Back to Front Page

ትግራይዋይ በመሆንህ አታልቅም፤ ኦሮሞ በመሆንህም አትተርፍም!

ትግራይዋይ በመሆንህ አታልቅም፤ ኦሮሞ በመሆንህም አትተርፍም!

ሙሉጌታ ወልደገብርኤል (ስትራቴጂስት) 05-10-20

ከ2500 ዓመታት በፊት በግሪክ ውስጥ ስለተካሄደው የፔሎፖኒስ (Peloponnese) የጦርነት ታሪክ የጻፈ፤ የታሪክ አባትና መሥራች መሆኑን የሚነገርለት፤ የመጀመሪያ የታሪክ መጽሐፍ ጸሐፊ ቱስይዲደስ (Thucydides) እንዲህ ብሎ ነበር “የአቴንስ መነሳትን ተከትሎ በስፓትራ ላይ የፈጠረውን ፍርሃት ነበር ጦርነትን እውን እንዲሆን ያደርገው” ይላል። የአንዱን መነሳትና የሌላኛው የመቋቋም መንፈስ የወለደው ኩራት፣ እብሪተኝነትና የስጋት ስሜት ሁለቱም ወደ ጦርነት እንዲገቡ እንዳስገደዳቸው ይተርካል። በዚህ ዘርፍ ጥልቀት ያለው ጥናትና ምርምር ያደረጉ በሃርቫርድ ጆን ኤፍ ኬነዲ የሥነ መንግስት ፕሮፌሰርና የፖለቲካ ሳይንቲስት የሆኑ አሜሪካዊው ግርሃም አሊሰን ከአስራ ስድስተኛ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ በዓለማችን በአስራ ስድስት ልዕለ ኃያላን መካከል ማለትም በነባሩ/ገዢ ኃይል (ruling power) እና በአዲስ ኃይል (rising power) መካከል በተደረገው የሥልጣን ሽግግር አስራ ሁለቱ በጦርነት እንደተገባደዱ ይናገራሉ። 

እኚህ ምሑር፥ የታሪክ ጸሐፊ ቱስይዲደስን በማጣቀስ ነባሩም ሆነ አዲሱ ጉልበተኛ ወደ ጦርነት የሚገቡበት ምክንያት በዋናነት ሁለት ቁልፍ ነጥቦችን ያነሳሉ። ይኸውም፥ አንደኛ፥ የአዲሱ ኃይል እየጨመረ የሚሄደውን ነገሮችን በሚፈልገው መንገድ የማስኬድ፣ የማድረግ፣ የማስፈጸም መብትና ከፍተኛ ፍላጎት ሲሆን ሁለተኛ፥ ደግሞ በአልሞት ባይ ተጋዳዩ በኩል የሚፈጠረው የማጣት ፍርሃት፣ ስጋትና ነባሩን ሥርዓት ለማስቀጠል በሚያደርገውና በሚያሳየው አቋም የተነሳ መሆኑን ይናገራሉ። በእርግጥ የህወሐት መሪዎች ከነበራቸው የፌደራል ሥልጣን ተባረው ጥጋቸው ያየዙ ቡድን ናቸው። እንደተገፋና እንደተባረረ ቡድን ጥጋችንን ይዘናል ብለው ግን አርፈው አልተቀመጡም። የህወሐት መሪዎች ጥግ የመያዛቸው ጉዳይ ግልጽነት ሲለሚጎድልበት (እውነተኛ መገፋትና መባረር የአብዲ ዒሌን አይነቱ መጠለዝ ነውና) በአገሪቱ የተፈጠረው የፖለቲካ አለመረጋጋት ለጥቅማቸው በማዋል የዳር ኃይል ሆኖው ጡንቻውን እያሳዩ ነው። የዐቢይ አህመድን መንግሥት ቁመና በሚገባ የገመገሙ የህወሐት መሪዎች ዕድላቸው ፈጽሞ እንዳልተሟጠጠና በሚገባ ገፍተው ቢመጡ ከዕዳ ነጻ መሆን ብቻ ሳይሆን የሥልጣን ተካፋይ ሊሆኑ እንደሚችሉም ያምናሉ። 

የህወሐት መሪዎች ዛሬም ከተጋባባቸው ድንጋጤ ያልተላቀቁ፣ እጅጉ መረጋጋት የራቀባቸው ቢሆኑም ባሉበት ሁኔታም ሆነው የዐቢይ መንግሥት እንደ መንግሥት ለመቀበል እንደሚቸገሩና ፍላጎቱም እንደሌላቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች በይፋ ግልጽ አድረጓል። ዐቢይ አህመድ፥ የምዕራቡና የባህረ ሰላጤ አገራት ተራ ተላላኪ ነው! አገር የመምራት አቅሙም ሆነ ብቃት የለውም! የሚለው የህወሐት መሪዎች ክስ እንደተጠበቀ ሆኖ፥ ዐቢይም ሆነ ዐቢይ አህመድ የሚመራውን ፓርቲ እኛ ጠፍጥፈን የሰራናቸው የእጃችን የስራ ውጤት ናቸው! በተጨማሪም፥ እኛ የላቀ የፖለቲካና የትግል ልምድ አለን! ብለው ስለሚያምኑም የዐቢይ አህመድ መንግሥትነት ከጉሮሮአቸው አልወርድ ብሎ አልዋጥ ብሏቸዋል።

የዐቢይ መንግሥት የህወሐት መሪዎች በከፊል የሚንቃቸው፥ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነትና ድጋፍ እንዳለሆኖ በዋናነት ግን ሰዎቹ ለምንም ነገር የማይበጁ፣ ያረጁና ያፈጁ የጋጋን ፈፎች ናቸው፤ ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሌብነታቸው፣ አታላይና አስመሳይ ባህሪያቸው የተነሣ አክ ብሎ የተፋቸውና የተጸየፋቸው የተናቁ ምናምንቴዎች ናቸው! የሚል እምነት ስላለው ነው። በተጨማሪም፥ ባለተራ እኔ ነኝ! ከእንግዲህ ወዲህ እኔ የምለውን ትሰማላችሁ! ለቃሌም ትታዘዛላችሁ! እንቢ ያላችሁ እንደሆነ ደግሞ በተለመደው መንገድ እደፈጥጣችኋለሁ! የሚለው በዐቢይ አህመድ የሚመራ መንግሥት መንፈስ የከነከናቸው የህወሐት መሪዎች ለዐቢይ መንግሥት ህልውና እውቅና እንዲነፍጉ፤ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ደግሞ በተገኘ አጋጣሚ ሁሉ የተለያዩ ኃይለቃሎች፣ የአሽሙር ቋንቋዎችና ተንኳሽ አገላለጾች በመጠቀም የህወሐት መሪዎችን ተጠያቂ ማድረግና የመጠቋቆም ፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ አድርጓል። ፕሮፌሰር ግርሃም አሊሰን ይህን ዓይነቱ መላላጥ የቱስይዲደስ ወጥመድ ይሉታል። 

Videos From Around The World

የህወሐት መሪዎች ወቅታዊና ነባራዊ ሁኔታ

የኖቤል ሽልማት፥ የክልል መንግስታት በሚያደርጉት ዓላማ የሌለው የስብሰባዎች ብዛት፤ ኮሽ ባለ ቁጥር በሚያወጡትና በሚሰጡት የመግለጫዎች ጋጋታ፤ ሁከትና ብጥብጥን ለመፍጠር ባላቸውና በሚያሳዩት ትጋትና መሰጠት የተመሰከረላቸው፤ አገር ምድሩ ዝም ሲላቸውና ሲረሳቸው መኖራቸውን ለማሳወቅ ሞታቸውን እያስነገሩ ዜና የሚሰሩ፤ የሐሰት ዜናዎችን በመፈብረክና በማሰራጨት ለተካኑ አጽራረ ሰላም፤ ከራሳቸው ከመሪዎቹ ይልቅ የከፉ ጠማማ ግለሰቦች በመፍጠር የተሳካላቸው፤ የሐሰት ሪፖርት በማዘጋጀት ህዝባቸውን ለሚደልሉና በርሃብ ለሚገድሉ፤ የህይወት መስዋዕነት የተከፈለበት ዓላማና አደራ የሚበሉ… አእምሮአቸው ለተወሰደባቸው የከሰሩ ፖለቲከኞች የሚሰጥ ሽልማት ቢሆን ኖሩ የህወሐት መሪዎች ዓመታት እያከታተሉ የኖቤል የነውጥ ተሸላሚዎች ይሆኑ እንደነበር አልጠራጠርም። 

ነውጠኞቹ የህወሐት መሪዎች የኖቤል ሽልማት ቢያመልጣቸውም አንድ ነገር ግን በሚገባ ተሳክቶላቸዋል። ይኸውም፥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምና ደህንነት በማወክና በማተረማመስ ረገድ ለጊዜው የተሳካልቸው ይመስላል። የህወሐት መሪዎች ህልውናና ተስፋ በዋናነት በሌሎች ክልሎች ላይ የተፈጠረውንና ያለውን ሁከትና ረብሻ፤ በአጠቃላይ እንደ አገር በኢትዮጵያ ያለውን አለመረጋጋት ላይ የተንጠላጠለ ለመሆኑም በገሃድ እያንጸባረቁት ካለው አቋም ለመረዳት ይቻላል። የህወሐት መሪዎች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ለመሰንበትም ሆነ ከፌደራል መንግሥት ለመደራደር ጉልበት ይሆነናል ወይም ይሰጠናል ብለው ያምናሉ። ክልሎች የተረጋጉና ሰላም የሰፈነባቸው ዕለት፤ የፌደራልና መንግሥት የተጠናከረና ጉልበት ያገኘ እንደሆነ ደግሞ የህልውናቸው ማብቂያ እንደሆነ አሳምረው ስለሚያውቁ፥ ሰላምንና ዕርቅን ለማውረድ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተጋግሎ እንዲቀጥል ተግተው ይሰራሉ። ይህ የህወሐት መሪዎች ከሶቬት ህብረት የኮረጁት የሶቬት መጫወቻ መጽሐፍ የተቀዳ ስልታቸው ነው። ሰላምንና መረጋጋትን የተለያቸው ክልሎችና ደካማ የፌደራል መንግሥት ማለት ለህወሐት መሪዎች ህልውና የኦክስጅን ያህል አስፈላጊና ጠቃሚ ነውና። ቀለል ባለ አማርኛ፥ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት የተፈጠረና የነገሰ ዕለት የህወሐት መሪዎች ዕድሜ አጭር ነው። የህወሐት መሪዎች ጸሎትና ስለትም በኢትዮጵያ ምድር ሰላምና መረጋጋት እንዳይወርድ ነው። 

በአንጻሩ፥ በመኖፖሊ በተቆጣጠሩት ሚድያ በኩል የሚሰሩት ፕሮፓጋንዳ የህወሐት መሪዎች ከዚህ በፊት የማናውቃቸው ክንፍ ቀረሽ ጻዲቅ ሆኖው ቁጭ ብሏል። ስለ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት፣ ስለ ፌደራሊዝምና መልካም አስተዳደር፣ ስለ ህገ መንግሥት የበላይነት፣ ስለ ፍትህና የህግ የበላይነት መከበር ከማንም በላይ ግድ የሚላቸውና የሚቆረቆሩ የጽድቅ አስተማሪዎች ሆነው ሌላውን ለማስተማር የሚሰሩትን ድራማ አጠናክረው ቀጥለውበታል። በአመዛኙ ስጋት ያጠላበት የተመሰቃቀለ የአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ደግሞ ለዚህ የተመቻቸ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። ትናንት በአደባባይ የፈጸሙትን ዘግናኝና አሰቃቂ ወንጀላቸው ለመደበቅ ብቻ ሳይሆን መቐለ ከተማ እንዲመሽጉ ከተገደዱ በኋላም ቢሆን ስልጣናቸው ለማደላደል በትግራይ ህዝብ ስም እየሰሩት ያለው ሴራና እየተጫወቱት ያለው አደገኛ ቁማር ለማድበስበስ ብሎም የትግራይን ህዝብ ለማዘናጋት የሌላውን በደል፣ ጥፋትና ኃጢአት ማውራት ተያይዘውታል። ባለፈው ሃያ ሰባት ዓመታትም ቢሆን እነርሱ ትክክል እንደነበሩና አሁንም ትክክል እንደሆኑ ለማሳመን ስብከት ላይ ተጠምደዋል። በአሁን ሰዓት የህወሓት መሪዎች ይህ የእኛ ጥፋት ነው! የሚሉት አንዳች ነገርም የላቸውም። ሁሉም ነገር ወደ ሻዕቢያ፣ ወደ አማራና ወደ የፌደራል መንግሥት ብሎም ወደ ዶ/ር አረጋዊ በርሀ ማሳበብ አጠናክረው ገፍተውበታል። 

በእርግጥ፥ ወንጀለኞች ሆነው ሳሉ ሌላውን በወንጀል መክሰስ የህወሓት መሪዎች አንዱ መገለጫ ባህሪይ ነው። በነገራችን ላይ፥ የህወሓት መሪዎች ትክክለኛ ማንነትና ነባራዊ ሁኔታ ለማወቅና ለመረዳት የህወሓት መሪዎች ሲናገሩ በጥሞና ማዳመጥን ይጠይቃል። ሌላውን በኃጢያት ሲወቅሱትና ሲወነጅሉት ስንሰማ፥ የህወሓት መሪዎች ራሳቸው ከዚህ ቀደም የፈጸሙት፣ ሲፈጽሙት የኖረ፣ እፈጸሙት ያለና ሊፈጽሙት እያሰቡት ያለውን ኃጢአት ወይም ወንጀል መሆኑት ልናውቅ ይገባል። የህወሓት መሪዎች አፋቸው በከፈቱ ቁጥር በትግራይ ህዝብ ስም ስለተማማሉ ሰዎቹ ስለ የትግራይ ህዝብ ግድ የሚላቸው እንዳይመስለን። 

የህወሓት መሪዎች፥ በአሁን ሰዓት የትግራይን ህዝብ ሰውተው የሚያገኙት ጥቅም ቢኖርና ዕድሉን ቢያገኙ ኖሮ ዓይናቸው ሳያሹ ያደርጉታል። ትናንት የፖለቲካ ስልጣናቸውን ተጠቅመው የዘረፉት የህዝብ ሀብትና ንብረት ላለመመለስና በንጹሐን ዜጎችና በሀገር ላይ በፈጸሙት ወንጀል ላለመጠየቅ የትግራይን ህዝብ መብትና ጥቅም አውላላ ሜዳ ላይ ጥለው ነፍሳቸውን ለማዳን ዝግጅዎች ናቸው። ምክንያቱም፥ የህወሓት መሪዎች ለትግራይ ህዝብ ብለው የከፈሉት መስዋዕትነት በታሪክ የለም ለወደፊቱም አይኖርምና። የትግራይ ህዝብ ጭንቀታቸው አይደለም። ሲጨንቃቸው ካልሆነ በስተቀር ትዝም አይላቸውም። 

ተባራችሁ ነው የመጣችሁ ሲባሉ “የለም! ወደ መቐለ የመጣነው የትግራይ ህዝብ ለማገልገል ነው!” ነበር ያሉት። ሰዎቹ በእውነቱ ነገር ዘመኑን የሚመጥን አእምሮ ቢኖሯቸው ኖሮ ግን ለዚህ ሁሉ ውድቀትና ኪሳራ የዳረጋቸው ውስጣዊ ቁመናቸውን በመገምገም የራሳቸውን ችግር ለመፍታትና የትግራይ ህዝብ የአጀንዳቸው ማዕከል አድርገው ስራ ለመስራት ዕድሉን ከመጠቀም ይልቅ የራሳቸውን ችግር ሳይፈቱ ከፍተኛ ወጪ እያፈሱ “የፌደራሊስ ኃይሎች” የሚል ሌላ ነጠላ ዜማ ለቀው ማዜም ተያይዘውታል። ሐቁ፥ የትግራይ ህዝብ ሰላምና ደህንነት ለህወሐት መሪዎች የተለመደ የመነገጃ የፖላቲካ ቋንቋ ከመሆን ያለፈ የህወሐት መሪዎች ለትግራይ ህዝብ ሲሉ የሚከፍሉት ቅንጣት ታክል መስዋዕትነት እንደሌለ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ የተገለጠ ርካሽ ማንነታቸው ነው። የህወሐት መሪዎች እምነትና የሞራል ኮምፓስ ሥልጣንና ገንዘብ ላይ የተመሰረተ ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ እምነት የላቸውም። ሥልጣናቸውንና የፖለቲካ ሥልጣን መከታ አድርገው የዘረፉት የህዝብ ሀብትና ንብረት ጠብቀው ለማስጠበቅ ደግሞ ማንኛውም ነገር ከማድረግ አይመለሱም። 

በነገራችን ላይ፥ ነገሮች አሁን ባሉበት ሁኔታ ከቀጠሉ የህወሐት መሪዎች የትግራይን ህዝብ የበለጠ ለማሸበርና ለመቆጣጠር፤ አማራ፣ ሻዕቢያ፣ የዐቢይ መንግሥት የትግራይ ህዝብ ጣምራ ጠላቶችህ ናቸው! ተከበሃል! የሚለው ትርክታቸው የበለጠ ለማጠናከርና ከኮረና ቫይረስ የተነሳ የቀዘቀዘው የጥላቻና የጦርነት ዘመቻቸው ዳግም ነፍስ ለመዝራት ሲሉ በትግራይ ከተሞች በአንዳቸው ላይ ቦንብ ማፈንዳታቸውና ከተቻለም የንጹሐን ተጋሩ ደም ማፍሰሳቸው የማይቀር ነው። የህወሐት መሪዎች የክህደትና የጭካኔ ትርጉም ናቸውና። ላለፈው አንድ ዓመት ተኩል፥ የመሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፣ መስፍን ኢንዳስትሪያል፣ አልመዳ ጨርቃ ጨርቅ፣ ዓዲ ግራት የመድኃኒት ፋብሪካ… ብቻ የተመረጡ ስሞች እየጠሩ ሊያፈነዳ ሲል ያዝነው! ወደ ከተማ ሊገባ ሲል ከአከባቢው ነዋሪዎች በደረሰን ጥቆማ መሰረት ተልዕኮውን ሳያሳካ ደረስንበት! ወዘተ እያሉ ህዝቡን ከዚህ ቀደም በሚገባ ስላለማመዱት አፈንድተው ሲገድሉት ደግሞ የበለጠ ጉልበት ያገኛሉ። ከመካከላቸው አንድ የአገልግሎት ዘመኑ ያለቀ አልያም በተሰመረው መስመር አልስማማ ያለ አንድ አመራር በአደባባይ በጥይት ደፍተው ሻዕቢያ ነው! ዐቢይ ነው! ደመቀ ነው! የገደለው በማለት ሌላ ሁከትና ብጥብጥ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። ይህ የተካኑበት የማስመሰልና የማታለል የህወሓት መሪዎች አረመኔያዊ ባህሪይ በሚገባ ሳንረዳ የቀረን እንደሆነ ግን በምድረበዳ እንደ ተተከለችው ሸምበቆ በህወሐት መሪዎች ጥቁር ፕሮፓጋንዳ ግራ መጋባታችንና መወሰዳችን የማይቀር ነው። በሞት ጣር ውስጥ ያሉ የህወሐት መሪዎች ጩኸት መጨረሻ ሊያሳስበን ይገባል

የህወሐት መሪዎች ከምኒሊክ ቤተ መንግሥት ከተባረሩና ከሸገር ተጠራርገው መቐለ ከገቡ ድፍን ሁለት ዓመት ሆኖታል። መቐለ ከመሸጉ ጊዜ ጀምሮ አለማቋረጥ ከመጮህ አልፈው “ወታደራዊ” ሰልፍ እስከማሳየት ደርሰዋል። እውነት ነው፥ የህወሐት መሪዎች አሁን ካሉበትና ከገቡበት አጣብቂኝ ውስጥ ለመውጣት አዋጪው መፍትሔ (dominant strategy) ከፌደራል መንግሥት (በተለይ ከአማራ ክልል) ጋር ሰላምን ማውረድ ብቻ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። ሆኖም ግን በዋናነት ሰዎቹ መረጋጋት ባለመቻላቸው፤ በመቀጠል ደግሞ ለራሳቸው ያላቸውን ግምት ከእውነት የራቀና እጅግ የተጋነነ በመሆኑ፤ ለጥቆም፥ ለማሸነፍ መሸነፍ! ማለት በእነሱ ዕይታ “መልካችንን ማበላሸት ነው!” ብለው ስለሚያምኑና ለገጽታቸው (public image) እጅግ አድርገው ስለሚጨነቁ ሰላምን ላለማውረድ በእንቢተኝነት እንደ ገፉ ነው። ከዚህ የተነሳም፥ የህወሐት መሪዎች ኃጢአታቸውን ለመናዘዝ ሳይሆን ለመካድና ለማሳሳት፤ ህብረትንና አንድነትን ለመፍጠር ሳይሆን ለመከፋፈል፤ ለመገንባት ሳይሆን ለማፍረስ ተማምለው ወጥተዋል። ሐቁ፥ ሰዎቹ ወደውም ሆነ ተገደው ሰላምና ዕርቅ ካላወረዱ በቀር ይህ ሁሉ ግርግር ከፍርሃትና ከመረበሽ ያለፈ የከፋ ቀውስና አለመረጋጋት ብሎም የእርስበርስ መጠላለፍ ለመግባት እንደሆነ ለመገመት የሚቸገር ሰው ይኖራል ብዬ አላምንም። 

የዛሬ አያድርገውና የህወሐት መሪዎች ውስጥ ለውስጥ ገዝግዞ ሰዎቹን በድንገት ጥግ ያስያዘ ጆከር ይዞ ካርታውን ሲበውዝና ሲያጫውት የኖረ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በጎ ፈቃድ፣ ይለፍና ይሁንታ ወደ ሥልጣን የመጣው የኦዴፓ ፓርቲ በአሁን ሰዓት ስፍር ቁጥር የሌለው ሠራዊት እያሰለጠነ “ኬኛ ነው!” የሚለውን ሁሉ በኃይል ለመጉበጥ፤ ምርጫ የተካሄደ እንደሆነ አሸነፈም ተሸነፈም የምርጫውን ውጤት አሜን! ብሎ የማይቀበል፤ በተለይ ምርጫውን ተጠቅመው የዐቢይ አህመድ መንግሥት ለጅትመሲ ወይም ህጋዊነት ለማሳጣትና ለመሻር እያሴሩ ያሉትን የህወሐት መሪዎች ከያሉበት ሰብስቦ የሚገባቸው ስፍራ ለማስቀመጥ ብሎም በኢትዮጵያ ላይ ሂሳቡን ለማወራረድ እያኮበኮበ እንደሆነ የአደባባይ ምስጢር ነው። 

ምርጫው ሳይካሄድ ገና ለገና ድህረ ምርጫ ስፍራችን የት ይሆን? በማለት እንቅልፍ ያጡ የህወሐት መሪዎችም በፊናቸው፥ ለዐቢይ መንግሥት የእንቢተኝነት መልዕክት መላክ ከጀመሩ ወራት ተቆጥሯል። የዘረፍነው አንመልስም! ትናንት በፈጸምነው ወንጀል አንጠየቅም! ማለታቸውን “ህገ መንግስትና የፌደራል ስርዓት ይከበር!” በሚል መፈክር ደጉሰው በትግራይ ህዝብ ስም “ህዝባዊ ወያነና ነዊሕን መሪሪን ኢዩ ዓወትና ናይ ግድን ኢዩ!” ማለትን አብዝተዋል። ለዐቢይ አህመድ እጅ መስጠት የማይታሰብ ነው! በማለትም ጥግ ይዘው በተቻላቸው መጠን ሁሉ የአገሪቱን ፖለቲካ ለማቃወስ በይፋ ዝግጅታችንን አጠናቀናል እያሉ ነው። ከዚህ የተነሳም፥ በነጋ በጠባ ቁርጥ በሚመለከታቸውም በማይመለከታቸውም ጉዳይ ሁሉ የአዞ እንባ እያነቡ አለማቋረጥ እንደ ጮኹ ነው። ጥያቄው፥ የዚህ ሁሉ ሰጣገባ ፍጻሜ ምን ሊሆን ይችላል? አገሪቱ አሁን ባለችበት ግራ የተጋባ አካሄድ የምትቀጥለው እስከ መቼ ነው? ውጥረቱ በሰላም ወይስ በጦርነት ይገባደድ ይሆን? የሚለውን የሰፊውን ህዝብ ስጋት በአግባቡ ምላሽ ማግኘት መቻል አለባቸው። 

እዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር፥ ሰውም ሆነ እንስሳ ዝም ብሎ አለምክንያት እንደማይጮህ ልብ ማለቱ አስፈላጊ ነው። ሰዎች ይጮሃሉ፣ መንግሥታትና አገራትም ይጮሃሉ። እ.አ.አ ሚያዚያ 5, 2020 ዓ/ም የቬንዝዋላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮ አሜሪካ በሐሰት ክስ ልታጠቃኝ እያደባች ነው! ሲሉ በአገሪቱ ወሳኝ ቦታዎች ላይ ከባድ መሳሪያ የታጠቀ ጦር ማስፈራቸውንና በተጠንቀቅ ይቆም ዘንድም ትዕዛዝ ከማስተላለፋቸው በተጨማሪ፤ ለመላ የዓለም መሪዎች ባልተለመደ ሁኔታ እርዱኝ! በማለት ሲጮኹ ተመልክተናል። ከኮቪድ አስራ ዘጠኝ የተነሳ ይለምናሉ፤ ከኮሚኒስት አገራት - ከኩባ፣ ከራሽያና ከቻይና እርዳታ ይቀበላሉ ተብለው የማይገመቱና የማይጠበቁ እነ አሜሪካና ጣሊያን የመሳሰሉ ኢንዳስትርያል አገራት የእርዳት ያለህ! በማለት ሲጮኹ አይተናል። የሚያስጮህ ነገር ሲፈጠርና ሲከሰት የማይጮህ ነገር የለም። ሁሉም ይጮሃል። የጠገበና ያማረው፣ የተበደ፣ ፍትህ የተጓደለበት፣ ያዘነ፣ የደነገጠ፥ ግለሰብ፣ ህዝብና አገር ይጮሃሉ። ጩኸት፥ የሐዘን፣ የድረሱልኝ ጥሪ አልፎ አልፎም የጥጋብ መገለጫ ሊሆን ይችላል። የተፈጥሮ ነገር ሆኖ ዘመኑን በሙሉ ሲጮህ የሚኖር ፍጡርም አይታጣም። ቁም ነገሩ፥ ሰውም ሆነ ሌላ ለሚጮኸው ጩኸት መንስኤ ምክንያት እንዳለው መረዳቱ ላይ ነው። 

ሰውም ሆነ ሌላ ለጩኸታቸው እንደ ምክንያት ሊጠቀሱ ከሚችሉ በርካታ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው ታድያ ፍርሃት ተጠቃሽ ነው። ሰው ሲፈራ፤ አውሬ ያየ እንደሆነ ይበላኛል! ይውጠኛል! ሲል ረዳትና ታዳጊ ፍለጋ ይጮሃል። የማይመች ሁኔታ ውስጥ ራሱን ሲያገኝ በህልሙም በውኑም ይጮሃል። መንግስታም እንዲሁ ይጮሃሉ፤ ሉዓላዊነታቸው በጉልበተኛ ሲደፈር ለተባበሩት መንግስታትና በኢኮኖሚና በወታደራዊ አቅማቸው ለፈረጠሙ ኃያላን ስምታቸውን ማቅለጥ የተለመደ ነው። ጩኸት አንዱ የፍርሃት መገለጫ ነውና። ፍርሃት ደግሞ ያልተጠበቀና የማይቀር ነገር ይወልዳል። ፍርሃት ከሚወልዳቸው አሰቃቂና አስደንጋጭ ክስተቶች አንዱ ታድያ ጦርነት ነው።  ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣውን አለመረጋጋትና ፍርሃት የወለደው የህወሐት መሪዎች ጩኸት በአገሪቱ ላይ እልቂትንና ደም መፋሰስን ሊያመጣብን እንደሚችል የታሰበሰት አይመስልም። የፌዴራል መንግሥት እንደ ስልት በዝምታው ቢገፋበትም የህወሐት መሪዎች አሁን ባሉበት ሁኔታ ረጅም ርቀት ሊጓዙ እንደማይችሉ አሳምረው ያውቃሉ። ካሉበት አጣብቂኝ ህይወት ውስጥ መውጣትን ይሻሉ። ይህን ለማድረግ ደግሞ አማራጭ ነው ያሉቱን መንገድ ሁሉ ለመጠቀም ወደኋላ አይሉም። ሁሉም ሞት ነውና። 

የህወሐት መሪዎች የሰልፍ መዓትና ማለቂያ የሌለው ጩኸት ምንጭ ምንም እንኳ “ህገ መንግስት ይከበር! ፌደራል ሥርዓት ይከበር! የህግ የበላይነት ይከበር!…” ወዘተ በሚሉ መፈክሮች የተደጎሰ ቢሆንም ሐቁ ግን ከዚህ የራቀ ነው። የህወሐት መሪዎች የጩኸት ምንጭ፥ ከዛሬ ነገ እንያዛለን፣ ተሰባስበን ወደ ውህኒ እንወርዳለን፣ መዋረዳችን ነው፣ አለቀልን! የሚል አለመረጋጋት፣ ፍርሃትንና ስጋትን የወለደው ጩኸት ነው። ይህ ዓይነቱ ጩኸት ደግሞ አደገኛ መሆኑን ብቻ ሳይሆን አገሪቱ ወደ አላስፈላጊ ጦርነትና ደም መፋሰስ ሊያስገባት እንደሚችል በመግቢያዬ ያሰፈርኩትን የቱስይዲደስ ትራፕ ልብ ማለቱ ለህወሐት መሪዎች ስጋትና ፍርሃት የወለደው ጩኸት ትክክለኛና ተገቢ መልስ እንድንሰጥ ይረዳናል። ነገሮች በጥንቃቄ ከማየትና ከመገምገም ውጪ በፈረሰኛ ብዛት ጦርነቱን ማሸነፍ እንችላለን! ሶማሌ ላይ የሆነውን በደቡብና በአማራ ክልል ተደግሞ ውጤታማ ሆኖ ሊሆን ይችል ይሆናል ይሁን እንጅ ይህን ዓይነቱ አፈጻጸም በትግራይ ላይ ለመድገም ማኮብኮብ ግን የዋህነት ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ታድያ፥ መንግሥት የአገሪቱን ሰላምና የህዝቦችዋን ደህንነት ጠብቆ ለማስጠበቅ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈልና ሌላ አማራጭ ስትራቴጂ እንዲነድፍ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ።

የህወሐት መሪዎች ለምን ጦርነትን ይመርጣሉ?

በጥቂቶች የሚዘወረው ህይወት አልባ የህወሐት ማዕከላይ ኮሚቴ ወንጀለኞቹን አሳልፎ ከመስጠት ይልቅ ከሰመጡ የከሰሩ የህወሐት መሪዎች ጋር አብሮ ለመስመጥ ቆርጧል። ሰዎቹ ከተለመደው ጩኸታቸው አለፈው ወታደራዊ ሰልፍ በማሳየት ጦርነት የማይቀር እንደሆነና ጦርነት የመግጠም ፍላጎትና ሸውሃት እንዳላቸውም በአደባባይ አሳይተዋል። ምንም እንኳ የሰልፉ ውስጠ ወይራ የስዎቹ የፍርሃት ጥግና የሞት ጣር ነጸብራቅ መሆኑን ባንስተውም። እውነት ነው፥ የህወሐት መሪዎች ተፈጥሯአዊ ባህሪይ ለማያውቅ ዜጋ ሰልፉን አይቶ ግራ ሊጋባና ከዚህም አልፎ የአገሪቱ የፖለቲካ አሰላለፍ ላይ የተዘባ አመለካከት እንድይዝ ሊገደድ ይችላል። ሐቁ ግን ቀደም ስል በስፋት እንዳተትኩት ከዚህ ሁሉ የራቀ ነው። በሞት ጣር ውስጥ የሚኖር ቀቢጸ ተስፋ መጻጉእ ሞትን እንደሚጠራ፣ እንደሚናፍቅና እንደሚሻ ሁሉ የህወሐት መሪዎች ወቅታዊ ሁኔታም ተመሳሳይ ነው።

የህወሐት መሪዎች እነሱ እንደሚያስቡት ብልሆችና የላቀ የፖለቲካ ልምድ ያላቸው ሰዎች አይደሉም እንጅ ብልሆች ቢሆኑ ኖሮ የገጠማቸው ፖለቲካዊና ማህበራዊ ኪሳራና ውድቀት በአሉታዊ መልኩ ከማየትና ዘራፍ ከማለት፣ የገጠማቸው ሽንፈትም በደመቀና በገዱ ከማሳበብና ከአማራና ከዐቢይ መንግሥት ጋርም አለን! የማለት ያህል እንካሰላንቲያ ለመለዋወጥ አላስፈላጊ ንትርክና ሰጣገባ ውስጥ ከመግባት ይልቅ የገጠማቸው ፖለቲካዊ ውድቀትና ኪሳራ በጸጋ ተቀብለው ሁኔታዎች በጣም ስሙዝ በሆነ መልኩ ለማስኬድ፣ ለመነጋገር፣ ለመደራደርና ሰጥተው ለመቀበል ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ ይችሉ ነበር። የህወሐት መሪዎች መውደቅና ወደ መቐለ ከተማ መሰብሰብም ለትግራይ ህዝብ እንደ ትልቅ ድል ሆኖ ይቆጠር ነበር። ሰዎቹ ሁልጊዜ ማታለል እንደሚችሉና ሌቦችና ወንጀለኞችም ስለሆኑ ግን ሌብነታቸውና ወንጀለኝነታቸው እንዳይታወቅባቸው በትግራይ ህዝብ ስም ማድበስበስን ተያያዙት። በባህሪያቸው ጊዜያዊ ጥቅም አሳዳጆች (ታክቲካል) ከመሆናቸው የተነሳ፤ በዋናነት ደግሞ የራሳቸውን ጥቅም እንጅ የትግራይ ህዝብ ጥቅምና መብት መከበር ግድ ስለማይላቸው፤ እንወክለዋለን ለሚሉት ህዝብም ለሉዓላዊነቱ ክብርና እውቅና ስለማይሰጡ የህዝቡን ሰላምና ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥልና የሚጎዳ ጊዜው ያለፈበት የ60ዎቹ የአሻጥር ፖለቲካ ውስጥ ዳግም ተዘፍቀዋል።

የፖለቲካ ሽንፈት ተከናንበው ጥጋቸውን የያዙ ሰዎች አሁን ድረስም የፖለቲካ ጌሙን መቋቋም ተስኗቸው በዝረራ በተደጋጋሚ በሽንፈት ላይ ሽንፈት እያስተናገዱ ያሉ ሰዎች ወታደራዊ ሰልፍ በማሳየት በጦርነት ማሸነፍ ይችላሉ! ብሎ የሚያምን ሰው ካለ በእውነቱ ነገር የዋህ ነው፤ አንድም፥ የዓለማችን ነበራዊ ሁኔታ ካለመረዳት የመነጨ ብቻ ነው ሊሆን የሚችለው። ከነተረቱ “በጃንሆይ ጊዜ የደነቆረ ጃንሆይ ይሙት!” እንዳለ ይኖራል እንደሚባለው የህወሐት መሪዎች አሁን የገቡበት አዙሪት ውስጥ ሊገቡ የቻሉበት ዋና ምክንያትም ዘመኑን በሚገባ መዋጀት ስላቃታቸውና “ገ እናበሉኻ ዶ ትጋገ” ተብለው ሲመከሩም ሰዎቹ ለመማር ዝግጅዎች ስላይደሉ ነው። 

በእርግጥ አንዳንዶቻችን፥ ዞሮ ዞሮ የሚፈለገው ሰላምን ማውረድ ነው! ሰዎቹ ለክብራቸው ይህን ያህል ከመጨነቅ ይልቅ በዘለቄታነት ለእነርሱም የሚጠቅመው ሰላማዊ መንገድ በመምረጥ የዘረፉት የህዝብ ሀብትና ንብረት ውስጥ ለውስጥም ቢሆን አስረክበው ለምን ሰላምን አያወርዱም? መንገድ ያልጠፋ በጦርነት ካልሆነ በስተቀር! የሚሉበት ምክንያት ምንድ ነው? በማለት ከሚገባ በላይ ራሳችንን እናስጨንቅ ይሆን። ሐቁ ያለው ግን ወዲህ ነው፥

አንድ፥ መጽሐፍ፥ አቤሜሌክም ወደ ግንቡ ቀርቦ ይዋጋ ነበር፥ በእሳትም ሊያቃጥለው ወደ ግንቡ ደጅ ደረሰ። አንዲትም ሴት በአቤሜሌክ ራስ ላይ የወፍጮ መጅ ጣለችበት፥ አናቱንም ሰበረችው። እርሱም ፈጥኖ ጋሻ ዣግሬውን ጠርቶ፦ እኔን ሴት ገደለችው እንዳይሉ ሰይፍህን መዝዘህ ግደለኝ አለው፤ ጕልማሳውም ወጋው፥ ሞተም። የእስራኤልም ሰዎች አቤሜሌክ እንደ ሞተ ባዩ ጊዜ እያንዳንዱ ወደ ስፍራው ተመለሰ። እንዲሁ ሰባ ወንድሞቹን በመግደል አቤሜሌክ በአባቱ ላይ ያደረገውን ክፋት እግዚአብሔር መለሰበት (መጽ. መሣፍንት 9፥ 50) እንዲል። በጽሑፉ በሰፊው ለማብራራት እንደሞከርኩ ጠፍጥፈን በሰራናቸው ግልሰቦችና ፓርቲ በሚሏቸው አካላት በተለይ እጅግ አድርገው በናቁትና በተጸየፉት በዐቢይ አህመድ እጅ የህወሐት መሪዎች ታሪክ በውርደትና በኪሳራ ተጠናቀቀ! ተብሎ ታሪክ እንዲጻፍ አይፈልጉም። ይልቁንም፥ ለትምክህተኛ መንግሥት እጅ አንሰጥም በማለት ከትምክህተኛውን ኃይል ጋር ተፋልመው በመስዋዕትነት አለፉ ተብለው ውርደታቸውን በክብር ለመሸፋፈን ስለሚሹ ነው። በነገራችን ላይ፥ ነፍስ ይማር! መጋቢት 1987-2010 ዓ/ም የህወሓት መሪዎች ታሪክ በውርደትና በበታላቅ ኪራ ተጠናቀቀ። ተብሎ ታሪክ ተከትቧል። በገበያ ላይ የዋለው “አንደመርም/የተከበሩ ወንጀለኞች” መጽሐፍ ያንቡ!

ሁለት፥ ትናንት አገር አንቀጥቅጦ ሲገዛ የነበረውን የሜቴክ ጄኔራል ክንፈ ዳኘው የተያዘበትና ከትግራይ ወደ አዲስ አዲስ አበባ የመጣበት ሁኔታ የህወሐት መሪዎች በወባ በሽታ የተመቱ ያህል በመሪዎቹ ላይ የፈጠረውን የስነ ልቦና ቀውስና መደናገጥ፥ በቁማችን ተዋርደን ከምንሞት ሞታችን አይቀር በጦርነት መሞት ይሻላል! ብለው እንዲያምኑ ስላስገደዳቸው ነው። የበሰበሰ … ዝናብ አይፈራም! ይሉሃል ይህ ነው። ሰዎቹ አሟሟታቸውን ለማሳመር ምርጫ ላይ ናቸው ለካ። በርግጥ ነፍሳቸው ከስጋቸው አልተለየችም እንጅ ሰዎቹ በቁማቸው ሞቷል። 

በነገራችን ላይ፥ ዛሬ ስላልተመቻቸውና ስለተከፉ በአደባባይ አፋቸውን ከፍተው እየረገሙት ያለውን መንግሥትና እያበሻቀጥዋት ያለችውን አገር ነገ ከአክሱምና ከፕላኔት ሆቴሎች ተገላግለው ወደ ሸገር የመመላለስ ዕድሉ ሲያገኙ፣ ሲሰጣቸው፣ ሲፈቀድላቸውና  ሲሞቆቃቸው ደግሞ በዛችው ተራጋሚ አንደበታቸው የፍቅርና የአንድነት መዝሙር ለመዘመር ማንም አይቀድማቸውም። በጠላትነት ፈርጀው ሲያወግዙትና ሲረግሙት፤ ሲያጣጥሉትና ሲያበሻቅጡት የኖሩትን ሁሉ ለማሞገስና ለማወደስ ሽርጉድ ሲሉ ለማየት ያብቃዎት። ያን ጊዜ ጠላት የነበረ ወዳጅ፥ ወዳጅ የነበረ የትግራይ ህዝብ ደግሞ ጠላታቸው ይሆናል። ታድያ፥ በጎረቤትዎ የማስመሰልና የማሽቃበጥ ባህሪ እየተገረሙ ዘወትር አበስ ገበርኩ! እያሉ በራስዎ የሚያፍሩ ከሆነ፤ ነገ በአደባባይ የሚያዩት የህወሐት መሪዎች እስስታዊ የመገለባበጥ ባህሪይ ሲያዩማ ምን ሊሉ ይሆን? የህወሐት መሪዎች እንደሆነ ኃፍረት አያውቃቸውም። ጊዜያዊ ጥቅም ለማግኘትና በውሸት ላይ የተገነቡት ሐሰተኛ ክብር ለመጠበቅ ነፍሳቸውን ሽጠው ሲሲለፉ ሊያዩ ስለሆነ ራስዎን ከወዲሁ ያዘጋጁ። 

ለዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የምለግሰው ምክር ይህ ነው 

የፌደራል መንግስት የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብም ሆነ ከኤርትራ ህዝብ ጋር እንደ ማንኛውም አጓራባች ህዝብ በሰላምና በፍቅር በመከባበር አብሮ እንዲኖር ህገ መንግሥታዊ ግዴታውንና ኃላፊነቱን በመወጣት የህወሐት መሪዎች መነጠልና ሰዎቹ በኤርትራ መንግስት ላይ ይከተሉት የነበሩትን ታክቲካል ፖሊሲ ያለፈ “watch and see strategy” ተግባራዊ በማድረግ የራሳቸውን መድኃኒት እንዲጎነጩ በማድረግ በቁማቸው ማመናመንና ለዕርቀ ሰላም እንዲገዙ ማስገደድ። ሰዎቹ በህይወት እያሉ የሞቱ ያህል እንደሌሉ በመቁጠር በዝምታና በአንክሮ በቅርብ ርቀት መመልከት ራሽያ በዩክሬን ላይ እየተከተለችው ያለው ጥሩ፣ አዋጪና የተፈተነ ስትራቴጂ ነውና። 

በነገራችን ላይ፥ የህወሐት መሪዎች የሳቱትና ያልገባቸው ነገር ቢኖር አሁን ያለው ውጥረትና አለመግባባት ዕልባት ለመስጠት ጊዜ በወሰዱ ቁጥር ሌላው ይቅር የመኖርና የአለመኖር ዕጣ ፈንታቸው የሚወሰነው በሌላ አካል እጅ እንደሚወድቅ ገና አልገባቸውም። ልብ ይበሉ፥ ከሚኒሊክ ቤተ መንግሥት ተባረው መቐለ ለመመሸግ ሲገደዱ በትግራይ ህዝብ ስር ጥላ ከለላ ለማግኘት ሲሉ ከአማራ ክልል ደምነትንና ጠላትነት የፈጠሩ እነሱ ናቸው፤ እኔም ሆንኩ የትግራይ ህዝብ ከአማራ ህዝብ ጋር ጠላትነት የለንም። ሌላው ቀርቶ ትግራይ እንደ አገር ለመቆም ብትገደድ፣ ብትችልና የሁሉም ስምምነት ቢሆን እንኳ የአማራ ህዝብ ምን ጊዜም የትግራይ ህዝብ ስትራቴጂክ ወዳጅና ጎረቤት ህዝብ ነው። ይህ የህወሐት መሪዎች ሊቀይሩት የማይችሉት ሐቅ ነው። የህወሐት መሪዎች፥ ከአማራ ክልል ጋር ሰላም ለማውረድ ደግሞ በትዕቢት የተወጠረው ልባቸው መተንፈስ አለበት።

የህወሐት መሪዎች የአፋር ክልል አመራሮች ከጎናቸው ለማሰለፍ ይሄ ነው የማይባል የትግራይ ህዝብ ሀብትና በጀት በክልሉ አመራሮች ላይ እያፈሰሱት ነው። ይህም ሆኖ ግን አፋር አስተማማኝ አጋር ሊሆን አይችልም፣ የከፋፈለን የህወሐት መሪዎች ናቸው! ብለው ስለሚያምኑ የህወሐት መሪዎች ለመበቀል ጥሩ አጋጣሚ ብቻ ነው የሚፈልጉና እየተጠባበቁም ያሉ። ኤርትራ፥ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ከህወሐት መሪዎች ጋር ያልተወራረድኩት ሂሳብ አለኝ! ባይ ስለሆኑ የህወሐት መሪዎች ለአቶ ኢሳይያስ ምን ዓይነት ገጸ በረከት በማበርከት ሊያለሳልስዋቸው እንደሚችሉ ስላልታወቀ እስከዛ ድረስ ግን ኤርትራ የህወሐት መሪዎች ተስፋ ልትሆን አትችልም። እንደውም የህወሐት መሪዎች በአቶ ኢሳይያስ ተስፋ የቆረጡ ይመስላሉ። በሱዳን በኩል የአልበሽር ከሥልጣን መውረድ ተከትሎ ሙሉ በሙሉ ለማለት ይቻላል ተስፋቸው ጨላልመዋል። ታድያ፥ በዚህ ሰዓት የዶ/ር ዐቢይ መንግሥት የናዚ ካርቦን ኮፒ የህወሐት መሪዎች የሚፈልጉትን በሚገባ በማጤን መሻታቸውን እንዳይሰጣቸው አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ፤ የሰላም ሚኒስተር ተብሎ የተሰየመውና የተቋቋመው ቢሮም ከእንቅልፉ ነቅቶ ስራ ይሰራ ዘንድ በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እወዳለሁ። 

ሁሉም የተጣለበት ኃላፊነት ለመወጣት ያቃተውና በእውነትና በጽድቅ ላይ ለመሸፈጥ የተነሳ እንደሆነ ግን በጽሑፌ መግቢያ እንዳሰፈረኩት በአንድ አገር አንድ መንግስት ለመፍጠርና አንዱ ጡንቻውን ለማሳየት ጥጉ የያዘ ቡድን ደግሞ እንዲሁ የዘረፈውን ላለመመለስና በፈጸመው ወንጀል ላለመጠየቅ ፍልሚያ ውስጥ መግባትታቸው የግድ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰላምና ደኅንነት ነው ሲሉ ያን ጊዜ ምጥ እርጕዝን እንደሚይዛት ጥፋት በድንገት ይመጣባቸዋል ከቶም አያመልጡም” እንዲል ፖለቲከኞች አፋቸው ሰላም እያወራ ለጦርነት መዘጋጀት የተለመደ ነውና ታድያ ያን ጊዜ፥ ትግራዋይ በመሆኑ የሚያልቅ፤ ኦሮሞ በመሆኑ የሚተርፍ ሰው አይኖርም!

Email: mahbereseytan@gmail.com

Back to Front Page