Back to Front Page

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሊት ጀርባ ያለው ድራማ

 

ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሙሊት ጀርባ ያለው ድራማ

ከይዲድያ ብፁእ

07-09-20

 

ሀ) ግብፆች እንዴት ድንገት እንዲህ ጸጥ-ረጭ አሉ?

ፖለቲካ አንዳንዴ ቁማር፤ሌላ ጊዜ የድብብቆሽ ጨዋታ ነው እየተባለ ሲነገርና ስሰማ አድጌለሁ፤ በሕይወቴም በግለሰቦችና በሃገር አያሌ ሸፍጦች፤ ደባዎችና ሸሮች ከፖለቲካ ድራማ መጋረጃ ጀርባ ስተውኑ አይቻለሁ። ከሰሞኑ በፖለቲካው መድረክ የተተወነ ትርኢት ጠቅላይ ምኒስትሩ ትናንት ለፓርላማው የግድቡ ሙሊት ከሁለት ቀን በኋላ ይጀመራል በማለት በተናገሩት ዙሪያ ያለው ስውር ድራማ ነው።

ይሄ ታድያ ጮቤ የሚያስረግጥና ከበሮ የሚያስደልቅ እንጂ፤ እንዴት ስጋት ሊያሳድርብህ ይችላል? ልባል እችላለለሁ። መድረኩ የፖለቲካ ትውና የሚካሄድበት ነውና፤ ከፖለቲካው መጋረጃ ጀርባ ያለውን ስውር ጉዳይ አሾልኮ ማየት የሚጠይቅ ነው።

ግብፆች ሙሉ ስምምነት ላይ ከመድረሳችንና ከመፈረማችን በፊት፤ ዘንድሮ ክረምት ላይ ግዱቡን መሙላት አትችሉም ብለው አሜሪካን ጋሻ ጃግሬ አድርገው፤ ግድቡን መሙላት ከጀመራችሁ፤ ይሄውና የፈረሶቻችንና የሠረገሎቻችን ብዝትና ብርታት በማለት በተሌቪዥኖቻችን መስኮት አሾልከው በማሣየት ሲያስፈራሩን ሰነባብተዋል።

Videos From Around The World

መንግሥታችንም በመገነኛ ብዙኃኞቹ፤ በግብፅ ላይ ያለ ወትሮው አጥብቆና አክርሮ መቃወም ጀምሮ ነበር። በዚህ መካከል ሦስቱም ሃገሮች በአፍሪካ ሕብረት ታዛቢነት ተቋርጦ የነበረው ድርድራቸው እንዲቀጥሉና ጉዳያቸውን በሁለት ሣምንት ውሰጥ እንዲቋጩ ተደርጓል ተብሎ ነበር።

ለ) ከሕዝቡ ተሸሽጎ የተከናወነ ድራማ ፦

አንዳንድ በተለያዩ በአረብኛ ቋንቋ መገናኛ ብዙኃን ኢትዮጵያን ወክለው በአረብኛ ቋንቋ የሚሞጉቱ ወገኖች ( በተለይም በአባይ ሚድያ ኡዝታዝ ጀማል በሽር የታበሉ ወገን) ከሣምንት በፊት እኛ ሳናውቅ አሜሪካና እስራኤል በስልጣናቸውና በጉልበታቸው ድርድሩን ከአፍሪካ ሕብረት እጅ ነጥቀው ጉዳዩ በተባበሩት የዓለም መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እንዲታይና እንዲቀጥል አድርገውት እንደ ነበረና ለሁለት ቀናት ተደራዳሪ አገራቱ ተደራድረው መግባባት ላይ እንዳልደረሱና፤ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት እንዲታይ እንደ መለሱት ገልጸውልን ነበር።

አሜሪካና እስራኤል ይህን እንዳደረጉ መንግሥታችን የጉዳዩ ባለቤት ለሆነው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ለምን አላስታወቀም? በአጋጣሚ ከላይ ከጠቀስክዋቸው ወገኖች ድርጊቱን መሰማት ቻልኩኝ እንጂ፤ ሆን ተብሎ የኢትዮጰያ ሕዝብ እንዳያቀው የተደረገ ድብቅ ተግባር ነው። ይህም ከድብብቅቆሾቹ እንደ አንዱ ክፍል ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ነው። ለመሆኑ በእነዚህ ሁለት የድርድር ቀናት በድርድሩ 90% ተስማምተናል፤ የቀረን ትንሽ ጉዳይ ነው ብላችሁ እንደ ነበር ይታወሣል። ያልተሳማማችሁበት ጥቂት ፐርስንት ምን ነበር? እንዴትስ መስማማት ተሣናችሁ?

ሐ) በግድቡ ሙሊት ጭንብል ወይም መጋረጃ የተፈጸመው የማደነጋገሪያ ሥራ፦

ተደራዳሪዎቻችን ከአባይ ተፋሰስ ብቻ ከኢትዮጵያ ለቆ ከሚወጣው ውሃ በዓመት ከ 31 ብልዮን ሜትር ኩብ በላይ መስጠት እንደማይችሉና፤ ግብፅ ደግሞ ቢያንስ 40 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት ማግኘት አለብኝ እንዳለች ይታወቃል። ያልተሰማማችሁት በዋናነት በዚህ የውሃ ድርሻ ክፍፍል መጠን አይደለምን?

በግድቡ ሁለ-ገብ አገነባብና አጠቃቀም ዙሩያ ብዙ የቀረ ነገር መኖሩ ቢታወቅም፤ ኢትዮጵያ በዓለም እውቅና ባለቸውና፤ የተካበተና የዳበረ ተመክሮ ባላቸው ባለሞያተኛ ድርጅቶች ቀጥራ ስለምትሠራ፤ ሱዳንና ግብፅ ስጋታቸውን ለመቅረፍ የግንባታው ሥራና አካሄዱም በመሳየት በቀላሉ መፍታት የሚቻል ነው። ከዚህ ጎን ለጎን ሕዝባችን ማውቅ የሚኖርበት፤ አባይ ኢትዮጵያን ለቆ ሲወጣ የሚፈሰው የውሃ መጠን በአማካይ 52. 6 ብልዮን ሜትር ኩብ በዓመት ነው። በዓመት ከኢትዮጵያ ለቆ ከሚወጣው 52. 6 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ ከሆነ፤ እንበልና ግብፅ ቀና እና ቸር ሆና ተደራዳሪዎቻችን እንሰጣለን ብለው በተሰማሙበት ከፍተኛ የውሃ መጠን በዓመት 31 ብልዮን ሜትር ኩብ ብንቀንስበት ቀሪው 21. 6 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት ነው።

ከቀሪው 21.6 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት፤ ሱዳን 15 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት በትጠይቅና፤ አባይ ከኢትዮጵያ ተነስቶ አስዋን ግድብ እስኪገባ በፀሐያማውና ሙቀቱ ከፍተኛ በሆነው በጣም ረጅም ረባዳ ምድረ- በዳ ጉዞው በትነትና የሚፈስበትን ምደር ለማርጠብና ለማረስረስ በአማካይ 4.6 ብልዮን ሜትር ኩብ ወሃ በዓመት በአመካይ ከባከነ፤ ኢትዮጵያ ከአባይ ሊተርፋት የሚችለው የውሃ መጠን ከ 2. 6 ብልዮን ሜትር ኩብ በዓመት ነው።

መ) በዓመት ከአባይ የሚተርፈው 2.6 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በእውን ለኢትዮጵያ በቂ ነውን?፦

ሕዝቧ በሚያሰደነግጥ ፍጥነት እየጨመረባት ያለችውና፤ በወቅቱ 110 ሚልዮን ሕዝብ ላላት ኢትዮጵያ 2. 6 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት ለመጠጥና ለመጸዳጃ፤ ገባር ወንዞችዋን ጠልፋ በመስኖ ለእርሻ ሰብል ለማልማት፤ ለውሃ ተርባይን ማመንጫና ለተለያዩ የእንዱስቱሪ አገልግሎት የሚውል የውሃ አቅርቦት በእውን በቂ ይሆንን? ተደራዳሪዎቻችን ይቅርና ለግብጽ ከ 31 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት በላይ በትንሹም ከፍ አድርጋችሁ መስማማት፤ እንስማማለን ያላችሁት ከፍተኛ መጠንም ፈጽሞ አዋጭ አይደለም። የኛውን ትውልድ እጣ ፈንታ ተውትና፤ ለሚመጡት ተከታታይ ትውልዶች የሚደቀንባቸው ከፍተኛ ተግዳሮት አሁን ላይ ስትደራዳሩ አስባችሁበት ይሆንን? ኢትዮጵያን ወክላችሁ ዘጠኝ ዓመት ሙሉ ከግብፆችና ከሱዳኖች ጋር በክብ ጠረጴዛ የተማጎታችሁበት የመጨረሻው ውጤት ይሄ ነበርን?

ሠ) አባቶቻችን ምን አሉ? ምንስ አደረጉ? እኛስ ምን አያልንና እያደረግን ነን?

አፄ ኃይለ-ሥላሴ በአባይ ድርሻ ላይ እንዲደራደሩ ግብፆች ሲወተውትዋቸው እኛ ግድብ ለመሥራት አሁን አቅም የለንም፤ ዳሩ ግን የልጅ ልጆቻችን አቅም ሲኖራቸው ሊጠቀሙበት ስለሚችሉ እስከዛው አንዋዋልም ማለታቸው የሚገርም ነው። ጉዳዩ እየተነከባለለ ቆይቶ ባባለ ድርሻው ትውልድ በእኛ ላይ ሲያርፍ፤ ተፈጥሮ የለገሰችን ጸጋ ሠርተን መጠቀም ስንችል፤ በፖለቲካው ሜዳ በዚህ መልኩ መልፈስፈሳችን በአያሌው የሚያሳዝን ነው።

ረ) በአፍሪካው ሕብረት አደራዳሪነት የተነሱና ያልተስማማችሁባቸው አንኳር ነጥቦች ምን ነበሩ? ለሕዝቡስ ለምን አልቀረበም?

ለመሆኑ ድርድሩ ወደ አፍርካ ሕብረት ከተመራ በኋላ የድርድሩ አንኳር ጉዳይ ምን ነበር? በምን ላይስ ተስማማችሁ? አዳሪ የሆነ ጉዳይስ አለን? ወይስ የውሃ መጠን ድርሻው ላይ ተስማምታችሁ ፈርማችኋልን? ከተሰማማችሁ ምን ያክል ሜትር ኩብ በዓመት? የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የቴክኒክ ቡድኑ ይሄንን ያውቃልን? ወይስ ከእናንተ ውጭ የተፈጸመና የተፈረመ ውል ይኖርን? በአፍሪካው ሕብረት አደራዳሪነት የተካሄደው ድርድር ለምን እንዲስበሰበስ ተደረገ? የት ላይ እንዳለን ጠፍቶብናልና እበካችሁ ሁኔታችንን ሳትሸሸጉ ንገሩን! ከ 31 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት በላይ ለግብፅ ፈቅዳችሁ ከሆነ፤ በአገርና በትውልድ ትልቅ ክህደት እንደ ፈጸማችሁና በታሪክም በጥቁር ቀለም እንደምትከተቡ ልታውቁ ይገባል።

ሰ) ግራ አጋቢው ያልተጠበቀ የግብፅ ዝምታ፦

ሶሞኑን ግብፆችን የበላ ጅብ ምን ነው ዝም አለ? ድምፁስ ለምን ጠፋ? ግብፆች ዝም ሲሉ የሚፈልጉት ነገር ሲያገኙና ጉዳያቸው ሲሰምርላቸው ብቻ ነው። ያለበለዝያማ የመፈረጋገጣቸው ጭሆትና የመወራጨታቸው ድምፅ አይጣል ነው። ምናልባት 35 ብልዮን ሜትር ኩብ ውሃ በዓመት ገጨትና ጎንጨት አድርገው ሊሆኑ ይችላሉኮ! እንዲህ ከሆነ ከሰማይ ልንሰጥ ብድርተኞች ልንሆን ማለት ነዋ! ግብፆች በውጤቱ እፎይ ካሉና በትልቁ ከተነፈሱ በኋላ፤ በሉ አስኪ ሙሊታችሀን ቀጥሉ፤ ለሕዝባችሁ በሰውር ያደረጋችሁት ድራማ ቆይቶ እስኪነቃባችሁ በሙሊቱ ዜናና አዋጅ አስደስቱት፤ ዳንኬራም አስመቱት! እያልዋችሁ ይሆኑን?

ሸ) የኤርትራው መሪ በድራማው መካከል ወደ ሱዳንና ወደ ግብፅ መብረር፦

ረዳት ጠ/ ሚንስትራችን አቶ ኢሳያስ አፈ-ወርቂ በእነዚህ ቀናት ወደ ሱዳንና በተለይም ወደ ግብፅ ለምን ጎራ አሉ? ይህ የድራማው የመጨረሻው ትዕይንት መጀመሪያው ነው። አቶ ኢሳያስ ግብፅን በድርድሩ ይህ ያክል ውሃ ካገኘሽ፤ ጥሩና አዋጭ ገበያ (Good deal) ነውና ዐይንሽን ሳታሺ ተቀበይው፤ እነርሱንም ሙሊቱን እንዲያደርጉ አትከልክያቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሆነ ዘንድሮ ሙሊቱ መደረግ እንዳለበት እንጂ የድርድሩ ወሳኝ የውሃ ድርሻ መጠን እንዳያይ ወፍራም መጋረጃ ከፊት ለፊቱ አስቀምጠው ጋርደውበታልና ሁሉም ከተፈረመ በኋላ ሕዝቡ ቢንጫጫና ዎዮ ቢል አንቺ ምን ገዶሽ? አድዮስ (adeus) አባይ!! ከዚህ በኋላ ናይል እንጂ አባይ ብለው ለመጥራት እንኳን ይቀፋቸዋል ያስጠላችዉማል፤ ከብዙ ልፋትና ንዝንዝ በኋላ ናይልን ገንዘብሽ አድርገሻልና እንኳን ገዱ ቀናሽ፤ ይብላኝ ለኢትዮጵያና ለሕዝቧ ይልዋታል።

በአጸፋው ግብፅ ወዳጄ ምክርህ ጉሩምና ድንቅ ነው፤ አፌን አልከፍትም፤ ዝምም እላለሁ፤ ሙሊቱ እንዲያደርጉም አልቃወምም። በሙሊቱ መጋረጃ ዐይኖቹ የተጨፈነው ሚስኪን ሕዝብ በሙሊቱ ለጊዜው ይቦርቅ፤ ጉድና ጅራት ከወደ ኋላ ነው እንዲሉ የተደገሰላቸው ሴራ ቆይተው ሲረዱ ለዘላለሙ አንጀታቸው እያረረና እየበገነ ይኖራሉ። እኛ ግን ገድ ቀንቶን ቅቤአችንን ጠጥተናል፤ የውሉ ፊርማም በፀጥታው ምክር ቤት ሕጋው ሰነድ ሆኖ ይሰነዳል። ወላህ ወአክበር!!!

ቀ) የድራማው የመጨረሻው ተውኔት መካከለኛው ክፍል፦

በድራማው የመጨረሻው ትዕይንት መካከለኛው ክፍል ጠቅላይ ምኒስትር አብይ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ሙሊቱ ሁሉም ዝግጅት ተደርጎ በታቀደው መሥረት ከሁለት ቀን በኋላ ይጀምራል ብሎ በይፋ ማወጅ ነው። ዋው! አላልናችሁም! ይሄው ነው እንጂ መሪ ማለት፤ ሙሊቱ እንዳ ተናገረው ይሄው በተያዘለት ቀን ሊሞላ ነው። አይሞላም ብላችሁ ታሳብቁና ተሟርቱ የነበራችሁ የኢትዮጵያ ባላንጦች እርማችሁን አውጡ! ይላሉ። ምናልባት ሙሊቱ በተባለው ቀን ተጀምሮ ሊሆን ይችላል፤ ፍሬ ነገሩ ሙሊቱ መጀመር ያይደለ የውሃው ድርሻ መጠን ክፍፍል ነው። ሙሊቱ ማሳሳቻ ጭንብል ነው። ይሄውና ትናንት በርካታ የመንግሥት አፈ- ቀላጤዎች የግቤ ሦስት ክሊፕ ተጠቅመው በታላቁ ጠቅላያችን በተባለው ቀን የግድቡ ሙሊት ዛሬ ተጀምራልና ተመልከቱ! በማለት እያሳዩ ናቸው።

በ) ከግብፅ አድማስ ስር ሰላምና እፎይታ ነገሷል፤ ግን እንዴት?

ከግብፆች መንደርና ቀየ የጥይት እሩምታና የቃላት ጋጋታ አይሰማም። ዝምና ጸጥ ብሏል፤ የቤት ሥራቸው በዚህን በዚያም ብለው በብልጠት ሠርተዋል በትጋትም አጠናቅቀዋል። ከኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ላይ የተጋረደው መጋረጃ ሲነሣና የተታለለ መሆኑ ሲያውቅ፤ ጭኾቱና ዎዮታው የትም የለሌ ነው። የደራማው መዝጊያውና የመጨረሻው መጨረሻ ይሄው ነው። አባቶቻችን እምቢ አንስማማው ብለው ለእኛ ክፍት አድርገው የተውልን በመጪዎቹ ተከታታይ ትውልዶች ላይ ወሳኙ ጉዳይ በስንፍናና በቸልተኝነት ከእጀችን እንዲወጣ አደረግንባቸዋል። ለዘመናት ክፍት ሆኖ እየተንከበላለ የመጣው ፋይል፤ በዚህ መልኩ በባለ ስልጣኖቻችን ተዘግቷል።

ቸ) የግሌ የልብ ትርታና የውስጤ ሃዘን፦

ይሄ ከመሆኑ በፊት ዋና ዋና ወደ ሆኑት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኋንና በግሌ fb የማስጠንቀቂያ ደወል ቀድሜ ባሰማም፤ አንዳቸውም ጀሮአቸውን ሊያውሱኝ አልፈለጉም፤ በዚህም አዝኛለሁ። ሕዘቡ የጋረደው ጭንብል ከፊቱ ተነስቶለት እውነታው ተረድቶ ሲያስን አብሬው አዝናለሁ። አባይ ደህና ሁን! የእኛና ለትውልዶች መሆን ስትችልና አብዝትህ ልትጠቅመን ስትችል በጥቂት ዜጎች ሻጥርና ንዝህላልነት አጥተንሃል። ቻው አባይ! ስትጮህ እየሰማንህና ስታጓራ እያየነህ ወይ አባይ! እያልን ቆሽታችን እያረረ በድህነት አረንቋ ልንኖር ተፈርዶብናል።

 

 

 


Back to Front Page