Back to Front Page

ከመቐለ የተፃፈ ደብዳቤ- የመንገድ ዳሩ የስዕል ማዕድ

መቐለ የተፃፈ ደብዳቤ- የመንገድ ዳሩ የስዕል ማዕድ

 

በ-ጂሆን

ግንቦት 2012 ዓ.ም

 

ክብሮም ሁሌ እዚችው ነው፤ ግና- ልብ ያለው ሰው ያለ አይመስልም፡፡

 

ህዳር እንዴት ይበርዳል?

 

ግድ የለም መውጪያው ነው እያሉ ማረጋጋቱን ይዘውታል፡ እኔን፡፡ ለከተማቸው እንግዳ እንደሆንኩ ገብቷቸዋል፡፡ ጥምቀት ሲገባ የመጨረሻው ነው፡፡ እነዚህ በመቐለ ከተማ ወስጥ ለውስጥ እየተምዘገዘጉ ከሚፈልሱት የኮብልስቶን መንገዶች ግራና ቀኝ እንደአሸን ከሚፈሉት የቡና ዛኒጋባዎች ጋ በርጩሜ ስበው ኝነትን እሚያጣጥሙ፡ ወሬ እሚጋሩት ጎረምሶች ናቸው፡፡

 

እንግዲህ ጥምቀት ታለፈ ሳምንቱ፡፡

 

ቁሩ ግና ሁዋላ ቀርቶ፡ አጥንቶቼ ሥር ገብቶ ይጎነታትለኛል፡፡ ቁር - እዚሁ ንፋሳም መቐለ ውስጥ ሃቅ ነው፡፡ ከቻልከውና ከተመቸህ ገናን፡ እልፍ ስትል ደግሞ ጥምቀትን ጨማምረህ እዚሁ ከተማ መልካም ጊዜ ማሳለፍህ አይቀርም፡፡ አንድ ወር ብትጨምር ደግሞ የ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ወደ ታች አገር በግል ተነሣሽነት ትግርኛውን ወደአማርኛ ገልብጠው ነው መሰል ትህነግ ማለት ጀምረዋል፡፡ ከባለቤቱ ያወቀ ቡዳ ሳይሆን ይቀራል?) እና የህዝቡ የትጥቅ ትግል የተጀመረበት የየካቲት 11 ቀን ዝግጅት ትታደማለህ፡፡ ጣራ የነካ፡ ዕብድ ያለ፤ ደግሞ መሬት የቆነጠጠ ፌሽታ፡፡ ዘንድሮ 45ኛው መሆኑ ነው፡፡

 

ዘንድሮ ግን- በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት እንደሆነው ሁሉ- እንዲሁ ፌሽታ ብቻ አልነበረም፡፡ ያገሬው ሰው፤ አጅግ ተናዳፊ ሆነው በቀጠሉት አሁን አዲስ አበባ በነገሱት ላይ ቁጣና ተስፋ መቁረጥን አርግዟል፡፡ በዚህ የከተማይቱ ክፍል፡ በቀበሌ 16 የመንገድ ዳር የጀበና ቡና ቤቶች- አስቀድሞ ድምፅ አልባ አሁን የጩኸት ሠፈር ውስጥ- ዕለታዊ ቡናየን፡ የሠፈሩንና ያገሩን ንዴት እኩል እየማግኩ ነበር፡፡ ከመቐለ ሆቴሎች አንዱ በሆነውና ተሻግሮ ከሚገኘው ታሪካዊና ዕድሜ ጠገቡ አብርሃ ካስትል ጋ ማረፌ እነዚህን ጎረምሶች በየቀኑ በሚባል ደረጃ ለወሬ ማግኘት በጣም ቀላል ነበር፡፡ በመሃል አገሩ የተስፋ መቁረጣቸው ምክንያቱ አንድያውን የመዝገን አንዱ መንገድ ይኸው ነው፡፡

 

Videos From Around The World

ለነገሩ በ 1897 ዓ. ም. ተገነባ የሚባለው አብርሃ ካስትል ለአዲሰ አበባው ጣይቱ ሆቴል የመቐለ መልስ ሆኖ ከርሟል፡፡ ከዓፄዉ እስከ የወታደሩና የታጋዮቹ፡ መንግሥት ድረስ ብዙ እጆች ተቀያይረውበታል፡፡ እንደስማቸው የህወሓት ታጋዮች በ1980 ዓ.ም. ትግራይን ነፃ ካወጡዋት በሁዋላ መቐለን የመንግሥታቸው መቀመጫ አደረጉዋት፡፡ ወደ ደቡብ አቅጣጫ መዝ ከመጀመራቸው በፊትም በዚያን ጊዜ የደርጅቱ መሪ ከሆነ ሁለት ዓመት ያልሞላው መለስ ዜናዊ አሜሪካዊዉን ፖል ሄንዝ እና እስራኤላዊውን ሃጋይ አርሊኽ (በኢትዮጵያ ጉዳይ በርካታ ፅሁፎች ያቀረቡ ተመራማሪዎች) ወደ መቐለ እንዲመጡ እንደጋበዛቸው ይነገራል፡፡ ችግር የለም፤ ማረፊያ አንደሁ አብርሃ ካስትል አለን ብሎ፡፡ የትግሉ ወዳጆች ወደ ኻርቱም በረው ትግራይ ለመዝለቅ ረዥሙን ድንበር አቋራጭ ጉዞ በሌሊት ነበር የሚጉዋዙት፡፡ ከጄት ድብደባ ለማምለጥ፡፡

 

የተቆለፈበት አገር መቼም መዉጫ አያጣም፡፡

 

ከአብርሃ ካስትል ቁልቁል ስትወርድ መቐለ የአደባባይና የሃውልቶች እጥረት እንደሌለባት ልብ ትላለህ፡፡ በብዛት የተዋቀሩትም በፀረ-መኃል መንግሥት የ17 ዓመታት የትግል ዘመን የወደቁትን ሰማዕታት በሚዘክሩ ወይንም በጦርነቱ ዉጤት ዙሪያ ነው፡፡ በዚህ በጉብታ ላይ በተገነባ የሆቴሉ የመኪና መግቢያ መንገድ ማዶ የሚታየው የብዕር ሀውልት (ብየዋለሁ) አንዱ ነው ፡፡ ግን በዚህ አደባባይ ያለዉ ቅርፅ በቀላሉ ሚንጣዕ (ሚሣይል ነገር) ሊመስል ይችላል፡፡ በእርግጥም እንዲያ የሚገምቱ የመቐለ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

 

ግን ለምን? ይህ ያገሪቱ ክፍል የበርካታ ዘመን-ዘለል ጦርነቶች ዓውድማ ስለነበረ? መልሱ ምናልባት ከዚሁ አደባባይ ወረድ ብለን ከምናገኘው ሃዉልት ሊገኝ ይችል ይሆን?

 

(እንደ ልምድ ሆኖ?) ገበያ የሚካሄደው ማልዶ ነው፡፡ እንግዲህ የሓውዜን ገበያም ሮብ ነው እሚዉል፡፡ በቀን፡፡ ቢያንስ እዚህ ሠፈር የውድቅት ሌሊት፤ የማታ ገበያ የለም፡፡ በሚግ-23 ዕይታ ሥር ተሁኖም ግብይት አይካሄድም፡፡ በውድቅት ሌሊት መንቀሳቀስ እማይሆንላቸው ሚግ 23ቶች ግና በሰኔ 15/1980 ዓመተ ምህረቱ የሓውዜን የቀን ገበያ፤ በጠዋቱ በጠራራ ፀሃይ በሓዉዜን ሰማይ ላይ ደነሱ፡፡ አፍታም ሳይቆይ 2500 ንፁሃን፡ ሠላማዊ ዜጎች ወደ ሞት ተሸኙ፡፡ ስለዚህም፡ ይኸው ሃውልት ሆነ፡፡ አንዳንዴ ሳስበው ያገሩን ሰው እንደጠላት አገር ህዝብ መፈረጅ የተጀመረው ያኔ ሳይሆን አይቀርም፡፡

 

የሓውዜን ሃውልት ቅልብጭ ያለ የገበያለት ጥፋት፤ ግልብ ዕልቂት፤ የተራረፈችን የጤንነት የመጨረሻ ምልክት ሆኖ አረፈው፡፡ ከዚህ ዕልቂት መትረፍ ከሦስት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ባለቤቶቹን ጨፍጫፊዎቹን ማፋጠጥ ማለት ነበር፡፡ ተርፈው ያንን ዕድል ያገኙ ግን ብዙ አልመሰሉኝም፡፡

 

አብርሃ ካስትል አጥር ሥር- ከብዕር ሃውልቱ ጥቂት ሜትሮች አለፍ ብሎ- ክብሮም አተኩሮ ሥዕሎቹን ለአላፊ አግዳሚው ያደራጃል፡፡ ማንጠልጠያ የለም፡፡ በብዛት የእርሳስ ንድፎች፡ የተወሰኑ በአክሪሊክ የተሠሩ መሰለኝ፡፡ አብዛኞቹም የፊት ምስሎች ናቸው፡፡ በብዛት የታወቁ ትግራዎት የፊት ምስሎች፡፡ ስለሓውዜን ዕልቂት እንድም ሥዕል ባላይ ለምን ብዬ አልጠየኩትም፡፡ የድህረ ጦርነት ገፅታዎች የሚያጠቃልሉት የሥራዎቹን ሥብጥር ልብ ብዬ ስመለከተው ግን ጉዳዩን ቸል እንዳላለው ገብቶኛል፡፡ የሓውዜን ጭፍጨፋ በሞት/ቶች፤ ጥፋቶች መሃል ተቸክሎ የሚገኝና አንዳንዶች መቐለ ያሉቱ ወገኖቸ እንደነገሩኝ ደግሞ ያንዲት በኢትዮጵያ ምህዋር ስትነጉድ የራሷን ምንነት ያልሳተች፡ ይልቁንም ጨልፋ ያስቀረች ብሄር የሞራል ስብዕናና የትግራዋይ መንፈስ ሽቅብ መውጣት ያበሰረ ነው፡፡

ይህ ከፊታችን የሚባዝነው ጎረምሳ ቀበሌ 16 ያሉቱ የእኩዮቹን ተሥፋ መሰነቅና እና መቁረጥ እየደጎሰ ስለመሆኑ መጠራጠርም አያስፈልግ፡፡

 

አንድ ዕሁድ ጠዋት- በህዳር ወር መሆኑ ነው- ወደ አርባ የሚጠጉ የሥዕል ሥራዎቹን ጠጋ ብዬ ልመልከት በሚል ሂሳብ እርሱ-ጋ ጎራ ብያለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ሥዕሎች ብደንብ ከማዉቃቸው ፎቶዎች የተገለበጡ ናቸው፡፡ ክብሮም ግሩም ኮፒ ያደርጋል፡፡ ሥራዎቹን በካሽ ለመለወጥ ሠፊ ፈገግታውንና ስስ ጉጉቱን እየለገሰኝ ሰላም፡ ከመይ ሓደርካ? አለኝ፡፡ ጠዋት ነው ብያለሁ፡፡ እንደምን አደርክ ማለቱ ነዉ፡፡ ከአደባባዩ ማዶ እንዳሉት አብዛኞቹ ጎረምሶች፡ ክብሮም ምናልባት በሃያዎቹ ማለቂያ፡ ግፋ ቢል ሠላሳዎቹ መጀመሪያ ቢሆን ነው፡፡ ብዙዉን ጊዜ ከሥዕሎቹ አጠገብ ሁኖ የሚሞነጫጭርበት ደብተሩን እያገላበጠ ወይንም ዝም ብሎ ማዶ ማዶዉን እያየ ነው እምትደርስበት፡፡ ዛሬ ጠዋት አረንጉዋዴ ሹራቡን፡ ጥቁር ጅንሱንና ጥቁር ጫማውን አድርጎ ሥዕሎቹን እንደቀኑ ስሜት አተኩሮ እየደረደራቸው ነበር፡፡

 

አንዱ ጥግ ታላቁ አፍሪካዊ ውጊያ ቀያሽ (ስትራቴጂስት)፤ የተዋጣላቸው አዛዥና በኢትዮጵያ የውትድረና ማዕርግ መዝገበ ቃላት ቦታውን ከማግኝቱ በፊት የደረሱበት ጄኔራል አሉላ ይታዩኛል፡፡ ግና፡ እውነት አሉላ ማን ናቸው? የዓድዋ ጦርነትና ድል ማስታወስ ይቻላል? የየካቲት 23፡ የ 1888 ዓ. ምህረቱ? እንግዲያው የምኒሊክ ጦር ከቦታው ብቅ ከማለቱ ከሰዓታት በፊት ነው ጦርነቱ ያለቀለት ሲል አጥብቆ ይነግረኛል አንድ የታሪክ አዋቂ ወዳጄ፡፡ ደጋግሞ፡፡ ሁሌ ትግራዋይ የራሱን ታሪክ በመንገር ዙሪያ ሆነ ታሪክን በራሱ መንገድ ከመንገር ላይ ባለው ይሉኝታ ከምር እንዳዘነ ነው፡፡ ፈፅሞ እማይመች ነገር ነው ይለኛል ሌላዉ በኢትዮጵያ ነገረ-ታሪክ ሁሌ ቆሽቱ እንዳረረ መደበቅ እማይሆንለት ሰው፡፡ ይህ ታሪክ እንደወረደ መነገር አለበት፡፡ የታሪክ ተመራማሪው ወዳጄ ይህን ትልቅና አስቸጋሪ የዓድዋ ጦርነትን ጉዳይ ከቦታው የማስቀመጥ ጣጣ ተሸክሞ ከጊዜ ጋር እየተሯሯጠ ነው፡፡ ከማሃል አገር ያሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ደኞቼ የአሉላ፡ እግረ መንገደቸውም የትግራይ ባላባቶች የጣልያንን ጦር በመደፍጠጥ የነበራቸውን ወሳኝ ድርሻ ለመቀበል አብዝተው ሲቸገሩ አያለሁ፡፡ ይገባኛል፡፡ ይህ የውይይቱን ማዕከል ከሸዋ ወደ የትግራይ ተራሮች ነቅሎ መውሰድ ማለት ሊሆን ስለሚችል፡፡

 

ስለ አሉላ እሚያውቀው ነገር እንዳለ ክብሮምን ጠየቅኩት፡፡ በዚያ ወሳኝ ዉጊያ ወሳኝ ሠው እንደነበሩ ከታሪክ አዋቂው ወዳጄ ጋር ይስማማል፡፡ ከዚያ ወዲያ መሄድም አያስፈልግ፡፡ የመቐለው አውሮፕላን ማረፊያ በሳቸው መሰየሙ በቂ ምስክር ነው፡፡

 

በትግራይ ጀግኖችን የመዘከሩ ጉዳይ ዳር ያለውም አይመስልም፡፡ በምዕራብ ትግራይ በሽረ-እንዳሥላሰ ያለው የአውሮፕላን ማረፊያ በሌላ ጀግና- በሓየሎም አርአያ- መሰየሙ ራሱ ሌላ በቂ ምስክር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከል ጦርነቶች ንቁ ተማሪና ተመራማሪ የሆነውና አንቱታን የተጎናፀፈው ምጡቁ አንድርያስ እሸቴ (ከዓመታት በፊት አንተ በለኝ፤ ደግሞ ተወው ፕሮፌሰርነቱን ስላለኝ እንደፍላጎቱ ሆኜለታለሁ) እንደሚለው ከሆነ ሓየሎም ኢትዮጵያ ከነበሩዋት ታላላቅ የጦርነት መሃንዲሶች ሥም ካተረፉት በጣም ጥቂቶቹ አንዱ ነው፡፡ ጨምቄ እያልኩት ነው፡፡ አንድርያስ ይህን ያለው በ1988 ዓ.ም. የዓድዋ መቶኛ ዓመት በአዲሳባው መስቀል አደባባይ ሲዘከር ነው፡፡ አንድ ምንጩ ባልታወቀ ሃብት ምክንያት ፈረንካውን ግራ-ቀኝ በሚበትን ጎረምሳ እጅ በቅርብ ርቀት የጥይት ምት ከአንድርያስ ጋር እያለ ነው የተገደለው፡፡ ታሪክ ያጋጣሚዎች መገጣጠም ሁኖ የዓድዋው ድል በዓል ከመከበሩ ከአንድ ወር በፊት ነበር፡፡ የሓየሎም ምሥል ሥዕሎች በክብሮም ክምችት በብዛት ይገኛሉ፡፡

 

ከሥር ከሥሩ እየዳኸ የሚከታተለዉ ፎቶ አንሺ የማይመቸው የሚመስለው መለስ ዜናዊ አንድ ሦስት ምስሎቹን እዚሁ ክምችት ውስጥ አይቻለሁ፡፡ ፎቶዎቹን ማን እንዳነሳ አናውቅም- ቢያንስ እኔ አላውቅም፡፡ ግን አንዱ በጣም የታወቀ ፎቶው ወጣት ታጋይ እያለ ምናልባት የህወሓት ስብሳባ ላይ እየተፋለመ ሊሆን ይችላል፡፡ በትክክል ቼ ጎ-ቬራን ይመስላል፡፡ ክብሮም እንዴት ኮፒ አድርጎታል? ሌላኛው የመለስ ሥዕል በስካንዲኔቪያ አገሮች (ዴንማርክ?) አፍሪካን ወክሎ ለዓየር ንብረት ድርድር ተጉዞ ወይም ሩሲያ ሄዶ ሳለ ይሆን? ጥቁር ካፖርት ደርቦ፤ ኒውስ-ቦይ እሚሉት ቆብ አድርጎ ሣለ በሆነ ሰው የተነሣ ነው፡፡ ትግራይ፡ ወዲያ ወዲያ ማዶ ድረስ ሥሙ ጣራ የነካው መለስ ባጭር ጊዜ ውስጥ ታሞ የዛሬ ስምንት ዓመት መሞቱ ገና ግራ የገባው ነገር ሁኖ አስካሁን ድረስ መቁዋጫ ፍለጋው አልቆመም፡፡

 

ደንቡ ሆኖ የመሃል አገር መሃለኞች ከመለስ ጋር ፍቅር የላቸውም፡፡ አሃዳዉያን ይሉዋቸዋል በዚህ ዘመን፡፡ ማፈር እሚሉት ሁላ ከራቃቸው ቆይቷል መሰል በለውጥ ተብየው ማግሥት ቅድስት ሥላሴ ቤተስኪያን ያረፈው የመለስ አጥንት ተቆፍሮ፡ ተለቅሞ ወደ መንደሩ ወደ ትግራይ ይላክ ሲሉ ባደባባይ ወተወቱ፡፡ በተወሰኑት ተጨበጨበላቸውም፡፡ ለነርሱ መለስ አዲሳባ አይገባውም፤ ሠፈሩ እዚህ አይደለም ነው፡፡ እሚገርመው ግና ባንደበታቸው ኢትዮጵያዊነትን እንጂ ዞሮ ዞሮ መሳሳማቸው ላይቀር ጎጥ የሚሉት አንስተውት አያውቁም፡፡ ከዚሁ ባልተናነሰ ከዛው መንደር የማይጠፋው ነገር ግን የመለስ ያገሩ ልጅ የሆነው (ህወሓት ከመሰረቱቱ አንዱ) አረጋዊ በርሀ- ይቅርታ ይደረግልኝ- አፉን ከፍቷል፡፡ በህወሓት አናት ላይ መቆየቱ ባይሆንለት ከነፃይቱ የትግራይ ምድር የዛሬ ሠላሣ አምስት ዓመት አሰናብቱኝ ብሎ ወደ ሱዳን መጭ ያለው- እዛው በቀላሉ ማስቀረት እየተቻለ ይሁን ተብሎ የተለቀቀው አረጋዊ- በመለስ ህልፈት እጅግ እንደተደሰተ በዚያው የ2004 ክረምት ሰሞን አራ፡፡ እንደሰው መስማት እሚሰቀጥጥ ነበር፡፡ የዛሬ ሠላሳ ምናምን ዓመት የተረፈች ነብስ ምስጋና ማቅረብ ተስኗት ለከት የለሽ አንደበትዋን ይዛ መጭ ስትል እንደማለት፡፡ ሲበዛ ካናት ወያና ጌታቸው ረዳ ከፊት ለፊቱ ቆይቶ ይህ የሆላንድ ድሪቶ ዳይኖሰር ብሎ ለኤግዚቢት ባያቀርበው ኖሮ ከዘመኑ የተጣላ፡ ጥንትኑ የከሰመ እና የነበረውን የጨረሰ ከንቱ ስለመሆኑ ማን ያስታውሰን ኖሯል? አረጋዊ ሆላንድ ለብዙ ዓመታት የኖረ በዚያውም በህወሓት ወጣ-ገባ ፍቅር ዙሪያ ላይላዩን በሄደበት ፅኁፍ ዱክትርናውን ያገኘ ፍጡር ነው፡፡ በመኃሉ (ኋላ እንደተነገረን) የመንግሥቱ ምክትል በነበረዉ በፍስሃ ደስታ አማጭነት ህወሓትን ለማጥፋት ከደርግ ፈረንካ ፈልጎ ነበር፡፡ ከህልም የዘለለ አይመስለኝም፡፡ ዳግማይ ቅሌቱ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ዘንድሮ ጥግ በደረሰውና ከህወሓት ጋር ላለው ጠብ እንዲጠቅም አክንፈው ሲያመጡት ነው፡፡ እንግዲህ ክብሮም ጋር አንድም የአረጋዊ ሥዕል የለም፡፡ ለምን ብሎ መጠየቅም አያስፈልግ፡፡ ምኑ ይሸጣል? (አገር ቤት ከገባ በኋላ) የመጨረሻውን የትግራይ ጉዞውን ያጠናቀቀው ከወጣቶች ጋር በነበረው ፍጥጫና እንካ ሰላንቲያ ነው፡፡ የሚዘገንን ትዕይንት ሊሆን ጫፍ ነበር የደረሰው፡፡ በትግራይ ወሰን የለሽ ፍርኃትና ክህደትን አስመልክቶ አንዳች ያልተፃፈ ቋሚ ስምምነት ያለ ይመስላል፡፡

 

ከትግራይ ውጪ- ግና ፈፅሞ ባዕድ ያልሆኑ- በዚሁ በክብሮም ስብስብ ውስጥ የምታገኛቸው የኃይለሥላሴ እና የስመኘው በቀለ ምስሎች ናቸው፡፡ ለምን ይለሥላሴ? ማወቅ ፈልኩኝ፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ- የአፍሪካ አንድነት መሥራች፤ አስቀድመው የነበሩ በመሆናቸው አለኝ፡፡ የምለው የምጨምረው አልነበረኝም፡፡ ለሦስተኛ ጊዜ ስጎበኘው የንጉሡ ስዕል እንደተንጠለጠለ ነበር፡፡

 

ስመኘው ግን እዚህ ጀግና ነው፡፡ ሃዘን በዳሠሠው ፊቱ የርሱ ሥዕሎች በጣም ይሸጣሉ አለኝ፡፡ ክብሮም የስመኘውን ሥዕል የሚሠራው በራሱ መንገድ የመሥጠት ድርሻው ለመወጣት ነው፡፡ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አሰኪያጅ፡ ከፕሮጀክቱ መቸም የማይነጠል ስም እና የግድቡ ዕውንነት ቁዋሚ ምልክቱ የሆነው ስመኘው በቀለ ክብሮም ከሚንገበገብላቸው ውድ ኢትዮጵያውያን አንዱ ነው፡፡ ተገዶ ማንሳቱ ላይቀር አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ዓሊ ሁለት ወር አልሆነውም ቢሮው ገብቶ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሙሰኞች የሚመራ፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የተጀመረና በአስር አመትም የማያልቅ በሎ ቁሻሻ ሳጥን ውስጥ ሲጥለው፡፡ (ይህ በተባለ) ብዙም ሳይቆይ አንድ የ2010 ዓ.ም. የሃምሌ ጠዋት መስቀል አደባባይ ጥይት በጭንቅላቱ ገብቶበት መኪናው ውስጥ ተገኘ አሉን፡፡ ከምርመራ በሁዋላ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ (የያኔው) የፌዴራል ፖሊስ ኪሚሽነር ዘይኑ ጀማል ስመኘው ራሱን እንዳጠፋ ገለፀ፡፡ ዘይኑ ብዙም ሳይቆይ የሠላም ሚኒስቴር ዴኤታ ተበሎ ተሹሞ ሄደ፤ በቅርቡም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅጥረኛ ሆኖ ወደ ናይሮቢ ማቅናቱ ሰማሁ፡፡ ለአብዛኛው ሞቱ ወይንም ግድያው እስካሁን ድረስ ያልተፈታ እንቆቅልሽ ግና መቸም ቢሆን እማይሟሟ ትዝታ ነው፡፡

 

በአራት ኪሎ የቅርብ ትዕዛዝ የከንቲባው አፈር ገልባጮች መስቀል አደባባይን እያረሱት ነው፡፡ ባደባባዩ ድርሻ አለኝ የምትለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተስኪያን ከሆነ በኋላ ቅሬታዋን ብታቀርብም መልሱ ወዲያው በከንቲባው አጃቢነት ሠፈሩን ማስጎብኘት ሆነ፡፡ ህዝበ ኦርቶዶክስም ዝምታን መረጠ፡፡ ለምናልባቱ ከማሕበረ ቅዱሳን ዋናዎቹ አንዱ አራት ኪሎ ውስጥ መቸንከሩ ለቤተስክያኗ እጅ መስጠት ዋናው ምክንያት ይሆን? በየቦታው ሲኬድ እንደሚታየው የቀድሞ ያዲሳባ መልክ በጥብቅ ካለእረፍት እየተገረሰሰ ነው፡፡ የወንጀሉ ቦታ የመጨሻዎቹ ምልክቶችም በቅርቡ ሄያጅ መሆናቸው አይቀሬ ነው፡፡ ምናልባት ኋላ ያደባባይ መኖሩ አስፈላጊነት ቢታሰብበትም ስመኘው መኪናው ውስጥ ሞቶ የተገኘበት ቦታ እንደርሱ እስከወዲያኛው ለማሸለብ ጫፍ ደርሷል፡፡

 

አምና- የክረምቱ መሃል ላይ- የጠራራ ፀሃይ ግድያው ወደ ጭካኔ የተሞላበት የማታ የነብስ ማጥፋት ዘመቻ አመራ፡፡

 

መንደርደሪያ ልስጥ፤

 

ጄኔራል አደም መሃመድ በሃምሳዎቹ የሚገኝ፡ ደቃቃና ኮስመን ያለ: ካለምንም ልምድ ወይም ትምህርት በኢትዮጵያ የደህንነት መ/ቤት አናት ላይ የተቀመጠ መኮንን ነበር፡፡ ዓብይ ተሰይሞ የሰው የቴሌፎን ቀፎ ወደመበርበርና ከአዉሮፕላን ወንበር ተገናኝቶ ለመብረር የተዘጋጀን ሰላማዊ ሰው ከጉዞ ወደማፈናቀል ተሻግሮ የፍጥነት ቁልቁል ከመውረዱ አስቀድሞ ከሱ በፊት የነበረው ጌታቸው አሰፋ- ያላችሁት በሉት- ይህንን መ/ቤት በአህጉሪቱ አሉ ከሚባሉ ጥቂት ተመሳሳይ ተቋማት ባልተናነስ መልኩ ላይ አድርሶት ነበር፡፡ ሰኔ 14/2011 ዓ.ም. ያኔ ጠቅላይ ኤታ ማጆር የነበረው አንደበተ-ለስላሳ፤ የሥልጣን ሰገነት ያልተዛመደውና ለስራ ሲሰማራ ማስተዋልን ከጀግንነት በቅጡ የሚያገናኘው ጄኔራል ሰዓረ መኮነን ባንዱ ጠባቂው ተገደለ፡፡ በዚያች ምሽት ዓብይ አሕመድ እንዲህ ሲሆን እንደለመደው ቴሌቪዥን (የአማራ ቴሌቪዥን) ላይ ወጣና ግድያው በባህር ዳር የተሞከረዉ መፈንቅለ መንግሥት አካል ነው አለ፡፡ አቤት ፍጥነት! ሥራ አስፈፃሚው ልክ ስመኘው ላይ እንደወሰኑት ፈጣን፡ ያልተጣራና ጉዳዩ ራሱ እንዲገደል የተፈለገ ይመስል ነበር፡፡ ሣምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዓብይ ካለምንም ሃፍረት አደም መሐመድን ቀጣዩ ጠቅላይ ኤታ ማጆር አድርጎ ሠየመው፡፡ የሰዓረን ትልቅ ጫማ የሞምላቱን ጣጣ ለጊዜው እንተወውና ሹመቱ እዚህ መቐለ ያሉቱ እንደሚያምኑት ተከታታይ መረጃዎችን የማዳፈን ታላቅ ሴራ አካል ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ግድያውን ማን እንዳቀነባበረውና እንደመራው እንኳን በቅጡ አናውቅም፡፡ እንግዲህ ይህንን ጊዜ የማይሽረውና ዝንታለማዊው ምፀት ልብ በሉት- ምሥክር ሆኖ መቆም የነበረበት ወታደር ወዲያ ግድም እየሸሸ ነው፡፡ ሌላ የወንጀል ቦታ (ክራይም ሲን) ተጨማልቋል፡ አሻራውም ጠፍቷል፡፡

 

ምነው የሰዓረ ምሥል አላየሁም እዚህ ክምችትህ ውስጥ? አልኩት፡፡ ከርሞ በግድያው ልቡ እንደተሰበረ የሚያስታውቀው ከብሮም ሥዕሉን በሰቀልኩ ቁጥር ወዲያው ነው የሚሸጠው አለኝ፡፡ ለሠዓሊው ሰዓረ ፈረንካ ማተሚያ ቁስ አይደለም፤ ወደ ትግራይ የሰማእታትና ሰማእትነት ዝክር ቀጥ ብሎ እሚዘልቅ አንድ ግዙፍ ስብዕና እንጂ፡፡

 

በዚያች የሰኔ ምሽት ከሰዓረ ጋር በግፍ የተገደለው ለበርካታ ዓመታት የመከላከያ ሚኒስቴር የሎጂስቲክስ ሃላፊ ሆኖ የሰራው ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ ነበር፡፡ የዚህ ዛሬ 20 ዓመታት ገደማ በተካሄደው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ወሳኝ የሎጂሰተቲክስ መሃንዲስ የነበረው የገዛኢ ምሥል በዚህ በክብሮም ስብስቦች ውስጥ ማየት የማይጠበቅ አልነበረም፡፡

 

ሰዓረን አጥብቄ አውቀዋለሁ፤ ገዛኢንም እንዲሁ፡፡ የሞታቸውን ወሬ የሰማሁት ላይ ጋይንት ሆኜ ነው፡፡

 

በአንድ ምሽት ሁለት አንቱ የተባሉ ጄኔራሎች ተለዩን፡፡ እንደገና ጉዳዩና ገዳዩ ሳይለዩ ከረምን፡፡

 

ሽኝት ወግ ሁኖ፡ በኢትዮጵያ ቴለቪዥን ከሚሊየኔም አዳራሽ በቀጥታ በተላለፈው ዝግጅት ዋናውን ጨምሮ ሌሎች አጎንብሰው ሲሰናበቱዋቸው ይህች ኬሪያ ኢብራሂም እምትባል- ሰሞኑን በሕገ መንግሥት ትርጉም ሰበብ ሲያዋክቧት የፌደሬሽኑን ላይኛውና ትልቁን ቤት ጥላላቸው የሄደችው ዘለግ ያለች ብርታት- ተራዋ ደርሶ ግራ እጅዋን ወደላይ ሰድራ በሁለት ሳጥን የተሸከፉት ዶቹዋን ስትለያቸው ካሜራው በዛ የክንድዋ እጥፋትና ፊትዋ መሃል አሾልኮ የሁነኛ ባለሥልጣናቱ ፊቶች ፍንትው ብለው እንዲታዩ በማድረግ ቅፅበትን ዘለዓለም አድርጓታል፡፡ ያችን ሁነት የሚደመስስ ምንም ቃል፡ ምንም ኩሸት፡ ምንም ድፍረት ከቶውኑ ሊመጣ አይቻለውም፡፡

 

የሥዕል ስብስቦቹን መቃኘት ቀጠልኩ፡፡ በርካታ የትጥቅ ትግሉ አርበኞች፡ የመልክዓ ምድር ዓይነት፡ ታሪካዊ ግንቦች (የላሊበላው ቤተ-ጊዮርጊስና የአኽሱም ሃወልት ይታዩኛል)፡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ምልክቶች፡ ወዘተረፈ፡፡ በጥቂት ሥዕሎች በትግራዋይ ማጀት ውስጥ ሁሌ የሚያደርጉትን ሲያደርጉ የምናያቸው ሴቶችና እናቶች ደግሞ ለሠዓሊው እጅግ ቅርብ ይመስላሉ፡፡

 

ክብሮም በአንድ የመቐለ ባለፀጋ በተሠራው የባለ 70 ሜትሩ መሥቀል ከተቸነከረበትና ከተማይቱን ቁልቁል ከሚያየው የጮምዓ ጋራ ሥር ትንሽ ቤት ተከራይቶ እንጀራ ጋግራ ከምትሸጠው ሚስቱ ጋር አብሮ ኑሮውን የሚገፋ ወጣት ነው፡፡ (የ)ወጣት ቤተሰብ፡፡ ልጅ ገና (አልመጣም)፡፡

 

ግና ህፃናት በሥዕሎቹ አብዝተው ይታያሉ፡፡ እናት ልጅዋን አዝላ፤ በርካታ ሌሎች እናቶች እንዲሁ በተመሳሳይ ሥራ ተደምጠው፤ የሆነ/ች ልጅ የሆነ ነገር ሲያ/ታደርግ፤ እናት ልጇን ሹሩባ ስትሠራ፤ ወዘተርፈ ከሌሎች ሥመ ጥር ወይንም ከሚታወቁ ሰዎች ሥዕል ጋ ተዘበራርቀው ይታያሉ፡፡ ዓብይ አሕመድ ከዚህ ተራ.፡ ከዝርዝሩ የለም፡፡

 

ምነው? አልኩት:: አንዳንድ ጥያቄ አለ

 

ማንም አይወደውም፡፡ ስለዚህ፤ ምልክቱም የለ እዚህ፡፡

 

ክብሮም ባለፉት 30 ዓመታት አንደአሸን ከፈሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ከሚኖርበት ጉብታ ብዙ ከማይርቀው የግል የሥዕል ትምህርት ቤቶች አንዱ ጋ ነው የተማረዉ፡፡ በቅርቡ ወደ መዲናዋ የመመለስ ዓላማ የለውም፡፡

 

(በዚህ ዓመት) በጥቅምት ወር በዛሬማ በኩል ትግራይ ገብቼ ታቹን ከአለ-ውሃ ወዲህ በዋጃ እስክወጣ ድረስ ዓደርቃይ፡ ቡያ፡ ማይ ፀብሪ፡ እምባ ማድረ፡ ቢንቶ ተከዘ፡ ዓዲ ገብሩ፡ እንዳባጉና (ሰዓረን ልብ ይሎታል)፡ እንዳሥላሰ፡ በለስ፡ ሰለኽለኻ (በርከት ያሉቱ ያሁኑ ክፍተኛ መኮንኖች በምርኮነት ከዚህ ከተማ የተገኙ ሳይሆን አይቀርም)፡ ውቕሮ፡ አኽሱም፡ ራህያ፡ ብላይ፡ ማይቅነጣል፡ ወርቅ አምባ፡ ማይ ለሚን፡ ዓብይ ዓዲ፡ ኣግበ፡ ስለወይኒ፡ እንዳማርያም፡ ስረት፡ ማይጉዋ፡ ሃገረሰላም (የልእልቲ አበበ ማለፊያ ሜስ-ጠጅ የክልሉ ወገብ ላይ መሆናችንን ያስታውሰናል) ፊለኣሳ፡ ቱኩል፡ ሮማናት፡ መቐለ፡ ዓዲ ጉደም፡ ሕዋነ፡ ዓዲ መስኖ፡ ዓዲ ቀይሕ፡ መኾኒ፡ ሂጂራ፡ ዓዲ ሻቦ፡ ኩኩፍቶ፡ ቶዎ፡ አላማጣ፡ አሁንም ዋጃ ድረስ እግረ መንገዴን ያልነካካሁት ሠፈር የለም፡፡ በዚህ ሁላ መንገድና መንደር ምንም ባፈላልግ፡ ምንም ብዟዟር፡ አንድ የዓብይ የአደባባይ ፎቶ ወይንም ምሥል- ባይሆን ታክሲ ላይ የተለጠፈ ስንዝር ሰቲከር- ከቶ ማየትና መለየት አልተቻለኝም፡፡ ቢቸግር ፍለጋዬ የመሃል አገር ታርጋ ካላቸው መኪኖች ላይ ሆነ፡፡ (ወይ አልነበራቸውም ወይም) እዚህ ድንበር ሲገቡ ስቲከሩን ላገሩ ህዝብ ክብር ሲሉ በመላጥ ነፃነታቸውን ያዉጃሉ፤ ወይንም

 

እልፍ ሲሉ ቆቦ፡ ኣራዱዋ፡ ሮቢት፡ ጎብዬ እና ወልዲያ፤ ባንዱ ግድም ሳንቃ፡ ደቦት፡ ሰቀላ፡ ድልብ፡ እየላ፡ ዴንሳ፡ ኩል-መሥክ፡ ዛሃ፡ ገነተ-ማርያም፡ ላሊበላ ነው፡፡ ተረቱም ሌላ፡፡

 

በርካታ የኢትዮጵያ ከተሞች አሁን አሁን በፍጥነት እየደበዘዙ የመጡ የዓብይ የአደባባይ ምሥሎች ባለቤቶች ናቸው፡፡ ጃዋር መሓመድ የመንግሥት ፀጥታ ሃይሎች መኖሪያ ቤቴን እየከበቡት ነው ብሎ በአንድ የጥቅምት የውድቅት ሌሊት በፌስቡክ መዝገቡ ላይ ባወጀ በንጋቱ የኦሮምያ ወጣት እንደጉድ ወጥቶ አገሩን ሲለበልብ፡ ድርሳኔ ነው የሚለው መደመርን ሲያቃጥልና ዓመድ ሲያደርገው፡ ትግራይ ድሮስ መች ነበርኩና እንደማለት ፀጥ ብላለች፡፡ የምታቃጥለው መፅሃፍና የሚነድ ወረቀት ከየት ይምጣ?፡፡ አስቀድሞም ቢሆን ዛር ያረፈባቸው እስኪመስል ድረስ ሥራ ፈት የየክልሉ ባለሥልጣናት ባዘጋጁት የመደመር የሟሟቂያ ገፀ-በረከትና የጨረታ ድግስ ሲያብዱና ሲያጉዋሩ፤ ትግራይ ውስጥ ወፍ የለም፡፡ በዚህ ድግስ ማዘጋጀትና ድርሳኑን በማሻሻጥ፡ የድርሳኑ ጌታ እንደ ኪም-ኢል ሱንግ ድርሳን በብርቅርቅ ጨርቅና ወረቀት ተለብዶ የመጣውን ድርሳን እራሱ ባለድርሳኑ እንዲመርቀው ሲሆን፡ ድንገት መጥቶ የደሰኮረበት እሚመስለው ግና ካሜራ ፊት አበርክቶ የተለማመደውን ሸፍጣዊ ወሬ እንዲያቀርብ ሲደረግ ቀድማ የተገኘችው አዲሳባ ናት፡፡ ባዲሳባ የተጀመረውና ከትግራይ በስተቀር በሁሉም ክልሎች በጉልበት የተዳረሰውን መደመርን ማቃጠል ለሚፈልግ ሁላ እንደእንጨት ክምር ተዘጋጅቶ ይጠብቀው ነበር፡፡ የኦሮምያ ወጣትም እንዳለ ነው በእሣት የወጣበት፡፡

 

አንዳንዴ ይኼ ኢሬቻ እንደው ቶሎ ባልመጣ እላለሁ፡፡ የወጣቱ ቁጣ የመጨረሻው እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡

 

መፅሃፉ፡ መደመርን አይታችሁታል? ትግራይ ውስጥ በቆየሁባቸው ሣምንታት ለማውቀውና ለማላውቀው ሰው ሁሉ ደጋግሜ ያቀረብኩት ጥያቄ ነው፡፡ እንደው ትግራይ እንደሚሉትና እንደሚነገርለት የተነጠለ ጎራ አይሆንም ብዬ፡፡ ከስንቱ አንድ ሰው ብቻ አዎን፤ ታድያ ፈጠን ብሎ ግን አለ፡፡ የሓበሻ ንግግር ውስጥ ነገር ግን የሚለዉን ብቻ ፈልግ ያለኝ የዛሬ ስንት ዓመት ገደማ ያገኘሁት የዓፋርና ሶማሊ ቅልቅል ጁቡቲያዊ ትዝ አለኝ፡፡ ክብሮም በቴሌቪዥን እንዳየው ሹክ ሲለኝ ልብ አልኩት፡፡ ቴሌቪዥን ማለት ደግሞ በተጣራ ሥምምነት የትግራይ ቴሌቪዥን ወይንም ድምፂ ወያነ ናቸው፡፡ ሁለቱም በራሳቸው መንገድ የድርሳኑን ድግሥ ዘግበውታል፡፡ በነገራችን ላይ በአንድም ሬስቶራንት፡ ሆቴል ወይም የግል ቤት ከሁለቱም ውጭ የተከፈተ ቴሌቪዥን አላየሁም፡፡ እዚህ የመቐለ ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ፡ ይህ የሆነው ዓብይ የሚመራዉና በትግራይ ላይ ባነጣጠረው የተደራጀ የዉሸት እና ጥላቻ የሜዲያ ዘመቻና ጥቃት ምክንያት ነው፡፡ አንድ እዚህ የተዋወቅኩት ሰው ከደቡብ አቅጣጫ ይመጣሉ ካላቸው በርካታ ክልከላዎችን የተወሰኑትን እንደምክንያት ዘርዘር አድርጎ ነግሮኛል፡፡ የቴሌቪዥን ኩባንያዎች፡ በተለይም የመንግሥቱ አ.ቲ.ቪ፡ ታይቶ የማይታወቅ ከ 1.5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ምዕመናን የተገኙበት የአኽሱሙ ሕዳር (ማረያም) ፅዬን እንዳይተላለፍ አድርጓል፡፡ መቐለ የተካሄደውና በሚቀጥለው ምርጫ ለዓብይ አስተዳደር ከባድ ፈተና የተባለው ትልቅ የፌደራሊስት ኃይሎች ጥምረት ስብስባ እንዳይተላለፍ ተክልክሎአል፡፡ ይዘርዘር ከተባለ ማቆሚያ አይኖረውም፡፡ በመንግሥት እርጥባን የፋፉት አ.ቲ.ቪ.፡ ዋልታ እና ፋና ትግራይ ውስጥ ለሚደረገው ትልቅ ጉዳይ ሁሉ ጀርባቸውን ከመስጠትና ከዚህ የሚሄዱትን ዜናዎች ከመግደል ዉጭ ሌላ ሥራ የላቸውም አለኝ የተዋወቅኩት ወዳጄ፡፡

 

(መቼስ) ዜና መግደል የጨዋታው ሕግ ሊሆን ይችላል፤ ሆን ተብሎ በዜና ውሥጥ ያለ ሰው መግደል ግና ዳር የለሽ ክፋት ከመሆን አያመልጥም፡፡ የሆነውም ይኸው ነው፡፡

 

አንድ የታሕሳስ የመጀመሪያ ሳምንት ከሠዓት በኋላ የትግራይ ም/ፕረዚደንት ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል የመሞቱ ዜና በዋልታ (ኢንፎሜሽን) ድረ-ገፅ ተለጠፈ፡፡ ይህ ድርጅት የተሰየመበት ዋልታ በ20ዎቹ መጀመሪያ የዕድሜ ክልል የነበረ፡ ገና ህወሓት ዳዴ ማለት ሳይጀምር በዛ ምህረት አልባ የትግራይ ተራሮች የተሠዋ የራሱ የደብረፅዮን ጓድ የነበረው የዮውሃንስ ገብረመድህን (ከጌታቸው አሰፋ በፊት የደህንነት መሥሪያ ቤቱ ሃላፊ የክንፈ ገብረመድህን ታላቅ ወንድም) የትግል ሥም ነው፡፡ ዋልታ፡ ደብረፅዮን በሚመራው ድርጅት በህወሓት የተመሠረተ፡ ከለውጥ ተብየው በኋላ ገና ወደፊት- ምናልባትም በቅርቡ- በምንሰማው አሻጥር ምክንያት ድንገት በብልጥግና ይዞታ ሥር ወድቆ የተገኘ ነው፡፡ የሞት ዜናው እንግዲህ ከየትም ባይመጣ ምንጩን ፍለጋ ባንሄድ አይፈረድብንም፡፡ ዜናው በትግራይ ምድር ድንጋጤን ፈጠረ፡፡ ያም ሆኖ እንዲህ ተበሏል ዋልታ ላይ ብላ ዓይታ የነገረችኝን የአንድ ወዳጄ ፀኃፊ ክምንም አልቆጠርኳትም፡፡ ደግማ ስትነግረኝ ደግሜ ችላ አልኳት፡፡ የዕለቱ ዕለት ጠዋት በእግሬ በሰማዕታት ሃውልት በኩል ወደ ፕላኔት ሆቴል ስሄድ በወታደር የታጀበ ላንድ ከሩዘር ወደላይ ሲያልፍ አይቼ ሰውየው መሆኑን ስለነገሩኝና በጥቂት ሠዓታት ህይወት ያለጡሩምባ እንዲሁ ታልፋለች ብዬ ስላልገመትኩ ሊሆን ይችላል፡፡ ዜናው እንግዲህ ብዙ ሰው በተንቀሳቃሽ ስልኩ ፎቶ በማንሳት በወጉ እስኪቀባበለው ድረስ ቆየ፤ እዛው ዋልታ ድረገፅ ላይ ተለጥፎ፡፡ በዚያች ምሽት ደብረፅዮን ከቢሮው ሆኖ በህይወት እንዳለ የሚያሳይ ቪዲዬ በሁለቱም ጣቢያዎች ተለቀቀ፡፡ በሚቀጥለውም ቀን ፋብሪካ ሲጎበኝ የሚያሳይ ዜና አየን፡፡ መላው ትግራይ እፎይ-በህይወት አለ-ተመስገን ሲል ተደመጠ፡፡ እዚህ መቐለ ውስጥ ደብረፅዬን የጀግንነት ምልክቱ፤ አገር እየታመሰች ወዳልታወቀ አቅጣጫ በምትፈልስበት በዚሁ በአሁኑ ወቅት ችቦውን የተሸከመ ሰው ነው፡፡ ብዙ ሰው የርሱን ሥዕል ስለሚፈልግ ወዲያው ወዲያው ነው የምሥለው፤ ብዙ ነው የምሸጠው አለኝ ክብሮም ፈገግ ብሎ፡፡ አንድ የባጃጅ ሾፌር ደግሞ በሱ ምክንያት፡ ቀና ብለን መሄድ- መናገር ሁሉ ጀምረናል ሲል አውግቶኛል፡፡ የመናገር ነፃነት እንደማለት፡፡

 

ዋልታ ያንድ ግሩም ታጋይ ሥም እንዳልነበረ ትግራይ ውስጥ ቃር ቃር ማለት እንደጀመረ ሁዋላ ነግረዉኛል፡፡ የሰሞኑ በክልሉ ላይ ያነጣጠረ ሌላ የኩሸት ዶኩሜንተሪ ልብ ይሉዋል፡፡ ዶኩሜንታሪ እሚሉት የፕሮዳክሽን ዘር እዚህ አገር እስከወዲያኛው አሰናብተውታል (ልበል)?

 

አንዳንዴ ችክ የምልበት ጉዳይ ሳይኖር አልቀረም፡፡ አሁንም እዚህ ከተማ በቆየሁባቸው ጥቂት ሳምንታት ስለ ዓብይ ከመጠየቅ አልቦዘንኩም፡፡ ያው ተማሣሣይ (መልስ) ነው፡፡ ጭራሽ አንዱማ እውነት? እንደማለት በስላቅ፡፡ ሌላኛው እንዲያ እሚባል ሰው አናውቅም አለኝ፡፡ ንዴት ቢጤ ይታይበታል፡፡

 

ለተወሰኑ ትግራዎት ነጋዴዎች ግን ዓብይ እውነትም አለ፤ ሠፈር ውስጥ፡፡ እንደእባብ ከስር ለስር እየተሳበ እንደደረሰን ወሬ ከሆነ ወደ ሃምሳ የሚጠጉትን ጥሩልኝ ብሎ በህወሓት እንዴት እንደተካደ፤ እንዳልተግባባ፤ እንዳልተመቻቸ (የትኛው እንደሁ እግዜር ይለየው) ከገለፀላቸው፤ ከተነፈሰባቸው፤ ካደነቆራቸው (የቱ እንደሆነ እግዜር ይወቀው) በኋላ መቐለ ደረስ ሄደው እንዲያስታረቁት፤ እንዲሸመግሉ፤ እንዲያግባቡዋቸው (በምን ጉዳይ እንደሆነ እግዜር ይወቀው) አበክሮ አስታወቃቸው፤ አስጠነቀቃቸው፡፡ እንደወሬው ከሆነ ሰውየው (ዓብይ) ህወሓትን ደፍጥጦ ብልፅግና ብሎ በሰየመው (ፓርቲው) ሥር አለመጣሉ እጅጉኑ ተበሳጭቶ፤ ተምታቶበት፤ ተመሰቃቅሎበት ነበር፡፡ ዋናው መልዕከቱም ቢዝነሳችሁ ወይንም ክልላችሁ የሚል አጣብቂኝ ውስጥ የሚከት ነበር፡፡ ከህወሓቱ ከደብረፅዮን ጋር ከተሰበሰቡ በኋላ ነጋዴዎቹ ወደ አዲሳባ-አራት ኪሎ ሲመለሱ ክፉኛ የተበሳጨ ሰው ነበር የጠበቃቸው፡፡ አስቀድሞ ሰምቶ ነበር ይሆን? አንድ ሹክ እሚል መቸስ አይጠፋም፡፡

 

እንደተጠበቀውም (ሰዎቹን) ለማስደንበር ዘለፋውንና ማስፈራራቱን ተያያዘው፡፡ የክልሉን ኢኮኖሚ ማሽመድመድ፡ መብራትና ቴሌኩሙኒኬሽን መቁረጥ ወዘተርፈ እንደሚችል አቅራራ፡፡ ዋናው ነጥብ ለትግራይ መንግሰት የሚገባ በርካታ ፈንድ ቆርጠው አስቀርተዋል፡፡ ዛቻ ሆኖ አልቀረም፡ ሀቁ ይኸው ነው፡፡ አድርጎታል፡፡ ግና ይች ደህና ሁኔታ ላይ ያለችውን ብቸኛ (የኢትዮጵያ) ክልል ለመቆጣጠር እንዲመቻቸው ትግራይ/ህወሓትን በፖለቲካ አጣብቂኝ በመክተት (እና አንቀው በመያዝ) ላይ ከተደመጡት የውጭ ሃይሎች ዕይታ ዉጭ ነው ትላለች አንድ የዕርዳታ ሠራተኛ የሚለውን ስም የማይመቻት ነገር ግን በክልሉ ለበርካታ ዓመታት የዕርዳታ ሠራተኛ ሆና የሠራች የውጭ አገር ዜጋ፡፡ እንደፈለገው መሆን ያልቻለ ነጭናጫ ሀፃን ልጅ ነው የሚመስለው፡፡ ይህንን ነው ታዲያ የለውጥ መሪ የሚሉት? እውነትም ዛቻ ብቻ አልሆነም፡፡ የበጀት ቅነሳ እንደተደረገ ሰምተናል፡፡ የክልሉ ሌላው ምክትል አስተዳዳሪ ዶ/ር አብርሃም ተኸስተ በቅርቡ ለኖርዌጂያዊው ፕሮፌሰር ሸቲል ትሮንቮል የነገረውን ከወሰድን በእርግጥም የባሰው ከፊት እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡

 

(ማየት ለሚፈልግ) ምልክቶቹም በበቂ አሉ፡፡ ቀደም ብሎ- በጥቅምት- በትግራይ ጉብኝት ሲያደርግ የነበረው የአምባሳደሮች ቡድን ጉዞውን እዲያቋርጥ እንደተነገረው ሰማን፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ የሄዱበትን (ጉዳይ) አጠናቀቀው ተመለሱ፡፡ ታህሳስ ዉስጥ የቻይና ቡድን ወደ መቐለ ለመጓዝ ቦሌ ከአውሮፕላን ውስጥ ገብተው ለመነሳት ሲጠባበቁ እንዲወርዱ ተደረገ፡፡ ዶ/ር አብርሃም ጉዞዉን በተከለከሉ በማግስቱ አዲሳባ ድረስ መጥቶ ከነሱ ጋር ተፈራረመ፡፡ ያም ሆኖ ይህን አስቀያሚ የዲፕሎማሲ ጥፋት ማንም አደባባይ ወጥቶ አልኮነነም፤ ምንም አልተባለም፡፡ (ቢቸግር) አንድ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዴኤታ (በቅርቡ በተካሄደው በሪፈረንደም ለክልልነት ሙሉ ድምፅ በሰጠው ከሲዳማ ክልል የተገኘ) የደህንነት መ/ቤቱ ብቸኛ እርምጃ ሊሆን እንደሚችል በመጠቆም መ/ቤቱ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቀው ነገር እንደሌለው ነገር ግን ቡድኑ ትክክለኛው መንገድ ተከትሎ ወደመቐለ ለመሄድ አገር ቤት እንደገባ ለሜዲያ አረጋገጠ፡፡ ሰውየው ብዙም ሳይቆይ ከቦታው እንዲነሳ ተደረገ፡፡

 

መቼም ቢሆን የዓብይ ሥዕል እዚህ የክብሮም ክምችት ውስጥ ቦታ እንደማይኖረው ግልፅ እየሆነልኝ መጣ፡፡

 

ነገሩ እንደዚህ ነው፡፡

 

በሕገመንግሥቱ መሠረት ምርጫው መካሄድ አለበት ባለው በትግራይ ላይ ያነጣጠረው ሚያዚያ መጨረሻ በፌስቡክ ገፁ በለቀቀው ቪዲዮ ዓብይ ያ ከተሞከረ በክልሉ እርምጃ እንደሚወስድ ዛተ፡፡

 

እንደው ለመሆኑ እንዴት እዚህ ደረስን?

 

በህዳር 2011 ዓ.ም. ዓብይ የአንድ ሰሞን ፖሊተከኛዋ ብርቱካን ሚደቅሳን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ኃላፊ እንድትሆን ከአሜሪካ ያስጠራታል፡፡ ኃላፊ ሆና በተሾመች ማግሥት ሥራዋን ባለመሥራትዋ ከግራና ከቀኝ መነቀፍ ጀመረች፡፡ በእርግጥም ሥራ በጀመረች በጥቂት ወራት ጊዜ ውስጥ መስቀል አደባባይ (አሁን በቡልዶዘር ታርሶ ሲያበቃ ምን ሥም እንደሚሰጠው ለማወቅ የጓጓው ብዙ ነው) ጀርባ ያለውን የቀድሞ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ፅ/ቤት ህንፃ እድሳት ላይ ተጠመደች፡፡ ያው እድሳትና (የነጭ) ቀለም ቅብ ያገሩ ደንብ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ከዚያም የግንቦት 2012 ምርጫን በሦስት ወር አራዝማ በነሐሴ እንደሚደረግ አስታወቀች፡፡ በዚህ የሦስት አሠርት ዓመታት የምርጫ ታሪክ- በዛ ጦርነትና ችጋር ባጋጠመ ዘመን ሁላ ያልሆነው- ለመጀመሪያ ጊዜ መተላለፉ ነው፡፡ ተጮኸ፤ ለምን በክረምት፡ በዝናብ ወር ይደረጋል ተብሎ፡፡ ይህ እንግዲህ ቦርዱ ኮሮና ቫይረስ ከመከሰቱ በፊት እግሩን እየጎተተ ስለመኖሩ በቂ ምልክት፡ ከተመቸም መረጃ ነው፡፡ በመሃሉ በቦርዱ ውስጥ ሆኖ የሚሠራ አንድ የውጭ አገር ዜጋ በቫይረሱ መለከፉ ታወቀ፡፡ በፍጥነት ቦርዱ ሠራተኞቹ ሥራ እንዳይገቡ አስጠነቀቀ፤ ይህንኑንም በሜዲያ አስነገረ፡፡ መጋቢት አጋማሽ ገደማ የቦርዱ ኃላፊዎች ተሰብስበው ይኼ ጣጠኛ ቫይረስ እያለ ምርጫ ማካሄድ እንደማይቻል ወሰኑ፤ ይህንን ዉሳኔያቸውንም (ለአስተዳደሪያቸው) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በደብዳቤ አሰታወቁ፡፡ ምርጫም መቼ ሊደረግ እንደሚገባ ሳያመላክት ምክር ቤቱም ያንኑን አፀደቀ፡፡

 

ገና ከጅምሩ፤ ገና ኮሮና እሚሉት ጣጣ ሳይንጠላጠል ህወሓት ምርጫ በህገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ይደረግ እያለ ሲወተውት እንደነበር ልብ ይሏል፡፡

 

እንግዲህ ዓብይ በዛ የቪዲዮ ንግግሩ ምርጫው በትግራይ ከተሞከረ ያንኑን ለማስቆም በሚወስደው የኃይል እርምጃ እናቶች ሊያለቅሱ እንደሚችሉ አፈራራ፡፡ የዛን ዕለት ማታ ጌታቸው ረዳ በፌስቡክ ገፁ ከቶ እንዴት ቢዳፈር ነው ኢትዮጵያውያን ላይ ምርጫ ለማካሄድ ባቀደ አንድ ክልል የኃይል እርምጃ እወስዳለሁ ብሎ እሚደነፋ ሲል ወረደበት፡፡ ወዲያዉንም አዚያው ላይ ያንን የማድረግ ዓቅሙንም አደርገዋለሁ ያለውን ማድረግ ሰለመቻሉ ሌላ ጉዳይ ሆኖ በማለት ከወፍራም ጥያቄ ቀለበት ውስጥ ይከተዋል፡፡

 

በፍጥነት፤ በጣም በፍጥነት አዲሶቹ የቀበሌ 16 ጎረምሦች ጓደኞቼ ይህቸን ዛቻ ልብ ሲሏት ይታዩኛል፡፡

 

ይኸኔ ክብሮም በዓይምሮው አንዳንድ ሥዕሎች እየነደፈ መሆን አለበት፡፡

###

Back to Front Page