Back to Front Page

የሰው ነብስ ከፖለቲካ በላይ ነው፡፡

የሰው ነብስ ከፖለቲካ በላይ ነው፡፡

ማህተመ ፍቅረስላሴ 06-03-20

 

ከሰሞኑን የአለም የሰብአዊ መብት ተማጓቹ አልመስቲ ኢንተርናሽናል በኢትዮጵያ በኦሮሚያ እና በአማራ እየተፈፀመ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት አስመልክቱ ያወጣው ሪፖርት በተለያዩ ሚድያዎች የተሰጠው አስተያያት የእውነት ግርምትን ፈጥሮብኛል፡፡

የአሁኑ አመራር ሆነ የቀድመዎ አንድ ከሚያደርጋቸው ነገሮች መካከል በተለያዩ አለማቀፍ ሚድያዎች የሚወጡ ሪፖርቶች ማጣጣላቸው ነው፡፡ እርግጥ ነው ዛሬ በአገራችን መንግስት የፈጠረው ችግር መሰረት አድርጎ ከማስተካከል ይልቅ፣ ፖለቲካው ወደ ፖለቲካዊ ብሽሽቅ ተቀይሮ ቀጥሏል፡፡

ሚድያዎቻችም እውነታውን መርምሮ እና አገናዝቦ ከመዘገብ ይልቅ ሁልጊዜ እና ምንግዜም የፖለቲካ ፓርቲዎች መላስ መሆናቸውን በድጋሚ አስመስክረዋል፡፡

በአገራችን ሞቶ የሚለቀስለት ወይም የሰው ሞት የሚሆነው እንደ ገዥው ፓለቲካ ይሆንታ መሆን ከጀመረ ሰንብቷል፡፡የሰው ሞቱ ሰሚ መንግስት እና ፖለቲካ መሪ ካለው ሞቱ የሰው ሞት ሆኖለት ይዘመርለታል ብሎም ይጮሁለታል፡፡ በተቃራኒው የሰው ሞቱ የሚሰማ መንግስት ከሌለው ደግሞ የሰው ሞት መሆን ቀርቶ እንደ ዝንብ ሳይቆጠር በዛው የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡

የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ሚድያዎች የወጣው ሪፖርት ሆን ተብሎ የተቀነባበረ እና የግብፅ እጅ እንዳለበት ብሎም የወያኔ ሴራም አንድ ላይ የተጨመረበት እንደሆነ ዘግበዋል፡፡

Videos From Around The World

ከኢሳት ሚድያ መሳይ የተባለ "ጋዜጠኛ" የእውነት የፃፈው ትንታኔ ሲነበብ አልፎም ቢተረክ ቀልብ የሚይዝ ማራኪ ፍሰት ያለው ቢሆንም ሂዶ ሂዶ ግን ግብፅ እና ወያኔ ላይ ወድቋል፡፡

ይመስለኛል አይመስለኝም በሙሉ ቃላት ችግሮች በቀላሉ እየተተነተኑ አንድ አገር እና ፖለቲካ ላይ የሚለጠፍ መደምደሚያ እንደ ዋዛ ዝም ብለው የሚያልፉ አይደሉም፡፡

መሳይ ስለግብፅ ሲያወድስ የግብፅ ህዝብ በአባይ ጉዳይ ላይ ከፕሬዝደንታቸው ጎን ቁመው ድጋፋቸውን ይሰጣሉ፤ የሚገርመው ግብፅ 3 ጀነራሎች ሙተውባት እንኳን ኢትዮጵያን ለማንበርከክ የማትቆፍረው ጉድጓድ እንደለለ እና የግብፅ ህዝብ ለፕሬዝዳንቱ ሙሉ ድጋፍ እየሰጡ እንደሆነ ይተነትናል፡፡

ይቀጥል እና ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ከካይሮ መቀሌ አዲስ አበባ የተዘረጋው መስመር እያለ ይተነትን እና የችግሩ ምንጭ ወያኔ እና የኦሮሞ ፅንፈኛች በጋራ የፈጠሩት መሆኑን ይደመድማል፡፡

ይህ አዳጋ ጋዜጠና ባይ ነኝ ባዩ እሱ ቃላት እያሳመረ አማርኛ እየመረጠ የሚፅፈው ፁሁፍ ከላይ እንደገለፅኩት አርጎ እየፃፈ እንዴት ብሎ የትዮጵያ ህዝብ ስለ አባይ ከመንግስቱ ጎን ሆኖ አንድ ላይ ይቁም፡፡

ፓለቲካ ድርጅቶች ከፖለቲካ አካላት ጋር እያጋጨ ህዝብን ከህዝብ ለማቆራረጥ እየጣረ እንዴት ተብሎ ህዝቡ አንድ ይሆናል፡፡

ስጋት ሲገለፅ ህዝብን እየጠቀሱ ከተማን እያሞቁ ፖለቲካ ድርጅትን ተጠያቂ እያደረጉ ሳይሆን በአግባቡ ምርመራ አድርጎ ጥናትቱን በመረጃ አስደግፎ የእውነት የአገራችን ፖለቲካ ፓርቲዎች ግለሰቦች በድርጊቱ ተሳታፊ ከሆኑ እንኳን ቃላት ተመርጦለት የፖለቲካ ፓርቲውን እንጂ ተከታዩን ስሜት በማይነካ፤ ግለሰቡን እንጂ ተከታዩን በማይነካ የምርመራ ዘገባውን ማቅረብ ይቻለል፡፡

እዚህ በጋዜጠኛ ስም ጥላቻን እስከጥ እየሰበኩ ገንዘብ የሚያገኙ ሚድያውን ስያዙት ብቻ የመሰላቸውን እየፃፉ ህዝብ እንዴት ብሎ አንድ ይሁን፡፡

የትግራይ ሚድያዎች የቀረበውን የሰብአዊ መብት ጥሰት ሪፖርት እንደ አንድ ነፃ እና ገለልተኛ ሚድያ ሳይሆን የዘገቡት የድል መንፈስ የተሞላው ዘገባ ማለትም የአብይ መንግስትን ለማጠልሸት የተሰጠ የደስታ መግለጫ የሚመሰል ስነ ልቦና ተይዞ የተዘገበ ነበር ፡፡

ያው የመንግስት ልሳን ቃል አቀባይ የሆኑት ኦ ይቅርታ የመንግስት ቢሆኑ እማ ይሻል ነበር ፤ የብልፅግና ቃል አቀባይ የሆኑት ሚድያዎችም እንደ ተለመደው ሪፖርቱን የሚያጣጥል ዘገባዎች ሲሰሩ እና ሲዘግቡ ነው የተገኙት፡፡

እነዚህ ሚድያዎች ዕድሜ በጨመሩ ቁጥር ይለወጣሉ ተብለው ቢታሰቡም ላልተወሰነ አመታት እንደማይለወጡ ስላመንኩ እነሱን በተመለከተ ቡዙም መፃፍ አይጠበቅም፡፡

ሌላው ስዩም ተሸመ የተባለ ግለሰብ ምን እንደምለው ግራ ስለገባኝ ጋዜጠኛ ለማለት ይከብዳል፣ አክትቪትም እንዳንለው የሚያጠነጥነው ነገር ጭብጥ የሌላው ነገር ሆነብኝ ወይም ሙሁር እንዳልለው ንግግሩ እና ፁሁፍ ከአንድ ሙሁር የሚጠበቅ አይደለም በአጠቃላይ ግለሰቡ ብለው ይሻላል፤ እናም በፌስ ቡክ ገፁ የሚያሰራጨው ትንተና እና ንግግር የእውነት በጣም የወረደ ከእንደሱ አይነት የማይጠበቅ ነገር ነው እና ይገርመኛል፡፡

ስዩም ተሸመ ለምን ወደ ፖለቲካ መድረክ እንደመጣ ዝምብየ ሳስበው ግርም ይለኛል፡፡ እውነት ነው አዕመሮው የተሻለ ስለነበር የዩኒቨርሲቲ አስተማሪ ሆናል፡፡ በዛው ቢቀጥል እና ተማሪን እያስተማረ እንደተከበረ ቢቀጥል ይሻል ነበር፡፡

ስዩም የተሻለ ሃሳብ ከማስተላለፍ ይልቅ ወያኔ እና ጃዋር አሁን ደግሞ የአየር መንገዱ ጉሩፕ ላይ ማለትም ተወለደ ላይ ተንጠልጥሎ የጥላቻ ዘመቻ በማረገብ ኑሮውን የሚደጉም ግለሰብ ነው፡፡

እውነት ነው ግለሰቡ በድሮውም የኢህአደግ የሚሰጠው አስተያየት ተገቢ ስላልነበር ታስሮ እንደተፈታ እውነት ነው፡፡እኔ በግሌ አንድ መድረክ ላይ ታድሜ በአካል ለማየት ሞክሬ ነበር እናም አስታውሳለው ሰማያዊ ፓርቲ ለተከታታይ ቀናት በአምባሳደር ሲኒማ የውይይጥ መድረክ ላይ ስዩም የትንታኔ ፁሁፍ አቅራቢ ሆኖ አቅርቦ ነበር እና እንደጠበኩት ስላለገኘሁት እሱን የሚተች ፅሁፍ በአንድ የታወቀ ጋዜጣ ላይ ፅፋለው፡፡

አመራር ስለወጥ የተሻለ ስብዕና ይዞ ይመጣል ተብሎ ሲታሰብ ጭራሽ ከኢንተርኔት ከእየታ በሚገኝ ገንዘብ ስራየ አድርጎ ፓርቲ ከፓርቲ የሚያጣላ፣ ህዝብ ከህዝብ የሚያጣላ ነገር ሲናገር ሲፅፍ ይውላል፡፡

እውነት ነው የጥላቻ ፁሁፍ ከመልካም ነገር በላይ ሰውን ስለሚሰበው ሰው ይከታተለዋል፡፡ ያ ማለት ሰው ያድንቀዋል ማለት ግን አይደለም ፡፡ መቶ ሺህ በላይ በፊስ ቡክ የሚከተለህ ስላደነቀህ ሳይሆን አብዛህኛው የክፋት ወሬ ጊዜው በመሆኑ እሱን ለማየት እና ለመስማት ነው፡፡

ጭራሽ ድፍረቱ በዝቶ ህዝብ የማስታወሽ በሽታ አለበት ብሎ በድፍረት መፃፍ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ እውነት ነው መሪውን ደ/ር አብይን አክብሮ ሌላውን ማቋሸሽ መቻሉ እንደልቡ የማይባል ነገር እንዲዘባርቅ አድርጎታል፡፡

እኔ የሚያሳዝነኝ ሰውየው ወይም ግለሰቡ የሚያራምደው ነገር ትክክል እንዳልሆነ መንግስት እያወቀ እሱን ብቻ ስለሚደግፍ ችላ ቢለውም ሌሎች ትልልቅ ሚድያዎች ግን ለምን በቁም ነገር እንደሚጋብዙት ግራ ይገባኛል፡፡ ለነገሩ አሁን አሁን ከዋናው ሚድያ እየራቀ የመጣው ተቀባይነቱ እየቀነሰ ስለመጣ ነው ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡

ዝሮ ዝሮ ዛሬ መንግስትን ደግፎ ሌላውን ቢያንቋሽሽ መንግስት ዝም ማለት የለበትም፤ ምክንያቱም መንግስት እንኳን የህዝብ ቀርቶ የእያንዳንዱ ዜጋ መንግስት ስለሆነ ህግን ማስከበር አለበት፡፡

የሆነ ጊዜ ግን ይመጣል፤ ሁሉም የክፋት ነገር የሚዘግቡ ተሰሚነት እንደሚነሳችሁ፡፡

ዝሮዝሮ የስዩም ተሾመ እውነታውን ከመናገር ይልቅ ድርጅቱ በጃዋር ምክንያት የተጎዱን ሰዎች ለምን አልዘገበም የሚል ትችት ነበር የፃፈው፡፡

ሁል ጊዜ የተሳሳተውን እያወጡ ከመኖር ያ አልፋል አሁን ግን የተባለው ነገር እውነት ከሆነ መርምሮ ተገቢው እርምጃ መንግስት እንዲወስድ የበኩልህን ሚና መጫዎት ሲገባው የሚደግፈውን ላለማስቀየም በራሱ ነብስ ላይ ያላግጣል፡፡

አንድ ያላግባብ የሞተ ነብስ ካለ ከሌላ ያላግባብ የጠፋ ነብስ ጋር ለፍክክር መቅረብ የለበትም፡ ምክንያቱም በሰው ነብስ ማንም መጫወት የለበትም፡፡

ለዚህም ነው የሰው ነብስ ከፖለቲካ በላይ መሆን ያለበት፡፡

በአጠቃላይ ጥላቸው አሁን መጥፋት አለበት፡፡

ብልፅግና በተለይም ደ/ር አብይ አህመድ የሚከተሉት የአገዛዝ ሂደት መለስ ብለው መመልከት ያለበት ጊዜ አሁን ነው፡፡

ከምንግዚው በላይ በውስጥ ከፓለቲካ ፓርቲዎች በውጭ ከግብፅ አሁን ደግሞ ከኮረና ጋር ከፍተኛ የሆነ ችግር እየወደቀን በመጣንበት ሰዓት አብይ በአቅሙ ከጥላቻ የፀዳች አገር መምራት እንዳለበት ይሰማኛል፡፡

አብይ ከስልጣን በፊት እና ስልጣን በያዘ ጢቂት ወራት በፊት ጥበበኛ የነበረ ነገሮችን በብልሃት ማለፍ የሚችል ድንቅ ሰው እንደነበር ከአንድ አንድ ድርጊቶቹ ለማወቅ ችያለው፡፡

በሂደት አብይ ጎራ መለየት እና ራሱን ማስቀጠል ጀመረ፡፡ ለዚች አገር ጣላት በውሰስጥህ አስቀምጦ ሌላን ጠላት አሸንፋለው ማለት ዘበት ነው፡፡

ስለዚህ የውስጥ ጠላት ተብሎ የታሰበውን ህወሃትን በፍቅር አንበርክክ፡፡ እርቅ በመካከላችሁ አውርድ ያጠፋህውን ነገር በይፋ ይቅርታ ጠይቅ ወያኔም እንዲሁ በድጋሚ ይቅርታ መጠየቅ ካለባት ትጠይቅ፡፡

መንግስታዊ ግንኙነት ይቀጥል ፤ ጥላቻውን አሁንም ስራየ ብለው የሚሰሩ እንደ እነ ስዩም ተሸመ ያለ ፣ ኢሳት ብሎም በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ ያሉ አመራሮች የትግራይ ብልፅግና ፓርቲ አመራሮችም ጨምሮ የሚጎዙበት ስነ ልቦና ከጥላቻ ወደ ፍቅር እንደለወጥ አድርግ፡፡

ፍቅርን በመስበክ ይቅርታ በማድረግ የጥላቻ ንግግሮች በተቻለ መጠን በማጥፋት ተፎካካሪ እና አማራጭ ሆኖ መቀጠል ይቻላል፡፡

/ር አብይ እውነት በጥላቻ ዝርዝር ውስጥ የተካተቱ ድርጅቶች ተፈትሸው ወደ ሰላም እና ፍቅር መመለስ አለበት፡፡

ምነው ያኔ እንደተመረጥክ ትግራይ ምድር ስትረግጥ የተደረገልህ መስተንግዶ ተረሳ እንዴ ፤ ለምን አሁን እንዲህ ሆነ ፤

ወደ ዋናው ሀሳቤ ስመለስ የሰው ነብስ ከሪፖርት በዘለለ የእውነት መከበር አለበት፡፡ እንደ ኮረና ያሉ ከባድ ወረርሽን ከመቶ ሺህ በላይ የአሜሪካ ህዝብ ሲገድል ሰዉ ኮረናን አልተቃወመም ምክንያቱም ኮረና በሽታ ነው ሰው አይደለም፡፡አንድ ጥቁር አሜሪካዊ ነብስ በፖሊስ ሲገደል ግን አሜሪካ እንዴት እያሳለፈች እንደሆነ አይተናል፡፡

የኛም ዜጋ ሰው ነው፤ እንደ ሰው ነብሱን ከማክበር ይልቅ ከፊቱ የፖለቲካ ሽፋን እየሰጠነው የምንቀጥል ከሆነ ከኮረና በላይ ኢትዮጵያን ሲኦል እንደሚያደርግ አልጠራጠርም፡፡

ሰላሙን እና ጤናውን ፈጣሪ ይሰጠን

ጠቢባን አገራችንን ይምራት

ከእኛ የሚጠበቀውን ጥንቃቂ እናድርግ፡፡

ውድ አንባቢያን የተፃፈው መልዕክት ከቅንነት እና ከመልካም የመነጨ ብቻ መሆኑን አስገንዝባለሁ፡፡

 

 

 

 

Back to Front Page