Back to Front Page

መደመርና ብልፅግና ፓርቲ ችግራችንን ይፈታሉ?!

ማስታወሻ

ይህ አጭር ፅሑፍ የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ (የአሁኑ የብልፅግና ፓርቲ)ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፃፉት “መደመር” በሚል ርእስ የተፃፈ የመደመር እሳቤ (ፍልስፍና) መፅሓፍ ላይ የቀረበ አስተያየት ነው፡፡ ትችት ብቻ ግን ኣይደለም መጨረሻ ላይ ሌላ የተሻለ አማራጭ አለ የሚለወን ሓሳብም ያቀርባል፡፡ ፍርዱን ለአንባቢ ትቶ የበኩሉን አስተዋፅኦ ለማድረግ ታስቦ የተፃፈ የችግራችን መፍተሔ ፍለጋ አካል ለመሆን ያለመ ነው፡፡

አቀራረቡ መደመር በሚል ርእስ የተፃፈውን መፅሓፍ ርእሶች ቅደም ተከተል የተከተለ ሆኖ በየክፍሉና በየምዕራፉ አስተያየቱንእያሰፈረ በመጨረሻ ላይ ግን ስለመፅሓፉ ማጠቃለያ አስተያየት የያዘ ነው ለአንባብያን የሚቀለው ይህ ዓይነት አቀራረብ ሳይሆን አይቀርም በሚል የተመረጠ አቀራረብ ነው

መቅድም

በመፅሓፉ መቅድም ገፅIII ላይ ፀሓፊው የሚከተለውን ብለዋል፡- “የመደመር ዕሴት የኛ ነው፡፡ ያመነጩትም ሆኑ ያዳበሩት ገባሮቹ ሁለት ናቸው፡፡ አንዱ በዘመናት ታሪካችን ውሰጥ የነበሩና ያሉ ሀገራዊ ባህሎቻችን አምጠው የወለዷቸውን የሕብረተሰባችን የልብ ትርታ የተቃኛባቸው ዕሴቶቻችን ሲሆኑ፣ ሌላው ደግሞ የተፈጥሮ ሕግ ነው፡፡ ለዚህም ነው ለቁልፍ ችግሮቻችን ቁልፍ መፍትሔዎችን እንደሚያቀብል የማምነው፡፡”

የህዝባችን ዕሴቶችና የተፈጥሮ ሕግን የፍልስፍናው ወይም የመደመር ዕሳቤ ምንጭ መሆን ላይሚና ቢኖራቸውም የሕብረተሰብ ማሕበራዊ ኢኮኖምያዊና ፖለቲካዊ ዕድገት ሕግጋቶችንለምን ዋናው መነሻ አላደረጉም? ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ አግባብነትና ጠቃሚነት ያለው፣ ለአንድ ሕብረተሰብ ዕሴቶችም መሰረት የሚሆነው የማሕበራዊ ሳይንስ መሰረተ ሓሳብ የሆኑ የማህበራዊ ዕድገት ነባራዊ ሕጐችን መነሻ ማድረግ ነው፡፡ ለምን እሱን መነሻ ማድረግ አልፈለጉም? ስለሰው ልጅ ማህበራዊ ኢኮኖምያዊና ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ ዕድገት በታሪክ፣ በሶሽዮሎጂ፣ በአንትሮፖሎጂ፣ በፖለቲካል ሳይንስ፣ በኢኮኖሚክስ የተደረጉ ዝርዝር ጥናቶችን በመቀመር የተገኘ ገዥ የሆነው የማህበራዊ ሳይንስ መሰረተ ሓሳብ ወይም የማህበራዊ ዕድገት ሕግን ወደጐን ትቶ በተፈጥሮ ሕግና በህዝቡ ዕሴት ላይ ብቻ ታጥሮ የተነደፈ ፍልስፍና ምን ያህል ሳይንሳዊ ይሆናል?

ለአሁን ግን አንድ ነገር ብቻ ጠቅሶ ማለፍ ይበቃል የማሕበራዊ ሳይንስ ሕግ የሕብረተሰብን ዕድገት ወደፊት የሚወስደው አሮጌውን ስርዓት ከነ ባለቤቶቹና አስተሳሰቡ አስወግዶ በለውጥ ሓይሎችና በለውጥ አስተሳሰብ፡፡በአዲስ ተቋማዊ ወይም መዋቅራዊ አደረጃጀት የሚተካ የስርዓት ለውጥ ትግል አማካኝነት ሲካሄድ ነው ይላል፡፡ የመደብ ትግሉ ተመሳሳይ የጋራ ጥቅም ያላቸውን ባንድ ላይ በማሰለፉ ተፃራሪ ጥቅም ያላቸውን በመታገል ሕብረተሰብን ወደፊት ይወስዳል ይላል፡፡ ተፃራሪ ጥቅሞችና ሓይሎችን ለመደመር መሞከር መጨረሻው የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጉልበቱ የላቀ የሆነው የበላይነቱን እንዲያረጋግጥ ያደርጋል እንጂ ሁለቱንም ተጠቃሚ አያደርግምና!!

ስለሆነም የማይደመሩትን የግድ ተደመሩ ብሎ ማስታረቅ የበታችናተገዥ ሆኖ የሚቀጥል ብዙሃን እንዲኖር ያደርጓል፡፡

መግብያ

ገፅ VI ላይ ፀሓፊው እንዲህ ይላሉ፡- “በዘውዳዊው ስርዓት ጊዜ ሁሉ ነገራችን እንደምዕራቡ ዓለም ለማድረግ ርእዬታችንና ፖሊሲዎቻችንን ወደዛ ያዘነበሉ እንዲሆኑ ስናደርግ ነበር፡፡ ከአብዬቱ በኃላ (ከየካቲት 1966 አብዬት በኃላ) ደግሞ አብዛኛው ወደ ምስራቁ ዓለም ያዘነበለ ርእዬትና ፖሊሲ ተከተልን” ካሉ በኃላ 2ኛውአንቀፅ ላይ “ዳሩ ግን ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ነገር አልተፈጠረምወደ ውጭ ያየነውን ያህል ወደ ውስጣችን ስላልተመለከትን ለሀገራችን ችግር ሃገር በቀል መፍትሔ ስላልፈለግንለት ችግሮቻቸን መልካቸውን ቀያየሩ እንጂ አልተወገዱም”  የማይካድ የጐላ ለውጥ አለ፡፡ በ1966 ዓ.ም በተካሄደው አብዬት ምክንያት በሂደት የንጉስ አገዛዝና የመስፍናዊ ስርዓት የመሬት ይዞታ ተወግዷል፡፡ በኢህአዴግ ገዥ ፓርቲነት ጊዜ ደግሞ ህዝባችን ተስፋ ያደረገበትና ተጠቃሚ መሆን የጀ መረበት ዓለም የመሰከረለት ልማትና ሰላም የዴሞክራሲ ጅምር ታይቷል፡፡ እንዴት የተሻለ ነገር አልተፈጠረም ይላሉ፡፡

በገፅ VII በ1ኛውና በ2ኛውአንቀፅ ላይ ደግሞ እንዲህ ይላል “ሀገራችን ለዘመናት ሲከማቹ ለቆዩት ችግሮችዎ መፍትሔ የምታገኘው ከባሕር ማዶ ቃርመን ካመጣናቸውና ምንም ሳንመረምር ከገለበጥናቸው የተወሶ አስተሳሰቦች ይልቅ እዚሁ በሀገራችን ለዘመናት ሲከማቹ ከቆዩት መልካም እሴቶቻችን እንደሚሆን መገንዘብ አለብን፡፡ እርግጥ ነው ከውጭ የምናገኛቸውን እውቀቶችም ሆኑ ልምዶች ከራሳችን ወግና ልማድ ጋር አስማምተን በልካችን ሸምነን መልበስ ለእኛ እንግዳ ተግባር አይደለም፡፡ መንገዳችን የራስ ጥሎ የሰው አንጠልጥሎ መሆን የለበትም የጐረቤትን ከራስ ጋር አላምዶና አዋድዶ እንጂ”

የንጉሱና የደርግ አገዛዞች ያደረጉትን ትተን ኢህአዴግ ግን ገዥ ፓርቲ ሆና ከባሕር ማዶ ቃርሞ ምንም ሳይመረምር ገልብጦ ተግባራዊ ያደረገው የውጭ አስተሳሰብ የለም ወቀሳው ኢህአዴግንም የሚያካትት መሆኑ የሚያመላክት ስለሆነ ኢህአዴግ ምንድነው ያደረገው ግልፅ መደረግ አለበት የኢህአዴግ አንቀፅ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲ) ወደ መዘርዘር ሳንገባ ከውጭ ምንነቱ ሳይመረመር የተገለበጠ ነበር ወይ? ባጭሩ መመለስ ይቻላል፡፡ ዋና ዋና ማሳያዎቹን ብቻ መጥቀስ ይበቃል፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ በኛ አገር ለብዙሃኑ ተጠቃሚነት የቆመ ለነፃ ገበያ ዕድገት ይሁን ለሶሻሊስት ስርዓት ግንባታ ማነቆ የሆኑ መስፍናዊ ስርዓትና ጥገኛ የነፃ ገበያ አቅጣጫን በማስወገድ የኪራይሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚን በልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በመተካት ለሶሻሊዝም ሳይሆን ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ለዴሞክራሲ ግንባታ ተጠቀመበት፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ወደ ሶሻሊዝም አቋራጭ መንገድ እንዲሆን ታሰቦ የተነደፈቢሆንም ኢህአዴግ ግን ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ለዴሞክራሲ እውን መሆን ተጠቀመበት፡፡

የምስራቅ ኤስያ አገሮች የተከተሉት ልማታዊ መንግስት ዴሞክራሲን ያገደ ነበር፡፡ግን ፈጣን ቀጣይና ፍትሓዊ ልማት ያመጣ ነበር፡፡ የልማት ስኬቱን እንደ መልካም ልምድ ወስዶ የዴሞክራሲ ጉድለቱን ግን አልተቀበለም፡፡ ዴሞክራስያዊና ልማታዊ መንግስት ከሆነ ነው የኢትዮጵያን ችግር የሚፈታው አለ፡፡ በዚህም ላይ ተመስርቶ የተሟላ ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶችን ያረጋገጠ፣ የግልና የቡድን መብት ያጣመረ ሕብረ-ብሄራዊ ፌዴራል ስርዓት የሚመስረትበት ሕገ-መንግስት እንዲፀድቅና እንዲተገበር አደረገ፡፡

ታድያ ንጉሱ እና ደርግ የውጭ ርእዬትና ፖሊሲ እንዳለ ገልብጠው ከሆነ እነሱን ለይቶ መውቀስ ነው እንጂ ኢህአዴግንም ያጠቃለለ ፍረጃ ሃቅነት የለውም፡፡ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በሚገባ የተገናዘበ ሕገ-መንግስትና ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራሊዝም፣ እንዲሁም ከምስራቅ ኤስያ መንግስታት የተለየ ዴሞክራስያዊ ልማታዊ መንግስት፣ ከነሱ የተለየ ግብርናና ገጠር ማእከል ያደረገ የልማት ስተራተጂ የነደፈና ተግባራዊ ያደረገ ኢህአዴግ እንዴት ከውጭ አገር ርእዬትና ፖሊሲ እንዳለ ከገለበጡት ጋር አብሮ ይፈረጃል? ሰብአዊና ዴሞክራስያዊ መብቶችን ያገዱ የተማከለ የመንግስት አደረጃጀትና የአንድ ፓርቲ ፖለቲካዊ ስርዓት የነበራቸው እንዱስትሪ መር የልማት ስትራተጂ የተከተሉ የምስራቅ ኤስያ ልማታዊ መንግስታት ርእዬትና ልምድን ምንም ሳይለውጥ እንዳለ ኢህአዴግ ገልብጦ በኢትዮጵያ ተግባራዊ አላደረገም፡፡ በዛ መንገድ መፈረጁ ሓቅነት የለውም፡፡ የፈጣን ቀጣይና ፍትሓዊ ልማት ልምዳቸውን ብቻ ነው የወሰደው፡፡

ገፅ VII ላይ ፅሑፍ እንዲህ ይላል፡፡ “จจበዋናነት “ለሀገር በቃል ችግር ሀገር በቀል መፍትሔ” በሚል መርህ መጓዝ መጀመር እንዳለብን ግን ፈፅሞ ሊዘነጋ አይገባም” ይህ መርሕ ከራሳችን ተጨባጭ ሁኔታ ሃቀኛ ግምገማ (ጥናት) የሚነሳ እሱን የሚፈታ ኢትዮጵያዊ ይዘትና አፈፃፀም ያለው መፍትሔ እንከተል የውጭ ልምድም ለዚህ ግብ በሚያገለግል መንገድ በቂ ትኩረት ተሰጥቶት መቀመርና ከሁኔታችን ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል ለማለት ከሆነ ኢህአዴግም ተግባራዊ ሲያደርገው የነበረ ነው፡፡ የውጭው ልምድ ባጠቃላይ ከረዥሙና ውስብስቡ የዓለም ህዝቦች ታሪክ የተቀመረ ሓሳብ ሆኖ እያለ አያስፈልገንም እኛም ወድቀን ተነስተን በራሳችን አቅም ምርጥ መፍትሔ ማፍለቅ እንችላለን ለማለት ከሆነ ቁምነገሩ በመቶዎች ዓመታት የተቀመረን የዓለም ልምድ ማናናቅና የወደቁበትን ለመድገም ለመላላጥ ሊሆን ይችላል ወይም ደግሞ በአጥጋቢ መንገድ መፍትሔ ተገኝቶለት ተመልሶ ያደረን ነገር እንደ አዲስ ለመመለስ መዳከር ነው(Re-inventing the wheel)

አልያም ከማን አንሼ በሚል ራስን የመካብ አባዜ ተነሳስቶ ወንዝ የማያሻግር የትም የማያደርስ ጥሬ ሓሳብ አምጥቶ አገሪቱንና ህዝቦችዋን የሙከራ ናሙና ማድረግ ይሆናል፡፡ ከባድ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እኛም ለዓለም ቢያንስ ለኛ ዓይነቶቹ ድሀ አገሮች መፍተሔ የሚሆን ሓሳብ ማመንጨት እንችላለን ለማለት ከሆነ ዳግም የአገራቸን ጥንታዊ ስልጣኔም ይሁን የቅርብ አመታት ስኬታማ የልማት ስራችን ለዓለም ያበረከተው ጥሩ ነገር አለ፡፡ አሁንም ወደፊትም ማበርከት እንችላለን በሚል ትርጉም ቢሆን ያስማማናል፡፡ ግን የመደመር ዕሳቤ አላማ ያለፈውንጥሩ ስራ ማጣጣል፣ ታሪካችንን ማዛባት ነው ስርዓቱን ማፍረስ ነው ጉድለቱን በልኩ ለይቶ ለማረምና ጥንካሬውን ለማስቀጠል ኣይደለም አዲስ ጥሩ ሓሳብ ለኛ ዓይነቶቹአገሮችም ለማመንጨት አይደለም፡፡ ቅልበሳ ነው፡፡የመደመር እሳቤ እውነት ለኢትዮጵያ መፍትሔ ይሆናል ወይ? የሚለው ጥያቄ ግን በሚገባ ምላሽ የሚያገኘው ይዘቱ ሲፈተሽ ይሆናል፡፡

ለማንኛውም ባለንበት ዘመነ ግሎባላይዜሽንና የመጠቀ ዕድገት ወቅት ከራስ ልምድና ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት ብቻ ሳይሆን በዛው ላይ ሌሎች ወድቀው ተነስተው ብዙ ዋጋ ከፍለው ጊዜ ወስዶባቸው ያገኙትን ዕድገት ባጠረ ጊዜ በጥራት ባነስተኛ ወጪ ትጉህ ተማረና ራሱን የሚያውቅ ተማሪ በመሆን ወስዶ የበለጠ ስኬት ማግኘት እንደሚቻል መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ዝግ በረኝነት በንግድና ኢንቨስትመንት አያስኬድም ካልን የሓሳብ ዝግ በረኝነት ዳግም የባሰ ይጐዳል፡፡

የሚቀጥለው ዝርዝር  አስተያየት ፅሑፉን ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታና ከማህበራዊ ዕድገት ሕግጋት አንፃር የሚተነትን ፖለቲካዊ ግምገማ ነው፡፡

ክፍል-አንድ

1.1.የመደመር ዕሳቤ መነሻ ሓሳቦች፣

ምዕራፍ - አንድ

በዚህ ምዕራፍ ሁለት መሰረት ሓሳቦች ቀርበዋል፡፡ አንደኛው የሰው ልጅ ፍላጐቶች ባንድ በኩል ትስስርና አንድነት አላቸው፡፡ በሌላ በኩልም ተቃርኖ አላቸው፡፡ ፍላጐቶቹን ማሟላት የሚቻለው ሲደመሩ ነው ይላል፡፡ ሁለተኛው ዳግም የሰው ልጅ ተቃራኒ ባህሪያት ያሉት መሆኑና እሱን በትክክል ለመረዳት ርእዬተ ዓለማዊ እይታን ከማስቀደም ለሰው ልጅ ተፈጥሮ ያለንን እይታ እናስቀድም እይታችን ብርእዬተ ዓለም ከሚቀዳ ከሰው ተፈጥሮ የሚነሳ ቢሆን ትክክኛ እውቀት ይሰጠናል የሚል ነው፡፡ አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

ገፅ 4 በ4ተኛው አንቀፅ ላይ “በመደመር መነፅር ሲታይ የሰው ልጅ ፍላጐቶች ተደማሪ ባህርይ እንዳላቸው መረዳት ይቻላል፡፡ በአንድ በኩል ፍላጐቶቹ እርሰ በርስ የተሳሰሩና ተደማሪ ፍላጐቶቹ ሲሆኑ በሌላ በኩል ደግሞ በመካከላቸው ተቃርኖ ስላለ ሰዎች ፍላጐቶቹን በተናጠል ሳይሆን በመደመር ብቻ ሊያሳኩዋቸው የሚችሉ ናቸው” ይላል፡፡ በመቀጠልም የሰዎች መልካም ባህርያትና አሉታዊ ባህርያትን ይዘረዝርና “ስለሆነም በአንድ በኩል በፍላጐቶቹ መካከል ያለውን ውስጣዊ ትስስርና አንድነት በሌላ በኩል ደግሞ በመካከላቸው ያለውን ተቃርኖ ስንመለከት ፍላጐቶቹን ማሟላት የሚቻለው ፍላጐቶቹም ሆነ ሰዎች ሲደመሩ መሆኑን መገንዘብ እንችላለን” ይላል፡፡(ገፅ 5፣ 4ተኛው አንቀፅ)

የዚህ መሰረተ ሓሳብ ፍሬ ነገር ተቃርኖ ያላቸው የሰው ልጅ ፍላጐቶችና ባህርያትን በመደመርዕሳቤ ማስታረቅ ይቻላል፡፡ በዚህ መንገድ ብቻ ነው የሁሉም ፍላጐቶች የሚሟሉት የሚል ነው፡፡

ይህ ጅምላዊ ትንታኔ ስህተተ ነው፡፡ የብዙሃኑ ጭቁኖች የተለያዩ ፍላጐቶች መለስተኛ ተቃርኖ እንጂ መሰረታዊ ተቃርኖ ስለሌላቸው ማጣጣም ማቻቻል ማስታረቅ ይቻላል፡፡ የጭቁኖች ወይም የቡዙሃኑ ፍላጐትና የገዥዎች የመዝባሪ ኪራይ ሰብሳቢዎች ፍላጐትን በመደመር ዕሳቤ ማስታረቅና ሁሉንም ተጠቃሚ ማድረግ ግን አይቻልም፡፡ የመሳፍንትና የአርሶ አደር የወራሪ ባዕድ ሓይልና የነፃ ሃገር ህዝብ ፍላጎቶችን በመደመር ሁለቱንም ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም፡፡

ለምንድነው የማይቻለው? ኪራይ ሰብሳቢዎች ከውድድርና ከሕግ ውጭ በሙስና በማጭበርበርና እጥረት በመፍጠር አለአግባብ የሚበለፅጉ ምንም እሴት ሳይፈጥሩ ሌላው የፈጠረላቸውን የሚዘርፉ ናቸው፡፡ ሰርቶ አደሩ ብዙሃን ግን ላባቸውን አንጠፍጥፈው ጥረው ግረው በሕግና ስርዓት ተገዝተው ኑሮአቸውን የሚያሻሽሉ እሴት ፈጣሪ ናቸው፡፡ ልማታዊ ባለሀብቶችም በውድድርና ሕግ በማክበር እሴት በመፍጠርሀብት የሚፈጥሩ ናቸው፡፡ ታድያ በምን ተአምር ነው ብዙሃኑና ልማታዊ ባለሀብቱ ከክራይ ሰብሳቢው ጋር ተደምረው የሁሉምፍላጐቶችና ጥቅሞች የሚሟሉት? ኪራይ ሰብሳቢው የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቱና ተግባሩን እርግፍ አድርጐ ትቶ ወደ ሕጋዊ ውድድርና እሴት ፈጣሪነት ልማታዊ መንገድ ካልገባ በስተቀር ሊደመር አይችልም፡፡ ሊቀነስ እንደሆነ እንጂ!! ካልሆነ ደግሞ ሁላችሁም የግድ ተደመሩ የሚባል ከሆነ ሁላችሁም በክራይ ሰብሳቢ አመለካከትና ተግባር ተጓዙ ለኪራይ ሰብሳቢዎች አገልጋይና ተገዥ ሁኑ ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለኪራይ ሰብሳቢዎች ጥቅም የቆመ ስርዓት ይፈጥራል፣ የኪራይ ሰብሳቢዎች መንግስት ይመሰርታል አያጅቦ ሳታማሃኝ ብላኝ አሉ!!

ስለሆነም መደመር የጭቁን የብዙሃን ህዝቦች ፍላጐትና ጥቅም ከኪራይ ሰብሳቢዎች ፍላጐትና ጥቅም ጋር ማጣጣም ማስታረቅ ይቻላል ብሎ የማይታረቁ የማይደመሩ ፍላጐቶችና ጥቅሞችን ያስታረቀ መስሎ ለጥቂቶቹ ለኪራይ ሰብሳቢዎቹ ጥቅም የቆመ መንግስትና ስርዓት የሚፈጥር የኋልዬሽየፍልስፍና ጉዞ ነው፡፡

ስለሁለተኛው መሰረተ ሓሳብ ደግሞ በገፅ 11-12 እንዲህ ይላል፡፡ በገፅ 11 በ2ኛው አንቀፅ ላይ “በአንድ በኩል የሰው ልጅ ስግብግብ ራስወዳድ፣ ተፎካካሪና ጠበኛ ፍጥረት ነው የሚለው ዕይታና በሌላ በኩል ደግሞ የሰው ልጅ በመሰረቱ መልካም ተባባሪና ለሌሎች አሳቢ ፍጥረት ነው የሚለው ዕይታ የክርክር አጀንዳ ፈጥራል” ይላል፡፡

በ4ኛው አንቀፅ ላይ ደግሞ “በዚህ የሰው ልጅ ተፈጥሮን በመበየን ሂደት ውስጥ የሚስተዋለው ዋናው ችግር ብያኔው ከርእዬተ ዓለም የሚቀዳ መሆኑ ነው፡፡ መሆን የሚገባው ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ ስለሰው ልጅ ተፈጥሮ ያለንን ዕይታ በነፃ አእምሮ ከመዘንን በኃላ ርእዬተ ዓለማችንን ብንቀርፅ የበለጠ ትክክል እንሆን ነበር ጋሪውን ከፈረሱ በማስቀደማችን ምክንያትም በሰው ልጅ ተፈጥሮ ላይ የምንሰነዝራቸው ድምዳሜዎች ርእዬተ ዓለማችንን ተመራጭ ለማድረግ የሚደረግ መቅበዝበዝ ነው” ይላል፡፡

መሰረተ ሓሳብ ስለሰው ባህርይ ስለሆነ የሚተነትነው የሰውን ባህርይ ይበልጥ በትክክል መረዳት የሚቻለው ከዘሩ፣ ከስነ-ሂወታዊ ተፈጥሮው በመነሳትና እሱን በመመርመር ነው እያለ ነው፡፡ ሰው አካላዊ ሁኔታው ነው በተፈጥሮው የሚወሰነው እንጂ አስተሳሰቡና ተግባሩ አጠቃላይ ባህርዩን በዋናነት የሚወሰነው በተፈጥሮው ሳይሆን በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታው ከዚያበሚመነጨው ፖለቲካዊና ባህላዊ አመለካከቶቹና ልምዶቹ ነው፡፡ የአከባቢውን ማህበራዊና ተፈጥሮአዊ ሁኔታን በጐላ ደረጃ መቀየርም የሚችል ንቁ ተዋናይ ፍጡር ነው፡፡ እንደ እንስሳ ስነ ሂወታዊ ተፈጥሮው በሰጠው ብቻ ባህርዩ የሚቀረፅ ፍጡር አይደለም እንስሶችም ቢሆኑ በአከባቢያቸው ባለው ተፈጥሮአዊ ሁኔታ ተፅእኖ ምክንያት ተፈጥሮአቸውና ባህርያቸው በተወሰነ ደረጃ ይቀረፃል፡፡ ስለሆነም የሰውን ባህርይ በትክክል ለመረዳት ዋናው መነሻ ማህበረ - ኢኮኖምያዊ ሁኔታው እንጂ ስነ ሂወታዊ ተፈጥሮው አይደለም፡፡ ባህርይ በተወሰነ ደረጃ በተፈጥሮው የሚቀረፅ ቢሆንም ስለሰው ባህርይ ያሉ ግምገማዎች ወይም ብይኖች ዋናው ችግራቸው ከርእዬተ ዓለም የተቀዱ መሆናቸው ነው፤ ከተፈጥሮው የተቀዱ መሆን ነበረባቸው የሚለው ሓሳብ ትክክል አይደለም፡፡ መነሻው የሰው ልጅ ስነ ሂወታዊ ተፈጥሮ ካደረገ ባህሪው በዋናነት ሲወለድ ወይም ሲፀነስ ጀምሮ ከነበረው ተፈጥሮ የሚመነጭ ነው ማለት ይሆናል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ዕድሜ ልኩን አይቀየርም አይደመርም አይቀነስም ማለት ይሆናል፡፡ የሰው ልጅ ዋናው ባህርዩ ማህበራዊ ፍጡር መሆኑ ነው ከእንስሶች በተለየ የሚያስብ ፈጠራ የሚችል ተፈጥሮንም በማይናቅ ደረጃ ለጥቅሙ የሚያውል አከባቢውን መቀየር የሚችል ባህርዩና ጥቅሞቹ አስተሳሰቡና ተግባሩ በሚኖርበት ማሕበረ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ የሚወሰን ንቁ ተዋናይ መሆኑ ነው፡፡

ባህርዩን የመረዳት አስተሳሰቡና ተግባሩን የመለወጥ ሳይንሳዊ ጥናትና የመፍትሔ ሓሳብ ከተፈጥሮው ሳይሆን ከርእዬተ ዓለም መነሳት ያለበትም ለዚህ ነው፡፡ ርእዬተ ዓለም ሲባል ደግሞ እያንዳንዱን ሕብረተሰብና ማሕበረሰብ በዛም የሕብረተሰብ ክፍልና ግለ ሰብ ጥቅሙ አስተሳሰቡ ባህሉና ተግባሩ ትስስሩ ይሁን ቅራኔው የሚመነጨው በዋናነት ከማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሁኔታው ነው በሚል መነሻ ሁሉንም ነገር የሚያይበት ሁለገብ አስተሳሰብ ማለት ነው ከርእዬተ ዓለም የሚመነጭ የሰው ባህርይ ትንታኔ ነው ለማሕበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቹ መፍትሔ ማስገኘት የሚያስችለው፡፡

ከሰው ተፈጥሮ የሚነሳ የሰው ልጅ በህርይ ትንታኔ ግን የሰው ልጅን በሽታና ጤናማነት እንዲሁም መለስተኛ ባህርያትን ያውቅ እንደሆን እንጂ የአንድ ሕብረተሰብ ባጠቃላይ ወይንም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መሰረታዊ ባህርይ ለማወቅ ይሁን መፍትሔ ለማምጣት አይረዳም፡፡ ይልቁንስ ጋሪውን ከፈረሱ ማስቀደም ይሉታል ይሄን ማድረግ ይሆናል፡፡

የሰውን ባህርይ በትክክል ማወቅና ለተፃራሪ ባህርዬቹ መፍትሔ ማግኘት የሚቻለው የትንታኔያችን ወይም የጥናትና ግምገማችን ዋናው መነሻ ርእዬተ ዓለም ሳይሆን የሰው ተፈጥሮ እንዲሆን ካደረግን ነው የሚለው መሰረተ ሓሳብ ወዴት ያመራናል? የዚህ ጥያቄ መልስ በምዕራፉ ድምዳሜ በገፅ 12 በ3ኛው አንቀፅ ላይ አለ “በመደመር ዕይታ መሰረት የሰው ልጅ የፍክክርም ሆነ የትብብር፣ የጠበኝነትም ሆነ የሰላማዊነት ዝንባሌው በእጁ ላይ ነው፡፡ የሚፈልገውን ባህርይ የመገንባትና የማጠናከር አቅሙ አለው፡፡ ወጣ ገባ ብሎ የሰበሰበው የሰው ልጅ ስልጣኔ የእያንዳንዱን ሰው ፍላጐት በማሟላት ሙሉ በሙሉ የበሰለ እውነተኛ ስልጣኔ እንዲሆን ይህን የሰው ልጆች አቅም መገንዘብ የግድ ይላል” ይላል፡፡ በዚህ መሰረት የክራይ ሰብሳቢው ሕገወጥነት ሙሰኛነትና ዘረኝነት ባህርይ በኪራይ ሰብሳቢው መልካም ፍላጐትና አቅም ያለምንም የሕግ የተቋምና የፖለቲካ ማዕቀፍ ሊቀየር ይችላል ማለት ነው ሆኖ አያውቅም፤

እዚህ ላይ ያለው ዋናው የአመለካከት ዝንፈት የሰዎችን ባህርይ በማህበራዊ እድገት ሕግጋት፣ በማሕበረ-ኢኮኖምያዊና ፖለቲካዊ ስርዓቱ ማዕቀፍ፣ በሰዎቹ ማህበራዊ ቦታ ከመተንተን ይልቅ በስነ-ሂወት ተፈጥሮአዊ ሕግጋት በየግል ባህርዩ ብቻ የመተንተን የተናጠል ቴክኒካዊና ሜታፊዚካላዊ እይታ መሆኑ ነው፡፡ ሜታፊዚካላዊ እይታ ነገሮችንና ሁኔታዎችን በተናጠል ያያል፣ ትስስራቸውን የመንስኤና ውጤት፣ የመልክና ይዘት፣ የውጫዊና ውስጣዊ ሁኔታቸው ሚናና ዝምድና አያይም፡፡ ግለሰቦች አካላዊ ሁኔታቸው የተፈጥሮአቸው ውጤት ሆኖ አስተሳሰባቸው ተግባራቸው ሚናቸው እና ጥቅማቸው ግን በማህበራዊ ቦታቸውና በኢኮኖምያዊ ዓቅማቸው ይወሰናል የሚለውን የማህበራዊ እድገት ሕግ አይቀበልም ግለሰቦች በማህበራዊ ዕድገት በልማት ይሁን በጥፋት ወሳኝ ሚና አላቸው የፈለጉትን መሆን ይችላሉ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ፍላጐታቸውና የሚያስፈልጋቸው ነገር ይለያያል፣ ፍላጐታቸውና እሱን የማሳካት አቅማቸው ይለያያል፡፡ የዚህም ዋና ምክንያት ተፈጥሮአቸው ሳይሆን የሚኖሩበት ማሕበረ-ኢኮኖምያዊ ሁኔታና ያላቸው ማህበራዊ ቦታ መሆኑ መረዳትና ማመን ያስፈልጋል፡፡

የመደመር ዕሳቤ የሰዎችን ባህርይ ሲተነትን እይታው ከሰው ተፈጥሮ አንፃር ብቻ እንዲሆን ለምን ተፈለገ? በግለሰብ ባህርይ ብቻ ለምን ታጠረ? ከማሕበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓቱ አንፃርና ከመደባዊ ባህርዩ ወይም ከማህበራዊ ቦታው አንፃር ለምን መተንተን አልፈለገም? ሁለት ምክንያቶች አሉት፡፡

አንደኛው ምክንያት በእያንዳንዱ ማህበረ-ኢኮኖምያዊ ስርዓት ውስጥ(በመስፍናዊ ስርዓት፣ በነፃ ገበያ ስርዓት) ስርዓቱ የፈጠራቸው የስርዓቱ ዋነኛ ምሰሶ የሆኑ ተፃራሪ ጥቅም ያላቸው መሰረታዊ መደቦችና ሌሎች መደቦች እንዳሉ ሁሉ በኛ አገርም ተፃራሪ ጥቅምና አመለካከት ያላቸው መደቦች ያሉ መሆኑ ስለማያምን ነው፡፡

ሁለተኛው ምክንያት በአገራችን ተፃራሪ መደቦች የሉም ከሚል መነሻ የሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎችና ዜጐች ጥቅሞችና ባህርዬች ማጣጣም ማስታረቅ ይቻላል፡፡ ይህን ማድረግ የሚቻለው በመደመር ዕሳቤ ነው ብሎ ለማሳመን ከስርዓቱና ከመደቡ ባህርይ ነጥሎ የግለሰብ ተፈጥሮአዊ ባህርይን ማጉላት መረጠ ፣የችግሩ ምንጭና መፍትሔ ያድበሰብሳል ሆን ብሎ ለገዥዎች ለኪራይ ሰብሳቢዎች ለጉልበተኞችየሚጠቅም ሓሳብ ነው ያመጣው፡፡

ምዕራፍ - ሁለት

የሁለት ርእዬቶች ተቃርኖ

በዚህ ምዕራፍ ሊበራሊዝም ሶሻሊዝም አብዬታዊ ዴሞክራሲ ተገምግመዋል፡፡ የሞከርናቸው ርእዬቶች ሁሉ ችግራችንን አልፈቱም ይልና ለምን ሊያሻግሩን አልቻሉም ለሚል ጥያቄ መልስ ሰጥቶ ሌላአማራጭ ያስፈልገናል ብሎ ይደመድማል፡፡እስቲ በየንኡስ ርእሱ ያሉትን ፍሬ ሓሳቦች አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

ይህ ምዕራፍ ገና ለገና ሲጀምር የሊበራሊዝም እና የሶሻሊዝም ምንነት ይሁን የርእዬተ ዓለም ክርክሮች ይዘትና አላማን አዛብቶ በመተርጐም ነው የሚጀምረው፡፡

በገፅ 13 ላይ እንዲህ ይላል፡፡ “በርእዬተ ዓለማዊ ውይይቶችና ክርክሮች ውሰጥ የሊበራሊዝምና የሶሻሊዝም ተቃርኖ ጐልቶ የሚነሳ ዋና ጉዳይ ነው፡፡ ርእዬተ ዓለማዊ ውዝግቦች በዋናነት ሁለቱን ርእዬቶች ለማስታረቅ የሚደረጉ ጥሪቶች ሆነው እናገኛለን፡፡ የሁለቱ ርእዬቶች ተቃርኖም ከሰው ልጅ ፍላጐቶች መሰረታዊ ተቃርኖ የሚመነጭ በዋናነትም በእኩልነትና በነፃነት መካከል ካለው ተቃርኖ የሚነሳ ነው፡፡ “ሊበራሊዝም” ለሰው ልጆች የነፃነት ፍላጐት ቅድምያ የሚሰጥ ርእዬት ሲሆን፣ በአንፃሩ “ሶሻሊዝም” ደግሞ ለሰው ልጆች የእኩልነት ፍላጐት ቅድምያ የሚሰጥ ነው፡፡”

እዚህ ጥቅስ ውስጥ ሶስት መሰረታዊ ስህተቶች አሉ፡፡ አንደኛው ስህተት “ርእዬተ ዓለማዊ ውዝግቦች በዋናነት ሁለቱን ርእዬቶች ለማስታረቅ የሚደረጉ ጥረቶች ሆነው እናገኛለን” የሚለው ነው፡፡ ሊበራሊዝም የከበርቴው ርእዬተ ዓለም ነው፡፡ ከበርቴውና የሱን ርእዬትና ጥቅም የሚጋሩ የተወሰኑ ከፍተኛ ሙሁራን ዓለምንና ሕብረተሰብን ተፈጥሮንና ማሕበረ-ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን የሚረዱበት የሚተነትኑበትና በዛ ማዕቀፍ ጥቅማቸውን የሚያራምዱበት ርእዬተ ዓለም ነው፡፡ ሶሻሊዝም ወይም የላቭአደሩ ርእዬተ ዓለም ደግሞ ላቭአደሩና የላቭአደሩ ወገን የሆኑ ሙሁራን ተፈጥሮንና ማሕበረ-ኢኮኖምያዊ ሁኔታን ዓለምንና ሕብረተሰብን የሚረዱበት የሚተነቱንበት ጥቅማቸውን የሚያራምደበት ርእዬተ ዓለም ነው፡፡ ርእዬት ሲባል ሁሉንም ነገር የምትረዳበት ሁለገብ እይታ ወይም አስተሳሰብ ማለት ነውና ተፃራሪ ርእዬቶች ስለሆኑና የተፃራሪ ጥቅም ያላቸው መደቦች እይታና ጥቅም ማስከበርያ ስለሆኑ በሁለቱ መካከል ሲደረግ የነበረው የርእዬት ትግልና ውዝግብ ባብዛኛው ይዘቱም አለማውም አንዱ ሌላውን ውድቅ አድርጐ የራሱ ርእዬትና ጥቅም በአሸናፊነት እንዲወጣለት ይደረግ የነበረ የሓሳብ ትግል ነው፡፡ አልፎ አልፎ ብቻ ነበር ሶሻል ዴሞክራሲ በአስታራቂነት የተቀነቀነውና የነፃ ገበያ ስርዓትን ሰብአዊ ገፅታ በመስጠት በአብዬትከመወገድ የታደገው ወይም ከማያቧራ ቀውስ ያወጣው ያኔ ብቻ ነበር ክርክሩ ወይም ውዝግቡ የአስታራቂነት ሚና የተጫወተው ታሪካዊ ሃቆችንና የሁለቱ ርእዬቶች ምንነት የሚያዛባ ልዩነቱን ለማድበስበስ ከመፈለግየመነጨ ሓሳብ ነው፡፡

ሁለተኛው ስህተት “የሁለቱ ርእዬቶች ተቃርኖም… በዋናነት በእኩልነትና በነፃነት መካከል ካለው ተቃርኖ የሚነሳ ነው” የሚለው ነው፤ አይደለም፡፡ በአንድ በኩል ሊበራሊዝም ለጥቂቶች ተጠቃሚነት ለብዙሃኑ መገለልና መደፈቅ፣ ለብዘበዛ ስርዓት ቀጣይነት የሚያገለግል ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሶሻሊዝም(የላቭአደሩ ርእዬት ለብዙሃኑ ተጠቃሚነት ለሁሉን አቀፍ ልማት፣ ብዝበዛ የሌለው ሰርዓት ለሰው ልጅ የተሟላ አርነትና እኩልነት የሚያገለግል ነው፡፡ ይህን ያህል ሁለገብና ሰፊና ጥልቀት ያለው መሰረታዊ ልዩነት እያላቸው ለነፃነት የመቆም ወይም ለእኩልነት የመቆም ልዩነት ነው ያላቸው የሚል ትንታኔ ቁንፅልና የልዩነቱን ባህርይ የሚያድበስብስ ነው፡፡ የሶሻሊዘም ርእዬት ተግባራዊ ይሁን አይሁን ይዘቱ ግን ከሊበራሊዝም ይህን ያህል የሰማይና የመሬት ልዩነት እንዳለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ሶስተኛው ስህተት “ሊበራሊዝም ለሰው ልጆች የነፃነት ፍላጐት ቅድምያ የሚሰጥ ርእዬት ሲሆን፣ በአንፃሩ ‘ሶሻሊዝም’ ደግሞ ለሰው ልጆች የእኩልነት ፍላጐት ቅድምያ የሚሰጥ ነው” የሚለው ነው፡፡ አረ አይደለም፡፡ ሊበራሊዝም ሲጀምር ለከበርቴውና ለጥቂት ሙሁራን ነፃነትና ሁለገብ መብት የቆመ እንጂ ለሰው ልጆች በሙሉ ነፃነት የቆመ አልነበረም፡፡ የሕብረተሰቡ ግማሽ ቁጥር የያዙ ሴቶችንና፣ ንብረት አልባ ብዙሃኑ ነጮችንና ጥቁሮችን ከዴሞክራሲ ያገለለ ነበር፡፡ የመምረጥ ይሁን የመመረጥ መብት፣ የመማር ይሁን የመሾም የመደራጀት ወ.ዘ.ተ መብቶች ንብረት ላላቸው ነጮች ወንዶች ብቻ የሰጠ ነበር፡፡ እስከ 20ኛው ክፍለዘመን መጀመርያ(እስከ 1ኛው የዓለም ጦርነት) የሊበራል ዴሞራሲ ስርዓቶች ሴቶችን ያገለሉ ነበሩ፡፡ የአመሪካ፣ ሊበራሊዝም እስከ 1960ዎቹ ድረስ ለጥቁሮች ዴሞክራሲ አልሰጠም፡፡

ሴቶች የመምረጥ ይሁን የመመረጥ መብት አልነበራቸውም የጥቁሮች መብት በአመሪካ የተከበረው በጥቁሮች ትግል በማርተን ሉተርኪንግ መሪነት በ1960ዎቹ ነበር፡፡ ሊበራሊዝም ለሰው ልጆች ሁሉ ነፃነት የቆመ ነበር ማለት አጉል መመፃደቅ ነው፡፡ አለፍ ብሎ ደግሞ እንዲህ ይላል፡፡ “የሊበራሊዝም ፍልስፍና ዋና ፍላጐቱ የሰው ልጆችን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት ማረጋገጥ ነው፡፡ ዙፋን የተቆናጠጡ ሓይሎች የጦር ሓይላቸውን መከታ በማድረግ የዜጐችን ሀብት የሚያጋብሱና የዜጐችን የብልፅግና ጥረት የሚገድቡ በመሆናቸው ይህን የፖለቲከኞች ማናለብኝነት ለመግራት የተተለመ ርእዬት ነው፡፡” እውነት ሊበራሊዝም ይህ ዓይነት ቅዱስ አላማና ተግባር ነበረው? ስልጣናቸውን መከታ በማድረግ የሚዘረፉና ብልፅግናን የሚገድቡ ንጉሳውያን ቤተሰብና መስፍኖችን ለማስወገድ የተነደፈ ርእዬት ሆኖ ጀመረና የራሱን የነፃ ገበያ መንግስት ባለስልጣኖችን በነፃ ፍርድ ቤትና በፓርላማ የሕግ የበላይነት በማረጋገጥ ሊቆጣጠር ሲሞክር ግን መብትና የምርጫ ካርድ በገንዘብና በሴራ የሚጠለፍ ነፃ ፍርድ ቤትም ለባለሀብቶቹ የሚያገለግል ሆኖ ቀረ ከነገስታቱና መሳፍንቱ የተሻለ ተጠያቂነትና ገደብ ቢያበጅም አሁንም ድረስ ብዙሃኑ የናጠጡ ባለሀብቶችንና መንግስታቸውን በአጥጋቢ ደረጃ መቆጣጠር እንዳልቻሉ ሊበራሎቹ ራሳቸው ያምናሉ፡፡

1.2. በሀገራችን የሞክርናቸው ርእዬተ ዓለሞች፡-

የመደመር ፅሑፍ በሀገራችን የሞከርናቸው ርእዬተ ዓለሞችን በተመለከተ ሲገመግም ስለ የ1960ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ እንዲህ ይላል በገፅ 22 በ2ኛው አንቀፅ ላይ “በተለይም ጀርመንና ኢራንን በመሳሰሉ ሀገራት የነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ በቀላሉ ወደ ሀገራችን በመዛመቱ የርእዬተ ዓለም ጉዳይ የዘመናዊ አስተሳሰባችን ማሟሻ ሆኖ መጣ፡፡ ሀገራችን የመጀመርያዎቹን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በምድሯ በከፈተችበት ወቅት በድንግል ልቦናችን ውስጥ “የሶሻሊዝም ርእዬት” ገባ፡፡”

በ3ኛው አንቀፅ ላይ ደግሞ “በዚህም ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሀገራችን ወጣት አፍ ማሟሻ ይሀው የሶሻሊዝም ርእዬተ ዓለም ሆነ፡፡ በዚህ ህልም መሰል የርእዬተ ዓለም ሙዚቃ ዳንኪራ ስንመታ ሀገራችን ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለችና ችግራችን ምን እንደሆነ እንኳን ቆም ብለን ለማስተዋል አልቻልንም” ይላል፡፡ እዚህ ላይ ሓሰትና የጥላቻ ቃላት ሰፍሮአል ደማቅ ታሪክን የማንቃሸሽና የማብጠልጠል ዘለፋ ተሰንዝሮአል፡፡ ሃቁ ግን ሌላ ነው፡፡ “በዚህ ህልም መሰል የርእዬተ ዓለም ሙዚቃ ዳንኪራ ስንመታ ሀገራችን ምን ዓይነት ሁኔታ ውስጥ እንዳለችና ችግራችን ምን እንደሆነ እንኳን ቆም ብለን ለማስተዋል አልቻልንም ” የተባለው የ1960ዎቹን ፖለቲካ የሚመለከት ሳይሆን አሁን በ2009-2011 ዓ.ም በጥላቻ ፖለቲካ መረን በለቀቀ ውሸትና በባዶ ተስፋ ቃላት በመደመር ፍልስፍና ሰክሮ ዳንኪራ እየመታ አገርን ያተራመሰ የለወጥ ሓይል ተብየውን ነው የሚመለከተው፡፡

የ1960ዎቹ የተማሪዎችና የሙሁራን ፖለቲካዊ ትግል የሀገራችን የያኔ አንገበጋቢና መሰረታዊ ችግሮች የመስፍናዊ ስርዓት መሬት ይዞታና የፖለቲካ ስልጣን በጥገኛ ቢሮክራቶችና በውጭ ጌታ ጣልቃ ገብነት ተፅእኖ ስር መግባቱና በብሄር ጭቆና ምክንያት የተፈጠረ የከረረ ቅራኔ መኖሩ፣ ኃላቀርነትና የዴሞክራሲ እጦት መሆኑ በጥናት ተንትኖ አንጥሮ አላስቀመጠም ወይ? የአርሶ አደሩ፣ የላቭአደሩ፣ የከተሜው የብሄር ብሄረሰቦች መሰረታዊ ጥያቄዎችን አንግቦ መፍትሔው ለዲሞክራሲ ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ለመሬት ለአራሹ ተግባራዊነት ለሀገር ሉአላዊነት ለዴሞክራስያዊ አንድነት ለእድገት መታገል መሆኑ በማያሻማ መንገድ ተንትኖ ታግሎ አላታገለም ወይ? በተራዘመው የገጠር ህዝቦች ጦርነትና በከተማ ፓለቲካዊ ትግል ተፋልሞ የሚያኮራ ህዝባዊነትና ጀግንነት አላሳየም ወይ?

በዚህ ሂደት የተፈጠሩ ዝንፈቶች ግጭቶች ውድቀቶች ቢኖሩም በመላው የኢትዬጵያ ብሄረ ብሄረሰቦች ትግል በኢህአዴግ ግነባር ቀደም ሚና ሰው በላው ፋሽሽቱ ደርግንና መስፍናዊ ስርዓቱን ከነ የበላይ ጠባቂዎቻቸው ድባቅ በመምታት ለድል አልበቃም? ማን እዚህ ባደረሰ ነው አሁን መልካሙን ታሪክ ደምስሶና ጥላ ሽት ቀብቶ ከኔ ወድያ ላሳር ባይ መሆን የተፈለገው፡፡ ታሪኩን በሚገባ ማጥናት አይሻልም ነበር?

ቀጥሎም በዛው በገፅ 22 በ4ኛው አንቀፅ ላይ “ከባሕር ማዶ የጐረፉትን ሓሳቦች በቀጥታ አምጥተን ህዝቡን በመጋት ሀገራዊ ስካር ውስጥ ገባን፡፡ ዞር ብለን ስናየው ትርጉም በማይሰጡት አንዳንዶቹም ፈገግ በሚያደርጉ ጉዳዬች እርሰ በርስ ስንራኮትና ስንጋደል አሳለፍን መድሃኒት ብለን ከውጭ የወሰድነው ርእዬተ ዓለም እርሱ በራሱ የሌላ በሽታ ምክንያት ሆነ፡፡” ይላል፡፡

ቀጠል ያደርግና በገፅ 23 በ1ኛው አንቀፅ ላይ “ርእዬተ ዓለሞቹን በእኛ ሀገር ሁኔታ ለመተርጐም የተደረገው ጥረት በእኛ ልክ ያልተገዛን ጫማ የመጫማት ያክል ነበር፡፡ ጉዳዩ በጫማ መግዛት ብቻም የሚቆም አልሆነም፡፡ ይልቁንስ እግርን በጫማው ልክ የመከርከም ያህል ተራመደ፡፡” ይላል፡፡

ከባሕርማዶ ባመጣነው ሓሳብ ሀገራዊ ስካር ውስጥ ገባን ትርጉም በማይሰጡት አንዳንዶቹም ፈገግ በሚያደርጉ ጉዳዬች እርስ በርስ ስንራኮትና ስንጋደል አሳለፍን ሲሉ ከሰው በላው ፋሽሽት ደርግ ጋር መፋለም ከንቱ ነበር ማለትዎ ይሆን? በህዝቦች ላይ ያወጀውና የተገበረውን ጭካኔ የተሞላበት ጦርነትና ቀይሽብር ነፃ እርምጃ ህዝቡና ዴሞክራሲያውያን ሓይሎች ሊመክቱት አይገባም አያስፈልግም ነበር ማለትዎ ይሆን? አሜን ብለው መገዛት መጨፍጨፍ ነበረባቸው ለማለት ይሆን?ስንቱን ህዝብ በጭካኔ የፈጀ ያፈናቀለ ለስደት ለእስር የዳረገ፣ ኢኮኒሚውን ያደቀቀ፣ የሰውን ልቦናና ህሊና የመረዘ ያመከነ፣ ለባዕድ የሶቭየት መንግስት አሳልፎ የሰጠን ደርግ መፋለምና ማስወገድ የሚፀፀቱበትና የሚወገዝ ነበር እንዴ?

ፈገግ የሚያደርጉ ጉዳዬችስ የትኞቹ ይሆኑ? የመላ ኢትዬጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) የተባለው አድርባይ ፖለቲካዊ ድርጅት ከደርግ ጋር ተሰልፎ ወጣቱን በቀይ-ሽብር የገጠሩን ህዝብ በጦርነት ሲያስፈጅ፣ ዘማችና አዝማች ሆኖ አገር ሲያጠፉ አደብ ግዛ ብሎ እሱን መፋለም እርስ በርስ ተላላቅን ያስብላል? ወይስ ፈገግ ያሰኛል? ከውጭ ያመጣነውን ርእዬተ ዓለም በልካችን ያልተገዛ እንዳውም ያልሆነ ጫማ መግዛታችን ብቻ ሳይሆን እግርን በሱልክ መከርከም ነበር ያሉት ደርግንና መኢሶንን ሊመለከት ይችላል፡፡ የተማሪዎች ንቅናቄና ያኔ የታገሉ ሌሎች የህዝብ ወገን የነበሩ ፓርቲዎችን ግን አይመለከትም፤ ለይተው ይውቀሱ በጅምላ ሁሉንም ማወገዝ ጥፋተኛና ጥፋተኛ ያልሆነወን በመደመር ስለፈረጁ ከዚህ በኃላ ስህተት የማይደገም እንዳይመስልዎት የማይደመር አይደምሩ ከዛ ወረድ ብሎም “………… መደማመጥ የጠፋበት መንገድ ስለተከተልን ውጤቱ በጦርነትና እርሰ በርእ ግጭት መተላለቅ ሆነ፡፡” ይላል (ገፅ 23 በ1ኛ አንቀፅ) ኢህአፓ፣ ህወሓት፣ ኢህአዴግ፣ የኤርትራ ድርጅቶች በየጊዜውከደርግ ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግና ሰላማዊ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ጥረዋል፡፡ አሻፈረኝ ብሎ በዕብሪት በጦረኝነት ግብኣተ መሬቱን ያቀላጠፈውና ብዙ ሂወትና ንብረትን ለጥፋት የደረገው ደርግ ነበር፡፡ ታድያ ለምን ሰላም ፈላጊውና ፍትሓዊ ጥያቄ የያዘውን ከግፈኛውና ዕብረተኛው ጦረኛ ጋር በጅምላ ይፈረጃል፡፡ ይህም በመደመር ዕሳቤ መሰረት ይሆን?

እላይ የተገለፀው ሃቅ ተቀብለን በዚህ ማዕቀፍ የተፈፀሙ የርእዬተ ዓለምና የፖለቲካ ስህተቶች እንደነበሩ ግን የሚካድ አይደለም፡፡ ዳርግና መኢሶን የፈፀሙት ግፍና ዝንፈት ከባህርያቸው የሚመነጭ ስለነበረ ያኔ የሚታረም አልነበረም፡፡ ኢህኤፓ ስልጣን በአቋራጭ ለመያዝና በመሬት አዋጅ ምክንያት አርሶ አደሩ ላይ እምነት በማጣት የፈፀመው የከተማ አመፅ ሙከራ(የታክቲክ ስህተት) ቅን ያሰቡ የራሱን አመራሮችና ብዙሃን አባላት አላዳምጥም ብሎ በዕብረት ወጣቱን ማስፈጀቱ ያስወቅሰዋል ህወሓት-ኢህአዴግም በትጥቅ ትግል ጊዜ ይሁን ስልጣን ላይ እያሉ የፈፀሟቸው ስህተቶችን ነቅሰው ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህ ሁሉ ግን በጐ አስተዋፅኦቸውን አያሳንስም፡፡ በእልህ መካረር፣ ቂም ይዞ መቀጠል፣ በሚያስማሙ ጉዳዬች አብሮ ተቻችሎ መስራት አለመቻል የ1960ዎቹ ትውልድ ጉድለቶች ነበሩ፡፡

ባጠቃላይ ግን ፀሓፊው ምን ለማለት ፈልገው ነው? የሚል ቁልፍ ጥያቄን ያጭራል፡፡ ርእዬተ ዓለሙ ከውጭ ማምጣታችን ነው ለዚህ ሁሉ ችግር የዳረገን ለማለት ከሆነ አሁንስ ባለፉት 18-20 ወራት ያጋጠመው መጠነ ሰፊ እልቂትና መፈናቀል፣ የኢኮኖሚ ድቀት፣ የገፅታ መበላሸት ምን ርእዬተ ዓለም ከውጭ ስለመጣብን ይሆን የተፈጠረው ወይንስ አገር በቀል የተባለው የመደመር እሳቤ የባሰ ለጥፋት የሚዳርገን በፍቅርና ይቅርታ ሽፋን በመደመር ስም ጥላቻና ግጭት ሙስናና የመበተን አደጋን ከድሮም በባሰ የሚያባዛ ሆኖ ይሆን?

በጣም የሚያሳዝነውና ለትዕዝብት የሚዳርጋቸው ደግሞ የተማሪዎች ንቅናቄ ይሁን ደርግን የተፋለሙ የፓለቲካ ድርጅቶች ሙሁራንና ወጣቶች መላ ብሄር ብሄረሰቦች ለመታገላቸው በቂ ፍትሓዊ መንስኤ ነበራቸው፣ በከፈሉትም መስዋእትነት ደርግን አስወግደን የልማትና የዴሞክራሲ ጅምር አይተናል ለማለት አልቻሉም፣ አልፈለጉም፡፡

ካለፈው ታሪካችን በጐውን እናመሰግን እንውረስ፣ ስህተቱንና ጥፋቱን እንማርበት አንድገመው የማይሉ ከሆነ፣ በጐውንም ክደውና ደምስሰው ጥፋት ብቻ ነበር ካሉ መደመሩ የቱ ጋ አለ? ሶሻሊዝምንና አብዬታዊ ዴሞክራሲን ለማውገዝና ከዛ የሚወርስ በጐ ነገር እንደሌለ ለማሳመን ብሎም የኢህአዴግ ይሁን የ1960ዎቹ ትውልድ አሻራ ድራሹ እንዲጠፋ በማድረግ የመደመር ዕሳቤ ብቸኛው አማራጭ ሆኖ ይወጣል ተቀባይነት ያገኛል ብለው ከሆነ እውነት ተዳፍኖ አይቀርምና መደመር በተግባር ሲታይ ባዶነቱ ይጋለጣል፡፡

የ1960ዎቹ ትውልድ ይሁን የኢህአዴግ በጐ ስራዎችም በህዝቦች ልብና በሰነድ ሰፍረዋልና አይደመሰስም፡፡ የመጣ መሪና የመጣ መንግስት ያለፈውን ሁሉ እያወገዘ እየደመሰሰ ከኔ ወድያ ላሳር እያለ ራሱን የማወደስ ራስን የመካብ አባዜ ነው፡፡

“ኢህአዴግ እና ሶሻሊዝም”

አብዬታዊ ዴሞክራሲ ልማታዊ መንግስት፡-

በመደመር መፅሓፍ ውስጥ በዚህ ርእስ ብገፅ 24-32 የተፃፈ ግምገማ ብዙ ዝንፈቶችና ውሸቶች ስላሉበት ወደ ዝርዝር ግምገማው ከመግባታችን በፊት ስለ አብዬታዊ ዴሞክራሲና ስለ ልማታዊ ዴሞክራሲ ስለ ልማታዊ መንግስት ምንነት መሰረታዊ ሃቆችን ባጭሩ ማየት ጠቃሚና ተገቢ ይሆናል፡፡ ከሶሻሊዝም ጋር ያላቸው መሰረታዊ ልዩነትና የነፃ ገበያ ስርዓትን የሚገነቡ መሆናቸው ወይም አለመሆናቸውም መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡

ዴሞክራሲና የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ እውን የሆነው በ18ኛው ክፍለ ዘመን በአመሪካና በፈረንሳይ በተካሄዱ በከበርቴው በተመሩ የነገስታትና የመሳፍንት አገዛዝ እንዲሁም የባርያና የጌታ ግኑኝነትን በስር-ነቀል መንገድ ባስወገዱ ዴሞክራስያዊ አብዬቶች አማካኝነት ነው፡፡ በእንግሊዝ የተጀመረው የእንዳስትሪ አብዬትና በ19ኛው ክፍለ ዘመን የተካሄደው የአውሮፓ ህዳሴ (ረነይሳንስ) ዳግም ስር-ነቀል የቴክኖሎጅና የአስተሳሰብ የባህል ለውጥ በማምጣት ለውጡን የፖለቲካ የኢኮኖሚ የባህልና የተቋማት የማህበራዊ ግኑኝነት ያካተተ ሁለ ገብ እንዲሆን ማድረግ አስቻሉ፡፡ ያኔ ከበርቴው ለነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ለዴሞክራሲ ማበብ ማነቆ የሆኑትን የመሳፍንትና የነገስታት አገዛዝና የኢኮኖሚ የማህበራዊ ግኑኝነት ማነቆዎችን ያስወገደው በመደብ ትግል በስር-ነቀል አብዬት ነበር፡፡ ስለሆነም መደባዊ ትግልና ስር-ነቀል አብዬት በማካሄድ የተሻለ ዕድገትና ዴሞክራሲን ማምጣት የተጀመረው በከበርቴው እንጂ በኮሚኒስቶች አይደለም፡፡

ያኔ ለለውጥ ለስር-ነቀል አብዬት ግንባር ቀደም ሆኖ የታገለና ያታገለ ከበርቴና የሱ ስርዓት ተጠቃሚ የሆኑ ሙሁራን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ የለውጥ ሓይል መሆንአቃታቸው ምክንያቱም ያኔ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚው የተፈጠረ ሀብትና ዴሞክራሲ ለከበርቴው እንጂ ለላቭአደሩና ለአርሶ አደሩ ፍተሓዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ስላልቻለ ይህንን በደል የሚቃወም የላቭአደርና የአርሶ አደር ተቃውሞ ተጠናክሮ ተስፋፋ፡፡

ይህን ሁኔታ በዝርዝር ያጠኑና በሳይንሳዊ ትንታኔ የነፃ ገበያ ስርዓት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ባህርይን ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይና ስርዓቱ ራሱን የሚያጠፋ ሓይል(ላቭአደር) እየፈጠረ መሆኑን በመለየት ሶሻሊስት-ኮሚኒስት ስርዓት መመስረትን እንደ መፍትሔ አወጁ፡፡ ማርክስና ኤንጅለስ የፃፉት ከብዙ ጥናትና በርካታ ረቂቅ ፅሑፎቻቸው የተጨመቀ “ኮሚኒስት ማኒዬሰቶ” በ1848 (በፈረንጅ አቆጣጠር) በኛ 1940 አካባቢ ይፋ አደረጉ የላቭአደሩ ርእዬትና ፓርቲ ፈጠሩ ፀረ-ከበርቴውና ፀረ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ብዝበዛ የሆኑ አመፆች በበርካታ የአውሮፖ አገሮች ተቀጣጠሉ(1848-1852) ከዝያን ጊዜ ጀምሮ ከበርቴው አብዬታዊ የለውጥ ሓይል መሆኑ አቋርጦ፤ ወላዋይ ሆኖ በስጋት ተዋጠ ከዚያ በፊት ራሱ የመራውን የዴሞክራሲ አብዬት የመምራት ፍላጐት ይሁን ብቃት አጣ፡፡

በዚህም ምክንያት እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ የአመራር ክፍተቱ ምላሽ ሳያገኝ ቆየ፡፡ዴሞክራስያዊ አብዬት ባልተካሄደባቸው ነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲ እንዳያብቡ ጠፍረው በያዙ የመሳፍንትና የነገስታት አገዛዝ ስርዓት ውስጥ ያሉ አገሮች በማን መሪነት እንዴት የዴሞክራሲና የነፃ ገበያ ስርዓትን እውን እንደሚያደርጉ ምላሽ የሰጠው ሌኒን ነበር፡፡ በ20ኛ ክፍለ ዘመን መጀመርያ በ1905 (በፈረንጅ አቆጣጠር) ሩስያ ውስጥ የተካሄደውና ሳይሳካ የቀረው ዴሞክራሲያዊ አብዬት ልምድ በመቀመር በታዳጊ አገሮችና ዴሞክራስያዊ አብዬት ባልተካሄደባቸው ግን በመስፍናዊ ስርዓት ውስጥ ጀማሪ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በነበራቸው አገሮች የሚካሄድ የዴሞክራሲ አብዬት በላቭአደር መደብ መሪነት በላቭአደርና አርሶ አደር አጋርነት ነው ወደ ሶሻሊዝም ማሻገር የሚቻለው አለ፡፡ ለዚህም አቋራጭ መንገዱ በአብዬታዊ ሙሁር የሚመራ የአርሶ አደሩና የመላ ብዙሃን ጥቅም የሚያረጋግጥ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራምን በቅድምያ መተግበር ነው አለ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ዳግም በተሟላ መንገድ በደቡብ ኮርያና በታይዋን በሲንጋፖር ተአምር የተባለለት ስኬት ያመጣ ከዛ በፊትም በጃፓን ድንቅ የተባለለት ስኬት ያስመዘገበ ልማታዊ ፕሮግራምና ልማታዊ መንግስት እውን ሆነ፡፡ በልማታዊ መንግስት የሚመራ ልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በአውሮፓና በአመሪካ ከተመዘገበው ፈጣን የነፃ ገበያ እንዳስትሪያዊ ዕድገት ይበልጥ የፈጠነ ዕድገት ባጭር ጊዜ ማስመዝገቡ በምዕራባውያኑ ልሂቃን ጥናት ተረጋግጦአል የግብርና ትራንስፎርመሽንም ከአውሮፓ በበለጠ ፍጥነት ነበር የተሳካው ተብሎለታል ልማቱ ከፍትሓዊነት አንፃርም ካብዛኞቹ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አገሮች የተሻለ እንደሆነ የዓለም ባንክና የምዕራቡ ዓለም ልሂቃን መስክረዋል፡፡

ስለሆነም አብዬታዊ ዴሞክራሲ ወደ ሶሻሊስት ሰርዓት አቋራጭ መንገድ ይሆናል ብቻ ሳይሆን ወደ ነፃ ገበያም ለመሻገር የሚያስችል አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል ምክንያቱም የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲ እንዳያብብ የሚያግዱ የመስፍናዊ ስርዓትና የውጭ ጥገኝነት ማነቆዎችን ይፈታልና፡፡ የቅድመ ነፃገበያ ሃላቀርና ፀረ-ዴሞክራሲ አስተሳሰቦችና ባህሎች በፈጣን ፍትሓዊ ልማት በሂደት ያከስማልና፡፡

አብዬታዊ ዴሞክራሲ አቋራጭ ወደ ሶሻሊስት ስርዓት መሸጋገሪያ መሆኑ ቀርቶ የዳበረ የነፃገበያ ስረዓት የመገንባት ተልእኮሊይዝ ከሆነ ግን መሰረታዊ የብዙሃን ውግንናውንና የስር-ነቀል ለውጥ መንገድ መሆን ባህርዬን ሳይቀይር ውሱን ማስተካከያ ማድረግ አለበት፡፡ ራሱን ወደ ልማታዊ ፕሮግራም ወደ ልማታዊ መንግስት ምስረታ ማሸጋገር አለበት፡፡ ሌኒን ባስቀመጠው መንገድ ወደ ሶሻሊስት ስርዓት አቅጣጫ ሳይሆን የዳበረ የብልፅግና ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ወደ መገንባት መሸጋገር አለበት፡፡ጃፓን ደቡብ ኮርያ፣ ታይዋን፣ ሲንጋፑር ኃላ ላይ ደግሞ ቻይና ያደረጉት ይሄን ነው፡፡

ኢህአዴግ ደግሞ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ዴሞክራሲ ለኛ የግድ ያስፈልገናል ብሎ ልማታዊ ዴሞክራሲን ተከተለ ልማታዊ ብቻ ሳይሆን ዴሞክራስያዊ መንግስትና ፌደራላዊ ስርዓት የተከለ ሕገ-መንግስት እውን አደረገ ኢህአዴግ ከትጥቅ ትግሉ ጊዜ ጀምሮ ያነገበውን የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ፕሮግራም በየጊዜው ከሁኔታዎች ጋር እያሻሻለው እያዳበረው መጥቶአል በአብዬታዊ ዴሞክራሲ የጭቁኖች ፓርቲዎች ብቻ ናቸው እንዳደራጁ የሚፈቀድላቸው ሲል የነበረው በደርግ ውድቀት ዋዜማ በተካሄደው የኢህአዴግ መስራች ጉባኤ የሁሉም መደቦችና የሕብረተሰብ ክፍሎች ፖርቲዎች ይደራጁ ሁሉም በእኩልነት ይወደዳሩ ብሎ በመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲተካ ፕሮግራሙ ላይ ማሻሻያ አደረገ፡፡ ቀጥሎም ወደ ሶሻሊስት ስርዓት መሸጋገር አይቻልም የነፃ ገበያ ስርዓት ነው የምንገነባው አለ፡፡

በ1993-1994 የኢህአዴግ ተሃድሶ ጊዜ ደግሞ ከኮሪያና ታይዋን የልማታዊ መንግስትና የልማታዊነት ፕሮግራም ልምድ ተቀመረ፡፡ ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር የግድ ተፈላጊ የሆነ ዴሞክራሲና ፌደራላዊ ስርዓትን በማከል ለኛ የሚሆን በልካችን የተሸመነና የተሰፋ ኢትዬያጵያዊ ስርዓት ለመገንባት አቅጣጫ አስቀመጠ፡፡ ከምስራቅ ኤስያ ሀገሮች የተለየ ግብርና መር የእንዳስትሪ ልማት የሚከተል የኢኮኖሚ ፓሊሲና ግብርናና ገጠር ማእከል ያደረገ የልማት ስትራተጂ ነደፈ፡፡ በዚህም መንገድ አብዬታዊ ዴሞክራሲ በየጊዜው በተደረገለት ማሻሻያ ወደ ሶሻሊስት ስርዓት አቋራጭ መንገድ መሆኑ ቀርቶ ፈጣን ቀጣይና ፍትሓዊ ዕድገት ያለው የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና የብዙሃኑ ተጠቃሚነትም የሚያረጋግጥ ዴሞክራሲ የሚገነባበት ዓላማ ያዘ፡፡ልማታዊ መንግስት የነበረበትን የዴሞክራሲ ጉድለት በማረም ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት ነው የምንተክለው አለ፡፡

ስለዚህ ኢህአዴግ የሚከተለው የአብዬታዊ ዴሞክራሲ አላማና አስተሳሰብ መሰረታዊ የህዝብውግንና ይሁን ዴሞክራሲ የማስፈን አላማውና ባህርዬን ሳይለቅ ወደ መደበለ ፓርቲ ስርዓትና ፌደራላዊ ስርዓት መትከል ተሻገረ ከዛም አልፎ ወደ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስት ምስረታ አደገ፡፡ ወደ ሶሻሊስት ስርዓት አቋራጭ መንገድ መሆኑ ቀርቶ የዳበረ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት መገንበያ መስመር መሆን ቻለ፤ ታድያ ኢህአዴግ አብዬታዊ ዴሞክራሲን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ሳያገናዝብ በልካችን ያልተሰፋ ባዕድ አቅጣጫ አምጥቶ ለችግር ዳረገን እንዴት ይባላል፡፡ እላይ የቀረበው ሃተታ የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ታሪካዊ አመጣጥና በሂደት የተቀየረና የዳበረ ተልእኮው ከልማታዊ ዴሞክራሲ ጋር ያለው የይዘት አንድነትና የተልእኮው መሻሻል ልዩነት ያሳያል፡፡ ለኢትዮጵያ በሚስማማ አግባብ የተነደፈበትና የተተገበረበት መንገድ እንደ መነሻ ወስደን በመደመር ፅሑፍ ላይ የሰፈረውን የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ግምገማ እንመርምረው፡፡

በገፅ 26 በ3ኛው አንቀፅ “አብዬታዊ ዴሞክራሲ የሶሻሊዝም ውሉድ ስለሆነ መሰረታዊ ዕሳቤው ኢኮኖሚያዊ አላላኪነት የተጫነው ነው፡፡ ይህም ማለት ችግሮችን ሁሉ ከኢኮኖሚ ጋር የማገናኘት ወይም በኢኮኖሚ ላይ የማላክክ ችግር ነው” ይላል፡፡ ከዚህ እምነቱ በመነሳትም ሀገራችን ለተከታታይ ነውጥና ትርምስ የምትዳረገው በድህነት ምክንያት ነው ብሎ ኢኮኖሚው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረጉ በሌሎች ምክንያቶች ጭምር የሚፈጠር ግጭትና ትርምስን አላስቀረም ይልና ሲደመድም “ይህም ዜጐች ማህበራዊ አገልግሎቶች ስላገኙ ብቻ ሰላም ይሰፍናል የሚለው አስተሳሰብ የተሳሳተ እንደሆነ በተግባር አሳይቶናል” ይላል፡፡

አብዬታዊ ዴሞክራሲ ወይንም አህአዴግ ልማትና ዴሞክራሲ ለኢተዬጵያ አንድ የተሻለ አማራጭ ብቻ ሳይሆኑ የህልውና ጉዳይም ናቸው ብሎ ለሁለቱም በእኩል ትኩረት እንደሚያይና በዛም እንደሚመራ በተደጋጋሚ አስረግጧል፡፡ የተሃድሶው መስመርና የኢትዮጵያ ህዳሴ በሚል የኢህአዴግ ፅሑፍ እንዲህ ይላል፡- “እናም ድርጅታችን በኢትዮጵያ ትላንትም ሆነ ዛሬ ልክ እንደልማቱ ሁሉ የዴሞክራሲ ጉዳይም የህልውና ጥያቄ ነው ብሎ በጥብቅ ያምናል፡፡ ልማታዊ መንግስታችን ዴሞክራስያዊ ሆኖ እንዳይጀመር የሚገድቡት ነገሮች አለመኖራቸው ብቻ ሳይሆን ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጀምር የሚያስገድዱት የህልውና ጥያቄዎች ስላሉትም ከመጀመርያው ልማታዊና ዴሞክራስያዊ ሆኖ የጀመረ መንግስት ነው፡፡ በዚህም በነኮርያ ከነበሩት ልማታዊ መንግስታት በዓይነቱ የተለየ መንግስት ነው ማለት ይቻላል፡፡”

ስለዚህ የኢህአዴግ አብዬታዊ ዴሞክራሲ በእምነት ደረጃ ልማትና ዴሞክራሲን በእኩል ደረጃ ያያል፡፡ በተግባርም ፌደራል ስርዓቱንለማጠናከር፣ የፓርላማ አሰራርና የምርጫ ስርዓት ለማጠናከር፣ ሰፊ ጥረት አድርጐአል፡፡ ችግሩ የነበረው ከልማት ስራ ውጭ ላሉ ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዬች ተገቢና ተከታታይ ጥረት አለማድረግ ሳይሆን ለተቋማት ግንባታ በተለይም ለሰው ሓይል የክህሎትና የአመለካከት ዕድገት፣ ለሀገረ መንግስት ግንባታ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ውጤት ማምጣት አለመቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው አሁንም ሰፊና የተካረረ የአመለካከት ልዩነትና መዛባት የሚታየው፡፡ በዋና ዋና ሀገራዊ ጉዳዬች ዙርያም የጋራ መግባባት መፍጠር ያልተቻለው እዛ ላይ የተሰራ ስራ ልፋት እንጂ ውጤት ተኮር ስላልነበረ ነው፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲና ኢህአዴግ ከልማት ውጭ ላሉ ጉዳዬች እምነት ስለሌላቸው አይደለም፡፡

ዜጐች ማህበራዊ አገልግሎት ካገኙ ሰላም ይሰፍናል ቢል ኖሮ ለምን ስለፌደራል ስርዓት ስለ ፍትሕ፣ ስለ ነፃ ፕረስና ስለምርጫ ያ ሁሉ የሕግ የአደረጃጀት የአሰራር ማሻሻያ አደረገ፡፡ ውጤቱ ግን አጥጋቢ አልሆነም በመቀጠልም የመደመር መፅሓፍ እንዲህ ይላል (በገፅ 29 በ2ኛው አንቀፅ) “መንግስት በልማት በኩል በሚያደርገው ጥረት ውሰጥ የመንግስት ሚና በግሉ ባለሀብት እየተተካ የሚመጣበትንና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ጠንካራ ባለሀብቶችን ለማፍራት ያስቀመጥነው ትልም ተጨናግፎ በሂደቱ የግሉ ባለሀብት በመንግስት እየተገፋ እንዲቀጭጭ ሆኗል”

መንግስት እስካሁን በባለቤትነት የያዛቸው የማምረቻና የአገልግሎት ተቋማት በአብዛኛው በሀገር ውስጥ ባለሀብት አቅም የማይሰሩና ለውጭ ባለሀብት ቢሸጥም ልማቱን የሚጐዱ ዓይነት ናቸው፡፡ ይህም ሆኖ ግን ወደ ግሉ ባለሀብት መተላለፉ የነበረባቸው መለስተኛ ተቋማትም በመንግስት እጅ ስላሉ እንደ ጉድለት ሊታይ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ ባለሀብቱ የቀጨጨበት ዋናው ምክንያት መንግስት ብዙ ነገር ጠቅልሎ ስለያዘ በመንግስት ሰለተገፋ አይደለም የኪራይ ሰብሳቢነት ፓለቲካዊ ኢኮኖሚ የበላይነት ስላለውና ነባራዊ ሁኔታው አሁንም ይበልጥ ለኪራይ ሰብሳቢዎች የተመቻቸ መሆኑ ነው፡፡ በዛ ላይ ደግሞ የኪራይ ሰብሳቢነት ምንጭ ለማድረቅና ለልማታዊው ባለሀብት በቂ ድጋፍ ለመስጠት መንግስት በቂ ርብርብ ስላላደረገ ነው፡፡ ይህን የሚያደርግ የመፈፀም አቅም አልፈጠረምና፡፡

መንግስት ተቋማቱን ለግል ባለሀብቱ እየለቀቀ እንዲሄድ የማይፈልጉ በመንግስት ስም የሚዘርፉ ስላሉና ይህን ዝርፍያ የምንቀጣጠርበት የሕግ ስርዓትና የሕግ የበላይነት በአብዬታዊ ዴሞክራሲ ስላልተዘረጋ የዘረፉ መረቡ ተጠናከረ ይላል መፅሓፉ(ገፅ 29 በ3ኛ አንቀፅ)ዘራፊ ባለሀብትና ባለስልጣን እንዲሁም የመንግስት ሰራተኛ ሙያተኛ አለ፣ በመንግስት እጅ ያሉ ተቋማትን የሚዘርፉ የሚያስዘርፉ አሉ፣ እንደውም አሁን ብሶበታል ጠንካራ የሕግ የበላይነት መተግበሪያ ስረዓትም አልነበረም አሁንም የለም፡፡ ግን የጃፓን የኮሪያ፣ የሲንጋፑር የታይዋንና የቻይና ልማታዊ መንግስታትኮ ጠንካራ አመራርና ውጤታማ ቢሮክራሲ ከነጠንካራ የተጠያቄነት ስርዓቱ ፈጥረው ይህን ችግር ተቋቁመውታል በአጥጋቢ ደረጃ ተቆጣጥረውታል፡፡ ስለዚህ የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ወይም የልማታዊ መንግስት ባህርያዊ ደክመት ሳይሆን የኛ መንግስትና ገዥ ፓርቲ ድክመት ነው፡፡ ጠንካራ የእርምትና የአቅም ግንባታ ስራ በመስራት እንደ ሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ችግሩን መቅረፍ ይቻላል፡፡

ይህን ጉዳይ ሲደመድም መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- (በገፅ 29 በ4ኛ አንቀፅ) “በመሆኑም በአብዬታዊ ዴሞክራሲም ሆነ በልማታዊ መንግስት ትግበራ ወቅት የተሳተው ዋነኛው ጉዳይ መሸጋገርያ ድልድይ መሆናቸውን መዘንጋታችን ወይም ሳንሸጋገር እንድንቆም መፈለጋችን ነው፡፡” አብዬታዊ ዴሞክራሲ የብዙሃኑ ባጠቃላይ የአርሶአደሩ ዳግም በተለይ ወገንተኝነት ያለው የፖለቲካ ፕሮግራም ስለሆነ ነፃ ገበያ ስርዓትን አጐልብቶ ለከበርቴው የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር መሸጋገርያ ሞግዚት ነው የሚል እምነት በኢህአዴግ ውስጥ ነበር፡፡ በህዋላ ደግሞ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ወደ ልማታዊ ዴሞክራሲ ካደገ በኃላ እንደሩቅ ምስራቅ አገሮች በልማታዊ ዴሞክራሲ ቀጥሎ ራሱ የዳበረ ነፃ ገበያ ስርዓት ይገነባል ወይንም እንደ ሰካንዲኔቭያን ሀገሮች ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ ይቀየራል የሚል አማራጭ አቅጣጫ በ1990ዎቹ በኢህአዴግ ተቀመጠ፡፡ አሁን በደቡብ ኮርያ፣ በታይዋን፣ በሲንጋፑር ያሉ ልማታዊ መንግስታት የበለፀገ የነፃ ገበያ ስርዓትን ገንብተዋል፡፡ ልማታዊ መንግስት የበለፀገ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚችል ተጨባጭ ማሳያ ናቸው፡፡

ስለዚህ ከሁለቱ አንዱ ጋር እስኪደርስ ገና ረዥም ጉዞ አለው መጀመርያ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር ኢኮኖሚ ይገነባል ከዛም ወደ ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ይሻገራል፡፡ ይህን ማሳካት ከ30 አመት በላይ ይወስዳል ወደ በለፀገ ከፍተኛ ገቢ ያለው አገር የመሸጋገር ጉዳይ ያኔ በሶሻል ዴሞክራሲ ወይም በልማታዊ ዴሞክራሲ ያስቀጥላል ከተሸነፈም በሊበራል ዴሞክራሲ ይተካል አሁን ያ ሁሉ ህልም ቀረና ኢህአዴግ ገና ካሁኑ ከአብዬታዊ ዴሞክራሲ ወይንም ከልማታዊ ዴሞክራሲ መስመር ወጥቷል፡፡

ገና ተልእኮውን ሳይጨርስ ከፍተኛ መካከለኛ ገቢ ያላት ሀገር ሳይፈጥር መሸጋገርያነቱን ዘነጋ ነው ፤ ምናልባትም ሳንሸጋገር ልንቆም ፈልገናል ብሎ የወቀሳ ግምገማ ማቅረብ ነገርየውን ሆን ብሎ ማጣመም ነው፡፡ አልያም የኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የበላይነት ባለበት፣ ክራይ ሰብሳቢዎች ከተወዳዳሪውና እሴት ፈጣሪው ልማታዊ ባለሀብት የበለጠ ጉልበት በያዙበት ጊዜ የኢህአዴግ ተልእኮአብቅቷል ለባለሀብት ያስረክብ ማለት ለኪራይ ሰብሳቢዎች ያስረክብ ማለት ይሆናል፡፡ የኪራይ ሰብሳቢዎች መንግስት ለመመስረት ማመቻቸት ይሆናል፡፡ አጠቃላይ የልማትና የዴሞክራሲ ጉዞአችን ተጓቷል ተወዳዳሪ ባለሀብት መፍጠር ላይ አጥጋቢ ስራ አልሰራንም ቢባል ግን ያስማማናል፡፡

በመቀጠል ሕገ-መብግስታዊ የመድበለ ፓርቲ ስርዓትን በአውራ ፓርቲ የሚተካ ሆኖአል ፤ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ይላል መፅሓፉ በገፅ 30 በ3ኛው አንቀፅ እንዲህ ይላል “จจจአልፎ አልፎ በህዝባዊ ተቀባይነት ምክንያት አውራ ፓርቲ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ችግር የሚሆነው አውራ ፓርቲ የተፈጠረው ቢሮክራሲውን በመቆጣጠርና በረቀቀ መንገድ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመደፍጠጥ በተፅእኖ መሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ከሕገ-መንግስቱ አላማ ጋር ተቃራኒ ነው፡፡”

በሀገራችን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በመደፍጠጥ በተፅእኖ ነው ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ የሆነው እያሉን ነው ፀሓፊው፡፡ አረ አይደለም! ለምን ቢሉ በኢህአዴግ እና ኢህአዴግ በሚመራው መንግስት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የሚደረግ ተፅእኖ እንደነበረ የማይካድ ቢሆንም የፓርቲዎች ደካማ መሆንና የአውራ ፓርቲ መፈጠር ዋናው ምክንያት ግን እሱ አይደለም እንላለን ተፅእኖው የሚያደርስባቸው ችግር ቀላል እንዳልነበረም ያስማማናል፡፡

ኢህአዴግ አውራ ፓርቲ ሆኖ የወጣበት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደካማ የሆኑበት ዋናው ምክንያት ግን ኢህአዴግን እና እሱ የሚመራውን መንግስት ሁሌ ከመውቀስ ባለፈ ህዝቡን የሚያሳምን የተሻለ አማራጭ ስለሌላቸው ነው፡፡ የሆነ አማራጭ አላቸው ግን ችግራችንን በትክክል መለየት ላይና የተሻለ መፍትሔ ማምጣት ላይ አልቻሉም፡፡ያቀረቡት አማራጭአንድም የአንዱ ብሔር የበላይነት የሚያነግስ አሃዳዊ ስርዓት ወይንም ጠባብ የብሄር ብሄረሰብ ጥቅም ብቻ የሚያራምድ ሆኖአል፡፡ ሁለቱም አማራጭ ህዝብ ለህዝብ የሚያጋጭ፣ አገርን የሚያተራምስ ሆኖአል፡፡

ሁለቱም ግን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅ ናቸው፡፡ የብዙሃን ጥቅም ሳይሆን የጥቂቶች ጥቅም የሚያስጠብቁ ናቸው፡፡ መሬት ይሸጥ ይለወጥ ይላሉ፣ መሬቱን ሽጦ ለሚፈናቀለው አማራጭ የገቢ ምንጭ የላቸውም ለሰፋፊ ዘመናዊ እርሻዎች የሚፈለግ ብዙ የውጭ ምንዛሬ ከየት እንደሚገኝ መልስ የላቸውም፡፡ መሬቱ በጥቂቶች እጅ ተጠቅልሎ ብዙሃኑን ለችግር ስለሚደረግ አርሶ አደርን አያሰልፍም እንዲስትሪ መር የልማት ስትራተጂ አሁኑኑ እንከተል ይላሉ፤ ለእንዳስትሪና ከተማ ልማት የሚያስፈልግ ብዙ የወጭ ምንዛረና የሀገር ውስጥ ባለሀብት አቅም ከየት ይገኛል አይመልሱም፡፡ በቋንቋ የተካለለ ፌደራል አደረጃጀት ይበትናል በጂኦግራፍያዊ ደንበር የተካለለ ይሁን ይላሉ፤ በዛው የብሄር ብሄረሰቦች ራስን የማስተዳደር፣ በቋንቋቸው የማስተዳደርና ባህል ታሪካቸውን በክልሉ የማጐልበት መብትን ይደፍቃሉ ለውጭ ሓይሎች የሚያጐበድዱና ትጉህ መልእክተኛ የሚሆኑም አሉ ማን ይከተላቸው፡፡

በተጨማሪም ወደ ገጠሩና ትናንሽ ከተሞች ወርደው ቀጣይና ውጤታማ የማደራጀትና የቅስቀሳ ስራ አይሰሩም ምርጫ ሲቃረብ ብቻ ነው የሚነቃነቁት፡፡ ስለዚህም የሚያሰባስቡት ትርጉም ያለው አባልና ደጋፊ አያገኙም፡፡

1.3. የሞከርናቸው ርእዬቶች ስለምን አላሻገሩንም?

በገፅ 33 በ3ኛው አንቀፅ ላይ “ልማታዊ መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ኢኮኖምያዊ ዕድገት በማስመዝገብ ረገድ ይበል የሚያሰኝ ውጤት ያሳየ ቢሆንም የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ በማረጋገጥ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ከማድረግ አንፃር ሰፊ ክፍተቶች ተስተውለውበታል፡፡ ከዚህም በላይ በፓለቲካ ነፃነት ባለመታጀቡ ሀገራችንን ወደ ከፋ ቀውስ ውስጥ ከቷል” ይላል፡፡

ችግሩ ይሄ ከሆነ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያጐለብትና የፖለቲካ ነፃነትን የሚያሰፍን የተጠና የተቋምና የሕግ የፖሊሲ ማሻሻያ ማድረግ ሊፈታው ይችላል፡፡ ሌላ አማራጭ ፕሮግራም(ርእዬት) ይሁን የፖሊሲና የስትራተጂ መሰረታዊ ለውጥ ማድረግ አይጠይቅም፡፡ የልማት ውጤታማነት ጥንካሬውን ይበልጥ አጐልብቶ የጐደለውን አሟልቶ መሄድ ተገቢና ጠቃሚ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ልማታዊ  መንግስት በምስራቅ ኤስያ ሀገሮች ተአምራታዊ ዕድገት እንደመጣ ፀሓፊው በዚሁ ገፅ አስረግጠው ገልፀውታል፡፡

ቀጠል አድርጐመፅሓፉ ሲያትት በዚሁ ገፅ 33 በ4ኛው አንቀፅ ላይ፡- “ባለፉት አምስት አሰርት ዓመታት ኢትዬጵያ ውስጥ የነበረው ትርምስ ከውጭ ያገኘነውን ዕውቀት ከሀገራችን ሁኔታ ጋር በደፈናው ስናላትመው የተፈጠረ ችግር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ውለን አድረን የትናንት ችግሮቻችንን እንደ አዲስ የምናልመዘምዝና አንድ ዕንቅፋት ብዙ ጊዜ የሚመታን ህዝቦች ሆነናል” ይላል፡፡ እዚህ ላይ ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች አሉ፡፡ አንዱ ስህተት የውጭ ልምድና ዕውቀት ከሁኔታችን ጋር ሳናጣጥም እንዳለ በደፈናው ስናላትመው ነበር የሚለው የውሸት ድምዳሜ ነው፡፡ ደርግ ሶሻሊዝም ይሁን ቅይጥ ኢኮኖሚ ቁምነገሩ ሳይገባው ሲባል ሰምቶ የህዝቡ ትግል የፈጠረበትን ጫና ለማላዘብ ሳይመረምር ከሁኔታችን ጋር ሳያዛመድ ገልብጦ ሊተገብር ሞክሮአል፡፡ ውድቀት አስከተለ ኢህአዴግ ግን በልማትና በሰላም በዲፕሎማሲ ስኬት ማስመዝገቡ አያከራክርም በዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ግን ብዙ ውድቀት አለው ከተባለ እሱም የወጭውን ገልብጦ ሰለተገበረ ነው አያስብልም በከፊል ነውና ያልተሳካለት እሱን አርሞ ስኬቱን አጐልብቶ ማስቀጠል ነው፡፡

ሁለተኛውና ዋናው ስህተት ግን ዋነኛ መመዘኛው ከውጭ መምጣቱ ወይም ሀገር በቀል መሆኑ እንዲሆን ተደርጐአል፡፡ የጀርመን የናዚ ዘረኝነትኮ ለጀርመናውያን አገር በቀል ፖለቲካ ነበር ግን ጀርመንን ያደቀቀ ነበር ሌሎችን ህዝቦችም የፈጀ 6ሚልዮን አይሁዳውያንን የጨረሰ ነበር የእንዲስትሪ አብዬት ለእንግሊዛውያን አገር በቀል ነበር ቀድመው እንዲያድጉ አስቻላቸው፤ ግን ሌሎች አገሮችም ከሁኔታቸው ጋር አጣጥመው ችግራቸውን በሚፈታ መንገድ የእንዳስትሪ አብዬት አካሂደው የተሳካ ዕድገት አስመዝገበዋል፡፡ የውጭ ነውና አንፈልግም ቢሉ አያድጉም ነበር፡፡

ስለዚህ ይህ ጠባብ የሆነ የአስተሳሰብ አድማስ ይዘን በዘመነ ግሎባላይዘሽን በዘመነ የመጠቀ ሳይንስና ቴክኖሎጂ የትም አንደርስም፡፡ ከሁኔታችን ጋር በሚገባ መጣጣም አለበት፤ ሀገራዊ ችግራችንን የሚፈታ መሆን አለበት ለማለት ከሆነ ደግሞ ሕገ-መንግስታችን የኢኮኒሚ ፖሊሲያችን ከሁኔታችን ጋር የተጣጣመ ነው፡፡ መሻሻል ካለበትም ተወያይቶ ማሻሻል ነው እንጂ ከዜሮ መጀመር መፍትሔ አይሆንም፡፡ የተሰራውን ስራ መቀልበስ  ደግሞ የባሰ ጉዳት ያስከትላል፡፡

ማጠቃለያ

ስለአብዬታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግስት

Videos From Around The World

የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ኢኮኖምያዊ ስትራተጂያዊ ግቦች የኢህአዴግ የ1987 ዓ.ም ፕሮግራም እንደሚከተለው ያስቀምጠዋል “6 የአገሪቱን ኢኮነምያዊ ነፃነት የሚያጐለብት፣ ህብረተሰብም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣንና ቀጣይነት ያለው እድገት የሚያረጋግጥ የልማት አቅጣጫ መከተል፡፡”

ከዚህ አኳያ ግቦቹ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ካፒታሊስት እድገት ማረጋገጥ በዚህ ላይ ተመስርቶ ጭቁኑ ህዝብ ከልማቱ በላቀ ደረጃ ተጠቃሚ የሚሆንበት፣ የአገራችን ኢኮኒምያዊ ነፃነት በቀጣይነት እየጐለበተ የሚሄድበት ሁኔታ መፍጠር ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ በነፃ ገበያ ክልል የሚመጣ ፈጣን እድገትንና የህዝብ ተጠቃሚነትን በሚመለከት የኢህአዴግ ግቦችና በነዚህ ግቦች መካከል ያለውን ትስስር አስመልክቶ አብዬታዊ ዴሞክራሲያዊ መለያ እምነቶቻችን በሚለው የኢህአዴግ ፅሑፍ (በ1990ዎቹ የተፃፈ) የሚከተለው ተቀምጧል፡፡ “ስለሆነም እኛ ኢህአዴጐች ሰፊው ህዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን እድገት ስንል ምኞትን መግለፃችን አይደለም፡፡ ሰፊውን ህዝብ ለመመፅወት መምከራችንም አይደለም፡፡ ህዝቡን የዛሬውን ቻለውና ነገ ብዙ ሚሊየነሮች ከፈጠርን በኃላ ቀስ በቀስ ያልፍልሃል (trickledown) ማለታችንም አይደለም፡፡ እነዚህ አባባሎች የተቃዋሚዎቻችን ናቸው፡፡ እኛን ከነሱ የሚለየን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የህዝቡን የማምረት አቅም ከፍ በማድረግ ላይ አተኩረን ሰፊው ህዝብ ከመጀመርያው አንስቶ የኢኮኖሚ እድገቱ ንቁ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያደርግ በተግባር የተፈተነና በስራ ላይ እየዋለ የሚገኝ የዕድገት አቅጣጫ በመያዛችን ነው፡፡

የኢህአዴግ እምነት ያለ ፈጣን ዕድገት ድህነትን በማስወገድ ሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ አይቻልም፡፡የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነት የማያረጋግጥ ፈጣን ዕድገት ደግሞ ትርጉም የለውም የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ኢህአዴግ ከሌሎች የሚለየው የሰፊውን ህዝብ ተጠቃሚነትና ፈጣን እድገትን የማይነጣጠሉ ግቦች አድርጐ በመውሰዱ ብቻ አይደለም፡፡ ኢህአዴግ በባህሪው ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን ሊነድፍና ተግባራዊ ሊያደርግ የሚችል መሆኑም ጭምር አህአዴግን ከሌሎች ይለየዋል፡፡” (ገፅ 11)

ከነዚህ ጥቅሶች ስለአብዬታዊ ዴሞክራሲ የምንረዳቸው ፍሬ ነገሮች አሉ አብዬታዊ ዴሞክራሲ የሶሻሊስት ስርዓት መሸጋገርያ አቋራጭ መንገድ እንዲሆን በሚል ተጀምሮ እሱ ሳይሳካ ሲቀር የነፃ ገበያ ስርዓት መገንበያ መንገድ ሆኖ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የነፃ ገበያ ዕድገት የማምጣት፣ መንገድ ሆኑ፡፡ በዚህ ላይ ተመስርቶ የህዝቡ ፍተሓዊ ተጠቃምነት የማረጋገጥ፣ በዚህ ሂደት ህዝቡ በድጐማ ሳይሆን የማምረት አቅሙን በማጐልበት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል በፈጣንና ቀጣይ ዕድገት ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ በመፍጠር በውጭ መንግስታትና ኩባንያዎች የማይሽከረከር እየጐለበተ የሚሄድ ተነፃፃሪ ነፃነት ያለው ኢኮኖሚና ሃገር መገንባት የሚያስችል መሆኑ እና ይህንን ተግባራዊ የሚያደርግበት ፖሊሲዎች ቀርፆ ተግባራዊ የማድረግ ባህርይና አቅም ያለው መሆኑ ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ነፃ ገበያ ኢኮኖሚው እንዴት እንደሚገነባ የአብዬታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምንነት (1993) በሚል ርእስ በተፃፈ የኢህአዴግ ፅሑፍ እንዲህ ይላል “ለ-የምንገነባው ኢኮኖሚ ካፒታሊስት ኢኮኖሚ ስለሆነ ከመልካም ፍላጐትና ምኞት ተነስተን የምናስቀምጣቸው ግቦችም ሆነ አቅጣጫዎች አይኖሩም፡፡ የካፒታሊዝምን የዕድገት ህግጋት በመከተል በካፒታሊስት ዕድገት የተዋጣላቸው አገሮች ልምድ በመቀመርና ይህንን ከአገራቸን ተጨባጭ ሁኔታና ከኢህአዴግ ባህሪ ጋር በማስተሳሰር የምናስቀምጣቸው ግቦችና አቅጣጫዎች ብቻ ናቸው የሚኖሩት፡፡”

የአብዬታዊ ዴሞክራሲ ፖለቲካዊ አለማዎች ደግሞ ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ምን ዓይነት መንግስት ይመሰርታል የሚለውን የአብዬታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ምንነት በሚለው ፅሑፉ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡ በፕሮግራሙም አስቀምጦታል፡፡ ፍሬ ነገሩ ሲጠቃለል፡-

  የዴሞክራሲው ዳር ድንበር በኢትዮጵያ ህዝቦች ተወካዬች በሕገ-መንግስት ጉባኤ የፀደቀው ሕገ-መንግስት መሆኑ፣

  ይህም ማለት የግለሰብና የብሄር ብሄረሰቦች ዴሞክራስያዊ መብትን በእኩል ዓይንና በተጣመረ መንገድ የሚያከብር መሆኑ፤ በዚህ ማዕቀፍ የሁሉም ዜጐችና የሕብረተሰብ አካሎች የብሄር ብሄረሰቦች መብት የሚከብር መሆኑ፣ ይህን መሰረት ያደረገ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት የሚከተል መሆኑ፣

  ከዚህ በተጨማሪ ከምርጫ ባለፈ ህዝቡ በቀጥታዊ ተሳትፎ እሰከ ቀበሌ ድረስ በማቀድና በመገምገም ቀጥተኛ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚያስችል አሰራር የሚዘረጋ መሆኑ፣

  የሚያምንበት ዴሞክራሲ ሁሉንምየሚያቅፍ ሆኖ ወገንተኝነቱ ግን ለብዙሃኑ መሆኑ ማለትም ህዝቡ በሕገ-መንግስቱ የተረጋገጡለተን መብቶች በሙሉ አሟጦና አሟልቶ እንዲጠቀም የሚያስችለው የማንቃት የማደራጀት ድጋፍ የሚያደርግ፣ ሳይጠቀምበት እንዳይቀር የሚያደርጉ ዕንቅፋቶችና ውሱንነቶች እንዲፈቱለት የሚጥር መሆኑ ነው፡፡

ስለሆነም አብዬታዊ ዴሞክራሲ የግለሰብ መብትንና የብሄረ ብሄረሰብ መብትን በእኩል ዓይን እንደሚያስከብር እንጂ በቡድን መብት ብቻ እንደማያተኩር በግልፅ አስቀምጦአል፡፡ ወገንተኝነቱም በአድልዎ ሳይሆን በድጋፍ መልኩ እንደሆነ ግልፅ አድርጐአል ህዝቡ መብቱን እንዲጠቀም ማስቻል፣ መብቱ ሲገፋ ዘብ መቆም ማለት እንደሆነ አብራርቷል፡፡ የአብዬታዊ ዴሞክራሲ አላማ እንዲህ በግልፅ ተቀምጦ እያለ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚና ዴሞክራሲ መገንበያ፣ የህዝብ ተጠቃሚነት ማረጋገጫና የአገር ሉአላዊነትና የአገር ኢኮኒሚ ተነፃፃሪ ነፃነት ማጐልበቻ ፖለቲካዊ ፕሮራም መሆኑ በይፋ ታወጆና በተግባርም ተፈፅሞ እያለ ለምንድነው እሱ አልጠቀመንምና በሌላ አማራጭ እንተካው የተባለው የመደመር ዕሳቤ አመንጪና የመፅሓፉ ደራሲ ዶ/ር አብይ አህመድ ጥቅምት 8/2012 ዓ.ም መፅሓፉን ሲያስመርቁ የተናገሩት ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ይሰጠን ይሆናል፡፡

ያኔ ባደረጉት ንግግር ስለሶሻሊዝምና አብዬታዊ ዴሞክራሲ ስለመሪ ፓርቲ ከማርክስና ከሌኒን ወስደን፣ ስለአርሶ አደር ከቻይናው የትጥቅ ትግል መሪ ከማኦ ወስደን ከሁሉም የተቀነጫጨበ ሓሳብ ወስደን ለኛ ስለማይሆን መተግበር አቃተን ብለው ነበር፡፡ “ሰፋፊ እርሻ ማረስ የማይቻልበት አገር አድርገን ስናበቃ ሃፍታም በሌለበት ምንም እንዳስትሪ በሌለበት እና ሰራተኛ በሌለበት በግድ የማርክስ ሓሳብ ተከታይ ለመሆን በመደብ ካልተከፋፈልን ብለን እንቸገራለን ማንን ከማን ነው የምንከፋፍለው ኢትዮጵያ ውስጥ ሃብታም እንደሆነ የለም จจจኢትዬጵያ ውስጥ ያለው ጥሮ ግሮ ሰርቶ ለመብላት የሚቸገር ሰው ነው” ብለዋል፡፡ እውነታው ግን እሳቸው እንዳሉት ሳይሆን ያለ ውድድር ከሕግ ውጭ እሴት ሳይፈጥሩ አለአግባብ የከበሩ ክራይ ሰብሳቢ ባለሀብቶች አሉ ያላፈሩት ሀብት እየዘረፉ፣ ጥራት የሌለው ምርትና አገልግሎት ከገበያ ዋጋ በላይ እየሸጡ፣ከሕግ ውጭ ንግድና ግብር ባለመክፈል በገፍ እያተረፉ ኢኮኒሚውን ጠፍረው የሚይዙ የነፃ ገበያ ዕድገት ማነቆዎች ናቸው፡፡ ፍትሕን በገንዘብ የሚያዛቡ በፅንፈኛ ብሄረተኝነትናበሃይማኖት ህዝቡን እያነሳሱና እያጋጩ ሰላምና ዴሞክራሲን የህዝቦች አንድነትን የሚያውኩ ፀረ-ዴሞክራሲና ፀረ-ድሀ ናቸው፤ እንዴት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ሃብታም የለም፣ መደቦች የሉም የሚባለው ፤ ይህ የመደብ ዕርቅ ሴራ ክራይ ሰብሰቢውን አትንኩት ወዳጃችሁ ነው ብሎ ለማስታረቅ ያለመ አይደል?

የሚታሰብ ያለ የመደመር ዕሳቤና የብልፅግና ፓርቲ (ኢህአዴግንአፍርሶ) የክራይ ሰብሳቢዎች ፓርቲ እንደሚሆን ሳይታለም የተፈታ ሆኖአል፡፡ ክራይ ሰብሳቢና ሰፊው ህዝብ ተደመሩ፣ ክራይ ሰብሳቢውና ተወዳዳሪው እሴት ፈጣሪው ሕግ አክባሪው ልማታዊ ባለሀብት ተደመሩሊባል ነው፡፡ አይጥና ድመት፣ ጅብና አህያ፣ ተኩላና ፍየል፣ እባብና ሰው ወ.ዘ.ተ ሲደመሩ የበላይነት የሚይዘውና የሚጠቀመው ማን እንደሆነ ግልፅ ነው፤

የማርክስና የሌንን ሓሳቦች በአንድ ርእዬተ አለም፣ ከአንድ ባህር የተቀዱ ናቸውና ከሁለቱም ሓሳብ መውሰድ የተቀነጫጨበ ሓሳብ አያስብልም፡፡ ከመፅሓፍ ቅዱስና ከወንጌል መወሰድ ወይም ከቁርኣንና እሱን መነሻ ካደረጉ ተአማኒነት ካላቸው የእስልምና መፃሕፍት መውሰድ፣ ወይም የኒዬሊበራሊዝም አባት ከሚባሉ የተለያዩ ፀሓፊዎች መውሰድ በምንም ምክንያት መቀነጫጨብ አያስብልም መቀነጫጨብ የለመደ ግን ሊመስለው ይችላል ወይም ሓሳቡን ያልተረዳ ሰው ይሆናል፡፡

ቀጠል አድርገውም የመደመር ዕሳቤ አመንጪው እንዲህ አሉ፡- “በሀገራቸው(በቻይና) የሰራተኛው መደብ ስለሌለ የአርሶ አደር መደብን ታሳቢ ያደረገ የማኦን እሳቤም እኛ ውግንናችን ለአርሶ አደሩ ነው ብለን ደግሞ ቅንጭብ አደረግን จจኢትዬጵያ ውስጥ የሚያሳዝነው ለከተማ ነዋሪው ዘይት ስንደጉም፣ ስንዴ ስንደጉምจจ ለአርሶ አደሩ ማዳበርያ እንኳን ማቅረብ ያልቻልንจจ በሰሙ የነገድን የስም ነጋዴዎች ነበርን እኛ፡፡ ይህ የስም ነጋዴነት ከመነሻው ከመርህ የተነሳ ነው”፡፡

በጣም የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ንግግር ነው፡፡ ኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ለአርሶ አደሩ ማዳበርያ ከመደጐም በላይ ብዙ መሰረታዊ ጥቅሙን የሚያረጋግጡ የተቀናጁና ቀጣይ ሁለገብ ድጋፎች አድርጐአል፡፡ ምርትና ምርታማነቱ እንዲያድግ ሁሉም ዓይነት የግብርና ግብአቶች በማቅረብ፣ ብድርና የባለሙያ ድጋፍ፣ ገበያ የገጠር መሰረተ ልማትና ማህበራዊ አገልግሎት እስከ ቀበሌ ድረስ በማቅረብ ደግፎአል፡፡

ይህ ሁሉ ድጋፍ የሚጠይቀው ወጪ ከማዳበርያ ድጐማ በላይ ነው፡፡ የኢህአዴግ የልማት አቅጣጫ አርሶ አደሩን የድጐማ ተመፅዋች ማድረግ ሳይሆን የራሱ የማምረት አቅም በሁለገብ መልኩ በማጐልበት በዘላቂነት ራሱን ችሎ ኑሮውን በቀጣይነት እንዲያሻሻል ማስቻል ነው፡፡ ይህ ዘላቂ ድጋፍ በሰሙ መነገድ አይባልም አርሶ አደሩን በተግባር ተጠቃሚ እያደረገ ያለን አብዬታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግስትን ማጥላላትና በሌላ መተካት ነው፣ የተፈለገው፡፡ ይልቁንስ የመፅሓፉ ደራሲ ቅንጣት ታህል የአርሶ አደር ተቆርቋሪነት የሌላቸው ሆነው እያለ ተቆርቃሪ ለመምሰል መሞከራቸው ነው በሰሙ መንገድ የሚያስብለው፡፡ የአዞ እንባ ነው የሚያነቡ ያሉ፡፡በአርሶ አደር ስም መነገድ የኢህአዴግ መርህ አይደለም፣ የክራይ ሰብሳቢ ፅንፈኛ ብሄረተኞችና የመደመር ዕሳቤ የለውጥ ሃዋርያ ተብየዎች መርህ ነው፡፡

የመደመር መፅሓፍ ደራሲው አንድ ወዳጄ እንደነገረኝ ይሉና “ከመነሻው ማኦ ሲጀምር አርሶ አደሩ ቅን የዋህ ነው፣ አንዴ ካመነ ለረጅም ጊዜ ይከተልሃል ይልና የራሱን ሓሳብ ማፍለቅ የማይችል እራሱን መምራት የማይችል የተውሰ አመራር የሚሻ ነው በሚል ተራማጅ ሙሁር አርሶ አደሩን ይምራው ይላል” አሉ፡፡ ለራሱ የማያውቅ ሓሳብ ማፍለቅ የማይችል የማይችልስለሆነ በንፁህ አእምሮ ይከተለኛል ከሚል እሳቤ እንጂ ከውግንና አይደለም ይላሉ፡፡

ጉድነው!! ከሃያ አመት በላይ ኢህአዴግ ውሰጥ የቆዩ ከተራ አባል እስከ ድረጅቱ ሊቀ-መንበረነት የደረሱ ሰው ስለ ኢህአዴግ እና አርሶ አደር የጠበቀ መግባባትና ውግንና ሽምጥጥ አድርገው ሲክዱ ለትዕዝብት ይዳርጋል፡፡ እንዳውም በኢህአዴግ እምነት ይሁን በማኦ እምነት ስለአርሶ አደሩ አስተዋይነትና ጥቅሙን በተሞክሮው ለይቶ ማወቅ ያላቸው ልምድና እምነት ጠንካራ ነው፡፡ ሙሁር ይምራው የተባለው ንድፈ ሓሳብና ስትራተጂ ፖሊሲ በጥናትና ምርምር ማመንጨት የትግል አደረጃጀትና አሰራር መቀየስ በተመለከተ ሙሁሩ የተሻለ ይሰራዋል፡፡ ስለሆነም የራሱ የአርሶ አደሩ ነባራዊ ሁኔታና ፈላጐትን መነሻ አድርጐ ተንትኖ ያቀርብለታል በተግባር ደግሞ አርሶ አደሩ ያዳብረዋል፣ ሙሁር አቅጣጫ ያስይዘዋል ለማለት ነው፡፡ ደራሲው ግን በህዝብኛ መንገድ ትርጉሙን አዛብተው አቀረቡት ከኢህአዴግ እና ከማኦ በላይ እውነት አርሶ አደሩን ይበልጥ ያወቁት ይሆን? ስለአርሶ አደሩ ከነሱ በላይ ተቆርቁረውለት ይሆን? ወይስ አሁንም የአዞ እንባ ነው ነገሩ፡፡

ለአርሶ አደሩ ብቻ ሳይሆን ለላቭአደሩም፣ ለባለሃብቱም ጭምር የተጠና የተተነተነ ሓሳብ በግልም በፓርቲ በኩልም የሚያቀርብላቸው ሙሁሩ መሆኑ ያውቃሉ፡፡ የመደመር ዕሳቤ በአርሶ አደር ተጠንቶ ተተንተኖ የቀረበ ይሆን እንዴ?

ስለ ኢህአዴግ ውህደት ደግሞ የሚከተለውን ብለዋል “የፓርቲ ውህደት ጉዳይ አላለቀም እኛ የመደመር ፍልስፍናን የምናምን ሰዎች በዴሞክራሲያዊ ውይይት ስለምናምን አንድ አመት ከስድስት ወር ሙሉ ተጠንቶ ያለቀ ሰነድ ቢሆንም ላለመበተን ስንለማመን እና ስንወያይ ከርመናል አሁንም ውይይቱ አልተቋጨም ውይይቱ ሳይቋጭ አንድ አንዶች ይህ የፓርቲ ውህደት መጨፈለቅ ነው እና ኢትዬጵያን ከፌደራላዊ ስርዓት ወደ አሃዳዊ ስርዓት መመለስ ነው የሚል በኛ ውሰጥ ታስቦታልም የማያውቀውን መርዶ አረዱን፡፡”

የውህደት ጥናቱ ከአንድ አመት ከስድስት ወር ሙሉ ተጠንቶ ያለቀ ነበር ያሉት እውነት አይደለም ጥናቱ ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ለውይይት የቀረበው በ2011 ዓ.ም 3ኛው ሩብ አመት ላይ ነበር ያልበሰለ ጥሬ ስለነበረ እጥረቱ ተለይቶ ተሟልቶ ይምጣ ተባለ፤ ከዛ ቡኃላ በ2011 ዓ.ም ክረምት እንደገና ቀርቦ ትችት ቀርቦበት ይበልጥ ይብሰል ተባለ በዚህ ሁኔታ የድሮው ኢህአዴግ የለም የአለማ ልዩነት አለ አብዬታዊ ዴሞክራሲ አይሰራም፣ ሕገ-መንግስቱ እና ፌደራል ስረዓቱም ጥያቄ ውሰጥ እየገባ ነው ይፈተሽ እየተባለ በኢህአዴግ አመራሮች በይፋ እየተነገረ ውህደት አይቻልም የሚል ሓሳብ በህወሓት ቀርቦ ነበር፡፡ ያኔ ሌሎቹ አመራሮች የሰጡተ ምላሽ የግለ ሰቦች አስተያየት ይሆናል እንጂ በነዚህ ጉዳዬች በድርጅት አመራር ደረጃ ልዩነት ያለው የለም የሚል ነበር፡፡ በህዋላ ግን የመደመር መፅሓፍ ሲመረቅ ሊቀመንበሩ ራሳቸው አብዬታዊ ዴሞክራሲን አጥላሉት ፡፡

መደመር ምንድነው ግልፅ ይደረግልን ተብሎ ለቀረበው ጥያቄም በፅሑፍ አቀረባለሁ ብለው ነበር ግን መፅሓፉ ለኢህአዴግ አመራር ቀርቦ ውይይት ሳይደረግበት ተመረቀ፣ ታወጀ፡፡ የኢህአዴግ ፕሮግራምና ሕገ ደንብን የሚቀይር የመደመር ዕሳቤ በዚህአዴግ አባል ድረጅቶች አመራሮችና ጉባኤዎች ተመክሮበት መጨረሻ ላይ በኢህአዴግ የጋራ ጉባኤ ነው መፅደቅ ያለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ውህደት ብሎ ነገር እንዴት ይሆናል በነበረው ፕሮግራምና(አላማ) ሕገደንብ ነው የሚዋሃዱት ወይስ በአዲስ ፕሮግራምና ሕገደንብ ግልፅ ሳይደረግ የውህደት ጥድፍያ ለምን ተፈለገ ?

በዚህ መንገድ እየሄደ ስለሆነ ነው ተቃውሞ የተነሳው አካሄዱ ግልፅነትና አሳታፊነት የለውም በስራ አስፈፃሚና በየድርጅቱ ከተውጣጡ አባላት መድረክ ብቻ ነው የመደመር ዕሳቤ ጥቅል ሓሳብ የቀረበው፡፡ በየድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴና ጉባኤ የሚቀርብ አዲስ ፐሮግራም አልተዘረጋም፣ አዲሱ አደረጃጀት የሚፈጠርበት ሕገደንብ አልተዘጋጀም፡፡ በአቋራጭ ግን ለታዳጊ ክልል ፓርቲዎች አመራሮች በመደመርና በውህደት ዙርያ ስልጠና ተሰጠ፤ እንዲህ ብሎም ዴሞክራሲ የለም፡፡ ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነ የአቋራጭ የለብለብ አካሄድ ነው፡፡

አካሄዱ ሕገ-ወጥም ነው ህዝቡ የመረጠው ኢህአዴግን ነው በቆየው የኢህአዴግ ፕሮግራም ነው ተመርጦ ገዥ ፓርቲ የሆነው የኢህአዴግ ፕሮግራምና ሕገደንብ የሚቀየር ከሆነ አዲስ ፓርቲ ነው በሕጉ መሰረት ሳይመዘገብ ገዥ ፓርቲ ሆኖ አገር ማስተዳደር አይችልም የሕግ ተቃውሞ ያሰነሳል፣ የሽግግር መንግስት ምስረታ ጥያቄ ያስነሳል ውዝግብ ይፈጥራል፡፡

ስለዚህ የውህደቱ አላማ ብሄራዊ ድርጅቶችን ማፍረስ ከዛም በማንነት ላይ የተመሰረተ አከላለልን ማፍረስ በጂኦግራፍያዊ አከላለል ሽፋን አሃዳዊ መንግስት መመስረት ይከተላል ነው የተባለው፡፡ ታድያ ውህደቱን ህወሓት ለምን ቀድሞውንስ ተሰማማበት የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ይሆናል ያኔማ(በ2010 እና ከዛ በፊት) ኢህአዴግ ፕሮግራሙን ሳይቀይር አደረጃጀቱንም ሳይቀይር መጀመርያ የታዳጊክልሎች ፓርቲዎችን በአባልነት ይቀበል፤ ከዚህ ጐን ለጐን የውህደት ጥናት ይደረግ ነበረ ያለው ያኔ የአላማ ለውጥ አልነበረም ከውህደት በኃላም የአዲሱ ፓርቲ አደረጃጀት ፌደራል ስርዓቱን የተከተለ ክልላዊ አደረጃጀት ይኖረዋል፡፡ በየክልሉ የራሳቸው የተመረጠ አመራር(ማእከላዊ ኮሚቴና ስራ አስፈፃሚ) የራሳቸው ክልላዊ ኮንፈረንስ ያላቸው ቅርንጫፍ ፓርቲዎች ይደራጃሉ የሚል ሓሳብ ይዞ ነው ለውህደት ይዘጋጅ የነበረው አሁን ግን የአላማ አንድነት ስለሌለ ውህደቱን ተቃውሟል፡፡

መስከረም 2011 ዓ.ም በአዋሳ በተካሄደ የኢህአዴግ ጉባኤ ስለ ውህደት ሙሉ ውክልና ለአመራር ሰጥቶናል ይላሉ ሊቀመንበሩ፡፡ ስለ አዋሳ ጉባኤ ውሳኔዎች ከተነሳ አይቀር ሙሉውን ሃቅ ነው መነገር ያለበት ያኔ የተወሰነው የኢህአዴግ ፕሮግራም(አላማ) አብዬታዊ ዴሞክራሲ ሆኖ እንደሚቀጥል፣ ለውጥ ካስፈለገ ወደፊት ተጠንቶ እንደሚታይ፣ የሚል ነበር፡፡ የውህደት ጥናትም ይቀጥል በኢህአዴግ ምክርቤት ይታይ ነበር የተባለው ይህ ሲባል ግን ፕሮግራም ሳይቀየር የአደረጃጀት ለውጥ ብቻ ይሆናል በሚል ታሳቢ ነበር፡፡

አሁን ግን በአዲስ አላማ(ፕሮግራም) እና በአዲስ ሕገደንብ፣ በአዲስ ዕሳቤ ነው እንዋሃድ የሚባል ያለ፡፡ ይህ ሓሳብ የአዋሳ ጉባኤ ውሳኔ አይደለም አሁን የመጣ ሓሳብ ነው ውህደት በራሱ አሃዳዊ ስርዓት አያመጣም የአሁኑ ውህደት ግን ወደ የማንነት ክልል ማፍረስ፣ ወደ ሕገ-መንግስት መቀየር የሚያመራ ሆን ተብሎ ታቅዶ እየተሰራበት ያለ ነው፡፡

የኢህአዴግ አደረጃጀት አግላይ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የታዳጊ ክልሎች ፓርቲዎችን በማግለል በአገራዊ ጉዳዬች እንዳይወሰኑ ከውስጣቸው ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆን ሰው እንዳይሾም አግዶ የቆየ ነበር ተብሎአል ኢህአዴግ ገዥ ፓርቲ ስለሆነ ሁሉንም ሌሎች ፓርቲዎች ካላካተተ አግላይ ነው ማለት የተዛባ አመለካከት ነው፡፡ በራሱ መመዘኛ አልቀበልም ቢል መብቱ ነው፤ ይሁን እንጂ ውህደት ቢዘገይም አሁን ባለው የኢህአዴግ አደረጃጀት ገብተው አባል እንደሆኑ ማድረግ ይቻላል፡፡

የፓርቲ አመራሮች ወደ ስልጣን በብዛት አለመምጣት ነው መመዘኛው ወይንስ የታዳጊ ክልሎች ህዝቦች በፓርላማ፣ በካቢኔና በሌሎች የፌደራል አካላት ፍትሓዊ ውክልና ማግኘት አለመግኘታቸው ነው? ስለታዳጊ ክልሎች የልማት ተጠቃሚነትና ራስን በራስ ማስተዳደር የተከለከሉት ነገር አለ ወይ? መነገር ያለበት ዋና ጉዳይ ስለ ህዝቦቹ ተሳትፎና ተጠቃሚነት እንጂ ስለፓርቲዎች በገዥ ፓርቲው መግባት መሆን የለበትም፡፡

ስለሆነም ህወሓት የኢህአዴግ ውህደትን የተቃወመው ስልጣን ስለተከለከለና ለውጥ ስለማይቀበል እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚል አይደለም፡፡ የተቃወመው የጋራ አላማው ስለተቀየረና የአላማ አንድነት ስለሌለ ነው፡፡ ከዛም በተጨማሪ ወቅቱ ስላልሆነና አካሄድም ሕገ ደንብ ያልተከተለ ኢዴሞክራስያዊ ስለሆነ ነው፡፡

ስለዚህ የመፅሓፍ ምረቃ ጊዜ የመፅሓፍ ደራሲ ያደረጉት ንግግር አብዬታዊ ዴሞክራሲንና የ60ዎቹ ትውልድን የሚያጥላላ፣ስለ አብዬታዊ ዴሞክራሲና ስለ የኢህአዴግ ውህደት የተዛባ መረጃ ያቀረቡበት ነበር በኢህአዴግ አመራሮችና ጉባኤ ያልተመከረበት ግን ለውህደቱና ለአዲሱ ፓርቲ የአላማ ለውጥ መነሻ የሚሆን መፅሓፉ ይፋ ያደረጉበት ነበር፡፡ ለብዙ ትዕዝብት የዳረጋቸው ነበር፡፡

አሁንም አልረፈደም ማጥላላትና የተዛባ መረጃ መስጠትን አርመው ሓሳባቸው በይፋ በመገናኛ ብዙሃን ክርክር ይካሄድበት፡፡ የኢህአዴግ አበል ድርጅቶች በየአመራራቸውና በየጉባኤቻው መክረውበት በኢህአዴግ ጉባኤእልባት ይደረግበት የኢህአዴግ ጉባኤ ከምርጫ ቡሃላ ይሁን ከምርጫ ጋር ጊዜ የሚሻማ የሚያሰናክል ስራ እንስራ ባይሉ ይሻላል፡፡ እስከዛው በነበረው የኢህአዴግ ፕሮግራምና ሕገደንብ ይቀጥሉ፡፡ ህወሓት መደመርንና ውህደትን እየተቃወመ ያለው ፀረ-ለውጥ ስለሆነ ወይንም በፌደራል መንግስትና በኢህአዴግ የነበረው ተሰሚነትና ስልጣን ስለቀነሰ አይደለም፡፡ የመደመር ዕሳቤ ያለፈውን መልካም የልማት ስራና የዴሞክራሲ ጅምር ያመጣልንን ልማታዊ መንግስትና ልማታዊ ዴሞክራሲን የሚያጥላላ የሚቀለብስ እኛ የበላይ እንሁን እንግዛችሁ ከሚሉ ክራይ ሰብሳቢ ባለሃብቶችና አሃዳውያን ጥቂት ሙሁራን ጋር ዕርቅ ብሎ እነሱ የበላይነታቸውን እንዲያስመልሱ የሚያመቻች ስለሆነ ነው፡፡ ሰላማችን እንዲፈርስ አንድነታችን አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሕገ-መንግስታችንና ፌዴራል ስርዓቱ ለአደጋ እንዲጋለጥ ስለሚያደርግ ነው፡፡

ውህደት እየተባለ ያለውም የነበሩትን አባል ድርጅቶች በያዙት አላማ ዙርያ ወደ አንድ ፓርቲ ማምጣት ሳይሆን የክራይ ሰብሳቢዎችና የውጭ ሓይሎች ጥቅም የሚያሳካ አዲስ አላማ የያዘ የብዙሃኑ ተጠቃሚነት የሚገድብ አዲስ ፓርቲ የሚፈጥር ስለሆነ ነው፡፡

ስለ ልማታዊ መንግስት

ስለ ልማታዊ መንግስት በርካታ የተዛቡ ሓሳቦችና መረጃዎች ስለተነሱ ጥቂት ነገር እንበል፡-

የልማታዊ መንግስት ሶስት መለያ ባህርያት-

ሀ) ህዝብና አገርን ከትርምስና ከብተና የሚያድን፣ ከውጭ ጥቃትና ከተመፅዋችነትም የሚያድን ከድህነትና ከሃላቀርነት የሚያላቅቅ የልማት ስራ ነው ብሎ በፅናት የሚያምን መንግስት መሆኑ፣ የሆነ ዓይነት ልማት ሳይሆን ፈጣን ቀጣይ ዕድገት ከፍትሓዊ ተጠቃምነት ጋር ያጣመረ የነፃ ገበያ ኢኮኖምያዊ ልማት የሚያመጣ መሆኑ፤ ሁሉንም ስራው፣ ሁሉንም ነገርለልማት ስራው ተገዥና አጋዥ የሚያደርግ፣ ዋናው ርብርቡ ልማት ላይ የሚያደርግ ለልማት ቆርጦ የተነሳ መንግስት መሆኑ ነው፡፡

ለ) የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ባለሀብት መልእክተኛና መጠቀምያ ሳይሆን ተነፃፃሪ ነፃነቱን ጠብቆ ባለሀብቱን የሚደግፍ፣ በባለሀብቱ ሊሰራ የማይችል የገበያ ጉድለት ባለበት የተመረጡ የምርትና የአገልግሎት አበይት ስራዎችን በባለቤትነት ይዞ ልማቱን የሚያፋጥን፣ የራሱ አቅም የባለሀብቱና የህዝቡ አቅም አቀናጅቶ የሚመራ በኢኮኖሚው የተመረጠ ጣልቃ ገብነት የሚያደርግ(Interventionist) መንግስት መሆኑ፣

ሐ) ሁሉም ሰርቶ በሕጋዊ መንገድ ኑሮውን ማሻሻል እንደሚችል በተግባር በማሳየት፣ እኩል ዕድል ተሰጥቶት በዛ ተጠቅሞና ተደግፎ በስራው ልክ ተጠቃሚ የሚሆንበት ፈጣን ቀጣይ ፍትሓዊ ልማት በማምጣት ልማታዊ አስተሳሰብ በተግባር በውጤቱ ታይቶ የህዝቡ ዋናው አስተሳሰብና ባህል እንዲሆን የሚያደርግ መንግስት መሆኑ፣

 

 

የልማታዊ መንግስት ሶስት ተልእኮዎች

ሀ) ልማትን በፓሊሲና ስትራተጂ በሕግ ብቻ ሳይሆን በጣልቃ ገብነትም በዕቅድም የሚመራና በፈጣን ቀጣይ ዕድገት ላይ የተመሰረተ ዕድገትና ተወዳዳሪነት በማስመዝገብ የአገሪቱ ሉአላዊነትና የኢኮኖሚዋ ተነፃፃሪ ነፃነት በቀጣይነት ማጐልበት፣

ለ) የነፃ ገበያ ዕድገት ማነቆ የሆነ የክራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብና ተግባርን እየመከተ በህዝብ ተሳትፎና በገበያ ውድድር እያከሰመ በሕግና በውድድር የሚያድግ ልማታዊ ባለሀብትን እየፈጠረ የክራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካዊ ኢኮኒሚን በልማታዊ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የበላይነት መተካት ክራይ ሰብሳቢነትን ከምንጩ ማድረቅ ፣

ሐ) ከፈጣንና ቀጣይ ልማቱ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍሎችና አካባቢዎች በየደረጃቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያደርግ፣ ፍትሓዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ የህዝቡ የማምረት አቅም ማሳደግና፣ ፍትሓዊ የመሰረተ ልማት የማህበራዊ ግልጋሎት ስርጭት እንዲኖር ማድረግ፣

የኢትዬጵያ ልማታዊ መንግስት ሁሉንም የልማታዊ መንግስት ባህርያትና ተልእኮዎች ከሞላ ጐደል የያዘ ሆኖ ግን ከምስራቅ ኤስያ አገሮች በተለየ ዴሞክራስያዊም ሆኖ ነው የተቋቋመውና ስራውን እየሰራ የቆየው፡፡ በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የብሄረ ብሄረሰቦች፣ የእምነቶችና የፖለቲካ አማራጭ ሓሳቦች በሰላማዊና ሕጋዊ መንገድ ለማስተናገድ የአገራችን አንድነትም ለማስቀጠል መንግስታችን የግድ ዴሞክራስያዊ መሆን ነበረበት፡፡ በህዝብ ይሁንታ በምርጫ የሚቋቋም፣ በሕገ-መንግስትና በሌሎች ሕጐች የሚገዛ፣ በመድበለ ፓርቲ ስርዓት በፌደራላዊ አወቃቀር የተደራጀ ሆኖአል፡፡

እዚህ ላይ ያለው ቁልፍ ጥያቄ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግስታችን ጥንካሬዎቹን አጐልብቶ ጉድለቶቹን አርሞ ማስቀጠል ነው የሚጠቅመን ወይስ ከነጭራሹ ልማታዊ መንግስት አያስፈልገንም ብለን በኪራይ ሰብሳቢዎች መንግስት መተካት? የሚል ነው፡፡ ሰላም ልማትና የዴሞክራሲ ጅምር ያመጣልንን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር ጥለን ገና በሚገባ ያልተጠና ያልበሰለ በተግባር ያልተሞከረ የመደመር ዕሳቤን እንከተል ካልን የቆጡን አወርድ ብላ የብብትዋን ጣለች ይሆናልና፡፡

 

 

ምዕራፍ - ሶስት

የመደመር ትርጉም በተመለከተ መፅሓፉ ላይ “መደመር ማለት፡-የመደመር ዋነኛ አላማ ሀገራችን ባለፉት ዓመታት ያስመዘገበቻቸውን የፖለቲካና የኢኮኒሚ ድሎች ጠብቆ ማስፋት፣ የተሰሩ ስህተቶችን ማረም እንዲሁም የመፃኢውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት ማሳካት ነው፡፡ በመሆኑም መደመር ከችግር ትንተና አንፃር ሀገር በቀል ነው፡፡ ከመፍትሔ ፍለጋ አንፃር ደግሞ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው” ይላል፡፡ (ገፅ 36)መፍትሔው ከውጭ የመጣ ከሆነ አገር በቀልነቱ ታድያ የት አለ?

የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ (የስርዓት ወይም የሕብረተሰብ ዕድገት ሕጐች ትንታኔ) ሊሆን ከሆነ ሁለንተናዊ አስተሳሰብ ሆኖ ርእዬት ሆኖ መቀረፅ ነበረበት፡፡ ፖለቲካውን ኢኮኒሚውን ማህበራዊና ባህላዊ ሁኔታን የመተንተን እይታ ወይም ርእዬት መሆን አለበት፡፡ የተሟላ ርእዬተ ዓለም ሊሆን ከሆነማ ተፈጥሮንም የሚረዳበትና የሚተነትንበት እይታ ጭምር ማካተት ነበረበት ፤ ከዚህ መመዘኛ አንፃር ርእዬት አይደለም፡፡ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሁለንተናዊ ትንታኔ አይደለም፡፡

ይዘቱ ያለፈውን የሚገመግም፣ ከዛ በጐውን የሚወስድና ስህተትን የሚያርም ነው ተብሎአል ስለዚህ ግምገማ ነው፡፡ መተንተኛ እይታው ምንድነው አይገልፅም፡፡ የመፃኢውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት ማሳካት ነው ተብሎአል ዕቅድ ይመስላል፡፡

የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሕግጋቶች ምን እንደሆኑና እንደየስርዓቱ፣ እንደየ አገሩ ዕድገት ደረጃ በምን መልክ እንዴት እንደሚለያይ በጐውን ማስቀጠል ችግሩን መፍታት እንዴት እንደሚቻል አያመላክትም፡፡ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሁለንተናዊ አስተሳሰብ ሳይሆን የግምገማና የታሪክ አስተምህሮ ይመስላል፡፡

ከመፍትሔ ፍለጋ አንፃር ደግሞ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው ተብሎአል፡፡ ታድያ ኢህአዴግ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ይሁን ልማታዊ መንግስትን ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምዶ ዴሞክራሲያዊና ፌደራላዊ ስርዓት ይሁን ብሎ የውጭም የአገር ውሰጥም ልምድ መቀመሩ ለምን ይወገዛል፡፡ ሳንመረምር እንዳለ በደረቁ ተገበርነው አልሰራልንም ለምን ተባለ? ዋናውመነሻ የአገራችን ሁኔታን በሚገባ አጥንቶና ገምግሞ ችግሮቹን ከለዩ በህዋላ መፍትሔ ማፈላለግ ላይ የአገራችንም የውጭም ልምድ በመቀመር የተገኘ አቅጣጫ አይደለም ወይ የ20 ዓመት ፈጣን ዕድገትን ያመጣልን፡፡ ምኑ ላይ ነው መደመር የተለየ ነገር ያመጣው፣ መፍትሔውን ከውጭ ልምድ ቀምረን ከሁኔታችን ጋር አገናዘብነው እየተባለ ነው፡፡ ኣልሸሹም ዞር ኣሉ ሆነ፡፡

ያለፈ ችግራችን ሁሉ ምንጩ ከውጭ የመጣ ርእዬትና አቅጣጫ ለመተግበር መምከራቸን ነው ሲባል ተከርሞ፣ የአሁኑ መደመር ግን አገር በቀል ነው ተብሎ ሲያበቃ የመደመር ትርጉም ሲቀመጥ ግን ተመልሶ እዛው ያወገዘው ነገር ላይ ዘጭ ብሎ ተገኘ፡፡ መደመር አገር በቀል ነው ሲባል ከራሳችን ችግር ጥናትና ከራሳችን የችግርና የመፍትሔ ቅደም ተከተል የመነጨ ለኛ በሚሆን በልካችን የተሰፋ ሲባል ነበር ልማታዊ መንግስትና ፌደራል ስርዓታችንስ በልካችን የተሰፋ አይደለም? ሕገ-ምንግስታችንስ? ካለፈው የተለየ ለመምሰል ከሆነ ያለፈውን ማውገዝ የተፈለገው አይጠቅምም፡፡ የዓለም ሕብረተሰብ ሁሉ በዘመናት ያከማቸውንመልካም ልምድና ትልቅ ዕውቀት መጠቀም የማይፈልግ ነው መደመር እንዳይባል ከሆነ የውጭም የአገር ውስጥም ልምድ የቀመረ ነው የተባለው አሁንም ቅንነት የጐደለው ከእውነት የራቀ ነገር ነው፡፡

አገር በቀል ሓሳብ ነው ሊባል ከሆነ በችግር መለየት ብቻ ሳይሆን በመፍትሔ ፍለጋም በዋናነት አገር በቀል መሆን አለበት በዛ የተቃኘ መሆን አለበት መደመር እንደዛ ነው ወይ? እውነት የአገራችንን ችግር ካለፈው በበለጠ ይፈታል ወይ? ወደ ዋናው ይዘቱ ስንገባ እናየዋለን፡፡ የመደመር እሴቶች በተመለከተ መፅሓፉ ላይ ሶስት እሴቶችን ያስቀምጣል፡፡ አንድ በአንድ ባጭሩ እንያቸው፡-

“ከመደመር እሴቶች አንዱ “ሀገራዊ አንድነት” ነው፡፡ ሀገራዊ አንድነት ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተገመደ፣ የተሰናሰለ እና የተዋሃደ መሆኑን አመላካች ነው፡፡ የሀገራችን ብሔሮች ዕጣ ፋንታ በጋራ ለማደግ የተሰራ ብቻ እንጂ ተለያይተን ወይም ተነጣጥለን ሉአላዊ ሀገር ሆነን የነጠላ ህልውናችንን አስጠብቀን በሰላም መቆየት አንችልም፡፡ ሀገራዊ አንድነታችን የምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ማስጠበቅ ጉዳይ ጭምር ነው” ይላል፡፡ (ገፅ 47)

ይሄ ሓሳብ ያፈጠጠ አሃዳዊ አመለካከት ነው፡፡ አንድነታቸን ከሁሉ በፊትና በዋናነት የሚረጋገጠው በዴሞክራሲና በፍትሓዊ ልማት ነው፣ በፍላጐትና በእኩልነት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም አማራጭ የሌለው ወደድክም ጠላህም ተቀብለህ የምትኖረው የግዴታ አንድነት አይሰራም ወይም ደግሞ ዕጣፈንታ ሆነብህ መለኮታዊ ግዴታ ሆነብህ እየተከፋህም የምትኖረው አይደለም፡፡

ስለዚህም በዴሞክራሲና በፍትሓዊ ልማት በፈጣንና ቀጣይ ዕድገት በሚፈጠር የአስተሳሰብና የፍላጐት ተመሳሳይነት፣ ብሔራዊ መግባባትና ኢኮኖሚያዊ ትስስር የሚፈጠር ነው፡፡ እንዳንለያይ ሆኖ የተጋመደ የተሰላሰለ የተዋሃደ አንድነት የሚባለው ያኔ ነው፡፡ ከተለያየን በየራሳችን መቆም አንችልም ምናልባትም እንፋጃለን ሰላም እንኳን አናገኝም ከሚል ስጋት የመነጨ አንድነት ዘላቂነት አይኖረውም፡፡ በዚህ ሓሳብ የተቃኘ ፖለቲካ ደግሞ ወደደም ጠላም አብሮ ይኖራታል እንጂ የትም አይሄድም የሚል መንግስትና ፓርቲ ስለ በፍላጐትና በእኩል ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ አንድነት ብዙም አይጨነቅም ለሓይል አንድነት፣ ለአሃዳዊ ስርዓት ቅርብ ነው፡፡

በተጨማሪ ደግሞ አንድነት እሴት አይደለም ራሱን የቻለ  ትልቅ አላማ ነው፡፡ መከባበር፣ መቻቻል፣ መተሳሰብ፣ ለጋራ ጥቅም መስራት ናቸው እሴት ሊባሉ የሚችሉት፡፡ እነዚህለዘላቂ አንድነት አላማ ማሳክያ መንገድ ይሆናሉ፡፡

ቀጥሎ መፅሓፍ ላይ እንዲህ ይላል “ሌላኛው የመደመር እሴት “የዜጐች ክብር” ነው፡፡ የዜጐች ክብር ኢትዬጵያውያን በሀገር ውሰጥም ይሁን በውጭ ሀገር ክብራቸው ተጠብቆና ሀገራቸውን መከታ አድርገው እንዲኖሩ ቅድምያ ሰጥቶ የመስራት ፍላጐት ነው”

ለዜጐች ክብር መቆም የመንግስትም የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው ተገቢ ነው፡፡ ግን በደፈናው ሲቀመጥ ተግባራዊ ላይሆን ይችላል የዜጐች ክብር በሚገባና በዘላቂነት የሚከበረው አገር ሲለማና በአገሪቱ ዴሞክራሲ ሲሰፍን፣ ዜጐች ሰርተው የምርታማነትና የመወዳደር ዓቅም አግኝተው ኑሮአቸው በቀጣይ ሲሻሻል፣ አገራቸው በዓለም ተወዳዳሪና ተፈላጊ ሆናስትከበር ነው፡፡ የድሀ አገር ዜጋ ወደ ሰው አገር ሲሄድ ላይከበር የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ሞያው ከሌለው ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ አገሩን የሚያከብርዋት ካልሆነች ዜጐቹም አይከበሩም፡፡ የዜግነት ክብር ምንጩ ሰው መሆን ብቻ የሚሆነው በአገሩ ሲኖር ነው፣ በአገሩም ዴሞክራሲ ሲኖር ነው፣ በሌላ አገር ሄዶ ሊከበር የሚችለው ደግሞ አገሩ በዓለም ያላት ቦታ ከፍ እያለ የሚሄድ ተፈላጊነት ሲኖራት ነው፡፡ ካልሆነ ግን አጉል ተስፋና መፈክር ሆኖ ይቀራል፡፡

ሶስተኛውን እሴት በተመለከተ ደግሞ “ከሌሎቹ እሴቶች ጋር እጅግ የተሳሰረው ሌላው የመደመር እሴት ብልፅግና ነው” ይላል መፅሓፉ፡፡ ብልፅግና እሴት ሳይሆን ዋናው አለማ ነው የሁሉም እሴቶች ማጐልበቻና ዋስትና ነው መባል አለበት፤ ስላለፈው ጉዞአችን መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “จจከነበረን ላይ ጨምረን ከመስራት ይልቅ የነበረውን አፍርሰን ጥራጊውን ካልደፋን የሰራን አይመስለንም የነበረው ነገር ምንም ይሁን በእሱ ላይ ቆሞ፣ ስህተቱን አርሞ ቀጣይ ጊዜን ከመተለም ይልቅ የነበረውን አፍርሰን እንደ አዲስ ለማጅ ሆነን እንጀምራለን፡፡” (ገፅ 42)

መልካም ሓሳብ ነበር ግን ቃሉና ተግባሩ አራምባና ቆቦ ሆኖአል፡፡ በእርግጥ የስርዓት ለውጥ ሲደረግ እና የተቋም ስር ነቀል ለውጥ ሲደረግ የሚፈርስ የሚወገድ ሓይል ወይም አደረጃጀትና አሰራር ወይም ሕግና አስተሳሰብ ይኖራል፡፡ ይሁን እንጂ መልካም የሆነና ለቀጣይም ጠቃሚ የሆነ ደግሞ ማስቀጠልና ማስፋት ማጠናከር አስፈላጊ ነው አስተዋይነት ነው፡፡ ንጉሳዊ አገዛዝ፣ መስፍናዊ የመሬት ይዞታ ስርዓት፣ የብሔርና የግለሰቦች መብት የሚያፍን ስርዓት መፍረስ ነበረበት ከነዚህ ጋር መታረቅና መደመር አይቻልም፡፡

በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የዕድገት ማነቆ የሆኑትን ሳይሆን የልማትና የዴሞክራሲ ማጐልበቻ ማፋጠኛ የሆኑትም ጭምር ሲፈርሱና ሲወገዱ እያየን ነው፡፡ ህዝባዊ ባህርይ ያለው ጠንካራ የመከላከያ ሰራዊታችን በሪፎርም ስም በውጭ ሓይሎች ፍላጐትና ጣልቃ ገብነት እየፈረሰ እየተቀየረ ነው፤ እሳት ማጥፋት ስራ ላይ እየተሰማራ ከህዝብ ጋር እየተጋጨ ነው፡፡ ተአምር የተባለለትን ልማት ያመጣ ልማታዊ መንግስታችንና ተስፋና አዲስ ኢትዬጵያዊነትን የፈጠረ ፌደራል ስርዓታችንና ሕገ-መንግስታችን የሁሉም ችግሮች ምንጭ ነው ተብሎ እየተወገዘ ነው ያለው፡፡ ያለፈው የልማት ስኬት የጨለማ ዘመን ተባለ፡፡ታድያ ቃልና ተግባሩ እየተጣረሰ አይደል !!

ምዕራፍ - አራት

የተደማሪነት ሳንካዎች

መፅሓፉ በገፅ 49 እንዲህ ይላል፡-

“መደመር በልኬት የሚታይ ፍልስፍና ነው፡፡ ለዚህ ፍልስፍና ያለን ቅርበት በመደመር ሜትር የሚለካና ከፍልስፍናው ሁለንተና ጋር ባለን ቅርበት መጠን የሚገልፅ ነው፡፡ ለመደመር ያለን ቅርበትም የመደመር ሳንካዎችን በምናፍልበት መጠን ላይ የሚወሰን ይሆናል፡፡ መደመር በጥቅሉ ሁለት ሳንካዎች አሉት፡፡ የግብር እና የአስተሳሰብ ”

ፍልስፍና ከሆነ በተቻለ መጠን ስለ ሕብረተሰብ ዕድገት ነባራዊ ሕግጋት በመጠኑ የሚያውቅና የሚተነትን፣ እነዚህ ደግሞ በፓለቲካ በኢኮኖሚ በማሕበራዊና በፖለቲካዊ መስክ እንዴት የሕብረተሰብ ዕድገትና ውድቀት አንድነትና ልዩነት እንደሚያሳዩ፣ ቅራኔዎችና ምንጫቸው ከነ አፈታታቸው የሚያመላክቱ መሆን አለባቸው፣ ታድያ እነኝህ ረቂቅ ማህበራዊ ሕግጋት እንዴት ነው በመደመር ሜትር የሚለኩት፡፡ ለምንስ ነው ስለፍልስፍናው መሰረታዊ ሓሳቦች ባግባቡ ላይተነተን ስለ ሳንካዎች የሚተነተነው፡፡ ለማንኛውም ሳንካዎቹን ስንፈትሽ ፍልስፍና ነው ወይስ አይደለም? ይዘቱስ ትክክል ነው ወይስ ስህተት እንረዳለን፡፡

የአስተሳሰብ ሳንካዎች ተብለው የተጠቀሱት ዋልታ ረጋጥነት፣ ጊዜ ታካኪነት፣ አቅላይነት ሞያን መናቅ፣ ሞገደኝነት፣ ፌዘኝነት እና አድር ባይነት ናቸው፡፡ ታድያ እነዚህ የሰው ባህርይና ጠባይ ወይንም አንዳንዶቹ ደግሞ ፖለቲካዊ አመለካከቶች ይሆናሉ እንጂ የፍልስፍና መሰረተ ሓሳብ ሊሆኑ አይችሉም የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሽታ ምንም የላቸውም፡፡ ግን ለማንኛውም የአንዳንዶቹን ይዘት እንየው፡፡

ስለ ዋልታ ረገጥነት መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “ፅንፍ የመያዝና እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል ግትርነት በሀገራችን የተለመደ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡ ለአብነት ያህል በሁለት ብሔረተኝነት እርሰ በራሱ እና በኢትዮጵያዊነት መካከል፣ በሃይማኖቶች መካከል፣ จจจበርእዬተዓለሞች መካከል፣ በተማከለና ባልተማከለ የመንግስት አስተዳደር ምርጫ จจจየመሳሰሉትን መጥቀስ ይቻላል” (ገፅ 50) ቀጠል ያደርግና መፍትሔ ሲጠቁም “ዋልታ ረገጥነትን የሚያጠፋው አንዱ መፍትሔ መሰረታዊ የአስተሳሰብ ሽግግር ማድረግ ነው፡፡ የአስተሳሰብ ሽግግር ጐራ የለሽ የልኬት ዕይታን የሚያዳብር ነው” (ገፅ 51) ይልና በመቀጠል “ነጭ ወይም ጥቁር ከማለት ይልቅ የጥቁረትን መጠን መለካት፣ ክፉ ወይም ደግ ከማለት ይልቅ የክፋቱን መጠን መለካት ወደ እውነቱ የበለጠ ያቀርበናል፡፡” ካለ ቦሃላ መፍተሔውን ሲቋጭ “በልኬት ላይ ባልተመሰረተ የጐራ ምደባነገሮችን ለመለወጥ አንችልም፡፡ ምክንያቱም አንዴ ጠላት ብለን በጐራ የለየነውን ሰው ወዳጅ ልናደርገው አንችልምና ነው” ብሎ ይደመድማል፡፡

ዋናው ፍሬ ነገሩ የማይታረቁትን ማስታረቅ፣ የማይደመሩትን መደመር ነው፣ የከበርቴና የላቭአደር ርእዬተ ዓለምን ማስታረቅ አይቻልም፡፡ ተፃራሪ ጥቅም ያላቸውን መደቦች ወይም የሕብረተሰብ ክፍሎች ርእዬት ስለሆኑ በየራሳቸው ስርዓት የራሳቸውን ርእዬት የበላይነት ያረጋግጣሉ እንጂ አስታራቂ ርእዬት አይፈጥሩም፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ግን የመብትና የጥቅም ድርድር ማድረግ ይችላሉ፡፡ ይህ ግን የርእዬት ድርድር ማለት አይደለም፡፡

ለብሔሩ ገዥ መደብ የበላይነት የሚሰራ የሌላውን ብሔር ማንነት የሚረግጥ የብሔር ፅንፈኝነትና ለብሔሩ ነፃነት የሚታገል አብሮ በእኩልነት መኖርን የማይቀበል ሌላው የብሔር ፅንፈኝነት ማስታረቅ አይቻልም፡፡ ከሁለቱ የተለየና ሁለቱንም ፅንፈኛ ብሔረተኝነቶች ያስወገደ ህዝቦችበእኩልነትና በመፈቃቀድ ለሚመሰረቱት አንድነት የሚታገል ዴሞክራስያዊ ብሔረተኝነት ማንገስ ነው መፍትሔው፡፡

ስለዚህ ሕብረተሰብ ውስጥ ያሉ ተፃራሪ ርእዬቶችና የተለያዩ ፓለቲካዊ አመለካከቶች የሕብረተሰቡ ሁኔታ ነፀብራቅ፣ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ውጤት ናቸውና የሉም ወይም እንደሌሉ እንቁጠራቸው ማለት አንችልም፡፡ ጐራ የለሽ አመለካከት እንከተል እሱ ነው የሚፈታው ማለት ነባራዊ እውነታውን መካድና ያስታረቀ መለሎ ነገሩን ማስቀጠል ማባባስ ወይንም ደግሞ በጉልበተኛው የበላይነት ማስቀጠል ይሆናል፡፡ ይህ ደግሞ ለገዥዎቹ ለኪራይ ሰብሳቢዎቹ ማመቻቸት ይሆናል፡፡

“ባለፉት ጊዝያት በተለይም ከ1960ዎቹ የተማሪዎች እንቅስቃሴ በህዋላ መድረኩን የተቆጣጠሩት የፖለቲካ ቃላትና አገላለፆች የሆነ ቡድንን ለማሸማቀቅ በሚውሉ ቃላት የተሞሉ ናቸው፡፡ ትምክሕተኝነት፣ ጠባብነት፣ ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ልማት፣ ፀረ-ህዝብ አድሃሪና የመሳሰሉት ቃላት ለዴሞክራስያዊ ንግግር የማይመቹና መቀራረብን ሳይሆን መራራቅን የሚያመጡ ናቸው” ይላል (ገፅ 53) ቃላቱን ማስወገድ በሌላ ለዘብተኛ ቃል መተካት እውነቱን መሸፋፈን ራሱን ማታለል ይሆናል እንጂ መፍተሔ አይሆንም ቃላቱን በሌላ ቃላት እንተካቸው ብለን ብንስማማ ቃላቱን የወለደ የጥቅምና የአስተሳሰብ ተቃርኖ፣ የአሰላለፍ ልዩነት ይቀየራል ወይ? ፀረ-ሰላም፣ ፀረ-ህዝብ፣ ፀረ-ልማት የተባሉት ሓይሎች ወደ የሰላም የልማት ሓይል መሆን ይቀየራሉ ወይ? ህዝባዊ ይሆናሉ ወይ?

ካልሆነ ለምንድነው የከረሩ ቃላትን እናለዝብ ወይም እንቀይር በሚል ሽፋን የማይታረቁትን ለማስታረቅ የተፈለገው? ለነፃ ገበያ ዕድገትና ለፍትሓዊ ተጠቃሚነት ማነቆ የሆኑትን ያለአግባብ የመበልፀግና የብሄር ፅንፈኝነት አመለካከትና ተግባር ያላቸውን ሓይሎች ጠበቃ መሆን የተፈለገው ለምንድነው? ብዙሃኑ ህዝቦች የነዚህ ሓይሎች ሰለባ እየሆኑ አገር እየተተራመሰ ያለው በነዚህ አመለካከቶችና እነሱን በሚያራምዱ ያሉ ሓይሎች ሆኖ እያለ በጐራ የለሽ ዕይታ ነው የሚፈታው የሚባለው? ለጅቡና ለተኩላው የሚመች እንጂ ለህዝቡ የሚመች ዕርቅ አይሆንም፡፡ የተዛባ አመለካከትና ጐጂ ተግባር ያላቸውን ሓይሎች ወይም ሰዎች በትግል በውድድር በሕግና በአስተምህሮ መግታት እንጂ አስታርቆ እንዲቀጥሉበት ማድረግ አይበጅም ፡፡

ነገሩን በጐራ የለሽ ዕይታ እንፍታው ማለት እነዚህ ፅንፈኛ አመለካከቶች የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረት እንዳላቸውና በዕርቅ ለማለዘብ መሞከር የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሕግጋትን የማይረዳ ምኞት አልያም እነሱን ለማዳን የህዝቡን ትግል ማለዘብና ማኮላሸት ይሆናል፡፡ በእርግጥ በከረሩ ቃላት መፈረጅ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ግን ዴሞክራሲ በማስፈን የዴሞክራሲ ተቋማት በማጐልበት ይፈታል፡፡ የህዝቦች እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማረጋገጥ፣ የህዝቦች መከባበርና መተሳሰብ በማጠናከር ይፈታል፡፡ የነፃ ገበያ ውድድርና ሞያና የስራ ውጤትን መሰረት ያደረግ ተጠቃሚነትን በማስፈን ሁሉም በስራው ልክና በሕጉና ስርዓቱ ብቻ እንዲጠቀም ማድረግ ይፈታዋል፡፡ ከዚህ ውጭየዕርቅና ይቅርታ አስተምህሮ ተደራቢ መፍትሔ ይሆን እንደሆን እንጂ ዋናው መፍትሔ አይሆንም፡፡ ነገሮችን ከስረ መሰረታቸው የማይረዳና ችግሮችን ከምንጫቸው የማያደርቅ የሚያድበሰብስ “ፍልስፍና” ነው፡፡

የግብር ሳንካዎች -

የግብር ሳንካዎች፣ የመደመር “ቀይ መስመሮች” የሚላቸውን ደግሞ መፅሓፉ እንደሚከተለው ያብራራል፡- “จจจበተለይም በላሸቀ ሞራል የሚደረጉ ዝርፍያዎችን የተደራጁ ሌብነቶችን የሚታገስበት ጐን የለውም” ይልና በመቀጠልም “መደመር ሁለት ነገሮችን የሚፀየፍ ፍልስፍና ነው፡፡ በነዚህ ሁለት ነገሮች ውሰጥ የተዘፈቀ ሰው ለመደመር ራሱን ከነዚህ ነገሮች የግድ ማፅዳት ይኖርበታል፡፡ ከህሊና ቢስነትና ከልግመኝነት” ይላል ትክክል ነው፡፡

የመደመር ፍልስፍና ችግር የሕብረተሰቡ ዕድገትን አንቀው የያዙ ችግሮች አምሮ የሚጠላና የሚታገላቸው መስሎ ዲስኩርና መፈክር ያበዛና ምንጫቸውና ዘላቂ መፍትሔያቸውን ማምጣት ላይ ግን እጅና እግሩ ይጠፋበታል፡፡ መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል “በሀገር ዕድገትና በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ሂደት ውስጥ አሉታዊ ሚናው ከፍተኛ የሆነው እና አደገኛ ካንሰር ተደርጐ የሚቆጠረውን ይህንን የህሊና ቢስነት በሽታ ከስሩ ነቅሎ ማጥፋት የመደመር መርህ ተደርጐ መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ይህ ደግሞ እውን የሚሆነው በተፈጥሮ የተቸርነውን የርትዕና የፍትሕ ዝንባሌ በዕውቀትና በተግባር በማበልፀግ በህሊና መመራትን ከለመድን ብቻ ነው፡፡” (ገፅ 73)

እንዲህ ያለ ባዶነት የተጠናወተው ፍልስፍና ምን ችግር ይፈታል፡፡ የሕብረተሰብ ዕድገት ሕግጋት፣ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረተ ሓሳብ ያልተረዳ ፍልስፍና ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የመነጨን መሰረታዊ ችግር በህሊናውነት አስተምህሮ በሞራል ስብከት ሊፈታው ይፈልጋል ለዚህማ በቤተክርስትያንና በመስጊድ ስንት የዚህ ዓይነት የግብረ ገብነት አስተምህሮ ሲሰጥ ቆይቶ የለም፡፡ ስግብግብነት፣ ዝርፍያ፣ ካለውድድር ካለሕጋዊ አካሄድ መክበር ከክራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የሚመነጭ ነው የገበያ ውድድር በኢኮኖሚው ባልሰፈነበት፣ ዴሞክራሲ ባልጐለበተበት፣ እጥረት በበዛበት የሚፈጠር የኪራይ ሰብሳቢዎች ተግባር ነው፡፡ ምንጩ ይሄ ስለሆነ መፍትሔውም በዋናነት የገበያ ውድድር ዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት፣ ልማታዊ ዕይታ በማስፈን መብቱን የሚያውቅ ዝርፍያን የሚጠየፍ ሕብረተሰብ በመፍጠር ነው፡፡

ዘላቂው መፍትሔ ችግሩን የፈጠረው የክራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ በልማታዊ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መተካት ነው፡፡ ይህም ማለት ውድድርን የሚያጐለብቱ እጥረትን በበቂ አቅርቦት የሚያቃልሉ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሚያሰፍኑና በስራ ውጤት ልክ መጠቀምን ዋናው ወይም ብቸኛው የተጠቃሚነት መንገድ እንዲሆን የሚያደርጉ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ሕጐች፣ የዴሞክራሲ ተቋማትና ሕግጋቶች ባህሎች ማጐልበት ነው፡፡ ከምንጩ ማድረቅ ማለት ይሄ ነው፡፡ ህሊናውነት በዚህ ላይ ተመስርቶና ደጋፊ ማጠናከርያ ሆኖ ብቻ ነው የመፍትሔው አካል የሚሆነው፡፡ ዋናው መፍትሔ አይሆንም፡፡ ክራይ ሰብሰቢውና ልማታዊው፣ አለአግባብ የሚበለፅጉትና ብዙሃኑ ይደመሩ ይታረቁ ጐራ መለየት አያስፈልግም፣ ጐራ የለሽ ዕይታ መያዝ ነው መፍትሔው የሚል ፍልስፍናና ፈላስፋ ይሄን ማድረግ አይችልም፡፡ መፈክርና ስብከት ከዛም ካለፈ የጠላው ላይ ያነጣጠረ አስተዳደራዊ እርምጃ ብቻ ነው መውሰድ የሚችለው፡፡

ታድያ የመደመር ሳንካዎችና ቀይ መስመሮች ብሎ ለይቶአቸው ሲያበቃ ምንጫቸውና ዘላቂ መፍተሔያቸው ማስቀመጥ ላይ ዳገት የሆነበት ለምንድነው? መነፅሩ የስነ ሂወትና የሞራል አስተምህሮ እንጂ የሕብረተሰብ ዕድገት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ነባራዊ ሕግጋት ስላልሆኑ፣ በደፈናው ሁሉን ነገር በመደመር በዕርቅና በስብከት ለመፍታት የሚሞክር ኢሳይንሳዊ ፍልስፍና ስለሆነ ነው፡፡

 

ማጠቃለያ አስተያየት

ስለ “መደመር” መሰረተ ሓሳቦች፡

በመቅድሙና በመግብያው ካሉ ሓሳቦች ጀምሮ መሰረታዊ ስህተቶች አሉበት፡፡ መቅድሙ ላይ “መደመር” የመነጨውና የዳበረው ከሕብረተሰባችን እሴቶችና ከተፈጥሮ ሕግ ነው ይላል፡፡ ከኢትዮጵያውያን እሴቶች መመንጨቱ ጥሩ ሆኖ ከተፈጥሮ ሕግ የመነጨና የደበረ መሆኑ ግን ስህተት ነው ፤ ምክንያቱም ስርዓት የሚገነባበት ፍልስፍና ሊሆን ከሆነ በዋናነት ከማህበራዊ ዕድገት ሕግጋት ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረተ ሓሳብ ነው መመንጨት ያለበት፡፡ የተፈጥሮ ሕግ የሰውን አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ ለመረዳት ይጠቅማል እንጂ የሕብረተሰብ በጠቅላላ ይሁን የተለያዩ የሕብረተሰቡ መደቦች ክፍሎች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ከዚያ የሚመነጩ የፖለቲካ አመለካከቶችና አሰላለፎች የጥቅም ትስስርና ግጭት ለመተንተን ይሁን የለውጥ ሓሳብ ለማመንጨት አይረዳም፤ ሰው ማህበራዊ ፍጡር እንጂ እንስሳ ወይም ግኡዝ ነገር አይደለምና፡፡

መግብያው ላይ ደግሞ ባለፉት ዘመናት ከውጭ አገር በተቀዱ ርእዬቶችና ፖለቲካዎች ስለተመራን ሳንመረምር ስለቀዳናቸው ችግራችን መልኩን ቀየረ እንጂ አልተፈታም ይላል፡፡ ሌሎች ሳይመረምሩ ከውጭ የቀዱትን ለመተግበር ሞክረው ሊሆን ይችላል፡፡ ኢህአዴግ ግን የአገራችን ችግር አጥንቶና ገምግሞ ችግራችንን ለይቶ አውቆ ከዛ በህዋላ የራሳችንና የውጭውን ልምድ ቀምሮ ነው ለአገራችን የሚሆን በኛ ሁኔታ የተቃኘ መፍትሔ ያመጣው፣ ውጤትም ያገኘው፡፡ መስፍናዊ ስርዓትን አስወግዷአል፡፡ ፌደራላዊ ዴሞክራስያዊ ስርዓት ተክሎአል፡፡ ተስፋ ሠጭ ልማት ሰርቷል፡፡

የመደመር ዕሳቤዎች መነሻ ሓሳቦች ብሎ ሁለት መሰረተ ሓሳቦችን ያስቀምጣል፡፡ የሰው ፍላጐቶች በአንድ በኩል ትስስርና አንድነት አላቸው በሌላ በኩል ተቃርኖ አላቸው ይልና በመደመር ብቻ ነው ፍላጐቶቹ የሚሟሉት፣ ፍላጐቶቹም፣ ሰዎቹም መደመር አለባቸው ይላል፡፡ ይህ ጀምላዊ ድምዳሜ ከማህበራዊ ዕድገት ሕግጋት ጋርና ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረተ ሓሳብ ጋር ይጋጫል፡፡

ተፃራሪ ጥቅሞች አይታረቁም በመደመር የሁለቱም ወገን ጥቅሞች አይሟሉም ይደመሩ ቢባል የተሻለ ጉልበት ያለው የበላይ ይሆናል፤ የአንበሳን ድርሻ ይይዛል ተቃርኖው ይቀጥላል ወይም ይባባሳል፡፡ለምሳሌ የመሳፍንትና የአርሶ አደሮች የጌቶችና የባርያ ፍላጐቶች ሊደመሩ አይችሉም፡፡ የወራሪና የቅኝ ግዛት አገር ወይም ህዝብ ፍላጐቶችም በመደመር አይፈቱም፡፡ በመደመር የጋራ ጥቅም የሚያረጋግጡት ተፃራር ጥቅሞች ሳይሆን መለስተኛ ልዩነት ወይም መለስተኛ የጥቅም ተቃርኖ ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ ሁሉም በመደመር ነው ጥቅማቸው የሚረጋገጠው የሚለው ሓሳብ ገዥና ተገዥ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ ታረቁ ብሎ ጭቆናና ብዝበዛን የሚያስቀጥል ገዥና የበላይ ለሆኑት የሚያደላ ሓሳብ ነው፡፡ በትርፍራፊ በድለላና በማድበስበስ ጭቁኖችን አስታግሶ ጭቆናና ብዝበዛ በማስቀጠል ለገዥዎች የሚመች ሁኔታን የሚፈጥር ሰላቢና የጭቁኖችን ትግል የሚያኮላሽ ነው፡፡

ከዛም ቀጥሎ የኢትዬጵያ ባለሀብት በመንግስት እየተገፋ ቀጨጨ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲና በመንግስት ጫና ተዳክመው እንደቀሩና አውራ ፓርቲ እንዲፈጠር ሆን ተብሎ ተሰርቶአል ይላል፡፡ ባለሃብቱን ያቀጨጨው ዋናው ምክንያት ነባራዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ለክራይ ሰብሳቢው የተመቸ ውድድር የሌለበት በመሆኑና ይህን ሁኔታ ለመቀየር መንግስት የሰራው ስራ በቂ ባለመሆኑ ነው፡፡ መንግስት በኢኮኖሚው ጣልቃ በመግባት ሊሰራው ከሚገባ በላይ አልፎ እየሄደ ባለሀብቱን ስለገፋው የተፈጠረ ችግር ቢኖርም መለስተኛ ነው፡፡ ተደራቢ ምክንያት እንጂ ዋና ምክንያት አልነበረም፡፡ የተዛባ ትንታኔ የቀረበው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ይቅር፣ ልማታዊ መንግስት አያስፈልግም ለማለት መነሻ እንዲሆን ተፈልጐ ይሆናል፡፡

አውራ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውሰጥ የተፈጠረው ገዥ ፓርቲው(ኢህአዴግ) ይሁን መንግስት ሆን ብሎ ስለ ደፈጠጣቸው(ተፎካካሪ ፓርቲዎችን) ሳይሆን ህዝቡን የሚያሰልፍበት ችግር ፈቺ አማራጭ ስላላቀረቡና መሬት ወርደው በገጠሩም በሁሉም ከተሞችም ቀጣይ በቂ የማደራጀትና የመቀስቀስ ስራ ስለማይሰሩ ነው፡፡ የያዙት አማራጭ ቢኖርም ይዘቱ ለአገራችን ችግሮች መፍትሔ የማይሆን ህዝቡ ያልተቀበለው ስለሆነ ነው፡፡ በመንግስትና በገዥው ፓርቲ የደረሰባቸው ጫና ቢኖርም ፖለቲካዊ ምህዳሩ አለመስፋቱተደራቢምክንያት ብቻ ነው የነበረው፡፡

ቀጠል አድርጐ ስለ ሶሻሊዝምና ሊበራሊዝም ምንነት የተዛባ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ሶሻሊዝም በዋናነት ለእኩልነት ቅድምያ ይሰጣል፡፡ ሊበራሊዝም በዋናነት ለነፃነት ቅድምያ ይሰጣል ይላል ትክክል አይደለም፡፡ ሊበራሊዝም ሲጀመር ለሰው ልጆች ነፃነት የቆመ አልነበረም፡፡ ዴሞክራሲውን ለባለሀብቱና ለጥቂት ሙሁራኑ ብቻ በመስጠት ጀምሮ ከዛ ሴቶችን፣ ንብረት የሌላቸውን ጥቁሮችን ጠቅልሎ ያገለለ ነበር ይህን ጉድለቱን ለማረም ከ100 አመት በላይ ትግል ጠየቀ፣ በባለሀብቱ ፍላጐት ሳይሆን በህዝቡ ትግል ነው ሊበራል ዴሞክራሲ ወደ ንብረት አልባና ወደ ሴቶች ወደ ጥቁሮች የተዳረሰው፡፡ ስለዚህ ሊበራል ዴሞክራሲ ወገንተኛ አግላይ ነበር ለሰው ልጆች ሁሉ ነፃነት የቆመ አልነበረም፡፡ ሶሻሊዝም ደግሞ ለእኩልነት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ከማንኛውም ዓይነት ጭቆናና ብዘበዛ የሰው ልጆችን በሙሉ ነፃ የማውጣት አላማ የያዘ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ደረጃ ተግባራዊ ሆኖ አያውቅም፡፡

የምከርናቸው ርእዬቶች ለምን አላሻገሩንም ለሚል ጥያቄ የሰጠው ምላሽ በዋናነት ሳንመረምር ከሁኔታችን ጋር ሳናገናዝብ ከውጭ የቀዳናቸው ስለሆኑ ነው ይልና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደግሞ ባለሀብቱን ወደ ጐን ስለገፋና በፖለቲካ ነፃነት ስላልታጀበ ነው ይላል፡፡ ስለዚህ ሌላ አማራጭ ያስፈልገናል ይላል፡፡ ግን የተገፋ ባለሀብት ካለ ማቀፍ፣ ለፖለቲካ ነፃነት ተገቢ ትኩረት መስጠት ይፈታዋል፡፡ አብዬታዊ ዴሞክራሲ ደግሞ በሕገ-መንግስቱ በኢኮኖሚ ፖሊሲዎቻችን ከሀገራችን ሁኔታ ጋር በሚገባ ስለተጣጠመ ወቀሳው ልክ አይደለም፡፡

አማራጭ ተብሎ የቀረበው “መደመር” ሲተረጐም ባለፈው የተመዘገቡ ድሎችን ማስፋት፣ ስህተቶችን ማረም፣ የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጐት ማሳካት ነው ይላል፡፡ ይሄ ከሆነ ፍልስፍናም ፖለቲካዊ ኢኮኖሚም አይደለም ገፋ ቢል ግምገማና የወደፊት ፖሊሲ ወይም ዕቅድ ሊሆን ይችላል፡፡ በምንም መስፈርት እንደ ሊበራሊዝም ወይም ሶሻሊዝም ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ(ልማታዊ ዴሞክራሲ) የማህበራዊ ዕድገት ትንታኔና የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረተ ሓሳቦች የሉትም ባዶ ነው ወንዝ አያሻግርም፤ የመደመር መፍትሔ ከሀገር ውስጥም ከውጭም ትምህርት በመውሰድ የተቀመረ ነው ይለዋል፡፡ ታድያ ልማታዊ ዴሞክራሲምኮ ከውጭ የልማታዊ መንግስታት ልምድ ወስዶ ከሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ለማጣጣምና በስም የተቃኘ ለማድረግ ደግሞ ዴሞክራሲም ፌደራል ስርዓተም ያስፈልገናል አለ፡፡

ግብርና መር የእንዱስትሪ ዕድገት ፖሊሲና ገጠርና አርሶ አደርን ማእከል ያደረገ የልማት ስትራተጂ ነደፈ፡፡ ምኑ ላይ ነው ታድያ ለራሳችን ችግር አገር በቀል መፍትሔ መከተል እንጀምር የተባለው?

የመደመር ዕሴቶችና ሳንካዎች ተብለው የቀረቡት ደግሞ መሰረተ ሓሳብ አይደሉም፡፡ አንዳንዳቸው ዕሴት ተብለው የቀረቡ (ለምሳሌ ብልፅግና) አላማ ናቸው፡፡ አላማ መሆን ሲገባው ዕሴት ነው ተብሎ የቀረበው አንድነት ደግሞ የአገራችንና የህዝቦቻችን አንድነት እንዳንለያይ ሆኖ የተጋመደ፣ የተሰናሰለ እና የተዋሃደ ነው ይለዋል፡፡ ይህ ከሆነ ወደድንም ጠላንም የግድ አንድ እንሆናለን የሚል አሃዳዊ አመለካከት ነው፡፡

ሲጠቃለል “መደመር” መነሻ ያደረጋቸው መሰረተ ሓሳቦች የተፈጥሮ ሕግና ዕሴቶቻችን ብቻ ስለሆኑ የማህበራዊ ዕድገት ሕግጋትና የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ይዘት የላቸውም፡፡ ፍልስፍና አይደለም፣ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚም አይደለም፡፡ የሕብረተሰብ መሰረታዊ ችግርን የመተንተን ይሁን መፍትሔ የማምጣት ብቃት የለውም የዕሴቶች ሚና መለስተኛ ነው የተፈጥሮ ሕግ ደግሞ ተፈጥሮን እንጂ የሕብረተሰብን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መተንተኛ አይሆንም፡፡ በተጨማሪ ደግሞ ተፃራሪ ጥቅሞችና ባህርዬች ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎችን በመደመር ይታረቁ ሁሉም ይጠቀማሉ ብሎ ጭቁኖችና ብዙሃኑ በጉልበተኞች ስር እንዲገቡ ያደርጋል፡፡ ያለፈውን ጉዞአችን ምንም ችግር ያልፈታ አድርጐ ዋጋ ቢስ ያደርጋል፡፡

የሊበራሊዝም፣ የሶሻሊዝምና የአብዬታዊ ዴሞክራሲ የልማታዊ መንግስት ትርጉምን አዛብቶ እያምታታ ሁሉም ለኛ አይሆኑም ብሎ የትም የማያሻግር “አገር በቀል” የመደመር ዕሳቤ እንከተል ይላል፡፡ ጐራ የለሽ አስታራቂ አማካይ ሓሳብ አመጣሁ ብሎ በክራይ ሰብሳቢዎችና በውጭ ሓይሎች ስር እንድንገባ በነሱ ጥቅም የበላይነት እንድንኖር ይወተውታል፡፡ መደመር ወገንተኛ አይደለም፣ ጐራ የለሽ ዕይታ እንከተል እያለ በተጨባጭ ይዘቱ ግን ወገንተኝነቱ ለጥገኛ ባለሀብቱና ለውጭ ሓይሎች ሆኖ ይታያል ባለሀብቱና ተፎካካሪ ፖርቲዎች ሆን ተብሎ በመንግስቱና በአውራ ፓርቲ ተገፍተዋል ብሎ የአዞ እንባ ያነባላቸዋል፡፡በድምር ሲታይ የመደመር ዕሳቤ የአገራችንን ተጨባጭ ሁኔታ በሚገባ ያላጠና ታሪካችንና ስኬታችን ሆን ብሎ የሚያዛባ፣ ፍልስፍና ኣይሉትፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ኣልሆነ የሃይማኖት አስተምህሮና የስነ-ሂወት ትምህርት ይመስላል፡፡ አጉል ሆኖ የቀረ የተቀነጫጨበ ሓሳብ ነው፡፡ በሺዎች አመታት ታሪክ በታወቁ ሙሁራን ተጠንቶ የሕብረተሰብ ዕድገት ሕግጋትና የተቀመረ ልምድን  ውድቅ አድርጎ ከዜሮ መጀመር የሚፈልግ ችግራችንን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብስ ዕሳቤ ነው፡፡

 

 

 

 

ክፍል - ሁለት

2.1.የሀገራችን የፖለቲካ ስብራትና የጥገና አማራጭ

 

ምዕራፍ- አምስት

ጭቆናና የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ህልውና

የዚህ ምዕራፍ ፍሬ ነገር ያለፉት የሀገራችን ነገስታት በአጣዳፊ ሀገር የመከላከልና የማረጋጋት ስራ ላይ ስለተጠመዱነው የህዝቡን ፍላጐት ማሟላት ያልቻሉት ህዝቡ ሲቃወም ደግሞ ጨቋኝ መሆን የስልጣን ማስጠበቅያ ዘዴ አደረጉት ብሎ ይጀምራል፡፡ ቀጥሎም ሁለት ዓይነት ጭቆና አለ፡- ሰው ወለድ ጭቆናና መዋቅር ወለድ ጭቆና ብሎ ያብራራል፡፡ እያንዳንዱን አጠር አድርገን እንፈትሽ፡፡

ስለኢትዮጵያ ነገስታት እንዲህ ይላል “จจነገስታቱ ከውስጥም ከውጭም የሚነሱትን አጣዳፊ የፖለቲካ ጥያቄዎች ለመፍታት ሲንገታገቱ ሀገሪቱን ለማበልፀግም ሆነ ለማሰልጠን የሚጠቅም አቅጣጫ ለመቅረፅም ሆነ ለመተግበር ፋታ አላገኙም፡፡” (ገፅ 78)

“ዋናውን ጉልበታቸውን የህዝብን ፍላጐት ለማሟላት ሳይሆን አጣዳፊ የህልውና አዳጋዎችን ለመመከት ስለሚያፈሱት የፍላጐት መጓደሉአመፁን ጉልበት ይሰጠዋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥም ጭቆናን ዋና የህልውና ማስጠበቅያ ዘዴ ያደርጉታል፡፡” (ገፅ 79)

በነዚህ ሁለት ጥቅሶች ውስጥ ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች አሉ፡፡ አንዱ ነገስታቱ ሀገርን በመከለከልና በማረጋጋት ስራ ላይ ስለተጠመዱ ነው አገርን ማበልፀግና ማሰልጠን ያልቻሉት የሚለው ነው፡፡

ሁለተኛው ደግሞ ጨቋኝ የሆኑት ህዝቡ ፍላጐቱ ስላልተሟላለት በማመፁእሱን አመፅ ለመግታትና ስልጣናቸውን ለማራዘም ነው የሚለው ነው፡፡

በአፄ ቴዎድሮስና በአፄ ዬሃንስ ዘመነ መንግስት የውጭ ወረራና የአከባቢ መሳፍንት ዓመፅ የማይያቋርጥ ስጋት የፈጠረባቸውና የጠመዳቸው ቢሆንም በመስፍናዊ ስርዓት ውስጥ ሆኖ ሊያመጡት የሚችሉ ብልፅግናና ስልጣኔ ከጀማሪ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ የማያልፍ ነው፡፡ ዴሞክራሲ ደግሞ በማንኛውም የመሳፍንት ስርዓት ተተግብሮ አያውቅም፡፡ ስለዚህ ፋታ ቢኖራቸውም ስልጣኔን ከማስጀመር ባለፈ የዳበረ ስልጣኔና ብልፅግና ማምጣት አይችሉም ነበር፡፡ መስፍናዊ የመሬት ይዞታውና ፀረ-ዴሞክራሲ ባህርያቸው ከዛ ያለፈ ነገር እንዲያመጡ አያስችላቸውም፡፡

ይህም ሃቅ በአፄ ሃይለስላሴ ጊዜ ታይቶአል፡፡ አፄ ሃይለስላሴን ፋታ ያሳጣ ከባድ ስጋት አልነበረም (አንዴ ከተከሰተው የጣልያን ወረራ ውጭ) በዛ በተረጋጋ ከ50 ዓመታት በላይ የነገሱበት ዘመን ከጅምር ያለፈ ስልጣኔ አላመጡም፡፡ ብልፅግና ያመጡ ነበር ብሎ ማሰብ የሕብረተሰብ ዕድገት ሕግጋትን የስርዓቶች ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ባህርያትን ማዛባት ነው፡፡ የመደመር ዕሳቤ በነዚህ ሕግጋት ላይ እምነት የሌለው ስለሆነና በሰው ስነ-ሂወትና የሞራል ባህርያት ላይ ብቻ ስለሚታጠር ይህን መቀበል አይችልምና፡፡

ጨቋኝ የሆኑት ደግሞ ህዝቡ ስላመፀ ሳይሆን ገና ሳያምፅ ጀምሮም ባህርያቸው ስለሆነ ረግጠውና አስገድደው መግዛትና መበዝበዝ የኑሮአቸውና የሀብታቸው የስልጣናቸው መሰረት ነው፡፡ መስፍናዊ ጭቆና ብስርዓቱ ባህርይ ከገዥዎቹ ጨቋኝ አገዛዝ የሚመነጭ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ነባራዊ ሕግ ነው፡፡ ህዝቡ ባያምፅም አስገድደው ጉልበቱን ሲበዘብዙና ከመሬቱ ሲያፈናቅሉት አለአቅሙ ግብር ሲያስከፍሉት ፍትሕ በአድልዎ ሲነፍጉት ኑረዋል፡፡ አመፁ የጭቆና ምንጭ ሆነ ሳይሆን ጭቆናው የአመፁ ምንጭ ሆነ ነው የሚለው የሕብረተሰብ ዕድገት ሕግጋቱና የፖለቲካዊ ኢኮኖሚው መሰረተ ሓሳብ፡፡ አሁንም መደመር ስነ-ሂወትና የሰው ሞራላዊ ባህርይን እንጂ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሕግጋትን የማያምን መሆኑ ያሳያል፡፡

መፅሓፉ ስለ ጭቆና ዓይነቶች እንዲህ ይላል “በማንኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሊሰፍን የሚችለውን ጭቆና በሁለት ከፍለን ልናየው እንችላለን፡፡ አንደኛው የጭቆና ዓይነት ከሰዎች ክፉ ሓሳብና ህሊና የሚመነጭና በሰዎች ፍላጐትና ዕቅድ የሚተገበር ጭቆና ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ጭቆና ጨቋኝና ተጨቋኝ ያሉበትና ጭቆናው የሚያበቃውም ጨቋኞችን ታግሎ ድል በማድረግ ይሆናል፡፡ ይኸኛውን የጭቆና ዓይነት “ሰው ወለድ ጭቆና” ልንለው እንችላለን፡፡ ሁለተኛው የጭቆና ዓይነት ደግሞ ከመዋቅር ወይም ከስርዓት የሚመነጭ ጭቆና ነው፡፡ ይሄኛውየጭቆና ዓይነት በዴሞክራስያዊ ሀገራትም ጭምር የሚስተዋልና ጭቆናው ሆነ ተብሎ የማይከወን፣ ነገር ግን የተዘረጋው ተቋማዊ መዋቅር ወይም ስርዓት ሰዎችን መርጦ የሚያጠቃና ፍላጐታቸውን የሚያጓድል ሲሆን ነው …በዚህም ምክንያት የጭቆናው ምንጭ መዋቅሩ ነው ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ጭቆና “መዋቅር ወለድ ጭቆና” ሊባል ይችላል፡፡” (ገፅ 82)

አሁንም ትንታኔው ሁለት መሰረታዊ ስህተቶች አሉበት፡፡ አንደኛው ስህተት “ሰው ወለድ ጭቆና” የተባለው ከሰዎች ክፉ ሓሳብና ህሊና የመነጨ ሳይሆን ከገዥዎች በዝባዥና ጨቋኝ ባህርይ የእነሱን ጥቅም ከማያስጠብቅ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ስርዓት የሚመነጭ ነው፡፡ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ይሁን ኢኮኖምያዊ ግኑኝነቱ የተዋቀረበት ነባራዊ ሕግ የወለደው ነው፡፡ ከስርዓት ወደ ስርዓትም ይለያያል፡፡ “መዋቅርወለድ ጭቆና” የተባለው ደግሞ የስርዓቱ ሌላው ገፅታና የገዥዎች አመለካከትና ፍላጐት የፈጠረው መዋቅር ነው፤ ሆን ተብሎ የሚዘረጋ የጭቆና መዋቅር ነው፡፡ ሁለቱም የጭቆና ዓይነቶች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅ ናቸው ሊነጣጠሉ አይችሉም፡፡

“ሰው ወለድ ጭቆና” የጨቋኝና ተጨቋኝ ግኑኝነት ነው፤ የሚፈታውም ጨቋኞችን ታግሎ ድል በማድረግ ነው ይላል መፅሓፉ፡፡ ሰው ወለድ ነው ማለቱ ስህተት ቢሆንም መፍተሔውን ግን በትክክል አስቀምጦታል ጐራ የለሽ ዕይታ ይኑረን የሚለው መደመር አሁን ደግሞ ስለጨቋኝና ተጨቋኝ ትግል ይተነትናል፡፡ በሌላ አነጋገር የመደብ ትግል ነው የሚፈታው እያለን ነው፤ ባንድ መፅሓፍ ሁለት እርሰ በርስ የሚጋጩ ሓሳቦች እየነገረን ነው፡፡

ግን ደግሞ “መዋቅር ወለድ” ጭቆና ሆን ተብሎ የሚከወን አይደለም ይለዋል ሰዎችን መርጦ የሚያጠቃና ፍላጐታቸውን የሚያጓድል ነው ይለዋል፡፡ በጣም የተምታታ ሓሳብ ነው፡፡ ሰዎችን መርጦ (ጥቁሮችን፣ ሴቶችን፣ አናሳ ብሄረሰቦችን፣ የአንዱ እምነት ተከታዬችን) የሚያጠቃ ከሆነ እንዴት ነው ሆን ተብሎ የማይከወን የሚባለው?

ትልቁ የፍልስፍናው ባዶነት የሚመነጨው ነገሮችን ነጣጥሎና በጣጥሶ የሚያይ በስነ-ሂወትና ስነልቦና ትንታኔ ዕይታ የሚረዳ የሕብረተሰብ ሕግጋት የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረተ ሓሳብ የማይቀበል ከመሆኑ ነው፡፡ ሁለቱም ጭቆናዎች መዋቅራዊ ሆነው እያለ አንዱን ከሰዎች ክፋት የሚመነጭ ሌላኛውን ከነባራዊ መዋቅር የሚመነጭ ብሎ ትርጉም ያሳጣቸዋል፡፡

መፍትሔ ይሆናል የሚለው ደግሞ መዋቅራዊ ጥገና ነው፡፡ ጠጋግኖ ማድበሰበስ ይሆንና አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ እንደሚባለው ይሆናል፡፡ መዋቅራዊ ጭቆና በድኖችን ነው የሚበድለው (ብሔር፣ አከባቢ፣ መደብ፣ ፆታ፣ ሃይማኖት ወ.ዘ.ተ) ይልና መዋቅራዊ ጭቆና ውስብስብ ስለሆነ ለመረዳትም መፍትሔ ለመሰጠትምአስቸጋሪና ጊዜ የሚወስድ ነው ይላል፡፡ እንዴት እንደሚጠገን እንኳ ጥርት ያለ ምላሽ አያስቀምጥም፡፡

በቡድን ላይ የሚደርስበደል በቡድን ተደራጅቶ(በብሔር፣ በፆታ፣ በዕድሜ) ለመፍታት መሞከር ወደ ቡድናዊ አክራሪነት ስለሚያመራ መፍትሔ አይሆንም ብሎ ያጣጥለዋል፡፡ መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል (ገፅ 90) “የግለሰብ መብት አቀንቃኞች የቡድን ማንነትን በማጥፋት ስም ጭቆናውን የሚያድበሰብስና የጭቆና ቅሪትን የሚተው መፍትሔ ነው ያመጡት ብለናል፡፡ ሆኖም በሌላ በኩል ደግሞ የቡድን ማንነትን ይዞ ከጭቆና ለመውጣት መታገል የቡድን አክራሪነትን በመፍጠር ከሚፈታው ይልቅ የሚፈጥረው ችግር እየባሰ መጥቷል” በቡድን ተደራጅቶ ቡድኑ ላይ የሚደርሰውን በደል መመከት የግድ ወደ አክራሪነት ያመራል ብሎ መደምደም ስህተት ነው፡፡ ለእኩልነት ለጋራ ተጠቃሚነት፣ በፍላጐትና በእኩልነት ለተመሰረተ አንድነት ከታገለ በዚህ አቅጣጫ ከተመራ አክራሪ አይሆንም፡፡

ቀጠል በማድረግ መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “የቡድን መብትን ለማስከበር የሚደረገው ትግል ጫፍ እየረገጠ፣ የሀገርን ሰላም የሚያናጋና ዜጐች ተቻችለው እንዳይኖሩ የሚያደርግ ነው፡፡ የዚህም ምክንያት የቡድን ማንነት ስነ-ልቦናዊ ገፅታ ስላለው የመብት ታጋዬቹ መብትን በማስጠበቅ ሂደት ወደ ስነ-ልቦናዊ ጦርነት ስለሚገቡ ነው፡፡ ስነ-ልቦናዊ ጦርነቱም ሀገርን ወደ ብጥብጥ ይወስዳታል፡፡” (ገፅ 90)

ይህ ሓሳብ የብሄር ብሄረሰቦች መብት ጥያቄ(የቡድን መብት ጥያቄ) የሀገርን ሰላም የሚያናጋ፣ ዜጐች ተቻችለው እንዳይኖሩ የሚያደርግ በታኝ ፀረ-አንድነት ጥያቄ ነው የሚል መልእክት የያዘ ነው፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የቡድን መብት ጥያቄ የሚነሳው ባብዛኛው ይህ መብት ሲታፈን የአንዱ የበላይነት ሲኖር ነውና ዋናው በታኝ ፀረ-አንድነት ሓይል የብሔር ወይም የሃይማኖት የበላይነት የፈጠረው ሓይል ነው፡፡ የአድልዎ የጭቆና ፖለቲካ የሚያራምደው ሓይል ነው፡፡ ሁለተኛ ሁሉም የቡድን መብት ጥያቄ ሰላም የሚያናጋና የህዝቦች ይሁን የዜጐች አንድነት የሚያናጋ አይደለም መንስኤውም የስነ-ልቦና ጦርነት ስለሚያካሂድ ሳይሆን(እሱ ተደራቢ ነገር ይሆናል) የቡድን መብት ጥያቄን ለማፈን የሚካሄድ ጭፍጨፋና ጅምላዊ ፍረጃ ስለሚኖር ነው፡፡

ዋናው አደገኛ ነገር ደግሞ ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳት የቡድን መብት ጥያቄና የብሔር ድርጅቶችን ብሎም በማንነት ላይ የተመሰረተ አከላለልን ለማፍረስ ለማስወገድ ተግባራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸው ነው፡፡ የተዛባ የመደመር አስተሳሰብ የመጣውም ይህን እርምጃ ለመውሰድ የሚረዳ ንድፈ ሓሳብ ለማምጣት ይመሰላል፡፡

ምዕራፍ - ስድስት

ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን የመፍጠር ትልም፡-

የዚህ ምዕራፍ ፍሬ ነገር ዴሞክራሲ ባብዛኛው የአብላጫ ድምፅ ልዕልና የሚያሰፍን ሆኖ ለሀገራችን ዓይነቱ የብሔርና የሃይማኖት ብዝሃነት ያላቸው አገሮች ግን የመግባባት ዴሞክራሲ ተመራጭ ይሆናል፡፡ እስካሁን ተገቢ ምላሽ ያላገኘው ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም የእስካሁን የዴሞክራሲ ጅምራችን ለነፃነትና ለወንድማማችነት ዝቅተኛ ትኩረት የሰጠ፣ እኩልነት ላይ ያተኮረ ነበርና፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል የሚል ነው፡፡

መፅሓፉ ላይ የኢትዮጵያ ህዝቦች ሶስት ጥያቄዎች ነበራቸው፡፡ የመሬት ጥያቄ፣ የብሔር ጥያቄ፣ የዴሞክራሲ ጥያቄ ይልና “እነዚህን ሶስት ጥያቄዎች ለመመለስ ቢያንስ ሁለት አብዬቶች አሳልፈናል፡፡ የ1966ቱ አብዬት ከነውሱንነቶቹም ቢሆን የመሬት ባለቤትነትን ጥያቄ መሬትን ለአርሶ አደሩ በማካፋፈል መልሷል ማለት ይቻላል፡፡ የ1983ቱ አብዬት ደግሞ የብሔር ጥያቄን ከነውሱንነቶቹም በሕገ-መንግስቱና በፌደራል ስርዓቱ በዋናነት መልስ እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ በሁለቱም አብዬቶች በአግባቡ ሳይመለስ እስከአሁን የዘለቀው የዴሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡” ይላል (ገፅ 93)

ቀጠል አድርጐም ከሶስት የዘመናዊነት ዕሴቶች ዴሞክራሲያችን እኩልነት ብቻ ነው ያጐላው፡፡ የነፃነትና የወንድማማችነት ዕሴቶች ሁለቱም አብዬቶች ዝቅተኛ ትኩረት ነበር የሰጡት፡፡ ስለሆነም በአገራችን ዴሞክራሲ ሊገነባ አልቻለም ይላል፡፡

የዴሞክራሲያችን ዋነኛ ጉድለቶች ነፃነትና ወንድማማችነት ናቸው ወይ? አይደሉም፡፡ እነዚህ የሌላ መሰረታዊ ጉድለቶች ውጤት ናቸው፡፡ የዴሞክራሲ መዳበርና ቀጣይነቱ መረጋገጥ መሰረቶችና ዋስትናዎች በዳበረ ኢኮኖሚ ላይ የተመሰረቱ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትና የዴሞክራሲ ባህል ያዳበረ ሲቪክ ማሕበረሰብ መፈጠር ናቸው፡፡ ነፃነትና ወንድማማችነት በነዚህ ላይ ተመስርተው የሚፈጠሩ የሚዳብሩ ውጤቶች ናቸው፡፡ አለበለዝያ መሰረት የሌላቸው መፈክሮችና ምኞቶች ሆነው ይቀራሉና፡፡

ዴሞክራሲያችን ወንድማማችነትን አላጠናከረም፣ ለሱ በቂ ትኩረት አልሰጠም የተባለው ስህተት ነው፡፡ ባለፉት ስርዓቶች የብሔር፣ የሃይማኖትና የፆታ አድልዎ በመንግስት ፖለሲና ሕግ የተደገፈ ነበር በዛሬው ሕገ -መንግስታችንና ፌደራል ስርዓታችን ግን የሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች እምነቶችና ፆታዎች እኩልነት ብቻ ሳይሆን መተዋወቅ መተሳሰብና መከባበርም ከድሮው በተሻለ እየጐለበተ መጥቶ ሰላምና መረጋጋት ሰፍኖ ነበር፡፡ ይህንን የወንድማማችነት ማጐልበት መልካም ጅምር ያደፈረሰው ነውጠኛውና ቂም በቀለኛው የአሁኑ የለውጥ ሓይል ተብየው ነው፡፡ በብሔሩ ማንነት ምክንያት ብቻ በጅምላ ህዝቡ እንዲገደል፣ እንዲዘረፍ እንዲፈናቀል እንዲገለል ያደረገ የጥላቻ ፖለቲካ ያራገበ ነውጥን ውድመትን እልቂትን እንደ ጀግንነትና የለውጥ ሃዋርያነት ያስፋፋ ህዝበኛ ነውጠኛ ራሱ ነው፡፡

ስለ አብላጫ ድምፅ ዴሞክራሲና ስለ መግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- “የሲቪል ባህል ባልተገነባባቸውና በተለይም በማንነት ፖለቲካ በተወጠሩ ሀገራት ላይ የአብላጫ ድምፅ ዴሞክራሲ አይሰራም የሚል ሓሳብ የሚያራምዱ ሊቃውንትና ፖለቲከኞች በድምፅ ብልጫ ሳይሆን በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ የተሻለ አማራጭ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በመግባባት ላይ የሚመሰረት ዴሞክራሲ ዘግይተው ወደ ዴሞክራሲ ለመግባትበሚሞኩሩና በተለይም በብሔርና በሃይማኖት ክፍፍል በሚታመሱ ሀገራት ዘንድ ተመራጭ እየሆነ የመጣ ይመስላል จจจበመግባባት ላይ የሚመሰረት ዴሞክራሲ ቢያንስ አራት ጉዳዬችን ሊያካትት ይችላል፡፡ ታላቅ ቅንጅት፣ የህዳጣን(የአናሳዎች) ድምፅን በድምፅ የመሻር ስልጣን፣ ተመጣጣኝ ውክልና እና የአካባቢ መርነት”(ገፅ 100-101)

የአብላጫ ድምፅ ዴሞክራሲ ብዙ ህዝብ ያላቸውን ብሔሮች ወይም ብዙ አማኝ ያላቸውን እምነቶች ይበልጥ ተጠቃሚ የማድረግ ችግር የሚያስከትል ነውና የእምነት ይሁን የብሔር ቅራኔ ውጥረቱን ለማለዘብና ለመፍታት የአናሳዎቹን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲ የተሻለ ይሆናል፡፡ የሚለው ሓሳብ ያስኬዳል፡፡ግን ይሄ አማራጭ በዴሞክራሲ ተቋማትና በሕግ-የበላይነት መስፈን ካልተደገፈ ውጤታማ አይሆንም፡፡

በመፅሓፉ ደራሲ ዕይታ በሀገራችን የተሞከረው ዴሞክራሲ በመግባባት ላይ የተመሰረተና በማህበረሰባዊ ብሔረተኝነት (በቡድን መብት) ላይ ያተኮረ ዴሞክራሲ ስለነበረ ብዙ ርቀት አልወሰደንም ይላሉ፡፡ መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- “በሀገራችን ሁለቱ ብሔርተኝነቶች በጣምራ በመኖራቸው ምክንያት በማህበረሰባዊ ብሔርተኝነት ላይ ብቻ ያተኮረ መፍተሔ ብዙ ርቀት አያስጉዘንም፡፡ በሀገራችን ባለፉት አመታት አነሰም በዛ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመዘርጋት ተሞክሮ ነበር፡፡

ለመዘርጋት የተሞከረው ስርዓት የህዳጣን(የአናሳዎችን) መብት በማስከበር በብሔር ልሂቃን ስምምነት ላይ የተመሰረተ ስርዓት ነው፡፡ ይህ ስርዓት ከነጉደለቱ የብሔሮችን መብት ለማስከበር የሞከረና በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲን ለመዘርጋት በቂ መነሻ ይዞ የተነሳ ነው፡፡ ሆኖም ይህ ሙከራችን በሀገራችን ያለውን የሲቪክ ብሔርተኝነት (የግለ ሰብ መብት) የዘነጋ ነበር፡፡” (ገፅ 105)

ዴሞክራሲያችን በማህበረሰብ ብሔረተኝነት (በቡድን መብት) ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር፡፡ የሲቪክ ብሔረተኝነትን (የግለ ሰብ መብት) የዘነጋ ነበር የሚለው ድምዳሜ ስህተት ነው፡፡ ሕገ-መንግስታችን የቡድንና የግለሰብ መብቶች በእኩልነት በተመጋጋቢነት እንደሚከበሩ ይደነግጋል ይሁን እንጂ መተግበር ላይ የተጠናከሩ የዴሞክራሲ ተቋማት ስላልተፈጠሩና ልሂቃንና ባለሀብቶች ወደ አንዱ ጫፍ እያዘነበሉ ስለተካረሩ በአጥጋቢ ደረጃ አልተተገበረም፡፡ አሁንም አዲስ ነገር ማምጣት ሳይሆን በሕገ-መንግስቱ የሰፈረውን የሚተገብሩ ጠንካራ የዴሞክራሲ ተቋማትና ባህል መፍጠር ይፈታዋል፡፡

የመፅሓፉ ደራሲ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ያስፈልገናል ይሉና ሰው ወለድ ጭቆናና መዋቅር ወለድ ጭቆናን የሚፈታ ማህበረሰባዊ እና ሲቪክ ብሔረተኝነትን (የቡድንና የግለሰብ መብትን) ያመጣጠነ ወይም ያጣመረ፣ በመግባባት ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲን በመደመር ዕሳቤ እንተግብር ይላሉ፡፡ “መደመር ማህበረሰባዊ ብሔርተኝነትን እና ሲቪክ ብሔርተኝነትን አመቻምቾ የሚጓዝ ባለው የመግባባት ዴሞክራሲ ላይ የጐደለውን የልሂቃን ትብብር ለማምጣት የሚሰራ የዴሞክራሲ አማራጭን ይከተላል” ብለውናል፡፡ (ገፅ 107)

ይሄ ከሆነ ምኑ ላይ ነው ልዩ ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ የሚያሰኘው፡፡ የአገራችን ሕገ-መንግስት ላይ የሰፈረውን በተሟላ መንገድ መተግበር፣ የአፈፃፀም ጉድለቶች የዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታና የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ መጓተት ችግሮችን በትኩረት መፍታት ለማለት ከሆነ ያሰማማናል የተለየ አዲስ ሓሳብ አልመጣም፡፡ የዜግነት ፖለቲካንና የብዝሃነት ዴሞክራሲን ማስታረቅ ከሆነ ግን እንዴት ይቻላል? ሲቪክ ብሔረተኝነት የዜግነት ፖለቲካ ለማለት ከሆነ የማሕብረሰብብሔርተኝነትን (የቡድን መብትን) አያስፈልግም ይከፋፍላል ዕንቅፋት ነው ስለሚል ሁለቱም ሊደመሩ አይችሉም፡፡ የግለሰብ መብትና የቡድን መብት ግን በሕገ-መንግስታችን እንዳሰፈረው በእኩልነትና ተመጋግበው ሊተገበሩ ስለሚችሉ ተጣጥመው ተግባራዊ መሆን ይችላሉ፡፡ ሁሉ አማረሽ የሆነ ሓሳብ ያደናብራል፡፡

ምዕራፍ - ሰባት

የሀገረ መንግስት ቅቡልነትን የማረጋገጥ ፈተና

በዚህ ምዕራፍ ያሉ ፍሬ ነገሮች አራት ናቸው፡፡ አንዱ የሀገረ መንግስት ቅቡልነት ችግር ከሁለት መሰረታዊ ጉዳዬች ማለትም ከቁስ ተሻጋሪ ዕሴቶችና ከሀገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ ጋር የተያያዘ መሆኑ፤ ሁለተኛ የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ በብሔር ጭቆና ላይ የተመሰረተ ስለነበረ የብሔር ማንነት ከሌሎች ማንነቶች ገኖ እንዲወጣ ያደረገ መሆኑ፤ ሶስተኛ በሀገረ መንግስትምስረታ ሂደት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በማህበረሰባዊ ብሔረተኝነት(የቡድን መብት የሚያጐላ) እና በሲቪክ ብሔርተኝነት መካከል በሚደረጉ የፖለቲካ ተዋስኦዎች(ክርክርእሰጥ አገባ) የተወጠረ እንዲሆን ማድረጉ፤ አራተኛ መፍትሔው ደግሞ ብሔራዊ ዕርቅና በነፃ ተቋማት መፍጠር የተደገፈ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር መሆኑ፤ የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ባጭሩ አንድ በአንድ እንያቸው፡፡

ስለ ሀገረ መንግስት ቅቡልነት መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- “የሀገረ መንግስት ቅቡልነት ችግር ከሁለት መሰረታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው ማለት እንችላለን፡፡ ከቁስ ተሻጋሪ ዕሴቶች እና ከሀገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ፡፡ จจቁስ ተሻጋሪ ዕሴቶችን በማዳበር የሀገረ መንግስት ቅቡልነትን ለማምጣት ዋናው ጉዳይ ኢኮኖሚያዊ ልማትን ማምጣት ቢሆንም ከኢኮኖሚ ስራዎች ጐን ለጐን ዕሴቶችን የሚገነባ የባህል ግንባታ ስራ በፖለቲካው መስክ መሰራት አለበት፡፡

በአጠቃላይ ቁስ ተሻጋሪ ዕሴቶችን ለማጐልበት የሚሰራው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስራ የሀገረ መንግስት ቅቡልነትን በማረጋገጥ ረገድ ዘላቂውና አስተማማኙ መንገድ ነው፡፡ จจበሌላ በኩል የሀገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ በምስቅልቅል የተሞላ ከሆነ ቅቡልነትን ማግኘት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡” (ገፅ 110) እነዚህ ሓሳቦች ያስማሙናል ትክክል ናቸው፡፡

ቀጠል አድርጐ ስለ ብሔርተኝነትና የኢትዮጵያ ሀገረ መንግስት ምስረታ ታሪክ መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- “አንዳንድ ማርክሲስቶች ብሔር በተሳሳተ መንገድ የተገለጠ የወደብ ንቃተ ህሊና ነው ይላሉ፣ ይህም ማለት በኢኮኖሚ ስርዓቱ ምክንያት የሚከሰተውን የመደብ ልዩነት ሌላ የማንነት ቀለም በመስጠት ዋናው ችግር እንዳይፈታ የሚያደርግና የመደብ ጭቆናውን የሚያድበሰብስ የሓሰት ማንነት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ ፈፅሞ አይሉም የተዛባ መረጃ ነው፡፡ በተለይ ዋነኞቹ የኮሚኒዝም መሪዎችና መምህራኑ (ማርክስ ኤንጅልስ፣ ሌኒን ስታሊን) ይህን ብለው አያውቁም የብሔር ጭቆና የመደብ ጭቆና አንዱ ገፅታና መገለጫ ነው፡፡ ምንጩም የመደብ ጭቆና ነው እሱ የወለደው ነው፡፡ የብሔር ጭቆና ፈፃሚውና ተጠቃሚው የአንዱ ብሔር ገዥ መደብ እንጂ የዛ ብሔር ህዝብ አይደለምና፡፡ ስለሆነም ለብሔር ማንነትና ለብሔር መብት ትግል እውቅናና ድጋፍ መሰጠት ተገቢ ነው፡፡ የብሔር ማንነት እውነተኛ ነባራዊ የአንዱ ህዝብ ማንነት ነውና ነው የሚሉት፡፡ የብሔር መብት የራስን ዕድል በራስ መወሰን እስከመገንጠል ነው ይላሉ ኮሚኒስቶች ሲባል ተከርሞአሁን ደግሞ የብሔር ማንነት የሓሰት ማንነት ነው ይላሉ የሚል ውንጀላ ከየት መጣ? ለምንስ መጣ?

ስለ ብሔር ማንነት ጐልቶ መውጣት ምክንያትና የልሂቃን ሚና መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡-“จจሌሎች ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው ብሔር ከሌሎች ማንነቶች ገንኖ የወጣበት አንዱ ምክንያት የብሔር ጥያቄ ነው” (ገፅ 114) አንድ የቡድን ማንነት እየጠነከረ የሚመጣውና ሰዎችን በዝያ ማንነታቸው ዙርያ የሚያንቀሳቅሰው ሰዎች ያን ማንነታቸውን መሰረት ያደረገ መድልዎ ወይም ጭቆና ሲደርስባቸው ነው፡፡ ሆኖም ይህ ጭቆና ዋነኛ የህዝብ ማንቀሳቀሻና የማንነት ፖለቲካ ማታገያ የሚሆነው ልሂቃን ጭቆናውን ለዓላማቸው በሚያውሉበት መጠን ነው” (ገፅ 115)

እዚህ ላይ መሰረታዊ ስህተት አለ፣ የብሔር ማንነት ጐልቶ የሚወጣበት ዋናው ምክንያት የብሔር ጭቆና ከሆነ የህዝቡ ማታገያ እንዲሆንም ያደርገዋል፡፡ ማታገያ የሚሆነው ልሂቃን ለአላማቸው ሲጠቀሙበት ነው የሚለው ስህተት ነው፡፡ ፅንፈኛ አቅጣጫ እንዲይዝ ካደረጉት ልሂቃኑ ለራሳቸው ጥቅም አዋሉት ሊባል ይችላል፡፡ ፅንፈኛነት ህዝቡን አይጠቅምም፤ ህዝብ ከህዝብ ጋር ያፋጃልና፡፡ ማታገያ የፖለቲካ ጥያቄ መሆኑ ግን በልሂቃን ፍላጐትና ጥቅም የሚወሰን ሳይሆን ልሂቃን ባይታገሉለትም የተጨቆነው ብሔር  ህዝብ በራሱ መንገድ በግብታዊ አግባብም ይታገላል፡፡ ማታገያ ፖለቲካ የሚያደርጉት ልሂቃኑ ናቸውና የህዝቡ ጥያቄ አይደለም ብሎ ይህን ሰበብ በማድረግ የብሔር ትግልንና የብሔር ድርጅትን ለመጨፍለቅ ተፈልጐ ከሆነ ሌላ ጉዳይ ነው፡፡

ስለሀገረ መንግስት ምስረታ በኢትዮጵያ ሲያትት መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- የብሔር ጭቆና መኖርና የ1960ዎቹ ሶሻሊዘምና ብሔር ተኮር ፍልስፍናዎች ለማንነት ፖለቲካ አጀንዳ መቀረፅ ምክንያት እንደሆኑ ይገልፅና “ይህ ሁኔታም የኢትዮጵያ ፖለቲካ በማህበረሰባዊ ብሔርተኝነት እና በሲቪክ ብሔርተኝነት (የቡድን መብት በሚያስቀድሙ እና የግለሰብ መብት በሚያስቀድሙ) መካከል በሚደረጉ ተዋስኦዎች(ክርክሮች፣ እሰጥአገባዎች) የተወጠረ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ የኢትዮጵያሀገረ ብሔር በአንድ በኩል በከፊል ስለተገነባ ሲቪክ ብሔረተኞችን ወልዷል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሂደቱ በአጭር ስለተቀጨ በየአካባቢው ማህበረሰባዊ ብሔርተኝነትን ፈጥሯል፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመለወጥና የሀገረ ብሔሩን ቅቡልነት ለማረጋገጥ በሁለቱ ብሔርተኞች መካከል ግማሽ መንገድ ተጉዞ መቀራረብ ያስፈልጋል፡፡” (ገፅ 116)

አሁን በስራ ላይ ያለው ሕገ-መንግስት የቡድን መብትና የግለሰብ መብት በእኩልነት ይከበሩ፣ ተመጋጋቢ ሆነው ይጐልብቱ ብሎ በደነገገው መሰረት ተግባራዊ እናድርግ አንዱ መብት ብቻ (የግለሰብ መብት ብቻ) ይበቃል የቡድን መብት በዛ ይካተታል ይፈታል ብለን አንደፍቀው በሚሉና የግለሰብ መብት ብቻ ይበቃል፣ የቡድን መብት በታኝ ነው ምንም አያስፈልግም ወይም በቋንቋ ማካለልና መገንጠልን የማያካትት ይሁን በሚሉት መካከል ያለ ልዩነት እንዴት ብሎ ነው ግማሽ መንገድ በመጓዝ በዕርቅ የሚፈታው? የመሰረታዊ ፖለቲካዊ እምነት ልዩነት ስለሆነ በዕርቅ ሳይሆን በሰላማዊ ፖለቲካዊ ውድድር ይፈታል፡፡

ስለብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም መፅሓፉ እንደሚከተለው ይላል፡- “จจበብዙ ጉዳዬች ላይ ተወያይተን ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ አለብን፡፡ ሆኖም ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ አስቀድመን ያለፉ ቁስሎቻችንን ማከምና ማዳን ያስፈልገናል፣ ዕርቀ ሰላም ማውረድ ያሻናል፡፡ ዕርቀ ሰላም ሳናወርድ ብሔራዊ መግባባት ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ነው፡፡” (ገፅ 119) ይልና በመቀጠልም፡- “ሂደቱ ተጠያቂነትንና ይቅርታን፣ ፍትሕና ዕርቅን፣ እንዲሁም ቅጣትንና ምሕረትን አቻችሎ ተጐጂዎችንም ሆነ አጥፊዎችን ካለፈው ተምረው የወደፊት ሕይወታቸውን ቀና እንዲያደርጉ የማድረግ ጥረት ነው፡፡ የፍርድ ሂደትንና ከፍርድ ሂደት ውጭ ያሉ ስልቶችን በሙሉ በመጠቀም የሚከናወን ሲሆን በመጨረሻም ጥፋታቸውን የተናዘዙ አካላት በይቅርታና በምሕረት እንዲለቀቁናይህን ያላደረጉ አካላት ደግሞ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የሚያደርግ ነው” ይላል፡፡ (ገፅ 120)

ይህ ዓይነት ዕርቀ ሰላም መንግስት ሲቀየር የሚካሄድ የሽግግር ፍትሕ ይለዋል፡፡ በምሳሌነት የደቡብ አፍሪካና የሩዋንዳን ልምድ ይጠቅሳል፡፡

ዕርቀ ሰላም ላይም ቅድመ ሁኔታ ይሆናል? በሕገ-መንግስትና በሕብረ-ብሄር ፌደራላዊ ስርዓት ላይ መግባባት ከተፈጠረ፣ ተአማኒነት ያለው ምርጫ ተካሂዶ ቅቡልነት ያለው መንግስት በተመሰረተ በህዋላና የፍትሕ ስርዓቱ ገለልተኛና ብቃት ያለው ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ሁሉንም በእኩል አይን የሚያይ ዕርቅና ፍትሕ ሊኖር የሚችለው፡፡ አሁን ባለው ተጨባጭ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ሁኔታ ከባድ ወንጀል የፈፀሙ በበቂ ማስረጃ የተረጋገጠባቸውን ብቻ በነፃ ፍ/ቤት ሂደት ይሁን በግለ ሂስ ሁሉንም በእኩል ዓይን የሚዳኝ ስርዓት አለ ወይ? የሁሉም ጥፋት ተጠያቂ አንድ ፖለቲካዊ ድርጅትና(ህ.ወ.ሓ.ት) የአንድ ብሔር(የትግራይ) ተወላጆች ናቸው እየተባለ እያለ ፍትሕና ዕርቅ ይኖራል ወይ?ወይንስ ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ህወሓት ወንጀለኛ ድርጅት ነው ተብሎ አመራሩ፣ አባላቱና ደጋፊዎቹን በሰዶ ማሳደድ ለማጥፋት ድርጅቱን ለመበተንና የትግራይን ህዝብ ለማንበርከክ ተፈልጐ ነው?

ምዕራፍ - ስምንት

የነፃ፣ ገለልተኛና ብቁ ተቋማት ግንባታ

በዚህ ምዕራፍ የተካተቱ ሓሳቦች የተቋማት ግንባታ ለሀገረ መንግስት ግንባታ ለልማትና ዴሞክራሲ ያላቸው ቁልፍ ሚና እውን ለማድረግ ዕውቀትና ችሎታ መመዘኛው ባደረገ አቅጣጫ እንዲገነቡ ማድረግ ወሳኝ መሆኑ፤ የተቋማት ግንባታ ከብሔራዊ መግባባት ጋር ጐን ለጐን ተቀናጅቶና ተመጋግቦ መሄድ እንዳለበት የሀገራችን የተቋማት ግንባታ ከዚህ አንፃር ምን ጉድለት እንደነበረውና ምን የመፍትሔ አቅጣጫ መከተል እንዳለብን የሚመለከቱ ናቸው፡፡

የተቋማት ግንባታ በተመለከተ በበለፀጉት አገሮችና በማደግ ላይ ባሉ አገሮች መካከል ስላለው ልዩነት መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “ከተቋማት ግንባታ ጋር ተያይዞ በበለፀጉትና ባልበለፀጉት ሀገሮች መካከል የሚታዩ ልዩነቶች በዋናነት የሚንፀባረቁት በሀገረ መንግስት ጥንካሬ፣ በሕግ የበላይነት መረጋጋት እና በተጠያቂነት መስፈን ጉዳዬች ዙርያ ነው፡፡ የበለፀጉት ሀገሮች ከሞላ ጐደል በሶስቱም ጉዳዬች ጠንካራ የማስተዳደርና የማስፈፀም ብቃት ያላቸው ተቋማትን የገነቡ ሲሆን፣በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ግን በእነዚህ መመዘኛዎች ሲመዘኑ በብዙ መልኩ ወደ ህዋላ የቀሩ ናቸው፡፡”(ገፅ 127)

እዚህ ላይ ግድፈቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ሶስቱ የማይተናነሱ ሌሎች መሰረታዊ ልዩነቶች አሉ፡፡ ለምሳሌ ብቁ ዜጋ የሚፈጥሩበት ስርዓተ ትምህርትና ብሔራዊ መግባባትየፈጠሩ መሆናቸው፤ሁሉም በስራ ውጤቱ ልክ የሚመዘንበትና የሚጠቀምበት ለውጤት የሚተጋበት ስርዓት፣ የሲቪል ሰርቫንት መዋቅር ገለልተኝነት ፖለሲ አስፈፃሚነት ከፖለቲካ አቋምና የፓርቲ ውግንና ለይቶ ማስኬድ የልዩነት ነጥቦች ናቸው፡፡

በጃፓን ተምሳሌትነት የምስራቅ ኤስያ ልማታዊ መንግስታትእውቀትና ችሎታ ላይ የተመሰረቱ ጠንካራ ተቋማት መገንባት መቻላቸው መፅሓፉ ላይ ተጠቅሶአል፡፡ የተቋማት ስኬታማ ግንባታቸው ምስጢር እሱ ብቻ አይደለም፡፡ አዲስ ትውልድን ብቁ ዜጋ አድርገው የሚገነቡበት ስርዓት፣ ሁሉንም በስራ ውጤት የሚመከትበትና በዛ ብቻ ተጠቃሚ የሚያደርጉበት የማበረታቻና የተጠያቄነት ስርዓትም ስላላቸው ነው፡፡

እኛ ታድያ እሱን ማድረግ ለምን አቃተን ለሚል ጥያቄ መፅሓፉ የሰጠው ምላሽ “በአንፃሩ በሀገራችን ምንም እንኳ ባለፉት 27 ዓመታት የልማታዊ መንግስት ፈለግን እንከተላለን ብንልም የልማታዊ መንግስት ዋነኛ መለያና የጥንካሬ ምንጭ የሆነውን ብቁ ተቋማትን የመገንባት ውስንነታችን ከፍተኛ ነው፡፡ ሀገረ መንግስቱ የተዋቀረባቸው ተቋማት በፓርቲና መንግስት መደባለቅ፣ መንግስታት ሲቀያየሩ አፍርሶ በመገንባት አባዜ እንዲሁም ከማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ጋር አብረው ተቋማት ባለመታደሳቸው የተነሳ ሀገረ መንግስቱ በደቀቁ ሙያዊ ብቃታቸው ዝቅተኛ በሆኑ እንዲሁም ነፃና ገለልተኛ ባልሆኑ ተቋማት የተደራጀ ነው” የሚል ነው (ገፅ 128)

ይህ ግምገማ ከሞላ ጐደል ትክክል ነው ብለን እንኳ ብንወስድ አሁንስ በለውጥ ስም አንድ ብሔርና የዛ ብሔር ፖለቲካዊ ድርጅት አባላትን ለይቶ በጅምላከፌደራል መንግስት ጠራርጐ የማውጣት፣ የቀሩትን ጥቂቶች ደግሞ በጥርጣሬ በአይነ ቁራኛ መከታተል፣ በሌላ ገፅታው ደግሞ የሌላውን አንድ ብሔርና ድርጅት አባላትን ከብቃት መመዘኛ ውጭ በሆነ መንገድ ጭምር በግፍ መሰግሰግ እየተካሄደ አይደል?

በመቀጠልም መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- “በአጠቃላይ ተቋማት በሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች የተነሳ የመልካም አስተዳደር እጦት የሰፈነበት ስርዓት እንዲኖር አድርገዋል፡፡ የመጀመርያው የቤተዘመድ መረብ (ፓትሪም ኒያሊዝም) ሲሆን ሁለተኛውም ደግሞ “ተቋማዊ ቸኮነት” ነው” ይላል (ገፅ 129)

ተቋማት የቤተዘመድ ስብስብ ናቸው የሚለው በደም ዝምድና ብቻ ሳይሆን በብሔርና በጥቅም የተሰባሰቡ ሰዎች የበዙበት ለማለት ይሆናል፡፡ ብለን ብንረዳው ትክክል ይመስለኛል፤ የሰጋ ዘመድ ከሆነ ጥቂት ነውና፡፡ በሰፊ ትርጉሙ ሲወሰድ ደግሞ ሁሉም መስርያ ቤት ወይም ባብዛኞቹ የአንድ ብሔር ስብስብ ነበሩ ለማለት ከሆነ ሓሰት ነው፡፡ ሲጀመር በደርግ ውድቀትማግሰት በማእከላዊ መንግስትና በአዲስ አበባ አስተዳደር የነበሩ የሲቪል ሰርቫንትና የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሓላፊዎችና ሰራተኞች እስከ 65-70% የአማራ ተወላጆች ነበሩ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ከ50% በላይ እነሱ ናቸው፡፡ ያም ሆኖ በሁሉም መስርያቤቶች የዛን ያህል መጠን ነበራቸው ማለት አይደለም፣ በርከት ባሉ የኢኮኖሚ መስርያቤቶችና የልማት ድርጅቶች እንዲሁም በውጭ ጉዳይ እንደዛ ነበር፡፡ የደርግ የአፈና መዋቅር ይፍረስ ተብሎ ደግሞ በመከላከያ፣ በደህንነትና በፖሊስ የትግራይ ተወላጆች አብዛኛውን ቁጥር ይዘው ነበር፡፡

እንደዚህም ሆኖ ዋናው የሹመትና የቅጥር መመዘኛ በሕግና በመመርያው ይሁን በትግበራው ደረጃ ዘመድ አዝማድና የብሔሩ ልጅ ማሰባሰብ ሳይሆን ባለፈው አመጣጡ ምክንያት የትምህርት ዕድሉ ይሁን ልምዱ ይበልጥ ያገኘውና በየስርዓቱ የተሻለ ብቃት ብቻ ሳይሆን ታማኝነትም አለው ተብሎ የገባ መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪ በተለይም ታማኝነት እንደዋነኛ መመዘኛ ተወስዶ የገባ የአማራም የትግራይም ሰው ቁጥሩ አነሰተኛ የሚባል አይደለም፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ የማመጣጠን ስራ ይፋጠን አለ፣ መመጣጠን አለ ተብሎ ጠንካራና የማያቋርጥ ወቀሳ ይሰነዘር የነበረው በፀጥታ ተቋማት ላይ ብቻ ነው፡፡ በሌሎቹ ተቋማት ይህ ወቀሳ አይነሳም ነበር፡፡

ለምን ቢባል ጤናማ ያልሆነ ፖለቲካዊ ምክንያት ነበረው፡፡ ስርዓቱንና ገዥ ፓርቲውን የሚቃወሙ ሓይሎች እንዲሁም የገዥው ፓርቲ አመራርና አባል ሆነው በርካታዎቹ የራሳቸውን ስልጣንና ልዩ ጥቅም ማጠናከር የሚፈልጉ የህወሓት ሚናን ለማዳከምና የፀጥታ ተቋማቱን ለመቆጣጠር ይፈልጉ ስለነበር ነው፡፡ ፍትሓዊ ተዋፅኦ ተደርጐ ተገቢ ማመጣጠን የማድረግ አላማ ቢኖራቸው ኑሮ በሁሉም ተቋማት ማመጣጠን ይደረግ፤ ብቃት ማእከል ያደረጉ ይሁኑ ይሉ ነበር፡፡ ታድያ ይህን እያወቁ የመፅሓፉ ደራሲ ይህን ሃቅ ሸፍነው ማለፍ ለምን ፈለጉ?

መፍትሔውን በተመለከተ መፅሓፉ ላይ ዕውቀትና ችሎታ መሰረት ያደረገ ገለልተኛና ውጤታማ ተቋማት እንገንባ ለዚህም ሲባል የሪፎርም አካሄዳችንን እንቀይር ይላል፡፡

“በመሆኑም ሀገራዊ ቅርፅ ከያዘ የሪፎርም አዲስ ፓኬጅ ይልቅ ያልተማከለና ለዘርፍ ልዩ ባህርይ ትኩረት የሚሰጥ፣ በዕውቀት የሚመራና የሴክተሩን ፍላጐት መሰረት ያደረገ ሪፎርም የበለጠ ውጤታማ ይሆናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ዘርፍና ተልእኮ ተኮር የተቋማት ግንባታ ሪፎርም ታክቲክ ስኬታማነት በዋነኛነት የሚወሰነው በየተቋማቱ የበቁ የለውጥ ሃዋሪያት ካሉ ነው፤ ይህን ለመፍጠር ደግሞ የአመራር ብቃት እጅግ መሰረታዊ ጉዳይ ነው፡፡” ይላል (ገፅ 133)

አቅጣጫው ሊያስኬድ ይችል ይሆናል፣ የለውጥ ሃዋሪያ መኖር ነው ዋናው ወሳኝ ነገር የሚለው ሓሳብ ግን በተግባር እንደምናየው ያለን የተደመረና ያጨበጨበ ወይም በሚፈለገው ብሔርና ፓርቲ አባል የሆነ ማለት ሆኖአል፡፡ ይህ ደግሞ በምንም ተአምር ብቃትና ውጤት ብቸኛ ወይም ወሳኝ መመዘኛው ያደረገ ተቋም የሚፈጥር አይደለም፡፡

ሲጠቃለል በዚህ ምዕራፍ የተቀመጡ የጉድለታችን ግምገማዎች እየተደገሙ ባለበት፣ የታረመ ጉድለት ብዙ በሌለበት እንዳውም ስህተት የተባለው ይበልጥ በተባባሰበት አካሄድ መፍትሔዎች ይተገበራሉ ማለት ዘበት ይሆናል፡፡

ምዕራፍ - ዘጠኝ

የፖለቲካ አመራር ከገዥነት ወደ መሪነት

በዚህ ምዕራፍ የተካተቱ ፍሬ ሓሳቦች የመሪዎች ሚና ለለውጥ ወይም ለውድቀት ቁልፍ መሆኑ የገዥዎችና የመሪዎች ልዩነት ምን እንደሆነ፣ ሀገራችንን ለማሳደግ ገዥዎች ሳይሆን ራእይ ያላቸውና ራእያቸውን ወደ ተመሪዎች በሓይል ሳይሆን በማሳመን የሚያጋቡ አቅሞችን የሚያሰባስቡ መሪዎች መፍጠር አለብን የሚሉ ናቸው፡፡

የግለሰብ መሪዎች ሚና በተመሰለከተ መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “จจከታሪክና ከነባራዊ ህይወታችን እንደምንረዳው ግን ግለሰቦች ራሳቸው የስርዓት ውጤት ቢሆኑም ስርዓትን የማስተካከል፣ ለውጥ የማምጣት አቅም አላቸው” (ገፅ135) ትክክል ነው፡፡ ግን ህዝበኛ መሪ ሲሆን ደግሞ የመላውን ህዝብ ፍላጐትና ችግር እኔ አውቃለሁ እኔ እወክላቸዋለሁ ነብይ ነኝ ለመምራት የተፈጠርኩ ነኝ ብሎ እኔን ያልተከተለሁሉ ውጉዝ ከመአርዬስ ይሁን የሚል ከሆነ አገር አጥፊ እንጂ አገር አልሚ አይሆንም፡፡

ስለገዥነትና መሪነት መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “መሪነትን ከገዥነት የሚለየው ጉዳይም ገዥነት ተከታዬቹን በጉልበት የማፍራትና የራስን ሕልም በሌሎች ላይ በሓይል የመጫን መንገድ ሲሆን፣ መሪነት ግን ከጉልበት ይልቅ በጐ ተፅእኖ ማሳደርንና ማሳመንን የሚጠይቅ መንገድ ነው” (ገፅ 136) በጐ ተፅእኖ የሚባለው ከድለላ ከውሸትና ከአጉል ተስፋ የፀዳ የተለየ ሓሳብንም ሳያፍን በልዩነት ለመጓዝና በሓሳብ ልዕልና ብቻ ህዝቡን ለማሳመን የሚሰራ ማለት ቢሆን ሓሳብ በመሰረቱ ትክክል ይሆናል፡፡ ለማለት የተፈለገው ግን ተደመሩ፣ አጨብጭቡ፣ ያልተደመረ ፀረ-ለውጥ ነው የሚል በጐ ተፅእኖ ነው፡፡ ከለውጥ ሃዋርያ ተብየዎች የተለየ ሓሳብ የያዘ ለሕገ-መንግስቱና ለሕብረ ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓቱ ዘብ የቆመ፣ የህዝብ ጥያቄዎችን ያስተጋባና የደገፈ ‘በበጐ ተፅእኖ’ ማስታገስ አልያም ከስልጣን ማግለል ወይም በሓሰት መወንጀል የማጥላላት ዘመቻ ማካሄድ ነው እያየን ያለነው፡፡

በሀገራችን የታየ የአመራር ጉድለት በተመለከተ መፅሓፍ እንዲህ ይላል፡- “ድክመቶቻችን በሁለት ከፍለን ልናያቸው እንችላለን፡፡ አንደኛው የህዝብን ስሜቶች የመረዳት ችግር ነው፡፡ จจህዝብና ተከታይ ሲከፋ ለምን እንደተከፋ መመርመር፣ የስሜቱን መጠንና አቅጣጫ ማጤን፣ እንዲሁም ስሜቱ ሊያስከትለው የሚችለውን አደጋ መገንዘብ አስፈላጊ ነው፡፡

ሁለተኛው ችግር ስሜትን ለመቆጣጠር ያለመቻል ነው፡፡ በሀገራችን ህልምን በጥበብ መጋራት የሚከብዳቸው መሪዎች ህዝቡን በጉልበት ለመግዛት ሲሞክሩና አልሳካ ሲላቸውም ከፍተኛ ንዴትና ግልፍተኝነት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ተመሪው ህልማቸውን ባለመጋራቱና እነርሱም በጉልበት ለሚገዙት አንድ ቀን ከስልጣኔ ያወርደኛል ብለው ይፈራሉ፡፡ በዚህም ፍርሃት ተውጠው ህዝቡን በጭካኔ ይቀጠቅጣሉ፡፡”(ገፅ 139-140)

ሁለቱ መሰረታዊ ጉድለቶች በትክክል ተተንትነዋል፡፡ አሳሳቢ የሚሆነው ጉዳይ አሁንስ አልደመርም ያለ፣ ብልፅግና ፓርቲን አልደግፍም ያለ በነፃነት ሕጋዊ ሰላማዊ ፖለቲካዊ ትግሉን ማካሄድና አማራጭ ሓሳቡን በነፃነት በድፍረት ማራመድን የሚያከብር ሰፊ ፖለቲካዊ ምህዳር አለ ወይ የሚል ነው? የለም፡፡

“በአጠቃላይ በዚህ ወቅት ሀገራችን የምትፈልገው አመራር ከማፍረስና ከተናጠል ጉዞ ይልቅ ባለው ላይ የሚያከማችና የተበታተነውን የዜጐች አቅም የሚሰበስብ ከስሜታውነት የፀዳ እንዲሁም በጋራ ግብ ዙርያ ተመሪዎችን ማስፈንጠር የሚችል ነው”ይላል፡፡ (ገፅ 143) በተግባር ግን የዚህ ተፃራሪ የሆነ አመራር ነው እያየን ያለነው፡፡

ምዕራፍ - አስር

የፖለቲካ ባህል ግንባታ፤ ዘላቂውና አስተማማኙ መንገድ

በዚህ ምዕራፍ ያሉ ፍሬ ሓሳቦች የተሟላና ዘላቂ ዴሞክራሲ ለማስፈን የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት ብቻውን አይበቃም፣ የዴሞክራሲ ባህል መገንባት የግድ ይላል፤ በሀገራቸን ለእርሰ በርስ ግጭት በቀጣይነት የዳረገን ጠበኝነትና በስሜት የመነዳት እሺ ባይነት ነው፡፡ ከነዚህ ችግሮች ለመወጣት መደማመጥ፣ መከባበርና የግጭት መፍቻ ባህላዊና ሕጋዊ መንገዶችን ማጐልበት የባህል እንዳስትሪው እሴቶችን በመገንባት በኩል ሚናውን እንዲጫወት ማስቻል የሚሉናቸው፡፡

መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡- “ጭቆናን አሸቀንጥሮ ጥሎ በህዝቦች ፈቃድ ላይ የተመሰረተና ተጠያቂነት ያለበት ስርዓት ለማስፈን ዘላቂውና አስተማማኙ መንገድ የዲሞክራሲ ባህል ግንባታ ነው የተቋማት ግንባታ በራሱ ስጋ ብቻ እንጂ ነፍስ የለውም፡፡ ተቋማቱ ህይወት ኖራቸው መንቀሳቀስ የሚችሉት ተቋማቱን መሸከም የሚችል ባህል ሲገነባ ብቻ ነው” (ገፅ 144) ይህ መነሻ ሓሳብ ትክክል ነው፡፡ ግን ቃሉን በተግባር የሚያውል መሪ የለም፡፡

የሀገራችን ችግር ከዚህ አንፃር ምንድነው ለሚለው ጥያቄ መፅሓፉ ላይ የሚከተለው ምላሽ አለ ซจจለሀገሪቱ ብሔራዊ ድህንነት ከፍተኛ የውስጥ ስጋት የሆነውና ለእርሰ በርስግጭት የዳረገን የመቻቻል ባህል አለመኖር ሲሆን ይህም ከእሺ ባይነት እሴት መግነን የመነጨ ነው” ይላል፡፡ (ገፅ 130) ለምን ብሎ ሳይጠይቅ ለጥፋት የሚነዱትን በስሜት ይከተላል ይላል፡፡ ታድያ ዋናው ጥፋተኛ የጥፋት ሓይሉ እንጂ ተከታዩ አይደለም፤ ተከታዩ ደግሞ በጭፍን እንዳይከተል የሚያደርግ የአዲስ ትውልድ ግንባታችን ደካማ ሆኗል፡፡ የእርሰ በርስ ግጭት ዋናው ምንጭ ግን የህዝቡ ጥያቄዎች ባግባቡና በወቅቱ አለመመለስ፣ በገዥዎችና በስልጣን ፈላጊ ጥቂት ሙሁራን አለአግባብ በበለፀጉ ባለሀብቶች የሚነሱ የጥላቻና የጥፋት መርዞች፣ ሴራዎች ናቸው፡፡ ከምንጩ ማድረቅ ነው የሚፈታው፡፡ በስሜት በጥላቻ መነዳት ምክንያታዊ አለመሆን ደግሞ አጥፊ መሆኑ ማስተማርና ተጠያቂነት ማስፈንተደራቢና ጠቃሚ መፍትሔ ይሆናል፡፡

መፅሓፉ ላይ “የውይይትና የክርክር ባህል በጭፍለቃና በመጠፋፋት ላይ እንዲመሰረት ያደረገውና ፖለቲካችንን ያበላሸው አንዱ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ጠበኛ መሆናችን ነው” ይላል፡፡ (ገፅ 153) መላውን የኢትዮጵያ ህዝቦች ጠበኛ ብሎ መፈረጅ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ህዝብ ለህዝብ ጠብ የላቸውም የሚያጣሉዋቸው ገዥዎችና ጥቅም ፈላጊ እናቅልሃለን ባይ ጥቂት ፖለቲከኞች ናቸው፡፡ እነሱን ለይቶ መውቀስ ነበር ተገቢ የሚሆነው፡፡

የዴሞክራሲ ባህል መገንባት ወሳኝ ጉዳይ መሆኑ ጐልቶ ተቀምጦ ሲያበቃ በሀገራችን ይህን የዴሞክራሲ ባህል እንዴት እንገነባው ለሚል ወሳኝ ጥያቄ ግን መፅሓፉ ላይ አጥጋቢ ምላሽ የለም፡፡ ባህላዊ ሽምግልናና ሕጋዊ ማዕቀፍ ማጠናከር፣ የባህል እንዳስትሪ(ከነ-ጥበብ ለማለት ይመሰላል) ሚናቸውን እንዲጫወቱ ማድረግ በሚል ብቻ ይመልሰዋል፡፡ ቁንፅል መፍትሔ ብቻ ነው የቀረበው፡፡ አፍሪካ ውስጥ እኮ ነው ያለነው፤ ምርጫን አጭበርብሮ ማሸነፍ ይቻላል፡፡ ምርጫ ቦርድ እና ፍ/ቤት በኔ ስር ነው ብሎ በይፋ የሚናገር መሪ እንዴት ብሎ መፍትሔ ያመጣል?

 

ማጠቃለያ አስተያየት

ስለ የሀገራችን የፖለቲካ ስብራትና የጥገና አማራጭ

በዚህ በክፍል ሁለት ውሰጥ በርካታ የተዛቡ ሓሳቦችና በማርና ቅቤ ቃላት የተዋቡ የማይተገበሩና ፀሓፊው ከልብ የማያምኑባቸው የድለላና የአጉል ተስፋ ሓሳቦች ሰፍረዋል፡፡ እዚህ የሰፈሩትና በተግባር እየተደረገ ያለው ፍፁም የማይገናኙ ተፃራሪ ናቸው፤ እስኪ ዋነኞቹን በዚህ ማጠቃለያ እንያቸው፡፡

ስለ ሀገረ መንግስት ምስረታ ሲተነትን የሀገራችን ነገስታት በግዝያቸው ብዙ የውጭና የውስጥ ፈተናዎች ስለገጠምዋቸው ጊዝያቸውን ሀገር በማረጋጋት አሳልፈውት ሀገረ መንግስት ለመገንባት ጊዜ አላገኙም፣ የህዝቡንም ችግሮች መፍታት ስላልቻሉ ህዝቡ ሲያምፅ ወደ ጭቆና ተግባር ገቡ ይላል፡፡ ይህ ሓሳብ ውስጡ ፈታ ሲደረግ በማረጋጋት ስራ ባይጠመዱ ኑሮ ነገስታቱ ሀገረ መንግስትን መገንባት ይችሉ ነበር ማለት ነው፡፡ የህዝቡ አመፅ ስጋት ባይፈጥርባቸው ጨቋኝ አይሆኑም ነበር ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ የነገስታት ጠበቃ የለውጥ መሪ ሲሆን ሰምተንም አናውቅ!! ነገስታት ሰላም ባለበትስ ሀገረ መንግስትን ገንብተው ያውቃሉ? ሀገረ መንግስት ግንባታ በከበርቴው በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚገነባ እንጂ በሆኑ ነገስታት የሚገነባ አይደለም፡፡ ጨቋኝ የሚሆኑትም ባህርያቸው ሆኖ ጥቅማቸው በጭቆናና ብዝበዛ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ እንጂ ህዝቡ ስለመጣ አይደለም፡፡ የህዝቡ አመፅ የተወለደው ጭቆና ስለነበረ ነው፡፡

ከሀገረ መንግስት ምስረታ ጋር አያይዞም መፅሓፉ ውሰጥ ሁለት ዓይነት ጭቆናዎች አሉ፤ ሰው ወለድ ጭቆናና መዋቅር ወለድ ጭቆና ይላል፡፡ ሰው ወለድ ጭቆና ከሰዎች ክፉ ሓሳብና ህሊና ይመነጫል መፍትሔውም ቀና ማሰብ መልካም ህሊና እንዲኖረን ማድረግ ነው ይላል፡፡ መዋቅር ወለድ ጭቆና ደግሞ ምንጩ ስርዓቱ ነው የተዘረጋው መዋቅር ነው፡፡ ሰዎችን ለይቶ ያጠቃል፣ ጥቅማቸውን ያጐድላል ይልና መፍትሔው መዋቅራዊ ጭቆና ብዙ ገፅታዎች ስላሉት እያንዳንዱን እያጠኑ በተናጠል ማረም ነው ይላል፡፡ እዚህ ላይ ይህ አስተሳሰብ መሰረታዊ ዝንፈት አለው፡፡ ሁለቱንም ጭቆናዎች የፈጠራቸው ስርዓቱ ነው፤ ገዥዎች ናቸውምንጩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ሆኖ እያለ ፀሓፊው ይህን የስርዓት፣ የመደብ ጭቆና ትንታኔ ስለማይቀበሉጭቆናው አንዱ የግለሰቦች ክፋት የፈጠረው፣ ሌላው ግኡዝ የሆነው መዋቅር የፈጠረው ነው ብለው ሸፋፍነው ምንጩና መፍትሔውን ደብዛው አጠፉት፡፡

ሆን ተብሎ ጉራ የለሽ ዕይታ እንከተል በሚል ሃቅን የሚሸፋፈን አስተሳሰብ የተቃኘ የችግር ማድበስበስና የገዥዎች ስርዓት ገመናን የማስተባበል ስልት ነው፡፡ ለገዥዎች ጥብቅና መቆም ነው፡፡

ከዚህ በባሰ ደግሞ የቡድን ማንነትን ይዞ ከጭቆና ለመውጣት መታገል የቡድን አክራሪነትን በመፍጠር ከሚፈታው ይልቅ የሚፈጥረው ችግር እየባሰ መጥቶአል፡፡ የቡድን መብትን ለማስከበር የሚደረገው ትግል ጫፍ እየረገጠ፣ የሀገርን ሰላም የሚያናጋና ዜጐች ተቻችለው እንዳይኖሩ የሚያደርግ ነው ይላል መፅሓፉ፡፡ በዚህ መሰረት ነው እንግዲህ የብሔር ድርጅቶችንና በማንነት ላይ የተመሰረተ ሕብረ-ብሄርፌደራሊዝምን የሚያፈርስ ሴራ በለውጥ ሓይል ነኝባዩ ተግባራዊ እየሆነ ያለው፡፡

ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲን የመፍጠር ትልም በሚል ርእሰ ስር የአብላጫ ድምፅ ዴሞክራሲ፣ የመግባባት ዴሞክራሲ፣ ማሕበረሰባዊ ብሔረተኝነት (የቡድን መብት የሚያጐላ) ሲቪክ ብሔረተኝነት (የግለሰብ መብት የሚያጐላ) እያነፃፀረ ሊቃውንት የፃፉትን ትንታኔ ካቀረበ በህዋላ የኛው ዴሞክራሲ ልዩነተን ከሚያጐላ ማሕበረሰባዊ ብሔረተኝነት ይልቅ ለሲቪክ ብሔረተኝነትንም እኩል ትኩረት የሚሰጥ ሕብረ-ብሄራዊ አደረጃጀትን የሚከተል ዕርቅ የሚፈጥር ቢሆን ተገቢና ውጤታማ ይሆናል ይላል፡፡ የቡድን መብትና የግለሰብ መብት በእኩል ደረጃ መከበር እንዳለባቸውና ተመጋጋቢ እንዲሆኑ በሕገ-መንግስታችን የሰፈረ ነው፡፡ ትግበራው ላይ ችግር ነበረ እሱን አስተካክሎ በእኩል ደረጃ መተግበር አለብን ተብሎ በኢህአዴግ ተሃድሶ ተወስኗል፡፡ እዚህ ላይ ምንም አዲስ መፍትሔ አልመጣም ከብሔራዊ አደረጃጀት ይልቅ ብዙ ማንነትን የሚያጐላ ፉክክርን የሚያበረታታ ሕብረ-ብሄራዊ አደረጃጀት ይመረጣል የሚል ሓሳብ ግን ብሔራዊ ድርጅቶችንና በማንነት ላይ የተመሰረተ አከላለልን ለማፍረስ መንደርደርያ የሚሆን የአሃዱአዊነት አመለካከት ነው፡፡

ከምዕራፍ ሰባት እስከ ምዕራፍ አሰር ያሉ ሓሳቦች ስለሀገረ መንግስት ቅቡልነት፣ ስለዕርቀ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት፣ ስለ ከገዥነት ወደ አመራርነት የመለወጥ ሂደትና አስፈላጊነት በማር የተለወሱ ግን መንግስት አሁን በተግባር እየሄደበት ካለ ጋር የሚጣረሱ አስመሳይ የድለላ ሓሳቦች ሰፍረዋል፡፡ አንድ ብሔርና አንድን ፖለቲካዊ ድርጅት(ህወሓት) የሁሉም ጥፋት ምንጭና ተጠያቂ የሚያደርግ የጥላቻ የቂም በቀል ፕሮፖጋንዳና የጥቃት እርምጃዎች እያካሄደ ተቋማትን እያፈረሰ ታማኝ ሰዎች ብቻ እየሰገሰገ ያለ መንግስት ይተገብራቸዋል ማለት ዘበት ነው፡፡

በቂም በቀል በጥላቻ ፖለቲካ ብሔርን ከብሔር፣ የአንድ እምነት ተከታዬችን ከሌላው ጋር ስያጋጩ የነበሩት የትግራይ ህዝብንና ህወሓተን በጠላትነት ፈርጀው ነጥለው ሲያጠቁ ሲወነጅሉ የነበሩ ሓይሎች የለውጥ አጋር ተብለው ተግባራቸውን ከለውጥ ሓይል ተብየው ጋር ተሰልፈው እንዲቀጥሉበት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም እንዴት ነው ሊፈጠር የሚችለው? ሳይታረሙ፡፡

የዕርቀ ሰላም ኮምሽን ተቋቁሞ ያጠፋ ሁሉ ጥፋቱን እንዲያምን ይደረጋል፣ ጥፋቱን ያላመነ በሕግ ይጠየቃል ለፍርድ ይቀርባል ይላል መፅሓፉ፡፡ የፈረደበት አንዱ ብሔርና ድርጅቱ ወንጀለኛ ተብለው ሊፈረጁና ሊጨፈጨፉ ታስቦ ካልሆነ በስተቀር በጥላቻ በቂም በቀል የሚያጠቃ ያለ አገርን የሚያተራምስ ያለ ህዝቡን ለስጋት የዳረገ መንግስትና ታማኝ አሃዳውያን አጋሮቹ እውነተኛ ዕርቅና ሰላም ሕግና መረጃን ብቻ መሰረት ያደረገ ፍትሕ ይሰጣሉ ማለት የማይታሰብ ነው፡፡

ሕገ-መንግስቱንና ሕብረ-ብሄር ፌደራላዊ ስርዓቱን ለማፍረስ አልሞ የትግራይን ህዝብና የዛ ህዝብ ፖለቲካዊ ድርጅት የሆነው ህወሓትን እና አናሳ ብሄረሰቦችን እያስጠቃና እያገለለ ያለ መንግስትና የለውጥ ሓይል ተብየው ስለዕርቀ ሰላም፣ ስለብሄራዊ መግባባትና ስለብቁ ተቋማት ግንባታ በድለላ ቃላት ቢመፃደቅ ተግባሩን አይተን ውሸትክን እንለዋለን፡፡

ፍቅር፣ ይቅርታ፣ መደመር በሚሉ መፈክሮች ታጅቦ ኢህአዴግን በማንቃሸሽ ያለፈውን ስራ ሁሉ በማንኳሰስ፣ ላለፈ ጥፋት በሙሉ ፈፃሚውና ተጠያቂው ህወሓት እና የትግራይ ተወላጆች ናቸው እያለ፤ ወያኔን በመወንጀል ጥላቻና ቂም በቀል በማጉላት ስሜት ቀስቅሶ ግዝያዊ ተቀባይነት ያገኘ፣ በአጉል የተስፋ ቃላት የደለለ የለውጥ ሓይል ተብየው ከስድስት ወር ዕድሜው በህዋላ ተቀባይነቱ ማሽቆልቆል ጀመረ፡፡ ለምን? ዕርቅ ይቅርታና ፍቅር ሳይሆን ፖለቲከኞች እና ጥቂት ሙሁራን ብቻ የፈጠሩት የትግራይ ህዝብና ህወሓት ላይ ያነጣጠረ የኦሮ-አማራ ያልተቀደሰ ሽርክና በአዲስ-አበባ ይገባኛል ጥያቄ ቅራኔ ፈጠረ፤ በአማራ ክልል መስተዳድር አመራሮች ግድያ ተወዛገበ፣ የኦሮምያ ወጣቶች ሙሁራንና ኦሮሞ በጠቕላላ ጥያቄያችን አይመለስም ያለ፣ ተረስቶ ቀረ፣ ለሀገር መሪነት ያበቃነው ዶ/ር አብይ የነፍጠኛ ጠበቃ ሆኖ አረፈው፣ ኦሮሞ በግፍ እየታሰረ እየተገደለ ነው፤ ለውጡ ለኛ አልሆነም አሉ፡፡ ግጭቶች በየቦታው ተበራከቱ፣ ቅማንት ቤንሻንጉል ጉምዝ በማንነታቸውና በፍትሓዊ ጥያቄዎቻቸው ምክንያት በጅምላ በተከታታይ ሲጨፈጨፉ ፌዴራል መንግስት ፀጥ አለ፣ እንዳይነገር የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ከለከለ፣ የጌደኦ ህዝብ ለም መሬቱ በጉልበት ተነጥቆ ሲፈናቀል ዝም ተባለ መልሶማቋቋም ይሁን ፍትሕ መስጠት ይቅርና የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታም በወቅቱ በበቂ መጠን ማግኘት አልቻሉም፡፡

የትግራይን ህዝብ ያገለለ የኢትዬ ኤርትራ ሰላም ድርድር ልባዊ ዕርቅ ስላልሆነናተቋማዊ አካሄድ ስላልነበረው ተንገራግጮ ቆመ፡፡ ትግራይና ኤርትራን የሚያገናኙ መንገዶችን ዘግቶ ዓሰብና አዲስ-አበባን፣ ኤርትራና ሑመራ ጐንደርን ብቻ የሚያገናኙ መንገዶች ተከፈቱ፡፡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከኤርትራ ጋር ግኑኝነት ለመፍጠር በቀጥታ ተገናኝቶ ከኤርትራ መንግስት ጋር ለመነጋገር በተደጋጋሚ ያቀረበው ጥያቄም ምላሽ ሳያገኝ ዘገየ፡፡

ይባስ ብሎ ደግሞ ኦሮሞውንና አማራውን በግፍ ያሰሩት፣ ኢሰብአዊ ምርመራ ያካሄዱበት፣ የገደሉት ትግርኛ ተናጋሪ መርማሪዎችና የድህንነት ሰራተኞች ሓላፊዎች ናቸው የሚል የዘር ማጥፋት እርምጃ እንዲወሰድ የሚቀሰቅስ አደገኛ ዘጋቢ ፊልም በለወጥ ሃዋርያ ተብየው መሪዎች ትእዛዝ እና አመራር በአገር አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ባንዴ ተላለፈ፡፡ እንደሩዋንዳ በመገናኛ ብዙሃን ቀስቃሽነት የዘር ማጥፋት እርምጃ እንዲወሰድ አጠገብህ ያለና ከፊትህ ያገኘሀውን የትግራይ ተወላጅ እንድትገድል የሚያነሳሳ ዘጋቢ ፊልም ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ህዝቦች ግን ጨዋነትና አስተዋይነት ስላላቸው ይሄን አላደረጉም፡፡ ከሸፈ፡፡

የተገባው ቃል ሁሉ አየር ላይና ወረቀት ላይ ሲቀር፣ የሆይሆይ ጊዜ አልፎ የከተማ ህዝቡ ሰከን ሲል መሪውንና የለውጥ ሓይል ነኝ ባዮን የሚጠላ፣ የማያምን፣ ከነሱ ምንም መፍትሔ አይገኝም የሚል በስጋት የሚኖር ህዝብ አብዛኛው ሆኖአል፡፡ እዩኝ እዩኝ ያለ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል ሆነ፡፡ ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደ ሙቀጫ ይሉታል ይሄ ነው፡፡ የፖለቲካ ስብራቱ ሊጠገን ይቅርና ባሰበት ወደ ከፋ ነገር እያመራ ነው፡፡

ክፍል - ሶስት

3.1. የሀገራችን የኢኮኖሚ ስርዓት ስብራትና የጥገና አማራጭ

ምዕራፍ አስራ አንድ

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትሩፋቶችና የዕድገት ጥራት ፈተና ፡-

    በዚህ ምዕራፍ የተካተቱ ፍሬ-ነገሮች ሶስት ናቸው፡፡ ባለፉት ሃያ ስምንት አመታት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ማህበራዊ ለውጥ እንደተመዘገበ፤ ግን ኢኮኖሚው ያደገበት መንገድ ጥራት የጎደለው ስለሆነ ፍትሓዊ ተጠቃሚነትን አላረጋገጠም (ማለትም ኢ-ፍተሓዊ የሀብትና የገቢ ክፍፍል፣ አስተማማኝና ዘላቂ የስራ ዕድል አለመፍጠር፣ የመሰረተ ልማት ጥራት ችግር ታይቶበታል)፣ ከፍተኛ የመንግስት ብድርና እርዳታን ማእከል በማድረግ መጪውን ትውልድ የጐዳ ነበር፤ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችም አለበት የሚሉ ናቸው፡፡

         ስለ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መፅሓፉ ላይ “… አንዳንድ ዕድገት ለጊዜው የተፈጥሮ ሀብትን አላግባብ በመጠቀም ወይንም በመጪው ትውልድ ላይ የማይገባ ዕዳን በመከመር ሊገኝ ይችላል፡፡ 

       ኣንዳንድ ዕድገቶች ዳግም በተፈለገው ደረጃና ወቅት ድህነት የማይቀርፉና በብዙ ዘርፎች የስራ ዕድል የማይፈጥር ሊሆን ይችላል፡፡ በተስተካከለ ቅኝት ውስጥ የማይፈፀሙ የዕድገት ዓይነቶች ቀጣይነት የሌላቸው ቦግ እልም የሚሉ እና የህዝባቸውን የልማት ጥም የማያረኩ ናቸው፡፡” ይላል (ገፅ 156)

         ቀጥሎም ለማስረጃ ያህል ብሎ በአሜሪካ ወረራ ስር የነበረች ዒራቅ ብዙ ህዝብ አልቆባት ተፈናቅሎባት ብዙ ሀብት ወድሞባት እያለ በተለመደው የዕድገት መለክያ ሲለካ ግን ኢኮኖሚው ከፍተኛ ዕድገት አሳይቶ ነበር ይላል፡፡ ፀሓፊው ምን ለማለት ፈልገው ነው? የኢትዮጵያ ዕድገት የተፈጥሮ ሀብትን አላግባብ ተጠቅሞ ለመጪው ትውልድ ከፍተኛ ዕዳ አሸክሞ የተገኘ የዒራቅ ዓይነት ዕድገት ነው እያሉን ነው፡፡ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ብዙሃንን አልጠቀመም እያሉን ነው፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ብ1983 – 2010 ዓ/ም የሀገር ምርት በአስር ዕጥፍ መጨመሩ፣ ከድህነት ወለል በታች የሚገኘው የሀገራችን ህዝብ በ1992 ዓ/ም ከነበረበት 44.2 በመቶ በ2008 ዓ/ም ወደ 23.5 በመቶ መውረዱን ይጠቅሳሉ /ገፅ 156/ ድህነትን በዚህ ደረጃ መቀነስ ብቻ ሳይሆን የነፍስ ወከፍ ገቢ በ1983 ዓ/ም ከነበረበት 164 ዶላር በ2010 ዓ/ም ወደ 883 ዶላር ደርሶኣል ይላሉ፡፡ ታድያ ለምን የወደመ የደቀቀ ኢኮኖሚ ካላት ኢራቅ ጋር ያወዳድሩታል?  ስኬቶቹን  የጠቀስዋቸው የተሰራው ጥሩ ነገር ክደዋል እንዳይባሉ ይሆን? ወይንስ ዕድገቱ ምንም አልጠቀመንም አሃዝ ብቻ ነው ለማለት ይሆን? መደመር ያለፈውን መልካም ስራ ማስፋት ነው እያሉ በተግባር ግን ማስፋት   ሳይሆን ማጥላላት እየሆነ አይደል?

         ኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን የፍትሓዊ ተጠቃሚነት ችግር አለበት (ኢፍትሓዊ ነው) ብለው በዜጎች መካከል የገቢ ልዩነት መስፋቱ፣ በቂና ዘላቂ የስራ ዕድል አለመፈጠሩ፣ እንደማሳያ ይጠቅሳሉ (ገፅ 158)  የሀብትና የገቢ ስርጭት መለክያ የሆነው ጀኒኮፈሽንት በ2003 ዓ/ም 0.30 የነበረ በ2008 በጀት አመት 0.33 ሆኖአል፡፡ ይህ ቁጥር ከፍ ማለቱ የሀብትና የገቢ ክፍፍል (ስርጭት) ልዩነት መስፋቱ ያሳያል ያምሆኖ ግን ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት አንፃር ሲታይ የተሻለ ነው ይላሉ፡፡ በዓለም አቀፍ ምዘናም የ2008 ዓ/ም አሃዙ ጥሩ ነው የሚባል መሆኑ ያውቃሉ፡፡ ስለ ዕድገታችን ኢ-ፍትሓዊነት ያ ሁሉ ወቀሳ የሚነገረው በዚች ትንሽ የአሃዝ ልዩነት ምክንያት ሳይሆን ሆን ተብሎ ልማቱን ለማጥላላት ለፖለቲካ ፍጆታ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ የመንገዶች የጤናና ትምህርት ተጠቃሚነት ስርጭት ወደ ገጠሩና ትናንሽ ከተሞች ወደ አዋጭነት የሌላቸው ግን ወደፊት እንዲለሙ ተብሎ የተሰራላቸው ሰፊ የቆዳ ስፋት ጥቂት ህዝብ የተበተነ አሰፋፈር ወዳላቸው ቆላማ ኣካባቢዎች ተዘርግቶአል፡፡ የፌደራል በጀት ድጎማ ቀመር ለክልሎች ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች በተወከሉበት በፌደሬሽን ምክር-ቤት እየተወሰነ ፍትሓዊ ልማት ለማምጣት አግዞአል፡፡

           ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ፣ ለብዙሃኑ የከተማ ህዝብ የማይጨነቅ መንግስት ቢሆን ይህ ሁሉ መሰረተ ልማትና ማህበራዊ ግልጋሎት በየገጠሩ በትናንሽ ከተማው የተበተነ አስፋፈር ባለበት ለማስፋፋት ባልተረባረበ ነበር፡፡ ሳይሰራ የቀረ በርካታ አለ የዚህ ምክንያት የኢኮኖሚ አቅም ውስንነትና የየክልሉ አመራር ብቃት ልዩነት፣ እንዲሁም የኮንትራት ስራ አመራር አቅም ማነስ ነው፡፡ የአድልዎ ፖሊሲ እንደሌላ የኢህአዴግ ስራ  አስፈፃሚና ምክር-ቤት የአሁኑ የለውጥ ሃዋርያ ነን  ተብየዎችም ጭምር በጥልቅ ተሃድሶ ጊዜ ተማምነውበታል፡፡ መካካድ መጣ እንጂ!! 

          ዘላቂ በቂ የስራ ዕድል አልተፈጠረም የተባለው ትክክል ነው፡፡ ምክንያቱ ግን የመንግስት ብድርና እርዳታ ማእከል ያደረገ ዕድገት መሆኑ ኣይደለም፡፡ ብድርና እርዳታው ለበርካታ የመንገድና የጤና መሰረተ ልማቶች ወሎአል ከዛ ውጭ ግን የኢኮኖሚያችን ዋና መሰረት የሆነው ግብርና እንዲሁም ከፍትኛ ትምህርትና ከዛ በታች ያለው የትምህርት ተቋማት ሽፋን በመንግስት ገቢ ነው የተሰራው፡፡ እንዳውም የጣና በለስና የተከዜ ሓይል ማመንጫዎች ከዛም ኣልፎ ታላቁ የህዳሴ ግድባችን በሀገር አቅም ነው የተሰሩትና እየተሰሩ ያሉት፡፡ ታድያ ለምንድነው ብድርና እርዳታን ማእከል ያደረገ መሰረተ ልማት ላይ ያተኮረ ዕድገት ነው የተመዘገበው ተብሎ የሚንቋሸሸው፡፡ ብድርና እርዳታው እያስፈልገንም ብለን በራሳችን ገቢና ሀብት ብቻ እንስራ ቢባል ኑሮ የተመዘገበው ልማት ይገኝ ነበር? ህዝብስ እነዛ መሰረተ ልማቶች ባይሰሩ ይታገስ ነበር? ባለሃብቱስ እስካሁን የሰራውን ኢንቨስትመንት ይሰራ ነበር? ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? እስቲ ካሁን በህዋላ ካለብድርና እርዳታ እንሂድ ከተባለ እናያለን በተግባር ግን በየጊዜው ከዓለም ባንክ ከዓለም ገንዘብ ድርጅት ከአረብ አገሮች፣ ከቻይናና ከአውሮፓ ብድር አገኘን እየተባለ ካለፈው ባልተለየ መንገድ ዜናና ስኬት ሆኖ እየተነገረ ነው፡፡

          በጣም የሚያሳዝነውና ለትዕዝብት የሚዳርገው ዳግሞ መሰረተ ልማቱ ጥቂት ባለሃብቶችን ነው የጠቀመው የሚል ነው፡፡ መፅሓፍ ላይ “ከፍተኛ የመንግስት ብድርን ማእከል ያደረገ የመሰረተ ልማት መስፋፋት በአብዛኛው የጠቀመው  በዘርፉ የተሰማራውን ውሱን ባለሃብት ነው፡፡” ይላል (ገፅ 159) የባለሃብት ኢንቨስትመንት የተከማቸው ባብዛኛው በአዲስ አበባና ለአዲስ አበባ ቅርብ በሆኑ የኦሮሚያ አካባቢዎች ነው፡፡ በሌላ አካባቢ ያለው መለስተኛ ሆኖ በክልልና በዞን ዋና ከተሞች በጥቂት ገጠሮች ያለ ነው፡፡ ባለሃብቱ ተጠቃሚ መሆኑ ተገቢ ሆኖ አብዛኛው መሰረተ ልማት ግን በሁሉም ክልሎች ያለውን የገጠርና የከተማ ህዝብን ነው ተጠቃሚ ያደረገው፡፡ ጥላሸት መቀባት ይሉታል ይሄ ነው፡፡

          የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት አለ በሚል ያቀረቡት ማሳያ መረጃዎች ባብዛኛው ትክክል ሆነው በአንዳንዶቹ ግን የተዛባ ሓሳብና መረጃ ነው የቀረበው፡፡ መዛባቱ በጎላ ደረጃ የታየባቸው የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ክፍተቱ እየሰፋ መምጣቱ፣ (ገቢው ንግድ እየናረ) የዋጋ ንረት በየጊዜው መከሰቱ የግብር ገቢ መድረስ ያለበት ደረጃ አለመድረሱ ናቸው፡፡ ቁጠባና የባጀት ጉድለት እንዲሁም የሀገር ውስጥ ገቢ ድርሻ በበጀት ጥሩ ዕድገት አሳይተዋል ፡፡ ስለዚህ ሁሉንም የማክሮ ኢኮኖሚ መለክያዎች የተዛቡ እንደነበሩ አድርጎ መፈረጅ ከሃቅ የራቀ ነው ለይቶ መተቸት ነው ተገቢ የሚሆነው፡፡

           ትክክል ያልሆነ መረጃና ሓሳብ የቀረበባቸው ዳግም የበጀት ጉድለትና የሀገር ውስጥ ቁጠባ የተመለከቱ ናቸው፡፡ መፅሓፉ ላይ “የ… በጀት ጉድለት ከተቀመጠው ገደብ እንዳያልፍ ሲባል ፍላጎት እንዲገደብ ተደርጓል፡፡ ይህም የዜጎቻችንን የመሰረተ-ልማት ፍላጎት የሚያሟሉት ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ፈጥሯል” ይላል፡፡ ስለማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት አስፈላጊነት እጨነቃለሁ የሚል መሪ መዛባቶችን እየተቸ እንደገና የበጀት ጉድለት የሚሸፍን ብድር ለምን ተገደበ ብሎ ወቃሽ ሊሆን ተራ የህዝበኝነት ትችት ነው፡፡ መሰረተ ልማቱ ባለሃብቱን ነው የጠቀመው እያሉ የበጀት ጉድለት በማናር መሰረተ ልማት መስራት ነበረበት ሲሉ ለትዕዝብት ይዳርግዎታል፡፡ የአዞ እንባ ነው፡፡

        “የቁጠባ ፍላጐት ያዳከመው የቁጠባ የወለድ ተመን ከዋጋ ግሽበት በማነሱ እንዲሁም በፋይናንስ ተቋሞች በኩል ቁጠባን የሚያበረታቱ አገልግሎቶች አለመስፋፋት ናቸው” ይላል (ገፅ 162) ሁለቱም መረጃዎች ስህተት ናቸው የሀገራችን ባለሀብት ይሁን መላው ህዝባችን የሚቆጥበው ገንዘብ እንዳይጠፋበት በቂ ዋስትና የሚሰጠው በፈለገው ጊዜም ሊወሰደው የሚፈቅድለትን የፋይናንስ ተቋም ማግኘቱ ነው ዋናው ትኩረቱ እንጂ ሲቆጥብ ለሚያገኘው ወለድ ብዙም ትኩረት አይሰጥም የሚል ጥናትና ግምገማ ነው በተደጋጋሚ በባንኮችና በገለልተኛ ኢኮኖሚስቶች የተካሄደው፡፡ ስለዚህ ፀሓፊው ያሉት ነገር መፅሓፍ ላይ ካገኙት ወይም ሲባል ሰምተው ይሆናል እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ የቁጠባ አመለካከትን ካጠኑት ሰዎች ያረጋገጡት አይደለም፡፡

          የፋይናንስ ተቋማት ቁጠባን የሚያበረታቱ አገልግሎቶች አላስፋፋም ያሉትም ስህተት ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወደ ሺዎች ያደጉ የባንክ ቅርንጫፎች በተለይ በንግድ በኩል እንደዚሁም በህዋላ በግል ባንኮች በኩል ወደየገጠሩና ትናንሽ ከተሞች የምርትና የአገልግሎት ተቋማት የተዘረጉት ቁጠባን ለማበረታታት አገልግሎትን በቅርብ ለመስጠት ነው፡፡ የሴቶች የታዳጊዎች የህፃናት፣ የሸሪዓ ሕግ ተከታዮች ቁጠባን ለማበረታታት ልዩ ልዩ ኣዳዲስ አገልግሎቶች ተዘርግተው በመገናኛ ብዙሃንና በሽልማት ተደግፈው ውጤት አስገኝተዋል አሁንም ይሄ በቂ አይደለም ሊባል ይችላል እንጂ ቁጠባን  የማስፋፋት አገልግሎቶች አልዘረጉም አያስብልም፡፡ የጠራ መረጃ ከትክክለኛ ምንጭ ማግኘት የተሰራን ስራ በልኩ ተገቢ እውቅና መስጠት፣ የጐደለውን የሚሞላ ተጨባጭ መፍትሔ ማቅረብ ከፈላስፋውና ኢኮኖሚስቱ ይጠበቃል፡፡ ግን ይህን ማድረግ አልቻሉም፡፡

 

 

ምዕራፍ - አስራሁለት

የኢኮኖሚ ስርዓቱ ስብራት መንስኤዎች

            በዚህ ምዕራፍ የተካተቱ ዋነኛ ሓሳቦች ስለ ገበያ ጉድለትና የመንግስት ጉድለት ምንነት ካብራራ በህዋላ እያንዳንዳቸውን በተናጠል በመተንተን መፍትሔ መፈለግ ሙሉ ስእል የማይሰጥ መሆኑ፣ ይልቁንስ የገበያና የመንግስት ጉድለትን አንድ ላይ በማጣመር በድምር አይቶ በስርዓት ጉድለት ማዕቀፍ ማየት ትክክለኛው ዕይታ መሆኑ፣ የስርዓት ጉድለት ሲባል ደግሞ የገበያና የመንግስት ጉድለት ብቻ ሳይሆን የመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የትምህርት ተቋማትም በተዋናይነት ያካተተ መሆኑ፣ በነዚህ አራቱ ተዋንያን መካከል ያለ ትስስርና መስተጋብር ለይቶና አጣምሮ የማጠናከር አቅጣጫ ዋናው መፍትሔ መሆኑ የሚተነትኑ ናቸው፡፡

           የገበያ ጉድለት ማለት በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በፍላጎትና አቅርቦት መካከል የጎላ አለመመጣጠን ሲታይ፣ ትርፍ ለማግኘት ሀብት ለማካበት ሲባል ሕብረተ-ሰብን የሚጐዱ ስራዎ ሲሰሩና ኢኮኖሚውን ወደ ወሳኝ የኢኮኖሚው ዘርፎች በትክክል ሳይፈስ ሲቀር የሚፈጠር መዛባት ወይም ክፍተት ገበያው ራሱ ወይም ባለሃብት ማስተካከል ሳይችል ሲቀር ነው፡፡ ባጭሩ በገበያው ሕግጋት በባለሃብቱ ዓቅም ይሁን ፍላጎት ሊፈታ የማይችል ክፍተት ማለት ነው፡፡

          የመንግስት ጉድለት ማለት መንግስት ገደብ የለሽ ጣልቃ ሲገባ በባለቤትነት ይዞ የሚያካሂዳቸው የምርትና አገልግሎት ተቋማት ለውድድርና  ለሕግ ተገዢ ሳይሆኑ ሲቀሩ፣ በልዩ ድጎማና አድልዎ ሲደገፉ ለሙስና ለብክነት ሲዳረጉ ተጠያቂነት ሳይኖራቸው ሲቀር ወይንም መንግስት ውድድርና የሕግ የበላይነት ቁጥጥር ሳያጎለብት ሲቀር የሚከሰት ነው፡፡

          የገበያ ሕግጋትና የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረት ሓሳብ እንደሚለው ከሆነ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ዋነኞቹ ተዋንያን ባለሃብቱ አምራቹና ተጠቃሚው ሕብረተ-ሰብ እና መንግስት ናቸው፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚው ሞተር ባለሃብቱ ስለሆነ ዋነኛው ትኩረት እሱን ምርታማ እሴት ፈጣሪ ተወዳዳሪና ለሕግ ተገዥ ማድረግ አቅሙን መገንባት ቁልፍ ስራ ይሆናል፡፡ እንደዚሁም ሕብረተሰቡ ክህሎትና ተነሻሽነት አጎልብቶ ምርታማና ተጠቃሚ ተወዳዳሪ ሆኖ የመግዛትና የማፍራት አቅሙ በቀጣይነት እንዲጎለብት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሁለቱም ተዋንያን ማድረግ ያልቻሉትን ዳግም መንግስት በተመረጠ አግባብ ጣልቃ እየገባ የምርትና  የአገልግሎት ባለቤት ሆኖ ክፍተቱን ይሞላል  አዋጪ ሲሆንና ባለሃብቱ አቅም ፈጥሮ ራሱ ሊሰራቸው ሲችል ይለቅለታል ሌላ ክፍተት ወደመሸፈን ይሸጋገራል በመንግስት እጅ የሚያዙ ተቋማት በውድድር በሕግ የሚገዙ ከባለሃብቱ የተለየ ልዩ ድጋፍ የማይደረግላቸው ተጠያቂነት ያላቸው እንዲሆኑ በማድረግ የመንግስት ጉድለትን መቀነስ ይቻላል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚሰራበት የታወቁ ኢኮኖሚስቶች የተቀበሉት በተግባር ውጤታማ የሆነ መሰረተ ሓሳብ ይሄ ነው፡፡

           የመደመር መፅሓፍ ፀሓፊው ግን ይህ መሰረተ ሓሳብና ከዚህ የሚመነጨጩ ፖሊሲዎች ለኛ ሀገር ሁኔታ ኣይሰሩም የስርዓት ጉድለት የሚባል ሁለቱን ጉድለቶች በመደመር ዕሳቤ አጣምሮ የሚያይና ሌሎች ሁለት ተዋንያንን ማለትም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችንና የትምህርት ተቋማትንም ያካተተ የአራቱም ትስስርና መስተጋብር ላይ ያተኮረ የስርዓት ጉድለት ዕይታ ነው ችግራችንን የሚፈታልን ይሉናል፡፡

መፅሓፍ ላይ እንዲህ ይላል፡-“የስርዓት ጉድለት ፅንሰ-ሓሳብ የገበያ ጉድለትና የመንግስት ጉድለት በተናጠል በሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመተንተን መጠቀም የችግሩን ሙሉ ስእል ለመረዳት ያዳግታል የሚል ነው፡፡

          በአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ውስጥ ከመንግስትና ከግል ዘርፍ በተጨማሪ በዋናነት ሁለት ተዋንያንን መለየት ይቻላል፡፡ እነሱም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የትምህርት ተቋማት ናቸው” (180)

          በመቀጠልም “ዘላቂና ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ሊረጋገጥ የሚችለው በእነዚህ ተዋንያን (መንግስት፣ የግል ዘርፍ፣ ምንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና መካነ ትምህርት) መካከል ጠንካራ ግኑኝነት ሲፈጠር ብቻ ነው፡፡ የአንዱ ወይም የሁሉም ተዋናይ በተናጠል ጠንካራ ሆኖ መውጣት ዘላቂና ጤናማ የኢኮኖሚ ዕድገትና ልማት ሊያረጋግጥ አይችልም በእነዚህ የኢኮኖሚ ተዋንያን መካከል ጠንካራ መስተጋብርና ግኑኝነት ሳይፈጠር ሲቀር የሚከሰተውን ሁኔታ የስርዓት ጉድለት እንለዋለን፡፡” (ገፅ 181)

         በእነኝህ ሓሳቦች ውስጥ ሶሰት ስህተቶች አሉ፡፡ አንደኛው ህዝብ ትልቁና ሶስተኛው የልማት ተዋናይ አድርጎ መውሰድ ሲገባው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በመለስተኛ ፕሮጀክቶች የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ከሚገባው በላይ በማጉላት ሚናቸውን አጋኖ ያቀርባል፣ የህዝብን ሚና ጠቅልሎ ይረሳል፡፡ ሁለተኛ የትምህርት ተቋማት የመንግስት ወይም የባለሃብት መሆናቸው የማይቀር ስለሆነ ከመንግስትና ባለሃብት ሚና ጋር መጠቃለል ሲችሉ ለብቻ አጉልቶ የላቀ ቦታ ይሰጣቸዋል ሶስተኛውና ዋናው ስህተት ዳግሞ ዋነኛ ችግር ይሁን መፍትሔ የነዚህ አራት ተዋናዮች ትስስርና መስተጋብር ጉዳይ ያደርገዋል፡፡ በኛ  አይነቱ ጀማሪና ደካማ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መንግስት ሊኖረው የሚገባ ልዩና የጎላ ሚናን ባለሃብቱ የሚኖረው የሞተርነት ሚናን ደፍቆና አድበስብሶ ከመንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና ከትምህርት ተቋማት ሚና ጋር በእኩል ደረጃ ያስቀምጠዋል፡፡ ችግሩን በማድበስበስ የገበያ ጉድለትና የመንግስት ጉድለትን መፍታት ላይ ያተኮረ ስትራቴጂያዊ መፍትሔ እንዳይመጣ የመንግስትና የባለሃብት ሚናና የሁለቱ ቅንጅት ዋናው ትኩረት እንዳያገኝ ያደርጋል፡፡

መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡-

       “በድምሩ ሲታይ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማት በተለምዶ ከዚህ በፊት የነበረውን የአንድ አቅጣጫ መሰመራዊ ዕይታ ከመከተል መሻገር አለበት፡፡ ይልቁንም የኢኮኖሚው ዋነኛ ተዋንያን በሆኑት መንግስታት የግሉ ዘርፍ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት፣ እና የዕውቀት ተቋማት መካከል በሚኖር ስርዓታዊ ትስስር የሚገለጥ አድርጎ መመልከት፣ ከአቅላይነት በፀዳ መልኩ የኢኮኖሚ መዋቅር ስብራትና መፍትሔዎችን ለማምጣት ይረዳል፡፡” (ገፅ 182)

            የጀማሪ ነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መሰረታዊ ችግር ባለሃብቱና ውድድር ደካማ መሆን፣ ምርታማነትና የነፃ ገበያ ተቋማት ደካማነት ከዚህ የመነጨ ኢኮኖሚው ከውድድርና ከሕግ ውጭ ለመከበር የተመቸ መሆን የመንግስት ጣልቃ ገብነትና አመራር የሚጠይቅ መሆን ነው፡፡ የተዋናዮች ቅንጅትና መስተጋብር ችግር የዚህ ውጤትና መገለጫ እንጂ የችግሩ ዋና ምንጭም መፍትሔም አይሆንም ኒዮ ሊበራል ሓይሎች የመንግስትን ሚና በሕግ ማስከበርና በመሰረተ ልማት ብቻ እንዲታጠር አድርገው አለአግባብ ለሚበለፅጉት ጥገኛ ባለሀብቶችና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶ ሰፊ ቦታ ይሰጥ የሚሉትን ነው ኢትዮጵያዊ ካባ አልብሰው የስርዓት ጉድለት ያሉት፡፡ ውስጡ ኒዮ ሊበራል ፖሊሲ ነው፡፡ የመንግስትን እጅ ከኢኮኖሚው ማስወጣት ነው፡፡

          በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች  ስለሚኖራቸው ሚና መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ “…በማንኛውም ዓይነት ሁኔታ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የመንግስትን አቅም ውሱንነት የሚያካክሱ ናቸው የመንግስትን አሰራር  ለማዘመንና ተጠያቂነትን ለመፍጠር ሚና ኣላቸው፡፡ በተለይም ማህበራዊ ፍትሕን በማስፈን በኩል ያላቸው ሚና ከፍተኛ ስለሆነ፣ እነሱን በተገቢው መጠን ያላሳተፈና ከእነርሱ ጋር በቂ መናበብ የማይፈጥር የኢኮኖሚ ስርዓት ጉድለት የሚያጋጥመው ይሆናል፡፡

     … እነዚህ ኣካላት በመንግስትና በግሉ ዘርፍ መካከል በመቆም የሁለቱን የኢኮኖሚ ተዋናይነት ሚዛን እንዲጠበቅ የሚያደርጉ ናቸው፡፡” (ገፅ 186 – 187)

      ምናለበት የዚህን ያህል ትኩረት ለህዝቡ ሚና በልማት ቢሰጡ!! የህዝቡ ጉልበት፣ ዕውቀትና ልምድ፣ በኢኮኖሚው ዕድገት ያለው የጎላ ሚና ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን ትተው ስለ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ይህን ያህል የተጋነነ ውደሳ ኣዘል ሓሳብ መስጠትዎ ጥብቅናዎ ለህዝቡ ሳይሆን ለኒዮሊበራል ሓይሎችና ለፖሊሲዎቻቸው  መሆኑ አንድ ተጨባጭ ማሳያ ነው መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዴት አድርገው ነው ለማህበራዊ ፍትሕ ለተጠያቂነት የጎላ ሚና የሚኖራቸው? ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች የሚሰሩት ስራ ቢኖርም እንደ ሰርቶ ማሳያ እንጂ ሰፊውን  ህዝብ ትርጉም ባለው ደረጃ ከድህነት የሚያወጡ ኣይደሉም ይባስ ብለው ደግሞ እነዚህ ድርጅቶች በግሉ ዘርፍና  በመንግስት መካከል ሆነው ሚዛን የሚጠብቁ ናቸው  ብለዋል፡፡ ፖለቲካ ውስጥ እየገቡ እንዳንዶቹ የውጭ ልኡካን ሆነው ሊያተራምሱ ካልሆነ ይህን ማድረግ ኣይችሉም፡፡ ዶሮ ብታልም ጥሬዋን ኣሉ!! መፍትሔ አለኝ ብለው ስለ ህዝቡ ሚና ረስተው የበጐ አድራጐት ድርጅቶች ሚና  ከሚገባ በላይ እያጋነኑ ማወደስ አለማው ምን ይሆን?

        መፅሓፉ ላይ የበለፀጉ ሀገሮች ረዥም ግዜ የወሰደባቸውን የኢኮኖሚ በተለይም የቴክኖሎጂ ዕድገት ታዳጊ ሀገሮች ከገበያ በመግዛትና አቅም በመገንባት በአቋራጭ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ቶሎ መሸጋገር ይችላሉ ይልና “በመሆኑም ወቅቱ የፈጠረልንን ሙቹ አጋጣሚ በመጠቀም አቋራጭ የቴክኖሎጂ ልማት ስልትን በመቀየስ በተፈጥሮ ላይ ጥገኛ የሁኑትን የኢኮኖሚ ሴክተሮች በራሳቸው እመርታዊ ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ በፍጥነት የዕውቀትና የአገልገሎት መር ኢኮኖሚን በመገንባት ሂደት ውስጥ መግባት ይኖርብናል” ይላል፡፡ (ገፅ 235) በአቋራጭ መሸጋገር የሚቻለው የበለፀጉ አገሮች ትተውት የሄዱትን በገበያ በቀላሉ የሚገኘውን ወይም በመኮረጅ የሚሰራውን ቴክኖሎጂ የሚመለከት ብቻ ነው፡፡ የዕውቀትና የአገልግሎት መር ኢኮኖሚ ግን ከፍተኛ የብልፅግና ደረጃ በደረሱ አገሮች የሚሰራ ነው ምክንያቱም የተራቀቀ ጥልቅ ዕውቀትና ክህሎት ያዳበረ የምርምር አቅም (የቴክኖሎጂ ጭምር) ይጠይቃልና ቢያንስ ዳግም እንደነኮርያ ብልፅግና ደረጃ የደረሱ መሆን ወይም የቻይና ዓይነት ሁለገብ ግዙፍ አቅም ይጠይቃል፡፡ አለበለዝያ ማንዩፋክቸሪንግ ያላሳካን ወደ ከባድ ኢንዱስተሪ ያልተሸጋገርን መካከለኛ ገቢ እንኳን ያልደረሰን ሀገር በምን ተአምር ነው ተሎ ወደ ተራቀቀ ዕውቀትና አገልግሎት መር ኢኮኖሚ የምንሸጋገረው (ወደ ናኖ ቴክኖሎጂ ማለት ነው)  

            እስካሁን ስለተመዘገበው የሀገራችን ፈጣን ልማት መፅሓፉ እንዲህ ይላል፡- “የሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገት በዋናነት በብድር ላይ የተመሰረተና በከፍተኛ መንግስታዊ ወጭ በተስፋፋ መሰረተ ልማት ኣማካኝነት የመጣ ነው” (ገፅ 238) ሆን ተብሎ የተዛባ መረጃ ነው በብድር የተሰሩት አውራ መንገዶችና ከፊል ሓይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ናቸው ዋናው የልማት ምንጭ በድምር ሲታይ ግብርና አገልግሎቶችና ኮንስትራክሽን ነበሩ፡፡ ግብርና ነው ዋናው የዕድገታችን ምንጭ የነበረው፡፡ ከዛ ቀጥሎ አገልግሎቶችና ኮንስትራክሽን ነበሩ፡፡ ብድርና ዕርዳታ የሀገሪቱ በጀት 30 ብቻ የሚሆንበት ደረጃ ደርሰን ነበር  በ(2006 – 2007) ዕዳችንን የመክፈል አቅም እየፈጠርን መሄድ ጀምረን ስለነበረና ብድርና እርዳታው ባብዛኛው ተገቢ ስራው ላይ ይውል ስለነበር ብድርና እርዳታው በዚህ መንገድ መጠቀም ምንም ጥፋት የለውም፡፡ አሁንም ልማቱን ማጥላላት ስለተፈለገ የቀረበ ትችት ነው፡፡

ክፍል- አራት

4.1. መደመር እና የውጭ ግኑኝነት-

        በዚህ ክፍል ስር ባሉ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ የዓለም አቀፍ አዝማምያዎችና ሀገራዊ እንድምታቸው ከዳሰሰ በኋላ በዓለም ደረጃ የብሄርተኝነት መግነንና የብሔር ፓርቲዎች በአጭር ጊዜ ሰፊ ተቀባይነት እያገኙ መምጣት ለሀገራችን ታላቅ ተግዳሮት ነው ብሎ ይደመድማል በቀጣዩ ምዕራፍ ዳግም የሀገራችን የውጭ ግኑኝነት ፖሊሲ በመደመር ዕሳቤ ሀገራዊ ጥቅምን ከማስቀደም ይልቅ ግኑኝነትን ማስቀጠልና ብሔራዊ ክብርን ማረጋገጥ የሚያስቀድም ይሆናል ይላል፡፡ በሌላ አነጋገር ሀገራዊ ጥቅምን በሚነካ መንገድም ቢሆን የውጭ ግኑኝነትን ከተለያዩ ሀገራት ማስቀጠልን እናስቀድም ማለት ነው፡፡  የሀገርን ጥቅም ሳይከበር ብሔራዊ  ክብር እንዴት ማስከበር እንደሚቻል ምላሽ አይሰጥም፡፡

       መፅሓፉ ላይ እንዲህ ይላል፡፡ “በጥቅሉ ዓለም አቀፋዊ የብሄርተኝነት መግነንና የብሄር ፓርቲዎች በአጭር ግዜ ሰፊ ተቀባይነት እያገኙ መምጣት ለሀገራችን ያለው አንድምታ ከፍተኛ ነው የህዝብን ጥያቄ መሰረታዊ በሆነ መልኩ የሚመልሱ አጀንዳዎችን ከሚቀርፁ ይልቅ ብሶትን የሚቀሰቅሱ እና መጤ ጠል የሆኑ ፖለቲካ ሃይሎች መበራከትና   የሚያገኙት ድምፅ እያደገ መምጣት ብዙሃነት ተጨባጭ ሁኔታ ለሆነባት ሀገራችን ታላቅ ተግዳሮት ነው ፡፡” (ገፅ 249)

     ብሔርተኝነትና የብሄር ፓርቲዎችን እንደ የስጋት ምንጭ ማየት ያውም ሁሉንም ዓይነት ብሔርተኝነትና የብሄር ፓርቲን በስጋት አይን ማየት ምክንያቱ ምንድነው?    ወዴትስ ያመራል? ብለን መጠየቅና ምላሽ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡፡ ብሄራዊ ፓርቲዎች እና ብሔርተኝነት ሁሉም ሁልጊዜ ፅንፈኛ ኣይሆኑም ፅንፈኛ ሆነው ህዝብን ከሌላ ህዝብ ጋር የሚያጋጩ አገርን ከአገር ጋር የሚያጣሉ አሉ፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ዴሞክራሲ ብሄራዊ ፓርቲዎች ዳግም የህዝቦች መከባበርን በእኩልነትና በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የህዝቦችና የሀገር አንድነትን ያራምዳሉ፡፡

         ይህን ሳይለዩ በጅምላ እንደየስጋት ምንጭ መፈረጅም ሆነ የተበደለን ብሔር ፍትሓዊ ጥያቄ ያነሱትንም ጭምር የሀገር አንድነት ስጋት አድርጎ መቁጠር ምክንያቱ የአሃዱአዊነት አመለካከት ነው፡፡ ፅንፈኝነትን እየታገሉ ፍትሓዊ የእኩልነት ጥያቄን በዴሞክራሲያዊ ስርዓት በእኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ተገቢ ምላሽ መስጠት ነው መፍትሔው፡፡ ከዛ መብቱና ጥቅሞቹ ሲረጋገጥለት ህዝቡ ራሱ የብሔር ፅንፈኝነትን ይታገለዋል፡፡

        ይህ አመለካከት ወዴት ያመራል? በኛ ሀገር ተጨባጭ ሁኔታ የብሔር ፖለቲካዊ ድርጅቶችን እንደስጋት አይቶ እነሱን በሰበብ አስባብ መገደብ፣ ማክሰም ያስከትላል፡፡ ሕብረ-ብሔር የፖለቲካ ድርጅቶችን ፅንፈኛ የሆኑትንም ጭምር ወደ ማጠናከር ያመራል፡፡ በሀገራችን በተግባር እየተደረገ ያለውም ይሄ ነው፡፡ እላይ ከተገለፀው አሃዳዊ አመለካከት የመነጨ ነው፡፡

       መደመር እና የውጭ ግኑኝነት በሚል ርእስ በተፃፈው ምዕራፍ ውስጥ እንዲህ ይላል:- “የውጭ ግኑኝነት ዕሳቤያችን ጥቅምን ሳይሆን ግኑኝነትን ያስቀደመና ችግሮችንለመፍታት ቀዳሚው ነገር ግኑኝነትን ማደስ ነው ብሎ የሚያምን ነው፡፡” (ገፅ 255)

      “… ብሔራዊ ጥቅም ለንግግር መሰናክል የሚሆንበትንና ለሓይል ፖለቲካ መንገድ የሚከፍተውን የግትርነት ተፈጥሮውን መቀየር አለበት ከሚል ሓሳብ የሚነሳ ነው፡፡ 

      “በውጭ ግኑኝነታችን ውስጥ “ቋሚ ወዳጅና ቋሚ ጠላት የለም” ከሚለው መርህ ይልቅ “ወዳጅና ጠላት ብሎ ነገር የለም” የሚል መርህ የምንከተል ይሆናል::” (ገፅ 257)

      እነዚህን ሓሳቦች ፈታ አድርገን እንመርምራቸው፡፡ ከሞላ ጎደል ሁሉም የዓለም መንግስታት የሀገሬን ብሔራዊ ጥቅም አስጠብቃለሁ፣ የሀገሬ ጥቅምን ለማስከበር ብየ ነው ይሄን ያደረግኩት ክእገሌ ሀገር ጋር የተወዳጀሁት ወይም ያልተግባባሁት ይላሉ፡፡ ባልተለመደ ሁኔታና በግላጭ የሀገራችን መሪ በመፅሓፉቸው ውስጥ የውጭግኑኝነታችን ጥቅምን ሳይሆን ግኑኝነትን ያስቀደመ ይሆናል ብለውናል፡፡ ብሔራዊ ጥቅም ሲባል‘ኮ ኢኮኖሚያችንን ሰላማችንን ዴሞክራሲያችንን ብሎም ብሔራዊ ደህንነታችንን ማስጠበቅ ማለት ነው፡፡ ታድያ እነዚህን ጥቅሞች የማያስጠብቅ ግኑኝነት ቢታደስ ባይታደስ ቢቀጥል ባይቀጥል ፋይዳው ምኑ ላይ ነው፡፡ ይህን ሓላፊነት የማይወጣ ገዥ ፓርቲና መንግስት በተግባር እንደምናየው ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚነካ ድርድር ከግብፅ ጋር በህዳሴ ግድብ ዙርያ እያደረገ ነው፡፡ ወዴት ያመራል ግልጥ ብሎ እየታየ ነው፡፡

         ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ለግኑኝነት መሰናክል የሚሆን ለሓይል ፖለቲካ ጠንቅ የሚሆን የግትርነት ተፈጥሮ አለው ብለውናል፡፡ የማንም መንግስት ቀዳሚ ሓላፊነት በሀገር ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የሕግ የበላይነት ማስከበርና በውጭ ግኑኝነት ዳግም ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የቻለውን ሁሉ ማድረግ ነው፡፡ የአሁኑ “የለውጥ ሃዋርያ” ተብየው ግን ብሔራዊ ጥቅም ማስቀደም ግትርነት ነው ለሓይል ፖለቲካ ጠንቅ ነው ብለውናል፡፡ ታድያ በዚህ እምነትዎ መሰረት እየመሩ የሀገራችንን ብሔራዊ ጥቅም ያስከብራሉ ብለን እንዴት እንመን?

      ለካ ከዚህ በመነጨ ነው ተስፋ የፈጠረ ልማታችንን የሚገታ ፌደራል ስርዓታችንን ሕገ-መንግስታችንን የሚቀለብስ አመለካከትና ተግባር በፖሊሲ ለውጥ ሪፎርም መልክ የሚቀላጠፍ ያለ፡፡ የሆነ ዓይነት ግኑኝነት ከማንም ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚጎዳ ሓይል ማስቀጠል ወይም ማደስ አለማ ያደረገ መንግስትና መሪ የሀገር ጥቅምን አሳልፎ ለመስጠት ምን ይከለክለዋል?

      ወዳጅና ጠላት ብሎ ነገር የለም ብለውናል፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ ጥቅማችንን ከሚጐዳ አገር ጋርም ግኑኝነት “ወዳጅነት” ማስቀጠል “መደመር” ተገቢ ነው እያሉን ነው ይህን አለማድረግ ግትርነት ነው እያሉን ነው፡፡ አገርህን የሚዘርፍ የሚወር ብሔራዊ ጥቅሜ የምትለውን ነገር እንዳትሰራ በጫና የሚከለክልም ወዳጅ ነው ጠላት የሚባል ነገር የለም እያሉን ነው፡፡ የመጣ ጉልበተኛ የሚጭንብንን ትእዛዝ ለግኑኝነት ስንል መቀበል አለብን ማለት ነው ይገርማል፡፡ መደመር መጨረሻው ይሄ ሆኖ አረፈው፡፡

        ብሄራዊ ክብርን የሚያረጋግጥ የውጭ ግኑኝነት በሚል ርእስ በዚሁ የመፅሓፉ የመጨረሻ ምዕራፍ እንዲህ ይላል፡፡ “ሀገራዊ ክብራችንን የሚፈታተነውና ዜጎቻችን ለከፍተኛ ጉስቁልና እና ውርደት እንዲዳረጉ የማያደርገው እንዱና ዋናው ፈተና ስደት ነው፡፡ …. ስለዚህም ሀገራዊ ክብራችንን የማስጠበቅ ቀዳማዊ ትኩረታችን ዜጎቻችን በስደት ውስጥ የሚገቡበትን መከራ ማስቆምና የዜጐችን ክብር ማረጋገጥ መሆን አለበት፡፡” (ገፅ 260 – 261)

       ስደት አንዱ ትልቅፈተና ይሆናል እንጂ ዜጎቻችንን ለከፍተኛ ጉስቁልናና ውርደት እንዲዳረጉ የሚያደርግ ዋናው ፈተና ድህነታችንና ህዋላ ቀርነታችን ነው፡፡ ስደት የዚህ ውጤት ነው፡፡ “ቀዳሚው ትኩረታችን ዜጎቻችን በስደት የሚያጋጥማቸውን መከራ ማስቆምና የዜጎቻችን ክብር ማረጋገጥ መሆን አለበት፡፡” የሚለውም ስህተት ነው፡፡ ድህነትና ህዋላ ቀርነት እስካለ ድረስ ስደት ኣይቀርም፡፡ የድሀ አገር ስደተኛ አይከበርም፡፡ ክብሩ የሚመነጨው ከአርበኝነት ከመፈክር ሳይሆን ልማትና  ዲሞክራሲ ሰላም በሀገር ውስጥ አረጋግጦ በዓለም ተፈላጊና ተደማጭ አገር እንድትኖረን በማድረግ ብቻ ነው የስደተኛ ዜጎቻችን ክብር የሚረጋገጠው፡፡ ለዚህም  ነው ዋናው ፈተና ድህነትና ህዋላ ቀርነታችን የሚሆነው ለዚህም ነው ዋናው መፍትሔ ድህነትና ህዋላ ቀርነትን ማስወገድ የሚሆነው የስርዓትን ችግር ከምንጩ የሚያደርቅ ሀገራዊ ክብርና የዜጎች ክብር የሚያረጋግጥ ይሄ ነውና፡፡

      ቀጠል ያደርግና መፅሓፉ እንዲህ ይላል “ብሔራዊ ክብራችንን ማስጠበቅ የዲፕሎማሲ ስራችን ዋናው መርህ መሆን አለበት “(ገፅ 261) እንዴት ብሎ?! ብሔራዊ ክብር ማስጠበቅ የሚቻለው‘ኮ ብሄራዊ ጥቅም ሲከበር ነው፡፡ ብሔራዊ ጥቅም ማለት ደግሞ ልማታችን ዴሞክራሲያችን ሰላማችን ማስጠበቅና ማስቀጠል ነው፡፡ አለበለዝያ በባዶ ሆድ በባዶ ኪስ ብሔራዊ ክብራችንን ማስጠበቅ የሚባለው ጥቃት መከላከል ሊሆን ይችላል እንጂ በዓለም ፊት መከበር ማለት ኣይሆንም፡፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የድርድር አቅም ሳይኖረን ልናስጠብቀው የምንችለው ብሔራዊ ክብር ትልቅ ውሱንነት አለው፡፡ የተለመደው አጉል ተስፋና መፈክር ሆኖ ይቀራል፡፡ የዲፕሎማሲያችን ዋና መርህ የውጭ ግኑኝነታችን ሁሉ ብሔራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ ማለትም ልማታችንን ዲሞክራሲያችንን ሰላማችንን ብሎም ተነፃፃሪ ሀገራዊ ነፃነታችንን ማስጠበቅ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ ውጭ ብሔራዊ ክብር የለምና

    መፅሓፉ ላይ “እስካሁን ያለው ልምዳችን ዲያስፖራውን በጠላትነት ፈርጆ የሚንቀሳቀስ ነበር፡፡” ይላል (ገፅ 266) የመንግስት ይሁን የኢህአዴግ ፖሊሲ ዲያስፖራውን ሁሉ በጅምላ በጠላትነት የሚፈርጅ ሆኖ አያውቅም ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን በሓይል ለመናድ አልመው አመፅና የብሔር የሃይማኖት ግጭት ሲያቀጣጥሉ የነበሩትን ብቻ ነው በጠላትነት የፈረጀው፡፡ አሁን ከዛ ሓይል ጭምር ወያኔን የማስወገድ ግብ ያለመ ሕብረት ተፈጠረና እሱን ማወደስ ብቻ ተፈለገ፡፡

ክፍል- አምስት

ማጠቃለያ አስተያየትና ሌላ አማራጭ

5.1. ማጠቃለያ አስተያየት -

    ስለ ‘መደመር’ መፅሓፍ ኣጠቃላይ ይዘቱ በተመለከተ ማጠቃለያ አስተያየት መስጠት ተገቢና ጠቃሚ ይሆናል፡፡

5.1.1. ስለ መደመር መሰረተ ሓሳቦች -

     የመደመር ‘ፍልስፍና’ የመነጨበት አንዱ ምንጭ የተፈጥሮ ሕግ መሆኑ የሰው ፍላጎቶች ባንድ በኩል ትስስርና አንድነት በሌላ በኩል ተቃርኖ ያላቸው ቢሆኑም የሁሉም ፍላጎች የሚሟሉት በመደመር ነው ማለቱ፣ ባለፉት አመታት ከ1960ዎቹ ጀምሮ ከውጭ ያመጣናቸው ርእዮቶችና ፖለቲካዊዎች ምንም አልጠቀሙንም ያመጡት ለውጥ የለም ማለቱ፣ መሰረታዊ ዝንፈቶች ናቸው፡፡

      ምክንያቱም ፍልስፍና ሁለ-ገብ አስተሳሰብ ስለሆነ ከማህበራዊ ዕድገት ሕግጋትና ከፖለቲካዊ ኢኮኖሚ መሰረተሓሳብ ይመነጫል እንጂ ከተፈጥሮ ሕግ ሊመነጭ አይችልም፡፡  ከዛ ከመነጨም ፍልስፍና መሆኑ ቀርቶ ስለሰው አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ ይተነትን እንደሆነ እንጂ ስለ ህብረተ-ሰብን የሚገዙ ነባራዊ ሕጎችና ሁኔታዎች መተንተን ኣይችልም፡፡ ሰውን በተፈጥሮ ሕግጋት የሚገመግም የሕብረተ-ሰብ ክፍሎች ጥቅምና ግኑኝነት፣ የፖለቲካውና የኢኮኖሚው ሕጎች የነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታዎች መስተጋብር ሊረዳና ችግሮችንም ሆነ መፍትሔዎችን በአግባቡ ሊለይ አይችልም፡፡ ለዛም ነው የመደመር ዕሳቤ ተፃራሪ ጥቅምና ባህርይ ያላቸውን መደቦች የሕብረተ-ሰብ ክፍሎችን ይደመሩ ብሎ የጉልበተኛ ልዕልና ያሰፍናል የምንለው በመደቦች የተከፋፈለ ሕብረተ-ሰብ  መኖሩን ይክዳል፣ ቅራኔውን ያድበሰብሳል፡፡ በጨቋኞችና በመዝባሪዎች ላይ የሚደረገውን ትግል ያኮላሻል፡፡

       ስለተከተልናቸው  ርእዮቶችና ስለ የሀገራችን ባለሀብት ደካማ መሆን ስለ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መደፍጠጥ ኢህአዴግንና መንግስትን ተጠያቂ ማድረጉ ከሃቅ የራቀ ነው፡፡  ባለፉት ዓመታት የሀገራችን ፖለቲከኞች የተከተልዋቸው የተለያዩ ርእዮቶች ጠቃሚነት ወይንም ጉጂነት መመዘኛው ይዘታቸውና ተግባራዊ ውጤታቸው  መሆን ሲገባው ከውጭ ስለመጡ ነው ብሎ በጅምላ መፈረጅ ሆን ብሎ ለማጥላላት ስለተፈለገ ነው ቢያንስ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዴሞክራሲና ልማታዊ መንግስት በሀገራችን መልካም የልማት፣ የሰላም፣ የፌደራል ስርዓት ጅምር አሳይተዋል፡፡ እንዴት ምንም አልተጠቀምንም ይባላል መደመር አገር በቀል ስለሆነ ብቻ የበለጠ ውጤት ያመጣል ለማለት ሌላውን መደምሰስ ሃቅነትና ቅንነት የጎደለው ጭፍን ፍረጃ ነው፡፡ ግፈኞቹ የመሳፍንትና የደርግ ስርዓቶችን አስወግደናል የመደመር ‘ፈላስፋው’ ግን የነዚህ ስርዓቶችን መወገድ፣ የነገስታቱና የደርግ ኢሰፓ አመራሮችና ካድሬዎች መሸነፍ አልተቀበሉም ይከነክናቸዋል ፋይዳ የሌለው የርስበርስ መገዳደል ብለውታል ውግንናቸው ለነሱ ስለሆነ ነው፡፡

       ለሀገራችን ባለሃብትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች መንግስትና ገዢ ፓርቲው አመቺ ሁኔታ አልፈጠሩላቸውም የኢኮኖሚውና የፖለቲካው ውድድርን የሚያጎለብት በቂ ድጋፍ አላደረጉላቸውም ቢባል ተገቢ ይሆናል እንጂ ለደካማነታቸው ዋናው ተጠያቂ መንግስትና ገዢ ፓርቲን ማድረግ ውንጀላ ነው፡፡ ደካማ የሆኑበት ዋናው ምክንያት ነባራዊ  የፖለቲካዊ ኢኮኖሚው ደካማነትና የራሳቸው እጥረቶች ናቸው፡፡ ባለሀብቱ በርካታው አቋራጭ መንገድ ይፈልጋል ኢኮኖሚውም ለዛ የተመቸ ነውና ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ህዝቡን ከነሱ ጎን የሚያሰልፍ የተሻለ አማራጭ ስላላቀረቡና ጠንክረው ስላልሰሩ ደካማ ሆኑ፡፡ ሃቁ ይሄ ነው፡፡

      የሊበራሊዝም፣ የሶሻሊዝም፣ የአብዮታዊ ዴሞክራሲና የልማታዊ መንግስት ትርጉም በማዛባት የምከርናቸው ያላለፉት ርእዮቶችና የፓለቲካ አማራጮች ጥቅም አልሰጡም አላሻገሩንም በማለት ሌላ አማራጭ ያስፈልገናል የሚል ድምዳሜ ያስቀምጣል፡፡ ያደርጋል፡፡ ጉድለቶችን አስተካክሎ ጥንካሬዎችን አጎልብቶ የተሻለ ውጤት ማምጣት እየተቻለ ያለፈን ሁሉ ጥሎና ደምስሶ እንደ አዲስ ተሰምቶ ተሞክሮ የማይታወቅ የመደመር አማራጭ ዕሳቤ ወይም ፍልስፍና ብሎ ማቅረቡ ተገቢነት የለውም፣ የተሰራውን የሚያፈርስ ነው፡፡

    መደመር ምንድነው ቢባል ዳግም ያለፉትን ድሎች ማስፋት፣ ስህተቶችን ማረም፣ የመጪውን ትውልድ ጥቅምና ፍላጎት ማሳካት ነው ተብሎኣል፣ ይህ ታድያ ግምገማና የወደፊት ዕቅድ እንጂ ፍልስፍና አይደለም ፍልስፍና ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚውን፣ ማህበራዊ እና በህላዊ ሁኔታውን ተፈጥሮንም ጭምር የምትረዳበት የምትተነትንበት አጠቃላይና ሁለ-ገብ አስተሳሰብ ነው፡፡ የመደመር ዕሴቶችና ሳንካዎች ተብለው የቀረቡትም በርካታ ስህተት ያላቸው ናቸው ብልፅግና አንድነት ዕሴቶች ናቸው ተብለዋል ግን ትላልቅ አለማዎች ናቸው፡፡ ዕሴትና አለማን ያምታታል፡፡

     ስለ አንድነታችን ሲናገር ደግሞ የኛ የኢትዮያውያን አንድነት እንዳንለያይ ሆኖ የተጋመደ የተሰነሰለ እና  የተዋሃደ ነው ይላል፡፡ የሚያለያየን መራራ አድልዎና የተለያየ በደል ከመጣም ወደድንም ጠላንም አንድ ሆነን እንቀጥላለን እንጂ መለያየት የለም የሚል የአሃዳዊነት አመለካከት ነው፡፡ አንድ የሚያደርገን ታሪካችን ብቻ ሳይሆን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ካለ ብቻ ነው፡፡ የብሄር ብሄረ-ሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን እስከ መገንጠል መብት  ከተከበረ፣ ራሳቸውን በነፃነት ማስተዳደር ከቻሉ ነው የእምነት ነፃነትና እኩልነት ከተረጋገጠ፣ እንዲሁም መንግስትና ሃይማኖት ከተለያዩና እንዱ በሌላው ጉዳይ ጣልቃ ካልገባ ነው፡፡ በተለይም ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓት ከተጠናከረ ብቻ ነው፡፡

5.1.2. ስለ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራትና ጥገናው ስለ ውጭ-ጉዳይ ፖሊሲ

        የፖለቲካ ስብራታችን የተነተነበት ዕይታ ብዙ መዛባት ያለበት ሆኖ መፍትሔው ኢትዮጵያዊ ዴሞክራሲ ነው ይሉና ይህም በዕርቀሰላም ቁስላችን እናክም፣ ጥፋቱን ያመነ  በይቅርታ ይታለፋል፣ ጥፋቱን ያላመነ በሕግ ይጠየቃል ይሉናል በአንድ ብሔርና በአንድ ፖለቲካ ድርጅት ላይ ያነጣጠረ ፖቲካዊ ዘመቻ እየተደረገ ባለበት ወደ ዘር ማጥፋት የሚያመራ የከፋ  ጥላቻ እየተረጨ ሴራ እየተጠነጠነ ባለበት ሁኔታ ፍትሕና ዕርቅ ሊኖር አይችልም ጎራ የለሽ ዕይታ እንከተል በኢትዮጵያ መደቦች የሉም ሁላችንም እንደመር ይሉናል አለ አግባብ የሚበለፅጉትን ለአድልዎ ለአፈና የቆሙትን አትጥሉ እያሉን ነው፡፡ ታድያ ከነሱ ጋር  ከተደመርን ሙስናን ጥላቻን እድልዎን እንዴት መመከት እንችላለን፡፡

        በሃገራችን ቀደም ብሎ ሀገረ መንግስት ያልተመሰረተው ነገስታቱ በውጭ ወረራና በሀገር ውጥስ ችግር ውጥረት ውስጥ ተጠምደው ፋታ ስላጡ ነው በሕብረተ-ሰብ ውስጥ ሁለት ዓይነት ጭቆና አለ ሰው ወለድና መዋቅር ወለድ ጭቆና ይሉናል፡፡ እነዚህ ሓሳቦች የነገስታትና የስርዓታቸው ጨቋኝና በዝባዥ ባህርይን የሚደብቁ ለነሱ ጥብቅና የሚቆሙ፣ ናቸው፡፡ የጭቆና ምንጭ ገዝዎች ሆነው ሳለ የሰው ክፋትና ግዑዝ ነገሩ መዋቅር የወለዳቸው ናቸው ይሉናል አሁንም በሕብረተ-ሰቡ ውስጥ ያሉትን ቅራኔዎችና መሰረታዊ ምንጫቸውን ሆን ብለው ያድበሰብሳሉ የችግሩ ምንጭ የሆኑት መዝባሪዎችና ዘረኞች እንዲወገዱ አይፈልጉምና፡፡  የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችን ዋናው ትኩረቱና መሰረቱ የሀገር ጥቅም ማስከበር ሳይሆን የዜጋ /የስደተኞች/ ክብር ማስከበርና ግኑኝነት በሆነ መልኩም ይሁን ማስቀጠል ነው ይሉናል፡፡ በዚህ የመደመር ዕይታ ሃገራዊ ጥቅም ኣይከበርም መደመር የሀገር ጥቅም አሳልፎ ይሰጣል፡፡

     ስለሆነም የመደመር ዕሳቤ ቀልባሽ ነው ያለፈውን መልካም የልማትና የሰላም የዲሞክራሲ ጅምር ጉድለቱን አርሞ ከማስቀጠል ይልቅ እሱን የሚያፈርስ ነው ጨቋኝና ተጨቋኝ አለአግባብ የሚበለፅግና ሰርቶ አዳሪውን ፅንፈኛውና ለዘብተኛው ዲሞክራቱን ታረቁ ተደመሩ ብሎ የበዳዮቹ የገዥዎቹ የበላይነት የሚያሰፍን ነው ለነሱ የሚሆን ዕሳቤና ፓርቲ እንዲሁም መንግስት የማፈጥር ነው፡፡ ሰላምና ልማት የማያመጣ ነው፡፡ የኢዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታን በተዛባ መንገድ የሚገመግምና የችግራችን ምንጭ የሰው ክፋትና መዋቅር ወለድ ናቸው ብሎ የሚያድበሰብስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታና ያለፈ ጉዞአችንን በተዛባ መንገድ የሚገመግም ያልሆነ መፍትሔ የሚያመጣ ነው፡፡

            ጎራ የለሽ ዕይታ እንከተል በሀገራችን መደቦች የሉም ብሎ ብዙሃኑ ለመብታቸው ለጥቅማቸው ሲሉ እንዳይታገሉ፣ ኣሜን ብለው ተደምረው እንዲገዙ የሚያደርግ የገዥዎች የፅንፈኞች፣ የአሃዳውያን አመለካከት ነው፡፡ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ስብራት ያለውን ከመጠገን ይልቅ የሚያባብስ፣ ኣለአግባቡ ለሚበለፅጉ የሚመች ሁኔታ የሚፈጥር፣ የአጅና የእግር ስብራቱን ወደ ጨርሶ መቁረጥ የሚያሻግር ነው፡፡ ትሻልን ፈትቼ ትብስን አገባሁ የሚያስብል ነው፡፡ የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች የሚያሰኝ ነው፡፡

      የመደመር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሀገራዊ ጥቅምን ወደ ጎን ትቶ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጥንካሬን መሰረት ያላደረገ ሰማይ ላይ የተንጠለጠለ የዜግነት ክብርና ግኑኝነትን በሆነ መልኩ የማስቀጠል ፖሊሲን ተከትሎ የሀገርን ጥቅም አሳልፎ የሚሰጥ ነው፡፡ ለውጭ ጣልቃ ገብነት ልቅ ፈቃድ የሚሰጥ ነው፡፡ አያሻግረንም!!

           የባሰው ነገር ዳግም በብሔር ተደራጅቶ የብሔር መብትን ለማስከበር መታገል ለአክራሪ ብሔርተኝነትንና ለሀገር ብጥብጥ ጠንቅ ስለሚሆን ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል የሚል ሓሳብ በመፅሓፉ በግልፅ መቀመጡ ነው ይህ ማለት የብሔር ድርጅቶችን ብሎም በማንነት ላይ የተመሰረተ ሕብረ-ብሄራዊ  ፌደራላዊ ስርዓትን አንደ አደጋ ኣይቶ ለማፍረስ በማሰብ የተቀመጠ መንደርደርያ ሓሳብ ነው፡፡ በተግባርም እያየነው ያለን እሱን ነው፡፡ ብሄራዊ ድርጅቶች በጫና ወደ ብልፅግና ፓርቲ በጥድፍያ እንዲገቡ ተደርገዋል፡፡ ከምርጫ በህዋላ ሕገ-መንግስት እንቀይር ተብሎ ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራል ስርዓቱን አፍርሰው በጀኦግራፊያዊ አከላለል ይተኩት ይሆናል፡፡ ከአሃዳውያን ጋር ያለው የብልፅግና ፓርቲና የለውጥ ሓይል ተብየዎቹ አመራሮቹ የጠበቀ ወዳጅነት ከዚህ የጋራ አላማ የሚነሳ ነው፡፡ በትግራይ ህዝብና በህ.ወ.ሓ.ት ላይ እየተደረገ ያለው የጥላቻ የማግለል የመወንጀል ዘመቻም ከዚህ የመነጨ ነው፡፡

    በማጠቃለል የመደመር ዕሳቤ ልማቱንና ጅምር ዲሞክራሲውን የሚቀለብስ አስተሳሰብ ነው፡፡ በመሆኑም-

-      ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት ለማፍረስ አንደመርም!!

-      ልማታዊ መንግስትና የልማት ጅምሩን ለመግታት አንደመርም!!

-      የሀገርን ጥቅም ኣሳልፎ ለመስጠት፣ አንደመርም!!

-      የቂምበቀል የጥላቻ ፖለቲካ ለማራመድ አንደመርም!!!

5.2. ሌላ ኣማራጭ አለ-

          የመደመር ዕሳቤ (‘ፍልስፍና’) ሕብረተሰብን ከመደቦችና ከሕብረተ-ሰብ ክፍሎች አንፃር ሳይሆን ከግለሰቦች ባህርይና ተፈጥሮ አንፃር ብቻ የሚተነትን፣ የመደቦች ይሁን የሕብረተ-ሰብ ክፍሎች የጥቅም አጋርነትና ግጭት የሚደብቅ ምንጭና መፍትሔው ሰው ወለድና መዋቅር  ወለድ  ጭቆና ብሎ የሚያድበሰብስ ብሎም  ጎራ የለሽ ዕይታ ኣንከተል ብሎ ተፃራሪ ጥቅምና አሰላለፍ ያላቸውን በውሸት ዕርቅ የጉልበተኞች የበላይነት ማንገስ የሚፈልግ ነው ብለናል ከዚህ በመነጨም በብሄር ተዳራጅቶ  መታገል ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል በሚል፣ ብሔራዊ ድርጅትንና ብሎም በማንነት ላይ የተመሰረተ ማካለልን ለማፍረስ መንደርደርያ የሚሆነው አቅጣጫ ያስቀመጠ ሆኖአል፡፡ ይባስ ብሎም የሀገራችን ህዝቦች አንድነት እንዳይለያይ ሆኖ የተጋመደ የተሰላሰለና የተዋሃደ ነው፡፡ አንድ ከመሆን ውጭ ሌላ አማራጭ  የለንም  ብሎ ህዝቦች ብሔር ብሔረ-ሰቦች ወደዱም ጠሉም የሓይል አንድነትም ቢሆን አሜን ብለው ተቀብለው በጭቆና በአድልዎ ስር ሆነውም እንዲገዙ በአፅንኦት ይደመድማል፡፡ በመጨረሻም የውጭ ጉዳይ የመደመር ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅምን ሳይሆን ግኑኝነት ማስቀጠሉን የሚያስቀድም የዜግነት ክብርን ማእከሉ የሚያደርግ ይሁን ይላል፡፡ ብሔራዊ ጥቅምን በሁለተኛ ደረጃ በማየት አሳልፎ ይሰጣል የሆነ ዓይነት ግኑኝነት ለማስቀጠል ሲባል ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ መስጠት ተገቢ ነው የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡

     ይህ ሁለ ግን ድህንነትንና ህዋላ ቀርነትን የሚያስቀጥል፣ ለጥቂት አለአግባብ የሚበለፅጉ ባለሃብቶ ጥብቅና በመቆም የሀገርን ጥቅም አሳልፎ በመስጠት አሃዳዊ ስርዓትን በመመለስ የጀመርነውን ልማት ሰላምና ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓትን የሚቀለብስ ነው፡፡ ልማት ኣያመጣም፣ ሰላም ኣያሰፍንም ዘላቂ አንድነት ኣይፈጥርም ቀልባሽ ነው፡፡ የዜግነት ፖለቲካና የግለሰብ መብትን እንጂ የብሔር ብሔረሰቦች መብትን በተሟላ መልኩ   አያረጋግጥም፡፡ መደመር ይሁን የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም /አላማ/ አንድና ያው ስለሆኑ የፓርቲው ፕሮግራም እስከ መገንጠል የሚለውን የቡድን መብት ሰርዞ፣ ልማታዊ መንግስትን አስወግዶ፣ መሬት በመንግስትና በህዝብ ባለቤትነት ሆኖ የተጠቃሚነት መብት ግን ይከበራል የሚለውን አስቀርቶ የስኬታችን ምንጭ የሆኑትን ምሶሶዎች አፍርሶኣል፡፡

       ስለሆነም የመደመር ዕሳቤና የብልፅግና ፓርቲ ፕሮግራም /አላማ/ ለኢትዮጵያ ህዝቦች የማይጠቅም ችግራችን የማይፈታ ብቻ ሳይሆን  የሚያባብስና ጅምር ስኬቶቻችንን  የሚቀለብስ ሆኖኣል በመሆኑም ከዚህ የበለጠ አማራጭ አለ ባለፈው ለስኬት ያበቃንን አቅጣጫ የሚያስቀጥል ጉድለቶቻችንን የሚያርም አዳዲስ ሓሳብም ያካተተ ሌላ አማራጭ ፍሬ ነገሩ ባጭሩ እንደሚከተለው ቀርቦአል፡፡

5.2.1. ምን ዓይነት ዴሞክራሲ ይበጀናል

ሀ- የግለሰብና የቡድን መብቶቻችን በእኩልነትና በተመጋገበ መንገድ የሚያስከብር፤

ለ- የቡድን መብት ሲባል በተሟላ መልኩ የሚተገብር መሆን ኣለበት ማለትም፡-

-      የብሔር ብሔረ-ሰቦችና ህዝቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል የሚያስከብር ይህን መብት እንደ ለመበተን በር ከፋች ሳይሆን እንደ ለዘላቂ አንድነት ዋስትና የሚሰጥ እንደ የባለትዳሮች የፍቺ መብት የሚቀበል መሆን አለበት የሚገለል የሚያኮርፍ ህዝብ እንዳይኖር የተሟላ እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነትን የተማላ ዴሞክራሲን ማጎልበት ግዴታ እንዲሆን የሚያደርግ ይሆናል፡፡

-      ብዝሃነትን በሁሉ  መልኩ /የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የፆታ/ እንደ ፀጋ አይቶ የሚያስተናግድ፤

-      የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር ሙሉ መንግስታዊ ስልጣን የሚያረጋግጥ፣የፌደራል ጣልቃ ገብነት በሕግ የተገደበና ተቋማዊ ቁጥጥር የሚዳረግበት ይሆናል፡፡ 

-      ስለዚህም ፍቱን መተግበርያ መንገዱ ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራል ስርዓት በማንነት ላይ በተመሰረተ ማካለል የሚተገብር፤

-      ክልሎች የራሳቸው የተለየ የማሕበረ-ኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂ የተለየ የአስፈፃሚ አደረጃጀት ሊኖራቸው እንደሚችል የሚቀበል፤

-      አሁን ባለው ሕገ-መንግስት የተደነገጉትን መብቶችና ስልጣን ከመተግበር አልፎ ተጨማሪ ስልጣን ለክልሎች የሚሰጥ

ሐ- ወደ አሃዳዊነት የሚያመራ ሕብረ ሀገረ መንግስት ሳይሆን ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ መንግስት የሚመሰርት፣ የፌደራልና የክልል መንግስታት የየራሳቸው የማይነካ ነፃ ስልጣን ያላቸው ግን የሚደጋገፉና ለጋራ ሀገር የማሰሩ በተቋማት በሕግ አግባብ ብቻ የሚሰሩ እንዲሆኑ ማድረግ፤

መ- ፓርላመንታዊ ስርዓት ጉድለቶቹን አርሞ የሚያስቀጥል በተለይም አስፈፃሚውንና የፍትሕ ስርዓቱን መቆጣጠር የሚያስችለው በቂ ተነፃፃሪ ነፃነት ከገዢ ፓርቲ እንዲኖረውና በተቋም የተደገፈ የሓሳብ ነፃነት የመቆጣጠር ብቃት እንዲኖርው ማድረግ፣

ረ- ዴሞክራሲው በምርጫ ላይ ያተኮረ ለሙሁራንና ለባለሃብቶች ብቻ  የተመቸ ሆኖ እንዳይቀር የህዝብ የተደራጀ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሚያረጋግጥ፣ ለዚህም ሲባል ሲቪክ ማሕበራት ከመንግስትና ከፓርቲዎች ነፃ ሆነው እንዲደራጁና እንዲንቀሳቀሱ የፓርቲ አመራር ያልተሰገሰጉባቸው የሕግ ጥበቃ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ፤

ሰ- ፖለቲካዊ ምህዳሩ በጠንካራ ተቋማትና በሕግ ጥበቃ በነፃ ፍርድቤቶች ተደግፎ እንዲሰፋ ማድረግ፤ የፓርቲና የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና አባላት ወይም ሰራተኞች /ጋዜጠኞች/ ባራመዱት ነፃ ሓሳብና ተጨባጭ መረጃን መሰረት አድርገው በሚያሰራጩት ሓሳብና መረጃ እንዳይጠየቁ ጥበቃ ማድረግ፤

ሸ- በመሰረታዊ የነፃ ገበያ ዴሞክራሲ መርሆችና በሕግ-መንግስት ዙርያ ብሔራዊ መግባባት መፍጠር፤ (በሌሎች ጉዳዮች የሚኖር ልዩነት ተከብሮ)

ቀ- በፍላጎትና በእኩልነት የሚኖሩ ህዝቦች ያሉበት በሕገ-መንግስት የሚተዳደር፣ ብቃትን ማእከል ያደረገ ግን ተዋፅኦን በተቻለ መጠን ያመጣጠነ የአገራችን ህዝቦች የሚመስል የመከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራል ፖሊስና፣ የፌደራል ቢሮክራሲ መገንባት የክልልና የፌደራል ቢሮክራሲና የትምህርት ጥራት ደረጃም ሆነ መሰረታዊ አገልግሎቶች ተቀራራቢ ሀገር አቀፍ ስታንዳርድ /መመዘኛ/ ያሟሉ እንዲሆኑ ማድረግ፣ በዚህ አማካኝነት አንድ የፖለቲካ ማሕበረ-ሰብ መፍጠር፤

        እነዚህ እላይ የተዘረዘሩ ነጥቦች ያካተተ፣ ለሃገራችን ተስማሚ የሆነ የህዝብወገንተንኘት ያለው ግን ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት የሚያይ ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚና ተሳታፊ የሚያደርግ ዲሞክራሲ ያስፈልገናል፡፡ ብዙዎቹ ነጥቦች አሁን ስራ ላይ ባለው የሀገራችን ሕገ-መንግስት የሰፈሩ ናቸው፡፡ ይህ ዓይነት ዴሞክራሲ ልማታዊ ዴሞክራሲ ይባላል፡፡ ከመደመር ዴሞክራሲ፣ ከሊበራል ዴሞክራሲ ከሶሻል ዴሞክራሲ በዓይነቱ የተለየና በእጅጉ የበለጠ ለብዙሃኑም የሚተርፍ ተራማጅ ዴሞክራሲ ነው፡፡

5.2.2. ምን ዓይነት ልማት ይበጃናል-

ሀ- በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ሕግጋት መሰረት የልማታዊ መንግስት አመራር የሚሰጥበት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ 

      ኢኮኖሚያችን ገና ጀማሪ፣ ገበያችን ገና በውድድር በመረጃ ስርዓት በተቋማት ያልተጠናከረ ባለሃብቱ ገና ያላደገና የውድድር ልምድ ያላዳበረ ስለሆነ ይህን ክፍተት የሚያካክስ የመንግስት አመራርና ጣልቃ ገብነት ያለበት ኢኮኖሚ ያስፈልገናል፡-

የልማታዊ መንግስት አመራርና ጣልቃ ገብነት ያለበት ሲባል ምን ማለት ነው፡-

-      የልማት የትኩረት አቅጣጫ በየዕድገት ምዕራፉ ምን መሆን እንዳለበት እየለየ የሀብት /የኢንቨስትመንት/ ፍሰት በውድድር ተደግፎ ወደየትኛው የኢኮኖሚ ዘርፍና ንኡስ ዘርፍ መሆን እንዳለበት አቅጣጫ ያስቀምጣል፡፡ ኢንቨስትመንት ወደዛ እንዲፈስ የተለያየ ማበረታቻ ይሰጣል /በምርምር፣ በብድር፣ በስልጠና፣ በመሰረተ ልማት፣ በግብርና ታክስ/ ያኔ ቅድሚያ የማይሰጣቸውን የኢኮኖሚው ዘርፎችና ንኡስ ዘርፎች ይህ ልዩ ማበረታቻ አያገኙም፤

-        ባለሃብቱ ሊሰራው የማይችል ወይም የማይፈልግ ስትራቴጂያዊ ፋይዳ ያለው የምርት ይሁን የአገልግሎት ትልቅ ኢንቨስትመንት መንግስት ዓቅሙ በፈቀደው መጠን ጣልቃ ገብቶ ኢንቨስት በማድረግ ባለቤት ሆኖ ያካሄደዋል፡፡ ይህን ስራ የሚሰሩ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ግን ሁሉም ሁልግዜ ከባለሀብት ተቋማት ጋር በእኩል ዓይን የሚታዩ የተለየ የአድልዎ ድጋፍ የማያገኙ በውድድር በተጠያቂነት በግልፅነት የሚሰሩ ገበያ የሚገዛቸው እንዲሆኑ ይደረጋሉ፡፡ አትራፊና ተፈላጊ ሲሆኑ፣ ባለሃብቱም ዓቕሙ ሲኖረው ለባለሃብት ይተላለፋሉ፤ መንግስትወደሌላ የገበያ ጉድለት ያለበት ይሸጋገራል፡፡ መንግስት በያዛቸው የልማት ድርጅቶች ሊታይ የሚችል የመንግስት ጉድለት /ሙስና፣ ብክነት፣ የብሔር ልጅና  ዘመድ አዝማድ መሰግሰግ/ ለመቆጣጠር ድርጅቶች ብቃትን ማእከል ያደረገ በውድድር የሚካሄድ ቅጥርና ግዢ እንዲፈፀሙ በተጠያቂነት እንዲሰሩ ማድረግ፡፡

 

-        ፖለቲካዊ ኢኮኖሚው አለአግባብ ለመበልፀግ የተመቸ ለውድድር ያልተመቸ ስለሚሆን ይህን እግር ለመፍታት ልማታዊ መንግስት አለአግባብ የመበልፀግያ መንገዶችን እያጠበበ ብሎም እየዘጋ፣ ውድድርን እያጎለበተ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚውን በመሰረቱ የሚቀይር ልማታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ የሚያነግስ ስራ ይሰራል፤ አለአግባብ መከበርን በዋናነት በአስተዳደራዊ እርምጃ ሳይሆን ውድድርን በማጎልበት፣ የሕግ የበላይነትን በማስፈን ተወዳዳሪ እሴት ፈጣሪ ሕግ አክባሪ ባለሃብትና ሰርቶ አዳሪ ህዝብን ይፈጥራል፤

 

 

-        ስለሆነም ሦስቱን የልማታዊ መንግስት ተልእኮዎች የሚፈፅም ማለትም አንደኛ ፈጣንና ቀጣይ ልማት ማምጣት፣ ሁለተኛ አለአግባብ መበልፀግያ መንገዶችን እየዘጋ ልማታዊ የውድድር የሰርቶ መኖርና መጠቀም ምቹ ሁኔታንና ልማታዊ ባለሃብትን ማበራከት፣ ሶስተኛ ልማቱን ፍትሓዊ ማድረግ ያሳካል፡፡ ይህን የመንግስት አመራር ስኬታማ ማድረግ የሚችል ብቁ ኣመራር ቀልጣፋና ውጤታማ ቢሮክራሲያዊ መዋቅር ይፈጥራል፡፡ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እየቀነሰ እንዲሄድ ያደርጋል፡፡

ለ- ባለሃብቱ የኢኮኖሚ ሞተር የሚሆንበት የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ መገንባት፡-

    ባለሃብቱ ሞተር ይሆናል ሲባል አራት አበይት ነገሮች ያጠቃልላል፡፡

-        ዋናው ኢንቨስት አድራጊ ባለሃብቱ ይሆናል ሰፋፊ እርሻዎች፣ ፋብሪካዎች የማዕድን ልማት፣ አገልግሎቶች ባብዛኛው በባለሀብቱ ይሰራሉ፤

-        ትልቁ ስራ ፈጣሪ ሰው ሓይል ቀጣሪ ባለሃብቱ ይሆናል፤

-        ትልቁ ግብርና ታክስ ከፋይ ባለሃብቱ ይሆናል

-        ትልቁ የቴክኖሎጂ አቅም የሚያከማችና የሚፈጥር ባለሃብቱ ይሆናል፤

ሐ - ልማቱ የጥቂት ባለሃብቶችና አከባቢዎች ልማት ሳይሆን ባለሃብቱም ሰፊው ህዝብም ከተማውም ገጠሩም፣ አርሶ አደሩም ለብ አደሩም አርብቶ አደሩም ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበት ይሆናል ይህን ተግባራዊ የሚያደርግ የመሰረተ ልማት ፍትሓዊ ስርጭት የፌደራል በጀት ድጎማ፣ ይኖራል፡፡ ህዝቡ የድጎማ ተመፅዋች ሳይሆን የማምረት አቅም ተፈጥሮለት /በስልጠና በብድር፣ በመሬት አቅርቦት/ ሰርቶ አዳሪ አምራች እንዳይሆን ይዳረጋል፡፡

       ይህ የልማት አማራጭ የልማታዊ መንግስትና የልማታዊ አስተሳሰብ መሪነትን ያረጋገጠ የልማታዊነት አቅጣጫ ይባላል፡፡ በሰሜን ምስራቅ ኤስያ ተአምር የሚባልለት ዕድገት ያመጣ፣ በኢትዮጵያም ተስፋሰጭ ፈጣን ልማት ያመጣ ኣማራጭ ነው ጉድለቶቹን አርም አጠናክሮ የማስቀጠል አማራጭ ነው እዚህ የቀረበው፡፡

5.2.3. ምን ዓይነት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ይኑረን?

      ዋናው የውጭ ግኑኝነት ፖሊሲያችን ትኩረትና ምሰሶ ሀገራዊ ጥቅምን ማእከል ያደረገ፣ በውስጣዊ ጥንካሬያችን የሚመሰረት እሱን የሚያገለግል ከውስጥ ወደ ውጭ የተቃኘ ተጋላጭነታችንን በፍጥነት የሚቀንስና የሚያከስም መሆን ይኖርበታል፡፡

      በዚህ ላይ ተመስርቶ ከሁሉም አገሮች ጋር በጋራ ጥቅም እና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግኑኝነት ለመመስረት ጥረት የሚያደርግ ግን ደግሞ ለቀጠናችን ልዩ ትኩረት የሚሰጥ ግኑኝነት ማድረግ ይሆናል፡፡

          በውስጣዊ ጥንካሬያችንና ተፈላጊነታችን ላይ ተመስርቶ የሀገርና የዜጎች ክብርና መብትን በቀጣይነት የሚያጎለብት፣ የማስፈፀም አቅምን የሚያጠናክር ይሆናል፡፡

አገራችንን ከብተና ለማዳን እንተባበር!!

ሕብረ-ብሄራዊ ፌደራላዊ ስርዓታችንን ለማስቀጠል እንታገል!!

የኢትዮያ ህዳሴን እውን እናድርግ!!

ሰላምና አንድነት ለኢትዮጵያ ህዝቦች!!!

 

 

Back to Front Page