሰድ አይፈልጉም። ትግራይም እንድትገነጠል ግፊት ቢደረግባትም ከገደብ ያለፈ ትእግስት ላይ ትገኛለች። ማእከላዊ መንግስት የትግራይን ምርጫ ውጤት ካልተቀበለ ነገሩ ወዴት እንደሚያመራ በግልፅ እየታወቀ "ህገ ወጥ ነው፣ እርምጃ እንወስዳለን" የሚለው ዛቻ "ወደ ግንጠላ ቢያመራም እሰየው ነው" የማለት ያህል ይመስላል። ብዙዎች የትግራይ ትእግስት መገንጠልን መፍራት አድርገው ቢተረጉሙትም ምክንያቱ እሱ አይደለም። ትግራይ ተገዳ ከተገነጠለች መቸም አዲስ እንደተወለደ ጥጃ ተንገዳግዳም ቢሆን መቆሟ አይቀርም። የትግራይ ስጋት የትግራይ መገንጠልን ተከትሎ በማይቀረው የ"ዶሚኖ መነካካት" ኢትዮጵያ ትፈርሳለች የሚል ነው። አምባሳደር እንዳለው ለዚህ አስከፊ ሂደት መጀመር ትግራይ ቀዳሚ መሆን አትፈልግም። የኢትዮጵያ መስራች ናትና ጭንቀቱ ቀላል አይደለም። ይህን የተገነዘበላት ግን ያለ አይመስልም። የኢትዮጵያ ፓለቲከኞች እንደበሬው እያዩ ያሉት ህወሓትን የማጥፋት ሳሩን እንጂ የአገር መበተን ገደሉን አይደለምና።

 

Back to Front Page