Back to Front Page

ጎንደሬው በረከት ሐገሩን ይወዳል

ጎንደሬው በረከት ሐገሩን ይወዳል

እኔ ከኢህአዴግ የኢትዮጵያን ህዝብ እወዳለሁ በረከት ስምዖን

ተፈሪ መኮንን 03-10-20

ችላባይነት (indifference) ወዳጅን የሚያጠቃ፤ ጠላትን የሚሸልም ድርጊት ነው፡፡ [የጠላቶቻችን ወዳጅ ነው፡፡] ችላባይነት ለአጥቂ እንጂ ከቶ ለተጠቂ አጋር ሆኖ አያውቅም፡፡ ችላባይነት አጥቂን እንጂ፤ አስታዋሽ እንደ ሌለው በተረዳ ጊዜ የግፍ ሸክሙ የሚበረታበትን ተጠቂ ደግፎ አያውቅም፡፡ ታዲያ በአንዲት ክፍል ታስሮ የተቀመጠ የፖለቲካ እስረኛ፤ በረሃብ አንጀቱ የታጠፈ ህጻን እና መጠጊያ ያጣ ስደተኛ የተሸከሙትን መከራ መዘንጋት የግፍ ግፍ ነው፡፡ አንዲት ትልስ ትልስ የምትል ደካማ የተስፋ ጭላንጭል ፈጥሮ እነዚህ ሰዎች የተሸከሙት መከራ ቀለል እንዲልላቸው አለማድረግ እና ከብቸኝነት ሸክማቸው ለአፍታ እንዲያርፉ አለማድረግ፤ ግፉአንን ከሰው ልጆች የህሊና ግቢ ገርፎ አስወጥቶ ስደተኞች እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ግፉአን ሰው የመሆን ክብርን እንዲያዩ አለማድረግም፤ የሰውነትን ክብር እና ፀጋ ማራከስ ነው፡፡ ስለዚህ ችላባይነት ሃጢአት ብቻ አይደለም፡፡ በግፉአን ላይ የሚሰነዘር የቅጣት ዱላም ነው፡፡ ሠናይን ከእኩይ ለመለየት ሰፊ ጥረት ያደረግው ይህ ሊሰናበተን የተዘጋጀው ምዕተ ዓመት ያሰተማረን አንድ ሁነኛ ትምህርት ይኸው ነው፡፡

Elie Wiesel

ነገረ ሥራው እንደ ጾም ያለ ነው፡፡ ዛሬ ጾሙን ልገድፍ ነው፡፡ ጾሙን ስገድፍ፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ አድባር የመስዋዕት በግ የሆነውን በረከት ስምዖንን አነሳለሁ፡፡ በረጅም የጋዜጠኝነት ሥራ ዘመኔ፤ እንዲህ ዓይነት ጽሑፍ ጽፌ አላውቅም፡፡ አንዲት ለአለቃ ታዬ የተጻፈች ግጥም እንዲህ ትላለች፡፡

ወፍ ትጠመዳለች፣ በእምር ታህል ጥሬ፤

እንደሞኝ እንስሳ፣ እንደማያውቅ አውሬ፤

ተሚያጠፋ መብል፣ ተጠንቀቅ አገሬ

ለህዝብ የሚጠቅም፣ ከልቤ መክሬ፤

እነሆ በገሃድ፤ ተናገርኩኝ ዛሬ፡፡

(አድዋ ነገስት፣ 1963)

Videos From Around The World

ይህ ጽሁፍ የተጻፈው በረከት በታሰረ ሣምንት ነበር፡፡ አለመታደል ሆኖ የአቶ በረከትን ያህል ታስሮ ቆየ፡፡ ጽሑፉን የጻፍኩት ለበረከት ጥብቅና ለመቆም አይደለም፡፡ የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ (ከ2005 እስከ 2010) የስብሰባዎች ወግ በተሰኘ አንድ መጽሐፍ እንደ ተጠቀሰው፤ አቶ በረከት እኔ ከኢህአዴግ [በበለጠ] የኢትዮጵያን ህዝብ እወዳለሁ (ገጽ፣ 121) እንዳለው፤ እኔም ከአቶ በረከት በበለጠ ሐገሬን እወዳለሁ፡፡ ኢትዮጵያን እና ህቦችዋን የሚዱ ሁሉ ወዳጆቼ፤ ኢትዮጵያን እና ህዝቦችዋን የሚጠሉ ሁሉ ጠላቶቼ ናቸው፡፡

እዚህ ላይ፤ ሐሳቤን ተነጻጻሪ የታሪክ ቁም ነገር በመጥቀስ ማስኬድ እፈልጋለሁ፡፡

ተነጻጻሪው የታሪክ ቁምነገር ነጋድራስ ገብረህይወት ባይከዳኝን የሚያስታውስ ነው፡፡ ስለ አቶ በረከት መልካም ነገር ለማንሳት በወሰንኩባት በዚህች ቅጽበት፤ የነጋድረስ ገ/ህይወት ባይከዳኝን ሸክም መሸከሜን አውቃለሁ፡፡ እንዲህ እንደኔ በጥፍር ቆሞ የመናገር የሠናይት ዕዳ የወደቀባቸው ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ የምኒልክ ዙፋን ወራሽ ለሆነው ለልጅ ኢያሱ ምክር እንድትሆን አስበው የጻፏት አንዲት መጽሐፍ አለቻቸው፡፡ ጥልቅ ዘመናዊ እሳቤዎችን በያዘችው በዚያች አጭር እና የመጀመሪያ መጽሐፋቸው፤ የአጼ ምኒልክን አስተዋጽዖ ለመገምገም ይሞክራሉ፡፡

ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ የየጁ የላስታ፣ የጎጃም እና የሸዋ መኳንንት ስለ አጼ ምኒልክ የነበራቸውን የተሳሳተ (በጎ ወይም መጥፎ) አመለካከት እያነሱ ጎጃም እንዲህ እንዲህ ይላል ብለው ይዘረዝሩና በማሳረጊያው እውነት ብለው ይደመድሙታል፡፡ የጁ እና ላስታ እንዲህ እንዲህ ይላሉ ብለው ይጠቅሱና እውነታቸውን ነው ብለው ያረጋግጣሉ፡፡ አሌ የሚሉት የትግራይ እና የሸዋ ሰዎችን ሐሳብ ነው፡፡

አጤ ምኒልክን የማውቃቸው ሰው ግን በብዙ ክፉ ነገር ያማቸዋል፡፡ አሁን ድንገት አንድ መኮንን ታሞ በሸዋ መሬት ቢሞት እግዚአብሔር ገደለው አይባልም -- ነገር ግን ያጤ ምኒልክ መድኃኒት፡፡ የደንቆሮ ሕዝብ ንጉሥ መሆን ያንድ ወገን ጥቅሙ ብዙ ሳለ ሐሜት ያመጣል፡፡ ሌላስ ይቅርና ሰማይ ዝናብን ባይሰጥ እርሻም ብዙ አላፈራ ቢል ትምህርት የሌለው ህዝብ በንጉሡ ያመካኛል ይላሉ፡፡

አያይዘውም፤ እንዲሁም ትግሬ ባጤ ምኒልክ ተጎዳ ቢባል ሀሰት ነው፡፡ እርስ በርሱ መስማማት ስላጣ ተበላሸ እንጂ፡፡ ትግሬን የሚያህል ትልቅ ያርበኞች ነገድ እርስ በእርሱ ከተስማማ ዘንድ ሊጎዱት አይቻልም፡፡ አጤ ምኒልክ ግን ባንዲት ነገር ሊታሙ የተገባ ነው በማለት ድንቅ ሐተታ ያስከትላሉ፡፡ ከዚያም እንግዴህ ከፀሐፊው ልብ ውስጥ ፍርሃት ተነሣ የሸዎችን ሐሳብ ሊመረምር ነውና፡፡ ዘመናይ ሁሉ ሊያመሰግኑት እንጂ ሊወቅሱት አይወድም፡፡ ነገር ግን ሰውን ፈርቶ እውነትን የሚሸሽግ ሰው እንደ ወንድ ይቆጠራልን? መንግስቱንም የሚወድ ሰው ያ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው አይደለም ጥፋቱን ይገልጥለታል እንጂ በማለት ወደ ጀመሩት ምርመራቸው ይመለሳሉ፡፡

ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ አጼ ምኒልክ የልማት ነገር የሰሩት ወደ መጨረሻው ዘመናቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ አጤ ምኒልክ ሞት የሌለባቸው ይመስል፤ ብዙውን ጊዜ በከንቱ አሳልፈው ወደ መጨረሻው ለሐገር ዕድገት የሚበጅ ስራ መሥራታቸውን ይገልጻሉ፡፡ አጤ ምኒልክ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመለወጥ አልሰሩም፡፡ ህዝቡ እምዬ ምኒልክ እያለ የሚጠራቸው ባህል እና ወጉን አክብረው ስለያዙት እንጂ፤ ለዕድገት የሚበጅ ጎዳና እንዲከተል ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ እምዬ የሚል መጠሪያ አያገኙም ነበር ይላሉ፡፡ እናም በአስረጅነት የሚጠቅሱት የአጼ ቴዎድሮስን ታሪክ ነው፡፡

አጼ ቴዎድሮስ የኢትዮጵያን ህዝብ ለመለወጥ እውነተኛ ጥረት ማድረጋቸውን የሚናገሩት ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ ህዝቡ ዓይንህ ለአፈር ብሎ መቅደላ አምባ ላይ ብቻቸውን እንዲቀሩ አድርጎ ለእንግሊዝ ወራሪ ጦር አሳልፎ እንደ ሰጣቸው ያወሳሉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስም ራሷ እንግሊዝ በላከችላቸው ሽጉጥ ራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡ እናም ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ ሐገሩን ለመለወጥ የሚሰራ መሪ ካለፈ በኋላ ነው እንጂ በህይወት ዘመኑስ አይመሰገንም ብለው ይደመድማሉ፡፡ አዎ አጼ ቴዎድሮስም ያገሬ ሰው ሥራት ግባ ብለው እምቢ ብሎ ተጣላኝ ሲሉ ሐዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ሐገርን ለመለወጥ የሚተጉ መሪዎች በህዝባቸው እንደማይወደዱ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ እንደኔ የአቶ በረከት ነገርም ከዚህ ይመሳሰላል፡፡

ገ/ህይወት ባይከዳኝ፤ እስከ ዛሬ ድረስ ሳይወዱ ሩቅ አገር ተሰደው ወይም አበሻችን ከሚመጡ ፈረንጆች ጥቂት ተምረው ያገራቸውን መንግስት ሊጠቅሙ የሚፈልጉ ወንድሞቻችን ፕሮቴስታንት፣ ካቶሊክም፣ መናፍቃን፣ የሌላ መንግስት ሰላዮች እየተባሉ ሲራቡ ሲከሰሱም እናይ የለምን፡፡ የነዚያን መከረኞች ስም ስንት ብለን እንቁጠር፡፡ የሚከተሉት የሁለት ሰዎች ስም ግን እንዲወሱ የግድ ነው፡፡ እነሱም ከንቲባ ገብሩና አለቃ ታዬ ናቸው፡፡ ሶስት ዓመት ሙሉ አዲስ አበባ ላይ ስቀመጥ እንደነዚህ ሁለት ሰዎች አድርጎ መንግስቱን] የሚወድ አላየሁም፡፡ እጅግ ያሳዝናል፡፡ የነሱን ዕድል ያየ ሰው የኢትዮጵያ መንግስት [ህዝብ] ለወዳጁ አይጠቅምም ብሎ ተስፋ ይቆርጣል ይላሉ፡፡

እናም እርሳቸው እንግዲህ የሸዋን ነገር ላነሳ ነው ልቤ ፈራ እንዳሉ፤ ዛሬ ስለ አቶ በረከት፤ በጥቅሉ ስለ ኢህአዴግ መልካም ነገር ለማንሳት የሚፈልግ ሰው እንግዲህ ይህን ነገር ላነሳ ነው ልቤ ፈራ ማለት ይኖርበታል፡፡ ሆኖም የበረከት ምኞት የኢትዮጵያ ምኞት ነው፡፡ ሰላም፣ ልማት፣ ዴሞክራሲ እና አንድነት ነው፡፡ ይህ ምኞት እውን መሆን አለመሆኑ ላይ መከራከር እንችላለን፡፡ በምኞቱ ግን የኢትዮጵያ ምኞት ነበር፡፡ ታዲያ አለመታደል ሆኖ፤ ደረቅ የአስታ እንጨትን አንድ ቦታ ላይ ለረጅም ጊዜ ፈግፍገን እሣት ለማግኘት እንደሚቻለው፤ የበረከትን ሥም ደጋግሞ በመፈግፈግ የጥላቻ እሣት ለመፍጠር የተቻለ ይመስለኛል፡፡ ግን እሣት ከሚፈጠርበት ቦታ ውጭ ያለው የእንጨቱ ክፍል አሁንም ቀዝቃዛ እንደሆነ ነው፡፡ እኔ እሣቱን ለማጥፋት አልሞክርም፡፡ ምክንያቱም ከንቱ ልፋት መሆኑን አስቀድሜ አውቀዋለሁ፡፡ ግን የእንጨቱ ቀዝቃዛ ክፍል ምን እንደሚመስል ለማየት ሞከርኩ፡፡ አየሁ፡፡ በረከት ሐገሩን ይወዳል አልኩ፡፡

ሆኖም ጊዜው ወጣት ድመቶች፤ አዛውንት አይጦችን የሚያሳድዱበት ጊዜ ነው፡፡ ስለዚህ ትኩሳት አለ፡፡ አዛውንቶቹ አይጦች ውለታው ብዙ የእግዚአብሔር፤ አመስጋኝማ ቢኖር ይላሉ እንጂ የሚሰማቸው አላገኙም፡፡ ሞገደኛ ነው ደፋር ዳኛ፣ ሁሉን አረገው መንገደኛ ይላሉ፤ ታዛቢዎች፡፡ በርግጥ አቶ በረከት እና ድርጅቱ ብአዴን (አዴፓ) ወይም ኢህአዴግ ያጠፉት እና የተሳሳቱት መኖሩ አያጠራጥርም፡፡ ታዲያ ይህ ምን ይገርማል፡፡ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት እንዳሉት ነው፡፡ እንዲህ ይላሉ፤

ራስ እና ጃንሆይ አሁን ተታለሉ፡፡ ወደፊት ገና ብዙ መታለላቸው አይቀርም፡፡ የኢትዮጵያ ዕድሏ መቼም ይኸው ነውና፡፡ መታለልና በከንቱ ማለቅ . (ገጽ፣ 63) ራስ መኮንን እና አጤ ምኒልክ በዘመናቸው የሰሩት ሥራ ሊደነቅላቸው የተገባ ነው፡፡ ነገር ግን፣ ስህተታቸውን በኋላ እየገመትኩት መገረሜ አልቀረም፡፡ ይሁን እንጂ፣ የዚያን ጊዜ ዕውቀት እና ኃይል በማነሱ ይቅርታ ሊደረግላቸው የተገባ ነው፡፡ እነሱ በደከሙበት ሥራ ተጠቅመናል፡፡ በስህተቶቻቸውም አደጋ ተቀብለንበታል፡፡ እኛ ደግሞ በተራችን እንደዚሁ ማድረጋችን አይቀርም (ኦቶባዮግራፊ (የህይወቴ ታሪክ) ገጽ፣ 73)፡፡

አቶ በረከትን በጥላቻ እና በወቀሳ የሚያነሳው ሰው ብዙ በመሆኑ፤ በረከት ሐገሩን እና ህዝቡን የሚወድ፤ ታታሪ፣ የማይቆለል፣ የተሰጠውን አደራ እና የህዝብ ንብረት አክብሮ የሚይዝ፣ በሙስና እጁ ያልቆሸሸ ሰው መሆኑን ለመመስከር የሚያስችል ቅርበት ያለው ሰው የሚያውቀውን ለመናገር ቢነሳ፤ አሁን ካለው የስሜት ስካር አንጻር ልቤ ፈራ ቢል እውነቱ ነው፡፡ ሰው ኤቀበላውም፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ግለትን የሚከተል የፖለቲካ ጉዳይ እንጂ፤ ስክነትን የሚጋብዝ የታሪክ አጀንዳ አይደለምና፡፡

ቀደም ሲል የጠቀስኩት መጽሐፍ፤ የኢህአዴግ የቁልቁለት ጉዞ (ከ2005 እስከ 2010) የስብሰባዎች ወግ የሚለው መጽሐፍ ከ2005 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት በህወሓት እና በግንባሩ (ኢህአዴግ) ስብሰባዎች ተሳታፊ በሆኑ ብርሃነ ፅጋብ የተባሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የተዘጋጀ ሲሆን፤ አቶ በረከት ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለውጥ ያስፈልገናል የሚል ጥያቄ ያነሳ እንደነበር ያመለክተናል፡፡ ፀሐፊው አቶ ብርሃነ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት በኋላ ፈጣን የቁልቁለት መንገድ መጓዝ ጀመረ የሚሉት ኢህአዴግ በሚያካሂዳቸው የምክር ቤት ጉባዔዎች በመገኘት ያዩ - የሰሙትን ለመጻፍ ሞክረዋል፡፡ ፀሐፊው፤ ዘወትር በሸፍጥ ፍልሚያ ተወጥረው ይጠናቀቁ በነበሩት በእኒያ ጉባዔዎች ይቀርቡ የነበሩ ሐሳቦችን አሳይተውናል፡፡ እውነቱን አሳይተው አሳዝነውናል፡፡

ዛሬ የለውጥ አደናቃፊ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው እንደ አቶ በረከት ስምዖን፣ ታደሰ ካሣ፣ ጌታቸው አሰፋ፣ አቦይ ስብሐት፣ አዲሱ ለገሰ፣ ህላዌ ዮሴፍ፣ ስዩም መስፍን ወዘተ ያሉ ሰዎች ገና ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ለውጥ ያስፈልገናል የሚል አጀንዳ ያራምዱ እንደ ነበር የአቶ ብርሃን መጽሐፍ አሳይቶናል፡፡

የመጽሐፉ ደራሲ፤ አቶ በረከት ከሥራ አስፈጻሚው ኮሚቴው ድምዳሜ በተለየ መልኩ ፊት ለፊት መግጠም ጀምሯል (ገጽ፣ 51) ይለናል፡፡ በርግጥ እርሱ ራሱ አቶ በረከትም በሁለተኛው መጽሐፉ (ትንሳዔ) ለውጥ እንዲመጣ ሲታገል መቆየቱን ነግሮናል፡፡ ሆኖም በጉባዔው ተሳታፊ ካልሆኑ ሰዎች ቃሉን አምኖ ለመቀበል ዝንባሌ የሚኖራቸው ጥቂት ሰዎች ይመስሉኛል፡፡

አቶ በረከት በሚያቀርባቸው ሐሳቦች ከጥቂቶቹ ሌቦች እና ለሥልጣናቸው ብቻ የሚጨነቁ [ሰዎች] ካልሆኑ በስተቀር አብዛኛው የምክር ቤቱ አባላት ይቺን አገር እና ህዝቧን በከፋ የችግር አረንቋ ውስጥ ከምንጥል በግላችን እና በሥልጣናችን የሚመጣን አደጋ መቀበል አለብን የሚል አስተሳሰብ መፍጠር እንደቻለ ፀሐፊው አንስተዋል፡፡ በዚህ የተነሳ፤ ፍርጥርጡ ወጥቶ መዳን ይሻላል የሚል ስሜት መጠናከር ቢጀምርም ከሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት የሚያዩትን ስሜት እያጤኑ፤ በአድርባይነት፣ የሐብት ምንጭ አድርገው የሚያዩትን ስልጣንን ለማስጠበቅ በትግሉ መግፋት እየተሳናቸው፤ የጥፋት እንጂ የመፍትሔ አካል መሆን አለመቻላቸውን ያሳየናል፡፡

አቶ በረከት ስምዖን የቆየው የምርጫ ህግ እንዲሻሻል እና የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲው እንዲጠናከር፤ . ኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ የክልል እና የፌዴራል ምክር ቤቶች አሸናፊ እየሆነ መሄዱ ጣጣው እንደሚበዛ ለመረዳት ችለው ነበር የሚሉት ፀሐፊው፤ .አቶ በረከት በ2007 ዓ.ም በሚካሄደው ምርጫ ዕቅድ ውይይት ተመስርተው አስተያየት.. ሲያቀርቡ በምርጫ 99% ወንበር አሸንፈናል ብለን ተቀምጠን መኖር ጣጣ አለው፡፡ እና የምርጫ ህጉን ብናሻሽለው ይበጀል በሚል ጀምረው፤ አሁንም ሁሉንም ወንበር በመያዝ ሃትሪክ ለመስራት ነው የምንሰራው ወይስ የምናሻሽለው ነገር አለ? የሚል ጥያቄ መሰል ተቃውሞ አሰምተዋል፡፡ አቶ በረከት የምርጫ ቦርድ እና ሚዲያን ኒውትራል እና ቀጥተኛ ብናደርገው፤ የውጭ አገር ታዛቢዎች የመጋበዝ ጉዳይ ደግመን ብናየው የተሻለ አይሆንም ወይ? (ገጽ፣ 86) ይል እንደበር ይነግረውናል፡፡

ምንም ተባለ ምን አቶ በረከት የፍልሚያውን በር በድፍረት ከፍተዋል (ገጽ፣ 86) የሚሉት ፀሐፊ፤ በአዲሱ እና በነባር አመራሮች መካከል ያለው ሽኩቻ፤ ደፈጣ፣ መቋሰል፣ መናናቅ እና መፋለም እየተጠናከረ መሄድ እንጂ መሻሻል አለማሳየቱንም ነግረውናል፡፡ ታዲያ ይህን መጽሐፍ የሚያነብ ሰው፤ አቶ በረከት ትግሉ አሁን በምናየው መልክ መጠናቀቁን ከተመለከተ በኋላም የተሰጠውን የአምባሳደር ሹመት ተቀብሎ ወደ ቤልጀም ለመሄድ ባለመወሰኑ ሊገረም ይችላል፡፡

አቶ በረከት ከአንድ የሐገር ቤት የሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ እንደ ጠቀሰው፤ ቤልጄም አምሳደር ሆኖ እንዲሄድ ጥያቄ እንደ ቀረበለት ገልፆ፤ ሐገሪቱ በዚህ ዓይነት ውስጥ እያለች ወደ ውጭ መሄድ አልፈልግም፡፡ እዚሁ ሆኜ ከህዝቡ ጋር የሚመጣውን ነገር እቀበላለሁ ሲል ተናግሮ ነበር፡፡

ከዓመት በፊት እንዲህ ያለ ፈተና የሚጋብዝ ጥያቄ ለዶ/ር መረራ ጉዲና ቀርቦላቸው ነበር፡፡ ዶ/ር መረራ ጉዲና ከአንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድን አመራር የመዳኘት ጥያቄ ቀርቦላቸው፤ መሪዎች መታየት ያለባቸው በታሪክ ሚዛን ነው አሉ፡፡ በዚህ ዓይነት ከዳኝት ለመራቅ ሞከሩ፡፡ እናም እርሳቸው እንደ ብዙዎች ሰዎች፤ ዶ/ር ዓቢይን እንደ መሲህ ለማየት እንደማይፈልጉ ተናገሩ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ የሚጋጩ ህልሞች ያላቸውን የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች ፍላጎት አጣጥሞ ሐገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመምራት ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህን ኃላፊነታቸውን በአግባቡ የመወጣት ብቃታቸውን የሚፈታተኑ በርካታ መሰናክሎች እንደተጋረጡባቸው እና ይህንም ፈተና ማለፍ መቻል - አለመቻላቸው የሚታየው በታሪኩ መደምደሚያ እንጂ በታሪኩ መጀመሪያ አለመሆኑን ገለፁ፡፡

ስለዚህ አቶ በረከት በታሪክ ዳኝነት የሚያገኘውን ፍርድ አሁን ለመናገር አይቻልም፡፡ በፖለቲካ ስሌት ግን እንኳንስ የፖለቲካ ባላንጣዎቻቸው እና ተራ ዜጎች፤ የገዛ ጓዶቻቸውም አምርረው ሲረግሟቸው እየሰማን ነው፡፡ በርግጥ ዶ/ር ዓቢይ አህመድ ወደ ሲመጡ ስለ ቀድሞ መሪዎች ከተናገሩት ነገር ለየት ያለ አንድ አስተያየት፤ ከዓመት በፊት በተካሄደ አንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአዘጋጀው የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ የፊርማ ስነ ስርዓት ላይ ፓርቲያቸውን ወክለው የተገኙት ዶ/ር ዓቢይ፤ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች በሥነ ሥርዓቱ ያደረጉትን ንግግር መነሻ አድርገው አስተያየት ሲሰጡ፤ ኢህአዴግ ለ17 ቀናት ራሱን በገመገመበት መድረክ፤ አሁን የምናጥላላቸው ሰዎች ጭምር፤ ለዴሞክራሲ ስርዓት እሴቶች ታምነው፤ በድምጽ ብልጫ ሲሸነፉ የማይደግፉትን ውሳኔ ሳያቅማሙ ተቀብለው ወጥተዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች ያን ውሳኔአችንን በወታደራዊ ኃይል አፍነው ሊያስቀሩት ይችሉ ነበር የሚል አስተያየት ሰንዝረው፤ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ህብረተሰብ የመገንባት አስፈላጊነትን አስረድተዋል፡፡ የቀድሞ መሪዎች በፖለቲካ ሒሳብም የሚጠቀስ በጎ ነገር አንዳላቸው ራሰቸው የለውጡ መሪ መስክረዋል፡፡ የሰከነው የታሪክ ሚዛን ደግሞ ከዚህ የተሻለ ወይም የወረደ ዋጋ ይሰጣቸው ይሆናል፡፡

ስለዚህ የኔ ትኩረት በፖለቲካው ምዕራፍ እንደ ታሪክ ያለ የሰከነ ሚዛን ይዤ ለመዳኘት ሳይሆን፤ በሐገሩ ሰው የሌለበት መስሎ እስኪታይ ድረስ ተስፋ የሚነጥቁ የተዛቡ አመለካከቶችን እና ግፎችን እያየሁ በዝምታ ለማለፍ የማልፈልጋቸውን ነገሮች በማንሳት የሐሳብ ቶኒክ ማቅረብ ነው፡፡ ይህ አስተያየቴ በብዙ ሰዎች ህሊና ተደላድሎ የተቀመጠን ፍርድ የሚነካካ እና የሚጋፋ በመሆኑ ተመቻችቶ መተኛት የሚፈልገውን ቁጡ አደገኛ ፍርድን የሚተናኮል በመሆኑ፤ አጸፋው አስፈሪ መሆኑን ከወዲሁ አውቀዋለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ዝምታው ስለ ራሴ የሚኖረኝን ግምት የሚያበላሽ እና ዕረፍት የሚነሳ በመሆኑ፤ ዝምታ የሚያስከትለውን ወቀሳ፤ በመናገር ከሚመጣብኝን የብዙዎች ቁጣ ጋር አወዳድሬ ምርጫ አደረግሁ፡፡

ይህን ጽሑፍ ስጽፍ እንደ ዘወትሩ ያለ የስሜት፣ የምርጫ እና የውሳኔ ጓዝ ይዤ አይደለም፡፡ ይህን ጽሑፍ ከመጻፌ በፊት እና በኋላ አንድ ዓይነት ሰው እንደማልሆን አውቀዋለሁ፡፡ ምናልባት ዕድሜ ልኬን የሚከተለኝን አንድ ነገር የሚፈጥር ጽሑፍ እንደሚሆን አልጠራጠርም፡፡ ይህን ጽሑፍ መጻፍ ሊያመጣ የሚችለውን ውግዘት በመፍራት ሳልጽፍ የሚኖረኝን ዕድሜ (እሱም በኔ እጅ አይደለም) እንድጸየፈው የሚያደርግ እውነት አለኝ፡፡ ይህን እውነት መደበቅ የዕድሜ ማርዘሚያ መድኃኒት ቢሆን እንኳን እንቀዋለሁ፡፡ ዕድሜዬን የምፈልገው እንደዚህ አላሳርፍ የሚሉኝን እውነቶች ለመመስከር ካልሆነ ቢበዛ 70 ቢበረታም 80 ነው፤ ከዚያ የተረፈው ድካምና መከራ ነው እንዳለ ቅዱስ ዳዊት፤ 80 ዓመትም 1ሺህ 960 ወራት ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ከግማሽ ከፍ የሚለው አልፏል፡፡ ቀሪው በዚህች ፍንቅል ድንቅል በምትል ሐገር እና ጦርነት በማያጣት ሐገር ብዙ አስተማማኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ እውነትን መሸፈጥ ከዕድሜ አንጻር ሊያስገኝ የሚችለው ትርፍ ያን ያህል የሚጓጓ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ እውነትን ተናግሮ ከመሸበት ማደር ብሎ የተረተው ሰው ስሜት አሁን ይበልጥ ገባኝ፡፡ አዎ የምታድርበት ቦታ ላይመችህ ይችላል፡፡ እውነቱን ተናግሬ ከመሸበት ቦታ ከማደር፤ ዋሽቼ አስቀድሞ ከተዘጋጀልኝ ምቹ ማደሪያ ማደርን እንድመርጥ የሚያደርገኝ የሚያጓጓ ነገር የለኝም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚያበረታኝ ነገር አለ፡፡

ዛሬ በረከት ሥልጣን ያለው ሰው አይደለም፡፡ በመሆኑም የማነሳው ሐሳብ ከማሸርገድ የሚታሰብ አይደለም፡፡ ይህም በጽሁፉ እንድደፍር ያደረገኝ ምክንያት ነው፡፡ የሆነ ሆኖ፤ ብዙ ጊዜ ዳር ዳር እያልኩ ቆይቻለሁ፡፡ አዎ፤- የሕግ የበላይነትነትን ለማክበር፡፡ ሆኖም አንድ ጓደኛዬ የኢትዮጵያ ፖለቲካ የቲም ልጅ የሚለውን አቶ በረከትን፤ በአክብሮት የምመለከተው ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ስለ አቶ በረከት ለመጻፍ ወሰንኩ፡፡ አውቃለሁ፤ በዚህ ወቅት ስለ በረከት ጎልቶ ከሚታየው አስተሳሰብ የተለየ ነገር መናገር አደገኛ ነው፡፡ በገራገር አስተያየት፤ አደገኛ ራስን የማጥፋት እርምጃ ተደርጎ የሚወሰድ ውሳኔ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ፤ ሊታረም የሚገባውን ሐገራዊ የፖለቲካ ወግ እያዩ፤ እንዲያው ለመመሳል በማሰብ ዝም ማለት፤ ራስን ሳይሆን ሐገርን የማጥፋት አደገኛ እርምጃ ነው፡፡

የአቶ በረከት ጉዳይ ሐገራችንን ከጎዳና ለማውጣት የሚታገሏት ሁለት በሽታዎች ጎልተው ታይተውበታል፡፡ እነዚህን በሽታዎች ፊት ለፊት ለመታገልም፤ ከአቶ በረከት ጋር ተያይዘው የተነሱ ጉዳዮችን አጀንዳ አድርጎ ከመወያየት የተሻለ ተመራጭ መንገድ አልታየኝም፡፡ ምነው ቢሉ፤ አንድም - ቀልብ ሳቢ አንጀንዳ በመሆኑ፤ አንድም - በረከት ብዙ የጥላቻ ድንጋይ የሚወረወርበት ሰው በመሆኑ፤ አንድም - ዜግነትን የሚገፍፍ በደል በጓዶቹ ሲፈጸምበት በማየት የፈጠረብኝን ቁጣ ለመግለጽ የሚያስችለኝ በመሆኑ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፖለቲከኞች ነውር የሚባል ነገር የሚያውቁ ጨዋዎች እንዳልሆኑ የሚያመለክት ተግባር የታየበት በመሆኑ፤ አንድም - ስለ በረከት የሚነገር በጎ ነገር ካለ፤ ይህን ነገር ለመናገር ከዚህ የተሻለ ጊዜ የሌለ በመሆኑ ነው፡፡

አቶ በረከት በሥልጣን ላይ እያለ ስለ እርሱ በጎ ነገር መናገር ሹመት ሽልማት በማሰብ የሚደረግ የአድርባይ ተግባር የመሆን ሰፊ ዕድል አለው፡፡ ሆኖም አሁን ስለ እርሱ መናገር ውግዘት እንጂ ሽልማት አያስገኝም፡፡ ዛሬ በረከት፤ አጼ ምኒልክ ለብዙ ጊዜ ከህዝብ ዓይን በመጥፋታቸው፤ ሐገር ውስጥ ውስጡን የሚያወራውን ነገር በቅኔ እንደ ገለጠው አዝማሪ፤

በሬ ስጠኝ ብዬ፣ እኔ አለምንህም፤

ፈረስ ስጠኝ ብዬ፣ እኔ አለምንህም፤

አምና ነበር እንጂ፣ ዘንድሮስ የለህም፤ በሚል የሚገለጽ ሰው ነው፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ የሚነገር በጎ ነገር፤ ከበረከት ብቻ ሳይሆን ከባለ ጊዜዎችም የሚያስገኘው ጥቅም የለም፡፡ ዛሬ በረከትን በበጎ የሚያነሳ ሰው፤ ከፖለቲካ ማዕበሉ በተቃራኒ የሚሄድ ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ውግዘትን እንጂ ሞገስን አያገኛትም፡፡ ይልቅስ አሁን ስለ በረከት በጎ ነገር መናገር፤ አስቸጋሪ የብቸኝነት እስር ቤት (Solitary confinement) ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ታዲያ እውነትን የሚፈልግ ሰው የብቸኝነት አስር ቤትን ሊያያት ግድ ይሆንበታል፡፡ ይህ እስር ቤት የሚያስፈራ ቢሆን እንኳን ከሁኔታዎች በላይ የመሆን የመንፈስ ጥንካሬን ያጎናጽፋል፡፡ ተናጋሪው እውነት ብሎ የሚያነሳው ነገር ደካማ እንኳን ቢሆን፤ አውዱ ጥንካሬን ይጨምርለታል፡፡ ተናጋሪው የተሳሳተ ቢሆን እንኳን፤ እዳሪ ለሚሆን ነገር የሚታገል ባለመሆኑ፤ ድርጊቱ ስህተት እንጂ ነውር አይሆንበትም፡፡ ክብሩ አይጎድልም፡፡ እውነትን የማክበር ሥነ ምግባራዊ ኃይሉ ሞገስ ይሰጠዋል፡፡ ለመንገዱም ብርሃን ይሆነዋል፡፡ ውሸትን ያሳፍራታል፡፡ ምናልባት፤ የታፈኑ እውነቶችን በአርዓያነት ይጠራቸዋል፡፡

የፖለቲካችን አደባባይ እንዲህ ያለ ፈውስ ያስፈልገዋል፡፡ ዴሞክራሲያችን ብዙ ጊዜ የሚጎድለውን የተቃራኒ ሐሳቦች ፍጭት እንዲያገኝ፤ ከፍጮቱም በሚገኘው ብርሃን አንዳንድ ጨለማ የወረሳቸውን ሐቆች ለዓይን ለማጋለጥ፤ እያዋከቡ ከጊዜ ወይም ከመንጋ የአመለካከት እና የአስተያየት ባቡር እንድንሳፈር የሚገፋፋንን ኃይል እምቢ የማለት ድፍረት ይዤ፤ ከባቡሩ ውጭ ሆኖ ነገሮችን ለመታዘብ የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ለመፍጠር ነው፡፡ እንዲሁም፤ ድፍን የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያወግዘው አቋም እንኳን ቢሆን፤ ያን አቋም የማራመድ ግለሰባዊ መብትን በማረጋገጥ፤ ኢትዮጵያውያን ከሚጠሉት ሐሳብ ጋር የመኖር ዴሞክራሲያዊ እሴትን እንዲለማመዱ አጋጣሚ ለመፍጠር ነው፡፡ በአጭሩ ሠናይትን የማክበር ጥረት እና ልምምድ ነው፡፡

ዛሬ በሐገራችን የመጨረሻ ቅርጹ የማያስታውቅ (ቅርጽ ሊኖረው የሚችል ከሆነ) የፖለቲካ ትግል እየተካሄደ ነው፡፡ ኢ-ሥነ ምግባራዊ ፖለቲካ ተስፋፋቷል፡፡ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ እንዳለው እንደ ህዝብ ሥነ ምግባራችን ሻሽሯል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሰው በዘረኝት ተጠልፏል፡፡ ከሥነ ምግባር ዙፋን ወርዷል፡፡ ሰው ከሰውነቱ ሸሽቷል፡፡ የጥላቻ እና የዘረኝነት መንፈስ ገንግኗል፡፡ ይህን ጽሁፍ የምጽፈው፤ ይህን የጥላቻ እና የዘረኝነት መንፈስ ለመክሰስ ነው፡፡ ይህን መንፈስ የምከሰውም የአቶ በረከት ጉዳይን በማንሳት ነው፡፡

ክሱ ውግዘትን ያስከትላል፡፡ ግን አስቀድሜ እንዳልኩት ውግዘት በመፍራት ሳልናገረው የምቀረው ሐሳብ እንዳይኖር እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን በህሊናዬ ፊት ቆሜ ቃል ገባሁ፡፡ እናም የአባት - የእናት ባልሆነ የእምነት ዕዳ ተያዝኩ፡፡ ይኸው የነብር ጅራት ሆኖ የሚታየኝን ጉዳይ በዕደ ህሊናዬ በድፍረት ጨብጬ መናገር ጀመርኩ፡፡ ይህ ሳደርግ በምናብ እንደ አርዓያ ሰብ ሆኖ የሚታየኝን አንድ የቻይና ባለታሪክን አነሳለሁ፡፡ እንዲህ ነው፤

አንድ እኩይ እና እቡይ የሆነ የቻይና ንጉሥ ነበር፡፡ ይህ ንጉሥ፤ ሰብቀኛ የሚያመጣለትን ነገር እየሰማ፤ በረባ ባልረባው ነገር ሰዎችን እያሰረ ሞት ይፈርዳል፡፡ ከባሟሎቹ ጋር ወደ መግደያው ሥፍራ እየሄደ ፍርዱን ያስፈጽማል፡፡ በመግደያው ቦታ እስከ ወገብ የሚደርስ ቁመት እና አግዳሚ እንጨት ያለው መሰየፊያ አለ፡፡ የሞት ፍርድ የተፈረደበት ሰው እጁ የፊጢኝ እንደ ታሰረ አንገቱን ከመሰየፊያው አግዳሚ እንጨት ያሳርፋል፡፡ ከዚያም አንገቱ በሰይፍ ይቀላል፡፡

እንዲህ ዓይነት ፍርድን በተደጋጋሚ በመመልከት በብዙ የሚያዝን እና ለንጉሡም ፍፁም ታማኝ የሆነ አንድ ባለሟል ነበር፡፡ ይህ ባለሟል ብዙ ሰዎች ሲገደሉ እየተመለከተ ሲያዝን ቆይቶ፤ ነገሩን በዝምታ ማለፉ እየከበደው መጥቷል፡፡ በመጨረሻም አሳምሮ በሚያውቀው አንድ ጉዳይ በሸፍጥ ተከስሶ የተፈረደበት ንፁህ ሰው የፊጥኝ ታስሮ፣ የሞት ጥላ በተጫነው እና ፀጥ ረጭ ባለው አደባባይ አንገቱን እንደ ደፋ ወደ መግደያው ሥፍራ ሲያመራ ባየው ጊዜ፤ እንደ ዘወትሩ ነገሩን ዝም ብሎ መመልከቱ አቃተው፡፡

የንጉሥን ፍርድ መቃወም ወንጀል መሆኑን በደንብ የሚያውቀው ያ ታማኝ ባለሟል፤ በአደባባዩ ያረበበውን ክቡድ የሞት ፀጥታ ወዲያ ገፍትሮ፤ ድምፁን ከፍ በማድረግ ንጉሥ ሆይ ተሳስተዋል!!! ብሎ ከፍ ባለ ድምጽ ጮኽ፡፡ የለበሰውን የክብር ካባ ወደ ኋላው ጥሎ ከሹማምንቱ መሐል ወጥቶ፤ በከባድ ድንጋጤ ጭው ብሎ የተፈጠረውን እንግዳ ነገር በሚመለከተው እድምተኛ ፊት፤ እንደ ተገደረ ሰይፍ አንገቱን ቀጥ አድርጎ፤ በቆፍጣና ዝግ ያለ እርምጃ ወደፊት እየተራመደ ሄዶ ከመግደያው ቦታ ደረሰ፡፡ ከዚያም ንጉሥ ሆይ ተሳስተዋል!!! ብሎ ሦስት ጊዜ ተናግሮ፤ አንገት ከሚሰየፍበት እንጨት አጠገብ እንደ ቆመ፤ ዙሪያ ገባውን ከገረመመ በኋላ አንገቱን ዘልሶ ለሰይፍ አመቻቸ፡፡ ጭንቅላቱን ከመሰየፊያው አግዳሚ እንጨት አሳረፈ፡፡ በዚህ ጊዜ በቁጣ የነደዱት የንጉሡ አጃቢ ወታደሮች ሰይፋቸውን ከአፎት መዘዙ፡፡ ሆኖም ንጉሡ ተጠበቅ! ብሎ በመጮኹ ታገሱ፡፡

ያ ንጉሥ ሆይ ተሳስተዋል! ያለው ባለሟልም አንገቱን ከመሰየፊያው እንጨት ሳያነሳ፤ የሚሆነውን ነገር ትንፋሹን ውጦ ይከታተላል፡፡ ፍቅር አግዶት ከሰማያዊ ዙፋኑ ወርዶ በመስቀል ተቸንክሮ እንደ ሞተው ኢየሱስ፤ ይህንም ሰው እውነት አግዳው ሠናይት አስጨክው - አጽንታው፤ ግፍን በመቃወም ቆመ፡፡ ይህ ባለሟል ከመሰየፊያው እንጨት እንዳጎነበሰ፤ በክስተቱ የተደናገጠው ንጉሥ ከመድረኩ ወርዶ ወደ ቤተ መንግስቱ ሲያመራ ጉባዔው አብሮ ተናደ፡፡ ከዚያች ዕለት ጀምሮ ያ ንጉሥ በሰብቀኛ ወሬ እየተመራ የሚፈጽመውን ግድያ አቆመ፡፡ ይልቅስ የህዝቡን ሐሳብ ለማድመጥ እና ለማወቅ የሚያግዝ አዲስ የአሠራር ዘዬ ዘረጋ፡፡ ስለዚህ ማንኛውም በደል የደረሰበት ሰው አቤቱታውን ለማሰማት የሚችልበት ዕድል ተፈጠረለት፡፡ እናም የባለሥልጣናት የበቀል እርምጃ ሳያስፈራው፤ በደሉን ሁሉ ዘርዝሮ በመጻፍ በቤተ መንግስቱ አቅራቢያ ወደ ተዘጋጀው የአቤቱታ ማቅረቢያ ሥፍራ ሄዶ፤ በጽሑፍ ያመጣውን አቤቱታ በማስቀመጥ ደወል ይደውላል፡፡ ደወሉን የሰሙት ባለሟሎችም አቤቱታውን ለንጉሡ ያቀርቡለታል፡፡ በዚህ መንገድ ፍትሕ በምድሪቱ ነገሠ፡፡

ያን ታማኝ ባለሟል ለእውነት እንዲቆም ግድ ያለችውን የህሊና ንግስት ጓደኛዬ ቶማስ (ስሙ ተለውጦ) ሠናይት ይላታል፡፡ ሠናይት እንዲህ ናት፡፡ ወንድሜ ቶማስ ሠናይት በጣም አስቸጋሪ ነች ይላል፡፡ መከራን ከፈራህ ከሠናይት ራቅ፡፡ በስህተት ከእርሷ ጋር ለአፍታም ከተጫወትክ፤ ምነው በብቸኝነት ስንት አውርተን እያለች ትከስሃለች፡፡ የአስቆርቱ ይሁዳን የህሊና ክስ ይዛብህ ትመጣለች፡፡ ስለዚህ መከራን ከፈራህ ሠናይትን አታጫውታት፡፡ ደፍረህ ከእርሷ ጋር ከተጫወትክ ግን መስክር እንጂ አትሸፍጥ ይለኛል፡፡ ሠናይት እንዲህ ናት፡፡ የበረከትም መዝሙር ይህች ናት፡፡

ለፍቼም አልቀረሁ፣ እንዳገልግሎቴ፤

ግምጃ ሱሪ እግረ ሙቅ፣ ወኅኒ ቤት ግዛቴ፡፡

ደክሜም አልቀረሁ፣ የኔም ጌጥ ይኸዋ፤

ግምጃ ሱሪ እግረ ሙቅ፣ ሰንሰለት ቢተዋ፡፡

ነጋድራስ ገ/ሕይወት ባይከዳኝ፤ ሕዝቦችን ሁሉ የሚፈጥር አንድ አምላክ ነው፡፡ ይህም አምላክ የምንለው የሕዝቦች ፈጣሪ ሕዝቦቹን ሁሉ ትክክል አድርጎ ፈጥሮ ላኗኗራቸውና ለልማታቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሁሉ ከሙሉ ፈቃድና ሥልጣን ጋራ በጃቸው ሰጥቷቸዋል፡፡ ስለዚህ ማናቸውም ሕዝብ ቢለማም ቢጠፋም በገዛ እጁ ነው፡፡ ሕዝብ የሚጠፋበት አንዳንድ ጊዜ ምክንያት ቢገኝ፤ ያውም ምክንያት ባንዳንድ ሰው ቢመካኝ፤ ነገሩ ትክክል አይሆንም፡፡ የልማትን መንገድ ለማግኘት የሚጥር ሕዝብ ቢገኝ፤ ባንዳንድ ክፉ ሰው ምክንያት ሊጠፋ አይችልም፡፡ እንዲሁም ደግሞ የልማትን መንገድ ለማግኘት የማይጣጣር ሕዝብ ባንዳንድ ደኅና ሰው ኃይል ልማት ሊያገኝ አይችልም፡፡ ደግሞም ማናቸውም ሕዝብ የሚለማበት መንገድ አንድ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ማናቸውም ሕዝብ የሚጠፋ ይህንን የልማት መንገድ ትቶ በሌላ መንገድ የሄደ እንደሆነ ነው፡፡ (መቅድም፣ 11-12)፡፡

የአውሮፓን ሥልጣኔ አይቼ፤ ለአገሬ መንግስት ቅንዓት እንደ እሣት በላኝ!!! አሉ አለቃ ታዬ፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ደግሞ ማነው . ምንትስ?

ማነው . ምንትስ?

ያው መቼም እኔም እንደ ሰው፤

አንዳንዴ፣ አንዳንዴ ብቻ፣ ሕሊናዬን እውነት ሲያምረው፤

ሰብሰብ ብዬ እማስበው፤

ቀድሞስ ቢሆን ለኔ ጤ፣ ለኔ ብጤ የሄዋን ዘር

አዳሜ በኔ ላይ በቀር፣ ለኔ መስክሮ አይናገር

ብዬ ከልቤ ስማከር

እኔው ከኔው ስከራከር

ተጨብጬ እማብላላው

ያው መቸም እኔም እንደ ሰው

የሐቅ ራብ ነፍሴን ሲያከው

ልቤ ልቤን ሲሞግተው .

እውነትስ ምንትስ ማነው?

እያለ ነው፡፡ .

 

Back to Front Page