Back to Front Page

ሲኖር ግብፃዊ፤ ሲሞት ኢትዮጵያ

ሲኖር ግብፃዊ፤ ሲሞት ኢትዮጵያ

(ዳንሾ ሄሮን 21/06/2012 ዓ/ም)

አዲሱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በሚያሳፍር ሁኔታ እየተጣሰ ይገኛል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሪያችን የሀገራችንን ሉዓላዊነት በማያናጋ  መልኩ ውስጣዊ የኢኮኖሚ፣ የሰላምና መረጋጋት፣ እና አጠቃላይ የፖለቲካ ሁኔታችን ለማስተካከል ጥረት ከማድረግ ይልቅ፤ የተለያዩ የውጭ ኃይሎ በሀገራችን ላይ ያላቸውን ፍላጎት ለማሳካት ለሚያደርጉት ጥረት ለመደገፍና ተግባር ላይ ለማዋል የተጠመዱ ግለ ሰብ ሆነዋል። ይህ በግላጭ ሲገለፅ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገራቸውን ለመሽጥና ለውጭ ኃይሎች አሳልፈው ለመስጠት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኝ ዘመናዊ መሪ ለመሆን በቅተዋል። በነዚህ የውጪ ኃይሎች እንደመሸሟቸው መጠን የተልዕካቸው አንኳሩ ጉዳይ ይህ ስለመሆኑ ፤ ዛሬ ኢትዮጵያዊያን በመላ ልንረዳው የሚገባና ሌላው የፖለቲካ አቋም ልዩነታችን እንደተጠበቅ ሆኖ በዚህ ጉዳይ ግን ተመሳሳይ አቋም ልንይዝበት የሚገባ  ተጨባጭ ሐቅ ነው። የጠቅላይ ሚኒትሩ ሹመት ዋነኛ ማጠንጥኛም እዚህ ላይ መሆኑ ለአፍታም ልንዘነጋው የማይገባ ጉዳይ ነው።

በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ ከአባይ ግድብ በተያያዘ ሉዓላዊነትዋ የሚፈታተን ከባድ ችግር ተደቅኖባታል። ጠ/ሚ ዓቢይ በሰጡት አቅጣጫ መሠረት ልትወጣው በማትችል አዘቅት ተዘፍቃ ትገኛለች። በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ እንዳሉት ሁሉ በጠ/ሚ ቡድን ምክንያት የውስጥ አበሳዋ ማስወገድ የተሳናት ሀገር፤ በራስዋ አቅምና ሃብት እንዲሁም የህዝቡ ከፍተኛ ተሳትፎ ተጨምሮበት የተገነባው የህዳሴ ግድም ለባዕድ አሳልፎ በመስጠትና ባለመስጠት ላይ የተመሠረተ ከፍተኛ  ትንቅንቅ ውስጥ ከቷታል። የጠ/ሚሩ ቡድንም በሁለት አማራጮች መሃል ቆሞ ይገኛል። የመጀመርያው አማራጭ የህዝቡን ጥያቄና ፍላጎት ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ መወሰን ሲሆን ፤ ሁለተኛው አማራጭ ቀጣሪዎቹን ማስደሰት ነው። ህዝቡን ፍላጎትና ውሳኔ አክበሮ ቀጣሪዎቹን የሚያሳዝንበት አማራጭ ይከተላል ብሎ መገመት ግን የዋህነት ስለመሆኑ ግልፅ ነው።  የጠ/ሚሩ ቡድን ከቀጣሪዎቹ እጅ ማምለጥ የሚችልበት አንድም ቀዳዳ የለም ባይባልም ፤ ሁለመናው ለባዕድ የሸጠ የልፍስፍሶች ስብስብና ምናልባትም ኢትዮጵያ በታሪክዋ ያጋጠማት ስለ ጥቅምና  ስልጣን እንጂ ስለ ሀገር ሉዓላዊነት ግድ የሌለው የመንግስት በትረ ስልጣን የተቆጣጠረ ቡድን በመሆኑ ምክንያት ችግሩ ውስብስብ እንደሚያደርገው ሳይታለም የተፈታ ነው።

Videos From Around The World

የዚህ ቡድን ሀገር ሻጭነትና ራሱን ሙሉ ለሙሉ ለባዕድ ቅጥረኛ ስለመሆኑ ከህዳሴው ግድብ በተየያዘ ጉዳይ በመመልከት ብቻ እርግጠኛ መሆን ይቻላል። እንደ አብነት የሚከተሉትን ጉዳዮች እንመርምር።

1.   የአባይ ተፋሰስ ሀገሮች የትብብር ማዕቀፍ መሠረት በማድረግ በመርህ ደረጃ የኢትዮጵያን ጥቅም ፍትሃዊ በሆነ  መንገድ ማረጋገጥና ሉዓላዊነትዋ ማስከበር እየተቻለ ለምን ወደ  አሜሪካና IMF መሄድ አስፈለገ?

2.   የህዳሴ ግድብን በተመለከተ የሶስትዮሽ ድርድር ማለትም የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የግብፅ ድርድር በኢህአዴግ ጊዜ መርህ ላይ ተመስርቶ የሶስቱን ሀገራት ጥቅም ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ሊያረጋግጥ በሚችልበት መንገድ ሲካሄድ ነበረ። በዚህ መርህ መሠረት የኢትዮጵያ አቋም የሶስቱን ሀገራት ጥቅም በማይጎዳ መንገድና በትብብር መንፈስ በጋር መስራት ዕድል እንዲከፍት ተደርጎ ስለተቀረፀ ተፅኖ ፈጣሪነቱ ትልቅ ነበር። በዚሁም ምክንያት ሱዳን የኢትዮጵያ አቋም ደጋፊ ነበረች። ይህንን መልካም አቋም ወደፊት ከማራመድ ይልቅ ራስህን በውጭ ኃይላት ተፅኖ  ሥር በማውደቅ “እባካችሁን ጥቅት ቀናት ስጡኝ” እያሉ ደጅ መፅናቱ ለምን አስፈለገ?

በጣም የሚያዛዝነው ጉዳይ የጠ/ሚር ዓቢይ ቡድን በህዝ ላይ የመቀለድ አባዜው እጨመረ መሄዱ ነው። ሁላችንም መገንዘብ ያለብን የህዳሴ ግድብ ላይ ተመስርተው የሚተላለፉ ውሳኔዎችና የሚፈፀሙ ስምምነቶች የእያንዳንዳችን ድምፅ እኩል ተደማጭ መሆን መቻል አለበት። እያንዳንዳችን ድምፃችን የሚናሰማው በወከልናቸው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት በኩል መሆኑ ደግሞ የሚንዘነጋው ጉዳይ አይመስለኝም። እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንደ አቅሙ ለግድቡ ግንባት ማሳካት የገንዘብም ይሁን የጉልበት አስተዋፅኦ ያደረገ ከመሆኑም በላይ በሀገር ሃብት እየተገደበ ያለ  ግድብ ነው። የህዳሴ ግድብ የጠ/ሚር ዓብይ አህመድ የግል ንብረት አደለም።  የጠ/ሚር ዓቢይ ቡድን በትረ ስልጣን ስለተቆጣጠረ ብቻ በሀገራዊ  ሃብታችን እንደፈለገ  የሚፈነጭበት ዕድል ልንሰጠው አይገባም። ስለዚህ በህዳሴ ግድብ የሚደረግ ማንኛውም ውሳኔና ስምምነት ከተወካዮች ምክር ቤት ዕውቅናና ውሳኔ ውጭ መሆን የለበትም። ጠ/ሚ ዓብይ አህመድ ሲፈጠሩ የህግ የበላይነት የማይገባቸው እንደ ህፃን የሚወራጩ ግለሰብ ቢሆኑም ቅሉ በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ግን የህዝቡን ድምፅ ማዳመጥ ግድ ይላቸዋል።

የዚህ ቡድን ቀጣፊነት መገንዘብ ያለብን በአንድ በኩል የህዝቡን ጥያቄ ለማድበስበስና  ለማረሳሳት ለቀጣሪዎቹ “እባካችሁ ጥቅት ቀናት ስጡኝ” ይላል። በሀገር ውስጥ መጋነኛ ብዙሃን በኩል ደግሞ (ማለትም በኢትቪ፣ በዋልታ፣ በፏናና ኢሳት በኩል) ኢትዮጵያ ሉዓላዊነትዋ ለማስከበር ድርድሩ እንደአቋረጠች አድርጎ ይነዛል። እውነታው ግን ይህ ቡድን ለቀጣሪዎቹ የላከው መልእክት “ድርድሩ አቋርጠናል” ሳይሆን “ ልናስብበት ጥቅት ቀናት ስጡን” ስለመሆኑ ዓለም አቀፍ የዜና አውታራት ገልጠውታል። ይህን ለማራጋገጥ የሚከተለውን መመልከት ይቻላል።

1.   “Ethiopia has asked the United States to postpone what was expected to be the final round of talks on its Grand Renaissance Dam, delaying the potential resolution of a years-long dispute with Egypt over access to water.” (https://uk.reuters.com/video/watch/ethiopia-asks-to-delay-final-talks-on-di-id685479801?chan=92jv7sln/)

2.   Why Ethiopia’s Decision to Skip the Ever Complicating GERD Talks in Washington Is Right: In an unexpected turn of events, Ethiopia’s Ministry of Water, Irrigation & Electricity said today that Ethiopia will not take part in the upcoming trilateral GERD talks with Egypt and Sudan, which was scheduled to take place in Washington D.C. on February 27-28. The Ministry said it was skipping the next talks because it did not finalize the ongoing discussions with Ethiopia’s country team of experts. . . (https://www.branapress.com/2020/02/27/why-ethiopias-decision-to-skip-the-ever-complicating-gerd-talks-in-washington-is-right/)

 

 ስለዚህ የጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ መንግስት ለምርጫ ፍጆታና ተቀባይነት ለማግኘት ተብሎ እንደልማዱ ህዝብን  በቀጣፊ መገናኛ ብዙሃን በኩል እያታለለ ስለመሆኑ ልንገነዘበው የሚገባ  እውነታ ነው። በጠራራ ፀሃይ የህዝብ ታማኝነታቸው ክደው የሀገር ሻጮች ቅጥረኛ ቡድን መሣርያ  በመሆን እያገለገሉ ያሉ ጥቅት የሀገራችን መገናኛ  ብዙሃን ፤ በአሜሪካና IMF የረቀቀውን የህዳሴ ግድብ ውል ለመፈረም እንዳስብበት ጥቅት ቀናት ይሰጠኝ ብሎ ለገዥዎቹ የተመፃደቀው የጠ/ሚ ዓቢይ መንግስት “የሀጋር ሉዓላዊነት ላለማስደፈር  ነው” ብለው ሽፋን የሰጡት ጉዳይ ነገሩ ዞር አሉ እንጂ አልሸሹም ነው። ምክምያቱም የጠ/ሚር ዓቢይ መንግስት ግብፅ ጊዜ ከሰጠችውና ቀጣዩን ምርጫ በማጭበርበር ስልጣን ላይ ከተቆናጠጠ፤ ይህ ስምምነት በምርጫ ማግስት በሁለት እጁ አረጋግጦ እንደሚፈርመው ማንኛውም ዜጋ ልዘነጋው የማይገባ ሐቅ ነው።ነገር ግን ግብፅ እስከ ክረምት መግብያ እንኳን በፍፁም ጊዜ አትሰጠም።

 

“ሲንኖር ኢትዮጵያውያን፤ ሲንሞት ኢትዮጵያ” በሚሉ ሸንጋይ ቃላት ታጅበው በተወካዮች ምክር ቤት ፊት ቃለመሃላ የፈፀመቱን ጠ/ሚ ዓቢይ ፤ በግብፁ ፕሬዚደት ፊትም ከግብፅ ጎን ለመቆም “ወላሂ አንጎዳችሁም” ብለው መሃላ ፈፅመዋል። ስለዚህ ከአረብ ሀጋራት ጋር ያለው ሽርጉድና የአሜሪካን ጥቅም ከማስጠበቅ አንፃር ስናየው ጉዳዩ “ሲኖር ግብፃዊ፤ ሲሞት ኢትዮጵያ” ስለመሆኑ በፍፁም አያሻማም።

 

ስለ እውነት እንነጋገር ከተባለ ኢትዮጵያ ዲፕሎማቲክ በሆነ  መንገድና በመርህ ደረጃ ሉዓላዊነትዋና ጥቅምዋ ማስከበር የሚትችለው የኢህአዴግን አካሄድ የሚመሳሰል መንገድ በመከተል ብቻ ይሆናል። የውጭ ኃይላት ኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የጂኦ ፖሊቲክስ ፍላጎትና የጆኦ ስትራተጂክ ጥቅማቸውን ለማረጋገጥ በጉግት አሰፍስፈው የሚናያቸው በጠ/ ሚሩና  ቡድናቸው ድክመትና የሀጋር ሻጭነት አስተሳሰብ ምክንያት ነው። ፕሬዚደንት ኢሳያስ አፈወርቅ ለምን በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገባ፣ ግብፅ ወዘተ እያልን የውጭዎቹን ከሚንወቅስ ፤ የጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ መንግስት ለምን ለውጭ ኃይላት ተጋላጭ እንድንሆን ፈቀደ ብለን ውስጣው ጉዳያችን መመርመር ይጠበቅብናል ብቻ ሳይሆን ፤ ለባዕድ ተጋላጭ እያደረገን ያለውን የጠ/ሚ ዓቢይ አህመድ ቡድን በግላጭ መቋወምና ማውገዝ ብሎም በምርጫ ካርድ ከስልጣን ማስወገድ አለብን።

 

በመሠረቱ ይህ ቡድን የብልፅግና  ፓርቲ ብሎ የመሠረተው የፖለቲካ ድርጅት፤ ጥቅት የቅጥረኛ ቡድኑ አባላት አብዝሃኛውን በመሸወድና በገንዘብ በመደለል ያቋቋሙት፤ ሀገር የመሸጫ መሣርያ ተደርጎ የተቀረፀ፣ የከሃዲዎች ፕሮግራም አንግቦ የሚንቀሳቀስ፣ “ብልፅግና” በሚል አጓጊ ቃል ታጅቦ ለጥፋት የተደገሰልን የኒኦሊበራሊስት ሥሪትና አጀንዳቸው ማስፈፀምያ እንደሆነ እያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን በራሳችን መንገድ ልናጠናውና ልንረዳው የሚገባ  ጉዳይ ነው። ይህ የፖለቲካ ድርጅት በሚከተለው ምርጫ የተመረጠ እንደሆነ ሁሉም የልማት ድርጅቶቻችን፣ በሀገራችን የተገደቡ የሃይድሮ ፓወር ግድቦች ህዳሴ ግድብን በዋናነት ጨምሮ፣ ትላልቅ መሠረተ ልማቶች በሙሉ እንደሚሸጣቸው እርግጠኞች መሆን አለብን። 

 

የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፤ ልብ ልትለው የሚገባ ታላቁ ቁምነገር የጠ/ሚር ዓቢይ መንግስት ታማኝነቱና ተጠርነቱ ለቀጣሪዎቹ መሆኑ ነው። ላንተ ለሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ አደለም። አንተንማ በብልፅግና  ስም እየሸወዱ የሀገርህን አንጡራ ሃብት ለኒኦሊበራሊስት ለማስረከብ አፋፍ ላይ ይገኛሉ። ኒኦሊበራሊስትም በበኩላቸው ይህ ቡድን ስልጣን ላይ እንዲቆይላቸው በሙሉ አቅማቸው ይደግፋሉ። አሁንም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ህዝብ ልብ ማለትና በአንክሮት መመልከት ያለብህ  ጠ/ሚ ዓቢይ የሚደሰኩርዋቸው በውሸት የተገነቡ የቃላት ክምር ሳይሆን በየደቂቃውና ሰዓቱ የሚያፈርሱዋቸው ትላልቅ እሴቶቻችንና ሃብቶቻችንን ነው።

 

ለመሆኑ በደህንነት ጽ/ቤቶች፣ በመከላከያና የሚኒስትር መስርያ ቤቶች ተሰግስገው የሚሰሩ የውጭ ዜጎች ላንተ  ብለው ሳይሆን ለሀገራቸው ጥቅም ለማረጋገጥ ብለው ነው። በአንተ ሃብት ሀገራቸውን ያበለፅጋሉ ፤ ላንተ ደግሞ በሚያማልሉ ቃላት መንፈስህን በተስፋ እየሞሉ ሳይታወቅብህ ወደ ባሰ የድህነት አረንቋ በጭካኔ ያወርዱሃል። ምክንያቱም የድህነት አማልክት ናቸውና። ስለዚህ አንጡራ ሃብቶቻችንን በጠ/ሚ ዓቢይ ፊርማ ምክንያት ከእጃችን ከማምለጣቸው በፊት ሁላችንም ጠንካራ ትግል የማድረግ ጉዳይ የግድ ሆነዋል። በተለይ ደግሞ ይህን ህብረ-ብሔራዊ ፌደሬሽን እንዲቀጠል የሚትፈልጉ የፌዴራል ኃይላት፤ ልዩነታችሁን አቻችላችሁ የሚትተባበሩበት ጊዜ ከማንኛውም ጊዜ በበለጠ ዛሬ ሆነዋል። ኢትዮጵያን ከውጭ ኃይላት ማዳናን ይህንን ፌዴሬሽን ማስቀጠል ዋነኛ አጀንዳችሁ አድርጋችሁ በትብብር የሚትሰሩበት ጠንካራ መድረክ ከፈጠራችሁ ስጋቶቻችንን የሚቀረፈበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ መገመት ይቻላል። ኢትዮጵያ ከፌዴራል ኃይሎች ትብብር ውጭ የመዳን ዕድልዋ ዜሮ በሆነበት ጊዜ ፤ ይህንን አንኳር አጀንዳ  ወደ ጎን ትታችሁ በትርኪ ምርኪ ስትዋልሉ ኢትዮጵያ ለከፍተኛ አደጋ ከተጋለጠች ፀፀታችሁ ከባድ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ።

 

 

 

Back to Front Page