Back to Front Page

27ቱ፣ 2ቱ እና 5ቱ

27ቱ፣ 2ቱ እና 5

ዳደ ደስታ

05-17-20

አሁን ኢህአዴግ ላይመለስ ባጭሩ ተቀጭቷል። የተቀጨውም 27ኛውን ግንቦት-20 ማክበር ሳይችል በኢህአዴጉ ጥልቅ-ፈጣን ተሃድሶ ማግስት ነው። 2ቱ ዓመታት ኢትዮጵያ በአንድ ጊዜ ወደ ሁሉም አቅጣጫ ለመጓዝ የሞከረችበት መደመር የተሰኘ የመደናበር ረዥም ዘመን ነበር። ቀጣዮቹ 5 ዓመታት ከፊታችን አሉ። በአገር ደረጃ ከተስፋ ይልቅ አደጋ ያጠላባቸው ስለመሆኑ በግልጽ ይታያል።

አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ሰዎችና ቡድኖች ኢህአዴግን በጦርነት አሸንፈውና ደምስሰው መምጣት የነበረባቸው ይመስላል። ምክንያቱም ምናቸውም ኢህአዴግ አይመስልም። በጦርነት አለመምጣታቸው ነው እንጂ ኢህአዴግንም አፍርሰውታል። ማፍረስ ከመደምሰስ በምን ያህል እንደሚለይ አላውቅም። ይህን የአመራር ቡድን የሚገልጸው አንድ ቃል ካለ አፍቅሮተ ስልጣን ነው። እዛ ቤት ስልጣን የላቀ ዓላማ ለማስፈጸም የሚፈለግ ሁኔታ ሳይሆን በራሱ የመጨረሻ ግብ ነው። ለዚያ ሲባል ህግ መጣስ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ይጣሳል። ተቋማትና ሹመቶች መሰረዝ፣ መደለዝ፣ መበወዝ ከጠየቀም እንዲሁ። ኢህአዴግን ማወደስ፣ ኢህአዴግን ማውገዝ፣ ሁለቱም እያቀያየሩ መጠቀም ምንም ነውር የለውም። አመራሩ ኢህአዴግን መሆን ችሏል፣ ኢህአዴግንም መግደል ችሏል። ስለዚህ የሽግግር መንግስት ይቋቋም የሚሉትን ዝም ለማሰኘት እኛ ሪፎርም እንጂ አብዮት አላመጣንም ሲሉ የኢህአዴግ አስተሳሰብና ሌጋሲ ወረሾችን ዝም ለማሰኘት ሲፈለግ ደግሞ በናንተ ስርአት ጊዜ፣ የጨለማው ጊዜ፣ የመንግስት አሸባሪነት ጊዜ፣ የጥፍር ነቀላ ጊዜ እያሉ ይገልጹታል።

Videos From Around The World

በአገራችን በዚህ ፋርሳዊ ትእይንት የማይጠገኑ ስንጥቃቶች እተፈጠሩና እየሰፉ መሄዳቸው እርግጥ ነው። አገር የሚፈርሰው መጀመሪያ የዜጎች ጭንቅላት ላይ ነው። ከዚያም ጠላት ከግራም ከቀኝም ስንጥቆቹን በማስፋትና በመቦርቦር ላይ ይዘምትበታል። ለወትሮው ይህን መከላከል ማየትና መከላከል የሚችሉት አገር ወዳድ ምሁራንና አርበኛ ልሂቃን ነበሩ። አሁን የት እንዳሉ ኣይታወቅም። የዋልያ ዝርያን ቀድመው ከምድረ ገጽ ጠፍተውም ከሆነ የነገረን የለም። ለምሳሌ ዛሬ ስለ ህገመንግስታዊ ትርጉም ሞያዊ አስተያየት እንዲሰጡ የተጠየቁት የህግ ምሁራን ያሳዩን ቁምነገር የፋርሱና ትራጀዲው ትእይንት አካል መሆናቸውን ነው። የኮቪድ ወረረሽን በምርጫ ወቅት ተከስቶ መደበኛውን የምርጫ ሥራ ስላስተጓጎለ እና መቀየር የነበረበት መንግስት መቆየት ስላለበት ለዚህ ሲባል ህገመንግስቱን መተርጎም የተሻለ መፍትሄ ነው ሲሉ አስረግጠው ተናግረዋል። በኋላ ስንሰማ እነዚህ ሰዎች ነበረ አራቱን አማራጮች አጥንተውና የተሻለው አራተኛው ማለትም ህገመንግስቱን ተርጉሞ የፓርቲ ስልጣን ማስረዘም የተሻለ መሆኑን ሃሳብ ያቀረቡት እነዚሁ የህግ ምሁራን ነበሩ። በፊት በር፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህገመንግስትና ህገመንግስታዊነት ጥርሳቸውን የነቀሉ ብቁ ተመራማሪዎች ያቀረቡት ጥናት ነው በሚል አንቆለጳጰሱዋቸው። እነዚሁኑ ምሁራን በጓሮ በር በኩል ተመልሰው ይኸው ጥናት ምን ያህል ህገመንግስታዊና የተሻለ እንደሆነ የነጻ ሞያተኛ ምስክርነት ሰጡ።

የሚገርመው ደግሞ የሰጡት ምስክርነት ይዘት ነው። ለስማቸውም አልተጨነቁም። የኮቪድ 19 ወረረሽኝ ምርጫቸውን እንዲያስተላልፉ ስለተገደዱት አገሮች ሲነግሩን ላለማስተላለፍ ወስነው ኮቪድን እየተከላከሉ ምርጫንም ለማካሄድ የውሰኑ ብዙ አገሮች እንዳሉ ግን አይነግሩንም። እዚሁ ቅርባችን ያለች ማላዊ እንኳን ምርጫዋን ልታራዝም አይደለም ቀድሞ እንዲደረግ ብላ ከነሃሴ ወደ ሃምሌ አመጣችው። እነዚህ የህግ አዋቂዎች ይህንን አይነግሩንም። ብዙ አገሮች ምርጫቸውን አልሰረዙም፣ አላራዘሙም። ያራዘሙትም አብዛኞቹ መጋቢት-ሚያዝያና-ግንቦት ሊደረግ የነበሩት ብች ናቸው። እንደውም አንዳንዶቹ 2 እና 3 ወራት ቆይቶ በዚሁ ክረምት እንዲደረግ ነው ቀን የቆረጡት። የኛ ምርጫ ለነሃሴ መጨረሻ ነበር ሊደረግ የታቀደው። የነሃሴ ምርጫ ለማራዘም የወሰነች አገር እስከ አሁን የለችም። የህግ አዋቂዎቹ ስለነዚህ ለምን አልነገሩንም? አንዷ የአጣሪው ጉባኤ አባል ለመሆኑ በኮሮና ምክንያት ለምን ያህል ጊዜ ነው ምርጫው የሚራዘመው? የሚል ጥያቄ ታቀርባለች። ከህግ ምሁሩ የተሰጣት መልስ ይህ የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ግምገማ የሚወሰን ነው የሚል ነው። ይኼ ምክንያታዊ መልስ ይመስላል። ነገር ግን ከመስከረም በኋላ በኮሮና ሰበብ ስልጣን ለማራዘም ሲፈለግ የጤና ባለሙያዎች አስተያየት አልተጠየቁም። መቸም ስልጣን ለማራዘም ግልጽ ድንጋጌና ገደብ በትርጉም ለመቀየር ማሰብ አስገራሚ ድራማ ነው። የትርጉም ጥያቄ ያቀረበው የማይመለከተው የማይገባው የተወካዮች ም/ቤት መሆኑ ደግሞ አስገራሚ ነው። መጪዎቹ 5 ዓመታት ካሁኑ ታውከዋል።

ውሸት ትርክት በዝቶና ተደራርቶ መለየት እስኪያስቸግር ሆኗል። እንደቀልድ የተዘሩ ውሸቶች አሁን ጎምርተው ማህበረሰባችንን በክለውታል። በሚድያ መድረኮች ዋናውን የአየር ሰአት በሰፊው የያዙት የውሸት ታሪኮች ናቸው። ይህ ማለት በቤተሰብ ደረጃ ጥዋት በቁርስ ሰዓት የሚወራው ነገር ከውሸት የጸዳ የመሆን አነስተኛ ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ራሱ ይጎመዝዛል። የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት መምህር ከተማሪዎቹ ጋር የሚያወራውስ ምን ያህል ንጹህና እውነት ይሆን? በአብያተ እምነቶች በመንፈስ አባቶችና አማኞች መካከል ያለው ነገርስ? የኢትዮጵያ ትንሳኤ የፈነጠቀበትን ዘመን የጭለማ ዘመን እየተባለ በአደባባይ ያለ ሃፍረት ሲዋሽ እንዴት አልከበደም? ባይ ባይጠፋ እንዴት የሚገስጽ አዋቂ፣ ምሁር፣ አባት፣ አገር ወዳድ፣ ወዘተ ይጠፋል? 27 ዓመት የኢትዮጵያውያን አማካይ የህይወት ዕድሜ ከ42 ዓመት ወደ 68 ከፍ በሏል፣ በነፍስወከፍ አማካይ ዓመታዊ ገቢ (per capita) 100 ዶላር ወደ 2200 ዶላር አድጓል። ይኸ ከተአምር የሚቆጠር ልዩነት አይደለምን?

2 ዓመታት በፊት ሁለት ትልልቅ የየ5 ዓመታት ግዙፍ አገራዊ የትራንስፎርሚሽን መርሃ-ግብሮች ነበሩን። ከ2 ዓመታት በፊት የመጀመሪያው የ15 ዓመት የሚሌኔም ግቦች አብዛኞቹን አሳክተን፣ ሁለተኛውን የ15 ዓመት የዘላቂ ልማት ግቦች መርሃ-ግብር ለማስጀመር እያሟሟቅን ነበር። የህዝብ ቁጥር ዕድገታችን በጣም ፈጣን ቢሆንም ዕድገታችንም እጅግ ፈጣን ስለነበር ድህነት በአጭር ጊዜ ከነበረው በግማሽ ቀንሶ ወደ መካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመግባት እየተንደረደርን ነበር። የምስራቅ አፍሪቃ ትልቁ ኢኮኖሚ የመባል ወግና መዓርግ ከኬንያ ነጥቀንም ነበረ።

የዘመናት የትውልዶች ግዙፍ ህልም ስኬት ትእምርት የሆነውን የአባይ ግድብም አስጀምረን፣ አጋምሰናል። እጅግ ብዙ የተገባደዱ እና የተጀመሩ አገራዊ ሜጋ ፕሮጀክቶች ነበሩን። የግል ሳይጨምር 50 ዩኒቨርሲቲዎች! እነ ጋምቤላ፣ አሶሳ፣ ጅግጅጋ፣ ሰመራም ባለ ይኒቨርሲት ከተሞች ሆኑ። የአዲስ አበባ ቀላልና ወደ ጂቡቲ ዘመናዊ የባቡር መስመሮች! ይኸ ሁሉ ለትንግርት የሚበቃ ስኬት ነበር/ነው። የግል ኢንቨስትመንትም በጥይት ፍጥነት እያደገ ነበር። ኢህአዴግ በእርሻና በአነስተኛ ይዞታ የነበረውን ሃብት ለኢንዱስትሪ ሽግግር ለማመቻቸት ሲባል ወደ አንድ ማእከል እንዲሰብሰብ በማድረጉ ከ70% በላይ የአገሪቱ ኢንቨስትመንት ፍሰት በአዲስ አበባና ኦሮሚያ ላይ እንዲከማች ማድረጉ አሁን ሲታይ ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል። እንዲያም ሆኖ ግን በቂ አልነበረም። ወጣቶች ከዚያ በላይ ይጠብቁ ነበር። ዜጎች በሙስናና ብልሹ አስተዳደር እየተማረሩ ነበር።

በእርግጥ ዴሞክራሲያችንና መልካም አስተዳደራችን ከ2 ዓመታት በፊትም እዩልኝ፣ መስክሩልኝ የሚያሰኝ አልነበረም። ለምሳሌ ኢህአዴግ እየተበላሸ በሄደበት ጊዜ 100% አሸናፊ ሆኖ የወጣበት ጊዜ በጣም አሸማቃቂ ነበር። ግን ሰው በሰላም ወጥቶ መግባት፣ አገር ውስጥ የትም ሄዶ መመለስ ያሰጋበት ጊዜ አልነበረም። ተማሪ ሴቶች ወጥተው ጠፍተው ሊቀሩ? አይታሰብም። ህገ-መንግስቱ በግላጭ በሚጠሉት መሪዎች እጅ ወድቆ አልታየም። ምርጫም ተስተጓጉሎ አያውቅም። ቅንጅት አገር ሙሉ ካልሆነ አዲስ አበባ ብቻ አልረከብም ብሎ፣ በየምርጫ ጣብያው ለህዝብ ተወካይነት ያሸነፉ ተመራጮቹ ፓርላማ አንገባም ብለው አዲስ አበባ እንዲረክቡ፣ ፓርላማም እንዲገቡ ገዢ ፓርቲ አኩራፊ አሸናፊዎቹን የሚያግባባበት ጊዜም አየን። ቅንጅት አዲስ አበባን አልረከብም ሲል እንግዲያው የአዲስ አበባ ህዝብ ባልመረጣቸው ሰዎች ከሚተዳደር የሞግዚት አስተዳደር ይደራጅ ተብሎ ተወሰነ። አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ሲተያይ ውሳኔውም መንፈሱም ለየቅል ነው። ሃገርም በዚህ ደረጃ ከህገመንግስታዊ ምህዋር ወጥታ አታውቅም። ህገ መንግስት፣ ስልጣን ለማስቀጠል ይተረጎም ዘንድ ሃሳብ ቀርቦ፣ ትርጉም የመጠየቅ ፈጽሞ ስልጣን የሌለው ፓርላማ ሲጠይቅ እንታዘባለን ብሎ ያሰበ የለም።

በአካባቢያችን ተጽእኖ ፈጣሪነታችን እየደመቀ ነበር። መጀመሪያ የውስጣችን ሰላም መገኘቱ ነበር ዋናው ውሳኝ ቁም ነገር። በነገራችን ላይ በሁለት መቶ ዓመታት ታሪኳ ውስጥ ኢትዮጵያ የተጎናፀፈችው ረዥሙ የውስጥ ሰላምና እፎይታ ያለፈው የኢህአዴግ ዘመን ነበር። ይኸም ታሪክ ስለሆነ ተመዝግቦ ይቀመጥ። ከዚሁ የተነሳ አካባቢያችን ወደ አንድ የልማትና የንግድ ቀጠና ለማስተሳሰር የሚያስችሉ ግዙፋን ፕሮጀችቶች እየታሰቡ ነበር። በ23 ቢልዮን ኢትዮጵያ፣ ጂቡቲይንና ኬንያን ለማስተሳሰር ተወጥኖ የነበረው እጅግ መጠነ-ሰፊ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክት ምራቃችን ውጠን ቀረን ማለት ነው። የሰላም ጠባቂ ኃይል ሲፈለግ በክብር እየተጋበዝን እንሰማራ ነበር። በቡድን 20 እና ቡድን 7ት ስብሰባዎችም እንጋበዝ ነበር። በአየር ንብረት ድርድሮች ላይ የአፍሪካ ድምጽ መሆን ጀምረን ነበር። በቀጠናችንም በዓለምም መድረኮች አዘቅዝቀው ሳይሆን አንጋጠው የሚመለከቱን እየበዙ ነበር። አሁን ሌላውን ሁሉ አራግፈን ኤርትራን ይዘናል። እርማት፡ የኤርትራን መሪ ይዘናል። እሳቸውም ቢሆኑ፣ ትልቅ አገርን የመዘወር የቆየ ኣምሮታቸው በኛ ቢወጡ አይፈረድባቸውም።

ከአያያዝ ይቀደዳል እንዲሉ፣ መልካሟን አጋራችን ሱዳንን እንዴት ወደ ግብጽ እቅፍ እንደገፈተርናት ግልጽ ማሳያ ናት። የኢትዮጵያ አስተማማኝ ደጋፊና ጥሩ ጎረቤት መሆኗ በቁርጥ መድረኮች ሳይቀር አሳይታናለች። አሁን ሰርግና ምላሽ የገቡልን የመሰሉን ኤሜሬትና ሳውዲ በዓረብ ሊግ መድረክ በግልጽ ኢትዮጵያን አይንሽ ላፈር በማለት ግብጽን በሙሉ ድምጽ ደግፈው ቆመዋ

። ዓረብ ያልሆኑት የሊጉ አባላት ጅቡቲይን የመሰሉ ጎረቤቶቻችን ጭምር ለመጀምሪያ ጊዜ ግብጽን ደግፈው የኢትዮጵያ መብትና ጥቅምን የሚያሳጣ አቋም ይዘው ተሰተውለዋል። ይኸም ከአያያዛችን የተቀደደ ጉርብትናና ወዳጅነት ነው። ሱዳኖች ግን በዚያ መድረክም፣ በዋሽንግተኑ የትራምፕ ድፍጠጣም እጅ ሳይሰጡ ጸንተው ደግፈውናል። በርግጥ አሁን ፊታቸውን አዙረዋል። ይኽም ራሱ ከአያያዛችን የመጣ ነው። የቀጠናችን ስበትና የቡድን 7 መድረክ ተጋሪዎች የነበርን፣ ኢጋድን ለኢሳያስ ሰውተን አሁን ውሏችን ከኢሳያስና ከፋርማጆ መሆኑ ድንቃድንቅ ውድቀት ነው።

ግን፣ ግን፣ ከሽንበቆ ወደ ሙቀጫነት ተቀይረን በብርሃን ፍጥነት ቁልቁል እንድንከባለል የሆንነው የቱ ጋር በሰራነው ስህተት ነው? የለውጡን አስፈላጊነት ለማስረገጥ ሲባል የጅምላና ውሸት እርግማን እንዲበዛ ተሰራ። አሁን ድረስ ይኸኮ ያው የድሮው ኢህአዴግ ነው ይባላል። አሁን እስቲ ይኸ ስርዓት ምኑ ነው ኢህአዴግ የመሰለው? DNAው ተመርምሮ ነው? አብዮታዊ ዲሞክራሲ አለ? ልማታዊ መንግስት አለ? እርሻ፣ ገበሬና ገጠር ላይ ትኩረት የሚያደርግ አመራር ነው? የፋይናንስ የቴሌኮም ሴክተሮች ለውጭ እንዳይበረገዱ የሚከላከል አመራር ነው? ኢጋድንና የአፍሪካ አንድነትን የሚያከብርና ከነሱ ጋር የሚሰራ መንግስት ነው? የመሰረተ ልማት ላይ መጠነ-ሰፊ ኢንቨስትመንት ስለማድረግ የሚገደው መንግስት ሆኖ ነው? ብሄርሰባዊ ፈደራሊዝም የሚያቀነቅን አመራር ነውን? ግንቦት 20ን ለማክበር የሚጠየፍ አመራር አይደለምን? የምናውቀው ኢህአዴግ ስለ ቤተመንግስት ዕድሳትና ስለ ዱባይ ማሸብረቅ ሲያወጋ ይነጋበታል? በእውነት ኢህአዴግ ምን እንደሚመስል በዚህ ፍጥነት ረሳነው ማለት ነው?

መደንቆርና አጉል ብልጠት በዝቷል። ድንቁርና የሆነው እንደ አገርና ህዝብ ተደምሮና ተዋራርዶ ውርደትና ኪሳራ ምንም ፋይዳ የሌለው በመሆኑ ነው። ብልጠት የመሰለው ደግሞ ታክቲክ የበዛበት አሰላለፍና ጨዋታ ገዢ ባህርይ ሆኖ መታየቱ ነው። ምክንያት የለሽ ጥላቻ ቂም የሰው አፀደ ስጋ መንፈስ የተቆጣጠረበት ዘመን ሆኗል። የወያኔ ሁለት ዓይኑ ይጥፋልኝ እንጂ የኔ አንድ አይን ቢፈስ ግድ የለኝም የሚል ጉደኛ ልሂቅና ሚድያ፣ 3 አይኖች ለከንቱ ለማባከን ቆርጦና ፈቅዶ የሚጠባበቅ ተስፈኛ ፖለቲከኛ የበዛ መሆኑ በጣም ያሳስባል። ደግሞ፣ ውጤቱን አይቶና ገምቶ እንኳን ቆም ብሎ ለማሰብ አይሞክርም። አሁንም ድረስ ወያኔ ዘረፈ ይላል። ዘራፊዎች የተባሉት በዱባይ፣ ባንኮክ፣ ወይም በአውሮፓ ከተሞች የሚዝናኑ ቱጃሮች መሆን አያሰኛቸውም? ወይም ትግራይ በብዙ ኢንቨስትሜንትና የመዋእለ ንዋይ ፍሰት ተጥለቅልቃ እናያት አልነበረብንምን?

ይኸን ገለባን ከፍሬ፣ ውሸትና ሃቅ፣ ማስመስልና መሆን፣ ውጤትና ምኞት፣ ቃልና ውሎ እየለየ መሄድ ያልቻለ አገርና ትውልድ ምሱ ውድቀትና ውርደት ከመሆን አይድንም። ይህን ያስተዋለ ጠላትም ይበልጥ ይጎዘጎዛል፣ ይገዘግዛል። ቁልቁለቱን በደንብ ልጨምራላቹህ፣ የሚለን ኃይል ሲመጣም ወጊድ ማለት አንችልም። ጊዜ ጨምሩልኝ ስንባልም ጆሮና ልብ እንሰጣለን። ምን ይታወቃል- ተጨማሪ ጊዜም እንሰጥ ይሆናል። እንደ ወንዞቻችን ቁልቁለት ቁልቁለቱን እየመረጥን እንሄዳለን። እንደ ወንዞቻችን በጀመርነው መንገድ ቁልቁል መፍሰስ እንጂ መቆም ወይም ሽቅብ መመለስ አይሆንልንም። መባነን የሌለበት መክሸፍ እንዲህ ነው። ፍሬውን ትቶ ገለባን መናፈቅ! ህጻኑን ከነታጠበበት ውሃ መድፋት!

ከዊንስተል ቸርችል በፊት የነበሩት የብሪጣንያ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ ኔቫይ ቻምበርሊን የሂትለር ተስፋፊና ወራሪ ውሳኔ ላይ ያሳዩት ተቅለሽላሽ አቋም Appeasement ነው የሚባለው። ቼክን ልወራት ነው ሲል ሂትለር ቻምበርሊን ፈቀዱ። በድርጎ አቅራቢነት የሚዘለቅ ነገር ግን አልነበረም። አንድ ጸሃፊ ሁኔታውን እንዲህ ነበር የገለጸው፣ ታላቋ ብሪጣንያ በውርደት ዋጋ ጦርነትን ለመሸሽ መረጠች፣ ነገር ግን ሁለቱም አልቀረላትም፣ ጦርነቱንም ውርደቱንም ታቀፈች! ብሪጣንያ አሁን ውግያ ላይ ሆኜ መንግስት መቀየር አልችልም ብትልና፣ የቻምበርሊንን የስልጣን ዕድሜ አራዝማ ቢሆን ውርደቱም ጦርነትም እጅግ የረዘመ፣ ምናልባትም ከዚያ በላይ የሆነ ኪሳራ ተከናንባና የታሪኳ ጠባሳ አትማ ትዘልቀው ነበር። በጦርነቱ መሃል ቸርችል መጣና ሁኔታውን ቀየረው። ብሪጣንያም አንገቷን ከመድፋት ተረፈች። ለአውሮጳም ተረፈች።

የኮሮና ውግያ ወደ ድል የሚቀየረው፣ የአባይ ፍልሚያም ሚዛኑን ማስቀየር የሚቻለው የዘመናችን ቻምበርለይኖች ከአመራር መድረክ ገለል ሲሉ ነው። የቁልቁለቱን ጉዞ መግታት እና ፊታችን መልሰን የዳገቱን የምንጀምረው ልባም፣ ብልህና ባለራእይ ሰው ሲመራንና ሲያስተባብረን ነው። ለኮቪድም ለሌላውም የሚያሻግረን ሁነኛ ሰው መፈለግ አለብን። የአሁኖቹ የሚችሉትን አድረገዋል። ቤተ መንግስቱን አድሰዋል። የማይችሉትን ሃላፊነት አንጫንባቸው። የኛንም የነሱንም ሽክም የምናወርድበት ፍቱን መድሃኒት ምርጫ ነው። ይህን የመድሃኒት ቀን አርቀን በመግፋት ህመማችንን አናራዝመው። ከሁሉ በላይ አድካሚና ከንቱ ልፋት ውሸትን ወደ እውነት ለመቀየር የሚኬደው መንገድ ነው። ውሸት መቼም እውነት ስለማይሆን ልፋቱን ፍሬ-አልባና ዘለአለማዊ ያደርገዋል። እውነቱን፣ እውነት፣ ውሸቱን ውሸት ማለት መቻል ራሱ ትልቅ መነሻ ነው። ከዚያ በኋላ ጥያቄው ቀላል ነው፡ greater good for the greater number ለበለጠው ጥቅምና ለበዛው ተጠቃሚ የትኛው መንገድ ይሻላል? የሚለው ይሆናል።~/~

 

Back to Front Page