Back to Front Page


Share This Article!
Share
አሳሪ መሆን ሲገባው ታሳሪ

አሳሪ መሆን ሲገባው ታሳሪ

 

ኡስማን ሙሉዓለም 3-8-19

 

በአሁኑ ወቅት ነገሩ ሁሉ የዞረበት ዘመንና ዓለም ውስጥ እንገኛለን። ባራክ ኦባማ በኢኮኖሚ ቀውስና በአለም የተጠላች አገር ተረክበው ሁኔታውን ለመቀየር ጥረት አድርገዋል። በኢኮኖሚው አገሪቱ እንድታገግም የተሳካ ስራ ፈፅመዋል። ከዓለም ህዝቦችና አገሮች አገራቸውን አሜሪካ ለማስታረቅ ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውነዋል። የሳቸው ዕድሜ ያህል ያስቆጣረውን የኩባና የአሜሪካ ፊጥጫ ለአንዴና ለመጨረሻ ለማስታረቅ ከፍታኛ የዲፕሎማሲ እርምጃ በመውሰዳቸው ከፍያለ ዝና አስገኝቶላቸዋል። ከኢራንም ጋር ተደራድረው ያልተገመተ መፍትሔ አስመዝግበዋል። በዓለም አስጨናቂ የሆነውን የአየር ንብረት መዛበት ለመቀነስ የፓሪስ ስምምነት ለመቀበልም በቅተዋል።

Videos From Around The World

ዶናልድ ትራምፕ መጥተው ይህን ሁሉ ስኬት እንዳልነበረ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ኦባማን በሀገር ክህደትና የአሜሪካን ጥቅም አሳልፈው የሰጡ መሪ አድርገው በተደጋጋሚ ገልፀዋቸዋል። ይህንም እንደ ምክንያትነት ሲያቀርቡ ኦባማ አሜሪካዊ ስላልሆኑ እንደሆነ ዘረኛ አቋማቸውን አንፀባርቀዋል። ኦባማ ኬርን፣ ከኩባና ኢራን የተደረጉ ስምምነቶችና የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ሁሉንም አልቀበልም አሉ። በሁሉም ነገር ለውጥ! አሉ። መሰረት የሌለው ለውጥ። አሜሪካ ትቅደም! ብቻ መፈክሩ ያደረገ ለውጥ። መጨረሻው ወደ ማይታወቅ የለውጥ ጉዞ። ዶናልድ ትራምፕ ትላንትና የተናገሩትን ካልተመቻቸው ዛሬ ይቀይሩታል። የመጀመርያውን ቃላቸው ስህተትነቱን ሳያሳዩ። አረ! አንዳንዴስ ሁለቱም ትክክል ነኝ ብለው ድርቅ ይላሉ። ከሚስታቸው ውጭ የፈፀሙት ዙሙት እያለ ብር አልከፈልኩም እንትና ከፍሎ ከሆነ እሱ ይጠየቅበት ብለው የዛሬውን ብቻ እንደምንም ማለፍ ላይ እየኖሩ ከአንድ አጀንዳ ወደ ሌላ አጀንዳ ህዝቡን ብቻ ሳይሆን ሚድያውንም በየደቂቃዉ በትዊተራቸው ያተራምሳሉ። ለሳቸው ያልተመቹዋቸው ሚድያዎች መዝጋት ባይችሉም እንኳን ሳያቋርጡ ስሞቻቸዉን በተደጋጋሚ ያጠፋሉ። በእሳቸዉ መንገድ የሚነዳ ከቶ ባያገኙም። ያን የዓለም ግዙፍና ትልቅ አገር እንዴት በአንድ ቱጃር ነጋዴ እየታመሰ ይመራል? ነገሩ ሁሉ የዞረበት ዓለምና ዘመን መሆኑ ብቻ ይገልፀዋል? እኔ እንጃ። ብዙ ፀሓፊዎች ይህ ነገር አሜሪካ ብቻ ሳይሆን አውሮፓም ላይ እይታየ እንደሆነ እየገለፁ ነው።

 

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ፅንፈኛ ብሄርተኝነትና ህዝበኝነት /ፖፑሊዝም/ የበላይነት አግኝታል። የፋሽዝም መሰረት የሆኑት እነዚህ አመለካከቶች ይነስም ይብዛም በሁሉም አገሮች እየተከሰቱ እንደሆነ ፀሓፊዎቹ በዝርዝር እየተረኩ ናቸው። ይህ ሁኔታ በአገራችንም ላይ በለውጡ ተሳቦ ከገባ አንድ አመት ሊሞላው ነው፡፡

 

በኢትዮጵያ አገራችን ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ፈጣን፣ ተከታታይና ሁለገብ ለውጥ የታየበትና ዓለም የመሰከረለት ስኬታማና ትክክለኛ የለውጥ ጉዞ ተመዝግቦ እንደነበር አይዘነጋም። ይህ ለውጥ ብዙ ሚልዮኖች ከድህነት ወለል በላይ እንዲሆኑና እንዲለወጡ በተጨባጭ አድርጓል። ይህም ለውጥ ማስመዝገብ የተቻለው ትክክለኛ ራእይና ራእዩን ተጨባጭ የሚያደርጉ ህዝብን ተጠቃሚ ማድረግ የሚችሉ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ፖሊሲዎችና መስመሮችን በመንደፍና እነዚህን ተግባራዊ ማድረግ የሚችልና ህዝባዊ ወገንተኝነት ያለው አመራር ህዝቡን አሳትፎና የሚያጋጥሙትንም ችግሮች እየተከታተለ ይፈታ ስለነበረ ነው። ይህ አመራር በብቃት ስለመራ ውጤታማ ሆነ።

 

ሆኖም ግን ኢህአድግ ከፈጣን እድገቱ ጋር የሚመጣጠን የአመራር ብዛት፣ ጥራትና ብቃት ጥያቄ ቀድሞ እየፈታ ባለመምጣቱ የስትራተጂካዊ አመራር ቀውስ ላይ እንዲወድቅ ዳረጎቷል። ፈጣን ዕድገቱና ለውጡ የሚጠይቀው የአመራር ብቃትና አገሪቱ ያላት ተጨባጭ አመራር በቁጥርም በጥራትም የሚቀራረብ ስላልነበረ ቀውሱ የግድ ሆነ። በሁሉም አካባቢ ያለው አመራር አቅመቢስ ስለነበረ የህዝብን ጥያቄ መመለስ ሲያቅተው ብቃትና ዓቅም ሲያንሰው ፅንፈኛነትና ህዝበኝነትን እንደምሽግነትና መሸሸግያ በመጠቀም የህዝቡን ጥያቄና ብሶት ምንጭ ሌሎች እንደሆኑ በማድረግ ሌላውጋ ማላከክ እንደ ዋነኛ ስልት መጠቀም ተያያዘው። አመራሩ ሌላ አማራጭ አልነበረውም። የነበረው ማንኛውም አመራር ከነበረው ሁኔታ ውጭ ማድረግ ተስኖት ነበር። ይሁን እንጂ ጭራሹን አመራሩ ከዚህ ውጭ ነፃ መሆን አይችልም ነበር ማለቴ እንዳልሆነ ግን ይታወቅልኝ። ነባራዊው ሁኔታው ከባድ የነበረ መሆኑን ለመግለፅ ያክል ነው።

 

አመራሩ በዚህ ፅንፈኝነትና ህዝበኝነት አመለካከት ሲነጉድና ሲመራ ብዙ ጥፋቶች ፈፅማል። ተጀምሮ የነበረው ልማትና ዕድገት እየተገራገጨ ነበር። በሶማሊ በኩል በነበሩ መሪዎች (በእነ አብዲ) በሶማሊ ህዝብና በአጎራባች ክልል ህዝብ ጉዳት ሲደርስ ነበር። ይሁን እንጂ መቻቻል ስለነበረና በኦሮሚያ ክልል በኩል የሚያጋግል አመራር ስላልነበረ በህዝቦች መካከል መቃቃር ሳይፈጠር ቆይታል። የህዝበኝነትና ፅንፈኛ ብሄርተኝነት በአጎራባች ክልል አመራር የበላይነት እያገኘ ሲመጣ ግን ሁኔታው ተቀየረ። የየራሳቸውን የመንግስት ፖሊስና ሚሊሻ ትጥቅ በመጠቀም በሌላው ክልል ህዝብ በማዝመት ጦርነት በግልፅና በአደባባይ ለማና አብይ ከኦሮሚያ እነ አብዲ ከሶማሊ አወጁ። የሃይለማርያም መንግስትም ተልፈስፍሶ ይህን ሁኔታ ከህዝቡ ጋር ወግኖ ሊፈታና ተጠያቂዎችን ሊጠይቅ ይቅርና አንዴ ከአንዱ ጋር አንዴ ከሌለው ጎራ በመሰለፍ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም የሚጠቅመውን ውሳኔ ለመምረጥ ሲዋዥቅ በግልፅ ታየ። የዚህ ውጤትም የብዙ ህዝብ ህይወት ለሞት መዳረግና ሚልዮኖች መፈናቀል ሆነ። በህዝቦች መካከል መቃቃር፣ ጥርጣሬና ጥላቻ እንዲፈጠር በአመራሮቹ በራሳቸው አንደበት ያለ ህፍረት በጀብደተኝነት በአደባባይ ተሰበከ። በጭብጨባ እየታጀበ። በውጭ በነበሩ የዚህ አስተሳሰብ ንጉሶች ለነዚህ ጀብደኞች ልዩ እውቅና ተቸራቸው። እነሱም እየሞቃቸው መጋለባቸውን ቀጠሉበት።

 

የኦሮሚያ ህዝብና ወጣት ጥያቄ ወደ ሌላ እንዲዞር ተደረገ። የህዝቡ አመፅ ቀዝቀዝ ሲል በራሳቸው በነለማ የሚመራ ድብቅ ቡዱን ተደራጅቶ የኦሮሚያ ጠንካራ የፖሊስ አዛዦችንና የዞን አስተዳዳሪዎችን መምታት ተጀመረ። በደምቢደሎና በአጠቃላይ በወለጋ ዙርያ በተከታታይ ግድያ ሲፈፀም ነበር። የድርጊቱ ፈፃሚዎች ሊያዙ ሲሉም ቀድሞ መረጃ እንዲደርሳቸው እየተደረገ ወይንም ፌደራል ጣልቃ አይግባብን በማለት ሳይያዙ እንዳሻቸው እንዲንቀሳቀሱና ሌሎች ላይ ተጨማሪ እርምጃ እንዲወስዱ በቀጥታ ያዛቸዋል። ተከበው እርምጃ በተወሰደባቸው የድብቅ ቡድኑ አባላት ምክንያት የፈደራል ፖሊስ አባላት አሁን እየተጠየቁበት ነው። አሁን ወደ ኦነግ እያላከኩት ያለውን ድርጊት በወለጋዎች እየፈፀሙት ያሉት እነዚሁ ወደ ስልጣን እርካብነት ያገለገለው ቡድን ነው። አሜሪካውያን ሶቭዮቶችን አፍጋኒስታን ላይ እንዲመታላቸው ቢንላዲንን ሲያሰለጥኑና ሲያስታጥቁ ቆይተው በሃላ የሆነውን ዓይነት መሆኑ ነው።

 

የኦሮሞን ወጣት እርስበርሱና ከሶማሊ ብቻ ሳይሆን ከደቡብ አጎራባች ህዝብም ጭምር እንዲጋጭ ተደርጓል። ከአማራ፣ ቤንሻንጉል፣ ከትግራይ ህዝቦች እንዲጋጭ ተቀስቅሳል። ይህ ቡድን በስመ ኦሮሞ ስልጣን ላይ እንዲወጣ ብቻ! ኦሮማራ የሚል ግንባር በማደራጀት በትግራይና በመሪ ድርጅቱ ላይ ጣት በመቀሰር አቅጣጫ ቀየሩ። የኦሮሞና አማራ ወጣት ጥያቄ ስራ ፍጠሩልኝ፣ ከመሬቴ አታፈናቅሉኝ ወይም ካሳ በወቅቱ ክፈሉኝ፣ መልካም አስተዳደር ይንገስ እንጂ ሌላ አልነበረም። አሁንም ጥያቄዬ አረ መልሱልኝ ቢል ሰሚ ሲያጣ ኦነግ፣ ፀረ-ለውጥ፣ በሌላ ሶስተኛ አካል የሚመራ በሚል ያልታወጀ አስቸካይ አዋጅ ታውጆበት እየተጨፈጨፈ ይግኛል።

 

የለማ የለውጥ ቡድን የተባለው አባላት ነበርን የሚሉትና በአብይም የተመሰከረላቸው እነገዱና መጨረሻ ላይ ተቀላቅሎ ልዩ ስራም እንደሰራ የተመሰከረለት ደመቀ መኮንንም ለውጥ ተብየውን ነውጥና ጥፋት እንዳመጡ ተሰበከ።

 

እነ ገዱና ደመቀም ከበሰበሱ የሃይለስላሴው ርዝራዥና የደርግ ርዝራዥ አባላትና ጥገኛ የኒዮ ሌበራሊዝም ተላላኪ ግምባር ስብስብ ከውጭና ከውስጥ በመሆን (እነገዱን በምርኮኝነት በመያዝ) ደርግን ደምስሶ የህዝብ መንግስትን ለመትከል አብሮ የተዋደቀውን የትግራይና የአማራ ህዝብን ሲያናቁሩና የቆዩትን አጀንዳዎች እንዳለ ውጠው መሳርያ ሆነው ቆይተዋል። ኤርትራና ቀይ ባሕር ነው ደምበራችን ሲል እንዳልቆየ ከኢሳያስ መንግስት ጋር አብሮ በመሰለፍ ብሎም የግብፅ ፋይናንስና ሌሎች ድጋፎችም ተችሮት ለአንዴና ለመጨረሻ የደርግን መፈክር አንግበው በስመ ፀረ-ወያኔና ፀረ-ሕገመንግስታዊ ስርዓቱ አብረው በውስጥና በውጭ ተነሱ። በግልፅና በስውር ፀረ-ሕገመንግስትና በተለይ ደግሞ ፀረ-ፌደራሊዝም ትርክታቸው በመያዝ በሁሉም አቅማቸው ተንቀሳቀሱ። መጀመርያ በፀገዴና ጠገዴ በሚል ከትግራይ ክልል ጋር እንኪያ ስላንቲያ ገቡ። በትግራይም የእነ አባይ ወልዱ፣ አዜብና ትርፉ ቡድን ህዝብን ማእከል አድርገው ማየት ሲገባቸው ጥገኝነቱ አፍንጫቸው ድረስ ጠልቆ ስለነበረ አካኪ ዘራፍ በማለት ጭቃው ውስጥ ገብተው ራሳቸውን የዳርድንበር ዘብ አድርገው ማቡኳት ላይ ገቡ።

የህዝብን ጥያቄ መመለስ ያቃታቸው ሁለቱም ቡድኖች በዚህ አጀንዳ ተደብቀው በየሚያስተዳድሩት ህዝብ ያለውን ችግር ዙርያ ራሳቸውን ማእከል አድርገው መገምገም ሲገባቸው ሌላውን ሰበብ በማድረግ የልማት ስራ መስራት እየተውት መጡ። እንኳን ዘንቦብሽ አቅምም የለም። የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል ሆኖ ሁለቱ ቡዱኖች ከሌላው መማር ሳይችሉ ቀሩ። የገዥዎች አመለካከት እየተካኑ ጆራቸው ጮማ ዘግቶት የህዝቡና የነባሩ አመራር ጥያቄዎችና ምክሮች መስማት ተሳናቸው። ነባር አቅምና ብቃቱ ያላቸውን ታጋዮች አናቀርብም በማለት እናንተ አታግዙንም በሚል ያለስማቸው ስም ተሰጥታቸው ቆይቷል። ከነዚህ ነባር አመራሮች አንዱ በረከት ነው፡፡ በረከት በሁለቱም ቡዱኖች ዒላማ የሆነበትና ሌሎቹ ደግሞ በየድርጅታቸው ዒላማ ተደርገው ከነአቅማቸው መክነው እንዲቆዩ እነዚህ ቡዱኖቹ ተረባርበው ስማቸውን ሲያጠፉ ሰነባብተዋል። በመሆኑም በሁለቱ ክልል አመራሮች የተፈጠረው ልዩነት በሽምግልና ተፈታ ሲባል እያገረሸ ቀጠለ። የቅማንት ችግር ሲፈጠር ይህን የፈጠረው ህወሓት ነው በማለት ሁለት አገሮች በመካከላቸው ችግር ሲፈጠር እንደሚያደርጉት መሆኑ ነው የወልቃይት ጥያቄ የሚባል ሌላ አጀንዳ ይፈጥራሉ። አቤት! ይህ ሁሉ አሉታዊ ጉልበት የህዝብን ጥያቄና እድገት በመመለስ ላይ ቢውል ምን ያህል ለውጥ ይመጣ ነበር?

 

ይህ ሁሉ ትርምስ በኢህአዴግ ውስጥ መሰነጣጠቅ መፈጠሩና የውጭ ሀይሎች የፈለጉትና ሊፈጥሩት ጥረት ሲያደርጉ የከረሙለት ሴራ አሁን ፍሬ ማፍራቱን በመታዘብ ጫና ማድረግ የሚችሉበት ጊዜ መድረሱ አውቀው እቅዳቸውን ከወቅታዊ የኢህአዴግና የአገሪቱ ሁኔታ ተመስርተው አደሱት። በኢህአዴግ ውስጥ የነበሩትን ምልምሎች በአገር ቤትም በውጭም ጠርተው ቀጣዩ እቅድ ላይ ተመካከሩ። ሌሎች በመመልመልም ለመጠባበቅያነት /ሪዘርቭ/ የሚሆኑ ባንዳዎች የማፋራትና የማደራጀት ሴራቸው ተያያዙት። በሁሉም መንገድ በቀጥታ በየኢምባሲያቸው ሆነው እርዳታቸውን አጠናክረው ቀጠሉ።

 

በሌላ በኩል በኢህአዴግ ውስጥ ለአብዮታዊ ዴሞክራሲ ስርዓትና ለህገመንግስቱ የቆመው ሃይል ለመጨረሻ የሚመስል ትግል በማድረግ ድርጅቱ ጥልቀት ተሃድሶ ማድረግ እንዳለበት ይወስናል። ሴራውን ለማክሸፍ ትግሉን ያቀጣጥላል። ሁኔታው ያለማራቸው ፈረንጆቹ ሁኔታው እንዳወቁ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ኢህአዴግን ማፍረስ ወይም መቆጣጠር የሚያስችላቸውን ሁለገብ እንቅስቃሴ በኢህአዴግ ውስጥም በውጭም ያሉዋቸውን ሰላዮችና ተላላኪ ባንዳዎች በተጠናከረ ሁኔታ አሰማሩ። በውጭ አገር ያሉ ፀረ ህዝቦች አደራጅተው በአንድ ግምባር ለአንድ አላማ ተሰልፈው እንዲቀሳቀሱ በተለይም የሚድያ ዘመቻ እንዲያደርጉ ኢሳት፣ ኦሚኤን. . . ወዘተ ሁሉም የሚያስፈልጋቸው ነገር አማሉላቸው። በተጨማሪም ለባናዳዎቹ የሶሻል ሚድያ ስልጠና ሰጥተው ይሄው ፈረሱ ይሄው ሜዳው አሉዋቸው። በዋናነት የተማመኑት ግን በኢህአዴግ ውስጥ የፈጠሩት ድብቅ ቡድንና የተፈጠረው ችግር እንደሆነ ፈረንጆቹ ያውቃሉ። እነዚህ ከውጭ ሆነው ድል አመጣን የሚሉት የድል አጥቢያ አርበኞች ማንም ተማምኖባቸው አልነበረም። ግን ለሟሟቅ ይጠቅማሉ ተብሎ ነበር ስልጠናውና ድጋፉ የተደረገላቸው። አሙቆች! ደሞ ጠቅመዋል። አቦራ ማንሳት ላይ ማን እንደነሱ አሰኝተዋል።

 

ህወሓት የጥልቅ ተሃድሶ ሂደቱ የምሩን አካሄደ። የተሰውት ሰማዕታት ዓላማ ያደሰ ተሃድሶ አደረገ። ምህረት የለሽ ሂስና ግምገማ በራሱ ላይ አደረገ። ማላከክና ሰበብ ፍለጋ ትቶ የትግራይ ህዝብ መበደሉን ተናዘዘ። በፌደራልም ያራሱን ድርሻ ፈትሾ ያለምንም ስጋት ችግሩን አንጥሮ አስቀመጠ። ዘግይቶም ቢሆን የፈፀማቸውን ጥሩ ነገሮች ሳያጋንና ሳያሳንስ መሬት እንደሚታዩት አስቀምጦ፣ ጉድለቶቹንና ድክመቶቹን ከነምንጫቸው ገምግሞ በህዝብ ፊት አቅርቦ ሊተች ወስኖ ስብሰባውን በውጤት ፈፀመ። በተግባር ደግሞ ወደ ስራ ገብቶ ተሃድሶውን ጥልቀት እንደሚጨምርበት ቃል ገባ።

 

ደህዴን ትግል በማድረግ ሃይለማርያምን አወረደ። መቆራረጥ ስላልነበረ ተከፋፈሉ ጂኒጃናካ/ምናምን እንዳይባል በሚል ነበር ራሱ ለቀቀ የተባለው። የውጭ ሃይልም እጅ እንዳለበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይሁን እንጂ ሸጉጤም ተሸጉጦ ቀረና የደህዴን የድርጅት ትግል የተጥናቀቀ አልነበረም። ድርጅቱ ተቆሳስሎ አሸናፊው ያልለየበት ነበር። ሃይለማርያም የአህያ ተረት ተግባራዊ በማድረግ በቀጥታ ደህዴንን በብሄር አሰላለፍ ቡዱን አዋቅሮ ክፍፍል ፈጠረ።

ብአዴን በሁለት ጎራ የለየለት የጋለ ትግል አካሄደ። ግን ምን የደረጋል? መድረክ የያዘ እንዳሻው የሚያደርግበት ሁኔታ ነበር። በበረከት፣ አዲሱ፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ ዝማም እና ሌሎች በተለይም ነባሩ የብአዴን ካድሬና አባል አርሶ አደሩ ባደረገው ትግል አብዮታዊ ዲሞክራቱ የበላይነት ቢያገኝም የገዱ ቡድን የተቀበለ መስሎ ስልታዊ ማፈግፈግ አድርጎ ምንም ሳይነካካ መሪነቱን ይዞ ዘለቀ። እንደ የንጉሱ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስተር አንዳልካቸው መኮነን ፋታ ስጡን ብለው ሸውደው አመለጡ፡፡ ወመኔዎቹ!

 

ኦህዴድ ምንም ሳያደርግ ጭራሹ እኛማ እነሙክታርን ስናነሳ ጠልቀናል አለ። ከአሰራር ውጭና በተቀነባበረ ሚስጥራዊ ሴራ ያደረጉትን የፓርቲ ኩዴታ ጥልቀት ተሃድሶ ነው ብለው አረፉት። ካድሬው እየፈራም ቢሆን ግልፅነት የለውም ቢላቸውም ባደራጁት አፋኝ ቡድን አማካኝነት አዋክበው ደፋፍነውት ታድሰናል ብለው መለሱ። አንተ ይህ በል! እኔ ይህ ብዬ እናገራለሁ! ብለው ከጀርባ ከስራ አስፈፃሚ ስብሰባ በፊት በሚያደርጋት ስብሰባ ተማምለው በመጡት መሰረት ድራማው ተወኑ። አረ ቁጣም ብጤ ይዘው አትጠርጥሩን! ብለው ፎክረዋል አሉ።

 

ሲጠቃለል የታህሳሱ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ይህ አይነት ሪፖርት አፀደቀው። ትልቁ ስህተቱ! የኢህአዴግ ምክር ቤትም ይህን እንዲያፀድቅ በተደራጀ መንገድ እንቅስቃሴ ሲደረግ በመቆየቱ እሱም አፀደቀው። ምክር ቤቱም ባልጠለቀ ተሃድሶ ላይ ሆኖ ምርጫ ገባ። የዘራውን አጨደ!!!

 

ምርጫውን የታዘቡ የአጋር ድርጅቶች ሊቀመናብርትና ምክትል ሊቀመናብርት እና ነባር የኢህአዴግ አባላትም ነበሩ። ከምርጫው በሃላ አብዲ ኤሌ እንዲህ ብሎ ነበር አሉ። ወደ ምርጫ ከመገባቱ በፊት የሻሂ እረፍት ነበር። በሻሂ እረፍት ወቅት የዋሆቹ የህወሓት ምክርቤት አባላት ሻሂ ሲጠጡ ሌለቹ የም/ቤት አባላት ማን ማንን መምረጥ እንዳለበቸው፣ ማንን መቃወም እንዳለባቸው ሎቢ ማድረግ ላይ ተጠምደው ነበር ብሎ ይናገር ነበር። (አደራ! /ቤት እንደማስረጃ እንዳታቀርቡበት!)

 

እናም በግልፅ የሆነው ሶስቱ ድርጅቶች ከጥቂት አባላት በስተቀር አብይን እንዲመርጡና ማን ማንን እንደሚጦቅም ታውቆ በወቅቱ አልመረጥም አልወዳደርም ያለው ደመቀ መኮንን ሊቀመንበር ሆኖ ጥቆማ ሲቀበል ማንን እድል እንደሚሰጥ ለማን እንዳማይሰጥ አውቆ በእቅድ የመራው። አሁንማ ይህ በአደባባይ የለማ ቲሞችም ሞቅ ሲላቸው ራሳቸው ጫፍ ጫፉን እያስነኩት የለ። እግረ መንገዳችንም የጀዋር መሀመድ ምስክርነትም እያስታወስን። የሆነው ሆኖ አብይ ተመረጠና ወያኔ ተሸነፈ እኩል የተራገቡበት ምስጥር ይህ ነው። የታደሰው ፀረ-ለውጥ ያልታደሰው ብቻ አይገልፀውም ሊታደስ የማይችለው የለውጥ መሪ የተባለለት ምክንያት የአራዳ ሽወዳ በመጫወት ስላሸነፈ ነው። አሸናፊና ተሸናፊ አትበሉ ይላሉ? ለምን አይባልም? ጫወታ ካለ አሸናፊና ተሸናፊ አለ!

 

አብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ባይሸነፍም ያነገበው የህዝብ ወገን ተሸንፋል። በዝረራ! ዘላቂነት ግን ያለው አይመስልም። ነገር ግን ሽንፈቱን መደበቅ አይቻልም። አይገባምም። ሓቅ ነው። ደግሞም ዳግመ ትግል ለማድረግ በትክክል ማስቀመጡ ተገቢ ነው እላላሁ። የተሸነፈበት ምክንያት ግን ፀረ-አብዮታዊ ዲሞክራሲ ሃይሉ ጠንካራ ስለሆነና አሸናፊ ሐሳብ ስለጨበጠ አይደለም። የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ያነገበው ሐይል መስመሩንና ህዝባዊ ወገንተኝነቱ ተሸርሽሮና ተዳክሞ በመቅየቱ ነው። አክራሪ ብሄርተኝነትና ህዝበኝነት የጥፋት መንገዶች ሲስፋፉ በወቅቱ ስላልታገላቸው ነው።

 

አሁን ስልጣን ላይ የወጣው ሃይል ለውጥ! ለውጥ! ቢልም በአቧራ ተሸፍኖ የቆየውን የቆዩትን ገዥዎቻችን አስተሳሰብ እያራመደ ነው። ለውጡ ፀረ-አብዮት ለውጥ ነው። ወደ ፊት ሳይሆን ወደኃሊት ቁልቁል የሚወስደን ነው። አቅጣጫው ገና ከአሁኑኑ እያየንው ነው። አገሪቱ እየተተራመስች ነው። ለችግር መፍትሄ ብለው የቀድሞዎቹ ገዥዎቻችን የሞኮርዎቸው ተልባ ቢንጫጫ በአንድ መውቀጫ! አንድነት ያለውዴታ በግዴታ! በለው! በለው! ግደለው! ስለሆኑ ችግሩ መባባስ ካልሆነ መሻሻል አያሳይም። ሳይፈታ ሲቀር ደግሞ ከደሙ ንፁህ የሆነውን ትክክል አይደላችሁም! ያሏቸው ልክክ ማድረግ ሃፍረትም አይሰማቸውም።

 

አብይና ጓዶቹ ስልጣን ሲያዙ ቂም በቀል የለም፣ ፍቅር! ዕርቅ! አንድነት! ብቻ ነው አሉ። ዲሞክራሲና የህግ የበላይነት ብለው ዘመሩ። ወንጀለኞችን አገር ክደው የኮበለሉትን አሸባሪዎችን ይቅርታ ሳይጠይቁ መስፈርት በሌለው መንገድ ያታሰሩትን ሲፈቱ ግብፅና ኤርትራ መሽገው የቆዩትን ፀረ ህዝቦችን አገርቤት እንዲገቡ በማድረግ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ትጥቁ አድርጎ ህዝባዊ ወገንተኛ የሆነውን ሐይልና ህግ ሲያስከብር የነበረውን ሐይል የወያኔ ስርዓት ናፋቂና ፀረ-ለውጥ በማለት ከፍተኛ ስም ማጥፋት ዘመቻ ተያያዙት። በፍቅር ፋንታ ቂም፣ በዕርቅ ፋንታ ጥላቻና በቀል፣ በአንድነት ፋንታ ለውጥ ፈላጊና ለውጥ የማይፈልግና ያልተደመረ በሚል መከፋፈል ተጀመረ። የውጭ አራጋቢዎችም ለውጡ የሚገባደደው እንትና መስርያቤት ሪፎርም ሲደረግ እነእንትና ስልጣናቸው ሲቀሙ ደግሞም ሲታሰሩ ነው ብለው አወጁ። ኢህአዴግን በሐይል እንጥላለን ሲሉ የነበሩ ደግሞ እንትና የተባለ የኢህአዴግ ፖለቲካ መሪን ከስልጣን አስወግዱ ጡረታ አስወጡ። በእንትና ወጣት መሪ ተኩ ይላሉ። ወዲያውኑ ይፈፀማል። በሚድያ ይነገራል የድል ዜና ተደርጎ።

 

አብዲ ኢሌን ኦሮሞዎችን ጨፈጨፍ አፈናቀለ ብለው ሲታሰር በአወዳይ በገለምሶ ሶማሊዎችን የጨፈጨፈ ቲም ለማ አሳሪ ሆኖ ቁጭ አለ። ወንጀለኛ ህግ አስከባሪን ይያዝልኝ ሲል የሚሰማ መንግስት የተፈጠረበት ጉደኛ አገር! ህገመንግስቱንና ህዝቡን ቀን ተለሊት ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ለዓመታት የጠበቁና ድንቅ ስራ የሰሩ የፌደራል ፖሊስ አባላትና የብሄራዊ ድህንነት ሰራተኞችን ስም በማጉደፍ በወንጀለኞች ተከሰው ለእስር የተዳረጉበት ሁኔታ ተፈጠረ። የሚያምን ሲያጡ የአይጥ ምስክር ድምቢጥ ሆነና ወንጀለኞቹ ቴሌቪዥን እየቀረቡ ጉዳቸውን ደብቀው በሉ የተባሉትን እንዲናገሩ ተደረገ። የትግራይ ተወላጆች ላይ ያነጣጠረው ክስና እስር ተጧጧፈ፡፡ የወያኔ አሽከር በሚል ከልብ ሙያዊ ፍቅር ሲያገለግሉ የነበሩትንም የሌላ ብሄር ተወላጆችንም ያካተተ ጥቃት ተፈፀመ። ይህም አልበቃ ብሏቸው በብዙ የተወገዘውን ድራማዊ ዶከመንተሪ (ፎክመንተሪ) በመስራት በትግራይ ህዝብ ላይ ያላቸውን ጥላቻ አንፀባረቁ።

 

ፀረ ሙስና ትግል በሚልም የትግራይ ነው በሚባል ሜቴክ ሲሰሩ የነበሩ ፀሓፊ ሳትቀር ብቻ ትግሬ ትሁን ማሰር ቀጠሉ፡፡ ዶከመንተሪም ተሰራ። ጄነራል ክንፈን ለመያዝ ሆሊውድን ያስናቀ ፊልም ተሰራ። 1997 አንዳርጋቸው ፅጌ ባልረባ ምክንያት /ቤት በዋስ ይፈታ በማለቱ የዋስ መብት ተከብሮለት በቦሌ ሲውጣ ዝም የተባለበት አገር አሁን አንዴ ሳይሆን በተደጋጋሚ የዋስ መብቱ ይረጋገጥለት የተባለ ተከሳሽ ግግም ብለው እንፈታም እምቢ! አሉ። የለውጡ ፍሬ መሆኑ ነው። አቃቤ ህግ ምን ያድርግ አድርግ የተባለውን ከማድረግ ውጭ። ዳኛው አልተደመርክም ብሎ ማሰሩ አይሻልም! የህግ የበላይነት ላይ የተካሄደው ሪፎርምም ይህ ነው።

 

እስቲ መጨረሻውን እናያለን ስንል ቀጥሎ ደግሞ ብአዴንን የገደለው የገዱ ቡድን አሜሪካ በመሄድ ከዳያስፖራ ሀሳብ መሪዎቹ ጋር በመሆን ከናንተ ጋር አንድ ነን እኛም እንደናንተ የብሄር ብህረሰቦችና ህዝቦችን መብት አናምንም አሉ። የወያኔ መንግስት ጣላችሁ ተብለው ሲሞጋጎሱ ቆይተው አሁንም የቤት ስራችሁን አልፈፀማችሁም እነ በረከትን ዝም ለምን ይባላሉ? ተብለው ሲወቀሱና ቀጣይ ትእዛዝ ሲቀበሉ ሰነባብተው ተመለሱ። መጥተው ሳይውሉ ሳያድሩ እንዴት እነበረከት እንይዛለን ብለው መከሩ። ለማዋረድ በረከት በጣም በሚጠየፈው እነሱ ግን በተዘፈቁበትና በአደባባይ በሚታሙበት ሙስና ክስስ አድርገው እርፍ! ነገር ዓለሙ የጠፋበት አገር፡፡ ድርጅት፡፡ አሳሪ መሆን ሲገባው ታሳሪ ይሉሃል እንዲህ ነው።

ኡስማን ሙሉዓለም

ከሐራ

የካቲት 2011

 

usman.mulualem@gmail.com

 

Back to Front Page