Back to Front Page

የእውነት ሰለባዎች (Victims of Truth)

የእውነት ሰለባዎች (Victims of Truth)

Faato, 05/12/2020

ናይጀሪያዊቷ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኔካ (Nneka) የእውነት ሰለባ (Victim of Truth) የሚል ድንቅ ሙዚቃ አላት። አቀንቃኟ በዚህ ሙዚቃ የምታነሳሳውና የምትወቅሰው በወቅቱ በሃገርዋ የነበረውን ፈላጭ ቆራጭ ሙሰኛ ወታደራዊ መንግስት ለመውቀስና ውስጥ ምሬቷን ለመግለፅ የቻለችበት እንደሆነ ይታመናል። በቀጠልም በህዝብ ስም ለውጥ እናመጣለን ፍትህ እናነግሳለን ብለው ተስፋ ሰጥተው ነገር ግን ስልጣን ላይ ሲወጡ የባሱ ዘራፊዎች፣ ገዳዮች፣ ጨቋኞች እና በቂም በቀል የተተበተቡ ፍርደ ገምድል ሲሆኑ ከሰው ልብ የራቁ ልቡን የሰጣቸውን ህዝብ መልሰው የሚያደሙ መሆናቸውን በምሬት የምትገልፅበት ሙዚቃ ይመስላል። በሃገራችንም ይህንን የሚያረጋግጥ ተመሳሳይ በደል እየተመለከትን ነው።

Videos From Around The World

ሚያዝያ 30 በዋለው የአማራ ክልል ፍርድቤት ችሎት አቶ በረከት ስምኦንና የትግል ጓዳቸው አቶ ታደሰ ካሳን (ጥንቅሹ)የስድስትና የስምንት ዓመት እስራት እንደተወሰነባቸው ስሰማ እኔም እንደ ዘፋኝዋ ልቤ ደማ አመረረ። እነዚህ ሰዎች በሙስና የሚታሙ ሳይሆኑበድርቅናቸው፣ በታታሪነታቸው፣ ላመኑበት ዓላማ በፅናት በመታገላቸው የሚታወቁ እንደሆነ ብዙዎች ይመሰክሩላቸዋል። እንደሌሎቹ ሆዳም ባለስልጣናት በግላቸው ይሄ ነው የሚባል ሃብት ያልተገኘባቸው ናቸው። በአዲስ አበባና በየመጡበት ክልል ዋና ዋና ከተሞች መሬትወስደው የቸበቸቡ፣ ከነጋዴ ጋር ተመሳጥረው የሃገርን ሃብት የመዘበሩ፣ የሃገርን ምስጢር ለጠላት አሳልፈው ሰጥቷል ተብለው የሚጠረጠሩ ወዘተርፈ በስልጣን ላይ ሰልጣን ሲሰጣቸው እያየን ነው። ሰዎችን የገደሉና ያስገደሉ፣ መፈንቅለ መንግስት ያካሄዱ፣ ህዝብን ብሄር ለይተው የጨፈጨፉና ለመናገር የሚቀፍ ወንጀል የፈፀሙ (ከተለያዩ የአቃቤ ሕግ ክሶችና የፍርድ ቤት ብይኖች እንደሰማነው) በምህረት ሲለቀቁ ወይም ክሳቸው ሲቋረጥ ምነው የነበረከት ጉዳይ የተለየ ሆነ ብለን ብንጠይቅ መልሱ የታወቀ ነው። የታሰሩበትና የተንገላቱበት ምክንያት የግል ወይም የቡድን ቂምበቀል፣ የቆዬ የፖለቲካ ቁርሾ (ያውም የተሸናፊዎች)፣ የውጭ ሃይል ጫና እና የፖለቲካ የፍየል መባ (scapegoat) ከመሆን አይዘልም።

ክሳቸው በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ክልል የሚታይ በመሆኑ ጉዳያቸው በአዲስ አበባ ከተማ መታየት ሲቻልና ሲገባ ባህርዳር መውሰድ የተፈለገበት ምክንያት በግብዝና ደካማ የአማራ ክልል የዘመኑ ባለስልጣናትና ተጽእኖ ፈጣሪ አክቲቪስቶች ሆን ተብሎ በተቀየሰ ክፍት የቀድሞ አመራሮቻቸውን ለማንገላታት፣ በስሜት በሰከሩ ወጣቶች ለማዋረድ እንዲሁም የፈለጉትን ለማድረግ እንዲመቻቸው የተደረገ ወራዳ ሴራ ነው። ይህ የአሳሪዎቹ የሞራል ዝቅጠትና የስነልቦና በታችነት ያሳያል። ይህንን ጸያፍ ድርጊት ያከናወኑት ሰዎች ለመገመት አዳጋች አይሆንም። የተከሳሾቹ ጠበቃ ለቢቢሲ የዜና አውታር እንደተናገሩት በአግባቡ እንዳይከራከሩና ምስክር እንዳያቀርቡ ተደርጓል። በመጀመሪያዎቹ ወራት ችሎት ሲቀርቡ ሲደርስባቸው የነበረው ወከባ፣ ስድብ፣ ዛቻና እንግልት በወቅቱ በሚዲያ መዘገቡ ይታወሳል። ምንም እንኳ ስሜቱ እየበረደ ወደበኋላ ቀለል ማለቱ ቢታወቅም ድርጊቱ የወረደ ነው። የፌዴራሉ መንግስትና ባለስልጣናትም ለዚሁ አጸያፊ ድርጊት ተባባሪዎች ነበሩ። ምክንያቱም ማድረግ የነበረባቸውን ባለማድረጋቸው (by omission)። አንዳንዶቹም በቀጥታ ድጋፍ ወይም ሽፋን መስጠታቸው (by commission) ተጠያቂ ከመሆን አያመልጡም።

ፀሃፊው ከበረከትም ሆነከታደሰ ጋር ምንም ዓይነት ዝምድናም ይሁን ትውውቅ የለውም። ሆኖም ግን ከሚወዱዋቸውም ይሁን በፖለቲካ አካሄዳቸው ከሚቃወሙዋቸው ነገር ግን የግል ቁርሾ ከሌላቸው በርካታ ሰዎች በውይይት መልክ ሰፊ መረጃ ለማግኘት ጥረት አድርጓል። ከሞላ ጎደል ሁሉም ከሙስና ሩቅ መሆናቸውን ያስባሉ ወይም ያምናሉ። ቀሪዎቹ ጥቂቶች ደግሞ ከሙሰኞች ሰልፍ ቢቀመጡ እንኳ ከሰልፉ የመጨረሻዎቹ አከባቢ እንደሚሆኑ ይስማማሉ። ተሰማርተውበት የነበረውና ያስከሰሳቸው ስራ በባህሪው ንግድ እንደመሆኑ መጠን ስህተት አይሰሩም ብሎ መከራከር ተገቢ አይሆንም። ለምን ቢባል የሚሰራ ይሳሳታል። በንግድ ስራ ደግሞ እድሉ ሰፊ ነው። ዛሬ ያዋጣል ያሉት ነገ አክሳሪ ወይም የተገላቢጦሽ ሊሆን ይችላል። የጥረት ስራ ደግሞ ራሳቸው የፈጠሩትና ከአነስተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ላቀ ደረጃ ያሳደጉት እንደራሳቸው የሚሳሱለት እና ማድረግ ያለባቸውን አድርገው አድጎና ተሽሎ ለማየት መፈለጋቸው አይቀርም። ከሌሎቹ መሰል የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች የፈጠሯቸው የንግድ ተቋማት (ዲንሾ፣ ወንዶ፣ ትእምትና ሌሎችም)ተሽሎ ለመገኘት መጣራቸው የማይቀር ነው። ይህም ለስህተት ሊዳርጋቸው የሚችል ቢሆንም የስራ ላይ ስህተት እንጂ ከሌሎች ነጥሎ ሊያስቀጣቸው የሚችል ሊሆን ባልተገባ ነበር። እውነት እውነት እንነጋገር ከተባለ ትላልቆቹ የማይጠረቁ ሙሰኞች፣ ዘራፊዎችና አዘራፊዎች ያውም ህዝብን፣ መንግስትንና ግለሰቦችን በሚጎዳ ዘግናኝ መልኩ የፈፀሙ በርካታ ሆዳሞች ባሉበት ሃገር ይህንን የመሰለ ፍርደ ገምድል የፖለቲካ ሴራ መመልከት የእውነት ሰላባ ወይም Victim of Truth በእውን ማየት ነው።

አቶ በረከትና አቶ ታደሰየእውነት ሰላባ የሆኑበት ምክንያት አንዱ ሰዎቹ የበሬ ግንባር ሊባል በሚቻል ሁኔታ የብአዴንን ፖለቲካ (ልክ ይሁን ስህተት እዚህ ላይ መከራከር አያስፈልግም) አጥብቀው ይዘው ተቋሚዎቻቸውን አምርረው ስለሚታገሉ፣ ሙሰኞችን ያለምህረት ስለሚገመግሙ፣ መሃል ሰፋሪ ወላዋዮችን ስለሚነቅፉና በግልፅ (boldly) ስለሚናገሩ ብዙ ጥርስ ሊነከስባቸው ችሏል። በተዛነፈ አረዳድ ወይም በአውቆ አጥፊዎች አማራን ነፍጠኛ ብላችኋል በሚል ውሃ የማይቋጥር ክስ የሰፊው የአማራ ህዝብ ጠላት ተደርገው እንዲታዩና የስለት በግ ሆነው እንዲቀጡ መፈለጉም አይቀርም። ስለእውነት ከሆነ ግን የአማራ ገዥ መደብ ነፍጠኛ ብሎ መጥራት አቶ ታምራት ላይኔ (ጊዜ ተቀይሮ የጀግና አቀባበል የተደረገላቸው)፣ አቶ ደመቀ መኮንን እና ሌሎችም የብአዴን ሃላፊዎች ሲናገሩት የነበረ የወቅቱ የተለመደ የፖሊቲካ ቋንቋ ነው (ተገቢ ይሁን አይሁን እዚህ ላይ መከራከር አስፈላጊ አይሆንም)። የአቶ በረከትን መፅሃፍ (የኢትዮጵያ ትንሳኤ)በኢህአዴግ ውስጥ የተንሰራፋውን ሙስናና የፖለቲካ ንቅዘት በመታገል በኩል ስለነበራቸው ጥረት ብዙ ነገር የሚያሳይ ቢሆንም ለምስክርነት ማምጣቱ አሳማኝ ላይሆን ስለሚችል በቅርቡ በአቶ ብርሃነ ፅጋብ የተፃፈውን የኢህአዴግ የቁልቁለት መንገድ የሚለውን መፅሃፍ መመልከቱ ሰውየው በሙስናና በብልሹነት ላይ የነበራቸውን ፅኑ አቋምና ሲያደርጉ የነበረውን ትግል ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

በሌላ መልኩ ደግሞ ኢህአዴግን ሲቃወሙ የነበሩ በተለይ የዲያስፖራው ሃይል፣ የአማራው ልሂቃንና የኤርትራ መንግስት በተለይ በአቶ በረከት ላይ ጫፍ የወጣ ዘመቻ ሲያካሂዱ ስለነበረ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን እነዚህ እንደ አጋር የሚያያቸው አክራሪ ሃይሎች ለማስደሰት ወይም ከጎኑ ለማሰለፍ ወይም ለውጥ መደረጉን ለማረጋገጥ የተወሰደ የሰበብ አስባብ እርምጃ ታክሎበት እንደሚሆን ተንታኞችና ታዛቢዎች ይተቻሉ። ምክንያታቸው በብዙ መንገድ ሊለያ ቢችልም በበረከት ላይ ያላቸው የቂም በቀል ፍላጎታቸው ያው ተመሳሳይ ነው። በተለይ ህወሃት/ኢህአዲግን ከስልጣን ለማውረድ ድርጅቱ በፈፀማቸው ጥፋቶች ሰበብ ተደርገው መንግስት ለመገልበጥ የተሸረቡ የፖለቲካ ሴራና ፕሮፖጋንዳ ጭምር የውሸት ውንጀላና ክስ ሰለባ የሆነ የመስዋእት በግ ቢኖር በረከት ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የቀድሞ ተሸናፊ የኢሕአፓ ሰዎችም በረከትና ታደሰ ላይ የመረረ ቂም ስላላቸውና አሁን የቤተመንግስት ባለሟሎች በመሆናቸው የአባባሽነት ሚና ሊኖራቸው እንደሚችል ይገመታል። በጎራ የሚመደቡት ከውጭ ሃገር የተመለሱት ሰዎች እነማን እንደሆኑ ስለሚታወቅ መግለፁ አስፈላጊ አይደለም። በተለያየ ወቅት ከብአዴን የተባረሩና (አንዳንዶቹያለሃጢያታቸው ተገፍተውና ተበድለው እንደሚሆን ይታመናል) ቂም የቋጠሩም እነበረከትን ለማዋረድ ድርሻቸውን እንደሚወጡ እሙን ነው። ይህም አንዳንዶቹ የቀድሞ ምልምሎቻቸውና ያሁን አሳሪዎቻቸው ያለሃፍረት እነዚህን የቀድሞ አመራሮቻቸውን በሚዲያ ወጥተው ሲያንቋሽሹና ሲሳደቡ በትዝብት ሰምተናቸዋል። የሰው ልጅ በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያን (ሴቶች በቅርብ ታሪካችን በስልጣን ላይ ስላላየናቸው አይመለከታቸውም) ግን ማስተማሪያ ሳያጣ ከሌሎች የማይማረውና አሳሪው ታሳሪ፣ ታሳሪው አሳሪ፣ አሳዳጅ ተሳዳጅ፣ ተሳዳጅ አሳዳጅ እየሆነ በጊዜ እየተፈራረቁ አንዱ ካንዱ ሳይሻል እስከመቼ በድንቁርና የክብዮሽ አዙሪት ይኖራል? መልስ ያላገኘ የዘወትር ጥያቄ ነው።

በተለይ በረከት ከነበረበት ተጋላጭነት አንፃር በውጭ ሃይሎች የተደገፉ በሴራ የተሞሉ የጥላቻ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ ከመሆንም ሊያመልጥ አይችልም። በተለይ ደግሞ በሃገራችን ጉዳይ ላይ አድራጊና ፈጣሪ እየሆኑ የመጡት የኤርትራው አምባገነን ኢሳያስ አፈወርቂ ጎንደርና ባህርዳር ሲጎበኙ የሰጡት ልዩ ትእዛዝ ሊኖች እንደሚችልም ታሳቢ ይደረጋል። ኢሳያስ ከመለስ ዜናዊ ቀጥሎ የሚጠሉት የኢህአዴግ ሰው ቢኖር በረከት ቢባል ማጋነን አይሆንም።

የኢትዮጵያን የፖሊሲ ነፃነትና ሉዓላዊነት የማይጥማቸው እጅ ጠምዛዥ የውጭ ሃይሎች ግድ የለሽነት ወይም ምክር ሰጪነትም ሊኖርበት ይችላል። የአንድ ወቅት የምርጭ ታዛቢ የነበሩትና የኢትዮጵያ ዜግነት ሳይሰጣቸው የኢትዮጵያ መንግስት ተቀዋሚ እስከመሆን የደረሱት ነገር ግን ለሃገራቸው ምንም ያልሰሩ ከንቱ አውሮፓዊቷ አዛውንት ከለውጡ በኋላ ስለበረከት በግላጭ በሚዲያ የሰጡት የጥላቻ ምስክርነት ማስታወስ በቂ ነው። በተመሳሳይ መልኩ የኢሳያስ አፈወርቂ የፐይሮል ፈራሚዋ የአትላንቲክ ካውንስል ሴትዮ በስልጣን ላይ ላለው ገዥ ቡድንና አጋፋሪዎቹ የሰጠችው ምክር ልብ ይሏል።

በመጨረሻም በልዩ ሁኔታ የሚያስተዛዝበው ደግሞ በረከትና ታደሰማንነትን ከአጥንትና ጉልጥምት አተያይ ብቻ በሚያስብ ኋላቀር አስተሳሰብ በተጠናወተው ህዝብ በዘር ግንዳቸው ምክንያት የሚሟገትላቸው አቅምና ድምፅ ያለው ቡድን/ወገን/ብሄር የሌላቸው መሆኑ ነው። ከዚህ ቀደም ስሙን የማላስታውሰው ፀሃፊ ዓይጋ ፎረም ላይ በለጠፈው ፅሁፍ ብሄር አልባ በሚል ምፀታዊ ቋንቋ ገልፆታል። ይህትክክል ሆኖ ሳይሆን በተግባር እየተደረገ መሆኑን ስለምናስተውል ብቻ ነው። በበረከትና በታደሰ ደረጃ የነበረ ወይም ያለ የኦሮሞ፣ የትግራይ ወይም የአማራ ተወላጅ በዚህ መልኩ ቢታሰር ቢንገላታ ብዙ እጅግ ብዙ ጩኸት በሰማን ከፍተኛ ጫና በተደረገ ነበር። ቢሆን ቢሆን ከተለመደው ወጥተው በአጥንት የማይተሳሰሩትን ህዝብ በባህሉና በእሴቶቹ ውስጥ በማደጋቸው ማንነታቸውን ከዚሁ ማህበረሰብ ማቆራኘታቸው ምስጋና በተገባቸው ነበር።

በረከትና ታደሰ እንደ ሌሎቹ የኦህዴድና የብአዴን ጓዶቻቸው ባይሾሙ፣አምባሳደር ባይባሉ የጡረታ አበል ተቆርጦላቸው (ተቀራራቢ በሚመስል ምክንያት እን ወንድወሰን ከበደ ያሉ የጡረታ አበል ያላገኙ እንዳሉም ሳይዘነጋ) የሰሩትን ስህተት የሚታረምበትን መንገድ እያስተማሩ ቀሪ ዕድሜአቸውን በሰላም መኖር ይገባቸው ነበር። አቶ በረከት በጣም ተፈላጊ ከሚባሉት የዲፕሎማሲ ከተሞች አንዷ በሆነችው ብራስልስ በአምባሳዳርነት እንዲሾሙ ተጠይቀው በሃገራቸው ኢትዮጵያ ለመኖር መርጠው አለመቀበላቸው እዚህ ላይ ማስታወስ ተገቢ ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ የሚንገላቱት ቤተሰቦቻቸው ምንኛ ይሰማቸው ይሆን?በምንም መለኪያ በምንም ንጽጽር እንግልትና የቅጣት ፍርድ አይገባቸውም ነበር። ጉዳዩ ከአቅማቸው በላይ እንደሚሆን በመገመት ዳኞቹን ለመውቀስ አልሞክርም ፖለቲከኞቹንና ዓቃቤ ሕጎቹን ካልሆነ በቀር። ተገቢውን ተፅእኖ ለማድረግ ምንም ያላደረጉት ከመንግስት ስልጣን ውጭ ያሉ የቀድሞ የብአዴን አመራር ባልደረቦቻቸው ግን ሳልወቅስ አላልፍም። ይህንን በደል የፈጸሙትና ያስፈጸሙትም የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ተመልሶ ሳያገኛቸው እንደማይቀር ከታሪካችን እንማራለን። ታሪክ ራሱን የሚደግመው በማይማሩ፣ በማይሻሻሉ፣ ባለህበት ሂድ በሚረግጡ ህዝቦች ብቻ ነው። እንደ ሃገር ሳንበታተን ከዚህ አዙሪት የምንወጣበት ዘመን እንዲመጣ እመኛለሁ። በረከትና ታደሰም ከዚህ ሁሉጥቂት መልካም ሰዎች አይጠፉምና የበላይ ተመልካች በንፁህ ህሊና ተመልክቶ መፍትሄ እንደሚሰጣቸው ተስፋ አደርጋለሁ።

አንባቢዎች Victim of Truth ሙዚቃን እንድታጣጥሙ ተጋብዛችኋል።

ለሁላችን ምህረቱን ይስጠን!

ከኮቪድ 19 ይጠብቀን!!

Back to Front Page