Back to Front Page

መዘዙ ቡዙ ነው ፡፡

መዘዙ ቡዙ ነው ፡፡

ከ አቤነዘር ሰሜን አሜሪካ 02-18-20

ሰላም አይጋዎች , ሰሞነኛ የሆነውን የጠ/ ሚኒስትሩን ንግግር በተለይ ህወሓትን በተመለከተ በፓርላማና በሶፈመር ዋሻ ያቀረቡትን እርስ በረሱ የሚጣረዝ እምነታቸውን ስሰማ ክቡር ጠ/ / ሩ አድማጮቻቸው የሚፈልጉትን ነው እየፈለጉ የሚናገሩት?? ወይስ መሬት ላይ ያለውን እውነታ ነው እየመነጠሩ ነው የሚገልጹት?? ብዬ የታዘብኩትን ላካፍላችሁ ብዬ ብእሬን አነሳሁ፡፡

የታወቀው የሊደርሽፕ ምሁርና ባለ ቡዙ መጽሃፍቶች ደራሲ ጆን ክራስዌል ( John Creswell ) የመሪዎችን ስነ ባህሪይ ( ካራክተር) በሚገልጽበት ጽሁፉ ላይ ያገሩንና የህዝቡን ጥቅም የሚያስቀድም መሪ ትክክለኛ መገለጫው ለሚናገረው ንግግርና ላመነበት ሃቅ ታማኝ ሲሆን ነው ይልና ፖፒሊስት ወይም ደግሞ ደጋፊና አድናቆት ፈላጊ መሪ ደግሞ ቅድሚያ የሚሰጠው ህሊናው የሚነግረው እውነትን ሳይሆን ያድማጮቹን ልብና ጆሮ የሚገዛለትን ርእስ ጉዳይ ማንሳት ና አቅላቸውን የሚይዝበትን መንገድ በማጥናት እንደሚጠመድ ያስረዳል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጆን ክረስዌል የመሪ ስብአናዎች ወይንም መገለጫዎች የሚላቸው ታማኝነት ( trust ) ግልጽነት ( transparency ),ሃሳብ አፍላቂነት (innovative idea ), ተጽእኖ ፈጣሪነት ( influential ) , የንግግር ችሎታነት ወይንም communication skill መሆናቸውን ያስቀምጣል፡፡

Videos From Around The World

ከነዚህ ሁሉ ግን የውነተኛ የመሪ ትክክለኛ መገለጫው ታማኝነት ወይንም trust ሲሆን ይሀ ታማኝነት ደግሞ የሚለካው በንግግሩ ውስጥ የሚያስተላልፈውን መልእክት ቦታና መድረክ እየመዘነ ሳይለዋውውጥ መግለጽ ሲችል ነው በማለት ያስረዳል፡፡ ክሬስዌልም ሆነ ሌሎች ምሁራን በጋራ የሚስማሙበት ዋናው ጉዳይ ጥሩ ተናጋሪ ጥሩ መሪ መሆን አይችልም ብለው ይደመድማሉ ፡፡ የመናገር ችሎታ ከመሪነት ስብእናዎች አንደኛው ቢሆንም በደረጃ ግን ከመጨረሻው ረድፍ ላይ ይቀመጣል፡፡ ትልቁ የመሪነት ፋይዳው መሪው በሚመራው ህዝብ ዘንድ ታማኝነት ( ትረስት ) ማግኘቱ ነው ሲሉም ያስረዳሉ፡፡

በዚህ የመሪዎች ህሳቤ ውስጥ ክቡር ጠ/ /ሩ የሚመሩትን መንግስትና የሳቸውንም የመሪነት ስብእና ለማየት ሞከርኩ፡፡ ይሄን እንድል ያነሳስኝ ሰሞኑን ወደ ባሌ ሄደው ለኢጆሌ ባሌዎች ያደረጉትን ንግግር ወይም ፓርቲያዊ ቅስቀሳ የሚመስለውን አቀራረባቸውን ስሰማ ነው ፡፡ ጠ/ / ሩ ተመሳሳይ በሆነ አጀንዳ ላይ በአፋን ኦሮሞ ሲሆን ሌላ ነገር ባፋን አማሪፋ ሲሆን ሌላ ነገር ይናገራሉ ሲባል እሰማ ነበር፡፡ እንደ ባሌው ግን ፈጦ የወጣ አልሰማሁም፡፡ እደምራችኋለሁ፣ አሸጋግርራችኋለሁ፣ ድልድይ እሆንላችኋለሁ ሲሉን የነበሩት መሪያችን ባሌ ላይ የሰበሩንን ሰብረናል፣ እንደ ዝሆን ደፍጠጠናል ፣ እያሉ ሰፎክሩ ጆን ክሬስ ዌል ትዝ አለኝ፡፡

ብልጽግና ፓርቲ አይደለም ለኢትዮጵያ ለፓን አፍሪካንዚም ( Pan- Africanism) ጥንስስ ነው ሲሉን የነበሩት መሪያችን ብልጽግና የኦሮሞ ሀብት ፣ የኦሮሞ ታቦት ነው ብለውት አረፉ፡፡ ታማኝነት ከንግግር ይጀምራል ይህን የሳይንቲስቶቹን አባባል ያገሬ ገበሬ ቀልል ባለ አማርኛ "መታመን በከንፈር" ሲል ይገለጸዋል፡፡ ሌላው ይበልጡኑ ያስድመመኝ ጉዳይ ደግሞ በል ሲላቸው እንደ ፓስተርም እንደ ቄስም የሚያደርጋቸው መሪያችን እንኳን ሰው ዳማ ከሴንና ጠጅ ሳርን, አርቲንና በሶ ብላን አዋህጄ ተፈጥሮን አንድ አደርጋለሁ የሚሉን ሰው ከሳቸው ባመለካከት የተለዩትን " ጠላቶቻችን" እያሉ ሲገልጹ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሁን በኋላ ባስተሳሰብ ልዩነት ምክንያት የሚሰደድም የሚያሳድድም የለም፣ መግደል መሸነፍ ነው፣ የሚሉን ወርቃማ አባባሎች ጊዜ መግዣ እንጂ የሳቸው እምነት እንዳልሆነ ገባኝ፡፡

እንግዲ ከሳቸው እምነትና አስተሳሰብ ውጭ የሆነውን እንዴ እንደ ሚዳቋ እዚህም እዛም የሚዘሉትን እንሳያችዋለን ሲሉ ፣ በሌላ ጊዜ ደግሞ እሳቸው ኢህአደግ የሚባለው ድርጅት ውስጥ እንዳልነበሩና የነበረውን ስርአት አይተውና ሰምተውት እንደማያውቁት በሚያሳብቅ ስሜት "ባለፉት 27 አመት ሲገድሉን ከነበሩት ጠላቶቻችን ጋር ደግመን አንሰራም" ሲሉን ማንን ለእርድ አቅርበው ማንን እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንጽሁ ነኝ ለማለት እንደፈለጉ ለመረዳት ተመራማሪ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ለመሆኑ ግን ሰሞኑን የወጣው የጥላቻ ንግግር ህግ የሶሻል ሚዲያን ተሳታፊዎችን ብቻ ነው የሚመለከተው ወይንስ መሪዎች ተመሳሳይ መልክት ሲያስተላላፉ እነሱ ላይ አይሰራም??

በፍቅር እስከ መቃብር መጽሃፍ ላይ ፍቅረኛውን የተቀማው በዛብህ ብሶቱን ለሰብለ ወንጌል ሲገልጽላትና ያባቷን የፊታውራሪ መሸሻ ጨካኝነትና የሱን አቅመ ደካማነት ሲያሳያት ዳሩ ዳኛ የለም ልተ ወው ግድ የለም የሚል በትካዜና በቁጭት ስሜቱን የገለጸበትን ሃረግ እናገኛለን፡፡ እንደኔ ግምት የጠ ሩ ዳኛ ሊሆን የሚገባው ፓርላማው ነበር፡፡ ፓርላማው ለቆመለት ህዝባዊና አገራዊ አላማ ታማኝ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ አንዲት ጥያቄ በህዝብና ባገር ስም ያቀርባል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሀውም

" የተከበሩ ጠ/ / ር ሆይ እንኳን ጥያቄአችንን ለመመለስ ወደ ተከበረው ምክር ቤት እንኳን በደህና መጡልን በሚል ሟሟሻ ይጀምሩና ሰሞኑን እዚህ እኛ እጋ መጥተው ህወሓትን በተመለከተ ከህወሓት ጋር በሃሳብ ብንለያይም ህወሓት በህዝብ ስለተመረጠ የትግራይ ህዝብ በፌዴራሉ ውስጥ ማግኘት ያለብትን መብትና ጥቅም እንዲሁም ሀገራዊ ጉዳዮችን በሚመለከት ከህወሓት ጋራ መስራት ግዴታችን ነው ብለውን ሲያበቁ ባሌ ሶፈመር ዋሻ ሲሄዱ ምን ውቃቢ ቢይዞት ነው ከህወሓት ጋር በጭራሽ አንሰራም ጠላቶቻችን ናቸው ዝሆን ሆነን ዝሆን አክለን ረጋግጠናቸዋል ያሉት? ወይ እኛን ዋሽተዋል ወይንም የባሌን ህዝብ ዋሽተዋል ፣ እውነቱ የቱ ነው?? ብሎ ጠ/ / ሩን በጥያቄ የሚያፋጥጥ ከመደመር ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ ያገርና የህዝብ ሃላፊነት የሚያሳስበው የተወካዮች ምክር ቤት አባል ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ በዛብህ ዳሩ ዳኛ የለውም ልተወው ግድ የለም ብሎ ይሄን ጉዳይ ለፈጣሪ ካልተወው በስተቀር፡፡

የዛሬን አያደርገውና ክቡር ጠ/ /ሩ ባገሪቱ ትላልቅ ሚዲያዎች ላይ እየቀረቡ በሚያማምሩ አበቦች መሃል በተሰካኩ ማይክራፎኖች ተከበው " የጉግ ማንጉግ ዘመን አልፎ የብርሃን ዘመን መጥቷል ይሉን ነበር ከእንግዲህ በኋላ የምንፋለመው በጠመንጃ ሳይሆን በወረቀትና በኢስክሪብቶ ነው " እያሉ ፍቅር የናፈቀውን ልባችንን አሸፍተውት ነበር፣ ታዲያ ዛሬ 180 ድግሪ ዞረው ከሳቸው እምነትና አመለካከት ጋር የማይስማማውን እንደ ሚዘል ሚዳቋ መመስል ወይንም እንደ ደመኛ አባት ገዳይ በ ማየት ከነሱ ጋራ አንሰራም ሲሉ የኚህ ሰው ታማኝነት ለራሳቸው የፖሎቲካ ጥቅም ነው ወይስ ለሀገርና ለህዝብ ነው ብሎ መጠየቅ የሀቀኛ ዜጎች ግዴታና ሀላፊነት ይመስለኛል፡፡ ዲሞክራሲ እኮ የምትፈልገውን የሙዚቃ ምርጫ ብቻ እየመረጥክ የምትሰማበት የዘፈን ምርጫ ክፍለ ጊዜ አይደለም፡፡ አገር የምትደነው የተለየ የፖሎቲካ እምነትና አስተሳሰብ ያለውን እንደ ደመኛ ጠላት አድርጎ በማየት ጦር አዝምትበት፣ መብራት ቁርጥበት በጀት ቀንስበት እያሉ በመፎከርና በማስፎከር ሳይሆን ሁሉንም አስተሳሰቦች ጠረጴዛ ላይ በማምጣት ፍርዱን ህዝብ እንዲሰጥ እድል ስንዲሰጠው ሲደረግ ብቻ ነው፡፡ ዲክታተሮች በመሳሪያ ብዛት ስልጣናቸውን እንዳላቆዩ ማወቅ ካለፉ መሪዎች በመማር ተመሳሳይ ስህተት በራሳችን ላይ እንዳንሰራ መማሪያ ሊሆነን ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከላይ የጠቀስነውን አይነት የፖሎቲካ ትግስት እንደሌላቸው የሶፎመር ዋሻ ንግግራቸው ጥሩ ማሳያቸው ሆኗል፡፡የሰበሩንን ሰበርናል ፣ ያዋረዱንን አዋርደናል እኛ ሳንፈቅድ ማንም ወደኛ ክልል እንዲመጣ አናደርግም እያሉ ኢጆሌ ባሌን ሲያስጨበጭቡ በመደመር ውስጥ ፍቅር አለ, በመደመር ውስጥ ይቅርታ አለ በሚል ልክፍት የተያዙ ወዳጆቼ ምን ሊሉ እንደሚችሉ እመቤታችን ትወቅ፡፡ አንድ እውነት ግን አለ ፡፡ ላቅመ አዳም መድረስ ላቅመ ፖሎቲካ መድረስን አያመለክትም፡፡ አሁን አሁን ግልጽ ሆኖ እንደሚታየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስልጣናቸውና በጥቅማቸው ላይ የሚመጣ ወይንም እሳቸው ከወለዱት የብልጽግና ፓርቲ የተለየ አመለካከት ያለው ድርጅት ከውጭ ሃይሎች ጋርም በመደራደር ለማስመታት የማይመለሱ መሆናቸውን በቅርቡ ከሰማነው ከኤርትራው መሪ ጋዜጣዊ መግለጫ መረዳት ይቻላል፡፡ የሁለቱ ሰዎች ፍቅር የሚጀምረው ካገርና ከህዝብ ፍቅር በመነጨ ሳይሆን የሁለታችንንም የጋራ ጠላት ለመምታት ባንድ ላይ እንስራ የሚል ምክረ ሃሳብ ( deal) እንደሆነ ለ መገንዘብ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ለማስረጃም ያህል ምርጫ የሚባል ነገር ሰምታ እንጂ አይታ የማታውቀው ሀገር መሪ " ኢትዮጵያ ምርጫ አያስፈልጋትም፣ የፌዴራሊዝም ስርአት ለኢትዮጵያ አይበጃትም" የሚለው አባባላቸው ለዶክተር አቢይ እጅ ስጡ፣ እሷቸው እንደጀመሩ ይጨርሷችሁ ብልጽግና ፓርቲን ሳትከራከሩ ተቀበሉት የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ስለመሆኑ ሁለቴም ማሰብ አያስፈልግም፡፡ ለዞህም ውለታቸው በትግራይ ያሉ የኤርትራ ስደተኞች ወደ ሌላ ክልል ( //) እንደፈለጉ ወደሚያሽከረኩሯቸው ክልሎች እንዲዛወሩና የትግራይን ህዝብንና ህወሓትን ለመለያየት ኢትዮጵያውያን ባንድ ላይ ተቃቀፈን የወደቅንበትን የባድመን ክልል ላቶ ኢሳያስ በስጦታ መልክ ለመስጠት እየተነጋገሩ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች እየተናገሩ ነው፡፡ በትግራይ ክልል ያሉ ኤርትራውያን ትግራይ ውስጥ እስካሉ ድርስ ላቶ ኢሳያስ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ስለሚሆኑና የትግራይ ክልልና ህዝብ አሳልፎ እንደማይሰጣቸው ስለተገነዘቡ ይሄ ስደተኛ ወጣት አንድ ቀን እንደ ማእበል ተነስቶ ይጠርገኛል የሚል ስጋት አላቸው፡፡ ይሄን መቅረፍ የሚችሉት ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ እንደ መናጆ ከላይ ሆነው የሚመሩት ክልል ውስጥ ከሆኑላቸው ራሳቸው አቶ ኢሳያስ እንደ በሚልኳቸው ደህነነቶች ዋናዎቹን የስደተኞች መሪዎች እያፈኑ ለመያዝ እንደሆነ መረጃዎች በስፋት እየናኙ ነው፡፡

ለማጠቃለል ያህል ኢትዮጵያ ሀገራችን ካለችበት ምስቅልቅል ወጥታ ህግና ስርአት ወዳለው መንገድ እንድትሄድ ፍትሃዊና ነጻ ምርጫ ተካሂዶ የተለያየ እምነትና አስተሳብ ያላቸው ፓርቲዎችና ግለሰስቦች ወደፓርላማ የሚገቡበት መንገድ እንዲመቻች ለዚህም ምርጫ ቦርድ ከፓርቲ ታማኝነት ወጥቶ ለህዝብና ላገር ታማኝ መሆን ሲጅመርና ትውልድ የማያስወቅሰውን ስራ ሲሰራና ፓርላማውም ያገሪቱን ህግ በማውጣትና በማስፈጸም ላይ ስልጣን እንዲኖረው ( ኢምፓወር) ሲደረግና የግለሰቦችን ወይንም የፓርቲ አመለካከቶችን ሳይሆን የመቶ አስር ሚሊዮን ህዝብ አመለካከትን ለማስተናገድ በሚችልበት ቁመና ላይ ሲገኝ ብቻ መሆኑን ልናስብበትና ልናተኩርበት ይገባል፡፡ አሁን እንደሚታየው ጉዳያችን ሁሉ ለብልጽግና ፓርቲ ወይንም ላንድ ግለሰብ አሳልፎ መስጠት አገራችንን ከነገበናዋ Amazon.com ላይ እያወጣነው እንደሆነ ለማወቅ አስማተኛ መሆን አያስፈልግም፡፡ አገር ያንድ ግለሰብ ሳትሆን የህዝብ ናት ፡፡ ግለሰቦች ላይ ከመስራት (invest) ከማድረግ ) ተቋማት ወይንም Instiution ላይ invest በማድረግ አገርን ማዳን ይቻላል፡፡ " እኛ ኢትዮጵያውያን ስንኖር ኢትዮጵያውያን ነን ስንሞት ኢትዮጵያን ነን " ማለትና "የሰበሩንን ሰብረናቸዋል !!" ማለት የሰማይና የምድር ልዩነት አላቸው፡፡ ጆን ክሬስ ዌል እንዳለው " በምትመራው ህዝብ ዘንድ ታማኝነትህን (Trust) ካጣህ ታላቁን የመሪነት ስብእናህን ተነጥቅሃል" ይላል፡፡ ቸር ሰንብቱ፡፡

አቤነዘር ነኝ ከሰሜን አሜሪካ፡፡

 

Back to Front Page