Back to Front Page

የትግራይ የምርጫ ነገር፣ ከበቀለ ብርሃኑ የቀጠለ

የትግራይ የምርጫ ነገር፣ ከበቀለ ብርሃኑ የቀጠለ

ዮሃንስ አበራ (ዶር)

08-02-20

 

ጋሽ በቀለ ምርቃቱንና ምስጋናውን ተቀብያለሁ እድሜ ይስጥልኝ። የሃገራችንን ሁኔታ መልክ ለማስያዝ የማደርጋት ኢምንት የምታክለው ጥረቴን ስላሞገሱልኝ በሃገራችን ስም ምስጋናየ ይድረሰዎት። ይህን ካልኩ በኋላ የትግራይን ምርጫ አንስተው ያቀረቡት አስተያየት ሳላደንቅ አላልፍም። የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ትግል የተካሄደው የህዝብ በነፃነት መሪዎቹን የመምረጥ መብት በሚያራምዱና ምን እንደምትፈልግ እኛ እናውቅልሃለን በሚሉ የጭቆና ሃይሎች መካከል ነው። ሌላው ሁሉ የዚህ ዘርፍም ቅርንጫፍም ነው። የመምረጥ ነፃነት ያህል ፀጋ ከየት ይገኛል። ሳይበሉ ማደር ይሻላል። እውነት እላችኋለሁ ምርጫ የይስሙላም ቢሆን እንኳ ከአለመምረጥ ይሻላል።

Videos From Around The World

አይኖች ሁሉ ትግራይ ላይ አርፈዋል አሉ አቶ ሙሉ አይጋ ፎረም ላይ። እውነት ነው ትግራይ እናት ስለሆነች ወደሷ መመልከቱ መልካም ነው። አሁን ሁሉም ትግራይ ላይ አይኑን ያሳረፈው ግን እኔ ባልኩት ምክንያት አይደለም። ምክንያቱ ምርጫ በማካሄድ የትግራይ ህዝብ "ወንጀል"  ሊሰራ ነው  ብለው በመገረማቸውና አንዳንዶችም በመናደዳቸው ነው። በዚች ዴሞክራሲ በራባት በጠማት አገር አንድ ህዝብ ምርጫ ሲያካሂድ እልል ይባላል እንጂ ማዘን መናደድ መፎከር ማስፈራራት ለሰሚው ግራ ነው።  ምርጫውን ለማውገዝና እርምጃ ለመውሰድ ከማሰብ በፊት አንድ መረጋገጥ ያለበት ነገር አለ። ህወሓት ህዝቡን ምርጫ ላይ እንዲሳተፍ አስገዳጅ ሁኔታ ጥላለች ወይስ ህዝቡ ያለ ተፅእኖ በራሱ ፍላጎት በምርጫ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ነው? የሚለው ጥያቄ ሳይጠየቅና በቂና አስተማማኝ መልስ ሳይገኝበት እንዲሁ የውግዘትና የማስፈራራት ቃል መሰንዘር ከመንገድ የወጣ ጭፍን የጥላቻ ስሜት የነዳው ተግባር ነው። በበኩሌ የህዝቡን ስሜት ለማግኘት ብዙ ጥረት አደረግሁና አንዳንድ በምርጫ አንሳተፍም ከሚሉ የፓለቲካ ፓርቲዎች በስተቀር ህዝቡ ምርጫውን እየተቃወመ ነው የሚል ነገር ከጆሮየ አልደረሰም። ተቀስቅሶ ነው፣ እያሳሳቱት ነው፣ ፈርቶ ነው፣ ወዘተ የሚሉትን ግምቶች ወደ ጎን ትተን ህወሓት እንዲህ አይነት ድርጊት ስኬቱ በህዝብ ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እያወቀች በሃይል ከየቤቱ እያስወጣሁ አስመርጠዋለሁ በሚል ስሌት ለምርጫ እየተዘጋጀች ነው የሚል አስተሳሰብ ካለ በጊዜ ቢታረም ይሻላል። እንግዲህ ህዝብ እመርጣለሁ እያለ ህወሓት ላይ ጣትን ቀስሮ ማውገዝ በተዘዋዋሪ ህዝቡ ላይ ጣት መቀሰር ነው። መምረጥ ወንጀል ከሆነ ወንጀለኛ የሆኑት ህዝቡም ህወሓትም ናቸው። ህዝብ እንደ ህዝብ በይትኛውም መመዘኛ አጥፊና ወንጀለኛ ሊሆን አይችልም። ህዝብን እንደ ህዝብ ወንጀለኛ አድርጎ የሚፈርጅ ራሱ ወንጀለኛ ነው። ህዝቡ ያለው ምርጫ እንመርጣለን እንጂ ሰው እንፈጃለን፣ አገር እናቃጥላለን አላለም። ምርጫ ወንጀል ሊሆን ከቻለ በአለም ላይ ወንጀል ላይሆን የሚችል ነገር የለም።

ይህ ምርጫ የሚካሄደው ህወሓት ስልጣን ይዛ መቀጠል ስለፈለገች በዚህ ግርግር ወንበሯን ለማረጋገጥ ነው የሚል ወሬ ይናፈሳል። ህወሓት ከምድረገፅ እንድትጠፋ የሚመኘው ሁሉ ይህ ምርጫ ይዘገንነዋል። እንግዲህ ራስህን አስተዳድር፣ መሪዎችህን ራስህ ምረጥ ተብሎ የክልል ደረጃ የተሰጠው ህዝብ እንኳንና ህወሓትን ጅራታም ሰይጣንን እመርጣለሁ ቢል የሚከለክለው ማነው? በዚህ ምርጫ ሆነ በሌላ ምርጫ ህወሓት ማጆሪቲ ፓርቲ ሆና እንደምትቆይ ሳይታለም የተፈታ ነው። የትግራይ ህዝብ የሚያዋጣው ህወሓትና አዲሱን ትውልድ ያቀፉ ሌሎች ፓርቲዎች ተቀናጅተው ህወሓት የሚመራው ጥምር መንግስት እንዲመሰርቱ ነው። ልምድ ያለው ልምድ ለሌለው ግን ወኔና ፍላጎት ላለው እያካፈለ የትግራይ ህዝብ ለፈታኝ ሽግግር ሳይጋለጥ በሰላም ወደ ልማቱ ይቀጥላል።

 

ይህ የትግራይ ክልል ምርጫ ህጋዊ ነው ምክንያቱም ህገ መንግስቱ በሚያዘው መሰረት የተወሰነ ነው። የፌደሬሽን ምክር ቤት የወሰነው ምርጫ ማራዘምም ተቀባይነት አለው። ለምን ቢባል ከትግራይ ውጪ ያሉት ገዥ ፓርቲዎችና የየክልሉ የህዝብ ተወካዩች "እኛ በኮሮና ጊዜ ምርጫ አናካሂድም" ማለት መብታቸው ነው። እስካሁን ድረስ ከክልል ህዝቦች ሆነ ከክልል ገዢ ፓርቲዎች የመጣ የእንምረጥ ግፊት አልሰማንም። ሁለቱም ወገን ትክክለኛ ውሳኔ ወስነዋል:- አንዱ በህገ መንግስት አንዱ በተገቢ ስጋት። ስለዚህ ይህ የዴሞክራሲ ባህል ስር ሊሰድ መሆኑ ጥሩ ምልክት እንጂ የሚያበሳጭና ክፉ የሚያሳስብ አይደለም። የምርጫ ቦርድም ቢሆን ነገሩን በበጎ ጎኑ ተመልክቶ ማን አሸነፈ በሚል እልክ ከመጋባት "ትግራይ ውስጥ ለምርጫ አመቺ የሆነ የህዝብ ይሁንታ እንዳለ አረጋግጠናል፣ ስለዚህ ምክር ቤቱ ትግራይ ውስጥ ምርጫ እንዲካሄድ በልዩ ሁኔታ ድጋፍ እንድንሰጥ ይወሰንልን" ብሎ ማቅረብ ይህን ያህል እንደ ጥቃት የሚቆጠር ነው ወይ? ህወሓት ድል አደረግሁ ብላ መፎከሪያ ይሆናታል ተብሎ ተፈርቶ ከሆነም ህወሓት የምትፎክርበት ድል የተቸገረች ድርጅት አይደለችም። ይልቁንም በተቃራኒው ህወሓትን አለዝቦ በሃገር አንድነትና ደህንነት ላይ ተሳትፎ እንድታደርግ እንደመጋበዝ ትቆጥረዋለች ብየ አስባለሁ። ለዚህ ምርጫ ፈቃድ በመስጠትና ድጋፍ በማድረግ የሚገኘው ትርፍ ትግራይ ውስጥ ያለ እውቅና የሚካሄደው ምርጫ የሚያከትለው ከባድ አገራዊ ኪሳራ በቅንነት ቢነፃፀሩ መልካም ነው እላለሁ።

አመፀኛን "እንደማበረታታት" ተቆጥሮ የትግራይ ምርጫ ያለምርጫ ቦርድ እውቅና ከተካሄደ ማንም እውነተኛ ኢትዮጵያዊ የማይመኘው ግን መቆጣጠርና መቀልበስ የማይቻል ሂደት ሊለኮስ ይችላል። ምርጫው ህጋዊ አይደለም ከተባለ በዚህ ምርጫ የሚመሰረተው የትግራይ ክልል መንግስት ህገወጥ መንግስት ሆነ ማለት ነው። የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ካላወቀው ደግሞ ሌላ አገር ሆነ ማለት ነው። ከዛ በኋላ ያለው የቁልቁለት መንገድ ላይ ትግራይና ኢትዮጵያ እንዴት ይሆናሉ የሚለው ጥያቄ በትክክል የሚመልሰው የሰማዩ ጌታ ብቻ ነው። ነገር ማቅለል የሚቀናቸው ሰዎች የትግራይ መገንጠል ከጣሪያ ላይ አንድ ሳር እንደመምዘዝ አድርገው ይቆጥሩታል። እነዚህ አይነት ሰዎች የታደሉ ናቸው ከእውነታው አለም ርቀው ስለሚያስቡ የጨጓራና የልብ ድካም ችግር የለባቸውም። ለሰላም እኮ የማይከፈል መስዋእትነት የለም። ህወሓትና የትግራይ ህዝብ እየጠየቁ ያሉት ባለው ህገመንግስት መሰረት ነው። ምርጫው የተራዘመው በቀጥተኛ አንቀፅ ሳይሆን በህገ መንግስት ትርጉም ነው። እዚህ ላይ ማንም አልተሳሳተም። ሁለቱም ልክ ሲሆኑ ሁለቱንም መተግበራቸው ነው የሚመረጠው።

 

Back to Front Page