Back to Front Page

ምርጫ 2012 የራስ እድል በራስ መወሰን እና ድርድር መወጣጫውስ?

ምርጫ 2012 የራስ እድል በራስ መወሰን እና ድርድር መወጣጫውስ?

ሰሎሞን መዝገቡ

05-19-20

 

 

ውጥንቅጥ

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዉጥንቅጥ ዉስጥ ገብቷል፡፡ አሁን የተቀመጠው ፓርላማ እድሜው አብቅቷል። ሲጀምር ህዝባዊ ቅቡልነት ሳያግኝ፤ በጉልቤ መቶ ፐርሰንት የውክልና ወንበር ዘርፎ፤ አገሪቷን ለቀውስ ዳርጋት። ኢህአዴግ መራሹ የሚፈረከርክበት ወቅት ሲደርስ አቢይ አህመድ በአቋራጭ ፊጢጥ አሉ። ግድየለም ሁለት አመት ሩቅ አይደለም እንታገሰው ይህ ሰው ወደ በጎ ዘመን ያሸጋግረን ይሆናል ተብለው በተስፋ ሲጠበቁ፤ ንጉስ ነኝ ብለው አረፉት። አንድ አመት ተኩል አገር በግርግር፤ በህዝብ እልቂትና መፈናቀል፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ደግሞ በዙረት፤ በፎቶ መነሳት፤ በውዳሴ ከንቱ ባከነ። የተፈናጠጡብትን የኢህአዴግ ፈረስ ውጉዝ ከም አርዮስ አስብለው በብጥነት ብልፅግና ፓርቲ ብለው መጡ (molded and influenced by ideologues of the Southern United States Property Gospel)። የኢህአዴግ በቢልዮኖች የሚቆጠር ንብረት ፤ አውታር አይቀር ሚልዮኖች ያሉበት አባልነት ወርሶ በልበ ሙሉነትና በእርግጠኝነት ጉዞ የጀመረው ብልፅግና፤ ገና ድክድክ ሳይል፤ ፍርሃት ያዘው፤ ዳገት ሳይወጣ ብርክ ብርክ አለው። እናም አቋራጭ ፈለገ፤ ምርጫውን ቢቻል በወረርሽኝ በሽታ ሳይሆን በሕገ-መንግስት ትርጉም ሰብብ አስባብ የስልጣን እድሜን ማራዝም። ኢህአዴግን ነቃቅየ ጥያሎህ ያለው ቡድን የለም የኢህአዴግ ሪፎርም ቀለም የተቀባሁ ወራሽ ነኝ ይላልበደርቁ ላጨኝ ነው ነገሩ ። ተቀናቃኞች የለም ቀልድህን አቁም፤ የባከነው ሁለት ዓመት ይቆጫል እያሉ ነው። ምርጫው በህግ በተደነገግው የፓርላማ እድሜ ማገባደጃ ይከናወን፤ ይህ ባይሆን የተቀናቃኝ ፍቃድ ያገኘ ስልጣኑ የተገደበ ባለአደራ አስተዳደር መንግስት ይረከብ፤ወይም እኛን የሚጨምር የሽግግር መንግስት ይቋቋም እያሉ ነው። ይህ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እሳቸው ላይ የተቃጣ የስልጣን ሽሚያ አርገው ወስደውታል። ጠቅላዩ ምኞታቸው የሚኮላሽ ቢመስላቸው፤ በንዴት አካኪ ዘራፍ እያሉ ነው፤ ህፃናት ያልቃሉ ፤እናቶች ያለቅሳሉ ብለው ይዝታሉ። የመንግስት አውታር ላይ ጉብ ያሉት፤ ለጊዜውም ቢሆን ፤ የፀጥታና የመከላከያ ኀይሉን የተቆጣጣሩት ጠቅላይ ሚንስትሩ ናቸው። ይኼን ኃይል በመጠቀምም የስልጣን እድሜ ማራዘም ፤ ውሳኔቸውን ያልተቀበሉት፤ አለፎም የተፃረሩት ላይ ወታደራዊ ኃይል እንደሚጠቀሙ እየዛቱ ነው። አይዞህ ባይም አላጡም። ተቀናቃኞቻቸዉ ዛቻው ይቆይ፤ አያዛልቅም፤ አይበጅም እንደራደር እያሉ ሲሆን ከክልሎችም የትግራይ መንግስት ድርድር አጠላም፤ ምርጫውን ግን የፌደራል ፍቃድና ሰሌዳ አልጠብቅም፤ በክልሉ ህግ መሰረት አከናዉናሎህ እያለ ነው (ለማስፈራራት ይሁን የምር የሚታይ ይሆናል)፡፡ በዚህም ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር ፍጥጫ ተፈጥሯል፡፡ የአቢይ አህመድ ዛቻ ተክትሎ (ሶሻል ሚዲያና አጫፋሪዎች እያራገቡት)፤ ህዝብ የጦርነት ስጋት ገብቶታል። አገር ያረጋጋሉ የተባሉት፤ አገሪቷን አምሰዋታል።

ከዚህ የቀውስ አጣብቂኝ አገሪቷ እንዴት ትላቀቅ? የፌደራል መንግስት፤ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ቡድኖች፤ የትግራይ ክልልና ሌሎችም ወደ ጠረጴዛ ድርድር እንዴት ይምጡ? የትኞቹ መንገዶች ወደ ጥፋት የትኛውስ ወደ ሰላምና ድህንነት ይወስዳሉ?

Videos From Around The World

ድርድር

ተቀናቃኞች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግስት ወደ ድርድር ለማምጣት ማድረግ ያለባቸዉ ምንድነዉ?

የክልል መንግስታት አማራጭስ ምንድነዉ? የሚለዉን ማየት ተገቢ ነዉ የዚህ ፍጥጫ ሂደት ውጤት አራት አማራጮች አሉ፡፡እነዚህ መንገዶች በሁሉም ዘንድ ተመራጭነት አይኖራቸውም፤ አንዳቸውም ቀላል ምርጫ አይደሉም፤ የተወሰኑት አደጋቸው ከፍተኛ ነው። ግን የያእንዳአንዱ መንገድና ሂድት ምክንያታዊ ውጤቶች ናቸው። እያንዳንዱ ሂደት በመጠኑ ዳሰስ አረገን፤ በተነፃፃሪ የተሻለ ዘለቄታው መርጋጋት ሊያስገኝ የሚችለውን በዝርዝር ቀጥሎ እንያለን።

1.   ጠቅላይ ሚንስትሩ የያዝኩት መንገድ አያዋጣም ብለው በግል ተነሳሽነትም ይሁን ከጀርባ በሚያበርታትዋቸው ምክር/ግፊት አዲስ አዋጭ መንገድ ሲቀይሱ፤ ከተቀናቃኞችም ከክልሎችም በተለይ ከትግራይ ክልል መንግስት ጋር መደራደር ይኖርብኛል ብለዉ ሃሳባችዉን መቀየር ቢችሉ? በዚሁ መንገድም መጓዝ ሲጀምሩ?

ይህ ሲበዛ የሰላም መንገድ ነው፡ እንዲያው ኢትዮጵያ ሎተሪ ወጣላት! የሁሉም ፀሎት ነው። መመኘት መልካም ነው፤ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣን ላይ ከቆዩበት ሁለት አመት አንጻር ሲታይ ይህ አማራጭ ተስፋ አስቆራጭ እና መሬት ላይ ጠብ የሚል አይመስልም፡፡ እስከአሁን በተግባር የታየው የዚሁ ተፃራሪ ነው። በግል፣ በቡድን፣ በግልፅ በአደባብይና በሚስጥር አረ ተው አደብ ግዛ ቢባሉ የሚመለሱ አልሆኑም። ስፍር ቁጥር የሌለው ሙከራ ተድርጓል፡ የሃይማኖት አባቶች፤ የአገር ሽማግሌዎች፤ ጥርሳቸውን በፓለቲካ የነቀሉ እንቶዎች፤ አለምአቀፋዊ ምድና እውቅና ያላቸው ከፍተኛ የፀጥታና የደህንነት አማካሪዎች፤ አንዴ በምክር፤ አንዴ በማባበል፤ አሊያም በግሳፄ ተው አይሆንም ቢባሉ የሚሰሙ አልሆኑም። ልባቸው ሸፍቷል። የእርሳቸው ንግስና ቅዠት ይሁን እውነት መለየት አቅቷቸዋል። ምክር ካዳመጡም በምናባዊው አለም ከጫፍ እስከጫፍ በይትብሃል የሰለሞን ስጋጃ (magic carpet) ከዳር እስከ ዳር ሲያዳርሱና፤ ተቆጥተው ሲግስፁ፣ ስጋጃው ተርገብግቦ፤ አርባ ሺ ሰራዊት እንደ ቅጠል ሲረግፍ የሚተሩኩላቸውን ነው። በዚህ በኩል ብዙ ተስፋ የለም።

2. ተቀናቃኝ ሃይሎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጫና የሚያሳድሩበትን መንገድ መፈለግ? በአለፉት አራት እና አምስት አመተት እንደታዩት ተቀናቃኞች የተጠቀሙበት አንዱ መንገድ እንደፋኖ እና ቄሮ የመሳሰሉ ቡድኖችን በማሰማራት በየከተማዉ አመፅ በማካሄድ በሚፈጠር ግርግር የመንግስት ለዉጥ እንዲኖር ማድረግ?

ብዙ ኪሳራ ያስከተለው ለወጥ የለውጥ ፈላጊ ሃይሎች እንደተመኙት ሳይሆን ተኖ ቀረ። አሁንም ይህንን መንገድ መከተል ውጤታማ ያደርጋል የሚለዉ አጠራጣሪ እና ምናልባትም ሀገሪቱን ወደከፋ ቀዉስ ሊወስዳትም የሚችል አማራጭ ነዉ፡፡ እነዚህን ቡድኖች አደራጅን የሚሉ ግለሰቦች እንዳለፉት አራት እና አምስት አመታት በነዚህ ቡድኖች በተለይ ወጣት ተከታዮቻቸዉ ላይ ተፅእኖ ለመፍጠር ያላችዉ ብቃት አጠራጣሪ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ተፅእኖ እንፈጥራለን ካሉት ግለስቦች አንዳንዶቹ ስልጣን ላይ ካለዉ መንግስት ጋር የተቀላቀሉ ግማሾቹም ኮብልለዉ ሽፍትነት የገቡ ሌሎችም ተስፋ ቆርጠው የሚንከራተቱ ወይ ወደ ስደት የሄዱ ናችዉ፡፡ስለዚህም እንደአዲስ ወጣቶችን አነሳስቶ መንግስት ላይ ጫና በመፍጠር የሚፈለገዉ ውጤት ይመጣል ብሎ መገመት ተግባራዊነቱ አጠራጣሪ ነው፡፡ በእርግጥ በግዥው ቡድን ተስፋ የቆረጡ ሃይሎች ዛሬም እንደትላንቱ መንግስት እንዲርድ ምናልባትም እንዲፍረከርክ ማረግ ይቻል ይሆናል። ነገር ግን ውጤቱ ሊቆጣጠሩት በማይቻል ስትራቴጅ ተስፋ ማድረግ፤ ተመራጭ አይሆንም።

3. ጠቅላዩ በማስፈራራት ምርጫዉን ብቻ ሳይሆን የስልጣን ዘመናችዉን ማራዝም የፀጥታ እና የመከላከያ ሀይላችዉን አሰማርትው አገሪቷን ፀጥ ለጥ አርገው መግዛት ሲችሉ?

ፓርላም፤ ፌዴሬሽን፤ አፅድቆልኛል፤ ህግ አዋቂ፤ ህግ አማካሪ እነ እንቶኔ ያስኬዳል ብለውኛል ስለዚህ ምርጫ አራዝማሎህ፤ ስልጣንም ላይ እቆያሎህ፤ ይኼንን የማይቀበል ክልል ካለ ቅጣት ይከናነባታል እንጂ አልለማመጥም፤ ትግራይ ገለ መሌ አፈራ (ለዛውም ኢሳያስን የመሰለ ከጎኔ ይዤ) ሰጠ ለጥ አርጌ እገዛሎህ በሚለው መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልጓዝ እያሉ ነው (እርሷም ይሞክሩት አይባል ነገር)

ከአዲስ አበባ ውጭ ፀጥታ ማስከበር ያቃተው መንግስት፤ የዪኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ድህንነት መጠበቅ ሳይችል ቀርቶ እንዲዘጉ የወሰነ መንግስት፤ በአብዛኛው ምዕራብ ወለጋን ድርሽ የማይል መንግስት፤ በየትኛው ቁመናው የትግራይ ክልልን ያህል በጉልበት ፍላጎቱን ማስፈፀም ይችላል? ወጠምሻ ወጠምሻውን በኮማንዶና በተለያየ ወታደራዊ ብቃት አሰለጥኖ፤ የግል ጠባቂ አድርጎ (Special Force, Elite Commando, Republican Guard) በየእለቱ እየጎበኙ፤ መፅናናትና ደረት መንፋት ትልቅ ሞኝነት ነው። ወታደራዊ ቁመናቸው ያማረ የግል ጠባቂዎችን ተማምኖ ኢትዮጵያን የሚያህል አገር እገዛሎህ ብሎ መደንፋት እንዲያው ቅዠት ነው። እንደዚህ አይነት ፈጥኖ ደራሽ የግል ጠባቂ ሃይል ቢልዮን ዶላር በቀጭን ትእዛዝ ለሚያሰማሩት ፓቭሎ ኢስኮባርን ጉዝማንም አልሆነም። ትርፉ ውንብድና ነው፤ ማለቂያውም አያምርም። ይህ ዛቻ ወደተግባር ቢተረጎም የሚፈጠረዉ ግጭት የሃይል ሚዛኑ የደፋለት የሚፈልገዉን ለማደረግ እድሉን እንዲጠቀምበት መፍቀድ ነዉ፡፡ይህ ሀገሪቱን ወደ ከፋ ቀዉስ የሚዳር ለዜጎችም ሞት፤ስደትና እልቂት የሚያመጣ የጥፋት መንገድ ነው፡፡ይህ አማራጭ ለአብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ስጋት የሆነዉን የመበታትን አደጋንም ሊያስከትል ይችላል፡፡

4. ክልሎች በተለይ የትግራይ መንግስት ተገዳዳሪ አቅማቸው ተጠቅመው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጫና በመፍጠር ወደ ድርድር እንዲመጡ ማድረግ?

በፌደራል መንግስት ላይ ጫና ማሳደር የሚችሉ አስተዳደራዊ አቅም፤ መንግስታዊ ቁመና፤ በተወሰነ መልኩም የፀጥታና የህግ አስከባሪ ሃይል ያላቸው የክልል መንግስታት ሲሆኑ እነዚህም በዋናነት ትግራይ፤ምናልባትም ኦሮምያ፤አፋር ክልል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ በተጨባጭ አብዛኞቹ ክልሎች ፌደራል መንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኙ ሲሆን የትግራይ ክልል መንግስት ግን ከጠቅላዩ ጋር ሆድና ጀርባ ሆኗል። አንዳንዶች ይህ ፍጥጫ ወደ ዘመን መሳፍንት ይመልሰን ይሆን የሚል ስጋት አላቸው፤ የመንና ሶርያም በጭንቀት ያማትራሉ። ክልሎች ልዩ ኅይል በከፍተኛ ትጥቅ ማደራጀታቸው ስጋቱን አባብሶታል። እንደ ትግራይ አይነቱ ደግሞ የኢትዮጵያ የጦር ሃይል ያደራጀና የመራ በቂ ተገዳዳሪ ሃይልና ትውልዶችና ዘመናት የተሻገረ የስኬታማ ጦርነት ልምድ ያለው መሆኑ የማያባራ ጦርነት እንዳያመጣ ስጋት መኖሩ የግድ ነው። የዚህ ፅሑፍ አላማ፤ ይሔንን ስጋት ከግምት አስገብቶ፤ ይህ አማራጭ ከስጋቱ ይልቅ ተስፋው የተሻለ መሆኑን ማሳየት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛቻቻውን ትተው ወደ ድርድር ለማምጣት የሚያስችለው መንገድ የተሻለ አማራጭ ይሄው ነው ብሎ ይኼ ፀሃፊ ያምናል። የትግራይ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ይኼን ተከትለው የራስ ማስተዳደር መርህ መሰረታዊ ትርጉም ከክልል እስከ ወረዳ politics is local በሚለው መርህ በባለቤትነትና በሙሉዕነት ስራ ላይ ቢያውሉት የተሻለ ውጤት በድርድር ማምጣት ይቻላል። እንዴት? ማንኛውም ሃይል እንዲደራደር ለማስገደድ ሁለት አውራ ጉዳዮች መሟላት ይኖርባቸዋል፡ቁመና (posture essentially from hard power) እና ጭብጦ (what you have to offer essentially from soft power)

ቁመና ስንል ምን ማለታችን ነው?

የመንግስት የመጀመሪያው ስልጣንና ህዝባዊ ቅቡልነትና (authority and legitimacy) የሚመንጨው፡ የጋራ ድህንነት መጠበቅና ከሞላ ጎደል የህግ ማስከበር አቅሙ ነው (collective security and law enforcement capacity)። በመንግስትና በዜጎች መካካል ያለው የመጀመሪያው መሰረታዊ ኮንትራት ይኽ ነው። ይህ የለም፤ መንግስት የለም። አንድ ሰው ከእነቤተሰቡ ከገበያም ይሁን ከስራ ገበታ ወይ ከዘመድ ጥየቃ በሰላም ውሎ መመለስ ካልቻለ የስም መንግስት ምን ትዳው? የአሁኗ ኢትዮጵያ “መንግስት የለም” “የት ያለ መንግስት” የሚባል የዕለት ተዕለት ምሬትክ እንደ “እንደምን አደራቹህ” የዘወትር ሰላምታ ከሆነ ሰነባብቷል። ለዚህ ለዚህ እንደአቅሚቲ የግል ጠባቂ ከፍ ሲል ደግሞ የሰፈር ሪፓብሊካን ጋርድ ማደራጀት ሳይሻል አይቀርም። በአንፃሩ ይህ ትግራይ ውስጥ ችግር አይደለም፤ ከፀጥታና ህግ ማስከበር አልፎ፤ ለህብረተስቡ መሰረታዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አግለግሎት ይሰጣል። አጥንቱ የደነደነ በተግባር የተፈተነ ሰፊ ማህበራዊ መሰረት ያለው የፀጥታ ሃይልም አለው። ቢያንስ ቢያንስ የራሱንና የአከባቢውን ፀጥታና ድህንነት የመጠበቅ አቅም አለው። ቁመና ማለት ይህ ነው።

ቁመና ሳይኖርህ፤ ሃይልህን ፕሮጀክት ማድርግ አትችልም፡ ተቀናቃኝህም ያአንተም የራሱም አቅሙ እንዲገምት ከፀብ ጫሪነትም ለዘብ እንዲል ቁመናህን በማዶም ቢሆን ማየት ይኖርበታል። ፌደራል መንግስቱም፤ በተሰጠው ሃላፊነት ልክ የሚመጥን የፀጥታ የማስከበር አቅም ባይኖረውም፤ ቢያንስ መቀመጫውንና አንዳንድ ከተሞችን የመቆጣጠር አቅም ይኖረዋል። በተጨማሪም ከፍተኛ ወታደራዊ ቁሳቁስና የፋይናንስ አቅም ከአይዞህ ባዮች እንደሚያገኝ (በተለይ ከግብፅና ሌሎች የአረብ መንግስታት) ጥርጥር የለውም። በአጭሩ የተወሰነ የማይናቅ ቁመና አለው። አብዛኛዎቹ ሌሎች ክልሎች ይኼን በተመለከተ በየአይነቱ ዝብርቅርቅ ነው። ከአንድ ጫፍ እየተንገዳገደ በድጋፍ ሊቆም የሚችል አለ ወደ አንዱ ጫፍ ደግሞ ፍፁም የተንበረከከ በተላላኪነት የሚመደብ ነው። እንደ አብዛኛው የአማራ ክልል ለጎጥ ሽፍታ ያደረም አለ። ስለዚህ ፌደራሉን ከሚግደራደርና ሙሉ ቁመና ካለው የትግራይ መንግስት ላይ ትኩረት እንደርጋለን።

ጭብጦ

ቁመና ለጦርነት በቂ ሊሆን ይችላል፤ ለድርድር ግን ጭብጦ ግድ ነው። በቁመና ፕሮጀክሽን ተገዳዳሪነትክን ካሳይህ በኋላ የምትቀበለውን (demand) ለማግኘት የምትስጠው ጭብጦ ሊኖርህ ይገባል (offer)። የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት offer የሚያረገው ብዙ ነው፤ ስልጣን መጋራት፤ፋይናንስ፤ ገበያ፤ አለማቀፍ ድጋፍ፤ አገናኝ መድረክ (ሁሉም በግልፅ በሚያውቀው ጉዳይ ከዚህ በላይ መዘርዝሩ አስፈላጊ አይደለም)

የትግራይ መንግስትስ ከቁመና በላይ ምን አለው?

በእርግጥ ከራሱ አልፎ ለአከባቢው የሚበቃ የፀጥታ ዋስትና አቅም አለው (hard power) ነገር ግን ትርጉም ላለው ሰላማዊ ድርድር ከዚህ በላይ ዳጎስ ያለው ጭብጦ ያለው ሶፍት ፖወር መያዝ ይኖርበታል። ይህም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ሙሉ በሙሉ የትግራይ ህግ-መንግስት በሚያዘው መሰረት ሲያከናውን ነው። የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ከመንግስት ሃላፊነቱና ግዴታዎቹ አንዱ፤ ወቅቱን ጠብቆ በክልሉ ህገ መንግስት መሰረት ምርጫ ማካሄድ ነው። አሁን አይንህ ለአፈር እንደተባባሉት የኢህአዴግ ወዳጆቹ ፤ ህወሓትም ቢሆን በጉልበት የተገኘ ስልጣን እንጂ በምርጫ የተገኘ ህዝባዊ ቅቡልነት እስካሁን የለውም። አሁን በትግራይ ሕዝብ ጫና ወዶም ይሁን ተገዶ ምርጫ ማካሄድ ይኖርበታል። ምርጫው ተፎካካሪ ፓርቲዎች (ዓረና፤ ሳለሳይ ወያነ፤ ባይቶና፤ ወዘተ) የግል ተወዳዳሪዎች ጋር በግልፅና በእኩልነት የተሳተፉበት መሆን ይኖርበታል። ሂደቱም፤ አተገባበሩም የሚወሰነው እዛው ትግራይ ነው። ትግራይ ይኼን የማድረግ አቅም ብቻ ሳይሆን፤ ምርጫ ለማስፈፀም የሚያስችል ሁኔታ (environment) አለ። የሕዝብ የስነ አእምሮ ዝግጅትም አለ። ትግራይ ይሔንን ማድረግ ይችላል፤ መደረግም አለበት። ይህ በዋናነት የትግራይ የራስ እድል በራስ የመወሰን መብትና አቅም (autonomy) ጭብጦውን ቢይዝ ለድርድር ያለው ብቃት ለማሳየት የሚደረግ ጥረት ቢሆንም በአገር አቀፍ ደረጃ ጠቀሜታው የጎላ ነው። ለምን ቢባል፡ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የማያባራ የድርድር ሂደትና ውጤት ነው። የሚገነባውም በድርድር፤የሚኖረውም፤ የሚተነፍሰውም በድርድር ነው። ታዲያ ምን ተይዞ መደራደር አለ? እንግዲህ የማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፡ የአስቸኳይ ጉባኤ መግለጫ እየተባለ፤ ከሁለት ዓመት በላይ ሁሉም በየፊናው ኝኝ ሲሉ ከርመዋል። እንግዲህ መግለጫ ጥርስ አይሆን! ጭብጦም አይደል! የትግራይ መንግስት ‘በወቅቱ ምርጫ እንካሄዳለን’ መግለጫም ከዛቻ አልፎ፤ መሬት ላይ ጠብ ይበል። ተዓማኒነትና ሕዝባዊ ቅቡልነት እንዲኖረው፤ ከዝግጅት እስከ ፍፃሜ ተፎካካሪ ቡድኖች በእኩል ይሳተፉበት።

የዚህ ምርጫ አንዱ ልዩ ባህሪ፤ እንደተለመደው ከላይ ተሹመው መጥተው ሕዝብ ለይስሙላ መርጠህ አፅድቅልን ከሚባለው ፍፁም የተለየ እንዲሆን ግድ ይላል። አብዛኛው ስልጣን ከአራት ኪሎ ወደ ክልል ይውረድ ስንል (devolve)፤ እዛው ክልል አዲስ ንጉስና መሳፍንት ለመፍጠር አይደለም። አብዛኛው ኗሪ የሚፈልገው የእለት ተእለት ጉዳይ ያለው ወረዳ ጋ ነው። ስለዚህ የክልል (ስቴት) ስልጣንም ፤ ከክልል ወደ ወረዳ መተላለፍ ይኖርበታል። ከህዝብ ጋር ቀጥታና የዘወትር ግንኙነት ያለው የወረዳ አስተዳደራዊ ስልጣን ነው። ይህ እርክን ካለ ምንም እንክን በፍፁም ሙለእነት ተጠያቂነቱ በቀጥታ ለመረጠው ለወረዳው ህዝብና ለወረዳው ህዝብ ብቻ መሆን አለበት። የህወሓት መሪዎች ስለ ምርጫ ሲያወሩ ይኼንን ለመተግበር በአስቸኳይ መዝጋጀት ይኖርባቸዋል። ይኼን ለመተግበር ቢትጉ መልካም ነው፤ አሊያ አራት ኪሎ እያሉ የደረሰውና እስከአሁን ዋጋ እየተከፈለበት ያለው መዘዝ መቐለም ይከተላቸዋል።

በእንደዚህ ነፃና ህጋዊ ምርጫ፤ ሕዝባዊ ቅቡልነትና የአብዛሃ ደምፅ ይዞ የመጣ መንግስት (legal, legitimate and popular) አራት ኪሎን ዘወር በል ቢል ያምርበታል። የሞራልና የህግ የበላይነት ይይዛል። እንግዲህ ጭብጦው ይህ ነው (this is the soft power)። ለሌሎች ክልሎችም አርአያ ይሆናል፤ተስፋን ይሰንቃል። በዚህ መንገድ አራት ኪሎ ላይ ተገቢ ጫና መፍጠር ይችላል። ጠቅላዩም ማጣፍያቸው ያጥራል፤ ወደ ድርድር እንዲመጡም ይገደዳሉ። ክልሉ ምናልባት ረስተው እንደሆን የወረቀት ነብር እንዳልሆነ በግቢር ያዩታል። እንግዲህ ጥቂት ብልሆች ካለፈ ልምድና ታሪክ ወስድው ባይተነብዩም መጪውን መገመት ይችላሉ። አንዳንዱ ደግሞ በሚጨበጥ በሚዳሰስ ነገር ነው የሚያምነው። ጠቅላዩ እንዲህ አይነት ሰው ቢሆኑ ሊገርም አይገባም። በተግባር በነቂስ ወጥቶ በነፃነት ሕዝብ ምርጫ ሲያካሂድ፤ ፍላጎቱንም ሲገልጽና ፤ ተወዳዳሪዎችም ውጤቱን በፀጋ ሲቀበሉ፤ ጠቅላዩ በሩቅ ከመታዘብ ምን ምርጫ ይኖራቸዋል። ይኼንን የሕዝብ ፍቃድና ፍላጎት ጥሰው፤ ወጠምሻ ሪፓብሊካን ጋርድ አዘምታሎህ ቢሉ ኪሳራውም ዕዳውም ብዙ ነው። የደለበ ክብር ዘበኛ ለነጋዳፊም አልሆነ።

ቋፍ ላይ ያሉ እንደ አፋርና ኦርሚያ፤ የክልል ምርጫ ለማድረግ ምከንያትና ድፍርት ሊኖራቸው ይገባል።

ከህወሓት የተናቆሩና በተለይ በሌላ ክልል የመንግስት ስልጣን ላይ ያሉ ወይም ተገዳዳሪ የሆኑ አካላት ይኼን መስመር ለመከተል ከህወሕት ጋር መታርቅ ግድ አይልም። የትግራይን አርአያ ተከትለው ፌደራሉን ሳይጠብቁ የየአከባቢ ምርጫ ቢያካሂዱ ወይ እንዲካሄድ ግፊት ቢያረጉ ከጠቅላዩ ጋር የሚኖራቸው ድርድር በእኩልነትና ሉዑላዊነት የተመሰረተ እንዲሆን ዕድላቸው ከፍ ያረገዋል። አለበለዚያ አሁን እንደሚታየው የራስ መብትንና ሉዑላዊነት ብኩርና ሽጦ ትርፍራፊ መልቀም ነው። የልመናና ከበታችነት የመነጨ የታዛዥነት ተልዕኮም ይቀጥላል። አያያዙን (ቁመናውን) አይቶ ጭብጦውን ቀማው ነው ነገሩ።

በእርግጥ ይኼም መንገድ እንደሌላው ለእያንዳንዱ ቡድን ትርፍና ኪሳራ አለው። የዚህ ፅሁፍ መከራከሪያ ለሕዝቡ ብቻ ሳይሆን በስልጣን ላይ ላሉት መቆየትም ለሚፍልጉት ኪሳራውና ትርፉ ተወራርዶ ደም ሳይፋሰስ የሚተርፍ እርባና አለው የሚል እሳቤ ነው። በዋንነት ህወሃት ብናይ፤ በክልሉ የሚደረግ ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ ፤ በእርግጠኝነት ወንበር ያሳጣዋል (100 ፐርሰንት ፌዝ የሚያስተናግድ ትከሻ ከአሁን በኃላ ትግራይ ውስጥ እንደማይኖር መሪዎቹ የገባቸው ይመስላል)። በነፃና ፍትሓዊ ምርጫ በተለይ የግል ተወዳዳሪዎች በብቃት በሚሳተፉበት ሁኔታ፤ ህወሓት ምናልባት በምክር ቤቱ ሲሶ ድምፅ ቢያግኙ (realistic) ነው። የወንበሮቹን ግማሽ ቢያገኙ ተዓምር ነው። ስለዚህ እዛው ትግራይ አይነኬነቱ ያልቅለታል፤ ከታችኛው ቀበሌ እስክ መቐለ ያሉ ባለስልጣናትም፤ ስልጣኑም ጥቅሙም ይቀራል ወይም ይጎድላል። ከዛም አለፎ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚኖራቸው ተፅእኖ፤ እስከና አካቴው ባይጠፋም ይደበዝዛል፤ አራት ኪሎም እየራቀ ይሄዳል (ዋናው ስጋታቸውም ይሔ ይመስለኛል)። የህወሓት መሪዎች፤ ከተፎካካሪዎቻቸው ጋር ተስማምተው ነፃና ፍትሓዊ ምርጫ፤በትግራይ ህግ-መንግስት መሰረት ምርጫ ቢያካሂዱ፤ አቢይ መጣ ኢሳያስ መጣ፤የትግራይ ሕዝብ ከጎናቸው ይቆማል። በተግባር እንደታየው ጥላ ከለላ ይሆናቸዋል። አይ ምርጫን እንደሸቀጥ ተጠቅመው፤ ከአቢይ ጋር እሞዳሞዳሎህ ቢሉ፤ የትግራይ ሕዝብ ላያቸው ላይ ይቆማል። ምርጫው የነሱ ነው። አሁን ከአቢይ ጋር ሆድና ጀርባ የሆኑት የህወሓት መሪዎች (ለዲሞከራሲ ትልቅ ፀጋ ነው) ይኼን ማድረግ ይችላሉ። እስካሁን ላጥፉት በደልና ላደረሱት ኪሳራ፤ መካስ ጀመሩ ማለት ነው። ሌሎች ቋፍ ላይ ያሉ የኦሮሚያና የሌሎች ማህበረሰብ የፓለቲካ ቡድኖች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸው ግነኙነት (አንዴ ሞቅ አንዴ ቀዝቀዝ ) መልክ አስይዘው፤ ትግራይ እንዲደርግ የምንግፋፋውን ከክልል እስከ ወረዳ የራስ እድል በራስ የመወሰን መንገድ ቢመርጡ ያዋጣቸዋል። ችግሩም መፍትሔውም ያለው እዛው ነው። ወረዳን የተቆጣጠረ ፓለቲካን ተቆጣጠረ! Politics is local as Tip O’Neil would love to say!

ቁመና ብቻውን ከጀብደኝነት ወይም ውንብድና አያልፍም!

ጭብጦ ብቻውን ከወንበዴ ወይም ዘራፊ አያስጥልም!

ቁመናም ጭብጦም ከተያዘ ግን የማይቻል የለም! ጥይት ሳይተኮስ ለዛውም በድርድር!

Back to Front Page