Back to Front Page


Share This Article!
Share
እውነት እነበረከት በአፈርሳታ (አውጫጭኝ) ላይ ከተመሰረተ የደቦ ፍርድ ነፃ የሆነ ፍትህ ያገኙ ይሆን?

እውነት እነበረከት በአፈርሳታ (አውጫጭኝ) ላይ ከተመሰረተ የደቦ ፍርድ ነፃ የሆነ ፍትህ ያገኙ ይሆን?

ከምስክር አለነ (08.02.19)

እነበረከት ረዘም ላሉ አመታት ለአማራ ህዝብ ጥቅም ብለው ከማንም በበለጠ ተንቀሳቅሰዋል። በዚህ ሂደት እንደማንኛውም የብአዴን አባላትና አመራር ደረጃው ይለያይ እንጅ ያለሙትም ያጠፉትም ይኖራል። አሁን እንደምናየው እነሱ ብቻ ተለይተው አጥፊዎች ተደርገው የተቆጠሩበት ምክንያቶች ግን ቂም በቀል፣ በጎጥ ላይ የተመሰረተ ጥላቻና ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ፍላጎት እንደሆኑ ለመረዳት አይከብድም። ለምሳሌ በተለያዩ ጊዚያት ጥፋት በመፈፀማቸው ምክንያት እነበረከት በመድረክ ፊት ለፊት የተጋፈጧቸው ሰዎች ቂማቸውን ለመወጣት ሲሉ በነሱ ላይ ያላወሩትና ጥላሸት ለመቀባት ያላደረጉት ጥረት የለም። በሌላ በኩል ሌሎች ብዛት ያላቸው የአዴፓ አመራሮችና አባላት እነበረከት እንዲሁም ሌሎች ነባር ጓዶቻችው አማራ አይደሉም የሚል የጎጥ ሃሳብ በማቀንቀን እንዲጠሉ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ ፍልጎ ማግኘት አስቸጋሪ ነው። እነዚሁ የአዴፓ አመራሮች እነበረከት አማራ ባለመሆናቸው ምክንያት ለአማራ ህዝብ እንዳንሰራ አድርገውናል እያሉ በመቀስቀስ የድክመቶቻቸው ሁሉ መሸፈኛ አድርገው ሲጠቀሙባቸው እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። በዚህ መልክ ሲካሄዱ የነበሩ በቂም በቀልና በጎጥ ላይ የተመሰረቱ ቅስቀሳዎች በአማራ ህዝብ ውስጥ በተለይም በወጣቱ ዘንድ የፈጠሩት መደናገር ቀላል አይደለም። በዚህም ምክንያት ቁጥሩ ቀላል የማይባል የአማራ ህዝብ ተደናግሮም ቢሆን በነበረከት ላይ ቅሬታ ቋጥሯል።

Videos From Around The World

ይህ በአመለካከት ደረጃ የተያዘ ቅሬታ ደግሞ በተግባርም ተቀይሮ በነበረከት ላይ ጥቃት ለመሰንዘር የተሞከሩባቸውን ሁኔታዎች ማየት ይቻላል። አንደኛ አማራ ክልል ውስጥ አንዳንድ አከባቢዎች በረከት ታየ ተብሎ የተለያዩ የጥቃት እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው የሚዘነጋ አይደለም። በተለይም ደብረማርቆስ ከተማ ውስጥ በረከት አርፎበታል ተብሎ የተገመተ ሆቴል ላይ የደረሰው ጥቃት የሚረሳ አይደለም። ያኔ በረከት እውነትም እዛ ሆቴል ውስጥ አርፎ ቢሆን ኖሮ ምን ሊደርስበት ይችል እንደነበረ መገመት በጣም ቀላል ነው።

ሁለተኛ እዚሁ አማራ ክልል ውስጥ እነበረከት የሆነ ቦታ ታዩ በሚል ጥቃት ይደርስባቸው ዘንድ በቅብብል ሲደርግ የነበረን የፌስቡክ ቅስቀሳ ያስታውሷል። ከዚህ ውጭ ደግሞ እነበረከት ባህር ዳር ላይ ፍርድ ቤት በቀረቡበት ቀንም በየመንገዱ የነበረውን ዘለፋና ዛቻ በከፊል ተመልክተናል። በዚያ ላይ የነበረከት ቤተሰቦች በቅርብ ሆነው ለመጠየቅና የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ የሚሰሙ ጭምጭምታዎች አሉ። በሌላ በኩል ከደቦ ፈራጁ ሃይል ሊደርስ የሚችልን ጥቃት በመፍራት ጠበቆች የነበረከትን ክስ አንይዝም ብለዋል የሚል ወሬም በፌስቡክ በኩል እየተናፈሰ ነው። በዚህ ረገድ አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ ያህል ሙሉቀን ተስፋው የተባለ ራሱን የፖለቲካ አቀንቃኝ (Activist) ብሎ የሚጠራ ሰው በፌሱክ ገፁ ላይ "ጠበቆች ሁሉ አቶ በረከት ላይ አመጹ አሉ፤ ብዙ ገንዘብ ቢቀርብም ለአቶ በረከት የሚቆም ጠበቃ ጠፍቷል" በሚል አስፍሯል። በሌሎች ሰዎች ፌስቡክ ላይ የተለጠፉ ተመሳሳይ መልዕክቶችም አሉ። እነበረከት ፍርድ ቤት ቀርበው ያረጋገጡትም ይህንኑ ነው። ባጠቃላይ እነበረከት እየተዳኙ ያሉት ከወዲሁ በአፈርሳታ/በደቦ የጥፋተኝነት ፍርድ የወሰኑባቸው ስብስቦች እየፈነጩ ባሉበት ሁኔታ እንደሆነ የሚያሻማ ነገር የለውም። ።

የአዴፓ አመራሮችም ቢሆኑ እየተፈፀመ ያለውን የደቦ እንቅስቃሴ እንደመልካም አጋጣሚ በመጠቀም እያበረታቱ እንደሆነ የማይካድ እውነታ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ ታትሞ በወጣ በረራ በተባለ ጋዜጣ ላይ የብአዴን ከፍተኛ አመራር የሆነ ሰው ገና ለገና ጊዜ ሰጠኝ ብሎ ስለበረከት የተናገረው የወረደና የበሬ ወለደ አይነት አስተያየት አንዱ ማሳያ ነው። የዚህ ሁሉ ምክንያት ደግሞ የአማራ ህዝብ ባጠቃላይና ወጣቱ በተለይ የልማትና የሰላም ጥያቄዎች እያነሳ ባላበት ወቅት የአዴፓ አመራሮች መልስ መስጠት ሲያቅታቸው ለጥቅምህ ያልቆሙልህን ሰዎች እያሰርንልህ ነው በማለት በህዝቡ ውስጥ እየተፈጠረ ያለን የተቃውሞ ስሜት ለማለዘብና የምርጫ ካርድ ለመግዛትም እየተጠቀሙበት መሆኑን ለማወቅ የግድ ጠንቋይ መቀለብ አያስፈልግም።

ይህን አላማቸውን ለማሳካት እየሄዱበት ያለው መንገድ ደግሞ እነበረከት ሙስና ፈፅመዋል በሚል እንዲታሰሩ ማድረግን ነው። እነበረከት ሙስና ፈፅመዋል ተብለው ተጠርጥረው ሲከሰሱ የቀረበው ዋነኛ ምክንያት የሃሳብ አመንጭ (Master Mind) መሆናቸው ተገልፆ ነው። ይህ ማለት እነበረከት በሙሉ ሃሳባቸውና ፈቃዳቸው ብሎም ፍላጎታቸው አቅደውና ሁኔታዎችን ሁሉ አቀነባብረው ራሳቸውን ወይም ሌላውን ለመጥቀም ሲሉ ጥረትን የሚጎዳ ድርጊት ፈፅመዋል ወይም መፈፀም የነበረባቸውን ድርጊት ሳይፈፅሙ ቀርተዋል ተብለው ነው። እነ በረከት ካላቸው ስብዕና አንፃር በዚህ ደረጃ ያለ ጥረትን የሚጎዳ የሙስና ወንጀል ፈፅመዋል ብሎ ለማመን የሚከብድ ቢሆንም እውነቱ የት ላይ እንዳለ ከሚቀርበው ክስና ከፍርዱ ሂደት ሊታይ የሚችል ነው። እንዲያውም የተለያዩ ሰዎች የሚገምቱት በነበረከት ላይ የቀረበው የሙስና ክስ ፖለቲካዊ ይዘት ያለውን ጥቃት ህጋዊ ሽፋን እንዲኖረው የሚያደርግ አካሄድ እንደሆነ አድርገው ነው። ያም ሆነ ይህ ትልቁ ጥያቄ ያለው ህጉ በትክክለኛ መንገድ ጥቅም ላይ ውሎ በነበረከት ላይ የሚወሰነው ውሳኔ ፍትሃዊ ይሆናል ወይ የሚለው ጉዳይ ነው። ይህ ጥያቄ ትልቅና አንገብጋቢ ነው ሊባል የሚችለው በሚከተሉት ምክንያቶች ነው። እነዚህም፥

1) ዳኞች፣ ጠበቆችና አቃቢያን ህጎች በሚኖሩበት ክልል ውስጥ ያለ አስተሳሰብ ተጋሪ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ፥

እነዚህ ሙያተኞች ፈቅደውም ሆነ ለማስመሰል በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ላለ ሃሳብ ተገዥ ሆነው የሚታዩበት ሁኔታ ይኖራል። በዚህ ጊዜ ሙያቸውን አክብረው በህግና በህግ ብቻ ተመስርተው ይሰራሉ ብሎ ማሰብ በጣም አስቸጋሪ ነው። ባሁኑ ወቅት በተደጋጋሚ እያየንና እየሰማን እንዳለው እነ በረከት የአማራን ህዝብ ጥቅም አላስጠበቁም በሚል በአዴፓ አመራሮች ግልፅ የሆነ ቅስቀሳ ተደርጎባቸዋል፣ አሁንም እየተደረገባቸው ነው። አብዛኞቹ መገናኛ ብዙሃንና የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲታዩም እነበረከትን አይናችሁን ላፈር የሚል ቅስቀሳ የሚካሄድባቸው መድረኮች ሆነዋል። ከዚህ አልፈውም እነዚህ የመገናኛ ብዙሃን የአፈርሳታ ሂደቱ አካል በመሆን ገና በህግ በተቋቋመ ፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይሰጥ እነበረከት ወንጀለኞች እንደሆኑ ደምድመዋል። ይህ አይነት ድምዳሜ ደግሞ ማንም ሰው ከፍርድ በፊት ንፁህ ነው ተብሎ የመገመት (Presumption of Innocence) የህግ መርህ የሚጥስ ስነ ምግባ የጎደለው ተግባር ነው። እነዚህና እነዚህን በመሳሰሉ የቂም በቀልና የጎጥ ቅስቀሳዎች ምክንያት በዚህ ፅሁፍ ላይ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የአማራ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ተደናግሮ የሃሳቡ ሰለባ በመሆን በነበረከት ላይ የጅምላ ፍርድ አስተላልፎ የደቦ ጥቃት ለማድረግ ሙከራ እስከማድረግ ደርሷል። በዚህ ውስጥ ያሉ ዳኞች ፣ አቃቢያን ህጎችና ጠበቆች ደግሞ የዚህ የደቦ ፍርድ ተገዥ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ነው። ምናልባትም እነብረከት ፖሊስ ጣቢያ እያሉ በቤተሰቦቻቸው እየተጎበኙ በነበሩበት ወቅት በፖሊስና በኋላም ፍርድ ቤት ቀርበው በነበረበት ወቅት በዳኛ ተነሱ ተብለው ፌስቡክ ላይ የተለቀቁት ፎቶዎች እውነትም በፖሊስና በዳኛ ተደርገው ከሆነ እነዚህ ሙያተኞች ምን ያህል በደቦ ፈራጁ ሃይል ተፅእኖ ውስጥ እንዳሉና ይህን ሃይል ለማስደሰትም የማይፈፅሙት ስነምግባር የጎደለው ፀያፍ ድርጊት ሊኖር እንደማይችል ነው። ከዚህ አንፃር ሲታይ እነበረከት ትክክለኛ ፍትህ ያገኛሉ ብሎ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።

2) ዳኞች፣ ጠበቆችና አቃቢያን ህጎች ለራሳቸውም ይሁን ለቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሊሰጉ የሚችሉበት ሁኔታ መኖሩ፥

ለሁሉም ግልፅ እንደሚሆነው በነበረከት ክስ ዙሪያ የሚሰሩ ዳኞች፣ አቃቢያነ ህጎችና ጠበቃዎች ከብረት የተሰሩ አይደሉም። ስለዚህ እነዚህ ባለሙያዎች ለህሊናቸውና ለሙያቸው ክብር ብለው በሚኖሩበት አከባቢ ባሉ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችና የጅምላ ውስኔዎች ተገዥ ባይሆኑ እንኳ ከብረት ያልተሰሩ ሰዎች ናቸውና ለራሳቸውና በዙሪያቸው ላሉ ቤተሰቦቻቸው ደህንነት ሲሉ በደቦ ፈራጁ ሃይል ተፅዕኖ ውስጥ ሊወድቁ አይችሉም ብሎ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም። ይህም እነበረከት ትክክለኛ ፍትህ እንዳያገኙ የሚያደርግ ሁኔታ ነው።

3) ዳኞች የስራ ዋስትና ማጣት ስጋት ሊሆንባቸው የሚችል መሆኑ፥

ከላይ በተለያየ መንገድ በተገለፀው የደቦ ፍርድና እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ዳኞች ለሙያቸውና ለህሊናቸው ብቻ ተገዝተው ቢፈርዱና ይህ ፍርድም እነበረከትን ከተከሰሱበት የሙስና ወንጀል ነፃ የሚያደርግ ቢሆን የአዴፓ አመራሮችም ይሁኑ የደቦ ፍርዱ ተሳታፊ የሆነ ሃይል ሊከፉ የሚችሉ መሆኑን ከወዲሁ ለመረዳት አይከብድም። እንዲያ ከሆነ ደግሞ የአዴፓ አመራሮች ከዚህ የደቦ ፈራጅ ሃይል የሚመጣውን ቁጣና ረብሻ ለማብረድ ሊወስዱ ከሚችሏቸው ርምጃዎች ውስጥ አንዱ ውሳኔ የሰጡ ዳኞችን ከስራ ማፈናቀል ሊሆን ይችላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የስራ አስፈፃሚው የመንግስት ክፍል በፍትህ አካላት ስራዎች ጣልቃ እንደሚገባ እየታወቀና በግልፅ እየተነገረ ባለበት ሁኔታ ዳኞቹ በሚሰጡት ውሳኔ ምክንያት ከስራ የመባረር አደጋ አይገጥመንም ብለው ከተፅዕኖ ነፃ ሊሆኑ የሚችሉበት ሁኔታ ብዙም ሰፊ አይደለ ም። በዚህ ረገድ የህግ ባለሙያዎች ማህበር የሆኑት አቶ ደበበ ሃይለገብርኤል ተናገሩት ተብሎ በሪፖተር ጋዜጣ የቀረበውን ዜና በሚገባ አንብቦ መረዳት ስራ አስፈፃሚው በፍትህ ስርዓቱ ላይ የሚያካሂደውን ግልፅ የሆነ ጣልቃ ገብነት ለመረዳት ይጠቅም ይህናል። ይህ በሆነበት ሁኔታ ዳኞች ገለልተኛ፣ ትክክለኛና ከተፅዕኖ ነፃ የሆነ ውሳኔ ያሳልፋሉ ብሎ እርግጠኛ ሆኖ መናገር አይቻልም።

ከዚህ በላይ የተገለፁት ስጋቶች ወይም ችግሮች ከምንም የተነሱ ሳይሆኑ አማራ ክልል ውስጥ ያሉ ዳኞችና አቃቢያን ህጎች የገለፁት እውነታ ነው። ይህ እውነታም እንዲህ ይነበባል፥

ነገን የተሻለ የምናደርገዉ የተረጋጋና ስልጡን ጨካኝ ያልሆነ ማሕበረሰብ ልንፈጥር የምንችለዉ የሕግ የበላይነትና ሥርዓትን ስናሰፍን ነዉ፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ጠንካራና ነፃ ደህንነታቸዉ የተጠበቀ የፍትሕ ተቋሞችና ባለሙያዎች እንዲኖሩ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ እኛም በተደጋጋሚ ስለሥርዓት እያወራን የዳኞችና የዓቃቤ ሕጎችን ደህንነት አጀንዳ አድርገን ስናቀርብ ነገን ከማሰብ እንጅ ከራስ በላይ ነፋስ በማለት አይደለም፡፡ አሁን በክልሉ እየታዬ ያለዉ ሥርዓተ አልበኝነት በፍትሕ ተቋሞች ያሉትን ባለሙያዎች ስራቸዉን እንዲለቁና እንዲሸሹ ያደርጋቸዋል፡

እንግዲህ ከላይ የተገለፁትን ሁኔታዎች ግምት ውስጥ በማስገባት ነው እውነት እነበረከት በአፈርሳታ ላይ ከተመሰረተ የደቦ ፍርድ ነፃ የሆነ ፍትህ ያገኙ ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳት አንገብጋቢ እየሆነ ያለው።

 

 

 

Back to Front Page