Back to Front Page

ዶር. አረጋዊ በርሀ (በሪሁ)፡ የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ ማን ቀሰቀሰው?

ዶር. አረጋዊ በርሀ (በሪሁ)፡ የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ ማን ቀሰቀሰው?

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 01-13-20

በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ጀርመናዊው የታሪክ ፀሃፊ ሊዮፖልድ ቮን ራንኪ ታሪክ እንዴት መፃፍ እንዳለበት ሲመክር እንዲህ አለ፡- ልክ እንደነበረው፡፡ በህወሓት የ45 አመት ታሪክ ውስጥ፤ጥቃቅን ግን በርካታ የሆኑትን የውስጠ ፓርቲ ፍትግያዎቹን ትተን፤ ድርጅቱን ከመሰረቱ የናጡ ሁለት ሕንፍሽፍሾች ተከስተዋል፡፡ በፓርቲ ፖሊቲካ አለም ውስጠ ልዩነት ጤንነት ነው፡፡ ፖለቲካ ፓርቲ የሚመሰረተው በአበይት አቋሞች ላይ የጋራ አመለካከት ሲኖር ብቻ እንጂ አባላቱ በሙሉ በሁሉም ጉዳዮች ላይ አንድ አይነት አመለካከት ስላለቸው አይደለም፡፡ የውጩ እንጂየውስጡ ድምፅ የማይሰማ ፓርቲ በርግጠኝነት የአምባገነንነት ባሕርይ አለው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ ሐወሓት ውስጥ የተከሰቱት ሁለት ዋና ዋና ሕንፍሽፍሾች የመጀመሪያው በ1969 ዓ.ም. በትግል ወቅት የተከሰተ ሲሆን ሁለተኛው ግን ከድል በኋላ በ1993 ዓ.ም. ነበር፡፡ ሁለተኛው ሕንፍሽፍሾች እኩል አቅም በነበራቸው አመራሮች መካከል የተካሄደና ሳሩ የተጎዳበት የዝሆኖች ትግል ነበር፡፡ ስለዚህ ሕንፍሽፍሽ መንስኤው ሆነ ውጤቱ በሁለቱም ጎራ አባላት በኤሌክትሮኒክና በህትመት ሚድያ በጥልቀት ተዘግቧል፤ተተንትኗልም፡፡ በህወሓት ታሪክ ወሳኝ ሚና የነበራቸው አመራሮች ድርጅቱን የለቀቁበት የሁለተኛው ሕንፍሽፍሽ በጊዜ ሂደት ድርጅቱን አዳክሞታል፡፡ ከዚህ በላቀ ደግሞ ድርጅቱን የለቀቁት አመራሮች በተቃዋሚነት ፖለቲካ ስለተሰማሩ ሰላም መልካም አስተዳደርና ልማት ግንባር ቀደም አጀንዳ መሆን በሚገባው ትግራይ ክልል ውስጥ አንዱ ባንዱ ላይ መሰናክል እያበጀ በመሆኑ ህዝቡ ግራ እየተጋባ ነው፡፡ የሁለተኛው ሕንፍሽፍሽ ዋና መንስኤ በትግራይ ውስጥ ባለ ዴሞክራሲ፤ መልካም አስተዳደርና የልማት እቅድ አፈፃፀም ሳይሆን በኤሪትርያና ኢትዮጵያ ጉዳይ ነበር፡፡

የመጀመሪው ማለት የ1969 ሕንፍሽፍሽ የተከሰተው ህወሓት ከተመሰረተች በቅጡ ሁለት አመት እንኳ ሳይሞላት ነበር፡፡ ነገሩ እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡ ታጋዩ ገና በአላማ ፍቅር በስሜት ግለት ላይ እያለ፤ ያውም አምስት መቶ ያልሞላ የታጋዮች ቁጥር በያዘ ድርጅት፤ ደርግ ህወሓትን ከጅምሩ እንዳይውጣት በሁሉም ዘንድ ስጋት በነበረበትና ጥንቃቄ በሚደረግበት በዛ ከባድ ጊዜ እንዲህ አይነት ውዝግብና ይህን ተከትሎም ብዙ አሳዛኝ ክስተቶች መፈጠራቸው ታላቅ እንቆቅልሽ ነበር፡፡ ይህ ውስጠ ፓርቲ ውዝግብ የተከሰተው ዶር. አረጋዊ በርሀ (የበርሃ ስሙ በሪሁ) የህወሓት ሊቀመንበር በነበረበት ወቅት ነበር፡፡ ምንም እንኳን ይህ የመጀመሪው ሕንፍሽፍሽ ከሁለተኛው ሕንፍሽፍሽ በላቀ ህወሓትን የውድቀት አፋፍ ላይ ያደረሳት ቢሆንም ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ማስመሰሉ ህወሓት ውስጥ እንደ ፖለቲካ ባህል የተቆጠረ ይመስላል፡፡ ብቻ አልፎ አልፎ በስብሰባ ላይ ወይንም በሚድያ የህወሃት የ17 አመታት ገድል ሲተረክ የ1969 ሕንፍሽፍሽ እንደዋዛ ይነሳና ህወሓትን ለማፍረስ በደርግ የተላኩ፤ አመራሩን እኛ ካልያዝነው የሚሉ፤ ርሃብ፡ ጥማት፡ ብርድና ሃሩር መቋቋም ባቃታቸው ግለሰቦች የተጎነጎነ ግን በጀግንነት የከሸፈ ሴራ ነበር እየተባለ ወደ አንድ ወገን ያጋደለ፤ንቀትና ማን-አለብኝነት በተላበሰ መንፈስ ይነገራል፡፡ ማንም ሆነ ማንም አብሮ ይሳተፍ የዛ ሕንፍሽፍሽ ሙሉ ሃላፊነት መውስድ ያለበት ዶር. አረጋዊ በርሀ ነው፡፡ ከህወሓት በራሱ የግል አለመግባበት ለቆ አውሮፓ ከኖረ በኋላ አሁን ወደ ትግራይ ፖለቲካ በተለመደው የአምባገነንነት ሰብእናው ተመልሶ ያለኔ አዋቂ የለም በሚል የበላይነት አባዜ አዲስ አበባ ተቀምጦ የትግራይን ፖለቲካ እያመሳቀለ ይገኛል፡፡ ከዚህ በፊት ዶር. አረጋዊ በርሀን የሚመለከቱ ፅሁፎች በአይጋ ፎረም አውጥቻለሁ፡፡ በሁሉም ፅሁፎቼ ትኩረት የሰጠሁት የዶር. አረጋዊ ፖለቲካ አካሄድ ከትግራይ ህዝብ አንድነትና ሰላም ጋር የሚጣረስ ሆኖ ስላየሁት አቧራ ማጨሱን አቁሞ ለትግራይ ህዝብ ሰላም በሚደረገው ጥረት የበኩሉን የተረጋጋ ተሳትፎ እንዲያደርግ ምክር ለመለገስ ነበር፡፡ ከትግል ሜዳ በትግስት ቆይተው ደርግን አሸንፈው ለትግራይ ህዝብ አንፃራዊ ሰላም ያጎናፀፉትን እየዘለፉ የድህረ ድል አርበኛ መሆን የሞራል ዝቅጠት ነው፡፡

Videos From Around The World

ባለፈው ሰኔ ወር ዶር. አረጋዊ በርሀ ትግራይ ውስጥ የፖለቲካ አልጋ ባልጋ እንዲሆንለት ሲጠብቅ አንድ ትራስና አንድ ፍራሽ ብቻ ያለበት ክፍል ውስጥ ታሰርኩ በማለት ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ የለም እያለ በአስሩ ሚድያ ሲያስተጋባው ከረመ፡፡ እንግዲህ አምላክ አፈር ላበደረ ጤፍ አይመለስ! ይህ አውሮፓ የፈጠረው የመርሳት በሽታ ፍራሽ ላይ ሳይሆን አፈር ውስጥ የተኙት ሰዎችንም አስረስቶ ነው? ወርዒ ሸለቆ ውስጥ ወይኔ ልጆቼ እያሉ አፈር ውስጥ የገቡት ሽማግሌስ ተረሱ? ዶር. አረጋዊ መቐለ ሄዶ ድብደባ እንደደረሰበት እንደጉድ ሲናገር ነበር፡፡ ይቺ ዱላ ሌላ ሰው ሲመታባት ስሜት አትሰጥም፤ በራስ ላይ ስትነሳ ግን በጣም ታስጮሃለች፡፡ ከሽሬ ደርግ የላከው ሰላይ ነው በሚል በገመድ ታስሮ ሲደበደብ ያደረው ምስኪን የሰው ፍጡር የታሰረበት ገመድ የክንዱን ጡንቻ ዙሪያውን በጥልቀት ቆርጦታል፤ አይኑ ሙሉ በሙሉ ደም ጎርሷል፤ ሰውነቱ ወባ እንደያዘው ይንቀጠቀጣል፡፡ ያ እንዳይበቃ ዓዲ ዳዕሮ በነበረው ጊዜያዊ አስር ቤት ተወረወረ፡፡ ይህ ኢሰብአዊነት የማን ድርጊት ነበር?የመቐለ ወጣቶች ድብደባ እንዳደረሱበት የተናገረው የኔን የበለጠ ትኩረት ስቧል፡፡ የመቐለ ወጣቶች ዶር. አረጋዊን ለመደብደብ ህወሓት እስክትልካቸው ድረስ ይጠብቃሉ ብየ አላስብም፡፡ በ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ ዶር. አረጋዊ ሚና ምን እንደነበር የሚተርክላቸው አባት፤ ታላቅ ወንድም፡ ወይንም ሌላ የደረሰበት ወይንም የሆነውን የሰማ ሰው ያጣሉ ብሎ መገመት ይቻላል? የትግራይ ምርጫ አሽንፎ መቐለ ከተማ ላይ ለመቀመጥ ማሰቡስ ራሱ በቀየሰው የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ የትግል ሞራላቸው ተሰልቦ፤ የመጣባቸው ነገር ምን እንደሆነ በቅጡ ሳይገነዘቡ ህይወታቸውን ለማዳን ከድርጅቱ የሸሹ፤ መሽሽ ሳይሳካላቸው የቀሩና የተጎዱ፤ ግራ እንደገባቸው ደርግ ፀረ-ህወሓት ሃይል አድርጎ የተጠቀመባቸውና ኋላም ወያኔ ናችሁ በማለት ራሱ ወህኒ ያጎራቸው፤ ከሕንፍሽፍሹ ጋር በተያያዘ ህይወታቸው ተበላሽቶ የቀሩ የእንደርታ ልጆች መራራ ታሪክ የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ነው፡፡ ከህወሓት ድል በኋላም በእንደርታ ህዝብ ላይ መረን የለቀቁ ቃላት ሲነገሩና አሰልሳይ የሆነ የኢኮሚ ቅጣት ሲደርስበት ቆየ፡፡ ጅራፍ ራሱ መትቶ ራሱ ሲጮህ! እንዳይታገል አደረጉት ስላልታገለ ቀጡት፡፡

1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽአነሳስ ከኔ የበለጠ የሚያውቀው ሰው አለ ብየ አልገምትም፤ ግንባር ቀደም ተጠቂ የነበርኩት እኔ ስለነበርኩ፡፡ ከድርጅቱ ለቅቄ ከወጣሁ በኋላም አብሮኝ ለደርግ እጁን ከሰጠው የእንደርታ ተወላጅ የመቐለ ልጅዶር. ታደሰ ኣባዲ (ኒክስን-ነፍስ ይማር) ጋር አንድ ላይየ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ መሪዎች ተብለን ተሰይመን ስማችን በህወሓት ታሪክ ውስጥ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የአባየን ለእማየ ወስዶ ልክክ የተባለው ይህ ነው፡፡ ህወሓትን ለማፍረስ ፍላጎቱ ቢኖረኝ ለደርግ እጄን ሰጥቼ ስገባ መሳሪያ ሳልይዝ መግባቴ ብቻ ሳይሆን መቐለ ከተማ ውስጥ ሲሰሩ የነበሩና በቅርብ የማውቃቸው የህወሃት አባላትን እንዳጋልጥ ስጠየቅ ትብብር አለማድረጌ ምስክር ነው፡፡ ከስድስት አመት በኋላ ፖሊስ አንድ ማስረጃ ሰነድ በማግኘቱ (ሰነዱ ትክክኛ ነበር) ክስ መስርቶብኝ ማእከላዊ ታሰርኩ፡፡ የተወነጀልኩት ከ1969 ዓ.ም. ጀምሮ የህወሓት ተልእኮ ስትፈፅም ነበር ተብየ ነው፡፡ የሞት ቅጣት ሊያስወስን የሚችለው በእግዚአብሄር ሃይልና በህፃናት ልጆቼ አምላክ ድጋፍ አራት አመት ታስሬ ወጣሁ፡፡ ሁለት ያጣ ጎመን ማለት ይህ አይደል፡፡ ከዛ በኋላም ከህወሓት ነፃ ነው ብሎ የሚያምነኝ ስላልነበረ በሰራሁባቸው ቦታዎች ሁሉ አንድም ቀን ሰላም አግኝቼ አላውቅም፡፡

ነብሱን ይማራት ታላቅ ወንድሜ የሆነውህንደያ አበራ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ የህወሓት አባል በመሆን በሙሉ ልብ ሲያገለግል የነበረ የእንደርታ ተወላጅ ነው፡፡ በርሃ እያለ የትግል ሞራሉን የሚነኩ ብዙ ችግሮች እንዳጋጠሙት መረጃ አግኝቻለሁ፡፡ እንዴት እንደተፈጠረ እስካሁንም ባላወቅነው ምክንያት መቐለ ከተማ በደርግ ካድሬዎች እጅ ከገባ በኋላ ነባር አባል መሆኑን ብቻ ሳይሆን ክፍለህዝብ መኖሩንም ስለደረሱበት ፈትተን እንድንለቅህ ከፈለግህ የምታውቀውን የህወሓት ምስጢር አንዲት ሳታስቀር ንገረን እያሉ በቶርች እግሩን አበላሹት፡፡ እሱ ግን አሻፈረን ስላለ ህወሓት ለዘላለም ትኑር እያለ በካድሬዎች ጥይት ተደበደበ፡፡ እስካሁን ህወሓት ውስጥ ጠላት ይመስል የህንደያ አበራ ስም አይነሳም፡፡ አስገደ ገ/ስላሴ ጋህዲ በተባሉት መፅሃፎቹ የተረሱ ጀግኖች በሚል የህንደያ አበራን ስም አራት ቦታ ላይ አስፍሮታል፡፡ ይህ እኔ የማውቀው፤እኔ ራሴ እድሜ ልክ የተጎዳሁበትና ውድ ወንድሜን ያጣሁበት የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽጦስ ነው፡፡ በስሜት በርሃ ከገባ በኋላ ግራ ተጋብቶ የተመለሰው የእንደርታ ወጣት የደረሰበትን የሞራል ስብራት ቤቱ ይቁጠረው፡፡ ሌላ በለኮሰው እሳት አንድ ወገን ተቃጣይ ሌላው ወገን ሟቂ ሆነናል፡፡

ለትግራይ ህዝብ ሰላምና አንድነት ስል የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ እውነተኛ ታሪክን ቀብሬው ለመቅረት ወስኜ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ዋናው ተዋናይ የነበረው ዶር. አረጋዊ ምንም እንዳልተፈጠረ ሆኖ በትግራይ ፖለቲካ ላይ መልሶ የመሪነት ሚና ለመጫወት ሲታገል የማይበት አይን ሊኖረኝ ስላልቻለ፤ በእንደርታ ህዝብ ላይም አጉል ንቀት እያንፀባረቀ ያለ መስሎም ስለታየኝ፤ ከእንደርታ በመጡ ታጋዮች የተመራ የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽየሚባል ነገር እንዳልነበረ በማረጋገጥ እጀምራለሁ፡፡ የሕንፍሽፍሽ መሪዎች የተባልነው እኔና በቅፅል ስሙ ዶር. ታደሰ አባዲ (ኒክሰን) ሁለታችንም ያቀናበርነው ነገር እንዳልነበረና ከሌሎች የእንደርታ ተወላጅ ከሆኑ ታጋዮች ጋር ለማውራት እድሉ ሲኖረንም በሚፈፀመው አድልዎ ምሬት ከማሰማትና ግራ ከመጋባት በስተቀር ምንም አይነት የድርጅትና የአመፅ ምልክት እንዳልነበረ በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፡፡ አንባቢ ቀጥሎ ከማቀርበው ትረካ ሊገነዘብ እንደሚችለው የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽበዶር. አረጋዊና ደጋፊዎቹ የተቀናበረ ፀረ-እንደርታ ዘመቻ እንደሆነ በግልፅ ያመለክታል፡፡የዚህን ትረካእውነተኛነት ሊያረጋግጡየሚችሉ በአገር ውስጥም በውጪ ሃገራትም ይገኛሉ፡፡ የዚህ ትረካ አላማው አሁን ትግራይ ውስጥ የሚታየው የእንደርታ ራስን ቀና የማድረግ አዝማሚያ በሌላ ተልእኮ እየተመነዘረ፤ ማለት ከአዲስ አበባው መንግስት ጋር በሚፈጠር ህወሃትን የማጥፋት ሽርክና ጋር በማያያዝ የቀለለውን ግን አደገኛውን መስመር ከመያዝ ይልቅ ጉዳዩን በበጎና በይቅርታ መንፈስ እያዩ ለአንድነት አብሮ መስራት ተመራጭ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው መፍትሄ የሚሆነው ነገሩን ከቅርንጫፉ ሳይሆን ከስሩ በማየት ነው፡፡

ትረካውን የምጀምረው ከአክሱም ነው፡፡ ደርግ በቀየሰው እድገት በህብረት የእውቀትና የስራ ዘመቻ ተመድቤ አክሱም የሄድኩት የካቲት 1/1967 ዓ.ም. ነበር፡፡ በሚገርምና ኋላም የህይወቴን መስመር በወሰነው አጋጣሚ ታላቅ ወንድሜ ህንደያ አበራ አክሱም ከተማ ውስጥ እያስተማረ ነበር፡፡ ከተገናኘን ጀምሮ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር እስከ ሶሰት ወር ድረስ ቤቱን አላሳየኝም ነበር፡፡ ከስራ መልስ በየመጠጥ ቤቱ ስንገኛኝ ስለነበር ብዙም ትኩረት አልስጠሁትም ነበር፡፡ በቅርቡ (የካቲት 11/ 1967) በይፋ የተመሰረተ ተጋድሎ ሓርነት ህዝቢ ትግራይ (ተሓህት) የሚባል ድርጅት እንዳለና የኔ ወንድምም በአካባቢው የማስተባባር፤ የምልመላ፤ የመረጃ ልውውጥና የፖለቲካ ፅሁፎች ስርጭት ላይ እንደተሰማራ ራሱ ነገረኝ፡፡ አንድ ቀን ባጋጣሚ የህወሓት በራሪ ፅሁፍ ከሱ ቤት ሲቀረፅ ባይኔ አይቻለሁ፡፡ የሰማሁት ነገር ለኔ ድንገተኛ ነገር አልነበረም፡፡ የወንድሜን ስሜት ቀደም ብየ አውቀው ነበር፡፡ በ1965 ዓ.ም. እኔ የቀኃሥ ዩኒቨርሲቲ አንደኛ አመት ተማሪ በነበርኩበት ወንድሜ ህንደያ አበራ ደቀመሓረ (ኤሪትርያ) ከነበረበት የማስተማር ስራ ለቆ መጥቶ ስድስት ኪሎ ግቢ ውስጥ ተገናኘን፡፡ ለምን ስራውን እንደተወ ስጠይቀው ወደትግራይ አዛውሩኝ ብያቸው እምቢ ስላሉኝ በአሰብ አድርጌ ከሃገር ልወጣ ነው ብሎ አስደነገጠኝ፡፡ አስተምሮ ለዩኒቨርሲቲ ያበቃኝ እሱ ነበረና ተደናገጥኩ፡፡ ስንለያይ የተናገረው ትንቢት ግን እስካሁን ያስገርመኛል፡፡ እንዲህ አለ፡-በአብርሃ ካስትል በኩል እየተኮስን መቐለ ስንገባ ታያለህ፡፡ ይህ አባባል ምን ማለት መሆኑ በወቅቱ ባይገባኝም በአሰብ በኩል መውጣት ስላልቻለ መቐለ ያለ ስራ ሁለት አመት ያህል ቆይቶ በ1967 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ በማስተማር ስራ አክሱም እንዲመደብ ማስደረጉ ለምን እንደሆነ ግልፅ ሆነልኝ፡፡

በዛው አመት ብዙ አስገራሚ ክስተቶች ተፈጠሩ፡፡ ለመጀመሪያጊዜ በሽሬ የተካሄደው የህወሓት ኦፐሬሽን አክሱም ሆነን ዜናውን ሰማን፡፡ ከዛ ቀጥሎም ክረምቱን ካለሁበት አክሱም ከተማ ውስጥ በህወሓት ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ተካሄደ፡፡ይህ ለሁላችንም እጅግ አስደናቂ ነገር ነበር፡፡ አሁን የህወሓት መመስረት ምንም የማያጠራጥር ሆነ፡፡ በሌላ አጋጣሚ በህወሓት አላማዎች ላይ አስቸጋሪ ምልክት ያየሁትም በዚህ አመት ሆነ፡፡ አጋጣሚው እንዲህ ነው፡-የ1967 ዓ.ም. የትንሳኤ በዓል ስናከብር አብዛኛዎቹ የእድገት በህብረት ዘማቾች የአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ነበሩና የንቡረእድ ቤት በሚባለው ዘመቻ ጣብያ ዘፈኑ (ጓይላው) ደምቆ ነበር፡፡ እኔም ያቅሜን ያህል እስክስታ ስሞክርየዘፈኑን ይዘት ልብ አላልኩትም ነበር፡፡ ቆሜ ሳዳምጥ ግጥሙ ለኔ የሚስደነግጥ ሆኖ አገኘሁት፡፡ እንዲህ ይል ነበር፡-ትግራይ ዓደየ፤ አክሱም ሽረ ዓድዋ፤ ትግራይ ዓደየ፤ አክሱም ሽረ ዓድዋ፡፡ ይህ ግጥም እሱ ብቻ የሚደጋገምና ሌላ ቀጣይ የሌለው መሆኑን ስረዳ ማብራሪ መፈለግ ነበረብኝ፡፡ ቀሪዎቹ አምስት አውራጃዎች ስማቸው አይጠራም፡፡ የልጆቹ ልጅነትና ጅልነት ነው እንዳልል ይህ ልጅ የሚጫወትበት አሻንጉሊት አይደለም፡፡ ለዚህ የሚሆን ማብራሪ ላገኝ የምችለው ከወንድሜ ዘንድ ብቻ እንደሆነ ስለገባኝ ጊዜ ሳልሰጥ አገኘሁት፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን እኔንም በአባልነት መልምሎኝ ስለነበር የረገጥኩበት መሬት በሚገባ ማወቅ ነበረብኝና እንዲህ ብየ ጠየቅሁት፡- ይህ ትግላችሁ እኛን አይጨምርምን?፡፡ በህይወቱ እኔን እንደዚህ ሲቆጣኝ አይቼ አላውቅም፡፡አላማው ሆዱ ውስጥ ከገባባት ሰው የሚጠበቅ ነበር፡፡ ከቁጣው በኋላ የሰጠኝ መልስ ግን በጣም አጭር ነበር፡፡ እንዲህ የሚል ተዋቸው፤ እነሱ ልጆቸ ናቸው፤ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ይቺ ጪስ ከስር የሆነች ትንሽ እሳት አታጣም ብየ ያሰብኩትን ብነግረው ቁጣው ይብስበታል ብየ ዝም አልኩኝ፡፡ ዘመቻ ጣብያውን ለቅቄ ቤተሰቤ ወዳለበት ወደ መቐለ ከተማ ተጓዝኩኝና የከተማ የህወሓት መዋቅሮች ውስጥ መሳተፍ ጀመርኩ፡፡ ብዙም ሳልቆይ በፖሊስ ክትትል መጠናከር የተነሳ ወንድሜ መቐለ ከተማ መጥቶ ወደ በርሃ ሸኘኝ፡፡ካላሽነይ አቲ ምንሽረይ ወላዊለ ሒዘኪ ናብ ዱረይ ስዉእ ተጋዳላይ ረምሃ ቀስቅስ

በአንድ ቀን ጉዞ ከመሪየ ጋር ሰብያ ስንደርስአብሮ አደግ፤ የትምህርት ቤት ጓደኛና የቅርብ ዘመድ ከሆኑት ከህያብ (ሱራፊል ምሕረተአብ)፤ አባይ (አምሃ) ፀሃየና፤ ተካ ካሕሳይ (ነፍስ ይማር--ሴሮ ውጊያ ላይ የተሰዋ) ጋር ተገናኘን፡፡ ሁላችንም በፊተኛው አመት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ስንገናኝ ስለነበር፤ በተለይ አባይ ፀሃየ በዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ከማንኛውም የህወሓት አመራር የላቀ ሚና የነበረው በታጋሽነቱም ጭምር አደንቀው ስለነበር፤ እነዚህ ከፍተኛ የስራና የእድገት ተስፋ የነበራቸው ምሁራን ለትግል ብለው ያንን ብሩህ እድላቸውን በመሻር ከገጠርና ከገበሬዎች ጋር ተዋህደው ስላገኘኋቸው አባቴን አስለቅሼ መምጣቴን አስረሳኝ፡፡ እነሱም የሚያለቅሱ አባቶችና እናቶች ነበሯቸውና፡፡ ሌሊቱን ከገበሬ ቤት አድረን በማለዳ ወደ ማሰልጠኛው ተጓዝን፡፡ ወረዓትለ የሚባለው የህወሓት ወታደራዊ ማሰልጠኛ እጅግ ሰበርባራ ከሆነው በኢሮብ ምድር ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡ ዓሲምባ የሚገኘውም ከዚሁ በቅርብ ርቀት ነው፡፡ ኢሮብ ውስጥ ድንጋይ ወርውረህ የምታደርስበት ቦታ ለመድረስ ሰአታት ሊፈጅ ይችላል፡፡ ለዚህም ነበር በማለዳ ከተነሳሁበት ዕዳጋ ሓሙስ ከተማ ወረዓትለ ለመድረስ ድፍን ሁለት ቀን የፈጀብኝ፡፡ እዚህ ላይ ሁለተኛው በህወሓት አላማ ላይ ሌላ ጥቁር ነጥብ የጣለብኝ ነገር አጋጠመኝ፡፡ የሁለቱ ቀን ጉዞ በድካም ብቻ ያለፈ አልነበረም፡፡ ተወልዶ እስኪያድግ ድረስ መቐለ ፒያሳ ላይ ማውደልደል የለመደው እግሬን ለማለማመድ ሲባል ያለ ካልሲ ያ ምላጭ የሆነውን ኮንጎ ጫማ ለብሼ በዛ ሰበርባራ መሬት ሁለት ቀን ስለተጓዝኩበት ሁለቱ እግሮቼ ክፉኛ ተልጠውና በፍትጊያ ብዛት ተቦርቡረው እግሬ አብጦ መራማድ እያቃተኝ ነበር የደረስኩት፡፡ ከማሰልጠኛው ጥበቃ ላይ ስደርስ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ውድ ጓደኛየ የነበረው አረፋይኔ (ፀሃየ?) ላዛ ፀጉሩን ጎፈሬ አበጥሮ እየሳቀ ከተቀበለኝ በኋላ ያ ነጭ እግሬን እያየ ይኸው ትግል እንዲህ ያደርጋል ብሎ አሾፈብኝ፡፡ ከአባይ፤ ከህያብና ከተካ ተጨማሪ አረፋይኔን በማግኘቴ የበለጠ የልብ ልብ ተሰማኝ፡፡

ወረዓትለ ወጣገባነት የሚበዛበት በፍለጋ ሊገኝ የማይችል የሚመስል ድብቅ ስፍራ ነው፡፡ መከራን ለማለማመድ ሆን ተብሎ የተመረጠ ስፍራ ይመስላል፡፡ መሬቱ ከበለስ እሾህ ጋር አብሮ የተለወሰ አሸዋ ነው፡፡ ከበቆሎ በስተቀር ሌላ ምግብ የለም፡፡ ነጋ ጠባ የጥርስ ጠላት የሆነውን በአሸዋ የተቆላ በቆሎ መመገብ ነበር፡፡ ሰው እዛ ማሰልጠኛ ውስጥ ቆይቶ ብረት ሆኖ ካልወጣ የትም ሌላ ቦታ ሊሆን አይችልም፡፡ ስልጠናውን የጀመርኩት በማግስቱ ነበር፤ ትንሽ ልረፍ የሚባል ነገር የለም፡፡ አሰልጣኛችን የአየር ሃይል ባልደረባ የነበረው አሕፈሮም ነበር (ነፍስ ይማር--ጨዓ መስከበት ላይ የተሰዋ)፡፡ አሕፈሮም ከፍተኛ ችሎታ የነበረው አስደናቂ አሰልጣኝ ነበር፡፡ ከነከባድ ቁስሌ ስልጠና ከጀመርኩ ጀምሮ ሶስት ወር ስልጠናው እስከጨረሽን ድረስ የእግሬ ቁስል አልዳነም ነበር፡፡ ሶስት ወር ሙሉ በሮጥኩኝና በተንከባለልኩኝ ቁጥር እየተጋጠ እንዴት ይዳን? ከአካል ቁስሉ ይልቅ ያጋጠመኝ የአይምሮ ቁስል ነበር፡፡ ስልጠና ላይ ቁስሌ እየተነካካብኝ ድንገት ስወድቅ የርእሲ ኹናት (የወረራ ስልት) ሰልፉን አበላሸው ነበር፡፡ ስልጠና ላይ መሞትም እንዳለ ባውቅም አሕፈሮም እኔ ላይ ሲያንፃበርቅ የነበረው ስሜትና ሲናገራቸው የነበሩት ቃላት ከስልጠናው መንፈስ ወጣ ያሉ ነበሩ፡፡ አሁንም ለዚህ ከአክሱም ቀጥሎ ያጋጠመኝ እንቆቅልሽ መልስ ለማግኘት ያነጋገርኩት ከእንደርታ (ግጀት) ለትግል የመጣውን ሰልጣኝ ኣብርሃ ገብረተኽለን ነበር፡፡ አውራጃ እየመረጥኩ ሳይሆን ማንኛውንም ብፃይ መጠየቅ እንደነበረብኝ ይገባኝል፡፡ ሆኖም ግን በሆዴ የተፈጠረ ጥርጣሬ ስለነበረ በዘፈቀደ አንዱን ብጠይቅ ሌላ ጣጣ ውስጥ እንዳልገባ ስለፈራሁ ነበር፡፡ ጉዳዩን ሳነሳለት አብርሃ ያለኝ ነገር ውስጤን አናወጠው፡፡ አብርሃ ያለኝ እንዲህ ነበር፡- አፍህን ዝጋ ዮሃንስ፤ ችግር አለ፤ ከእንደርታ የመጣነውን ከልባቸው አልተቀበሉንም፡፡ ከቆይታ በኋላ ግን ነገሮችን እያጋነን እንዳይሆን የሚል ስሜት አደረብኝና ነገሩን ትቼ ወደ ትግሉ ብቻ ማሰብ ቀጠልኩኝ፡፡ ከሶስት ወር በሁዋላ የዛለምበሳን አስፋልት አቋርጠን ገርሁ ስርናይ ለመድረስ የሃዘሞን ሜዳ (ኤሪትርያ) አቋረጥን፡፡ እዚህ ላይ አንድ ታምር ተፈጠረ፤ ሶሰት ወር ያመረቀዘው ቁስሌ ክው ብሎ ደረቀ፡፡ ሃዘሞ ሜዳ ላይ በምሽት እንደከዋክብት የሚያብለጨልጭ ፎስፎረስ እንዳለ ሌሊቱን እዛውሜዳ ላይ በማደራችን አስተውየዋለሁ፡፡ ጫማየ ክፍት ስለነበር ቁስሌን ያዳነልኝ እሱ መሆኑን ነገሩኝ፡፡

ከዛ በኋላማ በማያባራ እንቅስቃሴ ላይ ተጠመድን፡፡ ቁጥራችን እዚህ ግባ የሚባል ስላልነበረ፤ የመሳሪያችን አይነትም ደርግን ከልቡ ሊያስቀው የሚችል ጓንዴ፤ ካርባይን፤ ቺኮዝ፤ ግንፅል (ረሽ) ስለነበረ አንድ ቦታ ተቀምጠን ላለመታፈን ቀንም ሌሊትም መንቀሳቀስ ሆነ፡፡ እግራችን ስጋ የለበሰ አጥንት ሳይሆን ከአረብ ብረት የተሰራ ይመስል ነበር፡- እዚአቶም ኣታ እዚአቶም፤ ዓንኬል ቤቶም ሸይጣን ጎረቤቶም፤ ተሸነፍኹ ዘይብል አምዑቶም ብዙአየነ ዘገየ፡፡ሴሮ ላይ ከሻዕቢያ ጋር በመተባበር የደርግ ሜካናይዝድ ብርጌድን በሙሉ ቀን ጦርነት ከመታን በኋላ ጥራትያላቸው መሳርያዎች (ኤም 14) እንዲሁም ብዙ መጠን ያለው ስንቅ ተማረኮ ገርሁ ስርናይ ወስደን ስንከዝን ከቆየን በኋላ አንድ ምሽት የመብረቅ ያህል ያስደነገጠን ዜና ሰማን፡፡ መርዶው የተነገረን በድራር ለይቲ አማካይነት ነበር፡፡ ድራር ለይቲ ማለት የሌሊት ኮድ ነው፡፡ ድንገተኛ ችግር ቢፈጠርና መበታተን ቢመጣ ተጠራርቶ ለመገናኘት የሚጠቅም ነው፡፡ ድራር ለይቲ አይደገምም፡፡ በተለምዶ ድራር ለይቲ የትም ግንባር የተሰዉ ታጋዮች ስምን ይጠቀማል፡፡ ስለዚህ የመረጃ ዘዴም ጭምር ነበር፡፡ በዛ ምሽት በድራር ለይቲ የሰማናቸው ስሞች ግን ተገደን የገባንበት ለሁለት አመታት የዘለቀ ውጊያ ምክንያት የሆኑ ነበሩ፡፡ክስተቱ ሁሉም የህወሓት ሃይሎች ረዥሙን የአድያቦቆይታ ያስጀመረ ነበር፡፡ የዛ ምሽት ድራር ለይቲ ስሑል-ሰናይ የሚል ነበር፡፡ የመጀመሪያው የህወሓት አመራር የነበረውና በመደበኛ ስሙ ገሰሰ አየለ ሲባል የነበረው የፓርላማ አባል ነበር ነው፡፡ ይህ በትግራይ ውስጥ በጣም ታዋቂ የነበረ ሰው በዓዲ ነብሪኢድ ሲቪል የማደራጀት ስራ ሲሰራ በጠራናፊት (ኢዲዩ) ሃይሎች ተረሸነ፡፡ ህወሓት ለዚህ ድፍረት ምላሽ ለመስጠት ወደ አድያቦ ጉዞ ተጀመረ፡፡ የጠራናፊት ሃይሎች ብዙዎቹ ከጠመንጃ ጋር የኖሩ ስለሆኑ ህወሓትን የተማሪዎች ስብስብ እያሉ ይንቋት ነበር፤ ንቀታቸው ንቀት ብቻ ሆኖ ቀረ እንጂ፡፡ ሁለተኛው ከስሑል ጋር በጠራናፊት የተገደለው ሙሉጌታ ካሕሳይ የሚል መደበኛ ስም የነበረው ነበር፡፡ ከሱ ጋር አፄ ዮሃንስ ሃይስኩል 9ኛ አንድ ክፍል አብረን ተምረናል፤ ንቁና በትምህርቱም ጎበዝ ነበር፡፡ ለሱ እንደ ትግል ጓድ ብቻ ሳይሆን በግሌ እንደ ጓደኛም ተጨማሪ ኃዘን ተሰምቶኝ ነበር፡፡

ከገርሁ ስርናይ አድያቦ ለመድረስ ከአስር ቀናት በላይ ፈጅቶብናል፡፡ የአዲግራት አድዋ አውራ መንገድ ካቋረጥን በኋላ በዕዳጋ ዓርቢ-ማይቅነጣል-ዳጌና-ወርዒ-አዴት-ሰለኸለኻ-ሰመማ አድርገን ዓዲ ዳዕሮ ገባን፡፡ በየደረስንበት ከፖሊሶችና ከታጣቂዎች ጋር አነስተኛ ግጭቶች ከመኖራቸው በስተቀር የጎላ እንቅፋት አላጋጠመንም፡፡ ወደ አድያቦ የተደረገው ዙርያ ጥምጥም መንገድ ከጠራናፊት ደፈጣ ለመዳን የተደረገ ነው ብየ ተርጉሜዋለሁ፡፡ ምንም እንኳን ከፍተኛ የድካም ስሜት ቢኖርም ዓዲ ዳዕሮ ላይ እረፍት አልተደረገም፡፡ ከከተማዋ ወደ ዓዲ ነብሪኢድ መውጫ ላይ የህወሓት ሃይል መሽጎ ካደረ በኋላ ሲነጋጋ ዓዲ ነብሪኢድ ውስጥ መሽጎ ከነበረው የጠራናፊት ሃይል ላይ ተኩስ ተከፍቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በበርካታ ምርኮ ተጠናቀቀ፡፡ ለጠራናፊት ምርኮኞች ማቆያ ጊዜያዊ ቤቶች ስለተመደቡ የደህንነት ሃላፊ ከነበረው ከዶር. ሃይሉ ነጠበ (አለምሰገድ መንገሻ/ሌኒን የሚል የቅፅል ስም አፄ የሃንስ ሃይስኩል እያለን ያወጣንለት) ጋር አብሬ እንድሰራ ተመደብኩ፡፡ ዶር. ሃይሉ ነጠበ የ1967ዓ.ም. ነባር ታጋይ ነው፡፡ ሄዶ የማይደክምና በንቃቱና ቆራጥነቱ የሚታወቅ ነበር፡፡ ይህ የኔ ምደባ ግን በሰላም ነው ብየ ለማመን ተቸግሬ ነበር፡፡ ሃይሉ ነጠበ አብረን የተማርን ጓደኞች መሆናችን እንዳለ ሆኖ እኔ በማውቀው ጉዳይ ከዋናው የህወሓት አመራር አባልነት መወገዱን ሰምቻለሁ፡፡ ገና አክሱም እያለሁ የኔ ወንድም ህንደያ አበራ አክሱም ከተማ እያለ ከበርሃ ከሚመጣው ዶር. ሃይሉ ነጠበ ጋር የዘወትር ግንኙነት እንደነበራቸው ራሱ ነግሮኛል፡፡ የተራባ ወረቀት በአህያ እየጫነ እንደሚያመጣለትና አሱም ተቀብሎ በሻንጣ አድዋና ሽሬ እየሄደ ለመዋቅራቱ ያቀብል እንደነበረ አጫውቶኛል፡፡ ከእለታት ባነዱ ቀን በ1967 ዓ.ም. አጋማሽ በኋላ ይመስለኛል ዶር ሃይሉ ከትውልድ ቦታው ተንቤን ለድርጅቱ ስራ በሄደበት መውጫ አጥቶ እንደተከበበ መረጃ ደረሰኝ ብሎ ወንድሜ በጭንቀት ውስጥ ሆኖ አወራኝ፡፡ በምን ሁኔታ ከከበባው እንዳመለጠ ያወቅሁት ነገር ባይኖርም ወደ ሜዳ ከተመለሰ በኋላ በስራ ምክንያት ተከቦ ሳይሆን ለግል ጉዳዩ ነበር ቆይታውን ያራዘመው በሚል የዲሲፕሊን ክስ ከአመራር እንደወረደ ሰምቻለሁ፡፡ ዶር. ሃይሉ ነጠበን የእስረኛ ጠባቂ ሆኖ ሳገኘው ቅስሜ ተሰበረ፡፡ ሁለት ሳምንት አብረን በቆየንበት ጊዜ ስለ አመራሩና ሌሎች ሁኔታዎች በሰፊው ለማውራት እድል አግኝቻለሁ፡፡ ምንም ችላ ለማለት ብሞክርም የሚገጥመኝና የምሰማው ነገር ባመዛኙ የውሰጥ ስጋቴን የሚያጠናክር እንጂ የሚያላላ ሊሆንልኝ አልቻለም፡፡

ከዓዲ ነብሪኢድ ድል በኋላ ከጠራናፊት (ኢዲዩ) ጋር በርካታ ቀላልና ከባድ ውጊያዎች ተካሂደዋል፡፡ እኔ ሜዳ እስከ ነበርኩበት ጊዜ እንደ ጨዓመስከበት ያለ ከባድና ጎጂ ጦርነት ግን አላጋጠመም፡፡ ጨዓመስከበት ሸራሮን አልፎ ወደ ተከዘ ወንዝ አቅጣጫ የምትገኝ መንደር ናት፡፡ የኢዲዩ ሰራዊት ከሱዳን ባገኘው ዘመናዊ መሳሪያ ተጠናክሮ ስለመጣ ይህን ለማዳከምና ለመምታት በሃይለ ፖርት ሱዳን የሚመራ ሃይል መንጠብጠብ በሚባል መንደር ላይ ከበባ ሲያደርግ አደረ፡፡ ሌላ ሁለት ጋንታ በዋልታ (ዮሃንስ) የተመራ ምናልባት በሚል ጨዓመስከበት የነበሩ አዳራሽ ህድሞዎችን ሌሊቱን ሙሉ ከቦ አደረ፡፡ ሲነጋጋ ያልታሰበ ነገር ተፈጠረ፡፡ ከወልታ ጎን ቆሜ ስለነበረ ከኢዲዩ ጦር መሪዎች አንዱ ከጠባቂ ጋር ሆኖ ከኛ በቅርብ ርቀት ሲፀዳዳ እያየን ሳቃችንን ሳንጨርስ ከህድሞዎቹ አቅጣጫ ካቅም በላይ የሆነ የሲሞኖፍና የመትረየስ ተኩስ ተከፈተብን፡፡ ለካ የኢዲዩ ሙሉ ሃይል ያደረውጨዓመስከበት ከፊታችን ካሉት ህድሞዎች እንጂ ዋናው የህወሓት ሃይል ከተመደበበት መንጠብጠብ መንደር ውስጥ አልነበረም፡፡ ከመንጠብጠብ የአርፒጂ አስጀማሪ ተኩስ ሲጠብቅ የነበረው ዋልታ (ስዉእ-ነፍስ ይማር) ሃይለኛና ፋታ የማይሰጥ ጥይት ሲዘንብብን ከያገኘነው ድንጋይ ስር ሆነን እንድንጠብቅ ትእዛዝ ሰጠን፡፡ በዚህ ጥይት በሚዘንብበት ቀወጢ መሃል ሃይለ ፖርት ሱዳን በዝናብ የሚሄድ ይመስል በቁም ቀጥ ብሎ መጣ፡፡ በቅርብ ያገኘንን ወደ ህድሞው አጥር ለማስጠጋት ትእዛዝ ሰጠንና ተጠጋን፡፡ ሃይለ ፖርት ሱዳንን በሚመለከት በ1969 ሕንፍሽፍሽ ጋር የተያያዙ አበይት ጉዳዮች ስላሉ ወደኋላ በወሳኝነት እመለስባቸዋለሁ፡፡ አሁን ግን ስለሃይሌ ፖርት ሱዳን በመጠኑ ልግለፅ፡፡ ሃይሌ የመቐለ ተወላጅ ሲሆን በልጅነቱ ፖርት ሱዳን ሄዶ ወደብ ላይ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ለትግል ከሻዕቢያ ጋር ተቀላቀለ፡፡ ህወሓት ከመፈጠሯ በፊት በሻዕቢያ የተወሰነ ደረጃ የጦር መሪነት መደብ ይዞ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ ወደ ህወሓት በገዛ ፍላጎቱ ሲዛወር ሻዕቢያ ፈቃደኛ እንዳልነበረ ሲወራ ነበር፤ የሚያጡትን ስላወቁ ይሆናል፡፡ ሃይሌ ተወንጫፊ ተብላ ስትጠራ የነበረችውን የህወሓት ሃይል 11 ሲመራ የወታደራዊ አመራር ብቃቱ እጅግ የተደነቀ ነበር፡፡ ምንም እንኳ እነስየ፤ ፃድቃን፤ ሳሞራና፤ ሓየሎም በተለያ መደብ ሲሰሩ ቢቆዩም ሃይለ ፖርት ሱዳን በታጋዩ ዘንድ የነበረው ዝና ከፍ ያለ ነበር፡፡ ለታጋዮች የሚያደርገው እንክብካቤም ሌላ የሚታወቅበት ባህርዩ ነበር፡፡ ጨዓመስከበት ላይ ይህ ሁሉ ጥይት እየዘነበበት ቆሞ አመራር ሲሰጥ በውጊያው መጨረሻ ላይ ጭንቅላቱ ላይ በመጠኑ የጨረፈችውን ጥይት ብቻ ነበር ያስተናገደው፡፡ ሱዳን ሳለ ጥይት የማያስመታ መተት አሰርቶ ነው የሚሉተ በርካታ ነበሩ፡፡

የጨዓመስከበት ጦርነት በመበላሸቱና ከኋላም ከፊትም ይተኮስብን ስለነበር ለመከበባችን ምንም ጥርጣሬ አልነበረንም፡፡በዚህ ጦርነት ሙሴ የተሰዋ ሲሆን ከመሰዋቱ ከአምስት ደቂቃ በፊት ሙሴና ግደይ ዘራፅዮን ሆነው ውጊውን መልክ ለማስያዝ ሁለቱም ሽጉጥ ይዘው እኔና ኒክሰን ወደ መሸግንበት የካብ አጥር በመምጣት ወደ በረቱ እንድንገባ አዘዙንና እነሱም አኛን አልፈው ኢዲዩ ወደመሸገበት ወደ ህድሞው ቤት አቅጣጫ ሄዱ፡፡ ባንተያይም ነገሩ የጨበጣ ውጊያ ይመስል ነበር፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ግደይ ዘራፅዮን ለብቻው (ያለ ሙሴ) ከህድሞው ተመልሶ መጣና በጥድፊያ ስሜት ስለተከበብን በያቅጣጫው እየተኮሳችሁ ውጡ ብሎ ስላዘዘን በስርአት ለማፈግፈግ ስንሞክር ከፊቴ የነበረው ኒክስን በጥይት ተመትቶ ወደቀ፡ ጥይቱ የኒክሰንን የጥይት በርሳ በስቶ ስለገባ አሳት ፈጠረ፤ እኔም ጠመንጃየን ወደጎን ወርውሬ እሳቱን ከላዩ ላይ በእጄ እየደበደብኩ ለማጥፋት ስሞክር ተሳካልኝ፡፡ ኒክሰንን ወደ ሸራሮ በሰው አሸክመን ከላክን በኋላ እኛ እረፍት እንድናደርግ ተነገረንና ሌላ ሃይል ተተክቶ ውጊያውን ቀጠለ፡፡ ኒክሰን ላይ የተነሳው እሳት በማጥፋቴ ወደኋላ ያስገኘልኝን ህይወት አድን የሆነ ብድር ምለሳ ወደ ኋላ እመለስበታለሁ፡፡ የሙሴ መሰዋት፤ የሃይለ ፖርት ሱዳን ነገር፤ የኒክሰን የጥይት ቃጠሎ መጥፋት ለዚህ ለ1969 ሕንፍሽፍሽ ገለፃየ ጠቃሚ ግብአቶቼ ናቸው፡፡ ከጨዓመስከበት ማግስትም ተከዘ ሸለቆ ገብተን የኢዲዩን ካምፕ አጥቅተን ተመልሰናል፡፡ በመልሳችንም ሸራሮ በኢዲዩ ተጠቅታ ጠብቃናለች፡፡

በዛኞቹ ወራት በአንዱ ዓዲ ነብሪኢድ መሰል ከምትባለው መንደር አድረን ቁርስ ሲዘጋጅ አኔና ኒክሰን ህድሞዎቹ አኛቶች ላይ ዋርድያ ወጥተን ነበር፡፡ በዛን ሰአት ነበር በኢዲዩ ድንገተኛ ውጊያ የተከፈተብን፡፡ እኔና ኒክሰን ከህድሞዎቹ አናቶች ዘለን ስንወርድ ሃይል 11 ሲመራ የነበረው ሃይሌ ፖርት ሱዳን በከፍተኛ ፍጥነትና ጥበብ ሰራዊቱን ቦታ ቦታ ሲያስይዝ ደረስን፡፡ አኔም በቀኝ ክንፍና የጥቃቱ ጫና በበዛበት አቅጣጫ ተመደብኩ፡፡ የመትረየስ ቡድንም የተመደበው በዚህ አቅጣጫ ነበር፡፡ በዚህ ጦርነት አንድ ችግር ተከሰተ፡፡ ረምሃ ቀስቅስ የእንደርታ ተወላጅ ነው፡፡ የመጀመሪው የህወሓት ኪነት ድምፃዊ ከመሆኑ በተጨማሪ በሃይለ ፖርት ሱዳን የምትመራው የሃይል 11 የመትረየስ ቡድን አባል ነበር፡፡ ወደ ተሰዋበት ዓዲ ነብርኢድ መሰል ከመንቀሳቀሳችን በፊት ሸራሮ ላይ አንድ ጅምር ህንፃ መስኮት ላይ ተቀምጦ እኔን ጠራኝ፡፡ እንዲህም አለኝ፡- ዮሃንስ አድያቦኮ አፈራችን ናት፡፡ አባባሉ ግልፅ ቢሆንም ምን መነሻ አድርጎ እንዲህ አይነት ትንቢት እንደተናገረ እስካሁንም አልገባኝም፡፡ ዓዲ ነብርኢድ መሰል ምሽግ ውስጥ ሆነን ስንዋጋ የኤሮብ ተወላጅ የሆነ ከረምሃ ጋር የመትረየስ ቡድን አባል የነበረ ታጋይ እኔ ወደነበርኩበት ምሽግ መትረየሱን ይዞ መጣ፡፡ ምሽጉን ትቶ ለምን ወደኔ እንደመጣ ስላልገባኝ ትክ ብየ ሳየው አይኑ እንባ አዝሏል፡፡ ምነው ስለው ረምሃ እንደተሰዋ አረዳኝ፡፡ ሃያ ስድስት ከጠላት ጦር ሲገደል ከሃይል 11 የተሰዋው ረምሃ ብቻ ነበር፡፡ አጥብቄ በመጠየቅ የተረዳሁት ነገር ቢኖር ረምሃ የተመታው ከፊት ሳይሆን ከኋላ እንደነበር ነው፡፡ ምን አየተፈጠረ እንደሆነ ለመረዳት ያለ አምላክ ሃይል የሚቻል አልነበረም፡፡ የረምሃ ቀስቅስ አሟሟት ሁኔታ ሁላችንም የአይምሮ ረብሻ ፈጠረብን፡፡ የትግል ሰሜታችን ከግለት ወደ ግራ መጋባት መሸጋገር ጀመረ፡፡

ከአድያቦ ሳንወጣ አንድ ቀን ዓዲ ዳዕሮ ውስጥ እያለን የሆነው ነገር በ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽ የዶር አረጋዊ ሚና ምን እንደነበር ለመጀመሪያ ግልፅ የሆነበት አጋጣሚን ፈጠረ፡፡ ከኢዲዩ ጋር ሲደረግ የነበረው ተከታታይ ጦርነት ጋብ ካለ በኋላም አራቱም ሃይሎች (11፣ 21፣ 31 እና 41) አድያቦ ላይ እንደተከማቹ ብዙ ወራት አለፉ፡፡ ውሱን ስፍራ ላይ መከማቸታቸው ለደህንነታቸውም አደገኛ ቢሆንም ዋናው የህወሓት አላማ የሆነው የትግራይ ህዝብን ከዳር እስከዳር በህወሓት አላማዎች ስር የማደራጀት ስራ እንዲጓተት አድርጎታል፡፡ ስለዚህ አራቱ ሃይሎች በአራቱም የትግራይ መአዝናት ተሰማርተው እንዲሰሩ ሲወሰን ሃይሌ ፖርት ሱዳን የሚመራት ሃይል 11 የደቡብ ሃይል ተብላ ተመደበች፡፡ እንደ አጋጣሚ ይሁን ሆን ተብሎ በዚች ሃይል የነበሩት ታጋዮች ከደቡብ የመጡት በርከት ይሉ ነበር፡፡ ደቡብ ማለት እንደርታና ራያ መሆኑ ነበር፡፡ በዚች ሃይል ውስጥ የነበሩ የአዲግራትና የተምቤን ታጋዮችም በአመራሩ ላይ ቅሬታ እያስተናገዱ ስለመጡ የውስጥ መቋሰሉ እየጨመረ መጥቶ ነበር፡፡ ሃይል 11 ደቡብ ሃይል ተብላ ከተመደበች በኋላ ወደ ተመደበችበት ቦታ ሄዳ እስከዛ ድረስ የህወሓትን ምንነት አያውቅ የነበረው የእንደርታና የራያን ህዝብ እንደማንቃትና ማደራጀት አድያቦ ተጎልታ ቀረች፡፡ አሁን ትእግስታቸውን የጨረሱ የሃይል 11 (ደቡብ) አባላት ወደ ምድብ ቦታቸው የመሄድ ፈቃድ እንዲሰጣቸው የሚል ጥያቄ በሃይለ ፖርት ሱዳን በኩል ለዶር. አረጋዊ በይፋ እንዲቀርብ ወሰኑ፡፡

ይህ የሆነው ዓዲ ዳዕሮ በነበርንበት ወቅት ነው፡፡ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለጥያቄያችን መልስ እንደመጣ ሃይለ ፖርት ሱዳን ነግሮን የሃይል 11 (ደቡብ) አባላት አንድ ሰፊ ቤት ገብተን ተሰበሰብን፡፡ ሃይለ ፖርት ሱዳን የተናደደ መሆኑ በዛ ጥቁር ፊቱ ላይ ይታወቅበታል፡፡ ከበሪሁ የመጣላችሁ መልስ ስሙብሎ ማንበብ ጀመረ፡፡ መልሱ በስድብና ማስፈራሪያ የተሞላ ነበር፡፡ አንድ የታጠቀ ሃይልን መሳደብ ምን ይባላል? ለአላማ ብሎ የመጣ እንጂ የሱ አሸከር የሆነ ማንም አልነበረም፡፡ አሁንም እያደረገ እንዳለው እድሜ የማይሽረው የዶር. አረጋዊ የመጣለትን የመናገር አባዜ ነበር ህወሓትን ለችግር የዳረጋት፡፡ በሪሁ እንዲህ ብሎ ሃይል ሙሉ ታጋይን ተሳደበ፡- ጎጠኞች፡፡ የሃይል 11 ታጋይ ሁሉ ቅስሙ ተሰበረ፡፡ ሃይለ ፖርት ሱዳን ብስጭቱን መቻል አቃተው፡፡ እንደርታና ራያ ሄደን የህወሓትንአላማዎች ለህዝቡ እናስተምር ማለት ጎጠኝነቱ ምኑ ላይ ነው? ድዋና ሽሬ-አድያቦ በቆየንባቸው ብዙ ወራት ህዝቡን ስናስተምር መቆየታችን ይታወቃል፡፡ ልዩነቱ ምንድን ነው? ችግሩ ከኛ በኩል በአውራጃዊነት ስሜት የተከሰተ አመፅ ቢጤ ለማስመሰል የተወጠነ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አሳድሮብናል፡፡ ይህን ስድብ ከሰማን በኋላም ቢሆን ህወሓትን ለመፈታተን የተደረገ ነገር አልነበረም፡፡ በአመራሩ (ዶር. አረጋዊ) እየታየ የነበረውን አፍራሽ ተግባር በሚገባ የተረዳው ሱሳን ሸሞንተን በሚል ቅፅል ስም የሚታወቀው የአድዋ ልጅ የሆነ የጋንታ መሪ በአንድ ወቅት የተናገረውን ልጥቀስ፡፡ ሱሳን ሸሞንተን የሚል የቅፅል (የበርሃ) ስም የወጣለት በሆነ ነገር ሲገረም በተለምዶ አረ ሱሳን ሸሞንተን ይል ስለነበር ነው፡፡ ይህ ታጋይ ቆራጥና ባህሪዩ ለሁላችንም የተመቸ ነበር፡፡ ኮሽ ሲል የእንግሊዝ መትረየሱን ይዞ ቀድሞ ገዢ መሬት የሚይዘው እሱ ነበር፡፡ አንድ ቀን በድካም ምክንያት ብረት ትከሻየ ላይ አጋድሜ በመያዜ ከባድ ወታደራዊ ቅጣት ተቀጣሁ፡፡ ቅጣቱን ጨርሼ ለወሬ ሱሳን ሸሞንተን አጠገብ ሄጄ ስቀመጥ ቅጣቱ አላስፈላጊ እንደነበር ያስተዋለው ሱሳን ሸሞንተን በድርጊቱ እንዳዘነ አየሁ፡፡ ቀጥሎ የተናገረው ግን ታሪካዊ ነበር፡፡ ሱሳን ሸሞንተን እንዲህ አለ፡- ኣታ ብሽም ደቂ ዓድዋንዶ ምስ ኩሉ ከባእሱና፡፡ ትርጉሙ በአድዋ ልጆች ስም ከሁሉም ጋር ሊያጣሉን ነው፡፡ ሱሳን ሸሞንተን በህይወት ይኑር አይኑር አላውቅም ከእንደርታ ታጋዮች ውጪ ችግሩ ቀድሞ የገባው ግን አሱ ነበር፡፡

እነዚህ ብቅጥልቅ የሚሉት ግን ደብዛዛም ቢሆን አንድ አይነት ስእል እየሰጡ ያሉት ክስተቶች ወዴት እንደሚያመሩ ለማየት በትእግስት ከመጠበቅ በስተቀር አማራጭ አልነበረንም፡፡ በ1969 ዓ.ም. የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ዓድዋ ከተማን ለማጥቃት በወጣው እቅድ መሰረት ትኩረት የማበላሸት ወታደራዊ ታክቲክ ለመጫወት ያህል ከገረሁ ስርናይ እስከ ተምቤን ወርቂ እምባ ድረስ የሸማኔ ዙር ስናደርግ በነበረበት ጊዜ እንቲጮ ከተማ ውስጥ እያለን እጅግ የሚዘገንን ዜና ሰማሁ፡፡ ከመቐለ የመጣው ግርማይ ኪዳኑ አኔን ለብቻየ ገለል አድርጎ እንዲህ አለኝ፡- በሪሁ (አረጋዊ) ሰባት ከመቐለና ከተምቤን የመጡትን ልጆች ትጥቃቸውን አስወርዶ በኡዚ ረሸናቸው፡፡ ይህን ዜና የሚሸከም ጭንቅላት አልነበረኝም፡፡ ነገሮች እየለየላቸው እንደመጣ ገባኝ፡፡ የተነገረኝ የግድያ ዜና ግን ለማመን እጅግ የሚከብድ ነበር፡፡ አምኜ የተቀበልኩት ከብዙ ወራት በኋላ ኒክሰን ህወሓትን ሰንለቅ ይህ ጉዳይ ለመልቀቃችን እንደ በቂ ምክንያት አድርጎ ስለ ደገመልኝ ነው፡፡ ኒክሰን እንዲህ አለኝ አረጋዊ እኛንም አይለቀንም፤ ዞር ብንልለት ይሻላል፡፡ ይህ የግድያ ወሬ ውስጥ ለውስጥ በህወሓት ውስጥ በሰፊው ተሰራጭቶ ነበር፡፡ ከእንደርታ በመጡ ታጋዮች ዘንድ ሽብር ነገሰ፡፡ አንዳንዶቹ ግን እንዳይፈረጁ በመፍራት በጎ በጎውን በመናገር ላይ ተጠምደው ነበር፡፡ ዶር. አረጋዊ አርምጃውን ቀጠለ፡፡ የጎን ውጋቴ ናት ብሎ ያሰባትን በሃይለ ፖርት ሱዳን የምትመራው ሃይል 11 (ደቡብ) ወደ ተመደበችበት ደቡብሳትሄድ ባጭር ተቀጨች፡፡ ሃይሏ ተበትና ሌላ ሃይል 55 የሚባል ተፈጠረና ሃይለ ፖርት ሱዳን እንዲመራት ተደረገች፡፡ ለክትትል እንደምታመች ሆና የተዋቀረች ይመስለኛል፡፡ እኔም በአጋጣሚ ይሁን በብልሃት ከሃይለ ፖርት ሱዳን ጋር ደረሰኝ፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የተፈበረከው ሕንፍሽፍሽ የት እየተመረተ እንደሆነ ግልፅ የሆነው፡፡

የመቐለ ልጅ ስለሆነ ሳይሆን ሃይለ ፖርት ሱዳንን በጀግንነቱ፤ በጦር አመራሩ፤ በተግባቢነቱና ለታጋዮች መልካም አሳቢነቱ አደንቀውና እውደው ነበር፡፡ በዓድዋ ኦፐሬሽንም ህይወቴን አትረፏል፡፡ ዓድዋ ብሎኮ የነበልባል ጦር አባላትን ስናጠቃ ወደአጥሩ በጣም ተጠግቼ ስለነበርና የያዝኳት ካርባይንም አልሰራልኝ ስላለች ልከበብ መሆኔን ከርቀት የተመለከተው ሃይለ የማውቀውን ምልከት በመስጠት በዘዴ የኔ ጋንታ ወደ መሸገችበት እንዳፈገፍግ አግዞኛል፡፡ አንድ ቀን ሃይለ የሚመራት አዲሷ ኃይል 55 ነበለት (እምባስነይቲ) ከተማ ገባችና ሃይለ እንደተለመደው የሃይሏን ባላጽ ቦታ ቦታ ካስያዘ በኋላ እኔን ጠራኝ፡፡ ለወታደራዊ ትእዛዝ መሰሎኝ ሰጥ በል ብየ ብጠጋው እጄን ይዞ ራቅ ወዳለ ቦታ መራመድ ጀመረ፡፡ የሚወደኝ መሆኑን ባውቅም የሃይል አዛዥና ተራ ታጋይ እጅ ለእጅ ተያይዘው ዎክ ማድረጋችን እንቆቅልሽ ሆነብኝ፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች ዝምታ በኋላ ለእድሜ ልክ የሚሆን የነገር ስንቅ አቀበለኝ፡፡ ብፃይ ዮሃንስ አለኝ የህወሓት አመራር ትግሉን ጥየ እንድጠፋ እየገፋፉኝ ነው፤ እኔ ግን የሚፈጠረው ይፈጠራል እንጂ ንቅንቅ አልልም፡፡ መብረቅ የመታኝ ያህል ደነዘዝኩ፡፡ ከዛ በቀላሉ የማይተካ የህወሓት ታማኝና ብርቱ አገልጋይ አፍ እየወጣ መሆኑን ማመን አልቻልኩም፡፡ እንዲያውም እኔን እየሰለለኝ ያለ ሆኖ ተሰማኝ፡፡ ግን ከማመን በስተቀር ምርጫ አልነበረኝም፡፡ የሚመራት ሃይል ጎጠኛ ተብላ ስትሰደብና አሱም ሲበሳጭ በማየቴ አሱን ላለማመን በቂ ምክንያት አልነበረኝም፡፡ አሁን ለየለት፡፡ ሃይለ ፖርት ሱዳን ህወሓትን መርጦ ተከበረበትን ሻዕቢያን ጥሎ የመጣ ነው፡፡ በበርካታ አውደ ውጊያዎች ህወሓትን የታደገ ምርጥ የጦር መሪ ነበር፡፡ ሃይለ ይህን ጉድ ከነገረኝ በኋላ መልስም አልሰጠሁትም፤ በሃሳብ ብዛት ካጠገቡ አልነበርኩም፡፡ እጅግ የከበደ፤ ማንኛችንም ያልገባን ነገር እየመጣ መሆኑ ታየኝ፡፡ ሃይለ ህወሓትን ጥሎ እንዲኮበልል የተፈለገው ለምን እንደሆነ በርካታ መላምቶች አሰብኩ፡፡ ያጠፋ ታጋይ ተገቢው እርምጃ ይወሰዳል እንጂእንዴት በወቅቱ እንደ ከባድ ወንጀል ተወስዶ በሞት የሚያስቀጣውን እርምጃ እንዲውስድ ይገፋፋል? ከመላምቶቼ ሁሉ ጉልህ ሆኖ የታየኝ የስራ አስፈፃሚ ምርጫን የሚመለከተው ነበር፡፡ ሙሴ ጭዓመስከበት ከተሰዋ በሁዋላ የሱ ቦታ አልተተካም ነበር፡፡ ለዛ ቦታ ይመጥናል ተብሎ በታጋዮች ዘንድ በስፋት ስሙ ሲነሳ የነበረው ሃይለ ፖርት ሱዳን ነበር፡፡ ዶር. አረጋዊ ይችን ማሰናከል ነበረበት፡፡ እስካሁን በታየው አዝማሚያ ብቃት ቢኖራቸውም አመራር ውስጥ እንዲገቡ የማይፈለጉ ነበሩ ማለት ነው፡፡ አመራሩን የሚኒስትርነት እንጂ የመስዋእትነት ቦታ መሆኑን ያሰቡት አይመስልም፡፡ መሶብ ሰርቼ ላጤ አበርክቼ አለች ተስፈኛዋ እማወራ፡፡

ከዚህ የሃይለ መረጃ በኋላ፤ ፊት ከሰማኋቸው መረጃዎች ጋር ተደምሮ፡፤ በህወሓት አመራር (ዶር. አረጋዊ) ላይ የነበረኝ እምነት ተሸርሽሮ አልቆ ነበር፡፡ ዶር. አረጋዊ በኔ ላይ ያለው አመለካከት ምን እንደሆነ ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ፡፡ አንድ ቀን ግን ፍቅር ይሁን ጥላቻ መለየት ያልቻልኩበት ክስተት ተፈጠረ፡፡ ወርዒ የተከዘ ገባር ወንዝ የሚፈስበት አፅናፍ ድረስ የተዘረጋ በርሃማ ሸለቆ ነው፡፡ ይህ በርሃ የሽፍቶች መናሃሪያ ሆኖ የኖረ ሲሆን ህወሓት በአካባቢው መዘዋወር ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ ግን ነገሮች ስርአት እየያዙ መጥተው ነበር፡፡ ሙሉ የሚባል ሽፍታ ግን ሰላሳ ጭፍሮች ይዞ ስላስቸገረ በህወሓት በኩል ሰላማዊ ኑሮ እንዲኖር የተደረገለትን ጥሪ የሚነግሩት ሽማግሌዎች ወደሱ ተልከው ነበር፡፡ ሽማግሌዎቹ ለመልስ የተቀጠሩበትን ቀን ስላዘገዩ ዶር. አረጋዊ ከሁለት ታጋዮች ጋር ወደ ሽማግሌዎቹ መኖርያ እኔን ላከኝ፡፡ የተላክሁበት ሰአት ወርዒ በርሃ ውስጥ ደርሶ ለመመለስ እንደሚመሽ የታወቀ ነበር፡፡ በጨለማ ስንመለስ ተኩስ ተከፈተብንና የተኩስ መልስ ሰጠን፡፡ ከጥቂት ቆይታ በኋላ በወታደራዊ ጥንቃቄ ወደ ሰፈር መንገድ ስንጀምር ዶር. አረጋዊ በጨለማ ስሜን እየጠራ መጣ፡፡ ካጠገቡ ስደርስ የተፈጠረውን ስነግረው ራሱ ክላሽንኮቭ ይዞ ውደ ተተኮሰበት ሄደ፡፡ ይህ ለኔ ምስጢር ሆነብኝ፡፡ የህወሓት መሪ ለእርዳታ ሌሎች ታጋዮችን መላክ እየቻለ ራሱ እየሮጠ መምጣቱ እሰካሁንም ድረስ ያልገባኝ ምስጢር ሆኖ ቀረ፡፡ በአረጋዊ ጉዳይ በጎ በጎውን ለማሰብ ይቸግረኛል፡፡ ቀደም ባሉት ወራት ከሸራሮ ወደ ዓዲ ሃገራይ ከሁለት ታጋዮች ጋር ተልኬ ምንም ሳንሰራ መንገድ ላይ ጥሻ ውስጥ አድረን ተመልሰናል፡፡ ህወሓት ውስጥ አንድ ዘዴ ነበረ፡፡ የመኮብል እድል መፍጠርና ከተጠቀመበት አርምጃ መውስድ፡፡ የሸራሮውንም ሆነ የወርዒው ተልእኮ ከዚህ ፈተና አኳያ ጋር አገናዝቤዋለሁ፡፡ ብዙ ነገር እያየሁና እየሰማሁ ድርጅቱን ጥየ የመሄድ ሃሳብ ግን አልነበረኝም፤ ከአደጋ ለማምለጥ ብየ እስጋደረግሁት ቀን ድረስ፡፡

ሕነፍሽፍሽን ለማስጀመር ዝግጅቱ የተጠናቀቀ ይመስላል፡፡ የሚጀመርበት ሰበብ ብቻ ገና ነው፡፡ እኔን በማሰር ለመጀመር የታቀደ መሆኑን ያወቅሁት ግን ባልታሰበ ሰአት ነው፡፡ ኢሮብና ጋንታ አፈሹም አካባቢ ሽፍቶች ህብረተሰቡን እያስቸገሩ መሆናቸው ለህወሓት ጥቆማ ስለደረሰ የነበርኩባት ሃይል ሶሰት ጋንታዎች ለየብቻ አሰሳ ላይ ተሰማራን፡፡ የኛ ጋንታ መሪ ለጊዜው ባለመኖሩ (ለዮሃንስ በህይወት መኖር አምላክ ያበጀው ይመስላል) ጋንታውን ሲመራ የነበረው ኒክሰን ነበር፡፡ ይህ የሽፍቶች አሰሳ ታሪካዊቷ ማርያም ጉንዳጉንዲ ወደ ምትገኝበት ጥልቅ ሸለቆ ድረስ ወሰደን፡፡ አዛ በነበርንበት ሰአት ታሪክን የቀየረ ክስተት ተፈጠረ፡፡ ሰብያ ከሚገኘው የህወሓት የደህንነት ማእከል (ማእከላይ ሓለዋ ሳውራ) የተላከ አንድ ገበሬ ለኒክስን የሆነ መልእክት ሰጥቶት ይመለሳል፡፡ አኔ ይህንንከሩቅ ቆሜ እየተከታተልኩት ነበረ፡፡ አብሮ አደጌና የሰፈሬ ልጅ ጓደኛየ የነበረው የሁለተኛ አመት ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ኒክሰን (ዶር. ታደሰ አባዲ) መልእክቱን ከተቀበለ ብዙም ሳይቆይ ከሩቁ ጠራኝና መናገር የፈለገው ነገር እንደጠፋበት ዝም አለ፡፡ ከፊቱ ጭንቀት ይነበባል፤ ከባድ ጭንቀት፡፡ አቅም ሲያገኝ ነገሩን ተነፈሰው፡፡ መልእክተኛ እንደመጣ አይተሃል? እኔም አዎ ብየ መለስኩ፡፡ መልእክቱ የሚለው ይቺ ጋንታ ወደ ማእከላዊ ደህንነት (ማእከላይ ሓለዋ ሰውራ) ሰብያ መጥታ ሪፖርት እንድታደርግ ይላል አለኝ፡፡ አኔም መልእክቱ ያልተለመደ ስለሆነብኝ ለምንድነው ጋንታ ያህል ነገር ደህንነት ድረስ ሄዳ ሪፖርት የምታደርገው? ብየ ጠየቅሁት፡፡ አሱም ከጋንታዋ ሰው ማስቀረት ስለፈለጉ መሰለኝ አለኝ፡፡ አኔም በማያገባኝ ገብቼ በድፍረት የሚቀጥለውን ጥያቄ ጠየቅሁ፡-ሊያስሩ የሚፈልጉት ማንን ይሆን? ኒክሰን ያስጨነቀውን ነገር በፍጥነት አወጣው፡-አሁን የተፈለግኸው አንተ ነህ ብሎ አቅጩን ነገረኝ፡፡ እስቲ አስቡት፤ መልእክቱን የተቀበለው ኒክሰንስ ባይሆን ኖሮ! ዮሃንስ ለምን የመጀመሪው ታሳሪ እንደምሆን አልገባኝም፡፡ ግን ወዲያው ራሴን ከተበተንኩበት አሰባሰብኩና እንዲህ ብየ መለስኩለት፡- ኒክሰን ወንድሜ እኔ ውድቤን በቅንነት እያገለገልኩ ነው፤ ምንም የሰራሁት ጥፋት የለም፤ አሁን ይህን ሰምቼ ከማርያም ጉንዳ ጉንዲ ሸለቆ ውስጥ እንደወፍ በርሬ አልሄድም፤ የፈለጋቸውን ማድረግ ይችላሉ፤ እኔ የሞትኩት የሚያጠራጥር ነገር እየሰማሁ በእምነት ወደ ትግል ሜዳ የገባሁ ቀን ነው፡፡አዚህ ላይ ንግግራችን አበቃና ሰለመጣብኝ ክፉ እጣ እያሰብኩ ዋልኩኝ፡፡ በጊዜ ከማርያም ጉንዳጉንዲ ወጥተን ለማንም ግልፅ አላማ ወደ ስራዋት መንድር ወጣን፡፡ ኒክሰን ጋንታውን እየመራ ያለበት አካሄድ ባይገባኝም ስራዋት ግን አዲግራት ለነበረው የደርግ መድፈኛ ጦር አመቺ የሆነች ቦታ ነበረች፡፡ አስከ አዲግራት ድረስ ለጥ ያለ ሜዳ በመሆኑ ጦሩ መረጃ ካገኘ ጋንታችን ላይ ጥቃት ለመፈፀም ቀላል ነበር፡፡ ስራዋት ለአዲግራት ብቻ ሳይሆን ወደ መቐለ አቅጣጫ ለመጓዝም አመቺ ነበረች፡፡ ኒክሰን ማድረግ ስለሰበው የማውቀው ነገር ስላልነበረ ለምን ስራዋትገብተን እንዳደርን መገመት አልቻልኩም፡፡

አደገኛ ቦታ ሲታደር ሁለት ዋርዲያ ስለሚመደብ እኔና አንድ የራያ ልጅ ተመደብን፡፡ አሁን ሁሉም ነገር በጃችን ነው፡፡ አሱም በአመራሩ ላይ ብዙ ቅሬታ የነበረው ታጋይ ስለነበር ሌሊት የጥበቃ ተራችን ሳይበቃ ለመጥፋት ወሰንን፡፡ በማግስቱ የምታሰር መሆኔ የተነገረኝ ሰው ያመጣሁት ተለዋጭ ሃሳብ ግን የኔን የመኖር ተስፋ የሚያጨልም ነበር፡፡ የራያውን ታጋይ እንዲህ ብየአሳመንኩት፡-እኔ ሳልሄድ ብቀር ሞት እየተደገሰልኝ ነው፤ ሆኖም ግን አሁን እየጠበቅን ያለነው ቤት ሳይሆን አኛን አምነው የተኙት ወንድሞቻችንን ነው፤ ያለጠባቂ ከአዲግራት የመጣ ጦር ሊፈጃቸው ይችላል፤ ስለዚህ እኛ እንኖራለን ብለን የአድሜ ልክ ፀፀት አንግዛ፤ አምላክ ያውቅልናል፡፡ በዚህ በመተማመናችን ተራችንን ጨርሰን ለቀጣዩ አስረከብንና ተኛን፡፡ ህወሓትን ለማጥፋት አሲረሃል ተብሎ በማግስቱ አስር፤ ቁም ስቅልና ሞት የሚጠብቀው ሰው አይነት ሆኜ አይደለም በዛ ውድቅት ሌሊት ላለመክዳት የወሰንኩት፡፡ ሴረኛማ ይህን አጋጣሚ መጠቀሙ አይቀርም፡፡ የህወሓትን ታገዮችን ለማዳን ብሎ ራሱን ለመስዋእትነት አያቀርብም፡፡ እንደማይነጋ የለም ነጋ፡፡ ቀጥሎ የሆነው ግን አግዚአብሄር ሌሊት ያን ውሳኔ ስወስን እያየ እንደነበር ተገነዘብኩ፡፡ እግዚአብሄር አለ ብየ እርግጠኛ የሆንኩት በዛ ቀን ጧት ነበር፡፡ የተከሰተው አስገራሚ ነገር እንዲህ ነበር፡፡ ኒክሰን ጋንታዋን ሰልፍ ካስያዘ በኋላ አኔን ከሰልፉ እንድወጣና የያዝኩት ኤም 2 ግማሽ አውቶማቲክ ጠመንጃ ለአንዱ ታጋይ እንድሰጥ ትእዛዝ ሰጠኝ፤ ኒክሰን ራሱም የያዘውን ሲሞኖፍ አውቶማቲክ ለሌላ ታጋይ አስረክቦ የሃይል ውህደት ወደሚደረግበት ወደ ዛላምበሳ እንድትጉዋዝ ለጋንታዋ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ቀጥሎ እኔና ኒክሰን ብቻ ቀረን፡፡ ያኔ በነበረው ወታደራዊ ዲሲፕሊን ለምን እንደዛ ታደርጋላችሁ ብሎ መጠየቅ የለም፡፡ ኒክሰን ይህ ድራማ ሲሰራ ለምን እነደሆነ አሁን አልገባኝም፡፡ ትንሽ አብረን ከተራመድን በኋላ ህወሓትን ጥለን አብረን መሄድ እንዳለብን ነገረኝ፡፡ ይህን የሚያደርግበት በሁለት ምክንያት መሆኑን ነገረኝ፡- አንደኛ በሪሁ ሰባት የመቐለና የተምቤን ልጆች መረሸኑና ሁለተኛው ደግሞ ኒክሰን ጨዓመስከበት ውጊያ ላይ ከላዩ ላይ አሳት አጥፍቼ ህይወቱን ስላዳንኩት አሱም አሁን ከመጣብኝ ሞት ሊያድነኝ ዝግጁ መሆኑ፡፡ አሁን ሁሉም ነገር ገባኝ፡፡ ስለኔ መታሰር መልእክት ከደረሰው ሰአት ጀምሮ እኔን ለማዳን ውሳኔ እንደወሰነ ተረዳሁ፡፡ ወታደራዊ አመቺነት ወደሌለው ወደ ስራዋት የሄድንበት ምስጢርም ተከሰተልኝ፡፡ አስካሁን ድርስ ደስተኛ የምሆንበት ነገር ቢኖር በኔና በኒክሰን መኮብለል የጋንታዋ አባል ታጋዮች ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ከሃይል ጋር መቀላቀላቸው ነበር፡፡ ከሜዳ ከተመለስኩ በኋላ ከዛ ጋር የተያያዙ የእድሜ ልክ ችግሮች ቢያጋጥሙኝም እኔ ከመጎዳቴ በስተቀር በህወሓት ላይ ያሰብኩት የፈፀምኩት ምንም አይነት ክፉ ነገር ስላልነበረ ህሊናየ ንፁህ ሆኖ ይኖራል፡፡ በርካታ የማውቃቸውና የምወዳቸው በሕይወት ተመልሰው በአይነ ስጋ ስላየኋቸውም በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡

የኔና የኒክሰን ከህወሓት መልቀቅ በቀላሉ የታየ ክስተት አልሆነም፡፡ ከኛ በኋላ የለቀቀ አንድ ታጋይ እንደነገረን ዶር. አረጋዊና ሌላ አመራር አባል የኛን መኮብለል ዜና ሲነገራቸው ከእጃችን ነው ያመለጡት የሚል ቁጭት አሰምተዋል፤ ለምን? ምነ አጠፋን? በህወሓት ላይ በእንደርታ ታጋዮች የተቀናበረ አመፅ ነበረ ከተባለ አኛ እንዴት ሳናውቀው እንቀራለን? መቸም በወቅቱ እኔም ሆንኩኝ ኒክሰን ለእንደርታ ታጋዮች እንደ ኢሚንት የምንቆጥር አልነበርንም፡፡የአመፁ እኛ የማናውቀው ሌላ ቢሆን ኖሮ የነዶር. አረጋዊ ጦር ወደኛ አይዞርም ነበር፡፡ እኛ ደግሞ ይህንን አይነት ሴራ በህልምምቢሆን አላሰብነውም፡፡ የ1969 ዓ.ም. ሕንፍሽፍሽእንደርታን ከትግሉ ውጭ ለማድረግ ከኩይሳ የተፈጠረ ተራራ ነው፡፡ የኔና የኒክስን መቐለ ከተማ መግባት ከዛ በፊት ያልታየ ክስተት ስለነበረ የከተማው የህወሓት መዋቅር አባላት ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሮ ነበር፡፡ እነዚህ ቅን አባላት ለምን እንደተመለስን አጥብቀው ሲጠይቁን ሰነበቱ፡፡ ሰዉ ሁሉ አልገባውም፤ አኛስ ቢሆን መቼ ገባን! የኔና የኒክሰን ህወሓትን መልቀቅ ተከትሎ ሃይለ ፖርት ሱዳንና ሃይሉ ነጠበ ቤዝ ወስደው እንዳሰሯቸው ሰማን፡፡ የተፈለገው ይህ ነበር! በታመሰ ባህር ውስጥ አሳ ማጥመድ፡፡ ከዛ ተከትሎም የማጥራት ዘመቻ በሰፊው ተካሄደ፤ ስጋት ያደረባቸው የእንደርታና የሌሎች አውራጃ ታጋዮች ህወሓትን በጎርፍ መልክ ስለለቀቁ የ1969 ሕፍሽፍሽ ተብሎ ስም ወጣለት፡፡ ስሙ እንጂ ባለስሙ ግን የትም አልነበረም፡፡

 

Back to Front Page