Back to Front Page

እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ

እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ

ርእሶም ኣባኩኖም 6-23-20

 

ኣቶ ኢሳያስ ኣፈወርቂ የኤርትራ ነፃ ኣውጪ (ሻዕቢያ) መርተው ሃገራቸውን ከኢትዮጵያ ገንጥለው የሃገር መሪ ተባሉ እንጂ መምራት የሚፈልጉት የኣፍሪካ ቀንድን ብሎም ኣፍሪካ ነበር፤ ኣሁንም ያልማሉ። በቅርቡ ወደ ስልጣን ማማ የመጡት ዶ/ር ኣብይም ልክ እንደ ኣጎታቸው ህልማቸው ኣፍሪካን መምራት ነው። ይህን የዶ/ር ኣብይ እና የኣቶ ኢሳያስ ኣፍሪካን የመምራት ህልም በተሎ ካልተገራ ብዙ ኣላስፈላጊ መስዋእትነት ሊያስከፍል ይችላል።

ኣቶ ኢሳያስ ከኣቶ መለስ ዜናዊ ጋር የነበራቸው ቁርሾ የተሰሚነት እሽቅድድም ነበር። ኣንድ ጊዜ ኣቶ መለስ ስለ ኢሳያስ ተጠይቀው ሲመልሱ ኢሳያስ ዓለም የሚያይበት ኣንግል ከማንኛውም ጤነኛ ሰው ይለያል። ኢሳያስ ዓለም ለሱ ብቻ እንድትሰማው ወይም እንድታገለግለው ይፈልጋል፤ ዓለም ደግሞ የራሷ ዛቢያ ኣላት፤ ኢሳይስን ኣታውቀውም። እሱ ስለ ዓለም ሳይጠየቅ ይዘላብዳል፤ በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ ይፈተፍታል። ስለዚህ ከዓለም ጋር እንደተጣላ ይኖራል ብሎ ነብር። ይህ ኣባባል ኣሁን ኣሁን እውነት መሆኑ በግልፅ ይታያል። ለምሳሌ ኣቶ ኢሳያስ ማንም ሳይጠራው ወይም ማንም ኢትዮጵያዊ ሳይጠብቀው (ከዶ/ር ኣብይ በስተቀር) ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ኣይካሄድም ብሎ ከዶ/ር ኣብይ በፊት መግለጫ ብጤ ሰጥቷል። ይህ ኣስተያየቱ ከኢትዮጵያውያን የገጠመው ተቃውሞ ቀላል ኣይደለም። ሁሉም ሰው ምርጫ ቢኖር የሚፈልግም የማይፈልግም እኩል ነው የተቃወሙት። ሁሉም ኢሳያስ በኢትዮጵያ ጉዳይ ምን ኣገባው?! ነበር ያሉት። ይህ ለኣቶ መለስ ኣባባል ሁነኛ ምስክር ነው። ኢሳያስ ኢትዮጵያን ማስተማርና የሚላትን የምታደርግ ፍጡር እንድትሆን ይመኛል፤ ኢትዮጵያ ግን ኢሳያስን ኣታውቀውም!!!

Videos From Around The World

ኣቶ ኢሳያስ እንደ ኣባቱ መሓመድ ጋዳፊ የኣፍሪካ ጀግና ኣባት መባልን እስኪያቃጀው ድረስ ይፈልጋል። ለዚህም ይረዳው ዘንድ ሁሌም የሚደሰኩሮው በኣፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረው የደርግ ጦር ብቻው (ስንት መስዋእትነት የከፈሉት ኤርትራውያንም ሳይጨምር) ማሽነፉ ማስተማርና በዚያው መከበር ይፈልጋል። በተጨማሪም የተለያዩ የኣፍሪካ ሃገራት የኣመራር ዘይቤ ስህተቶች ተደጋጋሚ ይተነትናል። ከኣፍሪካ ኣልፎም ስለኣውሮፓና ኤሜርካ እንዲሁም ኤዥያ ሃገራት በተለይ ጃፓን፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር ወዘተ የፖለቲካል ኢኮኖሚና ኣስተዳደር ስህቶትች ምንም ሳይገባው በረሃብና በስጋት ለሚኖረው የኤርትራ ህዝብ ይዘላብዳል፤ መንግስታትንም ይሳደባል። በዚህም ኣቶ መለስ ኣንድ ጋዜጠኛ ኣቶ ኢሳያስ ሁሉም ሃገራት ይሳደባል ለምን ታዲያ ሃያላን ሃገራት ኤሜርካንም ጨምሮ ዝም ይሉታል ብሎ ሲጠይቀው ኢሳያስ ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለ ወይም መኖሩንም ስለማያስቡ ይሆናል ነበር ያለው። ስለዚህ በማያገባው የሃገራት የውስጥ ጉዳይ እየገባ መዘባረቅ ደምስሩ ውስጥ የገባ በሽታ ነው።

ታዲያ ይህ የስሙኝ ኣክብሩኝ ባይ የኣቶ ኢሳያስ ኣመል ከኛው ተስፈኛ ጋር ይጣጣማል ወይ? ወዴትስ ሊወስደን ይችላል?

የምስራቅ ኣፍሪካ ብሎም የኣፍሪካን ንጉስ ለመሆን የቀን ህልም ያነገቡት ዶ/ር ኣብይ በተለያየ ጊዜ በተለይ በመጀሪያዎቹ የሹመት ጊዘያቸው ስለ ኣፍሪካ ኣንድነትና ትብብር እንዲሁም ኣዲሱ ኣመራር ስለ ብቃታቸው ተናግረው ኣይጠግቡም ነበር። ኣሸንፊያቸዋለሁ ብለው ለሚያስቡዋቸው (ህወሓትን) የሚናገሩ ኣስመስለው እኛ እንኳን ኢትዮጵያን ኣፍሪካም መርተን እናሳያቸዋለን እያሉ በተደጋጋሚ የኣፍሪካ ንጉስ የመሆን የቀን ህልማቸውን ሲነግሩን ከርመዋል። ታዲያ ሁለት ንጉሶች ለኣንድ የንግስና ዙፋን የሚያልሙ ከሆነ መጨረሻቸው ምን ይሆናል? ይህን ለማወቅ ወደ የህልም ንግስናቸው የሚወስዳቸው መንገድ (Methodology) መመልከት ለማይቀረው ጣጣ በቂ ምላሽ ይሰጣል።

የኣቶ ኢሳያስ የኣፍሪካ ንጉስነትመንገድ

ኣቶ ኢሳያስ ኣፍሪካን በኣባትነት እንድትቀበላቸው የመጀመሪያ እና ዋና የድል ማማ ስራየ ብለው የሚያስቡት በተደጋጋሚ በጦር ሜዳ ድባቕ የመታቻቸው እና ዓለም ከጎንዋ ኣሰልፋ በኢኮኖሚና በፖለቲካ ማዕቀቦች ከዓለም እንዲገለሉ በማድረግ ህልማቸውን ያጨለመችው ኢትዮጵያን ብትንትን ማድረግ ነው። ይህ ለእሳቸው በኣፍሪካና ዓለም ኣቀፍ ደረጃ ማንነቴን ማስመስከሪያና ኪሎየ ይጨምርልኛል ብለው የሚያስቡት የመጀመሪያና ዋንኛ ግባቸው ነው። ይህን ካሳካሁ በኃላ ኣልውሃ ምላሽ ይዤ ሌሎቸ ጎሬበት ሃገራት በጦር መሳሪያ ጭምር እያስፈራራሁ ከኣስመራ ትእዛዝ ማስተላለፍ እችላለሁ ብለው ያልማሉ።

ይህ ህልማቸው እውን ለማድረግ ኣቶ ኢሳያስ ምን ሲሰሩ ነበር?

በኤርትራ የነበሩት የተለያዩ ነፍጥ ያነገቡ የትግራይ፣ኦሮሞ፣ ዎላይታ፣ ኣፋር፣ ኣማራ፣ ሲዳማ፣ ሱማሌ ወዘተ የፖለቲካ ድርጅቶች በየብሄራቸው ብቻ እንዲደራጁ ነበር ያደረጉት። እነዚህ ድርጅቶቸ በተለያየ ጊዜ የጋራ መድረክ ኢንዲኖራቸውና ወያኔን ለመጣል የጋራ እቅድና የምክክር መድረክ እንዲያደርጉ ሲጠይቁ ቀጭን ማስጠንቀቂያ ነበር የሚሰጣቸው። ይህን ጥያቄ የሚያነሱ የኣማፂ ቡዱን ኣመራር ኣባላትም በተለያየ ጊዜና መንገድ እንዲወገዱ ኣድርገዋል። በተለይ ከኣማራና ትግራይ ቡዱኖች ይነሳ የነበረው የኣንድነት ግንባር የመፍጠር ጥያቄ በግድያና ቶርቸር ነበር የሚቋጨው። ለምሳሌ የደምሒት መሪ የነበረው ኮሎኔል ፍስሃ በፓርቲ ውስጥ ስራና የኣንድነት ግንባር የመመስረት ዓላማችን ለምን ጣልቃ ትገባላችሁ ብሎ ሲጠይቅ፤ በኮሌኔል ፍፁም ቀጥታ ትእዛዝ መገደሉ መጥቀስ ይቻላል። ለምን ቢባል የተበታተነ ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገባ እርስ በእርስ እየተባላ ኢትዮጵያን ብትንትንዋ ስለሚያወጣት ለኢሱ የኣፍርልካ ንጉስነት የህልማቸው ትኬት ይቆርጥልኛል ብለው ስለሚያስቡ ነበር። ኣሁንስ?

ምርጫ ማስቀረት እንደ ቀዳሚ የህልም መሰላል

ኣሁን ደግሞ የከረመው ኢትዮጵያን የመበታተን ህልማቸው ምርጫ ማስቀረት በተቀዳሚ መንገድ ኣስቀምጧል። ኢትዮጵያ ከለውጡ በኋላ በየጉራንጉሩና ከሃገር ውጭ የነበሩት የፖለቲካ ፓርቲዎችና የስልጣን ጥመኛ ግለሰዎች፤ በኣዲሱ ንጉስ ጋባዥነት በየተራ በቦሌ ቀይ ምንጣፍ እየተነጠፈላቸው በትርኢትና ደማቅ ኣቀባበል ወያኔ ይውደም ኣብይ ይንገስ እያሉ ኣዲስ ኣበባ ገብቷል። ከነዚህ ውስጥ እንደ ኦነግና ጃዋር የመሳሰሉት በጣም የዳበረ የፖለቲካ፣የጉሬላ፣ ኣመራር እና የቅስቀሳ ልምድ ያላቸው ይገኙበታል። እንደ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካ ኣማተሮችም ሳንረሳ። እነዚህ ወገኖች ብቸኛው ዓላማቸው/ግባቸው ስልጣን መያዝ ብቻ ነው

ጋባዡ ደግሞ ለስልጣናቸው በጣም ቀናኢ፤ ስልጣናቸው ከሚያጡ ማንኛውም መስዋእት መክፈል የሚፈልጉ ዶ/ር ኣብይ ሲሆኑ፤ተጋባዦቹ ደግሞ ሃገር ካልመራን ኢትዮጵያን እርም የሚሉ ተቃዋሚዎች እንዲሁም በኣሃዳዊት ኢትዮጵያ እና ብሄራቸው ገንጥለው መምራት ለሚፈልጉ የዘር መድሎ ቂም በቀለኞች ናቸው። ኣሁን በነዚህ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ፤ የኣቶ ኢሳያስ ህልም እውን ሊያደርግላው የቀራቸው ስራ ቢኖር ትርምሱ በፊሽካ ማስጀመር ብቻ ነው።

ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚፈልጉት የፖለቲካ ስልጣን ነው። ቢያንስ ቢያንስ ምርጫ 2012 ካልተራዘመ የፓርላማ መቀመጫ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ናቸው፤ እውነትም ነው። የዶ/ር ኣብይ እድርም በኣሁኑ ሰዓት ፍትሃዊ ምርጫ ከተካሄደ ማንንም ማሽነፍ ኣይችልም። ይህንን ሁሉም ወገኖች ጠንቅቀው ያውቁታል። ስለዚህ ግብግቡ ኣይለዋል፤ ሃገርም ሊያፈርስ ይችላል።

ኣብይን እንደ መንገድ

ኣቶ ኢሳያስ ዶ/ር ኣብይን ልክ እንደ ፍሪዳ የፈለግከው የሚደረግ እንስሳ ኣድርጎ ነው የሚያስበው። ዶ/ር ኣብይ የኢትዮጵያ መሪ የሆነው ህዝቡ ወያኔ ስለጠላ ብቻ ነው ብሎ ያስባል። ስለዚህ ዶ/ር ኣብይ ወያኔን ካጠፋልኝ፤ ለተቀረው ህልሜ ቁልቁለት ነው ብለው ያሰበው። ስለዚህ ብቸኛው መንገዴ እጄ ውስጥ የገባው ግልገል ኣንተን የሚያክል ስለሌለ ኣንተ ምራን ብየ ጥግ ድረስ ለጋ ልቡ ማስፈንጠዝ ነው ብለው ኣጦዙት። ለነደመቀም ጓደኝነቱ ተትረፍርፈዋል። ኣብይ ኢሳያስን የሚመራው ወያኔ እስከሚጠፋ ድረስ ነው። ኢሳያስ ወያኔ እስኪጠፋለት ድረስ በጣም የሚጠላው የኣኣዩ ተማሪ በነበረበት እንካን የሚጠየፈው ኣማርኛን ተናግረዋል።

ከዚህ ሁሉ በኃላ ገን ትክክለኛው ኢሳያስ ከመቅፅበት ይወለዳል፤ወደ ንግስናው ሲያመራ፤ ኣብይም ደብዛው ይጠፋል። እንኳን ኤርትራ መደባለቅ ይቅርና በትምክህተኛው ስምዋ መጥራት ዋጋ ያስከፍላል።ይህ ድብቁ የኢሳያስ የንግስና መንገድ ነው።

የዶ/ር ኣብይ መንገድ

ዶ/ር ኣብይ ስልጣን የሁሉም ነገሮች መፍቻ ነው ብለው ያምናሉ፤ ለስልጣናቸው ቀናኢ ናቸው። በስልጣን ላይ ለመቆየት ማንኛውም ነገር ለመክፈል ኣያመነቱም። የትንሹ ንጉስ ወደ ኣፍሪካ መንገድ

ኤርትራን እንደስጦታ

ንጉሱ በኢትዮጵያ ውስጥ ንግስናቸውን ዘለኣለማዊ ለማድረግ ዋነኛ መሰላላቸው ኤርትራን በስጦታ ለትምክህተኛው ቡዱን ማቅረብ ይፈልጋሉ። ይህ ገፀበረከት ከተሳካላቸው በምስራቅ ኣፍሪካ ለመንገስ እርከኑ እንደሚያጥሩላቸው ገምቷል። ይህ ግብ በቀላሉ ለማሳካት ኢሳያስን በመደለልና የሳቸው ውቃቤ ማስታመም ዋና ስራቸው ኣድርገዋል። ለዚህም ወያኔ እስከ ነችግሩ በሃገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ሲያሰራቸው የነበሩ ፕሮጀክቶች የክብር እንግዳና ሪቫን ቆራጭና ዋና መራቂ ኣድርጎታል።

ይህ ግባቸው ለማሳካት ብዙ ውስጠ ወይራ ስምምነቶች ለማድረግ ሞኩሯል። ከነዚህ ውስጥ የጋራ የባህር ሃይል ማቋቋም ዋናው ስምምነት ነበር። ዶ/ር ኣብይ ከኣጎታቸው ጋር ወያኔ ይውደም! ፍቅራችን ይለምልም ብለው ሻምፓኝ ኣርከፍክፈው ውስኪ ከተጎነጩ በኃላ በሞቅታ ዕቅዱ ለማስጀመር የደርግ መኮንን የኢትዮጵያና የኤርትራ ባህር ኃይል ኣዛዥ ብሎ ሾመ።ይህ ውሳኔ በኤርትራውያን ከፍተኛ ድንጋጤና ቁጣ ሲፈጥር፤ በትምክህተኛው ቡዱን ግን ዶ/ር ኣብይንተኣምረኛው ንጉስ ተባለ። በዚያ ሰሞን ሟቹ ዶ/ር ኣምባቸው የራያ ቆቦ ህዝብ ሰብስበው ለ27 ዓመታት የወሎ ኣውራጃ የነበረውን ኣሰብን ወያኔ ሽጦት ነበር፤ ኣሁን ወያኔን ካስወገድን በኃላ የወሎ ታሪካዊ የባህር በሩን ይረከባል ብለው በህዝቡ ፊት የተናገሩት ከማስረጃ በላይ ነው።ጥብቅ ሚስጥር ተብሎ ለህዝቡ የተነገረው የብልፅግና ፓርቲ ኣመራሮች ለኣቶ ኢሳያስ የደገሱለት ስለት ነው። ታዲያ የቆቦ ህዝብ ባህሩንና ወደቡስ ባልጠላን፤ከትግራይ ህዝብ ጋር ተዋጉልን ማለት ግን መቸም ኣይሆንም ብሎ እቅዳቸውን ኣኮላሸው። ስለዚህ ዶ/ር ኣብይ ወያኔን እንዲወገድ የሚፈለጉት ትምክህተኛው ቡዱን ለማስደሰት ካላቸው ህዝበኛ ውቃቤ ብቻ የሚነሳሳ ይሆን፤ ኣቶ ኢሳያስን ማጥመጃ ወጥመድ ኣድርገው ስላሰቡት ነው።

በዚህ ሰሙን እንኳን ሁለቱም መሪዎች (ዶ/ር ኣብይና ኣቶ ኢሳያስ) ስለኣፍሪካ ኣፍርሶ መስራት ሲያላዝኑ ተስተውለዋል። ኣቶ ኢሳያስ ስለ ቀንድ ኣፍሪካ ህዝብ ብዛት፤ የተፈጥሮ ሃብትና በብቃት የማስተዳደሩ ስራ በፍርሃትና በስጋት ለሚኖረው ህዝባቸው ሲያወሩ ከርመዋል። ዶ/ር ኣብይም ሶማሊያንና ሶማሊ ላንድን ለማደራደር ሽማግሌ ተብለው ሄደው፤ ሃገር ልሁን በትለው ክ/ሃገርና ታላቋ ሶማሊያ (የኛ ሶማሌዎች ጨምሮ) እመሰርታልውሁ በሚለው ፎርማጆ ፊት እንደነዚህ ዓይነት ችግሮች ለመፍታት ሁሉም ሃገራት ተዋህደው በኣንድ መንግስት ስር ቢትራዳደሩ ይሻላል። ብለው የሁለቱንም ተሸማጋይ ወገኖች ተፃራሪ ሃሳብ ኣምጥተው የዲፕሎማሲ ውርዴት ተከናንበው ተመለስዋል። ይህ በፎርማጆና በዶ/ር ኣብይ ህልም መካከል ያለ ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ ኣንድ በሉልኝ።

ሲጠቃለል የዶ/ር ኣብይና የኣቶ ኢሳያስ የህልም ዓለም ቀንድ ኣፍሪካን የመምራት ህልም በጣም ኣደገኛ ነው። ኣሁን በፍቅር ያበዱ የሚመስሉት የጋር ጠላት ወያኔ ስላለ እንጂ ሆዳቸው ቢገለጥ የተንኮል መዓት የታይ ነበር።ወያኔ ቢወገድ በቀጣዩ ቀን ወይ ዶ/ር ኣብይ ወይም ኣቶ ኢሳያስ መሞት ግዴታ ነው፤ ኣንደኛቸው ሌላውን ይውጣል። ይህ ትንቢት ኣይደለም ቀጥተኛ በዓይን የሚታይና የሚዳሰስ ሃቅ እንጂ።ይህም ሁለተኛው ከወያኔ በኃላ የሚፈነዳ ፈንጂ ነው።

እንደ እኔ ግምት ኢሳያስ የሚሞት ይመስለኛል። ለምን ቢባል ምእራባውያን ኢሳያስን ማስወገድ ስለሚፈልጉ በዚያች ወሳኝ ቀን ኣብይ የሲ ኣይ ኤ እና የሌሎች ወገኖች የእቅድ ድጋፍ ስለሚያገኝ ሚዛኑ ወደ ኣብይ ያደላል፤ ይሁንና ኢሳያስም በቅንፀላ የተካኑ እነ ፍፁም (ወዲ መቐለ) ይዞ በኣሸናፊነት ለመወጣት እድሉ ዝግ ኣይመስልም። ኤኒወይስ ቀድሞ ምላጩ የሳበ ያሽንፋል። ይህ የመጠፋፋት ደባ ካልሰራ፤ ምስራቅ ኣፍሪካ ወደለየለት የጦርነት ቀጠና ይወስዱታል። ኤርትራም ቀጥታ ወደ የኢህኣዴጉ ዘመን፣ ዘመነ ማዕቀብ ትመለሳለች።

ኣንዱ ኣንዱን ለማጥፋት በሚሯሯጥበት ወቅት የኣፍሪካ ቀንድ ይታመሳል። ይህ ሁኔታ ህዝቦቹ እንደ ኢራቅ፣ ሶሪያና የመን ለእልቂትና ለስደት ይዳርጋል። ኣከባቢውም የሽባሪዎች መፈለፈያና መፈንጫ ይሆናል። ስለዚህ የኢትዮጵያ ምሁራን ይህ መረን የለቀቀ የስልጣን ጥምና ህልም ሳያጠፋን ማርገብ የግድ ይላል። ኢሳያስ እንኳን ለኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና ኣብሮውት ለታገሉ ታጋዮችና ቤተሰቦቻቸውም ሰላም ኣልሰጠም። ኢሳያስ ኤርትራን እንደግል ንብረቱ እንጂ እንደ ሃገር ኣያስባትም። ህዝቡም ለሱ ስብእና በቂ ነው ብሎ ኣያስብም፤ ሁሌ ስለ ብዙ ሚሊዮን ህዝብ ነው የሚያወራው።ይህ ኣባዜው ለማርካት የኤርታ ህዝብ እንደ መሰላል መወጣጫ ወይም ለሱ ብቻ የተበረከተ ኣገልጋይ፤ ጎረቤት ሀገራት ለማተራመስ ሲያስብም የሚዋጋ የሰው ሃይልና የሎጂስቲች ኣቀባይ ባርያ ነው እየተጠቀመበት ያለው።

ታዲያ ይህንን የኣቶ ኢሳያስና የዶ/ር ኣብይ ውስጡ በደባ የተሞላ ሰዓቱ እስኪደርስ የምናየው ኣሸሼ ገዳሜ እንደ ኣባቶቻችን እባብ ለእባብ ይተያያል ካብ ለካብ የሚሉት ተረት ኣይመጥነውም?

ሁሉንም ድራማ ለማየት፤ ዕድሜና ሰላሙን ይስጠን

ለማንኛውም ኣስተያየታችሁ resomab07@gmail.com

 

 


Back to Front Page