Back to Front Page

የኢትዮጵያ የዘመኑ ፖለቲካ፤ እሳት ላይ ጋዝ ማርከፍከፍ

የኢትዮጵያ የዘመኑ ፖለቲካ፤ እሳት ላይ ጋዝ ማርከፍከፍ

ዮሃንስ አበራ (ዶር) 05-18-20

አሳ አጥማጅ ባህሩ ፀጥ ሲል አይወድም ምክንቱም አሶቹ ስለሚረጋጉ መረቡን አይተው ሊሸሹ ይችላሉ ወይንም ከባህሩ ጥልቀት ውስጥ ሊሆኑ ያችላሉና፡፡ ባህሩ ወጀብ ሲመታው አሶች ወደላይና ወደ ዳርቻ ሊገፉ ይችላሉ፤ በተጨማሪም ግራ ተጋብተው ሳያውቁት ወደ መረቡ እየዘለሉ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ በታመሰ ዉሃ አሳ ማጥመድ የሚለው የኢንግሊዝኛ ተረት የፖለቲካ ጥቅም የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይንም ቡድኖች ህዝቡ ተረጋግቶ እንዳያስብና በውጥረትና በጭንቀት የነሱን መከታነት እንዲሻ የሚያደርጉበት ቅንነት የጎደለው ዘዴን ለማመልከት የታለመ ነው፡፡ ይህ ዘዴ የአሳው መኖሪያ የሆነው ባህርን ቀውጢ በማድረግ አሳው የመጣበትን አደጋ በእርጋታ እንዳያስተውል ሲያደርግ በአሳው የተመሰለው ህዝብም ኑሮው በውዝግብ የተሞላ በማድረግ የግለሰብ ፖለቲከኞች ሆነ የፖለቲካ ቡድኖችን ድብቅ አላማ ለማስተዋልና ጠንቅቆ ለመገንዘብ እንዳይችል ይሆናል፡፡

ሚድያዎን አፍነው ይዘው ከመፋቀር ይልቅ መጣላትን የሚያስቀድሙ፤ ይቅር በኛ ያብቃ ትውልድ ይዳን ከመባባል ይልቅ ቁስል ላይ ስንጥር በመትከል የጥላቻ ስሜት ተባብሶ ወደ ቀጣዮቹ ትውልዶች እንዲሻገር ለማድረግ ቀንና ሌሊት የሚታክቱ፤ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ እንዳትበቅል የሚሉ ላለፉት 50 አመታት ከስልጣን የተገለሉ ሶስት መንግስታትና ተከታዮቻቸው፡ ቀጣዩ መንግስት ከነሱ የባሰ እንዲሆን በማስደረግ ህዝብ እንዲናፍቃቸውና ወደፊት ሳይሆን ሁል ጊዜ ወደ ኋላ እያየ እንዲኖር የሚጥሩ፤ ኢትዮጵያ ያለችበት ጂኦፖለቲካዊ አቀማመጥና የነፃነት ተምሳሌት ሆና የመኖሯም ታሪክ ለሚያበሳጫቸው ሃይሎች ጥቃት ምቹ ሆና ብትገኝ የማያስጨንቃቸው፤ የግል ኑሯቸው የተደላለደለ እስከሆነ ድረስ በደሃው ህዝብ ላይ ቢነግሱ የማይጎረብጣቸው ኢትዮጵያ ሳትዘራቸው የበቀሉ አገሪቱን ወደ ጥፋት ጎዳና እየመሯት ነው፡፡ ስልጣን ጥቅም ከሌለው ማንም አይፈልገውም፤ ለህዝብ ራሱን አሳልፎ የሰጠ የመልአክ ዝርያ ያለው ካልሆነ በስተቀር፡፡ ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ የሚብስ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያውያን እርስ በርስ ይፋቀራሉ፤ አገራቸውን ይወዳሉ የሚሉ የላም በረት የማይባልባቸው ተረቶች አሉ፡፡ እንዲህ አይነት አባባሎች በተግባር አይታዩም፡፡ አገር ማለት ሰው ነው የሚለው አባባል ይመቸኛል፡፡ ለጋራና ሸንተረሩ እየዘፈኑ ጋራና ሸንተረሩ ላይ የሚኖረው በሚልዮኖች የሚቆጠረው ድሃ ወገን ተረጋግቶ የእለት ህይወቱን እንዳይገፋ ያለውን ልዩነትን እየለጠጡ አዲስም እየፈጠሩ ሰላም ማሳጣት ምኑ ላይ ነው አገር ወዳድነቱ?

Videos From Around The World

ባሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ እጅግ አስጨናቂ ነው፡፡ ለልማት ዋስትና ይሆነኛል ብላ የጀመረችው የግድብ ግንባታ ታላቅ ፈተና ገጥሞታል፤ ቀላል መፍትሄ ያለውም አይመስልም፡፡ አገራቸውን ወደው ፍላጎቱን ለማስፈፀም ቆርጠው በተነሱት ግብፆችና አገራቸውን በውዝግብ አዳክመው ለጥቃት አመቺ ያደረጉት ኢትዮጵያወያኖች ተፋጠዋል፡፡ የሁለቱ ሃይል ተመጣጣኝ አይደለም፤ የግብፅ አቅም ይበልጣል፡፡ ለምን ቢባል የጦር ሃይል ብዛትና ጥራት አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ስትዋጋና ስታሸንፍ የኖረችው ከሷ የበለጠ የጦር አደረጃጀት ከነበራቸው መንግስታት ጋር ነው፡፡ አሸናፊ የሚሆነው ከመሳሪያው በስተጀርባ ያለው የአላማ አንድነት ነው፡፡ ኢትዮጵያና ግብፅ ጦርነት ቢገጥሙ ኢትዮጵያ ልትሸነፍ የምትችለው በግብፅ ዘመናዊ ሄሊኮፕተሮች ወይንም ሚሳይሎች ሳይሆን በግብፅ ህዝብ አንድነትና አገራዊ የአላማ ፅናት ነው፡፡አካሄዱን አይተው ሸክሙን ይቀሙታል የሚባል ተረት አለ፡፡ ቀማኛ በተፈጥሮው ፈሪ ነው፡፡ብርም ንብረትም ቀምቶ በሰላም ቤቱ ገብቶ ለመጠቀም እንጂ በቅሚያ ላይ በጀግንነት መሞት አይፈልግም፡፡ለዚህም ነው የሚቀማውን መንገደኛ አቅም በአረማመዱ የሚለካው፡፡ይህ ተረት ለቀማኛ የተፈጠረ አይደለም፡፡ ደካማ ሰውና ደካማ አገር ፈሪም ቢሆን እንደሚደፍረው ለማመልከት ነው፡፡ ግብፅ የኢትዮጵያን አረማመድ በሚገባ አስተውላለች፡፡ ለዚህ የተልፈሰፈሰ አረማመዷ ግብፅ በሰፊው አስተዋፅኦ አድርጋለች፤ ቢሆንም ተጠያቂ አይደለችም፡፡ ተጠያቂው አገሬን እወዳለሁ፤ ውለታ ሰርቼላታለሁ፤ ከወያኔ አፅድቻታለሁ እያለ ሲፎክር ከርሞ በወያኔ ጊዜ የነበረውን አንፃራዊ ሰላም የሚያደፈርሰው ነው፡፡

ለኢትዮጵያ አንድነት መሰረት የሚሆነው መከባበር ነው፡፡ አንዱ ህዝብ ሌላውን ካላከበረው በመልሱ አክብሮትን መጠበቅ የለበትም፡፡ እኔ የምሰራው ሁል ጊዜ ትክክል፤ አንተ የምትሰራው ሁል ጊዜ ስህተት ነው የሚባባል ከሆነ ራስን የአምላክ ባህርይ አላብሶ ሌላውን ማሰይጠን ይሆናል፤ ይህን የሚቀበልም አይኖርም፡፡ የዚህ አይነት መነጋገር ሳይሆን ለየብቻ መናገር ውጤቱ መደነቋቆር ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ሲዳሞ በዘመቱት የእድገት በህብረት ዘማቾች ላይ በሬድዮ የተነገረው መግለጫ ከዚህ ጋር የሚሄድ ነው፡፡ በጩኸት የፈረሰች አገር ብትኖር ኢያሪኮ ብቻ ናት ይላል የመግለጫው ርእስ፡፡ መልእክቱ በጩኸት አገር አትፈርስም ነው፡፡ አገር በጩኸት ልትፍርስ የምትችለው ጩሀቱ እንድ አይነት ሲሆን ሳይሆን የተለያየና የማይሰማማ ሲሆን ነው፤ ድምፁ እየጨመረ የሚሄደው አንዱ የራሱ ጩኸት ብቻ እንዲሰማ በሚያደርገው ጥረት ነው፡፡ አራሱ ፈልጎ ወይም አሳምነውት ካልሆነ በስተቀር ማንም ሰው የራሱን ድምፅ ቀንሶ የሌላውን ኸት አይሰማም፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚያምሳትና ሊያፈርሳት የሚታገላት ጩኸት እኔ እበልጣለሁ፤ እኔን ብቻ ስሙኝ፤ እኔ ብቻ ልክነኝ ጩት ነው፡፡ ጩኸቱ ጎልቶ የሚሰማው አመድ በዱቄት ላይ ሲስቅ ነው፡፡

ሰሞኑን አገሬ አዲስ የተባሉ ፀሃፊ በአይጋ ፎረም ላይ ያወጡት መጣጥፍ ላይ የሰፈረው የግብፅና የኢትዮጵያ ሁኔታ እንዲሁም ስለኢትዮጵያዊነት ያሰፈሩት ትንተና በጣም የሚመስጥ ነው፤ ለዚህም ላመሰግናቸው ላከብራቸው እፈልጋለሁ፡፡ ስለኢትዮጵያ ህዝብ አንድነት አስፈላጊነት ሲያትቱ ግን ቃላት አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ አላደረጉም፡፡ ሰሜን ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰነዘሩ አስተያቶች ምንም ቢጨቀዩ ጠፈፍ ያሉ ናቸው፤ ደረቅ ናቸው እየተባሉ የሚታለፉበት ምሰጢር ምን ይሆን? ደርጎች፤ ብአዴኖች፤ ኦህዴዶች እንዲህ አደረጉ ብሎ ለመናገር የሚሸማቀቅ ፀሃፊ ድምፁን ከፍ አድርጎ ወያኔዎች እንዲህ አደረጉ በማለቱ ሙገሳ የሚዘንብለት ለምን ይሆን? አገሬ ስለ ህዳሴው ግድብ በሰፊው ፅፈዋል፤ ግንባታውን በድፍረት እንዲጀመር ያደረገውን ግን ለማሞገስ በጣም ተቸግረዋል፡፡ መለስ ግድቡን ያስጀመረው በራሱ ሰይጣናዊ አላማላይ ተመስርቶ ቢሆንም ማስጀመሩ ግን ለኛ እርግማን መስሎ ምርቃት ሆኖልናል (ትርጉሙ እንዳልተዛባ ተስፋ አለኝ)፡፡ መለስ የሰራቸው መጥፎ ድርጊቶች ይኖራሉ፡፡ ለዚህ የቦዘነ ሰው የለም የክልሉ ተወላጆችም በየብእራቸው ይተቹታል፤ ሞቶም አላሳረፉት፡፡ በመሰረቱ ራስን ወይንም የራሴ ነው የምትለውን ወውቀስ የስልጣኔ መገለጫ ነው፡፡ ህወሓትን በግንባር ቀደምትነት የሚተቿት አብዛኛዎቹ የትግራይ ተወላጆች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች በጎ ነገራቸውን እያገነንን እናሞግሳቸዋለን እንጂ በህዝብ ላይ የፈፀሙት በደል እኮ ዳር ድንበር አልነበረውም፡፡ ግን ስለመጥፎ ድርጊት ስናወራ ብንከርም ፋይዳ የለውም፤ አንድነታችንን ከማላለት በስተቀር፡፡

እርግጥ ነው ግድቡ ሲጀመር መለስ ይችን አገር ቁልቁል ሊደፋት ፈልጎ ነው ያሉ ሰዎች እንደነበሩ በጆሮየ ሰምቻለሁ፤ ይህ የአንድ ሁለት ሰው ብቻ ሳይሆን የሺዎች አመለካከት መኖሩም የአዋቂ ግምት አሳድሮብኛል፡፡ ከፅሁፉ የከፋው ነገር ግድቡን ለመስራት መለስ በሆዱ ይዞ ነበር ስለተባለው ስውር አላማ ነው፡፡ትግራይ ከኤሪትርያ ጋር በማበር የራሷን መንግስት ስትፈጥር መለስ ሆን ብሎ የፈጠረውን ደካማ የቤኒሻንጉል ክልል ግዛት በመጠቅለል ግድቡን ለራሷ ለማድረግ ነው፡፡ ይላል ፅሁፉ! ጨዋና ያልታረመ ሰው ያላቸው ልዩነት ከክር የቀጠነ ነው፡፡ ጨዋ የሆነውና ጨዋ ያልሆነው ሰው ሁለቱም በአንድ ነገር ላይ እኩል መጥፎ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል፤ ሁለቱም ወደ አፋቸው መጥፎ ቃል ሊመጣባቸው ይችላል፡፡ ልዩነታቸው ግን ጨዋው መጥፎ ቃሉን መልሶ ዋጥ ያደርገዋል፤ ጨዋ ያልሆነው ግን ወደ ውጪ ይተፋዋል፡፡ መለስ በሌላ ነገር ይወቀስ እንጂ በንዲህ አይነት ነገር መታማትም አልነበረበትም፡፡ በነገራችን ላይ አገሬ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ መምታት ችለዋል፡፡ በግድቡ የሰሜንን ሰው ሚና በማቃለል ሲረኩ በሌላ በኩል ደግሞ ቤኒሻንጉል ጉምዝን ክብር በመንካት የውስጥ ስሜታቸው ሳያስቡት ፈንድቶባቸዋል፡፡ በመሰረቱ እነዚህ የቤኒሻንጉል ሰዎች ክልላቸው በሰሜን ሲወረር ዝም ብሎ የመተባበር ባህል አላቸው እየተባሉ ነው? ለህልውናውና ለሰብአዊ ክብሩ የሚሞተው የተለየ ህዝብ ማነው ታዲያ? በዝባዝንኬ ትርክት አዘቅት ውስጥ ብዙ ሳንጓዝ ግድቡ ጉባ ላይ የተሰራበት ቴክኒካዊ ምክንያት እንዳለው መገንዘን ያስፈልጋል፡፡

በጣናና በግልገል አባይ ላይ ግድብ ለማሰራት ያቀዱት ቀዳማዊ ሃይለስላሴ ተሞግሰው ወደ ሱዳን ድንበር አስጠግቶ ግድብ ያስጀመረው መለስ ዜናዊ የተወቀሰበት ለኢትዮጵያ ከጉባና ከጣና ሃይ የትኛው ስለቀረበ ነው? ግድቡ ሱዳን ድንበር ድረስ የተጠጋው ግልገል አባይ ላይ ይሁን፤ ጣና ሃይቅ ላይ ይሁን በሺሎ፤ ጃማ ላይ ይሁን ወለቃ 6000 ሜጋዋት የሚያመነጭ በቂ ዉሃ ስለማይኖር ነው፡፡ አባይ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ የመጨረሻው የዉሃ ይዘት የሚኖረው ዲዴሳ፤ ዳቡስና በለስ ወንዞች ከተቀላቀሉት በኋላ ነው፡፡ ይህ የሚሆነውም ካማሺና መተከል ድንበር ላይ ካላው ጉባ ነው፡፡ ሳያጣሩ ወሬ፤ ሳይገድሉ ጎፈሬ ሆኖ ወደ ስም ማጥፋት ከመሮጥ ይልቅ የግድብ ስነዉሃ ባለሙያ ማነጋገር ይቀል ነበር፡፡ ለነገሩ ችግር የለም የሰሜንን ሰው በሰራውም ባልሰራውም መሳደብና ስም ማጥፋት የሚያስሞግስ እንጂ የሚያሰኮንን ወይንም የሚያስቀጣ አይደለም፡፡ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ ሁለት ሰው ሊሆን አይችልም፡፡ ሁዋላ ትግራይ ግድቡን ወራ ለመያዝ እንዲያመቻት አድርጎ ያዘጋጀላት መለስ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መሪ ሆና እንደትቀጥል የሚያስችላትን የአፍሪካ ህብረት ፅ/ቤት በአዲስ አበባ ለማቆየት የማይወዳቸውን መሬዎች ስም እያሞገሰ ሽንጡን ገትሮ ተሟገተ! በመሰረቱ ፎብያ የአይምሮ በሽታ ነው፡፡ ራቢስ የተሰራጨበት ሰው የፍጡራን ህይወት የሆነውን ዉሃን ይጠላል፡፡ ጥላቻ ከበሽታዎች ሁሉ የከፋ በሽታ ነው፡፡

የትግራይ ህዝብ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ፍላጎት የለውም፤ ትርጉምም አይሰጠውም፤ የተወሰኑ አዲስ ፖለቲካኞች ከመንጫጫታቸው በስተቀር፡፡ ይህም የሆነበት ምክንያት የመገንጠል አቅም ስለሌለው ወይም ከኢትዮጵያ መንግስት የሚያገኘው ጥቅም እንደይቀርበት ሳይሆን ኢትዮጵያ ምንም ባይተዋር ብታደርገውም እናት አገሩ ስለሆነች ነው፡፡ የመገንጠል ሃሳቡ ራሱ ለህዝቡ ባዕድ ነው፡፡ ጥላቻ የበረታባቸው ግለሰብ ፖለቲከኞች ግን በመሳደብ፤ በመወንጀል፤ በማባረር፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ደህንነትና ምቾት እንደይሰማው በተለያዩ ረቂቅም ገሃድም የሆኑ ዘዴዎች በመጠቀም የመገንጠል ፍላጎትን በግድ እያጎረሱት ነው፡፡ እልክ የሚያጋባ ተራ ንግግርም አለ፡፡ ለምሳሌ ትግራይ ከፈለገች ትገንጠል፤ ከኢትዮጵያ የምታገኘው እንጂ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው የላትም፤ ግልግል ነው፤ ከኢትዮጵያ ተገንጥለው አንድ ሌሊት አያድሩም ወዘተ፡፡ ራሱ በዚህ ተራ የሆነ ህዝብን የማግለል ድርጊት የሚሳተፍ እንጂ አደብ የሚያስገዛ መንግስት በሌለበት ሁኔታ ሰለባ ለሆነው ህዝብ ይህ ታላቅ ጭንቀት የፈጠረ ነው፡- እንዳትልሰው ፈጃት እንደትተወው ልጅ ሆነባት ይገልፀው ይሆን?

በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትግራይን የሚመለከት የፖለቲካ ሁኔታ በትግርኛ ተረት ለመግለፅ እሞክራለሁ፡- ኣይትፅብሕዮ እንተበልኩዋስ ትገጦላ፡፡ የዚህ ትርጉም የባሰ ስራ አትስሪ ለማለት ነው፡፡ ወጡን እያጠቀሰች መብላት እንዳይበቃት እያፈሰች በመጉረስ ያስቸገረቻትን እንግዳ ላይ በቁጣ የተናገረችው ነው፡፡ ህወሓት በሰላም ከፌደራል ስልጣን ወረደችና ሰዎቹ ወደ ትውልድ ስፍራቸው ሄዱ፡፡ ከስልጣን የተወገዱት በህገ መንግስቱ መሰረት በምርጫ መሆንሲገባው ኣልተደረገም፡፡ የህወሃት አመራሮች የሰሯቸው ጥሩ ተግባራት ቢኖሩም መጥፎዎቹ ገነው ታይተዋል፡፡ እውነትም ገነን ብለው ነበር፤ ዳኛ መሆን የነበረበት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ካርዱ አማካይነት ነበር፡፡ ችግሮቹ ገነው እንዲታዩ ምክንያት የሆነው ድርጊቶቹ ራሳቸው ብቻ ሳይሆኑ ባመዛኙ ሚዛን የጎደለው የአመለካከት ችግርም ነው፡፡ ያም ሆነ ይህ እነዚህ በጦር አድገው በጦር ያረጁ መሪዎች ድምፅ ሳያሰሙ ከአራት ኪሎ ወጥተው በሰላም ወደ ማረፍያቸው መሄዳቸው እፎይ የሚያሰኝ መሆን ነበረበት፡፡ ለክብራቸው መሳሪያ መዘው አራት ኪሎን ቀውጢ ቢያደርጉትስ ኖሮ እየተቀጣጠለ አገር መሆን እንችል ነበርን? ሰብአዊ ፍጡር ናቸውና ስሜታቸው እንደሚጎዳ ጥርጥር የለውም፡፡ የሄዱበት ክልል ህዝብ ምንም እንኳ በነሱ ላይ ብዙ ቅያሜ ቢኖረውም ልጆቹ ናቸውና በሰላም እያኖራቸው ነው፡፡ ነገሮች እዚህ ላይ መቆም ነበረባቸው፡፡ ቀጥሎ የመጣው ነገር የለቀቀን እንደወደቀ የመቁጠር አጉል ትእቢት ነበር፡፡ ከመሪዎች የማይጠበቁ የወረዱ ቃለት ሁሉ ባደባባይ መለፈፍ ጀመሩ፤ ሌላውም እንደ ወቅታዊ ፋሽን ተከተለው፡፡ ስድቡ መንገድ ላይ የልጆች መጫወቻ እስከ መሆን ደረሰ፡፡ አንዳንድ ክልሎች ላይም ሮሂንጃይዝም ተጀመሮ ተጧጧፈ፡፡ አጠፉ የተባሉት የህወሓት መሪዎች ለቀው ሄዱ፤ ሌሎችም በወረንጦ እየተለቀሙ ተባረሩ፡፡ መቸም ጉልበት ሃቅ ነውና ያልተፈለጉት ተወግደዋል፡፡ እዚህ ላይ አዳምን ያስገረመው በህዝብ ላይ የተከፈተው ዘመቻ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ፊትም ቢሆን ጥላቻው በህወሓት የአስተዳደር ችግር ብቻ ሳይሆን ከዛ ዘለግ ያለ ነበር ማለት ነው፡፡ አዋቂ ሰው የፈለገውን ሲያገኝ ጥንቃቄ መውሰድ አለበት፡፡ ነገሮችን ለማለዘብና ለድርድር ለምክክር ለፍቅርም እድል መስጠት አለበት፡፡ ፍላጎቱ ካለ በደል በቀላሉ እንዲረሳ ማድረግ ይቻላል፤ የት ይደርሳሉ፤ምን ያመጣሉ የሚሉ የእብሪት ስሜቶች ገዢ ስሜቶች እንዲሆኑ ካልተፈቀደላቸው በስተቀር፡፡ በዳይ ወገን የተበዳዩን መጥፎ ስሜት ለመሻር ጥረት ማድረግ ይገባዋል፡፡ ነብርን መውጫ መግቢያ ካሳጡት ወደ አሳዳጁ ይዘላል፤ ቢያዋጣው ባያዋጣውም ደመነፍስ ነውና!

ኮሮና ቨይረስ በአለም ዙሪያ ብዙ ህዝብ እየፈጀ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያን ያህል ደረጃ ባይደርስም ስጋቱ ግን ቀላል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያን የእድገት ጉዞ አንበርክኮታል፡፡ እድገትን ብቻ አይደለም የአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታም አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ምርጫው ይተላላፍ አይተላለፍ የሚል ሙግት ተጀምሯል፡፡ በሁለቱም ወገን ያለው የክርክር ሃሳብ ተገቢነት ማንም ሊረዳው የሚገባ ነው፡፡ ነሃሴ ውስጥ ምርጫ መካሄድ ነበረበት፤ በወርሺኙ ምክንያት ማእከላዊ መንግስት አይቻለኝም አለ፡፡ ልክ ነው ? አዎ ልክ ነው! ምንም እንኳን ምርጫ ማካሄድ ህገ መንግሰታዊግዴታ ቢሆንም ለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ የማያመች ሁኔታ ሲፈጠር ምርጫ ማካሄድ ምናልባት ውጤቱን ሊያበላሸ ይችላል የሚል ስጋት ተገቢ ስጋት ነው፡፡ፈተናው ግን ወረርሽኙ መቼ አብቅቶ ለምርጫ የሚመች ሁኔታ ይመጣል የሚለው አምላክ ብቻ የሚመልሰው ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ በተግባር ማራዘሙ ገደብ የለሽ ይመስላል፡፡ ህወሓት በፌደራል ካለተቻለ የክልሉን ምርጫ እናካሂድ አለች፡፡ ልክ ናት ? አዎ ልክ ናት! በህገ መንግስት ስንተዳደር ህገ መንግስቱን ተግባራዊ ለማድረግ ቀዳዳዎችን መፈለግ አለብን ባይ ናት፡፡ ሁለቱም ወገን ልክ ናቸው፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ውይይትና ድርድር ነው፡፡ ህወሓት ከፌደራል ስልጣን ብትወርድም አሁንም ክልል እያስተዳደረች ነው፡፡ የመወሰን ግዴታ አለባት፡፡ ፌደራል መንግስትም ሁኔታዎችን አይቶ የመወሰን ስልጣን አለው፡፡ በነዚህ ሁለት ውሳኔ የመወሰን ሃላፊነትና ስልጣን ባላቸው አካለት መካከል የሚፈጠር ልዩነት እንደ በጎ የዴሞክራሲ ልምምድ መወሰድ አለበት እንጂ የሌላ ቂም በቀል መወጫ መሳሪያ መሆን የለበትም፡፡ በመሃሉ የምትጎዳው አገር ናት፡፡ መደረግ አለበት ብየ የማስበው ምርጫው የትግራይ ህዝብም ፍላጎት ከሆነ ወረርሺኙ ከምርጫ አያግደንም ካለ መፍትሄ መስጠት ያለበት ምርጫ ቦርድ ነው፡፡ ምርጫ ቦርድ በትግራይ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ያመቸናል ባሉ ክልልሎችም ምርጫ እንዲካሄድ ድጋፍና የድርጅት አቅም መስጠት አለበት፡፡ ከዛ በተረፈ ግን የፊተኛው እንዳይበቃና ይቅርታ ሳይጠየቅበት ደግሞ ሌላ ግዴለሽ ንግግር አስፈላጊ አይደለም፡፡ እየተነገረ ያለው ስለምርጫ እንጂ ስለህወሓትና ብልፅግና ፓርቲ ፉክክር አይደለም፡፡ በምርጫ ቦርድ ድጋፍ የሚካሄድ የትግራይ ክልል ምርጫ የተሰጋውን የግንጠላ ሂደት የሚያስቀር ይሆናል፡፡ ለምን ቢባል ያለ ምርጫ ቦርድና ማእከላዊ መግስት ምርቃት በትግራይ የሚካሄድ ምርጫ ወደ ግንጠላ እንደሚያመራ ማንም ሰው መጠራጠር የለበትም፡፡ ማእከላይ ምንግስት ይህ እንዲሆን አይፈልግም ብየ አምናለሁ፡፡ አሁን የማእከላዊ መንግስት እልክ ለማንም የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ያለው ሁኔታ የአዛዥና ታዛዥ፤ የእምቢተኛና የፈቃደኛ ጉዳይ አይደለም፡፡ የሃገር ህልውና ጉዳይ ነው፤ ጥንቃቄና ትእግስት ይፈልጋል፡፡

ምርጫ የምታካሂዱ ከሆነ እርምጃ እንወስዳለን የሚለው አማርኛ ስለሚያስከትለው ጦስ ፍፁም ምክክር የተደረገበት አይደለም፡፡ ዛቻው ከጉዳዩ ጋር የተመጣጠነ አይደለም፡፡ሁለቱም ወገን የሚናገረው ስለ ህገመንግስት መከበር ነው፡፡ ይህ መልካም ነገር ነው፡፡ ብዙ ዘመን እኮ ለክርክር እድል ሳንሰጥ እኮ ተፋጅተናል፡፡ ከዚህ ጥንቃቄ ያልተወሰደበት ንግግር ብዙ ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ፡- ቀዳሚው፡ የሚወሰደው እርምጃ ምንድነው? የሚል ነው፡፡ አውራ መንገዶች መዝጋት? በጀት ማቆም? መብራትና ስልክ መቁረጥ? ጦር ልኮ ክልሉን መውረርና የህወሃትን አመራሮች አስሮ አዲስ አበባ ማምጣት? ወዘተ፡፡ ነገሩ የፊልም ስክሪፕት ይመስላል፤ አሸናፊ ግን አይኖርም! ችግርን ለመፍታት ሌላ በቀላሉ የማይፈታ የከፋ ችግር መጋበዝ ብልህነት አይደለም፡፡ አሁንም አልዘገየም፡፡ ማእከላዊ መንግስት ለኢትዮጵያ ሲባል ራሱን ከመጠን በላይ ማግዘፉን ትቶ ከክልል መሪዎች ጋር በእርጋታና በአገር ፍቅር ስሜት መነጋገር ያስፈልገዋል፡፡ባንዳ የሚለው የሚዘገንን ፍረጃም ጥንቃቄ ይደረግበት፡፡ ከአፍ የወጣ አፋፍ ነው፡፡ በወሬ፤ በግምትና የሞራል ጥቃት ለማድረስ በታሰበ ተንኮል ሳይሆን በተጨባች ማስረጃ ኢትዮጵያን አሳልፎ የሰጠን ሰው ስድብ ሳይሆን ፍርድ ቤት ይቅረብ፡፡ ሌላው አላስፈላጊ ትርፍ ቃል ነው፡፡ በኢትዮጵያ አንድ ቀረርቶ አላ፤ እንዲህ ይላል፡- ነካካቸው ነካካቸው አትስጣቸው ጤና፤ ምንጊዜም ደህና ሰው አልተባልክምና፡፡ ጥቃት የበዛበት ግለሰብም ሆነ ህዝብ ወዳልተፈለገ የእልክ ስራ ሊገባ ይችላል፡፡ ጉዳቱም የጋራ ነው፡፡

Back to Front Page