Back to Front Page


Share This Article!
Share
የሕዝብ ተወካይ ማን ነው?

የሕዝብ ተወካይ ማን ነው?

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ 3-5-19

የሰው ልጅ በታሪኩ ውስጥ በጊዜ ሂደት ባዳበራቸውና ባሰመራቸው ልዩነቶች የተነሣ በንቃትም (Consciously) ኾነ ያለ ንቃት (unconsciously) ፣ በሕግ፣ በኃይል፣ በተጽዕኖ፣ አማራጭ በማጣት፣ በተለምዶ፣ በባሕሪያዊና ጠባያዊ የመግለጽ እንቅስቃሴ - - - በመነሣት ውክልናና የውክልና ትንታኔ ይሰጣል፡፡

እንግሊዝኛው Websters Third New International Dictionary: ተወካይን (Representative) ፡-ከአካል፣ ከብቃት፣ ከተልዕኮ፣ ከኃላፊነት ጋር ካለና ከሚሰጥ ተግባር ፍጻሜ ጋር አያይዞ ያቀርበዋል፡፡ እነዚህም ብዙ የማያከራክሩና ብዠታ የማይፈጥሩ ሲኾኑ ውስብስብ (complex) የሚኾነው ተወካይነትን ከሥልጣን ፖለቲካ የሀገራችን ነባራዊ ኹኔታ/ዎች ጋር በኹለንተናዊ መንገድ አቆራኝተን ስንመለከተው ይኾናል፡፡

Videos From Around The World

ውክልና፣ ተወካይነትና ወካይነት እንደሕዝብ ትንታኔ በተለያየ አውድ የተለያየ ገጽታ ያለውና መገለጫው የበዛ ከግለሰብ፣ ከቡድን፣ ከተቋም ባሻገር ሁሉን በሚጠቀልል መንግሥትና ሀገር ላይ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ/ዎች የነበረ፣ ያለና የሚኖር ራሱን የቻለ ሰፊ አርዕስት ነው፡፡

የሕዝብና ሀገር ጉዳይን በሚመለከት በሚደረጉ ኹለንተናዊ ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች- በግለሰብ/ቦች፣ በቡድን/ኖች፣ በተቋማት/ቶች ስለሕዝብ ጉዳይ ሕዝብ ይህን ይፈልጋል!፤ ሕዝባችን እንዲህ ነው!፤ ሕዝብ ሊነሣ ይገባል!፤ ሕዝቡ እንዲህ ሊደረግለት ይገባል!፤እኛ ነን የሕዝብ ተወካዮች!፤ ሌሎች ሕዝቡን አይወክሉም!፤ ሕዝቡ እኛን መርጦናል!፤ የሕዝቡ አለኝታ - እኛ ነን! ሊሰማን ይገባል!፤ ሕዝብ ይህን ይላል!፤ የሕዝቡ ፍላጎት እኛ የምንለው ነው!፤ እኛ የሕዝብ ጠበቃ ነን!

ይህ ሕዝብ እንዲ ነው! - ያ ሕዝብ ግን እንዲያ ነው!፤ እኛ ከንትኖች ጋር ሕብረት የለንም!፤ ሕዝባችን አለኝታችን!፤ ሕዝባችን እንደሚያኮራን እንተማመናለን!፤ ጀግናው ሕዝባችን እንዲህ ያደርጋል!፤ ሕዝባችን በኛ መስመር ለድል ይበቃል!፤ ሕዝባችን ንቁ፣ ሥልጡንና ትዕግስተኛ ነው - ከተነሣ መመለሻ የለውም!፤ - - - ወዘተ የሚሉ ድምጾችን ሕዝቡ የከባቢ አልያም የኢትዮጵያ ሕዝብ ኾኖ ሳለ በሕዝቡ ስም እጅግ በርካታ ወክለነዋል ካሉናከወከሉት አካላት ያለ ልዩነት መስማት እጅግ የተለመደ የሀገራችን ኹለንተናዊ የውስጥና የውጭ ተርዕዮ ነው፡፡

እነዚህ ድምጾች በርዕዮተ አለም፣ በርዕዮተ ሀገር፣ በአስተሳሰብና አመለካከት፣ በእምነት፣ በእውቀት፣ በድርጊት፣ በስልት፣ በዓላማ፣ በስትራቴጂ፣ በግብ፣ በአካሄድ፣ በትኩረት አቅጣጫ - - - ወዘተ እጅግ የተለያዩ አካላት፤ እጅግ የተራራቁና እርስ በራስ ፈጽሞ ሊቀራረብ የሚችል ልዩነት የሌላቸው፤ አንዳንዶች ተመሳሳይነታቸው በዝቶ ልዩነታቸው ግን ትንሽ ቢኾንም - መሠረታዊ የሚባል ልዩነት ባይኖራቸውም - ከሚያመሳስላቸው ትልቅ ነገር ይልቅ በትንሹ ልዩነታቸው ላይ ድንበር፣ አጥር፣ ድልድይ ሰርተውና ጠላትነትን አበጅተው - እርስ በራስ በጎንዮሽ፣ ወደ ታችና ወደ ላይ እየተጋገሉ ከኹሉ በሚከፋ ብዙዎች በውስጣቸው ጠላትነት ሰፍኖ፣ ሰላም አጥተው እየተከፋፈሉ፣ በመንፈስ እጅጉን ተለያይተው - - - ወዘተ በከባቢያዊነት ላይ የተመሰረቱም ይኹኑ ሀገራውያን አልያም ሃይማኖታውያን ሁሉም ግን የሕዝብ ተወካይ ነን! በማለት ይመሳሰላሉ፡፡

ለአብነት፡- አንድ ሰው የሀገር መሪ አልያም ገዢ በመኾን የሚያደርጋቸው ስምምነቶች፣ ግንኙነቶች፣ ድርጊቶች፣ ገለጻዎች፣ መግለጫዎች - - - ወዘተ በመሪነቱና በገዢነቱ የሚያገኘው ሥልጣን በመኾኑ በዛ ደረጃ የሕዝቡ ተወካይ ተደርጎ በራሱ በሕዝቡም ኾነ ከዛ ውጭ ባሉ አካላት ዘንድ እንዲወሰድ ያደርገዋል፡፡ በዚህም በሕዝብ ስም የተለያዩ ኹለንተናዊ ተግባራትን ያከናውናል፡፡

ከሕግ ማዕቀፍ ውጭ በአንጻሩ የሀገራቸውን ሥርዓት በማውገዝ ሌላ ሥርዓት ያስፈልገናል ያሉ ኃይሎች በግለሰብና በቡድን ደረጃ ጀምረው ቀስ እያሉ ሕዝብን በተለያየ መንገድ በነሱ ዓላማና ግብ በማንቃት፣ በማደራጀት፣ በመምራት - - - በመጀመሪያ የሕዝብ ውክልና የሌላቸው ቢኾኑም ለሕዝብ ብለን ወጣን!፣ የናንተ ተወካዮች ነን! ብለው ራሳቸውን በራሳቸው ሾመው እየተንቀሳቀሱ ይቆዩና ከሚታገሉት ሥርዓት ጋር ያለው ትግል ሲያበቃና አሸናፊ ሲኾኑ በተለያዩ የውክልና ማዕቀፍ - የራስን ሕጋዊ ማዕቀፍ በመዘርጋትና ምርጫ በማካሄድ ተወካይነታቸውን በኃይል መጥተው - በሕጋዊነት ያረጋግጣሉ፡፡ ያስቀጥላሉ፡፡ በመጡበት መንገድ ሌሎች እንዳይመጡ ማሰሪያን ያበጃሉ፡፡

ሕጋዊነትን ለተሻለና ለላቀ ሕጋዊነት፤ ሕጋዊነትን ሕገ ወጥነትን ለመከላከያነት፤ ሕገ ወጥነትን ሕገ ወጥነት ነው ብለው ያመኑበትን በኹለንተናዊ መንገድ ለመታገል በመጠቀም ሕጋዊነትን የማስፈን እንቅስቃሴ ተርዕዮዎች - በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በተለያየ አውድ በኹለንተናዊ መንገድ ሲስተዋል የነበረ ክስተት መኾኑን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ከዚህ የሰው ልጅ የረዥም ጊዜ ታሪክ አካል የሀገራችንን ነጥለን ስንመለከት ስለኢትዮጵያ ኹለንተናዊ ጉዳዮች የሚመለከቱ አንደ አሸን የፈሩ ማህበራት፣ ድርጅቶች፣ ኃይሎችና ፓርቲዎች እዛም እዚም መመልከት የተለመደ ነው፡፡ለተመሳሳይ ሕዝብ ተመሳሳይ ለቁጥር የሚያታክቱ ተወካይ ነን ባዮች በተለያየ አውድ የበዙበት ኹኔታ እንመለከታለን፡፡

የሀገር እና የሕዝብ ኹለንተናዊ ጉዳዮች በባሕሪያቸው ኹሉንም የሚመለከቱ እያንዳንዱ ዜጋ የሚመለከተውና በባለቤትነት ሊይዘው የሚችል በመኾኑ ባሕሪው በራሱ ጉዳዩን እጅግ ውስብስብ (compex) ያደርገዋል፡፡

ማንም ግለሰብ/ቦች፣ ቡድን/ኖች ኾኑ ተቋማት/ች ባመኑበትና ባወቁት ተነሥተው ለማንኛውም ዓይነት፣ መጠንና ስፋት ላለው ፍላጎታቸው በሀገራዊና ሕዝባዊ ስም ኹለንተናዊ እንቅስቃሴ/ዎች ቢያደርጉ ጥያቄ አያስነሳም፡፡ ምክንያቱም መብት ስለኾነ ጥያቄ የሚያስነሣው እነዚህ አካላት በጊዜ ሂደት በሀሳቡ የሌለ፣ በዕምነት ያልተቀበላቸውን፣ በእውቀት የማያውቃቸውና በድርጊታቸው ያልተሳተፈና መሳተፍ የማይፈልግን በሕዝብና ሀገር ጥላ ስር ጨፍልቀው ተወካይህ ነኝ! ማለታቸው የማይቀር መኾኑ ነው፡፡

ብዙዎች በሕዝብና በሀገር ስም ተነሥተው ወድቀዋል፡፡ ተነሥተናልም ያሉ ብዙዎች ናቸው፡፡ እንዴት እንለያቸው? በማመን እንዳንል ሰውን ማመን ከባድ ነው፡፡ በተግባር እያየን እንዳል አስመሳይነት፣ ተለዋዋጭነትና አማራጭ አሳጪነት ቦታውን በሰፊው ይቆጣጠሩታል፡፡

በሕጋዊነት እንዳንል ከሕግ ውጭ የኾኑ ብዙ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ የሕጋዊ ማዕቀፍ አስከባሪነት የማይፈቅዳቸው አልያም በዛ ውስጥ በማለፍ ለውጥ አናመጣም ብለው የሚያስቡና የሚንቀሳቀሱ አካላት በርካታ ናቸው፡፡ በታሪክም ቢኾን በርካቶች ከሕጋዊ ማዕቀፍ በመውጣት ሕጋዊ ማዕቀፍን ለማስፈን ታግለው ሲሳካላቸውና ደማቅ ታሪክ ማስመዝገባቸውን እናውቃለን፡፡ በመመካከር እንዳንል ኹላችንም በተመሳሳይ ሰዓት፣ ጊዜና ቦታ ተመሳሳይ ነገር ማሰብ፤ ሀሳብን የጋራ ማድረግ እንጂ በጋራ ማሰብ ፈጽሞ አንችልም፡፡

በምርመራ እንዳንል ማን ይመረምራል? በምን መለኪያ? ከምን አንጻር? በምን መሣሪያዎች? መቼ? ማን ነህ ቢባል ምን ይመልሳል?

እሺ እንደፈለገ ይኹን እንዳንል ሕዝብና ሀገር ለትውልድ ትውልድ የሚተላለፍ አስከፊ ኹለንተናዊ መስዋዕትነት መክፈላቸው ይቆጨናል፡፡ ዛሬም የሚከፈለው ኹለንተናዊ መስዋዕትነት ያሳዝነናል፡፡ በዚሁ ከቀጠለ ደግሞ የሚከሰተው አደጋ በእጅጉ ያስጨንቀናል፡፡ ተስፋ እንዳናደርግ ይጋርደናል፡፡ ዜጎች በተለያየ መንገድ እንዲከፋፈሉ በማድረጉ ደግሞ በእምነት፣ በእውቀትና በመንፈስ እንዳይግባቡ ትልቅ እንቅፋት ኾኗል፡፡ በመኾን ላይ ይገኛል፡፡ ካልታረመም መኾኑም ይቀጥላል፡፡

የግል ድርጅት በራስ ለራስ ስለራስ በሚል ስለሚንቀሳቀሰ አያስቸግር ይኾናል፡፡ ሕዝባዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ግን በባሕሪያቸውና በጠባያቸው ከራስ ስለሚሻገሩ በእኛነት የሚተነተኑ ኾነው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ አንዳንዶች በእውነታ (Reality) እና በዕውነት (Truth) የሕዝብን ጉዳይ የሕይወታቸው አካል አድርገው ኹለንተናዊ ዋጋ እየከፈሉ የሚያንቀሳቀሱ እናገኛለን፡፡

በአንጻሩ እነሱ ምንም ዋጋ ሳይከፍሉ ሌሎችን ኹለንተናዊ ዋጋ እያስከፈሉ እንዲያውም በሌሎች ኹለንተናዊ መስዋዕትነት (የሕይወት፣ የአካል፣ የጊዜ፣ የዕውቀት፣ የገንዘብ - - -) ራሳቸውን በቁስ፣ በዝናና በተጽዕኖ እላይ የሰቀሉ የሕዝብ መዥገሮች ትላንት በታሪክ መኖራቸውን ከታሪክ መዛግብት እንደምንረዳው ኹሉ ዛሬም በአኗኗራችን የምናስተውለው ተርዕዮ ነው፡፡

ከአንቀሳቃሾችና አንቀሳቃሽ ተብዪዎች ስንነሣ አንዳንዶች ሥራ ስለሌላቸው ሕዝባዊና ሀገራዊ ጉዳይን ሥራቸው በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አንዳንዶች ለመታወቅ፣ ለመታወስና ተጽዕኖ ለመፍጠር እጅግ የቀለለው መንገድና አቋራጭ ብለው የሚጥሩበት ይህን ኾኖ እናገኛለን፡፡ አንዳንዶች ያለ ጸጋቸው፣ ያለ ችሎታቸው፣ ያለ ክህሎታቸውና ያለ ዕውቀታቸው - እንደሌላቸውም ለዓመታት በተግባር በአደባባይ ያስመሰከሩ ቢኾንም በማስመሰል ሲፈተፍቱ እናገኛለን፡፡

ከእንቅስቃሴያቸው ተግባር ስንነሣ ብዙዎች ከሰረተፍኬቱ በቀር በግለሰቦች ላይ የተመሰረቱ፤ ቢሮ እንኳ የሌላቸው፤ በብዛት አንዳንዶች እጅግ በጣት የሚቆጠሩ ግለሰቦች ያሉባቸው፤ በጊዜ ቆይታ መስራቾቹ እንደግል ንብረታቸው የሚያዙባቸው ከድርጅቱ ይልቅ እነሱ ጎልተው የሚታዩበት፤ በነሱና በድርጅቱ አስተሳሰብና አመለካከት መሐከል ልዩነት የማይታይ፤ የሕልውናቸው ማረጋገጫ ከመግለጫ ያልዘለለ፤ ከጥራት - ከጥራት አንጻር መነሻና መዳረሻቸው በግልጽ የተቀመጠ ማግኘት በጣም ከባድ እንደሚኾን ማንም አስተዋይ ዜጋ የማያጣው ጉዳይ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡

በሌላ በኩል አንዳንድ ጊዜ የውክልናው ጣጣ ብዙ ነው፡፡ አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ በራሱ ጥረትምይኹን በምቹ ኹኔታዎች ተነሣሥቶ መልካም የሚባል ተግባር ሲያከናውን እንደተወካይ እንዲታይ እንጥራለን፡፡ ስሙንና ተግባሩን እያነሣን፡፡እኛ እኮ!ብለን ተወካያችን እናደርገዋለን፡፡

በተቃራኒው አንድ ትውልደ ኢትዮጵያዊ መልካም ያልኾነ ተግባር ሲያከናውን እኛን አይወክልም፡፡የጥቂቶች እንጂ የአብዝሃ አይደለም! ብለን ያዙኝ ልቀቁኝ እንላለን፡፡ ሌላው በአንጻሩ እሱን እያነሣ እናንተ እኮ! እንዲህ ናችሁ፡፡ይኸው የናንተ ሰው! እንደዚህ አደረገ! ብሎ ለራሱ ዓላማና ግብ ይጠቀምበታል፡፡ በከባቢያዊነት ውስጥ ያለው እጅግ የሰፋ መወቃቀስ፣ መወዳደስ፣ መነቃቀፍና መጠላላትን እንዲሁም በሃይማኖት ተቋማት ተከታዮች ዘንድ እርስ በራስ ያለው መጠማመድ፣ ዕይታ፣ ብዥታና ፉክክር ለዚህ ዐቢይ ተጨማሪ ማሳያ ነው፡፡ ሁለቱን በምን እናስታርቅ?

እንደሀገር - እንደኢትዮጵያውያን የአንድ ነገር በተለይ የአብዝሃ ጉዳይን በሚመለከት ይህ ተወካይ ነው? ይህ ግን አይደለም የምንልበት መለኪያችን ምንድነው? በምን? እንዴት?

እኛ ኢትዮጵያውያን ሕዝባዊና ሀገራዊ ጉዳይን በተመለከተ ለኛትክክለኛና መልካም ነገር ምንድነው? የሚለው እንደተጠበቀ ኾኖ መልካም የኾነውን ካልኾነው በምንድነው የምንለየው? ማንስ ነው ይህን እውቅና የሚሰጠው? በምንስ ይፈጸማል?ተወካይ በመኾንና ተወካይ ለመኾን በሚደረግ ትጋት መሐከል ያለው ድንበር ምንድነው? ተወካያችንን ተወካይ ሊኾን ከማይችል የምንለየው እንዴት ነው? ማንም ሥራ ፈት በስማችን እንዳይነግድ ያስቀመጥነው አሰራር አለን? በስማችን በጎ አስተዋጽዖ ለማበርከት ለሚሹስ ተወካይነታችንን በምን መልኩ አስቀመጥን?

ለተወካይነት በመትጋትና በተወካይነት፤ የራስን ሀሳብ በመግለጽ፣ በመጻፍና በማስተላለፍ እና ሌላውን ወክሎ በመግለጽ፣ በመጻፍና በማስተላለፍ፤ ለመሪነት በመትጋትና መሪ በመኾን፤ የሕዝብ አንደበት በመኾንና የሕዝብ አንደበት ለመኾን በሚደረግ ኹለንተናዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ዕውን እኔ ማን ነኝ? ምን ሥልጣን አለኝ ይህን የማድረግ? ከምን አንጻር? ማንን - እንዴት - ከምን አንጻር - መወከል እችላለው?

በርግጥ በሀገራችን በመሪነትና በተመሪነት፣ በአዋቂነትና በታዋቂነት፣ በመምህርነትና በተማሪነት፣ በሰሪነትና በአሰሪነት፣ በአገልጋይነትና በምዕመንነት፣ በባለሙያና በአድናቂነት፣ በማፍቀርና በመውደድ፣ በአማኝነትና በተከታይነት፣ በሃቀኛነትና በአስመሳይነት - - - መሐከል መሠረታዊ የሚባል እጅግ የሰፋ ሀገራዊ መደነባበር በመኖሩ የተነሣ ኹለንተናዊ ዋጋዎችን ከፍለናል፡፡ በመክፈል ላይም እንገኛለን፡፡ ማስተካከል ካልቻልንም እየከፈልን በመኖር በመክፈል የሚገኝ ፍሬ እንደናፈቀን በኹለንተናዊ ዝቅጠት ውስጥ እንደምንኖር አያጠራጥርም፡፡

ግለሰቦች በራሳቸው ተነሣሽነት በእውነተኛ ሕዝባዊና ሀገራዊ ዓላማዎችና ግቦች ተነሥተው ሕዝባዊ ጉዳዮችን መሠረት አድርገው እንደሚንቀሳቀሱት ኹሉ ግለሰቦች ለራሳቸው የግልና የቡድን ፍላጎት፣ ዓላማና ግብ ብለው ደግሞ በሕዝባዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ስም ይንቀሳቀሳሉ፡፡ሁለቱን እንዴት መለየት ይቻላል? አንዱን ከሌላው እንዴት ተወካይ ማድረግና ከተወካይነት ማራቅ ይቻላል? ልስረቅ ብሎ የሚሰርቅ ሳይኾን በማልማት ስም የሚያለማና የሚሰርቅ ነውና ያለው እንዴት መለየት ይቻላል? በማን? እንዴት? አለም ከብዙ ዓመታት በፊት የተሻገረውን ጣጣ ገና ባለመሻገራችን ያለመሻገር ኹለንተናዊ ዋጋ ከፋይ ባለዕዳዎች ኾንን፡፡ ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድንየኹሉ ነገር ማዕከል ወደሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

 

 

Back to Front Page